TechIn2
1.16K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
የቶኪዮ አሎምፒክ ሜዳሊያዎች የተሰሩበት አሮጌ የኤሌክትሮኒክስ መሳርያዎች
====================
በየዓመቱ 53 ሚሊዮን ቶን የሚደርስ የኤሌክትሮኒክስ መሳርያ ውጋጅ (e-waste) በአለማችን ጥቅም ላይ ውሎ ይጣላል፡፡ የኤሌክትሮኒክስ መሳርያዎች የአገልግሎት ዘመናቸውን ጨርሰው እንደቆሻሻ በሚጣሉበት ጊዜ አግባብነት ያለው የአወጋገድ ስርዓት ካልተበጀላቸው አልያም ዳግም ጥቅም ላይ የሚለውሉበት ሂደት ከሌላቸው በአፈር እና በከርሰ ምድር ውሃ ላይ ጎጂ ውጤቶችን ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡

እነዚህ ቁሶች በተለይም በአፈሮቻችን ላይ የሚለቋቸው የአርሴኒክ፣ እርሳስ እና ካድሚየም ያሉ ከባድ መርዛማ የብረት ኬሚካሎች የእፅዋትን የአስተዳደግ ሂደት በመበከል እና በከርሰ ምድር ውሃ ላይ ጥፋት በማስከተል ህይወታቸውን በዚህ ላይ ለመሰረቱት የተለያዩ እንስሳት አደጋን ያመጣሉ፡፡ ይህ የስነ ምህዳር መዛባት አደጋ በእንስሳትና በእፅዋት የሚያበቃ ቢመስልም በጊዜ ሂደት በምግብ አቅርቦት ሰንሰለት እና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ወደሰዎች ማምራቱ የሚቀር አይደለም፡፡ ይህን አለም አቀፍ ችግር በሚቻለው አቅም ለመቅረፍ እና የወደፊቱን የሰዎች ጤናማ ህይወት በበጎ ለማረጋገጥ አንዲህ ያሉ ቁሶች ዳግም ጥቅም ላይ የሚለውሉበት ሂደት ማበጀቱ በብዘዎች የሚደገፍ ጉዳይ ነው፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ አሁን እየተካሄደ ባለው የቶኪዮ አሎምፒክ ውድድር ላይ አዘጋጇ ሃገር ጃፓን ለአሸናፊዎቹ የሚሰጠውን ሜዳልያ ለመስራት ጥቅም ላይ ያዋለቸው የኤሌክትሮኒክስ መሳርያ ውጋጅ የአለም አቀፍ ችግር ለሆነው ለዚህ ጉዳይ ጥሩ መፍትሄን ያሳየ ይመስላል፡፡ ሃገሪቱ ይህንን ስራ በትኩረት የጀመረችው በ2017 ሲሆን ቶክዮ 2020 ሜዳሊያ ፕሮጀክት በሚል በመላ ሀገሪቱ ተጥለው የሚገኙ የኤሌክትሮኒክስ መሳርያዎች (በተለይም የስልክ ቀፎዎች) እንዲሰበሰቡ አድርጋለች፡፡ በሃገሪቱ የኦሎምፒክ ኮሚቴ አስተባበሪነት ሲሰበሰብ የቆው የኤሌክትሮኒክስ ውጋጅ በ2019 ከተጠናቀቀ በኋላ በጥቅሉ 78,985 ቶን ውጋጅ እንዲሰበሰብ ሆኗል፡፡ ይህ የተሰበሰበው የኤሌክትሮኒክስ ቁስ መንግስት ፍቃድ በሰጣቸው የስራ ተቋራጮች ከተከፋፈለ በኋላ በተለያዩ ህጋዊ አሰራሮች አማካኝነት ወደስራ እንዲገቡ ተድርጓል፡፡

ከተሰበሰበው የኤሌክትሮኒክስ ውጋጅ የብረት ንጥረ ነገር ያለው ቁስ ቀልጦ ወደ ማጣራት ሂደት ያመራ ሲሆን ሌላ አይነት ይዘት ያላቸው እቃዎችም ተለይተው አንዲገቡ ተድረገዋል፡፡ የኦሎምፒክ ኮሚቴው ከዚህ ጠቅላላ ሂደት በኋላ 32 ኪሎ ግራም ወርቅ፣ 3,500 ኪ.ግ ብር እና 2,250 ኪ.ግ ነሃስ ማግኘት የቻለ ሲሆን ይህም ለኦሎምፒክና ለፓራኦሎምፒክ ውድድሮች የሚያስፈልጉትን አጠቃላይ 2,500 ሜዳሊያዎች መስራት የሚያስችል ነበር፡፡
https://interestingengineering.com/tokyos-olympic-medals-are-made-of-47-tons-of-recycled-e-waste
መንታዋን በሆዷ ይዛ የተወለደችው ህፃን
==========
በእስራኤል የተወለደች አንድ ህፃን መንትያዋን ይዛ መወለዷ ተዘገበ፡፡ ህፃኗ ለዚህ የበቃቸው እጅጉን አልፎ አልፎ በሚከሰትና በሳይንሳዊ አጠራሩ “ፌቱስ ኢን ፌቱ” የሚባል የጤና ሁኔታ ስለተከሰተባት ነው፡፡
ሀኪሞች ህፃኗ ከመወለዷ በፊት በአልትራሳውንድ ሲመለከቷት በፅንሱ ላይ ችግር ሊኖር እንደሚችልና ሆዷም ከተለመደው ከፍ ያለ መሆኑን ተረድተው ነበር፡፡ ህፃኗ ስትወለድም ሀኪሞቹ ኤክስሬይ እና አልትራሳውንድን ጨምሮ የተለያዩ ምርመራዎችን ሲያደርጉ በህፃኗ ሆድ ውስጥ ፅንስ ማደጉን ለመመልከት መቻላቸው ተዘግቧል፡፡
ፌቱስ ኢን ፌቱ “በፅንስ ውስጥ ፅንስ” እንደማለት ሲሆን ከተለመደው ወጣ ያለ (Abnormal) ፅንስ አንድ ጤናማ በሆነ ፅንስ ውስጥ ማደጉን የሚያመላክት የጤና ክስተት ነው፡፡ ክስተቱ እጅጉን አልፎ አልፎ የሚከሰት ሲሆን በየጊዜው ከሚወለዱ 500 ሺህ ህፃናት መካከል በአንደኛው ላይ ብቻ የሚመጣ ነው፡፡ እስካሁን ተጨማሪው ፅንስ በምን ምክንያት እንደሚፈጠር ግልፅ ባይሆንም የዋናው ፅንስ ጥገኛ መንትያ (Parasitic Twin) ሊሆን ይችላል ሲሉ ተመራማሪዎች መላ ምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ ተጨማሪው ፅንስ የሚፈጠረውም መንታዎች በሚፀነሱበት የመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ወቅት አንደኛውን ፅንስ ሌላኛውን ሲውጠው መሆኑ በባለሙያዎች ዘንድ ይነገራል፡፡
ህጻኗ የተወለደችበት የእስራኤሉ ኤሱታ ጤና ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ኦመር ግሎቦስ በበኩላቸው ሁነቱ የተፈጠረው ፅንሱ በማደግ ላይ ባለበት ጊዜ መሆኑን ገልፀው ተጨማሪው ፅንስ እዛው ቢኖርም በህይወት ግን እንደማይቆይ ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ህፃኗ ከተደረገላት የቀዶ ጥገና ህክምና በጥሩ ሁኔታ እያገገመች ሲሆን ወደ ቤቷ ተመልሳም ከእናቷ ዘንድ ለመሆን መብቃቷ ተገልጿል፡፡
ምንጭ፤ Live Science
ለተጨነማሪ፤ https://www.livescience.com/fetus-in-fetu-israel.html
የቶኪዮ ኦሎምፒክ መሮጫ መም እና ከበስተጀርባ ያለው ቴክኖሎጂው
===================
ባለፉት 4 ቀናት ውስጥ አትሌቶቻችን ሲንፈላሰሱበት የተመለከትነው የቶኪዮ ኦሎምፒክ መሮጫ መም ሞንዶ በተሰኘው ከአውሮፓውያኑ 1948 አንስቶ በ12 ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ላይ የመሮጫ መም ባቀረበው ኩባንያ የተሰራ ነው፡፡ እንደ ኩባንያው አገላለፅ የኦሎምፒኩን አትሌቲክስ ውድድሮች በሚያስተናግደው የጃፓን ብሔራዊ ስታዲየም የተዘረጋው መም በላይኛው ክፍሉ ባለ ሦስት እይታ በሆኑና ከተመረጠ የፖሊመር ስርዓት ጋር ተጣምረውና እንዲጠነክሩ ተደርገው በተሰሩ ጥቃቅን ጎማዎች ተሞልቷል፡፡ የማጠንከር (Vulcanization) ሂደቱም ሞለኪውላዊ ትስስሩን በማጠናከሩ ጠቅጠቅ ያለ ንጣፍን ፈጥሯል፡፡ በሌላ አነጋገር መሙ ፈጣን ነው እንደማለት ነው፡፡

ለስላሳ፣ ውብ እና እስከ ዛሬ ከሮጥኩባቸው ምርጥ የመሮጫ መሞች አንዱ ነው የሚለው የአሜሪካን 100 ሜትር ሯጩ ሮኒ ቤከር “በደመና ላይ የምራመድ ያህል ይሰማኛል” ሲል የመሙን ምቹነት ይገልፃል፡፡

ከምቾት ባለፈ ግን ስለ ፍጥነቱም እየተነገረለት ይገኛል፡፡ መሙ ከአራት ወራት በላይ ፈጅቶ ባለፈው ዓመት ህዳር ወር ላይ የተጠናቀቀ ቢሆንም የኦሎምፒኩን ለአንድ ዓመት መዘግየት ተከትሎ ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ ሳይደረግት በቶኪዮ ፀሐይ እየተጠበሰ መቆየቱ ጠንከር እንዲል አድርጎታል፡፡ ምን ያህል ፈጣን ነው የሚለውን ምናልባትም ከኦሎምፒኩ መገባደድ በኋላ የተመዘገቡ ክብረ ወሰኖችን በመመልከት የሚወሰን ቢሆንም ከአትሌች ምስክርነት ለማረጋገጥ እንደሚቻለው ግን መሙ ፍጥነታቸውን እንደጨመረላቸው ነው፡፡ ከነዚህ አትሌቶች መካከል አሜሪካዊው የ800 ሜትር ሯጭ ክሌይተን መርፊ መሙ ፈጣንና ምናልባትም በቀጣይ ክብረ ወሰኖች የሚሰባበሩበት ሊሆን እንደሚችል ይገልፃል፡፡ በዚህ ረገድ ጃማይካዊቷ የአጭር ርቀት ሯጭ ኤሌን ቶምሰን ሄራህ ለ33 ዓመት የቆየውን የ100 ሜትር የኦሎምፒክ ክብረ ወሰን መስበሯም ትኩረትን ስቧል፡፡

አምራች ኩባንያው ሞንዶ እንደሚለው ይህ የሚያነጥር መም የሯጮችን ፍጥነት እና በውድድሩ የሚያሳዩትን ብቃት ለማሳደግ ተብሎ የተሰራ ነው፡፡ የላይኛው የመሙ ንጣፍ የጠነከረ ጎማ መሆኑ በመለጠጥ ረገድ ይረዳዋል፡፡ በታችኛው ምንጣፉ ውስጥ ያሉት በአየር የተሞሉ ባዶ ቦታዎችም መሙ የሚረገጥበትን ኃይል በመሰብሰብና ይህንንም ወዲያው መልሶ ወደ አትሌቶቹ እንዲያሻግር አስችሎታል፡፡ ይህ ኃይልን ከሯጮች ሰብስቦ መልሶ ለሯጮች የመስጠት ብቃቱ ታድያ በአጭር ርቀት ሯጮች ዘንድም ተመስክሮለታል፡፡

ሆኖም ከመሙ ባሻገር ለሯጮቹ ፍጥነት ዘመናዊዎቹ ጫማዎችም ምክንያት ተደርገው ሊወሰዱ እንደሚችሉ ይነገራል፡፡ በውስጣቸው ዝርግ ካርበን ያለባቸውና በረጅም ርቀት ሯጮች ላይ ተተግብረው የዓለም ክብረ ወሰኖች እንዲሰባበሩ ባስቻሉት ጫማዎች ላይ ያለው ቴክኖሎጂ ለአጭር ርቀር ሯጮችም እንዲሆን ተደርጎ ወደመሰራት እያመራ ነውና፡፡ (ከአራት ቀናት በፊት በሐምሌ 21 2013 ዓ.ም “ሪከርድ ሰባሪዎቹ ጫማዎች” በሚል ርዕስ ስለ ጫማዎቹ ያቀረብንልዎትን ፅሁፍ በዚህ ሊንክ አማካኝነት ማየት ይችላሉ https://www.facebook.com/TechinEthiopia/posts/4179524768822243 )

ምንጭ፤ Tech Xplore
ለተጨማሪ፤ https://techxplore.com/news/2021-08-tech-tokyo-olympics-fast-track.html
ኢኮኖሚያዊ እድገትን በአይሲቲ ማፋጠን
-----------------------------------------
አይ.ሲ.ቲ በፈጣን ልማት ረገድ ከፍተኛ የሆነ የመወዳደርያ አቅምን መገንባት የሚያስችል ሲሆን፤ በተለይም በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እና በፖለቲካዊ ምህዳር ተጨባጭና ዘላቂ እድገትን ማስመዝገብ የሚያስችል ከመሆኑ በተጨማሪም በዓለም ዓቀፍም ሆነ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ለተፈጠሩት እና ለሚፈጠሩት ችግሮች መፍትሄ ለማስቀመጥ ሁነኛ አስተዋፅዖ አለው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ለፈጠራ፣ ለምርምር፣ ለፖሊሲና ለሌሎች መንገዶች ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡ በዚህ መንገድ አይ.ሲ.ቲ ዓለምን በመቀላቀል የስራ ዕድል፣ የተወዳዳሪነት መንፈስ፣ የገበያ መስፋፋት፣ ምርትና ምርታማነት ማስፈንና ሌሎችም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን ማግኘት ይቻላል፡፡ ዓለም አንድ መንደር እንድትሆን ባደረገው በሉዓላዊነት ዘመን የትም ቦታ ሆኖ ማንኛውንም መረጃ ማግኘትና ማቀበል ተችሏል፡፡
ሀገራት ነባራዊ ሁኔታቸውን እና ስነ-ምህዳራዊ ባህሪውን አጥንተው ተስማሚና ውጤታማ ለመሆን፤ ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት በማድረግ መስራታቸው ዓለም እየሄደችበት ባለው ፍጥነት ተሳታፊ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል፡፡ በተለይም እንደኛ ያሉ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ አንዳንድ የዕድገት መሰላል በመጠቀም እንደ ሌሎች ሀገራት በኢኮኖሚ ከፍታ ላይ ለመሰለፍ እና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እንዲሁም የማህበረሰቡን ገቢ ለማሳደግ ከድህነት አረንቋ ለማውጣት እና እድገትን በዘላቂነት ለማስቀጠል መሰረታዊ ጥቅም እንዳለው ሁሉም የሚስማማበት እውነት ነው፡፡ የግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንደስትሪ መር ለመለወጥና አስተማማኝ ኢኮኖሚ ለመገንባት የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ተገቢ ነው፡፡
የአይ.ሲ.ቲ ምጥቀት በኢንደስትሪው ዕድገት ውስጥም ከፍተኛ ድርሻ አለው፡፡ በተለይም በአሁኑ ሰዓት አድካሚና አሰልቺ የነበሩት በርካታ የኢንደስትሪ ስራዎች በቀላል መንገድ እንዲሰራ እና ፍጥነት እና ጥራት እንዲኖረው በማድረግ አይ.ሲ.ቲ የአንበሳ ድርሻን ተጫውቷል፡፡ ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ይህ ነው የማይባል በርካታ አስቸጋሪ እና አሰልቺ ጊዜን የሚሹ ጉዳዮችን በማቅለል እና ጠቀሜታ ወዳላቸው ነገሮች በመቀየር አሁንም ዓለማችን የበለጠ ተወዳጅ እንድትሆን እያደረጋት ይገኛል፡፡
ምንጭ፡ darden እና tech science
https://www.darden.virginia.edu/sites/default/files/inline-files/Chap%205_Fostering%20the%20Economic%20and%20Social%20Benefits%20of%20ICT
TECHIN seminar
=========
የቴክኢን ሴሚናር መርሃ-ግብራችን ነገ ሐሙስ የሚመለስ ሲሆን በዚህ ሳምንቱ የቴክኢን ሴሚናርም “Creating Awareness on Cyber Security” በሚል ርዕስ በተመራማሪ ገብሬ ኩታኖ እና ሱፋሬል መሃሪ አማካኝነት በተቋም ደረጃ ለሳይበር ደህንነት ሊሰጠው ስለሚያስፈልገው ትኩረት እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ገለፃ እና ውይይት የሚከናወን ይሆናል፡፡
ስፍራ፡ 4 ኪሎ በሚገኘው የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት መሰብሰቢያ አዳራሽ
ቀን፡ ነገ ሐሙስ ሃምሌ 28 ፤ 2013 ዓ.ም
ሰዓት፡ ከጠዋቱ 3፡30 ጀምሮ
TECHIN seminar will be back this week, @TECHINhall. For this session the two researchers Gebre Kutano and Surafel Mehari will discuss about Cyber Security issues.
Starting time: 9:30 AM
#TECHIN
#weeklyseminar
የሱፐር ኮምፒዩቲንግ ቴክኖሎጂ
==================
ሱፐር ኮምፒዩቲንግ ማለት ብዙ ኮምፒዩተሮችን በማዋሀድ ከመደበኛ ኮምፒዩተሮች ከምናገኘው ሀይል እጅጉን የበለጠ ሀይል በማግኘት ትልልቅ የሆኑ የሳይንስ፣ የምንህድንስና እና የቢዝነስ ችግሮችን መፍታት መቻል ነው። ሱፐር ኮምፒዩቲንግ ትልልቅ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት እንዲሁም የምርምር ስራዎችን ለመስራት ይጠቅማል። በመደበኛ ኮምፒዩተር ረጅም ሰአታት የሚወስዱ ሲሙሌሽኖች በሱፐር ኮምፒዩተር በጥቂት ሰከንዶች ውስጥ መሰራት ይችላሉ። ለአብነት በቅርቡ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ በሰሚት ሱፐር ኮምፒውተር የተከናወነው የምርምር ውጤት ብንመለከት የቴክኖሎጂው አስፈላጊነት ምን ያክል ወሳኝ እንደሆነ ሊያሳየን ይችላል፡፡

ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ስራ ላይ የዋለው ይህ ሱፐር ኮምፒውተሩ በተገጠሙለት የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ግብዓቶች አማካኝነት በሺዎች የሚቆጠሩ ማስመሰያዎችን (simulations) በማንቀሳቀስ ቫይረሱ የሚያርፍባቸውን ተጠቂ ህዋሳት በመመርመር የትኞቹ የመድኃኒት ውህዶች (drug compounds) ቫይረሱን ማቆም እንደሚችሉ ትልቅ ፍንጭ የሰጠ ከመሆኑም ባለፈ፤ ምናልባት በመደበኛው የኮምፒውተር ስሌት ብዙ ወራቶችን ሊወሰድ የነበረውን የተሳካ የምርምር ውጤት በቀናት ውስጥ እንዲካሄድ ያስቻለ ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአለማችን ላይ ያሉ ሀያላን አገራት ጃፓን፣ አሜሪካን እና ቻይናን ጨምሮ ከሚፎካከሩባቸው ነገሮች አንዱ ሱፐር ኮምፒዩቲንግ ነው። አሁን ላይ ከፍተኛ አቅም ያለው ሱፐር ኮምፒዩተር የጃፓኑ ፉጋኩ (Fugaku) ሲሆን የኮምፒውተር ሃይሉም 415.5 ፔታፍሎፕስ ነው። በሁለተኛ ደረጃ ላይ በ148.8 ፔታፍሎፕስ የኮምፒውተር ሃይል የአሜሪካው ሰሚት ሲከተል የቻይናው ሰንዌይ 93 ፔታፍሎፕስ በአራተኝነት እና የአሜሪካው ስዬራ በ94.6 ፔታፍሎፕስ በሶስተኛነት ይከተላል። የአንድ ኮምፒዩተር ሀይል የሚለካው ፍሎፕስ በሚባል መለኪያ ሲሆን አንድ ኮምፒዩተር ሱፐር ኮምፒዩተር ለመባል ሀይሉ ከአንድ ቴራፍሎፕስ በላይ መሆን አለበት። ይህም ማለት ከአንድ ትሪሊየን ፍሎፕስ በላይ መሆን አለበት ማለት ነው።

ከዚህ አንፃር በአለማችን እስከቅርብ ጊዜ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው "Summit" ሱፐር ኮምፒውተር በ2019 በአሜሪካ የኢነርጂ ዲፓርትመንት እና በIBM አማካኘነት የተሰራ የዓለማችን ፈጣኑ ሱፐር ኮምፒውተር ሲሆን፤ በሰኮንድ 200 ኳድሪሊዮን (15 ዜሮዎችን የሚስከትል) ስሌቶችን ኮምፒውት በማድረግ ውስብስብ ጥናቸን የሚያቀላጥፍ ነው፡፡ ኮምፒውተሩ 200 petaflops አጠቃላይ አቅም ያለው በመሆኑ ፈጣን ከሚባሉት ላፕቶፖች አንድ ሚሊዮን እጠፍ ስራውን ማከናወን ይችላል፡፡
ምንጭ፡AD. Information Technology እና tech science
https://www.techrepublic.com/article/top-5-supercomputers/
ሁለት ኢትዮጵያዊያን በአፍሪካ ምርጥ 10 ወጣት የህዋ ተመራማሪዎች ዝርዝር ውስጥ ተካተቱ
ሁለት ኢትዮጵያዊያን በአፍሪካ ምርጥ 10 ወጣት የህዋ ተመራማሪዎች ዝርዝር ውስጥ ተካተቱ
===================
ሁለት ኢትዮጵያውያን የህዋ ምርምር ባለሙያዎች በአፍሪካ ምርጥ 10 እድሜያቸው ከ30 በታች የሆኑ የህዋ ምርምር ባለሙያዎች ዝርዝር ውስጥ ተካተቱ፡፡ ስፔስ ኢን አፍሪካ ባወጣው በዚህ ዝርዝር ላይ የተካተቱት ሁለት ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ትንሳኤ አለማየሁ እና ቤተልሔም ግርማ ናቸው፡፡
የ29 ዓመቷ ቤተልሔም በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ውስጥ በረዳት ተመራማሪነት እያገለገለች የምትገኝ ሲሆን በተለያዩ የምህንድስና ፕሮጀክቶች ላይ ተሳታፊ ስለመሆኗም ተነግሯል፡፡ የከፍተኛ ትምህርቷን በቻይናው የናንጂንግ ኤሮኖቲክስ እና አስትሮኖቲክስ ዩኒቨርሲቲ ተከታትላ ባለፈው ዓመት የመጀመሪያ ዲግሪዋን ያገኘችው ቤተልሄም ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ ወደ ሀገሯ ኢትዮጵያ በመመለስ በኢንስቲትዩቱ ማገልገል ጀምራለች፡፡ ኢንስቲትዩቱ ውስጥ ባለው የስፔስ ኢንጂነሪንግ ጥናት እና ምርምር ዳይሬክቶሬት ውስጥም በሰው አልባ በራሪዎች (UAV) ንድፍ እና ማበልፀግ ላይ እየሰራች ትገኛለች፡፡ ከዚህ ስራዋ ባሻገርም በኢትዮ ስፔስ ኪድስ ክለብ ውስጥ አስተባባሪ ሆና እያገለገለች ነው፡፡
በ23ኛ ዓመት ዕድሜው ላይ የሚገኘው ትንሳኤ በበኩሉ የመጨረሻ ዓመት የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ተማሪና በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ነው፡፡ በተጨማሪም ከተባበሩት መንግስታት ጋር በተሳሰረውና ወጣቶችን የማስተሳሰር ስራ በሚሰራው የስፔስ ትውልድ አማካሪ ካውንስል (SGAC) ውስጥ የቀጠናዊ እና ሀገራዊ ሁነቶች ዝግጅት ቡድን አባልና የኢትዮጵያ ተቀዳሚ ሰውም ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ እዚሁ መዲናችን አዲስ አበባ ውስጥ በተካሄደው 3ኛው የአፍሪካ ስፔስ ትውልድ ወርክሾፕ ላይ የኢትዮጵያ አዘጋጅ ቡድንን የመምራት ስራን ተወጥቷል፡፡
ከታዳጊነት ዕድሜው አንስቶ በህዋ ምርምር እና ምህንድስና ላይ ፍላጎት ሲያሳይ መቆየቱ የተነገረለት ትንሳኤ ከአውሮፓውኑ 2012 እና 2013 አንስቶ ነው ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ እንዲሁም ከስፔስ ትውልድ አማካሪ ካውንስል ጋር መስራት የጀመረው፡፡ ላለፉት ሦስት ዓመታትም የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት-የመቀሌ ካውንስ (EiT-M) አባል ሆኖ ቆይቷል፡፡ በተጨማሪም በበርካታ ዓለም አቀፍ ስልጠናና ትምህርቶች ላይ ተሳታፊ ለመሆን በቅቷል፡፡
ትንሳኤ በአሁኑ ሰዓት ከስፔስ ቴክኖሎጂ ፎር ኧርዝ አፕሊኬሽንስ (STEA) ጋር በመቀናጀት ሳተላይት ላይ ተንተርሶ የእርሻ ግብርና እና ጤና ቁጥጥር አገልግሎቶችን በሚሰጥ ስርዓት ላይ እየሰራ ይገኛል፡፡
በዝርዝሩ ውስጥ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ከአልጄሪያ፣ ናይጄሪያ፣ ግብፅ ፣ ሞሪሺየስ፣ ዚምቧብዌ፣ አንጎላ እና ሴራሊዮን የተውጣጡ ወጣት ባለሙያዎች ሲካተቱ እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ወጣቶችን በማስመረጥ ግብፅ እና ኢትዮጵያ ብቸኛዎቹ ሀገራት ሆነዋል፡፡
ምንጭ፤ Africa News
ለተጨማሪ፤ https://africanews.space/class-of-2021-african-space-industry-top-10-under-30-award/?fbclid=IwAR25XjctS5ehP9CSFFVYEGh07JnSZ_QIq83z6Gko9Pdatrup2oSndnfkqQY
የሳይበር ደህንነት ማስገንዘቢያ መርሃ-ግብር ታከሄደ
=========================
የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት በየሳምንቱ ሃሙስ የሚያዘጋጀው የቴክኢን ሴሚናር በዛሬው ዕለትም የሳይበር ደህንነት ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን አድርጎ ተካሂዷል፡፡ በዛሬው የመወያያ መድረክ በኢንስቲትዩቱ ውስጥ በተመራማሪነት እያገለጉ ያሉት አቶ ገብሬ ኩታኖ ስለ ሳይበር ምህዳርና ደህንነት፣ ያሳይበር ስጋት በአለም አቀፍና በሃገር ውስጥ ምን መልክ እንዳለው፣ የሳይበር ጥቃቶች በምን መልኩ እየተፈጸሙ እንደሚገኝ እና ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ተቋም ድረስ የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል ምን መደረግ አንደሚኖርበት በሚሉት ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡
የሳይበር ደህንነት አውታረ-መረቦችን፣ መሣሪያዎችን፣ የሶፍትዌር ፕሮግራሞችን እና መረጃዎችን ከሳይበር ጥቃቶች ለመጠበቅ አስፈላጊ የሆኑ ቴክኖሎጂ እና ሂደቶችን በመያዝ የሚሰራ መሆኑን ያስረዱት አቶ ገብሬ በተቋም ደረጃ ለሳይበር ጥቃት ሊያጋልጡን የሚችሉ ማንኛውንም ክፍተቶችን በመድፈን እና ሊወሰዱ የሚገቡ አስፈላጊ ጥንቃቄዎችን በማድረግ ከማንኛውም የሳይበር ጥቃት ራስንና ተቋምን መከላከል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
አቶ ገብሬ አክለውም የሳይበር ጥቃት ሆን ተብሎ ያልተፈቀዱ የኮምፒውተር ስርዓቶች፣ መሰረተ-ልማቶች እና ኔትዎርኮች ላይ አጥፊ ሶፍትዌሮችን በመጠቀም በህገወጥ መንገድ ዳታዎችን የመበዝበዝ እና አገልግሎት የማስተጓጎል መጥፎ ተግባር በመሆኑ ማንኛውም በሳይበር ምህዳር ተጠቃሚ የሆኑ ግለሰቦች ድርጅታችን አነስተኛ ስለሆነ የሳይበር ጥቃት ሊደርስበት አይችልም የሚል የተሰሳሳተ ሃሳብ ከማራመድ አንስቶ ሌሎች አጋላጭ አመለካከቶችን በመቅረፍ ሊደርስ የሚችልን ጉዳት መቀነስ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በብዙ የመንግስት ተቋማት ተዳጋግሞ እየታ ያለው እና እየጨመረ የመጣውን የሳይበር ጥቃት ለመከላከል በሃገር አቅፍ ደረጃ የተለያዩ የሳይበር ደህንነት ማስገንዘቢያ መርሃ-ግብሮች ሲካሄዱ ቆይተዋል፡፡ የስራ ዘርፋቸው ከበይነ-መረብ ግንኙነት ጋር ብዙም ያልራቀ የመንግስት ተቋማት ለማንኛውም የሳይበር ጥቃት ተጋላጭ የመሆን እድል ስለሚኖራቸው መሰል መርሃግብሮች ተጠናክረው መቀጠላቸው እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ በተለይም ሀገራችን የዲጂታል ምጣኔ ሃብት ግንባታ ላይ ሰፊ እቅድ ይዛ በምትንቀሳቀስበት በአሁን ወቅት የትኛውም ከዲጂታል ትግበራዎች በዋናነት ከመረጃና የመረጃ መሰረተ ልማት ጋር የሚያያዙ በመሆናቸው ለየትኛውም የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነታቸው ሰፊ ነው።
ከዚህ አንጻር ሁለም የመንግስት ተቋማት እና ባለድርሻ አካለት እየጨመረ የመጣውን የዲጂታል የቴክኖሎጂ አጠቃቀም የሚመጥን የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ ይዘው እንዲገኙ የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ብዙ የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ ፕሮግራሞችን በመቅረፅ የተለያዩ ስልጠናዎችን እንደሚሰጥ በውይይቱ ላይ የተሳተፉት አቶ ሱራፌል ማሃሪ ተናግረዋል፡፡
ኢ ኢንቫይሮመንት እና የተፈጥሮ መጎዳት
======================
አየር ላይ የተለያዩ በካይ ወይም መጥፎ ጋዞች ሲገኙና እነሱን ተከትሎ ዝናብ ሰወርድ የሚወርደውን ዝናብ አሲዳማ ዝናብ እንለዋለን። ልክ እንደሌሎቹ ችግሮች አሲዳማ ዝናብም ከኢንዱስትሪ በሚወጡ ጭሶችና አንዳንዴ ከሚከሰት እሳተገሞራ ውስጥ በሚወጡ ጋዞች ይከሰታል። አሲዳማ ዝናብ ለሰዎች ጤንነት፣ ለዱር ሕይወትና በውሃ ውስጥ ለሚኖሩ ፍጥረቶች አደገኛ ስጋት አለው። ከላይ የተጠቀሱትን በዓለም ላይ በመከሰት ያሉ ትልልቅ ችግሮችን ስንመለከት ከፍተኛ አደጋ ውስጥ እንዳለን መመልከት ይቻላል።
የሰው ልጅ በዚህ ጥፋቱ ከቀጠለ ወደፊቱ ለሚመጣው ቀጣይ ትውልድ ጥሎ የሚያልፈው ነገር ከባድ ሊሆን ይችላል። የዓለም ህዝብ ቀን ከቀን ያለውን የአኗኗር ዘይቤውን መቀየርና የዓለም መንግስታቶች ችግሮቹ ላይ በትኩረትና በሃቅ መረባረብ ካልቻሉ የምድራችን መጎዳት ይበልጥ እየባሰ መምጣቱ አይቀርም። ይህ ሲባል ታዲያ በዓለም ላይ እየተፈጠሩ ያሉትን የአካባቢ ችግሮች በአንድ ቀን ማቆም እንችላለን ማለት ሳይሆን በተቻለን አቅምና ባለን እውቀት የምንችለውን ያህል ማድረግ እንደሚጠበቅብን ለማስገንዘብ ነው። ይህን ደግሞ የምናከናውነው በተለይ በአሁኑ ወቅት ቴክኖሎጂ ባደገበት ጊዜ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን በመጠቀም አካባቢያችንን ከተለያዩ ችግሮች መጠበቅና ሌሎችንም ማስተማር ስንችል ብቻ ነው። እዚህ ላይ የኢ ኢንቫይሮመንት (E-Environment) ሃሳብ በብዙዎች የሚነሳ ጉዳይ ነው፡፡
ኢ ኢንቫይሮመንት የአካባቢ ጥበቃንና የተፈጥሮ ሀብትን በተገቢ ሁኔታ አዘውትሮ ለመጠቀም የኢንፎርሜሽን ኮምኒኬሽን ቴክኖሎጂን የሚጠቀም ስርዓት ሲሆን ይህም ስርዓት የአካባቢን ሁኔታ፣ የተፈጥሮ ሀብቶችን፣ የአካባቢ ብክለት የሚያስከትሉ በካይ አካላትን እና ተቆጣጣሪ ስርዓቶችን ለመለየትና ለማበልፀግ፣ ሰው ሰራሽ ጥፋቶችን ለመቆጣጠርና ወደ ፊት ሊከሰቱ የሚችሉ ሁኔታዎችን ለመተንበይ የሚያስችል ነው። አገልግሎታቸውን በጨረሱና በሚጣሉ የኮምፒውተሮችና ሌሎች የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ተረፈ ምርቶች አማካኝነት የሚከሰተው የካርቦን ዳይኦክሳይድ ልቀት እንደ ሌሎች ከፋብሪካ እንደሚለቀቁ አየር በካይ ጋዞች ባይሆንም ለዓለም ሙቀት መጨመር እንዲሁም ብክለት ቀላል የማይባል አስተዋፅዖ አለው። ከዚህ አንጻር ኢ ኢንቫይሮመንት በሰው ልጆች አማካኝነት ወይም በሌሎች ምክንያቶች ሊከሰቱ ለሚችሉ ችግሮች ከመፈጠራቸው በፊት ለመከላከልና ከተፈጠሩም በኋላ ለመቆጣጠር ምቹ የሆኑ ሁኔታዎችን የሚፈጥር ቴክኖሎጂ ሲሆን ከዚሁ ጋር የሚያያዙት ሌሎች የቴክኖሎጂ ትግበራዎችም አካባቢ ላይ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመከላከል ያግዛሉ።
https://www.sciencedirect.com/.../S1877042814060327/