TechIn2
1.17K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
ዝነኛው የዳርዊን ቅስት ፈረሰ
================
በኢኳዶሩ የጋላፓጎስ ደሴቶች የሚገኘው ዝነኛው የዳርዊን ቅስት (አርች) የላይኛው ክፍል መውደቁ ተዘግቧል፡፡ ከአቅራብያው የብስ ክፍል 1 ኪ.ሜትርን ርቆ በዳርዊን ደሴት ላይ የሚገኘው ቅስቱ ተፈጥሮአዊ በሆነ መሸርሸር ምክንያት ነው ለመውደቅ የበቃው፡፡
የተፈጥሮ ቅስቱ ስያሜውን ያገኘው ለታዋቂው እንግሊዛዊ ባዮሎጂስት ቻርለስ ዳርዊን መታሰብያ ይሆን ዘንድ ነው፡፡ ይህም እርሱ በአውሮፓውያኑ 1830ዎቹ ጅማሮ ላይ በጋላፓጎስ ደሴቶች ላይ ሳለ ዝግመተ ለውጥን ከማጥናቱ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ አሁን ላይ ታድያ የቅስቱ የላይኛው ከፍል መውደቁን ተከትሎ አንድ አስጎብኚ ድርጅት የተቀሩት ሁለት ቋሚ ክፍሎቹን “የዝግመተ ለውጥ ምሰሶዎች” ሲል መጥራት ጀምሯል፡፡
ዳርዊን ደሴት በእሳተ ገሞራ አማካኝነት የተፈጠረና ከባህር ወለል በታች የ10 ሜትር ጥልቀት ያለው ድንጋያማ ደሴት ነው፡፡ ደሴቱ እንደየወቅቱ እጅግ ከፍተኛ መጠን ባላቸው የሻርክና ሌሎች አሳ ዝርያዎች በስፋት እንደሚሞላ ከዚህ ቀደም የተሰሩ ጥናቶች አመላክተዋል፡፡ ከነዚህ የአሳ ዝርያዎች መካከል የሀመርሄድና ሌሎች የሻርክ አይነቶች፣ የባህር ኤሊዎች፣ ማንታ ሬዮች እንዲሁም ዶልፊኖች ይገኙበታል፡፡
አካባቢው በተለይም የባህር ውስጥ ህይወትን ለመቃኘትና እና ቅስቱን ፎቶግራፍ ለማንሳት በሚሹ ሀገር ጎብኚዎች የሚዘወተር ነው፡፡ የዳርዊን ቅስት የሚገኝበት የጋላፓጎስ ደሴቶችን የከበበው የባህር ክፍልም በስፍራው ለተሰባሰበው የባህር ህይወት ሲባል ተከልሎ ጥበቃ የሚደረግለት ሲሆን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት ሳይንስ እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) አማካኝነትም በቅርስነት የተመዘገበ ተፈጥሮአዊ ሐብት ነው፡፡
ምንጭ፤ Live Science
ለተጨማሪ፤ https://www.livescience.com/darwin-arch-collaspes-in...
ኢንስቲትዩቱ አዳዲስ ተመራማሪዎችንና ሰራተኞችን የማስተዋወቅ ስራ ሰራ
==========================
የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩቱ በ2013 በጀት ዓመት አዲስ ወደ ተቋሙ የተቀላቀሉ ተመራማሪዎችንና ሰራተኞችን የተቋሙን አጠቃላይ እንቅስቃሴ እና እርስ በርስ የማስተዋወቅ ስራ አከናውኗል።
ይህ በስልጠና መልክ የቀረበው ዝግጅት የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ ፣ ፕሮጀክት አስተዳደር፣ የቴክኢን መዋቅር እና የሰራተኞች መብትና ግዴታ በሚሉ ርዕሶች በተለያዩ አቅራቢዎች የተካሄደ ነው። በመጀመሪያም በተቋሙ ም/ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ተሾመ አማካኝነት የተቋሙን ፖሊሲ የማስተዋወቅ ስራ ተሰርቷል። በዚህም የተቋሙ ፖሊሲ የመጨረሻ ግብ ዜጎች የተሻሻለ የአኗኗር ዘይቤን እንዲከተሉ ማድረግ ማስቻል ነው ሲሊ ገልፀዋል።
ከከሰዓት በኋላ የቀጠለው መርሃ ግብር በአቶ ዳውድ መሀመድ በቀረበው የተቋሙሙን አጠቃላይ ጅማሮ እና እድገት የተመለከተ ገለጻ ተጀምሯል ። ገለጻው የተቋሙን አወቃቀር የተመለከተ መረጃም የተካተተበት ነው። አቶ ዳውድ የተቋሙን አላማ፣ ሀላፊነትና ተልእኮ የሚያሳዩ ሀሳቦችን በገለጻ መልክ አቅርበዋል።
በሁለተኛ ደረጃም የፕሮጀክት አስተዳደርን የተመለከተ ገለፃ ከፕሮጀክት ማኔጅመት ክፍል በመጡት ተመራማሪ ቶማስ ጀማል አማካኝነት ቀርቧል። በገለፃውም የፕሮጀት አስተዳደር ለጊዜ፣ ለገንዘብ፣ ለጉልበት እንዲሁም የታለመን ግብ እውን ለማድረግ ያለውን ዝርዝር ጠቀሜታ የሚያንፀባርቁ ሃሳቦች ተነስተዋል።
በቀረበውም ገለፃ ዙሪያ ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቆዎችና ሃሳቦች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ አቶ ዳውድ የፌዴራል የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ ላይ ያተኮረ የሰራተኞችን መብትና ግዴታ የተመለከቱ ህግ ነክ ሀሳቦችንም ለተሳታፊዎች አቅርበዋል።
በመጨረሻም መነቃቃትና ግለሰባዊ ስብእና ግንባታ ጋር የተያያዘ ገለጻ በአቶ ቶማስ ጀማል አማካኝነት ቀርቦ የእለቱ ዝግጅት ተጠናቋል።
በቀዳሚው የኒውክለር ፍንዳታ አማካኝነት የተፈጠረው አዲስ ቁስ
===========================
የተለየና የማይደገም መዋቅር ያለው ኮዌሰክሪስታልን ሲፈልጉ የቆዩ ሳይንቲስቶች በመጀመሪያው የኒውክለር ቦምብ ሙከራ ወቅት የተፈጠረውን ኢምፖሲብል የተሰኘ አንድ ኮዌሰክሪስታል መለየት ችለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም አይታወቅ የነበረው ይህ ኮዌሰክሪስታል ከአይረን፣ ሲልከን፣ መዳብ እና ካልሺየም የተዋቀረና ምናልባትም በተነኑ የበረሃ አሸዋ እና ኮፐር ገመዶች ጥምረት የተፈጠረ እንደሆነ ተነግሮለታል፡፡ ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ የሆኑ ቁሶች በቤተ-ሙከራ ሴንተሳይዝ የተደረጉና በሜትሮይቶች ውስጥም የተገኙ ቢሆንም በንጥረ-ነገሮች ጥምረት ለመመስረት ግን ይህ የመጀመሪያው ኮዌሰክሪስታል ሆኖ ተገኝቷል፡፡
ኮዌሰክሪስታሎች ከተለምዶአዊዎቹ ክሪስታሎች በተለየ የአተሞች አወቃቀር የተገነቡ ናቸው፤ ተለምዶአዊዎቹ ክሪስታሎች ሲደጋገሙም ተመሳሳይ ሆነው ሲቀጥሉ ኮዌሰክሪስታሎች ግን የማይቻል ተብለው ይታሰቡ የነበሩ ሲሜትሪዎች አሏቸው፡፡ በአውሮፓውያኑ 1982 ይህን አይነት የማይቻል ሲንተቲክ አሎይን በማግኘት የመጀመሪያው ሰው የሆነው ዳንኤል ሼትማን ስራው በሂሳብ ስሌት የማይሆን ነው ባሉት አጥኚዎች ዘንድ ከጥርጣሬ ወድቆ ነበር፤ ምንም እንኳን የኋላ ኋላ እ.አ.አ 2011 ላይ የኖቤል ሽልማትን በኬሚስትሪ ዘንድ ለማሸነፍ ቢያበቃውም፡፡ በተመሳሳይ ወቅት ፖል ስቴንሀርዲት እና የሙያ አጋሮቹ የማይደገሙ የባለ ሦስት እይታ (3D) መዋቅሮችን በሀልዮት ማስቀመጥ ጀምረው ነበር፤ ይህም እንዴት ሒሳብ ላያገኛቸው ሊቀር እንደቻለ የሚያብራራ ነበር፡፡
በአውሮፓውያኑ ሀምሌ 16 1945 በጆርዳና ዴል ሙኤርቶ በረሃ ከተደረገው ትሪኒቲ የኒውክለር ቦምብ ሙከራ ፍንዳታ በኋላ አጥኚዎች ከበረሃ አሸዋ የተሰሩ አረንጓዴያማ መስታውት መሰል ቁሶችን በስፋት አግኝተው ነበር፡፡
ምንጭ፤ Nature
ለተጨማሪ፤ https://www.nature.com/articles/d41586-021-01332-0...
ከአገልግሎት ውጭ የሆነው የኢንተርኔት ማፈላለጊያ
********************************
ማይክሮሶፍት ኩባንያ የኢንተርኔት ማፈላለጊያ ፕላት ፎርሙ ከአገልግሎት ውጭ መሆኑን አሳወቀ፡፡ ይህ Internet Explorer የተሰኘው ማፈላለጊያ ለ25 ዓመታት ግልጋሎት የሰጠ ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት ተጠቃሚዎች እንደ ጎግል ክህሮምና የአፕሉ ሳፋሪ እየተጠቀሙበት ባለመሆኑ ከአገልግሎት ውጭ መደረጉ ተነግሯል፡፡ መረጃው ይፋ በሆነበት ወቅት ድርጅቱ ፕላትፎርሙ በተለይ በዊንዶው 10 በ Microsoft Edge መተካቱን አሳውቋል፡፡
ተቋሙ አክሎም ማይክሮሶፍት ኤጅ ከኢንተርኔት ኤክስፕሎረር የተሻለ ፈጣንና ደህንነቱ የተረጋገጠ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ቀስ በቀስ ከአገልግሎት ውጭ እየሆነ የመጣው ኢንተርኔት ኤክስፕሎረር በቀጣዩ የፈረንጆች አመት ሰኔ 15 2022 ሙሉ ለሙሉ አገልግሎቱ ተቋርጦ ከተቋሙ እንደሚሰረዝ ተነግሯል፡፡
ኢንተርኔት ኤክስፕሎረር ከተቋረጠ በኋላ በዚህ ማፈላለጊያ አማካኝነት ይሰሩ የነበሩ መተግበሪያዎችና ድረ-ገጾች እስከ 2029 ድረስ አገልግሎታቸውን በማይክሮሶፍት ኤጅ አማካኝነት እንደሚቀጥሉም ታውቋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የጎግሉ ክሮም የገበያውን 65 በመቶ የተቆጣጠረ ሲሆን በአፕል ካምፓኒ ተበልጽጎ ድርጅቱ ባመረታቸው ቁሶች የሚሰራው ሳፋሪ ደግሞ 19 በመቶ ገደማ ሽፋን ይዟል፡፡ ፋየር ፎክስ በ3.59 በመቶ ሽፋን ሲከተል ኤጅ ደግሞ 3.39 በመቶ የገበያውን ሽፋን ይዟል፡፡
ምንጭ techxplore
ተጨማሪ ንባብ https://techxplore.com/news/2021-05-microsoft-internet-explorer.html?fbclid=IwAR24t8M9vNpCTRtQnX6k8Wl32mPtoDXxQO1f6bTNTHdlcDU7AzfoxZVM1-A
ለፈጠራ ባለሙያዎች ሲሰጥ የቆየው ቅድመ ኢንኩቤሽን ፕሮግራም ፍፃሜውን አገኘ
============
በቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት ለአራት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የቆየው የቅድመ ኢንኩቤሽን ፕሮግራም ዛሬ ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡ ፕሮግራሙ ልዩ ልዩ የፈጠራ ባለሙያዎችን ከተለያዩ ቦታዎች እንዲውም ከኢንስቲትዩቱ በማሰባሰብ የተካሄደ ሲሆን ተሳታፊዎቹን በማንኛውም የኢንኩቤሽን ፕሮግራም ውስጥ ተሳታፊ ለመሆን ብቁ እንዲሆኑና የፈጠራ ሀሳቦቻቸውንም ወደ ቢዝነስ እንዲለውጡ የሚያደርግ ነው ተብሎለታል፡፡
የፕሮግራሙ መጠናቀቅያ በሆነው የዛሬው መርሀ ግብር ፕሮጀክቶችን በማስተዳደር፣ ሀሳብን ለሌሎች እንዴት ማቅረብ እንደሚቻል እና በሌሎችም አባይት ጉዳዮች ላይ ለተሳታፊዎች ገለፃ ቀርቧል፡፡ ተሳታፊዎቹ ሀሳባቸውን ለሌሎች በማስረዳት ረገድ ማድረግ ስለሚገባቸው ተግባራት የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪ በሆኑት አቶ በላቸው አለማየሁ አማካኝነት የክህሎት ስልጠና ሲሰጣቸው ይህን ክህሎት ማዳበር ይችሉ ዘንድም በተለይ በሀሳባቸው ላይ መዋለ-ነዋያቸውን በሚያፈሱ ባለሀብቶች ዘንድ በምን መልኩ መቅረብ እንዳለባቸው ግንዛቤ የሚያስጨብጥ የተግባር ልምምድንም ማድረግ ችለዋል፡፡
ፕሮግራሙን ላለፉት አራት ቀናት ሲከታተሉ ከነበሩት ተሳታፊዎች መካከል ቃለ መጠይቅ ያደረግንለት ዮሃንስ ቢምረው የተሰኘ የ12ተኛ ክፍል ተማሪ ፕሮግራሙ ከዚህ ቀደም በተገቢው መልኩ አይመለከታቸው የነበሩት እንደ አዕምሮ ንብረት ጥበቃ ባሉ ጉዳዮች ላይ ጠቃሚ ዕውቀትን የሰጠው መሆኑን ገልፆልናል፡፡ በአነስተኛ የኃይል ማመንጫዎች ግንባታ አማካኝነት ታዳሽ ኃይልን ለገጠሩ ማህበረሰብ የማዳረስ ፕሮጀክትን ይዞ በፕሮግራሙ ላይ የተሳተፈው ዮሃንስ በቆይታው በተለይም ሀሳብን ለሌሎች በመግለፅ ረገድ የተሰጡትን አስተያየቶች ለወደፊት በአግባቡ እንደሚጠቀምባቸው ተናግሯል፡፡
የዕለቱን መዝግያ ንግግር ያሰሙት በቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት የስታርታፕና ኢኖቨቬሽን ፕሮሞሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ አቶ በረከት አባይነህ የክህሎት ጠቀሜታ በመደበኛ ትምህርት ከሚገኘው ዕውቀትም የላቀ መሆኑን በመጥቀስ የፕሮግራሙ ተሳታፊዎችም በተለይ ሀሳባቸውን ለሌሎች የማስረዳትና ትስስር የመፍጠር ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የፈጠራ ባለሙያዎቹ የሚገጥሟቸውን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ወደ ዕድል እንዲለውጡ የተለያዩ ታዳጊ ሀገራት ምሳሌዎችን ለአብነት በማንሳት ተናግረዋል፡፡
ፕሮግራሙ ለተሳታፊዎች የምስክር ወረቀት በማበርከት መቋጫውን አግኝቷል፡፡
ቴክ ሳይንስን ዛሬ በ10 ሰዓት ይጠብቋት
==========
በዚህ ሳምንትም ከባዮፎውል እስከ ብረት ቴክኖሎጂ እንዲሁም የአቅጣጫ ማሳወቂያ ስርዓትን ከሰሩት ሁለት ታዳጊዎች በሙያቸው ላቅ ያለ ደረጃ እስከደረሱት ዶ/ር ፈቃዱ ማሴቦ ድረስ ዳሰሳ የሚያደርጉት የአብይ ፕሮግራም፣ ቴክኖሎጂ ታሪክ፣ ብላቴናት እና የተመራማሪዎች የህይወት ታሪክ መሰናዶዎቻችንን ይዘንልዎ እንመጣለን፡፡
ሁሉም ሙሉ ሁሉም ዝግጁ ሆኖ እርሰዎን እየጠበቀ ነውና ዛሬ ቅዳሜ በ10 ሰዓት ላይ ቻናሉን ወደ MOE TV በማዞር ለእርስዎም ሆነ መላው ቤተሰብዎ የሚሆን ልምድ እና ዕውቀትን ይሸምቱ፡፡
በየሳምንቱ ቅዳሜ እንዲሁም በድጋሚ ማክሰኞ 10 ሰዓት በMOE ቴሌቪዥን ከሚቀርበው በተጨማሪ ወደ ዩትዩብ ቻናላችንም ጎራ በማለት አዳዲሶቹን ጨምሮ እስከዛሬ የተሰሩትን ፕሮግራሞች በሙሉ መመልከት ይችላሉ (https://www.youtube.com/channel/UC6jvUOLRSkVEQtc
5Annfwvg)፡፡
በተለያዩ አማራጮችም ይከታተሉን:-
ቴሌግራም t.me/TechIn2
ትዊተር twitter.com/TechinEthiopia
ለአፍሪካ ተስፋ የሰጠው የኢትዮጵያ የብሎክ ቼን እንቅስቃሴ
*******************************
ኢትዮጵያ በብሎክቼን ቴክኖሎጂ ላይ ያሳየችው ጅማሮ ለዘርፉም ሆነ ለአፍሪካውያን ትልቅ ተምሳሌት እንደሚሆን ተነገረ፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ ቢትኮይን ይፋ ከተደገ በ2009 የብሎክቼን ቴክኖሎጂ እምብዛም ተቀባይነት አላገኘም ነበር፡፡ ይህም የሆነው ቴክሎጂው የሰዎችንና የተለያዩ የንግድ ስራዎች ላይ የሚኖረው ጥቅም በብዙዎች ዘንድ ስላልታወቀ ነበር፡፡
ብሎክቼን ክፍት የሆነ የመረጃ ምንጭ ሶፍትዌር ሲሆን ይህ ባህሪው አዲስ ምርትና አገልግሎት ይዘው ለሚቀርቡ ሰዎች ህጋዊና ያለዋጋ የቀረበ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ያልተማከለ የመረጃ አስተዳደር ስርዓትንም ጥቅም ላይ እንዲውል ያስችላል፡፡ በብሎክቼን አማካኝነት የሚሰጠው አገልግሎች በየትያውም አካል ቁጥጥር የማይደረግበት ሲሆን በኔትወርኩ ውስጥ የተካተቱትት ሁሉ በዚህ ስራ ላይ ተሳታፊዎች እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ እንዲሁም ደግሞ ብሎክቼን የተለያየለየዩ አካላት ያለሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ግንኙነቶችን እንዲያደርጉ ምቹ ሆኔታን ይፈጥራል፡፡
የመረጃ ምንጫችን በሚያዚያ ወር የኢትዮጵያ መንግስት ያወጣውን መረጃ ተከትሎ በሰራው ዘገባ ኢትዮጵያ በ3500 ትምህርት ቤቶች የሚገኙ አምስት ሚሊዮን ተማሪዎችንና መምህራንን ዲጂታል መታወቂያ ስርዓት ማስተዳደር የሚያችል ሀገራዊ የመረጃ ቋት ለመገንባት መፈራረሟን ገልጧል፡፡ ስምምነቱም የተማሪዎችን የትምህርት መረጃ ለማከማቸት የሚያስችል ነው፡፡ ይህም በመንግስት ደረጃ ከተፈረሙ ተመሳሳይ ስምምነቶች ውስጥ ትልቁ ስምምነት እንደሆነ የመረጃ ምንጫችን አሳውቋል፡፡
ምንጭ techxplore
ተጨማሪ ንባብ https://techxplore.com/news/2021-05-ethiopia-blockchain-watershed-moment-technology.html
የኢንክሪፕሽን መሰረታዊ ጥቅሞች ምንድን ናቸው
========================
መረጃዎችን ያለምንም ስጋት ከሰርጎ ገቦች ወይም ፍቃድ ከሌላቸው ሰዎች በመጠበቅ በድብቅ ማስቀመጥም ሆነ መላላክ እጅግ በጣም ወሳኝ ነው። ከቅርብ አመታት ወዲህ ኢንክሪፕሽን በብዛት አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን ወንጀለኞችን ለመከላከል፣ የሰዎችን መብት ለማስጠበቅ ፋይሎችን፣ ዶክመንቶችን፣ መልዕክቶችን ለመላክና ለመጋራት፣ በኢንተርኔት አማካኝነት የሚካሄድ ማንኛውንም አይነት የምስልም ሆነ የቪዲዮ ልውውጥ ያለምንም ሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ለማስተላለፍ፣ ዲጂታል ሚዲያዎችን በመጠቀም ሙዚቃዎችንና ቪዲዮችን በህገ ወጥ መንገድ እንዳይለወጡ፣ ክፍያ ሳይፈፀም እንዳይቀዱ ወይም ክፍያም ከተፈፀመ በኋላ ለሌላ ሶስተኛ ወገን እንዳይባዙ ለማድረግ ብሎም እንዳይነበቡ በማድረግ ለባለቤቶችና ለባለመብቶች ከፍተኛ የሆነ አገልግሎት ይሰጣል።
በዘመናዊ የኢንፎርሜሽን ዘመን የግብይት ስርዓትን በኤሌክትሮኒክስ አማካኝነት መጠቀም ተችሏል። በተለይ ደግሞ የባንኪንግ አገልግሎቶች መጀመራቸው እና ዲጂታል የክፍያ ሥርዓት መዘረጋቱ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም ብዙ የስርቆት ወንጀሎች ይፈፀማሉ። ይህንን የስርቆት ድርጊት ለመከላከል ደግሞ የኢንክሪፕሽን ወይም ክሪፕቶግራፊ ቴክኖሎጂ በጣም አስፈላጊ ነው። ማንኛውም አይነት የግብይት ስርዓት በሚፈፀምበት ወቅት መልዕክቶች የሚላኩበት ዘዴ ሚስጥራዊ እንዲሆን ከማስፈለጉ አንጻር ማንኛውም የኢንክሪፕሽን ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ እንዲውል ያስፈልጋል።
ኢንክሪፕሽን ከሚሰጣቸው መሰረታዊ ጠቀሜታዎች መካካል
የመረጃዎችን አስተማማኝነት ለማረጋገጥ - ይህም ማለት በመልዕክት የሚላኩ መረጃዎች የሚያገኙት ፍቃዱን ያገኙ አካላት ብቻ መሆናቸው እና ማን የላከው መልዕክት መሆኑን ለማወቅ የሚረዳ ነው።
የመረጃዎችን ተአማኒነት ለማረጋገጥ - መልዕክት ተቀባዩ የደረሰው መልዕክት ምንም ሳይነካ ወይም ማስተካከያ ሳይደረግበት መድረሱን ለማረጋገጥ የሚረዳ ነው።
የመረጃዎችን ባለቤትነት ለማረጋገጥ - ላኪው የላከውን መልዕክት መካድ እንዳይችል ለማድረግ እና ክህደትን ወይም ከላኪው በኩል የሚታይ እምቢተኝነትን ለማስቀረት ያግዛል።
https://www.genetec.com/.../what-is-encryption-and-how....