TechIn2
1.17K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
ኢንስቲትዩቱ ለክልል የሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋማት የአቅም ግንባታ ስልጠናን መስጠት ጀመረ
=====================
የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ለክልል የሳይንስ፣ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ተቋማት ያዘጋጀውን የአቅም ግንባታ ስልጠና አና የውይይት መርሃ ግብር በዛሬው ዕለት ጀምሯል፡፡ በወይይቱ መነሻ ስለስልጠናው አስፈላጊነት እና ስለኢንስቲትዩቱ ሃላፊነት ገለፃ በመስጠት መድረኩን የከፈቱት የሴክተር ሞደርናይዜሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰልማን መሃመድ ኢንስቲትዩቱ በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰራቸውን ስራዎች ወደታች ማውረድ እንዲችል ከክልል የሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋማት በጋር መስራት የሚኖረውን ጠቀሜታ አስረድተዋል፡፡
ለሦስት ቀናት ቆይታ በሚኖረው በዚህ የአቅም ግንባታ ስልጠና እና የምክክር መድረክ ላይ ከተለያዩ የክልል ርዕሰ መስተዳደሮች ተወክለው የተገኙት ሃላፊዎችና ባለሙያዎች በክልሎቻቸው የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ያብራሩ ሲሆን ከዚህ በመነሳትም ከኢንስቲትዩቱ ጋር በጋራ በመሆን በትብብር ሊሰሩ በሚችሉባቸው ጉዳዮች እና ትኩረት ሊሰጣቸው በሚያስፈልጉ ሃሳቦች ላይ ምክክር አድርገዋል፡፡
በመድረኩ ላይ ከክልል የተወጣጡ ሃላፊዎች እና ባለሙያዎች ባነሱት ጉዳዮች ላይ ሀሳብ ለመስጠት የሞከሩት የስታርታፕና ኢኖቬሽን ፕሮሞሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በረከት አባይነህ መድረኩ በክልል ተቋማት እየተሰሩ ያሉ ጉዳዮችን በመጠኑም ቢሆን ለመረዳት እና በጋራ ሊሰራባቸው በሚችሉ ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ መረዳት እንዲኖር የሚስችል መድረክ መሆነን ተናግረዋል፡፡ አቶ በረከት በተለይም እንዳነሱት በሚሰሩ ስራዎች ላይ የሚታዩ የተግባር መመሳሰሎችንና ተግዳሮቶችን በመለየት የጋራ ፕሮጀክት ለመቅረፅ እና ወደፊት ሊቀርቡ በሚገቡ የቴክኒክ፣ የሰው ሃይልና የስልጠና መርሃግብሮችን ከወዲሁ ለማዘጋጀት የውይይት መድረኩ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡
ጠዋት ከነበረው የውይይት መርሃ ግብር በመቀጠል ከሰዓት በተካሄደው የስልጠና መርሃ ግብር በእውቀት አስተዳደር ዳሬክቶሬት ውስጥ የቡድን መሪ በሆኑት አቶ ሚኒሊክ አማካኝነት በእውቀት አስተዳደር ጉዳዮች እና ተያያዥ ሀሳቦች ላይ ሳይንሳዊ ማብራሪያ ለታዳሚያን ቀርቧል፡፡ አቶ ሚኒሊክ በገለጻቸው ተቋማት የእውቀት አስተዳደር ስርዓቶችን ለመተግበር በሚያስችሏቸው ጉዳዮች እና ዘርፉ በተለይም ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋማት የሚኖረውን ጠቀሜታ በሰፊው በማንሳት ኢንስቲትዩቱ በተገበራቸው የእቀውቀት አስተዳደር ስርኣቶች ዙሪያ የክልል ተቋማት ሊወስዷቸው የሚችሉ ተሞክሮዎችን አብራርተዋል፡፡
ይህ የስልጠና እና የምክክር መድረክ በቅርቡ በኢንስቲትዩቱ እና በክልል የሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋማት መካከል የተፈጠረውን ስምምነት መነሻ በማድረግ የሚከናወን ሲሆን ተቋማቱ በሚፈልጉት የአቅም ግንባታ ዘርፎች ላይ በነገው ዕለትም በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረቱን አድርጎ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
በገጠር የበይነ-መረብ ግንኙነትን (ኢንተርኔት) ለማሳደግ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ
*************************
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና "ኢንተርኔት ሶሳይቲ" በገጠር የበይነ-መረብ ግንኙነትን (ኢንተርኔት) ለማሳደግ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ።
ስምምነቱ የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት የተጀመረውን ስራ የሚደግፍ፣ በገጠር ጠንካራ የበይነ መረብ ግንኙነትን ለማዳረስ፣ የበይነ መረብ መሰረተ ልማትን ለማስፋፋትና የበይነ መረብ አስተዳደርን ለማሳደግ የሚያስችል ነው ተብሏል።
ስምምነቱን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሐመድ (ፒ ኤች ዲ) እና የኢንተርኔት ሶሳይቲ የአፍሪካ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ዳዊት በቀለ (ፒ ኤች ዲ) ፈርመውታል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሐመድ (ፒ ኤች ዲ) አካታች ብልፅግናን ማረጋግጥን ግቡ አድርጎ የተዘጋጀው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ እውን እንዲሆን መንግስት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የልማት ድርጅቶችና ማህበራት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
ስትራቴጂው መሰረተ ልማቶችን ማሟላት፣ አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር፣ የዲጂታል መተግበሪያዎችን ማልማት እና ምቹ ከባቢያዊ ሁኔታን መፍጠር የሚሉትን ስለማካተቱም አብራርተዋል።
ስምምነቱ ይህንን ወደ ተግባር ለመቀየር የሚደረገውን ጥረት ይደግፋል ብለዋል።
የኢንተርኔት ሶሳይቲ የአፍሪካ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ዳዊት በቀለ (ፒ ኤች ዲ) ስምምነቱ የገጠር የበይነ መረብ ግንኙነትን በማሳደግ በገጠር ያለ ሁሉም ማህበረሰብ በዲጂታል ለውጥ ውስጥ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል ነው ብለዋል።
የኢንተርኔት ሶሳይቲ የዲጂታል የኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ትግበራን ለመደግፍ ቁርጠኛ መሆኑም አረጋግጠዋል።
ስምምነቱ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ቅድሚያ የተሰጣቸውን የግብርና፣ የማምረቻ፣ የአገልግሎትና ቱሪዝም ዘርፍን ለመደገ ያግዛል ተብሏል።
ምንጭ https://www.facebook.com/MInT.Ethiopia
የእናቶችን ድካም የሚያቀለው አዲሱ የእንሰት መፋቂያ ማሽን
---------------------------------------
የእንሰት ተክል አትዮጵያ ውስጥ በብዛት ከሚበቅሉ እና በተፈጥሮ ከታደልንባቸው ውድ ስጦታች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ከ 20 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ የሃገሪቱ ዜጎች መሠረታዊ ምግብ የሆነው ይህ ተክል በብዙ አካባቢዎች ጥያቄ ሆኖ የቀረውን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥም ትልቅ አቅም ያለው ነው፡፡ በደቡባዊ ኢትዮጵያ ከእንሰት ተዘጋጅቶ ለምግብነት የሚዘወተረው የቆጮ ምግብ አመራረቱና አዘገጃጀቱ ለብዙ እናቶች እጅግ አድካሚ እንደሆነ ይነገርለታል።
እንሰትን ለማምረትና ለማዘጋጀት በሚተገበረው ሂደት ዘመናዊ አሰራር ባለመኖሩ እና የአጠቃቀም ስርዓቱ ችግር የማያጣው በመሆኑ ከ24 እስከ 25 በመቶው የእንሰት ምርት ለብክነት የተዳረገ ይሆናል፡፡ ይህ ትልቅ ሃብት የተለያዩ የቴክኖሎጂ አመራጮች እና የአሰራር ስርዓቶች ተግባራዊ የሚደረግብት ከሆነ በአፍሪካ ቀጣናዎችም ይሁን በአለም ገበያ እጀግ ተወዳዳሪ የመሆን አቅም አለው፡፡ ታዲያ ይህን መነሻ በማድረግ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ማኑዩፋክቸሪንግ ፋኩልቲ የበለፀገው የእንሰት መፋቂያ ማሽን ዘመናዊ አሰራር ለመዘርጋት እና የእናቶችን አድካሚ ስራ ለማቅለል ትልቅ እገዛ የሚያደርግ ነው፡፡
አሁን ባለው አሰራር እናቶች አንድ የእንሰት ግንድ ፍቆ ለማጠናቀቅና ወደቀጣዩ ሂደት ለማዘጋጀት እጅግ አድካሚ በሆነ አሰራር ከአንድ ቀን በላይ የሚፈጅባቸው ሲሆን አዲሱ የፈጠራ ስራ ግን ብዛት ያላቸው የእንሰት ግንዶችን በአንድ ቀን ብቻ በቃላሉ ሊያከናውን ይችላል፡፡ በፋኩልቲው የኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ ትምህርት ክፍል የበለፀገው ይህ ማሽን በመጀመሪያ የእንሰት ግንዱን በትንንሹ በመፈልቀቅ እና በማሽኑ ልክ እንዲገባለት የሚያስፈልግ ሲሆን ከዚህ በመቀጠልም የተለያዩ የሜካኒካል ሂደቶችን በማለፍ እንሰቱን የመፋቅ ተግባር ያከናውናል፡፡
ዩኒቨርስቲው በየዓመቱ በሚያዘጋጀው የቴክኖሎጂ ሽግግር ፕሮግራም ላይ እንደእቅድ ተይዞ በትምህርት ክፍሉ ተመራማሪዎችና መምህራን ለውጤት የበቃው ይህ ፈጠራ በቀጣይ ሂደት ከሚኖረው የማሻሻየ ስራ በኋላ ወደ ጅምላ ምርት የሚገባበት እና ወደ ህብረተሰቡ የሚሰራጭበት ሂደት አንደሚኖር ተገልጿል፡፡
ምንጭ፡ ዶቼ ቬለ (DW)
https://fb.watch/61YoseU5QZ/
በነብሳት (ሶስት አጽቄዎች) ቅርጽ የተሰራ የኮምፒውተር ሲስተም
*****************************
ኢንሴክት ኮምፒውተር የተባለ ወረርሽኞች እና የተለያዩ አደጋዎች ከተከሰቱ በኋላ ለሚደረግ የአሰሳ ስራ ተግባር ላይ የሚውል ሲስተም ይፋ ተደረገ፡፡ ከሲንጋፖር፣ ቻይና፣ ጀርመንና እንግሊዝ የተውጣጡ የተመራማሪዎች ቡድን ይህን ልዩ ቴክኖሎጂ ሰርተው እንዳቀረቡ ተነግሯል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች መጠናቸውና ድግግሞሻቸው እጅግ ከፍ እያለ ይገኛል፡፡ በዚህም ምክንያት ተመራማሪዎች በአደጋዎች ለሚጠቁ ሰዎች ድጋፍ ለማድረግና የሞትና የአካል ጉዳት መጠንን ለመቀነስ የተለየ ስልት ያስፈልጋል ብለው ያምናሉ፡፡ እንደ ጎርፍ፣ ገሞራ ፍንዳታ፣ ሰደድ እሳት እና ሌሎች አደጋዎች በሚከሰቱበት ወቅት ሰዎችን በመጠቀም የሚደረገው የድጋፍ እንቅስቃሴ ተጨማሪ አደጋ የሚያመጣ በመሆነ በጣም አነስተኛ መጠን ያላቸው (ልክ እንደ ነብሳት) የቴክኖሎጂ ቁሶችን መጠቀም በጣም አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል፡፡
ተመራማሪዎች በማዳጋስካር የሚገኝን ክንፍ አልባ በረሮ ቅርጽን በሞዴልነት በመውሰድ እና በረሮው ሊሸከመው በሚችለው መልኩ ተዘጋጅቶ አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ በቦታዎቹ በመገኘት ፍለጋዎችንና የተለያዩ መረጃዎችን ማቀበል የሚያስችል ማይክሮ ቴክኖሎጂን ነው ያቀረቡት፡፡ ይህ ቴክኖሎጂም አምስት እርስ በርሳቸው የተገናኙ ሰርኪዩቶች ያሉትና እንደ ካሜራ፣ የግንኙነት ቺፕ፣ የካርቦን ዳይ ኦክሳይድ መለኪያ፣ ሚሞሪ እና ሌሎች አስፈላጊ ቴክኖሎጂዎች የተገጠሙለት ነው፡፡
ይህ አነስተኛ መጠን ያለው የኮምፒውተር ሲስተም በበረሮው ጀርባ ላይ በቀላሉ መቀመጥ እንዲችል ተደርጎ የተሰራ ነው፡፡ በተጨማሪም በረሮው አካባቢውን ለመረዳት የሚጠቀምበትን እንደ አንቴና ያለ ክፍል ላይ ኤሌክትሮድ በማስገባት የበረሮው እንቅስቃሴ በኤሌክርቲክ ሞገድ አማካኝነት በተሸከመው ማይክሮ ቴክኖሎጂ እንዲመራ ማድረግ ተችሏል፡፡
በሙከራ ወቅትም 94 በመቶ የተሳካ የተጎጅዎችን ፍለጋ ማካሄድ ተችሏል፡፡
ምንጭ techxplore
ተጨማሪ ንባብ https://techxplore.com/news/2021-06-insect-computer-hybrid-disasters.html
መቋጫውን ያገኘው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋማት አቅም ግንባታ ስልጠና
======================
በቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ተዘጋጅቶ በአራት የታዳጊ ክልሎች እና የድሬደዋ ከተማ አስተደዳደር ውስጥ ላሉ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ተቋማት ሲሰጥ የቆየው የሦስት ቀናት ስልጠና ዛሬ ተጠናቋል፡፡ በቢሾፍቱ ከተማ ሲሰጥ የቆየው ስልጠናው በስታርታፕ፣ ዲጂታል ተግባራት እንዲሁም የፕሮጀክት አስተዳደርና ሌሎች ጉዳዮችን የዳሰሰ ነበር፡፡
የመሰናዶው መጠናቀቅያ በሆነው የዛሬው ዕለትም በኢንስቲትዩቱ ተመራማሪዎች አማካኝነት ገለፃዎች ሲቀርቡ ቆይተዋል፡፡ የዕለቱን የመጀመሪያ ገለፃ ያቀረበችው ወ/ት አለሜ ወ/ገብርኤል የስታርታፕ ስነ ምህዳርን አስመልክታ በሀሳቡ ምንነት፣ የሚያስገኘው ጥቅም እንዲሁም የመንግስትና ሌሎች ድጋፍ ሰጪ አካላትን ጨምሮ ባለድርሻዎችን የዘረዘረች ሲሆን ከዚህም ባሻገር የህንድ እና ኢስቶኒያን እንቅስቃሴ እንደምሳሌ በማጣቀስ እንዴት ስኬታማ የሆነ የስታርታፕ ስነ ምህዳር መፍጠር እንደሚቻል አስረድታለች፡፡
ሌላኛው የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪ አቶ ሙሉጌታ አንበሴም እንዲሁ በሀገራችን ስታርታፖችን ለማውጣት የራሱን ሚና እንደሚጫወት በሚጠበቀውና ኢንስቲትዩቱ በሚያዘጋጀው የቅድመ ኢንኩቤሽን ፕሮግራም ዙርያ ማብራርያ ሰጥቷል፡፡ በያዝነው ዓመት ብቻ ኢንስቲትዩቱ ሁለት የቅድመ ኢንኩቤሽን ፕሮግራሞችን አዘጋጅቶ እንደነበር ያስረዳው አቶ ሙሉጌታ ፕሮግራሞቹ አንግበው በተነሱባቸው ዓላማዎችና ተጠቃሚ ባደረጓቸው የፈጠራ ባለሙያዎች እንዲሁም በቀጣይነት የኢንኩቤሽን ደረጃ ላይ ሲደረስም በሚኖሩት ሁኔታዎች ላይ ያውጠነጠነ ገለፃን አቅርቧል፡፡ ከዚህም ባለፈ እነዚህን መሰል ፕሮግራሞችን ወደ ክልል ከተሞች ቢስፋፉ ሊኖራቸው ስለሚችለው ጠቀሜታ ተናግሯል፡፡
ሌላኛው የዕለቱ ገለፃ አቅራቢ አቶ ደስታ አበራ በቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ስር ሆኖ የስልጠና እና ድጋፍ ስራዎችን በሚያከናውነው ዳይሬክቶሬት የስራ ክንውኖች ላይ አተኩረው ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡ የስራ ክፍላቸው ከማይክሮሶፍት አፍሪካ፣ ኮይካ፣ ሲስኮ እና ላይት ሃውስ ከተሰኙ የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ከስምምነት በመድረስ የጋራ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ያወሱት አቶ ደስታ በተለይም ከማይክሮሶፍት አፍሪካ ጋር በመተባበር 50 ያህል ሰዎች ጠቃሚ ስልጠናን እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ በዳይሬክቶሬቱ አማካኝነት በአጠቃላይ ከ600 በላይ ሰዎች ስልጠና እንዲያኙ መደረጉንና ከዚህም ባሻገር የፈጠራ ስራዎች ወደ ምርት እንዲያሳድጉ ታስበው ስለተከናወኑ የሰመር ካምፕ ዝግጅቶችንም ለታዳምያኑ አብራርተዋል፡፡
ቀና ብለን ስንመለከት ጊዜን ወደኋላ እየቃኘን ነው
-------------------------------------
ጊዜ ከማይክሮ ሴኮንድ ተነስቶ ሴኮንድ፣ ደቂቃ፣ ሰዓት፣ ቀናት፣ ወራት እና አመታት እያለ ይነጉዳል፡፡ ድምፅና ብርሃን በእነዚህ ጊዚያት ውስጥ ከመንጎድ ይልቅ ይበናሉ፡፡ ድምፅ በየሶስት ሴኮንዱ አንድ ኪሎ ሜተር ያክል የሚጓዝ ሲሆን፤ ብርሃን በበኩሉ በየአንድ ሴኮንዱ 300,000 ኪሎ ሜትር አቋርጦ ይሄዳል፡፡ ብርሀን በህዋ አካለት ውስጥ የመለኪያና የመግባቢያ ቋንቋ በመሆኑ ከምድራችን ውጭ ያሉ አለማትንና ከዋክብትን ለመቃኘት ይረዳናል፡፡ ለምሳሌ የኛዋ ፀሃይ ከመሬት ያላት ርቀት 150 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር በመሆኑ ከሷ የሚመነጨው ብርሃን ወደኛ ለመድረስ 8 ደቂቃዎች ብቻ ያስፈልጉታል፡፡ ይህ ማለት ፀሃይን በተመለከትናት ቁጥር በየስምንት ደቂቃው የሚኖራትን ገፅታ ተመለከትን ማለት ነው፡፡
በአንፃሩ ጨረቃ ከመላው ዩኒቨርስ እጅግ የምትቀርበን አካል በመሆኗ ከፀሃይ የምታገኘውንና ከገጿ ተንፀባርቆ የሚመለሰውን ብርሃኗን ለመመልከት ጥቂት ሰከንዶች ብቻ ያስፈልጉናል፡፡ ይህም ማለት ጨረቃ ከምድር የምትርቅበት መጠን 380,000 ኪ.ሜ በመሆኑ ከሷ የሚነሳ ብርሃን ወደኛ ለመድረስ 1.3 ሰኮንዶች ብቻ ያስፈልጉታል ማለት ነው፡፡ ጨረቃን በየ 1.3 ሰኮንድ ልዩነት ስለምንመለከታት ምንም አይነት ለውጥ አናይባትም፡፡ ይሁንና ከስርዓተ ፀሃያችን ውጭ ያሉ ከዋክበት ወይም ሌሎች የህዋ አካለት የሚያመነጩትን ብርሃን ስንመለከት ጊዜን ወደኋላ እየቃኘን ነው፡፡ ድቅድቅ ባለ ጨለማ ውስጥ ቀና ብለን ከምንመለከታቸው ክዋክብት መካከል አንዳንዶቹ በአሁኑ ጊዜ ህልውናቸው ያከተመ ሊሆን ይችላል፡፡
ለምሳሌ ለእኛ ፕላኔት ቅርቡ የሆነው አልፋ ሴንቸሪ የተሰኘው ኮከብ ከኛ አራት የብርሃን አመታት ይርቃል፡፡ ይህ ማለት ብርሃን በሴከንድ ሶስት መቶ ሺህ ኪሎ ሜትር እየተጓዘ አራት አመታት ያህል የሚወስድበት እርቀት ሲሆን ይህ ርቀት በኪሎ ሜትር ሲለካ ከሰላሳ ስድስት ትሪሊዮን ኪሎ ሜትር በላይ ነው፡፡ ይህ ማለት አሁን የምናየው የኮከቡ ገጽታ አሁን ያለውን መልኩን ሳይሆን ከአራት የብርሃን አመታት በፊት የነበረውን ነው፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው ከኮከቡ የዛሬ አራት አመት በፊት የተነሳው ብርሃን ከርቀቱ የተነሳ እኛ ጋ የደረሰው አሁን በመሆኑ ነው፡፡
አሁን ያለውን የኮከቡን መልክ ለማየት አራት የብርሀን አመታት መጠበቅ አለብን። ምክንያቱም ብርሃኑ ከኮከቡ ዛሬ ቢነሳ እኛ ጋ የሚደርሰው ከአራት የብርሃን አመታት በኋላ ስለሆነ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ለእኛ ቅርቡ የሆነው ኮከብ ያለው ርቀት ሲሆን በሚሊዮን የብርሃን አመታት ከእኛ የሚርቁ ከዋክብት አሁን የምናየው መልካቸው ከሚሊዮን አመታት በፊት የነበረ ነው፡፡ ምናልባት በአሁኑ ሰዓት በእድሜ ብዛት ሞተው ወይም ፈንድተው ድምጥማጣቸው ጠፍቶ ሊሆን ይችላል፡፡
https://theconversation.com/when-you-look-up-how-far-back-in-time-do-you-see-101176