TechIn2
1.22K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
ተቋማዊ የዕውቀት አስተዳደር ላይ ያኮተረ ወርክሾፕና የልምድ ልውውጥ መድረክ በመከናወን ላይ ነው
በቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት አማካኝነት የተዘጋጀው ወርክሾፑ በእውቀት አስተዳደር ስርዓት ዙርያ ግንዛቤ የመፍጠር፣ የልምድ ልውውጦችን ማድረግና በጉዳዩ ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ፅሁፎችን በማቅረብ ግንዛቤን የማስጨበጥ ስራን ለማከናወን ታልሞ የተዘጋጀ ነው፡፡ ከ30 ተቋማት የተውጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎች በተሳተፉበት በዚህ መድረክ የዕውቀት አስተዳደርን የተመለከቱ ውይይቶች ብሎም ልዩ ልዩ ጥናታዊ ፅሁፎች በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ እና ዕውቀትን ባካበቱ ምሁራን አማካኝነት ቀርበውበታል፡፡
በዓለም ሀገራት መካከል ላለው ሰፊ የማህበራዊ እና ምጣኔ-ሐብታዊ እድገት ልዩነት አንዱ ምክንያት “መረጃን እና ዕውቀትን ለልማት የመጠቀም ልዩነት ነው” ያሉት የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር ኢ/ር ተሾመ ሳህለማርያም ሀገራት ጠንካራ የዕውቀት እና ቴክኖሎጂ አስተዳደር ስርዓት በመዘርጋታቸውና ስራዎቻቸውንም በዚህ እንዲታገዙ በማድረጋቸው ፈጣን ምጣኔ-ሐብታዊ ዕድገት ማስመዝገባቸውን በመክፈቻ ንግግራቸው ላይ አመላክተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ቀደምት ስልጣኔ እና በዕውቀት አስተዳደር ውስጥም የራሷ ድርሻ እንደነበራት ያወሱት ኢ/ር ተሾመ አሁን ላይ ተቋማዊ የዕውቀት አስተዳደርን ለዕድገት በማዋል ረገድ በተለይም መረጃን በአግባቡ ያለመያዝ፣ ያለማደራጀት፣ ያለመተንተን፣ ያለማሰራጨት እንዲሁም መልሶ ጥቅም ላይ ያለማዋል ችግሮች መኖራቸውን ገልፀዋል፡፡ ኢንስቲትዩቱም የዕውቀት አስተዳደር ፋይዳን በመረዳት ተቋማዊ እና ሀገራዊ የዕውቀት አስተዳደር ስርዓት ለመገንባት ያከናወናቸውን የተለያዩ ተግባራት ጠቅሰው አስረድተዋል፡፡
በኢንስቲትዩቱ የመረጃ አደረጃጀት እና ዕውቀት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ቃልኪዳን ተሾመ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ ያለውን አደረጃጀት እንዲሁም በሕግ የተሰጡትን ተግባራት ለታዳሚው አብራረተዋል፡፡ አቶ ቃልኪዳን በኢንስቲትዩቱም ሆነ በእርሳቸው ዳይሬክቶሬት የተከናወኑትን እንደ ብሄራዊ የልማት አመላካች ዳሽቦርድ እና ኮቪድ-19 ተኮር የመፍትሄ ስራዎች ያሉ ዋና ዋና ክንውኖችን አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ስራቸው እየተከናወነ ያሉትንና በቅርብ ተጠናቀው ይፋ የሚሆኑትን በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ጆርናል እንዲሁም ተደጋጋሚ ግዢዎች ከመፈፀም የሚያድነው በኢትዮጵያ የሚገኙ የቤተ-ሙከራ ግብዓቶችን የመመዝገብና ለተጠቃሚ የማሳወቅ ስራዎች ተጠቅሰዋል፡፡
በጠዋቱ መርሃ ግብር ሁለት ምሁራዊ ጥናቶች ሲቀርቡ ቀዳሚ የነበረው “knowledge management practices in commercial bank of Ethiopia” በሚል ርዕስ በዶ/ር ተምትም አሰፋ የቀረበው ነው፡፡ ጥናቱ በዕውቀት አስተዳደር ረገድ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ ያለውን ሂደት አንዲሁም ክፍተቶችን እና ከሌሎች ተቋማት በተለየ በዕውቀት አስተዳደር ላይ ስኬታማ እንዲሆን ያስቻሉትን አብይ ጉዳዮች የዳሰሰ ነው፡፡ ሁለተኛውን ያቀረቡት ዶ/ር ጌታቸው ኃይለማርያም በበኩላቸው “frugal knowledge sharing for frugal innovation diffusion in Africa” በሚል ርዕስ በዝቅተኛ ምጣኔ ሐብታዊ ደረጃ ላይ ላለው ማህበረሰብ ግልጋሎት ሊሰጡ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ አዘጋጅቶ ወደ ታች እንዲወርዱ የማድረግ ስራን እንዴት ማከናወን ይቻላል በሚለው ላይ ገለፃ አቅርበዋል፡፡
ተሻሽሎ የቀረበው ፈጣን የህዝብ ማመላለሻ ጀት
*******************************
ከ 18 ዓመታት በፊት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ጥቅምት 24 2003 ከለንደን ወደ ኒዮርክ ጆንኦፍ ኬኔዲ አየር መንገድ አንድ ልዩ በረራ ተደረገ፡፡ ይህ በለንደንና በኒዮርክ መካከል ያለውን ርቀት የ3 ሰዓት ብቻ ለማድረግ የታለመው የታዋቂው ሱፐርሶኒክ አየር መንገድ ባለቤት ኮንኮርድ የመጨረሻ በረራ ነበር፡፡ ድርጅቱ ምንም እንኳን ከውጥኑ ትልቅ ህልም ይዞ የተነሳ ቢሆን በገጠመው ከቴክኖሎጂና ከንግድ ጋር የተያያዘ ችግር ውጥኑ ሳይሰምር ቀርቷል፡፡ በወቅቱ የኮንኮርዱ ሱፐርሶኒክ የመንገደኞች ተምዘግዛጊ ጀት በጣም ፈጣን የነበረ ሲሆን የድምጹ ጉዳይ ግን አይወራ አይነገር የሚያሰኝ ነበር፡፡
ከነዚህ ሁሉ አመታት በኋላ ፈጣን የህዝብ ማመላለሻ ጀቶች ወደ ስራ ሊመለሱ መሆኑ ተሰምቷል፡፡ ከቴክኖሎጂ አንጻር ከዚህ ቀደም የነበረውንና ለኮንኮርድ መክሰር ምክንያት የሆነው ችግር እንደተፈታ ቢገለጽም ከገበያና ከኢኮኖሚ አንጻር ያለው ችግር ግን አሁንም ሙሉ በሙሉ የተቀረፈ አይመስልም፡፡
የተለያዩ ድርጅቶችና የምርምር ተቋማት በአዲሱ ትውልድ ሱፐርሶኒክ የመንገደኞች አውሮፕላን ላይ ከፍተኛ በጀት አፍስሰው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል የአሜሪካው ቡም 196 ሚሊዮን ዶላር በመመደብ ኦቨርቱር የተሰኘ አዲስ ሱፐርሶኒክ ሞዴል በያዝነው የፈረንጆች አመት ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን አሳውቋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ናሳ የቀድሞውን ከፍተኛ ድምጽያለውን ሶኒክ ጀት X-59 የሚባል ፕሮጀክት ቀርጾ ድምጹን ለማሻሻል እየሰራ ነው፡፡ ፉክክሩ በዚህ ብቻ አላበቃም፤ ኤሪዮን ከቦይነንግ ጋር በመተባበር በ2025 ወደ አየር ሊወጣ የሚችል የቢዝነስ ሱፐርሶኒክ ጀት እያበለጸጉ ነው፡፡
በጣሊያኑ ቶሪኖ ፖሊቴክኒክ ዩኒቨርሲቲው ፐሮፌሰር ኒኮል ቪዮላ ስለ ሁኔታው ‹‹ከዚህ በኋላ ህልም ብቻ ሆኖ አይቀርም በሁሉም አካባቢ ርብርብ እየተደረገበት ነው›› የሚል ሀሳብ ሰንዝረዋል፡፡ የእነዚህ አይነት የመንገደኛ ጀቶች አንዱ ጥቅም አነስተኛ ድምጽ እንዲኖራቸው ተደርገው መሰራታቸው ነው፡፡
የድምጽ ብክለቱን ሁኔታ ለማስታወስ የጦር ጀቶችና ሚጎች በረራ ሲያደርጉ የሚፈጠረውን ድብልቅልቅ ማስታወስ በቂ ነው፡፡ አንዳንዴ እንዲህ አይነት በረራዎች ሲደረጉ አልፎ አልፎ ህንጻዎች ሊፈርሱ ወይም የበርና መስኮት መስታዎቶች ሊረግፉ ይችላሉ፡፡ ይህም ከሚፈጠረው ከፍተኛ ድምጽ የተነሳ ነው፡፡
በፈረንሣይ ኤሮስፔስ ላቦራቶሪ በሆነው ‹ኦኔራ› ከፍተኛ የአየር ኃይል ተመራማሪ የሆኑት ጄራልድ ኬሪየር ‘የሶኒክ ጀቶች ድምጽ ጥንካሬ በዋናነት በአውሮፕላኑ ቅርፅ ላይ የተመሠረተ ነው’ ብለዋል ፡፡ ተመራማሪው ተቆጣጣሪ ባለሥልጣናት በሶኒክ እና በዝቅተኛ ፍጥነት አውሮፕላኖች በሚወጣው ጩኸት ዙሪያ ማስረጃዎችን በሚሰበስበው ‹RUMBLE› ፕሮጀክት ውስጥ ተሳትል ፡፡
የአውሮፕላኑን ጆሜትሪያዊ ቅርጽ በማስተካከል ድምጹን ከ100 ዴሲቤል ወደ 70-80 ዴሲቤል ድረስ ማሳነስ እንደሚቻል ተመራማሪው ተናግረዋል፡፡ ይህም የአንድ የኤሌክትሪክ ማጽጃ ድምጽን የሚያክል ነው፡፡ የአውሮፕላኑ አፍንጫ ሹለት በተጨመረ ቁጥር የድምጽ መጠኑም እንደሚቀንስ ተረጋግጧል፡፡
ምንጭ technology.org
የቢትኮይን ዋጋ ለመጀመሪያ ጊዜ 50,000 ዶላር ደርሷል
=======================
ባለፉት ሁለት እና ሶስት አመታት ዋጋው አሽቆልቁሎ የነበረው ቢትኮይን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ ወጋው እየጨመረ መምጣቱ ተነግሯል፡፡ የፈረንጆቹ አዲስ አመት ከገባ ጀምሮ አንዱ የቢትኮይን ዋጋ 32,149 ዶላር ሲሸጥ የነበረ ሲሆን ይህ ዋጋ በቀጣዮቹ ጊዜያት ይበልጥ ጨምሮ በትናትናው ዕለት ከ50,000 ዶላር በላይ በማውጣት እስከዛሬ ያልታየ ሪከርድ ሰብሯል፡፡
የቢትኮይን ዋጋ እንዲህ ለመጨመሩ ዋና ምክንያት ተደርጎ የተወሰደው እንደ ቴስላ፣ ማስተርካርድ እና ቢ ኤን ዋይ ሜሎን ያሉ ግዙፍ ኩባንያዎች ታዋቂውን ክሪፕቶከረንሲ በከፍተኛ ሁኔታ በመግዛታቸው እና ሌሎች ትልልቅ ድርጅቶችም የክፍያ ስርዓታቸውን ወደዚህ የቢትኮይን አሰራር እየቀየሩ በመምጣታቸው ነው ተብሏል፡፡ ለአብነት ኤለን መስክ የሚመራው ቴስላ በአክስዮን ገበያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት እጅግ ከፍተኛ ዋጋ ካላቸው ኩባንያዎች በቀዳሚነተ የሚቀመጥ ሲሆን ይህ ኩባንያ በቅርቡ 1.5 በሊዮን ቢትኮይን ከመግዛቱም ባለፈ አንዳንድ ምርቶቹን በዚህ የክሪፕቶከረንሲ ለመገበያየት ማቀዱ የቢትኮይንን ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እንደጨመረው ተገልጿል፡፡
ከዚህ በለፈም ቢ ኤን ዋይ ሜሎን እየተባለ የሚጠራው አንጋፋ የአሜሪካ ባንክ ለቢትኮይን የግብይት ስርዓት ከፍተኛ ይሁንታ እና ድጋፍ ማድረጉ ሌላው ተጨማሪ ምክንያት ሲሆን እንደ ማስተርካርድ እና ማይክሮ ስትራቴጂ ያሉ ግዙፍ የፋይናንስና የቢዝነት ተቋማት በቢትኮይን ላይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ማካሄደቸው ለክሪፕቶከረንሲው ዋጋ መጨመር ሌሎች ምክንያት ናቸው፡፡ በ2016 ከፍተኛ የዋጋ እድገት የታየበት ቢትኮይን በተያዘው የፈረንጆቹ 2021 አመትም የ 72% ከፍተኛ ጭማሪ እንደሚያስመዘግብ ተነግሯል፡፡
ቢትኮይን የስነ-መሰውር (cryptography) ቴክኖሎጂን የሚጠቅም አንዱ የክሪፕቶከረንሲ ክፍል ሲሆን የብሎክቼን ቴክኖሎጂ ለመጀመሪያ ጊዜ የተተገበረበት እና አዲስ አይነት የዲጂታል ገንዘብ አጠቃቀምን እንዲሁም አከፋፈል ስርዓትን የሚዘረጋ ነፃ ሶፍተዌር ነው፡፡ ቢትኮይን በሁለት ሰው መካከል የዲጅታል፣ የገንዘብና የክፍያ ልውውጥ የሚካሄድበት አቻ ለአቻ (peer-to-peer) አሰራር ሲሆን የክፍያ ስርዓቱ ያለገንዘብ ተቋም ጣልቃገብነት ሊፈፀም ይችላል፡፡
ቢትኮይን መገበያያ እንደሌሎች የክሬፕቶከረንሲ አይነቶች ከልማዳዊው የገንዘብ አሰራር የተለየ ይዘት ያለው ሲሆን በኮምፒውተራችን ላይ ይህ ዲጂታል ገንዘብ ነው ብለን የምንጠቀመው ፋይል ወይም መረጃ የለም፡፡ ይህም የሚሆንበት ምክንያት ዲጂታል ገንዘቡ በየትኛውም አገር ስላልተፈጠረና በማንኛውም አገራዊ ወይም ዓለም አቀፋዊ የመንግስት ቷቋም ስለማይተዳደር ነው፡፡ የዲጂታል ገንዘብ ልውውጥ ስርዓቱም የሚከናወንባቸው ኮምፒውተሮች በተለያየ የዓለም ክፍል በሚገኙ ግለሰቦች ንብረትነት የሚተዳደሩ ናቸው፡፡ ይሄ አሰራር “distributed computation” የሚባል ሲሆን ዋና ዓላማውና ጥቅሙም የመረጃ ልውውጡና አስተዳደሩ በአንድ ተቋም ስር ሳይወድቅ ለሳይበር ጥቃት የማይመች ማድረግ እና የመረጃ ትክክለኝነቱ “data integrity” ዋስትና እንዲጠበቅ ማድረግ ነው፡፡ የቢትኮይን መገበያያ ቀድመው ከተፈጠሩ የክሬፕቶከረንሲ አይነቶች የመጀመሪያውና ዝነኛው ቢሆንም ከሱ በኋላ ግን ከ1500 በላይ የሚሆኑ የክሬፕቶከረንሲ አይነቶች አንደተፈጠሩ ተረጋግጧል፡፡
ምንጭ፡ Reuters እና Republicworld
የኮቪድ-19 ክትባትን ባንከተብስ? ምን ይመጣብናል?
====================
እንደ ታንዛኒያ እና ማዳጋስካር ያሉ ሀገራት ህዝባቸውን በኮቪድ-19 መከላከያ ክትባቶች የመከተብ ዕቅድ እንደሌላቸው አሳውቀዋል፡፡ በግለሰብ ደረጃም ክትባቱን መውሰድ የማይፈልጉ ሰዎች መኖራቸውን ሰምተን ይሆናል፡፡ ግን እንደዚህ አይነት እርምጃዎች ምን ሊያመጡ ይችላሉ?
ያን ያህል የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባትን ያልወሰዱ ዜጎች ባሉባት ሀገር ውስጥ የወረርሺኙ ቆይታ የመርዘሙ ዕድል የሰፋ ይሆናል፡፡ ቫይረሱ በዘላቂነት ማህበረሰቡን እያጠቃ የሚቆይበት ጊዜ በተራዘመ ቁጥር ደግሞ ቫይረሱም ይበልጥ እራሱን እየለወጠ ይመጣል፡፡ ይህ መለወጥ (mutation) ደግሞ ይበልጡን አደገኛ ለሆኑ የሳርስ-ኮቭ-2 አይነቶች ምቹ መፈልፈያን ሊፈጥር ይችላል፡፡ በበራሒ ኮዳቸው ላይ ለውጦችን አድርገው ብቅ የሚሉት አዳዲሶቹ የኮሮና ቫይረስ አይነቶች በበኩላቸው ቀድሞ ክትባቱን የወሰዱት ሰዎችን ጭምር የማጥቃት አቅምን የማዳበር ዕድል አላቸው፡፡ ክትባት አንድ የቫይረስ አይነትን ሰውነታችን እንዲያውቀው በማድረግ የበሽታ መከላከል ስርዓቱን እንዲቀሰቅስ ማድረጊያ ነውና ቫይረሱ ሲለወጥ ያለመታወቅ እድሉን ይጨምረዋል፡፡ በዚህ አኳሀን አብዛኛው ህዝብ የተከተበባቸው አካባቢዎች እንኳን ሌላ ቦታ ላይ አይነቱን በለወጠ ምናልባትም ከቀድሞው የበለጠ ተላላፊና ገዳይ በሆነ ቫይረስ ይጠቃሉ፡፡ ምድራችን ላይ ማንም ለብቻው ተከልሎ አለመገኘቱን ስናስብ ደግሞ ሁላችንም ክትባቱን ካላገኘን አንዳችንም ደህንነታችን በብቸኝነት ጠብቀን መኖር እንደማንችል እንረዳለን፡፡
ታድያ መፍትሄው ምንድነው?
ከዚህ ችግር ለመዳን መንግስታት ዜጎቻቸውን ከከተቡ በኋላ ድንበራቸውን ዘግቶ መቀመጡ ቀላል ነገር ስለማይሆን ከዚህ ይልቅ ክትባቶቹን በተቻለ ፍጥነት ለሁሉም ሀገራት ዜጎች ማዳረስ ቀዳሚው መፍትሄ ነው፡፡ አሁን ላይ በቫይረሱ የተያዘን ሰው የሚያድኑ ምንም አይነት መድሃኒቶች ስለሌሉም ክትባቱን የማዳረሱ እንቅስቃሴ በፍጥነት መከናወን ይኖርበታል፡፡ ይህን ቶሎ ማሳካት እንዲቻል መንግስታት ክትባቶቹን በማምረት እና ለሁሉም በማዳረስ ረገድ በጋራ መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ ለክትባቶቹ አምራቾች የሚደረገው የገንዘብ ድጋፍም ሊያድግና ተጨማሪ ሌሎች ማምረቻዎችም በማደግ ላይ ባሉት ሀገራት ጭምር ሊከፈቱ ይገባል፡፡ ይህም የቴክኖሎጂ ሽግግርን ጭምር የሚጠይቅ ተግባር ነው፡፡
ታድያ በርካታ ሀገራት ክትባቶቹን ለማግኘት ገና እየተጠባበቁ በመሆናቸው ወረርሺኙ ከተነሳበት ጊዜ አንስቶ ሲተገበሩ የቆዩትን እንደ ማስክ ማድረግ እና አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ያሉ የጥንቃቄ እርምጃዎችን መከወኑ ቢያንስ በአንድ ማህበረሰብ ውስጥም ሆነ ከአንድ ማህበረሰብ ወደ ሌላ ማህበረሰብ የሚኖረውን የቫይረሱን የስርጭት ይቀንሰዋል፤ ወደ ሆስፒታል የሚያመራውን እና ህይወቱን የሚያጣውን ሰው ቁጥርንም ያወርደዋል፡፡ በተጨማሪም በአንድ አካባቢ ከፍ ያለ ስርጭት መኖሩን የሚያሳይ መረጃ ሲገኝ አካባቢው ላይ የእንቅስቃሴ ገደቦችን ማድረግ ይገባል፡፡
በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን የተጠቂ መጠን በምርመራ መለየቱና የቫይረሱን በራሒ በቤተ-ሙከራ እየመረመሩ መከታተሉ ቀዳሚው ነገሮችን መረዳት የሚያስችል መንገድ ነው፡፡
ምንጭ፡ The Conversation
እናት የሁሉም ነገር መድሃኒት
*******************
በዓለማችን ላይ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ወረርሽኞች ተከስተው ጥቂት የማይባሉ ሰዎችን ቀጥፈዋል፡፡ ሞትና የተለየዩ ምክንያቶች የብዙ ፍጥረታትን ህልውና በተለያዩ ጊዜያት አደጋ ላይ ጥለዋል፡፡ ለዚህም ነው በአሁኑ ሰዓት ሊጠፉ የተቃረቡ የሚባሉ ፍጥረታት ያሉን፡፡ ከጥንት ጀምሮ የሰው ልጅን በጅምላም ሆነ በተናጥል ህይወቱን የሚቀጥፉ አጋጣሚዎች ቢፈጠሩም የሰዎች ቁጥር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አይስተዋልም፡፡ ለዚህ ነው እናት ‹መውለድ› የሚባል የሞት መድሃኒት አላት የሚባለው፡፡
አለማችን አሁንም በወረርሽኝ ላይ በመሆኗ የተሻለ መድሃኒት ፍለጋ ላይ ናት፡፡ በብዙ ጥረቶች የተወሰኑ መድሃኒቶች ቢገኙም የፍትሀዊነት ጉዳይ ግን በጥያቄ ውስጥ ያለ ነው፡፡ ምርምሮች አሁንም እየተደረጉ ሲሆን አሁን ተገኘ የተባለው አዲስ መረጃ ግን ወደ ዘጠኝ ወር ቤታችን፣ የልጅነት ምግባችን እንዲሁም የእድሜ ዘመን ወዳጃችን ወደ ሆነችው ውዷ እናት የሚወስድ ሆኗል፡፡
በሮችስተር የህክምና ማዕከል የተሰራ አንድ ጥናት ጡት ማጥባት የኮቪድ ቫይረስን እንደማያስተላልፍና ይልቁንም ህጻናት ቫይረሱን መቋቋም የሚችሉበትን አቅም እንደሚሰጣቸው አመልክቷል፡፡ በጥናቱም ከ18 በኪቪድ የተያዙ እናቶች የተወሰደ 37 የጡት ወተት ናሙና ውስጥ በአንዱም ቫይረሱ እንዳልተገኘ እና ይልቁንም በተወሰኑ ናሙናዎች ለቫይረሱ የሚሆኑ አንቲ ቦዲ ተገኝቶባቸዋል፡፡
በዚህም በኮቪድ 19 የተጠቁ እናቶች ከጨቅላ ልጆቻቸው መለየት እንደሌለባቸው ጥናቱ አመላክቷል፡፡ ባሳለፍናቸው ወራቶች የተለያዩ የጤና ተቋማት በጉዳዩ ዙሪያ አሻሚ መረጃዎችን ሲሰጡ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ለጥናቱም ቢልና ሚሊንዳ ጌትስ የተሰኘው ግብረ ሰናይ ድርጅት 130 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ፈሰስ አድርጓል፡፡
ምንጭ Technology.org
ኮካ ኮላ የመጀመሪያውን የወረቀት ማሸጊያ ሊሞክር ነው
====================
በአለማችን ላይ የተፈጥሮን ሚዛን በማዛባት ትልቅ ችግር ከሚፈጥሩ ምክንያቶች መካከል የፕላስቲክ ብክለት አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ በዚህ አለም አቀፍ ችግር ከፍተኛ የፕላስቲክ ገብዓት ጥቅም ላይ በማዋል የፕላስቲክ ብክለቱ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨመር ከሚያደርጉ ግዙፍ ተቋማት ውስጥ ደግሞ የኮካ ኮላ ኩባንያ በቀዳሚነት የሚቀመጥ ነው፡፡ በቅርቡ Break Free From Plastic የተሰኘው አለም አቀፍ ንቅናቄ ባዘጋጀው አመታዊ የደሰሳ ጥናት ላይ የኮካ ኮላ ኩባንያ ከየትኛውም አለም አቀፍ ተቋም በላይ ለፕላስቲክ ብክለት የመጀመሪያውን ደረጃ እንደሚወስድ አስታውቆ ነበር፡፡
በተፈጥሮ ላይ ከፍተኛ አደጋን በሚጠራው በዚህ አለም አቀፍ ችግር ላይ ትልቅ ድርሻን የሚወስደው የኮካ ኮላ ኩባንያ ይህን አደጋ በሚቀንስ መልኩ ወደፊት ለሚኖረው የምርት ግብዓት የመጀመሪያውን የወረቀት ማሸጊያ ጠርሙስ ለመሞከር በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ ከሰሞኑ በኩባንያው ድረ-ገፅ ላይ እንደተገለፀው ድርጅቱ በተያዘው የፈረንጆች አመት 2,000 የሚጠጉ የወረቀት ማሸጊያ ጠርሙሶችን በፕሮቶታይፕ ደረጃ በማዘጋጀት የንድፋቸውን ውጤታማነት ለመገምገም እንደሚሞክር ተጠቅሷል፡፡ ኩባንያው ይህን የፕሮቶታይብ ሙከራ በዴንማርክ መቀመጫውን ካደረገ ፓባኮ ከተባለ የምርምር ተቋም ጋር የሚካሂድ ሲሆን፤ በሚኖራቸው የሙከራ ሂደትም አዴዝ በተባለ የአትክልት ጭማቂ ላይ በሚሰራ ተቋም ጋር በጋራ በመሆን የተጠቃሚዎችን እርካታ የሚገመግምሙ ይሆናል፡፡
የወረቀት ማሸጊያ ጠርሙስ ለአለማችን አዲስ የማሸጊያ (packaging) አመራጭ ነው የሚሉት በአውሮፓ የኮካ ኮላ ኢኖቬሽን ማናጀር ስቴን ፍራንሰን ይህን ለመተግበር የምናደርገው ጥረትም ለወደፊቱ የአለማችን የአከባቢ ጥበቃ መልካም ተፅዕኖ እንደሚኖረው እናምናለን ይላሉ፡፡ አሁን በሙከራ ላይ የሚገኘው የወረቀት ጠርሙስ በተወሰነ መልኩ የፕላስቲክ ግብዓት ቢኖረውም በዘላቂነት ግን እንደማንኛውም የወረቀት አይነት መልሶ ጥቅም ላይ የሚውል የወረቀት ማሸጊያ ሊሰራ እንደታሰበ የኩባንያው ማናጀር ስቴን ፍራንሰን ይናገራሉ፡፡
ባለሙያዎች እንደሚገለፁት ይህ የወረቀት ማሸጊያ ጠርሙስ የመጠቀም እንቅሰቃሴ ለአለማችን የአካባቢ ጥበቃ መልካም ነግር ይዞ በሚጣም በቶሎ ለመተግበር ከባድ ከሚያደርጉት ምክንያቶች መካከል በካርቦን የተሞሉ ማንኛውም መጠቶች (carbonated beverage) በከፍተኛ ግፊት እንዲታሸጉ ከማስፈለጋቸው አንጻር በወረቀት ጠርሙስ የሚከናወነው ይህ የማሸግ ስራ ከባድ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች የተነሳ በተጠቃሚዎች ጤና ላይ መጠነኛ ተፅዕኖ ሊኖረው ስለሚችልም በዘርፉ የሚደረገው ረዥም የምርምር ሂደት እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ኩባንያው ይህን የሙከራ እንቅሰቃሴ ሲጀምር ረዥም ጊዜ የሚወስድ የምርምር ሂደት እንደሚያከናውን ባለሙያዎች ይገልፃሉ፡፡ ምንጭ፡ CTV NEWS
ፌስቡክ በአውስትራሊያ የጣለው የዜና ተደራሽነት እገዳ
****************************
ፌስቡክ አውስትራሊያውያን በፕላት ፎርሙ ዜናዎችን እንዳያገኙ ማገዱን አሳወቀ፡፡ እንደ ማህበራዊ ሚዲያው መረጃ ከሆነ እገዳው የተጣለው በሃገሪቱ ዲጂታል ማሰራጫዎች ለሚያሰራጩት መረጃ እንዲከፍሉ የሚጠይቅ ረቂቅ ህግ መውጣቱን ተከትሎ ነው፡፡ ድርጅቱ አክሎም በአውስትራሊያ የሚገኙ መረጃ አሰራጮች መረጃ ማውጣታቸው ያልተቋረጠ ሲሆን መረጃዎቻቸውና ሊንኮቻቸው በፌስቡክ አማካኝነት ለአውስትራሊያውያን ተደራሽ አይሆኑም ብሏል፡፡
በዚህ እገዳ ምክንያት በአውስትራሊያ የሚገኙ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች የሀገር ውስጥ ወይም አለማቀፍ መረጃዎችን የማያገኙ ሲሆን ከአውስትራሊያ ውጭ ያሉ ተጠቃሚዎች ደግሞ ምንጫቸውን በአውስትራሊያ ያደረጉ መረጃዎችን ማግኘት አይችሉም፡፡ የፌስቡክ አካባቢያዊ ማኔጂንግ ዳይሬክተር የሆኑት ዊሊያም ኢስቶን ረቂቅ ህጉ በፌስቡክ እና ፕላትፎርሙን በሚጠቀሙ የዜና ማሰራጫዎች መካከል ያለውን ግንኙነት ያልተረዳ ነው ሲሉ ትችታቸውን አቅርበዋል፡፡ ዳይሩክተሩ አክለውም በዚህ ሁኔታውን ባልተረዳ ህግ ምክንያት አጣብቂኝ ውስጥ እንደገቡና የዜና ይዘት ያላቸውን መረጃዎች ላማገድ እንደተገደዱ ተናግረዋል፡፡
ይህ መረጃም የወጣው ፌስቡክና ጎግል ከአውስትራሊያ የሚዲያ ተቋማት ጋር ተስፋ ሰጭ ስምምነት ላይ እንደደረሱ ከተነገረ በኋላ ነው፡፡ ፌስቡክ አሁን አንዳንድ ሙከራዎችን እያደረገ እንደሆነ ቢገልጽም የአውስትራሊያው ኮሚኒኬሽን ሚኒስቴር ፓውል ፍሌቸር ግን ከህግ ማስከበር ጋር በተያያዙ ጉዳዩች መንግስታቸው ወደኋላ እንደማይመለስ ተናግረዋል፡፡ ሚንስትሩ አክለውም ፌስቡክ ስራውን መልሶ ማግኘት ከፈለገ በፕላትፎርሙ ላይ በሚያወጣቸው ዜናዎች ዙሪያ ታማኝነቱን ማሳየት አለበት ብለዋል፡፡
በረቂቅ ህጉ ዙሪያ የአውስትራሊያ ፓርላማ እየመከረበት ሲሆን ሴኔቱም እንደሚመለከተው እየተጠበቀ ነው፡፡ በዚህ ረቂቅ ህግ አብሮ እየተከራከረ ያለው ጎግልም የመረጃ መፈለጊያ ፕላትፎርሙን ከአውስትራሊያ ሊያነሳ ይችላል ተብሏል፡፡
ምንጭ: Tech Xplore