TechIn2
1.17K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
ህንፃዎችን ወደ ግዙፍ ኃይል ማከማቻነት የሚለውጠው አዲሱ የሲሚንቶ ባትሪ
=======================
በአንድ የስዊድን የኒቨርሲቱ ተመራማሪዎች የተሰራው ጥናት ባትሪዎችን ከሲሚንቶ በማምረት ህንፃዎችን ወደ ግዙፍ ኃይል ማከማቻነት ለመለወጥ አልሟል፡፡ በቻልመርስ ዩኒቨርሲቲ የኪነ-ህንፃ እና ሲቪል ምህንድስና ትምህርት ክፍል አማካኝነት የተሰራው ይህ ምርምር እንደሚያመላክተው የሲሚንቶ ባትሪዎቹን ለመጀመሪያ ጊዜ እንደማንኛውም ባትሪ ቻርጅ እያደረጉ መጠቀም የሚቻል ሲሆን ባትሪዎችን ከታዳሽ/ዘላቂ ምንጮች ማግኛ መንገድ ተደርጎም ተወስዷል፡፡
ከተለያዩ ሙከራዎች በኋላ ተመራማሪዎቹ የደረሱበት ሰርቶ ማሳያ ይህን ይመስላል፤ በሲሚንቶ የሚሰራ ውህድ ውስጥ የተወሰኑ ካርበን ፋይበሮችን በመጨመር ኤሌክትሪክ የማስተላለፍ ብቃቱ እና የመተጣጠፍ ጥንካሬው እንዲያድግ ተደርጓል፡፡ በውህዱ መሃልም በብረት የተለበጠ የካርበን ፋይበር ድር በአኖዶቹ ላይ የሚጠቀም ይሆናል፡፡
ከዚህ ቀደም በሲሚንቶ የተሰሩ ባትሪዎች እጅግ አነስተኛ ብቃት ማሳየታቸውን የምትናገረው የምርምሩ ተሳታፊ ዶ/ር ኤማ ዣንግ ሌላ ኤሌክትሮዶችን ማምረቻ ዘዴ መፈለግ እንደነበረባቸው ትናገራለች፡፡ በዚህም ስኬታማ መሆናቸውንና በዓለማችን የመጀመሪያው ተደጋግሞ ቻርጅ መደረግ የሚችል የሲሚንቶ ባትሪ በቤተ-ሙከራ ውስጥ ሰርተው ማሳየታቸውን አስቀምጣለች፡፡
ዶ/ር ኤማ እና ፕ/ር ሉፒንግ ታንግ የሰሩት ይህ የሲሚንቶ ባትሪ በአንድ ካሬ ሜትር የሰባት ዋትሀወር ወይም በሊትር 0.8 ዋትሀወር እፍጋት አለው፡፡ ይህን ከግምት ወስደን ከቀድሞዎቹ የሲሚንቶ ባትሪ ሙከራዎች ጋራ ስናነፃፅረው አዲሱ ባትሪ በ10 እጥፍ የላቀ ብቃትን ይዞ እናገኘዋለን፡፡ ምንም እንኳን ይህ ብቃት ከሌሎቹ ተለምዶአዊ ባትሪዎች አንፃር አሁንም አነስተኛ ሊባል የሚችል የኃይል ክምችት ብቃት ቢሆንም ባትሪው እራሱ ህንፃውን ሆኖ የሚሰራ በመሆኑ ይህ ችግር የሚሆን አይመስልም፡፡
አሁን ላይ ቴክኖሎጂው ገና ጅማሬው ላይ በመሆኑ ብዙ ጥያቄዎችን መመለስ ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ አንድ የኮንክሪት ህንፃ ከ50 እስከ መቶ ዓመታት ድረስ መቆየት የሚችል በመሆኑ ባትሪውም እየታደሰ ከህንፃው እኩል ዕድሜ መዝለቅ የሚችልበትን መንገድ መፈለግ አለበት፡፡
ታድያ ቴክኖሎጂው ወደፊት ስኬታማ ሆኖ የሚቀጥል ከሆነ ዘርፈ ብዙ ግልጋሎቶችን ማቅረብ ይቻለዋል፡፡ በዚህም እንደ ድልድይ ባሉ መሰረተ ልማቶች ላይ ለሚገጠሙ የቁጥጥር ስርዓቶች የኃይል ምንጭ ሆኖ የማገልገል አቅም አለው፡፡
ምንጭ፤ Tech Xplore
ለተጨማሪ፤ https://techxplore.com/.../2021-05-world-concept...
የቅድመ ኢንኩቤሽን ስልጠና ሁለተኛ ቀን
**************************
በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት በተለያየ ደረጃ ላሉ የፈጠራ ሙያተኞች እየተሰጠ ያለው የክህሎት ማበልጸጊያ ስልጠና ዛሬም በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ቀጥሎ ውሏል፡፡ በዚህ በሁለተኛው ቀን መርሃ ግብር ከዜሮ እስከ ዚሊዮን፣ የፈጠራ ስነ-አእምሯዊ ዝግጅት፣ ሀሳብ ማፍለቅና መመዘን በሚሉ ርእሰ ጉጉዮች በዘርፉ የካበተ ልምድና እውቀት ባላቸው ሙያተኞች ገለጻ ቀርቧል፡፡
በመጀመሪያው ርእሰ ነገር የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የፋብ ቤተ-ሙከራ ማናጀር የሆነው ሐብታሙ ገብረ መስቀል አማካኝነት ገለጻ የቀረበ ሲሆን በገለጻውም ውስጥ ርዕይ አልሞ ግብ ስለማስቀመጥ፣ ይህንን ግብ እውን ለማድረግ የሚኬድባቸው መንገዶችና የሚያጋጥሙ ችግሮችን የሚመለከቱ ሀሳቦች ቀርበዋል፡፡ በዚህም ለእለቱ የመጀመሪያ በሆነው ገለጻ ላይ ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው በአቅራቢው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ለእለቱ ሁለተኛ የሆነው ርእሰ ጉዳይ ደግሞ በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች የተለያዩ ትምህርቶችን በመማር ከፍኛ ውጤት ማስመዝገብ የቻለውና የቻፓ መስራች የሆነው ናኤል ሀይለማርያም የቀረበ ሲሆን ትኩረቱንም የፈጠራ ስነ-አእምሯዊ ዝግጅት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በዚህም ገለጻ ተሳታፊዎች የተለያዩ ክህሎቶችን ማዳበር የሚችሉባቸውን መንገዶችና የያዙትን ሀሳብ እንዴት ትርጉም ወዳለው ችግር ፈች መፍትሔ መቀየር እንደሚችሉ የሚያመላክቱ ሀሳቦች ቀርበዋል፡፡
የእለቱ ስልጠናም በተያዘለት መርሃ ግብር የቀጠለ ሲሆን በእለቱ በቀረቡት ርእሰ ጉዳዩች ሰልጣኞች የፈጠራ ክህሎታቸውን ማዳበር የሚያስችላቸውን ቁም ነገር ይጨብጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በአለማችን የሚገኙ አእዋፋት ብዛት
**********************
ጥያቄው የእብደት ቢመስልም በ2015 ኮሬይ ካላግሃን የተባለ የስነ ህይወት ተመራማሪ አንድ ቀን ጠዋት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የወፍ መንጋዎች በዛፎች ላይ ሲያርፉ እና ዛፎቹ በአእዋፋቱ ሲዋጡ ከጓደኛው ጋር ተመልክተው እጅግ በጣም ተደነቁ፡፡ ከዚያም ለመሆኑ በአለማችን የሚገኙት አእዋፋት ስንት ይሆናሉ የሚል ጥያቄ መጣባቸው፡፡ ከዚያም ጊዜ ሳያጠፋ ካላግሃን እየተመለከተ ያለውን የአእዋፋት ስብስብ በመቁጠረር ስራውን ጀመረ፡፡
በመጀመሪያውም ቆጠራ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ አእዋፋትን መቁጠር ቻለ፡፡ ይህንንም ለማድረግ አእዋፋቱ የሰፈሩባቸውን ዛፎች በተለያየ አቅጣጫ ፎቶግራፍ በማንሳት እና የተለያዩ ልኬቶችን የመስራት ስልትን ተጠቅሟል፡፡ ምንም እንኳን በአለማችን የሚገኙ አእዋፋትን ቆጥሮ መጨረስ የማይታሰብ ነገር ቢሆንም ባዮሎጂስቱ ግን ከአንድ አመት በኋላ አንድ አስገራሚ ቁጥርን ማግኘቱን አሳውቋል፡፡ በአውስትራሊያዋ ሲድኒ ኒው ሳውዝ ዌልስ ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት ይፋ የተደረገው ቁጥርም 50 ቢሊዮን 428 ሚሊዮን ወፎች በምድር ላይ ይገኛሉ የሚል ነው፡፡
ጥናቱም ቀጥሉ አእዋፋቱን በየዝርያቸው የተጠኑ ሲሆን በዐለማችንም የሚገኙትን የአእዋፋት ዝርያዎች 92 በመቶ መሸፈን እንደተቻለ ተመራማሪዎቹ አሳውቀዋል፡፡ ምርምሩም በተለያዩ አስርት አመታት ውስጥ እየቀነሰ ያለውን የአእዋፋት ዝርያ መጠን መገመት የሚያስችልም ሆኗል፡፡
ምንጭ national geographic
ተጨማሪ ንባብ https://www.nationalgeographic.com/animals/article/how-many-birds-are-there-in-the-world-science-estimates?cmpid=org=ngp::mc=social::src=facebook::cmp=editorial::add=fb20210518animals-howmanybirds&sf245997971=1&fbclid=IwAR1vUUnpV8WUsy5JpWniJ_JJa3VVZdzChO2kc0HLT8aUirc8ZH_Aak5QrvE
ዝነኛው የዳርዊን ቅስት ፈረሰ
================
በኢኳዶሩ የጋላፓጎስ ደሴቶች የሚገኘው ዝነኛው የዳርዊን ቅስት (አርች) የላይኛው ክፍል መውደቁ ተዘግቧል፡፡ ከአቅራብያው የብስ ክፍል 1 ኪ.ሜትርን ርቆ በዳርዊን ደሴት ላይ የሚገኘው ቅስቱ ተፈጥሮአዊ በሆነ መሸርሸር ምክንያት ነው ለመውደቅ የበቃው፡፡
የተፈጥሮ ቅስቱ ስያሜውን ያገኘው ለታዋቂው እንግሊዛዊ ባዮሎጂስት ቻርለስ ዳርዊን መታሰብያ ይሆን ዘንድ ነው፡፡ ይህም እርሱ በአውሮፓውያኑ 1830ዎቹ ጅማሮ ላይ በጋላፓጎስ ደሴቶች ላይ ሳለ ዝግመተ ለውጥን ከማጥናቱ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ አሁን ላይ ታድያ የቅስቱ የላይኛው ከፍል መውደቁን ተከትሎ አንድ አስጎብኚ ድርጅት የተቀሩት ሁለት ቋሚ ክፍሎቹን “የዝግመተ ለውጥ ምሰሶዎች” ሲል መጥራት ጀምሯል፡፡
ዳርዊን ደሴት በእሳተ ገሞራ አማካኝነት የተፈጠረና ከባህር ወለል በታች የ10 ሜትር ጥልቀት ያለው ድንጋያማ ደሴት ነው፡፡ ደሴቱ እንደየወቅቱ እጅግ ከፍተኛ መጠን ባላቸው የሻርክና ሌሎች አሳ ዝርያዎች በስፋት እንደሚሞላ ከዚህ ቀደም የተሰሩ ጥናቶች አመላክተዋል፡፡ ከነዚህ የአሳ ዝርያዎች መካከል የሀመርሄድና ሌሎች የሻርክ አይነቶች፣ የባህር ኤሊዎች፣ ማንታ ሬዮች እንዲሁም ዶልፊኖች ይገኙበታል፡፡
አካባቢው በተለይም የባህር ውስጥ ህይወትን ለመቃኘትና እና ቅስቱን ፎቶግራፍ ለማንሳት በሚሹ ሀገር ጎብኚዎች የሚዘወተር ነው፡፡ የዳርዊን ቅስት የሚገኝበት የጋላፓጎስ ደሴቶችን የከበበው የባህር ክፍልም በስፍራው ለተሰባሰበው የባህር ህይወት ሲባል ተከልሎ ጥበቃ የሚደረግለት ሲሆን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት ሳይንስ እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) አማካኝነትም በቅርስነት የተመዘገበ ተፈጥሮአዊ ሐብት ነው፡፡
ምንጭ፤ Live Science
ለተጨማሪ፤ https://www.livescience.com/darwin-arch-collaspes-in...
ኢንስቲትዩቱ አዳዲስ ተመራማሪዎችንና ሰራተኞችን የማስተዋወቅ ስራ ሰራ
==========================
የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩቱ በ2013 በጀት ዓመት አዲስ ወደ ተቋሙ የተቀላቀሉ ተመራማሪዎችንና ሰራተኞችን የተቋሙን አጠቃላይ እንቅስቃሴ እና እርስ በርስ የማስተዋወቅ ስራ አከናውኗል።
ይህ በስልጠና መልክ የቀረበው ዝግጅት የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ ፣ ፕሮጀክት አስተዳደር፣ የቴክኢን መዋቅር እና የሰራተኞች መብትና ግዴታ በሚሉ ርዕሶች በተለያዩ አቅራቢዎች የተካሄደ ነው። በመጀመሪያም በተቋሙ ም/ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ተሾመ አማካኝነት የተቋሙን ፖሊሲ የማስተዋወቅ ስራ ተሰርቷል። በዚህም የተቋሙ ፖሊሲ የመጨረሻ ግብ ዜጎች የተሻሻለ የአኗኗር ዘይቤን እንዲከተሉ ማድረግ ማስቻል ነው ሲሊ ገልፀዋል።
ከከሰዓት በኋላ የቀጠለው መርሃ ግብር በአቶ ዳውድ መሀመድ በቀረበው የተቋሙሙን አጠቃላይ ጅማሮ እና እድገት የተመለከተ ገለጻ ተጀምሯል ። ገለጻው የተቋሙን አወቃቀር የተመለከተ መረጃም የተካተተበት ነው። አቶ ዳውድ የተቋሙን አላማ፣ ሀላፊነትና ተልእኮ የሚያሳዩ ሀሳቦችን በገለጻ መልክ አቅርበዋል።
በሁለተኛ ደረጃም የፕሮጀክት አስተዳደርን የተመለከተ ገለፃ ከፕሮጀክት ማኔጅመት ክፍል በመጡት ተመራማሪ ቶማስ ጀማል አማካኝነት ቀርቧል። በገለፃውም የፕሮጀት አስተዳደር ለጊዜ፣ ለገንዘብ፣ ለጉልበት እንዲሁም የታለመን ግብ እውን ለማድረግ ያለውን ዝርዝር ጠቀሜታ የሚያንፀባርቁ ሃሳቦች ተነስተዋል።
በቀረበውም ገለፃ ዙሪያ ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቆዎችና ሃሳቦች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ አቶ ዳውድ የፌዴራል የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ ላይ ያተኮረ የሰራተኞችን መብትና ግዴታ የተመለከቱ ህግ ነክ ሀሳቦችንም ለተሳታፊዎች አቅርበዋል።
በመጨረሻም መነቃቃትና ግለሰባዊ ስብእና ግንባታ ጋር የተያያዘ ገለጻ በአቶ ቶማስ ጀማል አማካኝነት ቀርቦ የእለቱ ዝግጅት ተጠናቋል።
በቀዳሚው የኒውክለር ፍንዳታ አማካኝነት የተፈጠረው አዲስ ቁስ
===========================
የተለየና የማይደገም መዋቅር ያለው ኮዌሰክሪስታልን ሲፈልጉ የቆዩ ሳይንቲስቶች በመጀመሪያው የኒውክለር ቦምብ ሙከራ ወቅት የተፈጠረውን ኢምፖሲብል የተሰኘ አንድ ኮዌሰክሪስታል መለየት ችለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም አይታወቅ የነበረው ይህ ኮዌሰክሪስታል ከአይረን፣ ሲልከን፣ መዳብ እና ካልሺየም የተዋቀረና ምናልባትም በተነኑ የበረሃ አሸዋ እና ኮፐር ገመዶች ጥምረት የተፈጠረ እንደሆነ ተነግሮለታል፡፡ ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ የሆኑ ቁሶች በቤተ-ሙከራ ሴንተሳይዝ የተደረጉና በሜትሮይቶች ውስጥም የተገኙ ቢሆንም በንጥረ-ነገሮች ጥምረት ለመመስረት ግን ይህ የመጀመሪያው ኮዌሰክሪስታል ሆኖ ተገኝቷል፡፡
ኮዌሰክሪስታሎች ከተለምዶአዊዎቹ ክሪስታሎች በተለየ የአተሞች አወቃቀር የተገነቡ ናቸው፤ ተለምዶአዊዎቹ ክሪስታሎች ሲደጋገሙም ተመሳሳይ ሆነው ሲቀጥሉ ኮዌሰክሪስታሎች ግን የማይቻል ተብለው ይታሰቡ የነበሩ ሲሜትሪዎች አሏቸው፡፡ በአውሮፓውያኑ 1982 ይህን አይነት የማይቻል ሲንተቲክ አሎይን በማግኘት የመጀመሪያው ሰው የሆነው ዳንኤል ሼትማን ስራው በሂሳብ ስሌት የማይሆን ነው ባሉት አጥኚዎች ዘንድ ከጥርጣሬ ወድቆ ነበር፤ ምንም እንኳን የኋላ ኋላ እ.አ.አ 2011 ላይ የኖቤል ሽልማትን በኬሚስትሪ ዘንድ ለማሸነፍ ቢያበቃውም፡፡ በተመሳሳይ ወቅት ፖል ስቴንሀርዲት እና የሙያ አጋሮቹ የማይደገሙ የባለ ሦስት እይታ (3D) መዋቅሮችን በሀልዮት ማስቀመጥ ጀምረው ነበር፤ ይህም እንዴት ሒሳብ ላያገኛቸው ሊቀር እንደቻለ የሚያብራራ ነበር፡፡
በአውሮፓውያኑ ሀምሌ 16 1945 በጆርዳና ዴል ሙኤርቶ በረሃ ከተደረገው ትሪኒቲ የኒውክለር ቦምብ ሙከራ ፍንዳታ በኋላ አጥኚዎች ከበረሃ አሸዋ የተሰሩ አረንጓዴያማ መስታውት መሰል ቁሶችን በስፋት አግኝተው ነበር፡፡
ምንጭ፤ Nature
ለተጨማሪ፤ https://www.nature.com/articles/d41586-021-01332-0...
ከአገልግሎት ውጭ የሆነው የኢንተርኔት ማፈላለጊያ
********************************
ማይክሮሶፍት ኩባንያ የኢንተርኔት ማፈላለጊያ ፕላት ፎርሙ ከአገልግሎት ውጭ መሆኑን አሳወቀ፡፡ ይህ Internet Explorer የተሰኘው ማፈላለጊያ ለ25 ዓመታት ግልጋሎት የሰጠ ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት ተጠቃሚዎች እንደ ጎግል ክህሮምና የአፕሉ ሳፋሪ እየተጠቀሙበት ባለመሆኑ ከአገልግሎት ውጭ መደረጉ ተነግሯል፡፡ መረጃው ይፋ በሆነበት ወቅት ድርጅቱ ፕላትፎርሙ በተለይ በዊንዶው 10 በ Microsoft Edge መተካቱን አሳውቋል፡፡
ተቋሙ አክሎም ማይክሮሶፍት ኤጅ ከኢንተርኔት ኤክስፕሎረር የተሻለ ፈጣንና ደህንነቱ የተረጋገጠ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ቀስ በቀስ ከአገልግሎት ውጭ እየሆነ የመጣው ኢንተርኔት ኤክስፕሎረር በቀጣዩ የፈረንጆች አመት ሰኔ 15 2022 ሙሉ ለሙሉ አገልግሎቱ ተቋርጦ ከተቋሙ እንደሚሰረዝ ተነግሯል፡፡
ኢንተርኔት ኤክስፕሎረር ከተቋረጠ በኋላ በዚህ ማፈላለጊያ አማካኝነት ይሰሩ የነበሩ መተግበሪያዎችና ድረ-ገጾች እስከ 2029 ድረስ አገልግሎታቸውን በማይክሮሶፍት ኤጅ አማካኝነት እንደሚቀጥሉም ታውቋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የጎግሉ ክሮም የገበያውን 65 በመቶ የተቆጣጠረ ሲሆን በአፕል ካምፓኒ ተበልጽጎ ድርጅቱ ባመረታቸው ቁሶች የሚሰራው ሳፋሪ ደግሞ 19 በመቶ ገደማ ሽፋን ይዟል፡፡ ፋየር ፎክስ በ3.59 በመቶ ሽፋን ሲከተል ኤጅ ደግሞ 3.39 በመቶ የገበያውን ሽፋን ይዟል፡፡
ምንጭ techxplore
ተጨማሪ ንባብ https://techxplore.com/news/2021-05-microsoft-internet-explorer.html?fbclid=IwAR24t8M9vNpCTRtQnX6k8Wl32mPtoDXxQO1f6bTNTHdlcDU7AzfoxZVM1-A