TechIn2
1.17K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
ቴክ-ሳይንስ የቴሌቪዥን ፕሮግራም፤ ዛሬም እንደተለመደው፡-
===================
• በአብይ ፕሮግራም፤ ባዮ ዲዝልን አስመልክቶ በወንዶ ገነት ግብርና ምርምር ስለተሰራው ጥናት
• የተመራማሪዎች ታሪክ፤ ዶ/ር ፍቃዱ ላይ ያተኮረውን ዝግጅት ክፍል ፪
• ተቋማት፤ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ያስገነባውን የዲጂታል ሜዲካል ላይብረሪ
• እንዲሁም በቴክኖሎጂ ታሪክ፤ ስለ ግዙፍ መረጃ ወይም (Big Data) መሰናዶን ያጠናቀርን ሲሆን ብላቴናትም ሰዓቱን ጠብቆ ይቀርባል፡
እርስዎም ዛሬ 10 ሰዓት ላይ የቻናል ምርጫዎን MOE ቴሌቪዥን ላይ በማድረግ ለእራስዎም ሆነ መላው ቤተሰብዎ የሚሆን የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዕውቀትን እንዲሸምቱ ስንጋብዝዎ በደስታ ነው፡፡
በየሳምንቱ ቅዳሜ በ10 ሰዓት እንዲሁም በድጋሚ ማክሰኞ 10 ሰዓት በMOE ቴሌቪዥን ከሚቀርበው በተጨማሪ ወደ ዩትዩብ ቻናላችንም በማቅናት አዳዲስና እስከዛሬ ለተመልካች የደረሱ የቴክ ሳይንስ ፕሮግራሞች አንድም ሳይጎል ማግኘት ይችላሉ (https://www.youtube.com/channel/UC6jvUOLRSkVEQtc5Annfwvg)፡፡
ኒው ዮርክ አቅራብያ ሲዘፍኑ የተገኙት አሳ ነባሪዎች
=======================
ተመራማሪዎች የውሃ ውስጥ መቀረፀ ድምፅ መሳርያዎችን በመጠቀም በተለምዶው የሀምፕባክ ዓሳ ነባሪዎች መራብያ ቦታ ከሆነው የካሪቢያን አካባቢ ርቀው ከበስተ ሰሜን በኒው ዮርክ የባህር ዳርቻዎች አካባቢ ሲያዜሙ የሚያሳይ የመጀመሪያውን ማስረጃ አግኝተዋል፡፡ ምንም እንኳን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሀምፕባክ ዓሳ ነባሪዎችን በአካባቢው መመልከቱ እየተደጋገመ ቢመጣም የእንስሳቱን ድምፅ በማሳየት ረገድ ግን ይህ በማሪን ማማል ሳይንስ ጆርናል ላይ ታትሞ የወጣው ጥናት የመጀመሪያው የተሟላ ጥናት ሆኗል፡፡
ተመራማሪዎቹ ጥናቱን ለማጥናት ከኒው ዮርኳ የሎንግ ደሴት በደቡብ አቅጣጫ 113 ኪ.ሜ ርቆ በሚገኝ የባህር ወለል ላይ በተቀመጡ የውሀ ውስጥ መቀረፀ ድምፆች አማካኝነት የተሰበሰቡና የ6,305 ሰዓታት ርዝማኔ ያላቸው የሀምፕባክ አሳ ነባሪ ድምፆችን በማዳመጥ ተንትነዋል፡፡ ድምፆቹ የተቀዱት ከአስር ዓመታት በፊት በአውሮፓውያኑ 2009 እና 2010 ቢሆንም የሀምፕባክ ዓሳ ነባሪዎችን እንቅስቃሴ ለመመልከት ተብሎ ትንታኔ የተደረባቸው ግን ገና በቅርቡ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም የተከናወኑ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት የሀምፕባክ ዓሳ ነባሪዎች የመራብያ ወቅታቸው መድረሱን እንዲያመላክትላቸው ዜማ ያዜማሉ፡፡ ሆኖም ከወንድም ሆነ ሴት ታዳጊ እንዲሁም ህፃናት የሚነሱ አንዳንድ ድምፆች እንስሳቱ በጋራ በሚሰበሰቡባቸው ጊዜያት የተለያዩ ማህበራዊ ሁናቴዎችን ለማመላከት የሚደረጉም ናቸው፡፡ ታድያ እንደ ተመራማሪዎቹ ሆነ እነዚህ ሀምፕባክ ዓሳ ነባሪዎችን ከመራብያ ወቅታቸውም ሆነ መራብያ አካባብያቸው ርቀው ከወደ ሰሜን ሆነው ሲያዜሙ መገኘታቸው ያልተለመደ ክስተት ነው፡፡ ይህም በተለይ በዓለማችን ካሉ በመርከብ ጉዞ እጅጉን ከሚጨናነቁ ስፍራዎች መካከል በሆነው በዚህ አካባቢ ለሚገኙት ዓሳ ነባሪዎች የበለጠ ጥበቃና እንክብካቤን ለማድረግ ዕድሉን እንደሚሰጥ ተነግሮለታል፡፡
ምንጭ፤ Independent
ለተጨማሪ፤ https://www.independent.co.uk/.../new-york-humpback...
በክብደት መጨመር ለተቸገሩ ሰዎች ከFDA አዲስ መድሃኒት
*********************************
የአሜሪካው የምግብና መድሃኒት አስተዳደር የሆነው FDA ለመጀመሪያ ጊዜ ክብደትን ለመቀነስ የሚያስችል መድሃኒትን ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቃድ ሰጠ፡፡ ይህ ከፍኛ ለውጥ ያመጣል የተባለለት መድሃኒት ዌጎቪ የተሰኘ ሲሆን የደኒሽ መድሀኒት ማምረቻ ኩባንያ የሆነው ኖቮ ኖርዲስ ምርት ነው፡፡ ይህም ከ2014 በኋላ በፌዳ እውቅና የተሰጠው ብቸኛው መድሃኒት ሆኗል፡፡
ስማግልቲዩድ የተሰኘ ተመሳሳይ መድሃኒት በአሜሪካ ለዘመናት ጸረ ዲያቤቲክ ህክምና ላይ አገልግሎት እየተጠ የነበረ ቢሆንም ይኸው መድሃኒት ከፍ ባለ መጠን ሲወሰድ ከምግብ ፍላጎት ጋር ለተያያዘ ችግር መፍትሔ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ዌጎቪ ስለ ተሰኘው መድሃኒት የወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው 2000 የሚደርሱ ከፍተኛ ውፍረት ያላቸው ሰዎች እንዲወስዱት ተደርጎ ከ15 በመቶ በላይ ክብደታቸውን መቀነስ መቻላቸውን አሳውቋል፡፡
ይህ መድሃኒትም ሰዎች ክብደታቸውን ለመቀነስ የሚያደርጉትን ቀዶ ህክምና በማስቀረት በመድሃኒት ብቻ መፍትሔ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል፡፡ ኖቮ ኖርዲስክ እስካሁን የመድሃኒቱን ዋጋ ይፋ ባያደርግም በወር 1300 የአሜሪካን ዶላር ሊያስከፍል ይችላል የሚሉ መረጃዎች እየተሰሙ ናቸው፡፡
ምንጭ sciencealert
ተጨማሪ ንባብ https://www.sciencealert.com/game-changer-treatment-is-first-new-weight-loss-drug-approved-by-the-fda-in-years?utm_medium=Social&utm_source=Facebook&fbclid=IwAR3rc6NU9Rs-xGK706QGwS7DyrOsCX72tBXiuHegad_PM42tiQKRPANycNk#Echobox=1623035219
በዓለማችን የውሃ አካላት የሚገኘው ኦክስጅን እያሽቆለቆለ ነው
=======================
የዓለማችን ሀይቅ እና ውቅያኖሶች በሟሟ ኦክስጅን (O2) የተሞሉ መሆናቸውና የውሀ ውስጥ እንስሳትም ይህን ተጠቅመው እንደሚተነፍሱ ይታወቃል፡፡ ሆኖም በኔቸር ጆርናል ላይ የወጣ አዲስ ጥናት እንደሚያመላክተው የሙቀት መጠኑ እንደየወቅቱ በሚቀያየርባቸው ሀይቆች (temperate lakes) ውስጥ የሚገኘው የኦክስጅን መጠን በፍጥነት እያሽቆለቆለ መሆኑን ነው፡፡
የተመራማሪዎች ቡድኑ በመላው ዓለም ባሉ 393 መሰል ሀይቆች ውስጥ ከአውሮፓውያኑ 1941 እስከ 2017 ያለውን ከ45 ሺህ በላይ የሟሙ ኦክስጅኖች ሁኔታን መርምሯል፡፡ በውጤቱም ከአውሮፓውያኑ 1980 በኋላ ብቻ በገፀ-ምድር የውሀ አካላት ውስጥ የሚገኘው የሟሟ ኦክስጅን በ5.5 በመቶ የወረደ ሲሆን ጠለቅ ባሉ የውሀ አካላት የሚገኘው ደግሞ በ18.6 በመቶ አሽቆልቁሏል፡፡
ከውቅያኖሶች ጋር ሲነፃፀር ሀይቆች ከ2.75 እስከ 9.3 እጥፍ በላቀ ፍጥነት ኦክስጅናቸውን እያጡ ነው ያሉት የጥናቱ ዋና ፀሀፊ ፕ/ር ኬቨን ሮስ ይህ የኦክስጅን ማሽቆልቆልም የባህር ውስጥ እንስሳት ዝርያዎችን ለመመናመን ስነ-ምህዳሩንም ለመዛባት የሚዳርግ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡
ለዚህ የኦክስጅን ማጣት ምክንያት ተደርጎ የተቀመጠው የገፀ-ምድር የውሀ አካላት ሙቀት በ0.38 ዲ.ሴ መጨመሩ ነው፡፡ ውሃ ሙቀት በውስጡ ሲበዛበት መያዝ የሚችለው የኦክስጅን መጠን የሚቀንስ መሆኑ ለዚህ ጥፋት መንስኤ ሆኗል፡፡ ሆኖም ጥልቅ የውሃ አካላት ያላቸው ሙቀት ባለፉት አራት አስርት ዓመታት ውስጥ ብዙም ለውጥን ያስተናገደ አልነበረም፡፡ ታድያ በነዚህ የውሃ አካላት ላይ የታየው የኦክስጅን መጠን መሳሳት በገፀ ምድር ውሃው ገፅ ላይ ያለው ሙቀት እየጨመረ መምጣቱ አነስተኛ እና ከፍተኛ ጥልቀት ባላቸው የውሀ አካላት መካከል ያለውን የእፍጋት መጠን ልዩነት በመጨመር ኦክስጅንን እንዳይቀላቀሉና ወደ ጥልቅ ውሃ መድረስ የሚችለው ኦክስጅንም እያነሰ እንዲመጣ አደርጎታል፡፡ ይህ አይነት የእፍጋት ልዩነት ከከባቢ አየር የሚገኘውን ኦክስጅን በጥልቅ ውሀ አካላት ላይ ማቀላቀልን አስቸጋሪ ስለሚያደርገው በዚያ ያለው የሟሟ ውሃ እንዲቀንስ ማድረጉን ኬቨን ሮስ ይናገራሉ፡፡
ሆኖም ይህ የኦክስጅን መጠን ማሽቆልቆል በሁሉም የዓለማችን ሃይቆች ላይ የሚስተዋል አይደለም፡፡ እንደውም በአንዳንድ አካባቢዎች የሙቀት መጠኑ እየጨመረ ሳለ እንኳን የኦክስጅ መጠኑ ከማሽቆልቆል ይልቅ ሲጨምር ተስተውሏል፡፡ ይህም ምናልባት በንጥረ ነገሮች ብክለት ሳብያ የመጣ ኦክስጅን አምራች ባክቴሪያ የሆኑት ሳያኖባክቴሪያዎች እንዲያብቡ ከማድረግ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል በተመራማሪዎቹ ተነግሯል፡፡
የዚህ ጥናት ውጤት በዓለማችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ለመጣው የዓለም ሙቀት መጨመር አንድ ማሳያ ሆኖ ቀርቧል፡፡
ምንጭ፤ Cosmos
ለተጨማሪ፤ https://cosmosmagazine.com/earth/water/oxygen-declining-in-the-worlds-lakes/?utm_content=buffere3bdf&utm_medium=social&utm_source=twitter.com&utm_campaign=buffer
በኤፍዲኤ እውቅና የተሰጠው የአልዛይመር መድሃኒት
**************************
የምግብና መድሃኒት አስተዳደር ተቋሙ (FDA) ከሁለት አስርት አመታት በኋላ አልዛይመር ለተሰኘው በሽታ መድሃኒትን ፈቃድ መስጠቱን አሳወቀ፡፡ በገበያ ስሙ አዱሄልም የሚባለው aducanumab በሰዎች ጭንቅላት ውስጥ የሚፈጠርን የመርሳት ችግር ለመቅረፍ ጥቅም ላይ የሚውል የመድሃኒት አይነት ነው፡፡ ተመራማሪዎች እንደሚናገሩት በጭንቅላት ውስጥ የሚፈጠሩ ጥቃቅን ነገሮች የጭንቅላት ህዋሳትን እንዲሞቱ በማድረግ ለአልዛይመር በሽታ መንስኤ የሚሆኑ የትውስታ መጥፋቶች እንዲከሰቱ ያደርጋሉ፡፡
በክሊኒካዊ ሙከራ ጊዜ መድሃኒቱ ለጭንቅላት ህዋሳት መሞት ምክንያት የሆኑ ንጥረ ነገሮችን በእጅጉ መቀነስ የቻለ ሲሆን የትውስታ መመለስን ግን እንዳላመጣ ተመራማሪዎቹ አሳውቀዋል፡፡ ከዚህም በኋላ መድሃኒቱ ፈቃድ ይሰጠው ወይስ አይሰጠው በሚለው ሃሳብ ዙሪያ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉባቸው ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡ በተካሄዱ ውይይቶችና በተሰሩ ዳሰሳዎች አዱሄልም የተሰኘው መድሃኒት በአልዛይመር ህመምተኞች ላይ ከሚያመጣው ጉዳት ይልቅ የሚሰጠው ጥቅም እንደሚበልጥ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
በአሜሪካ ብቻ በተሰራ ዳሰሳ ጥናት 6 ሚሊዮን የሚጠጉ የአልዛይመር ህመም ተጠቂዎች ይገኛሉ፡፡ የመድሃኒቱ አምራች የሆነው ባዩጂን መድሃኒቱን ለማምረት ከ2 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ በጀት መጠቀሙን አሳውቋል፡፡ አንዳንድ የምጣኔ ሀብት ተንታኞች መድሃኒቱ ለአምራቹ በአመት ውስጥ ከ10 እስከ 12 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሊያስገኝለት እንደሚችል ያላቸውን ግምት አስቀምጠዋል፡፡
ምንጭ sciencealert
ተጨማሪ ንባብ https://www.sciencealert.com/the-fda-just-approved-the-first-new-alzheimer-s-drug-in-18-years-but-not-everyone-is-impressed?utm_term=Autofeed&utm_medium=Social&utm_source=Facebook&fbclid=IwAR0WdfObS3MDWphET4E84u8TIY_MsPC2g-w7OIrJSZ2lMgR8fTkHg2g1WtI#Echobox=1623111891
ትልልቅ አለም አቀፍ ድረ-ገፆች ለሰዓታት ተቋርጠው እንደነበር ተገለፀ
========================
እንደፋይናንሺያል ታይምስ፣ አማዞን፣ ዘ ጋርዲያን እና ኒው ዮርክ ታይምስ ያሉ ትልልቅ አለም አቀፍ ድረ ገፆች ከአንድ ሰዓት በላይ ተቋርጠው እንደነበር እና ኋላ ላይ በተደረገላቻው ማስተካከያ ወደስራ መመለሳቸው ተነግሯል፡፡ አብዛኞቹ ድረ ገፆች ለሰዓታት Error 503 Service Unavailable የተሰኘ መልክት ሲታይባቸው መቆየቱን ያስታወቀው ቢቢሲ አገልግሎቱ የተቋረጠበት ምክንያትም ለብዙዎቹ ድረ ገፆች የክላዉድ ኮምፒዩቲንግ አገልግሎት የሚያቀርበው ፋስትሊ ላይ በተፈጠረ ችግር መሆንን አስታውቋል፡፡
ፋስትሊ የተባለው የቴክኖሎጂ ኩባንያ ድረ ገፆች ለሰዓታት ተቋርጠው በነበረበት ጊዜ እንደገለፀው ዓለም አቀፍ የይዘት አቅርቦት አውታረ መረብ (CDN) ላይ በተፈጠረ ችግር የተከሰተ መሆኑን እና አሱንም ለማስተካከል ሲሰራ እንደቆየ አስታውቋል፡፡ ከአንድ ሰኣት ለበለጠ ጊዜ ትልልቅ የሚባሉ ድረ-ገፆች እንዲቋረጡ ምክንያት የሆነው (CDN) በበይነ-መረብ ስርዓት ውስጥ ዋና አካል የሚባል ሲሆን ኢንተርኔት በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዲሰራም ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡
ጉዳዩ በተከሰተበት ሰኣት በዙ የሳይበር ባለሙያዎች እንደጠቀሱት ብዛት ያላቸው የበይነ-መረብ መሠረተ ልማቶች በጥቂት የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ቁጥጥር ውስጥ መግባታቸው አንድ ችግር በተፈጠረ ቁጥር ትልቅ አደጋ እንዲከተል እና በጅምላ የመቋረጥ ስጋት እንዲኖር ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡
ጄክ ሞር የተባለ አንድ የሳይበር ባለሙያ በተለይም እንደገለፀው ትልልቅ በሚባሉት አለም አቀፍ ድረ-ገፆች ላይ ለሰዓታት የተከሰተው ይህ ችግር ብዛት ያላቸው የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በበይነ-መረብ መሠረተ ልማት ግንበታዎች ላይ በይበልጥ መሳተፍ እንዳለባቸው እና ውክልናቸውም የግድ አስፈላጊ እንደሚሆን ያመላከተ ነው ብሏል፡፡
ምንጭ፡ ቢቢሲ
ለተጨማሪ https://www.bbc.com/news/technology-57399628
ፍላጎታችንን ከአእምሯችን መገመት የሚችሉ ኮምፒውተሮች
***********************
የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ የተጠቃሚዎችን ፍላጎት ከተጠቃሚው አእምሮ መረዳት የሚያችል ደረጃ ላይ መድረሱ ተነገረ፡፡ በኮፕንሃገንና ሄልሲንኪ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በተሰራ ጥናት የግለሰቦችን ምርጫና ፍላጎት ከሌሎች ሰዎች እሳቤ ጋር የሚኖረውን ዝምድና በመጠቀም በኮምፒውተር አማካኝነት ማወቅ እንደሚቻል አሳይተዋል፡፡
ይህ ቴክኖሎጂ ሰዎች ስለራሳቸው ያላቸውን እውቀት እንደሚጨምርላቸው ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል፡፡ ብዙውን ጊዜ በኦን ላይን ስራዎችን በምንሰራበት ጊዜ በብዛት የምንጎበኛቸውን ምንጮችና ፍላጎቶቻችንን መሰረት ያደረጉ የተለያዩ አማራጮች በኮምፒውተራችን አማካኝነት ይቀርቡልናል፡፡ ይህኛው ቴክኖሎጂ ግን ከዚህ በፊት የነበረንን ፍላጎት ሳይሆን አሁን ላይ እያሰብን ያለውን ከአእምሯችን መረዳት የሚችል ነው፡፡
ይህ ኮላቦሬቲቭ ፊልተሪንግ የተሰኘ ስልት ባህሪያችንን የሚያጠናና የምንሰራውን ስራ ከሌሎች ሰዎች ጋር በማነጻጸር በብዛት ፍላጎት የምናሳይባቸውን ነገሮች መረዳት የሚችል ነው፡፡ ይሁን እንጂ ተመራማሪዎቹ የዚህ ግምት ምንጩ የሰዎችን ባህሪ በመረዳት ብቻ አይሆንም የሚል ሀሳብን እያሰሙ ነው፡፡ ለዚህም ቴክኖሎጂው ከሰዎች ባህሪ ሳይሆን ከሰዎች አእምሮ ነገሮችን መረዳት ይችላል የሚል የሳይንስ ልቦለድ የሚመስል መከራከሪያን አቅርበዋል፡፡
ይህ ኮምፒውተር ሳይንስንና ኮግኒቲቭ ኒውሮ-ሳይንስን በማቀናጀት የሚሰራው ፕሮጀክት አእምሮን መሰረት ያደረገ ኮላቦሬቲቭ ፊልተሪንግ እውን እንደሆነ አሳይቷል፡፡ ይህንንም ለማድረግ የአንድን ሰው የአእምሮ ምላሽ የመስጠት ውቅር (patterns) ከሌሎች ሰዎች ጋር የማነጻጸር ስራ እንደሚሰራ ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
ምንጭ techxplore
ተጨማሪ ንባብ https://techxplore.com/news/2021-06-brain.html
የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ለክልል የሳይንስ፣ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ተቋማት ያዘጋጀውን ለሦስት ቀን የሚቆይ የአቅም ግንባታ ስልጠና እና የምክክር መድረክ በዛሬው እለት በቢሾፍቱ ከተማ በሚገኘው የጎልድማርክ ሆቴል በመስጠት ላይ ይገኛል።
ናይጄሪያ ሚዲያዎቿ ቲውተርን እንዳይጠቀሙ ከለከለች
*******************************
ናይጀሪያ ሁሉም የቴሌቪዥንና ራዲዮ ጣቢያዎች ቲውተር የተሰኘውን ማህበራዊ ሚዲያ በፍጹም እንዳይጠቀሙ አግዳለች፡፡ ይህም የሆነው የናይጀሪያው ፕሬዘዳንት ሞሃመድ ቡሃሪ ናይጀሪያን ለመከፋፈል የሚጥሩ ቡድኖችን ለመቅጣት እንደተዘጋጁ የሚገልጽን ጽሁፍ በቲውተር ገጻቸው ቢያሰፍሩም ቲውተር ግን መልእክቱን በማጥፋቱ ነው፡፡
የብሮድካስት ጣቢያዎች የሚጠቀሟቸውን የቲውተር መተግበሪያዎችና ማስፈንጠሪያ ሊንኮች አገልግሎት እንዲያቋርጡ በናይጀሪያ መንግስት ትእዛዝ ተላልፎባቸዋል፡፡ በመሆኑም የናይጀሪያ የሚዲያ ተቋማት ቲውተርን እንደ መረጃ ምንጫቸው መጠቀም አይችሉም፡፡ ይህንንም ማድረግ ናይጀሪያን ከሚወድና አንድነቷን ከሚፈልግ የሚዲያ ተቋም የማይጠበቅ እንደሆነ የ NBC ዳይሬክተር የሆኑት አርምስትሮንግ ኢድቻባ ተናግረዋል፡፡
ቲውተርም ጉዳዩን ትኩረት ሰጥቶ እየተሰራበት እንደሆነና ተጠቃሚዎች የሚፈልጓቸውን መረጃዎች እንደገና ለመመለስ ማሰቡን አሳውቋል፡፡ በናይጀሪያ 39 ሚሊዮን የሚደርሱ የቲውተር ተጠቃሚዎች እንዳሉ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ የናይጀሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከክስተቱ በኋላ የውጭ ሀገር ዲፕሎማቶችን በናይጀሪያ አቡጃ ሰብስቦ ያወያየ ሲሆን የአውሮፓ ህብረት፣ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ካናዳና አይርላንድ ተወካዮች የመረጃ ምጭን ሙሉ ለሙሉ ማቋረጥ መፍትሄ ሊሆን እንደማይችል ሀሳባቸውን መስጠታቸውን የመረጃ ምጫችን አስነብቧል፡፡
ምንጭ CGTN Africa
ተጨማሪ ንባብ https://africa.cgtn.com/
2021/06/07/nigeria-directs-broadcasters-to-delete-twitter/