TechIn2
1.16K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
አስትራዜንካ እና የደም መርጋት
*******************
እንግሊዝ አስትራዜንካ በተሰኘው የኮቪድ 19 ክትባት ምክንያት ተከስተዋል ያለቻቸውን 25 የደም መርጋት ክስተቶችን ይፋ አደረገች፡፡ ባለፈው የፈረንጆች መጋቢት 24 ከደም መርጋት ጋር በተያያዘ የተከሰተው ችግር 30 የደረሰ ሲሆን ሁሉም ከአስትራዜንካ ጋር የተያያዙ ናቸው ተብሏል፡፡ ሌላኛው የክትባት አይነት ፋይዘር በዚህ ጉዳይ ስሙ እየተነሳ አይደለም፡፡
በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የተዘጋጀው ይህ ክትባት በአውሮፓ እያሽቆለቆለ የመጣ ተቀባይነት ቢኖረውም ሀገራት ከወረርሽኙ ነጻ ለመውጣት ካላቸው ጉጉት በሚመስል ሁኔታ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ክትባቶችን እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ የእንግሊዙ የክትባት ኤጀንሲ እንዳሳወቀው 30ው ከደም መርጋት ጋር የተያያዘው ችግር የተስተዋለው ከ18.1 ሚሊዮን ክትባቶች ውስጥ ነው፡፡
ከመጋቢት 24 ቀደም ብሎ ባለው ቀን አምስት የደም መርጋት ችግሮች የተስተዋሉ ሲሆን ይህም ከተሰጠው 11 ሚሊዮን ክትባት ውስጥ ነው፡፡ ይህ የሚያመላክተው ክትባቱ ወረርሽኙን ለማስወገድ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ በጣም ከፍኛ መሆኑን ነው፡፡ በመሆኑም ሰዎች ያለ ስጋት ክትባቱን መውሰድ ይገባቸዋል ተብሏል፡፡
በተያያዘ ሮይተርስ ባወጣው መረጃ በኮቪድ 19 በጠቅላላው 29 ሺህ 300 ሰዎች ተይዘውባት ከነዚይም መካከል 909 ሰዎች የሞቱባት እና በቫይረሱ ቁጥጥር ከፍተኛ ስኬት ያስመዘገበችው አውስትራሊያ በስፋ የኦክስፎርዱን አስትራዜንካ እንደተጠቀመች ይናገራል፡፡ ይሁንና ባለፈው አርብ የተስተዋለውን አንድ የደም መርጋት ሁኔታ ከክትባቱ ጋር ያለውን ግንኙነት እንዳጠናች አሳውቋል፤ ዘገባው፡፡
ይህ በ44 ዓመት ጎልማሳው ላይ የተስተዋለው የደም መርጋት የደም ህዋሳት እጥረትም የተስተዋለበት ነበር፡፡ ችሩም ከክትባቱ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ የሀገሪቱ ተመራማሪዎች ይህ እንደ ትልቅ ችግር ሊወሰድ አይገባውም የሚል አቋም አላቸው፡፡ አውስትራሊያ በየካቲት ወር ብቻ 25 ሚሊዮን የአስትራዜንካ ክትባቶችን ማሰራጨቷ ይነገራል፡፡
ምንጭ Bloomberg እና Reuters
ድምጽን ብቻ በመጠቀም የኮቪድ 19 ተጠቂዎችን የሚለየው መተግበሪያ
*******************************
የሰዎችን ድምጽ ብቻ በመጠቀም የኮቪድ ተጠቂዎችን ለመለየት የሚያስችል በሰው ሰራሽ አስተውሎት የታገዘ መተግበሪያ መሰራቱ ተሰማ፡፡ ይህ መተግበሪያም 80 በመቶ የደረሰ ትክክለኝነት እንዳለውም ተሰምቷል፡፡ እንደሚታወቀው ኮቪድ 19 የሚያሳየው ምልክት ከሰዎች ሰዎች የተለያየ በመሆኑ ተጠቂዎችን መለየት እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ አንድ ሰው የጉሮሮ መከርከር፣ ሙቀት፣ ሳል ወይም የማሽተትና የመቅመስ ችግር ሲስተዋልበት የኮቪድ ምርመራ ማድረግ እንዳለበት ይመከራል፡፡
ይህንን ችግር የተመለከተው ቮካሊስ የተሰኘ ኩባንያ የኮቪድ ተጠቂዎችን ለመለየት የሚያስችል ድምጽንና የሞባይል መተግበሪያን የሚጠቀም ቴክኖሎጂን አበልጽጓል፡፡ ይህን ቴክኖሎጂ የተለየ የሚያደርገው ነገር በአንድ በቫይረስ የተጠቃም አካባቢ የሚገኙ ሰዎችን ለመለየት ሁሉንም ሰዎች ወደ ጤና ተቋም ማምጣት አስፈላጊ ቢሆንም ቴክኖሎጂው ልየታውን ለማድረግ ሰዎች ባሉበት ሆነው በድምጻቸው ብቻ ቫይረሱ በውስጣቸው መኖሩንና አለመኖሩን መለየት የሚያስችል መሆኑ ነው፡፡ ቴክኖሎጂው ይህን ለማድረግ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ይጠቀማል፡፡
ቮቻሊስ የተሰኘው ድርጅት ከሰዎች ድምጽ ጋር የተያያዙ ሰፊ መረጃዎችን የሰበሰበ ሲሆን የቴክኖሎጂ ተቋሙ የህመም ስሜት የሚሰማቸው ሰዎች የሚኖራቸውን ድምጽ ሰው ሰራሽ አስተውሎትንና የተሰበሰበውን የድምጽ መረጃ በመጠቀም የሚለይ ቴክኖሎጂን አበልጽጓል፡፡ ካምፓኒው ያበለጸገው ስልተ ቀመር 512 የሚደርሱ የተለያዩ የድምጽ ባህሪያትን የለየ ሲሆን ተገማች ህመሞችን መተንበይ የሚያስችለውን ምስል spectrogram ይሰራል፡፡
በሙከራ ወቅትም ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች ከ50 እስከ 70 የሚደርሱ ቁጥሮችን እንዲቆጥሩ በማድረግ ቴክኖሎጂውን የማለማመድ ስራ ተሰርቷል፡፡ በዚህም 275 ሺህ የሚደርሱ የተለያዩ ቋንቋዎችን የሚናገሩ ሰዎች ተሳትፈዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ይህ ቴከኖሎጂ በአሜሪካ፣ቺሊ፣ኢንዶኖዢያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ሉክሰምበርግ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ቮካሊስ የተሰኘው መሰረቱን እስራኤል ያደረገው ተቋም በ2019 የተመሰረተ ሲሆን በያዝነው አመት በህንድ ሙባይ 2000 ታካሚዎችን በመመርመር ነው ስራውን የጀመረው፡፡
ምንጭ The next web
በዓለማችን 50 በሚሆኑ ሰዎች ላይ ብቻ የሚገኘው አደገኛ የደም አይነት
===========================
ስለደም አይነቶች ስናወራ ወደሃሳባችን የሚመጡት A, B O የተባሉት ዋነኞቹ የደም አይነቶቸ ወይም ስርዓቶች ናቸው፡፡ እንደአውሮፓውያኑ በ1901 ለመጀመሪያ ጊዜ የተለዩት እነዚህ የሰዎች የደም ስርዓቶች በውስጣቸው 8 የደም አይነቶች እንደሚገኙባቸውም ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ የደም አይነቶች ውስጥ A, B, AB እና O ዋናዎቹ የሰዎች የደም አይነቶች ሲሆኑ ከዚህ በተጨማሪ አልፎ አልፎ በሰዎች ላይ የሚታዩ እጅግ ብዛት ያላቸው የደም አይነቶች እንዳሉም ይነገራል፡፡
እንደተመራማሪዎች ከሆነ በሰዎች የደም ስርዓት ውስጥ 342 አንቲጅንስ (antigens) የያዙ ቀይ የደም ሴሎች አሉ፡፡ በእነዚህ ሴሎች ውስት ያሉት አንቲጅኖች በሽታ የመከላከል አቅማችንን ለመፍጠር የሚስቸሉንን antibodies የሚያመርቱ ሲሆኑ የማናችንም የደም አይነት ዝርያም በእነዚህ የአንቲጅኖች መኖር እና አለመኖር ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ከ 342 የደም ቡድን አንቲጂኖች (blood group antigens) ውስጥ 160 የሚሆኑት በቀይ የደም ሴሎች ውስጥ የመሰራጨት እድል አላቸው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ማናችንም ከ160 ያላነሱ አንቲጂኖች በደማችን ውስጥ ከተገኘ ከላይ የጠቀስናቸው መደበኛ የደም አይነቶች ሊኖሩን ይችላል ማለት ነው፡፡
ይሁንና ከላይ ካነሳነው በተለየ ሁኔታ 99 በመቶ የሆኑት ሰዎች ያላቸውን ወይም positive የሆኑበትን አንቲጅን ያልያዙ ሰዎች አልፎ አልፎ የሚታይ የደም አይነት (rare blood type) አላቸው እንዲባል ያስችላል፡፡ ከዚህ በባሰ ሁኔታ ደግሞ 99.99 በመቶ የሆኑት ሰዎች ያላቸውን ወይም positive የሆኑበትን አንቲጅን በተፈጥሮ ያላገኙ ሰዎች የመከሰት እድሉ በጣም አናሳ የሆነ (extremely rare) የደም አይነት አላቸው እንዲባል ያስችላል፡፡ ታዲያ በአለማችን ከ50 ያነሱ ሰዎች ላይ ብቻ ይገኛል የሚባለው Rhnull የተሰኘው የደም አይነት መሰረታዊውን የ Rh አንቲጅን ወይም ፕሮቲን በቀይ የደም ሴላቸው ያልያዙ በመሆናቸው የመከሰት እድሉ በጣም አናሳ የሆነ (extremely rare) የደም አይነት ያላቸው ሰዎች እንዲባሉ ሆኗል፡፡
እንደአውሮፓውኑ በ1961 ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው ይህ የደም አይነት በደም ግሩፕ ስርዓት ውስጥ እጅግ ውስብስበ ከሚባሉት ቀዳሚው ሲሆን፤ ከዚህ ጊዜ አንስቶም በአለም ላይ ከ40 እስከ 50 በሚሆኑ ሰዎች ላይ ብቻ እንደሚገኝ ይነገራል፡፡ የመከሰት እድሉ በጣም አናሳ የሆነው ይህ የደም ዝርያ በአለማችን በጥቂት ሰዎች ላይ ብቻ የሚታይ በመሆኑ ደሙን ለማግኘት እጅግ ከባድ ደርገዋል፡፡ በዚህ የተነሳም ይህ የደም አይነት ያለቸው ሰዎች ለተለያዩ አደጋ ቢጋለጡ አንኳን የደም ባንክ እንደሌላቸው በማንሳት አደገኛ ስጋት ያለባቸው ሰዎች መሆናቸውን ብዙዎች ሲገልፁ ይሰማል፡፡
ደሙን ለማግኘት እጅግ ከባድ ከመሆኑ አንፃር አንዳንዶች ወርቃመው ደም ብለው የሚጠሩት ይህ የደም ዝርያ በአለማችን 8 የሚሆኑ ሰዎች ብቻ መለገስ እንደሚችሉ ይነገራል፡፡ ይሁንና እንደየሃገራቱ ህግጋት እና በሰዎቹ ላይ ሊፈጠሩ ከሚችሉ ያልታሰቡ ችግሮች አንጻር ደሙን የማግኘት እድሉ እጅግ የጠበበ ነው፡፡ ይህ የደም አይነት ያላቸው ሰዎች አንደአብዛኞቻቸን የነፃነት ህይወት ላይኖሩ ይችላሉ፣ አንቅስቃሴያቸውም ጥንቃቄ የተሞላበት ሊሆን ያስፈልጋል፤ ምክንያቱም በተለያየ ችግር የደም እጥረት ቢያጋጥማቸው እንኳን ደሙን የማግኘት እድላቸው እጅግ የጠበበ ነው፡፡
ምንጭ፡ Medicinenet እና bigthink
ከገበያ እየወጣ ያለው LG ስልክ
******************
ከአመታት የቁልቁለት ጉዞ በኋላ እውቁ የደቡብ ኮሪያ ኤሌክትሮኒክስ አምራች ኩባንያ LG ከስማርት ስልክ ገበያ ሊወጣ እንደሆነ ተሰማ፡፡ ይህም ኩባንያውን በዘርፉ ከተሰማሩና ሰፊ እውቅና ካላቸው የሞባይል ስልክ አምራች ኩባንያዎች ውስጥ የመጀመሪያው እንደሚያደርገው ተነግሯል፡፡ ምንም እንኳን ዘርፉ እጅግ አትራፊ እና ስልኩ በአሜሪካ ገበያ ውስጥ ከአፕልና ከሳምሰንግ ቀጥሎ ተመራጭ ስማር ስልክ ቢሆንም ኩባንያው በገጠመው የትኩረት ማጣት ችግር ምክንያት ራሱን ከገበያው ለማግለል እንዳሰበ በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ባወጣው መረጃ አሳውቋል፡፡
የካምፓኒው ከዘርፉ መውጣት በድርጅቱ ቦርድ የጸደቀ ሲሆን የሚመጣው ሐምሌ መጨረሻ ላይ ሙሉ በሙሉ ከዘርፉ ገበያ እንደሚወጣም ተሰምቷል፡፡ አንድ ካውንተር ፖይንት የተባለ የምርምር ተቋም እንዳወጣው መረጃ ከሆነ ባለፈው የፈረንጆች አመት በአሜሪካ ብቻ ከተሸጡ ስማርት ስልኮች ውስጥ 11 በመቶውን በመሸፈን LG በሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ኩባንያ ነበር፡፡ ተቋሙ ባወጣው መረጃ መሰረት ከስማርት ስልክ ገበያው መውጣት እንደ የኤሌክትሪክ መኪኖችና መለዋወጫዎች፣ የተለያዩ የኤሌክትኒክስ እቃዎች፣ ስማርት ቤቶችና በሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ ትኩረቱን እንዲያደርግ ያስችለዋል፡፡
የኩባንያውን ከገበያው የመውጣት መረጃ ተከትሎ ድርጅቱ ያለው የሼር ዋጋ በ2.52 ቀንሷል፡፡ በስማርት ስልክ ዘርፍ ተቋሙ ላለፉት ስድስት ዓመታት ሲንከባለል የመጣ የ4.5 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ እንደደረሰበት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በዓለም ገበያ ውስጥ ካሉ ስማርት ስልኮች ውስጥ LG የሚሸፍነው 2 በመቶውን ብቻ ነው፡፡
ምንጭ Forbs
የአለማችን ፈጣኗ የኤሌክትሪክ ጀልባ
***********************
የአለማችን ፈጣኗ እና በኤሊክትሪክ ሐይል ትሰራለች የተባለችው ጀልባ በፈረንጆቹ 2022 እየተጠበቀች ነው፡፡ ጀልባዋ በስዊዲኑ የጀልባ አምራች ኩባንያ በሆነው ካንዴላ እና በስዊዲን ትራንስፖርት አስተዳደር ትብብር የተዘጋጀች እንደሆነች ተሰምቷል፡፡ በአንዴ 30 ሰዎችን መያዝ የምትችለው ጀልባ በሰዓት 55 ኪሎሜትር ያክል እንደምትጓዝ ተነግሯል፡፡
በስቶኮልም የውሃ ላይ የህዝብ ትራንስፖር አገልግሎት ሀላፊ የሆኑት ሚካኤል ሃጋ ለመረጃ ምንጫችን እንደሰጡት መረጃ ከሆነ ዓላማቸው የዛሬንና የመጭውን ጊዜ የዘርፉን ፍላጎት ለማሟላት ነው፡፡ ይህ በሙከራ ደረጃ ያለው ፕሮጀክት ከአዋጭነት ጋር የተያያዙ የተለያዩ ጥናቶች እየተደረጉበት እስከ 2024 ድረስ የሚቆይ ሲሆን በውሃ ላይ ለሚደረገው የህዝብ ትራንስፖርት ትልቅ መፍትሔ ሕሆናል ተብሏል፡፡
ፕሮጀክቱ ይፋ እንዳደረገው ይህች P-30 የተሰኘች ጀልባ የሐይል ብክነትን መቀነስ የሚያስችል ቴክኖሎጂ የተገጠመላት ሲሆን አሁን ላይ አገልግሎት ከሚሰጡ ጀልባዎች አንጻር 80 በመቶ ሐይል መቆጠብ ያስችላል፡፡ ጀልባዋ ባህላዊ የውሃ ላይ መጓጓዣዎች በሚጓዙበት ውሃ ላይ መጓዝ የምትችል ሲሆን በአንድ ጊዜ ቻርጅም ሶስት ሰዓታትን መጓዝ ትችላለች፡፡
ምንጭ cities-today
ከ 500 ሚሊዮን በላይ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች የግል መረጃ በበይነ-መረብ ተለቋል
--------------------------------------
533 ሚሊዮን የፌስቡክ የተጠቃሚዎች የግል መረጃ በነፃ በኦንላይን መለቀቁን ቢዝነስ ኢንሳይደር ዘግቧል፡፡ ይህ የዜና ወኪል በመረጃ ደህነነት ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሰራ የምርምር ተቋምን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው በአለም አቀፍ ደረጃ 106 በሚሆኑ ሀገራት በሚገኙ 533 ሚሊዮን የፌስቡክ ተጠቃሚዎች የግል መረጃ በበይነ- መረብ እንዲለቀቅ መደረጉን አስታውቋል፡፡
መረጃው በወጣበት አፕሪል 3 በሰዓታት ልዩነት ስለጉዳዩ ምላሽ ለመስጠት የሞከረው ፌስቡክ ይህ የተጠቃሚዎች መረጃ እንደአውሮፓውያኑ በ2019 ሪፖርት መደረጉን እና ችግሩንም በማጣራት በዛው ዓመት ነሃሴ ወር ላይ ሊስተካከል እንደቻለ ገልጿል፡፡ ይሁናን የዘገባው ምንጭ ይህ የተጠቃሚዎች የግል መረጃ ቀድሞ የተመዘበረ ቢሆንም አሁንም ድረስ መረጃዎቹ በሳይበር ወንጀለኞች እና ሃከሮችን ለመጥፎ አገልግሎት ሊውሉ የሚችሉበት እድል ሰፊ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በእስራኤል መቀመጫውን ያደረገው ሁዱሶን ሮክ የተባለው ይህ የምርምር ተቋም በበይነ-መረብ ተለቀዋል ካላቸው የጠቃሚዎች የግል መረጃዎች መካከል የስልክ ቁጥሮች፣ መገኛዎች፣ ሙሉ ስሞች እና የኢሜል አድራሻዎች የሚገኙበት ሲሆን ከአፍሪካ ከ14 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች፣ ከአሜሪካ 32 ሚሊዮን፣ ከእንግሊዝ 11 ሚሊዮን እና ከህንድ ስድስት ሚሊዮን ተጠቃሚዎች መረጃቸው በኦንላን መለቀቁን ይፋ አድርጓል፡፡
ቢዝነስ ኢንሳይደር በኦንላይን ከተለቀቁት የጠቃሚዎች የግል መረጃ ውስጥ የታዋቂ ሰዎችን የፌስቡክ አካውንት በመውሰድ ለማነጻፀር እንደሞከረው አንዳንዶቹ የግል መረጃዎች አሁን እየተጠቀሙት ካለው ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው ለማረጋገጥ ችሏል፡፡ ይህም በበይነ-መረብ የተለቀቁት መረጃዎች የጠቃሚዎችን የግልዊነት ጥበቃ በመጣስ አሁንም ድረስ ጉዳት ሊያስከትሉ እንደሚችል የሚያመላክት ነው፡፡ የሁዱሶን ሮክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አሎን ጋል በቲውተር ገፁ ይፋ ካደረጋቸው የሀገራት ዝርዝር ውስጥ አትዮጵያ አንዷ ስትሆን 12,753 የፌስቡክ ተጠቃሚዎችም የግል መረጃ ይፋ እንደተደረገ ያሳያል፡፡ የፌስቡክ የተጠቃሚዎች መረጃ በበበይነ-መረብ ሾልኮ የሚወጣበት ሁኔታ ይህ የመጀመሪያው ባይሆንም በዚህ መጠን ግን የተጠቃሚዎችን የግል መረጃ ያወጣ ክስተት አልተፈጠረም፡፡
ምንጭ፡ DW እና businessinside
ከዶሮ እንቁላል እየተሰራ ያለው አዲሱ የኮቪድ 19 ክትባት
*******************************
ተመራማሪዎች አዲስ እና በቀላል ዋጋ ሊመረት የሚችል የኮቪድ ክትባትን የዶሮ እንቁላልን በመጠቀም እየሰሩ እንደሆነ ተነገረ፡፡ ክትባቱ ከደህንነትና ከውጤታማነት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ማለፍ ከቻለ ተመራማሪዎቹ በዓመት ውስጥ ከአንድ ቢሊዮን ብልቃጦች በላይ ለማምረት ማቀዳቸውን አሳውቀዋል፡፡ ይህ በብራዚል፣ ሜክሲኮ፣ ታይላንድና ቬትናም ለክሊኒካዊ ሙከራ የቀረበው ክትባት አለም ወረርሽኙን ለመከላከል እየሔደ ያለበትን መንገድ እንደሚቀይረው ታምኖበታል፡፡
NDV-HXP-S የተሰኘው የክትባት ዓይነት አሁን ጥቅም ላይ እየዋሉ ካሉት የክትባት አይነቶች የተለየ ሞሎኪዩላዊ መዋቅር ያለው ሲሆን የሰውነት የበሽታ መከላከል ብቃትን በሰፊው እንደሚያሳድግ ተነግሮለታል፡፡ ከአዲሱ ክትባት ጋር አብሮ ተያይዞ እየተነሳ ያለው ሌላው ጉዳይ ክትባቱን ለመስራት የሚያፈልጉ ግብዓቶችን የተመለከተ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር እንደ ፋይዘር ያሉ ክትባት አምራች ድጅቶች ለክትባቱ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን የማግኘት ችግር ሊገጥማቸው ይችላል ተብሎ የተሰጋ ሲሆን NDV-HXP-S ግን የዚህ ዓይነት ችግር እንደማይገጥመው ታምኗል፡፡ ለዚህ ክትባት የሚውለው ግብዓት ለኢንፍሎዊንዛ ቫይረስ ክትባት መስሪያነት የሚያገለግለው የዶሮ እንቁላል ነው፡፡
የግሎባል ሔልዝ ኢኖቬሽን ሴንተር ረዳት ዳይሬክተር የሆኑት አንድሪያ ቴይለር እንደሚሉት ከሆነ የመጀመሪያው ክሊኒካዊ ሙከራ የፊታችን ሐምሌ የሚጠናቀቅ ሲሆን ቀጣዩ ሙከራም ተጨማሪ ወራቶችን ይጠይቃል፡፡ በእንስሳት ላይ በተደረገው ሙከራ እጅግ ተስፋ ሰጭ የሆኑ ውጤቶች የተመዘገቡ ሲሆን ሙከራዎች ሲጠናቀቁ ለአለማችን ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ላቸው ሀገራት ትልቅ መፍትሔ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡
ምንጭ Firstpost
ጎግልና የተጠቃሚዎች የግል መረጃ
*******************
የአለማችን ግዙፉና ሀብታሙ ድርጅት ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን እንዲችል ያደረገውን ሀብት የሚሰበስበው ተጠቃሚዎች በብዛት የሚጎበኟቸውን ገጾች መሰረት አድርገው ከሚሰሩ ማስታወቂያዎች ነው፡፡ ይንንም ለማድረግ ጎግል ከፍኛ መጠን ያለው መረጃ ያስፈልገዋል፡፡ በስልኮቻችንና በሌሎች የጎግልን መተግበሪያ በሚጠቀሙ ነገሮች የምንሰራቸው እያንዳንዱ ስራዎችና የምንነካቸው ማስፈንጠሪያዎች ለጎግል መረጃዎችን በመስጠት ድርጅቱን አበልጽገውታል፡፡
ባሳለፍነው ታህሳስ ወር አፕል የተሰኘው የመተግበሪያ መደብር (App Store) እያንዳንዱ መተግበሪያ የሚሰበስባቸውን መረጃዎችና እነዚህ መረጃዎች ከእያንዳንዱ ተጠቃሚዎች ጋር ያላቸውን ግኙነት በመደብሩ ውስጥ ምልክት የሚሰጥ ማሳወቂያን ይፋ አድጎ ነበር፡፡ ይህም ከከፈትናቸው ማናቸውም መተግበሪያዎችና ማስፈንጠሪያዎች እስከ መገኛ ቦታችን ድረስ ያለውን የሚያጠቃልል ነው፡፡ በዚህ የአፕል እንቅስቃሴ ብዙም ያልተገረመ የሚመስለው ጎግል ተመሳሳይ እርምጃን ለመውሰድ ከኤሊ ተንቀራፍፏል፡፡
የጎግልን መተግበሪያ ከሚጠቀሙ ከ1 ቢሊዮን ከሚጠጉ ሰዎች በተጨማሪ ከስልሳ በላይ መተግበሪያዎችና ዘጠኝ የደረሱ የጎግል ምርቶችን የሚጠቀሙ ሌሎች 1 ቢሊዮን ሰዎች እንዳሉ ይታመናል፡፡ ሁለት ቢሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን መረጃ በመጠቀም ምን ያክል ሀብት ሊሰራ እንደሚችል ጎግል የደረሰበትን ደረጃ ብቻ በመመልከት መገመት ቀላል ነው፡፡ በጎግል ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ካላቸው የድርጅቱ መተግበሪያዎች ውስጥ ጂ-ሜል፣ ክሮምና መረጃ ማፈላለጊያው ጎግል ሰርች ዋነኞቹ ናቸው፡፡
እነዚህ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴዎቻችን የሚሰበሰቡ መረጃዎች የተጠቃሚዎች የግል መረጃዎች በመሆናቸው በአንዳንዶቹ ላይ እንደ ደንበኛ ተጠቃሚው ብቻ የሚያውቃቸው መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ለመሆኑ አንድ ተጠቃሚ ይህን መወሰን ይችል ይሆን? የክሮም ሴቲንግ አንድ ተጠቃሚ ከእሱ ወይም ከእሷ የሚሰበሰበውን መረጃ የመወሰን እድል ይሰጣል፡፡ በሌላ በኩልም በክሮም ሴቲንግ sync የሚለውን በማጥፋት (turn off) የተጠቀምናቸው ማስፈንጠሪያዎች ከስልካችን ወይም ከኮምፒውተራችን እንዳያልፍ ማድረግ እንችላለን፡፡ በጣም ትልቅ የሚባለው እንደ ተጠቃሚ ማድረግ የምንችለው የድርጊት መቆጣጠሪያውን (Activity Controls) በማስተካከል ነው፡፡ ምንጭ wired
የኮስሚክ ጨረሮች (Cosmic rays) ምንድን ናቸው
==========================
የኮስሚክ ጨረሮች ከስርአተ-ፀሀያችን ውጭ በሚገኘው በይነኮከባዊ ህዋ (Interstellar space) ውስጥ የሚገኙ እና ከፍተኛ ሀይል ያለው ፑሮቶን እና አተማዊ ኑክለስ (Atomic nucleus) የያዙ ጨረራዎች ናቸው። ተመራመሪዎች እንደሚገለፁት ክዋክብት በውስጠኛ አካላቸው የያዙት ሀይድሮጅን ሙሉ ለሙሉ ወደ ሂልየም ንጥረነገር ሲቀየር ኖቫ/ሱፐርኖቫ በተሰኘ ግዙፍ ፍንዳታ ውጨኛ አካላቸውን እንደሚበትኑ ይነገራል። በዚህ ፍንዳታ ወቅት ከፍተኛ መጠን ያለው የኮስሚክ ጨረሮች ከአዋራ (ኔቡላ) ጋር ወደ ህዋ የሚበተኑ ሲሆን ይህም አንዱ የኮስሚክ ጨረሮች ምንጭ ነው።
ሌላው እንደምንጭነት የሚጠቀሱት አክቲቭ ረጨታዊ ኑዩክለስ (Active Galactic Neucleus) የሚባሉት ናቸው። የጠፈር ተመረማሪዎች እንደሚያስረዱት ሱፐር-ማሲቭ ብላክ ሆል የተባለው የህዋ አካል ከፍተኛ የሆነ የጨረራ ቡልቅታ (Jets of radiation) እንደሚያመነጩ ይናገራል። ይህ ቡልቅታ ኮስማዊ ጨረሮች በውስጡ እንደያዘ ይታመናል። ከባህር ወለል በላይ ከ1000 ኪ.ሜ አንስቶ እስከ 60,000ኪ.ሜ ድረስ የሚካልለውን የቫን አለን የራዲዬሽን ቀበቶ (Van Allen radiation belt) በነዚህ ፓርቲክሎች የተዋቀረ ሲሆን እነዚህም በምድራችን መግነጢሳዊ መስክ (Magnetic field) ተስበው ምድራችንን ከበው የሚገኘ ናቸው። ይህን በምሳሌ ብንመለከተው
የብረት ፍቅፋቂዎችን ደብተር ላይ ብንበትን እና ከደብተሩ ስር ጠንካራ ማግኔት ብናኖር የብረት ፍቅፋቂዎቹ ማግኔቱ ወዳለበት ቦታ ይሰበሰባሉ። ነገር ግን የደብተሩ ወለል ስላል ከማግኔቱ ጋር እንዳይጣበቁ ያግዳቸዋል። ልክ እንደዚህ ሁላ ምድራችንም እንደ ግዙፍ ማግኔት ስትሆን ፓርቲክሎቹም በዚህ ማግኔት ተስበው ምድራችንን ከበው ተቀምጠዋል። ወደ ውስጥ እንዳይገቡ የምድር ከባቢ አየራዊ ርብራቦች ያግዷቸዋል። እነዚህን ቅንጣቶች ከምድር ጋር አጠቃሎ የያዘውን ክልል የምድር ከባቢ መግነጢስ (Magnetosphere) ብለን እንጠራዋለን። የቫን አለን የራዲዬሽን ቀበቶ ከምድራችን ውጪ ሌሎች ፕላኔቶች ላይም ሊገኝ የሚችል ሲሆን ከዚህ ክልል እየራቅን በሄድን ቁጥር ፕላኔቶች እና ሳተላይቶቻቸውን፤ አስትሮይዶችን እና ኮሜቶችን እያገኘን እንሄዳለን።
ምንጭ፡ Spacecentre
ተፈጥሯዊ ማዳበሪያ ለምግብ ደህንነት
**********************
የእርሻ ስራ የአለማችንን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ አማራጭ የሌለው መንገድ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ምንም እንኳን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ቢመጣም የእርሻ ስራ እንደ እኛ ባሉ ሀገራት ከፍተኛ ጉልበት የሚጨርስ ነው፡፡ ይህን የአርሶ አደሩን ህይወት እያዳከመ ያለውን የእርሻ ስራ በቴክኖሎጂ ማገዝ ቢቻል ድካምን ከመቀነስ ባሻገር የምግብ ዋስትናችንን ለማረጋገጥ የምናደርገውን ጥረትም እንደሚያፋጥነው ይታመናል፡፡ በአሁን ጊዜ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት ከእርሻ ጋር ያለው ችግር የምርታማነት ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም ውጤቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስተዋለ የመጣው ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ አጠቃቀም በሰዎች፣ በእንስሳትና ባጠቃላይ በስነ-ምህዳሩ ውስጥ ሊታሰብበት የሚገባ ነው፡፡
ተፈጥሮን ብቻ ማዕከል ያደረገ የእርሻ ስራ (organic farming) አርቲፍሻል የሆኑ የምርት ማሳደጊያ መንገዶችን የማይጠቀም የእርሻ አይነት ነው፡፡ ኦርጋኒክ የሚለው ቃል የተለያዩ መገለጫዎች ያሉት ሲሆን አንድ ለምግብነት የሚውል የግብርና ምርት ያለውን ይዘት የሚመለከት ነው፡፡ በUSDA የመረጃ ቋት ላይ እንደተቀመጠው መረጃ ከሆነ አንድ የምግብ ምርት ከ70 በመቶ ጀምሮ እስከ 100 በመቶ የሚለካ ተፈጥሯዊ ይዘት ካለው ኦርጋኒክ ሊባ ይችላል፡፡ የአንድ የግብርና ምርት የመቶኛ የይዘት መጠኑ እያነሰ በሔደ ቁጥር የተጠቃሚዎችን የጤና ሁኔታ በጥያቄ ውስጥ እያስቀመጠው ይሔዳል፡፡
የግብርና ምርቶችን ተፈጥሯዊ ይዘት ከሚቀንሱ መንስኤዎች መካከል በዋናነት የሚነሳው የኬሚካል ይዘት ያላቸው ማራበሪያዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ዓይነት ማዳበሪያዎች በቀጥታ የግብርና ምርቶች ላይ ከሚያስከትሉት የይዘት ለውጥ በተጨማሪ በእንስሳት፣ በእጽዋትና በአጠቃላይ በተፈጥሮ ላይ በሒደት የሚስተዋል ጉዳት ያመጣሉ፡፡ ለዚህም በግልጽ ከታዩት ውስጥ ከእንቦጭ አረም ጋር ተያይዞ በሀይቆቻችን ላይ የተጋረጠውን አደጋ ማንሳት ይቻላል፡፡ ከሰዎች ጤና ጋር በተያያዘ የሚመጣው ጉዳት በሒደት የሚስተዋል ቢሆንም ጉዳቱ ግን የማይቀር ነው፡፡
ይህን ከተፈጥሮ ጋር የተጣላ የአስተራረስ ወይም ምርትን የማሳደግ ዘዴ መጠቀሙ ሙሉ ለሙሉ ልምድ ከማድረጋችን ብዛት የተነሳ አንዳንድ አካባቢዎች ያለ ማዳበሪያ ምንም አይነት እንቅስቃሴ አይደረግም፡፡ የዚህ ጉዳቱ ከብዙ አቅጣጫ የሚመጣ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ተፈጥሯዊ ማዳበሪያ የመጠቀም ልምድን በማሳደግ የምግብ ደህንነትን ማስተካከልና እንስሳትንና እጽዋትን አስፈላጊ ካልሆኑ ኬሚካሎች መታደግ እንደሚቻል ከPHYS.ORG ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በአንድ ለ27 ዓመታት በተሰራ ጥናት ላይ እንደተመለከተው ተፈጥሯዊ በሆነና ሀገር በቀል በሆኑ እውቀቶች በታገዘ መንገድ የሚሰራ የእርሻ ስራና ከእንስሳት ጽዳጅ በሚገኝ ማዳበሪያ ወይም ኮምፖስት ለፓቶጅኖች ህልውና የማይመች በመሆኑና በተቃራኒው ፓቶጅኖችን የሚመገቡ ባክቴሪያዎችን የሚያፈራ በመሆኑ በጣም ጠቃሚ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ይህ በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የተሰራው ጥናት እንደሚያመለክተው በብዙዎች ዘንድ እየተተወ የመጣው የኮምፖስት ማዳበሪያ የተወሰኑ መሻሻያዎች ታክለውበት እንደገና ጥቅም ላይ ሊውል ይገባዋል፡፡ ይህም ተፈጥሯዊ በሆነ መልኩ የአፈርን ደህንነት የሚያስጠብቅ ከመሆኑ ባሻገር የምግብ ደህንነትንም በእጅጉ ያሻሽለዋል ሲል የጥናቱ ውጤት አመላክቷል፡፡
ምንጭ PHYS.ORG