TechIn2
1.17K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
በገጠር የበይነ-መረብ ግንኙነትን (ኢንተርኔት) ለማሳደግ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ
*************************
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና "ኢንተርኔት ሶሳይቲ" በገጠር የበይነ-መረብ ግንኙነትን (ኢንተርኔት) ለማሳደግ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ።
ስምምነቱ የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት የተጀመረውን ስራ የሚደግፍ፣ በገጠር ጠንካራ የበይነ መረብ ግንኙነትን ለማዳረስ፣ የበይነ መረብ መሰረተ ልማትን ለማስፋፋትና የበይነ መረብ አስተዳደርን ለማሳደግ የሚያስችል ነው ተብሏል።
ስምምነቱን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሐመድ (ፒ ኤች ዲ) እና የኢንተርኔት ሶሳይቲ የአፍሪካ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ዳዊት በቀለ (ፒ ኤች ዲ) ፈርመውታል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሐመድ (ፒ ኤች ዲ) አካታች ብልፅግናን ማረጋግጥን ግቡ አድርጎ የተዘጋጀው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ እውን እንዲሆን መንግስት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የልማት ድርጅቶችና ማህበራት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
ስትራቴጂው መሰረተ ልማቶችን ማሟላት፣ አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር፣ የዲጂታል መተግበሪያዎችን ማልማት እና ምቹ ከባቢያዊ ሁኔታን መፍጠር የሚሉትን ስለማካተቱም አብራርተዋል።
ስምምነቱ ይህንን ወደ ተግባር ለመቀየር የሚደረገውን ጥረት ይደግፋል ብለዋል።
የኢንተርኔት ሶሳይቲ የአፍሪካ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ዳዊት በቀለ (ፒ ኤች ዲ) ስምምነቱ የገጠር የበይነ መረብ ግንኙነትን በማሳደግ በገጠር ያለ ሁሉም ማህበረሰብ በዲጂታል ለውጥ ውስጥ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል ነው ብለዋል።
የኢንተርኔት ሶሳይቲ የዲጂታል የኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ትግበራን ለመደግፍ ቁርጠኛ መሆኑም አረጋግጠዋል።
ስምምነቱ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ቅድሚያ የተሰጣቸውን የግብርና፣ የማምረቻ፣ የአገልግሎትና ቱሪዝም ዘርፍን ለመደገ ያግዛል ተብሏል።
ምንጭ https://www.facebook.com/MInT.Ethiopia
የእናቶችን ድካም የሚያቀለው አዲሱ የእንሰት መፋቂያ ማሽን
---------------------------------------
የእንሰት ተክል አትዮጵያ ውስጥ በብዛት ከሚበቅሉ እና በተፈጥሮ ከታደልንባቸው ውድ ስጦታች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ከ 20 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ የሃገሪቱ ዜጎች መሠረታዊ ምግብ የሆነው ይህ ተክል በብዙ አካባቢዎች ጥያቄ ሆኖ የቀረውን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥም ትልቅ አቅም ያለው ነው፡፡ በደቡባዊ ኢትዮጵያ ከእንሰት ተዘጋጅቶ ለምግብነት የሚዘወተረው የቆጮ ምግብ አመራረቱና አዘገጃጀቱ ለብዙ እናቶች እጅግ አድካሚ እንደሆነ ይነገርለታል።
እንሰትን ለማምረትና ለማዘጋጀት በሚተገበረው ሂደት ዘመናዊ አሰራር ባለመኖሩ እና የአጠቃቀም ስርዓቱ ችግር የማያጣው በመሆኑ ከ24 እስከ 25 በመቶው የእንሰት ምርት ለብክነት የተዳረገ ይሆናል፡፡ ይህ ትልቅ ሃብት የተለያዩ የቴክኖሎጂ አመራጮች እና የአሰራር ስርዓቶች ተግባራዊ የሚደረግብት ከሆነ በአፍሪካ ቀጣናዎችም ይሁን በአለም ገበያ እጀግ ተወዳዳሪ የመሆን አቅም አለው፡፡ ታዲያ ይህን መነሻ በማድረግ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ማኑዩፋክቸሪንግ ፋኩልቲ የበለፀገው የእንሰት መፋቂያ ማሽን ዘመናዊ አሰራር ለመዘርጋት እና የእናቶችን አድካሚ ስራ ለማቅለል ትልቅ እገዛ የሚያደርግ ነው፡፡
አሁን ባለው አሰራር እናቶች አንድ የእንሰት ግንድ ፍቆ ለማጠናቀቅና ወደቀጣዩ ሂደት ለማዘጋጀት እጅግ አድካሚ በሆነ አሰራር ከአንድ ቀን በላይ የሚፈጅባቸው ሲሆን አዲሱ የፈጠራ ስራ ግን ብዛት ያላቸው የእንሰት ግንዶችን በአንድ ቀን ብቻ በቃላሉ ሊያከናውን ይችላል፡፡ በፋኩልቲው የኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ ትምህርት ክፍል የበለፀገው ይህ ማሽን በመጀመሪያ የእንሰት ግንዱን በትንንሹ በመፈልቀቅ እና በማሽኑ ልክ እንዲገባለት የሚያስፈልግ ሲሆን ከዚህ በመቀጠልም የተለያዩ የሜካኒካል ሂደቶችን በማለፍ እንሰቱን የመፋቅ ተግባር ያከናውናል፡፡
ዩኒቨርስቲው በየዓመቱ በሚያዘጋጀው የቴክኖሎጂ ሽግግር ፕሮግራም ላይ እንደእቅድ ተይዞ በትምህርት ክፍሉ ተመራማሪዎችና መምህራን ለውጤት የበቃው ይህ ፈጠራ በቀጣይ ሂደት ከሚኖረው የማሻሻየ ስራ በኋላ ወደ ጅምላ ምርት የሚገባበት እና ወደ ህብረተሰቡ የሚሰራጭበት ሂደት አንደሚኖር ተገልጿል፡፡
ምንጭ፡ ዶቼ ቬለ (DW)
https://fb.watch/61YoseU5QZ/
በነብሳት (ሶስት አጽቄዎች) ቅርጽ የተሰራ የኮምፒውተር ሲስተም
*****************************
ኢንሴክት ኮምፒውተር የተባለ ወረርሽኞች እና የተለያዩ አደጋዎች ከተከሰቱ በኋላ ለሚደረግ የአሰሳ ስራ ተግባር ላይ የሚውል ሲስተም ይፋ ተደረገ፡፡ ከሲንጋፖር፣ ቻይና፣ ጀርመንና እንግሊዝ የተውጣጡ የተመራማሪዎች ቡድን ይህን ልዩ ቴክኖሎጂ ሰርተው እንዳቀረቡ ተነግሯል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች መጠናቸውና ድግግሞሻቸው እጅግ ከፍ እያለ ይገኛል፡፡ በዚህም ምክንያት ተመራማሪዎች በአደጋዎች ለሚጠቁ ሰዎች ድጋፍ ለማድረግና የሞትና የአካል ጉዳት መጠንን ለመቀነስ የተለየ ስልት ያስፈልጋል ብለው ያምናሉ፡፡ እንደ ጎርፍ፣ ገሞራ ፍንዳታ፣ ሰደድ እሳት እና ሌሎች አደጋዎች በሚከሰቱበት ወቅት ሰዎችን በመጠቀም የሚደረገው የድጋፍ እንቅስቃሴ ተጨማሪ አደጋ የሚያመጣ በመሆነ በጣም አነስተኛ መጠን ያላቸው (ልክ እንደ ነብሳት) የቴክኖሎጂ ቁሶችን መጠቀም በጣም አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል፡፡
ተመራማሪዎች በማዳጋስካር የሚገኝን ክንፍ አልባ በረሮ ቅርጽን በሞዴልነት በመውሰድ እና በረሮው ሊሸከመው በሚችለው መልኩ ተዘጋጅቶ አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ በቦታዎቹ በመገኘት ፍለጋዎችንና የተለያዩ መረጃዎችን ማቀበል የሚያስችል ማይክሮ ቴክኖሎጂን ነው ያቀረቡት፡፡ ይህ ቴክኖሎጂም አምስት እርስ በርሳቸው የተገናኙ ሰርኪዩቶች ያሉትና እንደ ካሜራ፣ የግንኙነት ቺፕ፣ የካርቦን ዳይ ኦክሳይድ መለኪያ፣ ሚሞሪ እና ሌሎች አስፈላጊ ቴክኖሎጂዎች የተገጠሙለት ነው፡፡
ይህ አነስተኛ መጠን ያለው የኮምፒውተር ሲስተም በበረሮው ጀርባ ላይ በቀላሉ መቀመጥ እንዲችል ተደርጎ የተሰራ ነው፡፡ በተጨማሪም በረሮው አካባቢውን ለመረዳት የሚጠቀምበትን እንደ አንቴና ያለ ክፍል ላይ ኤሌክትሮድ በማስገባት የበረሮው እንቅስቃሴ በኤሌክርቲክ ሞገድ አማካኝነት በተሸከመው ማይክሮ ቴክኖሎጂ እንዲመራ ማድረግ ተችሏል፡፡
በሙከራ ወቅትም 94 በመቶ የተሳካ የተጎጅዎችን ፍለጋ ማካሄድ ተችሏል፡፡
ምንጭ techxplore
ተጨማሪ ንባብ https://techxplore.com/news/2021-06-insect-computer-hybrid-disasters.html
መቋጫውን ያገኘው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋማት አቅም ግንባታ ስልጠና
======================
በቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ተዘጋጅቶ በአራት የታዳጊ ክልሎች እና የድሬደዋ ከተማ አስተደዳደር ውስጥ ላሉ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ተቋማት ሲሰጥ የቆየው የሦስት ቀናት ስልጠና ዛሬ ተጠናቋል፡፡ በቢሾፍቱ ከተማ ሲሰጥ የቆየው ስልጠናው በስታርታፕ፣ ዲጂታል ተግባራት እንዲሁም የፕሮጀክት አስተዳደርና ሌሎች ጉዳዮችን የዳሰሰ ነበር፡፡
የመሰናዶው መጠናቀቅያ በሆነው የዛሬው ዕለትም በኢንስቲትዩቱ ተመራማሪዎች አማካኝነት ገለፃዎች ሲቀርቡ ቆይተዋል፡፡ የዕለቱን የመጀመሪያ ገለፃ ያቀረበችው ወ/ት አለሜ ወ/ገብርኤል የስታርታፕ ስነ ምህዳርን አስመልክታ በሀሳቡ ምንነት፣ የሚያስገኘው ጥቅም እንዲሁም የመንግስትና ሌሎች ድጋፍ ሰጪ አካላትን ጨምሮ ባለድርሻዎችን የዘረዘረች ሲሆን ከዚህም ባሻገር የህንድ እና ኢስቶኒያን እንቅስቃሴ እንደምሳሌ በማጣቀስ እንዴት ስኬታማ የሆነ የስታርታፕ ስነ ምህዳር መፍጠር እንደሚቻል አስረድታለች፡፡
ሌላኛው የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪ አቶ ሙሉጌታ አንበሴም እንዲሁ በሀገራችን ስታርታፖችን ለማውጣት የራሱን ሚና እንደሚጫወት በሚጠበቀውና ኢንስቲትዩቱ በሚያዘጋጀው የቅድመ ኢንኩቤሽን ፕሮግራም ዙርያ ማብራርያ ሰጥቷል፡፡ በያዝነው ዓመት ብቻ ኢንስቲትዩቱ ሁለት የቅድመ ኢንኩቤሽን ፕሮግራሞችን አዘጋጅቶ እንደነበር ያስረዳው አቶ ሙሉጌታ ፕሮግራሞቹ አንግበው በተነሱባቸው ዓላማዎችና ተጠቃሚ ባደረጓቸው የፈጠራ ባለሙያዎች እንዲሁም በቀጣይነት የኢንኩቤሽን ደረጃ ላይ ሲደረስም በሚኖሩት ሁኔታዎች ላይ ያውጠነጠነ ገለፃን አቅርቧል፡፡ ከዚህም ባለፈ እነዚህን መሰል ፕሮግራሞችን ወደ ክልል ከተሞች ቢስፋፉ ሊኖራቸው ስለሚችለው ጠቀሜታ ተናግሯል፡፡
ሌላኛው የዕለቱ ገለፃ አቅራቢ አቶ ደስታ አበራ በቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ስር ሆኖ የስልጠና እና ድጋፍ ስራዎችን በሚያከናውነው ዳይሬክቶሬት የስራ ክንውኖች ላይ አተኩረው ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡ የስራ ክፍላቸው ከማይክሮሶፍት አፍሪካ፣ ኮይካ፣ ሲስኮ እና ላይት ሃውስ ከተሰኙ የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ከስምምነት በመድረስ የጋራ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ያወሱት አቶ ደስታ በተለይም ከማይክሮሶፍት አፍሪካ ጋር በመተባበር 50 ያህል ሰዎች ጠቃሚ ስልጠናን እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ በዳይሬክቶሬቱ አማካኝነት በአጠቃላይ ከ600 በላይ ሰዎች ስልጠና እንዲያኙ መደረጉንና ከዚህም ባሻገር የፈጠራ ስራዎች ወደ ምርት እንዲያሳድጉ ታስበው ስለተከናወኑ የሰመር ካምፕ ዝግጅቶችንም ለታዳምያኑ አብራርተዋል፡፡
ቀና ብለን ስንመለከት ጊዜን ወደኋላ እየቃኘን ነው
-------------------------------------
ጊዜ ከማይክሮ ሴኮንድ ተነስቶ ሴኮንድ፣ ደቂቃ፣ ሰዓት፣ ቀናት፣ ወራት እና አመታት እያለ ይነጉዳል፡፡ ድምፅና ብርሃን በእነዚህ ጊዚያት ውስጥ ከመንጎድ ይልቅ ይበናሉ፡፡ ድምፅ በየሶስት ሴኮንዱ አንድ ኪሎ ሜተር ያክል የሚጓዝ ሲሆን፤ ብርሃን በበኩሉ በየአንድ ሴኮንዱ 300,000 ኪሎ ሜትር አቋርጦ ይሄዳል፡፡ ብርሀን በህዋ አካለት ውስጥ የመለኪያና የመግባቢያ ቋንቋ በመሆኑ ከምድራችን ውጭ ያሉ አለማትንና ከዋክብትን ለመቃኘት ይረዳናል፡፡ ለምሳሌ የኛዋ ፀሃይ ከመሬት ያላት ርቀት 150 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር በመሆኑ ከሷ የሚመነጨው ብርሃን ወደኛ ለመድረስ 8 ደቂቃዎች ብቻ ያስፈልጉታል፡፡ ይህ ማለት ፀሃይን በተመለከትናት ቁጥር በየስምንት ደቂቃው የሚኖራትን ገፅታ ተመለከትን ማለት ነው፡፡
በአንፃሩ ጨረቃ ከመላው ዩኒቨርስ እጅግ የምትቀርበን አካል በመሆኗ ከፀሃይ የምታገኘውንና ከገጿ ተንፀባርቆ የሚመለሰውን ብርሃኗን ለመመልከት ጥቂት ሰከንዶች ብቻ ያስፈልጉናል፡፡ ይህም ማለት ጨረቃ ከምድር የምትርቅበት መጠን 380,000 ኪ.ሜ በመሆኑ ከሷ የሚነሳ ብርሃን ወደኛ ለመድረስ 1.3 ሰኮንዶች ብቻ ያስፈልጉታል ማለት ነው፡፡ ጨረቃን በየ 1.3 ሰኮንድ ልዩነት ስለምንመለከታት ምንም አይነት ለውጥ አናይባትም፡፡ ይሁንና ከስርዓተ ፀሃያችን ውጭ ያሉ ከዋክበት ወይም ሌሎች የህዋ አካለት የሚያመነጩትን ብርሃን ስንመለከት ጊዜን ወደኋላ እየቃኘን ነው፡፡ ድቅድቅ ባለ ጨለማ ውስጥ ቀና ብለን ከምንመለከታቸው ክዋክብት መካከል አንዳንዶቹ በአሁኑ ጊዜ ህልውናቸው ያከተመ ሊሆን ይችላል፡፡
ለምሳሌ ለእኛ ፕላኔት ቅርቡ የሆነው አልፋ ሴንቸሪ የተሰኘው ኮከብ ከኛ አራት የብርሃን አመታት ይርቃል፡፡ ይህ ማለት ብርሃን በሴከንድ ሶስት መቶ ሺህ ኪሎ ሜትር እየተጓዘ አራት አመታት ያህል የሚወስድበት እርቀት ሲሆን ይህ ርቀት በኪሎ ሜትር ሲለካ ከሰላሳ ስድስት ትሪሊዮን ኪሎ ሜትር በላይ ነው፡፡ ይህ ማለት አሁን የምናየው የኮከቡ ገጽታ አሁን ያለውን መልኩን ሳይሆን ከአራት የብርሃን አመታት በፊት የነበረውን ነው፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው ከኮከቡ የዛሬ አራት አመት በፊት የተነሳው ብርሃን ከርቀቱ የተነሳ እኛ ጋ የደረሰው አሁን በመሆኑ ነው፡፡
አሁን ያለውን የኮከቡን መልክ ለማየት አራት የብርሀን አመታት መጠበቅ አለብን። ምክንያቱም ብርሃኑ ከኮከቡ ዛሬ ቢነሳ እኛ ጋ የሚደርሰው ከአራት የብርሃን አመታት በኋላ ስለሆነ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ለእኛ ቅርቡ የሆነው ኮከብ ያለው ርቀት ሲሆን በሚሊዮን የብርሃን አመታት ከእኛ የሚርቁ ከዋክብት አሁን የምናየው መልካቸው ከሚሊዮን አመታት በፊት የነበረ ነው፡፡ ምናልባት በአሁኑ ሰዓት በእድሜ ብዛት ሞተው ወይም ፈንድተው ድምጥማጣቸው ጠፍቶ ሊሆን ይችላል፡፡
https://theconversation.com/when-you-look-up-how-far-back-in-time-do-you-see-101176
በ28 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ጉዞ ወደ ጠፈር
************************
ከአማዞኑ መስራች እና እውቁ የአለማችን ሀብታም ጋር ወደ ጠፈር ጉዞ ለማድረግ ጨረታ ሲካሄድ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ የአለማችን እውቁ ባለሃብት ጄፍ ቤዞስ ከወንድሙ ማርክ ጋር በመሆን የፊታችን ነሐሴ 20 ወደ ጠፈር ለመምጠቅና ለመመለስ አስበው ብዙ ስራዎችን ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በዚህ በረራም አንድ ተጨማሪ ሰው አብሮ እንዲጓዝ በመታሰቡ ከፍተኛ የሆነ ጨረታ ሲካሄድ ነበር፡፡ በጨረታውም አንድ ማንነቱ ያልታወቀና በሚስጢር ሲወዳደር የነበረ ሰው በ28 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ማሸነፍ ችሏል፡፡
የአማዞኑ መስራች ጄፍ ቤዞስ ወደ ህዋ ለመምጠቅ የተነሳው የራሱ ካምፓኒ በሆነው ብሉ ኦሪጅን አማካኝነት በተሰራው ሮኬት ነው፡፡ ጨረታውን ያሸነፈው ተጓዥ በጨረታው 20 የሚደርሱ ተወዳዳሪዎችን ያሸነፈ ሲሆን በአጠቃላይ ሮኬቷ 4 ሰዎችን የምትይዝ ይሆናል፡፡ ሮኬቷ የምትወነጨፍበት ቦታ በበረሃማው የምዕራብ ቴክሳስ ክፍል ሲሆን የምድር ከባቢ አየርና የህዋ መለያ ነው ተብሎ በሚታሰበው ቦታ (የካርማን መስመር) ላይ ለ10 ደቂቃ ያክል አራቱን ተጓዦች ለማቆየት ታስቧል፡፡
በዚህ አመት መጨረሻ ላይ ከአማዞን ሀላፊነቱ ለመልቀቅ እንዳሰበ የተናገረው ጄፍ ቤዞስ በቀጣይ እንደ ብሉ ኦሪጅን ያሉ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ለመስራት እንዳሰበም ተናግሯል፡፡ አክሎም ወደ ህዋ መጓዝ የህይወት ዘመን ህልሙ እንደነበር ገልጧል፡፡ በብሉ ኦሪጅን አማካኝነት የተሰራው ሮኬት ከቴክሳስ ከ10 በላይ የሆኑ ሰው አላባ የተሳኩ ሙከራዎችን ማካሄድ ችሏል፡፡
ምንጭ phys.org
ተጨማሪ ንባብ https://phys.org/news/2021-06-space-jeff-bezos-mn.html
የባርኮድ ቴክኖሎጂ እንዴት ይሰራል
ባርኮድ የተለያዩ ቋሚ መስመሮችን በመጠቀም እቃዎች ላይ የሚታተም፣ ይህም በቀላሉ ስካን መደረግና በኮምፒውተር መነበብ የሚችል እና አንድን እቃ ለመለያነት የሚያገለግል ቴክኖሎጂ ነው። የባርኮድ መሳሪያ ለአጠቃቀም ቀላል፣ ፈጣን፣ ዋጋውም ከሚሰጠው አገልግሎት አንፃር ውድ የማይባል እና የሰዎችን ድካምና ለስህተት የመጋለጥ ችግሮችን የሚቀንስ ቴክኖሎጂ ሲሆን የአሰራር ሂደቱም እንደሚከተለው ነው። የቴክኖሎጂው አሰራር በባርኮድ መፍጠሪያ ወይም (Barcode Generator) የሚጀምር ሲሆን ይህም ወደ ባርኮድ መቀየር የምንፈልገውን ቁጥር፣ ፊደል፣ ቃል ወይም ምስል ወደ ሲስተሙ በማስገባት፤ ይህም የገባውን ፅሁፍ ወደ ተለያየ መጠን ወዳላቸው ቋሚ መስመሮች መቀየር የሚያስችል ነው። ይህንንም ለማንበብ የባርኮድ ማንበቢያ መሳሪያ ይጠቀማል። ባርኮዱ ላይ የሚገኙትን ዘንጎች ንፅፅራዊ ስፋትና ቦታቸውን በመለካት የዘንግ ሞዴሎቹን ተገቢ ወደሆኑ ፊደሎች በመተርጎም ወደ ኮምፒውተሩ ይልካቸዋል።
በመቀጠል በባርኮድ ማንበቢያ ባርኮድን በምናነብበት ጊዜ የምናገኛቸው ፊደሎች ባርኮዱ ላይ ባሉ ሰፊና ጠባብ ዘንግ መሳይ ሞዴሎች ይገለፃሉ። የባርኮድ ማንበቢያ ባርኮዱን በሚያነብበት ጊዜ ፎቶ ሴንሰር (Photo Sensor) በመጠቀም ባርኮዱን ወደ ኤሌክትሪካዊ ሲግናል (Electric Signal) ይቀይረዋል። በመቀጠልም የባርኮድ ማንበቢያው ባርኮዱ ላይ የሚገኙትን ዘንጎች ንፅፅራዊ ስፋትና ቦታቸውን በመለካት የዘንግ ሞዴሎቹን ተገቢ ወደሆኑ ፊደሎች በመተርጎም ወደ ኮምፒውተሩ ይልካቸዋል።
ማንኛውም ባርኮድ የባርኮዱ መጀመሪያ መሆኑን የሚያሳይ ለየት ያለ ዘንግ የሚኖረው ሲሆን፤ እንዲሁም በባርኮዱ መጨረሻ ላይ የባርኮዱ መጨረሻ መሆኑን የሚያመላክት ለየት ያለ ዘንግ ይይዛል። እነዚህ ኮዶች የባርኮድ ማንበቢያው በሚያነብበት ጊዜ ባርኮዱ እያነበበ ያለው ከመጨረሻ ወደ መጀመሪያ ወይም ከመጀመሪያው የባርኮድ ክፍል ወደ መጨረሻው የባርኮድ ክፍል መሆኑን ለይቶ እንዲያውቅ ይረዱታል።
ምንጭ፡ lightspeedhq
ተጨማሪ https://www.lightspeedhq.com/blog/how-do-barcodes-work/