TechIn2
1.16K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
5 በመቶ የኃይል ማመንጫዎች ለ73% የአለም የካርቦን ልቀት ተጠያቂ ናቸው
=======================
የዓለማችን የግሪንሀውስ ጋዝ ልቀት ከኢንዱስትሪ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ይበልጥ እያደገ እና ትልቅ ስጋት እየወለደ ይገኛል፡፡ አብዛኞቹ ኢንዱስትሪዎች በቀጣዮቹ 20 እና 30 ዓመታት የካርቦን ልቀት መጠንን በከፍተኛ ደረጃ ለማቀነስ እየሰራን ቢሉም አሁን ያላቸው የካርቦን ልቀት ከአመታት በኋላ የታቀደውን እቅድ ምናባዊ ያደርገዋል፡፡ ተመራማሪዎች ይህ የካርቦን ልቀት መጠን በሚፈለገው ደረጃ ለመቀነስ እነዲቻል ከፍተኛ የግሪንሀውስ ጋዝ የሚያወጡ ግዙፍ የሃይል ማመንጫዎች ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል ይላሉ፡፡ በኮሎራዶ ቡልድር ዩኒቨርስቲ የሚገኙት ተመራማሪዎች በአለማችን በከፍተኛ ደረጃ የካርቦን ልቀት የሚስከትሉ ግዙፍ የሃይል ማመንጫዎች ለመለየት ባከናወኑት ጥናት 5 በመቶ የሚሆኑት የኃይል ማመንጫዎች 73 በመቶ ለሚሆነው የአለም የካርቦን ልቀት ዋና ተጠያቂ መሆናቸውን ያነሳሉ፡፡

አንደተመራማሪዎቹ ጥናት ለአለማችን የካርቦን ልቀት መጨመር ከድንጋይ ከሰል ጋር የተያያዙ የሃይል ማመንጫ ኢንዱስትሪዎች ትልቁን ሚና ይጫወታሉ፡፡ ታዲያ በዚህ ዘርፍ ላይ ተሰማርተው የዓለማችን የግሪንሀውስ ጋዝ ልቀት እያባባሱ ከሚገኙ ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች መካከል አስሩ ለአለማችን የካርቦን ዳዮክሳይድ ልቀት ሶስት አራተኛውን ይሸፍናሉ፡፡ በዚህ ልየታ ውስጥ የእስያ ስምንት ሀገራት ዋና ተጠቃሽ ሲሆኑ፤ በዚህም ደቡብ ኮሪያ 3 በመያዝ፣ ቻይና ጃፓንና ህንድ ደግሞ የተቀረውን በማስመዝገብ በቁንጮነት ተቀምጠዋል፡፡ በአውሮፓ የፖላንዱ ቤልቻቶ ከሁሉም የኃይል ማመንጫ ኢንዱስትሪዎች ከፍተኛውን የካርቦን ልቀት በማስመዝገብ በቀዳሚነት ሲቀመጥ በጀርመን መቀመጫውን ያደረገ ሌላ የሃይል ማመንጫ ድርጅት እንዲሁ ከፍተኛ የካርቦን ልቀት በማስመዝገብ በተከታይነት ተቀምጧል፡፡

ተመራማሪዎች እንደሚያነሱት የዓለማችንን የካርቦን ልቀት መጠን በሚፈለገው ደረጃ ለመቀነስ ከፍተኛ የግሪንሀውስ ጋዝ የሚያወጡ እንዲህ ያሉ ግዙፍ የሃይል ማመንጫዎች ኢንዱስተሪዎች ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ ያስቀምጣሉ፡፡ የዓለምን የኢነርጂ ገበያ ብዙም በማያቃውስ መልኩ ከፍተኛ የካርቦን ልቀት በሚያስመዘግቡ መሰል ተቋማት ላይ አስፈላጊውን ቁጥጥር ማድረግ እና አንጻራዊ ቅነሳ እንዲያደርጉ መግፋት በዓለማችን የካርቦን ልቀት ምጣኔ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ተመራማሪዎች ይናገራሉ፡፡

ለአብነት ቻይና ብዛት ያላቸው ከድንጋይ ከሰል ጋር የተያያዙ የሃይል ማመንጫ ኢንዱስትሪዎች ቢኖሯተም የሚስመዘግቡት የካርቦን ልቀት በአንጻራዊነት እጅግ ዝቅ ያለ ነው፡፡ በቻይና ከፍተኛ የግሪንሀውስ ጋዝ የሚያወጡ አምስት በመቶ የሃይል ማመንጫዎች በሀገር ደረጃ ያላቸው የካርቦን ዳይኦክሳድ ልቀት ምጣኔ 25 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ይሁንና በአለም አቀፍ ደረጃ 73 በመቶ ለሚሆነው የአለም የካርቦን ልቀት ዋና ተጠያቂ የሚሆኑት የደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓን፣ ህንድ እና ጀርመን ያሉ ሀገራት በቁንጮነት ባስመዘገቧቸው የኃይል ማመንጫዎች ከፍተኛ የግሪንሀውስ ጋዝ የሚያወጡ ሆነው ይገኛሉ፡፡ ከዚህ አንጻር በእነዚህ ተቋማት ላይ አስፈላጊውን ቁጥጥር እና ግፊት ማድረግ እየተባባሰ የሚመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ አደጋ በመጠኑም ቢሆን ለመቀነስ እንደሚያግዝ ተማራማሪዎች ያስረዳሉ፡፡
ምንጭ፡ zmescience
https://www.zmescience.com/ecology/renewable-energy-ecology/world-power-plants-emissions-17082021/
ሳይንሳዊ ምርምሮች በአማርኛ ሊተረጎሙ ነው
ሳይንሳዊ ምርምሮች በአማርኛ ሊተረጎሙ ነው
=============
ዲኮሎናይዝ ሳይንስ ወይም ሳይንስን ከቅኝ ግዛት ማውጣት የተሰኘ አንድ ፕሮጀክት በአፍሪካርዚቭ ፖርታል ላይ የሚገኙ 180 የምርምር ፅሁፎችን አማርኛን ጨምሮ ወደ ስድስት የተለያየ አፍሪካዊ ቋንቋዎች የመተርገም ስራን ለመስራት አቅዷል፡፡ አማርኛ ከሉጋንዳ ቋንቋ ጋር ሆኖ ምስራቅ አፍሪካን በመወከል የተመረጠ ሲሆን ከደቡባዊ አፍሪካ ኢሲዙሉ እና ሰሜናዊ ሱቱ እንዲሁም ከምዕራባዊ አፍሪካ ሀውሳ እና ዮሩባ ተመርጠው ገብተዋል፡፡ አፍሪካርዚቭ ምርምራቸው ወደነዚህ በርካታ ሚሊዮኖች ወደሚናገሯቸው ቋንቋዎች እንዲተረጎምላቸው የሚፈልጉ ፀሀፊዎች ጥያቄ እንዲያቀርቡም መድረኩን ክፍት አድርጎ ነበር፡፡

ሳይንስን ከቅኝ ግዛት የማውጣት ፕሮጀክቱ በስድስቱ ቋንቋዎች የሚሰጡ ትርጓሜዎችን በበይነ መረብ አማካኝነት ለሳይንሱ ዓለም በነፃ የማቅረብ እና ትርጓሜዎችን ተጠቅሞም የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቀመሮችን በማሰልጠን የትርጓሜ ስራዎችን እንዲሰሩ ለማስቻል እቅድ ይዟል፡፡ ሆኖም በዋናነት ኢላማ ያደረገው ቋንቋዎቹ በዲጂታሉ ዓለም ውስጥ ቦታ እንዲኖራቸው በማድረግ ከዘመኑ ከመገለል ለመታደግ ነው፡፡

ፕሮጀክቱ የዛሬ ዓመት ገደማ ነበር በአውሮፓና ሰሜን አሜሪካን ባሉ መንግስትታና እና ግለሰቦች እንዲሁም ጉግል ኩባንያ ድጋፍ በይፋ የተጀመረው፡፡ በዚህ ስራው ትርጓሜ የሚሰጥባቸው ጥናታዊ ፅሁፎች በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና እና ሒሳብ ትምህርቶች ውስጥ ያሉ በርካታ ዘርፎችን የሚዳስሱ ይሆናሉ፡፡ ዋናው የጥናቱ ፀሀፊ አፍሪካዊ የሆነባቸው ጥናታዊ ፅሁፎችንም አስተርጓሚ በመቅጠር የሚያስተረጉም ይሆናል፡፡

በትርጉም ስራው ወቅት በቋንቋዎቹ ውስጥ አቻ ፍቺ የሌላቸው ቃላት ሲገኙ የቃላት ፍቺ እና የሳይንስ ተግባቦት ባለሙያዎች አዲስ ትርጓሜ እንዲያፈላልጉላቸው የሚተው ይሆናል፡፡ በዚህም ወደ ቋንቋው በመመልከት አዳዲስ ፍቺዎችን ለማግኘት ታስቧል፡፡ ተመሳሳይ ስራን በሳይንስ ተግባቦት ተቋም ውስጥ ሲሰራ የነበረ አንድ ባለሙያ አቻ ፍቺ ያልተገኘላቸው ቋንቋዎችን ቃላቱ ራሱ ወደተገኘበት የግሪክ አልያም ላቲን ቋንቋ በማምራት በዚያ ዘንድ ካለው ትርጓሜ ጋር የሚመሳሰል ፍቺን የመስጠት ስራ መስራቱን ይናገራል፡፡ ለምሳሌ ፕላኔት የሚለው ቃል ፕላኔቴስ ከሚለው የግሪክ ቃል የተገኘ ሲሆን ተጓዥ እንደማለት ነው፡፡ ስለዚህም በኢስዙሉ ቋንቋ ኡመህላባ ወይም ተጓዥ የሚል ስያሜ ሰጥቶ በስራ ላይ አውሎታል፡፡

ሳይንስን በራስ ቋንቋ አለመማሩ በአፍሪካ በተለይ በትምህርት ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ተፅዕንዖን ያሳድራል፡፡ ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ እንኳን 10 በመቶው የሚሆነው ሰው ብቻ እንግሊዝኛን በቤት ውስጥ መግባብያነት የሚጠቀምበት ቢሆንም በትምህርት ቤቶች ግን ዋነኛው የመማርያ ቋንቋ ነው፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያም ከጥቂቶች በቀር እንግሊዝኛንም ሆነ ሌላ ዓለም አቀፍ ቋንቋን በእለት ተዕት መግባብያነት የሚጠቀም ባይኖርም ወደ ትምህርት ስንመጣ እንግሊዝኛ ዋናው የመማርያ ቋንቋ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በዚህ ሳብያ ከ2 ሺህ በላይ የሚሆኑት አፍሪካዊ ቋንቋዎች ከቤት ውስጥ ግላጋሎት ባሻገር ከስራ፣ ትምህርት እና ሳይንሱ ዓለም እየተገለሉ መሆናቸውን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ በእንግሊዝኛ ተፅዕንዖ ስር በወደቀው ያለንበት ዓለም ነገሮች በዚህ መልኩ ቀጥለው አፍሪካዊ ቋንቋዎቹ በተለይ በዲጂታል ቴክኖሎጂው ውስጥ ተካታች የማይሆኑ ከሆነ ወደፊት የመጥፋት አደጋ እንደሚጋረጥባቸውም ተነግሯል፡፡

ዲኮሎናይዝ ሳይንስ የትርጉም ስራውን በወራት ውስጥ አጠናቆ እስከ ቀጣዩ ዓመት ማለትም 2014 ዓ.ም አጋማሽ ድረስ እንደሚያቀርብ ይጠበቃል፡፡

ምንጭ፤ ኔቸር
ለተጨማሪ፤ https://www.nature.com/articles/d41586-021-02218-x?utm_source=twt_nat&utm_medium=social&utm_campaign=nature
ድሮኖች እንደ ካፌ አስተናጋጅ
*********************
የአልፋቤት ድሮኖች ባለፈው አመት ውስጥ 10 ሺህ ሲኒ ቡና እና 1200 የተጠበሰ የዶሮ ስጋ በተለያዩ አካባቢዎች ማድረሳቸው ተነገረ፡፡ ይህም የሆነው በአውስትራሊያ ሎጋን ከተማ ዊንግ በተባለ ድርጅት አማካኝነት ነው፡፡ ይህ ዊንግ የተሰኘ ፕሮጀክት በ2019 በአውስትራሊያ ስራውን በይፋ ጀምሯል፡፡ ስራውን ለመጀመር ከ2014 ጀምሮ ተከታታይ የሆነ የድሮን በረራ ሙከራዎችን ሲያደርግ ነበር፡፡ ይህ ፕሮጀክት አልፋቤት የሚያካሂደው ሰዎች የሞባይል መተግበሪያን በመጠቀም የተለያዩ ምግቦችን እንዲያዝዙ የሚያስችል ጥናት አካል ነው፡፡

ስራው ከተጀመረ ጀምሮ እስካሁን ወደ 1 መቶ ሺህ የሚጠጉ ትዕዛዞችን በመቀበል ማስተናገድ መቻሉን ተቋሙ ያወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡ ይህ ዊንግ የተሰኘ ፕሮጀክት ለወደፊት በሁሉም የአለማችን ክፍሎች የተለያዩ ትዕዛዞችን በድሮን አማካኝነት ለማድረስ ራዕይ እንዳለው ተሰምቷል፡፡ በዚህ ዘርፍ እውቆቹ ዩ.ፒ.ኤስ፣ ኡበርና አማዞን የተለያዩ ሸቀጦችን በድሮን የማድረስ ስራዎችን እየጀመሩ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ድርጅቱ በመረጃ ገጹ ላይ ያስነበበው መልዕክት እንደሚያመለክተው በሀገሪቱ ካሉ የተለያዩ የቡና ሱቆችና በአለማቀፍ ደረጃ ከታወቁ 30 የሚደርሱ ድርጅቶች ጋር በጋራ እየሰራ እንደሆነ አሳውቋል፡፡ ባሳለፍነው አመት በኮቪድ ምክንያት ትምህርት በተቋረጠ ጊዜ ዊንግ ከቨርጂኒያ ትምህርት ቤት ጋር መጻህፍትን ለማድረስ ስምምነት አድርጎ እንደነበርም መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ዊንግ የተባለው የድሮን አገልግሎት ሰጭ ተቋም በ2019 በአሜሪካ ፌዴራል የአቪየሽን አስተዳደር የእውቅና ፈቃድ የተሰጠው የመጀመሪያው ድርጅት ነው፡፡

ምንጭ CNBC Technology
ተጨማሪ ንባብ https://www.cnbc.com/2021/08/25/alphabet-wing-drones-delivered-10000-cups-of-coffee-in-the-last-year.html?utm_term=Autofeed&utm_medium=Social&utm_content=Tech&utm_source=Facebook&fbclid=IwAR2v7uxu58B9ctKE41eLsgWVqesmddrNRBthBkxI4RHcqs3GCi_FkOeDIdw#Echobox=1629908227
በጤናው ሴክተር የናኖ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም
=========================
በህክምና ዘርፍ በሽታን ለመመርመርና ለማከም አጉልተው የሚያሳዩ መሳሪያዎችን መጠቀም የማይተካ ሚና አለው፡፡ በዚህ ረግድ ማይክሮስኮፕ፣ ኤክስርይ፣ ኤም አር አይ፣ አልትራ ሳውንድ ሌሎች መሳሪያዎች በጥቅም ላይ ውለዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የናኖ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በሴልና በሞሎኪል ድርጃ ያሉትን አካላትን አንጥሮ ለማየት ጥቃቅን ተንቅሳቃሽ የናኖ ንጥረ ነግሮች (ናኖ ፓርቲክልስ) የመጠቀም አስፍላጊነት እየጎላ መጥቷል፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ ጥቃቅን የሰውነት አካላትን በከፍትኛ ጥራት ከማሳየቱም ባለፈ የመዋሃድ ችግር ያለባቸውን መድኃኒቶች የመዋኃድ አቅማቸውን መጨመሩ የወደፊቱን የጤና ስርዓት በእጅጉ እንዲያግዝ ያስችለዋል፡፡

ናኖ ቴክኖሎጂ በጤናው ዘርፍ አመርቂ የተባሉ በርካታ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ ይገኛል። የናኖ ህክምና ዘርፍ እንደ ካንሰር ባሉ አደገኛ ህመሞች በመከላከል፣ በመመርመርና በማከም ረገድ ብሩህ ተስፋዎችን በመፈንጠቅ ላይ ይገኛል። በህክምናው ዘርፍ ቴክኖሎጂው መድሃኒትን ለይቶ ወደ ታመመ ሰውነት ክፍል ብቻ የማድረስ፣ በሰውነት ውስጥ የተጎዱ ወይንም የታምሙ የአካል ክፍሎችን በቀላሉ አጉልቶ ለማየት፣ በሰውነት ውስጥ የአካል ክፍሎችን የሚተኩ ተከላዎችን ማድረግ እንዲሁም ቲሹዎችን እንደ እዲስ ማሳድግ የመሳሰሉት ተጠቃሾች ናችው። ናኖ ቴክኖሎጂ የመዋሃድ ችግር ያለባቸውን መድኃኒቶች የመዋኃድ አቅማቸውን መጨመሩ፣ መድኃቶችን በቀላሉ በሰውነት ውስጥ ከሌሎች ንጥረ ነገሮች ጋር ተዋህድው ከአገልግሎት ውጪ እንዳይሆኑ ማገዙ፣ መድኃኒቶች ወደ ተፈለገው ቦታ፣ በተፈለገው ጊዜና መጠን በሰውነት ውስጥ እንዲሰራጩ መርዳቱ እንዲሁም መድሃኒት ባጭር ጊዜ ውስጥ እንዲመረት ማገዙ በጤናው ሴክተር ትልቅ ተስፋን አስገኝቷል፡፡

ከዚህ በተጓዳኛ ይህ ቴክኖሎጂ ዋነኛ አላማው ፈዋሽ ኬሚካሎችን ለሰውነታችን ተስማሚ በሆነ መንገድ እንዲሰሩ የሚረዳ ሲሆን ይህም የተለያዩ በናኖደረጃ ባሉ ተሸካሚዎች (nanocarriers) ማለትም ናኖ ፓርቲክሎች፣ ናኖካፕሱሎች፣ ዴንደሪመሮች እና ሌሎችንም መጠቀም ያጠቃልላል፡፡ ይህም ከላይ ለተጠቀሰው ኢላማውን ለጠበቀ መድኃኒት አሰጣጥ መንገድ ከፍተኛ አስተዋፆ ይኖረዋል፡፡
ምንጭ፡ scidev እና Tech science
https://www.scidev.net/global/features/nanotechnology-for-health-facts-and-figures-1/
ሩሲያ በሰማይ ላይ እርሻ ልትጀምር ነው
ሩሲያ በሰማይ ላይ እርሻ ልትጀምር ነው
===========
ሩሲያ እፅዋትን በከፍተኛ ደረጃ ለማምረት የሚያስችላትን ሙከራ ዓለም አቀፉ የህዋ ምርምር ጣብያ ላይ በሚገኘውና ኖውካ በሚሰኘው አዲሱ የምርምር ክፍሏ ልታከናውን ነው፡፡ በሩሲያ ሳይንስ አካዳሚ ስር ባለው ኢንስቲትዩት ኦፍ ባዮሜዲካል ፕሮብሌምስ ውስጥ የባዮሜዲካል ቤተ ሙከራ ዋና ሀላፊ የሆኑት ዩሪ ስሚርኖቭ እንደሚሉት ሙከራው ወደፊት በከፍተኛ ደረጃ እፅዋትን ለማምረት የሚችል የአትክልት ስፋራን ጠፈር ላይ ለመፍጠር ያለመ ነው፡፡

ሙከራው የሚከናወነው በቀንድ አውጣ አምሳል የተሰራ የአትክልት ስፍራን ጠፈር ላይ ባለው በዚህ ቦታ በመላክ ነው፡፡ ተመራማሪዎቹ እፅዋቱን በተለያዩ ወቅቶች አትክልት ስፍራው ላይ በተወሰነ ርቀት አከታትለው ሲተክሏቸው በየጊዜያቱም ምርቱን የሚሰበስቡ ይሆናል፡፡ በቦታው የሚተከለው የመጀመሪያው አትክልት የናፓ ጎመን ሊሆን እንደሚችልም ዩሪ ስሚርኖቭ ጠቁመዋል፡፡ ታድያ ከተሰበሰበው ምርት ውስጥ የህዋ ተመራማሪዎቹ ለመመገብ ሲፈቀድላቸው የተወሰነው ደግሞ ወደ ምድር እንደሚላክ ተነግሯል፡፡ ወደፊትም የህዋ ተመራማሪዎቹ አዝዕርት፣ ስራ ስሮችን እና ቲማቲምን በቦታው ያመርታሉ ሲሉ ዩሪ ገልፀዋል፡፡

ለተለተለያዩ የጥናት አገልግሎቶች የሚውለው የኖውካ ቤተ ሙከራ ከአንድ ወር በፊት ነበር ወደ ህዋ በማቅናት ከዓለም አቀፉ የህዋ ምርምር ጣብያ ጋር የተቀላቀለው፡፡ ቤተ ሙከራው ሩሲያ በዓለም አቀፉ የህዋ ምርምር ጣብያ ላይ ያላትን የምርምር ቦታ ከፍ የሚያደርግና በዚያ ለሚገኙት ተመራማሪዎቿም ተጨማሪ የመስሪያ፣ እቃ ማስቀመጫና የውሃና ኦክስጅን የማምረቻቸውን የመያዣ ስፍራ የሚሰጣቸው ነው፡፡ በተጨማሪም ለተመራማሪዎቹ ከዚህ ቀደም ባላቸው አንድ መፀዳጃ ቤት ላይ ሌላ ሁለተኛ ሲጨምርላቸው አንድ ሌላ ተመራማሪ ተመራማሪንም ማስቀመጥ የሚችል ቦታ አለው፡፡ ሌላኛው የዚህ አዲስ ቤተ ሙከራ ገፅታ ወደ ውጪ ሳይወጡ እዚያው ጣብያው ውስጥ ሆነው አንዳንድ ተግባራትን ለማከናወን የሚያስችለው የአውሮፓ ሮቦታዊ እጅ (ERA) የተገጠመለት መሆኑ ነው፡፡

የምርምር ስራው የሩሲያ ተመራማሪዎችን ከህዋ ተመራማሪነታቸው በተጨማሪ የሰማይ ላይ ገበሬም ያደርጋቸዋል ማለት ነው፡፡

ምንጭ፤ የሩሲያ ዜና ኤጀንሲ (ታስ)
ለተጨማሪ፤ https://tass.com/science/1323909
ቋንቋና ሙዚቃ የሚያስተምረው የጆሮ ማዳመጫ
************************************
ሂሬብል የተሰኘና ገመድ አልባ የሆነ የጀሮ ማዳመጫ በሰው ሰራሽ አስተውሎት በመታገዝ ቋንቋና ሙዚቃ እንዲያስተምር ተደርጎ መሰራቱ ተሰማ፡፡ ይህ የጀሮ ማዳመጫ መናገሪያ እና ማዳማጫን በአንድ አስተባብሮ የያዘ ነው፡፡ ጀሮ ማዳመጫው ሲሰራ ከኢንተርኔትና ከተለያዩ የኤሌክትሪኒክስ ቁሶች ጋር መገናኘት እንዲችል ተደርጎ እና በየእለቱ ያለምንም ችግር ጀሯችን ላይ ማድረግ እንድንችል ተደርጎ ነው፡፡

ይህ የጆሮ ማዳመጫ የተለያዩ ጥቅሞች ያሉት ሲሆን መደበኛ የጀሮ ማዳመጫዎች ከሚሰጡት አገልግሎት በተጨማሪ ነገሮችን ከመስማትና ከማስታወስ ጋር የተለያዩ ድጋፎችን ለተጠቃሚው የሚሰጥና ከድምጽ ጋር የተያያዙ የተለያዩ ተግባራትን የሚከውን ነው፡፡

ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም የጀሮ ማዳመጫው የጆሮን ደህንነት ከመከታተል ባለፈ አዲስ ቋንቋን ለመማር ከፍተኛ ድጋፍ ማድረግ የሚችል ነው ተብሏል፡፡ በዚህም ምክንያት ቴክኖሎጂውን ለትምህርቱ ዘርፍ ሊኖረው የሚችለውን ጥቅም በማጥናት ላይ መሆናቸውን አንዳንድ በትምህርት ዘርፍ ስላሉ ቴክኖሎጂዎች ጥናት የሚያደርጉ ተመራማሪዎች አሳውቀዋል፡፡ በትምህርት ዘርፍ በብዛት እውቀት የሚተላለፈው በጽሁፍ በመሆኑ ድምጽንም በተሻለ መጠን ለመጠቀም እንደሚያስችል ሀሳቦች እየወጡ ነው፡፡

አዲሱ ቴክኖሎጂ ተማሪዎች የተለያዩ ትምህርቶችን በቀጥታ መከታተል እንዲችሉ፣ የማስታወሻ መልእክቶችን እንዲሰሙና ሌሎች ከትምህርት ጋር የተያያዙ ድጋፎችን እንንያገኙ የሚያስችል ነው፡፡ በተጨማሪም ዌሬብል የተባለው ቴክኖሎጂ ተማሪዎች በትምህርት ጊዜ የሚፈልጉትን ድምጽ በመቅዳት የበለጠ መረዳት እንዲችሉ ያስችላቸዋል፡፡ ሌላው የዚህ ቴክኖሎጂ ጥቅም የተባለው ከአንድ ቋንቋ ወደ ሌላ ቋንቋ በመተርጎም ማስደመጥ መቻሉ ነው፡፡

ቴክኖሎጂው ያለው ባዮሜትሪክ አቅም ሰዎች ሙሉ የጤና ሁኔታቸውን መከታተል የሚያስችላቸው በመሆኑ ለጤና ትምህርትም እጅግ ጠቃሚ እንደሚሆን ታምኖበታል፡፡ ከመማር ማስተማሩ ማለትም መደበኛ እና መደበኛ ካልሆነው የትምህርት ሂደት በተጨማሪ ቴክኖሎጂው በቤት ውስጥ ያሉ የድምጽ ትዕዛዝ መቀበል የሚችሉ መገልገያዎችን በድምጽ ለማንቀሳቀስ እንደሚያስችል ተነግሯል፡፡

ምንጭ techxplore
ተጨማሪ ንባብ https://techxplore.com/news/2021-08-wearable-tech-ears-hearables-language.html
ዘመናዊ የሀገር አቋራጭ ባስ ትኬት መቁረጫ ስርዓት፤ ለኢትዮጵያውያን
ዘመናዊ የሀገር አቋራጭ ባስ ትኬት መቁረጫ ስርዓት፤ ለኢትዮጵያውያን
==============
ሰላምቴክ ቢዝነስ ኩባንያ ስማርትጉዞ የተሰኘውን አዲስና ተጠቃሚዎችን ከመጉላላት ሊታደግ ያለመ የኤሌክትሪኖኒክ ባስ ትኬት መቁረጫ ስርዓትን አቅርቧል፡፡ ስርዓቱ ተጠቃሚዎች በበይነ መረብ አማካኝነት የሀገር አቋራጭ ባሶችን ትኬት መቁረጥ የሚችሉበት ሲሆን ከትኬት መቁረጥ ባሻገርም ክፍያቸውን በኤሌክትሮኒክ መንገድ እንዲፈፅሙ፣ የመቀመጫ ወንበራቸውን እንዲመርጡ፣ ለሀገራችን የትራንስፖርት ዘርፍም ቢሆን ሪፖርት የማዘጋጀት ስርዓቱን በይነ መረብ ላይ ተመስርቶ እንዲከናወንና እንዲዘምን ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተነግሮለታል፡፡

ተጠቃሚዎች ጉዙ ለማድግ በሚፈልጉበት ወቅት ወደ ድረ ገፁ በማምራት፣ በስልክ መተግበሪያው አልያም 9211 ስልክ ቁጥርን ተጠቅሞ ወደ ማዕከሉ በመደወል አገልግሎቱን ማግኘት የሚችሉ ይሆናል፡፡ በዚህም መጠቀም የሚፈልጉትን የባስ አይነት፣ የሚነሱበትን ቦታ፣ መዳረሻቸውን፣ እንዲሁም ጉዞዋቸው የደርሶ መልስ ከሆነ የመመለሻ ቀናቸውን በማስገባት ትኬቱን መቁረጥ ይችላሉ፡፡ በተጨማሪም ስርዓቱ ለተጠቃሚዎች ቀላል ይሆን ዘንድ በሦስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ እና እንግሊዝኛ) እንዲሰራ ተደርጎ ቀርቧል፡፡ የተጠቃሚዎችን የጉዞ ታሪክ መዝግቦ የሚያስቀምጠው ስማርትጉዞ ተጠቃሚዎች ጉዞን እንዲሰርዙና ክፍያቸውም እንዲመለስላቸው እንደሚያድርግ አስቀምጧል፡፡

አሁን ላይ አገልግሎቱ የሚሰራው ለሐበሻ ባስ ተጠቃሚዎች ብቻ ሲሆን በመጪዎቹ ጊዜያት ግን ሌሎች የሀገር አቋራጭ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችን ወደ ዝርዝሩ ለመክተት እየሰራ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በክፍያ ረገድም በሲቢኢ ብር አማካኝነት ነው ለአሁኑ ትኬቱን መግዛት የሚችሉት፡፡

ስላምቴክ በወጣት የዩኒቨርሲቲ መምህራን የተቋቋመ ጀማሪ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ሲሆን የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማም አግሪፈንድ የተሰኘውንና እንደነ እርሱ ያሉ አዳዲስ ቢዝነሶች በቀላሉ ገንዘብ ማሰባሰብ የሚችሉበትን የበይነ መረብ ገፅ ሰርቶ በማቅረብ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

አገልግሎቱን ለማግኘት ወደ ድረ ገፃቸው (https://smartguzo.com/) በማምራት አልያም በጉግል ፕሌይ ስቶር (https://play.google.com/store/apps/details?id=com.smartguzo.passenger&hl=en&%20gl=US) አማካኝነት መተግበሪያውን አውርዳችሁ መጠቀም ትችላላችሁ፡፡

ምንጭ፤ ሸጋ
ለተጨማሪ፤ https://shega.co/post/selamtech-business-launches-smart-guzo-a-bus-e-ticketing-system/
የኮቪድ ክትባት የ140 ሺ ሰዎችን ህይወት ታድጓል
=======================
የኮሮናቫይረስ ከተከሰተ አንስቶ የዓለማችን ሁለንተናዊ መልክ በተለያየ ደረጃና ቅርፅ የመለዋወጥ አድል ገጥሞታል፡፡ ወረርሽኙ በዓለም ላይ እየተስፋፋ ሲመጠና በሰው ልጆች ህልውና ላይ ትልቅ ስጋት እየፈጠረ ሲሄድ ብዙዎች ነገን የማየት እድል እንዳይኖራቸውና ተስፋን እንዳይሰንቁ አድርጓቸዋል፡፡ የኮቪድ ክስተት ከዚህ በኋላ ለሚመጡት አመታት በአለም አቀፍ ደረጃ የሚያስከትለውን የረዥም ጊዜ አደጋ በተለያዩ ጥናቶች የሚዳሰስ ቢሆንም አለማችንን ባመሰበት በዚች ጥቂት ጊዜያት ውስጥ የሰዎችን ህይወት ከመቅጠፉ ባለፈ በማህበራዊ ትስስሩ፣ በኢኮኖሚ መሰረተ ልማት፣ በዜጎች የስራ እድል ፈጠራ እንዲሁም በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከባድ የሚባል ጫናን አሳርፏል፡፡

የኮቪድ ወረርሽኝ አለምን ባስጨነቀበት ጊዜያት ሰዎች ወደመደበኛ ህይወት የመመለስ ተስፋቸውን እዲሰንቁ ካደረጋቸው ምክንያቶች መካከል በፍጥነት ሲከናወኑ የነበሩት የኮቪድ ክትባቶዎች በቀዳሚነት ሊቀመጡ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ክትባቶች ውጤታማነታቸው እና ደህንነታቸው ይበልጥ ባደገ ቁጥር የወረረሽኙን አደጋ የመቀነስ እድላቸው የተረጋገጠ ቢሆንም በተጨባጭ ሁኔታ ክትባቶቹ የሰዎችን ህይወት በመታደግ እና የወረርሽኙን ስጋት በመቀነስ በኩል ያላቸው አስታዋፅዖ ገና ምርምር ይደረግባቸዋል፡፡ ወረርሽኙ በአለም አቀፍ ደረጃ ካደረሰው ጉዳት አንጻር በሁሉም ሀገራት የተሰራጨው የክትባት አይነት ምን ያህል ጉዳት ቀንሷል የሚለው ወደፊት በሚሰሩ ጥናቶች ይበልጥ የሚብራራ ቢሆንም ከሰሞኑ በአሜሪካ ብቻ በተሰራው ጥናት የክትባቱ ስርጭት ከሚታሰበው በላይ የሰዎችን ህይወት መታደግ እንደቻለ ያሳየ ነው፡፡

አጥኚዎች እስከግንቦት አጋማሽ ተካሄደው በነበሩ የክትባት ፕሮግራሞች ላይ ትኩረታቸውን አድርገው ባወጡት ጥናት በክትባቶቹ አጋዥነት በጥቅሉ የ140,000 ሰዎችን ህይወት መታደግ የተቻለ ሲሆን፤ ከሶስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ደግሞ በኮቪድ ወረርሽኝ እንዳይያዙ ማድረግ ተችሏል፡፡ ከብዙ ዩኒቨርስቲዎችና የምርምር ተቋማት በተወጣጡ ተማራማሪዎች የተከናወነው ይህ ጥናት በሁሉም ግዛቶች የተካሄዱትን የክትባት ዘመቻዎች እና የሟቾች ቁጥር ከአንድ የሂሳብ ሞዴል ጋር በማቀናበር ክትባቶቹ ባይሰጡ ኖሮ ሊኖር የሚቸለውን የሞት ምጣኔ እና ክትባቶቹ ሰዎች ጋር ደርሰውም ሊያጋጥም የሚችለውን የሞት ምጣኔ ከግምት ውስጥ በማስገባት የተከናወነ ነው፡፡

ተመራማሪዎች የክትባት ስርጭት መረጃዎች በትክክል መመዝገበ ከጀመረበት የመጋቢት ወር አንስቶ እስከ ግንቦት አጋማሽ ድረስ የነበሩ የክትባት ፕሮግራሞችን ከተገበሩት የሂሳብ ሞዴል ጋር በማጣመር በኮቪድ 19 ዙሪያ ይመዘገቡ የነበሩ የታማሚዎች ብዛት እና የሞት መጣኔዎች ላይ ትንተና ሰርተዋል፡፡ በዚህ ወጤት መሰረትም በኮቪድ ሊሞቱ የሚችሉ ከ139,393 እስከ 140 ሺ ሰዎች በክትባቶቹ አጋዥነት ህይወታቸውን ማዳን የተቻለ ሲሆን፤ ይህን የሞት ምጣኔ ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የ1.4 ትሪሊዮን የኢኮኖሚ ጥፋት እንዲሁ መታደግ ተችሏል፡፡

ይህ የጥናት ውጤት ከወረርሽኙ ተለዋዋጭነት አንጻር አስከግንቦት አጋማሸ ያለውን ብቻ የሚያጠቃልል ቢሆንም፣ በማሳያ ደረጃ የክትባቶች ስርጭት መፋጠን በአለም አቀፍ ደረጃ የብዙ ሚሊዮኖችን ህይወት ለመታደገ እና የኢኮኖሚ አደጋንም ለመቀነስ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው በግልጽ የሚሳይ ነው፡፡ ጥናቱ ባካለላቸው የአሜሪካ ግዛቶች በኮቪድ ምክንያት ብዙ ሞት የተመዘገበባቸው (99.5%) ቦታዎች በአንድም ይሁን በሌላ የክትባት ዘመቻውን ያልተቀበሉ ወይም ክተባቱን ያላገኙ ሰዎች ላይ ያነጣጠረ መሆኑ የክትባቶቹ ሚና ከሚታሰበው በላይ እጅግ የገዘፈ እንደነበር የሚያመላክት ነው፡፡
ምንጭ፡ zmescience
https://www.zmescience.com/science/news-science/covid-vaccines-saved-at-least-140000-lives-as-of-early-may/
ከሌጎስ እና እንደዋዛ በየጊዜው ከሚደረመሱት ህንፃዎቿ ምን እንማር?
ከሌጎስ እና እንደዋዛ በየጊዜው ከሚደረመሱት ህንፃዎቿ ምን እንማር?
==================
በህዝብ ብዛቷ ከአፍሪካ ከተሞች ቀዳሚ የሆነችው የናይጄሪያዋ ሌጎስ በአህጉሪቱ ካሉ ቀዳሚ የንግድ ምዕከሎች ውስጥ ትጠቀሳለች፡፡ ሆኖም የህንፃዎቿ ደህንነት ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ ከሚባሉት መካከል ያደርጋታል፡፡ በከተማይቱ ከአውሮፓውያኑ 2005 እስከ 2016 ባሉት ዓመታት ውስጥ ብቻ 115 ህንፃዎች መቆም አቅቷቸው በራሳቸው ጊዜ ፈርሰዋል፡፡ በዚህም ሳብያ 4 ሺህ ያህል ቤተሰቦች ወደ ቤት አልባነት እንዲወርዱና ብዙዎችም ውድ ህይወታቸውን እንዲያጡ ሆነዋል፡፡ በተለይ ሁኔታው ከፍተኛ በነበረባቸው 2011፣ 2012 እና 2019 ዓመታት ውስጥ 19፣ 14 እና 17 ህንፃዎች ተንደዋል፡፡

እነዚህ እንደ እምቧይ ካብ ተንደው ከፈረሱት ባለ በርካታ ወለል ህንፃዎች መካከል 76.6 በመቶው የመኖርያ፣ 13 በመቶው የንግድ፣ የተቀረው 9.4 በመቶ ደግሞ የተቋማት ህንፃዎች ነበሩ፡፡ ሁኔታው ላይ ጥናት አድርጎ የህንፃዎቹ መፍረክረክን በጥልቀት የመረመረው የዘ ኮንቨርሴሽኑ ፀሐፊ አዴጁዋን ሶዬንካ በከተማው የግንባታው ዘርፍ ባለሙያዎችን በማነጋገር ለእነዚህ ጥፋቶች በዋናነት፤ ህንፃዎቹ የተገነቡት ብቃቱ በሌላቸውና ለስራው በማይመጥኑ ሰዎች መሆኑ፣ ከደረጃ በታች የሆኑ የህንፃ ግንባታ ቁሳቁሶች ጥቅም ላይ መዋላቸው፣ ህንፃዎቹ ላይ የሚከናወን ሕገ ወጥ የአገልግሎት ቅያሬ ወይም ማስተካከያ እንዲሁም ለህንፃዎቹ የሚደረግ ጥገና ማነስ ነው ሲል አስቀምጧል፡፡ ለዚህም በዋናነት በኮንትራክተሮቹ በኩል ያለ ግድ የለሽነት እንዲሁም በመንግስት በኩል ያለው የቁጥጥር ማነስ እና በዘርፉ የተስፋፋው ሙስና በምክንያትነት ይጠቅሳሉ፡፡

የሌጎስ ከተማ አስተዳደር የህንጻዎቹን ሁኔታ ከንድፍ አንስቶ እስከ ግንባታና ህንፃ ሆነው እስከቆሙበት ጊዜ ድረስ ቁጥጥር የሚያደርጉ አራት ተቋማትን አቋቁሞ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ሆኖም በግንባታው ላይ ያሉ ባለሙያዎች እነዚህ ተቋማት የባለሙያ እጥረት ያለባቸው ከመሆናቸውም ባሻገር እንደ መኪና የሉ በቂ ግብዓቶች የማይቀርቡላቸው ናቸው ሲሉ ይገልጿቸዋል፡፡ የህግ እርምጃዎችን ከተመለከትን ከ10 ዓመት በፊት የፈረሱ ህንፃዎች ሲኖሩ ህንፃው በመንግስት ቁጥጥር ስር እንዲወድቅ የሚያዝ ሕግ ቢወጣም የህንፃው ባለቤት ጣቱን ህንፃውን ወደገነባው ድርጅት ከጠቆመ እራሱን ነፃ የሚያወጣና እርምጃውም የማይመለከተው ይሆናል፡፡ መንግስት ህንፃውን በገነባው አካል እና ባለሙያዎች ላይ ፍቃድን የመንጠቅና ሌሎችም የቅጣት እርምጃዎችን የማስተላለፍ ስልጣን ቢኖረውም እስካሁን ግን ለጥፋታቸው ቅጣት ያገኙ የሉም፡፡

እኛስ?

ምንም እንኳን በኢትዮጵያ ከተሞች በዚህ መልኩ ስር የሰደደ የህንፃዎች ተንዶ መፍረስ ስለመኖሩ በማስረጃ አስደግፎ መከራከሩ አዳጋች ቢሆንም በተለያዩ ወቅቶች ግን በተለይ በመዲናችን አዲስ አበባ በግንባታ ላይ ያሉ ህንፃዎች ተንደው ሰብዓዊም ሆነ ቁሳዊ ጥፋትን ሲያስከትሉ ተመልክተናል፡፡ ምጣኔ ሐብታዊ እንቅስቃሴው እያደገና ከገጠር ተነስቶ ወደ ከተሞች የሚፈልሰው ህዝብ ማደግንም ተከትሎ ከተሞቻችን መልካቸው ያለማቋረጥ እየተቀየረና የግንባታ ስራዎችም እየተስፋፉ እንደመሄዳቸው መጠን ከሌጎስ ውድቀት ተምሮ የቁጥጥር ስርዓቱን ጠበቅ ማድረጉ የብልህ እርምጃ ነውና ችላ ሊባል አይገባም፡፡

ምንጭ፤ ዘ ኮንቨርሴሽን
ለተጨማሪ፤ https://theconversation.com/building-collapses-are-all-too-common-in-lagos-heres-why-165674
ያለ ወንድ ዘር በራሷ አርግዛ ልጅ የወለደችው እናት
============
ከሰሞኑን ባልተለመደ ሁኔታ አንዲት ህፃን ያለ አባት መወለዷ ተሰምቷል፡፡ በጣልያኑ የካላ ጎኖኔ የውሃ ገንዳ ውስጥ የተወለደችውና ኢስፔራ የመል ስያሜ የተሰጣት አንዲት የስሙዝሀውንድ ሻርክ (Mustelus Mustelus) ለየት ባለ ሁኔታ ላለፉት አስር ዓመታት በውሃ ማጠራቀሚያው ውስጥ ከሌላ ሴት ሻርክ ጋር ብቻ ከኖረች እናቷ ተወልዳለች፡፡

በሳይንሳዊ አጠራሩ ፓተኖጀነሰስ ተብሎ የሚታወቀው ይህ ሁኔታ ሴቶች እንቁላላቸውን በራሳቸው ወደ ህይወት ማምጣት የሚችሉ ሆነው ሲገኙ እጅጉን አልፎ አልፎ የሚከሰት ነው፡፡ ፓተኖጀነሰስ ከዚህ ቀደም ሻርክና ሌሎች አሳዎችን ጨምሮ ከ80 በሚበልጡ የጀርባ አጥንት ያላቸው የእንስሳት ዝርያዎች ላይ የታየ ሁነት ነው፡፡ ሆኖም ተመራማሪዎች ሁኔታውን አይተው ሲመዘግቡ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜያቸው ሳይሆን አይቀርም፡፡ ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት ሁኔታውን የመመልከት ዕድሉ ያለው የሰው ልጅ ለይቶ ባስቀመጣቸው እንስሳ ላይ ብቻ በመሆኑ ነው ብዙም ሳይመዘገብ የቀረው፡፡

ፓተኖጀነሰስ እጅጉን አልፎ አልፎ የሚታይ ነገር ይሁን እንጂ በተለያዩ አይነት እንቁላሉን የሚጥሉም ሆነ ልጁን የሚወልዱ የሻርክ ዝርያዎች ላይ ሊታይ ይችላል፡፡ 15 ያህል የሻርክ ዝርያዎች ፓተኖጀነሰስ የማሳየት እድል እንዳላቸው ይነገራል፤ በተለይ ደግሞ የኋይት ስፖትድ ባምቡ (Chiloscyllium Plagiosum) እና ዜብራ (Stegostoma Tigrinum) ሻርኮች ላይ፡፡

በዱር የሚኖሩ እንስት ሻርኮች ከሌሎች በመራራቃቸው አልያም እንደ አየር ንብረት ለውጥ እና ዓሣ ማስገር ባሉ ሰው ሰራሽ ምክንያቶች ፈላጊ ወንድ ሲያጡ ፓተኖጀነሰስን እንደ መጨረሻ አማራጭ ወስደው ለዓመታት በዚህ መልኩ ሲወልዱ ታይተዋል፡፡ ሰው ለይቶ ባስቀመጣቸው ላይም እንዲሁ የወንድ ማጣት ሲኖር ተፈጥሮ ፓተኖጀነሰስን ልታስጀምርላቸው ትችላለች፡፡ ሌሎች ደግሞ በፓተኖጀነሰስ አማካኝነት ልጅ ሲያገኙ ከቆዩ በኋላ ወንድ ሲያገኙ ግን ዳግም ፆታዊ ግንኙነትን ተጠቅመው ወደ መውለድ ሊሸጋገሩ ይችላሉ፡፡

ፓርቴኖጀነሲስ በሁለት መልኩ ሊፈጠር ይችላል፤ አንደኛው ልከ እንደ እፅዋት ሁሉ በራሒን በማባዛት (Cloning) ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የተፈጥሮን በሚመስል የራስ ስነ-ተዋልዶ (Self-Fertilization) ነው፡፡ በዚህም እንቁላሉን ከዘር ፈሳሹ አዋህዶ ፅንስ ከመፍጠር ይልቅ የተዋሀደ ዘረ-መል (Complementary DNA) በመጠቀም ዘረ-መላቸውን ሙሉ በሙሉ ከእናታቸው ያገኙ ልጆች ይወለዳሉ፡፡

ብዙውን ጊዜ በፓተኖጀነሰስ አማካኝነት የተፈጠረ ፅንስ የመክሸፍ ዕድሉ የሰፋ እንደሆነ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ፡፡ ሆኖም በምን ያህል መጠን ይከሽፋል የሚለውን መከታተሉ አዳጋች ስለሆነ ማወቅ ይከብዳል፡፡ ይህች አዲስ የተወለደችው ሻርክ ግን በመልካም ጤና ላይ ናት ሲሉ ባለሙያዎቹ ተናግረዋል፡፡

ምንጭ፤ ላይቭ ሳይንስ
ለተጨማሪ፤ https://www.livescience.com/aquarium-shark-virgin-birth.html