TechIn2
1.16K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
ከዶሮ እንቁላል እየተሰራ ያለው አዲሱ የኮቪድ 19 ክትባት
*******************************
ተመራማሪዎች አዲስ እና በቀላል ዋጋ ሊመረት የሚችል የኮቪድ ክትባትን የዶሮ እንቁላልን በመጠቀም እየሰሩ እንደሆነ ተነገረ፡፡ ክትባቱ ከደህንነትና ከውጤታማነት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ማለፍ ከቻለ ተመራማሪዎቹ በዓመት ውስጥ ከአንድ ቢሊዮን ብልቃጦች በላይ ለማምረት ማቀዳቸውን አሳውቀዋል፡፡ ይህ በብራዚል፣ ሜክሲኮ፣ ታይላንድና ቬትናም ለክሊኒካዊ ሙከራ የቀረበው ክትባት አለም ወረርሽኙን ለመከላከል እየሔደ ያለበትን መንገድ እንደሚቀይረው ታምኖበታል፡፡
NDV-HXP-S የተሰኘው የክትባት ዓይነት አሁን ጥቅም ላይ እየዋሉ ካሉት የክትባት አይነቶች የተለየ ሞሎኪዩላዊ መዋቅር ያለው ሲሆን የሰውነት የበሽታ መከላከል ብቃትን በሰፊው እንደሚያሳድግ ተነግሮለታል፡፡ ከአዲሱ ክትባት ጋር አብሮ ተያይዞ እየተነሳ ያለው ሌላው ጉዳይ ክትባቱን ለመስራት የሚያፈልጉ ግብዓቶችን የተመለከተ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር እንደ ፋይዘር ያሉ ክትባት አምራች ድጅቶች ለክትባቱ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን የማግኘት ችግር ሊገጥማቸው ይችላል ተብሎ የተሰጋ ሲሆን NDV-HXP-S ግን የዚህ ዓይነት ችግር እንደማይገጥመው ታምኗል፡፡ ለዚህ ክትባት የሚውለው ግብዓት ለኢንፍሎዊንዛ ቫይረስ ክትባት መስሪያነት የሚያገለግለው የዶሮ እንቁላል ነው፡፡
የግሎባል ሔልዝ ኢኖቬሽን ሴንተር ረዳት ዳይሬክተር የሆኑት አንድሪያ ቴይለር እንደሚሉት ከሆነ የመጀመሪያው ክሊኒካዊ ሙከራ የፊታችን ሐምሌ የሚጠናቀቅ ሲሆን ቀጣዩ ሙከራም ተጨማሪ ወራቶችን ይጠይቃል፡፡ በእንስሳት ላይ በተደረገው ሙከራ እጅግ ተስፋ ሰጭ የሆኑ ውጤቶች የተመዘገቡ ሲሆን ሙከራዎች ሲጠናቀቁ ለአለማችን ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ላቸው ሀገራት ትልቅ መፍትሔ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡
ምንጭ Firstpost
ጎግልና የተጠቃሚዎች የግል መረጃ
*******************
የአለማችን ግዙፉና ሀብታሙ ድርጅት ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን እንዲችል ያደረገውን ሀብት የሚሰበስበው ተጠቃሚዎች በብዛት የሚጎበኟቸውን ገጾች መሰረት አድርገው ከሚሰሩ ማስታወቂያዎች ነው፡፡ ይንንም ለማድረግ ጎግል ከፍኛ መጠን ያለው መረጃ ያስፈልገዋል፡፡ በስልኮቻችንና በሌሎች የጎግልን መተግበሪያ በሚጠቀሙ ነገሮች የምንሰራቸው እያንዳንዱ ስራዎችና የምንነካቸው ማስፈንጠሪያዎች ለጎግል መረጃዎችን በመስጠት ድርጅቱን አበልጽገውታል፡፡
ባሳለፍነው ታህሳስ ወር አፕል የተሰኘው የመተግበሪያ መደብር (App Store) እያንዳንዱ መተግበሪያ የሚሰበስባቸውን መረጃዎችና እነዚህ መረጃዎች ከእያንዳንዱ ተጠቃሚዎች ጋር ያላቸውን ግኙነት በመደብሩ ውስጥ ምልክት የሚሰጥ ማሳወቂያን ይፋ አድጎ ነበር፡፡ ይህም ከከፈትናቸው ማናቸውም መተግበሪያዎችና ማስፈንጠሪያዎች እስከ መገኛ ቦታችን ድረስ ያለውን የሚያጠቃልል ነው፡፡ በዚህ የአፕል እንቅስቃሴ ብዙም ያልተገረመ የሚመስለው ጎግል ተመሳሳይ እርምጃን ለመውሰድ ከኤሊ ተንቀራፍፏል፡፡
የጎግልን መተግበሪያ ከሚጠቀሙ ከ1 ቢሊዮን ከሚጠጉ ሰዎች በተጨማሪ ከስልሳ በላይ መተግበሪያዎችና ዘጠኝ የደረሱ የጎግል ምርቶችን የሚጠቀሙ ሌሎች 1 ቢሊዮን ሰዎች እንዳሉ ይታመናል፡፡ ሁለት ቢሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን መረጃ በመጠቀም ምን ያክል ሀብት ሊሰራ እንደሚችል ጎግል የደረሰበትን ደረጃ ብቻ በመመልከት መገመት ቀላል ነው፡፡ በጎግል ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ካላቸው የድርጅቱ መተግበሪያዎች ውስጥ ጂ-ሜል፣ ክሮምና መረጃ ማፈላለጊያው ጎግል ሰርች ዋነኞቹ ናቸው፡፡
እነዚህ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴዎቻችን የሚሰበሰቡ መረጃዎች የተጠቃሚዎች የግል መረጃዎች በመሆናቸው በአንዳንዶቹ ላይ እንደ ደንበኛ ተጠቃሚው ብቻ የሚያውቃቸው መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ለመሆኑ አንድ ተጠቃሚ ይህን መወሰን ይችል ይሆን? የክሮም ሴቲንግ አንድ ተጠቃሚ ከእሱ ወይም ከእሷ የሚሰበሰበውን መረጃ የመወሰን እድል ይሰጣል፡፡ በሌላ በኩልም በክሮም ሴቲንግ sync የሚለውን በማጥፋት (turn off) የተጠቀምናቸው ማስፈንጠሪያዎች ከስልካችን ወይም ከኮምፒውተራችን እንዳያልፍ ማድረግ እንችላለን፡፡ በጣም ትልቅ የሚባለው እንደ ተጠቃሚ ማድረግ የምንችለው የድርጊት መቆጣጠሪያውን (Activity Controls) በማስተካከል ነው፡፡ ምንጭ wired
የኮስሚክ ጨረሮች (Cosmic rays) ምንድን ናቸው
==========================
የኮስሚክ ጨረሮች ከስርአተ-ፀሀያችን ውጭ በሚገኘው በይነኮከባዊ ህዋ (Interstellar space) ውስጥ የሚገኙ እና ከፍተኛ ሀይል ያለው ፑሮቶን እና አተማዊ ኑክለስ (Atomic nucleus) የያዙ ጨረራዎች ናቸው። ተመራመሪዎች እንደሚገለፁት ክዋክብት በውስጠኛ አካላቸው የያዙት ሀይድሮጅን ሙሉ ለሙሉ ወደ ሂልየም ንጥረነገር ሲቀየር ኖቫ/ሱፐርኖቫ በተሰኘ ግዙፍ ፍንዳታ ውጨኛ አካላቸውን እንደሚበትኑ ይነገራል። በዚህ ፍንዳታ ወቅት ከፍተኛ መጠን ያለው የኮስሚክ ጨረሮች ከአዋራ (ኔቡላ) ጋር ወደ ህዋ የሚበተኑ ሲሆን ይህም አንዱ የኮስሚክ ጨረሮች ምንጭ ነው።
ሌላው እንደምንጭነት የሚጠቀሱት አክቲቭ ረጨታዊ ኑዩክለስ (Active Galactic Neucleus) የሚባሉት ናቸው። የጠፈር ተመረማሪዎች እንደሚያስረዱት ሱፐር-ማሲቭ ብላክ ሆል የተባለው የህዋ አካል ከፍተኛ የሆነ የጨረራ ቡልቅታ (Jets of radiation) እንደሚያመነጩ ይናገራል። ይህ ቡልቅታ ኮስማዊ ጨረሮች በውስጡ እንደያዘ ይታመናል። ከባህር ወለል በላይ ከ1000 ኪ.ሜ አንስቶ እስከ 60,000ኪ.ሜ ድረስ የሚካልለውን የቫን አለን የራዲዬሽን ቀበቶ (Van Allen radiation belt) በነዚህ ፓርቲክሎች የተዋቀረ ሲሆን እነዚህም በምድራችን መግነጢሳዊ መስክ (Magnetic field) ተስበው ምድራችንን ከበው የሚገኘ ናቸው። ይህን በምሳሌ ብንመለከተው
የብረት ፍቅፋቂዎችን ደብተር ላይ ብንበትን እና ከደብተሩ ስር ጠንካራ ማግኔት ብናኖር የብረት ፍቅፋቂዎቹ ማግኔቱ ወዳለበት ቦታ ይሰበሰባሉ። ነገር ግን የደብተሩ ወለል ስላል ከማግኔቱ ጋር እንዳይጣበቁ ያግዳቸዋል። ልክ እንደዚህ ሁላ ምድራችንም እንደ ግዙፍ ማግኔት ስትሆን ፓርቲክሎቹም በዚህ ማግኔት ተስበው ምድራችንን ከበው ተቀምጠዋል። ወደ ውስጥ እንዳይገቡ የምድር ከባቢ አየራዊ ርብራቦች ያግዷቸዋል። እነዚህን ቅንጣቶች ከምድር ጋር አጠቃሎ የያዘውን ክልል የምድር ከባቢ መግነጢስ (Magnetosphere) ብለን እንጠራዋለን። የቫን አለን የራዲዬሽን ቀበቶ ከምድራችን ውጪ ሌሎች ፕላኔቶች ላይም ሊገኝ የሚችል ሲሆን ከዚህ ክልል እየራቅን በሄድን ቁጥር ፕላኔቶች እና ሳተላይቶቻቸውን፤ አስትሮይዶችን እና ኮሜቶችን እያገኘን እንሄዳለን።
ምንጭ፡ Spacecentre
ተፈጥሯዊ ማዳበሪያ ለምግብ ደህንነት
**********************
የእርሻ ስራ የአለማችንን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ አማራጭ የሌለው መንገድ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ምንም እንኳን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ቢመጣም የእርሻ ስራ እንደ እኛ ባሉ ሀገራት ከፍተኛ ጉልበት የሚጨርስ ነው፡፡ ይህን የአርሶ አደሩን ህይወት እያዳከመ ያለውን የእርሻ ስራ በቴክኖሎጂ ማገዝ ቢቻል ድካምን ከመቀነስ ባሻገር የምግብ ዋስትናችንን ለማረጋገጥ የምናደርገውን ጥረትም እንደሚያፋጥነው ይታመናል፡፡ በአሁን ጊዜ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት ከእርሻ ጋር ያለው ችግር የምርታማነት ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም ውጤቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስተዋለ የመጣው ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ አጠቃቀም በሰዎች፣ በእንስሳትና ባጠቃላይ በስነ-ምህዳሩ ውስጥ ሊታሰብበት የሚገባ ነው፡፡
ተፈጥሮን ብቻ ማዕከል ያደረገ የእርሻ ስራ (organic farming) አርቲፍሻል የሆኑ የምርት ማሳደጊያ መንገዶችን የማይጠቀም የእርሻ አይነት ነው፡፡ ኦርጋኒክ የሚለው ቃል የተለያዩ መገለጫዎች ያሉት ሲሆን አንድ ለምግብነት የሚውል የግብርና ምርት ያለውን ይዘት የሚመለከት ነው፡፡ በUSDA የመረጃ ቋት ላይ እንደተቀመጠው መረጃ ከሆነ አንድ የምግብ ምርት ከ70 በመቶ ጀምሮ እስከ 100 በመቶ የሚለካ ተፈጥሯዊ ይዘት ካለው ኦርጋኒክ ሊባ ይችላል፡፡ የአንድ የግብርና ምርት የመቶኛ የይዘት መጠኑ እያነሰ በሔደ ቁጥር የተጠቃሚዎችን የጤና ሁኔታ በጥያቄ ውስጥ እያስቀመጠው ይሔዳል፡፡
የግብርና ምርቶችን ተፈጥሯዊ ይዘት ከሚቀንሱ መንስኤዎች መካከል በዋናነት የሚነሳው የኬሚካል ይዘት ያላቸው ማራበሪያዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ዓይነት ማዳበሪያዎች በቀጥታ የግብርና ምርቶች ላይ ከሚያስከትሉት የይዘት ለውጥ በተጨማሪ በእንስሳት፣ በእጽዋትና በአጠቃላይ በተፈጥሮ ላይ በሒደት የሚስተዋል ጉዳት ያመጣሉ፡፡ ለዚህም በግልጽ ከታዩት ውስጥ ከእንቦጭ አረም ጋር ተያይዞ በሀይቆቻችን ላይ የተጋረጠውን አደጋ ማንሳት ይቻላል፡፡ ከሰዎች ጤና ጋር በተያያዘ የሚመጣው ጉዳት በሒደት የሚስተዋል ቢሆንም ጉዳቱ ግን የማይቀር ነው፡፡
ይህን ከተፈጥሮ ጋር የተጣላ የአስተራረስ ወይም ምርትን የማሳደግ ዘዴ መጠቀሙ ሙሉ ለሙሉ ልምድ ከማድረጋችን ብዛት የተነሳ አንዳንድ አካባቢዎች ያለ ማዳበሪያ ምንም አይነት እንቅስቃሴ አይደረግም፡፡ የዚህ ጉዳቱ ከብዙ አቅጣጫ የሚመጣ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ተፈጥሯዊ ማዳበሪያ የመጠቀም ልምድን በማሳደግ የምግብ ደህንነትን ማስተካከልና እንስሳትንና እጽዋትን አስፈላጊ ካልሆኑ ኬሚካሎች መታደግ እንደሚቻል ከPHYS.ORG ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በአንድ ለ27 ዓመታት በተሰራ ጥናት ላይ እንደተመለከተው ተፈጥሯዊ በሆነና ሀገር በቀል በሆኑ እውቀቶች በታገዘ መንገድ የሚሰራ የእርሻ ስራና ከእንስሳት ጽዳጅ በሚገኝ ማዳበሪያ ወይም ኮምፖስት ለፓቶጅኖች ህልውና የማይመች በመሆኑና በተቃራኒው ፓቶጅኖችን የሚመገቡ ባክቴሪያዎችን የሚያፈራ በመሆኑ በጣም ጠቃሚ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ይህ በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የተሰራው ጥናት እንደሚያመለክተው በብዙዎች ዘንድ እየተተወ የመጣው የኮምፖስት ማዳበሪያ የተወሰኑ መሻሻያዎች ታክለውበት እንደገና ጥቅም ላይ ሊውል ይገባዋል፡፡ ይህም ተፈጥሯዊ በሆነ መልኩ የአፈርን ደህንነት የሚያስጠብቅ ከመሆኑ ባሻገር የምግብ ደህንነትንም በእጅጉ ያሻሽለዋል ሲል የጥናቱ ውጤት አመላክቷል፡፡
ምንጭ PHYS.ORG
ኢሜዲሰን ቴክኖሎጂ ለህክምና አገልግሎት ተደራሽነትን
======================
በአሁኑ ጊዜ የኢሜዲሰን ወይም ኢኸልዝ ተግባራዊነት በዓለም የህክምና አገልግሎት ተደራሽነትን በማረጋገጥ በኩል ከፍተኛ የሆነ ተፅዕኖ በማሳደር ላይ ይገኛል። ኢሜዲሲን በኢንፎርሜሽን ኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ አማካኝነት የሰውን ገፅታ በማሽን በመተካት (human-machine interface) ለአካባቢው ማህበረሰብ ፈጣንና ወጪን ያማከለ የህክምና አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ ነው። በከፍተኛ ሁኔታ በማደግ ላይ ካለው ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መስፋፋት ጋር ተያይዞ፣ ኢሜዲሰን ከአጭር ጊዜ ወዲህ በዓለም ዙሪያ በሜዲካል መስክ በዲያግኖሲስ፣ በኢፋርማሲዩቲክስ፣ በቴሌኸልዝ፣ ቴሌሜዲሰንና በተመሳሳይ ዘርፎች ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል።
ቴሌሜዲሰን ከኢሜዲሰን ክፍሎች መካከል አንዱ ሲሆን በኤሌክትሮኒክ ኮምኒኬሸን መሳሪያዎች አማካኝነት መሠረታዊ የሆኑ የሜዲካል መረጃዎችንና ስራዎችን ከተለያዩ ስፍራዎች ወደ ሌላው ቦታ በማሰተላለፍ በአጭር ጊዜ፣ በአስፈላጊ ቦታ እና በቀላል ወጪ መፍትሄ እንዲያገኙ፣ እንዲሁም የጤና ትምህርቶችን በርቀት ለትውልድ ማሸጋገርና በሽተኛን ከችግሩ ለመታደግ ነው። ዋና ዓላማው በርቀት አካባቢ ለሚገኝ ወይም አስፈላጊውን የጤና መሰረተ ልማት ማግኘት ላቃተው ማህበረሰብ ኤሌክትሮኒካል መሳሪያዎችን በመጠቀም የጤና መሰረተ ልማቱንና የአሰጣጥ ሂደቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ ተደራሽ ማድረግና ማሻሻል ነው። ከዚው ጋር ተያይዞ ቴሌኸልዝ የሚጠቀስ ሲሆን በገጠር አካባቢ ለሚኖርና የጤና አገልግሎትን በአፋጣኝ ማግኘት ለማይችል ማህበረሰብ የጤና ጥበቃ ባለሙያዎች በአካባቢው ባይኖሩም እንኳን በኤሌክትሮኒካል መሳሪያዎች የጤና አግልግሎትን በርቀት መስጠት የሚያስችል ነው።
በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ኢኸልዝ በፍጥነት በማደግ ላይ ከሚገኙት ቴክኖሎጂዎች መካከል አንዱ እንደሆነ ይጠቀሳል። ኢኸልዝ ወጪን ያማከለና ምስጢራዊነት በመጠበቅ የአይ.ሲ.ቲ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ጤናንና የጤና አገልግሎት ዘርፎችን፣ የጤና መረጃዎችን፣ እንዲሁም በጤና ዘርፍ የሚሠሩ ምርምሮችን እና ውጤታቸውን ለቀጣይ ትውልድ በቀላል መንገድ፣ በቀላል ወጪ እና በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲተላለፍ በማድረግ ለጤና ሴክተር ከፍተኛ አስተዋፅዖ በማበርከት ላይ የሚገኝ የክፍለ ዘመኑ ተፅዕኖ አሳዳሪ ከሚባሉት ቴክኖሎጂ ውስጥ አንዱ ነው ።
በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ዘመናዊ ቴሌሜዲሰን መጠቀም የተጀመረው እ.ኤ.አ በ1984፣ በሳተላይት ሊንክ በርቀት ለሚገኝ በሽተኛ የጀኔቲክ ችግሮችን ምልክት ለመለየትና ዕርዳታ ለማድረግ ዝቅተኛ የስካኒንግ አቅም ባለው ቴሌቪዥን ትራንስሚሽን አማካኝነት ነው። እ.ኤ.አ በ1993 የአሜሪካ መከላከያ ሠራዊት በሳተላይት አማካኝነት በቪዲዮና በቪዡዋል መንገድ ቴሌሜዲሰን አግልግሎትን በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ ማድረግ የተቻለ ሲሆን ከዚህ ጊዜም አንስቶ ዘርፉ በመጠኑም ቢሆን እየተነቃቃ ይገኛል፡፡ በተለይም ከዘመኑ የሞባይል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ለኢሜዲሰን ቴክኖሎጂ ተግባራዊነትና መስፋፋት የኢመንግስት ዝግጁነት፣ የብዙ ሴክተሮች መካተት፣ አስቻይ ፖሊሲዎች እና የአቅም ግንባታ ፕሮግራሞች አወንታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ሁኔታዎች ናቸው።
ምንጭ Frontierinternet እና tech science
የወንዝ ዳር መዝናኛዎች መጨናነቅን የሚቆጣጠረው መተግበሪያ
***************************
እንግሊዝ ባሳለፍነው ዓመት ለኮቪድ 19 ስርጭት ዋነኛ ምክንያት የሆነውን የአካላዊ ቅርርብን ለመቆጣጠር በሚል የተሰራን አንድ መተግበሪያ በሀገር አቀፍ ደረጃ የወንዝ ዳር መዝናኛዎችን መጨናነቅ ለመቆጣጠር እንዲውል እያደረገች እንደሆነ ተሰማ፡፡ በአንድ BCP በተባለ ድርጅት የተሰራው ይህ መተግበሪያ ባሳለፍነው የፈረንጆች አመት ሰዎች በብዛት ወደ ወንዝ ዳር መዝናኛዎች መጉረፍ መጀመራቸውን ተከትሎ የተሰራ ሲሆን አሁን ላይ አካላዊ ርቀትን ለመጠበቅ ባለው አስተዋጽኦ ምክንያት በሁሉም የእንግሊዝ ከተሞች ጥቅም ላይ እንዲውል በመመሪያ የተደገፈ የበጀት ድጋፍ ተደርጎለታል፡፡
መተግበሪያውን የሰራው ድርጅት 55 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ የተደረገለት ሲሆን ድጋፉም መተግበሪያውን ለማሻሻልና ወደ ስራ ለማስገባት ያለመ ነው፡፡ መተግበሪያው ከሰዎች በተጨማሪ ሌሎች እንደ መኪና ማቆሚያና መንገዶች ያሉ መጨናነቆችን መቆጣጠር የሚያስችል እንደሆነ ተነግሮለታል፡፡ መተግበሪያው በአንድ የሐይቅ ዳር መዝናኛ ያለውን የሰዎች እንቅስቃሴ እና ብዛት ለተጠቃሚዎች የሚያሳውቅ ሲሆን ለተቋማትም ልዩ ልዩ የአስተዳደርና የመስተንግዶ ስራዎችን በቀላሉ እንዲሰሩ ያስችላቸዋል፡፡
መተግበሪያው እንደ አካባቢው ሁኔታ ለተጠቃሚዎች ሶስት አይነት ቀለማትን የሚያመላክት ሲሆን በጣም የተጨነናነቀ ቦታ ሲሆን ቀይ በተቃራኒው ለእንቅስቃሴ ምቹ ሲሆን ደግሞ አረንጓዴ ምልክቶችን ያሳያል፡፡ መተግበሪያው በአሁኑ ሰዓት በሙሉ የእንግሊዝ ግዛቶች በነጻ የቀረበ ሲሆን ለቀጣይ አንድ አመታት አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል አበልጻጊው ድርጅት ከእንግሊዝ መንግስት 110 ሺህ ይሮ ለመጠየቅ እንዳሰበም ይፋ አድርጓል፡፡
ምንጭ cities-today
በቻይና የቴክኖሎጂ ኩባንያ የተሰሩት ሮቦት ውሾች
******************************
በጣም ፈጣን የሆነና ትእዛዝ አክባሪ የሮቦት ውሻ በቻይና መሰራቱ ተሰምቷል፡፡ ይህ አልፋ ዶግ የተሰኘው ሮቦት ውሻ የቻይናን በቤት እንስሳትና በቴክኖሎጂ ላይ ያላትን ፍላጎት የሚያንጸባርቅ ነው ተብሎለታል፡፡ ውሻው ከፍተኛ ቴክኖሎጂን የሚጠቀም በሰው ሰራሽ አስተውሎት የታገዘ አካባቢውን ማየትና መስማት የሚያችል ብቃት ያለው ሲሆን ውደ ውጭ ይዘውት ወጥተው አብረውት ሊንቀሳቀሱ የሚችሉት ነው፡፡
ሮቦቱን ያመረተው ድርጅት ዌይላን የቴክኖሎጂ ሙያተኛ የሆኑት ማ ጄይ ሮቦቶ ከተፈጥሯዊው ውሻ ጋር ብዙ የሚያመሳስለው ነገር እንዳለ ተናግረዋል፡፡ የፈጠራ ባለቤቶቹ የሰሩት ሮቦት በሰዓት 15 ኪሎሜትሮች ያክል መጓዝ የሚችል እንደሆነና በዘርፉ ገበያ ላይ ካሉት በጣም ፈጣኑ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ከብረት የተሰሩት አራቱ እግሮቹ ከተፈጥሯዊው ውሻ የተሸለ የተረጋጋ አካሄድ እንዲኖረው አድርጎታል ብለው እንደሚያስቡ የመረጃ ምንጫችን አስነብቧል፡፡
ሮቦቱ በራሱ መንቀሳቀስ እንዲችል ፈጣን የሆነ የአምስተኛ ትውልድ ኔትወርክን የፈጠራ ባለቤቶቹ የተጠቀሙ ሲሆን የ5G ቴክኖሎጂን መጠቀማቸው ችግር በሚገጥመው ጊዜ አፋጣኝ መልስ መስጠት እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል፡፡ በመጀመሪያው የሽያጭ ወር 1800 ሮቦቶች የተሸጡ ሲሆን ዋጋቸውም 2400 የአሜሪካን ዶላር ወይም 16 ሺህ የቻይና ገንዘብ ነው፡፡ እንደ ሽያጭ ድርጅቱ መረጃ ከሆነ አብዛኛው ትእዛዝ የሚመጣው ከኮምፒውተር አበልጻጊዎች፣ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ከሚሰሩና ምርቱን ይወዱታል ተብለው ከተጠበቁት ከህጻናት ነው፡፡
ምንጭ Tech xplore
የጂ.አይ.ኤስ ቴክኖሎጂ ዋና ዋና ክፍሎች
=====================
ጂ.አይ.ኤስ ወይም ጂዮግራፊካል ኢንፎርሜሽን ሲስተም የኮምፒዉተር አፕሊኬሽን ሶፍትዌር ሲሆን ከጠፈር ላይ የሚወሰዱ መረጃዎችን የምናስቀምጥበት እንዲሁም የተሰበሰበዉን (አውዳዊ) መረጃ በሚፈለገው ሁኔታ ከምስሎች ጋር በማያያዝ ለማሳይት የሚያስችል ነው። ይህ ሲሰተም የተለያዩ ቦታዎችን እርስ በርሳቸው በምን አይነት መንገድ እንደሚገናገኙ የሚያሳይ ሲሆን አፕሊኬሽን ሲስተሙም ከቦታ ጋር የተገናኘን ዳታ በቀላሉ ለማየት ያስችላል። የጂ.አይ.ኤስ ቴክኖሎጂ ዋና ዋና ክፍሎች፡
ሃርድዌር (Hardware) - በጂ.አይ.ኤስ (GIS) ሲስተም ውስጥ ሀርድዌር የምንለው የጂኦግራፊካል ኢንፎርሜሽን ሲስተም ሶፍትዌር የሚጫንበት ሲሆን በአሁኑ ወቅት የተለያዩ አይነት ሀርድዌሮች ይገኛሉ። ከትልልቆቹ ሰርቨሮች ጀምሮ እስከ ዴስክቶፕና ታብሌቶች ድረስ በተለያዩ አውታር ዝርጋታዎች ላይ መጠቀም የሚቻል ሲሆን በመጠን፣ በአሰራር፣ በሚይዙት የማስታወሻ ቦታ (memory capacity) እንዲሁም በዋጋ የተለያዩ ናቸው።
ሶፍትዌር (Software) የጂዮግራፊካል ኢንፎርሜሽን ሲስተም ሶፍትዌር ኮምፒውተር ላይ ከተጫነ በኋላ መረጃዎች የሚቀመጡበት፣ እንዲሁም በተሰበሰቡበት መረጃዎች ላይ ትንተና በማካሄድ ወደ ስነ መልክዓ ምድር መረጃነት የሚቀየርበት የቴክኖሎጂው ክፍል ነው።
መረጃ - ካሉት የጂ.አይ.ኤስ ክፍሎች መካከል በጣም ከፍተኛውን ስፍራ የሚይዝ ሲሆን ጂ.አይ. ኤስ ከጠፈር ላይ ሆኖ አውዳዊ መረጃዎችን በመሰብሰብና ሌሎች ጥሬ መረጃዎችን በአንድ ዳታ ቤዝ የሚያስተዳድር ሲስተም ላይ የሚቀመጥበት ስልት ነው። የጂ.አይ.ኤስ ሲስተም ብቻውን ያለ ሰው እርዳታ አገልግሎት ሊሰጥ አይችልም። ስለሆነም ይህንን ሲስተም እንዲሰራና ተግበራዊ እንዲሆን እንዲሁም የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውን የሚቆጣጠሩት፣ የሚያስተዳድሩትና የጥገና እና የድጋፍ አገልግሎት የሚያገኙት በሰዎች አማካኝነት በመሆኑ ሰዎችም የዚህ ሲስተም አንዱ ክፍል ናቸው።
ዘዴዎች - ሃርድዌር እና ሶፍትዌር በምን ዘዴ መዋሀድ እንዳለባቸው፣ ምን ቴክኖሎጂና መሳሪያ ቢጠቀሙ ውጤታማ ይሆናሉ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የሚስፈልግ ሲሆን በሳይንሳዊ ዘዴ አካሄድ የአሰራር ንድፎችንና ሕጎችን ከመከተል አንፃር በአጠቃላይ ስለሲስተሙ አስተማማኝ የአሰራር ሂደትን የሚከታተል ነው።
ምንጭ Frontierinternet
ለአይናችን እረፍት የሚሰጥ መተግበሪያ
***********************************
መቼም የአይን ነገር ሲነሳ በተለይ የኮምፒውተርና የስማርት ስልክ ተጠቃሚዎች ምን ተባለ ይሆን ማለት አለባቸው ብለን እናስባለን፡፡ ምክንያቱም ከኮምፒውተርና ከስልካችን ስክሪኖች የሚፈነጥቀው ሰማያዊ ብርሃን በከፍተኛ ሁኔታ አይናችንን እየጎዳው በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ችግር ከቴክኖሎጂና ከአጠቃቀም ጉድለት ጋር ተያይዞ የሚከሰት ቢሆንም መፍትሔውንም ቴክኖሎጂ ይዞልን ቀርቧል፡፡ ይኸውም ጽሁፍን ወደ ድምጽ የሚቀይር መተግበሪያ ነው፡፡
ቴክኖሎጂን መጠቀም ማቆም የሚመከር ጉዳይ ባይሆንም አማራጭ መፍትሔዎችን መጠቀም ግን በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ለዚህም ነው የፈጠራ ባለሙያዎች Elocance የተሰኘ ጽሁፍን በንባብ የሚያሰማ መተግበሪያን ሰርተው ያቀረቡት፡፡ ይህም መተግበሪያ አንዴ በስልካችን ከጫንነው በኋላ ለሁል ጊዜ መስራት የሚችል ነው፡፡ በተጨማሪም መተግበሪያው በስልካችን ያሉ ጽሁፎችን (PDFs) የተለያዩ ህትመቶችንና የስብሰባ ማጠቃለያዎችን ወደድምጽ በመቀየር እንድንሰማቸው ያስችለናል፡፡ በመሆኑም መተግበሪያው እያንዳንዱን ጽሁፍ የሚያነብልን ረዳትና አደጋ ካለው ሰማያዊ ብርሃን የሚጠብቀን ትልቅ መፍትሔ ሆኖ ቀርቧል፡፡
በጣም ተፈላጊ የሆነው ይህ መተግበሪያ በመተግበሪያ መደብር (App Store) ውስጥ የ4.4 ኮኮብ ደረጃ ተሰጥቶታል፡፡ መተግበሪያው ግልጽ የሆነ አነጋገርን የሚከተል ሲሆን ከፍተኛ የሆነ የድምጽ ጥራትም እንዳለው ተነግሮለታል፡፡ የሆነው ሆኖ የዋጋውስ ነገር ያላችሁ እንደሆን 34.99 የአሜሪካን ዶላር ከፍለን ለሁልጊዜ መጠቀም እንድንችል የቀረበ ነው፡፡
ምንጭ iflscience
የአኳፖኒክስ (AQUAPONICS) አሰራር
===================
የአኳፖኒክስ የሽቅብ እርሻ አሰራር የሃይድሮፖኒክስ ስርዓትን አንድ ደረጃ በመጨመር እፅዋትንና ዓሳዎችን በአንድ ስርዓተ ምህዳር (Ecosystem) የማሳደግ ሂደት ነው። እንደሚታወቀው አለማችን 75 በመቶ በውሃ በመሸፈኗ አብዛኛው እፅዋት የሚገኘው በውሃ ውስጥ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ እጽዋትና ዓሳ በአንድ ስርዓተ ምህዳር መኖራቸው የታመነ ነው፡፡ በተመሳሳይ አኳፖኒክስም ይህን ስርዓተ ምህዳር በመፍጠር እፅዋትንና ዓሳን በአንድ ላይ እንዲመገቡ ያደርጋል።
አኳፖኒክስ ሁለት ስርዓቶችን አጣምሮ የያዘ ሲሆን እነሱም አኳካልቸር (Aquaculture) እና ሃይድሮፖኒክ ናቸው። ይህም ማለት እፅዋትን ያለ አፈር ለማሳደግ እና ዓሳን በአንድ ላይ ለማርባት ትክክለኛው ስርዓት ነው ማለት ነው። የአኳፖኒክስ አሰራርን አስገራሚ የሚያደርገው የዓሳው ውጋጅ (Waste) በንጥረ ነገር የበለፀገ በመሆኑ ለእጽዋት እንደምግብነት ማገልገሉ ነው። በተመሳሳይ እፅዋቱ ውጋጁን ከውሃው በመለየት መልሶ ወደ ዓሳ ማቆሪያ ይልካል ይህም ባለማቋረጥ በአኳፖኒክ ይከናወናል ፡፡
ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው የዓሳውን ውጋጅ ለተክሉ እንደምግብ እንዲጠቀመው የሚያደርገው ማይክሮብስ (Microbes) የተሰኘ ባክቴሪያ ነው። ይህም ባክቴሪያ አሞኒያ (Amonia) የተባለውን ጎጂ የዓሳ ውጋጅ በመመገብ ናይትሬት (Nitrate) ያመነጫል። ይህም የመነጨው ናይትሬት የናይትሮጅን ይዘት ስላለው ለተክሎች ፈጣን እድገት እጅጉን አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ በአንፃሩ ተክሎች ናይትሬቱን ከወሰዱ በኋላ ከሚዘዋወረው ውሃ ውስጥ አሞኒያ እና ናይትሬትን በማጥፋት ውሃው መልሶ ወደ ዓሳ ማቆሪያ በመሄድ ለዓሳዎቹ እንደአዲስ እንዲያገለግል ያደርጉታል። ይህንም ሂደት የአኳፖኒክስ ናይትሮጅን ስርዓተ ኡደት ብለን እንጠራዋለን፡፡
አኳፖኒክስ እንደሌሎች የሽቅብ እርሻ አይነቶች የእድገት ማከናወኛ ንጥረነገሮች የሚጠቀም ሲሆን ይህውም የተክሉ እድገት እንዲያፋጥን ይረዳል፡፡ ይህን የእርሻ ዘዴ ከሌሎች የሚለዩት በአንድ የእርሻ ስርዓት የእፅዋትንም ሆነ የዓሳን ምርት በአንድ ላይ ማስገኘት መቻሉ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከሌሎች ሽቅብ እርሻ ስርዓቶች በመለየት ኬሚካላዊ ንጥረ ነገሮችን አለመጠቀሙ አኳፖኒክስን ልዩ ያደርገዋል፡፡
ምንጭ፡ Sciencedirect እና tech science