TechIn2
1.16K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
ብዙ ሚሊዮኖችን ዘርፈው የመለሱት ሃከሮች
========================
በሳለፍነው ሳምንት የመረጃ መንታፊዎች ወይም ሃከሮች በዲጂታል ገንዘብ ታሪክ በአንድ ጊዜ የተፈጸመ እና እጅግ ግዙፍ የተባለዉን 600 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚተመን ክሪፕቶከረንሲ መዝረፋቸዉ ሲነገር ነበር። ይህ ከበድ ያለ የሳይበር ጥቃት በብሎክቼን ዘርፍ ላይ በተሰማራውና ፖሊ ኔትወርክ በተባለው ግዙፍ ድርጅት ያጋጠመ ሲሆን፤ በሲስተሙ ላይ ባጋጠመ መጠነኛ ተጋላጭነት በሺዎች የሚቆጠሩ የዲጂታል ገንዘቦች የተዘረፈበት ክስተት ነው፡፡
ከደረሰው የሳይበር ጥቃት በኋላ ድርጅቱ በቲውተር ገፁ እንደጠቀሰው የተካሄደበት የክሪፕቶከረንሲ ዝርፊያ በመደበኛው ገንዘብ ሲተመን እስካሁን ካጋጠሙ ስርቆቶች ተወዳዳሪ እንደሌለው እና ዝርፊያውም በ10 ሺ የሚቆጠሩ የክሪፕቶ ደንበኞቹን በቀጥታ የሚያጠቃ መሆኑን አንስቷል፡፡ ደርጅቱ አክሎም ዝርፊውን ያካሄዱ የመረጃ ጠላፊዎች በየትኛውም ሀገር ህግ ትልቅ የኢኮኖሚ ወንጀል መፈፀማቸውን ተረድተው መፍትሄ ሊያመጣ የሚችል ስምምነት ከድርጅቱ ጋር እንዲመሰርቱ በቲዊተር መግለጫው አስታውቋ ነበር፡፡
አሁን ላይ ይህን የሳይበር ጥቃት ያካሄዱ ሰዎች የዘረፉትን 600 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው የዲጂታል ገንዘብ ምንም አይነት ድርድር ሳያደርጉ ለድርጅቱ መመለሳቸው ታውቋል፡፡ Mr. White Hat በሚል ስም የተጠቀሱት የሳይበር ጥቃት አድራሾች እንዲህ ያሉ የደህንነት ጉድለቶችን ለማስተማር እና የግንዛቤ ስራ ለመስራት የሚንቀሳቀሱ ethical hacker መሆናቸውም ተነግሯል፡፡
የብሎክቼን ፎረንሲክ ምርመራ ላይ የሚሰራው ቼንአናሊስስ እንደጠቀሰው እስካሁን ከተፈፀሙት የሳይበር ጥቃቶች ከባድ በሆነው በዚህ ጥቃት ላይ የተሳተፉ ሀከሮች የሰረቁትን ገንዘብ ለመውሰድ ምንም አላማ እንዳልነበራቸው እና የድርጅቱን የብሎክቼን ስርዓት ለመፈተሽና ከፍተቱን ለመለየት ያደረጉት ሙከራ መሆኑን አንስቷል፡፡ የፖሊ ኔትወርክ ኩባንያ በብሎክቼን ሲስተሙ ላይ የነበረውን የደህንነት ተጋላጭነት ለጠቆሙት ለእነዚህ ሰላማዊ የመረጃ ጠላፊዎች የግማሽ ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ቢያቀርብም ጥቃቱን ያደረሱት ሃከሮች ምንም አይነት ገንዘብ መቀበል እንደማይፈልጉ ቼንአናሊስስ አስታውቀዋል፡፡
በብሎክቼን ያልተማከለ የዲጂታል መዝገብ ስርዓት እንዳንዱ ግብይቶች በይፋ የሚታወቁ በመሆናቸው ማንነቱ ያልታወቀ የመረጃ ጠላፊ የወሰደውን ገንዘብ በቀላሉ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚቸገር መሆኑን እነዚሁ የብሎክቼን ፎረንሲክ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡
ምንጭ፡ CNN
ተጨማሪ https://edition.cnn.com/.../poly-network-hack.../index.html
በግሪክ የተከሰተው ሰደድ እሳት በሳተላይት ምስል
========================
በሜዲትራንያን ባህር አካባቢ በሚገኙ ሃገራት ያጋጠመውን ከፍተኛ የሙቀት መጠን ተከትሎ የተቀሰቀሰው የእሳት ሰደድ ከባድ ጉዳቶችን ሲስከትል እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡ በዚህ ከፍተኛ የሰደድ እሳት ላለፉት 10 ቀናት በእጅጉ ስትፈተን የቆየችው ግሪክ ባጋጠማት አደጋ ከፍተኛ ስነ ምህዳራዊ ጉዳትን አስተናግዳለች፡፡ በሰደድ እሳቱ የግሪክ ጥንታዊ የኦሎምፒክ ስፍራዎች ጭምር አደጋ ላይ ወድቀው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን በትንሹ 50 ሺ ሄክታር የሚሸፍን ደን በቃጠሎው ወድሟል፡፡
የሰደድ እሳቱ ተከስቶ በነበረባቸው የሃገሪቱ አካባቢዎች ዝናብ መጣሉንና የሙቀት መጠኑ መቀነሱን ተከትሎ የእሳቱ መጠን እያነሰ እና በቁጥጥር ስር እየዋለ እንደሚገኝ የሃገሪቱ የዜጎች ጥበቃ የድንገተኛ እና እሳት አደጋዎች ዲፓርትመንት አስታውቋል፡፡ ኢቪያ በምትባለው የግሪክ ደሴት የተነሳውን ሰደድ እሳት በሳተላይት ምስል ያቀረበው የኮፐርኒከስ ሳተይላት የአለማችን ስጋት በሆነው የሙቀት መጨመር ምክንያት የተነሳው ሰደድ እሳት ያስከተለውን ከፍተኛ ጉዳት በቀላሉ ያስመለከተ ነው፡፡
ከኮፐርኒከስ ሳተይላት የተገኘው ምስል ብዙ የቃል ማብራራሪየዎች ሳያስፈልጉ የምድራቸን ሙቀት መጨመር እያስከተለ ያለውን ትልቅ አደጋ እና የደቀነውን የወደፊት ስጋት የሚያሳይ ነው፡፡ በደሴቲቷ ለ10 ቀን ብቻ በቆየው ሰደድ እሳት 50,910 ሄክታር መሬት ደን መጥፋቱ እና ከፍተኛ የስነ ምህዳር መዛባት መፍጠሩ ለአለማችን ከባድ መልእክት ይኖረዋል፡፡
ከሶስት አስርት አመታት በኋላ በታሪኩ እጅግ ከባድ የተባለውን የሰደድ እሳት ያስተናገደችው ግሪክ በአሰቃቂው አደጋ ብዙ ቤቶች፣ የንግድ ተቋማት እና ድርጅቶች ከተቃጠሉባት በኋላ የሰደድ እሳቱን መቆጣጠር የቻለችው እሳቱ ተከስቶ በነበረባቸው የሃገሪቱ አካባቢዎች ዝናብ መጣሉን ተከትሎ ነው፡፡ ይሁንና አሁንም በሙቀቱ የተነሳ ዳግም ሊከሰት ይችላል የሚባለው የሰደድ እሳት ከተፈጥሮ ዝናብ ውጪ በሰዎች ርብርብ ብቻ ለማጥፋት አስቸጋሪ መሆኑ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡
https://interestingengineering.com/satellite-images...
የመሬት መንሸራተት እና መንስኤዎቹ
የመሬት መንሸራተት እና መንስኤዎቹ
************************************
ከሰሞኑን በሀገራችን ሁለት የተለያዩ የመሬት መንሸራተት አደጋዎች ተከስተው መወያያ ጉዳይ ሆነው ነበር፡፡ ባሳለፍነው ሐሙስ ዓባይ በረሃ ውስጥ የተከሰተው የመሬት መንሸራተት ከአዲስ አበባ ወደ ባሕር ዳር የሚወስደውን መንገድ ዘግቶት ቆይቷል፡፡ ከዚያ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ነሐሴ 5 2013 ዓ.ም በምስራቅ ወለጋ ባኮ-ሻምቡ መንገድ ላይ ያጋጠመ መሬት መንሸራተትም እንዲሁ የተሸከርካሪ እንቅስቃሴን ሲያስተጓጉል ተመልክተናል፡፡ ለዛሬ እኛም እነዚህ ክስተቶችን ሰበብ አድርገን ስለ አስደናቂው መሬት መንሸራተት የተወሰኑ ነገሮችን ልንላችሁ ወደናልና አብራችሁን ቆዩ፡፡

የመሬት መንሸራተት የሚባለው መሬቱ፣ አለቶች፣ ወይም ስብርባሪ/ውጋጅ በቁልቁለታማ አካባቢ ላይ ወደታች ሲንቀሳቀስ ነው፡፡ እነዚህ የተፈጥሮም ሆነ ሰው ሰራሽ ክስተቶች በዋናነት ዝናብ፣ ድርቅ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ እሳተ ገሞራ ወይም ሌሎች ቁልቁለታማ ቦታው ተረጋግቶ እንዳይቀመጥ በሚያደርጉ ሁናቴዎች ምክንያት ይፈጠራሉ፡፡

የመሬት መንሸራተቶች ከሌሎች የስነ-ምድር (Geological) ክስተቶች በተለየ በብዙ አካባቢዎች ተደጋግመው የሚታዩ ናቸው፡፡ ከነዚህም ውስጥ ህዝብ ተሰብስቦ በሚኖርባቸው አካባቢዎች የሚከሰቱ የመሬት መንሸራተቶች ከባድ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመትን ሲያስከትሉ ይታያል፡፡ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ከአውሮፓውያኑ 1998 እስከ 2017 ድረስ ባሉት 20 ዓመታት ውስጥ ብቻ የመሬት መንሸራተት አደጋዎች በዓለማችን 4.8 ሚሊዮን ሰዎች ላይ ተፅዕንኦ ያደረሱ ሲሆን ቁጥራቸው ከ18 ሺህ የሚልቁትንም ህይወት ቀጥፈዋል፡፡

የመሬት መንሸራተቶች ሦስት አባይት መቀስቀሻ ምክንያቶች አሏቸው፤ ስነ-ምድራዊ፣ ስነ-ቅርፃዊ (Morphology) እና የሰው ልጅ ተግባራት፡፡ ስነ-ምድራዊ ምክንያት ሲባል መሬቱ ወይም አለቱ ጠንካራ ያልሆነ፣ የተሰነጣጠቀ አልያም ደግሞ የመሬቱ ንብርብር ንጣፎች አንዱ ከሌላው የተለያየ ጥንካሬ እና ጫናን የመቋቋም አቅም (Stiffness) ሲኖራቸው የሚከሰት ነው፡፡

ስነ-ቅርፃዊ በበኩሉ በተለይም እላያቸው ላይ የነበሩትን እፅዋት በእሳት አልያም ድርቅ ሳብያ የተገፈፉ ቁልቁለታማ ስፍራዎች ለመሬት መንሸራተት ይበልጥ ተጋላጭ ከመሆናቸው ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይህም ቀድሞ ዛፍም ሆነ ሌሎች እፅዋት በስራቸው አማካኝነት አፈሩን ቆንጥጠው ይዘውት ይቆዩ የነበር በመሆኑ የእነርሱ በስፍራው አለመኖር መሬቱ እንዲንሸራተት ሊያደርገው ይችላል፡፡ ሆኖም ከዕፅዋት መጥፋት ባሻገር በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የመሬት መንሸራተት ከመሬት መሸርሸርና በአየር ንብረቱ ሳብያ ከሚመጣ የመሬት ጥንካሬ መኮሰስ መንስኤነት የሚከሰተው የመሬት መንሸራተት ነው፡፡

በሀገራችን የሚቀሰቀሱ የመሬት መንሸራተቶችም ብዙውን ጊዜ መሰል በከባድ ዝናብ ምክንያትነት የተቀሰቀሱ መሆናቸውን በተለያዩ ዘገባዎች ሰምተናል፡፡ እንዲሁ አንድ ወቅት ላይ በአሜሪካኗ የዩታህ ግዛት በዘነበ ከባድ ዝናብ እና በፍጥነት እየቀለጠ የነበረውን በረዶ ተከትሎ የተከሰተ የመሬት መንሸራተት 305 ሜትር ወደ ጎን የሚሰፋ፣ 1.6 ኪ.ሜ የሚረዝምና 61 ሜትር የሚወፍር ግዙፍ የመሬት መንሸተትን አስከትሎ ነበር፡፡ ይህ በአውዳሚነቱ በሀገሪቱ እስከዛሬ ወደር ያልተገኘለት የመሬት መንሸራተት ታድያ ከበታቹ ይገኝ የነበረ ወንዝ ፍሰትን ከመገደብም ባሻገር የባቡር መንገድ እና አውራ ጎዳናን በመዝጋት 400 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ውድመትን አምጥቶ ነበር፡፡

የሰው ልጆች ምክንያት የሆኑበት የመሬት መንሸራተት አደጋዎችን ያየን እንደሆን በዋናነት እንደ ግብርና እና ግንባታ ባሉት እንቅስቃሴዎች ሳብያ የሚከሰቱትን ይመለከታል፡፡ የመስኖ እርሻ፣ ደን ምንጣሮ፣ ቁፋሮ እና ድንገተኛ የውሃ ፍሰት ቁልቁለቱ እንዳይረጋጋና ጠንካራ ሆኖ እንዳይቀጥል በማድረግ ለመሬት መንሸራተት ያጋልጡታል፡፡

ልክ እንደ መንስኤያቸው ሁሉ የመሬት መንሸራተቶች በአይነታቸውም ይለያያሉ፡፡ ለምሳሌ በእንቅስቃሴያቸው ረገድ ካየን የሚንሸራተት መሬት በመውደቅ፣ መናድ፣ መፍሰስ ወዘተ… መልኩ ሊንቀሳቀስ ይችላል፡፡ በሌላ መልኩ የመሬት መንሸራተቶች በደረጃ ቅርፅ እና ትራንዝሌሽናል መልኩም ሊንቀሳቀሱ ይችላሉ፡፡

ትራንዝሌሽናል የመሬት መንሸራተት፤ በመሬቱ ገፅ ላይ ያሉት ቁሶች በውስጥ ካሉት ጠንካራ የመሬቱ ክፍሎች ተለይተው የሚንሸራተቱበት ነው፡፡ በዚህ አይነቱ የመሬት መንሸራተት ከላይ ያለው ለስላሳ ክፍል በመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት ከጠንካራው የታችኛው ክፍል ሊለያይ ይችላል፡፡

የደረጃ ቅርፅ ያላቸው መሬት መንሸራተቶች፤ ይህ በመሬቱ ገፅ ላይ ያሉት ቁሶች ወደጎን ወይም መወጣጫ ደረጃ የሚመስል ቅርፅ ሰርተው ሲንቀሳቀሱ ይፈጠራል፡፡ ይህም እንደ መሬት መንቀጥቀጥ ያለ ጠንካራ ኃይል ምድሩ ልክ እንደ ውሃ በፍጥነት ሲንጠው የሚከሰት ነው፡፡

ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው እነዚህ የመሬት መንሸራተቶች ሲነሱ በውስጣቸው ድንጋይ፣ አፈር፣ እፅዋት ወይም ውሃን በመያዝ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ በተራራ ጫፍ ላይ የተነሳ መሬት መንሸራተትን ስናይ ደረቅና እየቀለጠ ያለ በረዶን በውስጡ ይዞ ሊነጉድ ይችላል፤ በአካባቢው አየር ንብረት እና የተራራው ከፍታ የሚወሰን ቢሆንም፡፡ የመሬት መንሸራተቱ የተነሳው በእሳተ ገሞራ ሳብያ ሲሆን ደግሞ ከፍንዳታው የሚወጣ አመድ እና ቅልጥ አለትን ይዞ ይወርዳል፡፡

እዚህ ላይ ለመጥቀስ በእሳተ ገሞራ ሳብያ የሚነሱት የመሬት መንሸራተቶች ላሀራስ በሚል ስያሜ የሚጠሩና ከመሬት መንሸራተቶችም እጅግ አደገኛ የሚባሉት ናቸው፡፡ ለምሳሌ እስከዛሬ በምድራችን ከተመዘገቡት የመሬት መንሸራተቶች ሁሉ ቀዳሚ የሆነው የቅድስት ሄለንስ ተራራ መሬት መንሸራተት ለዚህ ማሳያ ነው፡፡ ይህ በአሜሪካኗ የዋሽግተን ግዛት የተፈጠረ እሳተ ገሞራ አመጣሽ መሬት መንሸራተት 2.9 ኪዩቢክ ኪ.ሜ የሚሆንና 62 ካሬ ኪ.ሜ ቦታን የሚሸፍን የአመድ፣ አለት፣ አፈር፣ እፅዋት እና ውሃ ድብልቅን ከተራራው ላይ ተገምሶ እንዲንሸራተት አድርጓል፡፡ ይህ የተንሸራተተው የተራራው አካል የሸፈነውን መሬት ከሀገራችን ከተሞች ስፋት ጋር ብናነፃፅረው ከሀዋሳ እና መቐለ የበለጠ፣ የጎንደር አንድ ሦስተኛ፣ እንዲሁም የአዲስ አበባን አንድ ስምንተኛ መሬት የሚሸፍን ነው፡፡ ይህን መሰል እሳተ ገሞራ አመጣሽ የመሬት መንሸራተቶች መርዛማ ንጥረ ነገርን በውስጣቸው የያዙ መሆናቸውም ልዩ ያደርጋቸዋል፡፡

ሌላው አንዱ መሬት መንሸራተት ከሌላኛው የሚለይበት ጉዳይ የሚንሸራተቱበት ፍጥነት ነው፡፡ አንዳንዶቹ በሴኮንድ በርካታ ሜትሮችን በሚጓዝ ከባድ ፍጥነት ሲንሸራተቱ ሌሎቹ ደግሞ ዘገምተኛ ሆነው በዓመት አንድ እና ሁለት ሴ.ሜ ብቻ ይንቃሰቀሳሉ፡፡ ለዚህ በውስጣቸው ይዘውት የሚንሸራተቱት የውሃ፣ በረዶ እና አየር መጠን መለያየት የራሱን ሚና ይጫወታል፡፡ ለምሳሌ የጭቃ መንሸራተት ተብለው የሚታወቁት የመሬት መንሸራተቶች በውስጣቸው ከፍተኛ ውሃ የያዙና እንቅስቃሴያቸውም በጣም ፈጣን ነው፡፡ በሌላ መልኩ የተለያየ ዓይነት ቁስ ይዘው የሚንቀሳቀሱና በውስጣቸው ያለው የእንቅስቃሴ አይነትም የተዘበራረቀ የሆኑ ውስብስብ የመሬት መንሸራተቶች አሉ፡፡
ታድያ የመሬት መንሸራተቶች መሬት ላይ ብቻ የሚከሰቱ አይደሉም፤ ይልቁንም ሌሎች ፕላኔቶችም ላይ አሉ፡፡ ለዚህ አንድ ማሳያ የሚሆነን በአውሮፓውያኑ 2008 ተመራማሪዎች ከዚህ ቀደም ማርስ ላይ ተከስቶ የነበረ መሬት መንሸራተትን በተመለከተ ያገኙት መረጃ ነው፡፡ በአንድ ወቅት በፕላኔቷ ሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ አካባቢ በወደቀ አስትሮይድ ሳብያ የተከሰተ የመሬት መንሸራተት አረቢያ የተባለውን ግዙፍ አምባ እንደፈጠረ ይነገርለታል፡፡ በዚህ ወቅት የተንሸራተተው መሬት ታድያ የኢትዮጵያን ቆዳ ስፋት በዘጠኝ እጥፍ የሚበልጥ ቦታን የሸፈነ መሆኑ ይነገርለታል፡፡

ምንጭ፤ ናሽናል ጂኦግራፊክ እና የአለም ጤና ድርጅት
ለተጨማሪ፤ https://www.nationalgeographic.org/encyclopedia/landslide/#:~:text=Encyclopedic%20Entry%20Vocabulary-,A%20landslide%20is%20the%20movement%20of%20rock%2C%20earth%2C%20or%20debris,one%20type%20of%20mass%20wasting. እና https://www.who.int/health-topics/landslides#tab=tab_1
የአፍሪካ ሳይንቲስቶች ሙዝ ላይ ለሚከሰት በሽታ መፍትሄን አግኝተዋል
========================
ለብዙ ሚሊዮን አፍሪካውያን የምግብና የገቢ ምንጭ የሆነው የሙዝ ተክል በየዓመቱ በአለማችን 155 ሚሊዮን ቶን ምርት ይሰበሰብበታል፡፡ ሁሉም ለምርት የደረሱ የሙዝ ዓይነቶች ለተለያየ በሽታዎች ተጋላጭ የመሆን እድል ቢኖራቸውም አብዛኞቹ የሙዝ ዝርያዎች Banana xanthomonas wilt (BXW) በተባለው በሽታ በተደጋጋሚ ሊጠቁ እንደሚችሉ አጥኚዎች ያስረዳሉ፡፡ BXW በሙዝ ዝርያዎች ላይ በብዛት የሚከሰት የባክቴሪያ በሽታ ሲሆን ባለፉት 10 አመታት ብቻ ከሁለት እስከ ስምንት ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ውድመት አስከትሏል፡፡

በተለያዩ የተክል አይነቶች ላይ እንደሚታየው በሙዝ ዝርያዎች ላይ የሚስተዋለው የጎላ የጄኔቲክ ብዝሃነት እጥረት ወይም የበራሂ ልዩነት አለመኖር ለተባይና ለበሽታ በእጥፍ ተጋላጭ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህን ታሳቢ በማድረግ በኬኒያ በሚገኙ የአለም አቀፍ ትሮፒካል ግብርና ተመራመሪዎች የተከናወነው ጥናት በአብዛኞቹ የሙዝ ዝርያዎች ላይ ለሚከሰተው በሽታ አዲስ መፍትሄን ያሳየ ይመስላል፡፡ ተመራማሪዎች በዚህ የቅርብ ጥናት በአብዛኞቹ የሙዝ ዝርያዎች ላይ የሚከሰተውን በሽታ በደንብ መቋቋም የሚችል አዲስ ዝርያ ለማውጣት የጄኔቲክ ማሻሻያ ስርዓቶችን የተገበሩ ሲሆን በዋናነት በዚህ ዘርፍ ላይ ብዙ ተቀባይነት ያለውን CRISPR/Cas9 ቴክኒክ ጥቅም ላይ አውለዋል፡፡

በክሪስፐር ቴክኒክ አማካኝነት በቅርብ ጊዜያት የበራሂ ማሻሻያ የተደረገላቸው ወይም genome editing የተካሄደባቸው የሙዝ ዝርያዎች ያስገኙት መልካም ውጤት ለምርምሩ መነሻ እንደነበር የሚነገሩት ተመራማሪዎች በዚህ አዲስ ጥናትም የአገር በቀል የሙዝ ዝርያዎች የተሟላ ይዘታቸውን ሳይለቁ በሽታዎችን መቋቋም እንዲችሉ ብቻ የሚያደረግ ጥናት ማካሄዳቸውን ያስረዳሉ፡፡ በምርምሩ ሂደት ተመራመሪዎች ትኩረት ያደረጉበት downy mildew resistance 6 (DMR6) የተባለው ጂን ወይም በራሂ በብዙ የተክሎች ዝርያ ላይ በሽታዎችን የሚከላከል ጂን ነው፡፡ በክሪስፐር ቴክኒክ አማካኝነት ለናሙና በተወሰዱ የሙዝ ተክሎች ላይ ይህን የበራሂ ማሻሻያ ያደረጉት ተመራማሪዎች BXW የተባለውን በሽታ ከቀድሞዎቹ ተክሎች (unedited plants) በበለጠ ሁኔታ በ66 በመቶ መቋቋም የሚችል ዝርያ ማግኘት ችለዋል፡፡

እንደተማራማሪዎች ከሆነ የጥናቱ ግኝት በአብዛኞቹ የሙዝ ዝርያዎች ላይ የሚከሰተውን BXW እና ሌሎች በርካታ በሽታ አምጪ ተህዋስያንን ወይም (pathogens) ለመከላከል የሚውል ከመሆኑም በተጨማሪ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለበሽታ የሚጋለጡትን የሙዝ ተክሎች በ66 በመቶ የመከላከል አቅማቸውን ለመጨመር የሚያግዝ ግኘት ነው፡፡ ይህ የምርምር ውጤት አሁን ላይ ለናሙና በተወሰዱ የሙዝ ተክሎች ላይ ተሞክሮ ውጤት ያስገኘ ሲሆን በቀጣይ ሂደትም ብዛት ባላቸው የናሙና አይነቶች እና በተጨባጭ የአፈር እርሻዎች ላይ እንደሚተገበር ተነግሯል፡፡
ምንጭ zmescience
ለተጨማሪ https://www.zmescience.com/science/news-science/african-scientists-used-crispr-to-edit-bananas-and-make-them-more-resilient-to-disease/
ለምን ያህል ጊዜ ያለ እንቅልፍ መቆየት እንችላለን?
=========================
በሰው ልጅ ታሪክ አንድ ሰው ለብዙ ጊዜ ያለ እንቅልፍ የመቆየት ክብረ ወሰን ማስመዝገብ የቻለው ለ11 ቀን ከ25 ደቂቃ ያለ እንቅልፍ በመዝለቅ ነው፡፡ በአውሮፓውያኑ 1963 ይህን ክብረ ወሰን ያስመዘገበው ራንዲ ጋርድነር የተባለ በወቅቱ የ17 ዓመት ታዳጊ የነበረ ልጅ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ፊንላንዳዊው ቶኢሚ ሶኢኒ እንዲሁም ማውረን ዌስቶን እና ቶኒ ራይት የተባሉ ሁለት ብሪታኒያውያን ይህን ክብረ ወሰን መስበራቸውን ለዓለም ቢያውጁም አንዳቸውም ግን እንደ ራንዲ ጋርድነር በቅርበት ክትትል ሳይደረግባቸው በመቅረታቸው ትክክለኛነታቸውን ለማረጋገጥ አልተቻለም፡፡

ያለ እንቅልፍ ለረጅም ጊዜ መቆየት በደንብ የሚታወቁ የጤና ጉዳቶች ያሉት ችግር ነው፡፡ አንድ ሰው የእንቅልፍ ማጣት ሲገጥመው የተነሳሽነት ማነስ፣ የደም ግፊት ከፍ ማለት፣ በሰው ክትትል ውስጥ እንደሆኑ መሰማት፣ የማስታወስ ችግር፣ የጸባይ መቀየር፣ የእይታ ችግር እና በንግግሩ ላይ ችግር ሊያጋጥመው ይችላል፡፡ በዚህ ላይ የጤና ችግር እንደ መረበሽ፣ ውሳኔ ለማሳለፍ መዘግየት እንዲሁም ስለ ነገሮች በአንድ የተወሰነ መንገድ ብቻ ለማሰብ መገደድ ያሉት ምልክቶች ሆነው ብቅ ይላሉ፡፡
ራንዲ ጋርድነር ለረጅም ጊዜ ያለመተኛት ክብረ ወሰኑን ሲያሻሽል በቅርብ ሲከታተሉት የነበሩት ዊሊያም ዴመንት በወቅቱ ራንዲ ከላይ ከተጠቀሱት የእንቅልፍ ማጣት የጎንዮሽ ጉዳቶች ውስጥ አብዛኛውን ማሳየቱን ጠቅሰዋል፡፡ ክብረ ወሰኑን ሲያስመዘግብ ምንም አይነት እንቅልፍን የሚያሸሹ መድሃኒቶችን ባይጠቀምም በዙርያው ግን እርሱ እንቅልፍ እናዳይወስደው የመበጥበጥ ድርሻቸውን ሲወጡ የነበሩ ሰዎች አብረውት ነበሩ፡፡ በወቅቱ ራንዲ በጠቅላላው ለ264 ሰዓታት ከ25 ደቂቃ ቆይቶ ክብረ ወሰኑን ካስመዘገበ በኋላ ለ14 ሰዓታት ያለ ምን ማቋረጥ ሊተኛ በቅቷል፡፡

ከዚህ ሙከራ ውጪ ማንም ሌላ ሰው ከዚህ የበለጠ እንቅልፍ አልባ ቆይታ አድርጎ ማስመዝገብ አልቻለም፡፡ እስካሁንም ቢሆን የሰው ልጅ ለምን ያህል ጊዜ እንቅልፍ ሳይተኛ መቆየት እንደሚችል ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡

እዚህ ላይ ይህ የራንዲን ክብረ ወሰን ተመልክቶ ለማሻሻል መነሳቱ እጅጉን ፈታኝ ነው፡፡ አንድ ሰው ለረጅም ሰዓት እንቅልፉን ሳይተኛ ለመቆየት ቢሞክር እንኳን ወይ ባለበት ድንገት ጋደም ብሎ ሊከሽፍበት አልያም ሳያውቀውና ዓይኑንም ሳይከድን ባለበት ሆኖ ለሴኮንዶች ሊተኛ ይችላል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን እንቅልፍ ማጣት አደገኛ ነገር መሆኑንም መገንዘብ ያስፈልጋል፤ እስከ ሞት ድረስ የሚያደርስ ከፍተኛ የጤና ጉዳት ሊኖረው ይችላልና፡፡ የእንቅልፍ ማጣት ምልከታ የተደረገባቸው የቤተ ሙከራ አይጦች በአንድ ወር ውስጥ ህይወታቸውን ለማጣት በቅተዋል፡፡ ይህ ታድያ ለሰው ልጆችም የሚሰራ ጉዳይ ነው፡፡ በሰው ልጆች ላይ እጅጉን አልፎ አልፎ የሚከሰተውና ፋታል ፋሚሊያል ኢንሶምኒያ (Ffi) በተሰኘው እንቅልፍን የመተኛት ብቃትን በሚያሳጣ በሽታ የተጠቁ ግለሰቦች በተመሳሳይ በሦስት ወር ውስጥ ህይወታቸውን ሊያጡ ይችላሉ፡፡

ምንጭ፤ ኒው ሳይንቲስት
ለተጨማሪ፤ https://www.newscientist.com/question/how-long-can-you-go-without-sleep/?utm_term=Autofeed&utm_campaign=echobox&utm_medium=social&utm_source=Twitter#Echobox=1629092146
ሄይቲ ላይ የበረታው አሳዛኝ የመሬት መንቀጥቀጥ
ሄይቲ ላይ የበረታው አሳዛኝ የመሬት መንቀጥቀጥ
***************************
ባሳለፍነው ቅዳሜ መገኛዋን ካሪቢያን ያደረገችው ሄይቲ 7.2 ሬክታር ስኬል በሚለካ ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ ተመትታለች፡፡ እስካሁኗ ሰዓት ባለው መረጃ በአደጋው ምክንያት ከ1,400 በላይ ሰዎች ህይወታቸው ተቀጥፏል፣ ሆስፒታል ትምህርት ቤት እና ቤተ ክርስቲያኖችን ጨምሮ 700 ያህል ህንፃዎች ፈርሰዋል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ከጥቅም ውጪ ሆነዋል፡፡

የመሬት መንቀጥቀጡ የሀገሪቱ መዲና የሆነችው ፖርት አው ፕሪንስን በመናጥ ህንፃዎቿ እንዲፈራርሱ ቢያደርግም የአደጋው ዋና ማዕከል ግን ከከተማይቱ በስተምዕራብ አቅጣጫ 125 ኪ.ሜ ርቃ በምትገኘው ፔቲት ትሮ ደ ኒፕስ አቅራብያ ነው፡፡ ከባዱ የመሬት መንቀጥቀጥ ንቅናቄው 3,200 ኪ.ሜ ርቃ በምትገኘው ጃማይካ ጭምር የተሰማ ነበር፡፡ በተጨማሪም ዋናውን የመሬት መንቀጥቀጥ ከተከሰተ በኋላ ተከታትለው በመጡት ከ4.2 እስከ 5.2 ሬክታር ስኬል በሚለኩና ወደ 10 ኪ.ሜ ጥልቀት ባላቸው ተጨማሪ ንዝረቶች ተጠቅታለች፡፡

ሃይቲን ደጋግሞ የሚጎበኛት መቅሰፍት

ዜጎቿ በማያባራ የፖለቲካ ቀውስ፣ ደም አፋሳሽ አመፅ እና ከባድ ድህነት ውስጥ የሚማቅቁባት ይህች ጎስቋላ ሀገር ሰው ሰራሽ ቀውሱ አልበቃ ብሏት በተደጋጋሚ መሬት መንቀጥቀጥ ስትናጥ ቆይታለች፡፡ ከዛሬ 10 ዓመት በፊት በአውሮፓውያኑ 2010 የደረሰባት ከባድ መሬት መንቀጥቀጥ የ300 ሺህ ዜጎቿን ህይወት የበላ ነበር፡፡ ይህ ብቻም አይደለም በአውሮፓውያኑ 1751፣ 1770 እና 1860 የተከሰቱት ከባድ መሬት መንቀጥቀጦች ክፉኛ ጎድተዋት አልፈዋል፡፡ በተለይ የመጀመሪያዎቹ ሁለት መሬት መንቀጥቀጦች መዲናዋን ያጠፉ ነበሩ፡፡

ነገሮችን ይባስ አስቸጋሪ ያደረገው ደግሞ እንደ ሜክሲኮ፣ ጃፓን፣ አሜሪካን፣ እና ጣልያን ያሉት በምጣኔ ሐብት የተሻለ ደረጃ ላይ የሚገኙ የመሬት መንቀጥቀጥ ተጋላጭ ሀገራት አደጋው ከመከሰቱ ከጥቂት ቅፅበት በፊት ቅድመ ማሰጠንቀቂያ የሚሰጥ ስርዓት እና ጠንካራ መሰረተ ልማት ሲኖራቸው ሄይቲ ግን ህዝቦቿ ከቀድሞ ተምረው ከሚያደርጉት ጥንቃቄ ባሻገር ጠንካራ የቅድመ ዝግጁነት ስርዓት የላትም፡፡

ለዚህ ሁሉ አደጋ መነሻው ሄይቲ ከሁለት ቴክቶኒክ ፕሌቶች (የሰሜን አሜሪካን እና ካሪቢያን) መገናኛ ከሆነው አካባቢ በቅርብ ርቀት የምትገኝ መሆኗ ነው፡፡ የሰሜን አሜሪካኑ ቴክቶኒክ ፕሌት በዓመት 20 ሚ.ሜ ፍጥነት ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ይጓዛል፡፡ ይህ እንቅስቃሴ የፈጠራቸው ጠመዝማዛማ ስንጥቃቶች ሄይቲ የምትገኝበትን የሂስፓኒዮላ ደሴት አቋርጠው ያልፋሉ፡፡ ሁለቱ ፕሌቶች ሲተላለፉ ከፍተኛ የሆነ ኃይል የሚለቁ በመሆናቸውም የመሬት መንቀጥቀጥን ያመጣሉ፡፡ ሄይቲም ኢንሪኪዮ-ፕላንታይን ጋርደን ተብሎ በሚታወቀው የስንጥቃቱ ደቡባዊ ክፍል ሳብያ ነው የመሬት መንቀጥቀጦቹ አሳዛኝ በሆነ ሁኔታ ደጋግመው የሚጎበኟት፡፡ ምንም እንኳን ገና የሚጠና ቢሆንም የአሁኑ መሬት መንቀጥቀጥ ሁለቱ ፕሌቶች ሲተላለፉ የተከሰተ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡ በአንፃሩ የዛሬ 10 ዓመቱ መንቀጥቀጥ በተለያዩ የስንጥቃቱ ክፍሎች የተነሳ ግፊትን ተከትሎ የመጣ ነበር፡፡

ታድያ የአሁኑ መሬት መንቀጥቀጥ በታሪኳ አሰቃቂ ከነበረው የ2010ሩ መሬት መንቀጥቀጥ ጋር ሲነፃፀር ምድሩን በይበልጥ የናጠና የለቀቀው ኃይልም በእጥፍ የሚበልጥ ቢሆንም ያደረሰው ሰብዓዊ ጉዳት ግን በአንፃሩ አነስተኛ የሚባል ነው፤ ምስጋና ለህዝቡ ጥንቃቄ ይሁንና፡፡

ከዚህ ቀደም ስለ ቴክቶኒክ ፕሌቶች የፃፍነውን ፅሁፍ በዚህ ሊንክ አማካኝነት ማግኘት ይችላሉ (https://www.facebook.com/TechinEthiopia/posts/2762428397198561/)

ምንጭ፤ ላይቭ ሳይንስ፣ ሮይተርስ እና የተባበሩት መንግስታት ሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (OCHA)
ለተጨማሪ፤ https://reliefweb.int/sites/reliefweb.int/files/resources/Haiti%20-%20Flash%20Update%20-%20Earthquake%20-%2020210815.pdf ፣ https://www.livescience.com/magnitude-7-earthquake-strikes-haiti.html ፣ https://www.reuters.com/business/environment/why-does-haiti-have-earthquakes-2021-08-16/?taid=611b344beb335300017378f6&utm_campaign=trueanthem&utm_medium=trueanthem&utm_source=twitter ፣ እና https://www.reuters.com/world/americas/haiti-quake-revives-anger-over-aid-response-past-disasters-2021-08-16/?taid=611b45da029ed3000190e274&utm_campaign=trueanthem&utm_medium=trueanthem&utm_source=twitter
ማስተርካርድ በማግኔቲክ ስትራይፕ የሚሰሩ ካርዶችን ሊያቆም ነው
=========================
በምንጠቀማቸው የክሬዲት ካርዶች ላይ ከጀርባ በጥቁር መስመር የሚሰመረው ነገር ማግኔቲክ ስትራይፕ ወይም ማግስትራይፕ ተብሎ ይጠራል፡፡ በሁሉም የክሬት ካርዶች ላይ የምንመለከተው ይህ ጥቁር መስመር እጅግ ጥቃቅን ከሆኑ የብረት ይዘት ካላቸው መግነጢሳዊ ቅንጣቶች (magnetic particles) የሚሰራ ሲሆን ፕላስቲክ ከሆነው የክሬደት ካርድ ጋር አንዲስማማ ተደርጎ የሚፈበረክ ነው፡፡ በካርዱ ላይ ያሉት እያንዳንዱ ቅንጣቶች ከ20 millionths ኢንች የሚያንስ ቅጥነት ያላቸው ባር ማግኔቶች በመሆናቸው ብዛት ያለው መረጃን ሊያከማቹ ይችላል፡፡

ሁሉም የክሬዲት ካርዶች ከሚያነባቸው ማሽን ጋር በቀላሉ እንዲግባቡ የሚስችለው እና ትልቁን ሚና የሚጫወተው ማግኔቲክ ስትራይፕ የሂሳብ ቁጥራችንን፣ ስማችንን፣ የካንትሪ ኮዳችንን እና ሌሎች ስለኛ ማንነት የሚገልፁ ብዙ መራጃዎችን ይዞ የሚገኝ የክሬዲት ካርዱ ዋና ክፍል ነው፡፡ ማግኔቲክ ስትራይፕ በ1960ዎቹ በIBM አነሳሽነት ስራ ላይ መዋል እንደጀመረ የሚነገር ሲሆን በጊዜው ለሲአይኤ የስራ አባላት የማንነት መታወቂያ ሆኖ አገልግሏል፡፡

ከዚህ ጊዜ አንስቶ በባንክ አገልግሎቶች እና የፋይናንስ ስርዓት ውስጥ በሰፊው ግልጋሎት መስጠት የጀመረው የክሬዲት ካርድ ማግስትራይፕ አሁን ላይ ከሌሎች ቴክኖሎጂዎች መምጣት ጋር ተያይዞ በብዙ ሀገራት ከስራ ውጭ እየተደረገ ነው፡፡ በዚህ የክሬዲት ካርድ የክፍያ ስርዓት ግዙፍ ስም ካላቸው አለምአቀፍ ተቋማት አንዱ የሆነው ማስተርካርድ ለብዙ ዓመት ሲገለገልበት የቆውን የማግኔቲክ ስትራይፕ አሰራር ሊያቀቆም አንደሆነ ጠቁሟል፡፡ በ2033 ሁሉም ጥቅም ላይ የሚያውላቸው የዴብትና ክሬዲት ካርድ ቁሶች ከማግኔቲክ ስትራይፕ አሰራር ነጻ እንደሚሆኑ ያስተወቀው ማስተርካርድ በብዙ የአውሮፓና በሌሎች አህጉራት ያሉ ባንኮችም ከ2024 አንስቶ ማግስትራይፕ የሌላቸው ካርዶችን ጥቅም ላይ እንዲያውሉ በማድረግ ላይ ነው፡፡

በእንግሊዝና በአብዛኞቹ የአውሮፓ ሀገራት የፋይናንስ ስርዓት የማግኔቲክ ስትራይፕ አሰራር በሰሜኪንዳክተር ቺፕ እና የግል መለያ ቁጥር (ፒን) ካርድ (chip-and-pin) እየተተካ ከምጣቱ ጋር ተያይዞ የማግስትራይፕ አሰራር በ2006 ሙሉ ለሙሉ እንዳበቃ ይነገራል፡፡ ይሁንና በአብዛኞቹ የእስያ፣ አፍሪካ፣ ሰሜንና ደቡብ አሜሪካ ሀገሮች ይህ የክሬዲት ካርድ አሰራር ገና ስራ ላይ እነዳለ ይታወቃል፡፡ ማስተርካርድ የማግኔቲክ ስትራይፕ አሰራርን ተክተው ጥቅም ላይ ይውላሉ ያላቸው የ chip-and-pin አሰራሮች እና አዳዲስ የባዮሜትሪክ ካርዶች የደህንነት አቅምን በእጅጉ ማሳደጋቸው ይበልጥ ተፈላጊ የሚያደርጋቸው ነው፡፡
ምንጭ፡ ቢቢሲ
https://www.bbc.com/news/technology-58206591
https://money.howstuffworks.com/personal-finance/debt-management/magnetic-stripe-credit-card.htm
የኤች አይ ቪ ክትባት በሰዎች ላይ ሊሞከር ነው
****************************
ሞደርና የተሰኘው የክትባት አምራች ድርጅት የኤች አይ ቪ ቫይረስ ክትባትን በያዝነው ሳምንት በሰዎች ላይ ሊሞክር እንደሆነ ተሰማ፡፡ የአሜሪካ ብሔራዊ የክትባቶች ክሊኒካዊ ሙከራ ምዝገባ ተቋም ያወጣው መረጃ እንደሚጠቁመው በዚህ ሳምንት በሰዎች ላይ ሊሞከር የታሰበው የኤች አይ ቪ ክትባት mRNAን መሰረት ያደረገ ነው፡፡

የመጀመሪያ ደረጃ ሙከራው ከቫይረሱ ነጻ በሆኑና እድሜያቸው ከ18 እስከ 50 በሆነ 56 ሰዎች ላይ የሚካሄድ ሲሆን በዚህም የክትባቱን ደህንነትና ከበሽታ መከላከል ጋር የተያያዙ መረጃዎች የሚታዩበት ነው ተብሏል፡፡ ለአመታት ያክል የmRNA ክትባት ከፍተኛ ጥናት ሲደረግበት የቆየ ቢሆንም ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው ግን በፋይዘርና ሞደርና የኮቪድ 19 ክትባቶች ነው፡፡

እነዚህ ክትባቶች የ SARS-CoV-2 ወረርሽኝን በመግታት ረገድ ከፍተኛ የሆነ ውጤት ያስመዘገቡ ሲሆን ሞደርና ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሞክረው የጸረ ኤች አይ ቪ ክትባት በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ለጸረ ኤች አይ ቪ የሚሰጥ ክትባት ሲሆን መጠሪያውም mRNA-1644 እንደሆነ ተነግሯል፡፡
ሙከራው በአራት ቡድን ለተከፈሉ ሰዎች በተለያየ አኳኋን የሚሰጥ ሲሆን የመጀመሪያው ዙር ሙከራ በስኬት የሚጠናቀቅ ከሆነ ቁጥራቸው ከፍ ባሉ ሰዎች ለሁለተኛ እና ለሶስተኛ ዙር የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ክትባቱ ከሌሎች መደበኛ የክትባት አይነቶች የሚለየው ደካማ የሆነ ቫይረስ የተሸከመ ባለመሆኑ ነው፡፡

ምንጭ sciencealert
ተጨማሪ ንባብ https://www.sciencealert.com/moderna-s-experimental-hiv-vaccine-could-begin-human-trials-as-soon-as-this-week?fbclid=IwAR2vMMnRHYPXIjvwU0zC-YufntknmlgFYVXiPIfqaaqBSq7tPI3Wx4SeeCM
የውሃ ነጠብጣብ በተተኳሽ ሲበሳ የሚያሳይ ምስል
*****************************
ከፍተኛ ፍጥነት ያለው ካሜራ የውሃ ነጠብጣብ ሲበሳ የሚያሳይ ምስል ማሳየት ቻለ፡፡ የውሃ ንጥበትን እንደ መርፌ ቀጭን በሆነ ተተኳሽ በስቶ ለማሳለፍ መሞከር እጅግ አስቸጋሪ ቢመስልም የMIT እና በኔዘርላንድ የቲዌንቴ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ተመራማሪዎች የሰሩት አዲስ ጥናት ይህ እንደሚቻል አሳይተዋል፡፡ ይህ ጥናት ወይም የውሃ ንጥበትን የመብሳት ልምምድ እንደ ክትባት ያሉ የተለያዩ በመርፌ የሚሰጡ መድሃኒቶች ያለ መርፌ በቆዳ ብቻ እንዲሰጡ የሚያስችል ግኝት እንደሚሆን ተመራማሪዎቹ ይፋ አድርገዋል፡፡
ተመራማሪዎቹ በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ የአፕል ፍሬ በጥይት ሲበሳ የሚኖረውን ክዋኔ መሰረት በማድረግ ሙከራቸውን ማድረግ እንደጀመሩ ተናግረዋል፡፡ የMIT ተመራማሪዎች ይፋ ያደረጉት የቪዲዮ ምስል የውሃ ነጠብጣቡ በተተኳሽ ሲበሳ የሚያሳይ ሲሆን ተመራማሪዎቹ ተተኳሹ በውሃው ነጠብጣብ ውስጥ ሲያልፍ ሙሉ ለሙሉ መከታተል ችለዋል፡፡
በዚህም ምርምር አጥኝዎቹ በመርፌ የሚሰጡ መድሃኒቶን ስስና ተለጣጭ የሆነውን የሰውነት ቆዳ በምን ያክል መጠን እንደሚጎዳው ማየት ችለዋል፡፡ ከዚህም ተነስተው ያለ መርፌ መድሃኒቶችን በሰውነታችን ቆዳ ማስገባት የሚቻልበትም መንገድ ለመፈለግ ምርምራቸውን ቀጥለዋል፡፡
የምርምሩ አስተባባሪ የሆኑትና የቲዌንቴ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሩ ዴቪድ ፈርማንዴዝ ሪቫስ ፈሳሽ መድሃኒቶችን ያለመርፌ የሚሰጥበትን መንገድ በመፈለግ በቆዳ ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ ማሰባቸውን ተናግረዋል፡፡
ምንጭ phys.org
ተጨማሪ ንባብ https://phys.org/.../2021-08-high-speed-camera-captures...