TechIn2
1.22K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
ኢኖቬተሮችን በክህሎት ለመደገፍ የተሰናዳው የቅድመ ኢንኪዩቤሽን ዝግጅት ተጠናቀቀ
======================
የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት የኢኖቬሽን ባህልን ለማሳደግ እና ቀጣይነት ባለው መልኩ ኢኖቬተሮችን ለማፍራት ያግዝ ዘንድ ያሰናዳው የቅድመ-ኢንኪዩቤሽን ፕሮግራም የመጀመሪያ ዙር ስልጠና በትናንትናው ዕለት ፍፃሜውን አድርጓል፡፡ ከረቡህ ጥር 26 አንስቶ ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ዝግጅቱ ከተለያየ ዘርፍ የተውጣጡ 26 ኢኖቬተሮችን ያሳተፈ ነበር፡፡
ዝግጅቱ የተሳታፊዎችን ክህሎት ለማዳበር፣ ዕውቀትን ለመጨመር፣ ትስስር ለመፍጠር እንዲሁም ዕውቅና ለመስጠት ያለመ መሆኑን የተናገሩት የስታርትአፕ እና የኢኖቬሽን ፕሮሞሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በረከት አባይነህ ተሳታፊ ኢኖቬተሮቹ ከጠበቁት በላይ ትልልቅ ሀሳብን ያነገቡ ሆነው እንዳገኟቸውና ከእነርሱም ብዙ መማራቸውን ገልፀዋል፡፡ ለኢኖቬሽን ትልቁ አስፈላጊ ጉዳይ ክህሎት እና ትስስር ነው ያሉት አቶ በረከት ተሳታፊዎች የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች ለመሻገር በይበልጥ ወደ ራሳቸው እንዲመለከቱና ከመደበኛ ትምህርት ባሻገርም በንባብና ሌሎች መንገዶች እራሳቸውን እንዲያበቁ ተናግረዋል፡፡
በትናንቱ መርሃ ግብር ላይ ከኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት የመጡት አቶ በኃይሉ መልከፃዲቅ በአዕምሮ ንብረት እና ተጓዳይ ጉዳዮች ላይ ለተሳታፊ ኢኖቬተሮቹ ስልጠና ሰጥተዋል፡፡ ስልጠናው በምን በምን ጉዳዮች ላይ የአዕምሮ ንብረት ጥበቃ እንደሚደረግ በዝርዝር የተገለፀበት ሲሆን በፓተንት ምዝገባ ረገድም ተሳታፊዎቹ ፈጠራቸውን በፓተንት የማስመዝገባቸው ትልቅ ፋይዳና በምንም መልኩ አስመዝግበው ለፈጠራቸው ጥበቃ ማግኘት እንደሚችሉም የዳሰሰ ነበር፡፡
ያለ አዕምሮ ንብረት ጥበቃ ፈጠራዎች ትልቅ አደጋ ውስጥ እንደሚገቡ አፅዕንዖት የሰጡት አቶ በኃይሉ አስፈላጊውን ነገር ከማሟላትና ፈጠራቸውን ከማስመዝገብ ወደኋላ እንዳይሉ ለፈጠራ ባለሙያዎቹ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡
ዝግጅቱ የተለያዩ ቁም ነገሮችን ማግኘታቸውን የተናገሩት ተሳታፊ ኢኖቬተሮቹ ዝግጅቱ በተለይም በአዕምሮ ንብረት ጥበቃ ረገድ ቀድሞ የነበራቸውን አመለካከት ሙሉ በሙሉ የለወጠና ጉዳዩ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ትምህርት የሰጣቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ለሚዘጋጀውና የሦስት ወራት ቆይታ ለሚኖረው የሙሉ ኢንኪዩቤሽን መርሃ ግብር መሰናዶዎች በመደረግ ላይ መሆናቸውን በመድረኩ ላይ ያስታወቁት አቶ በረከት ይህ ዝግጅትም ለዚህ መንደርደሪያ እንደሚሆን ለተሳታፊዎች የምስክር ወረቀት ሲያበረክቱ ተናግረዋል፡፡
የሐይል መስመሮችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ድሮን ከወደ ዴንማርክ
************************
በደቡባዊ ዴንማርክ በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ በሚገኝ የምርምር ተቋም የሚሰሩ ተመራማሪዎች በሰው ሰራሽ አስተውሎት የታገዘ የከፍተኛ ሐይል ተሸካሚ መስመሮችን ደህንነት የሚቆጣጠር ድሮን መስራታቸው ተነገረ፡፡ ድሮኑ የሐይል ማስተላለፊያውን ሽቦ ከዝገትና ከሀይል ማቆራረጥ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፈተሸ የሚያግዝ ነው፡፡ በዴንማርክ ከ7000 ኪሎሜትሮች በላይ የሚሆን ርዝመት ያለው የከፍተኛ ሐይል ማስተላለፊያ መስመር አለ፡፡
እስካሁን ባለው ሁኔታ የመስመር ቁጥጥሩ ስራ ሄሊኮፍተር እና መኪኖችን በመጠቀም በሰው ሀይል የሚሰራ ሲሆን መስመሩ ከመሬት ከፍ ያለ በመሆኑ ለአደጋ የሚያጋልጥና ከዋጋም አንጻር አዋጭ አይደለም፡፡ ለዚህ አላማ የተሰሩት ድሮኖች በመስመሮቹ ዙሪያ በተከታታይ ያለማቋረጥ እየበረሩ ሊኖር የሚችልን ችግር ይከታተላሉ፡፡ በክትትሉ ወቅት ድሮኑ ችግር ካገኘ ሐይል ማስተላለፊያውን ለሚያስተዳድረው አካል መልዕክት ይልካል፡፡
የዚህ ድሮን ሌላው አስገራሚው ነገር ለመብረር የሚያስፈልገውን የባትሪ ጉልበት በሐይል ማስተላለፊያ መስመሩ ተጠግቶ ሲበር በሚያገኘው ወይም ከሀይል አስተላላፊ መስመሩ መግነጢሳዊ ክልል በሚያገኘው ሀይል ይሞላል፡፡ ስለዚህ ክትትሉን ያለማቋረጥ ማድረግ ይችላል፡፡ በዚህ መንገድ ድሮኑ የተበላሸን መስመር ለመፈለግ የሚጠፋውን ጊዜና ጉልበት በመቀነስ ትክክለኛው ችግር የተከሰተበትን ቦታ በማመልከት የጥገና ቡድን ለመላክ ያስችላል፡፡
አዲሱ ድሮን ረጃጅም መስመሮችን ብዙ ሆነው የሚከታተሉ ሲሆን በአስቸጋሪ አከባቢ ውስጥ ይሰራሉ ፡፡ በቤታችን ውስጥ ባሉ ሶኬቶች ውስጥ 230 ቮልት አለ ፣ ግን በላይኛው መስመር ላይ ያለው ቮልቴጅ 400,000 ቮልት ነው፡፡ ይህ በመብረቅ የመመታት እድሉን ከፍ ያደርገዋል፤ እናም ድሮኖቹ በከፍተኛው ሀይል ምክንያት ችግሮች ሊያጋጥሟቸው እንደሚችል ተገምቷል፡፡ ስለሆነም የሳይንስ ሊቃውንት ወደ ኬብሎች በጣም በሚጠጉበት ጊዜ ድሮኑን የሚከላከል ልዩ ስርዓት አዘጋጅተዋል፡፡
ምንጭ Technology.org
ደቡብ አፍሪካ የአስትራ ዜኒካ ክትባቶች ለህዝቧ እንዳይሰጡ አገደች
========================
ደቡብ አፍሪካ ለኮቪድ-19 ተብለው ከተሰሩ ክትባቶች ከቀዳሚዎቹ አንዱ የሆነውን የኦክስፎርድ-አስትራ ዜኒካ ክትባቶችን ሀገሪቱ ላይ ባለው አዲስ የኮሮና ቫይረስ ዓይነት (ቢ.1.351) ላይ ከዓለም አቀፉ የክትባት ደረጃ የወረደ የ25 በመቶ ብቻ ውጤታማነት ማሳየታቸውን ተከትሎ ዜጎቿን ክትባቶቹ መከተቡን እንዳገደች ትናንት አስታወቀች፡፡ ደቡብ አፍሪካ ውሳኔውን ያስተላለፈችው ክትባቶቹ 2ሺህ ያህል ተሳታፊዎችን ባካተተ ጥናት ላይ ቀላል እና መካከለኛ ደረጃ ላላቸው የኮቪድ-19 ህመሞች አነስተኛ ጥበቃን ማሳየታቸውን ተከትሎ ነው፤ ምንም እንኳን ጥናቱ በምሁራን ግምገማ ባይደረግበትም፡፡ ተመራማሪዎች የአስትራ ዜኒካ ክትባቶች በኮቪድ-19 የተነሳ የሚመጡ ከፍተኛ ህመሞችን እና ሞትን ያስቀራሉ አያስቀሩም የሚለው ላይም ጥናት የሚያደርጉ ይሆናል፡፡
መነሻውን ከደቡብ አፍሪካ ያደረገው ኮሮና ቫይረስ አይነት ከቀድሞውም በላቀ ተላላፊና አሁን በሀገሪቱ ካሉ የኮቪድ-19 ተጠቂዎች መካከልም የ90 በመቶውን ድርሻ የወሰደ ነው፡፡ ታድያ እስካሁን 1.5 ሚሊዮን ነዋሪዎቿ በኮቪድ-19 ተጠቅተውባት 46,000 የሚሆኑትን በሞት ያጣችው ደቡብ አፍሪካ አንድ ሚሊዮን የኦክስፎርድ አስትራ ዜኒካ ክትባት ፍሬዎችን ተረክባ ነበር፡፡ በያዝነው የፈረንጆች ዓመት ማለቂያ ላይም 67 በመቶ ወይም 40 ሚሊዮን ያህል ህዝቧን ለመከተብ ዕቅድ ያላት ሲሆን በግዳጅ ላይ ያሉ የጤና ባለሙያዎቿንም ከያዝነው ወር ጀምሮ ለመከተብ አቅዳ ስትንቀሳቀስ ቆይታለች፡፡
ቢ.1.351 ያሳየውን ተቋቋሚነት ተከትሎ የኦክስፎርድ-አስትራ ዜኒካ ክትባት አበልፃጊዎች እስከ ፈረንጆቹ የበጋ ወራት መባቻ ድረስ ማስተካከያ የተደረገባቸው የክትባት ፍሬዎችን እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል፡፡ ጉዳዩን አስመልክቶ ለቢቢሲ ቃለ መጠይቅ የሰጡት በኦክስፎርድ ቡድን ውስጥ መሪ አጥኚ የሆኑት ሳራህ ጊልበርትም ለደቡብ አፍሪካው የኮሮና ቫይረስ ዓይነት የሚሆን ክትባትን እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
አሁን ላይ የሀገሪቱ መንግስት ትኩረቱን በጆንሰንና ጆንስን እንዲሁም ፋይዘር አማካኝነት በሚመረቱት የኮቪድ-19 ክትባቶች ላይ የሚያደርግ ሆናል፡፡ ሆኖም እነዚህ ክትባቶችም ቢሆን በአዲሱ የደቡብ አፍሪካ ኮሮና ቫይረስ ዓይነት ላይ ያሳዩት ውጤታማነት ብዙም አበረታች አይደለም፡፡ በጆንሰንና ጆንሰን የተሰራው ክትባት በዚህኛው የቫይረሱ ዓይነት ላይ ውጤታማ መሆን የቻለው በ57 በመቶ ሲሆን ሌላኛው የኮቪድ-19 ከትባት ኖቫቫክስም ውጤታማነቱ 49 በመቶ ሆኗል፡፡
የአስትራ ዜኒካ ክትባቶች በደቡብ አፍሪካው የኮሮና ቫይረስ ዓይነት ላይ ያሳዩት ውጤት ከደቡብ አፍሪካም የተሻገረ ተፅዕንዖ ሊኖረው ይችላል፡፡ ባለው ረከስ ያለ ዋጋ እና በማንኛውም አይነት ማቀዝቀዣ ውስጥ ለማቆየት የሚቻል በመሆኑ ሳብያ ብዙ አፍሪካውያን ሀገራት የአስትራ ዜኒካ ክትባትን ለመጠቀም ሲያቅዱ ቆይተዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደሃ ሀገራትን የኮቪድ-189 ክትባቶች ተጠቃሚ ያደርግ ዘንድ የተወጠነው የኮቫክስ ጥምረትም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የአስትራ ዜኒካ ክትባቶችን ከህንዱ ሴረም ኢንስቲትዩት ገዝቷል፡፡
ምንጭ፡ DW እና science መፅሔት (ድረ-ገፅ)
ምናባዊ እውነታ (VR) የአዕምሮ እድገትን ለመለካት
*****************************
ተመራማሪዎች የሰዎችን የአዕምሮ እድገት ወይም ብቃት ለመለካት የሚያስችል ምናባዊ እውነታ ወይም ቨርቹዋል ሪያሊቲ መስራታቸው ተነገረ፡፡ ለወትሮው ይህ ቴክኖሎጂ የተለያዩ በኮምፒውተር የታገዙ ጨዋታዎችን ለመጫዎት የሚያስችል ሲሆን አሁን ላይ ተመራማሪዎች ሰዎች በገሃዱ አለም ውስጥ ያለውን መደበኛ እንቅስቃሴ እንዴት እንደሚከውኑ ማየት የሚያስችላቸው ቴክኖሎጂን አክለውበት የሰዎችን የአዕምሮ እድገት ለመለካት በሚያስችል መልኩ እንደሰሩት ተሰምቷል፡፡ ይህም የዕለት ከዕለት ተግባራቸውን ለመከወን የሚቸገሩ ሰዎችን በእጅጉ እንደሚያግዛቸው ታምኖበታል፡፡
ሂዩማን ቢሄቪዮር ሪፖርትሰ በተባለ ህትመት የወጣው መረጃ እንዳመለከተው ተመራማሪዎች ቨርቹዋል ሪያሊቲን ሰዎች ተግባራትን ለመከወን የሚጠቀሙትን የመረጃ ብዛትና የመፈጸም አቅማቸውን ለመለካት እንደሚያስችል መናገራቸውን አስነብቧል፡፡
42 ጤናማ የኮሌጅ ተማሪዎች በተሳተፉበት የሙከራ ወቅት ተሳታፊዎች ለቤት ውስጥ አገልግሎት የሚያስፈልጉ የምግብ ግብዕት ዝርዝሮችን አንብበው ገበያ ሄደው እንዲገዙ ከተደረገ በኋላ የማስታወስና የመርሳት መጠኑን ለመለካት ተችሏል፡፡ የዝርዝሩ መጠን እየጨመረ በሔደ ቁጥር የመዘንጋት ሁኔታውም እንደጨመረ ተነግሯል፡፡ ይህም የስራ መጠን በጨመረ ቁጥር የአዕምሮ የመፈጸም ብቃት እየቀነሰ እንደሚሔድ ማሳያ መሆኑን ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
ጥናቱ በአጠቃላይ ነገሮችን በአግባቡ ወይም ባሰቡት ልክ የመፈጸም ችግር ያለባቸውን ሰዎች ለማገዝ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ተመራማሪዎቹ አሳውቀዋል፡፡
ምንጭ Tech Xplore
This media is not supported in your browser
VIEW IN TELEGRAM
ማርስ 20 የሚደርሱ የበረዶ ዘመን ነበሯት
--------------------------------
በማያቋርጥ የአቧራ ማዕበል የተሸፈነችው ቀይዋ ፕላኔት ማርስ ወደኋላ በነበረው ዘመኗ ከስድስት እስከ ሃያ የሚደርሱ የተለያየ የበረዶ ጊዜያትን ወይም ዘመናትን ማሳለፏን የኮስሞሎጂ ባለሙያዎች እና የስነ ምድር አጥኚዎች ይናገራሉ፡፡ የማርስ በበረዶ መሸፈን ኦብሊኪዊቲ (obliquity) ተብሎ በሚጠራው ፕላኔቷ በምትሽከረከርበት ዛቢያ ዙሪያ ያዘመመችበት ዲግሪ ቋሚ ከመሆን ይልቅ የመለዋወጥ በህሪ ሲያሳይ የሚኖር ክስትት ሲሆን ተመራማሪዎችም የፕላኔቷን በበረዶ ግግር የመሸፈን ጊዜያት ወጥ እና ተከፋፍለው በነበሩ ረዥም የበረዶ ዘመናት (Ice Ages) ውስጥ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡
ናሳን ጨምሮ ከአሪዞና፣ ፊችበርግ እና ቴክሳስ-አዉስቲን ዩኒቨርስቲ የተወጣጡ ተመራማሪዎች የተሳተፉበት ይህ ምርምር በኮልጌት ዩኒቨርስቲ በሚገኙት የስነ ምድር ተመራማሪ ፕሮፌሰር ጆይ ሌቪ መሪነት የተከናወነ ነው፡፡ ተመራመሪዎች እንደሚሉት ፕላኔቷ አሁን የተሸፈነችበት በረዥም የጊዜ ሂደት የሚፈጠረውና በገፅዋ ላይ በዝግታ የሚንቀሳቀው ብዛት ያለው የበረዶ ግግር ወይም (glaciers) ከብዙ ሚሊዮን አመታት በፊት በፕላኔቷ ላይ የተለያዩ የበረዶ ዘመናት አንደነበሩ የሚያመለክት ነው ይላሉ፡፡
ፕሮፌሰር ሌቪና የምርምር ቡድናቸው በፕላኔቷ ምህዋር ላይ መቀመጫውን አድርጎ ለተለያዩ ምርምሮች የሚረዱ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ምስሎችን በሚያነሳው Mars Reconnaissance Orbiter ሳተላይት አማካኝነት የገኟቸው 45 የሚጠጉ የበረዶ ግግር ምስሎች ለጥናታቸው እንደግብዓት የተጠቀሙ ሲሆን፤ ከዚያ በተጨማሪም 60 ሺ የሚደርሱ የፕላኔቷን የድንጋይ ዐለቶች በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ አማካኝነት ትንተና እንዲደረግባቸው አድረገዋል፡፡
ተመራማሪዎች በእነዚህ መረጃዎች ላይ ባደረጉት ትንተና ቀይዋ ፕላኔት ማርስ ወደኋላ በነበረው ዘመኗ ከስድስት እስከ ሃያ የሚደርሱ የተለያየ የበረዶ ጊዜያትን ወይም ዘመናትን ማሳለፏን ያረጋገጡ ሲሆን ቢያንስ ከ300 እስከ 800 ሚሊዮን አመታት ውስጥ ይህ የበረዶ ዘመን ተከስቶ እንደነበርም ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ ፕሮፌሰር ሌቪ ይህ የምርምር ውጤት የፕላኔቷን የረዥም አመታት ታሪክ በሚገባ ለመረዳት እና ለሌሎች ተያያዥ ጥናቶች ጠቃሚ ግብዓት ለመስጠት እንደሚረዳም ተናግረዋል፡፡
ምንጭ፡ Big Think
የተሳትፎ ጥሪ፤ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሲምፖዚየም
===================
የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሲምፖዚየም ለማዘጋጀት ይፈልጋል። ስለሆነም በግብርና ዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ በፋይናንስ ዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ በጤና ዲጂታል ቴክኖሎጂ እንዲሁም የቢሮዎችን አሰራር ስርዓት የሚያዘምኑ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ውጤቶች ያላችሁ እና በዚሁ መስክ ላይ የተሰማራችሁ የግል፣ የመንግስት፣ የትምህርትና የምርምር ተቋማት ወይንም ግለሰቦች በዚህ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሲምፖዚየም እንዲካፈሉ ተጋብዘዋል።
ለምዝገባው የሚያስፈልጉ ነገሮች፡-
• ከ500 ቃላት ያልበለጠ ማብራርያ
• ከ150 ቃላት ያልበለጠ ስለ እርስዎ እና የፈጠራ ክንውንዎ የሚገልፅ ማብራርያ
• ከ1-3 የሚሆኑ ስለስራዎ የሚገልፁ ምስሎች (ከ1 ሜ.ባ ያልበለጠ) እና የቪዲዮ ሊንክ (ከተቻለ)
• የግንኙነት አድራሻ (ስም፣ የኢሜይል አድራሻ፣ ስልክ ቁጥር)፣ ሲቪ እንዲሁም የድረ-ገፅ፣ ትዊተር እና ኢንስታግራም አድራሻ
ስለሆነም ከዚህ በታች ባለው ማስፈንጠሪያ በመጠቀም መመዝገብ የምትችሉ መሆኑን እናሳውቃለን።
የመመዝገቢያ ገፅ፤ https://forms.gle/uLXgtzHVHZ79yabb8
የመመዝገቢያ ጊዜ፤ ከየካቲት 3 እስከ የካቲት 8 2013 ብቻ የሚቆይ ይሆናል።
ለተጨማሪ መረጃ 4 ኪሎ ከፓርላማ የትራፊክ መብራት ወደ ፒያሳ/ቸርችል ጎዳና በሚወስደው መንገድ 150 ሜትር ተጉዘው በሚያገኙት ዋና ቢሮዋችን ወይንም በኢ-ሜይል አድራሻ smd-team@techin.gov.et መጠቀም ይችላሉ
ሳይንቲስቶች ከዚህ በፊት አይተን የማናውቀውን የሂሳብ ትምህርት የሚያመነጭ ማሽን አግኝተዋል
*************************
ስሙ ስሪኒቫሳ ራማኑጃን ነበር ፣ እናም ሌሎች ሰዎች በጭራሽ የማያሰሏቸውን ጥቂት ሂሳቦችን ለማለም ልዩ ስጦታ ነበረው። ይህን ልዩ ችሎታውን ከፈጣሪ ስጦታ ጋር የሚያገናኙት ህንዶች ለዓለማችን በሺዎች የሚቆጠሩ የሒሳብ ስሌቶችንና ቀመሮችን አበርክተዋል፡፡ እንዲሁም ደግሞ እስካሁን ድረስ እውነትነቱ ያልተረጋገጠውና በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ያለው devising conjectures ሀሳብ አመንጪ በመሆን ይታወቃል፡፡
ይህ የተረጋገጡና ያልተረጋገጡ ሒሳባዊ እሳቤዎችን የመንደፍ ችሎታ በጣም በጥቂት ሰዎች የተለመደ ነው፡፡ የዚህን ልጅ ልዩ የሚያደረገው በዘርፉ በቂ የሚባል ስልጠና ያልወሰደ መሆኑ ነው፡፡ አሁን ላይ በእስራኤል ተመራማሪዎች የተሰራው ስልተ ቀመር ፈጠራ እንደ ራማኑጃን ያሉ የሂሳብ ግምቶች ግኝት በራስ-ሰር ሊረዳን ይችላል ፡፡
በ 32 ዓመቱ ህንድ ውስጥ በሞተው በራማውጃን ስም የተሰየመ - ‹የራማኑጃን ማሽን› እንደ π እና e ያሉ የሂሳብ ቋሚዎችን የሚያካትቱ እሳቤዎችን በራሱ የማመንጨት ችሎታ ያለው የኮምፒዩተር ስርዓት ነው ፡፡ በአሁኑ ሰዓት አዳዲስ የሚባሉ ሒሳባዊ ቀመሮች መገኘታቸውን መስማት የተለመደ አይደለም፡፡
አዲሱ ማሽን ከሒሳባዊ ፈጠራ ጋር የተያያዙ መዘግየቶችን ሊያፋጥን ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸው ተመራማሪዎቹ አሳውቀዋል፡፡ እስካሁን ድረስ አልጎሪዝም ማሽኑ በቀላሉ የሚናገሩ ግምቶችን የሰራ ሲሆን፣ እንደ π ያሉ ቋሚዎችን ለማስላት አዳዲስ ክፍልፋይ መንገዶችን በማፈላለግ እና ገና ያልተረጋገጡ ግምቶችን ይዞ መጥቷል፡፡
ከፍተኛ ደራሲና የፊዚክስ ሊቅ የሆኑት አይዶ ካሚር “ኮምፒዩተሩ ቀመሩን ቀላል ወይም ከባድ መሆኑን የሚያረጋግጥ ስለሆነ አዲሱ ውጤት በየትኛውም የሂሳብ ዕውቀት ላይ የተመሠረተ ሳይሆን በሂሳብ ቋሚዎች ውስጥ ባሉ ቁጥሮች ላይ ብቻ የተመሠረተ ነው” ብለዋል፡፡
ስልተ ቀመሩም ራሱ ያገኘውን ግምቶች ማረጋገጥ የማይችል መሆኑን መጠቆም አስፈላጊ ነው በዚህ ጊዜ ተግባሩ በሰው ሂሳብ ባለሙያዎች እንዲፈታ ተትቷል ሲሉ አክለዋል፡፡
ምንጭ Science Alert
ቮዳፎን እና ኦሬንጅ በኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎት ለመስጠት እንደሚወዳደሩ ተናገሩ
===================
ግዙፎቹ የፈረንሳይ እና እንግሊዝ የቴሌኮም ተቋማት ኦሬንጅ እና ቮዳፎን በኢትዮጵያ ለመስራት የሚያስችላቸውን የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድ ለማግኘት የመወዳደር እቅድ እንዳላቸው አስታወቁ፡፡ ኩባንያዎቹ በቅርቡ የኢትዮጵያ ኮምዩኒኬሽን ባለስልጣን የቴሌኮም ፈቃድ የማግኛ ጥያቄ ማቅረቢያ ቀኑን እስከ መጋቢት 27 ድረስ ማራዘሙን ተከትሎ ነው ከካፓሲቲ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ለመወዳደር ማቀዳቸውን የተናገሩት፡፡
የኦሬንጅ ቃል አቀባይ ኢትዮጵያ የቴሌኮም ገበያዋን ለመክፈት በምታደርገው ሂደት ውስጥ ተሳታፊ እንሆናለን ብለው ተናግረዋል፡፡ ባሳለፍነው ሰኔም ኦሬንጅ በገበያው ላይ ያለውን ፍላጎት ለኢትዮጵያ ኮምዩኒኬሽን ባለስልጣን በይፋ አሳውቆ ነበር፡፡ በተመሳሳይ ወቅት ቮዳፎንም እንዲሁ ያለውን ፍላጎት ለመንግስት አካላት አስታውቆ ነበር፡፡
እንደ ቮዳፎን ኃላፊ ከሆነ ፍቃድ በማግኘቱ እንቅስቃሴ ውስጥ በቮዳፎን ባለቤትነት የሚንቀሳቀሰው የኬኒያው ሳፋሪኮም ከፊት ተሰልፎ ሂደቱን የሚመራለት ሲሆን ቮዳፎን ቀዳሚ የአክሲዮን ባለቤት ከሆነበት የደቡብ አፍሪካው ቮዳኮም ጋራም ተቀራርቦ የሚሰራ ይሆናል፡፡ ቮዳፎን በስራው ላይ ከጃፓኑ ሱሚቶሞ የቴኖሎጂ ድጋፍን እንደሚያገኝ ይጠበቃል፡፡
የቴሌኮም ኩባንያው በኢትዮጵያ የመንቀሳቀስ ፈቃድ ለማግኘት ፍላጎት ያለው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ እያንዳንዱን የኢንቨስትመንት እድል በጥንቃቄ እንደሚመለከተውና አዋጭ ሆኖ ባላገኘው ስራ ላይ መዋለ ነዋዩን እንደማያፈስ ተናግሯል፡፡
በሌላ በኩል አንድ የኦሬንጅ ኃላፊ እንደተናገሩት እንደ ድርጅት በጉዳዩ ላይ የሚኖረውን ዝርዝር የቁጥጥር ደንብ እየጠበቁ ሰሆን ወደ ገበያው ለመግባት አመቺና በቂ ምጣኔ-ሐብታዊ ስፍራ ስለመኖሩም ክትትል እያደረጉ ነው፡፡ ሆኖም ተገኙ የተባሉ ይፋዊ ያልሆኑ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ኦሬንጅ በኢትዮ-ቴሌኮም ድርሻን ለመግዛት በሚደረገው ውድድር ላይም ተሳታፊ ለመሆን ማቀዱን ነው፡፡ ኩባንያው ከዚህ ቀደም ለሁለት ዓመታት የአስተዳደር ስራን ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋራ ሲሰራ መቆየቱም ይታወሳል፡፡
ባለፈው ሳምንት በአፍሪካ ብቻ 110 ሚሊዮን ደንበኞች ያሉት ግዙፉ የህንድ የቴሌኮም ኩባንያ ኤርቴል በውድድሩ ተሳታፊ እንደማይሆን በአፍሪካ ሰራ አስፈፃሚው ራጉናት ማንዳቫ አማካኝነት አስታውቆ ነበር፡፡ በአንፃሩ ከሀገሩ ውጪ በአፍሪካ ብዙም ታዋቂነት የሌለው ሼሪንግ ሞባይል የተሰኘው የቻይና ኩባንያ በውድድሩ እንደሚሳተፍ ተናግሯል፡፡ የኢትዮጵያ ኮምዩኒኬሽን ባለስልጣን የቴሌኮም ፈቃድ የማግኛ ጥያቄ ማቅረቢያ ሲያራዝም ዝርዝር የጥያቄ ማቅረቢያ ጊዜ እንዲሁም የፋይናንስ እና ቴክኒካል ደንቦችን አላስቀመጠም፡፡
እስካሁን ድረስ የኢትዮጵያን የቴሌኮም ገበያ ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥሮ የቆየው በመንግስት የልማት ድርጅት የሚተዳደረው ኢትዮ-ቴሌኮም ነው፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መንግስት የኩባንያውን 45 በመቶ ድርሻ ለመሸጥ ማቀዱን ይፋ አድርጎ የነበረ ሲሆን ለዚህ ይረዳ ዘንድም ኢትዮ-ቴሌኮም ኬፒኤምጂ የተባለውን ድርጅት ቀጥሮ ነበር፡፡
ምንጭ፡ Capacity Media
የተሳትፎ ጥሪ፤ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሲምፖዚየም
===================
የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሲምፖዚየም ለማዘጋጀት ይፈልጋል። ስለሆነም በግብርና ዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ በፋይናንስ ዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ በጤና ዲጂታል ቴክኖሎጂ እንዲሁም የቢሮዎችን አሰራር ስርዓት የሚያዘምኑ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ውጤቶች ያላችሁ እና በዚሁ መስክ ላይ የተሰማራችሁ የግል፣ የመንግስት፣ የትምህርትና የምርምር ተቋማት ወይንም ግለሰቦች በዚህ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሲምፖዚየም እንዲካፈሉ ተጋብዘዋል።
ለምዝገባው የሚያስፈልጉ ነገሮች፡-
• ከ500 ቃላት ያልበለጠ ማብራርያ
• ከ150 ቃላት ያልበለጠ ስለ እርስዎ እና የፈጠራ ክንውንዎ የሚገልፅ ማብራርያ
• ከ1-3 የሚሆኑ ስለስራዎ የሚገልፁ ምስሎች (ከ1 ሜ.ባ ያልበለጠ) እና የቪዲዮ ሊንክ (ከተቻለ)
• የግንኙነት አድራሻ (ስም፣ የኢሜይል አድራሻ፣ ስልክ ቁጥር)፣ ሲቪ እንዲሁም የድረ-ገፅ፣ ትዊተር እና ኢንስታግራም አድራሻ
ስለሆነም ከዚህ በታች ባለው ማስፈንጠሪያ በመጠቀም መመዝገብ የምትችሉ መሆኑን እናሳውቃለን።
የመመዝገቢያ ገፅ፤ https://forms.gle/uLXgtzHVHZ79yabb8
የመመዝገቢያ ጊዜ፤ ከየካቲት 3 እስከ የካቲት 8 2013 ብቻ የሚቆይ ይሆናል።
ለተጨማሪ መረጃ 4 ኪሎ ከፓርላማ የትራፊክ መብራት ወደ ፒያሳ/ቸርችል ጎዳና በሚወስደው መንገድ 150 ሜትር ተጉዘው በሚያገኙት ዋና ቢሮዋችን ወይንም በኢ-ሜይል አድራሻ smd-team@techin.gov.et መጠቀም ይችላሉ