TechIn2
1.22K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
የአይንን ብርሃን ማጣትና የአየር ብክለት
*************************
በአየር ብክለት ምክንያት የሚመጣ የአይን በሽታ የአይናችንን ብርሃን ላይመለስ እንደሚያሳጣን አንድ ጥናት አመለከተ፡፡ ጥናቱ የአየር ብክለት በብዙ መንገዶች የሰው ልጆችን አኗኗር እየጎዳ እንደሆነ ያረጋገጠ ነው፡፡ የአየር ብክለት በዓለማችን ውስጥ የሚኖሩ የሁሉም ፍጥረታት ችግር እየሆነ መምጣቱ የማይካድ ነው፡፡ እንደ አለም ጤና ድርጅት መረጃ ከሆነ 90 በመቶ የሚሆነው የአለማችን ህዝብ የሚኖረው ጤናማ ባልሆነ የአየር ንብረት ውስጥ ነው፡፡
ለአየር ንብረት መበከል መንስኤ ናቸው ተብለው የሚታመንባቸው እንደ ጥቃቅን ብናኞች፣ ናይትሮጅን ዳይ ኦክሳይድ፣ ሳልፈር ዳይ ኦክሳይድ እና ሌሎች ከመኪናዎች፣ ከግዙፍ ኢንዱስትሪዎቻና ከማገዶ እንጨት የሚወጡ ጭሶች ናቸው፡፡ PM2.5 እየተባሉ የሚጠሩት ጥቃቅን ብናኞች ዋናውን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡ እነዚህ መጠናቸው ከ2.5 ማይክሮ ሜትር የሆኑ ጥቃቅን የፕላስቲክ ብናኞች በሰውነታችን ሰርገው ወደ ሳንባና የደም ቧንቧዎች የመግባት አቅም አላቸው፡፡ ይህም ሰውነታችን የተለያዩ በሽታዎችን እንዲያዳብር እንደሚያደርገው ይታመናል፡፡
ጥቃቅን ብናኞቹ የሰዎችን የማየት አቅም የሚያዳክሙና የአተነፋፈስ ስርዓት የሚያዛቡ እንደሆኑ በጥናቱ ተረጋግጧል፡፡ ጥናቱ (AMD) እየተባለ የሚጠራውን ከእድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ የሚመጣውን የአይን ብርሃን ማጣትን ለማጥናት ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡ በሽታው ከአይናችን ጀርባ አካባቢ ካሉ የደም ስሮች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው ነው፡፡ የበሽታው ዋነኛ መንስኤዎች በመባል የሚታወቁት ዘርና ማጨስ ናቸው፡፡
በጥናቱም በእንግሊዝ የሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን በቤታቸው አካባቢ ያለው የአየር ሁኔታ መረጃ በጥናቱ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ በዚህም ከ2006 ጀምሮ 116 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች መረጃዎችን የሰጡ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 52 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች የአይን ምርመራ አድርገዋል፡፡ የጥናቱ ውጤትም በአካባቢያቸው ከፍያለ መጠን ላለው ብናኝ የተጋለጡ ሰዎች ለአይን መድከም ብሎም ለአይን ብርሃን ማጣት የመጋለጥ እድላቸውደ ከፍተኛ መሆኑን አረጋግጧል፡፡
ምንጭ Science Alert
ምድራችን ከተሞችን መሸከም እያቃታት ነው
**********************
የአለማችን ከተሞች ከእድገታቸው ጋር ተያይዞ እየጨመረ የመጣው ግዝፈታቸው የምድራችንን የመሸከም አቅም እየተፈታተነው እንደሆነ አንድ ጥናት አመለከተ፡፡ ለወትሮው በአለማቀፍ የሙቀት መጠን መጨመር ምክንያት እየጨመረ የመጣው የባህር ጠለል ከፍታ ለአንዳንድ የአለማችን ከተሞች በውሃ የመዋጥ ምክንያት ነበር፡፡ የአሜሪካ ጊኦሎጂካል ጥናት ኤጀንሲ የስነ-ምድር ተመራማሪ የሆነው ቶም ፓርሰንስ የሳንፍራንሲስኮን ሁኔታ ያጠና ሲሆን በውጤቱም የግዙፋን ከተሞች መስፋፋት ገፀ-ምድርን እየተጫነው እንደሆነ አሳይቷል፡፡
ከጥናቱ ውጤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ ሳንፍራንሲስኮ እድገቷ በጨመረ ቁጥር እስከ 80 ሚሊ ሜትር ድረስ ወደታች እየሰመጠች ትገኛለች፡፡ አካባቢው በባህር ጠለል ከፍታ መጨመር ምክንያት እስከ 2050 ድረስ 300 ሚሊ ሜትር የመስመጥ አደጋ እንደተጋረጠበት ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ 7.75 የሚደርስ የህዝብ ቁጥር ያላት ሳንፍራንሲስኮ ያሏት ህንጻዎች ክብደት ተሰልቶ 1.6 ትሪሊዮን ኪሎግራም እንደምትመዝን ጥናቱ አመልክቷል፡፡
ይህ ክብደት ከተማዋ የተገነባችበትን ተፈጥሯዊ ቅርፀ ምድር እንዲታጠፍ እንደሚያደርገው ተገምቷል፡፡ ከላይ የተገለጸው ክብደት ከህንጻ ውጭ ያሉ ሌሎች መሰረተ ልማቶችንና መገልገያዎችን እንዲሁም ህዝቡን የማይጨምር በመሆኑ የስጥመት መጠኑ ከ80 ሚሊ ሜትር ከፍ ሊል እንደሚችል በጥናቱ ተካትቶ ቀርቧል፡፡ ከከተሞች ክብደት በተጨማሪ የከርሰ ምድር ውሃ አጠቃቀምና የቴክቶኒክ አለታማ ንጣፎች መንሸራተትና ቦታቸውን መልቀቅ ሌሎች ለምድር መስመጥ ስጋቶች እንደሆኑ ተመራማሪዎቹ አክለው አሳውቀዋል፡፡
ምንጭ፡ Science Alert
ተቋማዊ የዕውቀት አስተዳደር ላይ ያኮተረ ወርክሾፕና የልምድ ልውውጥ መድረክ በመከናወን ላይ ነው
በቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት አማካኝነት የተዘጋጀው ወርክሾፑ በእውቀት አስተዳደር ስርዓት ዙርያ ግንዛቤ የመፍጠር፣ የልምድ ልውውጦችን ማድረግና በጉዳዩ ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ፅሁፎችን በማቅረብ ግንዛቤን የማስጨበጥ ስራን ለማከናወን ታልሞ የተዘጋጀ ነው፡፡ ከ30 ተቋማት የተውጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎች በተሳተፉበት በዚህ መድረክ የዕውቀት አስተዳደርን የተመለከቱ ውይይቶች ብሎም ልዩ ልዩ ጥናታዊ ፅሁፎች በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ እና ዕውቀትን ባካበቱ ምሁራን አማካኝነት ቀርበውበታል፡፡
በዓለም ሀገራት መካከል ላለው ሰፊ የማህበራዊ እና ምጣኔ-ሐብታዊ እድገት ልዩነት አንዱ ምክንያት “መረጃን እና ዕውቀትን ለልማት የመጠቀም ልዩነት ነው” ያሉት የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር ኢ/ር ተሾመ ሳህለማርያም ሀገራት ጠንካራ የዕውቀት እና ቴክኖሎጂ አስተዳደር ስርዓት በመዘርጋታቸውና ስራዎቻቸውንም በዚህ እንዲታገዙ በማድረጋቸው ፈጣን ምጣኔ-ሐብታዊ ዕድገት ማስመዝገባቸውን በመክፈቻ ንግግራቸው ላይ አመላክተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ቀደምት ስልጣኔ እና በዕውቀት አስተዳደር ውስጥም የራሷ ድርሻ እንደነበራት ያወሱት ኢ/ር ተሾመ አሁን ላይ ተቋማዊ የዕውቀት አስተዳደርን ለዕድገት በማዋል ረገድ በተለይም መረጃን በአግባቡ ያለመያዝ፣ ያለማደራጀት፣ ያለመተንተን፣ ያለማሰራጨት እንዲሁም መልሶ ጥቅም ላይ ያለማዋል ችግሮች መኖራቸውን ገልፀዋል፡፡ ኢንስቲትዩቱም የዕውቀት አስተዳደር ፋይዳን በመረዳት ተቋማዊ እና ሀገራዊ የዕውቀት አስተዳደር ስርዓት ለመገንባት ያከናወናቸውን የተለያዩ ተግባራት ጠቅሰው አስረድተዋል፡፡
በኢንስቲትዩቱ የመረጃ አደረጃጀት እና ዕውቀት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ቃልኪዳን ተሾመ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ ያለውን አደረጃጀት እንዲሁም በሕግ የተሰጡትን ተግባራት ለታዳሚው አብራረተዋል፡፡ አቶ ቃልኪዳን በኢንስቲትዩቱም ሆነ በእርሳቸው ዳይሬክቶሬት የተከናወኑትን እንደ ብሄራዊ የልማት አመላካች ዳሽቦርድ እና ኮቪድ-19 ተኮር የመፍትሄ ስራዎች ያሉ ዋና ዋና ክንውኖችን አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ስራቸው እየተከናወነ ያሉትንና በቅርብ ተጠናቀው ይፋ የሚሆኑትን በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ጆርናል እንዲሁም ተደጋጋሚ ግዢዎች ከመፈፀም የሚያድነው በኢትዮጵያ የሚገኙ የቤተ-ሙከራ ግብዓቶችን የመመዝገብና ለተጠቃሚ የማሳወቅ ስራዎች ተጠቅሰዋል፡፡
በጠዋቱ መርሃ ግብር ሁለት ምሁራዊ ጥናቶች ሲቀርቡ ቀዳሚ የነበረው “knowledge management practices in commercial bank of Ethiopia” በሚል ርዕስ በዶ/ር ተምትም አሰፋ የቀረበው ነው፡፡ ጥናቱ በዕውቀት አስተዳደር ረገድ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ ያለውን ሂደት አንዲሁም ክፍተቶችን እና ከሌሎች ተቋማት በተለየ በዕውቀት አስተዳደር ላይ ስኬታማ እንዲሆን ያስቻሉትን አብይ ጉዳዮች የዳሰሰ ነው፡፡ ሁለተኛውን ያቀረቡት ዶ/ር ጌታቸው ኃይለማርያም በበኩላቸው “frugal knowledge sharing for frugal innovation diffusion in Africa” በሚል ርዕስ በዝቅተኛ ምጣኔ ሐብታዊ ደረጃ ላይ ላለው ማህበረሰብ ግልጋሎት ሊሰጡ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ አዘጋጅቶ ወደ ታች እንዲወርዱ የማድረግ ስራን እንዴት ማከናወን ይቻላል በሚለው ላይ ገለፃ አቅርበዋል፡፡
ተሻሽሎ የቀረበው ፈጣን የህዝብ ማመላለሻ ጀት
*******************************
ከ 18 ዓመታት በፊት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ጥቅምት 24 2003 ከለንደን ወደ ኒዮርክ ጆንኦፍ ኬኔዲ አየር መንገድ አንድ ልዩ በረራ ተደረገ፡፡ ይህ በለንደንና በኒዮርክ መካከል ያለውን ርቀት የ3 ሰዓት ብቻ ለማድረግ የታለመው የታዋቂው ሱፐርሶኒክ አየር መንገድ ባለቤት ኮንኮርድ የመጨረሻ በረራ ነበር፡፡ ድርጅቱ ምንም እንኳን ከውጥኑ ትልቅ ህልም ይዞ የተነሳ ቢሆን በገጠመው ከቴክኖሎጂና ከንግድ ጋር የተያያዘ ችግር ውጥኑ ሳይሰምር ቀርቷል፡፡ በወቅቱ የኮንኮርዱ ሱፐርሶኒክ የመንገደኞች ተምዘግዛጊ ጀት በጣም ፈጣን የነበረ ሲሆን የድምጹ ጉዳይ ግን አይወራ አይነገር የሚያሰኝ ነበር፡፡
ከነዚህ ሁሉ አመታት በኋላ ፈጣን የህዝብ ማመላለሻ ጀቶች ወደ ስራ ሊመለሱ መሆኑ ተሰምቷል፡፡ ከቴክኖሎጂ አንጻር ከዚህ ቀደም የነበረውንና ለኮንኮርድ መክሰር ምክንያት የሆነው ችግር እንደተፈታ ቢገለጽም ከገበያና ከኢኮኖሚ አንጻር ያለው ችግር ግን አሁንም ሙሉ በሙሉ የተቀረፈ አይመስልም፡፡
የተለያዩ ድርጅቶችና የምርምር ተቋማት በአዲሱ ትውልድ ሱፐርሶኒክ የመንገደኞች አውሮፕላን ላይ ከፍተኛ በጀት አፍስሰው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል የአሜሪካው ቡም 196 ሚሊዮን ዶላር በመመደብ ኦቨርቱር የተሰኘ አዲስ ሱፐርሶኒክ ሞዴል በያዝነው የፈረንጆች አመት ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን አሳውቋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ናሳ የቀድሞውን ከፍተኛ ድምጽያለውን ሶኒክ ጀት X-59 የሚባል ፕሮጀክት ቀርጾ ድምጹን ለማሻሻል እየሰራ ነው፡፡ ፉክክሩ በዚህ ብቻ አላበቃም፤ ኤሪዮን ከቦይነንግ ጋር በመተባበር በ2025 ወደ አየር ሊወጣ የሚችል የቢዝነስ ሱፐርሶኒክ ጀት እያበለጸጉ ነው፡፡
በጣሊያኑ ቶሪኖ ፖሊቴክኒክ ዩኒቨርሲቲው ፐሮፌሰር ኒኮል ቪዮላ ስለ ሁኔታው ‹‹ከዚህ በኋላ ህልም ብቻ ሆኖ አይቀርም በሁሉም አካባቢ ርብርብ እየተደረገበት ነው›› የሚል ሀሳብ ሰንዝረዋል፡፡ የእነዚህ አይነት የመንገደኛ ጀቶች አንዱ ጥቅም አነስተኛ ድምጽ እንዲኖራቸው ተደርገው መሰራታቸው ነው፡፡
የድምጽ ብክለቱን ሁኔታ ለማስታወስ የጦር ጀቶችና ሚጎች በረራ ሲያደርጉ የሚፈጠረውን ድብልቅልቅ ማስታወስ በቂ ነው፡፡ አንዳንዴ እንዲህ አይነት በረራዎች ሲደረጉ አልፎ አልፎ ህንጻዎች ሊፈርሱ ወይም የበርና መስኮት መስታዎቶች ሊረግፉ ይችላሉ፡፡ ይህም ከሚፈጠረው ከፍተኛ ድምጽ የተነሳ ነው፡፡
በፈረንሣይ ኤሮስፔስ ላቦራቶሪ በሆነው ‹ኦኔራ› ከፍተኛ የአየር ኃይል ተመራማሪ የሆኑት ጄራልድ ኬሪየር ‘የሶኒክ ጀቶች ድምጽ ጥንካሬ በዋናነት በአውሮፕላኑ ቅርፅ ላይ የተመሠረተ ነው’ ብለዋል ፡፡ ተመራማሪው ተቆጣጣሪ ባለሥልጣናት በሶኒክ እና በዝቅተኛ ፍጥነት አውሮፕላኖች በሚወጣው ጩኸት ዙሪያ ማስረጃዎችን በሚሰበስበው ‹RUMBLE› ፕሮጀክት ውስጥ ተሳትል ፡፡
የአውሮፕላኑን ጆሜትሪያዊ ቅርጽ በማስተካከል ድምጹን ከ100 ዴሲቤል ወደ 70-80 ዴሲቤል ድረስ ማሳነስ እንደሚቻል ተመራማሪው ተናግረዋል፡፡ ይህም የአንድ የኤሌክትሪክ ማጽጃ ድምጽን የሚያክል ነው፡፡ የአውሮፕላኑ አፍንጫ ሹለት በተጨመረ ቁጥር የድምጽ መጠኑም እንደሚቀንስ ተረጋግጧል፡፡
ምንጭ technology.org
የቢትኮይን ዋጋ ለመጀመሪያ ጊዜ 50,000 ዶላር ደርሷል
=======================
ባለፉት ሁለት እና ሶስት አመታት ዋጋው አሽቆልቁሎ የነበረው ቢትኮይን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ ወጋው እየጨመረ መምጣቱ ተነግሯል፡፡ የፈረንጆቹ አዲስ አመት ከገባ ጀምሮ አንዱ የቢትኮይን ዋጋ 32,149 ዶላር ሲሸጥ የነበረ ሲሆን ይህ ዋጋ በቀጣዮቹ ጊዜያት ይበልጥ ጨምሮ በትናትናው ዕለት ከ50,000 ዶላር በላይ በማውጣት እስከዛሬ ያልታየ ሪከርድ ሰብሯል፡፡
የቢትኮይን ዋጋ እንዲህ ለመጨመሩ ዋና ምክንያት ተደርጎ የተወሰደው እንደ ቴስላ፣ ማስተርካርድ እና ቢ ኤን ዋይ ሜሎን ያሉ ግዙፍ ኩባንያዎች ታዋቂውን ክሪፕቶከረንሲ በከፍተኛ ሁኔታ በመግዛታቸው እና ሌሎች ትልልቅ ድርጅቶችም የክፍያ ስርዓታቸውን ወደዚህ የቢትኮይን አሰራር እየቀየሩ በመምጣታቸው ነው ተብሏል፡፡ ለአብነት ኤለን መስክ የሚመራው ቴስላ በአክስዮን ገበያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት እጅግ ከፍተኛ ዋጋ ካላቸው ኩባንያዎች በቀዳሚነተ የሚቀመጥ ሲሆን ይህ ኩባንያ በቅርቡ 1.5 በሊዮን ቢትኮይን ከመግዛቱም ባለፈ አንዳንድ ምርቶቹን በዚህ የክሪፕቶከረንሲ ለመገበያየት ማቀዱ የቢትኮይንን ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እንደጨመረው ተገልጿል፡፡
ከዚህ በለፈም ቢ ኤን ዋይ ሜሎን እየተባለ የሚጠራው አንጋፋ የአሜሪካ ባንክ ለቢትኮይን የግብይት ስርዓት ከፍተኛ ይሁንታ እና ድጋፍ ማድረጉ ሌላው ተጨማሪ ምክንያት ሲሆን እንደ ማስተርካርድ እና ማይክሮ ስትራቴጂ ያሉ ግዙፍ የፋይናንስና የቢዝነት ተቋማት በቢትኮይን ላይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ማካሄደቸው ለክሪፕቶከረንሲው ዋጋ መጨመር ሌሎች ምክንያት ናቸው፡፡ በ2016 ከፍተኛ የዋጋ እድገት የታየበት ቢትኮይን በተያዘው የፈረንጆቹ 2021 አመትም የ 72% ከፍተኛ ጭማሪ እንደሚያስመዘግብ ተነግሯል፡፡
ቢትኮይን የስነ-መሰውር (cryptography) ቴክኖሎጂን የሚጠቅም አንዱ የክሪፕቶከረንሲ ክፍል ሲሆን የብሎክቼን ቴክኖሎጂ ለመጀመሪያ ጊዜ የተተገበረበት እና አዲስ አይነት የዲጂታል ገንዘብ አጠቃቀምን እንዲሁም አከፋፈል ስርዓትን የሚዘረጋ ነፃ ሶፍተዌር ነው፡፡ ቢትኮይን በሁለት ሰው መካከል የዲጅታል፣ የገንዘብና የክፍያ ልውውጥ የሚካሄድበት አቻ ለአቻ (peer-to-peer) አሰራር ሲሆን የክፍያ ስርዓቱ ያለገንዘብ ተቋም ጣልቃገብነት ሊፈፀም ይችላል፡፡
ቢትኮይን መገበያያ እንደሌሎች የክሬፕቶከረንሲ አይነቶች ከልማዳዊው የገንዘብ አሰራር የተለየ ይዘት ያለው ሲሆን በኮምፒውተራችን ላይ ይህ ዲጂታል ገንዘብ ነው ብለን የምንጠቀመው ፋይል ወይም መረጃ የለም፡፡ ይህም የሚሆንበት ምክንያት ዲጂታል ገንዘቡ በየትኛውም አገር ስላልተፈጠረና በማንኛውም አገራዊ ወይም ዓለም አቀፋዊ የመንግስት ቷቋም ስለማይተዳደር ነው፡፡ የዲጂታል ገንዘብ ልውውጥ ስርዓቱም የሚከናወንባቸው ኮምፒውተሮች በተለያየ የዓለም ክፍል በሚገኙ ግለሰቦች ንብረትነት የሚተዳደሩ ናቸው፡፡ ይሄ አሰራር “distributed computation” የሚባል ሲሆን ዋና ዓላማውና ጥቅሙም የመረጃ ልውውጡና አስተዳደሩ በአንድ ተቋም ስር ሳይወድቅ ለሳይበር ጥቃት የማይመች ማድረግ እና የመረጃ ትክክለኝነቱ “data integrity” ዋስትና እንዲጠበቅ ማድረግ ነው፡፡ የቢትኮይን መገበያያ ቀድመው ከተፈጠሩ የክሬፕቶከረንሲ አይነቶች የመጀመሪያውና ዝነኛው ቢሆንም ከሱ በኋላ ግን ከ1500 በላይ የሚሆኑ የክሬፕቶከረንሲ አይነቶች አንደተፈጠሩ ተረጋግጧል፡፡
ምንጭ፡ Reuters እና Republicworld
የኮቪድ-19 ክትባትን ባንከተብስ? ምን ይመጣብናል?
====================
እንደ ታንዛኒያ እና ማዳጋስካር ያሉ ሀገራት ህዝባቸውን በኮቪድ-19 መከላከያ ክትባቶች የመከተብ ዕቅድ እንደሌላቸው አሳውቀዋል፡፡ በግለሰብ ደረጃም ክትባቱን መውሰድ የማይፈልጉ ሰዎች መኖራቸውን ሰምተን ይሆናል፡፡ ግን እንደዚህ አይነት እርምጃዎች ምን ሊያመጡ ይችላሉ?
ያን ያህል የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባትን ያልወሰዱ ዜጎች ባሉባት ሀገር ውስጥ የወረርሺኙ ቆይታ የመርዘሙ ዕድል የሰፋ ይሆናል፡፡ ቫይረሱ በዘላቂነት ማህበረሰቡን እያጠቃ የሚቆይበት ጊዜ በተራዘመ ቁጥር ደግሞ ቫይረሱም ይበልጥ እራሱን እየለወጠ ይመጣል፡፡ ይህ መለወጥ (mutation) ደግሞ ይበልጡን አደገኛ ለሆኑ የሳርስ-ኮቭ-2 አይነቶች ምቹ መፈልፈያን ሊፈጥር ይችላል፡፡ በበራሒ ኮዳቸው ላይ ለውጦችን አድርገው ብቅ የሚሉት አዳዲሶቹ የኮሮና ቫይረስ አይነቶች በበኩላቸው ቀድሞ ክትባቱን የወሰዱት ሰዎችን ጭምር የማጥቃት አቅምን የማዳበር ዕድል አላቸው፡፡ ክትባት አንድ የቫይረስ አይነትን ሰውነታችን እንዲያውቀው በማድረግ የበሽታ መከላከል ስርዓቱን እንዲቀሰቅስ ማድረጊያ ነውና ቫይረሱ ሲለወጥ ያለመታወቅ እድሉን ይጨምረዋል፡፡ በዚህ አኳሀን አብዛኛው ህዝብ የተከተበባቸው አካባቢዎች እንኳን ሌላ ቦታ ላይ አይነቱን በለወጠ ምናልባትም ከቀድሞው የበለጠ ተላላፊና ገዳይ በሆነ ቫይረስ ይጠቃሉ፡፡ ምድራችን ላይ ማንም ለብቻው ተከልሎ አለመገኘቱን ስናስብ ደግሞ ሁላችንም ክትባቱን ካላገኘን አንዳችንም ደህንነታችን በብቸኝነት ጠብቀን መኖር እንደማንችል እንረዳለን፡፡
ታድያ መፍትሄው ምንድነው?
ከዚህ ችግር ለመዳን መንግስታት ዜጎቻቸውን ከከተቡ በኋላ ድንበራቸውን ዘግቶ መቀመጡ ቀላል ነገር ስለማይሆን ከዚህ ይልቅ ክትባቶቹን በተቻለ ፍጥነት ለሁሉም ሀገራት ዜጎች ማዳረስ ቀዳሚው መፍትሄ ነው፡፡ አሁን ላይ በቫይረሱ የተያዘን ሰው የሚያድኑ ምንም አይነት መድሃኒቶች ስለሌሉም ክትባቱን የማዳረሱ እንቅስቃሴ በፍጥነት መከናወን ይኖርበታል፡፡ ይህን ቶሎ ማሳካት እንዲቻል መንግስታት ክትባቶቹን በማምረት እና ለሁሉም በማዳረስ ረገድ በጋራ መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ ለክትባቶቹ አምራቾች የሚደረገው የገንዘብ ድጋፍም ሊያድግና ተጨማሪ ሌሎች ማምረቻዎችም በማደግ ላይ ባሉት ሀገራት ጭምር ሊከፈቱ ይገባል፡፡ ይህም የቴክኖሎጂ ሽግግርን ጭምር የሚጠይቅ ተግባር ነው፡፡
ታድያ በርካታ ሀገራት ክትባቶቹን ለማግኘት ገና እየተጠባበቁ በመሆናቸው ወረርሺኙ ከተነሳበት ጊዜ አንስቶ ሲተገበሩ የቆዩትን እንደ ማስክ ማድረግ እና አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ያሉ የጥንቃቄ እርምጃዎችን መከወኑ ቢያንስ በአንድ ማህበረሰብ ውስጥም ሆነ ከአንድ ማህበረሰብ ወደ ሌላ ማህበረሰብ የሚኖረውን የቫይረሱን የስርጭት ይቀንሰዋል፤ ወደ ሆስፒታል የሚያመራውን እና ህይወቱን የሚያጣውን ሰው ቁጥርንም ያወርደዋል፡፡ በተጨማሪም በአንድ አካባቢ ከፍ ያለ ስርጭት መኖሩን የሚያሳይ መረጃ ሲገኝ አካባቢው ላይ የእንቅስቃሴ ገደቦችን ማድረግ ይገባል፡፡
በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን የተጠቂ መጠን በምርመራ መለየቱና የቫይረሱን በራሒ በቤተ-ሙከራ እየመረመሩ መከታተሉ ቀዳሚው ነገሮችን መረዳት የሚያስችል መንገድ ነው፡፡
ምንጭ፡ The Conversation