TechIn2
1.16K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
ከአልኮል ነፃ መጠጦች የአልኮል ሱሰኝነትን ይቀንሱ ይሆን?
====================
የአልኮል መጠጦች ጣዕም ያላቸው ግን ደግሞ በውስጣቸው ያለው የአልኮል መጠን ከ0.5 በመቶ በታች የሆኑት ከአልኮል ነፃ መጠጦች በመስፋፋት ላይ ናቸው፡፡ መጠጦቹ ገበያ ላይ ለጤና ተስማሚ እንደሆኑ የአልኮል አማራጮች ተደርገው ቢተዋወቁም መሰረቱን አውስትራሊያ አድርጎ የተሰራ ጥናት ግን እውነትም የአልኮል መጠጥ ፍጆታን ስለመቀነስ አለመቀነሳቸው አልያም በተቃራኒው ለበለጠ አልኮል ፍጆታ ማጋለጥ አለማጋለጣቸው ላይ ጥናት ሊደረግ እንደሚገባ አንስቷል፡፡

ሰዎች መጠጦቹን በምን መልኩ እየተጠቀሙ እንደሆነ ማረጋገጥ እንደሚገባ የጥናቱ ዋና ፀኃፊና በሜንዚስ ስኩል ኦፍ ኸልዝ ሪሰርች ውስጥ አጥኚ የሆኑት ዶ/ር ካሳንድራ ራይት ይገልፃሉ፡፡ አክለውም ከአልኮል ነፃ መጠጦቹ የመጠጥ ሱስ ውስጥ ለገቡ ጠጪዎች እንደ ጉዳትን ቀናሽ አማራጭ ሆነው ቢቀርቡም በአጠቃላይ ሲታይ ግን የአልኮል ፍጆታን ስለመቀነሳቸው የሚያሳይ ምንም ዓይነት መረጃ እንደሌለ ይናገራሉ፡፡

በአሁኑ ሰዓት ከአልኮል ነፃ መጠጦቹ ለማንኛውም ሰው ቢቀርቡ ችግር አለማምጣታቸውን የሚደግፍ በቂ ጥናት ባይኖርም በተለያዩ ሀገራት ግን እነዚህ መጠጦች እንደ ለስላሳ መጠጦች ተቆጥረው ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎችን ጨምሮ ለማንኛውም ሰው መሸጥ እንዲችሉ ተፈቅዶላቸው በመሸጥ ላይ ናቸው፡፡ እዚህ ላይ አስጊ ጉዳይ ሆኖ የሚቀርበው መጠጦቹ እጅግ የተወሰነ መጠንም ቢሆን አልኮልን መያዛቸው ብቻ ሳይሆን ታዳጊዎቹ መጠጦቹን መጠቀማቸው በአልኮል አወሳሰዳቸው ላይ ያለው ተፅዕንዖ አለመታወቁም ጭምር እንጂ፡፡

በሌላ መልኩ ጥናቱ የአልኮል ነፃ መጠጥ አቅራቢ ኩባንያዎቹ መጠጦቹን ለወትሮ አልኮል መጠጣት በማይፈቀድባቸው እንደ ስራ ቦታና ማሽከርከር ባሉ ቦታና ሁኔታዎች ጭምር መጠጣት እንደሚቻል አድርገው ማስተዋወቃቸው መጠጦቹ የአልኮል መጠጦችን ከመተካት ይልቅ በራሳቸው ሱስ እንዲሆኑ ሊያደርጉ እንደሚችል ጥናቱ አመላክቷል፡፡

ምንጭ፤ Cosmos
ለተጨማሪ፤ https://cosmosmagazine.com/health/body-and-mind/zero-alcohol-beverages-healthier-or-not/?utm_content=buffer9c884&utm_medium=social&utm_source=twitter.com&utm_campaign=buffer
የእጅ መዳፋችሁን አሻራ ልግዛችሁ የሚለን አማዞን
*****************************
አማዞን የተሰኘው የአለማችን ግዙፍ ተቋም ከተጠቃሚዎች ላይ የእጅ መዳፍ አሻራቸውን በ10 ዶላር ለመግዛት ማሰቡን ይፋ አድርጓል፡፡ እንደ ተቋሙ መረጃ ከሆነ የእጅ መዳፍ አሻራው በካምፓኒው ውስጥ የነጻ ምዝገባ ስርዓና ለሞርታር ስቶር አገልግሎት የሚውል ነው፡፡ ክፍያው በካምፓኒው የመገበያያ ስቶር ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን አንዳንድ የህግና የገበያ ስርዓት ምሁራን በግለሰቦች ላይ የደህንነት ስጋት ያመጣል ሲሉ የአማዞንን ሀሳብ ተችተዋል፡፡
በኖርዝ ኢስተርን ዩኒቨርሲቲ የህግና የኮምፒውተር ሳይንስ ፕሮፌሰር የሆኑት አሪ ዋልድማን ሰዎች ስማቸውን፣ የክሬዲት ካርድ መረጃቸውን እና ስልክ ቁጥራቸውን በፈለጉት ፍጥነት መቀየር የሚችሉ ሲሆን እንደ አሻራ ያሉ ስነ-ህይወታዊ መገለጫዎችን ግን መቀየር አይችሉም፡፡ በመሆኑም ግለሰቦች የግል መገለጫ ሆኑ ስነ-ህይወታዊ መለያዎችን ለድርጅቶች ከሸጡ ሁሌም በድርጅቱ ክትትል ውስጥ የሚወድቁ ይሆናሉ በሚል የአማዞን ሀሳብ አግባብነት እንደሌለው አሳይተዋል፡፡
አማዞን ባለፈው አመት Amazon One devices የተሰኘ የእጅ መዳፍ አሻራ ስካን ማድረጊያ ያቀረበ ሲሆን ደንበኞች የእጅ መዳፋቸውን በማወዛወዝ ብቻ የተለያዩ ክፍያዎችን እንዲከፍሉ ያስችላቸዋል፡፡ የእጅ መዳፍ አሻራቸውን ለተቋሙ ለሚሰጡ ፈቃደኞችን ካምፓኒው የአስር ዶላር ጉርሻን አቅርቧል፡፡ ይህን ለማድረግ የሚያስችለው መሳሪያ በአሁኑ ወቅት 53 በሚደርሱ በአሜሪካ በሚገኙ የአማዞን መደብሮች ጥቅም ላይ መዋል የጀመሩ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ የምግብ አቅርቦት ያለባቸው ሱቆች ይገኙበታል፡፡
የባዮሜትሪክ መለያን ለገበያ ስርዓት በመጠቀም ረገድ ከአማዞን በፊት አይፎን፣ ጎግል ፒክስል ስማርት ስልክ እና ሳምሰንግ ጋላክሲ ስልኮች የእጣት አሻራንና የፊት ገጽን መጠቀም የሚያስችሉ ተደርገው መሰራታቸው የሚታወስ ነው፡፡
ምንጭ techxplore
ተጨማሪ ንባብ https://techxplore.com/news/2021-08-palm-amazon.html
ለ90 ተከታታይ ቀናት እየበረረች መቆየት የምትችለው አውሮፕላን
===================
የአሜሪካን ባህር ኃይል ያለ ማቋረጥ ለ90 ተከታታይ ቀናት እየበረረች መቆየት የምትችል ሰው አልባ አውሮፕላን እየሰራ መሆኑ ተዘገበ፡፡ ስካይድዌለር የሚል ስያሜ የተሰጣት አውሮፕላኗ በስፔን-አሜሪካዊው የኤሮስፔስ ኩባንያ ስካይድዌለር ኤሮ አማካኝነት የምትመረት ይሆናል፡፡ አገልግሎት ላይ ስገባም ለወራት የባህር ኃይሉን ጦር መርከቦች በማጀብ በዙርያቸው ያሉ አካባቢዎችን መቃኘት የምትችል ይሆናል ተብሎላታል፡፡

አውሮፕላኗ ከዚህ ቀደም ተሰርታ በአውሮፓውያኑ 2015 እና 2016 ዓለምን በዞረችው ኢምፐልስ 2 የተሰኘች ሰው ጫኝ አውሮፕላን ላይ ተመስርታ የተሰራች ናት፡፡ ሆኖም ኩባንያው ይህች አውሮፕላን የነበሯት የአብራሪ መቀመጫዎቿን በማውጣት ንድፏን ሲቀይረው ነፃ የተደረጉት ቦታዎች ከሌሎች ማስተካከያዎች ጋር ተዳምረው አውሮፕላኗ ረዘም ላለ ጊዜ እንድትጓዝና መጫን የምትችለው ቁሳቁስ መጠንም እንዲጨምር አስችሏታል፡፡

ከተደረገላት ማስተካከያ በኋላ አውሮፕላኗ 72 ሜትር በሚረዝሙት ክንፎቿ ላይ 270 ካሬ ሜትር የሚሸፍኑ የፀሐይ ኃይል ማመንጫዎች ተገጥሞላቸዋል፡፡ ይህም 2ኪሎ ዋት የሚሆን ኃይል እንድታመነጭ አስችሏታል፡፡ በተጨማሪም በውስጧ ከ360 ኪ.ግ በላይ ክብደት ያላቸው የራዳር እና ካሜራ ግብዓቶችን የመሸከም አቅም እንዲኖራት ሆኗል፡፡

እንደ ስካይድዌለር ኤሮ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሮበርት ሚለር ከሆነ አውፕላኗ በቅድሚያ ራሷን ችላ እንድትበር፣ በመቀጠልም ራሷን ችላ እንድትነሳና እንድታርፍ፣ በመጨረሻም ሙሉ በሙሉ ራሷን ችላ በረራን እንድታከናውን የሚያደርጉ ሙከራዎችን የምትፈፅም ሲሆን እነዚህ ሙከራዎች ከተጠናቀቁ በኋላም ለ90 ቀናት የመበርረር ሙከራዋን ወደማድረግ የምትገባ ይሆናል፡፡ በተጨማሪም ኩባንያው አውሮፕላኗ ላይ የሀይድሮጅን ፊውል ሴሎችን ገጥሞ ብቃቷን ማሳደግያ አልያም የአየር ፀባዩ ተስማሚ በማይሆንበት ጊዜ መጠባበቂያ እንዲሆናት አቅዷል፡፡

ረዘም ላለ ሰዓት መብረር በተለያዩ ወታደራዊ ተልዕኮዎች ላይ ጠቃሚ ነገር ቢሆንም አሁን ላይ የአሜሪካን ባህር ኃይል የሚጠቀማቸው በመጠን ከፍ ከፍ ያሉት ሰው አልባ አውሮፕላን ወይም ድሮኖች እንኳን አየር ላይ እየበረሩ መቆት የሚችሉት ለሰላሳ ሰዓታት ብቻ ነው፡፡

ምንጭ፤ Futurism
ለተጨማሪ፤ https://futurism.com/the-byte/navy-solar-powered-plane-fly-90-days
ለፓርኪንሰን በሽታ አዲስ መፍትሄ ተገኘ
============
የአውስትራሊያው ፍሎሬይ ኒውሮሳይንስ እና የአዕምሮ ጤና ኢንስቲትዩት አጥኚዎች የፓርኪንሰን በሽታን በተሻለ ማከም ይችላል የተባለለትና ምናልባትም ሌሎች የነርቭ ስርዓትን ለሚያጠቁ የጤና እክሎችም መፍትሄ የሚሆን ሃይድሮጄልን ይዘው መጥተዋል፡፡ አዲስ የተሰራው ሃይድሮጄል ሕዋሳት እና ፕሮቲኖችን ለአንጎል በማድረስ በፓርኪንሰን የተጎዱ ሕብረ ህዋሳትን የሚጠግን ይሆናል፡፡

በአንጎል ውስጥ ከሚከሰት የዶፓሚን እጥረት ጋር ተያያዥነት ያለው የፓርኪንሰን በሽታ ብዙውን ጊዜ ህክምናው የሚከናወነው ከዶፓሚን ጋር የተያያዙ መድሃኒቶችን በመጠቀም ነው፡፡ ሙከራዎች እንዳሳዩት ግን በአንጎል ውስጥ ዋናዎቹ ህዋሳትን (Stem Cells) የመተካት ስልቱ ከእነዚህ የዶፓሚን ህክምናዎች በተሻለ ውጤታማና ተያያዥ የጎንዮሽ ጉዳቶችንም ማስቀረት የሚችል መሆኑ ነው፡፡ ሆኖም ህዋሳትን የመተካት ህክምናን ማከናወኑ በራሱ አዳጋች ነው፡፡

ሀይድሮጄሎች በውስጣቸው ውሃን የያዙ ጄሎች ሲሆኑ የፖሊመሮች ጥምረት ውጤት ናቸው፡፡ አዲስ የተሰራው ሃይድሮጄልም ፕሮቲንን ከሚሰጡት ዋና አካላት መካከል የሆኑት ተፈጥሮአዊ አሚኖ አሲዶችን በመጠቀም መሰራቱን የገለፁት የምርምሩ ተሳታፊ ፕ/ር ዴቪድ ኒስቤት ሀይድሮጄሎቹ ለህዋሳት መዋቅራዊ ድጋፍን በሚያደርጉትና ላሚኒነን ተብለው የሚጠሩት ፕሮቲኖች ውስጥ ያሉ አሚኖ አሲዶች አወቃቀርን መስለው የተሰሩ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ የሀይድሮጄሉ አሚኖ አሲዶች አወቃቀርም ህዋሳቱ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ትእዛዝ እንደሚያስተላልፍላቸው አክለው ጠቅሰዋል፡፡

ሀይድሮጄሉ ያለው የኬሚካል ይዘት በቀላሉ ወደ ፈሳሽ መለወጥ እንዲቻልና አንጎል ውስጥም ዘልቆ እንዲገባ ሲያደርገው አንጎል ውስጥ ዘልቆ ከገባ በኋላ ደግሞ ቀድሞ ወደነበረበት ጠጠር ወዳለ ቁመና በመመለስ የዶፓሚን ኒሮኖቻቸውን ላጡት ዋና ህዋሳት ድጋፍ ይሰጣል፡፡

ሀይድሮጄሉ የፓርኪንሰን መፍትሄ ተደርጎ ከመወሰዱ በፊት ገና በሰው ልጆች ላይ ተሞክሮ ዕውቅና ማግኘት ያለበት ቢሆንም አጥኚዎቹ በአይጦች ላይ ሞክረው ውጤታማ ሆኖ አግኝተውታል፡፡ በሰው ላይ የሚሰራ ሆኖ ከተገኘ ታድያ ሀይድሮጄሉን ለመስራት ዋጋው ርካሽ ከመሆኑ አንፃር በስፋት አምርቶ ለገበያ ለማቅረብ ቀላል ይሆናል ተብሎለታል፡፡

ምንጭ፤ Cosmos
ለተጨማሪ፤ https://cosmosmagazine.com/health/medicine/hydrogel-parkinsons/?utm_content=bufferefea5&utm_medium=social&utm_source=twitter.com&utm_campaign=buffer
This media is not supported in your browser
VIEW IN TELEGRAM
የዓለማችን የመረጃ ምርትና ጥርቅም
*****************************
በእጃችን ላይ ያሉት መረጃዎች የተበታተኑ ቢመስሉም ከፍ ብለን መመልከት ከቻልን ግን እርስ በእርሳቸው የተሳሰሩ እና አንዱ የአንዱ ውጤት እንደሆነ የሚያሳየን ግልፅ ምስል እንመለከታለን፡፡ መረጃ በእውነታ ላይ የተመሰረተና የተደራጀ ስለ አንድ ነገር ትክክለኛ ትርጉም የሚሰጥ ለሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቶች ከሚባሉት መካከል ሊመደብ የሚችል ከመሆኑም ባለፈ ለየትኛውም የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች ዋና መፍትሄ እየሆነ የመጣ ጉዳይ መሆኑም ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ስፍር ቁጥር የሌላቸው አያሌ መረጃዎች በእጃችን ሲገኙ ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ የፈለቁት መረጃዎች በሰው ልጅ ታሪክ እስካሁን ከተፈጠሩት መረጃዎች እንደሚልቅ ጥናቶች ያመላክታሉ። ለዚህም መከሰት አስቻይ ሚና ከሚጫወቱት መካከል በየቀኑ በዓለም ቢሊዮን የሚደርሱ የስልክ ጥሪዎች መመዝገባቸው፤ ለብዙ የግብይት አገልግሎቶች የእቃዎች መለያ የሚስጥር ፅሁፍ ባር ኮድ አገልግሎት ላይ መዋል፤ ቢሊዮኖች ፌስቡክና መሰል ማህበራዊ ድረ ገፆችን መጠቀማቸውና መረጃዎችን በስፋት ማሸራሸራቸው፣ አዳዲስ የኮምፒውቲንግና የማጠራቀሚያ ቴክኖሎጂዎች በስፋት መገኘት፣ የተራቀቁ የድምፅ፣ ምስል፣ የሳተላይት ምስል ዳታ መሰብሰቢያ መሳሪያዎች መበልፀጋቸው እና ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ከዚህ ባለፈ ያለንበት ጊዜ ዓለም ወደ አንድ የኢንፎርሜሸን መረብ (ግሎባላይዜሽን) የሚራመድበት ወቅት በመሆኑ መረጃ የሰው ልጆችን የእለት ከእለት ተግባራቸውን ሚለዋወጡበትና የሚግባቡበት መሳሪያ እየሆነ ከመጣ ውሎ አድሯል፡፡ አሁን ላይ የተለያዩ የስታቲክስ መረጃዎች እንደሚሳዩት በ2020 ብቻ በየሰኮንዱ በአንድ ግለሰብ 1.7 ሜጋባይት መረጃ ሲመረት ከዚህ ባለፈም በየቀኑ 306 ቢሊዮን ኢሜሎች ሲላኩ እና 350 ሚሊዮን ፎተዎች ድግሞ በፌስቡክ ብቻ ይጫነሉ፡፡ ይህ ለምሳሌ የተጠቀሰ ብቻ ቢሆንም ይህንና ሌሎች የቴክኖሎጂ ወጤቶችን ተጠቅሞ የአለም ህዝብ አሁን ላይ ማምረት የቻለው የመረጃ ብዛት ባለፉት በሁለትና ሶስት አመታት የተገኘ መሆኑ እጅግ ያስገርማል፡፡ ይህ በዋናነት በ2019 ተመርቶ የተጠራቀመውን 41 ዜታባይት መረጃ እና በ2020 የተመረተውን 59 ዜታባይት መረጃ ሳይጨምር ሲሆን ከዚህ አንጻር ገና በ2021 የሚመረተውም የመረጃ ብዛት 74 ዜታባይት መሆኑ እጅግ አስገራሚ ያደርገዋል፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ቴክኖሎጂዎች እና የአሰራር ስርዓቶች በቀላሉ መረጃዎችን ለማፍለቅ፣ ለመሰባሰብ፣ ለማከማቸት እና ለማሰራጨት የሚያስችሉ ቢሆንም፤ ከምናሰባስባቸው መረጃዎች እውቀትን አንጥረን ማውጣት ካልቻልን የዳታ መጥለቅለቅ ሊኖር እንደሚችል የሚጠበቅ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የተለያዩ መስሪያ ቤቶችና ድረ ገፆች መረጃ የማከማቸት አቅማቸው ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ቢመጣም ወደፊት ለሚያጋጥማቸው የመረጃ መጥለቅለቅ ጥሩ መላ መፈለፍ እንደሚኖርባቸው የሚመከር ነው፡፡ በተለይም በመረጃ ቋት (Database)፣ በዳታዌር ሀውስ ወይንም በሌሎች መረጃ ማጠራቀሚያ ሲስተሞች (Information Repositories) እጅግ ብዙ መረጃዎች ሲከማቹ መረጃዎቹን ለመተንተን እና ውሳኔ ለመስጠት እጅግ አዳጋች ስለሚያደርገው ሌሎች መንገዶችን መተግበር አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፡፡
ምንጭ cloverdx
ተጨማሪ https://www.cloverdx.com/.../how-much-data-will-the-world...
ለሀገራት ትልቅ የደህንነት ስጋት የሆነው የሳይበር ጥቃት
************************************
የኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ እድገት አለማችን አሁን ላለችበት ከፍተኛ እድገት የራሱ የሆነ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ የመረጃ ልውውጥ ፍጥነትና የተለያዩ ስራዎች ዲጂታል ወደ መሆን ማደጋቸው ከሚሰጠው ጥቅም ባሻገር የተለያዩ ስጋቶችም ተጋርጠውበታል፡፡ ከእነዚህ ስጋቶች በዋናነት የሚጠቀሰው የሳይበር ደህንነት ስጋት ነው፡፡ የአለማችን ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ሀገራት በያዝነው 21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሳይበር ጥቃት ምክንያት አንዱ የአንዱ ስጋት በመሆን ሲወነጃጀሉ መስማት የተለመደ ነው፡፡
አሁን ላይ ከጀማሪ ወይም አማተር የሳይበር ጥቃት አድራሾች ጀምሮ በሀገራት እስከሚደገፉ የተለያዩ ቡድኖች በየእለቱ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሳይበር ጥቃት ሙከራን በሀገራት ምስጢራዊ መረጃዎች፣ በተለያዩ አለማቀፍ ተቋማት እና የግል ድርጅቶች ሳይቀር ያደርጋሉ፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያም ከ35 ሺህ በላይ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች እንደተደረገባት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ይህን ተግዳሮት ለመሻገር እንዲያስችላት ሀገራችን ኢትዮጵያ በ2011 የመረጃ ደህንነት ፖሊሲን አውጥታ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሯ የሚታወቅ ቢሆንም ፖሊሲው የተለያዩ ክፍተቶች የተስተዋሉበት እንደሆነ በፖሊሲው ላይ ዳሰሳ ያደረጉ በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲቲዩት የፖሊሲና ስትራቴጂ ጥናት ዳይሬክቶሬት ተመራማሪዎች አሳውቀዋል፡፡
በኢንስቲቲዩቱ በተዘጋጀውና ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት በቀረበው የ2011 የመረጃ ደህንነት ፖሊሲ ዳሰሳ ላይ ተቋማት ሊገጥማቸው የሚችልን የሳይበር ደህንነት ስጋት በጋራ መከላከል የሚችሉበትን መንገድና ሀገራዊ ፖሊሲው ያሉትን ጠንካራ ጎኖችና ሊስተካከሉ የሚገባቸውን ክፍተቶች የተመለከቱ ሀሳቦች ጥናቱን ባደረጉት የኢንስቲቲዩቱ የፖሊሲና ስትራቴጂ ጥናት ዳይሬክቶሬት ተመራማሪዎች አማካኝነት ቀርቧል፡፡
እንደ ተመራማሪዎቹ ገለጻ ከሆነ የ2011ዱ ፖሊሲ በሶስት ምክንያቶች መሻሻል ሊደረግበት ይገባል፡፡ እነዚህም የለውጥ አመራሩ በ2025 በሀገራችን የሚገኙ 30 በመቶ የሚሆኑ ተቋማት አሰራራቸውን ወደ ዲጂታል ስርዓት መቀየር አለባቸው የሚል ግብ ያስቀመጠ በመሆኑ ይህ መስፋፋት የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነትን ከፍ የሚያደርግ በመሆኑ፤ በአለማችን የተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የሰዎችን የኑሮ ዘይቤ ከቀድሞ በተሻለ መልኩ ወደ ዲጂታል የቀየረ መሆኑ እና በሀገራችን እንደ ቴሌኮም ያሉ ተቋማትን ወደ ግል በከፊል የማዘዋወር ስራዎች መኖራቸው ለሳይበር ደህንነት ስጋት ተጋላጭ የመሆናችንን እድል ከፍ የሚያደርጉት መሆኑ ዋነኞቹ ናቸው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ፖሊሲው በወጣበት በ2011 የነበረው የቴክኖሎጂ እድገት ከአሁኑ ጋር ሲነጻጸር መጠነኛ በመሆኑ በፖሊሲው ውስጥ ሊካተቱ የሚገባቸው ቴክኖሎጂ አመጣሽ ለውጦች መኖራቸው፤ የ2011ዱ ፖሊሲ በሳይበር ደህንነት ዙሪያ የተለያዩ ስጋቶች መኖራቸውን አጽንኦት ሰጥቶ የሚያቀርብ ቢሆንም ችግሩን ለመቅረፍ መፍትሔን ያልጠቆመና የፖሊሲውን አፈጻጸም የሚከታተል አካል ያላስቀመጠ መሆኑ ከዚህም በተጨማሪ የግል ተቋማትን ያላካተተ መሆኑ ሌላው ፖሊሲው እንዲሻሻል የሚያስገድድ ጉዳይ እንደሆነ ዳሰሳ አቅራቢዎቹ ትኩረት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
ከሳይበር ደህንነት ጋር የተያያዘ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ሀገራችን ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የሳይበር ደህንነት ስጋት ካለባቸው ሀገሮች ተርታ የተመደበች ናት፡፡
ሃከሮች 600 ሚሊዮን ዶላር የሚተመን የክሪፕቶከረንሲ ዝርፊያ አካሄዱ
========================
በብሎክቼን ዘርፍ ላይ የተሰማራው ፖሊ ኔትወርክ የተባለው ግዙፍ ድርጅት በሲስተሙ ላይ ባጋጠመ መጠነኛ ተጋላጭነት በመረጃ ጠላፊዎች ወይም ሃከሮች እንደ Ether ያሉ በሺዎች የሚቆጠሩ የዲጂታል ገንዘቦችን እንደተዘረፈ አስታወቋል፡፡ ድርጅቱ በቲውተር ገፁ እንደጠቀሰው የተካሄደበት የክሪፕቶከረንሲ ዝርፊያ በመደበኛው ገንዘብ ሲተመን እስካሁን ካጋጠሙ ስርቆቶች ተወዳዳሪ እንደሌለው እና ዝርፊያውም በ10 ሺ የሚቆጠሩ የክሪፕቶ ደንበኞቹን በቀጥታ የሚያጠቃ መሆኑን አንስቷል፡፡
ያልተማከለ የዲጂታል መዝገብ ወይም የ (ledger) አገልግሎት በመስጠት ላይ የነበረው ፖሊ ኔትወርክ በኮንትራት ጥሪዎች ወይም ግንኙነቶች መካከል በተፈጠረ መጠነኛ ተጋላጭነት በመረጃ ጠላፊዎች ሊመዘበር መቻሉን ያወሳው የቢቢሲ ዘገባ በጠቅላላው Ether ከተሰኘው ክሪፕቶከረንሲ 267 ሚሊዮን ዶላር፣ ከ Binance coins 252 ሚሊዮን ዶላር እና USDC ከተባለው ዲጂታል ከረንሲ ደግሞ 85 ሚሊዮን ዶላር ሊዘረፍ መቻሉን ዘግቧል፡፡
ፖሊ ኔትወርክ ዝርፊውን ያካሄዱ የመረጃ ጠላፊዎች በየትኛውም ሀገር ህግ ትልቅ የኢኮኖሚ ወንጀል መፈፀማቸውን ተረድተው መፍትሄ ሊያመጣ የሚችል ስምምነት ከድርጅቱ ጋር እንዲመሰርቱ በቲዊተር መግለጫው አክሏል፡፡ የመረጃው ጠለፋ ኮይንቼክ እና ኤምቲ ጎክስ በተባሉ በቅርብ ጊዜ በተደረጉ የልውውጥ ጥሰቶች ላይ ተንተርሶ የተፈፀመ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት እንዳለም ዘገባው አትቷል፡፡
የሳይበር ደህንነት ባለሙያዎች እንደሚገለጹት አሁን ላይ ይህን መሰል ከባድ ጥቃት በክሪፕቶከረንሲ ገበያ ላይ የተፈፀመ ቢሆንም ባለፉት ሁለት አመታት ከተፈፀመው ጥቃት አንጻር እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ይህ ክሪፕቶከረንሲ የሳይበር ጥቃት በ2020 1.9 ቢሊዮን ዶላር ውድመት አስከትሎ የነበረ ሲሆን በ2019 ደግሞ 4.5 ቢሊዮን ዶላር ወንጅል የተፈፀመበት ክስተት ተፈጥሮ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ምንጭ፡ ቢቢሲ
ተጨማሪ https://www.bbc.com/news/business-58163917
የዓለማችንን መልክ የቀየሩት 20ዎቹ የምንግዜም ታላላቅ ኢኖቬሽኖች
========================
በሰው ልጆች ረዥም የህይወት ጉዞ ውስጥ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚና እንዲ በቀላሉ የሚገለፅ ጉዳይ አይደለም፡፡ ሰዎች ወደዚች ምድር ከመጡ አንስቶ አካላዊውን ዓለም ለመግራት የሚያስችሉ የተለያዩ ፈጠራዎችንና የኢኖቬሽን ውጤቶች ያለማቋረጥ ሲተገብሩ ቆይተዋል፡፡ እነዚህ መሳሪያዎች አለም አሁን ያላትን መልክ ያጎናፀፏት እና የቀጣዩንም ትውልድ እጣ ፋንታ በበጎም ይሁን በክፉ የመወሰን አቅማቸው በእጅጉ የተጠበቀ ነው፡፡ አለማችን እስካሁን ያየቻቸውን የኢኖቬሽን ውጤቶች ለሰው ልጆች ከሰጡት ግልጋሎት እና በታሪክ ውስጥ ካላቸው የገዘፈ ተጽዕኖ አንፃር የሚከተሉት ኢኖቬሽኖች ከምንግዜም ታላላቆቹ መካከል ይገኙበታል፡፡ በዘመን ቅደም ተከተል እንመልከታቸው፡

1. እሳት (FIRE) - ስለእሳት ስናነሳ ብዙዎች የሚከራከሩበት ጉዳይ ቢኖር እሳት ተፈለሰፈ ከሚባል ይልቅ ተገኝቷል የሚለው ሃሳብ እጅግ ተስማሚ መሆኑን ነው፡፡ ቀደምት የሰው ዘሮች እሳትን እንዴት መፍጠር እና መቆጣጠር እንደሚችሉ ከማወቃቸው በፊት የእሳትን አደጋዎች በየአጋጣሚው ተመልክተው ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን የእሳትን ምንነት ከተረዱና የሚሰጣቸውን ጥቅም ካወቁ በኋላ እሳትን እንደ አንድ ትልቅ መገልገያ መጠቀም ጀምረዋል፡፡ አንዳንድ የአርኪዎሎጂ አጥኝዎች እሳት ጥቅም ላይ የዋለው ከ2 ሚሊዮን አመት በፊት ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ 125 ሺ አመታት እንዳስቆጠረ ይገልፃሉ፡፡ ይህ ክርክር ምንም ተባለ ምንም በሰው ልጆች ታሪክ ታላቅ ግኝት የሆነው እሳት ሰዎች ራሳቸውን ከተለያዩ ነገሮች እንዲከላከሉ እና ማብሰል የሚባለውን ትልቅ ክህሎት እንዲረዱ ያስቻል አስገራሚ ግኝት ነው፡፡

2. ተሽከርካሪ ጎማ (WHEEL) - ይህ ፈጠራ የተገኘው በ3500 ዓመተ ዓለም (B.C) በሜሶፖታሚያ የስልጣኔ ዘመን ነበር፡፡ የሜሶፖታሚያ ህዝቦች ይህንን አስገራሚ ፈጠራ የሸክላ ቁሳቁሶችን ለማበጃጀት ሲጠቀሙበት የቆየ ቢሆንም ከሶስትና አራት መቶ አመታት በኋላ ፈጠራው ለሰረገላ ማሽከርከሪያ ጥቅም ላይ ከዋለ በኋላ የመሳሪያው ተፅዕኖ እጅግ እየናኘ ሄዷል፡፡ ተሽከርካሪ ጎማ ለሰው ልጆች የመጓጓዣ እና የንድግ ስርዓት መፈጠር ትልቅ ሚና ያለው ግኝት ነው፡፡

3. ኦፕቲካል ሌንሶች (OPTICAL LENSES) - የሰዎችን የእይታ አቅም ይበልጥ ለመጨመር እንደ ኦፕቲካል ሌንሶች ያሉ አስገራሚ ግኝቶች እጅግ ወሳኝ ነበሩ፡፡ ረዥም የፈጠራ ሂደት የነበራቸው እነዚህ ግኝቶች በጥንቱ የግብፅ እና የሜሶፖታሚያ የስልጣኔ ዘመን እንደበለፀጉ የሚታመን ሲሆን ከግሪክ የተገኙት የብርሃን ንድፈ ሃሳቦች ደግሞ ለግኝቱ እውን መሆን ትልቅ ሚና ነበራቸው፡፡ ኦፕቲካል ሌንሶች እንደቴሊቭዥን፣ ፎቶግራፍ እና ፊልም ያሉ ትልልቅ የሚዲያ ቴክኖሎጂዎች እንዲፈጠሩ መንገድ የጠረጉም ናቸው፡፡

4. ኮምፓስ (COMPASS) - ይህ እንቅስቃሴን ለመምራት የተዘየደው የቴክኖሎጂ ግኝት የሰው ልጆችን የአሰሳ ጥበብና አቅም ወደ አዲስ ምዕራፍ በመወሰድ ተተኪ የማይገኝለት አስገራሚ ግኝት ነው፡፡ የመጀሪያዎቹ ኮምፓሶች በተፈጥሮ የመግነጢሳዊ ይዘት ባላቸው የማዕድን ቁራጮች ወይም (lodestone) አማካኝነት የተሰሩ ሲሆን፤ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ 300 እና 200 አመተ አለም አካባቢ በቻይና እንደተሰሩም ይነገራል፡፡

5. ወረቀት (PAPER) - በ100 ዓመተ አለም አካባቢ በቻይና የተፈለሰፈው ይህ ግኘት የሰው ልጆችን የፅህፈት እና ሃሳብን የማጋራት ልምድ በእጅጉ የቀየረ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ ከዚህ ጊዜ በፊት በግብፅ እና በሜክሲኮ የስልጣኔ ዘመናት የተፈለሰፉት እንደ ፓፒረስና አሜት ያሉ የመፃፊያ ቁሶች ለወረቅት መፈጠር አስተዋፅዖ ቢኖራቸውም በቻይና የነበረው ግኝት ግን አሁን ላለው የወረቀት ቴክሎጂ ትልቅ መሰረት የጣለ ነው፡፡
6. ባሩድ (GUNPOWDER) - ከተለያዩ የኬሚካል ንጥረ ነገሮች ተቀይጦ የሚሰራው ይህ ተቀጣጣይ ፈንጂ በ9ኛው ክፍለ ዘመን በቻይና እንደተፈለሰፈ የሚነገር ሲሆን ለዘመናዊው የጦር ቴክኖሎጂ መስፋፋትም ፈር ቀዳጅ የሚባል ነው፡፡ ይህ ግኘት በሰው ልጆች የውጊያ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ተፅዕኖ ያሳደረ መሆኑም ይነገርለታል፡፡

7. ማተሚያ (PRINTING PRESS) - እንደአውሮፓውያኑ በ1439 በጀርመናዊው ዮሃንስ ጉተንበርግ የተፈጠረው ይህ መሳሪያ ለሰው ልጆች የአዲስ ህይወት መጀመሪያ ዘመን ተደርጎ በብዙዎች ይወሰዳል፡፡ ይህ አስገራሚ ቴክኖሎጂ በሰዎች እጅ እየተፃፈ የሚሰራጨውን አድካሚ የፅህፈት ስርዓት በሜካናይዝድ ማሽን በመተካት የእውቀት አድማስ በሰዎች ዘንድ በቀላሉ እንዲሰፋፋ እና የሃይማኖት አስተምህሮዎች በአለም ላይ በፍጥነት እንዲናኙ ያስቻለ አስገራሚ ግኘት ነው፡፡

8. ኤሌክትሪክ (ELECTRICITY) - የኤሌክትሪክ ፈጠራ ብዙ ብሩህ አዕምሮዎች ለሺህና ከዚያ በላይ አመታት አስተዋፅዖ ያደረጉበት እፁብ ድንቅ የሆነ የቴክኖሎጂ ግኝት ነው፡፡ በ18ኛው ክፍለ ዘመን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ቤንጃሚን ፍራንክሊን ስለኤሌክትሪክ የነበረውን የአለም መረዳት አንድ እርምጃ ያራመደ የመሪነት አበርክቶት እንደነበረው የሚገለፅ ሲሆን በምርምር ዘርፍ ደረጃ ለመስኩ የሰጠው ሁለንተናዊ ትኩረት የቴክኖሎጂውን እድገት በእጅጉ አፋጥኖታል፡፡ ከዚህ ሂደት በማስከተል በ1879 የቶማስ ኤዲሰን የብርሃን አምፖል መፈጠር የኤሌክትሪክ ቴክኖሎጂ ይበልጥ ወደሰዎች እንዲቀርብ ያስቻለ ክስተት ነው፡፡ ይህ የምንግዜም ታላቅ ፈጠራ የሰው ልጆችን የህይወት መንገድ እስከወዲያኘው የቀየረ ግሩም ቴክኖሎጂ ነው፡፡

9. የእንፋሎት ሞተር (STEAM ENGINE) - በስኮትላንዳዊው የፈጠራ ባለሙያ ጀምስ ዋት ከ1763 እስከ 1775 ተሰራ የሚባለው የእንፋሎት ሞተር ሌላኛው ለሰው ልጆች ትልቅ መሰረት የጣለ አስደናቂ የፈጠራ ውጤት ነው፡፡ ይህ የቴክኖሎጂ ግኝት በጊዜው ለነበሩት ባቡሮች፣ መርከቦች እና በጠቅላለው ለኢንዱስትሪው አብዮት ዋና የሃይል ምንጭ በመሆን ተከትሎ ለመጣው የሰው ልጅ አብርሆት ታላቅ ውለታ ያደረገ አስገራሚ ፈጠራ ነው፡፡

10. የነዳጅ ሞተር (INTERNAL COMBUSTION ENGINE) - በ19ኛው ክፍለዘመን የተዋወቀው ይህ የቴክኖሎጂ ፈጠራ በመጀመሪያ በቤልጄሚያዊው ኢንጅነር ኢትየን ሌኖየር (በ1859) የተፈጠረ ሲሆን ከጥቂት አመታት በኋላ በጀርመናዊው ኒኮላስ ኦቶ ይበልጥ ሊሻሻል ችሏል፡፡ ይህ አስገራሚ ፈጠራ የኬሚካል ኢነርጂን ወደ ሜካኒካል ኢነርጂ በመቀየር ቀድሞ የእንፋሎት ሞተር ሲሰጥ የነበረውን ግልጋሎት በተሻለ ሁኔታ በመተካት ለዘመናዊ መኪናዎችና አውሮፕላኖች ማገልገል የቻለ አስገራሚ ፈጠራ ነው፡፡

11. ስልክ (TELEPHONE) - የስኮትላንድ ተወላጁ አሌግዛንደር ግርሃም ቤል በሰው ልጆች የመገናኛ ጥበብ ውስጥ ትልቅ አብዮት የፈጠረውን የስልክ ቴክኖሎጂ በራሱ ስም ያስመዘገበ ታላቅ የፈጠራ ባለሙያ ቢሆንም ከሱ ቀደምና እሱ በነበረበት ዘመንም ብዙ የፈጠራ ባለሙያዎች ለቴክኖለጂው ማበብ የራሳቸውን አሻራ ጥለዋል፡፡ አሌግዛንደር ግርሃም ቤል አንደአውሮፓውያኑ በ1876 በኤሌክተሪክ ስልክ የመጀመሪያውን ፓትንት ካገኘ በኋላ የሰው ልጆች እርስ በእርስ የመገናኘት ልምድ እስወዲያኛው ተቀይሯል፡፡

12. ክትባት (VACCINATION) - የክትባት ግኘት ለአንዳንዶች አከራካሪ ፈጠራ ቢሆንም ብዙዎች እንደሚገልፁት ከሆነ ግን በአለም ላይ የተከሰቱ በሽታዎችን በማጥፋት እና የሰው
ልጆችን በመታደግ በኩል እስካሁን ከታዩ አስደናቂ ግኝቶች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው፡፡ በአለማችን ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰራው ክትባት እንደአውሮፓውያኑ በ1796 ለፈንጣጣ (smallpox) በሽታ የተሰራው ክትባት ሲሆን ኤድዋርድ ጄነር በተባለ ተመራማሪ የተገኘ ነው፡፡ ከዚህ ክትባት በኋላ በ1885 በፈረንዊው ኬሚስትና ባዮለጂስት ሊዩስ ፓስተር የተሰራው የሬቢስ (rabies) ቫይረስ ክትባት ደግሞ ለዘመናዊው የመድሃኒት ቴክኖሎጂ ትልቅ በር የከፈተ ነበር፡፡

13. መኪና (CARS) - ተሽከርካሪ መኪናዎች የሰዎችን የጉዞ ስርዓት እና ተያይዞ የመጣውን የከተሞች ባህሪ እስከወዲያኛው የቀየረ ግሩም የቴክኖሎጂ ፈጠራ ነው፡፡ ተሽከርካሪ መኪናዎች በዘመናዊው ቅርፃቸው በአለም ላይ ብቅ ማለት የጀመሩት በ19ነኛው ክፍለ ዘመን የመጨረሻ አመታት ላይ ሲሆን በዋናነት በጀርመናዊው ካርል ቤንዝ እና ባልደረቦቹ የተከናወኑ ናቸው፡፡ ካርል ቤንዝ እንደአውሮፓውያን አቆጣጠር በ1885 የመጀመሪያዋን ሞተር ብስክሌት ተግባራዊ ካደረገ በኋላ የመኪና ቴክኖሎጂ በአለም ላይ እየናኘ ሄዷል፡፡

14. አውሮፕላን (AIRPLANE) - በ1903 በአሜሪካውያን ወንድማማቾች ለውጤት የበቃው ይህ አስገራሚ ቴክኖሎጂ የሰው ልጆችን የረዥም ርቀት ጉዞ ፈጣን አማራጭ በመስጠት የትራንስፖረት ኢንዱስትሪን እስከወዲያኛው የቀየረ ነው፡፡ የአውሮፕላን ቴክኖሎጂ የአለም ሰዎችን ይበልጥ እንዲቀራረቡ በማድረግ የባህል፣ የምጣኔ ሃብት እና የእውቀት ልውውጦችን ይበልጥ ያዳበረ ቢሆንም በቴክኖሎጂው የማብሰሪያ ጊዚያት በአለም ላይ ለተከሰተው አለምአቀፍ ጦርነት ሌላ አባባሽ ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

15. ፔኒሲሊን (PENICILLIN) - እንደአውሮፓውያኑ በ1928 በስኮትላንዳዊው ሳይንቲስት አሌክዛንደር ፍሌሚንግ የተቀመረው ይህ ግኘት የፋርማሲዩቲካል ዘርፉን አንድ እርምጃ በማራመድ የመጀመሪያውን አንቲባዮቲክ መድሃኒት ለአለም ያስተዋወቀ ነው፡፡ ፔኒሲሊን እጅግ ብዛት ያላቸው ተላላፊ ባክቴሪያዎችን በመከላከል ለረዥም ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለ አንቲባዮቲክ ሲሆን ለዘመናዊው የመድሃኒት ቴክኖሎጂም ፈር ቀዳጅ የሚባል ነው፡፡

16. ሮኬቶች (ROCKETS) - ቀደምት የሚባለው የሮኬት ቴክኖሎጂ ሙከራ በቻይና የስልጣኔ ዘመናት እንደነበር የሚወሱ የታሪክ ማዛግብቶች ቢኖሩም አሁን ላይ የሚታወቀው ዘመናዊ የሮኬት ቴክኖሎጂ ግን በ20ኛው ክፍለ ዘመን የተዋወቀ ነው፡፡ ይህ ግኝት በሰው ልጆች የህዋ ምርምር እና የጠፈር አሰሳ ላይ ትልቅ አበርክቶት የነበረው ፈጠራ ሲሆን በወታደራዊው ዘርፍም የማይናቅ አስተዋፅኦ ያለው ነው፡፡

17. የኒውክለር ማብሊያ (NUCLEAR FISSION) - አተሞችን ይበልጥ ጥቃቅን ወደሆኑ ቅንጣቶች መከፋፈል እና በዚህም ከፍተኛ መጠን ያለው ኢነርጂ የመፍጠር ሂደት የኒውክለር ኃይል ማመንጫዎች እና አቶሚክ ቦምቦች እንዲፈጠሩ አስችሏል፡፡ ይህ አስገራሚ ግኘት በ20ኛው ክፍለ ዘመን በዚህ ዘርፍ ዙሪያ ሲሰሩ በነበሩ ስመጥር የፊዝክስ ሊቃውንት የተከናወነ ቢሆንም የኒውክለር ማብሊያውን በዋናነት በመስራት ረገድ ጀርመናውያኑ ኦቶ ሃን እና ፍሪትዝ ስታስመን አንዲሁም የኦስትሪያ ተወላጅ የሆኑት ሊዝ ማይትነር እና ኦቶ ፍሪሲች በቀዳሚነት ይጠቃሳሉ፡፡

18. ሴሚኮንዳክተሮች (SEMICONDUCTOR) - የአሜሪካ ወይም የአለም የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ማዕከል ከሆነችወ ሲልከን ቫሊ ቅጽል ስም ጀርባ የሚገኘው የሴሚኮንዳክተር ግኘት ብዙ ነገሩ ከሲልከን የተሰራ ሲሆን የአፈጣጠር ሁኔታውም በኤሌክትሪክ ዘመን እና እየመጣ በሚገኘው ዲጂታል ዘመን መካከል ላይ ነበር፡፡ የመጀመሪያው የሴሚኮንዳክተር ቁስን የያዘ መሳሪያ እንደአውሮፓውያኑ በ1947 የተዋወቀ ሲሆን በአሜሪካውያኑ ጆን ባርደን እና ዋልተር ብራታን የተሰራ ነው፡፡

19. የግል ኮምፒውተሮች (PERSONAL COMPUTER) - አንደአውሮፓውያኑ በ1970ዎቹ የተፈጠሩት የግል ኮምፒውተሮች የሰው ልጀችን ሁለንተናዊ አቅም በማሳደግ በኩል ተወዳዳሪ አልነበራቸውም፡፡ በ1974 በማይክሮ ኢኒስትሩመንቴሽን እና ቴሌሜትሪ ሲስተም (MITS) የመጀመሪያ የሚባለው የግል ኮምፒውተር ከተዋወቀ በኋላ ቀጥለው የመጡት እንደ አፕል፣ ማይክሮሶፍት እና አይ ቢ ኤም ያሉ ግዙፍ ኩባንያዎች ዘርፉን እስከወዲያኛው አራቀውታል፡፡

20. በይነ መረብ (INTERNET) - አሁን አሁን የሰው ልጅ እስትንፋስ እስከመሆን የደረሰው ይህ አስገራሚ ግኘት ከ1960ዎቹ ጀምሮ ሙከራዎች ሲደረጉበት የቆየ ቢሆንም አሁን በምናውቀም መልኩ ለሰው ልጆች መድረስ የጀመረው ከ1990ዎቹ ጀምሮ ነው፡፡ በጊዜው አንግሊዛዊው ቲም በርነር-ሊ የመጀመሪያውን የበይነ መረብ መግባቢያ የአለም አቀፍ ድር (WWW) ከቀመረ በኋላ አጠቃላይ የአለም መልክ ሊቀየር ችሏል፡፡ ከዚህ ጊዜ አንስቶ ንግዳችን፣ ፖለቲካችን፣ መዘናኛችን የፈለጋችሁን ስም ስጡት ብቻ ሁለ ነገራችን በኢንተርኔት እና በኢንተርኔት ሁኗል፡፡
ምንጭ፡ Bigthink
https://bigthink.com/paul-ratner/top-20-greatest-inventions-of-all-time
የአየር ንብረት ለውጥ እና የምግብ ዋስትና
======================
የምግብ ዋስትና በመሰረታዊነት አደጋ ውስጥ ሊገባባቸው ከሚችሉ ብዙ ምክንያቶች መካከል የአየር ንብረት ለውጥ በቀዳሚነት ይቀመጣል፡፡ በቅርቡ ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በተሰራ አንድ ጥናት ይህ የአየር ንብረት ለውጥ በምን ያህል መጠን የሰብል ምርታማነትን እና አለም አቀፍ የምግብ ዋስትናን እየተፈታተነ እንደሆነ ለማመልከት ሞክሯል፡፡

በሚኒሶታ ዩኒቨርስቲ የአካባቢ ጥናት ቡድን የተሰራው ይህ ምርምር በዓለም ዙሪያ በሰብል ምርታማነት ላይ ለአራት ዓመታት መረጃ በመሰብሰብ በምን ያክል መጠን በአየር ንብረት ለውጥ ወስጥ ያሉ ጉዳዮች የምግብ ዋስትናን እየተፈታተኑት እንዳለ ለማሳየት የሚሞክር ነው፡፡ የጥናት ቡድኑ በአለም ዙሪያ የፍጆታ መጠናቸው ከፍተኛ በሆኑ አስር የሰብል ምርቶች ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ እንደ በቆሎ፣ ሩዝ፣ ስንዴ እና ማሽላ ያሉ በአብዛኛው የአለም ክፍል የሚበቅሉ ታዋቂ ሰብሎች በምርምሩ ላይ ሊካተቱ ችለዋል፡፡ በአለማችን ላይ ከፍተኛ የፍጆታ መጠን ያላቸው እነዚህን አስር የሰብል ምርቶች 83 በመቶ የሚሆነውን የምግብ ካሎሪን የሚስገኙ የምርት አይነቶች እንደሆኑም ተመራማሪዎች ይናገራሉ፡፡

በአጭር አመታት ውስጥ በፍጥነት እየተቀያየረ ያለው የአየር ንብረት ለውጥ የጥናት ቡድኑ በለያቸው 10 የሰብል ዝርያዎች ላይ ቀላል የማይባል ተፅዕኖ እያሳደረ ቢሆንም በተወሰኑ የአለም ክፍሎችና የሰብል ዝርያዎች ላይ ያለው የምርት ሁኔታ ተነፃፃሪ እድገት የሚይበት ሆነ ተገኝቷል፡፡ ይሁንና እንደአጠቃለይ ያለው ውጤት ሲታይ በአየር ንብረት ለውጥ የተነሳ በአብዛኛው የአለም ክፍል ከፍተኛ ምርት የሚታይባቸው ሰብሎች ቀንሰው ሲገኙ፤ እንደ ሩዝና ስንዴ ያሉ ዋና ዋና የምግብ ዓይነቶች ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ደረጃ ምርታቸው ቀንሶ የተገኘ ነው፡፡

የጥናት ቡድኑ 20,000 በሚደርሱ በተለያዩ ሀገራቱ በተመረጡ መገኛዎች የሙቀት እና ዝናብ ተፅዕኖዎችን በመተንተን የሰብል ምርታማነት እንዴት በቀጥታ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት አደጋ ውስጥ እንደሚገባ ለማመልከት ሞክሯል፡፡ ከጥናቱ የተገኙ ውጤቶች ከቦታውና ከሰብል ዝርያዎች ጋር በተያየዘ አንዱ ከአንዱ ልዩነት ቢኖራቸውም እንደአጠቃላይ ከምርምሩ የተገኘው ውጤት እንደሚያመለከተው በአለማችን ከፍተኛ ምርት የሚታይባቸው ዋና ዋና የሰብል አይነቶች በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በመቀነስ ላይ መሆናቸውን ነው፡፡ ለአብነት በጥናቱ መሰረት የሩዝ ምርት በየዓመቱ ከ0.3% በላይ የምርት መቀነስ የታየበት ሲሆን በአለምአቀፍ ደረጃ የስንዴ ምርትም በየአመቱ በአማካኝ 0.9% እየቀነሰ እንደሚገኝ ጥናቱ ያሳያል፡፡ ይህም በቀጥታ የምግብ ዋስታናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በብዙ ፈርጆች እየተፈታተነው የሚገኝ ነው፡፡ ከአብዛኞቹ የሰብል ምርቶች ድርቅን እና የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅም ያለው የማሽላ ምርት ከሌሎቹ በተለየ ሁኔታ መጠነኛ እድገት የታየበት ሲሆን፤ በተለይም ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት፣ በደቡብ ምስራቅ እስያ እና በሌሎች አንዳንድ ቦታዎች ከ0.7 እስከ 0.9 እድገት የታየበት ምርት እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡
ምንጭ፡ Theconversation
ለተጨማሪ https://theconversation.com/to-what-extent-does-climate-change-affect-food-insecurity-what-we-found-in-lesotho-15652