TechIn2
1.16K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
ያለ ወንድ ዘር በራሷ አርግዛ ልጅ የወለደችው እናት
============
ከሰሞኑን ባልተለመደ ሁኔታ አንዲት ህፃን ያለ አባት መወለዷ ተሰምቷል፡፡ በጣልያኑ የካላ ጎኖኔ የውሃ ገንዳ ውስጥ የተወለደችውና ኢስፔራ የመል ስያሜ የተሰጣት አንዲት የስሙዝሀውንድ ሻርክ (Mustelus Mustelus) ለየት ባለ ሁኔታ ላለፉት አስር ዓመታት በውሃ ማጠራቀሚያው ውስጥ ከሌላ ሴት ሻርክ ጋር ብቻ ከኖረች እናቷ ተወልዳለች፡፡

በሳይንሳዊ አጠራሩ ፓተኖጀነሰስ ተብሎ የሚታወቀው ይህ ሁኔታ ሴቶች እንቁላላቸውን በራሳቸው ወደ ህይወት ማምጣት የሚችሉ ሆነው ሲገኙ እጅጉን አልፎ አልፎ የሚከሰት ነው፡፡ ፓተኖጀነሰስ ከዚህ ቀደም ሻርክና ሌሎች አሳዎችን ጨምሮ ከ80 በሚበልጡ የጀርባ አጥንት ያላቸው የእንስሳት ዝርያዎች ላይ የታየ ሁነት ነው፡፡ ሆኖም ተመራማሪዎች ሁኔታውን አይተው ሲመዘግቡ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜያቸው ሳይሆን አይቀርም፡፡ ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት ሁኔታውን የመመልከት ዕድሉ ያለው የሰው ልጅ ለይቶ ባስቀመጣቸው እንስሳ ላይ ብቻ በመሆኑ ነው ብዙም ሳይመዘገብ የቀረው፡፡

ፓተኖጀነሰስ እጅጉን አልፎ አልፎ የሚታይ ነገር ይሁን እንጂ በተለያዩ አይነት እንቁላሉን የሚጥሉም ሆነ ልጁን የሚወልዱ የሻርክ ዝርያዎች ላይ ሊታይ ይችላል፡፡ 15 ያህል የሻርክ ዝርያዎች ፓተኖጀነሰስ የማሳየት እድል እንዳላቸው ይነገራል፤ በተለይ ደግሞ የኋይት ስፖትድ ባምቡ (Chiloscyllium Plagiosum) እና ዜብራ (Stegostoma Tigrinum) ሻርኮች ላይ፡፡

በዱር የሚኖሩ እንስት ሻርኮች ከሌሎች በመራራቃቸው አልያም እንደ አየር ንብረት ለውጥ እና ዓሣ ማስገር ባሉ ሰው ሰራሽ ምክንያቶች ፈላጊ ወንድ ሲያጡ ፓተኖጀነሰስን እንደ መጨረሻ አማራጭ ወስደው ለዓመታት በዚህ መልኩ ሲወልዱ ታይተዋል፡፡ ሰው ለይቶ ባስቀመጣቸው ላይም እንዲሁ የወንድ ማጣት ሲኖር ተፈጥሮ ፓተኖጀነሰስን ልታስጀምርላቸው ትችላለች፡፡ ሌሎች ደግሞ በፓተኖጀነሰስ አማካኝነት ልጅ ሲያገኙ ከቆዩ በኋላ ወንድ ሲያገኙ ግን ዳግም ፆታዊ ግንኙነትን ተጠቅመው ወደ መውለድ ሊሸጋገሩ ይችላሉ፡፡

ፓርቴኖጀነሲስ በሁለት መልኩ ሊፈጠር ይችላል፤ አንደኛው ልከ እንደ እፅዋት ሁሉ በራሒን በማባዛት (Cloning) ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የተፈጥሮን በሚመስል የራስ ስነ-ተዋልዶ (Self-Fertilization) ነው፡፡ በዚህም እንቁላሉን ከዘር ፈሳሹ አዋህዶ ፅንስ ከመፍጠር ይልቅ የተዋሀደ ዘረ-መል (Complementary DNA) በመጠቀም ዘረ-መላቸውን ሙሉ በሙሉ ከእናታቸው ያገኙ ልጆች ይወለዳሉ፡፡

ብዙውን ጊዜ በፓተኖጀነሰስ አማካኝነት የተፈጠረ ፅንስ የመክሸፍ ዕድሉ የሰፋ እንደሆነ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ፡፡ ሆኖም በምን ያህል መጠን ይከሽፋል የሚለውን መከታተሉ አዳጋች ስለሆነ ማወቅ ይከብዳል፡፡ ይህች አዲስ የተወለደችው ሻርክ ግን በመልካም ጤና ላይ ናት ሲሉ ባለሙያዎቹ ተናግረዋል፡፡

ምንጭ፤ ላይቭ ሳይንስ
ለተጨማሪ፤ https://www.livescience.com/aquarium-shark-virgin-birth.html
ጉንዳኖች፣ አቮካዶና ሮቦቶች ወደ ህዋ
*********************************
ስፔስ ኤክስ ህዋ ላይ ወደሚገኘው አለማቀፍ የህዋ ምርምር ጣቢያ ጉንዳኖችን፣ የአቮካዶ ተክልንና የሮቦት የአካል ክፍልን መላኩ ተነገረ፡፡ በዚህ ጉዞም በህዋ ላይ ጣቢው ለሚገኙ ተመራማሪዎች እና ለምርምራቸው የሚሆኑ 2170 ኪሎግራም እቃዎች ተልከዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥም ለምርምር ስራ ው የሚያስፈልጉ ግብዓቶች፣ ትኩስ ምግቦች፣ አቦካዶ፣ ሎሚ እና አይስክሬምም ይገኙበታል፡፡

በዚህ ጉዞ ውስጥ የተለያዩ ተቋማት ለምርምር ስራ የሚያስፈልጉ ቁሶችን እና ነብሳትን የላኩ ሲሆን Girl Scouts የተባለው ድርጅት ጉንዳኖችን እና ለሙከራ የሚሆኑ ተክሎችን፤ የዊስኮነሲስ ማዲሰን ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ደግሞ የተለያዩ እጽዋት ዘሮችን ልከዋል፡፡

በጃፓኑ የቴክኖሎጂ ስታርትአፕ የተሰራው የሮቦት ክንድ ደግሞ ተመራማሪዎች የሚሰሯቸውን የተለያዩ ተግባራት እንዲሰራ ታስቦ እንደተላከ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

በዚህም በመጀመሪያ ተልእኮው በህዋ ላይ የምርምር ጣቢያው ውስጥ የሚገኙ ተግባራትን የሚከውን ሲሆን የGitai Inc. የወደፊት ሞዴል ሮቦቶች ከጣቢያው ውጭ በመሄድ የተለያዩ የሳተላይትና ሌሎች ጥገናዎችን እንደሚያደርግ የተቋሙ መረጃ ጠቁሟል፡፡ እስከ 2025 ድረስ እነዚህ ሮቦቶች ጨረቃ ላይ ለሚገነባው ቤዝ ድጋፍ ያደርጋሉም ተብሏል፡፡

ናሳ የስፔስ ሸትል ፕሮግራሙን በ2011 ከዘጋ ጀምሮ የተለያዩ ቁሶችንና የምርምር ቡድን አባላትን ወደ ህዋ ለመላክ የኤሎን ማስኩን ስፔስ ኤክስና ሌሎች ተቋማትን እየተጠቀመ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ምንጭ phys.org
ተጨማሪ ንባብ https://phys.org/news/2021-08-spacex-ants-avocados-robot-space.html
በሳይበር ምህዳሩ ከፍተኛ ስጋት የሆነው ማልዌር
======================
ማልዌር የራስ ወዳልሆነ ኮምፒውተር ህገወጥ በሆነ መንገድ ለመግባት ወይም ጉዳት ለማድረስ ታስቦ የሚዘጋጅ አጥፊ ሶፍትዌር ነው፡፡ ማልዌር /Malware/ የሚለው ቃል “malicious software” ከሚሉ ሁለት የእንግሊዘኛ ቃላት በመውሰድ የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡

አጥፊ ሶፍትዌሮች ዓይነታቸው የሚለያይ ሲሆን ስፓይዌር (spyware)፣ ራንሰምዌር (ransomware)፣ ዋርም /worms/፣ ትሮጃን ሆርስ /Trojan horses/፣ አድዌር /adware/ ወይም ማንኛውም ዓይነት ኮምፒውተርን ሊጎዳ የሚችል ኮድ የያዘ ሊሆን ይችላል፡፡

ኮምፒውተር በተለያዩ ምክንያቶች ለማልዌር ጥቃት ሊጋለጥ የሚችል ሲሆን ከነዚህም መካከል በኦፕሬቲንግ ሲስተም ዲዛይን ላይ በሚፈጠር ችግር፣ በአንድ ኔትወርክ ውስጥ ሁሉም ኮምፒውተሮች ተመሳሳይ ኦፕሬቲንግ ሲስተም የሚጠቀሙ ከሆነ ወይም ለተጠቃሚዎች በርካታ ፈቃዶችን የሚሰጥ ከሆነ በቀላሉ ለጥቃት ሊጋለጥ ይችላል፡፡

ማልዌር ጥቃትን ለመከላከል ሊወሰዱ ከሚገቡ ጥንቃቄዎች መካከል በኢ-ሜይል የሚላኩ አባሪዎችን ከመክፈታችን በፊት ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ፤ ከአጠራጣሪ ድረ-ገጾች መራቅ፤ ዝመናዎችን በየጊዜው እየተካታተሉ መጫን እና ጥራት ያላቸው ፀረ-ቫይረስ ፕሮግራሞችን መጠቀም ይመከራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ወሳኝ መረጃዎችን እንደመጠባበቂያ በማስቀመጥ ጥቃት ቢደርስብን እንኳን የጉዳቱን መጠን በእጅጉ መቀነስ ይቻላል፡፡
https://www.cisco.com/c/en/us/products/security/advanced-malware-protection/what-is-malware.html
ቻይና ታዳጊዎች በጌሞች ላይ የሚያሳልፉትን ሰዓት ገደበች
******************************************************

ቻይና ታዳጊዎቿ በሳምንት ውስጥ በበይነ መረብ ጌሞች ላይ ማሳለፍ የሚችሉትን ጊዜ በሦስት ሰዓት ገደበች፡፡ ከአሁን በኋላ የሀገሪቱ ታዳጊዎች ጌሞችን መጫወት የሚችሉት አርብ እና የእረፍት ቀናት እንዲሁም በህዝባዊ በዓላት ወቅት ከምሽቱ 2 እስከ 3 ሰዓት ብቻ ይሆናል፡፡ ይህም ቀድሞ ወጥቶ ሲሰራበት ከቆየው ህፃናቱ በእያንዳንዱ ቀናት ለአንድ ሰዓት ተኩል እንዲሁም በህዝባዊ በዓላት ወቅት እስከ ሦስት ሰዓት ጌም በመጫወት እንዲያሳልፉ ይፈቅድ ከነበረው ሕግም ጠበቅ ያለ ነው፡፡

አዲሱ ሕግ በቻይና ያሉና በዓለም ዙርያም እውቅናን ያተረፉ አንዳንድ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን መነቅነቅ ጀምሯል፡፡ ለአብነት ውሳኔውን ተከትሎ ዝነኛው የጌም ኩባንያ ቴንሴንት የአክሲዎን ዋጋው በ0.6 በመቶ ሲወርድ የገበያ ዋጋውም ቀድሞ ጣርያ በነካበት ወቅት ከነበረው የ573 ቢሊዮን ዶላር አሁን ላይ ወደ 300 ቢሊዮን ዶላር አሽቆልቁሏል፡፡ ኔትኢዝ የተሰኘው ሌላኛው ኩባንያም እንዲሁ የአክሲዮን ዋጋው በ9 በመቶ ወርዷል፡፡

ሕጉ ቻይና ከጌም አንስቶ እስከ ክፍያ አገልግሎት የሚሰጡ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎቿ ተፅዕኖዋቸው ከሚገባው በላይ እንዳይሆን ለመቆጣጠር በማሰብ እየወሰደች ያለችው የቁጥጥር እርምጃ አካል ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሀገሪቱ ላለፉት ዓመታት ከፍተኛ እድገት ሲያስመዘግቡ የቆዩትን የኤሌክትሮኒክ ንግድ እና በበይነ መረብ ትምህርት ሰጪ ኩባንያዎች ከፍትሀዊ ተወዳዳሪነት ጋር በተያያዘ አደብ ያስገዙልኛል ያለቻቸውን ደንቦች አውጥታ ነበር፡፡ በዚህም በበይነ መረብ አማካኝነት የሚሰጥ የተጨማሪ ሰዓት ወይም ቱቶሪያል ትምህርን በቅርቡ በማገድ በዘርፉ የተሰማሩትን ኩባንያዎችንም መና አስቀቀርታቸዋለች፡፡

ከሳምንታት በፊት ቴንሴንት እድሜያቸው ከ12 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት ጌሙን መጫወት እንዳይችሉና እንዲጫወቱ የሚፈቀደላቸውም በየቀኑ ከ1 ሰዓት በላይ በህዝባዊ በዓል ቀናት ደግሞ ከ2 ሰዓታት በላይ እንዳይጫወቱ ክልከላ እንደሚያሳልፍ ገልፆ ነበር፡፡

ምንጭ፤ ቴክስፕሎር
ለተጨማሪ፤ https://techxplore.com/news/2021-08-china-limits-children-hours-online.html
ባጋጠማት አደጋ ሳብያ መራብ የተሳናት ወጣት
==============
ብዙዎቻችን በጥቂቱም ቢሆን የምግብ መብያ ሰዓታችንን አሳልፈን ሰንገኝ የረሀብ ስሜቱ መቆምያ መቀመጫ ሊያሳጣን ይችላል፡፡ ሆኖም ከሰሞኑን አንዲት ወጣት እንስት ባጋጠማት ድንገተኛ ስትሮክ አማካኝነት ለ15 ወራት ያህል ምንም አይነት የረሀብ ስሜት ሳይሰማት መቆየቷ ተገልጿል፡፡
ታድያ ይህ እንግዳ የሆነ የጤና ሁኔታ አንድ ጥናት ይደረግበት ዘንድ ተመራማሪዎችን የጋበዘ ነበር፡፡ የጥናቱ ፀሐፊና በካናዳው የሞንትሪያል ዩኒቨርሲቲ ምሁር የሆኑት ዶ/ር ዳንግ ኮአ ነዌየን በ28 ዓመቷ ወጣት ላይ ከዓመት በፊት በቀኝ የሰውነት ክፍሏ ላይ ፓራላይዝድ የመሆን አደጋና የንግግር መስተጓጎል የደረሰባት መሆኑን ተከትሎ ህክምናን ከወሰደች ከአንድ ዓመት በኋላ የአንጎሏ የላይኛው ክፍል በሆነው በሰረብሪየሟ ውስጥ ባለውና ኢንሱላር ሎብ/ኮርቴክስ በሚሰኘወ አካል ላይ ስትሮክ ሊያገኙ ችለዋል፡፡
ወጣቷ ስትሮኩ ባጋጠማት ወቅት ለ11 ቀናት በሆስፒታል ቆይታ የህክምና ክትትል ሲደረግላት ቆይቷል፡፡ ሆኖም አገግማ ሆስፒታሉን ለቃ ከወጣች ከ6 ወራት በኋላ ሆስፒታሉን ለቃ ከወጣችበት ጊዜ አንስቶ ምንም አይነት የረሃብ ስሜት ተሰምቷት እንደማያውቅ ልትረዳ ቻለች፡፡ ምንም እንኳን በጉዳቱ ሳብያ ሌሎች እንደ ምግብ ጣእም እና ሽታ ያሉትን የመለየት ችግሮች ባያጋጥሟትም የረሀብ ስሜቷን ማጣቷ ግን ቀድሞ የምትወዳቸውን ምግቦች በመመገብ የምታገኘውን ደስታ እንኳን እንድታጣ አደረጋት፡፡ በተጨማሪም በወቅቱ ምንም አይነት ሌሎች ተጨማሪ የህመም ምልክቶች ሳያገጥሟትም ቀርተዋል፡፡
የአዕምሮ ጉዳቱ ካጋጠማት ከ16 ወራት በኋላ ዳግም ወደ ህክምና ባለሙያዎች የተመለሰችው ይህች ታካሚ ወደ ሀኪሞች ከመቅረቧ ከወር በፊት የረሀብ ስሜቷ ወደ ቀድሞው መመለሱን ገልፃለች፡፡ በነዚህ ረሀብ አልባ ጊዜያት ወቅት ግን ክብደቷ በ13 ኪ.ግ ቀንሶ ከ73 ወደ 60 ኪ.ግ ወርዶ ነበር፡፡
እንደ ጥናቱ ከሆነ ለ15 ወራት የቆየው የረሃብ ስሜት መሰወሩ ከመድሃኒት አወሳሰድ አልያም ከአዕምሮ ጤና ጋር ተያይዞ የመጣ አለመሆኑን ነው፡፡ ይልቁንም ዶ/ር ዳንግ እና አጋሮቹ ችግሩን ካጋጠማት ስትሮክ ጋር በማያያዝ ለህክምና ትምህርቱ ዓለም አዲስ የሆነ ጉዳይ መሆኑን አስቀምጠዋል፡፡ ቡድኑ እንደሚለው ኢንሱላር ሎቡ የተለያዩ የሰውነታችን አካላት ያሉበትን እንቅስቃሴ በመመልከት የስሜት መልዕክቶችን በመተንተን እና የምግብ ፍላጎትና የኃይል ሚዛንን በመቆጣጠር ውስጥ ትልቅ ሚናን ይጫወታል፡፡
ስራው እንዴት በስትሮኩ አማካኝነት ሊስተጓጎል ቻለ ለሚለውም ሁነቱ በአውቶኖሚክ የነርቭ ስርዓቱ ውስጥ በደረሰው የሚዛን መጓደል ነው ወደሚል ድምዳሜ አምርቷል፡፡ ኢንሱላር ሎቡ ሰውነታችን እረፍት ላይ ባለበት ሰዓት ኃይልን የማተራቀም ስራን ከሚሰራው የፓራሲምፕቴቲክ ነርቭ ስርዓቱ ጋርም የተገናኘ እንደመሆኑና በነዚህ ላይ የሚደርስ ጉዳት ረሀብ ሲመጣ የመረዳትን አቅም ሊጎዳ ይችላል፡፡
ምንጭ፤ ቱዴይ ኢን 24
ለተጨማሪ፤ https://today.in-24.com/News/315543.html
አዲሱ የአይፎን ስልክ የሳተላይት ግንኙነትን አካቷል፣ ይህ ምን ማለት ይሆን
=========================
አፕል በቅርቡ ይፋ የሚያደርገው የአይፎን ስልክ የሳተላይት ግንኙነትን የሚያስቸል በመሆኑ ለስልኩ ተጠቃሚዎች አስፈላጊው የአውታር-መረብ ሽፋን (cellular coverage) በሌለባቸው ቦታዎች መደበኛ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚስችል ነው፡፡ የማክሩመርስ ዘጋቢ ሚንግ ቺኩዎ እንደጠቀሰው አይፎን 13 የተባለው አዲሱ የአፕል ስልክ በተካተተለት የሳተላይት ግንኙነት ገፅታ የኔትወርክ ሽፋን አስቸጋሪ በሚሆንባቸው አካባቢዎች ተጣቃሚዎች ስልክ መደውል እንዲችሉ እና መልዕክት መላላክ እንዲችሉ የሚያግዝ ነው ብሏል፡፡

አዲሱ የአፕል ምርት የ4ጂ፣ 5ጂ እና ሌሎች የኔትዎርክ ሽፋኖች በሌሉባቸው ቦታዎች እንደ ስልክ መደውል እና መልዕክት መላላክ ያሉ መደበኛ አገልግሎቶችን ተጠቃሚዎች እንዲያገኙ የሚያስችለው በቀድሞ የገመድ ስልኮች ይገጠም የነበረ የዘመነ ሃንድሴት ሃርድዌር በማከሉ ነው፡፡ በአይፎን 13 ስልክ ላይ የሚገጠመው የዘመነ የሃንድሴት ሃርድዌር ዝቅተኛ የምድር ምህዋር ሳተላይቶች (low-Earth orbiting satellites) ጋር በቀላሉ ለመገናኛት ስለሚያስችለው የአውታር-መረብ ሽፋን (cellular coverage) በሌለባቸው ቦታዎች መደበኛ አገልግሎት አንዲሰጥ ያደርገዋል፡፡ የሳተላይት ግንኙነቱ ከስልኩ ጋር በደንብ እንዲግባባ Qualcomm X60 የተሰኘ የቤዝባንድ ቺፕ ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን ይህም አጠቃላይ የግንኙነት ስርኣቱን የሚያፋጥንና የሚደግፍ ይሆናል፡፡

ዝቅተኛ የምድር ምህዋር ሳተላይቶች ላይ የሚሰራው ግሎባል ስታር የተሰኘው የሳተላይት ግንኙነት አገልግሎት አቅራቢ ድርጅት አፕል በቅርቡ ይፋ ለሚያደርገው የስልክ ምርት የቴክኖሎጂና የኔትወርክ ሽፋን በመስጠት በጋራ የሚሰራ ነው፡፡ ግሎባል ስታር ዝቅተኛ የምድር ምህዋር (LEO) ላይ ብዙ ሳተላይቶችን በማሰማራት አገልግሎቱ ለሚያስፈልጋቸው ድርጅቶች ለብዙ አመታት አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ ድርጅት እንደነበር በዘገባው ተገልጿል፡፡ በዚህ ዘርፍ ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብዙ ስራዎችን በመስራት ላይ የሚገኘው የስፔስ ኤክስ ኩባንያ የኔትወርክ ሽፋን ባልተሟላላቸው በሁሉም የአለማችን ክፍሎች የ LEO ሳተላይቶችን በስፋት ጥቅም ላይ በማዋል በየትም ቦታ አገልግሎት ለመስጠት እየሰራ እንደሚገኝ ዘጋቢው ሚንግ ቺኩዎ ተናግሯል፡፡

አንዲህ ያሉ የቃጣይ ትውልድ የቴክኖሎጂ አማራጮች የኔተዎርክ ሽፋን በሌለባቸው ቦታዎች የሚኖሩ ብዙ ሚሊዮን ሰዎችን በእጅጉ የሚረዳ እና በብዙ የአለማችን ክፍሎች በግንኙነት እጥረት ምክንያት አስፈላጊውን እርዳታ ለማያገኙ ሰዎች ትልቅ እገዛ እንደሚኖረው ይታመናል፡፡ ይሁንና በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ለተጠቃሚዎች ይፋ ይደረጋል የሚባለው አይፎን 13 በተሟላ ሁኔታ የተባለውን አገልግሎት ለመስጠት ጊዜ እንደሚወስድበት የሚናገሩ አንዳንድ ባለሙያዎች የአገልግሎት አይነቱ መልክዕክት በመላክ የተወሰነ እና በተለይም አንደ አውሮፕላን አደጋ፣ የመርከብ መስጠምና ሌሎች ከባድ አደጋዎች ሲደርሱ በአጭር የፅሁፍ መልክት ለማሳወቅ የሚያስችል ብቻ መሆኑን ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
ምንጭ፡ macrumors
https://www.macrumors.com/2021/08/29/iphone-13-to-feature-leo-to-make-calls-and-text/
የአስትራ ሮኬት የማስወንጨፍ ሙከራ ከሸፈ
የአስትራ ሮኬት የማስወንጨፍ ሙከራ ከሸፈ
======================
በአሜሪካ የአየር ሃይል ክፍል ውስጥ አንድ ቅርንጫፍ በሆነው የስፔስ ፎርስ ፈንድ አድራጊነት ቅዳሜ ዕለት ወደ ጠፈር ሊወነጨፍ የነበረው የአስትራ ሮኬት በኢንጅን ክፍሎቹ ላይ ባጋጠመ ብልሽት አጠቃላይ የማስወንጨፍ ሙከራው ሊከሽፍ እንደቻለ ተነግሯል፡፡ አላስካ በሚገኘው የፓሲፊክ ስፔስፖርት ኮምፕሌክስ ሊወነጨፍ የነበረው የአስትራ 3.3 ሮኬት ለሁለት ደቂቃ ከግማሽ ወደላይ በመነሳት 50 ኪሎ ሜትሮችን ከተጓዘ በኋላ ከአምስቱ የኢንጅን ክፍሎች በአብዛኞቹ ላይ ባጋጠመ ብልሽትና የመጥፋት ችግር የማስወንጨፍ ሙከራው ከሽፎ ወደምድር እንደሚለስ መደረጉን ቢዝነስ ኢንሳይደር ዘግቧል፡፡

LV0006 የተባለች አነስተኛ የሳተለያት ቬክል ተሸኮሞ የነበረው የአስትራ ሮኬት ከዚህ በፊት በተያያዥ ምከንያቶች የተነሳ መሰል ችግር አጋጥሞት የነበረ ሲሆን ይህ አጋጣሚም ወደምህዋር ለመድረስ ከላካቸው እና ሳይሳኩ ከቀሩት የማስወንጨፍ ሙከራዋቹ ሶስተኛው ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ሮኬቱ ላይ ከደረሰው ከስተት በኋላ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሰጠው የአስትራ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ክሪስ ኬምፕ የተፈጠረው ነገር ለምን ሊከሰት እንደቻለ እየመረመርን ቢሆንም የማስወንጨፍ ሙከራው ገና እንደተጀመረ በሰከንዶች ልዩነት በአምስቱ የመጀመሪያ የኢንጅን ስቴጅ ክፍሎች ላይ ችግር አንዳጋጠመ ተመልክተናል ብሏል፡፡

የአስትራ 3.3 ሮኬት የኢንጅን መጥፋት ችግር ያጋጠመው ገና በሰከንዶች ልዩነት ቢሆንም ይህን ተቋቁሞ ለሁለት ደቂቃ በላይ ወደላይ በመነሳት 50 ኪሎ ሜትሮችን ከተጓዘ በኋላ ከአምስቱ የኢንጅን ክፍሎች በአብዛኞቹ ላይ ባጋጠመ ብልሽትና ሙሉ ለሙሉ የመጥፋት ችግር ሰዎች ላይ ጉዳት ሳያደርስ ኮዳያክ በተባለ ዴሴት ላይ ሊከሰከስ ችሏል፡፡ የማስወንጨፍ ሙከራው በተጀመረ በሰከንዶች ልዩነት የኢንጅን መጥፋት ችግር አጋጥሞትም እንኳን ለሁለት እና ከዚያ በላይ ደቂቃ መጓዝ ያቻለበት ሁኔታ አስገራሚ የጋይዳንስ ስርዓት እንደነበር የሚያመላክት ነው የሚለው የኩባንያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ክሪስ ኬምፕ ከዚህ በላይ ደግሞ በሰዎች ላይ ምንም አይነት ጉዳት ሳይደርስ ሮኬቱን ወደ ምድር ማውረድ መቻሉ ስራውን ሲያከናውኑ የነበሩ የባለሙያዎች ቡድን የሚያመስሰግን ነው ብሏል፡፡

ሮኬት የማስወንጨፍ ሙከራ ቢሊዮን ዶላሮች የሚንቀሳቀሱበት ከባድ ቢዝነስ ከመሆኑ አንጻር ለሶስተኛ ጊዜ የማስወንጨፍ ሙከራው የከሸፈበት የአስትራ ኩባንያ ከባድ ክስረት እንደሚሆንበት ተገልጿል፡፡ ከዚህ በፊት በነበሩት ጊዜያት ብዙ ኩባንያዎች የራሳቸውን ሳተላይት ወደ ምህዋር ለማስገባት እጅግ ይቸገሩ የነበረ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደ ስፔስ ኤክስ፣ ኦርቢት እና አስትራ ያሉ ግዙፍ የግል ኩባንያዎች እየተስፋፉ መምጣታቸው ሮኬት የማስወንጨፍ ሙከራን ይበልጥ እንዲዘምንና አንዲቀል አድርጎታል፡፡
ምንጭ፡ spacenews
https://spacenews.com/astra-rocket-3-3-launch-fails/
ዊንዶው 11 ቀን ተቆረጠለት
*************************
የዊንዶው 10 ተከታይ የሆነው ዊንዶው 11 የተሰኘው መጠቀሚያ በመጪው የፈረንጆቹ ጥቅምት 5 ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን ተነገረ፡፡ ላለፉት ጥቂት ወራት ሙከራ ሲደረግበት የነበረው ይህ ፕላትፎርም ከዚህ በፊት የነበረንን መጠቀሚያዎች ለማሻሻልና እንደ ዴል፣ ሌኔቮ ሌሎች የኮምፒውተር አይነቶች ላይ ተጭኖ እንደሚቀርብ ተነግሯል፡፡

በቀጠሮው እለት የሚቀርበውን ማሻሻያ የተደረገበትን የዊንዶው አይነት እንደቀድሞው (አሁን ላይ ጥቅም እየሰጠ ያለው ዊንዶው 10) ተመሳሳይ ማሻሻሎች (updates) ያሉት ሲሆን የቫይረስ ተጋላጭነቱ ዝቅተኛ ነው ሲል ማይክሮሶፍት አሳውቋል፡፡ ወደ ዊንዶው 11 ማሳደጊያውም በነጻ የቀረበ እንደሆነ ተሰምቷል፡፡

ዊንዶው 11 እንደሚጫንበት የኮምፒውተር አይነት የተለያየ ቢሆንም ሁሉም የኮምፒውተር አይነቶች በነጻ የቀረበውን ማሳደጊያ እስከ 2022 አጋማሽ ድረስ መጠቀም እንደሚችሉ ይፋ ተደርጓል፡፡ የምንጠቀመው ኮምፒውተር ለአዲሱ ዊንዶው የተፈቀደለት ከሆነ በማይክሮሶፍት በኩል ማሳወቂያ ይላካል ተብሏል፡፡

ይሁን እንጂ ሰዎች አዲሱን ዊንዶው መጠቀም ካልቻሉ ዊንዶው 10 እስከ ጥቅምት 2025 ድረስ አገልግሎት እንደሚሰጥ ማይክሮሶፍት አሳውቋል፡፡ ተቋሙ አክሎም የተለያዩ የአንዲሮይድ መተግበሪያዎችን ከዊንዶው 11 ጋር ለማቀናጀት ከአማዞንና ከኢንቴል ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አሳውቋል፡፡

በተለያዩ አማራጮች ይከታተሉን
ዩትዩብ youtube.com/channel/UC6jvUOLRSkVEQtc5Annfwvg
ትዊተር twitter.com/TechinEthiopia

ምንጭ Digital trends
ለተጨማሪ ንባብ https://www.digitaltrends.com/computing/windows-11-set-for-october-5-general-availaiblity/?utm_source=facebook&utm_medium=social&utm_content=socialorg_computing&fbclid=IwAR3ExNhGIerYwCmeK3gDt43-H0uB0DxM6SEMQKACqe6hU_EEovFZ6weiCP4
ከፍተኛ ብክለት ያለው የእርሳስ ነዳጅ ከዓለም ተወግዷል
========================
የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ፕሮግራም እንዳስታወቀው ለዘመናት በምድራችን ላይ አደጋ ሲያስከትል የነበረው የእርሳስ ነዳጅ (leaded petrol) ከብዙ አመታት ዘመቻዎች በኋላ በየትኛውም ሃገር ጥቅም ላይ የማይውልበት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ይፋ አድርጓል፡፡ ይህን መርዛማ ነዳጅ ለመጨረሻ ጊዜ አከማችታ ትሸጥና ትጠቀም የነበረቸው የሰሜን አፍሪካዋ ሃገር አልጄሪያ በሃምሌ ወር መጨረሻ ሙሉ ለሙሉ ክምችቷ መጠናቀቁን ተከትሎ ይህ የነዳጅ አይነት ከአለማችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሊወገድ ችሏል፡፡
በእርሳስ ውህድ የሚታከም ወይም የሚቀየጥ ነዳጅ (Tetraethyl lead) ቀደም ላሉት የጭነትና ሌሎች የመኪና ሞዴሎች የሞተር ማንኳኳትን (engine knocking) በመቀነስ የኢንጅኑን የመፈፀም አቅም ለመጨመር ታስቦ ጥቅም ላይ ይውል የነበረ ሲሆን፤ እንደአውሮፓውያኑ ከ1920 ጀምሮ በብዙ የዓለማችን ክፍሎች ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ ከዚህ መርዛማ ነዳጅ የሚወጣው በካይ ነገር በከባቢ አየር፣ በአፈር እና በወንዞችም ጭምር ለአንድ መዕተ አመት ጊዜ ያክል ከፍተኛ ብክለት በአለማችን ላይ ሲያስከትል ቆይቷል፡፡
ይህ ነደጃ በሚስከትለው ችግር ምክንያት ብዙ ሚሊዮኖች በልብ በሽታ፣ በካንሰር እና በስትሮክ እንደተጠቁ የሚነገር ሲሆን በህጻናት የአዕምሮ እድገት ላይ ከባድ ተፅዕኖ እንደነበረውም ይገለጻል፡፡ እንደአውሮፓውያኑ ከ1924 ጀምሮ እንዲህ ያለ ነዳጅን ጥቅም ላይ ማዋል ከፍተኛ ጉዳት እንደሚኖረው እየታወቀ ቢመጣም እስከ 1970ዎቹ ድረስ ብዙ ሀገራት ከእርሳስ ጋር የተቀላቀለ ነዳጅን ሲያመርቱና ሲሸጡ ቆይተዋል፡፡ በ1980ዎቹ በአለም አቀፍ ዘመቻና በሌሎች የማንቃት ፕሮግራሞች ብዙ ሀገራት ይህን ነዳጅ ከመጠቀም እየተቆጠቡ ቢመጡም የፈንጆቹ ሚሊኒየም እስኪገባ ድረስ በ86 ሀገራት ከእርሳስ ጋር የተቀላቀለ ነደጅ ጥቅም ላይ ይውል ነበር፡፡ ከ2002 በኋላ የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ፕሮግራም ከአለም ሀገራት፣ ከግል ኩባንያዎች እና ከሌሎች የሲቪኪ ማህበራት ጋር በህብረት ባካሄዱት ዘመቻ ባለፉት ሃያና አስራ አምስት አመታት ከፍተኛ ስኬት ማምጣት እንደተቻለ ይነገራል፡፡ ባለፉት ሶስት አመታት ይህን መርዛማ ነዳጅ መጠቀም ካቆሙት ኢራቅ፣ የመን እና አልጂሪያ በፊት በ2016 የነዳጁ ከፍተኛ ተጠቃሚ የነበሩት ሰሜን ኮሪያ፣ ማይናማር እና አፍጋኒስታን በሀገራቸው ነዳጁን መሸጥ ማቆማቸውን ተከትሎ ብዙ አመታት የወሰደው የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ፕሮግራም ዘመቻ በስኬት እንዲጠናቀቅ አድርጎታል፡፡
ከፍተኛ ብክለት የነበረው የእርሳስ ነዳጅ ከዓለማችን መወገዱን ተከትሎ በልብ፣ በካንሰር እና በስትሮክ በሽታ በየዓመቱ ህወታቸቀው ሊያልፍ ይችሉ የነበሩ አንድ ሚሊዮን ሰዎችን መታደግ እንደሚቻል የሚናገሩት የተባበሩት መንግስታት ዋና ፃሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ይህ የአለም አቀፍ ስኬት ሌሎች በምድራችን ላይ ያንዣበቡ ከባድ ስጋቶችን በህብረት መቀርፍ እንደምንችል የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡
ምንጭ፡ ቢቢሲ
https://www.bbc.com/news/world-58388810
ሉሲ እንድትገኝ ያስቻለው ተመራማሪ አረፈ
================
እውቁ የስነ ምድር ባለሙያና በሀገራችን ኢትዮጵያ አፋር ውስጥ ያለው የሀዳር ሸለቆ አፈጣጠርን በማግኘት ለአውስትራሎፒቲከስ አፋሬንሲስ ወይም በሌላ ስሟ ሉሲ መገኘት ትልቅ አስተዋፅዖ ያደረገው ሞውሪስ ታይብ በ86 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡

ሞውሪስ ታይብ ከ86 ዓመት በፊት ነበር በአውሮፓውያኑ ወርሀ ሐምሌ 1935 ቱኒዚያ ውስጥ የተወለዱት፡፡ የወጣትነት ጊዜያቸውንም እዚሁ አህጉራችን አፍሪካ ውስጥ ከነጋዴ አጎታቸው ጋር በመዘዋወር ነበር ያሳለፉት፡፡ በኋላም ወደ እናታቸው ሀገር ፈረንሳይ በማምራት በስነ ምድር የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡

ሞውሪስ በአውሮፓውያኑ 1968 አሰሳ ላይ ባሉበት ወቅት ሀዳር ሸለቆ በሚባለው ስፍራ ላይ የቀንድ አውጣ ቅሪትን ያገኛሉ፡፡ ይህም ቦታው ለቴክቶኒክ ፕሌቶች መገናኛ ካለው ቅርበት አንፃር ሌሎች በርካታ ቅሪቶችን ምናልባትም ጥንታዊ የሰው ልጅ ቅሪቶችንም ይይዝ ይሆናል ብለው እንዲጠረጥሩ አድርጓቸዋል፡፡ በዚህም ሳብያ ፓሊዮአንትሮፖሎጂስቶች (የጥንታዊ ሰው የሰውነት አካሎች እድገት ተመራማሪዎች) ቦታውን እንደዲመረምሩት ጥሪ አደረገላቸው፡፡ ከዚያም ከ4 ዓመታት በኋላ በ1972 ዓለም አቀፍ የአፋር ጥናት አሰሳን (IARE) ቡድንን በመመስረት አካባቢውን መመርመር ተያያዘ፡፡ ታድያ ከሁለት ዓመታት የጥናት ጉዞ በኋላ በሰው ልጅ የዝግመተ ለውጥ ጥናት መስክ እጅጉን ጠቃሚ ከሚባሉ ግኝቶች መካከል የሆነውን የሉሲ ቅሪተ አካል ከቡድኑ አስተባባሪዎች፣ እንዲሁም ከፓሊዮአንትሮፖሎጂስቶቹ ዶናልድ ጆንሰን እና ኢቭ ኮፐንስ ጋር በመሆን ሊያገኝ ችሏል፡፡

ከ2.9 እስከ 3.9 ሚሊዮን ዓመት እድሜ እንዳለው የሚገመተው 52ቱ የሉሲ አፅም ስብርባሪ በተገኙበት ወቅት ሞውሪስ እና ኢቭ በዶናልድ የመስክ ጥናት ቡድን ስር ሆነው ይሰሩ ነበር፡፡ ግኝቱ ከወገብ በላይ ያለው የሉሲ ክፍል አነስተኛ አንጎል እንዳላትና ከጦጣ ዝርያዎች ጋር እንደምትመሳሰል ሲያሳይ ከወገብ በታች ያለው ክፍሏ ግን በሁለት እግሯ የምትራመድ ስለመሆኗ አመላክቷል፡፡ ታድያ በወቅቱ “ሉሲ ኢን ዘ ስካይ ዊዝ ዳይመንድስ” የተሰኘው በዝነኛው የቢትልስ ባንድ የተቀነቀነ ሙዚቃ በካምፑ በስፋት ይደመጥ ስለነበር ሉሲም ከዚህ ሙዚቃ መነሻነት ስያሜዋን ልታገኝ ቻለች፡፡

የቅርብ ጓደኛው እና የስራ አጋሩ ዶናልድ ጆንሰን እንደሚለው ሞውሪስ በአፋር ኢትዮጵያ ያደረገው አሰሳ በቀጣይ በርካታ ባለሙያዎች የእርሱን ዱካ ተከለትለው በስፍራው ምርምር እንዲያደርጉ አድርጓል፡፡ ይህም 6 ሚሊዮን አመታትን የሚዘረጋው የአፋር የሰው ልጅ ታሪክ ዳራ በስፋት እንዲጠናና የኋላ ኋላም በርካታ ጥንታዊ ቅሪቶች ከስፍራው እንዲገኙ ማስቻሉን ዶናልድ ይናገራል፡፡

ምንጭ፤ ዘ ሳይንቲስት
ለተጨማሪ፤ https://www.the-scientist.com/news-opinion/maurice-taieb-geologist-who-discovered-lucy-site-dies-at-86-69134?utm_content=178244671&utm_medium=social&utm_source=twitter&hss_channel=tw-18198832
ትዊተር ለተጠቃሚዎቹ ገቢ ማስገኛ ስርዓት አዘጋጀ
*****************************************
****
ትዊተር የተባለው የማህበራዊ ሚዲያ አማራጭ ሱፐር ፎሎውስ የተሰኘ ብዙ ተከታይ ያላቸው ሰዎች ተከታዮቻቸውን እንደ ገቢ ምንጭ የሚጠቀሙበትን ስርዐት መዘርጋት ማሰቡን ይፋ አድርጓል፡፡ በተለይም በተለያዩ ዘርፎች ከዋክብት የሆኑና ተወዳጅ የሆኑ ሰዎች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተከታይ ያላቸው በመሆኑ ትዊተር እነዚህን ሰዎች አላማ አድርጎ የክፍያ ስርዓቱን ዘርግቷል፡፡
ለምሳሌ ሜካፕ አርቲስቶችና የስፖርት ተንታኞች ‹ከመጋረጃ ጀርባ› የሚባሉ ሁነቶችን ለተከታዮቻቸው ከ3 እስከ 10 ዶላር በሚደርስ ዋጋ እንዲያቀርቡ ሁኔታወችን ትዊተር አመቻችቷል፡፡ በሱፐር ፎሎው የትዊተር ተጠቃሚዎችና ብዙ ተከታይ ያላቸው ሰዎች ለተከታዮቻቸው የሚቀርቡ የተለያዩ ውይይቶችን ማቅረብ የሚችሉ ሲሆን በዚህም ገቢ ማግኘት ይችላሉ፡፡
እንደ ትዊተር መረጃ ከሆነ እንዲህ አይነት እድሎች ሊኖሯቸው የሚችሉ ተጠቃሚዎች አክቲቪስቶች፣ ጋዜጠኞች፣ ሙዚቀኞች፣ ጸሐፊዎች፣ የውበት ሙያተኞችና የመሳሰሉ ታዋቂ ሰዎች ናቸው፡፡ አሁን ላይ ትዊተር አዲሱን ስርዓት በመሞከር ላይ ሲሆን በሰሜን አሜሪካ የተወሰኑ የትዊተር ፈጣሪዎችን (creators) ወደ ስራ አስገብቷል፡፡ ሌሎች የአፕል ሞባየይልን የሚጠቀሙ የትዊተር ተጠቃሚዎች ሱፐር ፎሎውን በመጭዎቹ ሳምንታት ሊጠቀሙ እንደሚችሊ ተነግሯል፡፡
ትዊተር አንድ ሰው ከተከታዮቹ ከሚያገኘው ከ3 በመቶ በላይ እንደማይወስድ የተናገረ ሲሆን ይህም አንድ ተጠቃሚ በተዘረጋው ፕላት ፎርም 50 ሺህ ዶላር እስኪያገኝ ድረስ የሚቆይ ይሆናል፡፡ መሰረቱን በሳንፍራሲስኮ ያደረገው ካምፓኒ ከ50 ሺህ በኋላ ድርሻውን ወደ 20 በመቶ እንደሚሳድግም አሳውቋል፡፡ በዚህም በአሁኑ ሰዓት 200 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች ያሉት ድርጅት ብዙ ማስታወቂያዎችን ሳይሰራ ገቢውን ማሳደግ የሚያስችለው አሰራር መዘርጋቱ ተነግሯል፡፡
ምንጭ techxplore
ለተጨማሪ ንባብ https://techxplore.com/news/
2021-09-twitter-star-users-money-subscriptions
.html