TechIn2
1.16K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
ታላቁን ግፊት የተቋቋመችው ሰው ሰራሽ ዓሣ
=========================
አነስተኛ መጠን ያላት የሲሊኮን ሮቦት እጅግ ጠንካራ ከሆኑት በቀር ማንኛቸውንም ቁሶች ጨፈላልቆ የሚያስቀር ከፍተኛ ግፊት ባለበት የማሪያና ቦይ ወይም ማሪያና ትረንች ውስጥ 10,900 ሜትር ቁልቁል በመስጠም ምንም ሳትሆን ለመውጣት ችላለች፡፡ በቻይናው ሾሻንግ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በጉሮኢ ሊ የሚመራ የጥናት ቡድን በአንፃራዊ ጫናን የማይችል ለስላሳ አካል ያላቸው ግን ደግሞ በባሕር ውስጥ እጅጉን ጠልቀው ከሚኖሩ የዓሣ ዝርያዎች መካከል በሆነችው የስኔል ዓሣ ላይ በመንተራስ ነው የሮቦቷን ንድፍ የሰራው፡፡ ዓሣዎቹ ከዚህ ቀደም ከባሕር ጠለል በታች እስከ ስምንት ሺህ ሜትር ድረስ ጠልቀው ሲዋኙ ታይተው ነበር፡፡
ባሕር ሰርጓጅ ሮቦቷ ከማንታ ሬይ ዓሣ በሚመሳሰል መልኩ የ22 ሴንቲሜትር ርዝማኔ እና የ28 ሴንቲሜትር የክንፍ ስፋት ያላት ናት፡፡ ሮቦቷ በሲሊኮን ጎማ የተሰራች ሲሆን በውስጧ ያሉት የኤሌክትሮኒክ ግብዓቶቹም እንደሌሎቹ ባሕር ሰርጓጆች በአንድ ሰርኪውት ቦርድ ላይ ከመቀመጥ ይልቅ በአካሏ የተለያየ ክፍል ውስጥ ተሰራጭተው ያሉና በገመዶች የተሳሰሩ ናቸው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ የጥናት ቡድኑ ባደረገው ሙከራ ከፍተኛ ግፊት ውስጥ በሚኮንበት ጊዜ በጠንካራ ሰርኪውት ቦርድ ላይ ያሉት ትስስሮች የባህር ሰርጓጁ ስስ ብልት ሆነው እንደሚገኙ በማወቃቸው ነው፡፡
ሮቦቷ በውሃ ውስጥ ልክ በስኔል ዓሣ ላይ እንዳሉት ፊኖች ሆነው የሚያገለግሉ ግን ደግሞ የኤሌክትሪክ ከረንት በሚኖር ጊዜ ከሚሰበሰቡ ኤሌክትሪክ አስተላላፊ ፖሊመሮች በተሰሩ ሰው ሰራሽ ጡንቻዎች አማካኝነት የሚንቀሳቀሱ ሁለት ተርገብጋቢ ክንፎቿን በመጠቀም ነው የምትጓዘው፡፡ ይህም ፊኖቹን በ6.3 ዲግሪ የሚያንቀሳቅስና ሮቦቷንም በውሃው ውስጥ እንድትጓዝ የሚያስችል ነው፡፡
እጅግ ጥልቅ የሚባሉትን የባህር ክፍሎች ለመዳሰስ ታስባ የተሰራችው ይህች ሮቦት ለወትሮ ለትልልቆቹ ባሕር ሰርጓጅ መርከቦች ብቻ ይተው በነበረው የዓለማችን ዝቅተኛው የውቅያኖስ ወለል ማሪያና ቱቦ ተሞክራ በስከኬት ማጠናቀቅ ችላለች፡፡ ታድያ ወደ ፊትም ቀልጣፋና ቀላል ክብደት ያላቸው ባህር ሰርጓጅ መርከቦችን ለመገንባት መሰረት እንደምትሆን ተነግሮላታል፡፡
ሮቦቷ በገመድ ሳትታሰር ባደረገቻቸው ሙከራዎች ወቅት 3224 ሜትር ጥልቀት ባለው የደቡብ ቻይና ባህር ክፍል ውስጥ በሴኮንድ እስከ 5 ሴ.ሜ ፍጥነት መዋኘት ችላ ነበር፡፡ የጥናት ቡድኑ በቀጣይም የኮቪድ-19 ክልከላዎች ከተነሱ በኋላ በማሪያና ቱቦ ላይ ተመሳሳይ ሙከራዎችን በሮቦቷ ላይ ለማድረግ አቅዷል፡፡
ምንጭ፤ New Scientist
ሲጠበቅ የነበረው የዕቁብ መተግበሪያ ለተጠቃሚዎች ይፋ ሆነ
=========================
በሀገራችን “ሰውን ሰው ያደረገው እቁብ ነው” እስከሚባል ድረስ ከምጣኔ-ሐብታዊና ማህበራዊ ህይወታችን ጋር በጥብቅ የተሳሰረው ዕቁብ ለብዙዎች የስራ መጀመሪያ፣ ጎጆ መቀለሻና ወደ እድገት መወጣጫ ሆኗል፡፡ አሁን ላይ ታድያ ይህ የኢትዮጵያ ባህላዊ የቁጠባ ዘዴ የሆነው እቁብን ለማዘመን ታልሞ በእቁብ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂስ የተሰራው መተግበሪያ ለተጠቃሚዎች ይፋ ሆኗል፡፡ ከሳምንት በፊት በገጉግል አፕ ስቶር ላይ እንዲቀመጥ የተደረገው መተግበሪያው በእስካሁኑ ቆይታው ከ500 ጊዜ በላይ ዳውንሎድ ለመደረግ በቅቷል፡፡
የእቁብ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂስን ከአሌክሳንደር ህዝቂያስ ጋር በመሆን የመሰረተችውና አሁን ላይ በዋና ስራ አስፈፃሚነት የምትመራው ዮሃና ኤርሚያስ እንደምትለው መተግበሪያቸው በአካል ዕቁብ ላይ የሚከናወኑ ተግባራትን አስመስሎና የበለጠ ተጠያቂነት፣ የአጠቃቀም ቅለት እንዲሁም እቁቦቹ በሌሎች ሰዎች ይበልጥ እንዲገኙ እንዲያስችል ተደርጎ የተሰራ ነው፡፡ በባህላዊው አሰራር ላይ የሚከወኑትን ተግባራት መስሎ ከመስራትም ባሻገር የእቁብ መተግበሪያው እንደ ማስታወሻ፣ ቀን መቁጠሪያ፣ የክፍያ ስርዓቶች እና የመረጃ ጥንቅሮች ያሉ አዳዲስ ገፅታዎችን በመጨመር ለተጠቃሚ ምቹ ሆኖ የመጣ መሆኑን ዮሃና ትገልፃለች፡፡
እቁብ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂስ መተግበሪያው ይፋ ከተደረገበት ዕለት አንስቶ ባሉት ቀጣይ ሦስት ወራት ውስጥ 30 ሺህ ተጠቃሚዎችን ለመሳብ አልሟል፡፡ አሁን ላይ ከባንኮችም ሆነ የክፍያ ስርዓቶች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የፈጠረ ባይሆንም እቁብ ፔይ የተሰኘ ገፅታን በውስጡ አካቷል፡፡ ይህ ገፅታ ታድያ ተጠቃሚዎች ወቅታዊ መዋጮዋቸውን የሚያመላክት የባንክ መረጃቸውን እንዲያቀርቡና ገንዘቡ ስለ መግባቱ የሚያረጋግጥ ከባንክ የተሰጠ ማረጋገጫ በመከተል እቁቡ መጣሉን እንዲያረጋግጡ ያስችላቸዋል፡፡
መተግበሪያው በእቁብተኞቹ መካከል መተማመን እንዲኖር ለማድረግ ያስችሉኛል ያላቸውን ለየት ያሉ ገፅታዎችንም ይዟል፡፡ አንደኛው መንገድ አሁን ላይ በአካል ያሉ እቁቦችን ወደ መተግበሪያው ማስገባት ነው፡፡ በሌላ መልኩ የመተግበሪያ ተጠቃሚዎች በተለያየ ጊዜ የሚያሳዩትን ምግባር በመከታተል ነጥብ መስጠት እና የእቁብ አስተዳዳሪዎችም ይህን ነጥብ እንዲመለከቱ በማድረግ ወደ እቁባቸው ማን መቀላቀል ይችላል አይችልም የሚለውን ለመወሰን የሚረዳ ገጽታንም ይዟል፡፡ መተግበሪያው እቁቡ ስለተጣለባቸው ዙሮች እንዲሁም እቁቡን ሳይጥሉ ያሳለፉ እቁብተኞች ስለመኖራቸው የሚያሳዩ መረጃዎችን የሚያቀርብ ስለሆነም ተጠቃሚዎቹ የተሻለ ተዓማኒነት ያላቸውን እቁቦች ለይተው እንዲቀላቀሉ ያስችላል ተብሎለታል፡፡
የእቁብ መተግበሪያ በውጭ ሀገራት ከሚገኘው የዲያስቦራ ማህበረሰብን ዘንድ ተደራሽ ለመሆን ብሎም ከባንክ እና የሞባይል ክፍያ አቅራቢዎች ጋራም ቀጥተኛ የክፍያ ትስስርን ለመፍጠር አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
ታድያ ድርጅቱ ከዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ገቢ የሚያገኘው መተግበሪያውን የሚጠቀሙ እቁብተኞችን ታላሚ አድርገው ከሚሰሩ ማስታወቂያዎች እንደሆነ ከዚህ በፊት መተግበሪያውን አስመልክቶ በሰራነው ዘገባ መግለፃችን ይታወሳል፡፡
መተግበሪያውን መጠቀም የምትፈልጉ ተከታታዮቻችን ይህን ሊንክ በመጫን ከጉግል አፕ ስቶር ላይ አውርዳችሁ መመልከት ትችላላችሁ >> https://play.google.com/store/apps/details?id=com.equbapplication
ምንጭ፤ Shega
ካርቦን ዳይ ኦክሳይድን ወደ ድንጋይ የሚቀይረው የቴክኖሎጂ ፈጠራ
============================
ተመራማሪዎች ከከባቢ አየር ላይ እንደካርቦን ያሉ በካይ ጋዞችን ለይተው የሚያወጡ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን ለማበልፀግ ላለፉት አስርት አመታት የተለያዩ ሙከራዎችን ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ ይሁንና በዘርፉ የሚደረገውን የተመራማሪዎች ጥረት ወደውጤት ለማሸጋገር የሚስችል የባለሀብቶች ድጋፍ በደንብ መታየት የጀመረው ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ነው፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ በአለማችን ላይ የደቀነውን ከባድ ፈተና ለመከላከል የሁሉም አካላት ትብብር አስፈላጊ ቢሆንም የእነዚህ ባለሀብቶች የፋይናንስ ድጋፍ ውጤቱን ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እጅግ መሰረታዊ ነው፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም በቅርብ ጊዜያት የተለያዩ ኢንቨስቶሮች እና ባለሃብቶች ይህን የአለም አቀፍ ችግር ሊያቀሉ የሚችሉ የምርምር ስራዎች ላይ በመሳተፍ ላይ የሚገኙ ሲሆን በተለይም ከአየር ላይ ካርቦን የሚሰበስቡ ቴክኖሎጂዎች ላይ ኢንቨስት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ለአብነት የስፔስ ኤክስ መስራችና ዋና ስራ አስፈፃሚ ኤለን መስክ በቅርቡ ይፋ እንዳደረገው በዚህ የቴክኖሎጂ ዘርፍ ላይ የተሻለ ሃሳብ ለሚያቀርብ የምርምር ተቋም 100 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለመደገፍ ማቀዱ ለቴክኖሎጂው መተግበር የተሻለ እድል ይፈጥራል፡፡
በእነዚህ የቴክኖሎጂ ትግበራዎች ውስጥ ካርቦን ዳይ ኦክሳይድን ወደ ድንጋይ የሚቀይረው አስገራሚ የቴክኖሎጂ ፈጠራ አይስላንድ መቀመጫውን ባደረገ ካርብፊክስ በተሰኘ የምርምር ተቋም ሲበለፅግ የቆየ ሲሆን፤ እንደአውሮፓውያኑ ከ2015 አንስቶ በቴክኖሎጂው ላይ የተለያዩ ሙከራዎች ሲደረጉ ቆይተው ባለፉት ሁለት አመታት ውስጥ የተሻለ ውጤት ማምጣት የተቻለበት ግኝት ነው፡፡ እንዲህ ያሉ የምርምር ስራዎች እና የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ከፍተኛ የፋይናንስ አቅም ከመጠየቃቸው አንፃር የአለማችን ባለሃብቶች ኢንቨስትመንት እጅግ አስፈላጊ ሲሆን፤ ከዚህ ጋር ተያይዞም ቴክኖሎጂውን ይበልጥ ወደ መሬት ለማውረድ ቢል ጌት ያደረገው የገንዘብ ድጋፍና ኢንቨስትመንት የተሻለ እድልን ፈጥሯል፡፡
ካርብፊክስ ክላይምወርክ ኤጂ ከተባለ የስዊዘርላንድ ድርጅት ጋር በትብብር የሚሰራው ይህ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ካርቦን ዳይ ኦክሳይድን ከአየር ላይ በመሰብሰብ በማሽኑ አሰራር መሰረት ጋዙን በውሃ በማቅለጥ በሁለት አመታት ውስጥ ካርቦን ዳይ ኦክሳይድን እስከወዲያኛው ወደ ድንጋይ የሚቀየር አስገራሚ የቴክኖሎጂ ማሽን ነው፡፡ የቴክኖሎጂው አሰራር እጅግ ውስብስብ ይዘት ቢኖረውም ካርቦን ዳይ ኦክሳይድን የሚያስወግድበት መንገድ በሁለት መልኩ ይገለጻል፡፡ የመጀመሪያው ካርቦን ካፕቸር (carbon capture) የሚባለው ሲሆን ይህም ከፋብሪካ ጭስ ማውጫዎች እና ከሃይል ማመንጫዎች የሚወጣውን በካይ ጋዝ ወደ ከባቢ አየር ከመግባቱ በፊት የሚሰበሰብበት አሰራር ነው፡፡ ሁለተኛው ካርቦን ሪሙቫል (carbon removal) የሚባለው የቴክኖሎጂ አሰራር ሲሆን ይህም በከባቢ አየር ላይ ተከማችቶ ያለውን ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ በመሰብሰብ በማሽኑ አሰራር መሰረት ወደ ድንጋይ የሚቀይረው ነው፡፡
ይህ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለፉት ሁለት አመታት በሚዲያዎች ላይ ትልቅ ሽፋን አግኝቶ የቆየ ቢሆንም አሁን ላይ እንደቢልጌት እና ኤለን መስክ ያሉ ትልልቅ ባለሃብቶች ኢንቭስት እያደረጉበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የቴክኖሎጂ ምርምሩ ወደትግበራ የሚሄድበት ፍጥነት እጅግ የላቀ እንዲሆን ያስችላል፡፡
ምንጭ፡ Jwnenergy
ቁስልን ከኢንፌክሽን የሚከላከለው ስማርት መሸፈኛ (ባንዴጅ)
***************************
በየሱቁ የሚገኙትና በብዛት ለቀላል የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ የሚውሉ የቁስል መሸፈኛዎች ቀላል ቁስሎችን ለመሸፈን በጣም አስፈላጊ ናቸው፡፡ ሳይንስ ደግሞ እነዚህ የቁስል መሸፈኛዎች ማሻሻያ ቢደረግባቸው የቁስል መጽናትን ወይም ኢንፌክሽንን ሊያመለክቱ ይችላሉ እያለ ነው፡፡ ለዚህም አነስተኛ ሴንሰሮችን በመሸፈኛው በመለጠፍ ማሳካት እንደሚቻል ተመራማሪዎች አሳይተዋል፡፡
በሮዴ ደሴት ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ዳንኤል ሮክስበሪ እና መሐመድ ሞይን የተባሉ ተመራማሪዎች በአሜሪካ ብሔራዊ ሳይንስ ፋውንዴሽን እገዛ በሰሩት ምርምር ትንንሽ የቁስል መሸፈኛዎችን በመጠቀም የቁስልን ደህንነት መከታተልና መቆጣጠር የሚያስችል ስልት መቀየሳቸውን ተናግረዋል፡፡
በባንዴጁ ላይ በነጠላ የተለጠፈ የካርቦን ናኖቲዩብ በቁስሉ ላይ ያለውን የሀይድሮጅን ፐርኦክሳይድ ይዘት በመጠቀም የቁስሉን ደህንነት ይከታተላል ሲል ከተመራማሪዎቹ አንዱ የሆነው ሮክስበሪ ተናግሯል፡፡ እደተመራማሪው ገለጻ ከሆነ እነዚህን ናኖቲዩቦች አካባቢያቸውን መረዳት በሚያስችላቸው ስነ-ህይወታዊ ሁኔታ ላይ እንዲሆኑ ማድረግ አለመቻሉ ለእንደዚህ አይነቱ ተግባር እንዳይውሉ አድርጓቸዋል፡፡
ይህ ስማርት ባንዴጅ ተብሎ የተጠራው የተሻሻለው የቁስል መሸፈኛ ከቅርብ ርቀት ባለ ተለባሽ ገመድ አልባ ቴክኖሎጂ አማካኝነት ካርቦን ናኖቲዩቡ የሚሰጠውን ምልክት ወደ መረጃ መለወጥ እንዲችል ተደርጎ የተሰራ ነው፡፡ ከገመድ አልባው ቴክኖሎጂ የተገኘው ምልክት እንደ ስማርት ስልክ ባሉ ቁሶች አማካኝነት ታካሚው ወይም ክትትል የሚያደርገውን ሰው በአፋጣኝ ህክምና እንዲያገኝ ወይም ወደ ጤና ተቋም እንዲሔድ ምልክት ይሰጠዋል፡፡
ይህም አንድን ኢንፌክሽን እንደተጀመረ ወዲያውኑ በመለየት አስፈላጊውን ህክምና ለማድረግ እንደሚያስችል ተመራማሪዎቹ ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ቴክኖሎጂው የአጠቃላዩን ማህበረሰብ የጤና ሁኔታ በእጅጉ ያሻሽለዋል እሚል እምነት እንዳላቸው ተመራማሪዎቹ አክለው ተናግረዋል፡፡
ምንጭ Technology.Org
ሩሲያ በትዊተር ላይ ገደብ ጣለች
================
ሩስያ ሕጋዊ ያልሆኑ መረጃዎችን ከገፁ ላይ ለማጥፋት አልቻለም ባለችው ትዊተር ላይ ለተጠቃሚዎች የሚደርስበትን ፍጥነት እንደምትቀንስ አስታወቀች፡፡ የሩስያ ኮምዩኒኬሽን፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማስ ሚዲያ ቁጥጥር አገልግሎት ወይም ሮስኮምናትዞር እንደተናገረው ከሆነ በሀገሪቱ ያለውን የትዊተርን አገልግሎቶች ለመገደብ ከውሳኔ የተደረሰው ሩስያውያንን ለመጠበቅ እና ኩባንያው ለሩስያ ሕግ ተገዢ እንዲሆን ለማድረግ ነው፡፡ ሮስኮምናትዞር በመግለጫቀው እንደጠቀሰው እርምጃው ከዛሬ አንስቶ ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን ትዊተርን በተንቀሳቃሽ ስልካቸው አማካኝነት በሚጠቀሙት በሁሉም ላይ፤ በኮምፒውተር አማካኝነት በሚጠቀሙት ደግሞ በ50 በመቶው ላይ የገፁ ፍጥነት የሚቀንስባቸው ይሆናል፡፡
ከአውሮፓውያኑ 2017 አንስቶ የህፃናት ወሲባዊ ምስሎች፣ አደንዛዥ እፅ ላይ ያተኮሩ መረጃዎች እና ታዳጊዎች እራሳቸውን እንዲያጠፉ ጉትጎታ የሚያደርጉ ማስፈንጠሪያዎችን ያነሳ ዘንድ ከ28 ሺህ ጊዜ በላይ ሲጠይቅ መቆየቱን ሮስኮምናትዞር ገልጿል፡፡ ተቋሙ ትዊተር የሩሲያን ሕግ ችላ የሚል ከሆነ ከሀገሪቱ ሙሉ በሙሉ እስከማገድ የሚደርሱ ሌሎች ገደቦች ሊጣሉበት ይችላል ሲል አስታውቋል፡፡
ሞስኮ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ፅንፈኝነት እና አሸባሪነትን ለመከላከል እንዲሁም ታዳጊዎችን ለመጠበቅ በሚል በይነ-መረብ ላይ የምታደርገውን ቁጥጥር ጠበቅ እያደረገች ሲሆን ከሰነሞኑም ለተቃውሞ የሚቀሰቀሱ መልዕክቶችን እንዲያነሱ በምዕራባውያኑ የማህበራዊ ሚዲያ አውታሮች ላይ ጫናን በማሳደር ላይ ናት፡፡ እንደ ዴይሊ ሞሽን እና ሊንክድኢን ያሉ ድረ-ገፆችም ከመንግስት ጋር ለመተባበር ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ሳብያ ከሀገሪቱ ታግደው ይገኛሉ፡፡ በሌላ መልኩ 2019 ላይ ከወርልድ ዋይድ ዌብ የተነጠለ ሉዓላዊ በይነ-መረብን ለማበልፀግ ያለመ ሕግ አውጥታ ነበር፡፡ ሕጉ ግን በተለይ በመብት ተቆርቋሪዎች ዘንድ መንግስት ሳይበር ላይ ያለውን ቁጥጥር በማፅናት የመናገር ነፃነትን ሊገድብ ይችላል በሚል ስጋትን አጭሯል፡፡
ምንጭ፤ Tech Xplore
አዲሱ ግኝት ማየት ለተሳናቸው ሰዎች አርቴፊሻል እይታን ሊሰጥ ይችላል
========================
የሰዎችን የዓይን እይታ ማደስ ወይም መመለስ ለተመራመሪዎች እና ለሳይንስ ሊቃውንት ትልቅ ፈተና ሆኖ ቆይቷል፡፡ የሳይንስ ግኝቶች ሙሉ ለሙሉ ማየት ለተሰናቸው ሰዎች የማየት አቅምን ይመልሳሉ የሚለው በረዥም ጊዜ የሚመለስ ነገር ቢሆንም አሁን ላይ ሆኖ ሲታሰብ የሰዎችን የአይን ብርሃን ሙሉ ለሙሉ መመለስ አንዳች ተዓምር ሊያስፈልጋው ይችላል፡፡ ያም ሆኖ ወደዚህ ደረጃ የሚያደርሱ የምርምር ስራዎች መካሄዳቸው እስከቀጠለ ድረስ ይህን የሰው ልጆች ፈተና በቀጣይ ጊዜያት መመልስ እንደሚቻል አሁን እየታዩ ካሉ ግኝቶች በመነሳት ማውራት ይቻላል፡፡
ስዊዘርላንድ በሚገኘው የ EPFL ዩኒቨርስቲ የኒውሮ ምህንድስና ተመራማሪ የሆኑት ዲዬጎ ጌዚ በዚህ ዘርፍ ላይ ለረዥም ጊዜ ምርምር ሲያደርጉ የቆዩ ሳይንቲስት ሲሆኑ ከ2015 አንስቶ ከባልደረቦቻቸው ጋር ከፍተኛ ምርምር ሲያደርጉበት የነበረው ጉዳይ መልካም ውጤት አስገኝቶላቸዋል፡፡ ለረዥም ጊዜ የቆየው የተመራማሪዎች ጥናት ካሜራ ያላቸው ስማርት መነጽሮች እና ማይክሮ ኮምፒውተሮችን በማጣመር የሚሰራ የሬቲና ኢምፕላንትን የማበልፀግ ሂደት ነው፡፡ ከስማርት መነፅሮች እና ማይክሮ ኮምፒውተሮች ጋር በጥምረት የሚሰራው የሬቲና ኢምፕላንት (retinal implant) ከተፈጥሮአዊ የሬቲና ህዋስ አሰራር የተለየ ሂደት እንዳለው ተመራማሪዎች ይናገራሉ፡፡
በቴክኖሎጂው አሰራር መሰረት ካሜራዎች የተገጠሙለት ስማርት መነጽር የተመለከታቸውን ነገሮች ምስል በማንሳት በመነፅሩ የመጨረሻ ክፍሎች ላይ ለሚገኘው ማይክሮ ኮምፒውተሩ መረጃውን የሚስተላልፍ ሲሆን፤ ማይክሮ ኮምፒውተሩም የተቀበለውን መረጃ ወደ ብርሃን ሲግናሎች በመቀየር ብዙ ኤሌክትሮዶች የተገጠሙለት የሬቲና ኢምፕላንት መረጃውን በሚገባ እንዲረዳ ያደርገዋል፡፡ አዲሱ የሬቲና ኢምፕላንት ወደ ብርሃን ሲግናሎች የተቀየሩ መረጃዎችን በቀላሉ እንዲረዳ የሚያስችለው በአይኖቻቸን ውስጥ ያሉ የሬቲና ህዋሶችን ለማነቃቀት ወይም (stimulate) ለማድረግ በኢምፕላንቱ ላይ የተገጠሙትን ከ 10,000 በላይ ኤሌክትሮዶች በመጠቀም ነው፡፡ ማየት የተሳናቸው ሰዎች ይህን አዲስ ግኘት ሲጠቀሙ ወደ ብርሃን ሲግናሎች የተቀየሩትን መረጃዎች በነጭ እና በጥቁር መልክ በመመልከት የአርተፊሻል እይታ እንዲኖራቸው ይሆናል፡፡
በዚህ አዲስ ግኝት ላይ ከ10,000 እስከ 10,500 የሚደርሱት የሬቲና ኢምፕላንት ኤሌክትሮዶች ለአርተፊሻል እይታው መፈጠር ዋና ምክንያቶች ቢሆንም የኤሌክትሮዶች መብዛት እና ማነስ ለሚፈጠረው ትክክለኛ ምስል ወሳኝ በመሆኑ ወደፊት የሚደረጉ ተጨማሪ ምርምሮች እጅግ አስፈላጊ እንደሆኑ ተመራማሪዎች ይገልፃሉ፡፡ አዲሱ ግኝት ከ2015 አንስቶ ሲበለፅግ እና ምርምር ሲደረግበት የቆየ ቢሆንም እስካሁን ሰዎች ላይ ምንም አይነት ሙከራ አለማድረጉን የሚናገሩት የምርምሩ መሪ ዲዬጎ ጌዚ ይህን ለመተካት ይቻል ዘንድ የቨርችዋል ሪያልቲ ፕሮግራም በማዘጋጀት የአይን ታካሚዎች በኢምፕላንቱ አማካኝነት ምን መመልከት እንደቻሉ መርምረናል ብለዋሁኔታ
ይህ ተስፋ ሰጪ የቴክኖሎጂ ግኝት ማየት ለተሳናቸው ሰዎች ሙሉ ለሙሉ ብርሃናቸውን መመለስ ባይችልም በአርተፊሻል እይታ አማካኝነት የአይን ታካሚዎችን በተሻለ ሁኔታ እንደሚረዳ የሚናገሩት ተመራማሪው ዲዬጎ ጌዚ በቅርብ ጊዚያት ውስጥ የሬቲና ኢምፕላንት ሂደቱ በሰዎች ላይ እንደሚሞከርም ይገልጻሉ፡፡
ምንጭ፡ Neurosciencenews እና Dailymail
ፓን አፍሪካ መሰረት ያለውና ጀማሪ ስታርትአፖችን የሚደግፈው ሳቫና ፈንድ
***************************
ከተመሰረተ ከ2012 ጀምሮ ከ30 በላይ ስታርትአፖችን እንዳገዘ የሚነገርለት ሳቫና ፈንድ በአህጉራችን ያለውን የንግድ እንቅስቃሴ የሚያሳልጥና ጀማሪዎችን የሚደግፍ 25 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መመደቡን አሳወቀ፡፡ የቬንቸር ካፒታል ድርጅት ከመሆኑ አስቀድሞ ተቀባይነት ያለው የንግድ ሀሳብ ይዘው ለሚመጡ አዋጭ ሃሳብ ላላቸው ሰዎችና ድርጅቶች እስከ 30 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ ያደርግ ነበር፡፡
ከ2016 ጀምሮ የመጀመሪያ ደረጃ የንግድ ሀሳቦችን ለመደገፍ እንዲያስችለው ከ25 ሺህ እስከ 500 ሺህ ዶላር ኢንቨስት የሚያደርግ ቬንቸር ካፒታል ወደመሆን አድጓል፡፡ ይህ በተለያዩ አለማቀፍ ተቋማትና ባለሀብቶች የሚደገፈው የንግድ አጋር የአሁኑ ፈንድ በዘጠኝ አመቱ ውስጥ ሁለተኛው ነው፡፡ እስካሁንም በኬንያ፣ በደቡብ አፍሪካ እና በናይጀሪያ የተለያዩ ስራዎችን ሰርቷል፡፡
የመረጃ ምንጫችን TechCrunch እንደዘገበው ከሆነ የደቡብ አፍሪካው አግሪቴክ ኤሮባዮቲክስና ፍሌክስ ክለበ፣ በኢትዮጵያ የጤና ቴክኖሎጂ ላይ የሚሰራው ኦርቢት ሄልዝ እና መሰረቱን በኬንያ ያደረገው ሞሪንጋ ትምህርት ቤትና አንዶ ምግቦች በኢንቨስትመንቱ ተካትተዋል፡፡ ይህ የንግድ ስራ ሃሳብም በብዛት በኬንያ፣ በደቡብ አፍሪካና በታንዛኒያ የተገደበ ቢሆንም ለወደፊት ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ለመስፋት ትልቅ እቅድ አለው ተብሏል፡፡
ይህ የንግድ ትብብር አሁን ላይ የዕጣ ዋጋውን በእጥፍ አሳድጎ ከ50 ሺህ ዶላር ወደ 1 ሚሊዮን አሳድጎታል፡፡ ባሳለፍነው የፈረንጆች አመት የህብረቱ የፈንድ መጠን 118 ሚሊዮን ዶላር ደርሶ ነበር፡፡ የቅድመ ጅማሮ ድጋፍ ብዙ አፍሪካውያን የቴክኖሎጂ ፈጠራ ሙያተኞችን ህልም በማሳካት በአፍሪካ ውስጥ ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ የኢኮኖሚ መነቃቃት ማምጣት ይችላል፡፡ በዚህም ከሳቫና ጋር ህብረት በመፍጠር ድጋፍ የሚሹ ስራ ፈጣሪዎችን ማገዝ እንደሚቻል የመረጃ ምንጫችን ዘግቧል፡፡
ምንጭ TechCrunch
የቴፕ ካሴትን የፈጠረው ግለሰብ በ94 አመቱ አለፈ
======================
የኔዘርላንድ ተወላጁ ኢንጅነር ሉ ኦቴንስ ለሙዚቃ ባለውለታ የሆነውን የቴፕ ካሴትን በመፈልሰፍ ትልልቅ ፈጠራዎችን ከሰሩ ኢኖቬተሮች መካካል በቀዳሚነት ይመደባል፡፡ ቴክኖሎጀው እንደአውሮፓውያኑ ከ1960ዎቹ አንስቶ ግልጋሎት መስጠት ከጀመረ በኋላ በመላው አለም ከ100 ቢሊዮን በላይ የቴፕ ካሴት ምርት ሊሸጥ እንደቻለ ይነገራል፡፡
ኢንጅነር ሉ ኦቴንስ በ1960ዎቹ የቴፕ ካሴትን በሚያበለፅግበት ወቅት የፊሊፕስ ኩባንያ የምርት እድገት ዲፓርትመንት ዋና መሪ የነበረ ሲሆን በ1963 ቴክኖሎጂው በበርሊን የራዲዮ ኤሌክትሮኒክስ አውደ ርዕይ ላይ ቀርቦ ከታየ በኋላ በመላው አለም ዝናው እየናኘ ሄዷል፡፡ ኢንጅነሩ ኦቴንስ ከፊሊፕስ እና ሶኒ ካሉ ትልልቅ ኩባንያዎች ጋር በምርት ሽያጭ ዙሪያ ስምምነት ካደረገ በኋላ ይህን የቴክኖሎጂ ሞዴል፤ የፈጠራ ባለቤትነት መብት ሊያገኝብት ችሏል፡፡
ይህ የፈጠራ ሰው ከዚህ የካሴት ፈጠራው ባለፈ በተለምዶ የሲዲ ማጫወቻ ወይም (compact disk) ተብሎ በሚታወቀው የቴክኖሎጂ ፈጠራ ላይ ተሳታፊ የነበረ ሲሆን ይህ የቴክኖሎጂ ፈጠራም አገልግሎት መስጠት በጀመረበት እንደአውሮፓውያኑ ከ1982 አንስቶ በመላው አለም ከ200 ቢሊዮን በላይ ምርት ሊሸጥ ችሏል፡፡ አሁን ላይ ከቴክኖሎጂዎች መዘመን ጋር ተያይዞ እንደ ቴፕ ካሴት ያሉ ፈጠራዎች ቀድሞ በነበራቸው ልክ ግልጋሎት እየሰጡ ባይሆንም በውጪውም ይሁን በሀገራችን ታሪክ ለሙዚቃ አፍቃሪዎች እና ለራሱ ለሙዚቃ እድገት ትልቅ ውለታን ያደረጉ ግኝቶች ናቸው፡፡
እነዚህ እና ሌሎች ፈጠራዎችን ያበረከተው ኢንጅነር ሉ ኦቴንስ እንደአውሮፓውያኑ በ1926 ዱዜል በተባለች የኔዘርላንድ ከተማ የተወለደ ሲሆን፤ በተገኘባት ከተማ ከብዙ ፈጠረዎች እና ስራዎች በኋላ በ94 አመቱ ማክሰኞ ዕለት ህይወቱ ማለፉን ቤተሰቦች አስታውቀዋል፡፡
BBC
የሊቲየም አዮን ባትሪዎችን አቅም በሦስት ዕጥፍ የሚያሳድገው አዲስ ግኝት
========================
በሩስያው የሚሲስ ብሔራዊ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቱ የሚገኝ ዓለም አቀፍ የተመራማሪዎች ቡድን የሊቲየም አዮን ባትሪዎችን አቅም እና የአገልግሎት ዘመን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ የሚችል ግኝት ይፋ አድርገዋል፡፡ እንደ አጥኚዎቹ ከሆነ አሁን ላይ ባሉት የሊቲየም አዮን ባትሪዎች ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውለውን የግራፋይት ንጥረ-ነገር የሚተካ አዲስ የናኖ ቁስን አቀናብረዋል ወይም ሲንተሳይዝ አድርገዋል፡፡ የጥናት ውጤታቸውንም በጆርናል ኦፍ አሎይስ ኤንድ ኮምፓውንድስ ላይ አሳትመው አውጥተዋል፡፡
የሊቲየም አዮን ባትሪዎች ከስማርት ስልኮቻችን አንስቶ እስከ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ድረስ ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ እነዚህ ባትሪዎችን ቻርጅ የማድረግ ሂደቱ በሁለት ኤሌክትሮዶች ማለትም በኔጋቲቭ ቻርጅ ከሆነ አኖድ በፖዘቲቭ ቻርጅ ወደሆነ ካቶድ በሚደረግ የሊቲየም አዮኖች እንቅስቃሴ አማካኝነት ይከናወናል፡፡ የሊቲየም አዮን ባትሪዎች አገልግሎት ከቀን ወደ ቀን እያደገ ይሁን እንጂ ባትሪዎቹ ባላቸው የግራፋይት ይዘት ሳብያ አቅማቸው ላይ ይህ ነው የሚባል ትልቅ ለውጥ ሳይኖር መቆየቱን ተመራማሪዎቹ ያስረዳሉ፡፡ ታድያ የምርምር ቡድኑ ለአኖዶቹ የባትሪውን አቅም እና የአገልግሎት ዘመን ማሳደግ የሚችልን ቁስ ማግኘት ችለዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የፋንክሽናል ናኖሲስተምስ እና ሀይ ቴምፕሬቸር ማቴሪያልስ ዲፓርትመንት ውስጥ በረዳትነት የሚያገለግለው ይቭጊኒ ኮልስናይኮፍ እንደሚለው ማውጣት የቻሏቸው ባለ Cu0.4Zn0.6Fe2O4 ውህድ ወንፊታማ (Porous) ጥቃቅን የናኖ ቁሶችን እንደ አኖድ በመጠቀም አሁን ገበያ ላይ ካሉት ባትሪዎች በሦስት እጥፍ የላቀ አቅምን መስጠት ይቻላል፡፡ በተጨማም ለግራፋይቶች መተኪያነት ከሚቀርቡት አማራጮች በበለጠ ባትሪዎቹ ኃይላቸውን እየጨረሲ ቻርጅ የሚደረጉበትን ድግግሞሽንም በአምስት እጥፍ የሚያሰሳድግ መሆኑንና ይህ መሻሻልም ልዩ በሆኑ የናኖ ቁሶች እና ግልጋሎት ላይ በዋሉት ጥምር ንጥረ-ነገሮች ቅንጅት የመጣ ስለመሆኑ ይቭጊኒ ይናገራል፡፡
የማቀናበር ስራው የፓይሮሊሲስ ርጭት (Spray-Pyrolysis) መንገድን በመጠቀም የሚከወን በመሆኑም በውስጡ የተለያዩ ደረጃዎች ሳይኖሩት በአንድ እርምጃ ብቻ የሚካሄድ ነው፡፡ እንደ ተመራማሪዎቹ ማብራርያ ከልዩ የብረት አዮኖች የተጣመረ የኤኩየስ ውህድ በአልትራሳውንድ ረዳትነት ወደ ደመናነት የሚለወጥና በማስከተልም ከሜታል ሳልቶቹ ፍርስራሽ ጋር በመሆን ውሃው በ1200 ዲ.ሴ ሙቀት እንዲተን የሚደረግ ይሆናል፡፡ በውጤቱመም የሊቲየም አዮን ስርዓትን ለማንቀሳቀስ የሚያስፈልጉት ወንፊታማ ባለ ክብ ቅርፅ ጥቃቅኖች ተለይተው እንዲወጡ ይደረጋል፡፡
ምንጭ፤ Tech Xplore
አስደናቂው ሰዓሊ ሮቦት
============
ከቀናት በኋላ በሀገረ አሜሪካን ቴክሳስ ግዛት ውስጥ መካሄድ በሚጀምረው የሳውዝ ባይ ሳውዝዌስት ፎረም (SXSW) ከጃፓኑ የዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቶኪዮ የመጣ አንድ ለትርፍ ያልተቋቋመ ፕሮጀክት ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ተጠቅሞ ሥዕል በመሳል የሚያሳይ ሮቦትን ይዞ እንደሚቀርብበት ተነግሯል፡፡ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ተጠቅሞ የመሳል ፕሮጀክቱ ፈጠራን ከማሽኖች ጋር በማጣመር ሮቦቱ የቀለም መቀብያ ብሩሽ እና የሥዕል ሸራን አዋዶ ሥዕል የመሳል ጥበብን አጎናፅፎታል፡፡ ከያማሀ ጋር ባለ ትብብር እና ድጋፍ የተሰራው ሰዓሊው ሮቦት ከዩኒቨርሲቲው ተልከው በኤግዚቢሽኑ ላይ ከሚቀርቡት ስራዎች መካከል አንዱ ይሆናል፡፡
በሰው ሰራሽ አስተውሎት ሮቦት ፕሮጀክቶች ላይ እየሰራ ባለው የሱዙቭ ስታርታፕ ቡድን ውስጥ የፕሮጀክት መሪዋ ጂአሚን ፓን እንደምትለው ከሆነ የሮቦቱ አጠቃላይ ፅንሰ ሀሳብ ሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ የቁሳቁሶች በይነ-መረባዊ ትስስር (IOT)፣ ሮቦት እና ጥበብ ቅንጅት ላይ ያረፈ ነው፡፡ እንደ ጂአሚን ንግግር ይህን ሮቦት ከሌሎቹ ወደ ጥበብ ካጋደሉ ሮቦቶች ለየት የሚያደርገው ተስለው የተቀመጡ ምስሎችን ተመልክቶ ደግሞ ከመሳል ይልቅ በሚሰጠው መመርያ መሰረት የራሱን ሥዕል መሳሉ ነው.፡፡
ሰው ሰራሽ አስተውሎት እና ሮቦት የሰውን ልጆች አይነ ሕሊና መተካት ባይችልም እንኳን የሚያነሳሱ እና ወደ አዲስ አይነት ፈጠራ የሚመሩ ሊሆን ይችላል የምትለው ጂአሚን ብዙም ባልራቀ ጊዜ ውስጥ ከሰው ልጆች የተለየ አይነት ፈጠራን ይዘው የሚመጡ ልዩ ልዩ ፈጣሪ ሮቦቶችን የምናይበት እንደሚሆን ትናራለች፡፡
የሰው ሰራሽ አስተውሎት ሮቦቱ ሥዕሎቹን የሚስለው የሚሰጡትን የተለያዩ ሀሳቦችን ከተቀመጠለት የብሩሽ ሰረዝ ገደብ ጋር በማብቃቃት ነው፡፡ እንደ ጂአሚን ከሆነ የሚስለው ሥዕል ውስብስብነት ለሮቦቱ በሚሰጠው ትዕዛዝ ላይ የሚመሰረት ይሆናል፡፡ “ሮቦቱ 30 የብሩሽ ሰረዞችን ብቻ እንዲጠቀም የምንገድበው ከሆነ ወደ አብስትራክት የተጠጋ ጥበብን ሲፈጥር በአንፃሩ 300 የብሩሽ ሰረዞች ሲፈቀድለት በተሻለ ሕይወት ያለው ሥዕልን ይሰጠናል” ትላለች ጂአሚን፡፡
ቀጣን መስፍጠሪያ በመጫን ሰዓሊው ሮቦት በሸራ ላይ ሥዕሉን ሲያኖር መመልከት ትችላላችሁ >>> https://www.youtube.com/watch?v=dvbMJy1QspE
ምንጭ፤ Forbes
ቴክ-ሳይንስ ሳምንታዊ የቴሌቪዥን ፕሮግራም፤
================
በነገው ዝግጅታችን፤
በአብይ ፕሮግራም ፤ የአየር ላይ ቅየሳ
በብላቴናት፤ ከኮቪድ-19 የሚጠብቅ የባንክ ቤት ሶፍትዌር የሰራው ታዳጊ
የቴክኖሎጂ ታሪክ፤ ንፋስ ስልክ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ
በተቋማት፤ የሮኬት ቴክኖሎጂ
እንዲሁም በተመራማሪዎች ታሪክ በአ.አ ዩኒቨርሲቲ አክሊሉ ለማ ፓቶ ባዮሎጂ ኢንቲትዩት ውስጥ ተመራማሪ የሆኑትን ፕ/ር ምሩፅ ግደይን ሁለተኛ ክፍል ይዘንልዎ እንቀርባለን፡፡
እርስዎም ነገ ቅዳሜ በ10 ሰዓት MOE TV ላይ ይጠብቁን፤ ከአስተማሪ ዝግጅቶቻችን ለእርስዎም ሆነ ቤተሰብዎ ስንቅ የሚሆን ዕውቀትን ይገበዩበታል፡፡
ሳይሞላልዎት ቀርቶ ነገ ካመለጥዎም በዚሁ ቻናል ላይ ዕለተ ማክሰኞ 10 ሰዓት ሲደገም ያገኙታል፡፡ ይህም ካልሆነልዎ ወደ የዩትዩብ ቻናላችን (https://www.youtube.com/channel/UC6jvUOLRSkVEQtc5Annfwvg) ጎራ በማለት የዚህን ሳምንት ጨምሮ ከዓመታት በፊት ከተላለፈው የመጀመሪየው ክፍል አንስቶ ያሉትን ሁሉንም የቴክ-ሳይንስ ፕሮግራሞች አንድ በአንድ መመልከት ይችላሉ፡፡