TechIn2
1.16K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
መንታ እህቷን በውስጧ ይዛ የተወለደችው ህጻን
*****************************
በኮሎምቢያ አንዲት እናት በአስገራሚ መልኩ ሁለት ሴት ልጆችን ወልዳለች፡፡ አስገራሚው ነገር የቁጥሩ እንዳልሆነ አምስትና ስድስት አንዳንዴም ከፍያለ ቁጥር ያላቸው መንትዮች መወለዳቸው ስለሚሰማ መረዳት ይቻላል፡፡ የዚህችን ሴት ውልደት አስገራሚ ያደረገው አንዷ ህጻን የተወለደችው በእህቷ ውስጥ ሆና መወለዷ ነው፡፡ ሁለተኛዋ ህጻን በእህቷ ሆድ ውስጥ ሆና መወለዷ በጣም ያልተለመደ ቢሆንም ፈጽሞ ያልተከሰተ ግን አይደለም፡፡ እስካሁን በሳይንስ ታሪክ ውስጥ መቶ የሚደርሱ ተመሳሳይ ክስተቶች ተመዝግበዋል፡፡
ጉዳዩ የታወቀው በ35ኛው የእርግዝና ሳምንት ሲሆን በህጻኗ ሆድ ውስጥ ያለው ሽል እንደሆነ በተደረገ የአልትራሳውንድ ምርመራ ተረጋግጧል፡፡ እናትየዋ በ37ኛው ሳምንት የተገላገለች ሲሆን 3.2 በሆነ የጤነኛ ህጻን ክብደት ያላት ልጅንም ታቅፋለች፡፡ ሁኔታው fetus-in-fetu ነው ብለው ያመኑት ዶክተሮች ከአንድ ቀን በኋላ በህጻኗ ውስጥ ያለውን ሽል ለማስወጣት በማሰብ ምርመራ የጀመሩት ሀኪሞች በዚህ ወቅት ያስተዋሉት ነገን እጅግ ሳያስገርማቸው አልቀረም፡፡
በህጻኗ ውስጥ ያለውን ሽል ለማውጣት በተዘጋጁበት ወቅት ሀኪሞቹ ያስተዋሉት ይህ ሽል አሁንም እያደገ ያለና በህይወት ያለ መሆኑን ነው፡፡ መንትያው ሽል 14 ሚሊሜትር የሚረዝም ሲሆን የራሱ የሆነ ልብና ጭንቅላት የሌለው ነው፡፡ ሁኔታውን ለእናትየዋ የተናገሩት ሀኪሞች እናትየዋ ሁኔታውን አስተውላው እንደማታውቅ ተናግራለች፡፡ ሀኪሞቹም ሁለቱን ህጻናት ያገናኘውን የእንግዴ ልጅ መስመር (umbilical cord) ሲቆርጡት ሽሉ ሞቷል፡፡ ቀሪዋ ህጻንም አሁን ላይ በሙሉ ጤንነት ላይ እንዳለች ሀኪሞቹ ተናግረዋል፡፡
ምንጭ፡ iflscience
ተጨማሪ ንባብ፡ https://www.iflscience.com/health-and-medicine/baby-girl-born-with-her-twin-living-inside-her/?fbclid=IwAR2bsIvwNQk_rlGOtV2-V_2qFJeKYX4WnsEA37JCQRfcr57Tyh9IE96W780
የመጀመሪያው ኦክስጅን ከማርስ
*********************
ማርስ ላይ ያለውን እምቅ ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ወደ ኦክስጅን በመለወጥ ለወደፊት በማርስ ላይ ለታሰበው ህይወትና ሌሎች ተግባራት መሳካት የመጀመሪያ የሚባሉ ሙከራዎች እየተደረጉ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በተሰሙ መረጃዎች የማርስን ከባቢ አየር መሰረት ያደረጉ ህንጻዎች የሚገነቡበት ዲዛይን እንዲሁም በሚሰሩት ከተሞች መንቀሳቀስ የሚያስችሉ የትራስፖርት አማራጮች በንድፍ ደረጃ እየተሰሩ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ማርስ ላይ ከዚህ በተጨማሪ የኦክስጅን ጉዳይ ሌላው ከፍተኛ ምርምር እየተደረገበት ያለ ዘርፍ ነው፡፡
ከየካቲት ወር ጀምሮ ላለፉት 60 ቀናት ከማርስ ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ኦክስጅንን መስራት የሚያስችሉ የተለያዩ ሙከራዎች ሲሰሩ እንደነበር የመረጃ ምንጫችን ናሳን ዋቢ አድርጎ የሰራው ዘገባ ያመለክታል፡፡ ይህ ጥናት ወደ ውጤት የሚያመራ ከሆነ የሳይንስ ልቦለድ ታሪኮችን እውነት የመሆን እድል እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡ አሁን ላይ የመጀመሪያ በሚባል ሙከራ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የመጀመሪያ የሆነውን ኦክስጅን ከማርስ ማግኘት ተችሏል፡፡ ይህ ሙከራ ማደግ ከቻለ ተመራማሪዎች ከማርስ ወደ ምድር ለመመለስ የሚያስፈልጋቸውን የሮኬት ሀይል ከዚያው ከማርስ እንዲያገኙ ሲያደርጋቸው ከፍ ሲልም ሊተነፍሱት የሚችሉትን አየር ማግኘት ያስችላቸዋል የሚል ተስፋን ሰንቋል፡፡
እንደሚታወቀው የማርስ ከባቢ አየር በ96 በመቶ ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ የተሸፈነ ነው፡፡ ይህ MOXIE የተሰኘ የናሳ ቴክኖሎጂ ከካርቦን ዳይ ኦክሳይድ በከፍተኛ ሙቀት አማካኝነት የኦክስጅንና የካርቦን ቅንጣቶችን የመለያየት ተግባር በመስራት ከዚህ የሚገኘውን የካርቦን ሞኖ ኦክሳይድ ተረፈ ምርት ወደ ማርስ ከባቢ አየር ይለቃል፡፡ በመጀመሪየው ሙከራ ለ10 ደቂቃ መተንፈስ የሚያስችል 5 ግራም ኦክስጅንን ማምረት ተችሏል፡፡
ምንጭ technology.org
ተጨማሪ ንባብ https://www.technology.org/2021/04/22/nasas-perseverance-mars-rover-extracts-first-oxygen-from-red-planet/?fbclid=IwAR3zlI199iEN2zYImmyQqDk5abPEwfQV4Efpzj8dAd9oNRwt8HUhqmJV4O8
በኢንስቲትዩቱ አዘጋጅነት የተካሄደው የኢትዮጵያ የምርምር ተቋማት የምክክር መድረክ
=========================
በኢትዮጵያ ያሉ የምርምር መሰረተ ልማቶች ትብብር ላይ ያተኮረ ሀገር ዓቀፍ የምክክር መድረክ በቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት ተካሂዷል፡፡ Research infrastructure for national competitiveness በሚል ርዕስ ትናንት ሲካሄድ የዋለው የምክክር መድረኩ በሀገራዊ የምርምር መሰረተ ልማቶች እና ተያያዥ አስቻይ ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት እና ሌሎች መሰናዶዎችን ያካተተ ነበር፡፡
በፓናል ውይይቱ በዋናነት እንደ ሀገር ከምርምር ጋር ተያያዘው የሚነሱ የሰው ሀብት አያያዝ፣ የፖሊሲና ግብዓት አቅርቦት ችግር፣ የምርምሮች ሀገራዊ እርባና፣ ማበረታቻ እና የተቋማት ስፔሻላይዜሽን ላይ ያውጠነጠኑ ሀሳቦች ተነስተውበታል፡፡
ውይይቱን በጋራ የመሩት የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት እንዲሁም የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተሮች አቶ ሙሉቀን ቀሬና ዶ/ር ካሳሁን ተስፋዬ በተነሱት ጉዳዮች ላይ ምላሽ ሰጥተውባቸዋል፡፡ የተነሱት ጥያቄዎች አግባብነት ያላቸው መሆናቸውን ያወሱት አቶ ሙሉቀን ቀሬ የሚመሩት ኢንስቲትዩት ከባዩ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር መመስረት የቻለውን ጥምረት በምሳሌነት በመጥቀስ ተቋማቱ በጋራ በሚሰሩበት መንገድ ላይ ብሎም የፕሮኪውርመንት ፖሊሲ ዝግጅት እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ሀሳባቸውን አንፀባርቀዋል፡፡ በተጨማሪም በውይይቱ የተነሱ ሀሳቦች ከቃል ባለፈ ወደ ተግባር ይለወጡ ዘንድ የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ካሳሁን በበኩላቸው መንግስታዊ የግዢ ሕጉ የምርምር ተቋማትን እንዲያሰራ ሆኖ እየተዘጋጀ መሆኑን ለታዳሚው ተናግረዋል፡፡ በስፔሻላይዜሽን ረገድም በመሰረቱ የተቋማት በየቦታው መገንባት ስህተት ባይሆንም ሁሉንም የልህቀት ማዕከል ለማድረግ መሞከሩ ግን የተሳሳተ መሆኑን ዶ/ር ካሳሁን ተናግረዋል፡፡ ለተመራማሪዎች በሚሰጡ የድጋፍ እና ማበረታቻ ስራዎችም ማሻሻያ ተደርጎባቸው በስራ ላይ መዋላቸው እንደሚቀጥል አስቀምጠዋል፡፡
ከፓናል ውይይቱ ባሻገር መንደርደርያ የሆኑ ማብራርያዎች በተጋባዥ ምሁራን እና የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ተመራማሪዎች ቀርበዋል፡፡ በኢትዮጵያ የሳይንስ እና ኦኖቬሽን ፖሊሲ አላማ እንዲሁም አቅጣጫና ስትራቴጂዎች ላይ ያተኮረ ማብራርያ በቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር ኢ/ር ተሾመ ሳህለማርያም ቀርቧል፡፡ በኢንስቲትዩቲ ማንነት፣ ስልጣንና ተግባራት እንዲሁም ስኬቶች ላይ ደግሞ ወ/ሮ ህልውና ማሜ የተወሰነ ገለፃ አድርገዋል፡፡
በሌላ መልኩ በኢትዮጵያ የምርምር መሰረተ ልማት ስነ-ምህዳር እና የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ላይ ያተኮረ ማብራርያ በዶ/ር አብረሀም ደበበ፣ በምርምር ማዕከላት የኢኖቬሽን ስራዎች፣ የተመረጡ የአስተዳደር ተግባራትና የህግ ማሻሻያዎች እንዲሁም ህብረቶች ላይ ዶ/ር መላኩ ደረጀ በመጨረሻም አቶ ወገኔ ደምሴ የኢትዮጵያ የምርምር ማዕከላትን በሚለይ እና በሚያስተሳስር ፕሮጀክት ዙርያ ገለፃቸውን አቅርበዋል፡፡
የምክክር መድረኩን አስመልክቶ ያነጋገርናቸው የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬተር ኢ/ር ተሾመ ሳህለማርያም መድረኩ የምርምር መሰረተ ልማቶችን ማስተሳሰር እና ማን ምን እየሰራ መሆኑን ማወቅን በዓላማነት ያነገበ መሆኑን ገልፀውልናል፡፡ አያይዘውም መንግስት በኢኖቬሽን ዙርያ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ስለመሆኑና የተቀመጡ ተግዳሮቶችም በጊዜ ሂደት እየተፈቱ እንደሚሄዱ ተናግረዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ከሀገራችን ልዩ ልዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የምርምር ማዕከላት እና የሚመለከታቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ ምሁራን ተሳታፊ ሆነውበት አልፏል፡፡
ሩስያ የራሷን የጠፈር ላይ ጣብያ ልትገነባ ነው
========================
በአሜሪካኑ የጠፈር ምርምር ተቋም ናሳ እና በሩስያ አቻው ሮስኮዝሞስ ትብብር እ.አ.አ በ1998 ወደ ጠፈር የተላከው ዓለም አቀፉ የጠፈር ጣብያ እስከዛሬ ድረስ ግምባር ቀደም ሆኖ በግልጋሎት ላይ ይገኛል፡፡ ታድያ ይህ ለ23 ዓመታት በሩስያ እና አሜሪካን ትብብር ማሳያ ሆኖ የቆመ ጣብያ ጉዞ በቅርቡ ሊቋጭ እንደሚችል የሩስያ ባለስልጣናት ጠቁመዋል፡፡ የሩስያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዩሪ ቦሪሶቭ ሩሲያ በአውሮፓውያኑ 2025 ከዓለም አቀፉ የጠፈር ምርምር ጣብያ እንደምትለቅ መናገራቸው በሀገሪቱ ሚዲያዎች ተዘግቧል፡፡
እንደ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሆነ በዓለም አቀፉ ጠፈር ጣብያ ላይ ከእርጅና ጋር ተያይዞ እየታዩ ያሉት ጉዳቶች ለውሳኔው በዋና ምክንያትነት አስቀምጠዋል፡፡ የጣብያው መዋቅር እና ብረቶች ማርጀታቸውን የተናገሩት ዩሪ ቦሪሶቭ ነገሮች ወደ አደገኛ ሁኔታ ሊያመሩ እንደሚችሉና እነርሱም የጠፈር ተመራማሪዎቻቸውን ህይወት አደጋ ላይ መጣል እንደማይፍልጉ ተናግረዋል፡፡
ከሮስኮዝሞስ ኃላፊዎች ዘንድ የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩትም አሁን ላይ የሀገሪቱ ብሄራዊ ጠፈር ጣብያ ግንባታ የተጀመረ ሲሆን ከዚህ ቀደም በአውሮፓውያኑ 1970 እና 80ዎቹ ወደ ጠፈር ተልከው የነበሩት ሳሊዉት እና ሚር ጣብያዎችን እንደሚተካ ታውቋል፡፡ የተቋሙ ዋና መሪ ዲሚትሪ ራጎዚያንም በተመሳሳይ የጣብያው ስራ በአውሮፓውያኑ 2025 ሊጠናቀቅ ስለመቻሉ ተናግረዋለ፡፡ ሆኖም ሩሲያ የዚህ ጣብያ ስራ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ከዓለም አቀፉ የጠፈር ምርምር ጣብያ ለቃ እንደማትወጣ አስታውቀዋል፡፡
ይህ ውሳኔ በዓለም አቀፉ የጠፈር ጣብያ ላይ ጥገኛ ለሆኑት አሜሪካን እና ሌሎች ሀገራት የስራ ጫናን እንደሚፈጥርባቸው ተነግሯል፡፡ ባለ አነስተኛ ወጪ ሳተላይቶችን በማምረት የሚታወቀው ዳውሪያ ኩባንያ የቀድሞ ቃል አቀባይ ቪታሊ ኢጎሮቭ እንደሚሉት ያለ ሩሲያ አጋዥነት ሌሎቹ ሀገራት የጠፈር ጣብያውን መቆጣጠሩ ከባድ ቢሆንባቸውም በስፔስ-ኤክስ የሚቀርቡት የሰውና እቃ ማጓጓዝ አገልግሎቶች ይህን ክፍተት ሊሞሉ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
ምንጭ፤ Live Science
ለተጨማሪ https://www.livescience.com/russia-leaving-international-space-station.html
ሀገራትን የሚያገናኙ 5 የመዋሰኛ ድልድዮች
=======================
የመሸጋገሪያ ድልድይ ስራዎች ከሰው ልጆች እድገት ጋር በፍጥነት እየተለዋወጡ የመጡ ግኝቶች ናቸው:: ትልልቅ ዛፎችን አግድም በመጣል መሸጋሪያ ከመፍጠር ጀምሮ የገመድ ድልድዮች እና የደረጃ ድንጋዮች እስከ ዘመናዊ የእግረኛ መንገዶች ድረስ የመሸጋገሪያ ድልድይ ስራዎች ረዥም የምህንድስና እድገት የታየባቸው ወሳኝ ግኝቶች ናቸው፡፡ አንድን የየብስ ክፍል ከሌላ የየብስ ክፍል ጋር ለማገኛኘት ጥቅም ላይ የሚውሉት የድልድይ ስራዎች በዘመናዊው የሰው ልጅ ታሪክ የሀገራትን የንግድ እንቅስቃሴ ለማፋጠን እና የማህበራዊ መስተጋብርን ለማሳደግ ትልቅ ጥቅም ሰተው አልፈዋል፡፡
አሁን ላይ በአለማችን ሀገራትን ከሀገራት የሚያገናኙ ትልልቅ የመሸጋገሪያ ድልድዮች በብዛት የሚገኙ ሲሆን ለሚጋሯቸው ሀገራትም ትልቅ የኢኮኖሚ ጥቅም ከማስገኘት አልፎ የህዝቦችን የእርስ በእርስ ግንኙነት ለማጠናከርና ለማሳደግም ትልቅ እድል ይፈጥራል፡፡ በውብ የስነ-ሕንፃ ምህንድስናቸው ለቱሪስት መስህብነት ሳይቀር ጥቅም ላይ ከሚውሉት የተለያዩ የድንበር መሸጋገሪያዎች መካከል 5 አስገራሚ አለም አቀፍ ድልድዮችን በጥቂቱ ልናስቃኛችሁ ወደድን፡፡
1. አምባሳደር ብሪጅ የአሜሪካና የካናዳ ድንበር
በሚቺጋን ግዛት የምተገኘውን ዲትሮይት ከተማ ከካናዳዋ ኦንታሪዮ ግዛት የሚያዋስነውና የሚያገናኘው አምባሳደር በሪጅ በሰሜን አሜሪካ ውስጥ በብዛት ከሚገኙ ድልድዮች ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድበት መሸጋገሪያ ድልድይ ነው፡፡ ሁለቱ ሀገራት ካላቸው የንግድ አንቅስቃሴ 27 በመቶው በዚህ ድልድይ ላይ የሚካሄድ ሲሆን ሁለቱ ሀገራት ከላቸው ተመሳሳይ የድንበር መሸጋገሪያዎች ውስጥም በቀዳሚነት የሚጠራ ነው፡፡ እንደአውሮፓውያኑ በ1927 ስራው ተጀምሮ ከ1929 አንስቶ ግልጋሎት መስጠት የጀመረው ይህ ድልድይ በጥቅሉ 7,545 ጫማ ወይም 2,300 ሜትር ርዝመት እንዳለው ይነገራል፡፡
2. ስሪ ካንትሪስ ብሪጅ የፈንሳይ ጀርመንና ስዊዘርላንድ ድንበር
የሶስቱ ሀገራት የድንበር መዋሰኛ በሆነው ራይን ወንዝ ላይ የተዘረጋው ይህ አስገራሚ የመሸጋገሪያ ድልድይ በዋናነት በፈረንሳይ እና ጀርመን መካካል የተዘረጋ ደልድይ ቢሆንም በተወሰነ ክፍል የስዊዘርላንድ ከተማ የሆነቸውን ባዜል ያገናኛል፡፡ ሲንግል ስፓን ተብለው ከሚጠሩት የድልድይ አይነቶች በርዝመቱ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ስሪ ካንትሪስ ብሪጅ ከተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች በተጨማሪ በዋናነት ለእግረኞች እና ለብስክሌተኞች መጓጓዣ የሚያገለግል ነው፡፡ እንደአውሮፓውያኑ በ2007 ስራ የጀመረው ይህ ደልድይ አጠቃላይ ርዝመቱም 248 ሜትር ይደርሳል፡፡
3. ቪክቶሮያ ፎልስ ብሪጅ የዚምባብዌ እና ዛምቢያ ድንበር
በአፍሪካ በርዝመቱ በአራተኝነት በሚቀመጠው የዛምቤዚ ወንዝ ላይ የሚገኘው የቪክቶሪያ ፏፏቴ የሁለቱ ሀገራት መዋሰኛ ድንበር ሲሆን ቪክቶሮያ ፎልስ ብሪጅ ደግሞ ሀገራቱን ለማገናኘት የተዘረጋ ውብ የመገናኛ ድልድይ ነው፡፡ ከዚምባብዌ ቪክቶሮያ ፎልስን ከዛምቢያ ደግሞ የሊቪንግስተን ከተማን የሚያገናኘው ይህ ድልድይ የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች በኢኮኖሚና በንግድ ያስተሳሰረ ሲሆን በዋናነት ለመንገድ፣ ባቡርና እግረኞች መጓጓዣነት ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ እንደአውሮፓውያኑ በ1904 የግንባታ ስራው ተጀምሮ ከ1905 አንስቶ ማገልገል የጀመረው ይህ የመሸጋገሪያ ድልድይ 429 ጫማ ወይም 198 ሜትር እንደሚረዝምም ይነገራል፡፡
4. የታጃክና አፍጋን ፍሬንድሺፕ ብሪጅ
በሁለቱ ሀገራት የድንበር መዋሰኛ በሆነው የፓንጅ ወንዝ ላይ የተዘረጋው ይህ የታጃኪስታን እና የአፍጋኒስታን የመሸጋገሪያ ድልድይ እንደአውሮፓውያኑ በ2007 ስራውን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለሃገራቱ የንድግ እንቅስቃሴ እና የህዝቦች ትስስር ትልቅ ሚና የተወጣ ድልድይ ነው፡፡ በአሰራር ይዘቱ ቀላል ወይም ገርደር ብሪጅ ከሚባሉት የሚመደበው ይህ የመሸጋገሪያ ድልድይ በጥቅሉ 672 ሜትር እንደሚረዝምም ይነገራል፡፡
5. ጓዲያና ኢንተርናሽናል ብሪጅ የስፔን እና ፖርቹጋል ድንበር
በሁለቱ ሀገራት የድንበር መዋሰኛ በሆነው ጓዲያና ወንዝ ላይ የተዘረጋው ይህ የመሸጋገሪያ ድልድይ ከስፔን ኣያሞንቴ የተባለችውን ደቡባዊ ከተማ ከፖርቹጋል ደግሞ ካስትሮ ማሪም የተባለችውን ትንሽዬ ከተማ የሚዋስንና የሚያገናኝ ድልድይ ነው፡፡ ከሁለቱ ሀገራት የሚመጡ መንገደኞችንና ተጓዦችን የሚያገናኘው ይህ ድልድይ ለንግድ እንቅስቃሴዎችና ለቱሪስት መስህብነት ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ በአሰራር ይዘቱ ኬብል ስቴይድ ብሬጅ የሚባለው ይህ የመሸጋገሪያ ድልድይ እንደአውሮፓውያኑ በ1991 ስራውን የጀመረ ሲሆን፤ በጥቅሉም 666 ሜትር እንደሚረዝም ይነገራል፡፡
https://interestingengineering.com/-coolest-bridges-cross...
አስገራሚ ውጤት ያስገኘው የእጅ ንቅለ ተከላ
**************************************
በህንድ ሀኪሞች በቅርብ ጊዜ ለአንዲት ታካሚ የእጅ ንቅለ ተከላ አድርገውላት ነበር፡፡ ሸሪያ ሲዳናጎውዳ የተባለች የ19 ዓመት ወጣት በ2017 ለሁለት እጆቿ ንቅለ ተከላ አሰርታ ነበር፡፡ ጉዳቱ የገጠማት በደረሰባት የመኪና አደጋ ምክንያት ሲሆን በወቅቱ ሁለት እጆቿን አጥታ ነበር፡፡ ጉዳቱ ክርን እስከሚባለው መካከለኛ የእጅ ክፍል የገጠማት ሲሆን ጉዳቱ በደረሰባት ሰሞን ከሞተ አንድ ወጣት እጅ እንድታገኝ ተደረገ፡፡ የእጅ ንቅለ ተከላው በታካሚዋ የሰውነት ቆዳ እና አዲስ ባገኘችው እጅ ቆዳ ቀለም መካከል የተወሰነ መለያየት ከመኖሩ ውጭ በስኬት የተጠናቀቀ እንደነበር ሀኪሞቿ ተናግረዋል፡፡
አስገራሚው ነገር መታወቅ የጀመረው በያዝነው 2021 ነው፡፡ ይኸውም ታጊዋ የተሰጣት እጅ ከጊዜ ወደ ጊዜ የመንጣት ባህሪ እያሳየና ከቀሪው የሰውነት ክፍሏጋር እየተመሳሰለ መምጣቱ ነው፡፡ ሀኪሞቹ ይህ እንዴት ሊከሰት እንደቻለ ማስረዳት ሳይቸገሩ አልቀረም፡፡ ለዚህም በምክንያትነት የተጠቀሰው ተመሳሳይ ክስተቶች ተስተውለው አለማወቃቸው ነው፡፡
ዶክተሮቹ ጉዳዩን በጥብቅ እየተከታተሉት ሲሆን አሁን ላይ ያላቸው ግምት ለሰውነት ቆዳ እና ለፀጉር ቀለም ምክንያት የሆነው ሜላኒን የተሰኘ ተፈጥሯዊ ውህድ በሰውነቷ መመረቱ ነው የሚል ነው፡፡ በሌላም በኩል የተቀየረው እጅ በተፈጥሮ ቀለሙን እየለወጠ ሊሆን ይችላል የሚል መላምት አስቀምጠዋል፡፡
ከዚህ በፊትም በዚሁ ሆስፒታል የእጅ ንቅለ ተከላ የተደረገለት አንድ የአፍጋኒስታን ወታደር ተመሳሳይ የቆዳ ቀለም ለውጥ እንደተስተዋለበት የህንዱ አምሪታ ሆስፒታል ዶክተሮች ተናግረዋል፡፡ በዘርፉ ስራ የተጀመረው በ1998 ዓም ሲሆን ላለፉት 25 ዓመታት ከ100 ያነሱ የእጅ ንቅለ ተከላዎች በተለያየ ደረጃ ተደርገዋል፡፡
ምንጭ iflscience
ተጨማሪ ንባብ https://www.iflscience.com/health-and-medicine/doctors-baffled-by-transplant-patients-new-hands-changing-color/?fbclid=IwAR0Xy2CxQyczNs-nAj1P1EKfrVHMzGkxcDrhFU8aqCs05DvnsbCXO1zSVAk
ከሙዝ ቆሻሻ ምንጣፎችንና ጨርቃጨርቆችን የሚያመርተው የኡጋንዳ ስታርታፕ
=============================
ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ኡጋንዳ ከፍተኛ መጠን ያለው የሙዝ ምርት የምታቀርብ ሀገራት ናት፡፡ በሀገሪቱ ከሚመረተው ከፍተኛ የሙዝ ምርት ጋር ተያይዞ ወደቆሻሻ የሚጣለው የምርት ውጋጅም እጅግ ከፍተኛ ሲሆን ይህም በየአካባቢው ላሉ የሙዝ መሸጫ ስፍራዎችና መገበያያ ቦታዎች ትልቅ ችግር ይፈጥራል፡፡ ታዲያ ይህን ክፍተት ለመሙላት ኪማኒ ሙቱሪ በተባለ ግለሰብ የተቋቋመው አንድ ስታርታፕ ከሙዝ የሚወጣውን ውጋጅና ቆሻሻ በመጠቀም ለአካባቢ ተስማሚ የሆኑ የምንጣፍ፣ ጨርቃ ጨርቅ እና የፀጉር ማራዘሚያ ምርቶችን በማምረት ላይ ይገኛል፡፡
ቴክስፋድ የሚል ስያሜ ያለው ይህ የኡጋንዳ ስታርታፕ ከሙዝ የሚወጣውን የቆሻሻ ውጋጅ ጠቃሚነት ወዳላቸው ምርቶች ለመቀየር በመቁረጫ መሳሪያዎች ተቆራርተው ከተዘጋጁ በኋላ የሙዝ ውጋጆቹን ወደ ፋይበር መቀየር በሚያስችል ማሽን እንዲገቡ ይደረጋል፡፡ ይህ ከተከናወነ በኋላ ከማሽኑ የሚወጣውን የፋይበር ውጤት በረዣዥም ቅርፅ በማድረግና በፀሃይ በማድረቅ ወደ ቀጣዩ የማቀነባበር ሂደት እንዲያልፍ ይደረጋል፡፡ የስታርታፑ ባለሙያዎች ይህን ረዥም የማቀነባበር ሂደት አልፈው ጥራቱን የጠበቀ የጨርቃ ጨርቅ እና ምንጣፍ ውጤቶችን ከማምረታቸው ባለፈ ሁሉም ምርቶች ለአካባቢ ተስማሚ እንዲሆኑ ተደርገው መሰራታቸው ይበልጥ ተቀባይነት እንዲያገኙ አስችሏቸዋል፡፡
የድርጅቱ መስራች ኪማኒ ሙቱሪ ከሙዝ የቆሻሻ ውጋጅ የሚመረቱትን የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶች ረዥም ጊዜ በፈጀ የቤተ ሙከራ ሂደት እንደደረሱባቸው እና አሁን ላይ ከሙዝ በሚገኘው ፈይበር አማካኝነት ከምንጠፎች በተጨማሪ ለሴቶች ትልቅ ጥቅም የሚሰጥ ባዮዲግሬደብል የጸጉር ማራዘሚያ መስራት መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡ ሴቶች ይህን ምርት ቢጠቀሙ እደሌሎች የጸጉር ማራዘሚያ ውጤቶች ለመበስበስ የማይቸገሩ በመሆናቸው ለጓሮ አትክልቶችና ማሳደጊያ ቦታዎች እንደማዳበሪ ሊጠቀሙባቸው እንደሚችሉም ይገልጻሉ፡፡
የስታርታፕ ድርጅቱ አሁን ላይ የስራ እድል ከፈጠረላቸው 23 ሰዎች በተጨማሪ በቀጣይ ጊዜያት ይበልጥ ለማሳደግ እቅድ እንዳላቸው የሚናገሩት የድርጅቱ መስራች ኪማኒ ሙቱሪ ባለፍ አመት ካስገባው የ41 ሺ ዶላር ገቢም አሁን ላይ ከፍተኛ ጨማሪ እንደታየ እና የምንጣፍ ምርቱ አምና ከነበረው በእጥፍ ጨምሮ አሁን ላይ 2,400 እንደደረሰ ይገልጻሉ፡፡ በተለይ የምንጣፍ ምርቶቻቸውን ወደተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት መላክ መጀመራቸውን የሚናገሩት ኪማኒ በዚህም ከፍተኛ ገቢ ማስገባት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡
https://www.reuters.com/business/environment/uganda-start-up-bets-big-banana-waste-2021-04-16/
7 ጊዜ በመብረቅ ተመቶ የተረፈው ግለሰብ
======================
ሮይ ሰሊቫን የተባለው አሜሪካዊ ከአውሮፓውያኑ 1912 እስከ 1983 ድረስ ምድራችን ላይ በኖረባቸው 71 ዓመታት ውስጥ ለሰባት የተለያዩ ጊዜያት በመብረቅ ለመመታት በቅቷል፤ እንዲያውም አንዱን በገለልተኛ አካል ማረጋገጥ ስላልተቻለ ነው እንጂ በልጅነቱ ሌላ ስምንተኛ መብረቅ እንደመታው ይነገራል፡፡ ይህ አስገራሚ ሰው ከመብረቅ ብቻ አይመስልም ፀቡ፤ በህይወት ዘመኑ ለ22 ጊዜ ግዙፍና አደገኛ እንስሳ ከሆኑት ድቦች ጋርም ተፋልሟል፡፡
ግለሰቡ ለመጀመሪያ ጊዜ መብረቅ የጎበኘው እ.አ.አ በ1942 የመብረቅ መከላከያ ባልተገጠመለት ማማ ውስጥ ከዝናብ ተጠልሎ ሳለ ነበር፡፡ በወቅቱ ማማው እራሱ ሰባት ጊዜ በመብረቅ በመመታቱ የተነሳ በእሳት ስለተያያዘ እግሬ አውጪኝ ብሎ በተወሰነ ለመራቅ ቢሞክርም በህይወት ዘመኔ ከባዱ ነው ያለው የመብረቅ ቁጣ ከውጪ ተቀብሎታል፡፡ ይህም የቀኝ እግሩ ላይ ቃጠሎን አደረሰበት፡፡
በቀጣይ መብረቅ የጎበኘው ከ27 ዓመታት በኋላ እ.አ.አ በ1969 መኪና እየነዳ ሳለ ነበር፡፡ እንደ ተለምዶው ቢሆን የመኪና ብረት ከዚህ አደጋ ሊጠብቀው የሚገባ ቢሆንም በአካባቢው ዛፍ ላይ ወርዶ የነበረው መብረቅ ነጥሮ በተከፈተው የመኪናው መስኮት በኩል ገብቶ መቶታል፡፡ አደጋው ሲደርስ እራሱን እንዲስት ያደረገው ሲሆን ቅንድብ፣ የአይን ሽፋሽፍት እና ፀጉሮቹም ተቃጠሉ፡፡ ሁኔታውን ይበልጥ አስገራሚ የሚያደርገው ሮይ እራሱን በሳተበት ሰዓት ያለ ሹፌር ሲንቀሳቀስ የነበረው መኪናው ገደል አፋፍ ላይ ሲደርስ በራሱ የመቆሙ ነገር ነው፡፡
ሦስተኛው ጥቃት እ.አ.አ በ1970 ሲሆን በጓሮው ውስጥ ሳለ ነበር በወቅቱ የጣለው መብረቅ በአቅራብያ የተተከለውን የኤሌትሪክ ማስተላለፊያን ከመታ በኋላ ነጥሮ እርሱ ላይ አርፏል፡፡
አራተኛው ደግሞ ወደ ሁለት ዓመት ጠብቆ ሲመጣ እንዲሁ ፀጉሩን አቃጥሎት አልፏል፡፡
ከአንድ ዓመት በኋላም እ.አ.አ በ1973 እንደርሱ አነጋገር ከባድ ዝናብ ሊጥል የሚመስል ደመና ሲፈጠር ካየ በኋላ መኪናውን አስነስቶ ከአካባቢው ለማምለጥ ቢሞክርም ደመናው እግር በእግር ሲከተለው ቆየ፡፡ ታድያ ደመናው መከታተሉን አቁሟል ብሎ እንዳሰበ ከመኪናው ሲወጣ ከየት መጣ ያልተባለው አምስተኛው መብረቅ ድንገት ወርዶ አጩሎታል፡፡ መብረቁ በግራ እጁ እና እግሩ ተላልፎ ጫማው ላይ ያረፈ ሲሆን ፀጉሩም ከመቃጠል አልዳነም፡፡
ስድስተኛው መብረቅ ላይም እንዲሁ መብረቅ ሲከተለው ማየቱን ጠቅሶ ለማምለጥ ቢጥርም በመብረቁ መመታቱ ፀጉሩም መቃጠሉ አልቀረለትም፡፡
ሰባተኛው እና የመጨረሻው መብረቅ የመታው አሳ በማጥመድ ላይ ሳለ ነበር፡፡
ሮይ ለወትሮ ፈሪ የሚባል ሰው ያልነበረ ቢሆንም አራተኛው መብረቅ ከመታው በኋላ ግን ሊያጠፋው የሚሻ አንድ ኃይል እየተከታተለው መሆኑን አምኖ መፍራት መጀመሩ ተዘግቧል፡፡ ሌላው ሮይን ለየት የሚያደርገው ሁሌም በመኪናው ውሃ ይዞ የሚሄድ ሲሆን በዚህም መብረቁ ፀጉሩን ሲያቃጥለው እሳቱን ለማጥፋት ሲጠቀምበት ኖሯል፡፡ በመጨጨረሻው ጥቃት ላይ ታድያ አንድ ድብ መጥቶ ውሃውን ሊሰርቅበት ቢሞክርም በዱላ ተፋልሞ ማስጣሉን ይናገራል፡፡
የመብረቅ ቤተኝነቱ ታድያ በአንድ አጋጣሚ ወደ ቤተሰቡም ተጋብቶ ሳይሆን አይቀርም ባለቤቱም በጓሮዋቸው ልብስ እያሰጣች ሳለ በመብረቅ ተመታ ነበር፡፡ በወቅቱ ሮይ ደርሶላት ስለነበር ያለ ጉዳት ልታመልጥ ችላለች፡፡
ምንጭ፤ The Michigan Weather Center
ለተጨማሪ https://michigan-weather-center.org/thunder-lightning
ሳይንቲስቶች ወደምድር የቀረበ አነስተኛ ብላክ ሆል ማግኘታቸውን አስታወቁ
==========================
በኦሃዮ ስቴት ዩኒቨርስቲ የሚገኙ የኮስሞሎጂ ተመራማሪዎች ለምድር በጣም ቀርቦ በመገኘት እና በአነስተኛነቱ ሪኮርድ የሰበረ አዲስ ብላክ ሆል (Black Hole) ማግኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡ እስከዛሬ ሊገኙ ከቻሉት የብላክ ሆል አይነቶች በመጠኑ አነስተኛ ነው የተባለው ይህ ግኝት ከምድር ያለው ርቀትም 1,500 የብርሃን አመት እንደሚደርስ ተነግሯል፡፡
ዩኒኮርን ብለው የሰየሙት ይህ ብላክ ሆል ከኛዋ ፀሃይ በሶስት እጥፍ እንደሚልቅ ቢነገርለትም፤ ከሌሎች የብላክ ሆል ይዘቶች አንጻር እጅግ አነስተኛ መጠን እንዳለው ተጠቅሷል፡፡ አዲሱ ብላክ ሆል ሞኖሴሮስ (Monoceros) በተባለ የህብረ ከዋክብት መካማቻ ውስጥ እንደተገኘ የሚናገሩት የምርምሩ ተሳታፊ ዶ/ር ታሪንዱ ጃያሲጌ በዚህ የህዋ ክፍል መገኘቱ እና በአይነቱ የተለየ ብላክ ሆል መሆኑ ይህን የዩኒኮርን ስያሜ እንዲያገኝ ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡
በዚህ ህብረ ኮከብ ዙሪያ ሲደረግ የነበረው የስበት ንቅናቄ ታይዳል ዲሰቶርሽን የተባለ የሁለት እና ከዚያ በላይ የህዋ አካላት የመሳሳብ ውጤት መሆኑን የሚያስረዱት ተመራማሪው ይህም ከከኮቡ አጠገብ እንደ ብላክ ሆል ያለ ትልቅ የህዋ አካል የስበት ንቅናቄ እየፈጠረ መሆኑን የሚያሳይ ነው ይላሉ፡፡ የብላክ ሆሎ መገኘት በአይን የሚታይ ወይም በሌላ መስፈርት የሚገለፅ ሳይሆን ተመራማሪዎች በለኩት የብርሃን ልኬት እና ሌሎች የሞገድ ርዝመት መለኪያዎች መሆኑን የሚናገሩት ዶ/ር ጃያሲጌ በልኬቱም መሰረት ከከኮቡ የተገኙ መረጃዎች እንደሚያሳዩት እንደ ብላክ ሆል ሊጠራ የሚችል ግዙፍ የህዋ አካል የስበት ንቅናቄውን በመፍጠር በምድር እና በጨረቃ መሃል እንደላው የስበት ግንኙነት ሊከሰት መቻሉን ተናግረዋል፡፡
እንደተመራማሪዎች ገለፃ ብላክ ሆል በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች የሚመደብ ሲሆን ሁለቱም የየራሳቸው መገለጫ ያለቸው ናቸው፡፡ የመጀመሪያ ሱፐርማሲቭ ብላክ ሆልስ (supermassive blackholes) የሚባለው ሲሆን ይህም በታላላቅ ጋላክሲዎች መሀል የሚገኝ፣ ክብደቱ የፀሀያችንን ክብደት በሚሊዮኖች እጥፍ የሚበልጥና በግዙፍ የከዋክብት ፍንዳታ የሚፈጠረው ነው። ሁለተኛው እና ከአዲሱ ግኝት ጋር የሚያያዘው ስቴላር ማስ ብላክ ሆልስ (stellar mass blackholes) የሚባለው ሲሆን ይህም በጣም ግዙፍ ከዋክብት እድሜያቸውን ጨርሰው ሲፈነዱ የሚከሰት ነው፡፡ ከዚህ ፍንዳታ የሚፈጠረው ብላክ ሆል አብዛኛውን ጊዜ ክብደቱ የፀሀያችንን አነስተኛ እጥፍ ሊሆን ይችላል፡፡
https://www.usatoday.com/.../black-hole.../7349740002/