TechIn2
1.22K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
ምናባዊ እውነታ (VR) የአዕምሮ እድገትን ለመለካት
*****************************
ተመራማሪዎች የሰዎችን የአዕምሮ እድገት ወይም ብቃት ለመለካት የሚያስችል ምናባዊ እውነታ ወይም ቨርቹዋል ሪያሊቲ መስራታቸው ተነገረ፡፡ ለወትሮው ይህ ቴክኖሎጂ የተለያዩ በኮምፒውተር የታገዙ ጨዋታዎችን ለመጫዎት የሚያስችል ሲሆን አሁን ላይ ተመራማሪዎች ሰዎች በገሃዱ አለም ውስጥ ያለውን መደበኛ እንቅስቃሴ እንዴት እንደሚከውኑ ማየት የሚያስችላቸው ቴክኖሎጂን አክለውበት የሰዎችን የአዕምሮ እድገት ለመለካት በሚያስችል መልኩ እንደሰሩት ተሰምቷል፡፡ ይህም የዕለት ከዕለት ተግባራቸውን ለመከወን የሚቸገሩ ሰዎችን በእጅጉ እንደሚያግዛቸው ታምኖበታል፡፡
ሂዩማን ቢሄቪዮር ሪፖርትሰ በተባለ ህትመት የወጣው መረጃ እንዳመለከተው ተመራማሪዎች ቨርቹዋል ሪያሊቲን ሰዎች ተግባራትን ለመከወን የሚጠቀሙትን የመረጃ ብዛትና የመፈጸም አቅማቸውን ለመለካት እንደሚያስችል መናገራቸውን አስነብቧል፡፡
42 ጤናማ የኮሌጅ ተማሪዎች በተሳተፉበት የሙከራ ወቅት ተሳታፊዎች ለቤት ውስጥ አገልግሎት የሚያስፈልጉ የምግብ ግብዕት ዝርዝሮችን አንብበው ገበያ ሄደው እንዲገዙ ከተደረገ በኋላ የማስታወስና የመርሳት መጠኑን ለመለካት ተችሏል፡፡ የዝርዝሩ መጠን እየጨመረ በሔደ ቁጥር የመዘንጋት ሁኔታውም እንደጨመረ ተነግሯል፡፡ ይህም የስራ መጠን በጨመረ ቁጥር የአዕምሮ የመፈጸም ብቃት እየቀነሰ እንደሚሔድ ማሳያ መሆኑን ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
ጥናቱ በአጠቃላይ ነገሮችን በአግባቡ ወይም ባሰቡት ልክ የመፈጸም ችግር ያለባቸውን ሰዎች ለማገዝ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ተመራማሪዎቹ አሳውቀዋል፡፡
ምንጭ Tech Xplore
This media is not supported in your browser
VIEW IN TELEGRAM
ማርስ 20 የሚደርሱ የበረዶ ዘመን ነበሯት
--------------------------------
በማያቋርጥ የአቧራ ማዕበል የተሸፈነችው ቀይዋ ፕላኔት ማርስ ወደኋላ በነበረው ዘመኗ ከስድስት እስከ ሃያ የሚደርሱ የተለያየ የበረዶ ጊዜያትን ወይም ዘመናትን ማሳለፏን የኮስሞሎጂ ባለሙያዎች እና የስነ ምድር አጥኚዎች ይናገራሉ፡፡ የማርስ በበረዶ መሸፈን ኦብሊኪዊቲ (obliquity) ተብሎ በሚጠራው ፕላኔቷ በምትሽከረከርበት ዛቢያ ዙሪያ ያዘመመችበት ዲግሪ ቋሚ ከመሆን ይልቅ የመለዋወጥ በህሪ ሲያሳይ የሚኖር ክስትት ሲሆን ተመራማሪዎችም የፕላኔቷን በበረዶ ግግር የመሸፈን ጊዜያት ወጥ እና ተከፋፍለው በነበሩ ረዥም የበረዶ ዘመናት (Ice Ages) ውስጥ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡
ናሳን ጨምሮ ከአሪዞና፣ ፊችበርግ እና ቴክሳስ-አዉስቲን ዩኒቨርስቲ የተወጣጡ ተመራማሪዎች የተሳተፉበት ይህ ምርምር በኮልጌት ዩኒቨርስቲ በሚገኙት የስነ ምድር ተመራማሪ ፕሮፌሰር ጆይ ሌቪ መሪነት የተከናወነ ነው፡፡ ተመራመሪዎች እንደሚሉት ፕላኔቷ አሁን የተሸፈነችበት በረዥም የጊዜ ሂደት የሚፈጠረውና በገፅዋ ላይ በዝግታ የሚንቀሳቀው ብዛት ያለው የበረዶ ግግር ወይም (glaciers) ከብዙ ሚሊዮን አመታት በፊት በፕላኔቷ ላይ የተለያዩ የበረዶ ዘመናት አንደነበሩ የሚያመለክት ነው ይላሉ፡፡
ፕሮፌሰር ሌቪና የምርምር ቡድናቸው በፕላኔቷ ምህዋር ላይ መቀመጫውን አድርጎ ለተለያዩ ምርምሮች የሚረዱ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ምስሎችን በሚያነሳው Mars Reconnaissance Orbiter ሳተላይት አማካኝነት የገኟቸው 45 የሚጠጉ የበረዶ ግግር ምስሎች ለጥናታቸው እንደግብዓት የተጠቀሙ ሲሆን፤ ከዚያ በተጨማሪም 60 ሺ የሚደርሱ የፕላኔቷን የድንጋይ ዐለቶች በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ አማካኝነት ትንተና እንዲደረግባቸው አድረገዋል፡፡
ተመራማሪዎች በእነዚህ መረጃዎች ላይ ባደረጉት ትንተና ቀይዋ ፕላኔት ማርስ ወደኋላ በነበረው ዘመኗ ከስድስት እስከ ሃያ የሚደርሱ የተለያየ የበረዶ ጊዜያትን ወይም ዘመናትን ማሳለፏን ያረጋገጡ ሲሆን ቢያንስ ከ300 እስከ 800 ሚሊዮን አመታት ውስጥ ይህ የበረዶ ዘመን ተከስቶ እንደነበርም ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ ፕሮፌሰር ሌቪ ይህ የምርምር ውጤት የፕላኔቷን የረዥም አመታት ታሪክ በሚገባ ለመረዳት እና ለሌሎች ተያያዥ ጥናቶች ጠቃሚ ግብዓት ለመስጠት እንደሚረዳም ተናግረዋል፡፡
ምንጭ፡ Big Think
የተሳትፎ ጥሪ፤ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሲምፖዚየም
===================
የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሲምፖዚየም ለማዘጋጀት ይፈልጋል። ስለሆነም በግብርና ዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ በፋይናንስ ዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ በጤና ዲጂታል ቴክኖሎጂ እንዲሁም የቢሮዎችን አሰራር ስርዓት የሚያዘምኑ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ውጤቶች ያላችሁ እና በዚሁ መስክ ላይ የተሰማራችሁ የግል፣ የመንግስት፣ የትምህርትና የምርምር ተቋማት ወይንም ግለሰቦች በዚህ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሲምፖዚየም እንዲካፈሉ ተጋብዘዋል።
ለምዝገባው የሚያስፈልጉ ነገሮች፡-
• ከ500 ቃላት ያልበለጠ ማብራርያ
• ከ150 ቃላት ያልበለጠ ስለ እርስዎ እና የፈጠራ ክንውንዎ የሚገልፅ ማብራርያ
• ከ1-3 የሚሆኑ ስለስራዎ የሚገልፁ ምስሎች (ከ1 ሜ.ባ ያልበለጠ) እና የቪዲዮ ሊንክ (ከተቻለ)
• የግንኙነት አድራሻ (ስም፣ የኢሜይል አድራሻ፣ ስልክ ቁጥር)፣ ሲቪ እንዲሁም የድረ-ገፅ፣ ትዊተር እና ኢንስታግራም አድራሻ
ስለሆነም ከዚህ በታች ባለው ማስፈንጠሪያ በመጠቀም መመዝገብ የምትችሉ መሆኑን እናሳውቃለን።
የመመዝገቢያ ገፅ፤ https://forms.gle/uLXgtzHVHZ79yabb8
የመመዝገቢያ ጊዜ፤ ከየካቲት 3 እስከ የካቲት 8 2013 ብቻ የሚቆይ ይሆናል።
ለተጨማሪ መረጃ 4 ኪሎ ከፓርላማ የትራፊክ መብራት ወደ ፒያሳ/ቸርችል ጎዳና በሚወስደው መንገድ 150 ሜትር ተጉዘው በሚያገኙት ዋና ቢሮዋችን ወይንም በኢ-ሜይል አድራሻ smd-team@techin.gov.et መጠቀም ይችላሉ
ሳይንቲስቶች ከዚህ በፊት አይተን የማናውቀውን የሂሳብ ትምህርት የሚያመነጭ ማሽን አግኝተዋል
*************************
ስሙ ስሪኒቫሳ ራማኑጃን ነበር ፣ እናም ሌሎች ሰዎች በጭራሽ የማያሰሏቸውን ጥቂት ሂሳቦችን ለማለም ልዩ ስጦታ ነበረው። ይህን ልዩ ችሎታውን ከፈጣሪ ስጦታ ጋር የሚያገናኙት ህንዶች ለዓለማችን በሺዎች የሚቆጠሩ የሒሳብ ስሌቶችንና ቀመሮችን አበርክተዋል፡፡ እንዲሁም ደግሞ እስካሁን ድረስ እውነትነቱ ያልተረጋገጠውና በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ያለው devising conjectures ሀሳብ አመንጪ በመሆን ይታወቃል፡፡
ይህ የተረጋገጡና ያልተረጋገጡ ሒሳባዊ እሳቤዎችን የመንደፍ ችሎታ በጣም በጥቂት ሰዎች የተለመደ ነው፡፡ የዚህን ልጅ ልዩ የሚያደረገው በዘርፉ በቂ የሚባል ስልጠና ያልወሰደ መሆኑ ነው፡፡ አሁን ላይ በእስራኤል ተመራማሪዎች የተሰራው ስልተ ቀመር ፈጠራ እንደ ራማኑጃን ያሉ የሂሳብ ግምቶች ግኝት በራስ-ሰር ሊረዳን ይችላል ፡፡
በ 32 ዓመቱ ህንድ ውስጥ በሞተው በራማውጃን ስም የተሰየመ - ‹የራማኑጃን ማሽን› እንደ π እና e ያሉ የሂሳብ ቋሚዎችን የሚያካትቱ እሳቤዎችን በራሱ የማመንጨት ችሎታ ያለው የኮምፒዩተር ስርዓት ነው ፡፡ በአሁኑ ሰዓት አዳዲስ የሚባሉ ሒሳባዊ ቀመሮች መገኘታቸውን መስማት የተለመደ አይደለም፡፡
አዲሱ ማሽን ከሒሳባዊ ፈጠራ ጋር የተያያዙ መዘግየቶችን ሊያፋጥን ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸው ተመራማሪዎቹ አሳውቀዋል፡፡ እስካሁን ድረስ አልጎሪዝም ማሽኑ በቀላሉ የሚናገሩ ግምቶችን የሰራ ሲሆን፣ እንደ π ያሉ ቋሚዎችን ለማስላት አዳዲስ ክፍልፋይ መንገዶችን በማፈላለግ እና ገና ያልተረጋገጡ ግምቶችን ይዞ መጥቷል፡፡
ከፍተኛ ደራሲና የፊዚክስ ሊቅ የሆኑት አይዶ ካሚር “ኮምፒዩተሩ ቀመሩን ቀላል ወይም ከባድ መሆኑን የሚያረጋግጥ ስለሆነ አዲሱ ውጤት በየትኛውም የሂሳብ ዕውቀት ላይ የተመሠረተ ሳይሆን በሂሳብ ቋሚዎች ውስጥ ባሉ ቁጥሮች ላይ ብቻ የተመሠረተ ነው” ብለዋል፡፡
ስልተ ቀመሩም ራሱ ያገኘውን ግምቶች ማረጋገጥ የማይችል መሆኑን መጠቆም አስፈላጊ ነው በዚህ ጊዜ ተግባሩ በሰው ሂሳብ ባለሙያዎች እንዲፈታ ተትቷል ሲሉ አክለዋል፡፡
ምንጭ Science Alert
ቮዳፎን እና ኦሬንጅ በኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎት ለመስጠት እንደሚወዳደሩ ተናገሩ
===================
ግዙፎቹ የፈረንሳይ እና እንግሊዝ የቴሌኮም ተቋማት ኦሬንጅ እና ቮዳፎን በኢትዮጵያ ለመስራት የሚያስችላቸውን የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድ ለማግኘት የመወዳደር እቅድ እንዳላቸው አስታወቁ፡፡ ኩባንያዎቹ በቅርቡ የኢትዮጵያ ኮምዩኒኬሽን ባለስልጣን የቴሌኮም ፈቃድ የማግኛ ጥያቄ ማቅረቢያ ቀኑን እስከ መጋቢት 27 ድረስ ማራዘሙን ተከትሎ ነው ከካፓሲቲ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ለመወዳደር ማቀዳቸውን የተናገሩት፡፡
የኦሬንጅ ቃል አቀባይ ኢትዮጵያ የቴሌኮም ገበያዋን ለመክፈት በምታደርገው ሂደት ውስጥ ተሳታፊ እንሆናለን ብለው ተናግረዋል፡፡ ባሳለፍነው ሰኔም ኦሬንጅ በገበያው ላይ ያለውን ፍላጎት ለኢትዮጵያ ኮምዩኒኬሽን ባለስልጣን በይፋ አሳውቆ ነበር፡፡ በተመሳሳይ ወቅት ቮዳፎንም እንዲሁ ያለውን ፍላጎት ለመንግስት አካላት አስታውቆ ነበር፡፡
እንደ ቮዳፎን ኃላፊ ከሆነ ፍቃድ በማግኘቱ እንቅስቃሴ ውስጥ በቮዳፎን ባለቤትነት የሚንቀሳቀሰው የኬኒያው ሳፋሪኮም ከፊት ተሰልፎ ሂደቱን የሚመራለት ሲሆን ቮዳፎን ቀዳሚ የአክሲዮን ባለቤት ከሆነበት የደቡብ አፍሪካው ቮዳኮም ጋራም ተቀራርቦ የሚሰራ ይሆናል፡፡ ቮዳፎን በስራው ላይ ከጃፓኑ ሱሚቶሞ የቴኖሎጂ ድጋፍን እንደሚያገኝ ይጠበቃል፡፡
የቴሌኮም ኩባንያው በኢትዮጵያ የመንቀሳቀስ ፈቃድ ለማግኘት ፍላጎት ያለው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ እያንዳንዱን የኢንቨስትመንት እድል በጥንቃቄ እንደሚመለከተውና አዋጭ ሆኖ ባላገኘው ስራ ላይ መዋለ ነዋዩን እንደማያፈስ ተናግሯል፡፡
በሌላ በኩል አንድ የኦሬንጅ ኃላፊ እንደተናገሩት እንደ ድርጅት በጉዳዩ ላይ የሚኖረውን ዝርዝር የቁጥጥር ደንብ እየጠበቁ ሰሆን ወደ ገበያው ለመግባት አመቺና በቂ ምጣኔ-ሐብታዊ ስፍራ ስለመኖሩም ክትትል እያደረጉ ነው፡፡ ሆኖም ተገኙ የተባሉ ይፋዊ ያልሆኑ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ኦሬንጅ በኢትዮ-ቴሌኮም ድርሻን ለመግዛት በሚደረገው ውድድር ላይም ተሳታፊ ለመሆን ማቀዱን ነው፡፡ ኩባንያው ከዚህ ቀደም ለሁለት ዓመታት የአስተዳደር ስራን ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋራ ሲሰራ መቆየቱም ይታወሳል፡፡
ባለፈው ሳምንት በአፍሪካ ብቻ 110 ሚሊዮን ደንበኞች ያሉት ግዙፉ የህንድ የቴሌኮም ኩባንያ ኤርቴል በውድድሩ ተሳታፊ እንደማይሆን በአፍሪካ ሰራ አስፈፃሚው ራጉናት ማንዳቫ አማካኝነት አስታውቆ ነበር፡፡ በአንፃሩ ከሀገሩ ውጪ በአፍሪካ ብዙም ታዋቂነት የሌለው ሼሪንግ ሞባይል የተሰኘው የቻይና ኩባንያ በውድድሩ እንደሚሳተፍ ተናግሯል፡፡ የኢትዮጵያ ኮምዩኒኬሽን ባለስልጣን የቴሌኮም ፈቃድ የማግኛ ጥያቄ ማቅረቢያ ሲያራዝም ዝርዝር የጥያቄ ማቅረቢያ ጊዜ እንዲሁም የፋይናንስ እና ቴክኒካል ደንቦችን አላስቀመጠም፡፡
እስካሁን ድረስ የኢትዮጵያን የቴሌኮም ገበያ ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥሮ የቆየው በመንግስት የልማት ድርጅት የሚተዳደረው ኢትዮ-ቴሌኮም ነው፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መንግስት የኩባንያውን 45 በመቶ ድርሻ ለመሸጥ ማቀዱን ይፋ አድርጎ የነበረ ሲሆን ለዚህ ይረዳ ዘንድም ኢትዮ-ቴሌኮም ኬፒኤምጂ የተባለውን ድርጅት ቀጥሮ ነበር፡፡
ምንጭ፡ Capacity Media
የተሳትፎ ጥሪ፤ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሲምፖዚየም
===================
የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሲምፖዚየም ለማዘጋጀት ይፈልጋል። ስለሆነም በግብርና ዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ በፋይናንስ ዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ በጤና ዲጂታል ቴክኖሎጂ እንዲሁም የቢሮዎችን አሰራር ስርዓት የሚያዘምኑ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ውጤቶች ያላችሁ እና በዚሁ መስክ ላይ የተሰማራችሁ የግል፣ የመንግስት፣ የትምህርትና የምርምር ተቋማት ወይንም ግለሰቦች በዚህ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሲምፖዚየም እንዲካፈሉ ተጋብዘዋል።
ለምዝገባው የሚያስፈልጉ ነገሮች፡-
• ከ500 ቃላት ያልበለጠ ማብራርያ
• ከ150 ቃላት ያልበለጠ ስለ እርስዎ እና የፈጠራ ክንውንዎ የሚገልፅ ማብራርያ
• ከ1-3 የሚሆኑ ስለስራዎ የሚገልፁ ምስሎች (ከ1 ሜ.ባ ያልበለጠ) እና የቪዲዮ ሊንክ (ከተቻለ)
• የግንኙነት አድራሻ (ስም፣ የኢሜይል አድራሻ፣ ስልክ ቁጥር)፣ ሲቪ እንዲሁም የድረ-ገፅ፣ ትዊተር እና ኢንስታግራም አድራሻ
ስለሆነም ከዚህ በታች ባለው ማስፈንጠሪያ በመጠቀም መመዝገብ የምትችሉ መሆኑን እናሳውቃለን።
የመመዝገቢያ ገፅ፤ https://forms.gle/uLXgtzHVHZ79yabb8
የመመዝገቢያ ጊዜ፤ ከየካቲት 3 እስከ የካቲት 8 2013 ብቻ የሚቆይ ይሆናል።
ለተጨማሪ መረጃ 4 ኪሎ ከፓርላማ የትራፊክ መብራት ወደ ፒያሳ/ቸርችል ጎዳና በሚወስደው መንገድ 150 ሜትር ተጉዘው በሚያገኙት ዋና ቢሮዋችን ወይንም በኢ-ሜይል አድራሻ smd-team@techin.gov.et መጠቀም ይችላሉ
5ጂን ተሻግረው ለ6ጂ እየተፎካከሩ ያሉት ቻይናና አሜሪካ
========================
አብዛኛው የዓለማችን ክፍል በቀጣዮቹ ዓመታት ውስጥ የ5ጂ መሰረተ ልማትን ለመዘርጋት ገና እንቅስቃሴ ላይ ባለበት በዚህ ወቅት ቀጣዩን ቴክኖሎጂ የመቆጣጠሩ ጂኦፖለቲካዊ ውድድር በአሜሪካን እና ቻይና መካከል መጧጧፍ ጀምሯል፡፡ 6ጂን ቀድሞ አበልፅጎ በፓተንትነት መያዙ ኩባንያዎችንም ሆነ መንግስታት ከወዲሁ ቀጣዩ የኢንዱስትሪ አብዮት ተብሎ እየተነገረለት ካለው ከዚህ ቴክኖሎጂ ዋና የትርፍ ተቋዳሽ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡ ምንም እንኳን ቴክኖሎጂው ተግባራዊ ለመሆን ከዚህ በኋላ ቢያንስ 10 ዓመታት የሚፈጁበት ቢሆንም አሁን ላይ የተንቀሳቃሽ ግንኙነት ጣርያ ከሆነው 5ጂ አንፃር ፍጥነቱ በ100 እጥፍ የላቀ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ቀድሞ በሳይንሳዊ ልብ ወለዶች ላይ ብቻ ይታለሙ የነበሩትን እንደ ሆሎግራም፣ የበረራ ታክሲ እንዲሁም ከበይነ-መረብ ጋር የተገናኙ የሰው ልጅ የሰውነት አካላት በተለይም አንጎልን ሊያስተዋውቀን ይችላል፡፡
የቀድሞው የአሜሪካን ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ በስልጣል ላይ በቆዩባቸው አራት ዓመታት ውስጥ በቻይና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ላይ ያሳዩት ጠንካራ የተቃርኖ እንቅስቃሴ ኩባንያዎቹን ቢጎዳም ቻይናን በ5ጂ ቴክኖሎጂ ቀዳሚ ሆና ከመውጣት ግን አላገዳትም፡፡ አሁን ላይ ቻይና የዓለማችን ቀዳሚው የ5ጂ አሻራ ሲኖራት በአሜሪካን እና አጋሮቿ እየተገፋ ያለው ሁዋዌይም ከተፎካካሪ ኩባንያዎቹ ልቆ በዓለም የ5ጂ ቴክኖሎጂ መሪ ሆኗል፡፡ ታድያ 6ጂ አሜሪካ በ5ጂ ያጣቸውን የገመድ አልባ ግንኙነት መሪነት ድርሻ ዳግም የምትመልስበት ዕድል ሊሰጣት ይችላል፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎች አሜሪካን እንደ 5ጂው እድሏን እንደማታባክንና ለ6ጂ የሚደረገው ፉክክርም ከ5ጂ የላቀ ይሆናል ብለው ይናገራሉ፡፡
የ6ጂ ቴክኖሎጂ ጉዳይ በሁለቱ ሀገራት ፖሊሲ አውጪዎች ዘንድም ቦታ እየያዘ ይመስላል፡፡ ለምሳሌ የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ 6ጂን በተቻለ ፍጥነት ማግኘት እንደሚፈልጉ በትዊተር ገፃቸው ላይ አስፍረው ነበር፡፡ ቻይና በበኩሏ መንገዱን ቀድማ መጓዝ ጀምራለች፤ ሀገሪቱ ህዳር ወር ላይ ለ6ጂ የሚሆኑ አየር ሞገዶችን የሚሞክር ሳተላይት ያመጠቀች ሲሆን ሁዋዌይም የ6ጂ ጥናት ማዕከሉን በካናዳ መክፈቱ ተነግሯል፡፡ ሌላኛው ግዙፍ የቻይና የቴሌኮም ዕቃዎች አቅራቢ ኩባንያ ዜድቲኢ በበኩሉ ከቻይና ዩኒኮም ጋራ በመሆን ቴክኖሎጂውን ለማበልፀግ እየሰራ ነው፡፡
እነዚህ እንቅስቃዎች በቻይና ቢቀላጠፉም አሜሪካም እጇን አጣጥፋ አልተቀመጠችም፡፡ በአውሮፓውያኑ 2018 ለሦስት ወራት ዜድቲኢ የአሜሪካን ቴክኖሎጂዎችን መመግዛት እንዳይችል በማገድ የተቋሙን ህልውና የተገዳደረችውና የቻይና ኩባንያዎችን መጠፍነግ እንደምትችል ያሳየችው አሜሪካን ሁዋዌይ ላይም ተመሳሳይ ስልት በመጠቀም ቴክኖሎጂውን ማግኘት እንዳይችል ልትጥር ትችላለች፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ለፉክክረ የሚሆናትን ተጨማሪ መንገድ እያበጃጀች ያለችው ሀገሪቱ የቴሌኮምዩኒኬሽን ኢንዱስትሪ መፍትሄዎች ህብረት (ATIS) በተሰኘው የቴሌኮም ደረጃዎች አውጪ ተቋሟ አማካኝነት የ6ጂ መሪነትን ለማግኘት ያስችለኛል ያለችውንና አፕል፣ ኤቲ & ቲ፣ ኳልኮም፣ ጉግል እና ሳምሰንግን የመሳሰሉ ታላላቅ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን ያቀፈ ጥምረት መስርታለች፤ ሁዋዌይ ከዚህ ጥምረት ውጪ ተደርጓል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የ6ጂ ቴክኖሎጂን አስመልክቶ ወደፊትም አሜሪካን እና አጋሮቿ ከሁዋዌይ ጋር ያላቸቸውን ኩርፊያ እንደማያርቁ ይጠበቃል፡፡ አሁን ላይ ዓለም ሁዋዌይን አስመልክቶ በሁለት ጎራ ቆማለች፤ በአሜሪካን መሪነት ጃፓን፣ አውስትራሊያ፣ እንግሊዝ እና ሌሎችም አጋር ሀገራት ሁዋዌይን በ5ጂ መሰረተ ልማታቸው እንዳይሳተፍ አስወጥተውታል፡፡ ሀገራቱ ሁዋዌይ የ5ጂ ቴክኖሎጂን ለተስፋፋ የድሮን ስለላ እንዲሁም የአምባገነን አገዛዞች መጠቀምያ ያደርገዋል ብለውም ይሰጋሉ፡፡ በተቃራኒው ጎራ ደግሞ እንደ ሩሲያ፣ ፊሊፒንስ፣ ታይላንድ እንዲሁም ሌሎች የአፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ለሁዋዌይ እጃቸውን ዘርግተው ተቀብለውታል፡፡
ታድያ ምንም እንኳን የምርምር ስራው ገና ጅማሮው ላይ የሆነና ወደ ስራ ለመግባትም ዓመታትን የሚፈጅ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ 6ጂ አጓጊ ፍጥነትን ይዞ እንደሚመጣ ይታሰባል፡፡ ይህም በሴኮንድ ቢያንስ 1 ቴራ ባይት ሊሆን ይችላል፡፡ ከፍጥነት ባሻገርም አሁን ላይ በ5ጂ 1 ሚሊ ሴኮንድ ብቻ የሆነው የመረጃ ማስተላለፍያ ጊዜ (Latency) 6ጂ ወደ 0.1 ሚሊ ሴኮንድ እንደሚያወርደው ይነገርለታል፡፡
ሆኖም 6ጂ ያመጣቸዋል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ከአጓጊ ገፀ-በረከቶቹን ከማበርከቱ አስቀድሞ መሻገር ያለባቸው ቴክኖሎጂያዊ መሰናክሎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ተመራማሪዎች በጣም አጫጭር መንገድ የሚጓዙ አየርሞገዶች እንዴት በቁሶች ውስጥ ሰርገው መግባት ይችላሉ ለሚለው ጥያቄ መልስ መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተጨማሪም ትስስር ወይም ኔትዎርኩ እጅግ በጣም የተጠቀጠቀና ለዚህም ጣብያዎቹ በእያንዳንዱ መንገድ እና ህንፃ ላይ ብቻም ሳይሆን ሰዎች ሲግናሎችን ለመቀበል እና ለማስተላለፍ በሚጠቀሙባቸው መሳርያዎች ላይም ጭምር እንዲተከል ሊያስገድድ ይችላል፡፡ በጤና፣ ግላዊነት እና የከተማ ንድፍ ረገድ የሚነሱበት ጠንካራ ጥያቄዎችም እንዳሉ ናቸው፡፡
ከቻይናና አሜሪካን ውጪ የአውሮፓ ህብረትም በቴክኖሎጂው ላይ እንቅስቃሴ ማድረግ የጀመረ ሲሆን በኖኪያ የሚመራና ኤሪክሰን እንዲሁም ቴሌፎኒካ የተካተቱበት የ6ጂ ፕሮጀክት በታህሳስ ወር ይፋ አድርጓል፡፡
ምንጭ፡ Tech Xplore
ገበያ ባለ ተሰጥዖዎችን ከፈላጊዎች የሚያገናኝ የስልክ መተግበሪያ ይፋ አደረገ
=======================
ገበያ ታለንት የተሰኘ ባለ ተሰጥዖዎችን ከፈላጊዎች የሚያገናኝ የስልክ መተግበሪያ ማቅረቡን ገበያ አስታውቋል፡፡ መተግበሪያው በአፍሪካም ሆነ ዓለም ዙርያ ያለውን የትስስር ተደራሽነቱን እንደሚያሳድግለት የተናገረው ገበያ አሁን ላይ በአህጉሪቱ ያሉ ስራ ፈላጊ ባለ ተሰጥዖዎች በቀላሉ የማመልከት፣ እድል አቅም እና ልምዳቸውን ባገናዘበ መልኩ ተከፋይ እንዲሆኑ የማድረግ እንዲሁም ትስስር የመፍጠርና ከሌሎች ጥቅሞችም ተካፋይ ያደርጋቸዋል ብሏል፡፡ በያዝነው ወር መጨረሻ ላይም በይነ መረብ ላይ የተመሰረተ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ ስታርታፖች እና ትላልቅ ተቋማትን ከባለ ተሰጥዖዎች የሚያገናኝ መተግበሪያ ይፋ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡
የገበያ ታለንት መተግበሪያ ከመሰራቱ አስቀድሞ ወደ ተቋሙ የባለተሰጥዖዎች ትስስሩን ለመቀላቀል የነበረው ሂደት በሰው አማካኝነት ይሰራ እንደነበረና ይህም በከፍተኛ ደረጃ የሰዎችን ተሳትፎ እንደሚጠይቅ የሚናገረው ገበያ አሁን ላይ መተግበሪያው ሂደቱን እንደሚያሻሽለው እና በቅርቡም በሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ ጭምር ተንተርሶ ሂደቱን ይበልጥ የሚያቀላጥፉ ገፅታዎች ተካታች እንደሚያደርግበት ገልጿል፡፡ በዚህም ከምዝገባ አንስቶ እስከ ፈተናና ቃለ መጠይቅ ያሉትን ሂደቶች ለማከናወን የሚያስችል ይሆናል ብሏል፡፡ መተግበሪያው ሂደቶቹን ከማቅለልም ባሻገር በራሱ በገበያ ቁጥጥር የሚደረግበት ስለሆነ ከከዚህ ቀደሙ በተሻለ ከመላው አፍሪካ እና የዲያስቦራ ማህበረሰቡ የተውጣጡ ምርጥ ባለ ተሰጥዖዎ አፍሪካውያንን እንደሚያወጣ ተነግሮለታል፡፡
ዋና መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገው ኩባንያው በቀጣዮቹ ከሦስት እስከ አምስት ዓመታት ውስጥ ባለው ጊዜ 100 ሺህ ባለ ተሰጥዖዎችን ለመለየት ያቀደ ሲሆን ከነዚህ ውስጥም 20 ሺውን የሚመርጥ ይሆናል፡፡ እንደ ገበያ ከሆነ አሁን ላይ በስታርታፕ እና ኮርፖሬሽኖች በቀዳሚነት ተፈላጊ የሆኑት ተሰጥዖዎች የሶፍትዌር ማበልፀግ፣ ግራፊክስ እና ንድፍ፣ የፕሮጀክት አስተዳደር፣ ዲጂታል ማርኬቲንግ፣ ምርት አስተዳደር፣ ሳይበር ደህንነት እና ሰው ሰራሽ አስተውሎት ናቸው፡፡
በዋናነት አፍሪካውያን ባለ ተሰጥዖዎችን ከፈላጊዎች የማገናኘት እና ስልጠናዎችን የመስጠት አገልግሎት ላይ ተሰማርቶ የሚገኘው ገበያ ባለ ተሰጥዖዎችን ለማሰባሰብ እና ከፈላጊ ተቋማት ለማገናኘት ዘመን አፈራሽ ቴክኖሎጂን እንደሚጠቀም ይናገራል፡፡ ኩባንያው በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባ፣ ናይሮቢ እንዲሁም በአሜሪካኗ ዶቨር፤ ዴልዌር ቢሮዎችን ከፍቶ በመስራት ላይ ነው፡፡
ምንጭ፡ Shega
This media is not supported in your browser
VIEW IN TELEGRAM
ጎግል ክሮም በቆዩ የኮምፒውተር ፕሮሰሰሮች ላይ መስራት ሊያቆም ነው
--------------------------------------
በአለማችን ላይ በአሁን ወቅት በብሮውዘር የቴክኖሎጂ ዘርፍ በቀዳሚነት የሚሰለፈው ጎግል ክሮም እንደአውሮፓውያኑ ከ2005 በፊት ተሰርተው አሁንም በማገልገል ላይ በሚገኙ የኮምፒውተር ፕሮሰሰሮች ላይ መስራቱን አንደሚያቆም ተነግሯል፡፡ የ Chromium አበልጻጊ ቡድን ከሰሞኑ እንዳስታወቀው x86 CPUs የተሰኘው የቀድሞው ፕሮሰሰር በጎግል ክሮም ላይ ተቀባይነት እንደማይኖረው እና ብሮውዘሩ በቀጣይ ይዞት በሚመጣው ማዘመኛ የትኛውም የኮምፒውተር ፕሮሰሰር ቢያንስ አንኳን (Supplemental Streaming SIMD Extensions 3) SSE3 የተባለውን ሲስተም የማይቀበል ከሆነ ብሮውዘሩ ለመስራት አንደሚቸገር ተነግሯል፡፡
እንደመረጃው ከሆነ ከቴክኖሎጂው ማደግ ጋር ተያይዞ ብዙ ተጠቃሚዎች ዘመናዊ ሃርድዌሮችን ስራ ላይ የሚያውሉ በመሆናቸው ብዙ ተጎጂዎች ይኖራሉ ተብሎ ባይታሰብም ከ15 ዓመት በላይ እድሜ ባላቸው ኮምፒውተሮች ላይ አሁንም ክሮምን የሚጠቀሙ ሰዎች ግን ግልጋሎቱን ላያገኙ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡ የ Chromium አበልጻጊ ቡድን ይዞት ወጣ በተባለው ሰነድ ላይ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥ የሆኑ ወስብስብ መረጃዎች በስፋት የተለቀቁ ቢሆንም ከአሁን በኋላ ጎግል ክሮም አንዲሰራ SSE3 ሊደግፍ የሚችል ፕሮሰሰር የግድ አስፈላጊ እንደሚሆን ተነስቷል፡፡
ረዥም ግዜ የቆዩ የኮምፒውተር ፕሮሰሰሮች በጊዜ ሂደት በአንዳንድ ሶፍትዌሮች ላይ ተቀባይነት እንዳይኖራችው የማድረጉ ነገር ትልቅ ምከንያት የሚቀርብበት ባይሆንም አንዳንድ የኮምፒውተር ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ ግን ችግሩ ከእድሜ ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን ላይ አንደሚገለፀው እንደአውሮፓውያኑ ከ2000 እስከ 2005 ባሉት አመታት የነበሩት የኮምፒውተር ፕሮሰሰሮች በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እየተተኩ በመምጣታቸው አነዚህን ሃርድዌሮች የሚጠቀሙ ሰዎች በቁጥር እያነሱ መተዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ የኮምፒውተር ፕሮሰሰር አማካይ የሕይወት ዘመን ከ7-10 ዓመት በመሆኑም በአዳደስ መልኩ ከሚበለፅጉት ሶፍትዌሮች ጋር በፍጹም ሊጣጣም ወይም (compatible) ሊሆን አይችልም፡፡ ከዚህ አንፃር ተሻሽለው የቀረቡ የሃርድዌር አማራጮችን በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ጥቅም ላይ ማዋል እጅግ አስፈላጊ ይሆናል፡፡
በዚህ ዘገባ እንደተገለፀው ረዥም ግዜ በቆዩ የኮምፒውተር ፕሮሰሰሮች የሚገለገሉ ተጠቃሚዎች ከዚህ በኋላ የጎግል ክሮም በሃርድዌራቸው ላይ ድጋፍ እንደማይኖረው የሚያሳይ የማስጠንቀቂያ መልእክት የሚደርሳቸው ሲሆን፤ አዲስ ማዘመኛ ያላቸው እንደ Chrome 89 ያሉ ብሮውዘሮች ደግሞ ቆየት ባሉ ሃርድዌሮች ላይ መጫን እንደማይችሉም ተገልጿል፡፡
ምንጭ፡ Techradar እና tomsguide
ለወጣት ጋዜጠኞች የወጣ የዘገባ ውድድር ዕድል
=======================
ዕድሜያቸው ከ35 ዓመት በታች የሆኑና በዘላቂ ልማት፣ ታዳሽ ኃይል እና የአየር ንብረት ጉዳዮች ላይ ፍላጎት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞችን የሚያሳትፍ ውድድር በጀርመን ልማት ትብብር (GIZ) አማካኝነት ተሰናድቷል፡፡ በውድድሩ የሚመረጡ አምስት ጋዜጠኞች “Decentralized Energy Solutions in Rural Ethiopia” በሚል ርዕስ በሚዘጋጀው በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ ውድድርን እንዲዘግቡ የሚደረግ ሲሆን ውድድሩን አስመልክቶ ምርጥ ዘገባ የሰራ አሸናፊ ጋዜጠኛ ተሸላሚ የሚሆን ይሆናል፡፡ ስለሆነም ተከትለው የተቀመጡትን መስፈርቶች ማሟላት የምትችሉ ሁሉ በውድድሩ መመዝገብ ትችላላችሁ፡፡ ምዝገባው የሚከናወነው ከታች በተቀመጠው የድረ-ገፅ ሊንክ አማካኝነት ሲሆን ምዝገባው ከረቡህ የካቲት 10 (17 February) በፊት የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡
የውድድር መስፈርቶች፡-
• ዕድሜያችሁ ከ35 ዓመት በታች የሆነ
• ከዚህ ቀደም ጋዜጦች ላይ ፅሁፎችን ያወጣችሁ እንዲሁም በፎቶግራፍ፣ ዶክመንተሪ፣ አጫጭር ፊልም፣ ጦማሪነት እና የመሳሰሉት ላይ ልምድ ያላችሁና ለዚህም ማስረጃ ማቅረብ የምትችሉ
• በኃይል፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ወይም ዘላቂ ልማት ላይ ሪፖርቶችን የሰራችሁ
• ጥሩ የአማርኛ እና እንግሊዝኛ ብሎም ሌሎች የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ችሎታ ያላችሁ
• ኢትዮጵያ ውስጥ የምትኖሩ
የመመዝገቢያ ሊንክ፤ https://www.energy-cooperation.et/.../application-form-yj/
የተመረጡ ጋዜጠኞች በአርብ የካቲት 12 (19 February) መልዕክት የሚደርሳቸው ሲሆን የመጀመርያው ቨርቹዋል ወርክሾፕ በየካቲት 16 2013 ዓ.ም ይጀመራል፡፡
ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ይህን የኢሜይል አድራሻ ይጠቀሙ፤energy-cooperatio-et@giz.de