TechIn2
1.16K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
በምድር ላይ ሕይወት የተፈጠረው በከፍተኛ መብረቅ ሳብያ ሊሆን እንደሚችል ተነገረ
=======================
ትናንት የወጣ አዲስ ምርምር እንደሚጠቁመው በአንድ ቢሊዮን ዓመታት ጊዜ ውስጥ ምድር ላይ የወደቁ በትሪሊዮኖች የሚቆጠሩ መብረቆች ሕይወት እንዲፈጠር መሰረቱን እንደጣሉ የሚታመነው ፎስፈረስን ሰጥተዋል፡፡ የምርምሩ መሪና በዬል ዩኒቨርሲቲ የመሬት እና ፕላኔታሪ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ድህረ ምረቃ ተማሪው ቤንጃሚን ሄስ እንደሚለው ጥናታቸው ሕይወት በምድር ላይ በተጀመባቸው ከዛሬ 3.5 እስከ 4.5 ቢሊዮን ዓመታት በፊት ባሉት ጊዜያት የወረዱት የመጀመሪያዎቹ መብረቆች ሪአክቲቭ ፎስፈረስን እንደሰጡ አሳይቷል፡፡ በዚህም መሰረት ለሕይወት ማበብ ይረዳ ዘንድ መብረቅ ፎስፈረስን የማቅረብ ቁልፍ ሚናን ተጫውቶ ሊሆን ይችላል ሲል ይናገራል፡፡
መብረቅ እንዴት ወደ ሕይወት ያመራል?
ይህ ጥያቄ የፎስፈረስ አተሞች ከሌሎች ለሕይወት የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ጋር ተጣምረው ከሚሰሯቸው ኦርጋኒክ ቁሶች ጋር በተገናኘ የሚመለስ ነው፡፡ አዮኖች ከሦስተ ኦክስጅን እና አንድ ፎስፈረስ አተም ጋር የሚፈጥሩት ጥምረት በምድር ላይ ላለ ሕይወት በሙሉ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በምሳሌነት መውሰድ ይቻላል፡፡ ፎስፌቶች ለዘረ-መል (DNA)፣ አር.ኤን.ኤ እና ለህዋሳት ዋነኛ የኃይል ምንጭ ለሆኑት ኤዴኖሲን ትራይፎስፌቶች (ATP) የጀርባ አጥንት ሲሆኑ የአጥንት፣ ጥርስ እና የህዋሳት ሽፋኖች ወይም ሴል ሜምብሬኖችም ትልቅ ግብዓት ናቸው፡፡
ሆኖም ሊያሰራ የሚችል ከፍተኛ የውሃ እና ካርበን ዳይ ኦክሳይድ መጠን (ለህይወትም አስፈላጊ ናቸው) የመኖሩ ዕድል ከፍ ያለ ሊሆን በሚችልበት የዛሬ አራት ቢሊዮን ዓመት አብዛኛው የምድራችን ተፈጥሮአዊ ፎስፈረስ ሊሟሙ ከማይችሉ ድንጋዮች ጋር የተጣበቀና ከኦርጋኒክ ፎስፌቶች ጋርም ለማቀናጀት የማይቻል ነበረ፡፡
ታድያ እንዴት ምድራችን እነዚህን እጅግ አስፈላጊ ውህዶች ልታገኝ ቻለች?
በዚህ ላይ ማብራርያ የሚሰጥ አንድ ሀልዮት በነዚያ ዓመታት ምድራችን ፎስፈረስን ሽራይበሳይት የተሰኘ ከፎስፈረስ የተሰራና በውሃ የሚማሟ ንጥረ-ነገርን የያዙ ሜትሮይዶች ሲያርፉባት በቂ የሆነ ፎስፈረስ በከባቢ አየሯ ላይ እንደተለቀቀና ይህም ለሕይወት ጅማሮ መሰረትን እንደጣለ ያስረዳል፡፡ ሆኖም ሕይወት ተፈጠረ በሚባልባቸው የዛሬ 3.5 እስከ4.5 ቢሊዮን ዓመታት አብዛኛው በስርዓተ-ፀሐያችን የሚገኙ ፕላኔቶች እና ጨረቃዎች ቅርፃቸውን ያገኙበት እንደመሆኑ መጠን በምድር ላይ የሚወድቁ ሜትሮይዶች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ወርዶ ነበር፡፡ ግን ደግሞ በሌላ መልኩ እዚሁ ምድር ላይ በወረዱ በትሪሊዮን የሚቆጠሩ የመብረቅ ናዳዎች ሳብያ ሽራይበሳይቶች ተሰርተው ሊሆን እንደሚችል ቤንጃሚን ሄስ ይናገራል፡፡
የመብረቅ ጥቃቶች አንድን ቦታ እስከ 2,760 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ድረስ በማሞቅ ከዚህ ቀደም ያልነበሩ ንጥረ-ነገሮችን የመስጠት አቅም አላቸው፡፡ በአዲሱ ጥናትም የጥናት ቡድኑ ከአሜሪካኗ የኢለኖይ ግዛት በቁፋሮ የተገኙውን ፎልገራይት የተሰኘ በመብረቅ የተመታ ድንጋይን መርምሯል፡፡ ቡድኑ ባገኘው ውጤት መሰረት በድንጋዩ ውስጥ ከሌላ መስታውታማ ንጥረ-ነገሮች ጋር በመሆን አነስተኛ የሽራይበሳይት ኳሶች መፈጠራቸውን ለማወቅ ችሏል፡፡ በዚህ የመብረቅ ጥቃቶች በፎስፈረስ የታደሉ ሽራይበሳይቶችን እንደሚፈጥሩ በሚያሳይ ያልተረጋገጠ ማስረጃ መሰረት ቡድኑ በቂ መብረቅ ምድራችን ከፍተኛ መጠን ያለው ንጥረ-ነገርን ወደ ከባቢ አየር እንድትለቅ ስለማድረጉ ማስላት ነበረበት፡፡
አጥኒዎቹ ቀድሞ የነበራትን ከባቢ አየር ተጠቅመው በማስላት ምድራችን በየዓመቱ ምን ያህል መብረቅ ስታስተናግድ እንደነበር አሳይተዋል፡፡
ባለንበት ዘመን መሬት በየዓመቱ 560 ሚሊዮን መብረቆችን የምታስተናግድ ሲሆን፤ ከባቢ አየሩ በካርበን ዳይ ኦክሳይድ በተንበሸበሸበት (በዚህም ከፍተኛ ሙቀት እና ዝናብ ባለበት) የዛሬ 4 ቢሊዮን ዓመት ገደማ ግን በየዓመቱ ከ1 እስከ 5 ቢሊዮን የሚሆን መብረቅ ምድር ላይ ወርዶ ሊሆን እንደሚችል የጥናት ቡድኑ ስሌት አመላክቷል፡፡ ከነዚህ መብረቆች ውስጥ ከ100 ሚሊዮን እስከ 1 ቢሊዮን የሚሆኑት በየብስ ላይ ሲያርፉ፤ የተቀሩት ደግሞ ከውቅያኖሶች በላይ ወርደዋል፡፡ በዚህም በአንድ ቢሊዮን ዓመታት ውስጥ ብቻ ያኔ ገና ታዳጊ የነበረችው ፕላኔታችን እስከ አንድ ኩዊንቲሪሊየን (1,000,000,000,000,000,000) ጊዜ በመብረቅ ተደብድባለች፡፡ በቡድኑ ስሌት መሰረት በዚህ ዘመን ምድራችን ከ110 እስከ 11,000 ኪ.ግ የሚሆን ፎስፈረስን በየዓመቱ ታገኝ ነበር፡፡ ይህ ታድያ ሕይወት ይመሰረት ዘንድ ትልቁን ሚና እንደተጫወተ የቤንጃሚን ሄስ እምነት ነው፡፡ እንደርሱ አባባል ከሆነ በዚህ ሁናቴ ውስጥ ሕይወትን ለመፍጠር ለምሳሌ አንዲት ደሴት ላይ 110 ኪ.ግ የሚሆን ፎስፈረስ በዓመት ውስጥ ከተገኘ በቂ ቢሆንም ሁነቱ ግን በብዙ ተመሳሳይ ቦታዎች ሳይፈጠር አልቀረም፡፡
ምድራችን በዚህ ደረጃ ሕይወትን ለመፍጠር የሚያስችል የመብረቅ ናዳ አስተናግዳለች ወይ የሚለው አሁንም በጥያቄነት ቢቆይም ቢያንስ በሒሳብ ስሌት ረገድ ሚቻል መሆኑን ጥናቱ ማሳየቱ ተገልጿል፡፡ ተመራማሪዎቹም ምናልባትም ከአስትሮይድ እና መብረቅ ጥቃት ጥምረት ምድራችን እንደ ዘረ-መል እና አር.ኤን.ኤ ያሉትን ሞለኪውሎች ለመስጠት የሚያስችላትን ፎስፈረስ አግኝታ ሊሆን እንደሚችል በምርምራቸው ደምድመዋል፡፡
ምንጭ፤ Live Science
የመስኖ ልማትና ቴክኖሎጂዎች በኢትዮጵያ
========================
ኢትዮጵያ በብዙ ጅረቶች እና በትላልቅ ወንዞች የተከበቡ በሚሊዮን ሄክታር የሚቆጠሩ በመስኖ ሊለሙ የሚችሉ መሬቶች አሏት፡፡ በግብርናው ዘርፍ ለሚታየው ተጨባጭ ለውጥ የመስኖ ልማት መስፋፋት እጅግ መሰረታዊ ከመሆኑ አንጻር ይህን የተፈጥሮ ሃብት በሚገባ ጥቅም ላይ መዋል የአርሶ አደሩን ህይወት ይበልጥ ለማሻሻል እና ግብርና በሃገር ውስጥ ኢኮኖሚ የሚኖረውን አስተዋፅ ይበልጥ ለማሳዳግ በእጅጉ ይረዳል፡፡ በአፍሪካ ሊታረስ ከሚችለው ጠቅላላለ መሬት ስድስት በመቶ የሚሆነው ብቻ እስካሁን ድረስ በመስኖ የለማ ሲሆን የተቀረው መሬት ግን የመልማት ከፍተኛ አቅም እያለው በተለያዩ ምክንያቶች ጥቅም ላይ ሳየውል የቀረ ነው፡፡ አትዮጵያ ከዚህ የመስኖ ልማት ሬሾ ውስጥ የተሻለ እንቅስቃሴ የሚታይባት ሃገር ብትሆንም በተፈጥሮ ካላት ከፍተኛ የውሃ ሀብት አንፃር ውጤቱ የሚያኩራራ ላይሆን ይችላል፡፡
እንደአውሮፓውያኑ በ2018 የ Malabo Montpellier Panel ይፋ ያደረገው ሪፖርት እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ ከ1994 አንስቶ የመስኖ ልማት እድገቱ በ52 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፤ በ2007 ብቻ ለመስኖ ዝግጁ የሆነው የሚታረስ መሬት በሄክተር 858,340 ደርሶ እንደነበርም በሪፖርቱ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ በአገሪቱ በተለያዩ ክፍሎች አሁን ላይ አገልግሎት እያሰጡ ከሚገኙ የአነስተኛ መስኖ ቴክኖሎጂዎችን መካከል ትሪድል ፓምፕ፣ ሮፕ ፓምፕ፣ ዋሸር ፓምፕ እና የመሳሰሉት ቴክኖሎጂዎች በዋናነት ሊጠቀሱ ይችላሉ። እንደ ግብርና ሚኒስቴር መረጃ ከሆነ አሁን ላይ እነዚህ የመስኖ ልማት ቴክኖሎጂዎች ከላይ በተጠቀሰው አይነት ግልጋሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ይህም በአጠቃላይ 2299 በእጅ የሚሰሩ ጉድጓዶች እና 1179 ኢንጂን ፓምፖች በየክልሎቹ በተመረጡ 21 ፓይለት ስቴሽኖች ላይ አነስተኛ ዋጋ ያላቸውን የመስኖ ቴክኖሎጂዎችን በማዳረስ የግብርና ስርዓቱን ለማሻሻል እየተሰራ ነው፡፡
አገሪቱ ካላት የህዝብ ቁጥር አንፃር በአመት አንድ ጊዜ ብቻ የተመረተው ምርት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል መመገብ ይችላል ለማለት የማያስደፍር ነው። ነገር ግን የመስኖ ቴክኖሎጂዎችን የሚጠቀሙ አርሶ አደሮች አመቱን ሙሉ ማምረት እንዲችሉ በሩን ይከፍትላቸዋል። ይህም የተሻለ ገቢ አንዲኖራቸውና በአመትም ከአንድ ጊዜ በላይ ማምረት እንዲችሉ ያደርጋቸዋል። በአለማችን በእነዚህ ቴክኖሎጂዎች ላይ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ያሉ ተቋማት በቀላሉ መገኘት የሚችሉ የመስኖ ቴክኖሎጂዎችን አነስተኛ መሬት ላላቸው አርሶ አደሮች በማድረስ ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡ ፍርፍሬዎችና አትክልቶችን ማልማት እንዲችሉ በመስራት ላይ ይገኛሉ። ከዚህ አንጻር ከእነዚህ ተቋማት ጋር በህብርት መስራት የሚቻለበትን መንገድ ማመቻቸት የግብርና ስርዓቱን ለማሻሻል ቀዳሚው ሚና ይሆናል፡፡
አነስተኛ ዋጋ ያላቸው የመስኖ የፈጠራ ውጤቶችን ለማስፋፋት በሚደረገው ጥረት በዘርፉ ከተሰማሩት የውጭ እና የሃገር ውስጥ የግል ድርጅቶች በተጨማሪ በመንግስት መዋቅር ስር ያሉ የየደረጃው አስተዳደሮች ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል። መንግስት የርካሽ የመስኖ የፈጠራ ስራዎች ግብይት ዙሪያ መዋቅራዊ አደረጃጀት ያላቸው የማምረቻ ድርጅቶች የሚስፋፉበትን ሁኔታ መፍጠር ቢችል ድርጅቶችና በተጠቃሚው መካከል ያለውን ልዩነት ከማጥበብ አንጻር እንዲሁም በአምራች ድርጅቶችና በአርሶ አደሮች መካከል ሁለቱንም ባማከለ መልኩ ስምምነቶችን ከመፍጠር አንጻር ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል። ይህም የቴክኖሎጂዎቹን የግብይት ዋጋ ከአርሶ አደሮቹ አቅም ጋር የተመጣጠነ እንዲሆን የአምራች ድርጅቶቹን የመሸጫ ዋጋ ቋሚ የሚሆንበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የሚያስችል ይሆናል።
ምንጭ፡ Theconversation እና tech science
አፍሪካውያን አሁንም በዕውቀት ቅኝ ግዛት ውስጥ መሆናችን ተነገረ
============================
በዛሬው የቴክኢነን-ወግ መሰናዶ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢጁኬሽናል ፕላኒንግ እና ማናጅመንት ትምህርት ክፍል መመህር የሆኑት ዶ/ር ደሞዜ ደገፋ “why research incapacity the global south: the vicious circle of global pressures and local realities” በሚል ርዕስ በታዳጊ ሀገራት ስላለው የምርምርና ዕውቀት ሁናቴ ምሁራዊ ማብራያ አቅርበውበታል፡፡
ከቅኝ ግዛት ዘመን ማብቃት ማግስት የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች በታሪካቸው ወርቃማውን ጊዜ ማሳለፍ ስለመጀመራቸው የተናገሩት ዶ/ር ደሞዜ ለዚህም አዳዲሶቹ ሀገራት ጠንክሮ ለመቆም ትምህርት ያለውን አስፈላጊነት በመረዳት በከፍተኛ ሁኔታ ለዩኒቨርሲቲዎቻቸው ድጋፍ ማድረጋቸውና ያደጉት ሀገራትም ለነበረው የቅኝ ግዛት ብዝበዛ መካሻ ይሆን ዘንድ ድጋፍ ማድረጋቸውን በምክንያትነት አስቀምጠዋል፡፡ ይህ ግን በአንፃሩ ጤናማ ዕድገት አልነበረም ያሉት ዶ/ር ደሞዜ ዩኒቨርሲቲዎቹ በምዕራባውያን ሀገራት ያሉ አቻዎቻቸውን ስርዓት ወደ እነርሱ ገልብጠው መጠቀማቸው አሁንም ድረስ የስርዓት እና ባህል ጥገኛ እንዳደረጋቸው ገልፀዋል፡፡ በሌላ በኩል በወቅቱ ሰፍኖ የነበረው ከፍተኛ የምሁራን ፍልሰት ሀገራቱ ያፈሯቸውን ምሁራን እንዲያጡ አድርጓቸዋል ብለዋል፡፡
ይህ ሁኔታ ግን በ1970 እና 80ዎቹ (እ.አ.አ) ላይ አፍሪካ የገባችበት የፖለቲካ አለመረጋጋት እና ዓለም አቀፉን የምጣኔ ሐብት መውደቅን ተከትሎ በመቀየሩ አፍሪካውያን ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ጨለማው ዘመናቸው ገብተዋል ብለዋል፡፡ ዓለም አቀፍ የምጣኔ ሐብት ወድቀቱ ከምዕራባውያን ይደረጉ የነበሩ ድጋፎችን ሲያስቆም በሀገር ቤት የነበረው የፖለቲካ ችግር እና ምሁራንን በጥርጣሬ ዓይን የመመለከት አባዜም ምሁራኑን ለእስር፣ ስደት እና ሞት መዳረጉን በገለፃቸው አስቀምጠዋል፡፡ ኋላ ላይም ስትራክቸራል አጀስትመንት ፕሮግራም ተብለው የሚታወቁት ከምዕራባውያን የቀረቡ የማሻሻያ ጥያቄዎች ትምህርት በግሉ ዘርፍ በኩል እንዲሆን መጎትጎቱና በትምህርት ዘርፉ ይደረግ የነበረው ኢንቨስትመንትም ከፍተኛ ትምህርት እና ምርምር ይልቅ ትኩረቱ በከፍተኛ ደረጃ ወደ መጀመርያ ደረጃ ትምህርት ማዞሩ አህጉሪቱ ላይ ጉዳት ማስከተሉን ጠቅሰዋል፡፡
አፍሪካውያን በዕውቀት ቅኝ ግዛት ውስጥ መሆናችን የተናገሩት ዶ/ር ደሞዜ ባደጉት ሀገራት የሚሰጡ የስኮላርሺፕ ዕድሎች ከበጎ ጎናቸው ባሻገር ያላቸውን ፖለቲካዊ እንድምታ እንዲሁም ዕውቀት የኃያልነት ምንጭ እንደመሆኑ ያደጉት ሀገራት በማደግ ላይ ያሉትን ከጥናት አጀንዳ መምረጥ አንስቶ በዕውቀቱ ላይ ቅኝ ግዛታዊ ቁጥጥር እስከማድረግ በደረሰ ሁናቴ ታደጊ ሀገራትን ከመድረኩ ሆን ብለው ስለማግለላቸው አብራርተዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪዎች ተሳታፊ በነበሩበት በዚህ መድረከ በዋናነት አሁን ያለውን ችግር ለመቅረፍ በሚያስችሉ መንገዶች ላይ ያውጠነጠኑ ጥያቄ እና አስተያየቶች ቀርበው በዶ/ር ደሞዜ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
This media is not supported in your browser
VIEW IN TELEGRAM
ዘመናዊ የመረጃ መያዣ ቴክኖሎጂዎች ሂደት
======================
በአሁኑ ጊዜ ዓለም ወደ አንድ የኢንፎርሜሽን መረብ በመጣበት ወቅት መረጃ የሰው ልጆችን የእለት ከእለት ተግባራቸውን ሚለዋወጡበትና የሚግባቡበት መሳሪያ እየሆነ ከመጣ ውሎ አድሯል፡፡ በተለይ በኢኮኖሚ በጣም የበለፀጉ አገሮች የመረጃ አያያዝ ስርዓታቸውን በማሻሻል ዌብ ቤዝድ (Web based) የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት መረጃዎችን ስርዓት ባለው መልኩ በማደራጀትና በማሰራጨት ኦንላይን (Online) አገልግሎተ በመስጠት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ማቀላጠፍ ችለዋል፡፡
በዚህ የመረጃ ማከማቻ እና መያዣ ቴክኖሎጂዎች ጋር በተያያዘ በአሁኑ ጌዜ ብዙዎቻችን መረጃዎቻችንን የት እንደምናስቀምጥ ግልፅ ቢሆንም የመረጃ መያዣ ቴክኖሎጂ መቼ ተፈለሰፈ የሚለው ጉዳይ እጅግ አስገራሚ ትንታኔ የሚቀርበበት ጉዳይ ነው፡፡ አንዳንድ የዘርፉ ሳይንቲስቶች እኤአ ከ1890 አንስቶ የመረጃ መያዣ ቴክኖሎጂዎች እየተፈጠሩ መምጣቻውን የሚገልፁ ቢሆንም አብዛኞቹ የሚስማሙበት ግን ከ1930ዎቹ በኋላ መፈልሰፋቸውን ነው፡፡
የመረጃ መያዣ መሳሪያዎች አሁን ላይ ከደረሱበት እጅግ የተራቀቀ የቴክኖሎጂ ደረጃ በፊት ቀደም ባሉት ጊዜያት እጅግ ረዥም የፈጠራ ሂደቶችን ያሳለፉ ሲሆን ከ1990ዎቹ አንስቶ ከፍተኛ መረጃ የመያዝ አቅም ያላቸው ቴክኖሎጂዎች በተለያየ ይዘት እና ቅርፅ መቅረብ ጀምረዋል፡፡ ከእነዚህ ወስጥ ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ ከሞከርን የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
SD Card
እኤአ በ1999 ተሰራ የሚባለው Secure Digital ወይም (SD Card) በቶሺባ፣ ሳንዲስክ እና ፓናሶኒክ በተባሉ የአሜሪካ ተቋማት ትብብር የተሰራ የመረጃ ማስቀመጫ መሳሪያ ሲሆን በስልኮች፣ በፎቶ ካሜራዎች እና በሌሎች ተንቀሻቃሽ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ላይ መገጠም የሚችል የዲጂታል መረጃዎች ማከማቻ ነው፡፡ ቴክኖሎጂው ግልጋሎት መስጠት በጀመረበት ጊዜያት ከ2 ጌጋ ባይት አንስቶ መረጃ የማስቀመጥ አቅም የነበረው ሲሆን፤ አሁን ላይ በከፍተኛ ልህቀት እስከ ሁለትና ከዛ በላይ ቴራ ባይት መረጃ የሚይዝ SD Card ተሰርቷል፡፡
USB Flash Drive
የመጀመሪያው ፍላሽ እኤአ በ2000 ስራ ላይ የዋለ ሲሆን በጊዜው በሲንጋፖር መቀመጫውን ያደረገ ድርጅት መረጃ የመያዝ አቅሙ 8 ሜጋ ባይት ብቻ የሆነ ድራይቭ ያቀርብ ነበር፡፡ ከዚህ ጊዜ አንስቶ ይህ የመረጃ ማከማቻ በተለያዩ የአለም ክፍሎች መመረት ከጀመረ በኋላ መረጃ የማከማች አቅሙ እና መረጃ የማስተላለፍ ፈጥነቱ በክፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መቷል፡፡ እንደአውሮፓውያኑ በ2013 ኪንግስተን የተባለ የቴክኖሎጂ ኩባንያ አንድ ቴራ ባይት መረጃ የመያዝ አቅም ያለው USB Flash Drive ይፋ ካደረገ በኋላ የቴክኖሎጂው እድገት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል፡፡
External hard Drive
ይህ የመረጃ መያዣ ቴክኖሎጂ ከኮምፒውተር ሲስተም ውጪ ከፍተኛ መጠን ያለው ፋይል የምናስቀምጥበት መሣሪያ ነው፡፡ External hard Drive ፋይሎችን ይዞ ከቦታ ወደ ቦታ ለመንቀሳቀስ የሚያስችል እና ከኮምፒውተራችን ጋር በዩኤስቢ /USB/፣ በፋየርዋየር /Firewire/ አማካኝነት ወይም በገመድ አልባ /wirelesely/ ሊገናኝ የሚችል ነው፡፡
Networked Attached Storage
ይህ ከአንድ በላይ የሆኑ ኮምፒውተሮች በኔትወርክ ተገናኝተው መረጃ የሚቀመጥበት ሥርዓት ሲሆን ይህም በስርዓት የተደረደሩ፣ ያልተደጋገሙ የፋይል ማከማቻ ኮንቲነሮችን እና በርካታ የዲስክ ድራይቭ አካላትን የያዘ ነው፡፡ ይህም በፍጥነት መረጃ ለማግኘት፣ በቀላሉ መረጃዎችን ለማስተዳደርና ለማስተካከል የሚያስችል ዘዴ ነው፡፡
Cloud Data Storage
በክላውድ መረጃዎችን ማስቀመጥ እኤአ በ2006 በአማዞን የተጀመረ ሲሆን በኔትወርክ አማካኝነት በመገናኘት መረጃዎቻችን ክላውድ ተብሎ በሚጠራ የመረጃ መጠባበቂያ ሥርዓት /Cloud Server/ ውስጥ የምናስቀምጥበት መንገድ ነው፡፡ ይህ የቴክኖሎጂ አይነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ በመምጣቱ እና ሌሎች የክላውድ መረጃ ማስቀመጫ አማራጭና የቴክኖሎጂ ድርጅቶችም በመስፋፋታቸው በነፃ እና በክፍያ የግለሰብ እና የተቋማትን መረጃዎችን ውሂብ (web) ላይ በማስቀመጥ ኢንተርኔት ካለበት ቦታ በየትኛውም ቦታ ሳንገደብ መረጃዎችን መጠቀም የሚቻልበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ በርካታ የክላውድ ማከማቻ ሥርዓቶች በበየነ-መረብ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን እነዚህም በነጻ ወይም በክፍያ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው፡፡ iCloud፣ Dropbox፣ Google Drive እና OneDrive የታወቁ የመረጃ ማከማቻ መንገዶች ናቸው፡፡
ምንጭ Frontierinternet እና Dataversity
የደህንነት ካሜራ የሰራዉ ታዳጊ
====================
በጋምቤላ የሚኖረው ሮቤል ፍቱቤ ከተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች በማዋቀር የሰራው የደህንነት ካሜራ ወንጀሎኞን ለማደን እና የወንጀል አደጋን ለመቀነስ ትልቅ እገዛ ያደርጋል፡፡ በአንዶሮይድ ስልክ አማካኝነት የሚሰራው ይህ የደህንነት ካሜራ ሶስት መቶ ስልሳ ዲግሪ መዞር እንዲችል የሪሞት ሴንሰር ቴክኖሎጂን የሚጠቀም ሲሆን ሌሎች እንደዲናሞ፣ የኤሌክትሪክ ገመድ እና ባትሪ የመሳሰሉ ቁሳቁሶችም በስራው ላይ እንደግብዓትነት ተጠቅሟል፡፡ የ12 ክፍል ተማሪ የሆነው ሮቤል ይህን የደህንነት ካሜራ ይበልጥ ለማሻሻል ብዙ ስራዎችን እየሰራ ሲሆን ከአንድሮይድ ስልክ በተጨማሪ በኮምፒውተሮች እና ሌሎች መገናኛዎች ላይ ቴክኖሎጂውን ለመተግበርም ትልቅ ፍላጎት እንዳለው ይናገራል፡፡ https://www.youtube.com/watch?v=aCHtMqScigE
ቴክ-ሳይንስ ሳምንታዊ የቴሌቪዥን ፕሮግራም
=============
እንደተለመደው በዚህ ሳምንትም ቴክ-ሳይንስ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽኑን ዓለም ጠልቀው ከሚያሳዩ አስተማሪ ዝግጅቶቿ ጋር ነገ በ10 ሰዓት በMOE TV ብቅ ትላለች፡፡
በነገው መሰናዶም፤
በዓብይ ፕሮግራማችን ባሳለፍነው ሳምንት በጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት ከሚሰሩ ስራዎች መካከል የአየር ላይ ቅየሳን እንዳስመለከትናችሁ ሁሉ በዚህኛው ሳምንት ደግሞ ጂ.ፒኤስን በመጠቅም የሚከናወነው የምድር ላይ ቅየሳን እናስቃኛችኋለን፤
በብላቴናት ኮቪድ-19ን ከመከላከል አንፃር የሰዎች ንክኪን የሚቀንስ ሮቦት ሰርቻለሁ ያለንን አንድ ታዳጊ ይዘናል፤
ካለፉት ሁለት ሳምንታት በቀጠለው የተመራማሪዎች ህይወት ታሪክ መሰናዶዋችንም ፕ/ር ምሩፅ ግደይ “በህይወቴ ለዚህ ለመብቃቴ ትልቁ ምክንያት መምህር መሆኔ”...“መምህር ለመሆኔ ደግሞ አባቴ ትልቁ ባለድርሻ ነው”....ሲሉ ከሰፊው የሕይወት እና ምርምር ጉዞዋቸው በጥቂቱ ያስመለክቱናል፤
በቴክኖሎጂ ታሪክ ዝግጅታችን ደግሞ በተለምዶ ኤር ኮንዲሽነር ብለን ስለምጠራው የአየር ማቀዝቀዣ ፈጠራ ስራ የምላችሁ ይኖረናል፤
በተቋማትም በህክምና እቃዎች ላይ ያለውን የጨረር ልኬት በሚሰራው ዶዚ ሜድ የቴክኖሎጂ ተቋም ዙርያ ያጠናቀርነው ሰዓቱን ጠብቆ ወደ እናንተው ይደርሳል፡፡
ያስታውሱ ነገ ቅዳሜ በ10 ሰዓት፤ እንዲሁም በድጋሚ ማክሰኞ በተመሳሳይ ሰዓት በMOE TV አየር ላይ እንውላለን፡፡ በሌላ አማራጭም የዩትዩብ ቻናላችንን ( https://www.youtube.com/channel/UC6jvUOLRSkVEQtc5Annfwvg/featured ) በመጎብኘት ሙሉ ዝግጅቱን ከቴሌቪዥን ስርጭት በኋላ ማግኘት ይችላሉ፡፡
ሀሳብ አስተያየትዎንም ለእኛው ማድረሱን እንዳይረሱ፡፡
ምስራቃዊ አውስትራሊያን ያመሰው ከፍተኛ የአይጦች ወረራ
===============
በምስራቃዊ አውስትራሊያ ኩዊንስ ላንድ እና ሳውዝ ዌልስ የተከሰተው የአይጦች ወረራ አካባቢው ላይ በአንድ ጊዜ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ አይጦች በየመንገዱ እና ቤቱ እንዲራወጡ ከማድረጉም በላይ ጥለውት የሄዱት ቆሻሻቸውን ለማፅዳት ብቻ ስድስት ሰዓታትን ወስዷል፡፡ በሌላ መልኩ ከወረራው ጋራ በተያያዘ ሦስት ሰዎች በአይጥ ተነክሰው ወደ ሆስፒታል ለማምራት በቅተዋል፡፡ አንድ ገበሬ እንደተናገረው ሁኔታው በአካባቢው ፈፅሞ አይተውት የማያውቁት አይነት ነው፡፡ በአይጦቹ ወረራ ሳብያ ሙሉ ማሳቸውን ያጡ ገበሬዎችም አሉ፡፡ አንድ የምግብ እና ሌሎች እቃዎችን መሸጫም በአንድ ምሽት ብቻ 600 ያህል አይጦችን መያዙን አስታውቋል፡፡
በአውትራሊያው ብሔራዊ የምርምር ተቋም ውስጥ በአጥኚነት የተሰማራው ስቲቭ ሄንሪ እንደሚለው ወረራው በአካባቢው የተገኘውን ከፍተኛ የእህል ምርት ተከትሎ የመጣ ነው፡፡ በቂ ምግብ እና መጠለያ የሚያገኙት አይጦቹ የመራባት ስራቸውን ቀደም ብለው እንደሚጀምሩትም ይናገራል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች ወረራውን ለመመከት በየቦታው ተጨማሪ ወጥመዶችን ሲያስቀምጡ በኩዊንስላንድ አቅራብያ የሚገኝ ገበሬ ደግሞ በድሮን አማካኝነት የአይጥ መርዝን በላያቸው ላይ ለማውረድ ፈቃድ ወስዷል፡፡ ታድያ እነዚህ ሁሉ ጥረቶች ቢደረጉም አይጦች ለመራባት አጭር ጊዜ የሚወስድባቸው ከመሆኑ አንፃር ወረራው ገና ጅማሬው ላይ ነው ሲሉ ገበሬዎቹ በመናገር ላይ ናቸው፡፡ እዚህ ላይ የደረሱ አይጦች በየ ሁለት ሳምንት ልጅ መውለድ መቻላቸውን ልብ ይሏል፤ ይህም በአንድ የመራብያ ወቅት ብቻ ጥንዶች እስከ 500 ህጻናትን መውለድ ያስችላቸዋል፡፡
የአይሮቹ ወረራ ከአውዳሚነትም ባሻገር ሌላው ይዞት የመጣው ስጋት የበሽታ ስርጭት ነው፡፡ አይጦች በዋናነት ከሚያሸጋግሯቸው ባክቴሪያዎች መካከል ሳልሞኔላ የተሰኙት በተበከለ ሽንት ወይም የአይጥ አር አማካኝነት በተጠቁ ምግቦች በኩል ወደ ሰዎች የሚተላለፉት በሽታ አምጪ ባክቴሪያዎች ይገኙበታል፡፡ ይህም የጨጓራ ህመምን (Acute Gastroenteritis) የሚያስከትል ነው፡፡
ምንጭ፤ Live Science
ደም ያነባችው ሴት
------------------
የወር አበባ ወቅቷ የደረሰ አንዲት ሴት የተለየ አይነት እንባን ማንባቷ ተዘግቧል፤ የደም እንባ፡፡ በ25ኛ ዓመት ዕድሜዋ ላይ የምትገኘው ይህች ሴት ከሁለቱም ዓይኖቿ የደም እንባዎች መውረዳቸውን ተከትሎ ወደ ድንገተኛ ክፍል ህክምና ያመራች ሲሆን መሰል ችግር ሲያጋጥማትም በሁለት ወራት ውስጥ ይህ ለሁለተኛ ጊዜዋ ነው፡፡
የደም እንባ ሂሞላክሪያ ተብሎ የሚጠራ እጅጉን አልፎ አልፎ የሚከሰት የጤና ችግር ነው፡፡ መነሻውም በተለያዩ ምክንያቶች ሊሆን ይችላል፡፡ የልጅቷ ግን ሁለቱም ዓይኖቿ ጤናማና ምንም አይነት ህመምም ሆነ ጉዳትን ያላስተናገዱ ቢሆኑም የወር አበባ ወቅቷ መድረሻ ጊዜውን እየጠበቀ ነው የሚወርደው፡፡ የወር አበባ አንዳንድ ጊዜ ቪካሪየስ ሜንስትሩዌሽን ተብሎ በሚታወቅ መልኩ በየወቅቱ ከማህፀን ውጪ መድማትን ሊያስከትል ይችላል፡፡ የልጅቷ የደም እንባዎችም ምናልባትም በሂሞላክሪያ እና ቪካሪየስ ሜንስትሩዌሽን ያልተለመደ ጥምረት ሳብያ የመጣ ስለመሆኑ በሪፖርቱ ላይ ተቀምጧል፡፡
ምንም እንኳን የልጅቷ የደም እንባ አሳሳቢ ቢመስልም ሀኪሞቹ በመረመሯት ጊዜ አይኖቿ ጤናማና የራስ ምታት፣ መደንዘዝ (dizziness) ወይም ከሌሎች የጤና እክሎች ጋር የተቆራኘ ምልክትም ሆኖ አልተገኘም፡፡ በተጨማሪም በአፍንጫ አካባቢ፣ የእንባ ትቦ፣ ወይም በራሱ በደሟ ውስጥ ስላለ ከተለምዶ ውጪ የሆነ ሁኔታ ምልክት ሆኖ አለመገኘቱን ጉዳዩን አስመልክቶ ጆርናል ላይ የወጣው ፅሁፍ ያሳያል፡፡
ብዙውን ጊዜ የደም እንባን የሚያመጡት የጤና እክሎች ማቃጠል፣አሰቃቂ ገጠመኝ፣ቁስለት እብጠት እና ከፍተኛ የደም ግፊት እንዲሁም ሌሎች በሽታዎች ናቸው፡፡ ታድያ ሀኪሞቹ ለልጅቷ የደም እንባ ምክንያቱ እነዚህ ሁሉ የጤና ችግሮቸ አለመሆናቸውን ካረጋገጡ በኋላ የችግሩ መንስኤ ቪካሪየስ ሜንስትሩዌሽን የተባለውና በአፍንጫ፣ ጆሮ፣ ሳንባ፣ የጡት ጫፍ፣ አንጀት ብሎም ቆዳ ላይ መድማትን የሚያስከትለው የጤና ሁናቴ መሆኑን ደምድመዋል፡፡ ልጅቷም ቢሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ደም ባለቀሰችበት ወቅት የአፍንጫ መንሰርም እያጋጠማት ስለመሆኑ ተናግራ ነበር፡፡
አንዳንድ የዓይን ህብረ ሕዋስ አይነቶች በሆርሞን ለውጥ ምክንያት ተፅዕንዖ ውስጥ ሲወድቁ ይታያል፡፡ ለምሳሌ የኮርኒያ እጥፋት እና ውፍረት በወር አበባ፣ እርግዝና እና ጡት ማጥባት ውስጥ ባሉ የተለያ ጊዜያት ውስጥ ሲለዋወጡ ይስተዋላል፡፡ ይህም በራሱ ልጅቷ ደም ለማልቀሷ ማብራርያ ሆኖ ሊቀርብ እንደሚችል በሪፖርቱ ተቀምጧል፡፡ ሀኪሞቹም በወሊድ መቆጣጠርያ መድሃኒቶች አማካኝነት ያከሟት ሲሆን ለሦስት ተከታታይ ወራትም የሆርሞን ህክምናን ስትከታተል ከቆየች በኋላ ዳግም የደም እንባን አላነባችም፡፡
ሀኪሞቹ ከዚህ ቀደም ሁኔታውን ሊያብራራ የሚችል ምንም አይነት የምርምር ፅሁፎች አለመኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡ የልጅቷ የደም እንባም በምን ምክንያት እንደተከሰተ እርግጥ በሆነ መልኩ ለመረዳትና መሰል ሁኔታንም በምን መልኩ በተሳካ ሁኔታ ለመከላከል እንደሚቻልም ለማወቅ እንዲያስችል ሌሎች ተጨማሪ ጥናቶች ሊደረጉ ይገባል ሲሉ አጥኚዎቹ ገልፀዋል፡፡
ምንጭ፤ Live Science
ከእፅዋት ጋር የሚያወራው አዲሱ የቴክኖሎጂ መሳሪያ
===========================
የምናሳድገውን ተክል ስለቅጠሎቹ ቀለም አልያም ስለ አበቃቀል ሂደቱ ጠይቀን መረዳት አንዳች ተዓምር ወይም የሳይንስ ልቦለድ ሊመስል ይችላል፡፡ ይሁንና አዲስ የቴክኖሎጂ ማሳሪያ ያበለፀገው የሲንጋፖር ዩኒቨርስቲ ይህን የሳይንስ ልቦለድ የሚመስል ነገር ወደ እውናዊው አለም የቀየረው ይመስላል፡፡
በሲንጋፖር መቀመጫውን ያደረገው ናንያንግ የቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ይፋ ያደረገው የምርምር ውጤት ከእፅዋቶች የኤሌክትሪክ ሲግናል በመቀበል እና በመስጠት በሚሰራው አዲስ የቴክኖሎጂ መሳሪያ አማካኝነት ሰዎች ከእእፅዋቶች ጋር እንዴት መግባባት እንደሚችሉ የሚሳይ ነው፡፡ ኔቸር ኤሌክትሮኒክስ እና አድቫንስድ ማቴሪያልስ በተባሉ አለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ የታተመው ይህ የምርምር ውጤት Venus flytrap በተሰኝ የእፅዋት ዝርያ ላይ አዲሱን ቴክኖሎጂ መሳሪያ እንደሞከረ ተገልጿል፡፡
ተመራማሪዎች ከእፅዋት የሚወጣውን የኤሌክትሪክ ሲግናል በትክክል ለመለካትና ለመረዳት ሞርፋብል (morphable) የተሰኘ ጄል መሰል ኤሌክትሮድ (electrode) ማበልጸግ የቻሉ ሲሆን፤ ይህም ከእፅዋቱ ስር ጋር በሚገባ ለመግባባት ያስችላል፡፡ ተመራማሪዎች Venus flytrap በተባለው እፅዋት ላይ ቴክኖሎጂውን ሞክረው ለመገንዘብ እንደቻሉት ከአጽዋቱ የሚወጣውን የኤሌክትሪክ ሲግናል ከመቀበል ባለፈ እፅዋቱ የእንቅስቀሴ ትእዛዞችን እንዲፈፅም የሚያስችል የመግባባት ሂደት ላይ መድረስ እንደሚቻል ከምርምሩ መረዳት ችለዋል፡፡
አዲሱ የቴክኖሎጂ መሳሪያ በተጠናከሩ ሁኔታ ከሌሎች የእጽዋት አይነቶች ጋር ለመግባባት የሚያሰችለውን ተጨማሪ ምርምር እያከናወኑ መሆናቸውን የሚናገሩት የጥናቱ መሪ ፕሮፌሰር ሎህ ዢያን ጁን ይህ የምርምር ውጤት በእፅዋት የኤሌክትሮ ፊዚዮሎጂ የትምህርት ዘርፍ ላይ አዲስ እይታ በመጨመር ከዚህ በኋላ ለሚሰሩ ከእፅዋት ጋር የተያያዙ ቴክኖጂዎች መልካም እድል እንደሚፈጥር ይናገራሉ፡፡ ተመራመሪዎች በአዲሱ መሳሪያ አማካኝነት አጠቃላይ የሰብሎችን የአበቃቀል ሂደት መቆጣጠር እና በሚለቁት የኤሌክትሪክ ሲግናል መሰረት የእፅዋቶችን የጭንቀት ምልክቶች ወይም ያልተለመዱ ነገሮች በጊዜ የመረዳት አቅም የሚኖራቸው ሲሆን ይህም ለወደፊቱ በአየር ንብርት