TechIn2
1.16K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
ፖስተኛው የኡበር ሮቦት
*************
ኡበር የተሰኘው የትራንስፖርትና መጓጓዣ አገልግሎት ሰጭ ድርጅት ፖስታዎችን ወደየተላኩበት አድራሻ የሚያደርስ ሮቦትን ለአገልግሎት ማሰማራቱ ተሰማ፡፡ ይህ ሰርቭ ሮቦቲክስ በሚባል አዲስ ድርጅት ስር የሚንቀሳቀሰው በተለያየ ከተማ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ለደንበኞች የሚያቀብል እንደሆነ ተነግሮለታል፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ በተለይ አለማችን በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት የእንቅስቃሴ ገደቦችን ጥላ በነበረበት ወቅት የተለየዩ የቤት ውስጥ ፍጆታ እቃዎችን ንክኪ አልባ በሆነ መንገድ ለደንበኞች በማድረስ አዋጭነቱና አስተማማኝነቱ ተረጋግጧል፡፡
ይህ ስራ በትራንስፖርትና ምግብ አቅርቦት ላይ ብቻ ተሰማርቶ ለነበረው ኡበር ተጨማሪ የስራ አማራጭ እንደሚሆንለት የተነገረ ሲሆን የሮቦት መልዕክት ገበያ ወይም በሮቦት የታገዙ ስራዎች በአለማችን ታላላቅ ከተሞች ላይ እየተለመዱ በመምጣታቸው ገበያው አትራፊ መሆኑ አይቀርም ተብሏል፡፡ የሰርቭ ሮቦቲክስ መስራች እና ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት አሊ ካሻኒ ስራቸውን ከራስ ነድ መኪኖች ጋር አነጻጽረው ያቀረቡ ሲሆን እንደ እርሳቸው ገለጻ ራስ ነድ መኪኖች አሽከርካሪን በማስቀረት አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን እነዚህ ሮቦቶች ደግሞ ተሸከርካሪውንም ማስቀረት የቻሉና ለብዙዎች ተዳራሾች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
እንደ ካሻኒ ገለጻ የፊታችን ሁለት አስርት አመታት አዳዲስ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ አገልግሎት የሚሰጡ አዳዲስ ሮቦቶች ለአብዛኛው የሰው ልጅ ፍላጎት ተደራሽ ይሆናሉ፡፡ ድርጅቱ እንዳወጣው መረጃ ለምሳሌ በአሜሪካ ወደ ግማሽ የሚደርሱ ምግብ ቤቶች ምግባቸውን ወደ ደንበኛቸው ለማድረስ በአማካኝ 40 ደቂቃዎች ያስፈልጋቸዋል፡፡ ኡበርም እነዚህን Postmates የተሰኙ ሮቦቶች በ2.65 ቢሊዮን ዶላር ለመግዛት እንዳሰበ ባለፈው አመት አሳውቆ ነበር፡፡
ምንጭ Tech Xplore
በሶላር የሚሰሩ ስማርት የህዝብ መቀመጫ ቴክኖሎጂዎች
=====================
በከተሞች የወደፊት እድገት ላይ በሶላር የሚሰሩ ስማርት የህዝብ መቀመጫ (Smart Benches) ቴክኖሎጂዎች እጅግ ወሳኛ ናቸው፡፡ አከባቢን በማይጎዳ መልኩ በፀሃይ ኃይል አማካኝነት የሚሰሩት እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ከመደበኛው የሰዎች የመቀመጫ አገልግሎት ባለፈ የከተማን ውበት በጠበቀ መልኩ ሰዎች ስልኮቻቸውን ቻርጅ እንዲያደርጉ፣ የዋይፋይ አገልግሎት እንዲያገኙ እና ሌሎች ጠቃሚ የሚባሉ አገልግሎቶችን እንዲሰጠ ተደርገው የሚሰሩ ፈጠራዎች ናቸው፡፡
በስማርት ከተማ ባህሪያት ውስጥ ቅለትን ተላብሰው ብዙ ግልጋሎት ሊሰጡ የሚችሉ የፈርኒቸር ንድፎች፣ በየቦታው ያሉ እንቅስቃሴዊችን የሚያሳልጡ የቴክኖሎጂ ግብዓቶች እና ተፈጥሮኣዊ እይታዎችን የሚያጎሉ የህዝብ ማረፊያዎች አንድ ከተማ ስማርት ለመባል ከሚያስችሉት እጀግ የበዙ ባህሪያቶች መካከል በቀዳሚነት የሚቀመጡ ናቸው፡፡ እንዲህ ያሉ ፈጠራዎች ዲጂታል እየሆነ በመጣው አለም ውስጥ ሰዎች የበይነ-መረብ አገልገሎትን በየትም ቦታ እንዲያገኙ እና ከተቀረው አለም ጋር ያላቸውን ፈጣን ግንኙነት እንዲያጠናክሩ የሚያግዝም ነው፡፡
ቴክኖሎጂው ለከተሞች ከሚሰጠው ውብ ገፅታ በተጨማሪ በአሰራር ስርዓቱ የሶላር ኢነርጂን መሰረት ያደረገ በመሆኑ ብልሽት ሳያጋጥመው ለረዥም ጊዜ መቆየት እንዲችል እና ባስፈለገ ሰዓት አዳዲስ አገልግሎቶችን እንዲካተቱበት ለማድረግ የሚያስችል ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ፈጠራዎች ከከተሞች ባለፈ በተለያዩ የትምህርት፣ የባንክ እና የጤና ተቋማት ላይም በቀላሉ ልንተገብራቸው የምንችላቸው በመሆናቸው የሚያስገኙት ጥቅም እጅግ የላቀ ነው፡፡
ኩቤ ስማርት ቤንች የተባለው የሃንጋሪ ድርጅት ለሥነ-ምህዳር ተስማሚ የሆነ ዘመናዊ የህዝብ መቀመጫ ቴክኖሎጂን በመስራት ለከተሞች ከሚያቀርቡ የፈጠራ ድርጅት መካከል አንዱ ሲሆን ከሰሞኑ በሚገርም ዲዛን የቀረባቸው በሶላር የሚሰሩ ስማርት የህዝብ መቀመጫ ምርቶች እጅግ ተቀባይነት አስገኝቶለታል፡፡ የሶላር ኃይልን መሰረት አድርጎ የተሰራው የድርጅቱ ባለአዲስ ንድፍ የህዝብ መቀመጫ ስልኮችን ገመድ አልባ በሆነ መልኩ ቻርጅ የሚያደርግ፣ የዌፋይ አገልግሎትን ለተቀመጡ ሰዎች የሚያቀርብ፤ እና ከዚህ ባለፈም ሰዎችን ሊያዝናና የሚችል ምስሎች የሚታይበት ስክሪን ያለው ጠቃሚ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ነው፡፡ በዚሁ ዘርፍ በአለማችን ላይ ተወዳዳሪ ከሚባሉት ተቋማት ውስጥ ኢንጎ ፕላኔት ሌላኛው ሲሆን ይህ የፈጠራ ድርጅትም ውበትንና ቅለትን ማዕከል ያደረጉ ዘመነናዊ የህዝብ መቀመጫ ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ የሚታወቅ ድርጅት ነው፡፡
ምንጭ፡ growingworld24 እና enelx
ሳይከፈት የተነበበው የ300 ዓመቱ ደብዳቤ
***************************
ተመራማሪዎች ለ300 ዓመታት ያክል ሳይከፈት ተጠቅልሎ የተቀመጠን ደብዳቤ ቨርቹዋል አንፎልዲንግ ሲሉ በሰየሙት መንገድ ደብዳቤውን ሳይከፍቱ በውስጡ ያለውን ይዘት ማንበባቸው ተነገረ፡፡ ‹‹የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ›› እንደሚባለው ታሪክን ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት እሙን ነው፡፡ ቅርሶች በሚጠኑበትም ሆነ እንክብካቤ በሚደረግላቸው ጊዜ ታሪካዊና ቅርሳዊ ይዘታቸውን በማይጎዳ መሆን ይገባዋል፡፡ በተለይ እንደ እኛ ባለች የታሪክ መዝገብ በሆነች ሀገር የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ቅርሶችን ከንክኪ ጠብቆ ለማጥናት ይህ መንገድ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡
ይህ አለማቀፍ የተመራማሪዎች ቡድን በጥንት የአውሮፓ ዘመን የተጻፈውን የታሸገ ደብዳቤ ሳይከፍት የተለያዩ ኮምፒውተራዊ ስልቶችን በመጠቀም በውስጡ የያዘውን መልዕክት ማንበብ ችሏል፡፡ ይህ በኔቸር ኮሚኒኬሽን ታትሞ የወጣውና በመረጃ ምንጫችን SciTechDaily የተዘገበው መረጃ እንደሚያመለክተው MIT ቤተ-መጽሐፍትና የኮምፒውተርና ሰው ሰራሽ አስተውሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ትብብር የተሰራና ይፋ የሆነ ነው፡፡ ቨርቱዋል አንፎልዲንግ የተባለው ስልትም ኤክስ ሬይ ማይክሮቶሞግራፊን በመጠቀም የተሰራ ነው፡፡
ሌተርሎኪንግ ወይም ደብዳቤን በሚስጥራዊ መንገድ አሽጎ መላክ በጥንታዊው የሀገራት ስርዓት ውስጥ በጣም የተለመደ ነው፡፡ በዚህ ደብዳቤውን ሳይከፍቱ በማንበብ ሒደት የቅርስ ጥበቃ ሙያተኞች፣ ታሪክ አዋቂዎች፣ ኢንጅነሮች፣ የምስል ሙያተኞችና ሌሎች ተመራማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡ በዚህም የብዙዎች መተባበርና በጋራ መስራት ትልልቅ የሚባሉ ችግሮችን መፍታት የሚያስችል መሆኑን መረዳታቸውን ከተመራማሪዎቹ አንዱ ተናግረዋል፡፡
ያልተከፈተን ደብዳቤ ማንበብ የሚያስችለውን ስልተ ቀመር ያበለጸጉት ኤማንዳ ጋሻይ እና ሆሊ ጃክሰን የተባሉ በኤልክትሪካል ኢንጅነሪንግና ኮምፒውተር ሳይንስ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የሚሰሩ ተማሪ ተመራማሪዎች ናቸው፡፡ በዚህ ስልተ ቀመር በመጠቀም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ሐምሌ 31፣ 1697 የተጻፈ የአንድ ደብዳቤን ይዘት ማንበብ ችለዋል፡፡
ምንጭ SciTechDaily
ሀገራት እና ቅመማ ቅመሞች የበዛባቸው ምግቦቻቸው መነሻ
በሳይንሱ ዓለም ለምግብነት የምንጠቀማቸው የቅመማ ቅመሞች ነገር ሲነሳ ሁል ጊዜም በተመራማሪዎች መካከል ውዝግብን የሚፈጥር አንድ ጥያቄ አለ፤ ይህም ሞቃታማ የአየር ንብረት ያላቸው ሀገራት በዋናነት በቅመማ ቅመም የታጀበ ምግብ ሊኖራቸው ቻለ የሚለው ነው፡፡ አሁን ላይ ታድያ ከመላው ዓለም የተውጣጡ 34 ሺህ ያህል የምግብ አዘገጃጀቶች ላይ የተሰራ ትንታኔ ነገሮችን ይበልጥ ግልፅ እያደረገ ይገኛል፡፡
እንደተወሰኑ አጥኚዎች ጥርጣሬ ከሆነ በሞቃታማ አየር ንብረት ውስጥ የሚኖሩ ማህበረሰቦች ሚጥሚጣ፣ የሎሚ ሣር እና ሌሎችንም ቅመማ ቅመሞች መጠቀም የጀመሩት እነዚህ ቅመማ ቅመሞች በውስጣቸው ባለው የፀረ-ባክቴሪያ ይዘት እንዲሁም ምግቡ እንዳይመረዝና እንዳይበላሽ የማድረግ አቅም ስላላቸው ነው፡፡ ይህን ምልከታ ከአውስትራሊያ ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ የሆነችው ሊንድል ብሮማም እና አጋሮቿ በመካከላቸው 93 ዓይነት ቅመማ ቅመሞችን የያዙ 70 የምግብ አይነቶች ላይ ትንታኔን ሰርተዋል፡፡ አጥኚዎቹ አንድ የስታትስቲካዊ ሞዴል በማዘጋጀት እንደ ከባብያዊ የአዝእርት ብዝሀነቱ ያሉ ሁኔታዎች ከአካባቢው ምግቦች የቅመማ ቅመም ይዘት ጋር ይገናኝ እንደሆን መርምረዋል፡፡ ከዚህ ቀድሞ ከተሰሩት ጥናቶች በተለየ መልኩ የእነርሱ ጥናት በምግብ አይነቶቹ መካከል ያለውን መልከአ ምድራዊ እና የባህል ትስስር ከግምት ያገባ ነበር፡፡
በውጤቱ የአጥኚ ቡድኑ በየሀገራቱ ያለው የምግብ ቅመማ ቅመሞች አጠቃቀም ከምግብ አመጣሽ በሽታዎችም በላይ ከሌሎች መነሻዎች ጋር ይበልጥ እንደሚተሳሰር ለማወቅ ችለዋል፡፡ ታድያ የቅመማ ቅመም አጠቃቀሙም እንደ አማካኝ የዕድሜ ጣርያ እና ጥቅል ሀገራዊ ምርት (ጂዲፒ) ካሉ የማህበራዊ- ምጣኔ ሐብታዊ ሁኔታዎች ጋር የተሳሰረ ነው፡፡
ምንጭ፤ Nature
'Deep Nostalgia' የቆዩ ፎቶዎችን ነፍስ የሚዘራባቸው የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ስልት
==============================
ከአድዋ ክበረ-በዓል ጋር ተያይዞ የአፄ ምንሊክን ምስል በአዲሱ የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ስርዓት አማካኝነት አሁን ወደምንመለከተው ተንቀሳቃሽ ምስል መቀየር ተችሏል፡፡ ከ125 አመታት በፊት የተነሳውን ይህን የአፄ ምንሊክ ፎቶግራፍ ለእውነታ በቀረበ መልኩ እንዲህ ወደ ተንቀሳቃሽ ምስል የቀየረው አስገራሚ ቴክኖሎጂ ደግሞ 'Deep Nostalgia' የተባለው የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ስርዓት ነው፡፡
የማሽን ለርኒንግ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ቆየት ያሉ የሰዎች ምስሎችን እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችለው አዲሱ የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ስልት በእስራኤል መቀመጫውን ባደረገ MyHeritage በተባለ ኩባንያ የበለፀገ አስገራሚ የኦን ላይን አገልግሎት ነው፡፡ በሰዎች ቀደምት የዘር ሃረግ ወይም (genealogy) ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሰራው የኩባንያው አገልግሎት ቆየት ያሉ የፊት ምስሎችን በዲፕ ማሽን ለርኒንግ ትንተና ካደረገባቸው በኋላ ቀድሞ በተዘጋጀለት ሲስተም አማካኝነት ምስሎቹ አንዲንቀሳቀሱ ያስችላቸዋል፡፡
በየካቲት ወር መጀመሪያ ላይ ይፋ የተደረገው 'Deep Nostalgia' የተሰኝው የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ስልት ማንኛውንም ከአንገት በላይ ያለ የሰዎችን ወይም ሌሎች ተያያዥ ምስሎችን በመውሰድ የፈገግታ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ፣ ጭንቅላታቸውን እንዲነቀንቁ እና አይናቸውን እንዲያንቀሳቅሱ የሚያስችል የዲፕ ማሽን ለርኒንግ ስርዓት ቢዘጋጅለትም ከአንገት በታች ያለውን ምስል ለማንቀሳቀስ የሚያስችል ሲስተም ግን አልተሰራለትም፡፡ አሁን ላይ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ እንደመጡት የዲፕ ፌክ ቴክኖሎጂ ስርዓቶች ሁሉ ይህ የኦንላይን አገልግሎት የቆሞ ምስሎችን (static images) ለማንቀሳቀስ ቢችልም አንዳንድ የፊት እንቅስቃሴዎቹ ተፈጥሮአዊ ገፅታ የሌላቸው እና በቡድን የተነሱ ፎቶዎችን ማስተናገድ አለመቻሉ የሲስተሙ ሌሎች ውስንነቶች ናቸው፡፡
ይህ የማሽን ለርኒንግ ስልት ኩባንያው ባቀረበው የኦንላይን አገልግሎት አማካኝነት ሰዎች የሚፈልጉትን ምስሎች በሲስተሙ በማስገባት ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ወይም (animations) በቀላሉ እንዲፈጥሩ የሚያስችል ሲሆን፤ የሰዎችን የግላዊነት ጥበቃ ለማክበር እና መስሎች ያለአግባብ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ በማሰብም የተንቀሳቃሽ ምስሎቹ ውጤት ድምፅ አልባ እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡ D-ID ከተባለ የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ፕላትፎርም ጋር በትብብር የሚሰራው ይህ የኦን ላይን አገልግሎት ሰዎች የቆዩ የቤተሰቦቻቸን ፎቶዎች ወደተንቀሳቃሽ ምስል በመቀየር ናፍቆታቸውንና ስሜቶቻቸውን በቴክኖሎጂ በመታገዝ እንዲገልፁ ያለመ ነው፡፡
MyHeritage እንደአውሮፓውያኑ በ2003 ምስርታውን ካደረገ በኋላ ከቤተሰብ ጋር የተያያዘ የቆዩ ምስሎችን በአዲስ መልክ ለማቀናበር፣ ባዘጋጀው የኦን ላይን ዲ ኤን ኤ ምርመራ የራሳችን እና የዘመዶቻችን የስጋ ትስስር ለለማነፃፀር እና ሌሎች ከዘር ሃረግ ወይም (genealogy) ጋር የተያየዙ መረጃዎችን በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ በመታገዝ አስገራሚ ገፅታዎችን ለመፍጠር የሚያስችል የኦን ላይን ፕላትፎርም ነው፡፡
ምንጭ፡ Big Think እና myheritage.com/deep-nostalgia
በየዓመቱ ብዙ ሚሊዮኖችን ሊያጠግብ የሚችል ምግብ እንደ ቆሻሻ ይጣላል
=========================
በምድራችን በየዓመቱ ከሚመረተው ምግብ ውስጥ ከአንድ ስድስተኛ በላይ የሚሆነው ወደ ቆሻሻ እንደሚጣል የተባበሩት መንግስታት ጥናት አሳየ፡፡ እንደ ጥናቱ ከሆነ በአውሮፓውያኑ 2019 ብቻ 931 ሚሊዮን ቶን ምግብ ከቤቶች፣ ምግብ አከፋፋዮች፣ ሬስቱራንቶች እና ሌሎችም ስፍራዎች ወጥቶ ተጥሏል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ፕሮግራም (UNEP) ከአንድ በዚሁ በአካባቢ ጉዳይ ላይ አተኩሮ ከሚሰራ የእንግሊዝ በጎ አድራጎት ተቋም ጋር በመጣመር የሰራው ጥናቱ በተለያየ የገቢ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሀገራት ውስጥ ያለውን የምግብ ብክነት የአካዳሚክ ጥናቶችን እና መንግስታዊ መረጃዎችን በመሰብሰብ ተመልክቷል፡፡ በውጤቱም 17 በመቶ ያህሉ ምግብ ለሽያጭ የቀረበ ምግብ ወደ ቆሻሻ መጣያ እንደሚያመራ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከዚህ ብክነት ውስጥ ከፍ ያለው ድርሻ ማለትም 11 በመቶውን የሚወስደው ከቤቶች ወጥቶ የሚጣለው ነው፡፡ ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድ ሰው በአማካኝ 121 ኪሎ ግራም የሚመዝን ምግብ በየዓመቱ ይጥላል ማለት ሲሆን ከዚህ ውስጥ 74 ኪሎ ግራሙ የሚከሰተው በቤቶች ውስጥ ነው፡፡
ታድያ ይህ የምግብ ብክነት ባደጉት ሀገራት ብቻ የሚከሰት አይደለም፤ ጥናቱ እንዳረጋገጠው ከሆነ በሀብታም ሀገራት የሚገኙ ዜጎች በየቤታቸው በአማካኝ 79 ኪ.ግ ምግብን ወደቆሻሻ መጣያ ሲጥሉ በአነስተኛው መካከለኛ ገቢ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሀገራት ዜጎች ግን 91 ኪ.ግ ምግብን ከቤታቸው ያስወግዳሉ፡፡ ጥናቱ የሚበሉ እንዲሁም እንደ አጥንትና የአትክልት ልጣጭ ያሉትን መጣል ያለባቸው የማይበሉ አካላትን አካቶ የተሰራ ነው፡፡ በዝቅተኛው የመካከለኛ ገቢ ላይ የሚገኙት ሀገራት የምግብ ብክነታቸው ከፍ ለማለቱ ምናልባትም ዋነኛው ምክንያት ከፍተኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት በተቃራኒ ምግብን ሙሉ በሙሉ በራሳቸው ስለሚያዘጋጁት ሊሆን እንደሚችልም ተጠቁሟል፡፡ እዚህ ላይ ግን በተለይ በማደግ ላይ ባሉት ሀገራት ስላለው የሚበላም ሆነ ማይበላ ምግብ ከዚህም በላይ መረጃ እንደሚያስፈልግ የተባበሩት መንግስታት የከባቢ ፕሮግራም ቃል አቀባይ ተናግረዋል፡፡
ከእርሻ ላይ ሳይሰበሰብም ሆነ ከተሰበሰበ በኋላ እንዲሁም በገዢዎች እጅ ላይ የምግብ ብክነት ለአየር ንብረት ለውጥም የራሱን ድርሻ ይወስዳል፤ 9 በመቶ የሚሆነውን የበካይ ጋዝ ልቀት ድርሻን በመያዝ፡፡ በተጨማሪም ለግብርና የሚውለውን መሬት እና ውሃ ፍላጎት ጭምር እንዲያሻቅብ ያደርጋል፡፡
ይህን ያህል የምግብ ብክነት መኖሩን ይበልጥ አሳዛኝ የሚያደርገው በዓለማችን ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ሰው የምግብ እጥረት ያለበት መሆኑን ከግምት ስናስገባ ነው፡፡ የተባበሩት መንግስታት መጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ በኮሮና ቫይረስ አማካኝነት በከፍተኛ ደረጃ ማሻቀቡ ከከግምት ሳይገባ እንኳን በዓለማችን 690 ሚሊዮን ዜጎች ምግብ ሳይበሉ ወደ መኝታቸው የሚያመሩ ሲሆን 3 ቢሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ለጤና የተስማማ ምግብ በመመገብ ላይ አይገኙም፡፡
ምንጭ፤ New Scientist
ከኮሮና ያገገሙ ሰዎች በሽታው ሳይዛቸው ከተከተቡ ሰዎች 500 እጥፍ የሆነ የአንቲቦዲ ልዩነት አላቸው
*********************************
ከዚህ በፊት በኮሮና ቫይረስ ተይዘው ያገገሙ ሰዎች አንድ ክትባት ብቻ ቢከተቡ ከስጋት ነጻ እንደሚሆኑ ተነገረ፡፡ የሰውነት የበሽታ መከላከል አቅማቸው ቫይረሱ ሳይዛቸው ክትባቱን ከሚወስዱ ሰዎች እጅግ የተሸለ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡ በአሁኑ ወቅት በዘመቻ መልክ በተለያዩ ሀገራት ሁለት ብልቃጥ የኮሮና ክትባት ሰዎች እንዲከተቡ እየተደረገ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ምንም እንኳን የበሽታ ምልክት ሳይታይባቸው ከህመሙ ያገገሙ ሰዎች ከሁለቱ አንዱን ብቻ ቢከተቡ በቂያቸው እንደሆነ ጥናቶች አመልክተዋል፡፡
ተመራማሪዎች 59 የሚሆኑ የፊዘርንም ሆነ የሞደርናን ክትባት የወሰዱ የጤና ባለሙያዎችን የሰውነት የበሽታ የመከላከል ብቃት ለክተዋል፡፡ ከእነዚህ ፈቃደኞች አንዳንዶቹ ከ8 እና ከ9 ወራት በፊት በኮቪድ ተጠቅተው የነበሩ ናቸው፡፡ በዚህም ከዚህ በፊት በኮቪድ ተይዘው ያገገሙ ሰዎች የመጀመሪያውን ክትባት እንደወሰዱ የአንቲቦዲ መጠናቸው ከፍ ማለት ችሏል፡፡ በኮቪድ 19 ሳይጠቁ ክትባቱን ከወሰዱ ሰዎች አንቲቦዲ መጠን ጋር ሲወዳደርም የ500 እጥፍ ልዩነት እንዳለው ተረጋግጧል፡፡
በዚህም ምክንያት ከኮቪድ ያገገሙ ሰዎች እንደሁኔታው ታይቶ አንድ ክትባት እንዲያገኙ ወይም የክትባቱ የመጨረሻ ተጠቃሚዎች መሆን ይገባቸዋል ሲሉ የሜሪላንድ የህክምና ትምህርት ቤት ተመራማሪዎች ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል፡፡ እንደ ማሳያም በአሜሪካ 9 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ከኮሮና አገግሟል፡፡ ከዚህ ቁጥር ላይ አንድ ክትባት ማትረፍ ቢቻል ከ4 እስከ 5 በመቶ ክትባት ለሌሎች ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል ሲሉ አቅርበዋል፡፡
ምንጭ፡ Science news
ቴክ-ሳይንስ፤ ነገ በ10 ሰዓት ይጠብቁን
ከሪቪው መልስ በዚህ ሳምንት እንደቀድሞው በተለያዩ አስተማሪ ዝግጅቶች ይመለሳል፡፡ በበነገው መሰናዶዋችንም፤
በአብይ ፕሮግራም ፤ የቆዳ ምርምርን
በብላቴናት፤ አፍሪካን ኮድ አሸናፊዋ ሶልያና ግዛው
የቴክኖሎጂ ታሪክ፤ ቪዲዮ ጌም፡ ጅማሮው ምን ይመስላል? ጥቅምና ጉዳቶቹስ?
በተቋማት፤የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት
እንዲሁም በተመራማሪዎች ታሪክ በአ.አ ዩኒቨርሲቲ አክሊሉ ለማ ፓቶ ባዮሎጂ ኢንቲትዩት ውስጥ ተመራማሪ የሆኑትን ፕ/ር ምሩፅ ግደይን የመጀመሪያ ክፍል ይዘን እንቀርባለን፡፡
ከእርሰዎ የሚጠበቀው ነገ ቅዳሜ በ10 ሰዓት ወይም በድጋሚ ማክሰኞ ሰዓት ላይ የቻናል ምርጫዎን ወደ MOE TV በማድረግ መከታተለ ብቻ ነው፡፡ በተጨማሪም የዩትዩብ ቻናላችንን (https://www.youtube.com/channel/UC6jvUOLRSkVEQtc5Annfwvg) ሰብስክራይብ ማድረጉን እንዳይረሱ፤ ከዓመታት በፊት ከተላለፈው የመጀመሪየው ክፍል አንስቶ ያሉትን ሁሉንም የቴክ-ሳይንስ ፕሮግራሞች አንድ በአንድ መመልከትና ለእርስዎም ሆነ ቤተሰብዎ ዕውቀትን መገብየት ይችሉበታልና፡፡
ከ USB አስር እጥፍ የሚፈጥን የመረጃ ማስተላለፊያ ግኝት
***************************************
ተመራማሪዎች መረጃን በከፍተኛ ፍጥነት ማስተላለፍ የሚያስችል ስልትን ማበልጸጋቸው ተሰማ፡፡ ይህ የመረጃ ማስተላለፊያ ዘዴ ከመደበኛው የመረጃ ማስተላለፊያ ዘዴ አስር እጥፍ እንደሚፈጥን የተነገረለት ሲሆን በመረጃ ቋቶች አካባቢ የሚስተዋለውን የሐይል ፍላጎትም እንደሚያሻሽለው ተሰምቷል፡፡ በተጨማሪም ከፍኛ ፍሪኩየንሲ የሲልከን ቺፕ አና የፖሊመር ገመዶችን ይጠቀማል፡፡
ከርቀት ሆኖ የተለያዩ ስራዎችን መስራት እየተለመደ በመጣበት በዚህ ዘመን ፈጣን የመረጃ ማስተላለፊያ ዘዴዎች መኖራቸው እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በኮምፒውተር ቺፖች፣ ክላውድ ኮምፒውቲንግ፣ ኢንተርኔት እና በመሳሰሉት ከፍኛ የሆነ የመረጃ መተላለፍ ሂደት አለ፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው ደግሞ በተለመደው የኮፐር ሽቦ ወይም ገመድ አማካኝነት ነው፡፡ እንደ USB እና HDMI ባሉ መረጃ ማስተላለፊያዎች ውስጥ የሚገኘው የኮፐር ሽቦ ከፍተኛ መጠን ያላቸውን መረጃዎች በሚያስተላልፉ ጊዜ ክፍ ያለ የሀይል ፍልጎት አላቸው፡፡ በሚባክነው ሀይልና በሚተላለፈው መረጃ መካከል አለመመጣጠን አለ፡፡
በአሁኑ ሰዓት የመረጃ በፍጥነት መተላለፍ ፍላጎት በሴኮንድ 100 ጌጋ ባይት ድረስ እያደገ ቢሆንም የመረጃ ማስተላለፊያ መንገዱ ግን አሁንም ረጃጅም የኮፐር ገመዶችን በመጠቀም ነው፡፡ ከኮፐር ገመዶች ውጭ ሌላኛው አማራጭ የመረጃ ማስተላለፊያ ፋይበር ኦፕቲክ ገመድ ሲሆን እሱም ቢሆን የራሱ የሆኑ ውስንነቶች ያሉበት ነው፡፡ ይህ ፎቶኖችን የሚጠቀመው የመረጃ ማስተላለፊያ ቁስ መረጃን በፍጥነትና በቀላል ሀይል የሚያስተላልፍ ቢሆንም የሲልከን ኮምፒውተር ቺፖች ፎቶኖችን ለመጠቀም አያስችሉም፡፡ በአሁኑ ሰዓት የፋይበር ኦፕቲክስ መረጃ ማስተላለፊያ መንገድ የሆኑትን ፎቶኖች በሲልከን እንዲሰሩ የማድረጊያ ዘዴዎች የሉም፡፡ እነዚህና መሰል ችግሮች መኖራቸው ተመራማሪዎች ሌላ ፈጣንና ሀይል ቆጣቢ የሆነ መንገድን እንዲያስቡ አስገድዷቸዋል፡፡
የምርምር ቡድኑም በኮፐር እና በፋይበር ገመዶች የሚስተዋሉ ችግሮችን በማሻሻል አዲስ ስልትን ማበልጸጉን ተናግሯል፡፡ አዲሱ ግኝት በፕላስቲክ ፖሊመር የተሰራ በመሆኑና እጅግ ቀላልና ከተለመዱ ገመዶች በተቃራኒው በቀላል ወጭ መመረት የሚችል ነው፡፡ እንዲሁም ግኝቱ ያለተጨማሪ ግብዓት ከሲልከን ቺፖች ጋር ተዋህዶ መስራት የሚችል ነው፡፡
ምንጭ SciTechDaily
በማቴሪያል ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ ፈርቀዳጅ የሆነችው ኢትዮጵያዊት ተመራማሪ፡ ፕሮፌሰር ሶስና ኃይሌ
===========================
ዛሬ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ነውና እኛም ከዚህ ቀደም ወደ እናንተ ካደረስናቸው ፅሁፎቻችን መካከል ዕውቋን የሀገራችን የሳይንስ ኮከብ ፕ/ር ሶስና ኃይሌን የቃኘንበት ፅሁፋችንን መልሰን ልናስነብባችሁ ወደድን፡፡ አብራችሁን ቆዩ፡፡
ፕሮፌሰር ሶስና ኃይሌ እ.ኢ.አ በ 1958 ከአዲስ አባባ የተገኘች ኢትዮጵያዊት ሳይንቲስት ናት፡፡ በ1967 በሃገሪቱ የመንግስት ለውጥ መምጣት ተከትሎ ከቤተሰቦቿ ጋር ወደ አሜሪካ ለመሰደድ የተገደደችው ፐሮፌሰር ሶስና አብዛኛውን የህይወት ጊዜዋንም በዚህ አንድታሳልፍ ሆናለች፡፡ ፐሮፌሰር ሶስና ከቤተሰቦቿ ጋር አብራ በመሆን የልጅነት ጊዜዋን በሚኒሶታ ሃገረ ግዛት ገጠራማ አካባቢ ካደረገች በኋላ በ1986 የመጀመሪያ ዲግሪዋን በማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት በማቴሪያል ሳይንስና በኢንጂነሪንግ ማግኘት የቻለች ሲሆን፤ ሁለተኛ ዲግሪዋን ደግሞ በካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ በተመሳሳይ የትምህርት ዘርፍ ማሳካት ችላለች፡፡
ፐሮፌሰር ሶስና በቀጣዮቹ ጥቂት ዓመታት የፒችዲ ትምህርቷን ለመማር እንዲያስችላት የመጀመሪያ ዲግሪዋን ካገኘችበት የማሳቹሴትስ የቴክኒሎጂ ኢኒስቲትዩት ያቀናች ሲሆን፤ በዚህም እንዲሁ በምትወደው የማቴሪያል ሳይንስና ኢንጂነሪንግ ዘርፍ መመረቅ ችላለች፡፡ ፐሮፌሰር ሶስና ከዚህ የተሳካ የትምህርት ጉዞዋ በኋላ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ካገኘችበት የካልቴክ ፋካልቲ ከማምራቷ በፊት ሲያትል በሚገኘው የዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ በረዳት ፕሮፌሰርነት የሰራች ሲሆን በዚህ የሶስት ዓመት ቆይታዋም ሀገሯን የሚያኮራና አፍሪካንም የሚያስጠራ ትልልቅ የምርምር ስራዎችን ለመስራት በቅታለች፡፡
ፐሮፌሰር ሶስና ድምራቸው ከ150 በላይ የሆነ የጥናትና ምርምር ፅሁፎችን በግል እና ከሌሎች ምሁራን ጋር በጋራ በመቀናጀት ሰርታ ለህትመት አብቅታለች፡፡ በስሟ የተመዘገቡላት ፓተንቶችም ቢሆን አስራ አምስትን ተሻግረዋል፡፡
ከነዚህ የህትመት እና ምርምር ውጤቶች ውስጥ ብዙሃኑ በጠጣር የአዮን ቁስ እና መሳሪያዎች ላይ ያጠነጠኑ ናቸው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከሚያጠነጥኑት የፕሮፌሰር ሶስና ስራዎች መካከል ደግሞ ከዓመታት በፊት የሰሩት አዲስ ዓይነት የፊውል ሴል ከሌሎች ፈጠራዎቿ ይጠቀሳል፡፡ በወቅቱ ሶስና ኬሚካሎችን ወደ ኤሌክትሪክ ሃይል በመቀየር ለመኪኖች፣ ሃይል ማመንጫዎች እንዲሁም ሌሎች ሃይልን ለሚጠይቁ ተግባራት ንፁህ የሃይል ምንጭ በመሆን እንዲያገለግለ፤ በማሰብ የፊውል ሴሎችን በከፍተኛ ደረጃ የሚያሻሽል ቁስን ለመስራት አልማ ተነሳች፡፡ ይህ ሃሳቧም በአይነቱ አዲስ የሆነ የኃይል ማመንጫን ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ሊቀንስ የሚችል የሱፐርፕሮቶኒክ ቅንብር መስራትን ያጠቃልላል፡፡ ሆኖም ይህ ሃሳቧን ተቀብለው የአሰራር ስርዓታቸውን ሙሉ በሙሉ ወደ አዲስ ከመቀየር የታቀቡት የፊውል ሴል አምራቾች የራሷን ቤተ-ሙከራ ተጠቅማ በዓለም የመጀመሪያውን ጠጣር የአሲድ ፊውል ሴል ቁስ አካል እንድትፈበርክ ምክንያት ሆኗት፡፡ ኋላ ላይ ይህን አዲስ ፈጠራዋን የቀድሞ ተማሪዎቿ በንግድ ሰርቶ ማሳያነት የተጠቀመበት ሲሆን ለተመራሪዋም በአረንጓዴ የሃይል ልማት ዘርፍ ዕውቅናን እንድትሸምትበት አስችሏታል፡፡
ፕሮፌሰር ሶስና በአሁኑ ሰዓት ጠጣር ፊውል ሴሎችን በተለይም ለከባቢ ተስማሚ የሃይል ምንጭ መሆን በሚችሉት ላይ አተኩሮ የሚሰራን የምርምር ቡድን በሃላፊነት በመምራት ላይ ትገኛለች፡፡ በዚህ ረገድ ይህ ቡድን የተለያዩ ስኬቶችን በማስመዝገብ ላይ ሲገኝ ከቅርብ ስኬቶቹ መካከልም ውሃና ካርቦን ዳይ ኦክሳይድን በቴርሞ ኬሚካል ሂደት አማካኝነት በመጠቀም የፀሐይን ኃይል ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ ሌላ ምዕራፍን የከፈተ ነበር፡፡ በፕሮፌሰር ሃና እና ቡድኗ እየተሰራባቸው ካሉት ስራዎች ውስጥ ፕሩቶንን አስተላላፊ ጠጣር አሲድ እና ፐሮቭስካይት ኤሌክትሮይቶች፣ የኤሌክትሮን እና ኦክስጅን ድብልቅን አስተላላፊ ፍሎሪት እና ፐሮቭስካይት እንዲሁም ኢ-ስቶይኪዮሜትሪክ ኦክሳይዶችን ማበልፀግ ይገኝበታል፡፡
ይህች ኢትዮጵያዊት እንቁ ተመራማሪ በትልቁ ስሟን ከሚያስጠሩ ስራዎቿ አንዱ ከሆነው የፊውል ሴል ፈጠራዋ በተጨማሪ በሴራሚክ ሳይንስ፣ በኤሌክትሮኬሚካል እና በፋንክሽናል ሶሊድ (electrochemical and functional solids) የደረገቻቸው ምርምሮች እና ያሳተመቻቸው ፅሁፎች በተሰማራችበት የሳይንስ ዘርፍ ከሚኖረው አበርክቶት ባለፈ ለብዙ ወጣት ኢትዮጵያውያን እና ሴት ተመራማሪዎች የሚኖረው ጠንካራ መልእክት ቀላል የሚባል አይደለም፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ ፐሮፌሰር ሶስና ለሰራቸው ስራና ላበረከተችው የምርምር ውጤት እውቅና የሚሆን ሽልማቶችን ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ያገኘች ሲሆን ከእንዚህ ውስጥም በ1989 በማቴሪያል ሳይንስ ባደረገችው ሰፊ ምርምር ያገኘችው የሃርዲ አዋርድ፣ በ2002 በፊውል ሴል ፈጠራዋ ያገኘችው የኬሚካል ፖይነር አዋርድ እንዲሁም በ2004 በሴራሚክ ሳይንስ ምርምሯ ያገኘቸው የዓለም አቀፍ የሴራሚክ ፕራይዝ በጥቂቱ የሚጠቀሱ የእውቅና ሽልማቶቿ ናቸው፡፡
ምንጭ፡ ቴክ-ሳይንስ ቅፅ 15
መልካም የሴቶች ቀን ይሁንላችሁ !!!