TechIn2
1.16K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
ከሙዝ ቆሻሻ ምንጣፎችንና ጨርቃጨርቆችን የሚያመርተው የኡጋንዳ ስታርታፕ
=============================
ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ኡጋንዳ ከፍተኛ መጠን ያለው የሙዝ ምርት የምታቀርብ ሀገራት ናት፡፡ በሀገሪቱ ከሚመረተው ከፍተኛ የሙዝ ምርት ጋር ተያይዞ ወደቆሻሻ የሚጣለው የምርት ውጋጅም እጅግ ከፍተኛ ሲሆን ይህም በየአካባቢው ላሉ የሙዝ መሸጫ ስፍራዎችና መገበያያ ቦታዎች ትልቅ ችግር ይፈጥራል፡፡ ታዲያ ይህን ክፍተት ለመሙላት ኪማኒ ሙቱሪ በተባለ ግለሰብ የተቋቋመው አንድ ስታርታፕ ከሙዝ የሚወጣውን ውጋጅና ቆሻሻ በመጠቀም ለአካባቢ ተስማሚ የሆኑ የምንጣፍ፣ ጨርቃ ጨርቅ እና የፀጉር ማራዘሚያ ምርቶችን በማምረት ላይ ይገኛል፡፡
ቴክስፋድ የሚል ስያሜ ያለው ይህ የኡጋንዳ ስታርታፕ ከሙዝ የሚወጣውን የቆሻሻ ውጋጅ ጠቃሚነት ወዳላቸው ምርቶች ለመቀየር በመቁረጫ መሳሪያዎች ተቆራርተው ከተዘጋጁ በኋላ የሙዝ ውጋጆቹን ወደ ፋይበር መቀየር በሚያስችል ማሽን እንዲገቡ ይደረጋል፡፡ ይህ ከተከናወነ በኋላ ከማሽኑ የሚወጣውን የፋይበር ውጤት በረዣዥም ቅርፅ በማድረግና በፀሃይ በማድረቅ ወደ ቀጣዩ የማቀነባበር ሂደት እንዲያልፍ ይደረጋል፡፡ የስታርታፑ ባለሙያዎች ይህን ረዥም የማቀነባበር ሂደት አልፈው ጥራቱን የጠበቀ የጨርቃ ጨርቅ እና ምንጣፍ ውጤቶችን ከማምረታቸው ባለፈ ሁሉም ምርቶች ለአካባቢ ተስማሚ እንዲሆኑ ተደርገው መሰራታቸው ይበልጥ ተቀባይነት እንዲያገኙ አስችሏቸዋል፡፡
የድርጅቱ መስራች ኪማኒ ሙቱሪ ከሙዝ የቆሻሻ ውጋጅ የሚመረቱትን የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶች ረዥም ጊዜ በፈጀ የቤተ ሙከራ ሂደት እንደደረሱባቸው እና አሁን ላይ ከሙዝ በሚገኘው ፈይበር አማካኝነት ከምንጠፎች በተጨማሪ ለሴቶች ትልቅ ጥቅም የሚሰጥ ባዮዲግሬደብል የጸጉር ማራዘሚያ መስራት መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡ ሴቶች ይህን ምርት ቢጠቀሙ እደሌሎች የጸጉር ማራዘሚያ ውጤቶች ለመበስበስ የማይቸገሩ በመሆናቸው ለጓሮ አትክልቶችና ማሳደጊያ ቦታዎች እንደማዳበሪ ሊጠቀሙባቸው እንደሚችሉም ይገልጻሉ፡፡
የስታርታፕ ድርጅቱ አሁን ላይ የስራ እድል ከፈጠረላቸው 23 ሰዎች በተጨማሪ በቀጣይ ጊዜያት ይበልጥ ለማሳደግ እቅድ እንዳላቸው የሚናገሩት የድርጅቱ መስራች ኪማኒ ሙቱሪ ባለፍ አመት ካስገባው የ41 ሺ ዶላር ገቢም አሁን ላይ ከፍተኛ ጨማሪ እንደታየ እና የምንጣፍ ምርቱ አምና ከነበረው በእጥፍ ጨምሮ አሁን ላይ 2,400 እንደደረሰ ይገልጻሉ፡፡ በተለይ የምንጣፍ ምርቶቻቸውን ወደተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት መላክ መጀመራቸውን የሚናገሩት ኪማኒ በዚህም ከፍተኛ ገቢ ማስገባት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡
https://www.reuters.com/business/environment/uganda-start-up-bets-big-banana-waste-2021-04-16/
7 ጊዜ በመብረቅ ተመቶ የተረፈው ግለሰብ
======================
ሮይ ሰሊቫን የተባለው አሜሪካዊ ከአውሮፓውያኑ 1912 እስከ 1983 ድረስ ምድራችን ላይ በኖረባቸው 71 ዓመታት ውስጥ ለሰባት የተለያዩ ጊዜያት በመብረቅ ለመመታት በቅቷል፤ እንዲያውም አንዱን በገለልተኛ አካል ማረጋገጥ ስላልተቻለ ነው እንጂ በልጅነቱ ሌላ ስምንተኛ መብረቅ እንደመታው ይነገራል፡፡ ይህ አስገራሚ ሰው ከመብረቅ ብቻ አይመስልም ፀቡ፤ በህይወት ዘመኑ ለ22 ጊዜ ግዙፍና አደገኛ እንስሳ ከሆኑት ድቦች ጋርም ተፋልሟል፡፡
ግለሰቡ ለመጀመሪያ ጊዜ መብረቅ የጎበኘው እ.አ.አ በ1942 የመብረቅ መከላከያ ባልተገጠመለት ማማ ውስጥ ከዝናብ ተጠልሎ ሳለ ነበር፡፡ በወቅቱ ማማው እራሱ ሰባት ጊዜ በመብረቅ በመመታቱ የተነሳ በእሳት ስለተያያዘ እግሬ አውጪኝ ብሎ በተወሰነ ለመራቅ ቢሞክርም በህይወት ዘመኔ ከባዱ ነው ያለው የመብረቅ ቁጣ ከውጪ ተቀብሎታል፡፡ ይህም የቀኝ እግሩ ላይ ቃጠሎን አደረሰበት፡፡
በቀጣይ መብረቅ የጎበኘው ከ27 ዓመታት በኋላ እ.አ.አ በ1969 መኪና እየነዳ ሳለ ነበር፡፡ እንደ ተለምዶው ቢሆን የመኪና ብረት ከዚህ አደጋ ሊጠብቀው የሚገባ ቢሆንም በአካባቢው ዛፍ ላይ ወርዶ የነበረው መብረቅ ነጥሮ በተከፈተው የመኪናው መስኮት በኩል ገብቶ መቶታል፡፡ አደጋው ሲደርስ እራሱን እንዲስት ያደረገው ሲሆን ቅንድብ፣ የአይን ሽፋሽፍት እና ፀጉሮቹም ተቃጠሉ፡፡ ሁኔታውን ይበልጥ አስገራሚ የሚያደርገው ሮይ እራሱን በሳተበት ሰዓት ያለ ሹፌር ሲንቀሳቀስ የነበረው መኪናው ገደል አፋፍ ላይ ሲደርስ በራሱ የመቆሙ ነገር ነው፡፡
ሦስተኛው ጥቃት እ.አ.አ በ1970 ሲሆን በጓሮው ውስጥ ሳለ ነበር በወቅቱ የጣለው መብረቅ በአቅራብያ የተተከለውን የኤሌትሪክ ማስተላለፊያን ከመታ በኋላ ነጥሮ እርሱ ላይ አርፏል፡፡
አራተኛው ደግሞ ወደ ሁለት ዓመት ጠብቆ ሲመጣ እንዲሁ ፀጉሩን አቃጥሎት አልፏል፡፡
ከአንድ ዓመት በኋላም እ.አ.አ በ1973 እንደርሱ አነጋገር ከባድ ዝናብ ሊጥል የሚመስል ደመና ሲፈጠር ካየ በኋላ መኪናውን አስነስቶ ከአካባቢው ለማምለጥ ቢሞክርም ደመናው እግር በእግር ሲከተለው ቆየ፡፡ ታድያ ደመናው መከታተሉን አቁሟል ብሎ እንዳሰበ ከመኪናው ሲወጣ ከየት መጣ ያልተባለው አምስተኛው መብረቅ ድንገት ወርዶ አጩሎታል፡፡ መብረቁ በግራ እጁ እና እግሩ ተላልፎ ጫማው ላይ ያረፈ ሲሆን ፀጉሩም ከመቃጠል አልዳነም፡፡
ስድስተኛው መብረቅ ላይም እንዲሁ መብረቅ ሲከተለው ማየቱን ጠቅሶ ለማምለጥ ቢጥርም በመብረቁ መመታቱ ፀጉሩም መቃጠሉ አልቀረለትም፡፡
ሰባተኛው እና የመጨረሻው መብረቅ የመታው አሳ በማጥመድ ላይ ሳለ ነበር፡፡
ሮይ ለወትሮ ፈሪ የሚባል ሰው ያልነበረ ቢሆንም አራተኛው መብረቅ ከመታው በኋላ ግን ሊያጠፋው የሚሻ አንድ ኃይል እየተከታተለው መሆኑን አምኖ መፍራት መጀመሩ ተዘግቧል፡፡ ሌላው ሮይን ለየት የሚያደርገው ሁሌም በመኪናው ውሃ ይዞ የሚሄድ ሲሆን በዚህም መብረቁ ፀጉሩን ሲያቃጥለው እሳቱን ለማጥፋት ሲጠቀምበት ኖሯል፡፡ በመጨጨረሻው ጥቃት ላይ ታድያ አንድ ድብ መጥቶ ውሃውን ሊሰርቅበት ቢሞክርም በዱላ ተፋልሞ ማስጣሉን ይናገራል፡፡
የመብረቅ ቤተኝነቱ ታድያ በአንድ አጋጣሚ ወደ ቤተሰቡም ተጋብቶ ሳይሆን አይቀርም ባለቤቱም በጓሮዋቸው ልብስ እያሰጣች ሳለ በመብረቅ ተመታ ነበር፡፡ በወቅቱ ሮይ ደርሶላት ስለነበር ያለ ጉዳት ልታመልጥ ችላለች፡፡
ምንጭ፤ The Michigan Weather Center
ለተጨማሪ https://michigan-weather-center.org/thunder-lightning
ሳይንቲስቶች ወደምድር የቀረበ አነስተኛ ብላክ ሆል ማግኘታቸውን አስታወቁ
==========================
በኦሃዮ ስቴት ዩኒቨርስቲ የሚገኙ የኮስሞሎጂ ተመራማሪዎች ለምድር በጣም ቀርቦ በመገኘት እና በአነስተኛነቱ ሪኮርድ የሰበረ አዲስ ብላክ ሆል (Black Hole) ማግኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡ እስከዛሬ ሊገኙ ከቻሉት የብላክ ሆል አይነቶች በመጠኑ አነስተኛ ነው የተባለው ይህ ግኝት ከምድር ያለው ርቀትም 1,500 የብርሃን አመት እንደሚደርስ ተነግሯል፡፡
ዩኒኮርን ብለው የሰየሙት ይህ ብላክ ሆል ከኛዋ ፀሃይ በሶስት እጥፍ እንደሚልቅ ቢነገርለትም፤ ከሌሎች የብላክ ሆል ይዘቶች አንጻር እጅግ አነስተኛ መጠን እንዳለው ተጠቅሷል፡፡ አዲሱ ብላክ ሆል ሞኖሴሮስ (Monoceros) በተባለ የህብረ ከዋክብት መካማቻ ውስጥ እንደተገኘ የሚናገሩት የምርምሩ ተሳታፊ ዶ/ር ታሪንዱ ጃያሲጌ በዚህ የህዋ ክፍል መገኘቱ እና በአይነቱ የተለየ ብላክ ሆል መሆኑ ይህን የዩኒኮርን ስያሜ እንዲያገኝ ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡
በዚህ ህብረ ኮከብ ዙሪያ ሲደረግ የነበረው የስበት ንቅናቄ ታይዳል ዲሰቶርሽን የተባለ የሁለት እና ከዚያ በላይ የህዋ አካላት የመሳሳብ ውጤት መሆኑን የሚያስረዱት ተመራማሪው ይህም ከከኮቡ አጠገብ እንደ ብላክ ሆል ያለ ትልቅ የህዋ አካል የስበት ንቅናቄ እየፈጠረ መሆኑን የሚያሳይ ነው ይላሉ፡፡ የብላክ ሆሎ መገኘት በአይን የሚታይ ወይም በሌላ መስፈርት የሚገለፅ ሳይሆን ተመራማሪዎች በለኩት የብርሃን ልኬት እና ሌሎች የሞገድ ርዝመት መለኪያዎች መሆኑን የሚናገሩት ዶ/ር ጃያሲጌ በልኬቱም መሰረት ከከኮቡ የተገኙ መረጃዎች እንደሚያሳዩት እንደ ብላክ ሆል ሊጠራ የሚችል ግዙፍ የህዋ አካል የስበት ንቅናቄውን በመፍጠር በምድር እና በጨረቃ መሃል እንደላው የስበት ግንኙነት ሊከሰት መቻሉን ተናግረዋል፡፡
እንደተመራማሪዎች ገለፃ ብላክ ሆል በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች የሚመደብ ሲሆን ሁለቱም የየራሳቸው መገለጫ ያለቸው ናቸው፡፡ የመጀመሪያ ሱፐርማሲቭ ብላክ ሆልስ (supermassive blackholes) የሚባለው ሲሆን ይህም በታላላቅ ጋላክሲዎች መሀል የሚገኝ፣ ክብደቱ የፀሀያችንን ክብደት በሚሊዮኖች እጥፍ የሚበልጥና በግዙፍ የከዋክብት ፍንዳታ የሚፈጠረው ነው። ሁለተኛው እና ከአዲሱ ግኝት ጋር የሚያያዘው ስቴላር ማስ ብላክ ሆልስ (stellar mass blackholes) የሚባለው ሲሆን ይህም በጣም ግዙፍ ከዋክብት እድሜያቸውን ጨርሰው ሲፈነዱ የሚከሰት ነው፡፡ ከዚህ ፍንዳታ የሚፈጠረው ብላክ ሆል አብዛኛውን ጊዜ ክብደቱ የፀሀያችንን አነስተኛ እጥፍ ሊሆን ይችላል፡፡
https://www.usatoday.com/.../black-hole.../7349740002/
አርባ ቀናት በዋሻ ውስጥ
*************
ምንም አይነት የቀን ብርሃንና የሰዓት መቆጣጠሪያ ሳይኖራቸው ለአርባ ቀናት ያክል በዋሻ ውስጥ የቆዩ ሰዎች ከዋሻ ሲወጡ ለ30 ቀናት ያክል ብቻ እንደቆዩ እንደተሰማቸው ተናገሩ፡፡ ይህ የሆነው በፈረንሳይ የሚገኙ ራሳቸውን ከቀን ብርሃንና ከውጨኛው አለም ለማግለል በማሰብ ወደ ዋሻ በገቡ ሰዎች ነው፡፡ ሰዎቹ ወደ ዋሻ ሲገቡ የብርሃን መስተካከል እንዲኖር በማሰብ በቅድሚያ የጸሐይ መነጸር ለብሰው ገብተዋል፡፡ ከጥቂት ቆይታ በኋላ ግን ጊዜን መቆጣጠር እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡
በዋሻ ውስጥ ሳሉ ብርሃን ለማጋኘት እዲያስችላቸው በፔዳል የሚሰራ የሐይል ማመንጫ የተጠቀሙ ሲሆን የሚጠጣ ውሃም ከዋሻው 45 ሜትር ርቀት ውስጥ እየቀዱ እንደተጠቀሙ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ውጭ ምንም አይነት ስልክም ሆነ ሌላ ብርሃን ያለውና ጊዜን ሊያሳውቅ የሚችል ቁስ አልያዙም፡፡
ተመራማሪዎች የፈቃደኞቹን አካላዊ፣ ስነ-ልቦናዊና ጤና ነክ ሁኔታዎች ከመግባታቸው በፊት የመዘገቡ ሲሆን በዋሻ ውስጥ ሳሉም ከአዲሱ አካባቢ ጋር ባላቸው መስተጋብር የነበራቸውን ግብረ-መልስ መዝግበዋል፡፡ አንዳንድ ፈቃደኞች የአእምሮ እንቅስቃሴያቸውን የሚቆጣጠርና የሚመዘግብ መሳሪያ ተገጥሞላቸው ነበር፡፡
ፕሮጀክቱ አላማ ያደረገው የሰው ልጅ የተለዩና ያልተለመዱ አካባቢዎች ለውጥ የሚኖርበት ሁኔታ ቢገጥመው የሚኖረውን ምላሽና መላመድ ለማጥናት ነው፡፡
ምንጭ፡ iflscience
ተጨማሪ ንባብ https://www.iflscience.com/.../a-group-of-people-just.../...
የአየር ማረፊያን የፀሐይ ሐይልን ለመሰብሰብ
***************************
አንድ ጥናት በአውስትራሊያ የሚገኝ አንድ የአየር ማረፊያ በአካባቢው ለሚገኙ 136 ሺህ ቤቶች የሚሆን የኤሌክትሪክ ሀይልን ከፀሐይ ማመንጨት እንደሚችል አመለከተ፡፡ በአውስትራሊያ የተለያዩ አካባቢዎች አነስተኛና መካከለኛ የፀሐይ ሐይል መሰብሰቢያ ንጣፎች የሚገኙ ሲሆን ጥቂት ለማይባሉ ቤቶች አማራጭ የሐይል ምንጭ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ የታዳሽ ሐይል ፍላጎትን ለማሟላት እንዲቻል በአየር ማረፊያዎች ሰፋፊ የሆኑ ንጣፎችን መትከል አሁን ላይ በከተሞች እየተሰበሰበ ካለው የፀሐይ ሐይል 10 እጥፍ መሰብሰብ እንደሚያስችል RMIT የተባለ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች አሳውቀዋል፡፡
ከካርቦን ነጻ ለመሆን የሚደረገው ጥረት በትንንሽ ንጣፎች በሚሰበሰብ ታዳሽ ሐይል ብቻ የሚሳካ ባለመሆኑ ከፍተኛ ይዞታ ያላቸው የፀሐይ ሐይል መሰብሰቢያ ንጣፎችን መትከልና ከፍ ያለ መጠን ያለው ታዳሽ ሐይል መሰብሰብ አስፈላጊ ነው ሲሉ የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪ ዶክተር ቻይን ሰን ተናግረዋል፡፡ ዶክተሯ አክለውም ይህ ምርምር የተለያዩ የፖሊሲ አማራጮች ታሳቢ እንዲሆኑና በእያንዳንዱ ከፍተኛ የግንባታ ስራ በሚሰራበት አካባቢ ሰፋፊ የፀሐይ ሐይል መሰብሰቢያ ንጣፎችን መትከል የግሪን ሀውስ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ ያስችላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ለእንደዚህ አይነት ግዙፍ የፀሐይ ሐይል መሰብሰቢያ ፕሮጀክት የአየር ማረፊያዎች ወሳኝና ተመራጭ አካባቢዎች ናቸው ያሉት ተመራማሪዎቹ ለዚህም እንደ ምክንያትነት ያቀረቡት ኤርፖርቶች በትልልቅ ህንጻዎች፣ በዛፎች ወይም በሌላ የፀሐይ ብርሃንን ሊከልል በሚችል ነገር የማይሸፈኑ መሆናቸው ነው፡፡ ኤርፖርት አካባቢ ያልተከለለ ፀሐይ የሚገኝበት አካባቢ ነው፡፡
በምርምር ሂደቱ ጊዜ የፀሐይ ሐይል መሰብሰቢያ ንጣፍን ለማንጠፍ የሚያስችሉ የቤት ጣሪያዎችን የመለየት ስራ የተሰራ ሲሆን በዚህም 2.61 ኪሎ ሜትር ስኩየር ቦታን መለየት ተችሏል፡፡ ለዚህም ስራ እንደ ፐርዝና ሜልቦርን ያሉ ኤርፖርቶች እጅግ ምርታማ ሆነው ተገኝተዋል፡፡
ምንጭ techxplore
ተጨማሪ ንባብ https://techxplore.com/.../2021-04-airports-solar-energy...
አፕል ወደ መኖርያ ከተማችን እየመጣ ነው
=====================
አፕል ሚውዚክ በመኖርያ ከተሞቻችን በቀዳሚነት እየተደመጡ ያሉ ሙዚቃዎችን ዝርዝር ማቅረብ ሊጀምር መሆኑን አስታውቋል፡፡ ምንም እንኳን አሁን ላይ አገልግሎቱ በአዲስ አበባም ሆነ ሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ማግኘት ባይቻልም ኒው ዮርክ፣ ቶኪዮ እና ሌጎስን ጨምሮ በተወሰኑ የአለማችን ከተሞች ላይ የሚሰራ ይሆናል፡፡
አፕል ትናንት በአገልግሎቱ ተደራሽ ይሆናሉ ያላቸውን ከ100 በላይ ከተሞች ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ በእነዚህ ከተሞች ውስጥም በእያንዳንዳቸው በቀዳሚነት ተከፍተው እየተደመጡ ያሉ የ25 ሙዚቃዎችን ዝርዝር ያሳያል፡፡ አገልግሎቱን በቅድሚያ ከሚያገኙት መካከል 25 የሚሆኑት እንደ ሎስ አንጀለስ፣ ቫንኩበር፣ ቶሮንቶ፣ ቺካጎ ማያሚና ኒው ዮርክ ያሉት የሰሜን አሜሪካን ከተሞች ይሆናሉ፡፡ በአውሮፓም ፓሪስ፣ በርሊን፣ ደብሊን፣ ሮም፣ ማድሪድ፣ ለንደን እና ሌሎች ዋና ዋና ከተሞች የአገልግሎቱ ተደራሾች ናቸው፡፡
አገልግሎቱ ከምዕራቡ ባሻገር የተወሰኑ የአፍሪካ እሲያና ደቡብ አሜሪካን ሀገራት ላይም እንዲሰራ ተደርጓል፡፡ በዚህም መሰረት ናይሮቢ እና ጆሀንስበርግ ከአፍሪካ፣ ሲኦል፣ ባንኩክ እና ማኔላ ከእሲያ፣ ሪዮ ዴ ጄኔሮ እና ቦጎታ ከደቡብ አሜሪካን እንዲሁም ቴል አቪቭ፣ ኢስታንቡል እና ዱባይ ከመካከለኛው ምስራቅ ተመራጭ ከተሞች ሆነዋል፡፡
አፕል ሚውዚህ ከዚህም ባሻገር በዓለም አቀፍ ደረጃ በቀዳሚነት እየተደመጡ ያሉ የሙዚቃ አልበሞችን የሚያሳይበት የሙዚቃ ሰንጠረዥ እንዳለው ይታወሳል፡፡
ምንጭ፤ Tech Xplore
ለተጨማሪ፤ https://techxplore.com/.../2021-04-apple-music-city...
የ 4 ዓመቷ ህጻን በእድሜ ትንሿ የማይክሮሶፍት ባለሙያ ሆናለች
==========================
ከፓኪስታን የተገኘችው የአራት አመት ህፃን ኤሪሽ ፋጢማ በማይክሮሶፍት የባለሙያዎች ዝርዝር ውስጥ በእድሜ ትንሿ ባለሙያ በመሆን አዲስ ታሪክ ፅፋለች፡፡ የፓኪስታን መንግስት በይፋዊ የትዊተር ገፁ አንዳስታወቀው የአራት አመቷ ኤሪሽ ፋጢማ በማይክሮሶፍት የባለሙያዎች ማህደር ውስጥ በእድሜ ትንሿ በመሆን የሀገሯን ህዝብ በበጎ እንዳስጠራች ጠቅሷል፡፡
በሀገሪቱ ያለ እንድ ሚዲያ እንደዘገበው ህፃኗ ማይክሮሶፍት በሚያዘጋጀው የማይክሮሶፍት የተረጋገጠ ባለሙያዎች ፈተና (MCP) ላይ ተወዳድራ ማግኘት ከሚገባት 700 ነጥብ 831 ማርክ በማምጣት የመጀመሪያዋ በእድሜ ትንሿ የማይክሮሶፍት ባለሙያ ሆናለች፡፡ በሃገሪቱ የሲንዲህ ግዛት የካራቺ ከተማ ተወላጅ የሆነቸው ኤሪሽ ፋጢማ ይህን ለማሳካት በተፈጥሮ ካገኘችው የአእምሮ ልህቀት በተጨማሪ በወረርሽኙ ወቅት ከአባቷ ጋር በቤት ውስጥ የነበራት የኮምፒውተር ትምህርት በእጅጉ እንዳገዛት ተገልጿል፡፡ የኣይቲ ባለሙያ የሆነው ወላጅ አባቷ ከኮምፒውተር ጋር የተያያዙ የተለያዩ ስራዎችን በሚሰራበት ወቅት በከፍተኛ ትኩረት ስትከታተል የነበረችው ኤሪሽ ማይክሮሶፍት በሚያዘጋጀው የፕሮፌሽናል አይቲ ባለሙያዎች ፈተና ላይ በመወዳደር ከእድሜዋ በላይ ከፍተኛ ውጤት ማምጣት የቻለች ነች፡፡
ከኤሪሽ በፊት የማይክሮሶፍትን የ MCP ፈተና በማለፍ የዛው የፓኪስታን ተወላጅ የሆነና በእንግሊዝ ያደገው የ 5 ዓመቱ ህጻን ኣያን እንደአውሮፓውያኑ በ2014 በእድሜ ትንሹ የማይክሮሶፍት ባለሙያ መሆን ችሎ ነበር፡፡ ታዲያ አሁን የሀገሩ ልጅ የሆነችው ኤሪሽ ይህን ሪከርድ በማሻሻል የመጀመሪያው በእድሜ ትንሿ የማይክሮሶፍት ባለሙያ የሆነች ታዳጊ ህጻን ናት፡፡
ማይክሮሶፍት የሚያዘጋጀው የ MCP ፕሮግራም የአይቲ ፕሮፌሽናሎች ከማይክሮሶፍት ጋር ተያያዥነት ባላቸው የቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ የሚወዳደሩበት የሰርተፍኬት ፕሮግራም ሲሆን በሚዘጋጁት ፕሮፌሽናል ፈታናዎች ላይ ከ700 በላይ ውጤት የሚያመጡ ተወዳዳሪዎች ወደ ድርጅቱ የተረጋገጠ ባለሙያነት ሊያድጉ የሚችሉበት እድል ነው፡፡ ይህ ፕሮግራም በስድስት ዘርፎች የሚከፈል ሲሆን እነሱም ክላውድ፣ ፕሮዳክቲቪቲ፣ ሞቢሊቲ፣ አፕ ቢውልደር፣ ዳታ እና ቢዝነስ አፕልኬሽን ተብለው ይከፋላሉ፡፡
https://www.republicworld.com/.../four-year-old-pakistan...
እየተነዳ ቅርፁን መለወጥ የሚችለው ጎማ
====================
ተመራማሪዎች የጃፓን ባህላዊ ወረቀት አስተጣጠፍ ስልት በሆነው ኦርጋሚ ላይ በመንተራስ ተሽከርካሪው እየተንቀሳቀሰ ሳለ ቅርፁን መለወጥ የሚችል ጎማን ሰርተዋል፡፡
መነሻውን ከብዙ መቶዎች ዓመታት በፊት ሀገረ ጃፓን ላይ ያደረገው ኦርጃጋሚ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስመ ጥር መዝናኛ ለመሆን በቅቷል፡፡ አሁን ላይ ታድያ መሀንዲሶች የኦርጋሚ ንድፍን በመጠቀም የብረት እና ፕላስቲክ እቃዎችን ለመስራት እየተንደረደሩ ይገኛሉ፡፡ በአዲሱ ጎማም አጥኚዎቹ ዋተርቦምብ ቴስሌሽን የተባለውን የኦርጋሚ ነንድፍ አይነትን በመውሰድ እንደተጠቃሚው ቅርፁን የሚለዋውጥ ጎማ ሰርተዋል፡፡ ለዚህ ይረዳ ዘንድም የጎማውን የፊት አካል በአልሙኒየሙች ሲሰራ አልሙኒየሞቹን ደግሞ በሌላ ግብዓት የማስተሳሰር ስልትን ተጠቅመዋል፡፡
አጥኚዎቹ ጎማውን ሲሰሩት በተለያዩ መጠን አድርገው ነው፤ አንዳንዶቹም በመኪና ጎማ ልክ ናቸው፡፡ ጎማዎቹ ተሽከርካሪው ላይ በሚኖረው የክብደት መለዋወጥ ሲያጋጥማቸው እንዲሁም የቦታው ሁኔታን ከግምት በማስገባት እነርሱም ለዚህ ተስማሚ በሆነ መልኩ ቅርፃቸውን ይለውጣሉ፡፡ ይህም ለምሳሌ አንድ አሽከርካሪ ከፍታው ዝቅተኛ በሆነ ድልድይ ስር ሲያልፍ የጎማውን ቅርፅ ለውጦ መኪናው ሳያቆም ዝቅ ብሎ ማለፍ እንዲችል ያደርገዋል ማለት ነው፡፡
ይህ ምርምር ገና በጅማሮው ላይ ያለ በመሆኑ ባሉን መንገዶች ላይ ግልጋሎት ለመስጠት ዝግጁ አይደለም፡፡ ወደፊት ግን በተለይ እንደ ጨረቃና ማርስ ባሉ አስቸጋሪ ገፆች ላይ መጠቀም ይቻል ዘንድ አጥኚዎቹ አልመዋል፡፡
ምንጭ፤ Tech Xplore
ለተጨማሪ፤ https://techxplore.com/.../2021-04-origami-based-vehicle...
የሰው ሰራሽ አይን ቴክኖሎጂን የሚያሻሽል የኮምፒውተር ሞዴል
***********************************
ተመራማሪዎች ለአይነ-ስውራን ባለ ቀለም እና ጥራት ያለው ምስል እንዲያዩ የሚያስችሉ ሲግናሎችን ማበልጸጋቸው ተሰማ፡፡ በአለማችን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአይን ብርሃናቸውን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያጡ ያሉ ሰዎች አሉ፡፡ ፒግመንቶሳ በመባል የሚታወቀው በዘር የሚተላለፈው በሽታ ብቻ እንኳን በአለማችን ከ4 መቶው አንዱን የሚያጠቃ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት እንዲህ ባለ ችግር ምክንያት የአይን ብርሃናቸውን ላጡ ሰዎች ግማሽ መፍትሔ የሚሆን ቴክኖሎጂ አለ፡፡
ከእነዚህ ቴክኖሎጂዎች በዋናነት የሚጠቀሰው the Argus II የሚባለው ነው፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ በዘርፉ የአለማችን የመጀመሪያው ቴክኖሎጂ ሲሆን ለእይታ ወሳኝ የሆኑ የተወሰኑ የአይን ክፍሎችን አቅም እነደገና መመለስ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ቴክኖሎጂው ሙሉ ብርሃናቸውን ላጡ ሰዎች እንቅስቃሴንና ቅርጽን መለየት እንዲችሉ ያደርጋቸዋል፡፡
ይህ retinal prostheses የሚሰኝ ዘርፍ በህጻን እድሜ የሚገኝ ዘርፍ ሲሆን በአለማችን ለሚገኙ ጥቂት ለማይባሉ ሰዎች ኤሌክትሮኒክ አይን በመሆን አለምን እንዲረዱ እያደረጋቸው ነው፡፡ ይህ በጅማሮ ላይ ያለ ቴክኖሎጂ ለአይነስውራን ከእንቅስቃሴና ከቅርጽ ባሻገር ቀለማትንና ጥራት ያለው ምስል መመልከት እንዲችሊ ለማድረግ በተመራማሪዎች የተለያዩ ማሻሻያዎች እየተደረጉበት ነው፡፡
ምንጭ scitechdaily
ተጨማሪ ንባብ https://scitechdaily.com/advanced-computer-model-enables-improvements-to-bionic-eye-technology/