TechIn2
1.16K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
ቤተሰባዊ ቆይታ፤ በላምባዲና
===========
የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ሶሻል ኮሚቴ የሆነው ላምባዲና አማካኝነት መላው የኢንስቲትዩቱን ቤተሰቦች ያሰባሰበ የቡና ጠጡ መሰናዶ በዛሬው ዕለት ሸጎሌ አካባቢ በሚገኘው የኢንስቲትዩቱ ጽ/ቤት አዘጋጅቷል፡፡ ከኢንስቲትዩቱ የተለያዩ ማዕከላት የተውጣጡ በርካታ ሰራተኞችን አካቶ በተሰናዳው ዝግጅቱ ላይ ላለፉት ሁለት ዓመታት ኮሚቴውን ሲመሩ የቆዩ የኮሚቴው አባላት አዲስ ለተመረጡት የኮሚቴ አባላት ኃላፊነታቸውን አስረክበዋል፡፡
የኮሚቴውን የሁለት ዓመት ቀይታ የተመለከተ ዝርዝር ሪፖርት የኮሚቴው አባል በሆነችው ወ/ት ዮዲት አማካኝነት በዕለቱ ቀርቧል፡፡ በሰራተኞች መካከል ቤተሰባዊ ቅርበትን ከሚፈጥሩ መሰናዶወዎች ባሻገር በሁለቱ ዓመታት ውስጥ ከሰራተኞች እና ሌሎች ምንጮች በተሰበሰበ ገንዘብ አማካኝመነት ህፃናትን ከማሳደግ አንስቶ የተቸገሩ ወገኖችን እስከመደገፍ ያሉ ኮሚቴው የሰራቸውን በርካታ የበጎ አድራጎት ተግባራት በሪፖርቱ ተካተው ለሰራተኞች ተብራርቷል፡፡
ከኮሚቴው ቀዳሚ አባላት መካከል የሆነው አቶ ሰልማን መሐመድ በበኩላቸው ኮሚቴው ከምስረታው አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ባሳለፋቸው ሰባት ዓመታት ውስጥ ሰፈራተኞችን አቀራርቦ የተለያዩ ተግባራትን በሕብረት በማከናወን ረገድ ያደረጋቸው መልካም እንቅስቃሴዎችን በዝግቱ ላይ ገልፀዋል፡፡
በዛሬው መሰናዶ በቅርቡ ጎጆ ለቀለሱ አዳዲስ ባለትዳር ሰራተኞች እንዲሁም ከኢንስቲትዩቱ ለተሰናበቱ ሰራተኞች የስጦታና ሽኝት ዝግጅት ተደርጓል፡፡
ባቢሎናዊያን ከግሪኮች ቀድመው የፓይታጎረስ ቲዎረምን ይጠቀሙ እንደነበር አዲስ ጥናት አመላከተ
ባቢሎናዊያን ከግሪኮች ቀድመው የፓይታጎረስ ቲዎረምን ይጠቀሙ እንደነበር አዲስ ጥናት አመላከተ
====================
በባቢሎን ምድር የተገኘ ዕድሜው ወደ 3,700 የሚጠጋ አንድ የድንጋይ ላይ ፅሁፍ እንዳሳየወድ ባቢሎናውያን የፓይታጎረስ ቲዮረም ፈጣሪ ነው ከሚባልለት የግሪኩ ፈላስፋ ፒታጎራስ ውልድት 1ሺህ ዓመታትን ቀድመው የፓይታጎረስ ቲዮረምን ያውቁትና ይጠቀሙበት ነበር፡፡ ሲ.427 (Si.427) ተብሎ የሚጠራው የድንጋይ ላይ ፅሁፉ ጥንታውያኑ ባቢሎናውያን በእርሻ መሬቶቻቸው መካከል ትክክለኛውን ድንበር ለማስመር ይረዳቸው ዘንድ ሦስት ማዕዘኖን ይጠቀሙ እንደነበር ያሳየ ነው፡፡ ይህም የድንጋይ ላይ ፅሁፉን በዕድሜ ቀዳሚው የአፕላይድ ጂኦሜትሪ ምሳሌ አድርጎታል፡፡
የፈረንሳያውያን አርኪዮሎጂስቶች ቡድን ይህን የተሰራበት ዓመት ከ1900 እስከ 1600 ዓ.ዓ እንደሆነ የሚገመት የድንጋይ ላይ ፅሁፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘው በአውሮፓውያኑ 1894 የአሁኗ ሀገረ ኢራቅ ውስጥ ሲሆን አሁን ግን ፅሁፉ በቱርክ አርኪዮሎጂያዊ ቤተ መዘክር ውስጥ ተቀምጦ ይገኛል፡፡ ይህ ይሁን እንጂ ተመራማሪዎች በድንጋይ ፅሁፉ ላይ የሰፈረውን ነገር ጥቅም የተረዱት አሁን ገና ነው፡፡
ከዚህ ቀደም ባለ ሦስት ማዕዘኖችን የሚቃኘው የሒሳብ ክፍል ሰማይን በምሽት በሚያጠኑ ግሪካውያን አማካኝነት እንደተጀመረ ሲነገር ቆይቷል፡፡ ሆኖም በአዲሱ ግኝገት መሰረት የድንጋይ ላይ ፅሁፉ አሁን ላይ በስፋት ከሚታወቀው የፓይታጎስ ቲዎሪየም ጋር ፍፁም ተመሳሳይ ነገርን ባይገልፅም ባቢሎናውያን የራሳቸው የሦስት ማዕዘኖችን መጠቀምያ ሒሳባዊ ስልትን ይጠቀሙ እንደነበረ አሳይቷል፡፡ የድንጋይ ፅሁፉ ገፅ ላይ ያለው ዝርዝር ማማዎችን ጨምሮ የተለያዩ ህንፃዎች የተገነቡበት አንድ ረግረጋማ ሜዳን ያሳያል፡፡ የድንጋይ ፅሁፉ በሦስት የፓይታጎረስ ሦስትዮሾች፤ ማለትም የሁለት እኩያ ስኩዌሮች ድምር ከሦስተኛው ጋር እኩል መሆኑን የሚያመላክቱ ሦስት ሙሉ ቁጥሮች ላይ ተመስርቶ የተቀረፀ ነው፡፡ በላዩ ላይ የተቀረፁትና መሬት ላይ የሚገኝ ድንበርን ለመለየት ጥቅም ላይ ውለው ሊሆን ይችላሉ የተባለላቸው እነኚህ ቁጥሮች 3፣ 4፣ 5፤ 8፣ 15፣ 17 እንዲሁም 5፣ 12፣ 13 ናቸው፡፡
ምንም እንኳን ከባቢሎናውያኑ 1 ሺህ ዓመት በኋላ የፓይታጎረስ ሕጎች በስነ ስርዓት ተቀምጠው እስካሁንም እያንዳንዳችን በትምህርት ቤት ቆይታችን ተምረን እንድናልፋቸው ቢደረግም ግሪኮች ግን የሒሳብ አስተምሮትን ከግብፆች፤ ግብፆች ደግሞ ከባቢሎናውያን መውረሳቸው በምሁራኑ ዓለም ለረጅም ጊዜ ታውቆ የቆየ ሀቅ ነው፡፡ ሆኖም በአዲሱ ግኝት ላይ አስገራሚ ሆኖ የተገኘው ነገር ባቢሎናውያኑ በነዚያ የሰው ልጅ ሥልጣኔ ገና ጅማሮውን እያደረገ በነበረባቸው ወቅቶች በሒሳቡ ላይ የነበራቸው ውስብስብ መረዳት ነው፡፡
ምንጭ፤ Live Science
ለተጨማሪ፤ httpswww.livescience.comearliest-form-of-pythagorean-triplet
ቴስታ መግጨትና የጤና መዘዙ
===========
ከዚህ ቀደም በግላስኮ ዩኒቨርሲቲ ተሰርቶ የወጣ አንድ ጥናት እንዳመላከተው እግር ኳስ ተጫዋቾች ከሌላው ሰው አንፃር ደሜንሻ በተሰኘው የአዕምሮ በሽታ የመሞት እድላቸው በ3.5 እጥፍ የላቀ መሆኑን በአልዛይመር ወይም የመርሳት በሽታ የመያዝ እድላቸውም በ5 እጥፍ የላቀ መሆኑን አመላክቶ ነበር፡፡ ሆኖም ይህ ለምን ሊሆን እንደቻለ ግን አመላከተም፡፡

ታድያ ከአውሮፓውያኑ 1930 እስከ 1998 ድረስ እግር ኳስን ሲጫወቱ በነበሩ 7676 የቀድሞ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋቾች ላይ የተጠናውን ጥናት መሰረት በማድረግ የተደረገ ሌላ አዲስ ምልከታ እንዳሳየው ደግሞ በእግር ኳስ ጨዋታ ላይ ኳስን ከግብ ክልል ለማራቅ በተደጋጋሚ ቴስታ የሚገጩት የተከላካይ መስመር ተጫዋቾች ከሌላ ማንኛውም ሰው አንፃር በአዕምሮ በሽታ የመያዝ እድላቸው በ5 እጥፍ የላቀ መሆኑንና የመሀል መስመር ተጫዋቾችም ከዚህ ብዙ ያላነሰ መሆኑን አመላክቷል፡፡ ከተከላካዮች እና መሀል ሜዳ ተጫዋቸፖች በመቀጠል አጥቂወዎች 2.79 እጥፍ የላቀ በአዕምሮ በሽታ የመያዝ ዕድል ሲኖራቸው ብዙም ኳስን በግንባራቸው የማይጫወቱት ግብ ጠባቂዎች ግን በአዕምሮ በሽታ የመያዝ ዕድላቸው ከማንኛውም ሰው ያልተለየ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

እግር ኳስ ተጫዋቾች ከሚጫወቱበት ቦታ ባለፈም የሚጫወቱበት ዓመት ብዛትም በአዕምሮ ጤናቸው ላይ ተፅዕንዖው የጎላ ነው፡፡ በዚህም 15 ዓመታትን እና ከዚያ በላይ እግር ኳስን በመጫወት ያሳለፉት ተጫዋቾች ደሜንሻን ጨምሮ በተለያዩ የአዕምሮ በሽታዎችን የመታመም ዕድላቸው በአምስት ዕጥፍ የላቀ ሆኖ ተገኝተዋል፡፡

የአዕምሮ በሽታ ላይ ከወደቁት የእግር ኳስ ተጫዋቾች መካከል የቀድዎቹ ስኮትላንዳዊያን የሴልቲክ ተጫዋቾች ቢሊ ማክኔል እና ስቲቭ ቻመርስ፣ የቀድሞው የስኮትላንድ እና ማንቼስተር ዩናይትድ ተከላካይ ጎርደን ማክዊን እንዲሁም የእንግሊዝ እግር ኳስ ጀግናው ሰር ቦቢ ቻርልተን ይገኙበታል፡፡

ከሁለት ዓመታት በፊት ግር ኳስ ተጫዋቸች በጤናቸው ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ከሌሎች እግር ኳስን እንጀራ ብለው ተጫውተው ከማያውቁ 23,028 ሰዎች ጋር በማነፃፀር የተሰራው ጥናቱ የተሳታፊዎችን ፆታ፣ የትውልድ ዓመት፣ ማህበራዊ-ምጣኔ ሀብታዊ ሁናቴ እንዲሁም የመኖርያ አድራሻን ጭምር ከግንዛቤ ያስገባ ነው፡፡ ከ23 ሺው እግር ኳስ ተጫዋች ያልሆኑ የጥናቱ ተሳታፊዎች ውስጥ 366ቱ የአዕምሮ በሽታው ሲገኝባቸው በአንፃሩ አነስ ያለ ቁጥር ያላቸው እግር ኳስ ተጫዋች የጥናቱ ተሳታፊዎች (7676) መካከል ግን 386ቱ የአዕምሮ በሽታዎች ተጠቂ ሆነው ተገኝተዋል፡፡

በሁሉም ሀገራት ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ በመላው ዓለም ባሉ ሰዎች ዘንድ ተወዳጅ የሆነው እግር ኳስ ከስፖርቶች ሁሉ ቀዳሚው ነው፡፡ ታድያ የጥናቱ ተሳታፊ ባለሙዎችም ይህን ዝነኛ ስፖርት በበላይነት የሚመራው ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ወይም ፊፋ ለእግር ኳስ ተጫዋቾች ጤና ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራና ተጫዋቾችም በዚህ ረገድ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መክረዋል፡፡

ምንጭ፤ The Herald
ለተጨማሪ፤ https://www.heraldscotland.com/news/homenews/19485256.glasgow-university-dementia-football-study-reveals-risk-five-fold-defenders/
ከ2015 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ቬኑስ ጉዞ ሊደረግ ነው
=============================
የአውሮፓ ስፔስ ኤጀንሲ ንብረት የሆኑ ሁለት መንኮራኩሮች በዚህ ሳምንት ውስጥ በሰኣታት ልዩነት ወደ ቬኑስ ጉዙ እንደሚያደርጉ ተነግሯል፡፡ ሶላር ኦርቢተር የተባለው የኢ ኤስ ኤ መንኩራኩር ከናሳ ጋር በጋራ በመሆን ዛሬ ነሃሴ ዘጠኝ ጉዞውን የሚደርግ ሲሆን ከ33 ሰዓታት ልዩነት በኋላ ከአውሮፓ በተጨማሪ የጃፓን ተመራማሪዎች የተሳተፉበት ቤፒኮሎምቦ የተሰኘው ሁለተኛ መንኮራኮር ተልዕኮውን ለመፈጸም ጉዞውን ወደ ቬኑስ የሚደርግ ይሆናል፡፡

አንደአውሮፓውያኑ ከ2015 በኋላ ምንም አይነት ጉዞ ያልተደረገባት ቬኑስ በዚህኛው ተልዕኮ ስለፓላኔቷ ካባቢ አየር በስፋት ለመረዳትና የተለያዩ ምርምሮችን ለማድረግ የሚስችል መረጃ ለመሰብሰብ የታቀደ ነው፡፡ በ2020 ወደ ስፔስ ተጉዞ ፀሃይ ካለችበት ከ26 ሚሊዮን ማይልስ ርቀት ላይ ይገኝ የነበረው ሶላር ኦርቢተር በመጀመሪ ወደ ቬኑስ ጉዞውን በማደርግ ፕላኔቷ ካለችበት 7,995 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ኦብዘርቬሽኑን የሚያከናውን ይሆናል፡፡ በአንጻሩ በ2018 ወደ ሜርኩሪ መስመር ተልኮ የነበረው ቤፒኮሎምቦ የተሰኘው ሁለተኛ መንኮራኮር ከሰዓቶች በኋላ ወደ ቬኑስ በማምራት በ550 ኪሎ ሜትር ርቀት ፕላኔቷን የሚጠጋት ይሆናል፡፡

እንደሚታወቀው በሰማይ ላይ ከምናያቸው አጠቃላይ አካላት ከጨረቃ ቀጥሎ ደማቅ የሆነችው ቬኑስ ከዘጠኙ ፕላኔቶችም በጣም ሞቃታማዋ ፕላኔት ናት። እስከ 462 ሴልሽየስ የሚደርስ ሀሩር የአየር ንብረት አላት። የአየር ግፊትዋ በጣም ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ቬኑስ ላይ የተቀመጠ ሰው ባህር ውስጥ የተቀመጠ ያህል ይጫጫነዋል። የአየር ንብረቱዋ 96.5% ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ (CO2) ነው ሲሆን ይህም ከፀሀይ የሚመጣውን ጨረር አምቆ በመያዝ ፕላኔቱዋ እጅግ እድትሞቅ ያደርጋታል።

ፕላኔቱዋን እንዲያጠኑ እ.ኤ.አ ከ 1962 ጀምሮ ብዙ መንኮራኩሮች ተልከዋል። በ2006 venus express space shuttle የተባለች መንኮራኩር የተላከች ሲሆን እስካሁን ድረስ መረጃ በመሰብሰብ ላይ ትገኛለች። አሁን ወደ ፕላኔቷ እንዲጓዙ የተደረጉት ሁለቱ መንኮራኩሮች ከቬኑስ የስበት ሃይል ጋር ራሳቸውን በማስማማትና በርቀት በመቅረብ ስለፕላኔቷ የማግኔቲክና ፕላዝማ ከባቢ መረጃዎችን የሚሰበስቡ እና ምስሎችንም የሚያነሱ ይሆናል፡፡
ምንጭ፡ interestingengineering
https://interestingengineering.com/two-esa-probes-will-visit-venus-within-hours-of-each-other-next-week
ከአልኮል ነፃ መጠጦች የአልኮል ሱሰኝነትን ይቀንሱ ይሆን?
====================
የአልኮል መጠጦች ጣዕም ያላቸው ግን ደግሞ በውስጣቸው ያለው የአልኮል መጠን ከ0.5 በመቶ በታች የሆኑት ከአልኮል ነፃ መጠጦች በመስፋፋት ላይ ናቸው፡፡ መጠጦቹ ገበያ ላይ ለጤና ተስማሚ እንደሆኑ የአልኮል አማራጮች ተደርገው ቢተዋወቁም መሰረቱን አውስትራሊያ አድርጎ የተሰራ ጥናት ግን እውነትም የአልኮል መጠጥ ፍጆታን ስለመቀነስ አለመቀነሳቸው አልያም በተቃራኒው ለበለጠ አልኮል ፍጆታ ማጋለጥ አለማጋለጣቸው ላይ ጥናት ሊደረግ እንደሚገባ አንስቷል፡፡

ሰዎች መጠጦቹን በምን መልኩ እየተጠቀሙ እንደሆነ ማረጋገጥ እንደሚገባ የጥናቱ ዋና ፀኃፊና በሜንዚስ ስኩል ኦፍ ኸልዝ ሪሰርች ውስጥ አጥኚ የሆኑት ዶ/ር ካሳንድራ ራይት ይገልፃሉ፡፡ አክለውም ከአልኮል ነፃ መጠጦቹ የመጠጥ ሱስ ውስጥ ለገቡ ጠጪዎች እንደ ጉዳትን ቀናሽ አማራጭ ሆነው ቢቀርቡም በአጠቃላይ ሲታይ ግን የአልኮል ፍጆታን ስለመቀነሳቸው የሚያሳይ ምንም ዓይነት መረጃ እንደሌለ ይናገራሉ፡፡

በአሁኑ ሰዓት ከአልኮል ነፃ መጠጦቹ ለማንኛውም ሰው ቢቀርቡ ችግር አለማምጣታቸውን የሚደግፍ በቂ ጥናት ባይኖርም በተለያዩ ሀገራት ግን እነዚህ መጠጦች እንደ ለስላሳ መጠጦች ተቆጥረው ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎችን ጨምሮ ለማንኛውም ሰው መሸጥ እንዲችሉ ተፈቅዶላቸው በመሸጥ ላይ ናቸው፡፡ እዚህ ላይ አስጊ ጉዳይ ሆኖ የሚቀርበው መጠጦቹ እጅግ የተወሰነ መጠንም ቢሆን አልኮልን መያዛቸው ብቻ ሳይሆን ታዳጊዎቹ መጠጦቹን መጠቀማቸው በአልኮል አወሳሰዳቸው ላይ ያለው ተፅዕንዖ አለመታወቁም ጭምር እንጂ፡፡

በሌላ መልኩ ጥናቱ የአልኮል ነፃ መጠጥ አቅራቢ ኩባንያዎቹ መጠጦቹን ለወትሮ አልኮል መጠጣት በማይፈቀድባቸው እንደ ስራ ቦታና ማሽከርከር ባሉ ቦታና ሁኔታዎች ጭምር መጠጣት እንደሚቻል አድርገው ማስተዋወቃቸው መጠጦቹ የአልኮል መጠጦችን ከመተካት ይልቅ በራሳቸው ሱስ እንዲሆኑ ሊያደርጉ እንደሚችል ጥናቱ አመላክቷል፡፡

ምንጭ፤ Cosmos
ለተጨማሪ፤ https://cosmosmagazine.com/health/body-and-mind/zero-alcohol-beverages-healthier-or-not/?utm_content=buffer9c884&utm_medium=social&utm_source=twitter.com&utm_campaign=buffer
የእጅ መዳፋችሁን አሻራ ልግዛችሁ የሚለን አማዞን
*****************************
አማዞን የተሰኘው የአለማችን ግዙፍ ተቋም ከተጠቃሚዎች ላይ የእጅ መዳፍ አሻራቸውን በ10 ዶላር ለመግዛት ማሰቡን ይፋ አድርጓል፡፡ እንደ ተቋሙ መረጃ ከሆነ የእጅ መዳፍ አሻራው በካምፓኒው ውስጥ የነጻ ምዝገባ ስርዓና ለሞርታር ስቶር አገልግሎት የሚውል ነው፡፡ ክፍያው በካምፓኒው የመገበያያ ስቶር ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን አንዳንድ የህግና የገበያ ስርዓት ምሁራን በግለሰቦች ላይ የደህንነት ስጋት ያመጣል ሲሉ የአማዞንን ሀሳብ ተችተዋል፡፡
በኖርዝ ኢስተርን ዩኒቨርሲቲ የህግና የኮምፒውተር ሳይንስ ፕሮፌሰር የሆኑት አሪ ዋልድማን ሰዎች ስማቸውን፣ የክሬዲት ካርድ መረጃቸውን እና ስልክ ቁጥራቸውን በፈለጉት ፍጥነት መቀየር የሚችሉ ሲሆን እንደ አሻራ ያሉ ስነ-ህይወታዊ መገለጫዎችን ግን መቀየር አይችሉም፡፡ በመሆኑም ግለሰቦች የግል መገለጫ ሆኑ ስነ-ህይወታዊ መለያዎችን ለድርጅቶች ከሸጡ ሁሌም በድርጅቱ ክትትል ውስጥ የሚወድቁ ይሆናሉ በሚል የአማዞን ሀሳብ አግባብነት እንደሌለው አሳይተዋል፡፡
አማዞን ባለፈው አመት Amazon One devices የተሰኘ የእጅ መዳፍ አሻራ ስካን ማድረጊያ ያቀረበ ሲሆን ደንበኞች የእጅ መዳፋቸውን በማወዛወዝ ብቻ የተለያዩ ክፍያዎችን እንዲከፍሉ ያስችላቸዋል፡፡ የእጅ መዳፍ አሻራቸውን ለተቋሙ ለሚሰጡ ፈቃደኞችን ካምፓኒው የአስር ዶላር ጉርሻን አቅርቧል፡፡ ይህን ለማድረግ የሚያስችለው መሳሪያ በአሁኑ ወቅት 53 በሚደርሱ በአሜሪካ በሚገኙ የአማዞን መደብሮች ጥቅም ላይ መዋል የጀመሩ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ የምግብ አቅርቦት ያለባቸው ሱቆች ይገኙበታል፡፡
የባዮሜትሪክ መለያን ለገበያ ስርዓት በመጠቀም ረገድ ከአማዞን በፊት አይፎን፣ ጎግል ፒክስል ስማርት ስልክ እና ሳምሰንግ ጋላክሲ ስልኮች የእጣት አሻራንና የፊት ገጽን መጠቀም የሚያስችሉ ተደርገው መሰራታቸው የሚታወስ ነው፡፡
ምንጭ techxplore
ተጨማሪ ንባብ https://techxplore.com/news/2021-08-palm-amazon.html
ለ90 ተከታታይ ቀናት እየበረረች መቆየት የምትችለው አውሮፕላን
===================
የአሜሪካን ባህር ኃይል ያለ ማቋረጥ ለ90 ተከታታይ ቀናት እየበረረች መቆየት የምትችል ሰው አልባ አውሮፕላን እየሰራ መሆኑ ተዘገበ፡፡ ስካይድዌለር የሚል ስያሜ የተሰጣት አውሮፕላኗ በስፔን-አሜሪካዊው የኤሮስፔስ ኩባንያ ስካይድዌለር ኤሮ አማካኝነት የምትመረት ይሆናል፡፡ አገልግሎት ላይ ስገባም ለወራት የባህር ኃይሉን ጦር መርከቦች በማጀብ በዙርያቸው ያሉ አካባቢዎችን መቃኘት የምትችል ይሆናል ተብሎላታል፡፡

አውሮፕላኗ ከዚህ ቀደም ተሰርታ በአውሮፓውያኑ 2015 እና 2016 ዓለምን በዞረችው ኢምፐልስ 2 የተሰኘች ሰው ጫኝ አውሮፕላን ላይ ተመስርታ የተሰራች ናት፡፡ ሆኖም ኩባንያው ይህች አውሮፕላን የነበሯት የአብራሪ መቀመጫዎቿን በማውጣት ንድፏን ሲቀይረው ነፃ የተደረጉት ቦታዎች ከሌሎች ማስተካከያዎች ጋር ተዳምረው አውሮፕላኗ ረዘም ላለ ጊዜ እንድትጓዝና መጫን የምትችለው ቁሳቁስ መጠንም እንዲጨምር አስችሏታል፡፡

ከተደረገላት ማስተካከያ በኋላ አውሮፕላኗ 72 ሜትር በሚረዝሙት ክንፎቿ ላይ 270 ካሬ ሜትር የሚሸፍኑ የፀሐይ ኃይል ማመንጫዎች ተገጥሞላቸዋል፡፡ ይህም 2ኪሎ ዋት የሚሆን ኃይል እንድታመነጭ አስችሏታል፡፡ በተጨማሪም በውስጧ ከ360 ኪ.ግ በላይ ክብደት ያላቸው የራዳር እና ካሜራ ግብዓቶችን የመሸከም አቅም እንዲኖራት ሆኗል፡፡

እንደ ስካይድዌለር ኤሮ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሮበርት ሚለር ከሆነ አውፕላኗ በቅድሚያ ራሷን ችላ እንድትበር፣ በመቀጠልም ራሷን ችላ እንድትነሳና እንድታርፍ፣ በመጨረሻም ሙሉ በሙሉ ራሷን ችላ በረራን እንድታከናውን የሚያደርጉ ሙከራዎችን የምትፈፅም ሲሆን እነዚህ ሙከራዎች ከተጠናቀቁ በኋላም ለ90 ቀናት የመበርረር ሙከራዋን ወደማድረግ የምትገባ ይሆናል፡፡ በተጨማሪም ኩባንያው አውሮፕላኗ ላይ የሀይድሮጅን ፊውል ሴሎችን ገጥሞ ብቃቷን ማሳደግያ አልያም የአየር ፀባዩ ተስማሚ በማይሆንበት ጊዜ መጠባበቂያ እንዲሆናት አቅዷል፡፡

ረዘም ላለ ሰዓት መብረር በተለያዩ ወታደራዊ ተልዕኮዎች ላይ ጠቃሚ ነገር ቢሆንም አሁን ላይ የአሜሪካን ባህር ኃይል የሚጠቀማቸው በመጠን ከፍ ከፍ ያሉት ሰው አልባ አውሮፕላን ወይም ድሮኖች እንኳን አየር ላይ እየበረሩ መቆት የሚችሉት ለሰላሳ ሰዓታት ብቻ ነው፡፡

ምንጭ፤ Futurism
ለተጨማሪ፤ https://futurism.com/the-byte/navy-solar-powered-plane-fly-90-days