TechIn2
1.17K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
ዲጂታል ገንዘቦች በ5 ዓመት ውስጥ ብቻ የገንዘብ ኖቶችን ይተካሉ ተባለ
=================
በእውቁ ዓለም አቀፍ የአማካሪ ኩባንያ ዲሎይት አማካኝነት የፋይናንስ ኢንዱስትሪው አንቀሳቃሾችን በማሳተፍ ጭምር የተሰራ አንድ ሰርቬይ የዲጂታል መገበያያ በአምስት ወይም አስር ዓመታት ውስጥ ብቻ የገንዘብ ኖቶችን እንደሚተካና ባንኮችም ይህን አውቀው የጥንቃቄ እርምጃ እንዲወስዱ አሳስቧል፡፡ የዲሎይት 2021 ዓለም አቀፍ የብሎክቼይን ሰርቬይ ባንኮች የማይቀረው የዲጂታሉን ዓለም መቀበል ያለባቸው መሆኑንና የፋይናንስ ዘርፉ መሪዎችም ከጊዜ ወደ ጊዜ ዲጂታል መገበያያ ገንዘቦች የመጪው ጊዜ ተረካቢዎች መሆናቸውን እየተቀበሉ መምጣታቸውን አመላክቷል፡፡

በጥናቱ ላይ ከተሳተፉት ባለድርሻዎች መካከል 76 በመቶ ያህሉ የዲጂታል ገንዘቦች በቀጣዮቹ ከ5 እስከ 10 ዓመታት ውስጥ የገንዘብ ኖቶችን ሙሉ በሙሉ ይተካሉ አልያም ጠንካራ አማራጭ ሆነው ይወጣሉ ብለው እንደሚያምኑ ገልፀዋል፡፡ ይህም የዲጂታል ገንዘብ አብዮቱ ምናልባትም ከሚጠበቀው በላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ገስግሶ እየመጣ ስለመሆኑና የእርሱን መንገድ ያልተከተሉትንም ከገበያው ውጪ ስለማድረጉ ጠንከር ያለ ማመላከቻ ነው ተብሎለታል፡፡

አሁን ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በዲጂታል መልኩ እየተቀመጠ ሲሆን በዚህም ሳብያ ተቋማትና ኢንቬስተሮች ከሁኔታው ጋር ተላምደው የሚሰሩበትን መንገድ እንዲያፈላልጉ ተገደው ይገኛሉ፡፡ አዲሱ ሪፖርትም ቢሆን የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ባለድርሻዎች ወደዱትም አልወደዱትም ለውጦቹ መምጣታቸው እንደማይቀር ጠንካራ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ ሪፖርቱ እንደሚለው ከሆነ በዘመነ ዲጂታሉ ላይ ተሳታፊ መሆን የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን አይቀሬ ነገር ነውና የዘርፉ አንቀሳቃሾች የዲጂታል መገበያያን እና የአዲሱ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ አገልግሎት መሰረተ ልማትን እንዴት ለራሳቸው አድርገው መጠቀም እንዳለባቸው ለመምረጥ ብቻ መገደዳቸውን ያስረዳል፡፡

እንደ አትላንቲክ ካውንስል መረጃ ከሆነ በአሁኑ ሰዓት ከዓለማችን ምጣኔ ሐብት ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነውን የሚያንቀሳቅሱት 81 ሀገራት የራሳቸውን ብሔራዊ ዲጂታል መገበያያ ለመተግበር ከጥናት አንስቶ እስከ ሙከራና ትግበራ ድረስ በመስራት ላይ ናቸው፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዷ የሆነችው ቻይና ምድሯ ላይ በምታስተናግደው መጪው የበጋ ኦሎምፒክ ላይ የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች ለቻይና ህዝባዊ ባንክ የፓስፖርት መረጃቸውን ከሰጡ ዲጂታል ዩሀንን መጠቀም እንዲችሉ አድርጋ እየሰራች ትገኛለች፡፡ ከቻይና ጋር ለመስተካከል ብዙ እርምጃ ቢቀራቸውም አራቱ ግዙፋን የማዕከላዊ ባንኮችም (የአሜሪካን፣ አውሮፓ ህብረት፣ ጃፓን እና እንግሊዝ) እንዲሁ በሩጫው ውስጥ ናቸው፡፡ ከነዚህ ባሻገር ግን ሌሎች 5 የዓለማችን ሀገራት የዲጂታል ገንዘብን ሙሉ በሙሉ ስራ ላይ አውለዋል ይገኛሉ፡፡

ምንጭ፤ ፊውቸሪዝም እና አትላንቲክ ካውንስል
ለተጨማሪ፤ https://futurism.com/banks-crypto-replace-dollar እና https://www.atlanticcouncil.org/cbdctracker/
የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን ያለገመድ ቻርጅ የሚያደርግ ቤት
===============================
በአንዱ የህንፃ ክፍል ስንገባ ስልካችን ወይም ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎቻችን ባሉበት ራሳቸውን ቻርጅ ሲያደርጉ ብናገኝ ምን ሊሰማን ይችላል፡፡ ሁለት ዩኒቨርስቲዎች በጥምረት ያበለፀጉት ለየት ያለ ቴክኖሎጂ ኤሌክትሪክን በጥንቃቄ በአየር ውስጥ አንዲተላለፍ በማድረግ ቤታችን ውስጥ ምንም አይነት ሶኬት መሰካት ሳያስፈልግ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን ያለገመድ ቻርጅ እንዲያደርጉ የሚያስችል ነው፡፡

ከሚቺጋን እና ቶክዮ ዩኒቨርስቲ የተወጣጡት ተመራመሪዎች ያበለፀጉት አዲስ የቴክኖሎጂ ሲስተም ኤሌክትሪክን በጥንቃቄ በአየር ውስጥ አንዲተላለፍ በማድረግ 50 ሜጋዋት የሚደርስ የኤሌክትሪክ ሃይል ማቅርብ እንዲችል ተደርጎ የተሰራ ሲሆን፤ አጠቀላይ የኤሌክትሪክ ማስተላለፍ ሂደቱን የሚከውነው የመግነጢሳዊ መስክን (magnetic field) በመጠቀም ነው፡፡ ቀድም ባለው ጊዜ አንዲህ አይነት ቴክኖሎጂ በተመራማሪዎች መበልፀግ ቢችልም በሰዎች ላይ ሊያደረስ የሚችለው ከባድ የማይክሮዌቭ ጨረር ምርመሩ ወደፊት እንዳይገፋ አግዶታል፡፡

ይሁንና በአዲስ መልክ የቀረበው የቴክኖሎጂ ግኝት ለሰዎች ፍጹም ደህንነቱ የተጠበቀ መሆኑና በየትኛውም ህንፃዎች ላይ ተገጥሞ ሊሰራ መቻሉ ለየት የሚያደርገው ነው፡፡ አዱሱ የቴክኖሎጂ ሲስተም ጠንካራ የመግነጢሳዊ መስክ በቤቶች ውስጥ በማመንጨት የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ራሳቸውን ቻርጅ እንዲደርጉ የሚያስችለቸው በእያንዳንዱ የግድግዳ ክፍተቶች በሚቀመጡ ላምፕድ ካፓሲተሮች (lumped capacitors) አማካኝነት ነው፡፡ እነዚህ የካፓሲትር አይነቶች ሃይልን በኤሌክትሪክ ፊልድ ላይ በማከማቸት እንደመስራታቸው መጠን የኤሌክትሪክ ሃይል ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ በቤት ወስጥ እንዲሰራጭ ያደርጋሉ፡፡

በገመድ አልባ የሃይል ስርጭት ሙከራዎች ላይ አዲሰ ነገር የጨመረው ይህ የተመራማሪዎች ግኝት በጠባብ ቦታዎች ክፍተኛ የኤሌክትሪክ ሃይል ማቅረብ የሚችል ነው፡፡ ተመራማሪዎች ምርምሩን ባደረጉበት የዩኒቨርስቲ ካምፓስ ሙከራውን በስኬት ማጠናቀቅ ቢችሉም ወደ ተጠቃሚዎች ቴክኖሎጂውን ለማሸጋግር ግን ጥቂት ጊዜ እንደሚወስድ ይናገራሉ፡፡ እንዲህ ያሉ የገመድ አልባ የሃይል ስርጭት ትግበራዎች ላይ እንደ ዋይ ቻርጅ፣ ኤነርጎስ እና ኦሲያ ያሉ ትልልቅ ድርጅቶች እየሰሩበት የሚገኝ ሲሆን በቀጣዩ የሰዎች የኤሌክትሪክ ሃይል አጠቃቀም ላይ ትልቅ ለውጥን ያመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
https://www.scientificamerican.com/article/this-room-could-wirelessly-charge-all-your-devices/
መረጃ የሚሰርቀው የቻርጀር ገመድ
****************************
ማርክ ግሪን የተባለ የደህንነት ተመራማሪ OMG የተሰኘው የቻርጀር ገመድ የተጠቃሚውን መረጃ በመውሰድ ወደ ሌላ ቦታ እንዲያስተላልፍ አድርጎ መስራቱ ተነገረ፡፡ ይህም ገመድ በተለይ ሀከሮች (የመረጃ መንታፊዎች) ከተለያዩ ኮምፒውተሮችና የሞባይል ስልኮች ላይ የሚፈልጉትን መረጃ ማስተላለፍ እንዲችሉ የሚያስችላቸው ነው ተብሏል፡፡ ገመዱ ከተሰካበት ኮምፒውተር ወይም ስልክ ላይ ያሉ የይለፍ ቃላትንና ሌሎች ምስጢራዊ መረጃዎችን ለመመንተፍ ሁነኛ ዘዴ ተደርጎም ተወስዷል፡፡
ከዚህ በፊት የነበረው ላይትኒንግ የተሰኘው ገመድ ስልኮቻችንን ከኮምፒውተር ጋር በማያያዝ ሀይል መሙላት የሚያስችል የነበረ ሲሆን ማርክ ግሪንና ጓደኞቹ ለዚህ ገመድ ማሻሻያ አድርገውለታል፡፡ አሁን ላይ ገመዱ መረጃን አከማችቶ ከመያዝ በተጨማሪ በውስጡ በተገጠመለት የ WiFi ቺፕ አማካኝነት መረጃውን ወደ ሌሎች ቦታዎች ማስተላለፍ ይችላል፡፡
ማርክ ግሪን ይህንን ገመድ በዚህ መልክ ያሻሻለበትን ምንያት ሲናገር በቴክኖሎጂው ዙሪያ ያሉ ሰዎች ይህን ማድረግ አይቻልም የሚል እምነት የነበራችው በመሆኑ፤ በተለይም መረጃን ለማከማቸት እና ለማስተላለፍ የሚረዱ ቁሶችን በገመዱ ውስጥ መግጠም ያስቸግራል ስለሚሉ ይህ እንደሚቻል ለማሳየት እንደሆነ ተናግሯል፡፡
አንድ ሰው ይህን ገመድ በመጠቀም ስልኩን ቻርጅ ሲሞላ ወይም መረጃ ሲያስተላልፍ ገመዱ ስራውን ውስጥ ለውስጥ ይሰራል፡፡ ሀከሮችም ገመዱ የሚሰራውን ስለሚያውቁ ባዘጋጁት የመረጃ ቋት በኩል ሆነው ይጠባበቃሉ፡፡
ይህም የሚያሳየን የምንጠቀማቸውን ኬብሎች ምንነት መለየት እንዳለብን ነው፡፡ በተለይ ከፍተኛ የሆኑ ሀገራዊ ተቋማትና ድርጅቶች ውስጥ የምንጠቀማቸው የኤሌክትሮኒክስ ቁሶች ምንነት በሙያተኛ ተጣርቶ መጠቀም ይገባናል፡፡
ምንጭ techxplore
ለተጨማሪ ንባብ https://techxplore.com/.../2021-09-omg-cables-user...
በሌሎች አማራጮችም ይከታተሉን
ዩትዩብ youtube.com/channel/UC6jvUOLRSkVEQtc5Annfwvg
ቴሌግራም t.me/TechIn2
ትዊተር twitter.com/TechinEthiopia
ሞትን እስከወድያኛው ለማስቀረት እየተሰራ ያለው ምስጢራዊ ምርምር
=====================
የቴክኖሎጂ መንደር በሆነው ሲልከንቫሊ ውስጥ እየተከናወነ ያለ አንድ ሚስጥራዊ ምርምር እርጅናን ለማስቀረት በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ ምንም እንኳን መሰል የምርምር ስራዎች ሲከናወኑ አዲስ ባይሆንም ይህ አልቶስ ላብስ በተሰኘ የቴክኖሎጂ ኩባንያ የሚሰራውን ምርምር ግን ለየት የሚያደርገው የተለያዩ ቢሊየነሮች ኪሳቸውን የከፈቱለት መሆኑ ነው፡፡

አልቶስ ላብስ ባዮሎጂያዊ ሪፕሮግራሚንግ ላይ የሚሰራ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ሲሆን በዚህ ምርምሩ እንደ አማዞኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ ጄፍ ቤዞስ እና ዩሪ ሚልነር ያሉ ቢሊየነሮችን መሳብ ችሏል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፤ ኩባንያው በዓለማችን አሉ የሚባሉ ምርጥ ምርጥ ተመራማሪዎችን ከሚከፈላቸው ደሞዝ በአምስት እና አስር እጥፍ የበለጠ በመክፈልና ያልተገደበ ነፃነት በመስጠት እያሰራ ይገኛል፡፡ ኩባንያውን ከተቀላቀሉ እውቅ ተመራማሪዎች መካከልም የሰው ልጅ እና አሳማ ሕዋሳትን ለማቀናጀት በሚሰራው ምርምሩ የሚታወቀው ኡዋን ካርሎስ ኢዚፕዋ ቤሎሞንቴ እና የህዋሳትን ዕድሜ በሚመልሰው ስራው የኖቬል ሽልማት አሸናፊ የሆነው ሺኒያ ያማንካ ይገኙበታል፡፡

ባዮሎጂያዊ ሪፕሮግራሚንግ ሕዋሳት ዳግም እድሜያቸውን እንዲያድሱ በማድረግ ምናልባትም ሞትን ሊያስቀር የሚችል ስልት ነው፡፡ በዚህ ምርምር ላይ የተሰማሩ ልዩ ልዩ አዳዲስ ኩባንያዎች ቢኖሩም አንዳቸውም ግን የአልቶስ ላብስን ያህል የባለሀብቶችን ቀልብ መሳብ አልቻሉም፡፡ ታድያ የእነዚህ የናጠጡ ሀብታሞች ዘላለም የመኖር ሩጫ አስገራሚ ባይሆንም የኩባንያው አካሄድ ግን ሚስጥራዊ ሆኗል፡፡ ዘገባዎች እንደሚያመላክቱት ከሆነ ለኩባንያው የተቀመጠጡለት ጠንካራ ግቦችም ሆነ ለተመራማሪዎቹ በዚህ ወቅት ስራችሁን ጨርሳችሁ አቅርቡ የሚል ቁርጥ ያለ ጊዜ አልተቀመጠላቸውም፡፡ ከዚህ ይልቅ ኩባንያው ታላቁ ሳይንስ የተሰኘውን ስራ ለመስራት የሚንቀሳቀስ ይሆናል፡፡

ኩባንያው ሀብታሞችን ጨምሮ በርካታ መሞት የማይፈልጉ ሰዎች በመኖራቸው ሳብያ ለምርምሩ ድጋፍ ለማግኘት እንዳስቻለው ምስጢር ባይሆንም ከሌሎች ተለይቶ እንዴት በዚህ ልክ የቢሊየነሮችን ድጋፍ ሊያገኝ ቻለ የሚለው ግን ለጊዜው አጠያያቂ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ ሊሆን የሚችለው ደግሞ ስራው ስኬታማ ከሆነ እነማን የዚህ ዕድል ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ የሚለው ጥያቄ ነው፡፡

ምንጭ፤ ፊውቸሪዝም
ለተጨማሪ፤ https://futurism.com/the-byte/altos-labs-wealthy-investors
ሞትን እስከወድያኛው ለማስቀረት እየተሰራ ያለው ምስጢራዊ ምርምር
ወታደራዊ ድሮኖች እና እያደገ የመጣው ግልጋሎታቸው
===================
ባለንበት ዘመን በድሮኖች አማካኝነት ስለሚከወን ጥቃት መስማት የተለመደ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ሆኖም የዛሬ 20 ዓመት ገደማ በወርሀ መስከረም የኒው ዮርክ መንትያ ህንፃዎች ላይ ከደረሰው ጥቃት ከአንድ ወር በኋላ ነበር አንድ የአሜሪካን አየር ኃይል አብራሪ ዘመናዊ ድሮንን ተጠቅሞ የግድያ ጥቃትን በመሰንዘር የመጀመሪያው ሰው የሆነው፡፡ ከዚህ በኋላ ግን በርካታ ርቀው ባሉ አብራሪዎች የሚንቀሳቀሱ አውሮፕላኖች (RPA) ተመራጭ የውጊያ መሳርያ ወደመሆን ተሸጋግረዋል፡፡ አሜሪካን እንኳን እንደምሳሌ ወስደን ብናይ ከአውሮፓውያኑ 2015 በኋላ በአፍጋኒስታን ውስጥ ብቻ ከ14 ሺህ በላይ የድሮን ጥቃቶችን አድርሳለች፡፡

ይህ መንግስታት በወታደራዊ ድሮኖች ላይ እያሳዩት የመጡት ከፍተኛ ፍላጎት ታድያ ሦስት አባይት ውጤቶችን አስከትሏል፡፡ የመጀመሪያው በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የወታደራዊ ድሮኖች ስርጭት መጨመሩ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ብዙዎቹ የዓለማችን ታላላቅ ብሎም በየአካባቢያቸው ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑት ሀገራት ድሮኖችን ለስለላና የአየር ላይ ምልከታ (ISR) አልያም ጥቃትን ለመሰንዘር እየተጠቀሙባቸው ይገኛሉ፡፡ ሁለተኛው ውጤት የመጀመሪያውን ተከትሎ የሚመጣ ነው፤ የድሮኖች መብዛትን ተከትሎ እነርሱን ማብረር እንዲችል ተደርጎ የሰለጠነ ወታደር የማፍራት ጉዳይ፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ድሮኖቹ በይበልጥ መሳርያን እየታጠቁ መምጣታቸው ነው፡፡

ምንም እንኳን ዘመናዊ ድሮኖችን ተጠቅሞ ጥቃት መሰንዘር ከተጀመረ ገና 20 ዓመታት ባያልፉትም ወታደራዊ ድሮኖች ግን የዘመኑ አዲስ ግኝቶች አይደሉም፡፡ እንዲያውም አውሮፕላን ከተፈጠረ ብዙም ሳይቆዩ ነው ድሮኖችም ገና በጠዋቱ በ1920 እና 30ዎቹ (እ.አ.አ) ከርቀት ሆኖ ጥቃትን ለመሰንዘር በማሰብ ወደ መድረኩ ብቅ ያሉት፡፡ ለምሳሌ ሚሳኤሎችም በሰው እየተመሩ ወደ ተልዕኮዋቸው የሚያመሩ ሲሆኑ ነገር ግን ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም የሚሰጡና ምንም አይነት ስለላን የማከናወን ብቃት የሌላቸው ናቸው፡፡ ሆኖም ዘመናዊ ወታደራዊ ድሮኖችን ለየት ከሚያደርጓቸው ውስጥ በመጀመሪያ አብራሪዎቻቸው ከደህንነት ከጥቃት የተጠበቁ መሆናቸው ነው፡፡ ሌላው እነዚህ ዘመናዊ ድሮኖች ኢላማቸውን ጠብቀው ጥቃት መሰንዘር የሚችሉ ስለሆኑ እንደ ሚሳኤል ካሉት አንፃር ጥቃት በሚፈፀምበት ቦታ ላይ አላስፈላጊ ተያያዥ ጉዳቶችን በተሻለ ያስቀራሉ፡፡ በተጨማሪም ለወታደሮቹ እና የቴክኖሎጂ ባለሙያዎቹ ያለማቋረጥ መረጃን ይሰጣሉ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ድሮኖችን አስመልክቶ ከፍተኛ የሆነ የተሳሳተ ግንዛቤ ይታያል፤ በተለይም ድሮኖቹ እንዴት ይንቀሳቀሳሉ በሚለውና በአብራሪዎቹ ላይ፡፡ ድሮኖች የሚበሩት እነርሱን ለማብረር በማሰብ ተመልምለው በሰለጠኑ ወታደሮች አማካኝነት ነው፡፡ ታድያ እነዚህ አብራሪዎች እንደ ማንኛውም የአውሮፕላን አብራሪ ሁሉ ለሚከውኗቸው ተግባራት ኃላፊነትና ተጠያቂነት ቢኖርባቸውም በማህበረሰብም ሆነ በሌሎች ወታደሮች ዘንድ ግን በመልካም አይታዩም፡፡ ለምሳሌ ድሮኖችን ማብረር የቪዲዮ ጌሞችን ከመጫወት ጋር በማያያዝ የሚቀለድ ሲሆን አብራሪዎቹም ቢሆን ከሌሎች የአውሮፕላን አብራሪዎች አንፃር የስራ እድልን ሲከለከሉ ይታያል፡፡ ይህም የድሮን አብራሪዎች እጥረትን አስከትሏል፡፡ በሌላ መልኩ የድሮን አብራሪዎች ከአንድ አደጋ በኋላ የሚከሰት የጭንቀት በሽታ (Post traumatic stress disorder) ምልክት ቢታይባቸውም በወታደራዊ ተቋማቱ ጭምር የምር ተወስዶላቸው ህክምና ሲያገኙ አይስተዋልም፡፡

በሌላ መልኩ ጥቃት በሚፈፅሙበት ጊዜ ተያይዘው የተከሰቱ የንፁሀን ሞት በማህበረሰብ ዘንድ በመጥፎ እንዳይታዩ አድርጓቸዋል፡፡

ምንጭ፤ ቴክስፕሎር
ለተጨማሪ፤ https://techxplore.com/news/2021-09-legacy-drone-warfare-view-military.html
የወደፊቱን የመጓጓዣ ዘርፍ ይቀይራል የተባለለት ሀይፐርሉፕ
*******************************
ሀይፐርሉፕ የወደፊቱን የሰዎችና የእቃ ማጓጓዣ ስርዓት በእጅጉ ይለውጠዋል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ በሰዓት 1200 ኪሎሜትሮችን መምዘግዘግ ይችላል የተባለለት ይህ ቴክኖሎጂ በምን ደረጃ ላይ እንዳለ የዘርፉ ምሁራን በያዝነው የፈረንጆቹ መስከረም 14- 16 ምክክር ይደረግበታል ተብሏል፡፡
ሀይፐርሉፕ የተሰኘው የመጓጓዣ ቴክኖሎጂ ሰዎችና የተለያዩ ቁሶች ዙሪያውን ዝግ በሆነ እንደ ሳጥን ባለ ነገር (capsule) ውስጥ ሆነው በከፍኛ ፍጥነት በቶቦ ውስጥ ከቦታ ቦታ እንዲጓዙ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ከመደበኛ ባቡሮች በተቃራኒ ፉርጎዎችን የማይጠቀም ሲሆን በወና ውስጥ በመግነጢሳዊ ሀይል በመታገዝ የሚንቀሳቀስ ነው፡፡ ይህ ባቡር መሰል መጓጓዣ ለመንቀሳቀስም ሆነ ለመቆም መግነጢሳዊ ሀይልን ይጠቀማል፡፡ መግነጢሳዊ ሀይሉ የፍትጊያ ሀይልን በመቀነስ ሀይፐርሉፑ በከፍተና ፍጥነት እንዲጓዝ ያስችለዋል፡፡
የመጀመሪያው ቨርጂን ሀይፐርሉፕ የተሰኘው መጓጓዣ በላስቬጋስ በረሃማ ስፍራ መንገደኞችን በማሳፈር የተሳካ ሙከራ ማካሄዱ የሚታወስ ሲሆን ይህ ከሳይንስ ፊክሽን እንኳን ላቅ ያለ ቴክኖሎጂ በቅርብ እውን የመሆን እድል እንዳለው እየተነገረ ነው፡፡ ሀይፐርሉፕ በጣም ዝቅተኛ የሆነ የካርቦን ተጽዕኖ ያለው መሆኑ እውን የመሆኑን ተስፋ ከፍ አድርጎታል፡፡
ይህ ዘመናዊ መጓጓዣ በሰፊው ጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት ተመራማሪዎች አንዳንድ መመለስ ያለባቸው ጥያቄዎች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አዲሱን ቴክኖሎጂ አሁን ላይ ጥቅም እየሰጡ ካሉት የመጓጓዣ ቴክኖሎጂዎች ጋር እንዴት ማቀናጀት ይቻላል፣ አለማቀፍ የሆነ መሰረተ ልማት እንዴት መስራት ይቻላል እና የቴክኖሎጂውን ማህበራዊ ጥቅም እንዴት ማሳደግ ይቻላል የሚሉ መሰረታዊ ጥያቄዎች ይገኙበታል፡፡
ይህንን የተመለከተው ውይይት የፊታችን መስከረም 16 በፍራንክፈርት የሚካሄድ ሲሆን በኮንፈረንሱም አለማቀፍ የሆኑና በጉዳዩ ዙሪያ የሚሰሩ የትራንስፖርት ድርጅቶች፣ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች እና ሌሎች አምራቾች ይሳተፋሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ ሁለት አጀንዳዎች የተቀረጹ ሲሆን እነዚህም ቴክኖሎጂው መንገደኞችን ለማጓጓዝ የሚገጥመውን ተግዳሮትና ከእቃ ማጓጓዝ ጋር ሊኖር የሚችለውን ችግር የተመለከቱ ናቸው፡፡
ከተሳታፊ ድርጅቶች መካከል ዋና ዋና የሚባሉት የቱቦ አምራቾች፣ የቫኪዩም ቴክኖሎጂ አምራቾች እና ከሀይፐርሎፕ ቴክኖሎጂ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ተቋማት ቴክኖሎጂውን በማበልጸግ ረገድ የደረሱበትን ደረጃ ያቀርባሉም ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡
ባለፈው አመት ህዳር ወር ላይ በዲጂታል አማካኝነት ውይይት የተካሄደ ሲሆን የዘንድሮው ሁሉንም ባለድርሻዎች ፊት ለፊት የሚያገናኝ ይሆናል፡፡
ምንጭ Cities today
ለተጨማሪ ንባብ https://cities-today.com/.../hyperloop-tube-mail-traffic/...
ኤልሳልቫዶር ቢትኮይንን ህጋዊ መገበያያ ማድረጓ መነጋገሪያ ሆኗል
ኤልሳልቫዶር ቢትኮይንን ህጋዊ መገበያያ ማድረጓ መነጋገሪያ ሆኗል
=======================
አለም የቢትኮይን ጥቅምና ጉዳት ላይ ገና ክርክሩን ጨርሶ ባላጠናቀቀበት ሁኔታ ኤልሳልቫዶር ቢትኮይንን ህጋዊ መገበያያ አድርጋ መወሰኗ አስገራሚ ሆኗል፡፡ ከትናትና ዕለት አንስቶ የንግድ ልውውጦችና ክፍያዎች በዲጂታል ገንዘብ እንዲሆን እያስገደደ ያለው የሃገሪቱ መንግስት ዜጎች የቢትኮይን ዲጂታል ዋሌት መተግበሪያ እንዲያወርዱና በምትኩ 30 ዶላር ዋጋ እንዲከፍሉ የሚያዝ መመሪያ አስቀምጧል፡፡

በሰኔ ወር መጀመሪያ ቢትኮይንን ህጋዊ መገበያያ ለማድረግ የሚያስችል አወዛጋቢ የህግ ረቂቅ ያሳለፈችው ሃገሪቱ ከመስከረም 7 ጀምሮ ደግሞ ህጉ የሚፀናበት ቀን እንደሚሆን አስቀምጣ ነበር፡፡ በዚህ መሰረት ከትላንት ጀምሮ ስራ ላይ የሚውለው ይህ መመሪያ 4 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ያላትን ኤልሳልቫዶር ቢትኮይንን ህጋዊ መገበያያ ያደረገች ብቸኛ ሀገር ያደርጋታል፡፡

ህጉ ውሳኔ ከተላለፈበት በኋላ የሃገሪቱ ዜጎች በቀላሉ የንግድ ልውውጥ ለማድረግ እንዲመቻቸው የቢትኮይን ሳንቲምን ወደ ዶላር የሚቀይሩ 200 የኤት ኤ ኤም ማሽኖችን ያስገጠመው የሃገሪቱ መንግስት በመደበኛው ገንዘብ ሲተመን 21 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ 400 የቢትኮይን ዲጂታል ገንዘብ ከአለም አቀፍ ገበያው እንደገዛም ተዘግቧል፡፡ የኤልሳልቫዶር ፕሬዝዳንት ናይብ ቡኬሌ ቢትኮይንን የሃገሪቱ መገበያያ የማድረጉ ውሳኔ በረሚታንስ የኢኮኖሚ ዘርፉ ላይ ትልቅ መሻሻሎችን እንደሚያመጣ ቢናገሩም በውሳኔው ላይ አስተያየት የተጠየቁ ብዙ የሃገሪቱ ዜጎች ቢትኮይንን ህጋዊ መገበያያ የማድረጉ እርምጃ ግራ ኣጋቢ እንደሆነባቸው እንስተዋል፡፡

አወዛጋቢ በሆነው የቢትኮይን ገበያ ብዙ የአለም መንገስታት ዲጂታል ገንዘቡን ለማስተዳደር የሚያስችሉ ማዕቀቦችን እና ልዩ አሰራሮችን እያበጁ ቢሆንም በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ መንግስታት ደግሞ ይህን የዲጂታል ገንዘብ እንደ ህጋዊ መገበያያ ለማድረግ መወሰናቸው ክርክሮችን እያስነሳ ይገኛል፡፡ እንደ ቻይና ያሉ ሀገራት የቢትኮይን ገበያ ቁጥጥር ውስጥ ለማድረግ እየሰሩ ባሉበት በአሁኑ ወቅት የኤልሳልቫዶርን ውሳኔ ተከትለው ቢትኮይንን ህጋዊ መገበያያ ለማድረግ እየጣሩ ያሉት ፓራጓይ እና ኩባ በአለም አቀፍ መድረክ ትልቅ መነጋገሪያ አድርጓቸዋል፡፡
https://www.cnbc.com/2021/09/07/el-salvador-buys-400-bitcoin-ahead-of-law-making-it-legal-currency.html
የሩሲያ ተመራማሪዎች ይዘውት የመጡት አዲስ የካንሰር ህክምና ስልት
የሩሲያ ተመራማሪዎች ይዘውት የመጡት አዲስ የካንሰር ህክምና ስልት
========================
በሩሲያው የቶምስክ ፖሊቴኒክ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ እንዲሁም ሌሎች ሩሲያውያን ተመራማሪዎች አክቲኒየም-225 በመጠቀም በ40 በመቶ የበለጠ ውጤታማ የሆነ የካንሰር ህክምናን አስተዋወቁ፡፡ እንደ ተመራማሪዎቹ ከሆነ ለአክቲኒየሙ ልዩ የሆነ የናኖ ማሸግያ በማዘጋጀት ከ6 እስከ 10 እጥፍ በላቀ የሰውነት አካልን ከመርዛማ ዲግሬድ ያደረጉ ንጥረ ነገሮች (degradation products) የመጠበቅ አቅም አለው፡፡

አክቲኒየም-225 መጀመሪያ የዩራኒየም-233 ዲግሬድ ያደረገ ንጥረ ነገር ሆኖ የተገኘ የራዲዮአክቲቭ አይዞቶፕ ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች እንደሚሉትም ይህ ዲግሬድ ያደረገ ንጥረ ነገር ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱትን ጨምሮ የተለያዩ አይነት ካንሰሮችን ለማከም ሊውል የሚችል የህክምና ራዲዮኮምፓውንድ (ራዲዮፋርማቱቲካል) ነው፡፡

ይህ በተለይም አክቲኒየም አልፋ ፓርቲክሎችን ስለሚለቅና ይህም ጤናማ ህዋሳትን ሳይነካ የካንሰር ሴሎችን ለይቶ የመምታት ብቃቱ የበለጠ ውጤታማ ስለሚያደርገው ነው፡፡ ሆኖም አክቲኒየምም እንደ ፍራንሲየም-221 እና ቢስሙዝ-213 ያሉ በጉበት፣ ኩላሊት እና ጣፍያ ውስጥ የሚጠራቀሙ መርዛማ ዲግሬድ ያደረጉ ንጥረ ነገሮችን ይሰጣል፡፡ ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት ከሆነም ይህ ነው አክቲኒየም በህክምናው በስፋት ጥቅም ላይ እንዳይውል የሚያግደው፡፡

ለዚህ መፍትሄ ይሆን ዘንድ ታድያ ተመራማሪዎቹ ለየት ያለ አይሶቶፕን ወደ ፖሊመር-ካፕሱሎች የማሸግ ስልትን አስተዋውቀዋል፡፡ እንደተመራማሪዎቹ ከሆነም ይህ መንገድ መርዛማ አይሶቶፖችን ለማርከስ እና የአክቲኒየም ውጤታማነትንም ለመጨመር ያስችላል፡፡ በእንስሳት ላይ የተደረጉ ሙከራዎች እንዳመላከቱትም በኩላሊት ውስጥ የሚቀረው ከ5 በመቶ የማይበልጥ ሲሆን ይህም አሁን ያሉ የህክምና መንገዶች ከ30 እስከ 50 በመቶ የሚሆነውን እንደማስቀረታቸው ትልቅ መሻሻል ነው፡፡

ተመራማሪዎቹ ካፕሱሎቹን ለመስራት ኬሚካላዊ መንገድን ተጠቅመው በመጀመሪያ አክቲኒየሙን የፕሮቲን ሞለኪውል ከሆነው ከአልቡሚን ጋር በማጣበቅ በፖሊመር ውህዱ ውስጥ አስቀምጠውታል፡፡ አልቡሚኒኑ ከፖሊመሩ ጋር በደምብ ተጣምረውም ለአይሶቶፑ ከለላ ይሰሩለታል፡፡
ምንጭ፤ ስፑትኒክ
ለተጨማሪ፤ https://sputniknews.com/20210903/russian-scientists-create-universal-cure-for-cancer-1083789334.html
የሮቦት ፖሊሶችን በሲንጋፖር ስራ ጀመሩ
የሮቦት ፖሊሶችን በሲንጋፖር ስራ ጀመሩ
===========
ሲንጋፖር ራስ ገዝ ሮቦቶች በመጠቀም በተማይቱ ማጨስን እና የኮቪድ 19 ደንቦችን መተላለፍን ጨምሮ ልዩ ልዩ ያልተፈለጉ ማህበራዊ ባህርያትን የመቆጣጠር ሙከራን እያከናወነች ትገኛለች፡፡ ዣቨር የተሰኙት ሮቦቶቹ 360 ዲግሪ መመልከት የሚያስችል ካሜራ ያላቸው ሲሆን በተጨማሪም በካሜራቸው የሚመለከቱትን ነገር በመተንተን ጥሰቶችን እዲለዩ የሚያስችል ሴንሰር ተገጥሞላቸዋል፡፡

ሮቦቶቹ ያልተፈለጉትን ማህበራዊ ባህርያት በሚመለከቱበት ጊዜ ወደ ቁጥጥር ማዕከሉ መረጃ በመላክ ማዕከሉ ውስጥ የሚገኙት ፖሊሶች በሮቦቱ በኩል አልያም በግንባር ተገኝተው እርምጃ እንዲወስዱ ያስችላል፡፡ 5 ያህል የሀገሪቱ ተቋማት ተሳታፊ የሆኑበት ይህ ሙከራ ፖሊሶች የግድ ለሁሉም ጉዳይ በአካል ለመገኘት እንዳይገደዱና ስራዎችም በተሻለ መልኩ እንዲሰሩ ያችላል ተብሎለታል፡፡

ሮቦቱ ቁጥጥር የሚያደርግባቸው ያልተፈለጉ ማህበዊ ባህርያት የሚከተሉት ናቸው፤ በተከለከለበት ቦታ ላይ ማጨስ፣ ሕገ-ወጥ ንግድ፣ አግባብ ባልሆነ መልኩ ብስክሌቶችን ማቆም፣ የኮቪድ 19 ደንብን በመጣስ ለ5 ወይም ከዚያ በላይ መሰብሰብ እንዲሁም በእግረኛ መንገድ ላይ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች፡፡

ሲንጋፖር ከዚህ ቀደምም እንዲሁ በህዝባዊ መናፈሻዎች ውስጥ የኮቪድ ሕግጋት መጣስ አለመጣሳቸውን በሮቦቶች አማካኝነት ለመቆጣጠር ሙከራ አድርጋ ነበር፡፡ ለዚህ ሙከራም በቦስተን ዳይናሚክስ አማካኝነት የተፈበረኩትን እና ከ1 ሜትር በታች ተቀራርበው በተገኙ ሰዎች ላይ ልክ እንደ እውነተኛ ውሻ የሚጮሁ የሮቦት ውሻዎችን ተጠቅማ ነበር፡፡ እነዚህ የሮቦት ውሻዎችን ተጠቅሞ አንዳንድ የፖሊስ ስራዎችን የመስራት ሙከራ በአሜሪካንም ተከናውኖ የነበረ ሲሆን በተለይ በኒውዮርክ ከተማ ግን ከህዝብ በገጠመው ተቃውሞ ምክንያት ሙከራው ሊቋረጥ ችሏል፡፡

ምንጭ፤ ቴክስፕሎር
ለተጨማሪ፤ https://techxplore.com/news/2021-09-singapore-robots-patrol-streets-undesirable.html
ካርቦንን ለመቀነስ ተብሎ የተሰራው ፋብሪካ
ካርቦንን ለመቀነስ ተብሎ የተሰራው ፋብሪካ
********************************************
ለወትሮው ግዙፋን ኢንዱስትሪዎች በተገነቡ ቁጥር ትልቁ አሳሳቢ ጉዳይ በከባቢ አየር ላይ የሚኖራቸው ተጽዕኖ ነበር፡፡ ይኸውም ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ የሆነ ካርቦንን ወደ ከባቢ አየር ስለሚለቁ በቀጥታ የከባቢ አየር ደህንነት ስጋቶች በመሆናቸው ነው፡፡ ይህኛው መረጃ ግን ከዚህ በተቃራኒው ካርቦንን ለመቀነስ ግዙፍ ፋብሪካ ስራ መጀመሩን የሚናገር ነው፡፡

ይህ ኦርካ የተሰኘ ፋብሪካ በአለማችን በግዝፈቱ የሚተካከለው የለም የተባለ ሲሆን ስራውም ከከባቢ አየር ውስጥ ካርቦን ዳይ ኦክሳይድን ብቻ ለይቶ በመምጠጥ ከአለት ጋር እንዲቀላቀል የሚያደርግ ነው፡፡ ስያሜውም በአይስላንድ ቋንቋ "orka" ከሚለው የተወሰደ ሲሆን ‹ሀይል› የሚል ፍች አለው፡፡

የስዊዘርላንድ እና የአይስላንድ በሆኑ ሁለት ድርጅቶች የተገነባው ይህ ፋብሪካ በየአመቱ 4000 ቶን ካርቦንዳይ ኦክሳይድን ከከባቢ አየር ውስጥ ለይቶ እንደሚያወጣ ተሰምቷል፡፡ እንደ አሜሪካው የአካባቢ ጥበቃ ተቋም መረጃ ይህ መጠን ከ870 መኪኖች የሚለቀቅን በካይ ጋዝ የሚያክል ነው፡፡

የመረጃ ምንጫችን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስን ጠቅሶ ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው የተሰበሰበው ካርቦን በከፍተኛ ሙቀት ውስጥ ካለፈ በኋላ ከውሃ ጋር ተቀላቅሎ 1000 ሜትር ወደሚጠልቅ አለታማ አካባቢ ይለቀቃል፡፡ በዚህም ሂደት ካርቦኑ በጥልቅ አለታማ አፈር ውስጥ ተውጦ ይቀራል፡፡

ካርቦንን የመሰብሰብንና የማከማቸትን ሀሳብ የሚደግፉ ሙያተኞች ይህ ቴክኖሎጂ አለማችን ከከባቢ አየር ለውጥ ጋር በተያየዘ እየገጠማት ያለውን ችግር ለመቅረፍ አጋዥ መንገድ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ቴክኖሎጂው ውድ በመሆኑና የሚታይ ለውጥ ለማምጣት ብዙ ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ ተገቢነቱ ላይ ጥያቄ ያላቸው ሰዎች እንዳሉ ተሰምቷል፡፡

ምምጭ sciencealert
ለተጨማሪ ንባብ https://www.sciencealert.com/world-s-largest-project-for-turning-carbon-dioxide-into-rock-has-begun?fbclid=IwAR0miX8Y-YWaQi6e4JkXm_jFHlG7GE2J4eONJ9onljo30QVjeqs3u8yFuhY