TechIn2
1.16K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
የኢኖቬሽን አምባሳደር ፕሮግራም ተጀመረ
========================
ማህበረሰባዊ የኢኖቬሽን ባህልን ለማስፋፋት ታስቦ በቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት የተሰናዳው የኢኖቬሽን አምባሳደር ፕሮግራም ዛሬ ተጀመረ፡፡ ዛሬ ጠዋት በተከናወነው ፕሮግራሙን በይፋ የማስጀመርያ ዝግጅትም ከተለያዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተውጣጥተው በኢኖቬሽን አምባሳደርነት የተሰየሙ ተማሪዎችን፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪዎችን ተሳታፊ አድርጓል፡፡
የዝግጅቱን መክፈቻ ንግግሩን ያሰሙት የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢ/ር ተሾመ ሳህለማርያም የተማሪዎቹ በኢኖቬሽን አምባሳደርነት መሰየም የሀገራችንን ምጣኔ ሀብታዊ ሁናቴ ከፍ ያደርግ ዘንድ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ መንግስት ለቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ነው ያሉት ኢ/ር ተሾመ ኢንስቲትዩቱም የተቋማትን አሰራር በማሻሻል ለሀገር ምጣኔ ሀብት መሻሻል አስተዋፅዖ የሚያደርጉ ግልጋሎቶችን እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በዕለቱ በክብር እንግድነት ተገኝተው ለተማሪዎቹ ዕውቀታቸውን ያካፈሉት ዝነኛው የአንድሮሜዳ ቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ እና ፊዮሎጂስት መጋቢ ሀዲስ ዶ/ር ሮዳስ ታደሰ “ግኝትን እንዴት እናግኝ” በሚል ርዕስ የአዕምሮን ኃይል ተጠቅሞ ግኝትን ዕውን ስለማድረግ የሚያውጠነጥን ንግግርን አቅርበዋል፡፡ በንግግራቸው ላይ ዶ/ር ሮዳስ ተማሪዎቹ ለስኬታማ ኢኖቬተርነት ለመብቃት ንቁ ሆነው ዙርያቸውን እንዲመለከቱ፣ አዕምሮዋቸውን በምልዓት እንዲጠቀሙ፣ ሁሌም የራስ የሆነን ነገር ለማምጣት እንዲሞክሩ እና ተፈጥሮን እንዲመለከቱ መክረዋል፡፡ አክለውም ሌላኛው የግኝቶች ዋና መነሻ ነው ያሉት ህልምን አስመልክቶ ተማሪዎቹ በህልም የሚያዩትን ነገር ወደ ምርምር እንዲለውጡት አሳስበዋል፡፡
ሌላው በመድረኩ ከልምዱ ለማካፈል የተገኘው ወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ ኢዘዲን ካሚል በበኩሉ እስካሁን በታዳሽ ኃይል፣ ደህንነት፣ ጤና እና የመሳርያዎች በይነ መረባዊ ግንኙነት (IOT) ላይ ያተኮሩ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎቹን በጥቂቱ አስቃኝቷል፡፡ ወደ 18 ፈጠራዎችን ያበረከተውና ከነዚህም ውስጥ 13 ያህሉን በፓተንት ለማስመዝገብ የበቃው ኢዘዲን በኢኖቬሽን ዓለም ጉዞው ውስጥ ስላጋጠሙት ተግዳሮቶች፣ እነርሱን ስላለፈበት መንገድ እና ስላገኛቸው ዕድሎች ልምዱን ያካፈለ ሲሆን ይህ የኢኖቬሽን ጉዞውን አስመልክቶ ከተሳታፊዎችም ጥያቄ ጥያቄዎች ቀርቦለትም ምላሽ ሰጥቶባቸዋል፡፡
በመድረኩ የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩትን ምስረታ፣ ርዕይ፣ ተልዕኮ እና ኃላፊነቶቹን አስመልክቶ የኢንስቲትዩቱ ስልጠና እና ድጋፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሯ ወ/ት ቤተልሄም መርጊያ ማብራርያ ሰጥታበታለች፡፡ የአምባሳደር ፕሮግራሙን በማስመልከትም ስለተዘጋጀው የስልጠና እና ሰመር ካምፕ ቆይታ ከዚያ በኋላም ተማሪዎቹ ስለሚሰሯቸው ፕሮጀክቶች እና በአጠቃላይ ፕሮግራሙ ይኖረዋል ተብለው ስለሚጠበቁት ውጤቶች ላይ የዳይሬክቶሬቱ ባልደረባ ወ/ሮ ለምለም ሙላት ገለፃ አቅርባበታለች፡፡
የ HTTP እና የ HTTPS ምንነት
******************
ለተለያዩ ተግባራትና መረጃ ፍለጋ ኢንተርኔት ስንጠቀም በስልካችን ወይም በኮምፒውተራችን የአድራሻ መፈለጊያ ሳጥን ላይ የምንፈልገውን መረጃ በትክክል እንድናገኝ ከሚረዱን የማስፈንጠሪያ መነሻዎች ውስጥ HTTP እና HTTPS የተለመዱ ናቸው፡፡ ለመሆኑ እነዚህ ሁለቱ መነሻዎች ምንድን ናቸው?
HTTP ይህ Hypertext Transfer Protocol ለሚለው ምጻረ ቃል ሲሆን በሰርቨርና በደንበኛው መካከል ለሚደረግ ጥያቄና መልስ የተግባቦት ኮድ ነው፡፡ ደንበኛ የሚባለው አንድ ሰው ኢንተርኔትን በመጠቀም የተለያዩ መረጃዎችን የሚፈልግበት ስልክ ወይም ኮምፒውተር ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ምህጻረ ቃል በስልካችን ወይም በኮምፒውተራችን የመፈለጊያ ሳጥን ውስጥ የጻፍነው ጥያቄ መልስ የሚገኝበት አድራሻ ነው፡፡ የመጨረሻውን ትዕዛዝ ስንሰጥ ሰርቨሩ ምን ማድረግ እንዳለበት እንዲረዳ ያደርገዋል፡፡ ይህ ያስቀመጥነው ጥያቄ ወይም ፍለጋ በየትኛውም አድራሻ በማይኖር ጊዜ “404 Not Found” የሚል መልዕክት ይደርሰናል፡፡ HTTP የሚለው የመፈለጊያ መነሻ የተሰራው WWW የሚለውን የመፈለጊያ መነሻ ጽንሰ ሀሳብ በሰራው ቲም በርነርስ ሊ በተባለው ሰውና በጓደኞቹ ነው፡፡
ይህ የመረጃ መገኛ አድራሻ መፈለጊያ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው በ1991 ሲሆን በዚህ መነሻነት ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው መረጃም HTTP/0.9, በሚል የታተመ ነው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜም የተለያዩ ለውጦች ተደርገውበታል፡፡
ሌላኛው HTTPS የሚባለው ደግሞ በ1993 አካባቢ በኔትስኬፕ ኮሚኒኬሽን የተጀመረው ሲሆን ‘S’ የሚለው ጭማሪ ‘secure’ ን የሚተካ ነው፡፡ ይህም HTTPS ን የሚጠቀም ድረ-ገጽ ከስልካችን ወይም ከኮምፒውተራችን ጋር ሚስጢራዊ ትስስር በመፍጠር የምንልከውን መረጃ ምስጢራዊነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ በሚስጢር ቁልፍ የታሰረው መረጃም ማንም በቀላሉ እንዳይረዳው ‘xkndsoumnkjbktkctfc’ በዚህ መልክ የሚቀርብ ነው፡፡
የHTTPS ፕሮቶኮልን የሚጠቀሙ ድረ-ገጾች SSL የሚባል ፈቃድ እንዲኖራቸው ያስፈልጋል፡፡ ይህም የመረጃ ምንጩን ታማኝነት ለማወቅ ያስችላል፡፡ በ HTTP እና HTTPS መካከል ያለው ልዩነት በጣም ጥቂት ሲሆን ሁለተኛው የተሸሻለ የደህንነት ማረጋገጫ ያለው ነው፡፡ እንዲሁም ደግሞ የመጀመሪያው የፖርት ቁጥሩ 80 ሲሆን የሁለተኛው 443 ነው፡፡
ምንጭ፡ fossbytes
የሲውዲኗ ማህበረሰብ አንቂ አስገራሚ ውሳኔ
**************************
ግሬታ ቱንበርግ ትባላለች በሲውዲን በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ትኩረት አድርጋ የምትሰራ የማህበረሰብ አንቂ ናት፡፡ በዚህም ስራዋ የተነሳ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዙ በሚዘጋጁ ዝግጅቶች ላይ እየተጋበዘች ትታደማለች፡፡ ይሁን እንጂ እንስቷ ከኮቪድ 19 ክትባት ጋር በተያያዘ የአለማችንን ሀብታም ሀገራት ሳትታዘባቸው አልቀረችም፡፡ ለዚህም ምክንያቷ በአለም ላይ ከተሰራጩ የኮቪድ ክትባቶች ውስጥ ሶስት አራተኛ የሚሆነው መጠን የተሰራጨው ወደ አለማችን ሀብታም ሀገራት ብቻ መሆኑ ነው፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት በቲውተር ገጽዋ ላይ እንዳሰፈረችው ከሆነ ግሬታ ተንበርግ ኢ ፍትሀዊነት ለአየር ንብረት ቀውስ ዋነኛ ምክንያት ነው፡፡ በመሆኑም ሁሉም ሰዎች ክትባቱን አግኝተው የማይከተቡ ከሆነ በቀጣይ በሚዘጋጀው የአየር ንብረት ለውጥ ስብሰባ ላይ እንደማትገኝ አሳውቃለች፡፡
ከክትባት ስርጭት ጋር ተያይዞ በወጣ መረጃ መሰረት እስከ መጋቢት 30 ድረስ በአለማችን ከተመረተው ክትባት ውስጥ አነስተኛ ገቢ ላላቸው ሀገራት የተሰራጨው 0.1 በመቶ የሚሆነው ብቻ ነው፡፡ አንዳንድ ሀገራት ክትባቱ በይፋ መሰጠት ከመጀመሩ በፊት ከሚያስፈልጋቸው በላይ ለአምራቾች ማዘዛቸው የማይረሳ ነው፡፡ አለማቀፉ የአየር ንብረት ጉባኤ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አማካኝነት የሚዘጋጅ ሲሆን በመጭው ህዳር ወር ላይ በስኮትላንድ ግላስጎው የሚካሄድ ነው፡፡
ምንጭ firstpost
ተመራማሪዎች ግማሽ ሰው ግማሽ ጦጣ የሆኑ ፅንሶችን በቤተ-ሙከራ ማሳደግ ቻሉ
=======================
ተመራማሪዎች የሰው ልጅ ህዋሳትን ገና ማደግ በጀመረ የጦጣ ፅንስ ውስጥ በመክተት የሁለቱ ፍጥረታት ቅልቅል የሆነና በቤተ-ሙከራ ውስጥ ለ20 ቀናት መቆየት የቻለ ፅንስን ማሳደግ መቻላቸው ተዘገበ፡፡ የሰው-ጦጣ ፅንሶቹ አንድ ቀን በሰው ልጅ በሽታዎች፣ የፅንስ ዕድገት እና እርጅና ላይ ለሚደረጉ ምርምሮች ጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተመራማሪዎቹ የተናገሩ ሲሆን ፅንስ ውስጥ በሰው ልጅ እና ሌሎች እንስሳት ህዋሳት መካከል ያለውን መስተጋብር በመመልከትም ወደ ፊት የሰው ልጅ የሰውነት አካላትን በእንስሳቱ ውስጥ የማሳደግ አቅም ሊፈጠር እንደሚቻል ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም መሰል ምርምሮች በሰው ልጆች ላይ ብቻ በመሞከር ይታወቁ የነበሩ ነገሮችን በነዚህ ድቅሎች ላይ በመመራመር የማወቅ ዕድልንም ይከፍታል፡፡
ከዚህ ቀደም ለንቅለ ተከላ ህክምና የሚሆኑ የሰውነት አካላትን ለማሳደግ በማሰብ ተመራማሪዎች የሰው ልጅ ህዋሳትን ከአሳማ እና በግ ፅንሶች ጋር ለማዋሃድ ሲጥሩ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም የሰው ልጆች ከነዚህ እንስሳት ጋር ያላቸው ርቀት ሰፊ በመሆኑ ሳይሆን አይቀርም በሙከራዎቹ ውስጥ ጥቂት የሰው ልጅ ህዋሳት ብቻ ነው መትረፍ የቻሉት፡፡ የስነ-ህይወት ምሁሩ ፕ/ር ሁዋን ካርሎስ ኢስፒሱዋ እንደሚሉት የሰው ልጅ ለመጨረሻ ጊዜ የጋራ የዘር ግንድን ከእነዚህ እንስሳት ጋር ይጋራ ከነበረበት ከዛሬ 90 ሚሊዮን ዓመታት በፊት አንስቶ በየራሳቸው የተለያየ መንገድ ሲጓዙ ቆይተዋል፡፡ አዲሱ ጥናት ላይ ታድያ ተመራማሪዎቹ በአንፃራዊነት ከሰው ልጆች ጋር ቀረብ ያለ ርቀት እንዳላቸው የሚታመኑት ጦጣዎችን መጠቀማቸው ድቅሎቹ ውስጥ ህዋሳቶቹ በተሻለ መስተጋብር እንዲፈጥሩ እንዳደረጋቸው ፕሮፌሰሩ ይናገራሉ፡፡
ሆኖም ይህ አይነት ከሁለት የተለያዩ ፍጥረታት የተወሰዱ ህዋሳትን የያዙ ድቅሎች (chimeras) የራሳቸው የሆነ ስነ-ምግባራዊ ጥያቄዎች አሉባቸው፡፡ እዚህ ላይ አንደኛው ስጋት የነዚህ ድቅሎች ወደ ሰው የተጠጉና ከሰው ልጅ የተመሳሰለ የአስተሳሰብ ብቃት ይኖራቸው ይሆን ወይ የሚለው ነው፡፡ ምንም እንኳን በአዱሱ ጥናት ላይ ድቅል ፅንሶቹ ወደ ማህፀን ውስጥ ለመግባት ሳይታደሉ ቆይታቸው እንዲገደብ መደረጉ ከዚህ አይነት ስጋት ያላቀቀ ቢሆንም ወደፊት ቆይታቸው ምን ያህል ሊሆን ይገባል የሚለው ሌላ በባለሙያዎች ዘንድ ጥያቄን የሚያስነሳ ይሆናል፡፡
የሰው-ጦጣ ድቅሎቹን ለማግኘት ተመራማሪዎቹ በመጀመሪያ ቅድመ እንቁላሎችን (oocytes) ከአንድ ጦጣ በመውሰድና ይህን ህዋስ ከዘር ፈሳሽ ጋር በማጣመር አሳድገዋቸዋል፡፡ የጦጣዎቹ ህዋሳትን በቤተ-ሙከራው ካሳደጓቸው ከስድስት ቀናት በኋላ 25 የሰው ልጅ ህዋሳትን በእያንዳንዳቸው ውስጥ አስገቡባቸው፡፡ በዚህ ሂደት ከ132ቱ ፅንሶቹ ውስጥ ሁሉም ከሰው ልጅ ህዋሱን ከተቀበሉ ከአንድ ቀን በኋላ ህዋሳቱ ሲገኝባቸው ከነዚህ መካከል ግን 111 የሚሆኑት ብቻ የቤተ-ሙከራ ሰሀኑ ላይ መጣበቅ ችለዋል፡፡ እስከ 9ኛው ቀን ድረስ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በሕይወት ያሉ ፅንሶች የሰው ህዋሱ ሲገኝባቸው በ13ኛው ቀን ይህ ቁጥር ወደ አንድ ሦስተኛ ወርዶ ነበር፡፡ በሌላ መልኩ ከ111ዱ ውስጥ 103ቱ ለ10 ቀናት ያህል መቆየት ሲችሉ ከ15 እስከ 19 ባሉት ቀናት ውስጥ ግን ቁጥራቸው በከፍተኛ ደረጃ ሊቀንስ ችሏል፡፡ በመጨረሻም ሦስቱ ብቻ እስከ ጥናቱ መቋጫ ሊቆዩ ችለዋል፡፡
በፅንሶቹ ውስጥ ያለው የትኛው ህዋስ መቆየት ቻለ ከሚለው በተጨማሪም ተመራማሪዎቹ ፅንሶቹ ላይ የበራሂ ለውጥ መታየቱንና ፕሮቲኖችን ማምረት መቻላቸውንም ተመልክተው ነበር፡፡ በውጤቱም ከሰው ልጅ ህዋስ ጋር መገናኘታቸውን ተከትሎ አንዳንድ የጦጣ ህዋሳት ላይ ለውጥን ማስተዋል ችለዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ተመራማሪዎቹ ፅንሶቹን ወደ እንስሳቱ ማህፀን ስላላስገቧቸው ሙሉ ለሙሉ ሊያድጉ አልቻሉም፤ ለጊዜው ያን ማድረግ የጥናቱ አላማ አልነበረም፡፡ አሁን ላይ ይህን ማድረጉ በስነ-ምግባር ረገድ እጅጉን አወዛጋቢ ስለሚሆን ወደዚያ ደረጃ ከመገባቱ በፊት ተመራማሪዎችና የተቀረው ህዝብ ውይይት ሊያደርግበት ይገባል፡፡ በተጨማሪም ሙከራው የሚደረግባቸው እንስሳት ደህንነትም ጥያቄን ያስነሳል፡፡
ምንጭ፤ Live Science
ለተጨማሪ https://www.livescience.com/human-monkey-chimeric-embryos...
አየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ በከፍተኛ መጠን የጨመረው መብረቅ
==========================
ከዓመት ዓመት በፍጥነት እየሞቀ ባለው አርክቲክ ላይ የሚወርደው የመብረቅ መጠን ከአስር ዓመት በፊት ከነበረበት ከሰባት እጥፍ በላይ መጨመሩን አዲስ ጥናት አስታወቀ፡፡ ይህም በአካባቢው ያለውን የሰደድ እሳት እና አደጋ ስጋት ከፍ ማድረጉ ተገልጿል፡፡
ከሞቃታማ የምድራችን ክፍሎች አንፃር ቀዝቃዛማማ አካባቢዎች አነስተኛ የመብረቅ መጠንን ያስተናግዳሉ፡፡ አሁን ላይ ታድያ ይህ ለወትሮው አነስተኛ የነበረው የመብረቅ መጠን ጨምሮ እንደሆን ለማረጋገጥ በአሜሪካኑ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዋሽንግተን የሚያገለግለው ሮበርት ሆልወርዝ እና የሙያ አጋሮቹ በመላው ዓለም በተተከሉ የምድር ላይ ሴንሰሮች አማካኝነት ተመዝግበው የተቀመጡ የመብረቅ ክስተቶችን በካርታ ለይተዋል፡፡ በዚህም አጥኚዎቹ በበጋ ወቅቶች በሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ ከ65 ዲግሪ ላቲቲውድ በላይ በሚገኙት አካባቢዎች የሚከሰተው መብረቅ በአውሮፓውያኑ 2010 ከነበረበት 35,000 ባሳለፍነው ዓመት 2020 ወደ 250,000 ማደጉን ማረጋገጥ ችለዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ አብዛኛው የተከሰተው በአርክቲክ ውስጥ ባለው የሳይቤሪያ ክፍል ነው፡፡
ታድያ በተመራማሪዎቹ ድምዳሜ መሰረት በአርክቲክ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው የሙቀት መጠን በአካባቢው የሚፈጠረውን ደመና ይበልጥ እንዲበዛ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡ በዚህም ደመናዎቹ ውስጥ ያሉት የበረዶ ክሪስታሎች ሲጋጩና በኤሌክርትሪክ ቻርጅ ሲሆኑ መብረቁ እንዲፈጠር ያደርጋሉ፡፡
ይህ የመብረቅ መጨመር ለእሳት አደጋ ተጋላጭ ለሆኑት የአርክቲክ አካባቢዎች የሰደድ እሳት ስጋቱን ጨምሮባቸዋል፡፡ በተጨማሪም በረዶ አልባ በሆነው የአርክቲክ ክፍል የሚንቀሳቀሱ መርከቦችም ለዚህ የመብረቅ አደጋ ይበልጡን ተጋላጭ እንዲሆኑ ስለማስቻሉ አጥኚዎቹ ገልፀዋል፡፡
ምንጭ፤ Nature
ለተጨማሪ ( https://www.nature.com/articles/d41586-021-00797-3 )
በዓለም ዙሪያ አንድ ቢሊዮን ሰዎች በሚተኙበት ጊዜ ለረዥም ሰከንዶች መተንፈስ ያቆማሉ፡ ለምን
=======================
እንደየራሳችን አቅም እና እንዳለንበት ሁኔታ መጠነኛ ለውጥ ቢኖረውም ሁላችንም የሰው ልጆች በተፈጥሮ ስሪታችን ሶስቱን የህይወት መሰረቶች በሚያስፈልገው ልክ ካላገኘን ህይወታችን አደጋ ውስጥ ነው፡፡ ያለ ኦክስጅን ሶስት ደቂቃ፣ ያለውሃ ሶስት ቀን፣ ያለምግብ ሶስት ሳምንት መቆየት ባይቻለንም በተለያዩ አጋጠሚዎች ከዚህ የተለየ ወጤት የሚታይባቸው ሁኔታዎች ይኖራሉ፡፡ ይሁንና አብዛኞቻችን እነዚህ የህይወት መሰረቶች በተባለው የጊዜ ገደብ ያልተሟሉልን እንደሆነ ህይወታችን አደጋ ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡
በአለማችን አደገኛ የእንቅልፍ ችግር በሚባለው ስሊፐ አፒኒያ ወይም በሙሉ ስያሜው obstructive sleep apnea ምክንያት አንድ ቢሊየን ሰዎች ከ10 ሰኮንድ አንስቶ እስከ 60 እና 70 ሰኮንድ አየር ወደ ውስጣቸው ማስገባትና ማስወጣት ሊቸገሩ ይችላሉ፡፡ በዚህ የጤና እክል ምክንያት ለረዥም ሰኮንዶች መተንፈስ የሚያቆሙ ሰዎች በአንድ የእንቅልፍ ምሽት ከ300 እስከ 400 ጊዜ ዳጋግሞ ሊያጋጥማቸው የሚችል ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ ችግሩ ያለባቸው ሰዎች መተንፈስ ማቆማቸውን እንኳን ላይረዱ ይችላሉ፡፡
በህይወት ለመኖር የግድ ከሚያስፈልጉን የተፈጥሮ ስጦታዎች በቀዳሚነት የሚቀመጠው ኦክስጅን በዚህ የእንቅልፍ ችግር ተጽዕኖ ውስጥ የሚገባበት ሁኔታ እንደሰዎች አቅምና ባህሪ መጠነኛ ለውጥ ቢኖረውም አብዛኞቹ የችግሩ ተጠቂዎች ግን በአየር ማስወጫና ማስገቢያ አካላቶቻቸው ላይ የመታፈን ነገር በመፍጠር ትክክለኛውን የኦክስጅን መጠን እንዳያገኙ የሚግድ የጤና ችግር ነው፡፡ በተለይም ከጉሮሯችን ወደሳምባችን አየር ለማዘዋወር በሚያስችለን የአየር ቧንቧ ወይም (windpipe) ላይ ትክለኛው የኦክስጅን መጠን እንዳይወጣና እንዳይገባ በማገድ በተወሰነ የእንቅልፍ ሰኣት ለሰከንዶች መተንፈስ እንድናቆም የሚያደርገን ችግር ነው፡፡
ይህ የጤና እክል ያለባቸው ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ወንዶችና እድሜያቸው ከ40 አመት በላይ የሆኑ ሰዎች ቢሆኑም ሴቶች እና እድሜያቸው ከዛ በታች በሆኑ ሰዎች ላይም የመከሰት እድል አለው፡፡ ብዙዉን ጊዜ የችግሩ መከሰቻ ምክንያት በመተንፈሻ ኣካላት ላይ ያለ ተፈጥሮአዊ ባህሪ ወይም ከቤተሰብ የሚወረስ ተያያዥ ችግር ቢሆንም በዛው መጠን ግን ከአኗኗር ዘይቤ ጋር የተያያዙ የሰውነት ክብደት፣ አልኮልና የሲጋራ ሱስ ችግሮች ለዚህ የጤና እክል ሊያጋልጡን ይችላሉ፡፡ ይህ የእንቅልፍ ችግር የሚታይባቸው ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ከፍተኛ የጩኸት መጠን ያለው የማንኮራፋት ድምፅ የሚሰሙ ሲሆን፣ ለተወሰነ ሰከንድ ደግሞ ትንፋሽ ማውጣት ይቸገራሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በቀን ውሏቸው ከፍተኛ የድካም ስሜት የሚታይባቸው ሲሆን፣ በስራ ቦታ እና በሌሎች እንቀቅስቀሴዎች ላይም ከባድ የእንቅልፍ ስሜት ይሰማቸዋል፡፡
ይህ የጤና እክል ያለባቸው ሰዎች በተገቢው ሁኔታ ህክምና የማያገኙ ከሆነ ከባድ ችግር በጤናቸው ላይ ሊከሰት ይችላል፡፡ በተለይም ከፍተኛ የደም ግፊት፣ የልብ ስራ ማቆም፣ ስትሮክ እና የማስታወስ ችግሮች በዚህ የጤና እክል ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ ከባድ የጤና ቀውሶች ናቸው፡፡ በዓለም ዙሪያ አንድ ቢሊዮን ሰዎች በሚተኙበት ጊዜ ይህ የጤና እክል እንደሚጋጥማቸው የሚገለፅ ቢሆንም ብዙ የችግሩ ተጠቂዎች ግን በሽታው እንዳለባቸው እንኳን ላያውቁ ይችላሉ፡፡
ምንጭ፡ https://www.sleepapnea.org/learn/sleep-apnea/ እና businessinsider
የአዶቤ መስራችና የ PDFs አበልጻጊ በ81 ዓመታቸው አረፉ
**********************************************
አዶቤ የተሰኘው የሶፍትዌር ካምፓኒ መስራች እና የፖርቴብል ዶክመንት ፎርማት (PDF) ማበልጸግ ላይ ከፍተኛ እገዛ ያደረጉት ቻርልስ ጌሽቼክ በ81 ዓመታቸው ማረፋቸው ተሰምቷል፡፡ ካምፓኒው እንዳወጣው መረጃ ከሆነ የእኚህ የቴክኖሎጂ ሰው ህልፈት ለቴክኖሎጂው ዘርፍ በተለይ ለአዶቤ ካምፓኒ ትልቅ ጉዳት ነው፡፡
የአዶቤ ካምፓኒ በቻርልስ ጌሽቼክ እና በጆን ዋሞክ ቅንጅት የተመሰረተ የሶፍትዌር ካምፓኒ ነው፡፡ ተቋሙ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ትልቅ እገዛ ያደረጉ እንደ አዶቤ ፖስት ስክሪፕት፣ ፒ.ዲ.ኤፍ፣ አክሮባት፣ ኢሉስትሬተር፣ ፕሪሚየር ፕሮ እና ፎቶ ሾፕ ያሉ ሶፍትዌሮችን አበርክቷል፡፡
ጌሽቼክ ከካርንጌ ምሎን ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከሰሩ በኋላ ዜሮክስ ፓሎ ለቶ በሚባል የምርምር ማዕከል መስራት ጀምረዋል፡፡ በዚህም ተቋም እያሉ ነው የአዶቤ አጋራቸውን የተዋወቁት፡፡ ከዚያም በ1982 የምርምር ተቀዋሙን ለቅቀው አዶቤ የተሰኘውን የሶፍትዌር ማበልጸጊያ ድርጅት አቋቁመዋል፡፡
በ2009 የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ የአዶቤ መስራች ለሆኑት ጌሽቼክና ዋርኖክ ብሔራዊ የቴክኖሎጂ ሜዳልያን ሸልመዋል፡፡ የመረጃ ምጫችን ጌሽቼክ በ1992 ከተቃጣባቸው የጠለፋ ሙከራ እንዳመለጡ ተናግሯል፡፡
ምንጭ፡ Tech Xplore
ለተጨማሪ ንባብ https://techxplore.com/news/2021-04-founder-adobe-pdfs-dies-age.html
የካንሰር ህመም በጭንቅላት ውስጥ እንዴት እንደሚስፋፋ ሞዴል የሰራው ኢትዮጵያዊ
********************************
ዶክተር ብስራት ጎደፋይ ደበበ ይባላሉ በቴክሳስ ዩኒቨርሲቲ የአንደርሰን ካንሰር ማዕከል ረዳት ፕሮፌሰር ሲሆኑ የካንሰር ህመም በጭንቅላት ውስጥ የሚያደርገውን መስፋፋት የሚያመለክት ሞዴል ሰርተው ማቅረባቸው ተሰምቷል፡፡ ዶክተር ብስራት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በእንስሳት ህክምና ዘርፍ ያጠኑ ሲሆን የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በ USAID አመቻችነት አላባማ ውስጥ በሚገኝ ቱስኬጊ የኒቨርሲቲ በኢፒዲሞሎጂ በ2005 አጠናቅቀዋል፡፡
ለመጀመሪያ ዲግሪያቸው ማጠናቀቂ የሰሩት ጥናታዊ ጽሁፍ በወተት ላሞችና በወተት ማከፋፈያ መደብሮች አካባቢ የሚኖርን ባክቴሪያዊ ብክለት የተመለከተ ሲሆን በዚህም ዩኒቨርሲቲው ሜዳሊያ ሸልሟቸዋል፡፡ ይህ በ2000 አም ለህትመት የበቃው የምርምር ውጤት ጥናትና ምርምር እንዴት እንደሚሰራ የተማርኩበት ነው ሲሉ ዶክተር ብስራት መናገራቸውን የመረጃ ምንጫችን ዘግቧል፡፡
ዶክተር ብስራት የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከቴክሳሱ A&M ዩኒቨርሲቲ በ2008 አግኝተዋል፡፡ የዶክትሬት ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ አደገኛ በሆነው የጡት ካንሰር ዙሪያ ጠንከር ያለ ስራ መስራት እንደጀመሩ የሚነገርላቸው ዶክተር ብስራት በዘርፉ የተለያዩ ምርምሮችን አድርገዋል፡፡
ከ2017 ጀምሮ MD አንደርሰን የካንሰር ማእከል ውስጥ ረዳት ፕሮፌሰር በመሆን እያገለገሉ ሲሆን በዚህ ወቅት ነው ስለ metastasis በጥልቀት ማጥናት የጀመሩት፡፡ በአሜሪካን የካንሰር ማህበረሰብ የሚደገፍና የካንሰር ህዋሳት እንዴት ጭንቅላት ውስጥ እንደሚስፋፉ የሚያጠና ምርምርን ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ሲያጠኑ ቆይተዋል፡፡ በትግራይ ሀይደር ሆስፒታል የካንሰር ህሙማንን የመለየትና ህክምና የመስጠት አቅምን ለማሳደግ የሚያችሉ የተለያዩ ስራዎችን ሲሰሩ የቆዩት ዶክተር ብስራት በትግራይ ውስጥ በተፈጠረው ግጭትና የህግ ማስከበር ምክንያት እንቅስቃሴያቸው ቢቋረጥም ጥግራይን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ውስጥ ለመሳተፍ እንደተዘጋጁ የመረጃ ምጫችን ዘግቧል፡፡
ምንጭ፡ the-scientist
በተለያዩ አማራጮች ይከታተሉን
ዩትዩብ youtube.com/channel/UC6jvUOLRSkVEQtc
5Annfwvg
ቴሌግራም t.me/TechIn2
ትዊተር twitter.com/TechinEthiopia
ለተጨማሪ ንባብ https://www.the-scientist.com/scientist-to-watch/bisrat-debeb-models-how-cancer-spreads-to-the-brain-68575?utm_content=162711473&utm_medium=social&utm_source=facebook&hss_channel=fbp-212009668822281&fbclid=IwAR2mHMfSw23CSfEIb71bBzp3HV61fhzovs4yzgJ1E6Le0vpuSCRO0o86kRc
አጥኚዎች አልበርት አንስታይንን ወደ ህይወት መልሰው ከሰዎች ጋር እንዲነጋገር አደረጉት
=============
ከወደ ጥንቆላው ዓለም በሙት መንፈስ አማካኝነት ከብዙ ዓመታት በፊት ያለፉ ቤተሰብ እና ሌሎች ወዳጆችን ማዋራት እንደሚቻል ሲነገር ብዙዎቻችን ሰምተን ይሆናል፡፡ ታድያ በእንግሊዙ የድምፅ ሰሪ ኩባንያ ኤፍሎሪዝሚክ እና በኒውዚላንዱ የዲጁታል ሰብ አበልፃጊ አኒኪው ወስጥ ያሉ አጥኚዎችም ታሪካዊውን የሳይንስ ሊቅ አልበርት አንስታይንን በድምፅም በምስልም መስሎ የሚናገር የሰው ሰራሽ አስተውሎት ስርዓትን ይዘው መጥተዋል፡፡
ሁለቱ ተቋማት ተጠቃሚዎች ልክ እራሱ አልበርት አንስታይንን እንደሚያዋሩት በሚመስላቸው መልኩ ጥያቄዎችን እንዲጠይቁት አልመው ነው ይህን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ስርዓት በትብብር የገነቡት፡፡ ኩባንያዎቹ እንደሚሉት ከሆነ ስመ ጥሩን ሳይንቲስት ለዚህ ስራ የመረጡት በሰዎች ዘንድ ባለው የባለ ምጡቅ አዕምሮ ባለቤትነት እይታ፣ ታሪካዊ ስብዕና፣ የቴክኖሎጂ ልክፍተኝነቱ እንዲሁም ብዙዎች የተለያዩ ጥያቄዎችን ሊያቀርቡለት የሚፈልጉት ሰው ነው ብለው በማመናቸው ነው፡፡
ምስለ አንስታይን ሊቅነቱን እንዲያስመሰክርና በተቻለ መጠንም እውነተኛ ይመስል ዘንድ የረቀቁ ኮምፒውተራዊ ስልቶችን አኒኪው ሰጥቶታል፡፡ ሆኖም የአልበርት አንስታይንን ድምፅ በትክክል በማስመሰሉ ረገድ ነገሮች ፍፁም አልሆኑም፡፡ አጥኚዎቹ ማግኘት የቻሏቸው የሳይንቲስቱ ታሪካዊ ንግግሮች የሚያመላክቱት አልበርት አንስታይን እንግሊዝኛው ከፍተኛ የጀርመንኛ ተፅዕንዖ ያለበት፣ ሲናገርም በዝግታ፣ ትህትና፣ ጠቢብነት እንዲሁም ሞቅ ባለ ቶን ተሞልቶ መሆኑን ነው፡፡ ሆኖም አልበርት በሚናገረው እንግሊዝኛና የድሮ መቅርፀ ድምፆች ባላቸው የጥራት መጓደል ሳብያ ተመራማሪው ትክክለኛው ድምፁ ምን ሊመስል ይችላል የሚለውን ለመለየት አስቸግሯቸው ነበር፡፡
ታድያ ብዙዎቹ ተጠቃሚዎች በቴክኖሎጂው አማካኝነት ከአንስታይን ጋር ሲገናኙ ስለ ድምፁ ትክክለኝነት ብዙም ግድ እንደማይሰጣቸው አምነዋል፡፡ ይህን ከግምት በማስገባትም አጥኚዎቹ ከዚህ ስመጥር የፊዚክስ ተመራማሪ ጋር አንድ አይነት ያልሆነ፤ ግን ደግሞ በሚያነጋግሩት ተጠቃሚዎች ዘንድ ሊቀር የሚችል ሌላ ድምፅ ለምስለ አንስታይኑ ሰጥተውታል፡፡ ይህ አዲስ ድምፅ ምስለ አልበርት አንስታይን የተወሰነ ጀርመንኛ ዘዬ ባለው መልኩ እንዲናገርና ለተጠቃሚዎችም ንግግሩ የተጫዋችና በወዳጅ ቅርበት የተዋዛ መስሎ እንዲታያቸው የተሰራ ነው፡፡ በተጨማሪም አጥኚዎቹ ይህ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ስርዓት ምስለ አልበርት ተጠቃሚዎችን ሲያነጋግር ልክ ከራሱ ዕውቀት ተነስቶ የሚናገር ሊቅ እንዲመስል ጭምር አድርገውታል፡፡
ከድምፁ ባሻገርም ይህ የአልበርት ዲጂታል ምስለእኔን ሲሰሩት ልክ እንደ ደንበኞች አገልግሎት ጥሪ ወይም የግል ረዳት ሁሉ የተጠቃሚዎችን ጥያቄ በፍጥነት እንዲመልስ አድርገው መስራት ነበረባቸው፡፡ አጥኚዎቹ ይህን ለማሳካት ሰው ሰራሽ አስተውሎቱን ከረቀቀ ኮምፒውተራዊ አሰራር ያቀናጁት ሲሆን ማሻሻያዎቹን ማድረግ ከጀመሩበት ከሁለት ሳምንታት በኋላም ስርዓቱ ለጠያቂዎቹ ምላሽ ለመስጠት የሚወስድበትን ጊዜ ከ12 ሴኮንድ ወደ 3 ሴኮንድ ማውረድ ችለዋል፡፡
ታድያ ተመራማሪዎቹ ይህ የአልበርት አንስታይን ዲጂታል ምስለእኔ በሰው ልጆች እና ሰው ሰራሽ አስተውሎት ስርዓት መካከል ሊደረግ ስለሚችለው መስተጋብር የመጀመሪያ እርምጃ አድርገው ተመልክተውታል፡፡
እርስዎም ይህን ሊንክ በመጠቀም አልበርት አንስታይንን ሊያዋሩት ይችላሉ https://einstein.digital
humans.com/
ምንጭ፤ Tech Xplore
የኮሌጅ ዲግሪን በ6 ወር የምስክር ወረቀት ለመተካት ያሰበው ጎግል
******************
የቴክኖሎጂ ኩባንያ የሆነው ጎግል ከኮሌጅ ዲግሪ ይልቅ የስድስት ወር ርዝማኔ ያላቸውን ኮርሶች በመስጠት ሰራተኞችን ለመቅጠር ማቀዱን አሳውቋል፡፡ ኩባንያው አራት አመት በሚረዝም የዩኒቨርሲቲ ዲግሪ ስራ ለመቀጠር ከሚወዳደሩ ሰዎች ይልቅ ድርጅቱ የሚያዘጋጀውን የስድስት ወር ኮርስ በማጠናቀቅ ምስክር ወረቀት ያላቸውን ሰዎች ተመራጭ እንደሚያደርግ ተናግሯል፡፡
ለዚህ ስልጠና የሚያስፈልገው ክፍያ እስካሁን ይፋ ባይደረግም ከዚህ ቀደም ድርጅቱ ከሚሰጣቸው ስልጠናዎች ዋጋ በመነሳት እስከ 300 የአሜሪካን ዶላር ሊደርስ እንደሚችል ተገምቷል፡፡ ድርጅቱ 100 ሺህ የሚደርሱ የትምህርት እድሎችን እንዳመቻቸ ያሳወቀ ሲሆን በትምህርታቸው የተሻለ አፈጻጸም ያላቸው ተማሪዎች ኮርሱን ቢወስዱ ከፍተኛ ከፋይ በሆኑ ተቋማት የመቀጠር እድላቸውን እንደሚያሰፋላቸው ተነግሯል፡፡
በዚህ የስድስት ወር ፕሮግራም ውስጥ እንደ መረጃ ትንተና እና የፕሮጀክት አስተዳደር ያሉ ኮርሶች ተካተውበታል፡፡ እነዚህ የስልጠና አይነቶች የጎግል ተቀጣሪ የሆኑ ሙያተኞችን ክህሎት ለማዳበር ታስበው የተዘጋጁ ሲሆን ሰራተኞቹ ከስልጠናዎቹ አዳዲስ ክህሎቶችን እንደሚማሩባቸው የተናገሩት የጎግል አለም አቀፍ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዘዳንት ኬንት ዎከር አክለውም በስልጠናዎቹ የሚሳተፉ ሰዎች ስራ ለማግኘት የሚያደርጉትን ጥረት እጅግ እንደሚቀልላቸው ገልጸዋል፡፡ ለስልጠናዎቹም ምንም አይነት ዲግሪም ሆነ የስራ ልምድ አይጠየቅም ተብሏል፡፡
የዚህ ፕሮግራም አላማ እንደ ድርጅቱ መረጃ ከሆነ በተለይ በአሜሪካ የኮሌጅና የዩኒቨርሲቲ ዲግሪ ለሁሉም ተደራሽ አለመሆንና ኢኮኖሚያዊ ደህንነትን ለማረጋገጥ የግድ የኮሌጅ ዲግሪ አስፈላጊ ባለመሆኑ ሲሆን በተለይ በአጫጭር ስለጠናዎች ሊሰሩ የሚችሉ ስራዎችን ለመስራት አራትና አምስት አመት በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ሆኖ ጊዜን፣ ገንዘብንና ጉልበትን መጨረስ አያስፈልግም በሚል እሳቤ እንደሆነ ታውቋል፡፡
ምንጭ፡ iflscience
ተጨማሪ ንባብ https://www.iflscience.com/policy/google-plan-to-replace-the-need-for-college-degrees-with-sixmonth-certificates/?fbclid=IwAR3kngUgDi-ItPY9gtQRZ4BrRzu12BQEbopIlOuUspLuXdRE2JPK18Xaf5A
ኢትዮ ቴሌኮም የሞባይል ክፍያ አገልግሎት በቅርቡ ሊጀምር ነው
=======================
ኢትዮ ቴሌኮም በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ደንበኞች ስልካቸውን በመጠቀም ብቻ ገንዘብ እንዲልኩ፣ እንዲቀበሉና ግዢ እንዲፈፅሙ የሚያስችል የሞባይል ክፍያ አገልግሎት ሊጀምር መሆኑ ተነገረ፡፡ ቴሌብር የተሰኘው የክፍያ ስርዓቱ ደንበኞች ካሽ ወይም ቼክ ሳያስፈልጋቸው ዘርፈ ብዙ ክፍያዎችን እንዲፈፅሙ የሚያደርግ ነው፡፡
ቴሌብር ደንበኞች በሀገር ውስጥም ሆነ ዓለም አቀፍ ደረጃ በሁሉም የትስስር መንገዶች ላይ ገንዘብ መላላክን፣ ለዕቃና አገልግሎቶች ግዢ የሚደረጉ ክፍያዎችን መፈፀም እንዲያስችል ተደርጎ መሰራቱ ተገልጿል፡፡ በዚህም ደንበኞች ለምሳሌ የትምህርት ቤት፣ የውሃና ኤሌክትሪክ እንዲሁም ሌሎች መሰል ክፍያዎችን በስልካቸው እንዲፈፅሙ ያስችላቸዋል፡፡ በተጨማሪም በኢትዮ ቴሌኮም ለሚቀርቡ እንደ አየር ሰዓት ግዢ ላሉ አገልግሎቶች ክፍያን እንዲፈፅሙ ያመቻቸ ነው፡፡ በሌላ መልኩ አገልግሎቱ የኩባንያው ደንበኞች ከሀገር ውጪ ካለው ዲያስቦራ ገንዘብ እንዲቀበሉ፣ ገንዘባቸውን እንዲቆጥቡ፣ ብድር እንዲያገኙና የባንክ አካውንታቸውን ከቴሌብር ጋራ እንዲያስተሳስሩ የሚፈቅድ ይሆናል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎቱን ያስጀምር ዘንድ ከአንድ ዓመት በፊት ለዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶች ፍቀድ ለሚሰጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥያቄውን አቅርቦ ነበር፡፡ ባንኩም ለአገልግሎቱ አረንጓዴ መብራት ከሰጠ በኋላ ነው ኩባንያው እንቅስቃሴውን የጀመረው፡፡
ደንበኞች ለቴሌብር ለመመዝገብ የኢትዮ ቴሌኮም ሲም ካርድ ያለበት ተንቀሳቃሽ ስልካቸውን እና ማንነታቸውን የሚገልፅ መታወቂያ ይዘው ወደ ቴሌብር ወኪሎች አልያም የኢትዮ ቴሌኮም ሽያጭ ማዕከላት በማምራት መመዝገብ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡
ምንጭ፤ Capital
ለተጨማሪ ንባብ https://www.capitalethiopia.com/.../telebirr-to-launch.../