TechIn2
1.16K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
ከጂፒኤስ ፈጠራ ጀርባ ያሉት ጥቁር አሜሪካዊት ተመራማሪ
========================
በተወለዱባት የቨርጂኒያ ግዛት ዲንዊዲ ካንትሪ ቤተሰቦቻቸው ባወረሷቸው የእርሻ መሬት ላይ ህይወታቸውን መቀጠል ያልፈለጉት ግላዲስ ዌስት ለጥቁሮች አስቸጋሪ በነበረበት በዚን ጊዜ ትልቅ ህልም ይዘው ትኩረታቸውን በትምህርት ላይ ለማድረግ ቆርጠው ተነሱ፡፡ በአንድ ወቅት ዘ ጋርዲያን ለተባለው እውቅ ጋዜጣ እንደተናገሩት በጊዜው ለትምህርት ካለኝ ፍላጎት የተነሳ ከቤተሰቦቼ ጋር ለመራራቅ ተገድጃለሁ ብለዋል፡፡
በ1930 ወደዚህች አለም የተቀላቀሉት እኝህ የሂሳብ ሊቅ ከቤተሰባቸው ከወረሱት የእርሻ ስራ ተነስተው በ1952 በተመቻቸላቸው የስኮላርሺፕ እድል የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከብላክ ቨርጂኒያ ስቴት ኮሌጅ በሂሳብ ሊመረቁ ችለዋል፡፡ ከዚህ ጊዜ አንስቶ በሂሳብ የትምህርት ዘርፍ ይበልጥ እየተሳቡ የመጡት ግላዲስ ዌስት በ1955 የማስተርስ ዲግሪያቸውን በሂሳብ በመስራት ለጥቁሮች አስቸጋሪ በነበረበት በዚያን ሰዓት በትልልቅ መድረኮች ራሳቸውን መከሰት ጀመሩ፡፡
በ1960ዎቹ በሂሳብ ሙያ ተቀጥረው ሲሰሩበት በነበረው የአሜሪካ የባህር ሃይል ላብራቶሪ በአንድ የአስትሮኖሚ ምርምር ላይ መሳተፍ የቻሉት ግላዲስ ዌስት በዚህ ግዙፍ ጥናት ላይ ትልቅ ሚና በመጫወት ምርምሩ ለሽልማት እንዲበቃ አድርገዋል፡፡ በ1960ዎቹ አካባቢ በአሜሪካ ከጥቁሮች መብት ጋር ተያይዞ ሰፊ ንቅናቄዎች እና ሰላማዊ ሰልፎች የተበራከቱበት ጊዜ በመሆኑ ግላዲስ ዌስት እንደሌሎች ጥቁሮች ሁሉ ንቅናቄው ላይ ለመሳተፍ ቢሞክሩም ከስራቸው ባህሪ ጋር ተያይዞ መሰል እንቅስቃሴዎች ላይ እንዳይሳተፉ በመንግስት አካላት ይከለከሉ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
እንደአውሮፓውያኑ በ1973 የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር Global Positioning System ወይም ጂፒኤስ የተባለውን የመከታተያ ስርዓት ለማበልፀግ በሚሞክርበት ጊዜ የመሬትን ቅርፅ በትክክል ማሳየት የሚችል የሂሳብ ሞዴል አስፈልጎ ነበር፡፡ ለጂፒኤስ መተግበር እጅግ አስፈላጊ የሆነው ይህ የሂሳብ ሞዴል geodetic model ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ግላዲስ ዌስት በሚመሩት እና በጊዜው ከሌለች የኮምፒውተር ስርዓቶች ፈጣን በሆነው የኮምፒውተር ፕሮግራም አማካኝነት ትክከለኛው የሂሳብ ሞዴል ሊሰራ እንደቻለ ዘ ጋርዲያን ያወጣው የህይወት ድርሳናቸው ያስረዳል፡፡ በአለማችን የቴክኖሎጂ ታሪክ ውስጥ ጂፒኤስ ለፈጠረው ትልቅ አብዮት እንደመነሻ የሆኑት እኝህ ተመራማሪ ስራቸውን በዚህ ሳያቆሙ ጡረታ እስከወጡበት የእርጅና ዘመናቸው ድረስ በአሜሪካ የወታደራዊ ተቋም ውስጥ ትልልቅ ምርምሮችን ያደረጉ የሂሳብ ሊቅ ናቸው፡፡
የጂፒኤስ ቴክኖሎጂ አሁን ላይ ከደረሰበት መራቀቅ እና ለሰው ልጆች ከሰጠው ትልቅ ግልጋሎት አኳያ የቴክኖሎጂው መነሻ የሆኑት እኝህ ተመራማሪ በ2018 በህይወት ዘመናቸው ለበረከቱት ትልቅ አስተዋፅዖ እና ለስራ ትጋታቸው የአሜሪካ የአየር ሃይል ተቋም በጠፈር ምርምር እና በሚሳይል ፕሮግራም ፈር ቀዳጅ ተመራማሪ በሚል ሽልማት አበርክቶላቸዋል፡፡ እንደአውሮፓውያኑ በ2000 ዓ/ም በሰባ አመታቸው የፒኤችዲ ትምህርታውን በአስተዳደርና በፖሊሲ ጉዳዮች ያገኙት ዶ/ር ግላዲስ ዌስት አሁን ላይ 91 አመታቸው ላይ የሚገኙ ሲሆን የሕይወት ታሪካቸውን የሚያሳይ የሆሊውድ ፊልምም በ2016 Hidden Figures በሚል እንደወጣ ይታወቃል፡፡ ለጂፒኤስ ቴክኖሎጂ እውን መሆን ትልቅ ሚና ያላቸው ዶ/ር ግላዲስ ዌስት አሁን ላይ በ30 ሴንቲ ሜትር ርቀት ያለንበትን ቦታ ለመለየት በቻለው አስገራሚ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ባይሆኑም ለአሁኑ ትውልድ እና ገና ለሚመጣውም ትውልድ ትልቅ አሻራን ያኖሩ ጠንካራ ሴት ናቸው፡፡
ምንጭ፡ Theguardian
የመጀመሪያው የማርስ ላይ ከተማ እቅድ
**************************
የስነ-ህንጻ ተመራማሪዎች ለቀዩዋ ፕላኔት የመጀመሪያ የሆነ 250,000 ሰዎችን ማኖር የሚያችል በዋሻ መልክ የሚገነባ የከተማ ዕቅድ ይፋ አደረጉ፡፡ ይህ ከተማ ኑዋ የሚል መጠሪያ የተሰጠው ሲሆን ስያሜውንም ያገኘው በቻይና ከሚነገሩ ተረቶች በአንዱ አምስት ድንጋዮችን በማቅለጥ ጠንካራ ምሰሶ ያለው ቤት ከሰራው ጣኦት ስም እንደሆነ ተነግሯል፡፡ ከዚህ ሀሳብ ጀርባ እንዳለው እንደ ABIBOO መረጃ ከሆነ አንድ ሰው ወደማርስ ለጉብኝት ለመሔድ በሚከፍለው ሶስት መቶ ሺህ ዶላር ለህይወት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች በሙሉ የተሟሉለትን ከተማም የመጎብኘት እድል አለው፡፡ በከተማው የሚገነቡት ቤቶች ከ25 አስከ 35 ስኩየር ሜትር ስፋት የሚኖራቸው ሲሆን በዚያ የሚኖሩ ሰዎችም ከ60 እስከ ሰማንያ በመቶ የሚሆነውን የስራ ሰዓታቸውን የሚያሳልፉት በከተማዋ በሚሰጥ ስራ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
በማርስ ለመኖር በዋናነት ራስን ከአደገኛ ጨረር ለመጠበቅ የሚያስችል መከላከያ የሚያፈልግ መሆኑን ያስታወሰው የስነ-ህንጻ ምርምር ድርጅቱ ከዚህ በተጨማሪም ሁሉንም ምግብ ከምድር መውሰድ ስለማይቻል ማርስ ላይ የምግብ ሰብሎችን ለማምረት የሚያስችል ሁኔታ መመቻቸት እንዳለበትም እምነቱን ገልጧል፡፡ እነዚህን ሁለት መሰረታዊ ችግሮች ለመቅረፍም ተቋሙ ሶኔት ኔትወርክ ከተባለ የምሁራን ስብስብ ጋር አብሮ እየሰራ ነው፡፡ ለዚህም ይረዳቸው ዘንድ የተመራማሪዎች ስብስቡ ቴምፔ ሜንሳ የተባለ የማርስ አካባቢን ለይተዋል ሲል የመረጃ ምጫችን ዘግቧል፡፡
ABIBOO አክሎም ሰዎች በተለየው አለታማ አካባቢ በተሰሩ ዘመናዊ ዋሻዎች የሚኖሩ መሆኑን የገለጸ ሲሆን ሌሎች ለጨረር የተጋለጡ አካባቢዎችን አስፈላጊ ሲሆን ብቻ እንደሚጎበኙ ገልጧል፡፡ ለትራንስፖርትም ከጥብቅ አካባቢው ውጭ መንቀሳቀስ የሚችሉ ባቡሮችና አውቶቢሶች የታሰቡ ሲሆን በጥብቅ አካባቢው ወይም ለመኖሪያ በተሰራው አካባቢ ደግቦ ትላልቅ አሳንሰሮችን ጥቅም ላይ ለማዋል ታቅዷል፡፡
በመኖሪያ ክልሉ መሰረት አካባቢ መልኣ ማርስን መመልከት የሚያስችሉ የተለያዩ ማማዎች እንደሚሰሩ እና ከአደገኛ ጨረር ለመጠለል የሚያስችሉ ተንቀሳቃሽ ጣሪያዎችም ይገነቡላቸዋል ተብሏል፡፡ የመኖሪያ መንደሩ አስፈላጊ የሚባሉ እንደ ሆስፒታል፣ ትምህርት ቤት፣ የገበያ ስፍራዎች፣ የስፖር ማዘውተሪያዎችና ዩኒቨርሲቲዎችም የተሟሉለት ነው፡፡
የማርስ ላይ ከተማ እቅዱ ከምግብ ሰብሎች በተጨማሪም የተለያዩ እንስሳትንም ያካተተ ነው፡፡ ምንም እንኳን ኤሎን ማስክ በ2050 የማርስ ላይ ከተማው እውን እንደሚሆን የተናገረ ቢሆንም የABIBOO ቃል አቀባይ ግን እስካሁን የከተማ ግንባታው የሚጀመርበት ጊዜ እንዳልታወቀ እና በ2054 ይጀመራል የሚል ሀሰተኛ ወሬ እንዳለም ተናግረዋል፡፡
ምንጭ Popular Mechanics
የህክምና ላይ የጊዜ እጥረትን በቴክኖሎጂ
*************************
ከርቀት በሚደረግ ቁጥጥር የሚሰራ የቴክኖሎጂ ቁስ ለህክምና ሙያተኞች ጊዜን እንደሚያተርፍላቸው ተነገረ፡፡ በዓለማችን በተለይ አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች አገልግሎት በሚሰጡ ሆስፒታሎች የታካሚዎች ክትትል ከሀኪሞች የጊዜ እጥረት ጋር የተያያዘ ከፍተኛ ችግር ያጋጥማል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ዲጂታል የሆኑ መገልገያዎች አለመኖራቸው በእጅ የሚሰሩ ተጨማሪ ስራዎች ስራውን የበለጠ ከባድ ያደርጉተል፡፡
EIT በተባለ የዲጂታል ማስተር ትምህርት ቤት በሚመራ አንድ ፕሮጀክት ስር ያሉ ተማሪዎች አዲስ የሆነ የታካሚዎችን ወቅታዊ ሁኔታ ከርቀት መከታተል የሚያችል የቴክኖሎጂ ቁስ መስራታቸው ታውቋል፡፡ የቴክኖሎጂ ቁሱ እንደ የሰውነት ሙቀት፣ የኦክስጅን አጠቃቀም፣ የልብ ምትና የአተነፋፈስ ስርዓትን መቆጣጠር የሚያስችል ሲሆን በ 3D ህትመት የተዘጋጀ በእጅ ላይ የሚታሰር ግብዓትን ይጠቀማል፡፡
ይህ የታካሚዎችን የጤና መረጃ ሚስጥራዊ በሆነ መልኩ ለዚሁ ዓላማ ወደተዘጋጀው የዲጂታል ህክምና ፕላትፎርም የሚልክ ሲሆን በተመሳሳይ ሰዓት ብዙ ታካሚዎችን መከታተል የሚያስችል ስልት ነው፡፡ በዚህም የተጨናነቀውን የህክምና ሙያተኞች ሰዓት ማቃለል ያስችላል ተብሎለታል፡፡ የህክምና ቁሱን ስድስት የሚደርሱ አለማቀፍ ተማሪዎች ያዘጋጁት ሲሆን በ2020 የEUvsVirus ሽልማትን አሸንፈውበታል፡፡
ምንጭ Technology.org
ከ 1,300 ዓመታት በላይ በአንድ ቤተሰብ ሲተዳደር የቆየው ጥንታዊ ሆቴል
==========================
ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ 705 AD ተመሰረተ የሚባለው የአለማችን ጥንታዊ ሆቴል ከ 1,300 ዓመታት በላይ በአገልግሎት መቆየቱ ብቻ ሳይሆን በአንድ የቤተሰብ ትውልድ ይህን ያክል ዘመን መተዳደሩ ብዙዎችን ያስገረመ ጉዳይ ነው፡፡ በጃፓኗ ያማናሺ ግዛት መቀመጫውን ያደረገው ይህ ጥንታዊ ሆቴል ፉጂዋራ ማሂቶ በተባለ የአካባቢ መሪ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተመሰረተ በኋላ የሱ ቤተሰብ የሆኑ 52 ትውልዶች ሆቴሉን በማስተዳደር አሁን ላሉት ትውልዶች ማስተላለፍ ችለዋል፡፡
በአስገራሚ የህንጻ ንድፍ የተዋበው ይህ ጥንታዊ ሆቴል በውስጡ 37 ከፍሎች ሲኖሩት በዙሪያውም በደቡባዊ ጃፓን ታዋቂ በሆነው አካይሺ ተራራ ተከቧል፡፡ ከ1,316 አመታት አንስቶ ለተገልጋዮች በሩን ክፍት ያደረገው ይህ ሆቴል በዘመን ቅብብሎሽ ውስጥ በየጊዜው የተከሰቱ ሁነቶችን በመታዘብ የጊዜን ውጣ ውረድ የተረዳ የሰዎች መሰብሰቢያ ሆኗል፡፡ እንደአውሮፓውያኑ በ2011 በጊነስ የአለም ሪከርድ መመዝገብ የቻለው ይህ ጥንታዊ ሆቴል ፉጂዋራ ማሂቶ በተባለው ግለሰብ ከተመሰረተ በኋላ እስከ 1997 ድረስ ብዛት ያላቸው ግንባታዎችና ጥገናዎች ሲደረጉለት ቆይተዋል፡፡ ሆቴሉ በየዘመኑ በነበሩ የቴክኖሎጂና የፈጠራ አይነቶች ሲያሸበርቅ ቆይቶ በ2019ም የዘመናችን የቴክኖሎጂ ትሩፋት የሆነው የዋይፋይ አገልግሎት ሊገጠምለት ችሏል፡፡ በሆቴሉ ላይ በየዘመኑ ሲደረጉ የነበሩ እድሳቶች (renovations) ሆቴሉ ለዚህን ያህል ጊዜ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ያደረጉት ምክንያቶች ናቸው የሚሉት ባለሙያዎች ለዚህም የጃፓን ባህላዊ አርክቴክቶች ትልድ ድርሻ እንደሚወስዱ ይናገራሉ፡፡
Keiunkan የሚል ስያሜ ያለው ይህ ጥንታዊ ቅርስ አብዛኛው አካላቱ ከእንጨት የተዋቀረ ሲሆን በአገሪቱ አብዛኛው ክፍሎች ተደጋግሞ የሚከሰተውን የመሬት መንቀጥቀጥ ለመቋቋም ሲባል የእንጨት ዝርያዎች ይበልጥ ተመራጭ ሆነዋል፡፡ በዚህ ጥንታዊ ሆቴል የሚገኘው ሞቃት የውሃ አካል ወይም ምንጭ ቅርሱ ለብዙ ዘመናት በብዙዎች እንዲጎበኝ ያስቻለ ተጨማሪ ምክንያት ሲሆን የውሃውም ሙቀት 36.7 ዲግሪ ሴልሺየስ ይደርሳል፡፡
ጥንት በነበረው አረዳድ ሆቴል ሲባል ተጓዦች እና መንገደኞች ረዥም መንገድ አቋርጥ ሲመጡ የሚያርፉበት መጠለያ ነገር ሲሆን አሁን በምናውቀው የሆቴል አረዳድ ግን በ1770ዎቹ በእንግሊዝ የተዋወቀው ግራንድ ሆቴል የመጀመሪያው ዘመናዊ ሆቴል ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
ምንጭ፡ Interesting engineering
መረጃ ስለ ስዊዝ መተላለፊያ (ስዊዝ ካናል)
*********************
የስዊዝ ካናል ወይም የውሃ ላይ መተላለፊያ ከአውሮፓ ወደ እስያ የሚደረገውን የባህር ላይ ጉዞ ለማሳጠር ታስቦ የተሰራ መተላለፊያ ነው፡፡ ምንም እንኳን ይህ 120 ማሎች ወይም 193 ኪሎሜትሮች ያክል የሚረዝም መተላለፊያ በአውሮፓ የመስፋፋት አላማን (ኮሎኒያሊዝም) ለማሳካት እንግሊዝና ፈረንሳይ ወደ አፍሪካና እስያ ለሚያደርጉት መስፋፋትና ጥሬ እቃዎችን ለማጓጓዝ ታልሞ የተሰራ ቢሆንም ከዚህ በፊት በአካባቢው በግብጻውያን የተሰራ አጠር ያለ መተላለፊያ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
መተላለፊያው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1869 የተጠናቀቀው መተላለፊያ ሜዲትራኒያን ባህርንና ቀይ ባህርን የሚያገናኝ ነው፡፡ መተላለፊያው ከአውሮፓ ወደ እስያ ለሚደረገው የባህር ላይ ጉዙ እጅግ ተመራጭ ነው፡፡ ከመተላለፊያው መሰራት በፊት ከአውሮፓ ወደ እስያ የሚደረገው የባህር ላይ ጉዞ እጅግ አስቸጋሪ እና በአፍሪካ ደቡባዊ ጫፍ በኩል የሚደረግ ነበር፡፡ ካለው ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ አኳያ መተላለፊያው በየእለቱ ግዙፋን መርከቦችን የሚያስተላለፍ ሲሆን ከፍተኛ ጥበቃም ይደረግለታል፡፡
የመተላለፊያው ምስረታ ዋና መቀመጫውን ፈረንሳይ ፓሪስ ባደረገው የስዊዝ ካምፓኒ አማካኝነት ሲሆን የካናሉ 52 በመቶ ድርሻ የፈረንሳይ መንግስት ሲሆን 44 በመቶው ደግሞ የግብጽ መንግስት ነበር፡፡ በ1875 የግብጽ ግርሻ ካናሉን በማስተዳደር ስታግዝ ለነበረችው ለእንግሊዝ መሸጡን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በ1888 በቁስጥንጥንያ በተደረገው ስምምነት መሰረት መተላለፊያው በሰላምም ሆነ በጦርነት ሰዓቶች ለሁሉም ሀገራት ክፍት የተደረገ ቢሆንም በጦርነት ወቅቶች የተለያዩ መርከቦች በካናሉ በኩል እንዳያልፉ ተደርገዋል፡፡ በተለይም በአንደኛውና ሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት፡፡ ከ1956-57 በግብጽ እና እስራኤል መካከል በነበረው ውጥረት ምክንያት ካናሉን ግብጽ ዘግታው የነበረ ሲሆን እንዲሁም በ1967 በአረብና እስራኤል መካከል ጦርነት ምክንያት ተዘግቶ ነበር፡፡
በ2018 የተሰበሰበው መረጃ እንደሚያመለክተው መተላለፊያው በዓመቱ 18 ሺህ 174 ጉዞዎችን ያስተናገደ ሲሆን በ2019 ቁጥሩ ወደ 18 ሺህ 880 ከፍ ብሏል፡፡ ይህም በቀን 51.5 ማለት ነው፡፡ በእነዚህም ዓመታት አብላጫውን የሚወስደው የኮንቴነሮችና ታንከሮች በብዛት ተጓጉዘዋል፡፡
ምንጭ: Britannica
በህዋ ላይ የሚደረጉ የተመራማሪዎች ዩኒፎርም ይዘት
=========================
በጠፈር ላይ የሚደረጉ የተመራማሪዎች ዩኒፎርም የሰውን ልጅ ከነበረበት ለህይወት ተስማሚ ዞን (Habitable zone) ወደ አዲስ እና ለህይወት አደገኛ ወደሆነው (Harsh zone) በሚሄድበት ወቅት ምድር ላይ የነበረውን የአየር ግፊት (air pressure) ፣ የሙቀት መጠን (Temprature) ፣ እና የኦክስጂን መጠን በተመጣጠነ ሁኔታ ይዞ ተመራማሪው ስራውን እንዲያከናውን የሚረዳ የደንብ ልብስ ነው። ዩኒፎርሙ ብቻውን ከነ ኦክስጂን ሳጥኑ እና ሌሎች መሳሪያዎቹ እስከ 90 ኪ.ግ ሊመዝን ይችላል። እጅግ ከባድ ቢመስልም ጠፈር ላይ የስበት ሀይል ስለሌለ የዩኒፎርሙ ክብደት ለተመራማሪው ብዙም አይታወቀውም።
የአየር ግፊት፦ እንደተመራመሪዎች አገላለፅ ምድራችን ውስጥ ያለው የአየር ግፊት 1 አትሞስፌር (1atm) ነው። ውሀ በዚህ ግፊት ውስጥ ፈሳሽ ሲሆን ግፊቱ ከዚህ ከበዛ ወይንም ካነሰ ውሀው ወደ ጋዝ ይቀየራል። ህዋ ላይ የሚደረግ ዩኒፎርሙም በዚሁ ግፊት መሞላት ያለበት ሲሆን ይህ ካልሆነ ግን ተመራማሪው ገና ከመንኮራኩሩ እንደወጣ በደሙ ውስጥ የሚገኘው ውሀ ወደ ጋዝነት ስለሚቀየር በአማካኝ በ 15 ሴኮንድ ውስጥ ህይወቱን ሊያጣ ይችላል።
ኦክስጂን፦ የጠፈር ተመራማሪው በጀርባው የሚሸከመው የአየር ሳጥን ምድር ላይ ባለ አየር አይሞላም ይልቁንም (78% ናይትሮጅን፣ 21% ኦክስጂን፣ 1%ሌሎች ጋዞችን) በማድረግ ሳጥኑ ይሞላል። ምክንያቱም የግፊት አለመኖር በሳንባችን ያለውን የኦክስጂን ኮንሰንትሬሽን ከፍ ስለሚያደርገው መተንፈስ ያዳግታል። ስለዚህ ተመራማሪው መተንፈስ ያለበት 100% ተቀጣጣይ ኦክስጂን ይሆናል ማለት ነው።
የሙቀት መጠን (temprature) ፦ ህዋ እጅግ በጣም ቀዝቃዛ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እጅግ በጣም ሊሞቅ ይችላል። ከፀሀይ የሚነሱ ሞቃት የጨረር ነፋሶች (solar wind) ተመራማሪዎቹን ያለዩኒፎርም ካገኛቸው ወዲያው ሊገሏቸው ስለሚችሉ ተመራማሪዎች የሚያደርጉት ዩኒፎርሙ ሙቀት በማያስገባ ንጣፍ ወይም (layer) ተለብጦ ይሰራል። ከዚህ በተጨማሪ ለጭንቅላታቸው እንደመከላከያ የሚጠቀሙት ሄልሜት (helmet) ከውጭ የፀሀይ ጨረርን በማያስገባ (reflector layer) ተለብጦ የሚሰራ ሲሆን ከውስጥ ደግሞ ጉም በማይፈጥር (anti-fog layer) ተሸፍኖ ይሰራል።
ምንጭ፡ Spacecentre
ኢንስቲትዩቱ የዘጠኝ ወር እቅድ አፈጻጸሙን ገመገመ
የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት የ2013 በጀት አመት የዘጠኝ ወር እቅድ አፈጻጸሙን የተቋሙ ከፍተኛ ኃላፊዎችና የየክፍል ኃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ መጋቢት 21 ቀን 2013 ዓ.ም አራት ኪሎ በሚገኘዉ ዋናዉ ቢሮዉ ገምግሟል፡፡
በእቅድ አፈጻጻም ግምገማዉ በዘጠኝ ወሩ በእቅዱ መሰረት የተሰሩ፤ ከእቅድ በታች የተከናወኑ እንዲሁም ከእቅድ ዉጭ በተከናወኑት ስራዎች ላይ ሰፋ ያለ ግምገማና ዉይይት ተድረጓል፡፡ በዚህም መሰረት በዘጠኝ ወሩ ለማከናወን ታቅደዉ ነገር ግን አስቻይ ባልሆኑ ምክንያቶች ያልተከናወኑ ስራዎች በቀጣይ የአስራ አምስት ቀን የትግበራ እቅድ በማዘጋጀት በአፋጣኝ መሰራት እንዳለባቸዉ ስምምነት ላይ በመድረስ የግምገማ መድረኩ ተቋጭቷል፡፡
ገዳይ ከሆኑ የካንሰር ዓይነቶች አንዱ የሆነው የጡት ካንሰር መንስኤ ታወቀ
******************************
የአውስትራሊያ ተመራማሪዎች በዓለማችን ገዳይ ከሆኑ የካንሰር አይነቶች አንዱ ለሆነው የጡት ካንሰር ህመም ምክንያት የሆነውን ጅን ማግኘታቸው ተሰማ፡፡ ይህ የገዳዩ የጡት ካንሰር ህመም ምክንያት የሆነው ጅን ዝቅተኛ የሆነ በህይወት የመቆየት አቅም (survival rates) ያለው እንደሆነ ታውቋል፡፡ በመሆኑም በበሽታው የሚሰቃዩ ሰዎችን ለማከም ያለው ስኬት አልባ ድካም እንደሚሻሻል ተስፋ ማስገኘቱን የሀሪ ፓርኪንስ ሜዲካል የምርምር ተቋሙ ፒላር በላንስፎርት ተናግረዋል፡፡
የጡት ካንሰር በሚል ጥቅል ስም ውስጥ የተለያዩ የካንሰር አይነቶች ያሉ ሲሆን እንደ ኢስትሮጅንና ፕሮጀስትሮን ላሉ ሆርሞኖች ሴንሲቲቭ የካንሰር ዓይነቶች የተለያዩ ህክምናዎች ያሏቸው ሲሆን ሆርሞን ሴንሲቲቭ ካልሆኑ የጡት ካንሰር አይነቶች ይልቅ የተሻለ ምላሽ ይታይባቸዋል፡፡ በ2012 አንድ የተመራማሪዎች ቡድን የጡት ካንሰር አይነቶችን ኢንተግሬቲቭ ክላስተሪንግ በሚል አከፋፈል ከ10 መድቧቸው ነበር፡፡ እነዚህም እያንዳንዳቸው የየራሳቸው የጀኔቲክ ለውጥ እና ክሊኒካዊ ውጤት ያላቸው ናቸው፡፡
ከአስሩ የጡት ካንሰር ንዑስ ምድቦች ውስጥ IntClust2 የሚባለው የጡት ካንሰር ዓይነት ይህ ነው የሚባል ህክምና የሌለው ነው፡፡ በተሰራው ምርምርም AAMDC የተሰኘ በጡት ካንሰር ውስጥ የሚገኝ የጅን አይነት ለጡት ካንሰር መከሰት ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ታውቋል፡፡ ይህም የታወቀው በጡት ካንሰር ውስጥ የሚገኝን ይህንን ጅን በመያዝ የሰውነት ህዋሳት እንደገና ራሳቸውን የማደስ ባህሪ ስለተስተዋለባቸው ነው፡፡
ምንጭ Science alert
በቨርጂን ጋላክቲክ ይፋ የተደረገው አዲስ ትውልድ አውሮፕላን
*******************************
በስፔስ ክራፍት ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተለያዩ አስደናቂ ግኝቶችና ፈጠራዎች በየጊዜው ይፋ እየተደረጉ እና ጥቅም ላይ እየዋሉ ይገኛሉ፡፡ በዚህኛው ትውልድ አውሮፕላን አዲስ ከሆኑ ነገሮች አንዱ የአውሮፕላኑ ሙሉ አካል ብራማ በሆነ የብረት ቁስ የተሸፈነ መሆኑ ነው፡፡ ይህም ለአውሮፕላኑ የቆየ የሚመስል ፋሽን እንዲላበስ አድርጎታል፡፡ እንደ ኩባንያው ፕሬዘዳንት ማይክ ሞሰስ መረጃ ከሆነ የዚህ ፈጠራ ሀሳብ የመጣው በኩባንያው መስራች ሪቻርድ ብራንሰን አማካኝነት ነው፡፡
ይህ V.S.S. Imagine የተሰኘው ስፔስ ክራፍት ለማምረት እጅግ ቀላል በመሆኑ ኩባንያው የዚህ ቀጣይ ትውልድ የሆነውንና V.S.S. Unity የተባለው በምርት ሂደት ላይ መሆኑን የኩባንያው ፕሬዘዳንት ተናግረዋል፡፡ በፍጥነት መመረት ከመቻሉ በተጨማሪም ይህ አዲሱ ዲዛይን የጥገና ወጭን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንስ የተነገረ ሲሆን በብዛት ተመርቶ ለአገልግሎት ለማሰማራትም ታቅዷል፡፡
በቀጣዮቹ ጥቂት ወራት ውስጥ የሙከራ በረራ እንደሚካሄድና በቀጣዮቹ የበጋ ወራት በመደበኛ በረራዎችን ያደርጋል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ካምፓኒው V.S.S. Unity የተሰኘውን የኤሌክትሮ መግነጢስ ጣልቃገብነት ያጋጠመውን ሞዴል በመጪው ግንቦት ወር ለመሞከር ያሰበ በመሆኑ ለኩባንያው መጭው ጊዜ የተጨናነቁ ሙከራዎች የሚካሄዱበት ይሆናል፡፡
ምንጭ Forbs