TechIn2
1.17K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
የሰሞኑ ዝናብ እና የክላውድ ሲዲንግ ሙከራዎች ውጤታማነት
==========================
ከሰሞኑን በሀገራችን መነጋገርያ ሆኖ በሰነበተው የደመናን ማዝነብ ወይም ክላውድ ሲዲንግ ቴክኖሎጂ ላይ ያተኮረ የበይነ መረብ ውይይት ዛሬ ተካሄደ፡፡ በውይይቱ ላይ በሰሞናዊው የደመናን ማዝነብ ሙከራ ከዚህ ቀደም በበልግ ወቅት ተመዝግቦ ከነበው የተሻለ ዝናብ ማግኘት ችለናል ያሉት አቶ ዮዳሄ ዘሚካኤል (በጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት የቴክኖሎጂ አማካሪ) በሙከራው ወቅቶች እስከ 2 ቶን ሀይድሮስኮፒክ ቁሶች ጥቅም ላይ መዋላቸውን ተናግረዋል፡፡ በመንግስት በኩል ይህ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ሲውል የግብርናውን ዘርፍ መርዳትና የኃይል ማመንጫ ግድቦችን መሙላት በዋና ዓላማነት ተይዞ መሆኑን ያወሱት አቶ ዮዳሄ ለዚህም ይረዳ ዘንድ በየዕለቱ ሰሜናዊ አዲስ አበባ እና መላው የአባይ ተፋሰስን ጨምሮ በየዕለቱ ከ30 እስከ 40 ቦታዎች ላይ ደመናን የማዝነብ ስራው ሲከናወን ቆይቷል ብለዋል፡፡
በውይይቱ ላይ ከሰሞኑን ሙከራዎች ባሻገርም ስለ ክላውድ ሲዲንግ ቴክኖሎጂ ምንነት፣ ለኢትዮጵያ ስለሚሰጠው ጥቅም፣ የዋጋው ጉዳይና ለህብረተስብ ግንዛቤ በማስጨበጥ ረገድ ስለሚከናወኑ ስራዎች ዳሰሳ ተደርጓል፡፡ በክላውድ ሲዲንግ ምንነት እንዲሁም ስለ ደመና አፈጣጠር፣ ባህርያት እና ዓይነቶች ዙርያ በብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ውስጥ በሚቲዎሮሎጂስትነት የሚያገለግሉት አቶ ለታ በቀለ ገለፃ የሰጡ ሲሆን በቴክኖሎጂው ሀገራዊ አስፈላጊነት ረገድም የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ክንፈ ኃ/ማርያም፣ በተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን የሃይድሮሎጂና ውሃ ጥራት ዳይሬክተሯ ወ/ሮ ሰሙነሽ ጎላ እንዲሁም በግብርና ሚኒስቴር ውስጥ በአማካሪ ሚኒስትር ደኤታነት እያገለገሉ ያሉት አቶ ኢፋ ሙለታ ማብራርያ አቅርበዋል፡፡ ቴክኖሎጂው በተለይም ሀገራችን በተደጋጋሚ ድርቅ የምትመታ ከመሆኗና ምስራቃዊው የሀገራችን ክፍልም ዝናብ አጠር ከመሆኑ አንፃር በተለይም በግብርና ዘርፍ ከፍተኛ ጥቅምን እንደሚያጎናፅፍ በኃላፊዎቹ ተነግሯል፡፡ ከዚህም ባሻገር ግን ከዝናብ ተቀላቅሎ የሚመጣ በረዶን ለመከላከል፣ ጭጋግን ለመበተን እንዲሁም በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች ላይ ጠቀሜታ አለው ተብሏል፡፡
ከቴክኖሎጂው ውድነት እና ተቋማቸውም ለዚህ መፍትሄ በማበጀት ረገድ ምን እየሰራ እንዳለ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ተወክለው የተገኙት አቶ ዋሲሁን በቀለ ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡ አቶ ዋሲሁን ቴክኖሎጂው ውድ ሊባል የሚችል ቢሆንም ከሚያስገኘው ጠቀሜታ አንፃር በአንፃራዊነት የተሻለ እንደሆነ አስቀምጠዋል፡፡ አያይዘውም ተቋማቸው የቴክኖሎጂውን ከፍተኛ ወጪ በመቀነስ ረገድ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ስለመሆኑ ተቋማቸው አንዳንድ የቴክኖሎጂው ግብዓቶችን እዚሁ በሀገራችን ለመስራት የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎችን ለአብነት ጠቅሰው ተናግረዋል፡፡
ውይይቱን ያስተባበሩትና በቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ውስጥ በሳይንስ ጋዜጠኝነት እያገለገሉ ያሉት ወ/ት ፍሬህይወት ረታ ቴክኖሎጂውን ለማህበረሰቡ በማስተዋወቅ ረገድ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን አብራርተዋል፡፡ እንደ ኢንስቲትዩት መሰል ውይይቶችን የማዘጋጀት እንዲሁም በቅርቡ ወደ ህብረተሰብ የሚደርሱ ቴክኖሎጂውን የተመለከቱ አስተማሪ ዘጋቢ ፊልሞችን ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት ጋር በመተባበር መዘጋጀታቸውንም ወ/ት ፍሬህይወት ተናግረዋል፡፡
ስልካችንን ወደተራቀቀ የሳይንስ መመርመሪያ የሚቀይረው አዲስ ግኝት
==========================
ባለፉት አስርት ዓመታት የስማርትፎን ካሜራዎች ጥራት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል፡፡ አሁን ያሉት የስማርትፎን ካሜራዎች ምስሎችን የሚያነሱ ብቻ ሳይሆኑ በሚጨንባቸው ልዩ ልዩ መተግበሪያዎች አማካኝነት የማይክሮስኮፕ አገልግሎቶችን፣ የኦግመንትድ ሪያሊቲ ሲሲተሞችን፣ የልብ ምት ልኬትን እንዲሁም ሌሎች በተለያዩ መሳሪየዎች የሚከወኑ ድርጊቶችን በቀላሉ ለመፈፀም ያስችላሉ፡፡
ታዲያ አሁን ከአንድ የምርምር ተቋም የተሰማው መረጃ እንዳሳየው የስማርትፎን ካሜራዎች ከላይ ከተጠቀሰው አገልግሎት በተጨማሪ የተራቀቁ የሳይንስ ምርምሮችን ለማከናወን እና አንዳንድ የበሽታ አይነቶችን ለመመርመር የሚያሰችል ውጤት እንደተገኘበት ተገልጿል፡፡ በአሜሪካ በሚገኝው ቴክሳስ ኤ ኤም ዩኒቨርስቲ ይፋ የተደረገው አዲስ ግኝት የስማርትፎን ካሜራን እና 50 ዶላር የሚገመት ቀላል መሳሪያን አንድ ላይ በመጠቀም ኬሚካሎችን፣ መድኃኒቶችን፣ ባዮሎጂካዊ ሞለኪውሎችን፣ በሽታ አምጪ ተህዋሲያንን እና ሌሎች የተራቀቁ የሳይንስ ምርምሮችን እንዴት ማከናወን እንደሚቻል ያመላከተ ግኝት ነው፡፡
Review of Scientific Instruments በተባለ አለም አቀፍ ጆርናል የታተመው አዲሱ ግኝት ስፔክትሮስኮፒ (spectroscopy) በተሰኘ ቴክኒክ ውስጥ የሚመደቡ ሁለት አሰራሮችን ተመርኩዞ የተከናወነ ሲሆን፤ እነሱም ፍሎረሰንስ ስፔክትሮስኮፒ እና ራማን ስፔክትሮስኮፒ በመባል ይታወቃሉ፡፡ ተመራማሪዎች ይህን ቴክኒክ በመጠቀም የቁሶችን ኬሚካላዊ ይዘት ለመለየት የቻሉ ሲሆን በስፔክትሮስኮፒ የሚመደቡትን ሁለት አሰራሮች በመተግበርም ብርሃን ከተለያዩ የቁስ ዓይነቶች ጋር የሚፈጥረውን መስተጋብርም ለማጥናት ሞክረዋል፡፡
የ ኤ ኤም ዩኒቨርስቲ ተመራመሪዎች ይህን ሳይንሳዊ ቴክኒክ በቀጥታ ከስማርትፎን ካሜራው ጋር ለማጣመር በርሃን አመንጪ የሌዘር ዳዮድ እና ብዛት ያላቸው የፕላስቲክ ሌንሶች ጥቅም ላይ አውለዋል፡፡ ይህንን አዲስ ግኝት በተለያዩ ቁሶች ላይ ለመሞከር የቻሉት አጥኚዎቹ በተለይም በካሮቶችና ባክቴሪያዎች ላይ ባደረጉት ሙከራ አስገራሚ ውጤቶችን መመልከታቸውን አስረድተዋል፡፡ የስማርትፎን ካሜራን 50 ዶላር ከሚገመት ቀላል መሳሪያ ጋር አጣምረን የኬሚካልና የባክቴሪያ አይነቶችን በቀላሉ ለመለየት ችለናል የሚሉት ተመራማሪዎች ከዚህ ግኝት በመነሳትም ለወደፊቱ የሞባይል ስልክን በመጠቀም ሌሎች ከባድ ስራዎችን ለመተግበር እንደሚያስችል የተመለከትንበት ነው ብለዋል፡፡
ግኝቱን ወደ ተግባር ለመለወጥ በተመራማሪዎች ጥቅም ላይ የዋለው የስፔክትሮስኮፒ ቴክኒክ ወደፊት በስማርትፎኖች ላይ በዲጂታል መንግድ የሚተገበር ከሆነ ሰዎች በስልኮቻቸው ብቻ በሽታ አምጪ ተሕዋስያንን ለይቶ ለማወቅ፣ በምግብ ውስጥ ያሉ ቆሻሻዎችን በቀላሉ ለመለየት እና ጠቃሚ ማዕድናትን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ የሚገለገሉበት ይሆናል፡፡
ምንጭ፡ Bigthink
ለተጨማሪ https://bigthink.com/technology.../spectrometer-phone
በንፋስ የተሰበረው የመስታውት ድልድይ
===================
የመስታውት ወለል ያላቸው ድልድዮች በዋናነት ለቱሪስት መስእብነት ታልመው የሚገነቡ አስፈሪ ድልድዮች ናቸው፡፡ ከሰሞኑን በቻይና የተከሰተ አንድ ሁነት ታድያ ታድያ በተለያዩ ዓለማት የተሰሩት የመስታውት ድልድዮችን ደህንነትን ጉዳይ በጥያቄ ምልክት ውስጥ ከቷል፡፡ ባሳለፍን ሳምንት በሰሜን ምስራቃዊው የሀገሪቱ ክፍል የሚገኘው የሎንግጂንግ መስታውት ድልድይ በሰዓት 150 ኪ.ሜ በሚጋልብ ከፍተኛ ነፋስ ምከንያት መሰበሩ የተነገረ ሲሆን በድልድዩ ላይ ሲጓዝ የነበረ ግለሰብም 91 ሜትር ከፍታ ባለው ድልድይ ላይ በፍርሀት ተንጠልጥሎ ለመቆየት ተገዷል፤ ምንም እንኳን ግለሰቡ ላይ ጉዳት ባይደርስበትም፡፡
በሼፍልድ ሃላም ዩኒቨርሲቲ የማቴሪያል ሳይንስ ተመራማሪ የሆኑት ፖል ቢንግሀም መሰል የመስታውት ድልድዮች በከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሰሩ መሆናቸውን በማውሳት በእነርሱ ላይ መራመዱ አስጊ ሊሆን እንደማይገባ ይናገራሉ፡፡ ጠንካራ የመስታውት ወለል ያላቸው ድልድዮችን ለመገንባት የተለያዩ ስልቶች አሉ፡፡ ለዚህ አንደኛው ስልት መስታውቱን ከችግሮች ይጠብቁት ዘንድ እንደ ፖሊመር ካሉ ሌሎች ግብዓቶ ጋር ቀላቅሎ መስራት ነው፡፡ በዚህ መልኩ የሚፈበረኩ መስታውቶች በውስጣቸው የሚያልፉ የብርሃን ጨረሮችን በትክክል እንዲያሳልፉና እንደማንኛውም መስታውት ሆነው እንዲታዩ ይሆናሉ፡፡ የተለያዩ መስታውት አምራቾችም በመስታውቶቹ ንብርብር መካከል ፖሊመርን በማስገባት አንደኛው ወለል ቢሰበር እንኳን የተቀሩት ጠንክረው እንዲቆዩ ማድረግ ይችላሉ፡፡
እንደ ፖል ቢንግሀም ከሆነ የተሰበረው የቻይና ድልድይ እነዚህን መሰል የማጠናከርያ ቁሶች የነበሩትና ከሚደርሱበት ስብራቶች ተነስቶ እንዲጠነክር ተደርጎ መሰራቱን ይገልፃል፡፡ ይህ ሲባል በላይኛው ንጣፍ ላይ የሚደርስ መሰበር በኬሚካሎች እንቅስቃሴ አማካኝነት ውስጡ እንዲለጠጥ በማድረግ ማጠንከር ነው፡፡ የዚህ ድልድይ መሰበር ታድያ መስታውቱ ሲሰራ በነበረበት የአሰራር ችግር ምክንያት ሊሆን እንደሚችልና ይህም ስንጥቆች እንዲስፋፉ ማድረጉ ይነገራል፡፡
መሰል ድልድዮች ጠንካራና የሚጠቀማቸው ሰውም ስጋት ሊኖረው እንደማይገባ ቢገለፅም ቅሉ የቻይናውን ድልድይ እንዳጋጠመው ከፍተኛ ነፋስ አይነት ከአቅም በላይ የሆኑ የተፈጥሮ ግፊቶች ሊሰብሩት እንደሚችል ግን ተገልጿል፡፡
ምንጭ፤ new scientist
ለተጨማሪ፤ https://www.newscientist.com/.../2277226-should-you.../...
የእስራኤሉ የሮኬት ጥቃት መከላከያ መሳሪያ
*****************************
በፍልስጤሙ ሃማስና በእስራኤል መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት ብዙ ኪሳራዎችን እያስከተለ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህ ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ በግጭቱ እየተከሰቱ ያሉ እያንዳንዱ ሁኔታዎች እየተዘገቡ ይገኛሉ፡፡ በግጭቱ ከተሰሙ መረጃዎች መካከል እስራኤል ከሀማስ የተተኮሰባትን ከ1500 በላይ ሮኬቶች የመከተችበት መከላከያ ወይም አይረን ዶም አንዱ ነው፡፡
አይረን ዶም ጥምር ተግባር ያለው መሳሪያ ሲሆን በየትኛውም የአየር ጸባይና መልክዓ ምድር ውስጥ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል እስከ 70 ኪሎሜትር ርቀት ውስጥ ያለን ከየትኛውም አቅጣጫ የሚነሳን የአየር ላይ ጥቃት በተመሳሳይ ሰዓት ማክሸፍ የሚችል መሳሪያ ነው፡፡ መሳሪያው በራፌል አድቫንስድ ዲፌንስ ሲስተም የተመረተ ሲሆን በእስራኤል የአየር ሀይል ከ2011 ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ይህ የራዳር ቁጥጥር ስልት በመጀመሪያ የተበለጸገው በኤልታ አማካኝነት ነው፡፡
ለዚህ ራዳር ጸረ ሮኬት መሰራት ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ የሚነገረው ከ2000 ወዲህ በሄዝቦላህ እና ሀማስ በተወሰዱ ከባድ የሮኬት ጥቃት ነው፡፡ በ2013 ይፍታህ ሻፑር በተባለ ተመራማሪ የተሰራ ጥናት እንደሚያመለክተው መሳሪያው ጥቃት የሚፈጸምበትን ወይም የተተኮሰው ሮኬት የሚያርፍበትን ትክክለኛ ቦታ መለየት የሚችልና ሊያደርስ የሚችለውንም ጉዳት መተንበይ የሚያስችል ነው፡፡ ይህም ጉዳት የማያደርስ ሮኬት ላይ ሀይል እንዳይባክን ያደርጋል፡፡
መሳሪያው እስካሁን በሺዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶችን ማምከን የቻለ ሲሆን የስኬታማነት መጠኑም ከ90 በመቶ በላይ እንደሆነ አምራቹ አሳውቋል፡፡ ይህ ሁሉ ግን ከሰላም አይበልጥምና ለአለማችን ሰላም ተመኘን
ምንጭ The Hindu
ተጨማሪ ንባብ https://www.thehindu.com/.../explaine.../article34556339.ece
አሳማና አይጦች በቂጣቸው መተንፈስ እንደሚችሉ ተረጋገጠ፤ የሰው ልጆችስ?
========================
ተመራማሪዎች ይህን እውነት ማረጋገጥ የቻሉት እንስሳቱ ላይ በቂጣቸው በኩል ኦክስጅንን በመላክ ነው፡፡ ይህን ለመሞከር ምን አነሳሳቸው የሚል ጥያቄ ከጫረብዎት፤ መልሱ የኮቪድ-19 ወረርሺኝን ተከትሎ በጉሮሮ በኩል አየር በማቅረብ ለብዙዎች እርዳታ እየሰጠ ላለው የቬንትሌተር አሰራር ሌላ አማራጭን ለማምጣት በማሰብ ነው፡፡
ቬንትሌተሮች ኦክስጅንን ወደ ሳንባ የሚልኩና ካርበን ዳይ ኦክሳይድንም መልሰው የሚያወጡ ናቸው፡፡ ሆኖም በአሁኑ ሰዓት ከፍተኛ የሆነ የቬንትሌተር እጥረት አጋጥሟል፡፡ ለዚህ መፍትሄ ይሆን ዘንድ ሀኪሞች ኤክስትራኮርፖሪያል ሜምብሬን ኦክስጅኔሽን (ECMO) የተሰኘውን ስልት ተጠቅመው ደምን ከሰውነት እያወጡ በኦክስጅን ሞልተው ዳግም ወደ ሰውነት መመለስ የሚችሉ ቢሆንም ስልቱ እንደ ደም መርጋትና መድማት ያሉ የጤና ችግሮችን የመከሰት ስጋትን ያዘለ ከመሆኑም ባሻገር ማሽኖቹ እራሳቸው ከቬንትሌተሮች የበለጠ አነስተኛ መሆናቸው የተወሰነ ስጋት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡
ለዚህ ችግር መፍትሄ በመሻት ተመራማሪዎቹ አንጀታቸውን ተጠቅመው የሚተነፍሱ የውሃ ውስጥ እንስሳትን ተመልክተው ሙከራዎችን አድርገዋል፡፡ በውጤቱም መሰረት ለሙከራ አነስተኛ ኦክስጅን ባለበት ስፍራ እንዲቀመጡ የተደረጉ አይጦች በ11 ደቂቃዎች በላይ መቆየት ሳይችሉ የቀሩ ሲሆን አየር ወደ ልባቸው እንዲደርስ ተደርጎ በአንጀታቸው ላይ የቬንትሌሽን ስርዓት የተቀመጠላቸው አይጦች ግን 75 በመቶው ለ50 ደቂቃዎች ያህል በሕይወት መቆየት ችለዋል፡፡ የጥናት ቡድኑ ተመሳሳይ መንገድን በመጠቀም ግን ደግሞ የሚገባውን ኦክስጅን ከጋዝ ይልቅ በፈሳሽ መልኩ እንዲሆን ሲያደርግም አይጥ እና አሳማዎቹ ላይ በተመሳሳይ አበረታች የሆነ ውጤትን አግኝቶበታል፡፡
ይህ ስልት በሰው ልጆች ላይ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ከዚህም በላይ ሙከራ የሚያስፈልገው ይሆናል፡፡ ለምሳሌ በዚህ ስልት አማካኝነት አንጎልንና አንጀት የሚያገናኘው የቫገስ ነርቭን ሊጎዳ መቻል አለመቻሉን በቅድሚያ መመልከት ይገባል፡፡ በተጨማሪም ሙከራው የተደረገባቸው እንስሳት በኮቪድ የተያዙ ሰዎች ያሉበትን የጤና ሁኔታ የሚወክሉ አይደሉም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን የጥናት ቡድኑ በቀጣዩ የፈረንጆች አመት ላይ ሙከራን በሰው ልጆች ላይ ለማድረግና ህክምናውንም መስጠት ለመጀመር አቅዷል፡፡
ምንጭ፤ Live Science
ለተጨማሪ፤ https://www.livescience.com/mammals-can-breathe-through...
የአሜሪካን አየር ኃይል በዓይነቱ የተለየ ራስ ገዝ አውሮፕላንን ሞከረ
=======================
የአሜሪካን አየር ኃይል በተገጠመለት ሶፍትዌር እና ሀርድዌር አማካኝነት በራሱ የሚንቀሳቀሰውንና ስካይቦርግ ተብሎ የተሰየመውን ሰው አልባ በራሪ ባሳለፍነው ወር ለመጀመሪያ ጊዜ መሞከሩ ተነገረ፡፡ ጦር ኃይሉ በዚህ ቴክኖሎጂ አማካኝነት በሰው ልጅ አማካኝነት በሚንቀሳቀሱና ሰው አልባ በሆኑ አውሮፕላኖች አማካኝነት ያለውን ቅንጅት ለማሳደግ ያለመ ነው።
በፍሎሪዳው የቲንዳል የአየር ኃይል ማዕከል ውስጥ ለ130 ደቂቃዎች ያህል በተደረገው የሙከራ በረራ ደህንነቱ መጠበቁን የሚያመላክቱት የአዲሱ አውሮፕላን መሰረታዊ ባህርያት ተገምግመውበታል፡፡ አውሮፕላኑም በተቀመጠለት የከባቢ ወሰን (geo-fences) ውስጥ በመቆየት የጉዞ ትዕዛዝ ሲቀበልና የተቀናጁ እንቅስቃሴዎችን ሲከውን ቆይቷል፡፡
የአሜሪካን አየር ኃይል የምርምር ቤተ-ሙከራ በሰው የሚንቀሳቀሱ አውሮፕላኖችን ሙሉ በሙሉ የሚተኩ ግን ደግሞ በሰው አማካኝነት መንቀሳቀስን እንደ አማራጭ የያዙ አውሮፕላኖችን ለመስራት በመንቀሳቀስ ላይ ነው።
አዲሱ አውሮፕላንም የወደፊቱ የስካይቦርግ ቴክኖሎጂ ማዕከል እንዲሆን የሚጠበቅበት ሲሆን በሌላ አጠራር አውቶኖሚ ኮር ሲስተም (ACS) በሚል ስያሜ በሚታወቁት ሰው አልባ አውሮፕላኖች ላይም ያለውን ዕምነት ለመገንባት እንደሚረዳ ተነግሮለታል፡፡
የአሜሪካን አየር ኃይል የምርምር ቤተ-ሙከራ በመጪዎቹ ጊዜያት ውስጥ አውቶኖሚ ኮር ሲስተምን ተጠቅመው በሚንቀሳቀሱትን አውሮፕላኖች ላይ ጭምሮ የተለያዩ ሙከራዎችን ለማድረግ አቅዷል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም ስካይቡርግን የፈበረከው ቡድን ሰው አልባ አውሮፕላኖቹ ተልእኮዎችን ሙሉ በሙሉ በራሳቸው የሚወጡና ይህን ሲያደርጉም ኪስን በማይጎዳ መልኩ እንዲሆን ያልማል፡፡ በጠቅላላው ቴክኖዎሎጂው ጦር ሜዳ ላይ ውሳኔዎችን በኮምፒውተር ፍጥነት መስጠት እንዲችልና የሰው ልጅ ይሆኑት ወታደሮችን ህይወትም መጠበቅ እንዲችል ታልሞ የተሰራ ነው።
ምንጭ፤ Tech Xplore
ለተጨማሪ፤ https://techxplore.com/.../2021-05-air-autonomous-drone...
ወደ የትኛውም የአለማችን ክፍል በ4 ሰዓት ውስጥ በ100 ዶላር
********************************
ቡም ሱፐር ሶኒክ የተሰኘው ፈጣን የአየር መንገድ ወደ የትኛውም የአለማችን ክፍል በ4 ሰዓት ውስጥ በ100 ዶላር ሰዎችን ለማድረስ ዝግጅቱን መጨረሱ ተሰማ፡፡ በአሁኑ ወቅት የበረራ ኢንዱስትሪው በትልቅ ኪሳራ ውስጥ ሲሆን ከካርቦን ልቀት ጋር የተያያዘ ችግርን ጨምሮ ብዙዎቻችን የአየር በረራን የመጠቀም ልምዳችን ዝቅተኛ ነው፡፡ ከኮንኮርድ መዳከም ጋር ተያይዞ ተቀዛቅዞ የነበረው የከፍተኛ ፍጥነት የአየር ትራንስፖርት በቡሙ ሱፐርሶኒክ ትልቅ ህልም ማንሰራራት ጀምሯል፡፡
በእንግሊዝና ፈረንሳይ ጥምረት ተቋቁሞ የነበረው ኮንኮርድ ፈጣን የአየር ትራንስፖርት በዘርፉ ከ1969 እስከ 2003 የቆየ ሲሆን ዋጋው የማይቀመስና ለከባቢ አየር ከፍተኛ ጠንቅ ነበር፡፡ አሁን ቴክኖሎጂው እያደገ የፈጠራ ሙያተኞች ከአካባቢ ጋር የተስማሙና በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት የሚሰጡ ሱፐርሶኒክ እና ሀይፐርሶኒክ የአውሮፕላን ፕሮጀክቶችን ቀርጸው እየሰሩ ነው፡፡
ሲኤንኤን ትራቭል ከድርጅቱ ሀላፊ ጋር አደረግኩት ባለው የመረጃ ልውውጥ ፕሮጀክቱ በ2026 መደበኛ ስራ ለመስራ ወደ አየር እንደሚወጣ አሳውቋል፡፡ የድጅቱ ሀላፊ የሆኑት ብሌክ ስኮል ሌሎች የረጅም ጊዜ እቅዶች እንዳሏቸውና እስካሁን በበረራ ዘርፍ ባልታየ ፍጥነት አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አሳውቀዋል፡፡
እነዚህ ከ65 እስከ 88 ተጓዦችን ማስተናገድ እንዲችሉ ታስበው ዲዛይን የተደረጉት ፈጣን አውሮፕላኖች ውቅያኖስ አቋርጠው የሚጓዙ ናቸው፡፡ በፍጥነት ደረጃም ከሎሳንጀለስ ወደ ሲድኒ ስምንት ሰዓት ተኩል ብቻ የሚጨርስ ይሆናል፡፡ ይህ በመደበኛ በረራ አስራ አምስት ሰዓት ከ10 ደቂቃ የሚወስድ ነው፡፡
ምንጭ CNN
ተጨማሪ ንባብ https://edition.cnn.com/.../boom-supersonic.../index.html...
ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎችን ያሰባሰበው የቴክኢን ቅድመ ኢንኩቤሽን ፕሮግራም ተጀመረ
=================
የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ያዘጋጀውና የአራት ቀናት ቆይታ የሚኖረው ቅድመ ኢንኩቤሽን ፕሮግራም ዛሬ በይፋ ተጀመረ፡፡ ከተለያዩ የትምህርት ደረጃ እና ሙያ ዘርፍ የተውጣጡ የፈጠራ ባለሙያዎችን በማሳተፍ የተካሄደው ይህ ፕሮግራም ተሳታፊዎቹን በማንኛውም የኢንኩቤሽን ፕሮግራም ውስጥ ተሳታፊ ለመሆን ብቁ የሚያደርጋቸውና ሀሳባቸውንም ወደ ቢዝነስ እንዲለውጡ የሚያስችላቸው ነው፡፡
ኢትዮጵያ የፈጠራ ሀሳባቸውን ወደ ተግባር መለወጥ የሚችሉ ሰዎች እንዳላት ይታመነናል ያሉት የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር ኢ/ር ተሾመ ሳህለማርያም እነዚህን ሰዎች የማሰባሰቡን ድርሻ ኢንስቲትዩታቸው ወስዶ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ብዙዎቹ ታላላቅ ምጣኔ-ሐብትን መገንባት የቻሉት ሀገራት ለስኬት የበቁት በትምህርት እና የፈጠራ ሀሳብ ላይ በመስራታቸው መሆኑን ያወሱት ኢ/ር ተሾመ የዝግጅቱ ተሳታፊዎችም የፈጠራ ሀሳባቸውን በአግባቡ አንፀው ወደ ቢዝነስ ሀሳብ በመለወጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፎካካሪ የሆነ ቢዝነስ መገንባት እንዳለባቸው በዚሁ የመክፈቻ ንግግራቸው አሳስበዋል፡፡
በዛሬው መሰናዶ ላይ በክብር እንግድነት በመገኘት ለተሳታፊ የፈጠራ ባለሙያዎቹ የማነቃቅያ ንግግር ያቀረበው ወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ እንዲሁም የአይከን አፍሪካ መስራችና ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆነው አቶ ኢዘዲን ከሚል ነበር፡፡ እርሱ ባይኖር ኖሮ የራሴን ድርጅት መመስረትም ሆነ አሁን ባለውበት ደረጃ ለመድረስ አልችል ስነበር “ኮቪድ ለእኔ ትልቅ ዕድል ነው” ያለው አቶ ኢዘዲን ተሳታፊ የፈጠራ ባለሙያዎቹም የሚገጥሟቸው ተግዳሮቶችን ወደ እድል እንዲለውጡ ምክሩን ለግሷል፡፡ አያይዞም የኮቪድ 19 ወረርሺኝን የተመለከቱትን ጨምሮ እሳካሁን በአራት ዘርፎች 36 የተለያዩ ፈጠራና ምርቶችን መስራት መቻሉን እና ከነዚህ ውስጥም 13 ያህሉን በፓተንት ማስመዝገብ መቻሉን ለተሳታፊዎች አሳይቷል፡፡
ከነዚህ በተጨማሪም በዛሬው መርሀ ግብር የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪ በሆኑት አቶ ሙሉጌታ አንበሳ፣ አቶ አባይሰው አየለ፣ አቶ በላቸው አለማየሁ እና አቶ አብዱለጢፍ ሀቢብ በተለያዩ ጉዳዮች ዙርያ ገለፃ ቀርቧል፡፡ አቶ አባይሰው የሰው ልጅ ስላለፈባቸው የፈጠራ ሂደቶች፣ የኢኖቬሽን ምንነት፣ በሀገራችን ያሉ መፍትሄ የሚያሻቸው ተግዳሮቶች እንዲም በአሁኑ ሰዓት ዓለምን በከፍተኛ ደረጃ እየመሩ ባሉት እንደ ቢግ ዳታ ኮምፒውቲንግ፣ ዲኤንኤ ባዮቴክኖሎጂ፣ ብሎክቼይን የመሳሰሉ ቴክኖሎጂዎች ላይ ያተኮረ ገለፃን አቅርበዋል፡፡ አቶ በላቸው በበኩሉ የኢትዮጵያ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ፖሊሲ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ እና በኢትዮጵያ ስላለው የኢኖቬሽን ገፅታና ተግዳሮት ያብራራ ሲሆን የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ምንነት፣ ምስረታና ተግባራት እንዲሁም በቅድመ ኢንኩቤሽን ፕሮግራሙ ላይ ያተኮረውን ገለፃ ደግሞ አቶ ሙሉጌታ አማካኝነት አቅርቧል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ የተሳተፉት ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች የፈጠራ ሀሳብ ያላቸው ሆነው የሀሳባቸው ጥንካሬ ላይ ምልከታን ባደረገ ውድድር አማካኝነት የተመለመሉ ናቸው፡፡ ይህ ፕሮግራምም ከላይ ከተገለፁት ዓላማዎች ባሻገር ይህ ሀሳባቸውን እንዲያንፁና ወደ አዋጭ ቢዝነስነት እንዲለውጡ የሚያስችላቸው ስለመሆኑ በአዘጋጆቹ ተነግሯል፡፡
ህንፃዎችን ወደ ግዙፍ ኃይል ማከማቻነት የሚለውጠው አዲሱ የሲሚንቶ ባትሪ
=======================
በአንድ የስዊድን የኒቨርሲቱ ተመራማሪዎች የተሰራው ጥናት ባትሪዎችን ከሲሚንቶ በማምረት ህንፃዎችን ወደ ግዙፍ ኃይል ማከማቻነት ለመለወጥ አልሟል፡፡ በቻልመርስ ዩኒቨርሲቲ የኪነ-ህንፃ እና ሲቪል ምህንድስና ትምህርት ክፍል አማካኝነት የተሰራው ይህ ምርምር እንደሚያመላክተው የሲሚንቶ ባትሪዎቹን ለመጀመሪያ ጊዜ እንደማንኛውም ባትሪ ቻርጅ እያደረጉ መጠቀም የሚቻል ሲሆን ባትሪዎችን ከታዳሽ/ዘላቂ ምንጮች ማግኛ መንገድ ተደርጎም ተወስዷል፡፡
ከተለያዩ ሙከራዎች በኋላ ተመራማሪዎቹ የደረሱበት ሰርቶ ማሳያ ይህን ይመስላል፤ በሲሚንቶ የሚሰራ ውህድ ውስጥ የተወሰኑ ካርበን ፋይበሮችን በመጨመር ኤሌክትሪክ የማስተላለፍ ብቃቱ እና የመተጣጠፍ ጥንካሬው እንዲያድግ ተደርጓል፡፡ በውህዱ መሃልም በብረት የተለበጠ የካርበን ፋይበር ድር በአኖዶቹ ላይ የሚጠቀም ይሆናል፡፡
ከዚህ ቀደም በሲሚንቶ የተሰሩ ባትሪዎች እጅግ አነስተኛ ብቃት ማሳየታቸውን የምትናገረው የምርምሩ ተሳታፊ ዶ/ር ኤማ ዣንግ ሌላ ኤሌክትሮዶችን ማምረቻ ዘዴ መፈለግ እንደነበረባቸው ትናገራለች፡፡ በዚህም ስኬታማ መሆናቸውንና በዓለማችን የመጀመሪያው ተደጋግሞ ቻርጅ መደረግ የሚችል የሲሚንቶ ባትሪ በቤተ-ሙከራ ውስጥ ሰርተው ማሳየታቸውን አስቀምጣለች፡፡
ዶ/ር ኤማ እና ፕ/ር ሉፒንግ ታንግ የሰሩት ይህ የሲሚንቶ ባትሪ በአንድ ካሬ ሜትር የሰባት ዋትሀወር ወይም በሊትር 0.8 ዋትሀወር እፍጋት አለው፡፡ ይህን ከግምት ወስደን ከቀድሞዎቹ የሲሚንቶ ባትሪ ሙከራዎች ጋራ ስናነፃፅረው አዲሱ ባትሪ በ10 እጥፍ የላቀ ብቃትን ይዞ እናገኘዋለን፡፡ ምንም እንኳን ይህ ብቃት ከሌሎቹ ተለምዶአዊ ባትሪዎች አንፃር አሁንም አነስተኛ ሊባል የሚችል የኃይል ክምችት ብቃት ቢሆንም ባትሪው እራሱ ህንፃውን ሆኖ የሚሰራ በመሆኑ ይህ ችግር የሚሆን አይመስልም፡፡
አሁን ላይ ቴክኖሎጂው ገና ጅማሬው ላይ በመሆኑ ብዙ ጥያቄዎችን መመለስ ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ አንድ የኮንክሪት ህንፃ ከ50 እስከ መቶ ዓመታት ድረስ መቆየት የሚችል በመሆኑ ባትሪውም እየታደሰ ከህንፃው እኩል ዕድሜ መዝለቅ የሚችልበትን መንገድ መፈለግ አለበት፡፡
ታድያ ቴክኖሎጂው ወደፊት ስኬታማ ሆኖ የሚቀጥል ከሆነ ዘርፈ ብዙ ግልጋሎቶችን ማቅረብ ይቻለዋል፡፡ በዚህም እንደ ድልድይ ባሉ መሰረተ ልማቶች ላይ ለሚገጠሙ የቁጥጥር ስርዓቶች የኃይል ምንጭ ሆኖ የማገልገል አቅም አለው፡፡
ምንጭ፤ Tech Xplore
ለተጨማሪ፤ https://techxplore.com/.../2021-05-world-concept...