TechIn2
1.17K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገው አፍሪካን ዩኒቲ ፎር ሬነሳንስ ኮንፈረንስ
===========================
በምድረ አፍሪካ ለሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን አስቻይ የሆነ ከባቢ መፍጠርን አልሞ የሚካሄደው ዓመታዊው አፍሪካን ዩኒቲ ፎር ሬነሳንስ ኮንፈረንስ (AURC) ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያን ተካሄደ፡፡ ኮንፈረንሱ በዋናነት በኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት አማካኝነት የተለያዩ ኢትዮጵያውያን ምሁራን፣ ተመራማሪዎችና ባለድርሻዎችን በማሰባሰብ በራዲሰን ብሉ ሆቴል ሲካሄድ ከወደ ደቡብ አፍሪካም በዙም አማካኝነት ተሳታፊዎችን አካቶ ተደርጓል፡፡
በኮንፈረንሱ ላይ “Africa’s Future Beyond COVID-19” በሚል ርዕስ መቀመጫቸውን ደቡብ አፍሪካ ያደረጉ ምሁራን በዙም አማካኝነት የፓናል ውይይት ያደረጉ ሲሆን እዚሁ ኢትዮጵያ በነበረው ዝግጅትም አራት ያህል የጥናትና ምርምር ስራዎችና ለታዳሚው ቀርበዋል፡፡ በእለቱ ከቀረቡት የምርምር ስራዎች መካከል የጎማ ውስጥ አየር አሞላል በመኪናው የነዳጅ ፍጆታ ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕንዖ የሚዳስሰው የአቶ ንጋቱ በላይነህ ጥናት ይገኝበታል፡፡ ብዙውን ጊዜ መኪኖች የጎማቸው አየር ከሚገባው በላይ አልያም በታች ሆኖ እንደሚሞላ የተናገረው አቶ ንጋቱ ይህ የሚያሳድረውን ውጤትም በአንበሳ የከተማ አውቶብሶች ላይ ካደረገው ሙከራ ጋር በማያያዝ ለታዳምያኑ አስቃኝቷል፡፡
ሌላው በዕለቱ የቀረበው ጥናት በቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት አማካኝነት በሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ተቋማትን በመዳሰስ ተጠንቶ ለህዝብ በቀረበው የብሔራዊ ኢኖቬሽን ሰርቬይ ላይ ነው፡፡ የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪ በሆኑት አቶ በላቸው አለማየው አማካኝነት ለታዳምያን እንዲደርስ በተደረገው በዚህ ዳሰሳ በኢትዮጵያ ያሉ ሀገራዊ የኢኖቬሽን ደረጃዎች ተመላክተውበታል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ተቋማት በተገበሯቸው የኢኖቬሽን ስራዎች አማካኝነት ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን የተናገረው አቶ በላቸው ለዚህ ያበቃቸው ዘንድ ተቋማቱ ሲተገብሯቸው የሚስተዋሉ የኢኖቬሽን አይነቶች እንዲሁም ወደ ኢኖቬሽን ለመግባት መነሻ ምክንያቶቻቸው ናቸው ያላቸውን በዝርዝር አሳይቷል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን በኢትዮጵያ ያለውን የኢኖቬሽን እንቅስቃሴ እጅግ ዝቅተኛና በውስን ሁናቴዎች ላይ የተንጠለጠለ በመሆኑ ይህን እንደ ሀገር ያሻሽላሉ የተባለላቸው ጠንካራ የአዕምሮ ንብረት ጥበቃ ስርዓት ግንባታ፣ የገንዘብ ድጋፍ እና የዕውቀት ሽግግርን ጨምሮ ልዩ ልዩ የመፍትሄ እርምጃ ጥቁምታዎች ተሰጥተውበታል፡፡
ከሁለቱ በተጨማሪ “Termal Regulating Leather for Hot Environment” እንዲሁም “Analysis Factors Affecting Firm Level Innovation Activity in Ethiopia” በሚል ርዕስ የምርምር እና ጥናት ስራዎች የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪ በሆነው አቶ ወገኔ ደምሴ እና ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ በመጣው አቶ አበባው አቢቦ ቀርበዋል፡፡ በአጠቃላይ የቀረቡት ጥናቶች እና የፓናል ውይይትንም አስመልክቶ በመድረኩ ተገኝተው በነበሩ ምሁራን አማካኝነት ጥያቄና አስተያየት ሲሰጥባቸው ቆይቷል፡፡
አፍሪካን ዩኒቲ ፎር ሬነሳንስ ኮንፈረንስ ላለፉት 10 ዓመታት ሲካሄድ ቢቆይም ከደቡብ አፍሪካ ውጪ ሲደረግ ግን ይህ ለመጀመሪያ ጊዜው ነው፡፡ ኮንፈረንሱ በኢትዮጵያ ሊካሄድ ዕቅድ ተይዞለት የነበረው ባለፈው ዓመት ቢሆንም በኮቪድ-19 ወረርሺኝ ምክንያት ወደዚህ ዓመት ሊሸጋገር ችሏል፡፡
በኪንግ ደሴት የተገኘው የተለየ እንቁላል
*************************
የእንግሊዙ የተፈጥሮ ታሪክ ሙዚየም አካል የሆነ አንድ የተመራማሪዎች ቡድን በአየነቱ የተለየ ኢምዩ የተሰኘች በአውስትራሊያ ብቻ የምትገኝ የማትበር ወፍ እንቁላልን ማግኘቱን ይፋ አደረገ፡፡ እንቁላሉም ከሌሎች ተመሳሳይ አእዋፋትና ከሌሎች ዝርያዎች እንቁላል በእጅጉ የተለየ እንደሆነ ተሰምቷል፡፡
ኢምዩ በአውስትራሊያ እና በአካባቢው በሚገኙ ደሴቶች ብቻ የምትገኝ የማትበር ወፍ ስትሆን በግዝፈቷ ከሰጎን ቀጥሎ የምትጠራ ናት፡፡ በአውስትራሊያ የሚገኙ ታስማኒያ፣ ካንጋሮ እና ኪንግ የተሰኙ ደሴቶች የራሳቸው የሆነ የኢምዩ ዝርያ አላቸው፡፡ እነዚህ የወፍ ዝርያዎች በተለያዩ ምክንያቶች የድንክነት ችግር እንዳጋጠማቸው ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡
ይህ የወፍ ዝርያ በሚኖርባቸው አካባቢዎች ለመኖር ምቹ አለመሆን ምክንያት ሊጠፋ የተቃረበ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ተመራማሪዎች ዝርያውን ከጥፋት ለመታደግ የሚያስችል የተለያዩ ስራዎችን ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ለብዙ ጊዜያት የዚህን ወፍ እንቁላል ሲፈልጉ የቆዩት ተመራማሪዎች በታስማኒያ እና በካንጋሮ ደሴቶች ብዛት ያላቸውን እንቁላሎች ማግኘት ችለው የነበረ ቢሆን ኪንግ በተባለችው በመጠኗ አነስተኛ በሆነችው ደሲት ግን ምንም እንቁላል ማግኘት አልቻሉም ነበር፡፡
እስካሁን ምንም እንቁላል ያልተገኘባት የጊንግ ደሴት አሀን ላይ አንድ ከተለመደው መጠን ከፍ ያለ እንቁላል ተገኝቶበታል፡፡ ጉዳዩን የተመለከቱት ተመራማሪዎች ለዚህ ትልቅ እንቁላል መፈጠር ምክንያቱ በደሴቱ ያለው የማይመች ሁኔታ ወፏ በአንድ ስፍራ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ተወስና በመቆየቷ እና የተሸለ ሙቀት በማግኘቷ ሊሆን ይችላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ምንጭ phys.org
ተጨማሪ ንባብ https://phys.org/news/2021-05-extinct-dwarf-emu-egg-king.html
ኢትዮጵያ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ ጥቅም ለማዋል በምታደረገው ጥረት ሩስያ የሰው ሃይል አቅም ግንባታ ላይ ድጋፍ ታደርጋለች።
========================
ኢትዮጵያና ሩስያ ከዚህ ቀደም የነበሩ ስምምነቶች ወደ ስራ በሚገቡበትና አዳዲስ የስምምነት ማዕቀፎችን መመስረት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር አድርገዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሀመድ (ፒ ኤች ዲ) እና በኢትዮጵያ የሩስያ አምባሳደር የቭጊኒ ተርኪን ሁለቱ ሃገራት በሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን መስክ በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።
ኢትዮጵያ የኒውክሌር ሃይልን ለሰላማዊ ጥቅም ለማዋል ከዚህ በምታደረገው እንቅስቃሴ ሩስያ በሰው ሃይል አቅም ግንባታ ድጋፍ እንደምታደርግ አምባሳደሩ አረጋግጠዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ድኤታ አህመዲን መሐመድ (ፒ ኤች ዲ) ሁለቱ ሀገራት ከዚህ ቀደም ያደረጓቸው ስምምነቶች የትብብር ማዕቀፍ በመፍጠር በፍጥነት ወደ ስራ መግባት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ከኢትዮጵያ የ10 አመት መሪ እቅድ ጋር የሚጣጣሙ አዳዲስ ስምምነቶች እንዲደረጉም ጠይቀዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር
የፊልም ተዋንያን የውጭ ቋንቋዎችን በብቃት እንዲናገሩ የሚያስችለው ቴክኖሎጂ
=============================
የትወና ተዕይንቶች ወይም ፊልሞች በውጭ ቋንቋ ተተርጉመው ቋንቋውን ለማይረዱ ሰዎች ተዘጋጅተው ሲቀርቡ ተመልከተናል፡፡ ይሁንና አብዛኛውን ጊዜ የትርጉም ስራውን ለሚሰሩ ብዙ ባለሙያዎች የተዋንያኑን የከንፈርና የፊት እንቅስቃሴን ከትርጉሙ ጋር በትክክል ለማጣጣም አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ ጥቅም ላይ የዋለው የዲፕፌክ ቴክኖሎጂ የትወና ትዕይንቲች በመደበኛ ቋንቋቸው የተሰሩ እስከሚስል ድረስ ተዋንያን የውጭ ቋንቋዎችን በብቃት እንዲናገሩ የሚያስችል ነው፡፡
የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ስርዓትን መሰረት አደርጎ የሚሰራው አዲሱ ቴክኖሎጂ የፊልም ትዕይንቶችና ድራማዎች ወደ ውጭ ቋንቋዎች ተተርጉመው የሚሰሩበትን ነባር አሰራር ይበልጥ እንደሚለውጥና እንደሚያዘምን ይጠበቃል፡፡ ቴክኖለጂው እንግሊዝ ውስጥ መቀመጫውን ባደረገ ፍሎውለስ በተሰኘ ኩባንያ የበለፀገ ሲሆን ማንኛውም የፊልም ትዕይንቶች ላይ ያለ ንግግርን ተዋናዩ እንደራሱ ቋንቋ እንዲናገራቸውና እንዲተውን የሚያስችል ነው፡፡ በኩባንያው ድረገፅ እንደ ሳምፕል የተቀመጠው በእግሊዘኛ የተሰራ የፊልም ትዕይንት፤ ፍፁም በሌላ ቋንቋ የተሰራ በሚመስል መልኩ ተዋኒያኑ የፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ጃፓን ቋንቋዎችን አስመስለው ሲናገሩ ፊልሙ በእንግሊዘኛ ሳይሆን በእነዚህ ቋንቋዎች ተሰርቶ የቀረበ ሊመስል ይችላል፡፡
ስኮት ማን በተባለ ግለሰብ የተመሰረተው ይህ ኩባንያ ከድምጽና ምስል ቀረጻ በኋላ የሚኖሩ የቮይስ ኦቨር (voiceovers) ማስተካከያዎችን እና የደቢንግ (Dubbing) አሰራሮችን በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ በመታገዝ ለማሳደግ እና ብዙ ግዜ በትርጉም ስራዎች ላይ የሚከሰተውን የከንፈር ማስመሰል (lip-sync) ችግሮችን ለማስቀረት ያለመ ነው፡፡ የኩባንያው ዳይሬክተር ስኮት ማን እንደሚናገሩት ሰዎች ይህን ቴክኖሎጂ ተጠቅመው መሰል የፊልም ትዕይንቶችን ሲመለከቱ ፊልሙ በመደበኛነት በየትኛው ቋንቋ እንደተሰራ እስኪያጠራጥራቸው ድረስ በሚሰሙት ቋንቋ የተሰራ ትዕይንት ሊመስላቸው ይችላል ይላሉ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰዎች በዚህ የዲፕፌክ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ማንኛውንም ምሰል እና ቪዲዮ ወደሚፈልጉት ባህሪና ቅርፅ መለወጥ የሚችሉበት ደረጃ ላይ የደረሱ ሲሆን፤ አንዳንዶች ይህ ቴክኖሎጂ በተገቢው ሁኔታ ካልተያዘ ጥልቅ ማጭበርበሮችና ማሳሳቻዎች በሕብረተሰቡ ላይ ሊያስከትል እንደሚችል ሲያስጠነቅቁ ይሰማል፡፡ በተለይም ብዙ ተከታይ ባላቸው ታዋቂ ሰዎች ላይ መሰል የማጭበርበሪያ ቪዲዮዎችን በመልቀቅ ለእኩይ ኣላማና ፕሮፖጋንዳ ሊውል የሚችልበት እድል እንዳለ ብዙዎች ሲገልፁ ይሰማል፡፡
https://wonderfulengineering.com/this-new-ai-can-make.../
በአውሮፓ የግለሰባዊ መረጃ ደህንነት ተሟጋች ቡድኖች ተቃውሞ
********************************
በአውሮፓ አምስት ከተሞች Clearview AI የተሰኘ የሰዎችን የፊት ገጽ ከተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች በመውሰድ የማመሳከርና የሰዎችን ማንነት የመለየት ስራን የግለሰባዊ መረጃ ደህንነት ተሟጋች ቡድኖች መቃወማቸው ተሰማ፡፡ ይህም የሆነው ክሊር ቪው የተሰኘው ቴክኖሎጂ የህግ ማስከበር ሂደትን ያግዛል በሚል የአውሮፓ መንግስታት ቴክኖሎጂውን በስፋት የመጠቀም አዝማሚያ እየታየባቸው በመሆኑ ነው፡፡
ይህ ቴክኖሎጂ የሰዎችን ማንነት በትክክል ለመለየት ካለው ጥቅም በተጨማሪ ያለ ሰዎች ፈቃድ መረጃን ለመውሰድ እና አላስፈላጊ ቁጥጥር ለማድረግ መንግስታት ሊጠቀሙበት ይችላሉ የሚል ነቀፋ ደርሶበታል፡፡ ለዚህም ቻይና ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ከፍተኛ የሆነ የደህነት ስራ ስትሰራ ነበር እየተባለች መታማቷን በማሳያነት ይነሳል፡፡
በአውሮፓ በዘርፉ የሰዎች መብት መጣስ የለበትም የሚሉ ከአራት በላይ የሰዎች ዲጂታል መብት ተከራካሪዎች ሲኖሩ በአውሮፓ ካሉ ሀገራት እንደ ፈረንሳይ፣ ኦስትሪያ፣ ጣልያን፣ ግሪክና እንግሊዝ ባሉት የሚገኙ ተቆጣጣሪዎችን በጉዳዩ ዙሪያ እየጠየቁ እንደሆነ ተሰምቷል፡፡
እንደ ፌስቡክ፣ ቲውተር፣ ዩቲዩብና ማይክሮሶፍት ኩባንያዎች የክሊር ቪውን እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ተቃውመውታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ይህ የሰዎችን ማንነት ለመለየት የሚያስችል ቴክኖሎጂ የዘረኝነት ችግር እየተነሳበት መሆኑን መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡
ምንጭ techxplore
ተጨማሪ ንባብ https://techxplore.com/.../2021-05-eu-privacy-groups...
የድሮን ቴክኖሎጂን በመጠቀም መድሃኒቶችን እና ክትባቶችን የሚያቀርበው ኢትዮጵያዊ ኩባንያ
==========================
አቪዮን ሰው አልባ አውሮፕላን ወይም ድሮንን በመጠቀም የህክምና አቅርቦቶችን በተለያዩ የታዳጊ ሀገራት የሚያቀርብ ኢትዮጵያዊ ኩባንያ ነው፡፡ አቪዮን በአፍሪካ ውስጥ በሚገኙ ለመጓጓዣ አስቸጋሪና ሩቅ አካባቢዎች የመድሃኒት ቁሳቁሶች ተደራሽነትን ለማስፋት የድሮን ቴክኖለጂዎችን እያመረተና እየተገበረ የሚገኝ ድርጅት ነው፡፡ ድሮንን መሰረት አድርገው ከሚዘዋወሩ የህክምና ቁሳቁሶች መካከል ደግሞ ክትባቶች እና መድሃኒቶች በዋናነት ይገኙበታል፡፡
አቪዮን የሚያመርታቸው ድሮኖች ሃይብሪድና ራስ-ገዝ ከሚባሉት የድሮን አይነቶች ውስጥ የሚመደቡ ሲሆን፤ እስከ 150 ኪሎ ሜትር ድረስ 5 ኪሎ ግራም የሚመዝኑ ክትባቶች እና መድሃኒቶች ጭነው መጓዝ የሚችሉ ናቸው፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የበረራ ሙከራውን በተሳካ ሁኔታ ያደረገው ኩባንያው በቅርቡ ከጤና ሚኒስቴርና ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በሃገር አቅፍ ደረጃ ተንቀሳቅሶ መስራት የሚያስችለውን ህጋዊ ማረጋገጫ አግኝቷል፡፡
አቪዮን አሜሪካ ውስጥ በሚገኝ Y-Combinator በተሰኘ የስታርታፕ አክስለሬተር ኩባንያ በሚዘጋጅ የሶስት ወር ፕሮግራም ላይ እንደኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በመሳተፍ ለፕሮጀክት ማስጀመሪያ የሚግዝ የ120 ሺ ዶላር የሲድ ኢንቨስትመንት ሊያገኝ ችሏል፡፡ በዚህ የስታርታፕ አክስለሬተር ፕሮግራም ውስጥ መሳተፍ የቻሉት የአቪዮን ኩባንያ አባላት በዓመት ሁለቴ በሚዘጋጀው በዚህ ፕሮግራም ላይ መሳተፋቸው ለስራ ማስጀመሪያ የሚያግዝ የውጭ ምንዛሪ እንዲያገኙ ትልቅ በር እንደከፈተላቸው ይናገራሉ፡፡ አሁን ላይ በተገኘው የፋይናንስ አቅምና መልካም ምላሽ ስድስት በሚጠጉ የከተማ ጣቢያዎች 24 ድሮኖችን በመጠቀም በየቀኑ 120 በረራዎችን ለማድረግ ያቀደው ኩባንያው በዚህም የህክምና አቅርቦቶች ላልተሟሉላቸው 2 ሺ የሚደርሱ ጤና ጣቢያዎች አገልግሎቱን የሚያቀርብ ይሆናል፡፡
አቪዮን መዲናችን አዲስ አበባ ሰው አልባ አውሮፕላን የሚመረትባት የድሮን የማምረቻ ሃብ ለማድረግ ሰፊ ራዕይ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን ከኢትዮጵያ ውጪም በአፍሪካ፣ ላቲን አሜሪካ እና ደቡብ እስያ ሀገራት አገልግሎቱን ለማስፋት እቅድ አለው፡፡
https://shega.co/.../the-story-of-yc-incubated-ethiopian.../
አሞሌ በስልክ ብቻ 100 ሺህ ብር መበደርን ሊያስችል ነው
=======================
አሞሌ የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ ደንበኞች እስከ 100 ሺህ ብር ድረስ መበደር የሚችሉበትን የብድር አገልግሎት ሊያስጀምር ነው፡፡ ግለሰቦችንም ሆነ ተቋማትን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የተነገረለት አገልግሎቱ በተለይም ለንግድ ተቋማት በመተግበሪያው አማካኝነት አንድን እቃ ገዝተው ሒሳቡን በኋላ መክፈል የሚያስችላቸው ይሆናል፡፡
ሞንቴና ቴክኖሎጂስ ከዳሽን ባንክ ጋራ በመተባበር የዛሬ ሦስት ዓመት ይፋ ያደረገው አሞሌ የስልክ መተግበሪያ 2.1 ሚሊዮን ተጠቃሚዎችን በማፍራት እንደ አገልግሎት ክፍያ፣ የስታዲየም መግቢያ ትኬትና የስልክ አየር ሰዓት ግዢ ያሉ አገልግሎቶችን ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ በዚህ የሁለት ዓመት ቆይታው ባከናወናቸው ከሦስት ሚሊዮን የሚልቁ ዝውውሮች አማካኝነት 7.3 ቢሊዮን ብር የሚሆን የገንዘብ ዝውውርን ማከናወን ችሏል፡፡ ሆኖም አብዛኛው የገንዘብ ዝውውር ከስፖርት፣ መዝናኛ፣ ት/ቤት ክፍያ እና ሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ ጋር የተያያዙ እንደመሆናቸው የኮቪድ-19 ወረርሺኝ ሲከሰት የዝውውር መጠኑ በ85 በመቶ ሊወርድ ችሏል፡፡ ይህም ለተቋሙ ትምህርት ሆኖት በኤሌክርትሮኒክ ኮሜርስ እና ዕቃ ማድረስ ላይ እንዲሰራ አድርጎታል፡፡
ባሳለፍነው ወር ይፋ ያደረገው ዓለም አቀፍ የኢ-ኮሜርስ አገልግሎቱም እንዲሁ ነጋዴዎች ክፍያቸውን በዳሽን ባንክ በኩል መቀበል እንዲችሉ የሚያደርግ ነው፡፡ የክፍያ ስርዓቱን የሚያስችልለት የቴክኖሎጂ መሰረተ-ልማትን ለመዘርጋት ይረዳው ዘንድም በናይጄሪያውያን ተመስርቶ መቀመጫውምን አሜሪካን ካደረገው የፋይናንስ ቴክኖሎጂ ኩባንያ ፍላተርዌቭ ጋር ጥምረት መመስረቱም ተዘግቧል፡፡
ይህ የብድር አገልግሎት ምናልባትም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለህዝብ ይፋ ሊሆን እንደሚችል ተነግሯል፡፡ ሆኖም ከተጠያቂነት አንፃር ቀለል ያሉ ሆነው የሚገኙት የንግድ ተቋማት ቀዳሚ ተጠቃሚ የመሆን እድላቸው የሰፋ ነው፡፡ በሌላ መልኩ የብድር ወለዱ በባንኮች ላይ ካለው ከፍተኛ መጠን በእጅጉ ያነሰ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
ምንጭ፤ Addis Fortune
የሩሲያ ሀከሮች ጥቃት እንደቀጠለ ነው ሲል ማይክሮሶፍት ተናገረ
=====================
ባሳለፍነው የፈረንጆች አመት በርካታ የአሜሪካን ተቋማትን ያጠቃውና በሩሲያ መንግስት ይደገፋል ተብሎ የሚታማው የሀከሮች ቡድን በሀገሪቱ የመንግስት ቢሮዎች፣ የምሁራን መድረኮች፣ አማካሪዎች እንዲሁም ሌሎች ድርጅቶች ላይ ጥቃቱን ቀጥሏል ሲሉ ኃላፊዎችና አጥኚዎች ተናገሩ፡፡ በማይክሮሶፍት አማካኝነት ባሳለፍነው ሳምንት የወጣው መረጃ የሚያመላክተው ኖቢሊየም የተሰኘው ቡድኑ በተለይ በውጪ ጉዳይ ፖሊሲዎች ላይ ትኩረታቸውን አድርገው በሚሰሩ መንግስታዊ ተቋማት ላይ የሚያደርሰውን ጥቃት መጨመሩን ነው፡፡ የአሜሪካን ሳይበር ደህንነት እና መሰረተ-ልማት ኤጀንሲም ይህን የማይክሮሶፍት መረጃ በመጠቆም የሚመለከታቸው ተገቢውን የመከላከያ እርምጃ ይወስዱ ዘንድ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡
በማይክሮሶፍት የቀረበው መረጃ ውስብስብ እና በከፍተኛ መጠን የተስፋፋ የጥቃት ወጥመድ የሆኑ ኢ-ሜይሎችን (Phishing) የመላክ ዘመቻ ማስተዋሉን ይገልፃል፡፡ ይህም እንደ ማይክሮሶፍት ምክትል ፕሬዘዳንት ከሆነ ከ150 የተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ 3 ሺህ ኢ-ሜይል አካውንቶች በጥቃት ኢላማው ውስጥ ያስገባ ነው፡፡ ይህ ዜና የተሰማው ዋሽንግተን በባለፈው ዓመት የሶላርዊንድ ጥቃትና ሌሎች መንስኤዎች መነሻነት የተወሰኑ የሩሲያ ዲፕሎማቶችን ከሀገሯ ካባረረችና በሩሲያ ላይም ማዕቀብ ከጣለች ከወራት በኋላ መሆኑ ትኩረትን ስቧል፡፡
አዲሱ ጥቃት ሀከሮቹ የኢ-ሜይል ሰርቨሮቹ ውስጥ መግባትና ሀሰተኛ ኢሜሎችን በስፋት እንዲልኩ ማስቻሉ ተጠቅሷል፡፡ ከተላኩት ሀሰተኛ ኢ-ሜይሎች መካከልም የቀድሞው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ማጭበርበር ዙርያ አዲስ ሰነድ ይፋ ማድረጋቸውን የሚገልፅ ይገኝበታል፡፡ ይህን ተመልክተው ሊንኩን የተጫኑ ሰዎች ታድያ ሀከሮቹ የግል መረጃዎቻቸውን እንዲበረብሩባቸው የሚያስችለው ሶፍትዌር እንዲጫንባቸው ይሆናል፡፡
ባሳለፍነው ዓመት የተሰነዘረው የሶላርዊንድ ጥቃት 18 ሺህ ደንበኞችን እና ከ100 በላይ የሀገሪቱን ተቋማትን ተጎጂ አድርጎ ነበር፡፡ የጥቃቱ ሰለባ ከሆኑት መካከል በዓለማችን 500 ግዙፋን ኩባንያዎች ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት የአሜሪካን ኩባንያዎች ይገኙበታል፡፡
ምንጭ፤ Tech Xplore
ለተጨማሪ፤ https://techxplore.com/.../2021-05-russian-hackers...
በኢትዮጵያ የሚገነባው የባቡር አካዳሚ
====================
በሚቀጥሉት ዓመታት የመገንባት እቅድ ለተያዘላቸው እና በስራ ላይ ለሚገኙት የባቡር ፕሮጀክቶች በቂ የሰው ኃይል ማፍራት የሚያስችል የባቡር አካዳሚ እየተገነባ መሆኑን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አስታወቋል፡፡ ከኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ ጋር ቆይታ የነበራቸው የኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ ሃላፊ አቶ በሃይሉ ስንታየሁ ኢትዮጵያ በባቡር ግንባታ ዘርፍ አሁንና ወደፊት ለሚኖራት ሰፋፊ እቅዶች ከዘመኑ የቴክኖሎጂ አቅም ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችል የሰለጠነ የሰው ሃይል ለማፍራት ያስቸላት ዘንድ ይህ የባቡር አካዳሚ ግንባት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በቢሾፍቱ ከተማ ሚገነባው ይህ የማሰልጠኛ ተቋም ኢትዮጵያ በዘርፉ ያለባትን የባለሙያዎች እጥረት ለመፍታት እና ከዚህ በኋላ ሊሰሩ እቅድ ለተያዘላቸው ግዙፍ የባቡር ፕሮጀክቶች ክህሎታቸው የተረጋገጠ ኤክስፐርቶችን ለማውጣት የሚያስችል ነው፡፡ ለስልጠና ማዕከሉ ግንባታ ዝግጅት እየተደረገ ሲሆን ለዚህም ከዓለም ባንክ እና ከቻይና መንግስት ብድር የተገኘ መሆኑን አቶ በሃይሉ አብራርተዋል፡፡
የባቡር አካዳሚው ሥራ በሚጀምርበት ወቅት በርካታ ባለሙያዎችን በማፍራት ለባቡር ትራንስፖርቱ የሚያስፈልገውን የሠለጠነ የሰው ኃይል ፍላጎት ለማሟላት ከማገዝ ባሻገር፣ ከኢትዮጵያ የውጭ ባለሙያዎችን በመላክ ለማሠልጠን የሚወጣውን ወጪ ለማስቀረት የጎላ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡ በኢትየጵያ እንዲህ ያሉ የማስልጠኛ ተቋማትን የመመስረት እቅድ በየጊዜው ሲንከባለል የቆየ ቢሆንም በፊት ከነበሩ ልምዶች ተነስቶ አሁን ላይ እውን ሊሆን የተቃረበው ይህ የአካዳሚ ምስረታ የኢትዮጵያን የባቡር ኢንዱስትሪ በእጅጉ እንደሚያሰድገው ይታሰባል፡፡
በክህሎት እጥረት ሳቢያ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ አገራት የባቡር ሶፍትዌር መሐንዲሶችን፣ የኃይል አቅርቦትን፣ የአሠራር ጥገናን፣ ግንባታን እና ሌሎች ባለሙያዎችን ከምዕራቡ ዓለም ሲያስገቡ መቆየታቸውን የሚያነሱት አቶ በሃይሉ የአካዳሚው ግንባታ የአገር ውስጥ ባለሙያዎችን አቅም በሁሉም ዘርፍ ለማጎልበት ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡
ምንጭ፡ Ethiopian Press Agency
https://www.press.et/english/?p=35712#
ለመጀመሪያ ጊዜ ያለ ሰው ትዕዛዝ ግድያ የፈፀመው ድሮን
=======================
ባሳለፍነው የአውሮፓውያን ዓመት 2020 አንድ መሳርያን የታጠቀ ራስ-ገዝ ድሮን ሊቢያ ውስጥ ያለ ማንም ትዕዛዝ ሰዎችን አድኖ መግደሉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ፡፡ ድርጅቱ በሪፖርቱ እንዳስታወቀው ካርጉ-2 የተሰኘው ቱርክ ሰራሽ ባለ 4 ሽክርክር ድሮን በሊቢያ መንግስታዊ ኃይሎችና ከእነርሱ ተገንጥለው በመውጣት በሊቢያ ብሔራዊ ጦር አዛዡ ካሊፋ ሀፍታር በሚመራው ክንፍ መካከል በተፈጠረው ግጭት ላይ ነው የአጥፍቶ መጥፋት ስራን እንዲሰራ ሁለት ፈንጂዎችን ታጥቆ የተሰማራው፡፡
በወርሀ መጋቢት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፀጥታው ምክር ቤት ባለሙያዎች መድረክ ላይ የቀረበው ሪፖርቱ በኒው ሳይንቲስት መፅሔት አማካኝነት ነው ለህዝብ ይፋ የሆነው፡፡ አንደኛው የሪፖርቱ ክፍልም ካሊፋ ሀፍታር በሽሽት ላይ ሳሉ እንዴት እጅግ ውጤታማ በሆነ መልኩ ያለ ማንም ትዕዛዝ ሲንቀሳቀሱ በነበሩት የካግሩ-2 ድሮኖች ሲታደኑ እንደነበር ያመላክታል፡፡ ራስ-ገዝ ድሮኖቹ የተገጠመላቸው ስርዓት ከትእዛዝ ሰጪዎች ጋር ምንም ዓይነት በይነ-መረባዊ ግንኙነት ሳያስፈልጋቸው በራሳቸው ተነሳሽነት ኢላማውን ፈልጎ ጥቃት መሰንዘር የሚያስችለው መሆኑም ተነግሯል፡፡
በአንድ የአሜሪካን ፀረ-ሽብር ምርምር ላይ በተሰማራ ተቋም ውስጥ የሚሰራው ዛክ ካለንቦርን እንደሚለው ከሆነ ይህ ጥቃት ምናልባትም ያለ ሰው ትእዛዝ የተፈፀመ የመጀመሪያው ራስ ገዝ የድሮን ጥቃት ነው፡፡ ይህም በተለይ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ስርዓቶች የሚመለከቱትን ነገር ሁሉ በትክክል ለመተርጎም ካለመቻላቸው ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ስጋትን የሚጭር ጉዳይ መሆኑን ገልጿል፡፡ እንግሊዛዊው የውትድርና ምሁር ጃክ ዋትሊንግ በበኩሉ ድሮኖቹ ይህን ጥቃት ሲፈፅሙ በርቀት ቁጥጥር እየተደረገባቸው ይሁን አይሁን የሚያውቁት ድሮኖቹን ሲቆጣጠሩ የነበሩት ሰዎች መሆናቸውን ገልፆ ይህ ራስ-ገዝ የጦር መሳርያዎችን ለመቆጣጠር የማይቻል መሆኑን አያሳይም ሲል ይናገራል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ቴክኖሎጂው ቆሞ የሚጠብቀን ስላልሆነ በፍጥነት ውይይት ሊደረግበት እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
በዚህ ከሰው ቁጥጥር ውጪ ነበር በተባለለት ጥቃት ምን ያህል ሰዎች ስለመሞታቸው የሚያሳይ መረጃ አልተገኘም፡፡
ምንጭ፤ Daily Star
ለተጨማሪ፤ https://www.dailystar.co.uk/news/world-news/killer-ai-drones-hunted-down-24203431