TechIn2
1.16K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
አነስተኛ እርሻዎችና ትልቁ ጥቅማቸው
=====================
በአነስተኛ መሬት ላይ የሚሰሩ እርሻዎች ከትልልቆቹ አንፃር ይበልጥ ምርታማ፣ አትራፊና ለአካባቢው ስነ-ምህዳርም ይበልጥ ተስማሚ ናቸው ተባለ፡፡ በዓለማችን አብዛኛው የምግብ ምርት ከሰፋፊ እርሻዎች የሚሰበሰበው ቢሆንም አነስተኛ እርሻዎችም ብዙ ያልተባለለት ትርፋማነትን እንደሚያጎናፅፉ ተነግሯል፡፡
በዓለማችን ካሉ አርሶ አደሮች ውስጥ 84 በመቶ የሚሆኑት ከሁለት ሄክታር ባነሰ መሬት ላይ እያረሱ ይገኛሉ፡፡ ታድያ ብዙ የፖሊሲ አውጪዎች እና የሳይንሱ ተመራማሪዎች እነዚህ በአነስተኛ መሬት ላይ የሚከወኑ እርሻዎች የዓለማችንን አብዛኛውን ሰብል ከሚሰጡት ሰፋፊ እርሻዎች በላቀ ውጤታማ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ቪንሰንት ሪቺያርዲ እና በካናዳው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ብሪቲሽ ኮሎምቢያ የሚገኙ የሙያ አጋሮቹ ከ50 ዓመታት በተሻገረ ጊዜ ውስጥ በ51 ሀገራት ላይ የተሰሩ 118 ጥናቶችን በመተንተን የአንድ እርሻ መሬት ስፋት ከምርት ዕድገት ባሻገር ስለሚያመጣው ልዩነት ምልከታን አድርገዋል፡፡
በዚህም ቡድኑ ምናልባትም በቤተሰብ የሰው ጉልበት ምክንያትም ሊሆን ይችላል ባለው መልኩ አነስተኛ ማሳዎች ከትላልቆቹ የተሻለ ምርትን እንደሚሰጡ መመልከት ችሏል፡፡ በተጨማሪም እነዚ አነስተኛ እርሻዎች ከትላልቆቹ እርሻዎች በበለጠ የአዝእርት ብዝሀነት እና ከሰብል ውጭ ያለ ስነ-ምህዳርንም ይዘው ተገኝተዋል፡፡ ለዚህም ከትላልቆቹ የእርሻ ኢንዱስትሪዎች ጋር ሲነፃፀሩ አነስተኛ ፀረ-ተባይን መጠቀማቸው፣ በተለያየ አይነት የመሬት አቀማመጦች ላይ መገኘታቸው እንዲሁም ሰፋ ያለ ከማይታረሰው መሬት ጋር የሚለይ ነፃ መሬትን መያዛቸው በምክንያትነት ተጠቅሷል፡፡
አጥኚዎቹ ባቀረቡት ምክረ ሀሳብ መሰረት አነስተኛ እርሻዎችን መደገፉ በአንድ እጅ የምግብ ምርትን በከፍተኛ ደረጃ ሲያሳድግ በሌላ እጅ ደግሞ እጅግ ጠቃሚ ሰብአዊና ስነ-ምህዳራዊ ጥቅሞችን ያመጣል፡፡
ምንጭ፤ Nature
ሦስት ብልቶችን ይዞ የተወለደው ህፃን
====================
ሁለት ተጨማሪ ብልቶችን ይዞ በኢራቋ የዱሆክ ከተማ የተወለደው ህፃኑ ሁለቱን ብልቶች የማስወገድ ቀዶ ህክምና ተደርጎለታል፡፡ በቀዶ ህክምናው የተወገዱት ሁለቱ ብልቶች ሲሆኑ ሦስተኛው ግን በትክክለኛው ቦታ ላይ ያደገ ነው፡፡ በኢንተርናሽናል ጆርናል ኦፍ ሰርጀሪ ኬዝ ሪፖርትስ ላይ ታትሞ የወጣው ፅሁፍ እንደሚያመላክተው ህፃኑ የቀዶ ህክምናው ከተደረገለት ከአንድ ዓመት በኋላ በተደረገለት ምርመራ በመልካም ጤንነት ስለመገኘቱ ማወቅ ተችሏል፡፡
ትርፍ የወንድ ብልቶችን ይዞ መወለድ እጅጉን አልፎ አልፎ የሚመጣ የጤና ሁኔታ ሲሆን ከ5 እስከ 6 ሚሊዮን በህይወት ከሚወለዱ ህፃናት መካከል በአንዱ ላይ ብቻ የሚከሰት ነው፡፡ የእነዚህ ተጨማሪ ብልቶቹ እድገት ከሁኔታ ሁኔታ የሚለያይ ነው፡፡ የዚህ ህፃን ትርፍ ብልቶችም ኮርፐስ ካቭርኖሰም የተባሉ የኢሬክታይል ህብረ ሕዋሳትን የያዙ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ኮርፐስ ስፖንጂዮሰም የተባሉ ህዋሳትን በመያዛቸውም ሽንት የሚያልፍበትን የዩሪትራ ቱቦ እንዲደግፉ አድርጓቸዋል፡፡ ይህ ታድያ ትርፍ የሰውነት አካላቱን ለማስወገድ ቀላል አድርጓቸዋል፡፡
በጥናቱ ላይ ተሳታፊ ያልንበሩት በቅዱስ ሉዊስ ዩኒቨርሲቱ የህክምና ትምህርት ክፍል የሰውነት ክፍሎች ጥናት ፕሮፌሰሩ ጆን ማርቲን እንደሚናገሩት የትርፍ ብልቶች ነገር ብዙም የሚታወቅ አይደለም፡፡ ፕሮፌሰሩ ነገሩን ለመጀመሪያ ጊዜ መረዳት የቻሉት በሟቾች የተለገሰ ሬሳን ተጠቅመው በሚያስተምሩበት ጊዜ ነበር፤ ከተለገሳቸው ሬሳዎች መካከል አንደኛው ሁለት ብልቶች ያሉት መሆኑን በማየት፡፡ በ84 ዓመታቸው የሞቱት ሰው የሆነው ሬሳው ላይ ያሉት ብልቶች ሁለቱም ትክክለኛ መጠን ያላቸውና በታችኛው መሰረታቸው ላይም ሁለት የሽንት መተላለፊያዎችን የያዙ ናቸው፡፡ ለጋሹ ከመሞታቸው በፊት ስለ ሁኔታው ምንም አላሉም ነበር፡፡ ሰውየው ሁለት ልጆች እንዳሏቸው የሚናገሩት ፕሮፌሰር ጆን ልጆቹ የእርሱ ስለመሆናቸው አልያም ሌላ ስልትን በመጠቀም ስለመወለዳቸው ግን ማወቅ እንዳልተቻለ ያክላሉ፡፡ ታድያ ፕሮፌሰር ጆን ሁኔታውን ለመረዳት ያስችላቸው ዘንድ በተለገሰው ሬሳ ላይ የበራሂ ምርመራ ሲያከናውኑ በብልት እድገት ላይ ድርሻ አላቸው በሚባሉት በራሂዎች ላይ የተለያዩ ለውጦችን (mutations) መመልከት ቻሉ፡፡ ለውጡ ከታየባቸው መካከል ሲሊያ ተብለው በሚጠሩት የፀጉር መሳይ ነገሮች ዕድገት ላይ የሚሳተፉት ይገኙበታል፡፡
ፕሮፌሰር ጆን እንደሚሉት ሲሊያዎች ወደ አንድ አቅጣጫ ስለሚያዘነብሉና በዚህም እያደገ ባለው ኢምብሪዮ በአንድ ወይም በሌላ ጎን በኩል እንዲሆን ያስችላሉ፡፡ መሰል ከተፈጥሮ ሁኔታ የመውጣት ነገር በሌሎች ስፍራዎች ላይም የታየ ሲሆን ከነዚህ ውስጥም አካላት በጤናማ ሁኔታ መገኘት ከሚገባቸው አቀማመጥ በተቃራኒ በሚቀመጡበት ሁኔታ ላይ ነው፡፡
ታድያ ይህን ህፃን ያከሙት ሀኪሞች እንዳረጋገጡት በልጁ እርግዝና ወቅት ምንም አይነት ሁኔታውን ሊያስረዳ የሚችል የኬሚካል ተጋላጭነት አልነበረውም፡፡
ምንጭ፤ Live Science
የአለማችን ግዙፉ ጥንቸል ተሰረቀ
--------------------------------------
በአለም የድንቃድንቅ መዝገብ ውስጥ 129 ሳንቲ ሜትር በመርዘም የአለማችን ረጅሙ ጥንቸል በመባል የተመዘገበው ጥንቸል መጥፋቱ ተነገረ፡፡ ጥንቸሉ የጠፋው ወርሴስቴርሸር ከተባለው የማቆያ ስፍራው ነው፡፡ የጥንቸሉ ባለቤት የጥንቸሉን መጥፋ ካረጋገጡ በኋላ ጥንቸሉ የሚገኝበትን ቦታ ላመለከተ 1 ሺህ ይሮ ማዘጋጀታቸው ተሰምቷል፡፡
ዳሪየስ የተሰኘው ይህ ጥንቸል እድሜው ከፍ ያለ በመሆኑ የመራባት እድል እንደሌለው ተሰምቷል፡፡ ጉዳዩን የያዘው ፖሊስ ጥንቸሉ ከሚንቀሳቀስበት ሜዳማ ስፍራ እንደተሰረቀ የሚገልጽ መረጃን አውጥቷል፡፡ የጥንቸሉ ባለቤት የሆነችው አኔቴ ኤድዋርድ ጥንቸሏ የጠፋበት ቀን እጅግ ያዘነችበት ቀን እንደሆነ ተናግራለች፡፡ አክላም የወሰዱባት ሰዎች ጥንቸሉን እንዲመልሱላት በቲውተር ተማጽኖዋን አቅርባለች፡፡
ጥንቸሉ የጠፋው በፈረንጆቹ ሚያዚያ 10 ለ11 አጥቢያ ሲሆን በጉዳዩ ዙሪያ ምንም አይነት መረጃ ያለው ሰው ትብብር እንዲያደርግ እና ጥንቸሉ ከተገኘ ቃል የተገባው የ1 ሺይሮ ፓውንድ ሽልማት እንደሚበረከትም ፖሊስ አሳውቋል፡፡
ምንጭ sky news
የኢኖቬሽን ፕሮግራም ጅማሮ
===============
ኢኖቬሽንን በሀገራችን ለማስፋፋት በማለም በቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት የተሰናዳው የኢኖቬሽን ፕሮግራም ሐሙስ ሚያዝያ 7 ይጀመራል። ለዚህ ፕሮግራም ማስጀመሪያ ይሆን ዘንድም ልዩ ልዩ የሀገራችን የኢኖቬሽን ተዋንያንን ያካተተ መርሀ ግብር በማዶ ሆቴል ተሰናድቷል። በመርሀ ግብሩ ላይ ተሳታፊ ከሚሆኑት መካከል መጋቢ ሀዲስ ዶ/ር ሮዳስ ታደሰ፣ ወጣቱ የፈጠራ ሰው ኢዘዲን ካሚል እና ከተለያዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተወጣጡ በኢኖቬሽን አምባሳደርነት የተሾሙ ተማሪዎች ይገኙበታል።
በኢኖቬሽን ፕሮግራሙ ላይ ከትምህርት ቤቶቹ የተውጣጡት ተማሪዎች ለአንድ ወር ገደማ ስልጠና ከተሰጣቸው በኋላ ኢንስቲትዩቱ ወዳዘጋጀው ለሁለት ወራት የሚቆይ ሰመር ካምፕ በመግባት የራሳቸውን ፕሮጀክቶች እንዲቀርጹ የሚደረግ ይሄናል።
የሶፍትዌር ማሻሻያ እየጠበቀች ማርስ ላይ ያለችው የናሳ ሔሊኮፍ
*************************
ከጥቂት ቀናት በፊት በማርስ ውስጥ የተለያዩ ቅኝቶችን ለማድረግ ታስባ የተሰራችው ሄሊኮፍተር ከምድራችን ውጭ የቅኝት በረራን የምታደርግ የመጀመሪያዋ ሄሌኮፍተር ተብላ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ማርስ ላይ ያለበረራ ተቀምጣለች፡፡ የህዋ ምርምር ኤጀንሲው ሄሊኮፍተሯ የሶፍተዌር ማሻሻያ እንደሚያስፈልጋት ተናግሯል፡፡ የምርምር ተቋሙ ይህን ይበል እንጂ የሄሊኮፍተሯን የአካል ክፍል የሚከታተሉ ኢንጅነሮች በውጨኛው ተሸከርካሪ ክፍል (rotor) ላይ ችግር እንዳስተዋሉ ተናግረዋል፡፡
ኢንጂነሮቹ ባስተዋሉት ችግር ምንያት ኢግኒዩቲ የተሰኘችው አነስተኛ ሄሊኮፍተር የሙከራ በረራዋ እንዲዘገይ አድርገዋል፡፡ ችግሩ ከታወቀበት ጊዜ ጀምሮ መፍትሔዎችን በማፈላለግ ላይ ያሉት ኢንጅነሮቹ የሙከራ በረራውን ለማድረግ ጥረቶችን እያደረጉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
እንደ ናሳ መረጃ ከሆነ ችግሩን ለመፍታት የተሻለው ሀሳብ የሄሊኮፍተሯን ሶፍትዌር ማሻሻል ነው፡፡ በናሳ ውስጥ የጄት ምርምር ቤተሙከራ የኢግኒውቲን ተልእኮ እየመራ ሲሆን የተሸሻለውን ሶፍትዌር በመሞከር ላይ ሲሆን ትክክለኛነቱ ሲረጋገጥ ወደ ማርስ ለመላክ እንደታሰበ ተነግሯል፡፡ ይህንንም ለማድረግ ጥቂት ጊዜ ያስፈልጋል ተብሏል፡፡
አሁን ላይ ሄሊኮፍተሯ ከሀይል፣ ከግንኙነትና ከሙቀት አንጻር በታሰበው ልክ ያለች ሲሆን ሄሊኮፍተሯን ተሸክሞ ወደ መልክዓ ማርስ የወሰዳት ሮቭረም ያለምንም ችግር እየሰራ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ እንደተመራማሪዎቹ ሀሳብ ከሆነ የኢግኒዩቲ በረራ ዋና ተልዕኮው የምርምር ስራ ሳይሆን የቴክኖሎጂ ሙከራ ነው፡፡
ምንጭ ፡ Independent
የውድድር ጥሪ ማስታወቂያ
=============
ኢኖቬሽን ለልማት (Innovation for Development) በሚል ፕሮግራም ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከሌሎች የልማት አጋር ተቋማት እና ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ወደ ስራ መገባቱ ይታወቃል፡፡
በዚህ ፕሮጅክት ከሚከናወኑ ተግባራት አንዱ በኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያሉ ስታርታፖችንና ጥቃቅንና አነስተነኛ ተቋማትን (CT and ICT related startups and SMEs) በማወዳደር እና በመመምረጥ የማልማት ስራ ሲሆን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ከስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን፣ ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም እና ከኮሪያ ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ ጋር በመሆን የተዘጋጀ ፕሮግራም ነው፡፡
አመልካቾቸ ማሟላት ያለባቸው መስፈርቶች
• ኢትዮጲያዊ ዜግነት ያለው/ያላት
• በኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ እና ተዛማጅ ዘርፎች ላይ ሀሳብ ያለው/ያላት
• ኢኖቫቲቭ የቢዝነስ ሀሳብ ያለው/ያላት
• በተጠየቀው የፕሮፐዛል ይዘት መሰረት ሃሳቡን ማቅረብ የሚችል/የምትችል
ይህ ማስታወቂያ ከተገለጸበት ቀን ጀምሮ ለአንድ ወር በ www.mint.gov.et መመዝገብና ማመልከት ትችላላችሁ።
ለበለጠ መረጃ ፡ +251 -967 -944 -500 ይደውሉ
ሴት አመልካቾች ይበረታታሉ!!!
ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር
በዓይን አምሳል የተሰራው አነጋጋሪ ካሜራ
====================
ከጀርመኑ ሳርላንድ ዩኒቨርሲቲ የተውጣጡ ኮምፒውተር ሳይንቲስቶች ለየት ያለ ንድፍን በመከተል እኛን የሚከታተሉ መሳርያዎችን የምንመለከትበትን መንገድ የሚያጠይቅ ካሜራን በአይን አምሳል ሰርተዋል፡፡ አዲሱ ካሜራ የሰው ልጅን አይን መስሎ ንድፍ የተደረገ ብቻም ሳይሆን በእንቅስቃሴም እንዲመስለው ሆኖ የተሰራ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ካሜራው አይኑን ያርገበግባል ቅንድቡንም ያንቀሳቅሳል፡፡
ማርክ ቴዠር እንደሚለው የዚህ ካሜራ ዋና አላማ ከእስከዛሬዎቹ የተሻለ ንድፍን ማስተዋወቅ ሳይሆን በዕለት ተዕለት ውሎዋችን ውስጥ በእኛ ላይ ክትትል በሚያደርጉት መሳርያዎች ስለመከበባችን ሰዎች አትኩሮት እንዲሰጡና ውይይትን መቀስቀስ ነው፡፡ ሌላኛው የኮምፒውተር ሳይንቲስት ማሪዮን ኮኤሌ በበኩሉ በዓይን አምሳል የተሰራው ካሜራን (Eyecam) በመጠቀም የመሳርያዎች ንድፍ ተግባራቸውን መምሰል ይኖርበት እንደሆን እየመረመርን ነው ብሏል፡፡ አክሎም ካሜራው የተለያዩ አይነት የዕይታ መንገዶችን በመጠቀሙና ድምፅ አልባ መልዕክቶችን በመላኩ ከዚህ ቀደም ቴክኒካል በሆኑ መሳርያዎች ላይ ያልነበረ አዲስ የግንኙነት መንገድን እንደሚፈጥር ይናገራል፡፡
የካሜራ ስራው በአውሮፓ ህብረት ድጋፍ አማካኝነት የሚከናወነው በሰው ልጆችና ኮምፒውተሮች መካከል ያለውን መስተጋብር ለማሻሻል ያለመ ፕሮጀክት አካል መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ በዚህኛው ፈጠራቸው አማካኝነትም የካሜራቸውን ልዩ የቴክኖሎጂ ትሩፋቶች ተጠቅመው ያልተቋረጠ ምልከታ ገፅታዎችን የሚዳስሱ ይሆናል፡፡ በሌላ መልኩ ይህ በሰው አምሳል የተሰራ ካሜራ ተጠቃሚው ኮምፒውተር ላይ ሲያመሽ የድካም ገፅታን እየተላበሰ የመስታውትነት አልያም እንደማንኛውም የቤት ውስጥ እንስሳ ባለቤቱ ወደ ቤቱ ሲመጣ በደስታ ስሜት እየተመለከተ የመቀበል ሚናን ሊወጣ ይችላል፡፡
ምንጭ፤ Tech Xplore (https://techxplore.com/.../2021-04-webcam-human-eye...)
የኢኖቬሽን አምባሳደር ፕሮግራም ተጀመረ
========================
ማህበረሰባዊ የኢኖቬሽን ባህልን ለማስፋፋት ታስቦ በቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት የተሰናዳው የኢኖቬሽን አምባሳደር ፕሮግራም ዛሬ ተጀመረ፡፡ ዛሬ ጠዋት በተከናወነው ፕሮግራሙን በይፋ የማስጀመርያ ዝግጅትም ከተለያዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተውጣጥተው በኢኖቬሽን አምባሳደርነት የተሰየሙ ተማሪዎችን፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪዎችን ተሳታፊ አድርጓል፡፡
የዝግጅቱን መክፈቻ ንግግሩን ያሰሙት የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢ/ር ተሾመ ሳህለማርያም የተማሪዎቹ በኢኖቬሽን አምባሳደርነት መሰየም የሀገራችንን ምጣኔ ሀብታዊ ሁናቴ ከፍ ያደርግ ዘንድ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ መንግስት ለቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ነው ያሉት ኢ/ር ተሾመ ኢንስቲትዩቱም የተቋማትን አሰራር በማሻሻል ለሀገር ምጣኔ ሀብት መሻሻል አስተዋፅዖ የሚያደርጉ ግልጋሎቶችን እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በዕለቱ በክብር እንግድነት ተገኝተው ለተማሪዎቹ ዕውቀታቸውን ያካፈሉት ዝነኛው የአንድሮሜዳ ቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ እና ፊዮሎጂስት መጋቢ ሀዲስ ዶ/ር ሮዳስ ታደሰ “ግኝትን እንዴት እናግኝ” በሚል ርዕስ የአዕምሮን ኃይል ተጠቅሞ ግኝትን ዕውን ስለማድረግ የሚያውጠነጥን ንግግርን አቅርበዋል፡፡ በንግግራቸው ላይ ዶ/ር ሮዳስ ተማሪዎቹ ለስኬታማ ኢኖቬተርነት ለመብቃት ንቁ ሆነው ዙርያቸውን እንዲመለከቱ፣ አዕምሮዋቸውን በምልዓት እንዲጠቀሙ፣ ሁሌም የራስ የሆነን ነገር ለማምጣት እንዲሞክሩ እና ተፈጥሮን እንዲመለከቱ መክረዋል፡፡ አክለውም ሌላኛው የግኝቶች ዋና መነሻ ነው ያሉት ህልምን አስመልክቶ ተማሪዎቹ በህልም የሚያዩትን ነገር ወደ ምርምር እንዲለውጡት አሳስበዋል፡፡
ሌላው በመድረኩ ከልምዱ ለማካፈል የተገኘው ወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ ኢዘዲን ካሚል በበኩሉ እስካሁን በታዳሽ ኃይል፣ ደህንነት፣ ጤና እና የመሳርያዎች በይነ መረባዊ ግንኙነት (IOT) ላይ ያተኮሩ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎቹን በጥቂቱ አስቃኝቷል፡፡ ወደ 18 ፈጠራዎችን ያበረከተውና ከነዚህም ውስጥ 13 ያህሉን በፓተንት ለማስመዝገብ የበቃው ኢዘዲን በኢኖቬሽን ዓለም ጉዞው ውስጥ ስላጋጠሙት ተግዳሮቶች፣ እነርሱን ስላለፈበት መንገድ እና ስላገኛቸው ዕድሎች ልምዱን ያካፈለ ሲሆን ይህ የኢኖቬሽን ጉዞውን አስመልክቶ ከተሳታፊዎችም ጥያቄ ጥያቄዎች ቀርቦለትም ምላሽ ሰጥቶባቸዋል፡፡
በመድረኩ የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩትን ምስረታ፣ ርዕይ፣ ተልዕኮ እና ኃላፊነቶቹን አስመልክቶ የኢንስቲትዩቱ ስልጠና እና ድጋፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሯ ወ/ት ቤተልሄም መርጊያ ማብራርያ ሰጥታበታለች፡፡ የአምባሳደር ፕሮግራሙን በማስመልከትም ስለተዘጋጀው የስልጠና እና ሰመር ካምፕ ቆይታ ከዚያ በኋላም ተማሪዎቹ ስለሚሰሯቸው ፕሮጀክቶች እና በአጠቃላይ ፕሮግራሙ ይኖረዋል ተብለው ስለሚጠበቁት ውጤቶች ላይ የዳይሬክቶሬቱ ባልደረባ ወ/ሮ ለምለም ሙላት ገለፃ አቅርባበታለች፡፡
የ HTTP እና የ HTTPS ምንነት
******************
ለተለያዩ ተግባራትና መረጃ ፍለጋ ኢንተርኔት ስንጠቀም በስልካችን ወይም በኮምፒውተራችን የአድራሻ መፈለጊያ ሳጥን ላይ የምንፈልገውን መረጃ በትክክል እንድናገኝ ከሚረዱን የማስፈንጠሪያ መነሻዎች ውስጥ HTTP እና HTTPS የተለመዱ ናቸው፡፡ ለመሆኑ እነዚህ ሁለቱ መነሻዎች ምንድን ናቸው?
HTTP ይህ Hypertext Transfer Protocol ለሚለው ምጻረ ቃል ሲሆን በሰርቨርና በደንበኛው መካከል ለሚደረግ ጥያቄና መልስ የተግባቦት ኮድ ነው፡፡ ደንበኛ የሚባለው አንድ ሰው ኢንተርኔትን በመጠቀም የተለያዩ መረጃዎችን የሚፈልግበት ስልክ ወይም ኮምፒውተር ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ምህጻረ ቃል በስልካችን ወይም በኮምፒውተራችን የመፈለጊያ ሳጥን ውስጥ የጻፍነው ጥያቄ መልስ የሚገኝበት አድራሻ ነው፡፡ የመጨረሻውን ትዕዛዝ ስንሰጥ ሰርቨሩ ምን ማድረግ እንዳለበት እንዲረዳ ያደርገዋል፡፡ ይህ ያስቀመጥነው ጥያቄ ወይም ፍለጋ በየትኛውም አድራሻ በማይኖር ጊዜ “404 Not Found” የሚል መልዕክት ይደርሰናል፡፡ HTTP የሚለው የመፈለጊያ መነሻ የተሰራው WWW የሚለውን የመፈለጊያ መነሻ ጽንሰ ሀሳብ በሰራው ቲም በርነርስ ሊ በተባለው ሰውና በጓደኞቹ ነው፡፡
ይህ የመረጃ መገኛ አድራሻ መፈለጊያ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው በ1991 ሲሆን በዚህ መነሻነት ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው መረጃም HTTP/0.9, በሚል የታተመ ነው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜም የተለያዩ ለውጦች ተደርገውበታል፡፡
ሌላኛው HTTPS የሚባለው ደግሞ በ1993 አካባቢ በኔትስኬፕ ኮሚኒኬሽን የተጀመረው ሲሆን ‘S’ የሚለው ጭማሪ ‘secure’ ን የሚተካ ነው፡፡ ይህም HTTPS ን የሚጠቀም ድረ-ገጽ ከስልካችን ወይም ከኮምፒውተራችን ጋር ሚስጢራዊ ትስስር በመፍጠር የምንልከውን መረጃ ምስጢራዊነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ በሚስጢር ቁልፍ የታሰረው መረጃም ማንም በቀላሉ እንዳይረዳው ‘xkndsoumnkjbktkctfc’ በዚህ መልክ የሚቀርብ ነው፡፡
የHTTPS ፕሮቶኮልን የሚጠቀሙ ድረ-ገጾች SSL የሚባል ፈቃድ እንዲኖራቸው ያስፈልጋል፡፡ ይህም የመረጃ ምንጩን ታማኝነት ለማወቅ ያስችላል፡፡ በ HTTP እና HTTPS መካከል ያለው ልዩነት በጣም ጥቂት ሲሆን ሁለተኛው የተሸሻለ የደህንነት ማረጋገጫ ያለው ነው፡፡ እንዲሁም ደግሞ የመጀመሪያው የፖርት ቁጥሩ 80 ሲሆን የሁለተኛው 443 ነው፡፡
ምንጭ፡ fossbytes