TechIn2
1.22K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
ዓለምን ለማጥፋት ያልማሉ? ቁልፉ ይኸውልዎ
ለዘመናት ጨካኝ የሳይንስ ተመራማሪዎች ዓለምን ለማጥፋት የሚያስችላቸውን መንገድ ለመያዝና ተጠቅሞ በማስፈራራት ንዋይ፣ ጉልበት፣ ዕውቅና እና ክብር ማግኘትን ሲያልሙ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም ይህን ማድረግ ቀላል ተግባር አይደለም፡፡ አደገኛ የኒውክለር መሳሪያዎችን፣ ሰዎችን ሁሉ ማጥፋት የሚችል በሽታ በማሰራጨት አሊያም ከባቢ አየርን በማጥፋት ህይወት ያለውን ፍጡር ሁሉ መኖሪያ በማሳጣት ምድርን ህይወት አልባ ስፍራ ማድረግ ይቻል የሆናል፡፡ ግን ይህ ሁሉ ሆኖም ቢሆን ከስራችን ያለው ድንጋይ ህይወት አልባ ሆኖ በዛቢያው እና ፀሐይ ዙሪያ ከመሽከርከር በቀር ምንም የከፋ ጉዳት አያጋጥመውም፡፡ ታድያ እርስዎም ምድርን እስከነ ጭራሿ ለማጥፋት ከሚያልሙት አንዱ ከሆኑ ተከታዮቹን ሂደቶች መጓዝ የግድ ይልዎታል፡-
፩ኛ. ሂሳቡን በትክክል ያስሉት
ፕላኔታችን ተያይዛ ያለችው በራሷ ስበት አማካኝነት ነው፡፡ ልክ ከድንጋይ እንደተሰራ ሽንኩርት ናት፡፡ በጥልቁ የውስጣዊ ስፍራዋ የሚገኘው ኮር የተባለው አካል በላዩ ላይ ተደርቦበት የሚገኘውን ንጣፍ አጣብቆ ይይዛል፡፡ ከዚያም የሁለቱ ድምር የስበት ኃይል ተከታዩን ድርብ ንጣፍ አጣብቆ ይይዘዋል፡፡ ይሄም ተከታዩን፤ በተመሳሳይ መንገድ እያጣበቀ በመጨረሻም እኛን እና ለኑሮ የሚያስፈልጉንን ግብዓቶች ሁሉ ስቦ አስቀምጧል፡፡ ስለዚህ ምድርን ማጥፋት ከፈለጉ ይህችን የቅልጥ እና ደረቅ ድንጋይ ንብርብር የሆነች ሽንኩርት አንድ በአንድ ንጣፍ በንጣፍ መገነጣጠል እና ወደ ጠፈር እንዲቀኑ ማድረግ ይጠበቅብዎታል፡፡ ታድያ ይህ ሲሆን ወደ ጠፈር የላኩት ድንጋይ በምድር የስበት ኃይል ተጎትቶ ዳግም እንዳይመጣ ማድረጎን እንዳይረሱ፡፡ በሌላ ቋንቋ ሁሉም ቁሶች ከምድራዊ የስበት ቀንበር ነፃ ማውጣት አለብዎ፤ ግን ቀላል አይሆንልዎትም፡፡
በተለምዶአዊው መንገድ ይህን ለማድረግ ግዙፍ ሮኬቶችን ተጠቅመው የምድርን አለት አንድ በአንድ ቶን በቶን ከምድራችን ምህዋር እስኪርቁ መሸኘት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ሂደት ከምድር ላይ አንድ ኪ.ግ ድንጋይ ባጎደሉ ቁጥር የስበት ኃይሏን በአንድ ኪ.ግ ይቀንሱባታል፡፡ ስለዚህም ቀጣዩን ድንጋይ ለማሸሽ ቀላል እየሆነልዎ ይመጣል፡፡
ይህን ሂደት ተከትሎ ምድርን ለመገነጣጠል የሚያስፈልገው ኃይል እኩሌታ ታድያ ምድርን አጣብቆ ለመያዝ ከሚያስፈልገው ኃይል መብለጥ አለበት፡፡ ታድያ ምድርን ለመገነጣጠል ካሰቡ በትንሹ 10^32 ጁልስ (Joules) የሚሆን ኃይል ያስፈልግዎታል፡፡
፪ኛ. ኃይል ማሰባሰብ
ከላይ የተቀመጠው ኃይል እጅግ ብዙ ነው፡፡ ለንፅፅር እንኳን ብናይ የማገዶ እንጨት፣ ሞተር እና ኤሌክትሪክን ጨምሮ የሰው ልጅ በ2013 የተጠቀመው እያንዳንዱ ኃይል ቢደመር መጠኑ 10^20 ጁልስ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን የሰው ልጅ እየተጠቀመ ያለውን ኃይል አንድም ሳያስቀሩ እንኳን ምድርን ለመገነጣጠል ተግባር ለማዋል ከከጀሉ አስፈላጊውን ኃይል አሰባስቦ ለመጨረስ አንድ ትሪሊዮን አመታትን መጠበቅ ይኖርብዎታል፡፡ ሆኖም ይህን ማድረግ ስለማይቻልዎ (የእርስዎ ዕድሜ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የኃይል ምንጮቻችን መሰረት የሆነችው ፀሐይ እንኳን ከዚህ በኋላ የቀራት ዕድሜ አምስት ቢሊዮን አመታት ብቻ ስለሆነም ጭምር እንጂ) ከሌላ ዕቅድ እናስተዋውቅዎ፡፡
ፀሐይ የምታመነጨውን ኃይል ቢጠቀሙስ? አዎ ፀሐይ በየአንዳንዱ ሴኮንድ ውስጥ 4 ሚሊዮን ቶን የሚሆን ሃይድሮጅንን ስትጠቀም፤ በውጤቱም ወደ ሂሊየም በመቀየር ወይም ፊዩዝ በማድረግ እጅግ ከፍተኛ ኃይልን በጨረር መልክ ትለቃለች፡፡ ፀሐይ ከምታመነጨው ይህ ሁሉ ኃይል ውስጥ ቅንጣት ያህሉ ብቻ ምድር ላይ ሲደርስ ሌላው በህዋ ላይ ባክኖ ይቀራል፡፡ ምድርን ከሚነካው የፀሐይ ኃይል መጠቀም አንደኛው የኃይል ማሰባሰቢያ መንገድ ነው፡፡ ይህን አልጌዎች ከቢሊዮን ዓመታት በፊት አንስቶ እያደረጉት ያሉት ተግባር ሲሆን እኛም ቢሆን ምሳና እራታችንን የምናገኘው ከዚህ ሂደት ተነስቶ የምግብ ሰንሰለቶችን (Food Chain) በማለፍ የሚቀርብልንን ምግብ ነው፡፡
፫ኛ. የጊዜ ጉዳይ
እንደተገለፀው ምድር ላይ የሚያርፈውን የፀሐይ ኃይል ምድርን በፀሐይ ኃይል ማመንጫዎች (Solar Panels) ሸፍነዋት ሙሉ በሙሉ መጠቀም ከቻሉ ምድርን ለመበተን የሚያስችልዎትን ኃይል በ18 ሚሊዮን ዓመታት ውስጥ ማግኘት ይችላሉ፡፡ ይህ ትሪሊዮን ዓመታትን ከሚፈልገው የቀድሞው ዕቅድ አንፃር እጅግ የተሻለ ቢሆንም 18 ሚሊዮን ዓመታትን እንደማይኖሩ ግን መገመት ይቻላል፡፡ ከዚህ በተለየ ግን ፀሐይ የምታመነጨውን ኃይል አንድም ሳያባክኑ መጠቀሚያ ዘዴ ካበጁ የተሻለ ውጤት ያገኛሉ፡፡ ፀሐይ ከምታመነጨው ኃይል ውስጥ አንድ ቢሊየንኛው ብቻ ነው ምድርን የሚነካት፤ መላው የፀሐይን ኃይል መጠቀም ከቻሉ ግን ምድርን እንዲበታትኗት የሚያስችሎትን ኃይል በአንድ ሳምንት ውስጥ ብቻ ማግኘት ይችላሉ፡፡
ምንጭ፡ Space.Com
የዝሆኔ በሽታን በሚከላከሉ ምርቶች ላይ የዘጠና ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ሊደረግ ነው
**********************************************መቀመጫውን አሜሪካን ያደረገው ፈርትል ክርኤቲቭ ላብስ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ከሼዲ ግሮቭ ግሩፕ አማካሪ ተቋም ጋር በሚሰሯቸው የዝሆኔ በሽታን (Mycetoma) ተከላካይ ጓንት እና ጫማዎች ዙሪያ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት ውስጥ ውይይት አድርገዋል፡፡ በውይይቱም የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌታሁን መኩሪያ እንዲሁም የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳንዱካን ደበበን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት ተወካዮች የተሳተፉበት ሲሆን የፈርትል ክርኤቲቭ ላብስ እና ሼዲ ግሮቭ ገሩፕ ሃላፊ የሆኑት ዶ/ር ሙሉጌታ አለምሰገድ እና ዶ/ር ደረጄ ተሰማ ተገኝተውበታል፡፡ ተቋሙ በኢትዮጵያ ለማምረት ስላቀዳቸው የዝሆኔ በሽታን መከላከያዎች በዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር ሙሉጌታ አለምሰገድ አማካኝነት ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን ስለ ተቋማቸው ምንነት፣ ስለሚያከናውኗቸው ተግባራት እንዲሁም ለኢትዮጵያ ሊያመጡ ባቀዷቸው ትሩፋቶች ዙሪያ ለታዳሚዎቹ ገለፃ አቅርበዋል፡፡
ፕሮጀክቱ እነዚህን የመከላከያ ጓንት እና ጫማዎችን የዝሆኔ በሽታ በብዛት በሚታይባቸው አራት ዋና ዋና የዓለማችን ክፍሎች የሚያሰራጭ ሲሆን ኢትዮጵያም ከሌሎች የአፍሪካ ቀንድ ሃገራት ጋር በጋራ በመሆን ዞን አንድ ውስጥ ተካታለች፡፡ ታድያ የመከላከያዎቹ ቅድመ ምርት ስራዎቹ በሃገረ አሜሪካን የሚሰሩ ሲሆን የማምረት እና ማሰራጨት ተግባራቱ ግን እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ይከወናሉ፡፡ በዚህም ሳቢያ የዘጠና ሚሊዮን ዶላር መዋዕለ ንዋይ ፈሰስ ኢትዮጵያ ውስጥ ለማድረግ ታቅዷል፡፡ ይህም 1,600 የፋብሪካ ውስጥ እና 2,400 ከምርት ሽያጭ ጋር ለተገናኙ የስራ ዕድሎች መፈጠር ምክንያት እንደሚሆን ታምኖበታል፡፡ ምርቱን ተግባራዊ ለማድረግ ከተለያዩ የሃገሪቱ የምርምር እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በጋራ እንደሚሰሩ ዶ/ር ዮናታን በውይይቱ የገለፁ ሲሆን ከመንግስት አፋጣኝ የኢንቨስትመንት ፍቃድን ከማግኘት አንስቶ የተለያዩ ድጋፎች ይደረግላቸው ዘንድ ጥያቄን አቅርበዋል፡፡
ፈርትል ክርኤቲቭ ላብስ መቀመጫውን ሚሺጋን አሜሪካን ውስጥ በማድረግ የተመሰረተና እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ካሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በጋራ የሚሰራ ኩባንያ ሲሆን በምርምር እና ስርፀት ላይ ትኩረቱን በማድረግ ይንቀሳቀሳል፡፡ ሳና ብሎ የሰየማቸው የዝሆኔ በሽታን መከላከያ ጫማና ጓንቶቹም በአይነታቸው የመጀመሪያ ናቸው፡፡ እነዚህ ምርቶች ፀረ-ባክቴሪያ እና ውሃን የማያሳልፉ ከመሆናቸውም ባሻገር ምቹና ሌሎች ገፅታዎችንም አቅፈው የያዙ ናቸው፡፡ የምርት ሂደታቸውም በዋነኝነት በ3ዲ ማተሚያ ማሽኖች ላይ የተመሰረተ ነው፡፡
ከባድ አጫሾች ዓይናቸው ሊጠፋ ይችላል
***************************************
ምንም እንኳን ማጨስ በጤናችን ላይ የሚያስከትለውን ትልቅ አደጋ የሚያመላክቱ የተለያዩ ሳይንሳዊ እውነታዎችና ማረጋገጫዎች መውጣታቸውን የቀጠሉ ቢሆንም አሁንም ሰዎች ጆሮ ዳባ በሚመስል መልኩ ማጨሳቸውን ቀጥለዋል፡፡

እስካሁን ድረስ እንኳን በተረጋገጡ ጥናቶች መሰረት ማጨስ ከሚያመጣብን ከፍተኛ የጤና ጉዳት መካከል አስም፣ የሳምባ በሽታ፣ ስትሮክ እና ካንሰር በቀዳሚነት የሚጠቀሱ በሽታዎች ናቸው፡፡ ከዚህ ባለፈ ከልብ ችግር ጋር በተገናኘ በየቀኑ አንድ ሲጋራ የሚያጨስ ሰው ለልብ በሸታ የመጋለጥ እድሉ በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ታዲያ ሰሞኑን በወጣ አንድ ጥናት በከባድ ሁኔታ ሲጋራ ማጨስ ከላይ ከተጠቀሱት በሽታዎች ባሻገር ለእውርነት እንደሚዳርግ ተገልጿል፡፡ በአሜሪካ ሩትጀርስ ዩኒቨርስቲ በተከናወነው በዚህ ጥናት ተመራማሪዎች እንደገለፁት ከሆነ በቀን ውስጥ ከ20 በላይ ሲጋራዎችን የሚጨስ ሰው የዓይን መታወር ሊደርስበት እንደሚችል ገልፀዋል፡፡

ጥናቱ ላይ ከ25 እስከ 45 የሚገመቱ 71 ሰዎች በጠቅላለው የተሳፉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥም ትንሽ ቁጥር ያለቸው አልፎ አልፎ የሚያጨሱና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ደግሞ ከ20 በላይ ሲጋራዎችን በየቀኑ የሚያጨሱ እና ከሱሳቸው ማየል የተነሳ አንድም ጊዜ ለማቆም የልሞከሩ ናቸው፡፡ በዚህም መሰረት ተመራማሪዎቹ የተሳተፊዎቹን የቀለም ልየታና የዕይታ ንፅፅር ለመረዳት እንዲያስችላቸው 19-ኢንች ከሚሆን የካቶድ ሬይ መቆጣጠሪያ 59 ኢንች ርቀው አንዲቀመጡ ካደረጉ በኋላ ስቲሙሊው (stimuli) እንዲገለፅና ሁለቱም ዓይኖቻቸው እንዲመረመሩ ተደርጓል፡፡

በወጤቱም መሰረት አጥኘዎቹ እንደገለፁት በአጫሾቹ የቀለም ልየታ ላይ ሰፊ ለውጥ ማየታቸውን ተናግረዋል፡፡ በተለይም የጥናቱ ዋና መሪ ስቴቨን ሲልቨርስቲን እንደሚናገሩት በሲጋራ ውስጥ ለፍጆታ የሚውሉት የኒዩሮቶክሲክ ኬሚካሎች የአዕምሮን የዕይታ ማመዛዘኛ ሂደት በማሰተጓጎል ወይም እንቅስቃሴውን በመቀነስ አጠቃላይ የእይታ አቅምን አንደሚያዳክም ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ተመራማሪው እንደሚገልፁት ከባድ አጫሾች የዕይታ ንፅፅር አቅማቸው ሳይቀር አልፎ አልፎ ከሚያጨሱት ተሳታፊዎች አንፃር በእጅጉ እንደሚቀንስ ተናግረዋል፡፡

ምንጭ፡ Tech Explorist
የዓለማችን ግዙፉ ንብ ዳግም ተገኘ
******************************
የዓለማችን ግዙፉ ንብ በዓለም ዓቀፍ አጥኚዎች አማካኝነት ገጠራማው የኢንዶኔዚያ ክፍል ውስጥ መገኘቱ ትናንት ይፋ ተደርጓል፡፡ ሜጋቺሊ ፕሉቶ ወይም በተለምዶው አጠራሩ የዋላስ ግዙፍ ንብ ተብሎ የሚጠራው ይህ የንብ ዝርያ የአራት ሴ.ሜ ርዝማኔ ሲኖረው የክንፎቹም ስፋት እስከ 7.5 ሴ.ሜ ይለካል፡፡ ለንፅፅር ብናቀርበው እንኳን ንቡ የሰውን ልጅ አውራ ጣት በሚስተካከል መጠን ላይ ይገኛል፡፡
በፕሪንስቶን ዩኒቨርሲቴ የኤቲሞሎጂ ምሁሩ ኤሊ ዋይማን ከሁለት ሳይንቲስት እና አንድ ፎቶ አንሺ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ከወር በፊት ነበር የሁለት ሳምንታት አሰሳውን የጀመሩት፡፡ አሰሳውም ንቡ ከዚህ በፊት እንደታየባቸው የሚነገርባቸውን ሶስት የኢንዶኔዢያ ደሴቶች ያካለለ ነው፡፡ በመጨረሻም ለሰላሳ ስምንት ዓመታት ከዓለም ዕይታ ተሰውሮ የቆየው ይህ ንብ ባሳለፍነው ወር ሞሉካስ በተሰኘው ደሴት ላይ ነበር ተመራማሪዎቹ ያገኙት፡፡
ይህ የንብ ዝርያ ዳግም ጠፍቶ ሲገኝ የአሁኑ የመጀመሪያው አልሆነም፡፡ በቀዳሚነት በእንግሊዛዊው ናቹራሊስት አልፍሬድ ሩሴል ዋላስ አማካኝነት ከተገኘበት እ.አ.አ 1858 አንስቶ በአሜሪካዊው ኤቲሞሎጂስት አዳም ሜሰር አማካኝነት ዳግም እስከተገኙበት 1981 ድረስ በሳይንሱ ዓለም እንደጠፋ ይቆጠር ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ ባለፉት ዓመታት ውስጥ ከዓይን ከመሰወሩ ባሻገር ግሎባል ዋይልድ ላይፍ ኮንሰርቬሽን በተሰኘው ተቋም አማካኝነት 25 እጅግ ከሚፈለጉ የነፍሳት ዝርያዎች ተመድቦ ቆይቷል፡፡
ምንጭ፡ Science News
ለምን እናዛጋለን? ሳይንሳዊ ብያኔ
*******************************
ሰዎች ስለማዛጋት ሲሰሙም ሆነ ሲያነቡ ቀጥታ ሊያዛጉ እንደሚችሉ በጉዳዩ ላይ ምርምር ያካሄዱ ባለሙያዎች ይገልፃሉ፡፡ በዚህም የተነሳ ምናልበትም ይህን ፅሀፍ አያነበቡ ባሉበት ወቅት ከመቅፅበት አዛግተው ሊሆን ይችላል፡፡

ለመሆኑ ግን ማዛጋት የተለየ ሳይንሳዊ ምክንያት ይኖረው ይሆን? ሰዎችስ ተኝተው ከተነሱ በኋላ አልያም አንድን ስራ ጨርሰው ወደሌላ ለማለፍ በሚጥሩበት ወቅት ማዛጋት ተደጋግሞ የሚመጣው ለምን ይሆን? ለእነዚህ እና ሌሎች መሰል ጥያቂዎች ሳይንስ የሚሰጠውን ብያኔ እንመልከት፡፡

ሰዎች ከመኝታ በኋላ ሲነቁ፣ በስራ ሲደክሙ፣ ሲደብራቸው አልያም የሆነ አዲስ ነገር ለመጀመር ሲያስቡ ማዛጋት ከመቅፅበት ሊመጣባቸው ይችላል፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን በቅርባቸው ያለ ሰው ሲያዛጋ ከተመለከቱ በደቂቃ ልዩነት ውስጥ አነሱም ሊያዛጉ ይችላሉ፡፡ ይህ ደግሞ ማዛጋት የሚባለው ነገር አንዳች ተላላፊ (contagious) ባህሪ የያዘ ነው የሚል ብያኔ አንዲኖር አድርጓል፡፡

ከዚህ ባለፈ ግን በኒዎርክ ፖሊቴክኒክ ኢኒስቲትዩት የተደረገ አንድ የሳይንቲስቶች ጥናት የማዛጋት ምክንያትን ሲያስቀምጥ የአእምሮ ማቀዝቀዣ ዘዴ ወይም (brain cooling mechanism) ነው ብሎ ይበይናል፡፡ ይህንንም ሲያብራራ ሰዎች በሚያዛጉበት ወቅት መንጋጋቸውን በሰፊው ከፍተው አየር ወደ ውስጣቸው ከሳቡ በኋላ ከመቅፅበት ወደ ውጭ የሚተነፍሱበት ሂደት አለ፡፡ ይህ ደግሞ ወደ ራስ ቅል የሚሄደውን ከፍተኛ የደም ፍሰት በማፋጠን የሴሬብራል ቅዝቃዜን ይጨምረዋል፡፡ ስለዚህም በሰውነታችን ውስጥ ያለው የሙቀት መጠን ከፍተኛ ሲሆን የድካምና የእንቅልፍ ስሜት የሚሰማን በመሆኑ ይህን ስሜት ለመገደብ ማዛጋት አይነተኛው መንገድ እንደሆነ ያስቀምጣሉ፡፡

ይህም በሌላ አገላለፅ ዶክተር ጋለፕ እንደሚሉት አዕምሯችን የማዘዣ ጣቢያ እንደመሆኑ መጠን ራሱን ዝግጁ ለማድረግና ለቀጣዩም አንቅስቃሴ ሌሎቹን የሰውነት ክፍሎቻችንን ለማዘጋጀት እንዲረዳው የሚደርገው የማንቃት እና የመቀስቀስ ድርጊት ነው ብለው ይገልፁታል፡፡

ይህ ብያኔ አስካሁን ብዙዎች የሚቀበሉት ቢሆንም ለሌላ ሳይንሳዊ አመክንዮች ክፍት መሆኑን የሚናገሩት ተመራማሪዎቹ በማዛጋት ዙሪያ ሁላችንም እርግጣኛ መሆን ያለብን ግን ስለማዛጋት ተላላፊነት (contagiousness) ነው ይላሉ፡፡
ምንጭ፡ The New York Times
የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት ሰራተኞች የደም ልገሳ አከናወኑ

የደም ልገሳ ለተቀባዩ ህይወት፤ ለለጋሹም የህሊና ሐሴት ብሎም ሰብዓዊ ሃላፊነት ነው፡፡ ይህን የተረዱት የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት ሰራተኞችም በትናንትናው ዕለት በኢኒስቲትዩቱ ቅጥር ውስጥ የደም ልገሳን በማከናወን ሰብዓዊ ሃላፊነታቸውን ተወጥተዋል፡፡ የደም ልግሳው “ላማባዲና” በተሰኘው የተቋሙ ሰራተኞች ሶሻል ኮሚቴ አዘጋጅነት የሚካሄድ ሲሆን በየሶስት ወራት ልዩነት ይደረጋል፡፡ የተቋሙ ሰራተኞች ይህን መሰል በጎ ተግባራትን በተለያዩ ወቅቶች ከውነው አልፈዋል፡፡ በደም ልገሳ ረገድም የአሁኑን ጨምሮ ለስምንት ጊዜያት ደም የመለገስ ስነ-ስርዓት ተካሂዷል፡፡
በበጎ ፍቃድ የሚለገስ ደም በአደጋና ሌሎች ሁናቴዎች ምክንያት ደም ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ብቸኛው የደም ምንጭ እና ህይወትን ማስቀጠያ መንገድ ነው፡፡ በዓለም ላይ በዓመት እስከ 80 ሚሊዮን ዩኒት የሚሆን ደም ከበጎ ፍቃደኞች የሚሰበሰብ ቢሆንም የደም ልገሳ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት ውስጥ በዝቅተኛ ደረጃ ይከወነል፡፡ ለአብነት እንኳን ብናይ ከሰሃራ በታች ባሉ ሃገራት ያለው የደም ፍላጎት 18 ሚሊዮን ዩኒት ቢሆንም ከዚህ ውስጥ የሚሰበሰበው 15 በመቶ ያህሉ ብቻ ነው፡፡ በኢትዮጵያም ያለው የደም ፍላጎት ከ80 እስከ 120 ሺህ ዩኒት ሲሆን በዓመት የሚሰበሰበው ግን ከ43 በመቶ አይበልጥም፡፡
ታድያ ይህን መሰል በበጎ ፍቃደኝነት ደምን የመለገስ ተግባራት በተለያዩ የመንግስት እና የግል ተቋማት፣ ማህበራት እንዲሁም ሌሎች ማህበረሰቡን በሚያስተሳስሩ አደረጃጀቶች በዘላቂነት ቢከወኑ የሚሊዮን ወገኖችን ህይወት ማዳን ይቻላል፡፡
እርስዎስ ለስንት ጊዜ ደም ለግሰዋል?
የልብ በሽታ ከመከሰቱ ጥቂት ወራት በፊት ሰውነታችን የሚያሳየን 5 ምልክቶች
*******************************************
በዓለማችን ከ30 በመቶ በላይ ለሚሆነው የሰዎች ሞት የልብ በሽታ ዋነኛው መንስኤ ነው፡፡ ከዚህ የልብ በሽታ መንስኤ ውስጥ ደግሞ አብዛኛውን ሰው ለሞት የሚዳርገው ventricular fibrillation የተባለው የልብ ችግር ሲሆን ይህም ተጠቂው በበሽታው መያዙን ሳያውቅ ህይወቱን የሚያጣበት ሁኔታ ሲፈጠር ነው፡፡ ይህ በሽታ ምንም አንኳን ምልክቶቹን አይተን ጥሩ ህክምና የምናገኝበት ሁኔታ ሲፈጠር ከ90 በመቶ በላይ የመዳን እድል ቢሰጠንም ብዙ ሰዎች ግን ምልክቶቹን ባለማወቃቸው ምክንያት የህክምና እርዳታ ሳያገኙ ህይወታቸውን እንዲያጡ ይሆናል፡፡ በመሆኑም የልብ በሽታ ከመከሰቱ ጥቂት ወራት በፊት ሰውነታችን የሚሳየንን የማስጠንቀቂያ ምልክት ችላ ሳንል ተገቢውን የህክመና ሂደት መጀመር ያስፈልጋል፡፡

እጅግ በጣም ከፍተኛ የድካም ስሜት
ለቀናት፣ ለሳምንታትና ለወራት የቆየ ከፍተኛ የድካም ስሜት የሚሰማን ከሆነ የልብ በሽታ ሊከሰት መሆኑን የሚያሳየን የመጀመሪያው መንገድ ነው፡፡ ይህ የድካም ስሜት ምናልባት ከእንቅልፍ ማጣትና ከሌሎች በሽታዎች ጋር የተያያዘ የድካም ስሜት ሳይሆን ለብዙ ጊዜያት የሚቆይ እና በመጠኑም እጅግ በጣም ከፍተኛ ሊባል የሚችል የድካም ስሜት በመሆኑ በጥንቃቄ ማየት ያስፈልጋል፡፡

የትንፋሽ ማጠር
አንዳንድ ጊዜ ቀላል ሊባል የማይችል የአተነፋፈስ ችግር ሲያጋጥም ከሳምባ ጋር ማገናኘት የተለመደ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከልብ ጋር ተያይዞ በሚዘዋወረው ደማችን ውስጥ ያለው የኦክስጅን ማነስ ለትንፋሽ መቆራረጥና ማጠር ምክንያት ሊሆን ስለሚችል በጥንቃቄ ማየት ይበጃል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በአንድ ጥናት እንደተገለፀው በልብ በሽታ ከሚያዙ ሰዎች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት እስከ ስድስት ወር የሚዘልቅ የትንፋሽ ማጠር እንደሚታባቸው አስቀምጧል፡፡

ከፍተኛ መጠን ያለው ላብ እና የደረት ህመም
አብዛኛውን ጊዜ ሞቃታማ አየር ሲኖርና አድካሚ ስራ ስንሰራ ጤናማ የሆነ ላብ ሊያልበን ይችላል፡፡ ነገር ግን ምንም አይነት የሚያደክም ስራ ሳንሰራ ባልተለመደ ሁኔታ በደረታችን፣ በእጃችን፣ በአንገታችን እና በመንጋጋችን ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው ላብ ካየን እና በተለይም በደረታችን ላይ የህመም ስሜትና ምቾት ያለመሰማት ነገር ከተመለከትን የልብ በሽታ ምልክት ሊሆን ይችላልና የህክምና ሂደት መጀመሩ ጥሩ ነው፡፡

የእንቅልፍ ማጣት፣ ድብርትና የፀጉር መመለጥ
ከጭንቀትና ድብርት በመነጨ የሚመጣ የእንቅልፍ ማጣት በተለያየ መልኩ የኦክስጅን መጠንን በማውረድ ለልብ በሽታ የመጋለጥ እድልን እንደሚጨምር በተደጋገሚ የተሰራ ጥናት ያሳየል፡፡ ከዚህ ባለፈ የፀጉር መመለጥ በግልፅ የሚታይ በልብ በሽታ የመጋለጥ ምልክት ሲሆን በተለይም 50 ዓመት በሞላቸው ወንዶች ላይ እና አንዳንድ ሴቶች ላይ በግልፅ የመታየት እድሉ ሰፊ ነው፡፡

ያልተለመደ የልብ ምት
ብዙውን ጊዜ ለአንድና ለሁለት ደቂቃ የሚቆይ ያልተለመደ የልብ ምት ለመፍዘዝ እና ለድካም የሚዳርግ ሲሆን ፍጥነቱን ሳይቀንስ የሚቀጥልበት ሁኔታ ደግሞ በአጠቃላይ ላልተስተካከለ የልብ ምት (arrhythmia) እና ለከፍተኛ የልብ ምት (tachycardia) ይዳርጋል፡፡ በመሆኑም እነዚህን ምልክቶች ስንመለከት አዘውትረን የምናከናውነውን የአኗኗር ዘይቤ ከመፈተሽ ባለፈ የሃኪም ምርመራ የምናደርግበትን ሁኔታ መጀመር እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡

ምንጭ፡ My Science Academy እና Bright Side
ተመራማሪዎች የብሬል ላፕቶፕ ሰሩ
*************************
በህንድ ደልሂ መቀመጫውን ባረገው የህንድ ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት የሚገኙ ተመራማሪዎች ለአይነ ስውራን የሚሆን የብሬል ላፕቶፕ መስራታቸውን አስታውቀዋል። ረዘም ያለ ጊዜ በወሰደው በዚህ አዲስ ፈጠራ ተመራማሪዎቹ እንደገለፁት ከሆነ የተሰራው የብሬል ላፕቶፕ መሰረታዊ የሆኑትን የኢሜል እና የዌብ ብሮውዘር አገልግሎቶች ከመስጠት ባለፈ የሶስተኛ ወገን መተግበሪያዎች ሊጫኑበት እንደሚችል ገልፀዋል፡፡

DotBook የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ የብሬል ላፕቶፕ ሁለት አይነት መልክ ኖሮት የተሰራ ሲሆን እነሱም 40Q እና 20P የሚል ስያሜ ተሰቷቸዋል፡፡ 40Q የተባለው የብሬል ላፕቶፕ አርባ ፊደሎችን ወይም (characters) በየመስመሩ የያዘ የብሬል ኪቦርድ ሲሆን 20P የተሰኘው ደግሞ ሃያ ፊደሎችን በየመስመሩ የሚይዝ ነው፡፡

እስካሁን ዋጋቸው እጅግ ውድ የሆኑ 40 የሚደርሱ የብሬል መሳሪያዎች መሰራታቸውን የገለፁት ተመራማሪዎቹ ይህ ችግርም አዲሱን የብሬል ላፕቶፕ ለመስራት እንዳነሳሳቸው ገልፀዋል፡፡ ላፕቶፑ ከህንድ የቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት በተጨማሪ ኖኢዳ እና ክሪቲካል ሶሊዩሽን ከተባሉ የግል ድርጅቶች ጋር በትብብር የተሰራ ሲሆን በመጋቢት ወር መጨረሻም ለተጠቃሚዎች እንደሚቀርብ ተገልጿል፡፡

ምንጭ፡ Tech Explorist