TechIn2
1.16K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
የቴፕ ካሴትን የፈጠረው ግለሰብ በ94 አመቱ አለፈ
======================
የኔዘርላንድ ተወላጁ ኢንጅነር ሉ ኦቴንስ ለሙዚቃ ባለውለታ የሆነውን የቴፕ ካሴትን በመፈልሰፍ ትልልቅ ፈጠራዎችን ከሰሩ ኢኖቬተሮች መካካል በቀዳሚነት ይመደባል፡፡ ቴክኖሎጀው እንደአውሮፓውያኑ ከ1960ዎቹ አንስቶ ግልጋሎት መስጠት ከጀመረ በኋላ በመላው አለም ከ100 ቢሊዮን በላይ የቴፕ ካሴት ምርት ሊሸጥ እንደቻለ ይነገራል፡፡
ኢንጅነር ሉ ኦቴንስ በ1960ዎቹ የቴፕ ካሴትን በሚያበለፅግበት ወቅት የፊሊፕስ ኩባንያ የምርት እድገት ዲፓርትመንት ዋና መሪ የነበረ ሲሆን በ1963 ቴክኖሎጂው በበርሊን የራዲዮ ኤሌክትሮኒክስ አውደ ርዕይ ላይ ቀርቦ ከታየ በኋላ በመላው አለም ዝናው እየናኘ ሄዷል፡፡ ኢንጅነሩ ኦቴንስ ከፊሊፕስ እና ሶኒ ካሉ ትልልቅ ኩባንያዎች ጋር በምርት ሽያጭ ዙሪያ ስምምነት ካደረገ በኋላ ይህን የቴክኖሎጂ ሞዴል፤ የፈጠራ ባለቤትነት መብት ሊያገኝብት ችሏል፡፡
ይህ የፈጠራ ሰው ከዚህ የካሴት ፈጠራው ባለፈ በተለምዶ የሲዲ ማጫወቻ ወይም (compact disk) ተብሎ በሚታወቀው የቴክኖሎጂ ፈጠራ ላይ ተሳታፊ የነበረ ሲሆን ይህ የቴክኖሎጂ ፈጠራም አገልግሎት መስጠት በጀመረበት እንደአውሮፓውያኑ ከ1982 አንስቶ በመላው አለም ከ200 ቢሊዮን በላይ ምርት ሊሸጥ ችሏል፡፡ አሁን ላይ ከቴክኖሎጂዎች መዘመን ጋር ተያይዞ እንደ ቴፕ ካሴት ያሉ ፈጠራዎች ቀድሞ በነበራቸው ልክ ግልጋሎት እየሰጡ ባይሆንም በውጪውም ይሁን በሀገራችን ታሪክ ለሙዚቃ አፍቃሪዎች እና ለራሱ ለሙዚቃ እድገት ትልቅ ውለታን ያደረጉ ግኝቶች ናቸው፡፡
እነዚህ እና ሌሎች ፈጠራዎችን ያበረከተው ኢንጅነር ሉ ኦቴንስ እንደአውሮፓውያኑ በ1926 ዱዜል በተባለች የኔዘርላንድ ከተማ የተወለደ ሲሆን፤ በተገኘባት ከተማ ከብዙ ፈጠረዎች እና ስራዎች በኋላ በ94 አመቱ ማክሰኞ ዕለት ህይወቱ ማለፉን ቤተሰቦች አስታውቀዋል፡፡
BBC
የሊቲየም አዮን ባትሪዎችን አቅም በሦስት ዕጥፍ የሚያሳድገው አዲስ ግኝት
========================
በሩስያው የሚሲስ ብሔራዊ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቱ የሚገኝ ዓለም አቀፍ የተመራማሪዎች ቡድን የሊቲየም አዮን ባትሪዎችን አቅም እና የአገልግሎት ዘመን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ የሚችል ግኝት ይፋ አድርገዋል፡፡ እንደ አጥኚዎቹ ከሆነ አሁን ላይ ባሉት የሊቲየም አዮን ባትሪዎች ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውለውን የግራፋይት ንጥረ-ነገር የሚተካ አዲስ የናኖ ቁስን አቀናብረዋል ወይም ሲንተሳይዝ አድርገዋል፡፡ የጥናት ውጤታቸውንም በጆርናል ኦፍ አሎይስ ኤንድ ኮምፓውንድስ ላይ አሳትመው አውጥተዋል፡፡
የሊቲየም አዮን ባትሪዎች ከስማርት ስልኮቻችን አንስቶ እስከ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ድረስ ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ እነዚህ ባትሪዎችን ቻርጅ የማድረግ ሂደቱ በሁለት ኤሌክትሮዶች ማለትም በኔጋቲቭ ቻርጅ ከሆነ አኖድ በፖዘቲቭ ቻርጅ ወደሆነ ካቶድ በሚደረግ የሊቲየም አዮኖች እንቅስቃሴ አማካኝነት ይከናወናል፡፡ የሊቲየም አዮን ባትሪዎች አገልግሎት ከቀን ወደ ቀን እያደገ ይሁን እንጂ ባትሪዎቹ ባላቸው የግራፋይት ይዘት ሳብያ አቅማቸው ላይ ይህ ነው የሚባል ትልቅ ለውጥ ሳይኖር መቆየቱን ተመራማሪዎቹ ያስረዳሉ፡፡ ታድያ የምርምር ቡድኑ ለአኖዶቹ የባትሪውን አቅም እና የአገልግሎት ዘመን ማሳደግ የሚችልን ቁስ ማግኘት ችለዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የፋንክሽናል ናኖሲስተምስ እና ሀይ ቴምፕሬቸር ማቴሪያልስ ዲፓርትመንት ውስጥ በረዳትነት የሚያገለግለው ይቭጊኒ ኮልስናይኮፍ እንደሚለው ማውጣት የቻሏቸው ባለ Cu0.4Zn0.6Fe2O4 ውህድ ወንፊታማ (Porous) ጥቃቅን የናኖ ቁሶችን እንደ አኖድ በመጠቀም አሁን ገበያ ላይ ካሉት ባትሪዎች በሦስት እጥፍ የላቀ አቅምን መስጠት ይቻላል፡፡ በተጨማም ለግራፋይቶች መተኪያነት ከሚቀርቡት አማራጮች በበለጠ ባትሪዎቹ ኃይላቸውን እየጨረሲ ቻርጅ የሚደረጉበትን ድግግሞሽንም በአምስት እጥፍ የሚያሰሳድግ መሆኑንና ይህ መሻሻልም ልዩ በሆኑ የናኖ ቁሶች እና ግልጋሎት ላይ በዋሉት ጥምር ንጥረ-ነገሮች ቅንጅት የመጣ ስለመሆኑ ይቭጊኒ ይናገራል፡፡
የማቀናበር ስራው የፓይሮሊሲስ ርጭት (Spray-Pyrolysis) መንገድን በመጠቀም የሚከወን በመሆኑም በውስጡ የተለያዩ ደረጃዎች ሳይኖሩት በአንድ እርምጃ ብቻ የሚካሄድ ነው፡፡ እንደ ተመራማሪዎቹ ማብራርያ ከልዩ የብረት አዮኖች የተጣመረ የኤኩየስ ውህድ በአልትራሳውንድ ረዳትነት ወደ ደመናነት የሚለወጥና በማስከተልም ከሜታል ሳልቶቹ ፍርስራሽ ጋር በመሆን ውሃው በ1200 ዲ.ሴ ሙቀት እንዲተን የሚደረግ ይሆናል፡፡ በውጤቱመም የሊቲየም አዮን ስርዓትን ለማንቀሳቀስ የሚያስፈልጉት ወንፊታማ ባለ ክብ ቅርፅ ጥቃቅኖች ተለይተው እንዲወጡ ይደረጋል፡፡
ምንጭ፤ Tech Xplore
አስደናቂው ሰዓሊ ሮቦት
============
ከቀናት በኋላ በሀገረ አሜሪካን ቴክሳስ ግዛት ውስጥ መካሄድ በሚጀምረው የሳውዝ ባይ ሳውዝዌስት ፎረም (SXSW) ከጃፓኑ የዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቶኪዮ የመጣ አንድ ለትርፍ ያልተቋቋመ ፕሮጀክት ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ተጠቅሞ ሥዕል በመሳል የሚያሳይ ሮቦትን ይዞ እንደሚቀርብበት ተነግሯል፡፡ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ተጠቅሞ የመሳል ፕሮጀክቱ ፈጠራን ከማሽኖች ጋር በማጣመር ሮቦቱ የቀለም መቀብያ ብሩሽ እና የሥዕል ሸራን አዋዶ ሥዕል የመሳል ጥበብን አጎናፅፎታል፡፡ ከያማሀ ጋር ባለ ትብብር እና ድጋፍ የተሰራው ሰዓሊው ሮቦት ከዩኒቨርሲቲው ተልከው በኤግዚቢሽኑ ላይ ከሚቀርቡት ስራዎች መካከል አንዱ ይሆናል፡፡
በሰው ሰራሽ አስተውሎት ሮቦት ፕሮጀክቶች ላይ እየሰራ ባለው የሱዙቭ ስታርታፕ ቡድን ውስጥ የፕሮጀክት መሪዋ ጂአሚን ፓን እንደምትለው ከሆነ የሮቦቱ አጠቃላይ ፅንሰ ሀሳብ ሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ የቁሳቁሶች በይነ-መረባዊ ትስስር (IOT)፣ ሮቦት እና ጥበብ ቅንጅት ላይ ያረፈ ነው፡፡ እንደ ጂአሚን ንግግር ይህን ሮቦት ከሌሎቹ ወደ ጥበብ ካጋደሉ ሮቦቶች ለየት የሚያደርገው ተስለው የተቀመጡ ምስሎችን ተመልክቶ ደግሞ ከመሳል ይልቅ በሚሰጠው መመርያ መሰረት የራሱን ሥዕል መሳሉ ነው.፡፡
ሰው ሰራሽ አስተውሎት እና ሮቦት የሰውን ልጆች አይነ ሕሊና መተካት ባይችልም እንኳን የሚያነሳሱ እና ወደ አዲስ አይነት ፈጠራ የሚመሩ ሊሆን ይችላል የምትለው ጂአሚን ብዙም ባልራቀ ጊዜ ውስጥ ከሰው ልጆች የተለየ አይነት ፈጠራን ይዘው የሚመጡ ልዩ ልዩ ፈጣሪ ሮቦቶችን የምናይበት እንደሚሆን ትናራለች፡፡
የሰው ሰራሽ አስተውሎት ሮቦቱ ሥዕሎቹን የሚስለው የሚሰጡትን የተለያዩ ሀሳቦችን ከተቀመጠለት የብሩሽ ሰረዝ ገደብ ጋር በማብቃቃት ነው፡፡ እንደ ጂአሚን ከሆነ የሚስለው ሥዕል ውስብስብነት ለሮቦቱ በሚሰጠው ትዕዛዝ ላይ የሚመሰረት ይሆናል፡፡ “ሮቦቱ 30 የብሩሽ ሰረዞችን ብቻ እንዲጠቀም የምንገድበው ከሆነ ወደ አብስትራክት የተጠጋ ጥበብን ሲፈጥር በአንፃሩ 300 የብሩሽ ሰረዞች ሲፈቀድለት በተሻለ ሕይወት ያለው ሥዕልን ይሰጠናል” ትላለች ጂአሚን፡፡
ቀጣን መስፍጠሪያ በመጫን ሰዓሊው ሮቦት በሸራ ላይ ሥዕሉን ሲያኖር መመልከት ትችላላችሁ >>> https://www.youtube.com/watch?v=dvbMJy1QspE
ምንጭ፤ Forbes
ቴክ-ሳይንስ ሳምንታዊ የቴሌቪዥን ፕሮግራም፤
================
በነገው ዝግጅታችን፤
በአብይ ፕሮግራም ፤ የአየር ላይ ቅየሳ
በብላቴናት፤ ከኮቪድ-19 የሚጠብቅ የባንክ ቤት ሶፍትዌር የሰራው ታዳጊ
የቴክኖሎጂ ታሪክ፤ ንፋስ ስልክ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ
በተቋማት፤ የሮኬት ቴክኖሎጂ
እንዲሁም በተመራማሪዎች ታሪክ በአ.አ ዩኒቨርሲቲ አክሊሉ ለማ ፓቶ ባዮሎጂ ኢንቲትዩት ውስጥ ተመራማሪ የሆኑትን ፕ/ር ምሩፅ ግደይን ሁለተኛ ክፍል ይዘንልዎ እንቀርባለን፡፡
እርስዎም ነገ ቅዳሜ በ10 ሰዓት MOE TV ላይ ይጠብቁን፤ ከአስተማሪ ዝግጅቶቻችን ለእርስዎም ሆነ ቤተሰብዎ ስንቅ የሚሆን ዕውቀትን ይገበዩበታል፡፡
ሳይሞላልዎት ቀርቶ ነገ ካመለጥዎም በዚሁ ቻናል ላይ ዕለተ ማክሰኞ 10 ሰዓት ሲደገም ያገኙታል፡፡ ይህም ካልሆነልዎ ወደ የዩትዩብ ቻናላችን (https://www.youtube.com/channel/UC6jvUOLRSkVEQtc5Annfwvg) ጎራ በማለት የዚህን ሳምንት ጨምሮ ከዓመታት በፊት ከተላለፈው የመጀመሪየው ክፍል አንስቶ ያሉትን ሁሉንም የቴክ-ሳይንስ ፕሮግራሞች አንድ በአንድ መመልከት ይችላሉ፡፡
በከፍተኛ መጠን እያሻቀበ የመጣው የመንታ ህፃናት መወለድ
===========================
መንትዮች ከየትኛውም ወቅት በላይ አሁን በዝተው እንደሚወለዱ በመላው ዓለም የተሰራ ጥናት አመላከተ፡፡ አጥኒዎቹ በዓለም ዙርያ ከ100 በላይ ሀገራት የወሰዱትን መረጃ በመመልከት ከአውሮፓውያኑ 1980 ዎቹ አንስቶ መንታ ሆነው የሚወለዱ ህፃናት ቁጥር እያሻቀበ መጥቶ አሁን ላይ በአማካኝ ከሚደረጉት 42 ውልጃዎች መካከል አንዱ የመንትዮች እንደሆነ ማወቅ ችለዋል፡፡ ንፃሬውም የዛሬ 40 ዓመት ከነበረው በአንድ ሦስተኛ አድጓል፡፡ ይህም ሲባል በየዓመቱ 1.6 ሚሊዮን መንትያ ህፃናት ይወለዳሉ እንደማለት ነው፡፡ አጥኚዎቹ ታድያ በቅርብ ዓመታት መረጃዎች ላይ በመመስረት አንዳንድ ሀገራት የመንትዮች ውልደት ጣርያን የነኩ አልያም ወደታች እያሽቆለቆሉ መሆናቸውን ተከትሎ ቁጥሩ ከዚህ በኋላ እያደገ እንደማይሄድና ይልቁንም የመንትዮች ጣርያ ላይ ስለመድረሳችን ይጠቁማሉ፡፡
መንትያ ህፃናት በሁለት መልኩ ይፀነሳሉ፤ አንደኛው እንቁላሉ ለሁለት ሲከፈል ተፀንሰው በመልክ እጅጉን የሚመሳሰሉ ህፃናትን ሆነው ሲሆን በአንፃሩ ግን ማህፀን ውስጥ ሁለት እንቁላሎችን በአንድ ጊዜ ሲጣሉና ሲፀነስ እንደሌላው ወንድምና እህት ያን ያህልም መልካቸውን ለመለየት የማያስቸግሩ መንትያዎች ሆነው ይወለዳሉ፡፡ አሁን ላይ ብዙዎቹ መንትያዎች የሚወለዱት እንደ እንቁላል መጨመር (Ovarian Stimulation) እና ከሰውነት ውጪ የወንድ ዘርን ከእንቁላል ጋር የማገናኘት ስልት (IVF) (ከጤና አኳያ በብዙ ሀገራት በማይበታታው በቤተ-ሙከራ ውስጥ ጭምር) ያሉትን የተዋልዶ ህክምናዎች ተከትሎ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ተመሳሳይ መልክ ያላቸው መንትያ ህፃናት ውልጃ በስፋት ያለባቸው ቦታዎች ብዙም ለውጥ ሳያሳዩ ቢቆዩም በተዋልዶ ህክምና ምክንያት የሚወለዱ መንትያዎች ቁጥር በመላው ዓለም እየጨመረ ይገኛል፡፡ ለዚህ ዕድገት ተቀዳሚ ምክንያቶቹ ከላይ የተጠቀሱት እና ሌሎችም የተዋልዶ ህክምናዎቹ ያላቸው ተደራሽነት መጨመር ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም መንታ ልጆችን የመውለድ ዕድል በሚጨምርበት ከ35 እስከ 39 ባለው ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚፀንሱ እናቶች መጨመርም ተጠቃሽ ነው፡፡
አጥኚዎቹ ከአውሮፓውያኑ 2010 እስከ 2015 ባሉት ዓመታት ውስጥ 99 በመቶውን የዓለም ህዝብ በሚይዙ 165 ሀገራት ላይ ያለውን የመትዮች ውልደት ምጣኔ መርምረዋል፡፡ ከነዝያ ውስጥም በ112ቱ ላይ በአውሮፓውያኑ ከ1980 እስከ 1985 ያለውን የውልጃ መረጃን መርምረዋል፡፡ በውጤቱ ማረገጋገጥ እንደቻሉት የመንታዎች መወለድ በዚያው በ1980ዎቹ ከነበረበት ከ1 ሺህ ውልጃዎች ዠጠኙ መንታ የመሆን ምጣኔ ወደ 12 አድጓል፤ ሁናቴው ከሀገር ሀገር የሚለያይ ቢሆንም፡፡ በዚህም ከፍተኛ ጭማሪን ያሳዩት ክፍለዓተ ዓለማት ሰሜን አሜሪካን (71 በመቶ)፣ አውሮፓ (60 በመቶ) እና እሲያ (32 በመቶ) ሆነው ተገኝተዋል፡፡ አፍሪካ ተፈጥሮአዊ በሆነ ሁኔታ ከሁለት የተለያዩ እንቁላሎች ከሚወለዱት መንትያዎች ውስጥ ከፍተኛው ድርሻ ሲኖራት ከእሲያ ጋር በመሆንም 80 በመቶውን መሰል የመንትያዎች ድርሻ ትይዛለች፡፡ ጥናቱ እንደሚጠቁመው ከሆነ ከደቡብ አሜሪካ በስተቀር የመንታዎች ቁጥር በሁሉም አህጉር ጨምሯል፡፡ አፍሪካም ሆነ ሰሜን አሜሪካን የመንታዎች ቁጥር ከ80 በመቶ በላይ ጭማሪ ቢያሳይም አፍሪካ ላይ የታየው ጭማሪ ግን ሙሉ በሙሉ ሊያስብል በሚያስደፍር መልኩ ከህዝብ ቁጥር ዕድገት ጋር በተያያዘ የመጣ ነው፡፡
ታድያ እንደ ባለሙያዎች ከሆነ ባደጉት ሀገራት ከተዋልዶ ህክምና ጋር ተያይዞ ሲያድግ የቆየው የመንትያዎች ቁጥር አሁን እየቀነሰ መምጣቱ ሀገራቱ የመንትያዎች ውልጃ ጣርያን ነክተው እየተመለሱ ስለመሆናቸው ማሳያ ቢሆንም እንደ እንቁላል መጨመር እና ከሰውነት ውጪ የወንድ ዘርን ከእንቁላል ጋር የማገናኘት ስልት ያሉት የህክምና ስልቶች በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት መስፋፋት መጀመራቸው (ባደጉት ሀገራት ባለው ልክ ባይሆንም) ስጋትን አጭሯል፡፡ በሌላ መልኩ ምንም እንኳን አብዛሀው ጤናማ ሆኖ የሚወለድ ቢሆንም መንታዎችን ማርገዝ አንድ ልጅ ከማርገዝ በላይ ለህፃኑም ሆነ እናትየው መንታ ካልሆኑት እርግዝናዎች አንፃር ከፍ ያለ ስጋትን የሚፈጥር መሆኑ ነገሩን በትኩረት እንዲታይ ያደርገዋል፡፡
ምንጭ፤ The Guardian
የፊታችን መጋቢት 12 ትልቅ አስትሮይድ ምድርን ተጠግቶ ያልፋል
*******************************
ናሳ በፈረንጆቹ መጋቢት 21 አንድ ትልቅ አስትሮይድ ምድርን ተጠግቶ እንደሚያልፍ ተናገረ፡፡ እንደ የህዋ ምርምር ተቋሙ መረጃ ከሆነ ትልቁ አስትሮይድ ከምድር 1.25 ሚሊዮን ማይሎች ያክል ይቀርባታል፡፡ ይህ አጋጣሚም ለተመራማሪዎች አስትሮይድን በቅርበት የመመልከት እድል ይፈጥርላቸዋል ሲል አሜሪካዊው የህዋ ምርምር ተቋም ተናግሯል፡፡ ተቋሙ አክሎም አስትሮይዱ ከ20 ዓመታት በፊት የተገኘ እና በመጠኑም 3000 ጫማዎች የሚያክል ዲያሜትር ይደርሳል ብሏል፡፡
ለመሬት ቅርብ የሆኑ ነገሮችን የሚያጠናው ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ፓውል ኮዳስ የዚህን 2001 FO32 ኦርቢታዊ መተላለፊያ በትክክል እናውቀዋለን ያሉ ሲሆን አስትሮይዱ ከ1.25 ሚሊዮን ማይሎች በላይ ወደ ምድራችን ሊቀርብ አይችልም ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡ ይህም በግርድፉ መሬት ከጨረቃ ካላት ርቀት 5.25 እጥፍ ያክል ማለት ነው፡፡ ምንም እንኳን አስትሮይዱ እንዲህ ባለ ርቀት መሬትን እንደሚያልፋት ቢነገርም ለአደጋ የሚያጋልጥ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡
ይህ አስትሮይድ በሰዓት 77 ሺህ ማይሎች ያክል እየተምዘገዘገ ያለ ሲሆን ከሌሎች አስትሮይዶች አንጻር ሲታይ በጣም ፈጣን እንቅስቃሴ ላይ ያለ ነው፡፡ አሁን ላይ ስለ አስትሮይዱ የታወቁት ነገሮች ጥቂት ሲሆኑ ወደ ምድር የበለጠ እየተጠጋ ሲሄድ ብዙ ነገሮችን መረዳት ይቻላል ሲሉ አንድ የናሳ ተመራማሪ ተናግረዋል፡፡
ናሳ እንደሚለው ከሆነ የስነ ፈለክ ተመራማሪዎች ስለ አስትሮይዱ ስሪትና መጠን ተጨማሪ መረጃዎችን ለማዎቅ ትልቅ ተስፋን ሰንቀዋል፡፡ ተቋሙ የፀሐይ ብርሃን አስትሮይዱን በሚያገኘው ጊዜ በአለቱ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ማዕድናት ሞገዶችን ሲውጡ አንዳንዶች ደግሞ ያንጸባርቃሉ ሲል ተናግሯል፡፡ እነዚህን ተንጸባራቂ ሞገዶች በመጠቀም ተመራማሪዎች በአስትሮይዱ ላይ የሚገኙ ማዕድናትን ምንነት መለየት እንደሚችሉ የምርምር ተቋሙ አስገንዝቧል፡፡
አስትሮይዱንም በደቡባዊ ንፍቀ ክበብ እንዲሁም በሰሜናዊ ዝቅተኛ አካባቢ ሲያልፍ መካከለኛ ቴሌስኮፕን በመጠቀም መመልከት ይቻላል ሲል ናሳ ተናግሯል፡፡ ይህንንም ለማድረግ የኮከብ ቻርትን መጠቀም አስፈላጊ ነው፡፡
ምንጭ PHYS.ORG
ቴክኢን-ወግ
======
በየጊዜው ወሳኝ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ተኮር ሙያዊ ብሎም ሀገራዊ ጉዳዮች ተነስተው ዳሰሳ የሚደረግበት የቴክኢን-ወግ ዝግጅታችን በመጪው ሐሙስ መጋቢት 9፤ 2013 ዓ.ም የሚመለስ ይሆናል፡፡ በዚህ ሳምንቱ ዝግጅታችን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢጁኬሽናል ፕላኒንግ እነ ማናጅመንት ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ዶ/ር ደሞዜ ደገፋ “why research incapacity the global south: the vicious circle of global pressures and local realities” በሚል ርዕስ ገለፃ ያቀርባሉ፡፡ በዕለቱ ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ጀምሮ አራት ኪሎ በሚገኘው የቴክኖሎጂ እና ኢኖቨቬሽን ኢንስቲትዩት ዋና ፅ/ቤት በሚገኘው የስብሰባ አዳራሽ በሚካሄደው በዚህ መድረክ የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪዎች እና ልዩ ልዩ ባለሙያዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑበት ይጠበቃል፡፡
በተጠቀሰው ርዕሰ-ጉዳይ ገለፃውን የሚያቀርቡት ዶ/ር ደሞዜ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ፖሊሲ እና አመራር በረዳት ፕሮፌሰርነት እያገለገሉም ሲሆን በ transnational knowledge transfer; academic career development, policy borrowing, lifelong learning; qualitative studies እና ሌሎችም ዘርፎች ላይ ጥናት የሚያደርጉ ምሁር ናቸው፡፡
አማዞንና እየተባባሰ ያለው የአየር ንብረት ለውጥ
****************************
በአለማችን ካሉት ጥቅጥቅ የደን ሀብቶች መካከል አማዞን አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ደን ለብዙ ችግሮች እየተጋለጠ በመሆኑ የአየር ንብረት ለውጥን እያፋጠነ እንደሆነ እየተነገረለት ነው፡፡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት አማዞን ለከፍተኛ ጭፍጨፋ ተጋልጧል፡፡ 30 የሚደርሱ ተመራማሪዎች በተሳተፉበት ጥናት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው የደኑ ሁኔታ የምድራችንን ከባቢ አየር እያሞቀውና ለከፋ ሁኔታ እየዳረገው እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡
ይህ የምድራችን የካርቦን ማከማቻ የሆነ ስፍራ በሰዎች ምክንያት ከፍተኛ የሆነ ጫና እየደረሰበት ነው፡፡ ለወትሮው ይህ ጫካ በተለያዩ ምንያቶች የሚለቀቅን ካርቦን ከከባቢ አየር ላይ በመሰብሰብ የአለማችንን ሙቀጥ በማስተካከል የሚታወቅ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ግን ከዚሁ ጫካ የሚለቀቀው ካርቦን ተጽእኖው እያየለ እንደሆነ ተመራማሪዎች ጠቁመዋል፡፡
በዚህ ጫካ ላይ የተሰሩ ስነ ምድራዊና ስነ-ህይወታዊ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የደን መመናመኑ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ እስከ 2035 ጫካው ከሚሰበስበው የካርቦንዳይ ኦክሳይድ መጠን ይልቅ የሚያመነጨው ሊልቅ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ በአካባቢው ያለው ህገወጥ የመሬት ምንጠራና ወረራ ችግሩን እያፋጠነው እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡
ካርቦንዳይ ኦክሳይድ ለአየር ንብረት ለውጥ ብቸኛ ተጠያቂ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታው ውስጥ በአለማቀፍ ደረጃ የልቀጥ መጠናቸው እየጨመረ የመጡት ናይትረስ ኦክሳይድና ሜቴን ጋዝ በአማዞን በተሰራውም ጥናት የተገኘው መረጃ የሚያመለክተው የሁለቱ መጠን በአካባቢው እየጨመረ መምጣቱን ነው፡፡ ሁለቱ ጋዞች ከካርቦንዳይ ኦክሳይድ በበለጠ 300 እጥፍ ሙቀትን ሰብስቦ የመያዝ አቅም አላቸው፡፡
ምንጭ Science Alert
በግርግዳዎች አሻግሮ ማየት የሚያስችለው ወታደራዊ መነፅር
=========================
ከዚህ በኋላ ዘመናነዊው ጦርነት በሰዎች መካከል የሚደረግ ጦርነት አይመስልም፤ በየጊዜው አየተፈለሰፉ ባሉ ቴክኖሎጂዎች መካከል እንጂ፡፡ ከሀገራት የቴክኖሎጂ መራቀቅ ጋር ተያይዞ በየዘርፉ የሚታዩት የቴክኖሎጂ ምጥቀቶች በውትድርናው ዘርፉም በስፋት እየታዩ ይገኛል፡፡ ከሰሞኑ በአሜሪካ የጦር ድርጅት ይፋ የተደረገው የጦር ቴክኖሎጂም በአለማችን ላይ በዘርፉ ከታዩ የቴክኖሎጂ ልህቀቶች እንደ አንዱ ይመደባል፡፡
በአሜሪካ ወታደራዊ ተቋም የበለፅገው አዲሱ ቴክኖሎጂ Integrated Augmented Vision (IAVS) በተባለ ሲስተም አማካኝነት የሚሰራ ወታደራዊ መነፅር ሲሆን በቅርበት በሚካሄዱ የውጊያ አይነቶች ላይ በመዋል ወታደሮች በግርግዳዎች አሻግረው ማየት እንዲችሉ፣ በዙሪያቸው ምን አየተከሰተ እንዳለ እንዲረዱ እና የውጊያ ስልቶችን ከዲጂታል ካርታ ምስሎች ጋር አጣምረው አንዲመለከቱ የሚያግዛቸው ነው፡፡
በጦር ውጊያ ውስጥ ሁኔታዊ ግንዛቤ ወይም (situational awareness) እጅግ መሰረታዊ ከመሆኑ አንጻር ወታደሮች በአደገኛ ቦታዎች ላይ ምን እየተፈጠረ እንዳለ በቀላሉ ለመመልከት እንዲችሉ አዲሱ ቴክኖሎጂ ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ የሚናገሩት ፊሊፕ ባርቴል፤ ያሉበትን የደህንነት ቀጣና ሳይለቁ ኢላማቸውን በትክክል እንዲተገብሩ እና ሌሎች ተያያዥ ግዳጆችን በብቃት ለመፈፀም እንዲችሉም ቴክኖሎጂው ትልቅ እገዛ እንደሚኖረው ይናገራሉ፡፡
ይህ ወታደራዊ መነፅር በተገጠሙለት ስማርት ካሜራዎች አማካኝነት በአውደ ውጊያው ዙሪያ ያሉ የበስተኋላ እና የዳር እይታዎችን ለወታደሮች በሚገባ የሚያቀርብ ሲሆን በጨለማ ሰዓትም እየሆነ ያለውን ነገር ለመመልከት የሚቸገር አይደለም፡፡ በመሰረታዊነት በእግረኛ የውጊያ ስልት ላይ ይተገበራል ተብሎ የሚጠበቀው የ IAVS ወታደራዊ መነፅር ከላይ የተጠቀሱትን ዋነኛ ጥቅሞች ለወታደሩ በመስጠት የውጊያ አቅምን በብዙ መልኮች እንደሚያሻሽል ተነግሮለታል፡፡
ምንጭ inceptivemind
በኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት በከፍተኛ ተመራማሪነት ሲያገለገሉ የቆዩት ዶ/ር ገነነ ተፈራ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ
ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ በተለያዩ የሀገራችን የምርምር ተቋማት ውስጥ በተመራማሪነትና ኃላፊነት ሲያገለግሉ የቆዩት ዶክተር ገነነ ተፈራ ከትናንት በስትያ ዕሁድ መጋቢት አምስት ነው ባደረባቸው ድንገተኛ ህመም በሞት ያጣናቸው፡፡
ከአቶ ተፈራ በልሁና ከእናታቸው ወ/ሮ አልማዝ ተፈራ ህዳር 12 1955 ዓ.ም በአርሲ ሮቤ የተወለዱት ዶ/ር ገነነ የአንደኛና መለስተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአርሲ ቡልቡላ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤትና በአርሲ ሮቤ ሳህለ ሥላሴ መለስተኛ ደረጃ ት/ቤት ተምረዋል፡፡ የ2ኛ ደረጃና ኮምፕሪሄንሲቭ ትምህርታቸውን አርሲ ሮቤ ዲዳአ 2ኛ ደረጃ ት/ቤትና አርሲ አሰላ ኮምፕሪሄንሲቭ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተምረዋል፡፡ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም በቺኮዝላቫኪያ ብሩኖ ዩኒቨርሲቲ 1975 ዓ.ም. እስከ 1981 ዓ.ም. በመከታተል በቬተርነሪ ሳይንስ የዶክተርነት ዲግሪ ያገኙት ዶ/ር ገነነ በድጋሚ በዚያው በቼክ ብሩኖ ኢንስቲትዩት ኦፍ ማይክሮ ባዮሎጂ ኤንድ ኢሚዩኖሎጂ ፋክልቲ ቬተርነሪ ሜዲሲን ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቬተርነሪ ኤንድ ፋርማሴዩቲካል ሳይንስ 1991 ዓ.ም. እስከ 2002 ዓ.ም. በማይክሮ ባዮሎጂ ኤንድ ኢሚዩኖሎጂ ፒኤችዲ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡
ከውጭ ሀገር የትምህርት ቆይታ በኋላ ወደ ሀገራቸው በመመለስም ከ1982 አንስቶ ህይወታቸው እስካለፈበት ዕለት ድረስ በግብርና ሚኒስቴር ስር ባሉ የተለያዩ የምርምር ተቋማት እንዲሁም ያለፉት 18 ዓመታትን በደቂቀ አካላት ብዝሀ ሕይወት ላይ ከተባባሪ ተመራማሪነት እስከ ከፍተኛ ተመራማሪነት በቆዩበት የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት አገልግለዋል፡፡ በነዚህ ዓመታት የምርምር ቆይታቸውም በግልና ከባልደረቦቻቸው ጋር በመቀናጀት ከ35 በላይ የምርምር ስራዎችንን በሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ደረጀ ያሳተሙ ሲሆን በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችም የድህረ ምረቃ ተማሪዎችን ሲያማክሩ ቆይተዋል፡፡
ዶ/ር ገነነ ተፈራ ከባለቤታቸው ወ/ሮ የሺ ፀጋዬ አንድ ወንድ እና አንድ ሴት ልጆችን አፍርተዋል፡፡
በዶ/ር ገነነ ሞት የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እየገለፅን ለመላው ቤተሰቦቻቸው እና የሙያ አጋሮቻቸው መፅናናትን እንመኛለን፡፡
ዘንድሮም ያልረገበው የሁዋዌይ እና አሜሪካን መቃቃር
=======================
ባሳለፍነው ዓርብ የአሜሪካን ተቆጣጣሪ ባለስልጣናት ሁዋዌይን ብሔራዊ የደህንነት ስጋትነት ዝርዝር ውስጥ በማስቀመጥ ከሰሞኑን ተስፋ ተጥሎበት በነበረው የተስፋ ጭላንጭል ላይ ቀዝቃዛ ውሃን ቸልሰውበታል፡፡ ከሁዋዌይ በተጨማሪም የብሔራዊ ደህንነት ስጋት ናቸው ተብለው ከተቀመጡት ሌሎች ተቋማት መካከል ዜድቲኢ፣ ሃይቴራ ኮምዩኒኬሽንስ፣ ሀንግዦ ሂክቪዥን ዲጂታል ቴክኖሎጂስ እና ዳሁአ ቴክኖሎጂ ይገኙበታል፡፡ እርምጃውን ቀድሞ ከተሰሩት ለሀገሪቱ ስጋት የሚሆኑ የኮምዩኒኬሽን መሳርያዎችን የመጠቀም ስህተቶች የተማረና በኮምዩኒኬሽን መረባችን ላይ ዳግም አመኔታን የሚመልስ ነው ሲል የፌደራል ኮምዩኒኬሽን ኮሚሽን እርምጃውን ገልፆታል፡፡
ባሳለፍነው ወር የሁዋዌይ መስራች እና ዋና ስራ አስፈፃሚ ሬን ጃንግፌ ኩባንያቸው በቀድሞው የአሜሪካን ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በተላለፈበት ማዕቀብ መጎዳቱን ተከትሎ አዲሱ ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን ማስተካከያዎች እንዲያደረጉ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡ ኩባንያው በተለይ በምዕራቡ ዓለም እንደ ደህንነት ስጋት ተፈርጆ ጫና ውስጥ ቢገኝም ዋና ስራ አስፈፃሚው ሁዋዌይ የመቋቋም ኃይሉ ማደጉን ተናግረዋል፡፡ የአሜሪካን ኩባንያዎች እንደ ሴሚኮንዳክተር ያሉ የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን ለሁዋዌይ እንዳይሸጡ መታገዳቸው ተፅዕንዖን ባሳደረበት በዚህ ሰዓት አስተያየቱን የሰጡት ሬን ጃንግፌ ድርጅታቸው አሁንም ከአሜሪካን ኩባንያዎች ጋር ለመገበያየት ፍላጎት እንዳለውና ይህም ሁሉንም ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
በአውሮፓውያኑ 1987 የተመሰረተው ሁዋዌይ የዓለማችን ቀዳሚው የቴሌኮም ግብዓቶች እና ተንቀሳቃሽ ስልክ አምራች እስከሚሆን ከውጭ ሀገር መንግስታት ተፅዕንዖ ሳይደርስበት ቆይቷል፡፡ ታድያ ይህ የተለወጠው የቀድሞው የአሜሪካን ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገራቸው ከቻይና ጋር ያላት የንግድ ግንኙነት በሻከረበትና ወደ ንግድ ጦርነት በገቡበት ሰዓት ኩባንያውን በኢላማቸው ውስጥ ሲያስገቡት ነበር፡፡ የ49 ዓመቷ የሬን ጃንግፌ ልጅ እና የኩባንያው ሀላፊ ሜን ዋንጆውም የንግድ ምስጢሮችን በመስረቅ እና አሜሪካን በኢራን ላይ የጣለችውን ማዕቀብ ተላልፋ የሴራ እና ማጭበርብር ወንጀሎችን ፈፅማለች በሚል በአሜሪካን የሕግ ሰዎች ክስ አጋጥሟታል፡፡
ምንጭ፤ Tech Xplore
የ 2,000 ዓመት ዕድሜ ያለው የመጀመሪያው ኮምፒውተር
--------------------------------------------
ከ120 አመታት በፊት ተመራማሪዎች እጅግ በጣም ሚስጥራዊ ከሆኑት የአርኪኦሎጂ ግኝቶች አንዱ የሆነውን አንቲኪቴራ ሜካኒዝም (Antikythera Mechanism) የተሰኘ በእጅ የሚሰራ ጥንታዊ የግሪክ መሣሪያ በሜዲትራኒያን ባህር ውስጥ ባለ የአንቲኪቴራ ደሴት አገኙ፡፡ ከዚህ ጊዜ አንስቶ በዚህ ሚስጥራዊ መሳሪያ ላይ ብዛት ያላቸው ምርምሮች ከተደረጉ በኋላ እንደአውሮፓውያኑ በ2008 በተሰራ ጥናት መሳሪያው በጊዜው ለነበሩ የግሪክ መሃንዲሶችና ፈላስፋዎች የፀሐይ፣ የጨረቃ እና የሌሎች የሰማይ አካላት አቀማመጥን እና እንቅስቃሴን ለመለካት የሚያገለግል ሜካኒካል መሳሪያ እንደነበር ሲገለፅ ቆይቷል፡፡ የአሰራር ይዘቱ በዛ ዘመን ይፈጠራል ተብሎ የማይታሳበው ይህ ውስብስብ የእጅ ስራ ተመራማሪዎች ካገኙበት ውጤት ተነስተው በጊዜው ለነበሩ ፈላስፋዎች ጊዜን መለካት የሚችል የአስትሮኖሚ ካልኩሌተር እና የመጀመሪያው የአናሎግ ኮምፒውተር ሊባል እንደሚችልም ገልፀዋል፡፡
እንደአውሮፓውያኑ በ1900 በግሪክ ደሴት አንቲኪቴራ አቅራቢያ በሰመጠ ጥንታዊ መርከብ ተገኘ የሚባለው ይህ ሚስጥራዊ መሳሪያ የተሟላ አካሉን በቦታው ማግኘት ባይቻልም ውስብስ የጊር ስርኣቱ እና አስደናቂ ንድፉ ተመራማሪዎችን ለብዙ ዘመናት ምርምር እንዲያደርጉበት የጋበዘ ምክንያት ነበር፡፡ ይህ የምርምር ፍላጎት አሁን እስካለንበት ጊዜ ድረስ ዘልቆ ተመራማሪዎች የዚህን መሳሪያ አሰራር በሚገባ ለመረዳት እና አጠቃላይ ግልጋሎቱን ለማወቅ አሱን የሚመስል መሳሪያ የ3ዲ ቴክኖሎጂን በመጠቀም እንዲያበለፅጉ አነሳስቷቸዋል፡፡
በለንደን ግሎባል ዩኒቨርስቲ መቀመጫቸውን ያደረጉት እነዚህ ተመራማሪዎች አካላዊ ገፅታው ከጥንቱ መሳሪያ ጋር የሚመሳሰለውን ረፕሊካ (replica) በ3D የኮምፒውተር ሞዴሊንግ በመጠቀም እያበለፀጉ ሲሆን፤ ዘመናዊ ቁሶችን ተጠቅመው የሚሰሩት ተመሳሳይ መሳሪያም የአንቲኪቴራ ሜካኒዝም ሚስጥራዊ አሰራርን በተወሰነ መልኩ እንዲረዱ ያስችላቸዋል፡፡ ተመራማሪዎች እንደሚሉት በዚህ ተመሳሳይ መሳሪያ አማካኝነት በአንቲኪቴራ ሜካኒዝም ላይ በጥንቷ ግሪክ በስፋት የሚታወቁትን የሜርኩሪ፣ ቬነስ፣ ማርስ፣ ጁፒተር እና ሳተርን እንቅስቃሴዎች መለካት እንደሚችል የታወቀ ሲሆን ሌሎች የፀሃይ እና የጨረቃ ግርዶሽ ከስተቶችን ለማወቅም የጥንቱ መሳሪያ ያገለግል እንደነበር ከአምሳያው መሳሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡
የአርኬኦሎጂ ጥናቱን ሲያደርጉ በነበሩ የበፊት ተመራማሪዎች ሲገለፅ እንደነበረው ምስጢራዊው መሳሪያ ከ120 አመት በፊት በግሪክ ሲገኝ የተሟላ አካሉ ሳይሆን የመሳሪያው አንድ ሶስተኛ አካል የተገኘ በመሆኑ ሙሉ ለመሉ የጊር ስርኣቱን እና አካለዊ ንድፉን መቅዳት እንዳልተቻለ የሚናገሩት የምርምሩ መሪ ፕሮፌሰር ቶኒ ፍሪዝ አሁን ላይ ከሌሎች የታሪክ ማስረጃዎች እና መፅሃፍቶች ጋር በማጣመር የመሳሪያውን የጂዮሜትሪ ንድፈ-ሀሳባዊ ልህቀት ብቻ መመርመር እንደተቻለ ይነገራሉ፡፡ በቀጣይ ጊዜያት ከጥንቱ መሳሪያ ጋር ይበልጥ የሚመሳሰል ግብዓት በመጠቀም እና ሰፊ ምርምር በማድረግ የመሳሪያውን አምሳያ በተሻለ ሁኔታ ለመስራት እንደታሰበ የሚናገቱት እኝህ ተመራማሪ ከዛሬ 2,000 አመት በፊት እንዲህ አይነት የምህንድስና ጥበብ መሰራቱ ለማመን የሚከብድ ነው ይላሉ፡፡
ባለሙያዎች እንደሚሉት ኮምፕዩተር ማለት ማንኛውንም ኢንፎርሜሽን ፕሮሰስ የሚያደርግ ማሽን ወይም ማሰሪያ ሲሆን ይህንም የሚያደርገው በተርታ የተቀመጡ ትዕዛዞች በመፈጸም ነው። ለብዙ ሰዎች ኮምፒዩተር ሲባል ዐዕምሯቸው ላይ የሚመጣው የግል (ፐርሰናል) ኮምፒዩተር ነው። ነገር ግን ኮምፒዩተር ሲባል ከላፕቶፕ፣ ዴስክቶፕ፣ ማይክሮ-ኮምፒዩተር እና ሱፐር-ኮምፒዩተር በተጨማሪ ካልኩሌተር ፣ዲጂታል ካሜራ እና ሌሎች ትእዛዝ ፈፃሚ መሳሪያዎችም በኮምፒውተር ውስጥ ሊጠቃለሉ የሚችሉ መሳሪያዎች ናቸው፡፡
ምንጭ፡ Livescience እና Theengineer