TechIn2
1.16K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
ከ65 ዓመታት በኋላ መንቀሳቀስ የቻለው ግዙፉ ባቡር
=====================
በእንፋሎት ይሰራ የነበረ የሎኮሞቲቭ ተጎታች ባቡር ያለስራ ቆሞ ከነበረበት ከ65 ዓመታት በኋላ ከሃያ ዓመት በላይ በተደረገለት መሉ እድሳት ከሰሞኑ መንቀሳቀስ ጀምሯል፡፡ በ1999 በታሪካዊ የባቡር ስራዎች ላይ የሚንቀሳቀስ የበጎ ፍቃድ ማህበር እንደፕሮጀክት ይዞ ሲሰራው የነበረው ይህ የባቡሩ እድሳት በአሜሪካ የኒው ሜክሲኮ ግዛት የሚገኝ ግዙፍ ባቡር ነበር፡፡ በእድሳት ስራው የተሳተፉ ባለሙያዎች ባበሩ ስራ አቁሞ ከነበረበት የኒው ሜክሲኮ ግዛት አልቡኪርካይ ፓርክ ላይ በ1999 ባበሩን በግዥ ከተረከቡ በኋላ ለድፍን 20 ዓመታት እድሳት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

እንደአውሮፓውያኑ ከ1956 በኋላ ምንም አይነት ጉዞ ማድረግ ያልቻለው ይህ ግዙፍ ባቡር ለ20 ዓመታት ሲደረግለት ከቆየው የእድሳትና የጥገና ስራ በኋላ በሃምሌ 24 2021 ከ65 ዓመታት በኋላ የመጀመሪያውን ጉዞ ማድረግ ችሏል፡፡ Santa Fe 2926 የሚል ስያሜ ያለው ይህ ግዙፍ ባቡር ከ250 ቶን በላይ የሚመዝን ሲሆን ለመንገደኞች ከተሰሩ ግዙፍ ባቡሮች መካከል በመጀመሪያዎቹ ደረጃ የሚገኝ ነው፡፡

ይህ የባቡር ስሪት እንደአብዛኞቹ በእንፋሎት የሚሰሩ ባቡሮች በድንጋይ ከሰል የሚንቀሳቀስ ሳይሆን በነዳጅ የሚሰራ መሆኑ ለየት የሚደርገው ነው፡፡ እንደአውሮፓውያኑ በ1944 ባልድዊን ሎኮሞቲቭ በተባለ ኩባንያ ለመንገደኞች መጓጓዣና ለእቃ ጭነት እንዲውል ተደርጎ የተሰራው ይህ ግዙፍ ባቡር አሁን ላይ በኒው ሜክሲኮ ግዛት እንዲንቀሳቀስ እና እንዲጓዝ የተፈቀደለት ርዝመት ከ300 ጫማ የማይበልጥ ነው፡፡

ባለሙያዎች እንደሚገለፁት እንዲህ ያሉ የባቡር የትራንስፖርት አማራጮች ከሌሎች የአየርና የመርከብ መጓጓዣዎች አንፃር ዝቅተኛ የአየር ብክለት ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ይበልጥ ተመራጭ ያደርገዋል፡፡ Santa Fe 2926 ባቡር በ1950ዎቹ ሲሰጥ የነበረውን አገልግሎት ካቆመና ከ65 ዓመታት ቆይታ በኋላ ታሪካዊውን ጉዞ ከተማዋ ውስጥ በሚገኝ የባቡር ሃዲዲ መስጠት መጀመሩን የሲኤንኢቲ ዘገባ ያሳያል፡፡
https://www.cnet.com/.../see-a-giant-steam-locomotive.../
የሰው ልጅ ስልጣኔ ወደ ፍፃሜው እያመራ ነው ሲል አዲስ ጥናት አመላከተ
የሰው ልጅ ስልጣኔ ወደ ፍፃሜው እያመራ ነው ሲል አዲስ ጥናት አመላከተ
=====================
በአውሮፓውያኑ 1972 የማሳቹሴት ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ ተመራማሪዎች ያጠኑት ጥናት የያዝነው ኢንዱስትሪያዊ ስልጣኔ በ21ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ እንደሚቋጭ መላምቱን አስቀምጦ ነበር፡፡ ጥናቱ በጊዜው ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠመው ቢሆንም አሁን ላይ የወጣ አዲስ ጥናት ግን የቀድሞው ጥናት ትንበያ በአሳሳቢ ሁኔታ እውነት እየሆነ መምጣቱን አመላክቷል፡፡

በያል ጆርናል ኦፍ ኢንዱስትሪያል ኢኮሎጂ ላይ የወጣው አዲሱ ጥናት የ1972ቱን ጥናት ተመልክቶና ከእርሱ በኋላ ነገሮች በምን መልኩ እየሄዱ እንደሆነ በምጣኔ ሐብት እድገት እና ሐብት አጠቃቀም ላይ ያተኮሩ ተጨባጭ መረጃዎችን በመመርመር ነው የተከናወነው፡፡ በዚህም የሰው ልጅ ስልጣኔ እውነትም ወደ ፍፃሜው እየገሰገሰ መሆኑንና ምናልባትም በጣም ቀረበ ከተባለ ይህ ለሺህ ዓመታት የዘለቀ የስልጣኔ ጉዞ ከ20 ዓመታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በአውሮፓውያኑ 2040 ሊገታ ይችላል ብሏል፡፡ ሆኖም ይህ የሚሆነው የምድርን ሀብት አሁን በምናደርገው ልክ እየበዘበዝን የምንቀጥል ከሆነ ብቻ መሆኑን አስቀምጧል፡፡

ሆኖም የሰው ልጅ ስልጣኔ ያበቃል ማለት የሰው ልጅ ይጠፋል ማለት እንዳልሆነ ተመራማሪዎቹ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ምጣኔ ሐብታዊ እና ኢንዱስትሪያዊ እድገት ቆሞ የቁልቁለት ጉዞ ጅማሬ ይሆናል ብሎም የህይወት ዘይቤያችን በከባዱ ይጎዳል እንደማለት ነው፡፡ በዚህ የቁልቁለት ጉዞ ውስጥ የምግብ ምርት እና የሰው ልጆች ኑሮ ደረጃ ተጎጂዎች ይሆናሉም ተብሏል፡፡

በተቃራኒው ግን እስካሁን ስንከተል የቆየነውን አካሄድ በማስተካከል መጓዝ ከጀመርን የሰው ልጅ ስልጣኔ አሁንም ተስፋ ያለው መሆኑ በአዲሱ በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡
ምንጭ፤ Futurism
ለተጨማሪ፤ https://futurism.com/the-byte/mit-prediction-civilization-collapse-on-track
ከፓርክ አምልጣ ወደ ከተማ የገባችው አንበሳ
ከፓርክ አምልጣ ወደ ከተማ የገባችው አንበሳ
============
የኬኒያ ዱር ጥበቃ ኃላፊዎች በትናንትናው እለት በመዲናዋ ናይሮቢ ደቡባዊ ክፍል በሚገኙ የመኖርያ መንደሮች ውስጥ ስትንቀሳቀስ የነበረችውን አንበሳ መያዛቸውን አስታውቀዋል፡፡ የኬኒያ ዱር ህይወት አገልግሎት (KWS) እንዳለው አንበሳዋን በጠዋቱ ሰፈራቸው ውስጥ ከተመለከቷት የናይሮቢ ነዋሪዎች በደረሰ ጥቆማ መሰረት የዱር ጥበቃ ኃይሎች እና የእንስሳት ሀኪሞች ወደቦታው ተልከው ነበር፡፡

ኦንጋታ ሮንጋይ ተብሎ በሚጠራው የናይሮቢ ሰፈር በአርማታ በተገነባ ግድግዳ እና ቆርቆሮ መሃል ታጥራ የተገኘችው አንበሳዋ ዳግም ወደ ፓርኩ ከመለቀቋ በፊት ወደ እንስሳት ጤና ማዕከል መወሰዷን ተቋሙ አስታውቋል፡፡ በተቋሙ የተለቀቀው የቪዲዮ ምስልም የዱር ጥበቃዎቹ በማደንዘዣ መድኃኒት እንድትደነዝዝ የተደረገችውን አንበሳ በሸራ ጠቅልለው ወደ መኪና ሲከቷትና ከመኖርያ መንደሩ ሲወስዷት አሳይቷል፡፡

በአፍሪካ ብቸኛው በዋና ከተማ ውስጥ ያለ የአደን ፓርክ በሆነው የናይሮቢ ብሄራዊ ፓርክ ዙርያ ለረጅም ጊዜ ሰዎች ሲሰፍሩበት ቆይቷል፡፡ ዙያውን በከተማው እየተከበበ መምጣቱን ተከትሎ ፓርኩ በሦስት አቅጣጫዎች ታጥሯል፡፡ አጥር ባልታጠረበት ደቡባዊው ክፍሉ ግን ፆታዊ ግንኙነታቸውን መፈፀም ለሚፈልጉ አንበሶች ምቹ ቦታ ሆኗል፡፡ ብዙውን ጊዜም እንስሳቱ በዚህ በኩለ በማለፍ ወደተለያዩ ቦታዎች ሲያቀኑ ተስተውሏል፡፡

በአሁኑ ጊዜ 2ሺህ ያህል አንበሶች በኬኒያ ይገኛሉ፡፡ እንደ አካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች ከሆነ ፓርኩን ሰንጥቆ የሚያልፈው የባቡር መስመር እና የመኪና መንገድ በእንስሳቱ ባህርይ ላይ ተፅዕኖውን ማሳደር ጀምሯል፡፡ በዚህም ሳብያ አናብስቱ ፀጥ ያለ የአደን ቦታ ፍለጋ ከፓርኩ ለማምለጥ እንደሚሞክሩ ባለሙያዎቹ ይገልፃሉ፡፡

ምንጭ፤ Reuters
ለተጨማሪ፤ https://www.reuters.com/world/africa/kenyan-wildlife-authorities-capture-lion-residential-area-outside-capital-2021-07-28/?taid=6101b3c1cb403700019041af&utm_campaign=trueanthem&utm_medium=trueanthem&utm_source=twitter
የኢትዮጵያን የቡና ዘርፍ የሚያሻሽለው ታዳጊ ስታርታፕ
===================
እ.ኤ.አ. በ 2019 ናሆም ሚካኤል እና አሌክሳንደር ህዝቂያስ በተባሉ ወጣቶች የተመሰረተው ዘ ጎት ካፌ (The Goat Café) የኢትዮጵያን የቡና ዘርፍ በአዳዲስ አሰራሮች በመታገዝ ለማሻሻል እና ለማማነቃቃት እየሰራ የሚገኝ የተቀናጀ የቡና ኩባንያ ነው፡፡ ድርጅቱ ምስረታውን ካደረገበት አመት አንስቶ በኢትዮጵያ የቡና ኢንዱስትሪ በጉልህ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

ዘ ጎት ካፌ አርሶአደሮች ከቡና አቅርቦት የሚያገኙትን የክፍያ መጠን ተጨማሪ እሴት በማከል ከማሳደግ አንስቶ በቡና አመራረትና ቅንብር ሂደት የሚታዩ የጥራት ደረጃዎችን ለመማሻሻል እና ለተጠቃሚው ማህበረሰብም በልዩ የአቀራረብ መንገድ ቡናን በማቅረብ ዘርፉን ለማሻሻል ያለመ ነው፡፡ ኩባንያው በተለይም ለውጭ የቡና ተጠቃሚዎች ፈጠራ የታከለበት፣ ዘላቂነት ያለው እና እሴት የተጨመረበት የቡና አቅርቦትን በማረጋገጥ ዘመናዊ የሽያጭ ስርዓትን እንደሚዘረጋ ተነግሯል፡፡

ኩባንያው በተያዘው አመት በመዲናችን አዲስ አባባ የተለያዩ ቅርንጫፎችን በመክፈት እየተንቀሳቀሰ ሲሆን በዚህም መደበኛውን የአረቢካ ቡና ውጤቶች ከሌሎች ተያያዥ መጠጦች ጋር በማጣመር ለተጠቃሚዎች በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡ ድርጅቱን በመመስረት ሂደት ትልቅ ሚና የነበረው ወጣት ናሆሞ እንደሚናገረው ዘ ጎት ካፌ ቀላል ያሉ እና ዘመናዊ የሽያጭ ስርዓቶችን በመዘርጋት ዘርፉን ለማሳደግ እየሰራ ቢሆንም በቅርብ አመታት ውስጥ ከትልልቅ ድርጅቶች ጋር ህብረት በመፍጠር እሴት የታከለባቸው የቡና ምርቶችን በአለም አቀፍ ደረጃ ባማቅረብ አጠቃላይ የግብይት ሰንሰለቱን ለማዘመን እንደሚሰራ ገልጿል፡፡

ኩባንያው አሁን በከፈታቸው ቅርንጫፎች እና ትእዛዝ የመቀበያ አንላይን ፕላትፎርም በመታገዝ በየወሩ ከ500 እስከ 1000 ተጠቃሚዎች በመስተናገድ ላይ ሲሆን በቀጣይ ጊዜያትም ዘመናዊ የቡና ሮስተሪ ፋሲሊቲ በመገንባት እታች ካለው አርሶአደር ጋር ግንኙነት ለመፍጠር እና የምርምር ማካሄጃ መዕከልን ለማቋቀም በመስራት ላይ ነው፡፡
https://shega.co/post/this-coffee-startup-wants-to-change-how-ethiopian-coffee-is-sourced-processed-consumed/
የኦሎምፒክ ሜዳልያዎች ከምን ይሰራሉ?
የኦሎምፒክ ሜዳልያዎች ከምን ይሰራሉ?
==============
ከሁሉ አስቀድመን ከሰዓታት በፊት በወንዶች 10 ሺህ ሜትር ሩጫ ላይ በሰለሞን ባረጋ አማካኝነት ኢትዮጵያ የቶኪዮ ኦሎምፒክ የመጀመሪያ ወርቅ ሜዳልያዋን ስላገኘች እንኳን ደስ አለን!!! ይህን ብለን ስናበቃ ሰለሞን ባረጋም ሆነ ሌሎች በቀጣይ ውድድሩ ላይ ድል የሚጎናፀፉ አትሌቶቻችን ስለሚሸለሙት ሜዳልያ ትንሽ ብናወጋችሁ ብለን አሰብን፡፡

እንደምናውቀው በየ ኦሎምፒኩ አትሌቶች ከአንድ እከከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው ሲያጠናቅቁ የወርቅ ብር እና ነሀስ ሜዳልያ ይበረከትላቸዋል፡፡ እዚህ ላይ ግን እንደ ስሙ በትክክለኛ ንጥረ ነገሩ የሚሰራው ሜዳልያ የብር ብቻ መሆኑን ያውቁ ይሆን? በዚህ ፅሁፍ ቀሪዎቹ ሁለት ሜዳልያዎች ከምን እንደሚሰሩ እንቃኛለን፡፡

ወርቅ

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው የወርቅ ሜዳልያዎች ከንፁህ ወርቅ አይሰሩም፤ ይልቁንም ከንፁህ ብር ተሰርተው እላያቸው በስድስት ግራም ወርቅ የተለበጡ ሜዳልያዎች ናቸው፡፡

ወርቅ እና ብር ሁለቱም የተረጋጉ የሚባሉ ንጥረ ነገሮች ናቸው፡፡ ወርቅ ደግሞ ይበልጥ የተረጋጋ ነው፡፡ አንድ አትሌት የተሸለመውን የወርቅ ሜዳልያ አቅልጠን ናይትሪክ አሲድ ውስጥ ብንከተው ብሩ ወደ ሲልቨር ናይትሬትነት የሚለወጥ ሲሆን ወርቁ ግን ተረጋግቶ ይቀመጣል፡፡ በዚህም ሁለቱን ንጥረ ነገሮች ለያይተን ማውጣት እንችላለን፡፡

በዋጋ ረገድ ከተመለከትነውም አንድ የወርቅ ሜዳልያ 556 ግራም ይመዝናል፡፡ በዓለም አቀፍ ገበያው ላይ የአንድ ግራም ወርቅ ዋጋ 80 ዶላር ሲሆን ብር ደግሞ 1 ዶላር ነው፡፡ በዚህም ለወርቁ 480 ለብሩ ደግሞ 550 በድምሩ የአንዱ ወርቅ ሜዳልያ ዋጋ ከ1 ሺህ ዶላር በላይ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህ ዋጋ እንደተጠበቀ ሆኖ አንዳንድ አትሌቶች ያገኙትን የወርቅ ሜዳልያ በሚሊዮን ዶላሮች ጭምር ሲሸጡት ተስተውለዋል፤ ሜዳልያው በኦሎምፒክ አሸናፊነት የተገኘ ነውና በውድ ቢሸጥ አይገርምም፡፡

ብር

የብር ሜዳልያ ከሦስቱም ሜዳልያዎች ብቸኛው ለስሙ ያደረ ሜዳልያ ነው፡፡ 550 ግራም ከሚመዝን ብር የሚሰራው ሜዳልያው ምናልባትም አንድ አትሌት ከውድድሩ ክብር ይልቅ አቅልጦ ለሌላ አገልግሎት ማዋሉ ከበለጠበት እንደ ሌሎቹ ሜዳልያዎች ከሌላ ንጥረ ነገር ጋር ስላልተደባለቀ በ962 ዲ.ሴ በማሞቅ ብቻ ያለ ተጨማሪ ማጣራት ለፈለገው አገልግሎት ሊያውለው ይችላል፡፡

ነሀስ

ነሀስ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለው ቢሆንም በራሱ ግነ ንፁህ ንጥረ ነገር አይደለም፡፡ ነሀስ (Bronze) የመዳብ እና ቲን ድብልቅ ነው፡፡ ሆኖም በነሀሰ ሜዳልያዎች ላይ የሚውለው ነሀስ ግን ይህ ሳይሆን በእንግሊዝኛ አጠራሩ ብራስ (brass) ተብሎ የሚጠራው የመዳብ እና ዚንክ ድብልቅ ነው፡፡ ሜዳልያዎቹ ቀይ ብራስ ተብለው ሲጠሩ 95 በመቶ ኮፐር 5 በመቶ ደግሞ ዚንክ ናቸው፡፡ ይህ ግን በበተለምዶው ኢንዱስትሪዎች ላይ ቀይ ብራስ ተብሎ ከሚጠራውና 85 በመቶ ኮፐርን ከያዘው አንፃር በተሻለ ጥራት ያለው ነው፡፡
ምንም እንኳን ከሁለቱ ሜዳልያዎች አንፃር ባላቸው የ450 ግራም ክብደት ቀላሎቹ ቢሆኑም ከጥንካሬ አንፃር ግን በቀዳሚነት ይቀመጣሉ፡፡

ወደ ቶኪዮ ኦሎምፒክ ስንመለስ በውድድሩ ላይ ለአሸናፊዎቹ የሚሰጡት ሜዳልያዎች ሙሉ በሙሉ ዳግም ጥቅም ላይ የዋሉ ቁሶች ናቸው፡፡ ይህም ሲባል ጃፓናውያን ከአውሮፓውያኑ 2017 እስከ 2019 ድረስ የተለያዩ አሮጌ የኤሌክትሮኒክስ መሳርያዎቻቸውን የለገሱ ሲሆን ከነዚህ የኤሌክትሮኒክስ መሳርያዎች ውስጥም ለሜዳልያዎቹ ማሰርያ የሚሆኑ ውድ ቁሶች ተለይተዋል፡፡ በአጠቃላይ ከተለገሱት አንድ ሚሊዮን ቶን ከሚመዝኑ ኤሌክትሮኒክሶች ውስጥ 32 ኪ.ግ ወርቅ፣ 3500 ኪ.ግ ብር እና ለነሀስ ሜዳልያዎቹ የዋሉ 2200 ኪ.ግ ኮፐርና ዚንኮችን ማግኘት ተችሏል፡፡

በድጋሚ እንኳን ደስ አለን!!!

ምንጭ፤ cosmos
ለተጨማሪ፤ https://cosmosmagazine.com/science/chemistry/olympic-medal-composition/?utm_content=buffer1c989&utm_medium=social&utm_source=twitter.com&utm_campaign=buffer
አምስተኛዉ ትዉልድ የሞባይል ኔትዎርክ 5G
-----------------------------
የ 5G ቴክኖሎጂ የአምስተኛው ትውልድ የሞባይል ቴክኖሎጂ ሲሆን የዲጂታል ዓለሙ የሚፈልገውን ፈጣን ግንኙነት ለመፍጠር ትልቅ እርምጃ ያራመደ ቴክኖሎጂ ተደርጎም ይወሰዳል። የ 5G ቴክኖሎጂ የመረጃ መለዋወጫ ፍጥነትን አሁን ካለው የ4G ቴክኖሎጂ ከ10 እስከ 100 የተሻለ እጥፍ እንደሚልቅ ይገምታል። ይህም ማለት የሞባይል ኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን እስከዛሬ ከነበረው የm/s ፍጥነት ወደ g/s ያሳድገዋል ማለት ነው።
የአምስተኛው ትውልድ ኔትዎርክ (5G) ቀድሞ በነበሩት የኔትዎርክ አስተላላፊዎች ላይ ቁጥራቸው በርከት ያሉ በመጠን አነስተኛ የሆኑ አንቴናዎችን በመጨመር እንዲሁም የማስተላለፍ አቅማቸውን በማሳደግ ከፍተኛ የሆነ የመረጃ መላላኪያ ፍጥነትን በመጨመር የተፈጠረ ሲሆን የመረጃ መዘግየትን በእጅጉ ይቀንሳል። እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ከዚህ በተጨማሪም በፊት ከነበሩት የኔትዎርክ አስተላላፊዎች ያነሰ የኤሌክትሪክ ሃይል መጠቀማቸውም ልዩ ያደርጋቸዋል።
ጥንቅሩን ይመልከቱ
https://www.youtube.com/watch?v=9jCLBDFlhjI&pp=sAQA
የክሪስፐር ቴራፒን በመጠቀም ለመጀመሪያ ጊዜ የሰውነት በራሂ መዛባት ችግርን መፈወስ ተቻለ
===========================
ተመራማሪዎች የክሪስፐር ህክምና (CRISPR therapy) ተብሎ የሚታወቀውን የህክምና ቴክኖሎጂ በመጠቀም የሰዎችን የበራሂ መዛባት ችግር (genetic disorder) በተሟላ ሁኔታ ለማከም የሚያስችል ደረጃ ላይ መገኘታቸው ተነገረ፡፡ ከዚህ በፊት የክሪስፐር ቴራፒን በትክክል ወደ ደም ዝውውር ውስጥ በማስገባት ማስተካከያ የሚፈልገውን የህዋስ አይነት ለይቶ ለማከም አስቸጋሪ የነበረ ቢሆንም ከብዙ አመታት ሙከራዎች በኋላ ይህን ችግር በተሟላ ሁኔታ መቅረፍ ተችሏል፡፡

በዚህ ሙከራ ላይ ምርመሩን በማድረግ የተሳተፉት የኢንቴሊያ ቴራፒዩቲክስ እና ሬጄኔሮን ፍራመሲዩቲክልስ ተመራማሪዎች አልፎ አልፎ በሰዎች ላይ የሚታይ የበራሂ መዛባት ችግር ያለባቸውን 6 ሰዎች በመምረጥ NTLA-2001 የሚል ስያሜ የተሰጠው የክሪስፐር ቴራፒ ወደ ሰዎቹ ደም ዝውውር ውስጥ በማስገባት ማስተካከያ የሚፈልገውን የህዋስ አይነት ለማከም ሞክረዋል፡፡ ከጉበት ጋር በተያያዘ አልፎ አልፎ በሰዎች ላይ የሚከሰተው transthyretin amyloidosis የተባለው ይህ የበራሂ ችግር አደገኛ ፕሮቲኖችን እንደሚረቱ በማድረግ በሰዎች ጤና ላይ ከባድ ተፅዕኖ የሚያስከትል ነው፡፡

ተመራማሪዎች በመጀመሪየው የክልኒካል ሙከራ ይህ የበራሂ ችግር ያለባቸውን 6 ሰዎች በክሪስፐር ቴራፒ አማካኝነት NTLA-2001 የተባለውን መርፌ ከሰጧቸው በኋላ ማስተካከከያ የሚስፈልገውን ጂን በማከም ከ transthyretin amyloidosis የሚገኘውን አደገኛ የፕሮቲን ምርት ማቋረጥ ችለዋል፡፡ በዚህ የክልኒካል ሙከራ ከተሳተፉ 6 ታካሚዎች መካከል በተለይም ሶስቱ በዚህ የበራሂ መዛባት ችግር የተፈጠረባቸውን አደገኛ ፕሮቲኖች ከ80 እስከ 96 በመቶ መቀነስ መቻላቸው ታውቋል፡፡

ይህ የምርምር ውጤት ለህክምናው አለም ሰዎች እና ለህሙማን መልካም ዜና ነው ያሉት የክሪስፐር መስራች ፕሮፌሰር ጅኔፈር ዳውድና ጥናቱ አሁንም የሚቀጥል ቢሆንም ለበዙ አመታት ለክሪስፐር ቴራፒ መሰናክከል ሆኖ የቆውን ይህን ችግር በተሟላ ሁኔታ መፍታት መቻሉ ለህክምናው አለም ትልቅ ድል ነው ብለዋል፡፡

እንደሚታወቀው የክሪስፐር ቴራፒ ከዘመናዊ የህክምና ቴክኖሎጂ እንደ አንዱ የሚመደብ ሆኖ በዋናነት የሰዎችን የበሽታ ምንጭ ከበራሂ አይነታቸው በመፈለግ እና እክሉንም ራሱን በራሂውን በማስተካከል ወይም gene editing በማከሄድ በሽታውን ለመፈወስ የሚደረግ ሂደት ነው፡፡ በህክምናው አለም የበራሂ መለዋወጥ ወይም genetic mutations የሚባለው ፅነሰ-ሀሳብ ከ6,000 የሚበልጡ በሰዎች ለሚከሰቱ በሽታዎች ዋና ምክንያት በመሆኑ ይህ የክሪስፐር ቴራፒ ይህን የበራሂ መለዋወጥ በማስተካከል ወይም በማከም የሰዎችን በሽታ ከስር ከመሰረቱ ለማከም የሚሞክር ነው፡፡ እንደአውሮፓውያኑ በ2001 ይፋ የተደረገው ይህ የህክምና ቴክኖሎጂ በ2012 አና 2015 ካስገኘው የህክምና ትሩፋት በኋላ ለአለማችን ትልቅ ተስፋ ያስገኘ የህክምና ግኘት ሆኗል፡፡
ምንጭ bigthink
ተጨማሪ https://bigthink.com/technology-innovation/crispr-therapy-cures-genetic-disorder
የቶኪዮ አሎምፒክ ሜዳሊያዎች የተሰሩበት አሮጌ የኤሌክትሮኒክስ መሳርያዎች
====================
በየዓመቱ 53 ሚሊዮን ቶን የሚደርስ የኤሌክትሮኒክስ መሳርያ ውጋጅ (e-waste) በአለማችን ጥቅም ላይ ውሎ ይጣላል፡፡ የኤሌክትሮኒክስ መሳርያዎች የአገልግሎት ዘመናቸውን ጨርሰው እንደቆሻሻ በሚጣሉበት ጊዜ አግባብነት ያለው የአወጋገድ ስርዓት ካልተበጀላቸው አልያም ዳግም ጥቅም ላይ የሚለውሉበት ሂደት ከሌላቸው በአፈር እና በከርሰ ምድር ውሃ ላይ ጎጂ ውጤቶችን ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡

እነዚህ ቁሶች በተለይም በአፈሮቻችን ላይ የሚለቋቸው የአርሴኒክ፣ እርሳስ እና ካድሚየም ያሉ ከባድ መርዛማ የብረት ኬሚካሎች የእፅዋትን የአስተዳደግ ሂደት በመበከል እና በከርሰ ምድር ውሃ ላይ ጥፋት በማስከተል ህይወታቸውን በዚህ ላይ ለመሰረቱት የተለያዩ እንስሳት አደጋን ያመጣሉ፡፡ ይህ የስነ ምህዳር መዛባት አደጋ በእንስሳትና በእፅዋት የሚያበቃ ቢመስልም በጊዜ ሂደት በምግብ አቅርቦት ሰንሰለት እና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ወደሰዎች ማምራቱ የሚቀር አይደለም፡፡ ይህን አለም አቀፍ ችግር በሚቻለው አቅም ለመቅረፍ እና የወደፊቱን የሰዎች ጤናማ ህይወት በበጎ ለማረጋገጥ አንዲህ ያሉ ቁሶች ዳግም ጥቅም ላይ የሚለውሉበት ሂደት ማበጀቱ በብዘዎች የሚደገፍ ጉዳይ ነው፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ አሁን እየተካሄደ ባለው የቶኪዮ አሎምፒክ ውድድር ላይ አዘጋጇ ሃገር ጃፓን ለአሸናፊዎቹ የሚሰጠውን ሜዳልያ ለመስራት ጥቅም ላይ ያዋለቸው የኤሌክትሮኒክስ መሳርያ ውጋጅ የአለም አቀፍ ችግር ለሆነው ለዚህ ጉዳይ ጥሩ መፍትሄን ያሳየ ይመስላል፡፡ ሃገሪቱ ይህንን ስራ በትኩረት የጀመረችው በ2017 ሲሆን ቶክዮ 2020 ሜዳሊያ ፕሮጀክት በሚል በመላ ሀገሪቱ ተጥለው የሚገኙ የኤሌክትሮኒክስ መሳርያዎች (በተለይም የስልክ ቀፎዎች) እንዲሰበሰቡ አድርጋለች፡፡ በሃገሪቱ የኦሎምፒክ ኮሚቴ አስተባበሪነት ሲሰበሰብ የቆው የኤሌክትሮኒክስ ውጋጅ በ2019 ከተጠናቀቀ በኋላ በጥቅሉ 78,985 ቶን ውጋጅ እንዲሰበሰብ ሆኗል፡፡ ይህ የተሰበሰበው የኤሌክትሮኒክስ ቁስ መንግስት ፍቃድ በሰጣቸው የስራ ተቋራጮች ከተከፋፈለ በኋላ በተለያዩ ህጋዊ አሰራሮች አማካኝነት ወደስራ እንዲገቡ ተድርጓል፡፡

ከተሰበሰበው የኤሌክትሮኒክስ ውጋጅ የብረት ንጥረ ነገር ያለው ቁስ ቀልጦ ወደ ማጣራት ሂደት ያመራ ሲሆን ሌላ አይነት ይዘት ያላቸው እቃዎችም ተለይተው አንዲገቡ ተድረገዋል፡፡ የኦሎምፒክ ኮሚቴው ከዚህ ጠቅላላ ሂደት በኋላ 32 ኪሎ ግራም ወርቅ፣ 3,500 ኪ.ግ ብር እና 2,250 ኪ.ግ ነሃስ ማግኘት የቻለ ሲሆን ይህም ለኦሎምፒክና ለፓራኦሎምፒክ ውድድሮች የሚያስፈልጉትን አጠቃላይ 2,500 ሜዳሊያዎች መስራት የሚያስችል ነበር፡፡
https://interestingengineering.com/tokyos-olympic-medals-are-made-of-47-tons-of-recycled-e-waste
መንታዋን በሆዷ ይዛ የተወለደችው ህፃን
==========
በእስራኤል የተወለደች አንድ ህፃን መንትያዋን ይዛ መወለዷ ተዘገበ፡፡ ህፃኗ ለዚህ የበቃቸው እጅጉን አልፎ አልፎ በሚከሰትና በሳይንሳዊ አጠራሩ “ፌቱስ ኢን ፌቱ” የሚባል የጤና ሁኔታ ስለተከሰተባት ነው፡፡
ሀኪሞች ህፃኗ ከመወለዷ በፊት በአልትራሳውንድ ሲመለከቷት በፅንሱ ላይ ችግር ሊኖር እንደሚችልና ሆዷም ከተለመደው ከፍ ያለ መሆኑን ተረድተው ነበር፡፡ ህፃኗ ስትወለድም ሀኪሞቹ ኤክስሬይ እና አልትራሳውንድን ጨምሮ የተለያዩ ምርመራዎችን ሲያደርጉ በህፃኗ ሆድ ውስጥ ፅንስ ማደጉን ለመመልከት መቻላቸው ተዘግቧል፡፡
ፌቱስ ኢን ፌቱ “በፅንስ ውስጥ ፅንስ” እንደማለት ሲሆን ከተለመደው ወጣ ያለ (Abnormal) ፅንስ አንድ ጤናማ በሆነ ፅንስ ውስጥ ማደጉን የሚያመላክት የጤና ክስተት ነው፡፡ ክስተቱ እጅጉን አልፎ አልፎ የሚከሰት ሲሆን በየጊዜው ከሚወለዱ 500 ሺህ ህፃናት መካከል በአንደኛው ላይ ብቻ የሚመጣ ነው፡፡ እስካሁን ተጨማሪው ፅንስ በምን ምክንያት እንደሚፈጠር ግልፅ ባይሆንም የዋናው ፅንስ ጥገኛ መንትያ (Parasitic Twin) ሊሆን ይችላል ሲሉ ተመራማሪዎች መላ ምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ ተጨማሪው ፅንስ የሚፈጠረውም መንታዎች በሚፀነሱበት የመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ወቅት አንደኛውን ፅንስ ሌላኛውን ሲውጠው መሆኑ በባለሙያዎች ዘንድ ይነገራል፡፡
ህጻኗ የተወለደችበት የእስራኤሉ ኤሱታ ጤና ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ኦመር ግሎቦስ በበኩላቸው ሁነቱ የተፈጠረው ፅንሱ በማደግ ላይ ባለበት ጊዜ መሆኑን ገልፀው ተጨማሪው ፅንስ እዛው ቢኖርም በህይወት ግን እንደማይቆይ ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ህፃኗ ከተደረገላት የቀዶ ጥገና ህክምና በጥሩ ሁኔታ እያገገመች ሲሆን ወደ ቤቷ ተመልሳም ከእናቷ ዘንድ ለመሆን መብቃቷ ተገልጿል፡፡
ምንጭ፤ Live Science
ለተጨነማሪ፤ https://www.livescience.com/fetus-in-fetu-israel.html
የቶኪዮ ኦሎምፒክ መሮጫ መም እና ከበስተጀርባ ያለው ቴክኖሎጂው
===================
ባለፉት 4 ቀናት ውስጥ አትሌቶቻችን ሲንፈላሰሱበት የተመለከትነው የቶኪዮ ኦሎምፒክ መሮጫ መም ሞንዶ በተሰኘው ከአውሮፓውያኑ 1948 አንስቶ በ12 ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ላይ የመሮጫ መም ባቀረበው ኩባንያ የተሰራ ነው፡፡ እንደ ኩባንያው አገላለፅ የኦሎምፒኩን አትሌቲክስ ውድድሮች በሚያስተናግደው የጃፓን ብሔራዊ ስታዲየም የተዘረጋው መም በላይኛው ክፍሉ ባለ ሦስት እይታ በሆኑና ከተመረጠ የፖሊመር ስርዓት ጋር ተጣምረውና እንዲጠነክሩ ተደርገው በተሰሩ ጥቃቅን ጎማዎች ተሞልቷል፡፡ የማጠንከር (Vulcanization) ሂደቱም ሞለኪውላዊ ትስስሩን በማጠናከሩ ጠቅጠቅ ያለ ንጣፍን ፈጥሯል፡፡ በሌላ አነጋገር መሙ ፈጣን ነው እንደማለት ነው፡፡

ለስላሳ፣ ውብ እና እስከ ዛሬ ከሮጥኩባቸው ምርጥ የመሮጫ መሞች አንዱ ነው የሚለው የአሜሪካን 100 ሜትር ሯጩ ሮኒ ቤከር “በደመና ላይ የምራመድ ያህል ይሰማኛል” ሲል የመሙን ምቹነት ይገልፃል፡፡

ከምቾት ባለፈ ግን ስለ ፍጥነቱም እየተነገረለት ይገኛል፡፡ መሙ ከአራት ወራት በላይ ፈጅቶ ባለፈው ዓመት ህዳር ወር ላይ የተጠናቀቀ ቢሆንም የኦሎምፒኩን ለአንድ ዓመት መዘግየት ተከትሎ ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ ሳይደረግት በቶኪዮ ፀሐይ እየተጠበሰ መቆየቱ ጠንከር እንዲል አድርጎታል፡፡ ምን ያህል ፈጣን ነው የሚለውን ምናልባትም ከኦሎምፒኩ መገባደድ በኋላ የተመዘገቡ ክብረ ወሰኖችን በመመልከት የሚወሰን ቢሆንም ከአትሌች ምስክርነት ለማረጋገጥ እንደሚቻለው ግን መሙ ፍጥነታቸውን እንደጨመረላቸው ነው፡፡ ከነዚህ አትሌቶች መካከል አሜሪካዊው የ800 ሜትር ሯጭ ክሌይተን መርፊ መሙ ፈጣንና ምናልባትም በቀጣይ ክብረ ወሰኖች የሚሰባበሩበት ሊሆን እንደሚችል ይገልፃል፡፡ በዚህ ረገድ ጃማይካዊቷ የአጭር ርቀት ሯጭ ኤሌን ቶምሰን ሄራህ ለ33 ዓመት የቆየውን የ100 ሜትር የኦሎምፒክ ክብረ ወሰን መስበሯም ትኩረትን ስቧል፡፡

አምራች ኩባንያው ሞንዶ እንደሚለው ይህ የሚያነጥር መም የሯጮችን ፍጥነት እና በውድድሩ የሚያሳዩትን ብቃት ለማሳደግ ተብሎ የተሰራ ነው፡፡ የላይኛው የመሙ ንጣፍ የጠነከረ ጎማ መሆኑ በመለጠጥ ረገድ ይረዳዋል፡፡ በታችኛው ምንጣፉ ውስጥ ያሉት በአየር የተሞሉ ባዶ ቦታዎችም መሙ የሚረገጥበትን ኃይል በመሰብሰብና ይህንንም ወዲያው መልሶ ወደ አትሌቶቹ እንዲያሻግር አስችሎታል፡፡ ይህ ኃይልን ከሯጮች ሰብስቦ መልሶ ለሯጮች የመስጠት ብቃቱ ታድያ በአጭር ርቀት ሯጮች ዘንድም ተመስክሮለታል፡፡

ሆኖም ከመሙ ባሻገር ለሯጮቹ ፍጥነት ዘመናዊዎቹ ጫማዎችም ምክንያት ተደርገው ሊወሰዱ እንደሚችሉ ይነገራል፡፡ በውስጣቸው ዝርግ ካርበን ያለባቸውና በረጅም ርቀት ሯጮች ላይ ተተግብረው የዓለም ክብረ ወሰኖች እንዲሰባበሩ ባስቻሉት ጫማዎች ላይ ያለው ቴክኖሎጂ ለአጭር ርቀር ሯጮችም እንዲሆን ተደርጎ ወደመሰራት እያመራ ነውና፡፡ (ከአራት ቀናት በፊት በሐምሌ 21 2013 ዓ.ም “ሪከርድ ሰባሪዎቹ ጫማዎች” በሚል ርዕስ ስለ ጫማዎቹ ያቀረብንልዎትን ፅሁፍ በዚህ ሊንክ አማካኝነት ማየት ይችላሉ https://www.facebook.com/TechinEthiopia/posts/4179524768822243 )

ምንጭ፤ Tech Xplore
ለተጨማሪ፤ https://techxplore.com/news/2021-08-tech-tokyo-olympics-fast-track.html
ኢኮኖሚያዊ እድገትን በአይሲቲ ማፋጠን
-----------------------------------------
አይ.ሲ.ቲ በፈጣን ልማት ረገድ ከፍተኛ የሆነ የመወዳደርያ አቅምን መገንባት የሚያስችል ሲሆን፤ በተለይም በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እና በፖለቲካዊ ምህዳር ተጨባጭና ዘላቂ እድገትን ማስመዝገብ የሚያስችል ከመሆኑ በተጨማሪም በዓለም ዓቀፍም ሆነ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ለተፈጠሩት እና ለሚፈጠሩት ችግሮች መፍትሄ ለማስቀመጥ ሁነኛ አስተዋፅዖ አለው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ለፈጠራ፣ ለምርምር፣ ለፖሊሲና ለሌሎች መንገዶች ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡ በዚህ መንገድ አይ.ሲ.ቲ ዓለምን በመቀላቀል የስራ ዕድል፣ የተወዳዳሪነት መንፈስ፣ የገበያ መስፋፋት፣ ምርትና ምርታማነት ማስፈንና ሌሎችም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን ማግኘት ይቻላል፡፡ ዓለም አንድ መንደር እንድትሆን ባደረገው በሉዓላዊነት ዘመን የትም ቦታ ሆኖ ማንኛውንም መረጃ ማግኘትና ማቀበል ተችሏል፡፡
ሀገራት ነባራዊ ሁኔታቸውን እና ስነ-ምህዳራዊ ባህሪውን አጥንተው ተስማሚና ውጤታማ ለመሆን፤ ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት በማድረግ መስራታቸው ዓለም እየሄደችበት ባለው ፍጥነት ተሳታፊ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል፡፡ በተለይም እንደኛ ያሉ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ አንዳንድ የዕድገት መሰላል በመጠቀም እንደ ሌሎች ሀገራት በኢኮኖሚ ከፍታ ላይ ለመሰለፍ እና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እንዲሁም የማህበረሰቡን ገቢ ለማሳደግ ከድህነት አረንቋ ለማውጣት እና እድገትን በዘላቂነት ለማስቀጠል መሰረታዊ ጥቅም እንዳለው ሁሉም የሚስማማበት እውነት ነው፡፡ የግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንደስትሪ መር ለመለወጥና አስተማማኝ ኢኮኖሚ ለመገንባት የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ተገቢ ነው፡፡
የአይ.ሲ.ቲ ምጥቀት በኢንደስትሪው ዕድገት ውስጥም ከፍተኛ ድርሻ አለው፡፡ በተለይም በአሁኑ ሰዓት አድካሚና አሰልቺ የነበሩት በርካታ የኢንደስትሪ ስራዎች በቀላል መንገድ እንዲሰራ እና ፍጥነት እና ጥራት እንዲኖረው በማድረግ አይ.ሲ.ቲ የአንበሳ ድርሻን ተጫውቷል፡፡ ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ይህ ነው የማይባል በርካታ አስቸጋሪ እና አሰልቺ ጊዜን የሚሹ ጉዳዮችን በማቅለል እና ጠቀሜታ ወዳላቸው ነገሮች በመቀየር አሁንም ዓለማችን የበለጠ ተወዳጅ እንድትሆን እያደረጋት ይገኛል፡፡
ምንጭ፡ darden እና tech science
https://www.darden.virginia.edu/sites/default/files/inline-files/Chap%205_Fostering%20the%20Economic%20and%20Social%20Benefits%20of%20ICT