TechIn2
1.17K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
በኢትዮጵያ የሚገነባው የባቡር አካዳሚ
====================
በሚቀጥሉት ዓመታት የመገንባት እቅድ ለተያዘላቸው እና በስራ ላይ ለሚገኙት የባቡር ፕሮጀክቶች በቂ የሰው ኃይል ማፍራት የሚያስችል የባቡር አካዳሚ እየተገነባ መሆኑን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አስታወቋል፡፡ ከኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ ጋር ቆይታ የነበራቸው የኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ ሃላፊ አቶ በሃይሉ ስንታየሁ ኢትዮጵያ በባቡር ግንባታ ዘርፍ አሁንና ወደፊት ለሚኖራት ሰፋፊ እቅዶች ከዘመኑ የቴክኖሎጂ አቅም ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችል የሰለጠነ የሰው ሃይል ለማፍራት ያስቸላት ዘንድ ይህ የባቡር አካዳሚ ግንባት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በቢሾፍቱ ከተማ ሚገነባው ይህ የማሰልጠኛ ተቋም ኢትዮጵያ በዘርፉ ያለባትን የባለሙያዎች እጥረት ለመፍታት እና ከዚህ በኋላ ሊሰሩ እቅድ ለተያዘላቸው ግዙፍ የባቡር ፕሮጀክቶች ክህሎታቸው የተረጋገጠ ኤክስፐርቶችን ለማውጣት የሚያስችል ነው፡፡ ለስልጠና ማዕከሉ ግንባታ ዝግጅት እየተደረገ ሲሆን ለዚህም ከዓለም ባንክ እና ከቻይና መንግስት ብድር የተገኘ መሆኑን አቶ በሃይሉ አብራርተዋል፡፡
የባቡር አካዳሚው ሥራ በሚጀምርበት ወቅት በርካታ ባለሙያዎችን በማፍራት ለባቡር ትራንስፖርቱ የሚያስፈልገውን የሠለጠነ የሰው ኃይል ፍላጎት ለማሟላት ከማገዝ ባሻገር፣ ከኢትዮጵያ የውጭ ባለሙያዎችን በመላክ ለማሠልጠን የሚወጣውን ወጪ ለማስቀረት የጎላ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡ በኢትየጵያ እንዲህ ያሉ የማስልጠኛ ተቋማትን የመመስረት እቅድ በየጊዜው ሲንከባለል የቆየ ቢሆንም በፊት ከነበሩ ልምዶች ተነስቶ አሁን ላይ እውን ሊሆን የተቃረበው ይህ የአካዳሚ ምስረታ የኢትዮጵያን የባቡር ኢንዱስትሪ በእጅጉ እንደሚያሰድገው ይታሰባል፡፡
በክህሎት እጥረት ሳቢያ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ አገራት የባቡር ሶፍትዌር መሐንዲሶችን፣ የኃይል አቅርቦትን፣ የአሠራር ጥገናን፣ ግንባታን እና ሌሎች ባለሙያዎችን ከምዕራቡ ዓለም ሲያስገቡ መቆየታቸውን የሚያነሱት አቶ በሃይሉ የአካዳሚው ግንባታ የአገር ውስጥ ባለሙያዎችን አቅም በሁሉም ዘርፍ ለማጎልበት ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡
ምንጭ፡ Ethiopian Press Agency
https://www.press.et/english/?p=35712#
ለመጀመሪያ ጊዜ ያለ ሰው ትዕዛዝ ግድያ የፈፀመው ድሮን
=======================
ባሳለፍነው የአውሮፓውያን ዓመት 2020 አንድ መሳርያን የታጠቀ ራስ-ገዝ ድሮን ሊቢያ ውስጥ ያለ ማንም ትዕዛዝ ሰዎችን አድኖ መግደሉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ፡፡ ድርጅቱ በሪፖርቱ እንዳስታወቀው ካርጉ-2 የተሰኘው ቱርክ ሰራሽ ባለ 4 ሽክርክር ድሮን በሊቢያ መንግስታዊ ኃይሎችና ከእነርሱ ተገንጥለው በመውጣት በሊቢያ ብሔራዊ ጦር አዛዡ ካሊፋ ሀፍታር በሚመራው ክንፍ መካከል በተፈጠረው ግጭት ላይ ነው የአጥፍቶ መጥፋት ስራን እንዲሰራ ሁለት ፈንጂዎችን ታጥቆ የተሰማራው፡፡
በወርሀ መጋቢት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፀጥታው ምክር ቤት ባለሙያዎች መድረክ ላይ የቀረበው ሪፖርቱ በኒው ሳይንቲስት መፅሔት አማካኝነት ነው ለህዝብ ይፋ የሆነው፡፡ አንደኛው የሪፖርቱ ክፍልም ካሊፋ ሀፍታር በሽሽት ላይ ሳሉ እንዴት እጅግ ውጤታማ በሆነ መልኩ ያለ ማንም ትዕዛዝ ሲንቀሳቀሱ በነበሩት የካግሩ-2 ድሮኖች ሲታደኑ እንደነበር ያመላክታል፡፡ ራስ-ገዝ ድሮኖቹ የተገጠመላቸው ስርዓት ከትእዛዝ ሰጪዎች ጋር ምንም ዓይነት በይነ-መረባዊ ግንኙነት ሳያስፈልጋቸው በራሳቸው ተነሳሽነት ኢላማውን ፈልጎ ጥቃት መሰንዘር የሚያስችለው መሆኑም ተነግሯል፡፡
በአንድ የአሜሪካን ፀረ-ሽብር ምርምር ላይ በተሰማራ ተቋም ውስጥ የሚሰራው ዛክ ካለንቦርን እንደሚለው ከሆነ ይህ ጥቃት ምናልባትም ያለ ሰው ትእዛዝ የተፈፀመ የመጀመሪያው ራስ ገዝ የድሮን ጥቃት ነው፡፡ ይህም በተለይ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ስርዓቶች የሚመለከቱትን ነገር ሁሉ በትክክል ለመተርጎም ካለመቻላቸው ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ስጋትን የሚጭር ጉዳይ መሆኑን ገልጿል፡፡ እንግሊዛዊው የውትድርና ምሁር ጃክ ዋትሊንግ በበኩሉ ድሮኖቹ ይህን ጥቃት ሲፈፅሙ በርቀት ቁጥጥር እየተደረገባቸው ይሁን አይሁን የሚያውቁት ድሮኖቹን ሲቆጣጠሩ የነበሩት ሰዎች መሆናቸውን ገልፆ ይህ ራስ-ገዝ የጦር መሳርያዎችን ለመቆጣጠር የማይቻል መሆኑን አያሳይም ሲል ይናገራል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ቴክኖሎጂው ቆሞ የሚጠብቀን ስላልሆነ በፍጥነት ውይይት ሊደረግበት እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
በዚህ ከሰው ቁጥጥር ውጪ ነበር በተባለለት ጥቃት ምን ያህል ሰዎች ስለመሞታቸው የሚያሳይ መረጃ አልተገኘም፡፡
ምንጭ፤ Daily Star
ለተጨማሪ፤ https://www.dailystar.co.uk/news/world-news/killer-ai-drones-hunted-down-24203431
በማርስ ሰማይ ላይ የታየው ብሩህ ደመና
*************************
ናሳ አነስተኛ የቅኝት ሄሊኮፍተርን ወደ ማርስ ከላከ ወዲህ የተለያዩ አዳዲስ ነገሮችን እያሰማን ይገኛል፡፡ በአሁኑ ደግሞ ያልተለመደ እና ሚስጢራዊ የሆነ ብሩህ ደመናን በማርስ ከባቢ አየር ውስጥ ሲርመሰመስ የሚያሳይ መረጃን አቅርቧል፡፡ ይህ በማርስ ከባቢ አየር ውስጥ የታየው ብሩህና ነጣ ያለ ደመና የናሳ ተመራማሪዎችን ሳይቀር እጅግ አስደንቋቸዋል፡፡
ከምድር አንጻር ሲታይ ደመናን በማርስ ሰማይ ውስጥ መመልከት በጣም ያልተለመደ ነው፡፡ ቀዩዋ ፕላኔት ስስና ደረቅ ከባቢ አየር ያላት በመሆኑ አልፎ አልፎ ደመና መታየቱ ግን ተለምዷል፡፡ እንደ ህዋ ምርምር ተቋሙ መረጃ ከሆነ ኪሪዮሲቲ የተሰኘውን ሮቨር በመጠቀም በተለያዩ ጊዜያት ያልተለመዱ የደመና አፈጣጠር ክስተቶችን በማርስ ሰማይ ላይ ማስተዋል ተችሏል፡፡ የምርምር ተቋሙ በማርስ ውስጥ ደመናማ ቀናት የሚስተዋሉት በማእከላዊው የፕላኔቷ አካባቢ እና በቀዝቃዛማው የፕላኔቷ ወቅት ነው፡፡
ለወትሮው ማርስ ከፀሐይ እጅግ በምትርቅበት ወቅት ይፈጠር የነበረው ደመና ከሁለት አመታት ወዲህ ባልተለመደ መልኩ ቀድሞ መፈጠር ጀምሯል፡፡ በማርስ ከባቢ አየር ውስጥ የሚፈጠር ደመና አብዛኛውን ጊዜ በረዷማ ውሃ የፀሐይ ብርሃን ጋር ሲያገኝ የሚፈጠር ሲሆን አሁን ላይ እየተስተዋለ ያለው ደመና ግን በዚህ መንገድ የተፈጠረ ላይሆን እንደሚችል የናሳ ተመራማሪዎች ይፋ አድገዋል፡፡
በበረዷማ ውሃ አማካኝነት ይፈጠራል ተብሎ የሚታሰበው የማርስ መደበኛ ደመና በ60 ኪሎሜትር ከፍታ ላይ የሚገኝ ሲሆን አሁን ላይ በኪዩሮሲቲ አማካኝነት የታየው ደመና ግን ከዚህ ላቅ ባለ ከፍታ ውስጥ የተስተዋለ እና ከገገረ ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ የተፈጠረ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡ ይሁን እንጂ ተጨማሪ ጥናቶች እንደሚያስፈልጉት የህዋ ምርምር ተቋሙ አልሸሸገም፡፡
ምንጭ
ተጨማሪ ንባብ https://www.sciencealert.com/mysterious-shining-clouds-seen-above-mars-are-both-beautiful-and-unusual?utm_term=Autofeed&utm_medium=Social&utm_source=Facebook&fbclid=IwAR2WWYtxjo5Fekvj79OH7mMYZwklXsEI8Mi7FOEvuU5nfm_G85-OTMU5tSQ#Echobox=1622495369
በዩጋንዳ የሞተርሳይክል ራይድ አገልግሎትን እያስፋፋ ያለው ተቋም
======================
በሀገራችን ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሞተረኞች ቁጥር በእጅጉ አድጎ እናገኘዋለን፡፡ ምንም እንኳን ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ምጣኔ-ሐብታዊ ጠቀሜታው ባይካድም ከተለያዩ አሉታዊ ጉዳዮች ጋር ስሙ ሲያያዝ ይታያል፤ መንግስትም ይህን ይቀርፋሉ ያላቸውን እርምጃዎች ሲወስድ ቆይቷል፡፡ ታድያ በዚህ ረገድ በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚችል አንድ የዩጋንዳ የሞተር ሳይክል ራይድ አገልግሎት ሰጪ ኩባንያን ለመመልከት ወደድን፡፡
ከዩጋንዳ እስከ ኬንያ በድንበር አልባነት የሚዘዋወሩትና በሀገሬው ዘንድ ቦዳ ቦዳ ወይም ከድንበር እስከ ድንበር በሚል ስያሜ የሚታወቁት የሞተርሳይክል ታክሲዎች ለሀገረ ዩጋንዳ መዲና ካምፓላ የደም ስሯ ናቸው፡፡ የታክሲ አገልግሎቱን የሚሰጡት 150 ሺህ የሚደርሱ ሞተር ሳይክሎች ሀገሪቱ በተለይ በመሰረተ-ልማት እና ብዙሀን ትራንስፖርት ረገድ ያለባትን ክፍተት የመሙላት ትልቅ ሚናን በመጫወት ላይ ይገኛሉ፡፡ ታድያ ሞተር ሳይክሎቹ ያን ያህልም ደህንነታቸው የተጠበቀ ካለመሆናቸውም ባሻገር ለቁጥጥር አዳጋች መሆናቸው ባይደበቅም በዋጋቸው ርካሽ እና ለወጣቶችም የስራ ምንጭ ሆነዋል፡፡
በነዚህ የሞተርሳይክል ታክሲዎች የስራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች መካከል ሪኪ ራፓ አንዱ ነው፡፡ ጓደኛውን በትራፊክ አደጋ እስከሚያጣ ድረስ ሂልሜት ማድረግን አያዘወትር ነበረው ሪኪ የጓደኛውን ሞት ተከትሎ ጥንቃቄውን በመጨመር ብቻ ሳያበቃ መቀመጫቸውን እዚሁ አህጉረ አፍሪካ ውስጥ ካደረጉት ሁለት የቴክኖሎጂ ስራ ፈጣሪዎች ማክሲም ዲዩዶን እና አላስታር ሳሲክ ጋር በመሆን ሴፍቦዳ የተባለውን የሞተርሳይክል ራይድ ኩባንያ አቋቋመ፡፡ አሁን ላይ የአራት ሚሊዮን ነዋሪዎች ቤት በሆነችው ካምፓላ ውስጥ 1.5 ሚሊዮን ያህል ጊዜ ዳውንሎድ የተደረገው መተግበሪያው ከአውሮፓውያኑ 2017 አንስቶ 35 ሚሊዮን ያህል የራይድ ጉዞዎችን በ22 ሺህ የሞተርሳይክል አሽከርካሪዎች አማካኝነት እንዲከወን ማድረግ ችሏል፡፡ ይህም መተግበሪያውን ዩጋንዳ ውስጥ የራይድ አገልግሎት ከሚሰጡ ተቋማት ሁሉ ቀዳሚው ያደርገዋል፡፡
ደንበኞች ለአገልግሎቱ የሚያቀርቡት ክፍያ ሙሉ በሙሉ በሞባይል የገንዘብ ዝውውር አማካኝነት የሚፈፀሙ ሲሆኑ ኩባንያውም በመተግበሪያው አማካኝነት እያንዳንዱ አሽከርካሪ የራይድ አገልግሎት ሰጥቶ በአማካኝ ከሚያገኘው የ1.12 ዶላር ገቢ ላይ 10 በመቶውን ይወስዳል፡፡ ይህም መልስ ለመስጠት የሚኖረውን ውጣ ውረድ ከማስቀረትም ባሻገር ጉቦ ጠያቂ ትራፊክ ፖሊሶችንንም በእጅጉ መቀነስ ችሏል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ሞተር ሳይክሎች እዚህም እዚያም ውር ውር በሚሉባት ካምፓላ ከሴፍቦዳ ራይድ አገልግሎት ጋር የሚሰሩ ሞተረኞችን መለየቱ አስቸጋሪ አይደለም፤ ሂልሜት ያደርጋሉ፣ የትራፊክ መብራቶችን ያከብራሉ፣ ለትራፊክ ፖሊሶችም ታዛኝ ናቸው፡፡ ይህም ይሆን ዘንድ እያንዳንዳቸው የሴፍቦዳ ሞተረኞች ወደ ስራ ከመሰማራታቸው አስቀድሞ የመንገድ ደህንነት፣ ደንበኞች አገልግሎት፣ የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና እርዳታ፣ የሞተርሳይክል ጥገና እንዲሁም እንደ ሞተረኛው ፍላጎት የገንዘብ አያያዝን የተመለከቱ ስልጠናዎችን እንዲያገኙ ይገደዳሉ፡፡ ስልጠናውን ካጠናቀቁ በኋላ ስማርት የስልክ ቀፎዎች፣ ብርቱካናማ አንፀባራቁ ጃኬትና ሁለት ብርቱካናማ ሂልሜቶች (አንዱ ለራሳቸው፤ ሌላኛው ደግሞ ለተሳፋሪያቸው) የሞተረኛው ቁጥር በጉልህ ታትሞበት ከተሰጣቸው በኋላ ወደ ስራ ይገባሉ፡፡
ኩባንያው እያስገባ ስላለው ገቢ መረጃዎችን ባይሰጥም ትርፍ እያተረፈ እንዳልሆነ ግን አላስታር ሳሲክ ይናገራል፡፡ ሆኖም ኢንዱስትሪው በከፍተኛ ምስቅልቅል ውስጥ ይዋጅ የነበር እንደመሆኑ ዋናው አላማቸው ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ኢንዱስትሪውን የተሻለ ማድረግ ላይ መሆኑን ሪኪ ራፓ ይናገራል፡፡
ምንጭ፤ Financial Times
ለተጨማሪ፤ https://www.ft.com/.../8a9b4326-b676-4ebf-8af5-29b995f6da9d
ትክክለኛ መገኛውን የሚያውቀው አዲስ ካሜራ
**************************
ተመራማሪዎች ትክክለኛ መገኛውን የሚያውቅ ካሜራን መስራታቸው ተሰማ፡፡ በብሪስቶል ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ተመራማሪዎች በአይነቱ ልዩ የሆነ ስማርት ካሜራን ሰርተዋል፡፡ ይህም ካሜራ የሚያነሳቸውን ምስሎች እንደ ካርታ በመጠቀም የት አካባቢ እንደነበረ እና አሁን የት ላይ እንደሚገኝ ማወቅ የሚችል እንደሆነ ተነግሮለታል፡፡ ይህ ቴክኖሎጂም ስማርት ሴንሰሮችን፣ ራስ ነድ መኪኖችንና የተለያዩ ሮቦቶችን ለመስራት የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ የሚያግዝ እንደሚሆን ታውቋል፡፡
ጉዙ በሚደረግበት ወቅት ተጓዡ የሚገኝበትን ትክክለኛ ቦታ በካርታ ላይ ማወቅ እጅግ ጠቃሚ ነገር ነው፡፡ ይህም ወደፊት ወዴት መሄድ እንዳለብንና እስካሁን የመጣንበትን መንገድ እንድናውቅ ያደርገናል፡፡ ይህ አይነት ስልት እንደ ጽዳት ላይ የተሰማሩ ሮቦቶች፣ የቁሳቁስ ማጓጓዣ ድሮኖች እና የጤና ክትትል የሚያደርጉ ተለባሽ ሴንሰሮች ያሉ ስማርት ቁሶች እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡
ይሁን እንጂ ካርታዎችን መጠቀም የሚኖርባቸው ቴክኖሎጂዎች እንደ GPS ያሉ ውጫዊ ሲግናሎችን መጠቀም ይኖርባቸዋል፡፡ እነዚህ ሲግናሎች በተለይ በቤት ውስጥ እምብዛም አገልግሎት አይሰጡም፡፡ ወይም ደግሞ ለእንቅስቃሴ ከፍኛ የሆነ የሐይል ፍላጎት ይኖራቸዋል፡፡
ይሁን እንጂ በብሪስቶል ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች የተሰራው አዲሱ Pixel Processor Array (PPA) የተሰኘው ስማርት ካሜራ በሴንሰሩ አማካኝነት የተለያዩ ፕሮሰሶችን የሚሰራ ነው፡፡ ይህም ማለት ምስሎችን ሴንስ በማድረግ ከምስሉ ምንአይነት መረጃ መያዝና ማስወገድ እንዳለበት ካሜራው መወሰን ይችላል፡፡ እንዲሁም በወቅቱ እየተሰራ ላለው ስራ አስፈላጊ የሆነውን መረጃ ብቻ መለየት ያስችለዋል፡፡
በሌላ አገላለጽ የዚህ ካሜራ ስልተ ቀመር አዲስ የሚመለከታቸውን ቦታዎች ብቻ ይዞ እንዲያስቀር የሚያደርገው ሲሆን አንድን ምስል ካነሳ በኋላ ከዚህ በፊት ካነሳቸው ምስሎች ጋር በማነጻጸር የተለየ መሆኑንና አለመሆኑን ይወስናል፡፡
ምንጭ techxplore
ተጨማሪ ንባብ፡ https://techxplore.com/news/2021-06-camera.html
በዓይነቱ ልዩ የሆነው የሰማይ ላይ መዋኛ ገንዳ
=====================
በእንግሊዟ መዲና ለንደን የተገነባው በዓለማችን የመጀመሪያው ተንጠልጣይ የመስታውት መዋኛ ገንዳ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል፡፡ በመስታወት የተሰራው መዋኛ ገንዳው በሁለት የመኖርያ አፓርታማዎች አስረኛ ፎቅ ላይ እንደ ድልድይ ሆኖ የተንጠለጠለ ነው፡፡ “የሰማይ ላይ መዋኛ ገንዳ” ተብሎ የተሰየመው ገንዳው የ25 ሜትር ርዝማኔ ሲኖረው ከዚህም ውስጥ 14 ሜትሩ በሁለቱ ህንፃዎች መካከል ያለውን ክፍት ቦታ የሚሸፍን ነው፡፡
ገንዳው ከዚህ ቀደም ስመ ጥሩን የሲድኒ ኦፔራ አዳራሽ ኪነ-ህንፃዊ ንድፍ በሰራው የአራፕ አሶሴሽንና ሌሎች አጋሮች አማካኝነት የተሰራ ነው፡፡ ታድያ የገንዳው መገኛ ለንደን ይሁን እንጂ የተፈበረከው በሀገረ አሜሪካን ኮሎራዶ ውስጥ ነው፡፡ እንዲህ በአስደናቂ ሁኔታ ከመገጠሙ በፊትም አትላንቲክን በመርከብ መሻገር ነበረበት፡፡ ሺዎች ኪሎሜትሮችን ተጉዞ ከስፍራው ከደረሰ በኋላም ከምድር አንስቶ አሁን ወዳለበት የ35 ሜትር ከፍታ ለማድረስ የአንድ ባለ 750 ቶን ተንቀሳቃሽ ክሬን እና ሌላ ተጨማሪ ባለ 50 ቶን ክሬን አስፈልጎታል፡፡
ዙርያ ገባውን ያየን እንደሆን መዋኛ ገንዳው የ5 ሜትር የጎን ስፋትና 3 ሜትር ጥልቀት ሲኖረው በውስጡ የሚይዘው 40 ሺህ ጋሎን ውሃ ብቻ የ375 ቶን ክብደት እንዳለው ተዘግቧል፡፡ ይህን ውሃ ያቆሩት ሁለት የጎን ግድግዳዎቹ 200 ሚሊ ሜትር ውፍረት ሲኖራቸው የታችኛው ወለሉም 300 ሚሊ ሜትር ውፍረት አለው፡፡ በገንዳው ሁለቱም ጫፎች ላይም የመግቢያ ደረጃና የውሃ ማጣርያ ስርዓቶች የተገጠሙለት ሲሆን በዋናተኞቹ ዘንድ ምትሀታዊ ስሜትን እንዲፈጥርም አምስት አይነት መብራቶችን ይዟል፡፡
ታድያ የገንዳውን ተመርቆ መከፈትን ተከትሎ ብዙዎችን እያነጋገረ ይገኛል፡፡ ገንዳው ውስጥ አስደናቂ በሆነ መልኩ ከውሃው በታች ያለውን ከባቢ ቁልቁል እየተመለከቱ መዋኘቱ አስደማሚ ዕይታና ልዩ ስሜትን የሚፈጥር መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ መዋኘት የሚፈልጉበትን ያህል ግን ገና ከሩቁ የፈሩት አልታጡም፡፡ ሆኖም ደህንነቱ የተጠበቀ ይሆን ዘንድ ስውር በሆኑ የብረት መቃኖች የተደገፈና ከባድ ነፋስ ሲመጣም በተወሰነ መልኩ ወደጎን በመወዛወዝ እንዲያሳልፈው ተደርጎ የተሰራ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር አሜሪካን ውስጥ በመሰራት ሳለ ለጥንካሬው ማረጋገጫ የሰጡ ሙከራዎች ተደርገውለታል፡፡
መዋኛ ገንዳው ለአፓርታማው ነዋሪዎችና እንግዶቻቸው ብቻ የ24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጥ ይሆናል፡፡
ምንጭ፤ CNN እና The Points Guy
ለተጨማሪ፤ https://edition.cnn.com/.../sky-pool-embassy.../index.html
https://thepointsguy.com/news/see-through-pool/
ለህክምናው ዓለም ባለውለታ የሆኑት የሄኔሪታ ላክስ የማይሞቱ ህዋሶች
--------------------------------------------
ሄኔሪታ ላክስ በገቢ አቅማቸው ዝቅተኛ ከነበሩ እና በትምባሆ እርሻ ከሚተዳደሩ የአፍሪካ አሜሪካ ወላጆች በ1920ዎቹ በቨርጂኒያ ግዛት የተወለደች ጥቁር አሜሪካዊት ናት፡፡ ሄኔሪታ ላክስ የቤተሰቦቿን የእርሻ ስራ ከወረሰች በኋላ በወጣትነት ዘመኗ ሃሊፋክስ ካንትሪ ወደተባለ አካባቢ በመሄድ የረሷን ህይወት መስራታ መኖር ጀመረች፡፡ በትዳር ህይወቷ ሁለት ልጆች የነበሯት ይህች ሴት ሶስተኛ ልጇን ለመውለድ በደረሰችበት ጊዜ የማህፀን ጫፍ ካንሰር እንዳለባት በህክምና ምርመራ አረጋገጠች፡፡ ይህ በሽታ ከተከሰተባት ከጥቂት ጊዜያት በኋላ በ31 ዓመቷ ከዚህ አከለም በሞት የተለየችው ሄኔሪታ ላክስ የካንሰር ምርመራ በሚደረግላት ጊዜ ያለሷ ፍቃድ ወይም እውቅና የህዋስ ናሙናዎቿን እንደምርመራው አካል የሰበሰቡት ዶክተሮች የሄኔሪታ ላክስ ህዋሶች ህይወቷ ካለፈ በኋላም ራሳቸውን ማራባት እንደሚችሉ እና እስካሁን ባልታየ መልኩ የማይሞቱ ህዋሶች የነበሯት ሴት መሆኗን አረጋገጡ፡፡
በ1950ዎቹ እና ከዛ በፊት በነበሩት አመታት የህክምና ሳይንስ ተመራማሪዎች የሰው ልጆችን ህዋስ ከሰውነት አካል በማውጣት ህዋሶቹ በራሳቸው በህይውት መቆየት እንደሚችሉ እንደማይችሉ ሲያጣሩ ቆይተዋል፡፡ ይሁንና የሄኔሪታ ህይወት እስኪያልፍ ድረስ ሙከራ የተደረገባቸው ብዙ ህዋሶች ምንም ውጤት ሊያስገኙ አልቻሉም ነበር፡፡ ሄኔሪታ በ1951 ከዚህ ዓለም በሞት ስትለይ በጊዜው ጥቁሮችን በማከም ብቸኛው በሆነው የጆን ሆፕኪንስ ሆስፒታል በተደረገላት የካንሰር ምርመራ ተዓምር ሊባል በሚችል መልኩ የህዋስ ናሙናዎቿ ህያው ሆነው ተገኙ፡፡
በ1951 በጆን ሆፕኪንስ ሆስፒታል ውስጥ ባለው የምርምር ማዕከል በህዋሶቹ ላይ ምርምር ሲያደረግ የነበረው የካንሰር ተመራማሪ ዶ/ር ጆርጅ ኦቶ ጌይ የሄኔሪታን የህዋስ ናሙናዎች ቲሹ ካልቸር በተባለው ህዋሶችን ከሰውነት አካል ወጪ በላብራቶሪ የማበልፀግ ሂደት ውስጥ በማስገባት ሰፋፊ ምርምሮችን ማከናወን ጀመረ፡፡ ተመራማሪው የህዋሶቹን ናሙና HeLa የሚል ስያሜ በመስጠት በመላው ዓለም ለምርምርና ሌሎች ጉዳዮች በማሳራጨት በክፍለ ዘመኑ ለተገኙት ትልልቅ የህክምና ሳይንስ ግኝቶች የመጀመሪውን መንገድ ጠረገ፡፡ ዶ/ር ጆርጅ ኦቶ ጌይ በ HeLa ህዋሶቹ ላይ ምርምር ለማድረግ ለሚፈልጉ ተመራመሪዎች ናሙናው መላክ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በመላው ዓለም እጅግ ብዛት ያለው ናሙና በፋብሪካ ውስጥ በብዛት ተመርቶ በዓለም ዙሪያ ይላክ ነበር፡፡
የሄኔሪታ ላክስ ህዋሶቿ ለህክምናው ዓለም ያደረጉት ውለታ ተዘርዝሮ የሚያልቅ ባይሆንም እጅግ ግዙፍ ከሚባሉት የባዮሎጂካል ምርምሮች እና የመድሃኒት ግኝቶች መካከል የሚከተሉት ሊጠቀሱ ይችላል፡፡ የመጀመሪው እንደአውሮፓውያኑ በ1954 ዮፖሊዮ ክትባት ለማዘጋጀት ጥቅም ላይ የዋለበት አጋጣሚ ሲሆን በ1980 ደግሞ ኤች አይ ቪ ቫይረስን ለመለየት በሚደረገው ጥረት የነበረው ትልቅ አስተዋፅዖ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በህክምናው ዘርፍ ለተደረጉ ከ67 ሺ በላይ ጥናቶች የሄኔሪታ ላክስ ህዋሶቿ ትልቅ ሚና የነበራቸው ሲሆን በጥቅሉም የሰዎችን በሽታ የመከላከል ስርኣት ለመመርመር፣ ለጄኖሚክስ ጥናት እና ለካንሰር ምርምር ያደረጉት አስተዋፅዖ በቀላሉ የሚገለፅ አይደለም፡፡ የ HeLa ህዋሶችን መሰረት አድርገው በ ተለያዩ የህክምና ዘርፍ ላይ ምርመር ያደረጉ ሁለት ሳይንቲስቶች በ2008 አና በ2009 የኖቤል ሽልማት ያገኙበት አጋጣሚ የሄኔሪታ ላክስ ህዋሶች ሌላኛው ትሩፋቶች ናቸው፡፡
ከ1951 አንስቶ እስከ አሁኗ ሰዓት ድረስ ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉት የ HeLa ህዋሶች ከሄኔሪታ ፍቃድ ውጭ ጥቅም ላይ በመዋላቸው የስነ ምግባር ጥያቄ እንዲነሳባቸው ምክንያት ሆነ ነበር፡፡ የሄኔሪታ ላክስ ቤሰተቦች በሄኔሪታ ህዋሶች አማካኝነት አለም አቀፍ የህክምና ሳይንስ ምርምሮች እየተደረጉ መሆኑን ያወቁት ሄኔሪታ ህይወቷ ካለፈ ከ20 እና 30 ዓመት በኋላ ነው፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ከፍተኛ ክርክር ሲያስነሱ ቆይተው ኋላ ላይ የአሜሪካ መንግስት ሆስፒታሎች ያለታካሚዎች ፈቃድ የሰዎችን ህዋሶች ወይም ባዮፕሲዎችን እንዳይጠቀሙ የሚግድ ህግ እንዲያወጣ አስገድዶታል፡፡
የሄኔሪታ ላክስ አስገራሚ የህይወት ገፅታ እና ስለማይሞቱት ህዋሶቿ የሚዳስሰው The Immortal Life of Henrietta Lacks መፅሃፍ ሬቤካ ስክሎት በተባለች ፀሃፊ በ2010 የወጣ ሲሆን እሱን መሰረት አድርጎም በ2017 የወጣው ፊልምም በኦፕራ ዊንፍሪ መሪ ተዋናይነት አውነታውን ሲገልፅ ይታያል፡፡
ምንጭ፡ Iflscience እና immunology
https://www.iflscience.com/.../the-strange-story-of.../...
https://www.immunology.org/hela-cells-1951
ጉዞ ወደ ቬነስ
******
በስርዓተ ፀሐይ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ቬነስ ስያሜዋን በጥንታውያን የሮም የፍቅርና የውበት አምላክ ከሆነችው እንዳገኘች ይነገራል፡፡ ቬነስ በስርዓተ ፀሐይ ከጨረቃ ቀጥላ ብሩህ የሆነች ፕላኔት እንደሆነች ይነገራል፡፡ ታዲያ የአለማችን ግዙፉ የህዋ ምርምር ተቋን በመጪው 2030 ሁለት ጉዞዎችን ወደ ቬነስ ላማድረግ ማቀዱን ይፋ አድርጓል፡፡ የጉዞውም አላማ ገጸ ቬነስ (ገፀ-ምድር እንደሚባለው) እንዴት በአለታማ ከፈረታዎች እንደተሞላ ለማጥናት ነው፡፡
መልክዓ ቬነስ በቀላጭ ሊድ የተሞላ ሲሆን እነዚህ በናሳ ሊደረጉ የታሰቡ ጉዎች የቬነስ ቅልጥ ሊድ ምንጩ ምን እንደሆነና ተያያዥ ጥናቶችን ለማድረግ ያለመ ነው፡፡ ይህ ጥናትም ለ30 ዓመታት ያክል ምንም አይነት ጥናትም ሆነ ጉዞ ስላልተደረገባት ብሩኋ ፕላኔት ለተመራማሪዎች ትልቅ የምርምር እድል የሚሰጥ ነው ተብሏል፡፡ ተልእኮው በናሳ የ500 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በጀት የተያዘለት ሲሆን ጉዞውም ከ2028 እስከ 2030 ባሉት ጊዜያት እንደሚደረግ ተነግሯል፡፡
በቬነስም DAVINCI+ የተባለ በቬነስ ከባቢ አየር ውስጥ የሚገኝን የኖብል ጋዝ፣ ኬሚስትሪ እና ምሰላ በተመለከተ እንዲሁም ከፍተኛ መጠን ያለውን የቬነስ ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ክምችት እንዴት ሊፈጠር እንደቻለ ለማጥናት ያለመ ስራ ለመስራትም ታስቧል፡፡
በአጠቃላይ በተልእኮዎቹ በቬነስ ውስጥ ያሉ የተለያዩ የጋዝ ክምችቶችን፣ አሀን ላይ ለሚስተዋለው የግሪን ሀውስ ጋዝ ክምችን መንስኤውን፣ ከእስካሁኑ የተሸለ የቬነስን ምስል እንዲሁም በፕላኔቷውስጥ ከዚህ በፊት ውቅያኖስ ወይም የውሃ አካል መኖርና አለመኖሩን ለመመርመር የታለመ እንደሆነ ከመረጃ ምንጫችን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ምንጭ sciencealert
ተጨማሪ ንባብ https://www.sciencealert.com/we-re-going-back-to-venus-nasa-announces-two-new-missions-by-2030?utm_term=Autofeed&utm_medium=Social&utm_source=Facebook&fbclid=IwAR2VzcuJrFB9g83WtyIoLX653tCpcYyvXCtEiESuZF7WVxp_BRhzLKag-DU#Echobox=1622695106
የአለማችን የመጀመሪያው ከመሬት ጋር ያልተገናኘው ሰማይ ጠቀስ ህንጻ
በወትሮው ልማድ ጠራነው እንጂ ለነገሩ መባል ያለበት ምድር ጠቀስ ህንጻ ነበር መባል የነበረበት፡፡ እስካሁን የአየር ላይ ጓሮ በቻይና፣ ተንሳፋፊ ከተማ በፓስፊክ ተሰርተው አይተን አድንቀናል፡፡ ይህ የስነ-ህንጻ ጥበብ አሁን ደግሞ ከፍ ወዳለ ደረጃ ደርሷል፡፡ መቀመጫቸውን በኒዮርክ ያደረጉ የስነ ህንጻ ጠበብቶች ከአስትሮይድ ላይ ተንጠልጥሎ ቁልቁን ወደ ምድር 50 ሺህ ኪሎሜትር ያክል የሚርቅ ምድር ጠቀስ ህንፃን ለመገንባት ዲዛይን አቅርበዋል፡፡
ይህ ክላውድስ አርኪቴክቸር በተሰኘው ኩባንያ ዲዛይን የተደረገው ህንጻ በአለማችን ረጅሙ ከመሆኑ በተጨማሪ ብቸኛው መሰረቱ ከላይ የሆነ የተንጠለጠለ ህንጻም ነው፡፡ ኩባንያው ከዚህ በፊት የማርስ ላይ የበረዶ ቤቶችን ዲዛይን ሰርቶ ማቅረቡ የሚታወስ ነው፡፡ እንደ ኩባንያው መረጃ ከሆነ ዩኒቨርሳል ኦርቢታል ሰስፔንስ ሲስተም ሲሉ በጠሩት ዘዴ (UOSS) አማካኝነት ህንጻውን ለማንጠልጠል አስበዋል፡፡
የህንጻው ዲዛይን እቅድ እንደሚያሳየው ከሆነ ህንጻው ግዙፍ ብቻ ሳይሆን በብዙ የተከፋፈሉ ግን የተቀጣጠሉ ሰፋፊ ከተሞችም እንደሚወጣው ታውቋል፡፡ የኦርቢታዊ ጉዞው በ24 ሰዓታት የየማያቋርጥ እንቅስቃሴ የሚያልፍ ሲሆን ሰሜንና ደቡብ ንፍቀ ክበብን በመከተል እንደ ሃቫና፣ ፓናማ እና ኒዮርክ አይነት ግዙፋን ከተሞችን ቁልቁል እየተመለከተ ይንቀሳቀሳል፡፡
ለሀይል አቅርቦትም የፀሐይ ሐይል መሰብሰቢያ ንጣፎችን የሚጠቀም ሲሆን ለውሀ አቅርቦትም የዝናብ ውሃን መሰብሰብ በሚያስችል መልኩ እንደሚገነባ ተሰምቷል፡፡ መጠሪያው አናሌማ ታወር የተሰኘው ይህ ልዩ ኪነ- ህንጻ ብዙ መልስe የሚያስፈልጋቸው ጥያቄዎች ቢኖሩበትም የአለማችንን ብዙ ሪከርዶች የሚሰብር ልዩ ህንጻ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
ምንጭ iflscience.
ተጨማሪ ንባብ https://www.iflscience.com/technology/worlds-first-skyscraper-designed-to-hang-suspended-from-an-asteroid/?fbclid=IwAR3w4RPf05sDmoG4xEZnUOQpGvA5E-ejIMrskM7ILXHt-kxWCGw-sO_DH2o
ሁዋዌይ በ2.1 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የአይሲቲ ማዕከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስገነባ
==========================
ግዙፉ የቻይና ቴክኖሎጂ ኩባንያ ሁዋዌይ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን የአይሲቲ ልምምድ ማዕከልን በዩኒቨርሲቲው ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የፋርማሲ ካምፓስ ውስጥ አስገንብቶ አስመርቋል፡፡ ተማሪዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች የተግባር ልምድ እንዲያገኙበት ታልሞ የተገነባው ማዕከሉ በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት ውስጥ ከ2000 በላይ ተማሪና መምህራን መሀንዲሶችን በማሰልጠን የተሰጥዖ ስነ-ምህዳሩ እንዲያብብ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡ በነዚህ ሦስት ዓመታት ውስጥ ታድያ የዕውቀት ሽግግር ከተደረገ በኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማዕከሉ መቶ በመቶ ባለቤት እንደሚሆን ሸጋ ዘግቦታል፡፡
አዲሱ ማዕከል የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሩ ዶ/ር ሙሉ ነጋ፣ የሁዋዌይ ሰሜን አፍሪካ ምክትል ዋና ፕሬዘዳንት ፊሊፔ ዋንግ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ፕ/ር ጣሰው በተገኙበት ተመርቆ ተከፍቷል፡፡ በምርቃት ስነ-ስርዓቱ ላይም ሁዋዌይ ለ10 ተማሪዎች ድህረ ምረቃ ትምህርት ዕድል ይውል ዘንድ የ30 ሺህ ዶላር ድጋፍ ለዩኒቨርሲቲው አበርክቷል፡፡
በፋርማሲ ካምፓሱ ውስጥ ለትምህርት እንዲውል ዘመናዊ የቴሌኮም መሳርያዎች የስራው አካል ሆኖ የተገጠመ ሲሆን 1.9 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው የቁሳቁስ፣ ስልጠና የተግባር ማሳያዎች ለአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መምህራን የሚሰጥም ይሆናል፡፡
በዓለማችን ቀዳሚ የቴሌኮም ግብዓት አቅራቢ የሆነው ሁዋዌይ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ተማሪና ባለሙያዎችን የአይሲቲ አቅም የሚገነቡ ተግባራትን ሲከውን ቆይቷል፡፡ አሁን ላይ ከ36 የሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ከስራ ፈጠራ ኮሚሽን ጋር በትምህርትና ተሰጥዖን ማብቃት ላይ በትብብር እየሰራ ይገኛል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን የውድድር መርሀ ግብሮችን በማዘጋጀት ታዳጊዎችን የማብቃት ስራ እየሰራ ሲሆን በቅርቡም አንድ ሺህ ያህል ተማሪዎችን እንደሚያሳትፍ የሚጠበቀው 6ኛው የሁዋዌይ ዓለም አቀፍ የአይሲቲ ውድድን እዚሁ ኢትዮጵያ የሚያዘጋጅ ይሆናል፤ ለውድድሩ የመመዝገቢያ ሊንክ (https://e.huawei.com/en/talent/#/ict-academy/ict-competition/regional-competition?zoneCode=&zoneId=98269503&compId=85131961&divisionName=Huawei%20ICT%20Competition%20Ethiopia%202021)፡፡
ምንጭ፤ Shega
ለተጨማሪ፤ https://shega.co/post/huawei-launches-a-2-1m-ict-practice-center-in-addis-abeba-university/