TechIn2
1.22K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
የኢላማ ለውጥ ያደረጉት ሀከሮች
==============
ባሳለፍነው የፈረንጆች ዓመት 2020 ሀከሮችና የሳይበር ላይ ቀበኞች የግለሰቦችን መረጃ ከመስረቅ ይልቅ ትኩረታቸውን ከፍ ያለ ትርፍ በሚያስገኙ ተቋማት ላይ ማድረጋቸውን ከአይደንቲቲ ተፍት ሪሶርስ ሴንተር (ITRC) የወጣ ሪፖርት አመላከተ፡፡ የሳይበር ጥቃት የደረሰባቸው ግለሰቦች ላይ ትኩረቱን አድርጎ ሚንቀሳቀሰው ድርጅቱ እንዳስታወቀው በአሜሪካን የመረጃ ስርቆት በ13 በመቶ ሲቀንስ በግለሰብ ደረጃ የሚደርሰው የሳይበር ጥቃት ግን ከቀደመው ዓመት አንፃር በ66 በመቶ ወርዷል፡፡
በኮምፒውተር ስርዓቶች ላይ ጥቃት ሰንዝሮ በማበላሸትና ወደነበረበት ለመመለስ ክፍያ መጠየቅ ከፍ ያለ ትርፍን በማስገኘታቸው ተመራጭ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ ድርጅቱ እንዳስታወቀው እነዚህ ጥቃቶች በደቂቃዎች ውስጥ ብቻ የሚያስገኙት ገቢ ለወራት ያህል በመቶዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦችን በማጥቃት ከሚገኘው ጋር ተነፃፃሪ ነው፡፡ የሳይበር ደህንነት ተቋም እንደሆነው ኮቭዌር መረጃ ከሆነ በ2020 ከነዚህ ጥቃቶች የሚገኘው ገንዘብ በ2018 ከነበረበት 10 ሺህ ዶላር በሁለት ዓመት ውስጥ ብቻ ከ20 እጥፍ በላይ አድጎ 233 ሺህ ዶላር ደርሷል፡፡ ይህ ግን ግለሰቦች የሳይበር ጥቃትን ችላ ማለት አለባቸው ማለት እንዳልሆነ ባለሙያዎች ያሳስባሉ፤ አሁንም በብዙ መቶ ሚሊዮንች የሚቆጠሩ ግለሰቦች የጥቃት ሰለባ እየሆኑ ነውና፡፡
አሁን ላይ እየተስተዋለ ያለው የጥቃት ስልት በሦስተኛ አካል በኩል የሚከናወነው ነው፡፡ ለምሳሌ አነስተኛ ተቋማት ለራሳቸው የዘረጉት የሳይበር ደህንነት ቁጥጥር የላላ ቢሆንም አብረውት ከሚሰሩትና ዋናው የጥቃት ዕቅድ ከሆነው ተቋም ጋራ ትስስር ያላቸው በመሆኑ የሳይበር ቀበኞቹ በእነርሱ በኩል ትልቁን አሣ ማጥመድ ይችላሉ፡፡ በተጨማሪም የኮቪድ-19 ወረርሺኝን ተከትሎ ብዙ ሰዎች ከቤት ሆነው ስራ መስራታቸው ተቋማቸው ለእነዚህ ወንጀለኞች ተጋላጭ እንዲሆን እስችሎታል፡፡
ምንጭ፡ Tech Xplore
ስልጠና፣ ምርምርና ቢዝነስ የሃገራችንንና የህዝቦቿን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል
***********************
የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት በአምስቱ ሴንተሮች የሚገኙ ተመራማሪዎችንና ፈጻሚዎችን የሚያስተዋውቅና በ2012ዓ.ም ተቋሙ ሲያከናውናቸው በነበሩ ተግባራት ለመጣው ውጤት የተሻለ አፈጻጸም ለነበራቸው የተቋሙ ሰራተኞችና ፈጻሚዎች በትላንትናው ዕለት የእውቅና አሰጣጥ መርሃ ግብር አከናውኗል፡፡ በእንጦጦ ፓርክ በተዘጋጀው በዚህ መርሃ ግብር የተቋሙ ቤተሰቦች የተሳተፉበት የጠዋትና የከሰዓት ዝግጅቶች ተካሂደዋል፡፡ የጥዋቱ መርሃ ግብር አራት ኪሎ ከሚገኘው የተቋሙ ዋና መስሪያ ቤት ወደ አዲሱ የእንጦጦ ፓርክ በተደረገ ጉዞ ተጀምሯል፡፡ በፓርኩ ውስጥ እሴት በተጨመረበትና በተፈጥሮ በተዋበው ጫካ ውስጥ የእግር ጉዞ የተካሄደ ሲሆን የጥዋቱ መርሃ ግብርም አዝናኝ በነበረው የፈረስ ግልቢያ ውድድር ተጠናቋል፡፡
የከሰዓት በኋላው ዝግጅት ከምሳ ግብዣ በኋላ የቀጠለ ሲሆን የዚህን ዝግጅት መክፈቻ የቷቋሙ ዋና ዳሬክተር አቶ ሙሉቀን ቀሬ በንግግር አቅርበዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ ንግግራቸውን ላለፉት ጊዜያት እንደ አለም እና እንደ ሀገር በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ማለፋችንን አስታውሰው የጀመሩ ሲሆን በተደራረበ ችግር ውስጥም ቢሆን የቴክኢን ቤተሰቦች ችግር ፈቺ የሆኑ የተለያዩ ስራዎች መስራታቸውን አስገንዝበዋል፡፡ አቶ ሙሉቀን አክለውም ‹‹ቴክኢን ሰው ነው፤ ሰው ያስባል፣ ያቅዳል እንዲሁም ይፈጽማል፡፡ ስለዚህ በተቋሙ ውስጥ ያሉ ተመራማሪዎችና ሁሉም ሰራተኞች ያላቸውን የማሰብ፣ የመፍጠርና የመፈጸም አቅም በብቃት መጠቀም አስፈላጊ ነው›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ ያለባትን የፈጠራ፣ የጥናትና ምርምር እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግር ክፍተት ለመሙላት ታስቦ በተደራጀ ተቋም ውስጥ የምንሰራ ሙያተኞች የሀገራችንንና የህዝቦቿን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት ችግር ፈቺ ስልጠና፣ ምርምርና ቢዝነስ ተኮር ተግባራትን በመስራት የበኩላችንን ሀላፊነት ልንወጣ ይገባል ሲሉ አቶ ሙሉቀን ተናግረዋል፡፡
በንግግራቸው ማብቂያ ላይም አቶ ሙሉቀን ፕሮግራሙ የተዘጋጀው አምስቱን የተቋሙን ሴንተሮች ማቀላቀል፣ ባለፉት ጊዜያት የተሰሩ ስራዎች በተቋሙ ሰራተኞች የተከናወኑ በመሆናቸው ለስኬቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላላቸው ተመራማሪዎችና ፈጻሚዎችን ለማበረታታትና በስድስት ወር ውስጥ በአስደናቂ ጥራትና ፍጥነት ከተሰራው ፓርክ ልምድ መውሰድ የሚሉ ሶስት አላማዎችን ያነገበ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በመቀጠልም የተቋሙ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ተሾመ ከጥቂት ዓመታት በፊት ተቋሙ በሰው ሃይልና በመፈጸም አቅም የነበረበትን ሁኔታ አስታውሰው ዛሬ ላይ ከ340 በላይ ሰራተኞችን ሲይዝና በአምስት ሴንተሮች ሲደራጅ ተጨማሪ ሀላፊነቶችንም በመጨመር ነው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ተቋማችን የተለያዩ ኢንዱስትሪዎችና ተቋማት የተሸለ የአሰራር ስርዓት እንዲኖራቸው የሚጠበቅብንን ሀላፊነት መወጣት አለብን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ከተቋሙ ሃላፊዎች በተጨማሪም ተጋባዥ እንግዳ የነበረው አዲስ ቡርሃን (ሙሃመድ አሊ ቡርሃን) ለተቋሙ ሰራተኞች በጣም ጠቃሚ የሆነ በማሰብና በአእምሮ ብቃት ላይ ያተኮረ ንግግርን አቅርቧል፡፡ ከቀረበው ንግግርም በመነሳት ታዳሚዎች የተለያዩ ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲሆን አዲስም ምላሾችን ሰጥቷል፡፡
በመጨረሻም በ2012 በተቋሙ ውስጥ የተሻለ አፈጻጸም የነበራቸው ተመራማሪዎችና ሌሎች ፈጻሚዎች የተዘጋጀላቸውን የምስክር ወረቀት እና የማበረታቻ ሽልማት ከተቋሙ ዋና ዳይሬክተር እጅ ተቀብለዋል፡፡ ዝግጅቱም አቶ ሙሉቀን ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር ተጠናቋል፡፡
በነገው የቴክ-ሳይንስ መሰናዶዋችን
================
በአብይ ፕሮግራም፤ ወደ ደሴ አቅንተን ስመ ጥሩን ወ/ሮ ስህን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ
በተመራማሪዎች ታሪክ፤ ዶ/ር ተስፋዬ ሽምብር
በብላቴናት፤ የህክምና ቁሳቁሶችን ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ የሚረዳ ሮቦት የሰራው ታዳጊ
በተቋማት፤ የጎግል ዳታ ሴንተር የደንበኞቹን መረጃ እንዴት እንደሚጠብቅ
በቴክኖሎጂ ታሪክ፤ የልብስ ስፌት ማሽን
ከነዚህ አባይት ዝግጅቶቻችን ባሻገር የስኮላርሺፕ መረጃንም ጨምረን ነገ በ10 ሰዓት እና ዕለተ ማክሰኞ በተመሳሳይ ሰዓት በMOE TV እንጠብቃችኋለን፡፡
የዩትዩብ ቻናላችንንም (https://www.youtube.com/channel/UC6jvUOLRSkVEQtc5Annfwvg) ሰብስክራይብ ማድረጉን እንዳይረሱ፤ ከዓመታት በፊት ከተላለፈው የመጀመሪየው ክፍል አንስቶ ያሉትን ሁሉንም የቴክ-ሳይንስ ፕሮግራሞች አንድ በአንድ መመልከትና ለእርስዎም ሆነ ቤተሰብዎ ዕውቀትን መገብየት ይችሉበታልና፡፡
ፌስቡክ የፖለቲካ ነክ ፖስቶችን ተደራሽነት ሊቀንስ ነው
=================
ከፖለቲካ ጋራ የተገናኙ ግሩፕ ወይም ቡድኖችን ለተጠቃሚዎቹ ሪኮመንድ ማድረግ እንደሚያቆም ፌስቡክ ይፋ አድርጓል፡፡ ከፖለቲካዊ ውዝግቦች ጋራ ተያይዞ የጠለሸው ስሙን ለማደስ የተነሳው ግዙፉ የማህበራዊ ሚዲያ ገፅ ሀገራዊ ምርጫን ተከትሎ ይህን እርምጃ በአሜሪካን ሲተገብር ቆይቷል፡፡ “የሲቪክ እና ፖለቲካ ቡድኖችን ለረጅም ጊዜ ሪኮመንድ ከማድረጉ ለማስቀረት እና ይህንን ፖሊሲም ወደተቀረው ዓለም ለማስፋፋት አቅደናል” ሲል የፌስቡክ ዋና ስራ አስፈፃሚ ማርክ ዙከንበርግ ተናግሯል፡፡ በተጨማሪም ከፋፋይ ውይይቶችን ለመገደብ እና ግለቱን ለመቀነስ በማሰብ ፖለቲካ ነክ ፖስቶች ያላቸውን ተደራሽነት እንደሚቀንሱም በማከል ገልጿል፡፡
እርምጃው ፌስቡክ ካለበት እንደ ነውጥ እና የተሳሳተ መረጃ ማዕከል ተደርጎ የመታየት ችግር ለመውጣት ታልሞ የተወሰደ ነው፡፡ ከሳምንታት በፊትም ተቋሙ የአሜሪካን ምክር ቤቶች የሚገኙበት የካፒቶል ህንፃ ላይ በፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች አማካኝነት ነውጥ መነሳቱን ተከትሎ የፕሬዘዳንቱን አካውንት ማገዱ ይታወሳል፤ ባለፈው ሳምንትም እገዳው ይዝለቅ ወይስ ይቁም የሚለው ላይ የሚወስን ገለልተኛ ተቆጣጣሪ ኮሚቴ ማዋቀሩን አስታውቆ ነበር፡፡ የኮሚቴው አባላት ከጥቂቱ በቀር አብዛኛዎቹ ተመልክቶ ፈቃድ ከመስጠት ባለፈ ፌስቡክ በቀጥታ ያልመረጣቸው ሲሆኑ ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡም ናቸው፡፡ በኮሚቴው ከተካተቱት ውስጥ የቀድሞው የዴንማርክ ጠቀላይ ሚኒስትር እና የኖቬል የሰላም ሽልማት አሸናፊ እንዲሁም የተለያዩ የህግ ባለሙያ፣ ጋዜጠኛ፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን ጨምሮ 20 ግለሰቦችን ያሰባሰበ ነው፡፡
ፕሬዘዳንቱ ላይ የተላለፈው እገዳ ሁለት የተለያዩ ግብረ መልሶችን አስተናግዶ ነበር፤ በአንድ በኩል ፌስቡክ ይህን ማድረግ የነበረበት ከረጅም ጊዜ አንስቶ ነው የሚሉና በሌላ በኩል ደግሞ የፕሬዘዳንቱ ድምፅ በድርጅቱ መታፈኑን መቃወማቸውን የሚገልፁ፡፡ በዚህ ረገድ በድርጅቱ የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዘዳንት ኒክ ክሌግ “ውሳኔያችን አስፈላጊና ትክክለኛ እንደነበረ አምናለው” ሲሉ ምላሻቸውን ያስቀምጣሉ፡፡
ፖለቲካ ነክ ጉዳዮች ላይ የተላለፈው ተደራሽነትን የመገደብ ውሳኔን አስመልክቶ በሰጠው አስተያየት ውይይቶች መኖራቸውን እንደሚደግፍ የተናገረው ማርክ ግን ደግሞ ከገፁ ተጠቃሚዎች እየመጡላቸው ያሉት ግብረ መልሶች አገልግሎቱን ሲጠቀሙ ስለ ፖለቲካና ግጭት መመልከት እንደማይፈልጉ የሚጠቁም መሆኑን ተከትሎ የተላለፈ ውሳኔና በመላው ዓለምም ተግባራዊ የሚሆን መሆኑን ገልጿል፡፡
ምንጭ፡ Tech Xplore
በምስል ብቻ የእፅዋት በሽታን የሚለይ ቀመርን የሰራው ኢትዮጵያዊ የቴክኖሎጂ ኩባንያ
======================
መቀመጫውን በጅማ አድርጎ በሁለት ወጣቶች የተመሰረተው ደቦ ኢንጂነሪንግ ምስልን በመጠቀም ብቻ የእፅዋት በሽታዎችን የሚለይ ቀመርን አበልፅጓል፡፡ ቴክኖሎጂው በሽታውን ከለየ በኋላ መወሰድ አለባቸው የሚላቸውን እርምጃዎች ለተገልጋዮቹ የሚጠቁም ሲሆን ከአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆን ደንበኞች በበይነ መረብ ወይም የስልክ መተግበሪያ አማካኝነት በሚገኝ ወርሀዊ አባልነት ደንበኛ መሆን የሚጠበቅባቸው ይሆናል፡፡
በግብርናው ላይ ስማርት ቴክኖሎጂን በመጠቀም የተለያዩ መፍትሄዎችን ለማፈላለግ የሚሰራው ደቦ ኢንጂነሪንግ የሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ ግዙፍ መረጃ (Big Data)፣ ምስል ፕሮሰሲንግን የመሳሰሉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ስራዎቹን ያከናውናል፡፡ ጀማሪ የቴክኖሎጂ ኩባንያው በተጨማሪነትም የተለያዩ የንግድ እርሻዎች እና የምርምር ተቋማት ስለ ስራቸው አስፈላጊውን ትንተና ለመስራት የሚያስችላቸውን የኮምፒውተር መተግበሪያ የሚያቀርብና ለሰፋፊ እርሻዎችም የድሮኖች ኪራይ አገልግሎትንም የሚሰጥ ነው፡፡ ባሳለፍነው ዓመት ብቻ በዋናነት በጅማና አካባቢው ለሚገኙ ከ300 በላይ ደንበኞቹም አገልግሎት ሰጥቷል፡፡
ደቦ ኢንጂነሪንግ የከፍተኛ ትምህርታቸውን በተለያዩ የምህንድስና ዘርፎች በተከታተሉት ሁለት ወጣቶች፤ ቦአዝ ብርሀኑ እና ጀርሚያ ባይሳ አማካኝነት ነው ምስረታውን ያገኘው፡፡ የ2019 ግሪን ኢኖቬሽን እና አግሪቴክ ስላም የቢዝነስ ውድድር እንዲሁም በሜስት አፍሪካ የኢትዮጵያ አሸናፊ ሆነዋል፡፡ እነዚህ እውቅናዎች የቢዝነስ ሀሳቦቻቸውን ዕውን ያደርጉ ዘንድ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲያገኙ የረዱ ሆነውላቸዋል፡፡ ድርጅቱ በቀጣይም አዳዲስ ገፅታዎችን ለመጨመር እንዲሁም የገመድ አልባ ሴንሰሮች መረብ እና የቁሳቁሶችን በይነ መረባዊ ግንኙነትን (IOT) በመጠቀም የእርሻ ማሳ ላይ በቀላሉ ተቀምጦ ቴክኖሎጂው ያለማቋረጥ መረጃን የሚያቀርብ እንዲሆን እየሰራ ነው፡፡
ምንጭ፡ Shega
በአጠቃቀማቸውና በአገልግሎታቸው ብዙዎች የሚመርጧቸው የ ቪ.ፒ.ኤን አይነቶች
------------------------------
በኦን ላይን በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ወቅት በተለያዩ አካላት የሚደርሱ የመረጃ ስርቆት ተግባራትን፣ ማጭበርበሮችን እና ሌሎች የሳንሱር እቀባዎችን እንደአስፈላጊነቱን ለመከላከል እና አጠቃላይ የበይነ መረብ ደህንነትን ለማስጠበቅ የ ቪ.ፒ.ኤን (VPN) ሚና ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ይህ የደህንነት ስርዓት በዋናነት ከሚሰጣቸው ግልጋሎቶች መካከል በኦን ላይን የምናካሂደውን የመረጃ ልውውጥ የተመሰጠረ ወይም (encrypt) በማድረግ ማንነታችን እንዳይታወቅ የሚያስችለን ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም በሃከሮች፣ ህገወጥ የመረጃ ነጋዴዎች እና ከራሱ ከበይነ መረብ አገግሎት አቅራቢ (ISP)ም ጭምር ደህነታችን የተጠበቀ እንዲሆን የሚያስችልን ፕላትፎርም ነው፡፡
ይህን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ እጅግ ብዛት ያላቸው የ ቪ.ፒ.ኤን አይነቶች በተለያየ መልኩ ተሰርተው የቀረቡ ቢሆንም ሁሉም ቪ.ፒ.ኤንዎች ተመሳሳይና እኩል አገልግሎት ይሰጣሉ ማለት አይደለም፡፡ አንዳንድ ቪ.ፒ.ኤንዎች በኦን ላይን የምናካሂደውን የመረጃ ልውውጥ የተመሰጠረ ወይም (encrypt) ከማድረግ ይልቅ እየተጠቀምንበት ባለው የበይነ መረብ ማሰሻ (browser) ላይ ይበልጥ ለአደጋ እንድንጋለጥ ሊያደርጉን ይችላሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ የመረጃ ልውውጣችንን የተመሰጠረ እንዲሆን ቢያስችሉም የበይነ መረብ ፍጥነትን ከሚገባው በላይ የሚያወርዱ በመሆናቸው የተሟላ ጥቅም እንዳናገኝ ሊያደርጉን ይችላሉ፡፡
ከዚህ ባለፈ ብዙ የተሻሉ ገፅታዎች የተጨመሩላቸው የ ቪ.ፒ.ኤን አይነቶች በአጠቃቀም ክብደታቸው ወይም ውስብስብነታቸው የተነሳ አገልግሎቱን በተሻለ ሁኔታ እንዳናገኝ የሚያግዱን ሲሆን፤ የኛን የግላዊነት ጥበቃ በመውረርም (invading privacy) የራሳቸውን ጥቅም ለማጋበስ የሚሞክሩ የ ቪ.ፒ.ኤን አይነቶችም አሉ፡፡ ከዚህ አንጻር የተሟላ ጥቅም ልናገኝባቸው የምንችላቸውን የ ቪ.ፒ.ኤን አይነቶች ለኮምፒውተሮቻችን እና ለስልኮቻችን መምረጥ አጠቃላይ የበይነ መረብ ደህንነታችንን ለማስጠበቅ እና የተሻለ አገልግሎት ለማግኘትም በእጅግ ይረዳናል፡፡
ከዚህ በታች የተጠቀሱት የ ቪ.ፒ.ኤን አይነቶች ይህን የተሟላ አገልግሎት ለማግኘት ብዙዎች የሚመርጧቸው መተግበሪያዎች ሲሆኑ ከላይ ካነሳናቸው ወሳኝ ገፅታዎች አንፃርም በቀዳሚነት የሚሰለፉ አስፈላጊ የደህነት ማስጠበቂያ ስርዓቶች ናቸው፡፡
1. ExpressVPN 2. NordVPN
3. Surfshark 4. TunnelBear
ምንጭ፡ Techradar እና Futurism
This media is not supported in your browser
VIEW IN TELEGRAM
በሃውልት ላይ የተቀረፁ ጥንታዊ የሮም ነገስታትን ምስል ወደ እውነተኛ ምስል የቀየረው የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ስልት
======================
የማሽን ለርኒንግ ቴክኖሎጂ የጥንት ምስሎችን እና ቪዲዮዎችን እንደ አዲስ ለማውጣት እና አሁን ባለው ገፅታ ለመከሰት ጥቅም ላይ መዋል ከጀመረ ትንሽ ሰነባብቷል፡፡ ይህ አስደናቂ ቴክኖሎጂ በዚህም ብቻ ሳያበቃ በሃውልቶች ላይ የተቀረፁ ጥንታዊ የነገስታት ምስሎችን ወደ እውነተኛው መልካቸው ወይም (photorealistic images) በመቀየርም የሰዎችን በምናብ የመጓዝ ፍላጎት በእጅጉ እያራቀቀው ይገኛል፡፡
የቨርቿል ሪያሊቲ ዲዛየነር የሆነው ዳንኤል ቫሸርት በሃውልት ላይ የተቀረፁ 54 ጥንታዊ የሮም ነገስታትን ምስል ወደ እውነተኛ መልካቸው ለመቀየር የተጠቀመበት የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ በማሽን ለርኒንግ ዘርፍ ውስጥ አንድ የሰራር ዘዴ ሲሆን ቆየት ያሉ ስእሎችን እና የመሬት አቀማመጦችን በምንፈልገው መልኩ ለመላዋወጥና ለመከሰት የሚስችለን የማሽን ለርኒንግ ዘዴ ነው፡፡ Generative Adversarial Network (GAN) የሚል ስያሜ ያለው ይህ የማሽን ለርኒንግ ስልት በተለያዩ የኦን ላይን ፕላትፎርሞች እና መተግበሪያዎች የሚገኝ ሲሆን ይህን ምርምር ያከሄደው ዳንኤል ቫሸርትም ArtBreeder የተባለውን የኦን ላይን ፕላትፎርም ለምርምሩ ተጠቅሟል፡፡
ይህን የማሽን ለርኒንግ ስልት የተገበረው ተመራማሪው የ54ቱን ነገስታት ምስሎች ከሃውልቶች፣ ከሳንቲሞች እና የጥንት ስእሎች ከውሰደ በኋላ በጥቅሉ 800 የሚጠጉ የነገስታቱን ምስለ ቅርፅ ArtBreeder በተባለው የኦን ላን ፕላትፎርም በማስገባት ትንተና እንዲደረግባቸው አድርጓል፡፡ በዚህ የትንተና ሂደትም የነገስታቱን እውነተኛ የፊት ቅርፅ፣ ገጽታ፣ የቆዳ አይነት በቀላሉ ሊያመለክት የሚችል እውነተኛ ምስል ከፕላትፎርሙ ሊገኝ ችሏል፡፡ ተመራማሪው ዳንኤል ቫሸርትም ይህን አውነተኛ ምስል ከነገስታቱ ግላዊ የታሪክ ጽሁፎች እና ከሌሎች የስነ ጥበብ መዘግብቶች ጋር ካነፃፀረ በኋላ በፎቶሾፕ መተግበሪያ ይበልጥ ሊቀራረብ የሚችል የነገስታቱን እውነተኛው መልክ ወይም (photorealistic images) ከምርምሩ ማውጣት ችሏል፡፡
54ቱ የነገስታት ምስሎች የሰዎች አዕምሮ እና የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ አንድ ላይ ምን ሊፈጥሩ እንደሚችሉ የሚያሳይ ስራ ነው የሚለው ዳንኤል ቫሸርት በዚህ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ሰዎች እጅግ አስገራሚ ስራዎችን ከዚህ በኋላም እንደሚሰሩ ይናገራል፡፡ ምንጭ፡ Big Think
የዶሮን ፆታ በእንቁላል ሳለ መቀየር ይቻላል?
===================
በዘመናዊ የዶሮ እንቁላል ኢንዱስትሪ ውስጥ ጫጩቶች ሲፈለፈሉ ወንድ እንዳይሆኑ ስለሚፈለግ በየዓመቱ ከ7 ቢሊዮን በላይ ወንድ ሆነው የሚፈለፈሉ ጫጩቶች ይሰዋሉ፡፡ ይህንንም ለማስቀረት እ.አ.አ በ2017 የተመሰረተው የእስራኤሉ ሱስ ቴክኖሎጂ ጫጩቶች ገና በእንቁላላቸው ውስጥ ከተፀነሱበት ጊዜ አንስቶ ባለው ዕድገታቸው ውስጥ ፆታቸውን በመቀየር የእንቁላል ማስጣል ስራን ወጪ ቆጣቢ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል፡፡ ለዚህ ስራ ጥቅም ላይ የሚውለው ቴክኖሎጂ እንቁላሎቹን ለድምፅ ንዝረት በማጋለጥ የዲ.ኤን.ኤ ትዕዛዞች ወደ ተግባር የሚለወጡበትን ሂደት (Gene Expression) ላይ ባሉት አዳዲስ የተፀነሱ ጫጩቶች ላይ ለውጦችን በማምጣት ነው ፆታቸውን ከወንድ ወደ ሴት እንዲቀየር የሚያደርግ ነው፡፡ እንደ ድርጅቱ ከሆነ አሁን ላይ ባለው የሙከራ ምርቱ ቢያንስ 60 በመቶው እንቁላሎቹ በእርግጠኝነት ሴት ሆነው እንዲፈለፈሉ እያደረገ ነው፤ ወደፊትም ድርሻው ከዚህም በላቀ እንደሚያድግ ይናገራል፡፡ አሁን ላይ ቴክኖሎጂውን እዛው እስራኤል ውስጥ ባለ የእንቁላል ማስጣያ እርሻ ጋራ በመስራት ላይ ሲገኝ በቀጣይም ከጣልያን እና አሜሪካን እንቁላል አምራቾች ጋራ የሚሰራ ይሆናል፡፡
ድምፅን ተተቅሞ የጫጩቶችን ፆታ የመለወጡ ነገር እንዲሁ ስናስበው የሚሆን መስሎ ላይታየን ይችል ይሆናል፡፡ ሆኖም ሌላ ውጫዊ ተፅዕንዖ የሆነው ሙቀት በተለያዩ የዓሳ እንዲሁም እንደ እንቁራሪት፣ አዞ እና መሰል ፍጥረቶች የፆታ ለውጥን ሲያመጣ ይታያል፤ ምንም እንኳን ይህ ለወፍ ዝርያዎች የሚሰራ ባይሆንም፡፡ በሌላ መልኩ ጥናቶች የሚያሳዩት የዲ.ኤን.ኤ ትዕዛዞች ወደ ተግባር የሚለወጡበት ሂደቶች ለድምፅ ሲጋለጡ በተፅዕንዖ ስር እንደሚወድቁ ነው፡፡
የሱስ ቴክኖሎጂ ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ያኤል አልተር እንደምትለው ከሆነ ድርጅቱ እንቁላሎቹን ስፒከር በተገጠመላቸው የጫጩት ማስፈልፈያ ማሽኖች ውስጥ የመጀመሪያዎቹን 13 ቀናት ለሰው ጆሮ ሊሰማ በሚችል መጠን የጩኸት ድምፅ (beeping) ይለቀቅባቸዋል፡፡ ድምፁ በቀን ውስጥ ያለማቋረጥ ለረጅም ሰዓታት እንቁላሎቹ ላይ እየጮኸ ይውላል፡፡ እዚህ ላይ ዋናው ነገር የድምፁ ከፍታ እና ፍሪኩዌንሲ ላይ ነው፤ ሙቀት እና ወበቁም ቁጥጥር ይደረግባቸዋል፡፡ በዚህም ሳብያ በድምፅ ፆታን ወደ ሴት እንዲያደላ የማድረግ ስልቱን በተደጋጋሚ በሺዎች እንቁላሎች ላይ ሞክረው በውጤቶቹ ከ60 በመቶ በላይ ሴት ጫጩቶች መፈልፈል እና በአንዳንድ አካባቢዎችም ድርሻው እስከ 70 በመቶ የደረሰ መሆኑን ያኤል አልተር ትናገራለች፡፡
እንደ ያኤል ግምት ከሆነ ለውጡ ሊመጣ የቻለው በዶሮዎች ፆታዊ አፈጣጠር ላይ ትልቅ ሚናን የሚጫወተው ዲኤምአርቲ1 (DMRT1) በራሒን በድምፁ አማካኝነት ማስቆም በመቻሉ ነው፡፡ ሆኖም በተቃራኒው ስለ ዶሮዎች በማጥናት ላይ ያሉትና በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኤደንብራ እና በሞናሽ ዩኒቨርሲቲዎች የሚያገለግሉት ማይክ ክሊንተን እና ግሬግ ስሚዝ ዲኤምአርቲ1 ሊቆም የሚችል ነገር እንዳልሆነ ይገልፃሉ፡፡ እንደነርሱ ከሆነ በመጀመሪያ ዲኤምአርቲ1ን በመቀነስ ፆታቸው ወደ ሴትነት የተለወጡ የዶሮ ጫጩቶች ወንድነታቸው የማይለቃቸውና በአካልም ወንድ መስለው የሚፈለፈሉ ናቸው፡፡ ይህም አዕዋፍ በጎኔዳል ሆርሞኖች የተነሳ የሚመጣባቸው ተፅዕንዖ አነስተኛ በመሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛው፤ ተፀንሰው ሳለ ዲኤምአርቲ1ን በመቀነስ ፆታቸው ከወንድ ወደ ሴትነት የተቀየሩ ዶሮዎች እንቁላሎችን እንደማይጥሉ ገና ታትሞ ያልወጣው ጥናታቸው አሳይቷል፡፡
ክሪስተን ናቫራ የተባለች ሌላ ተመራማሪም በበኩሏ ድርጅቱ አገኘው የሚለውን ውጤት በሳይንሳዊ መንገድ የመጣ ስለመሆኑ በምሁራን የተፈተኑ ጥናቶችን ማቅረብ እንዳለበት ታስረዳለች፡፡ በዚህ ረገድ ሱስ ቴክኖሎጂም የጥናቱን አስፈላጊነት ዕውቅና በመስጠት የሰራቸው ምርምሮቹን ለማሳተም እየሰራ መሆኑንም የሳይንቲፊክ ዳይሬክተሯ ሮተም ካዲር ተናግራለች፡፡
በዘመናዊ የዶሮ እንቁላል ኢንዱስትሪ ውስጥ እንቁላሎች እንዲጣሉ የወንድ አውራ ዶሮዎች ድርሻ ቢያስፈልግም ለእንቁላል ጣይነት የሚፈለጉ ጫጩቶች ሲፈለፈሉ ግን እነርሱም እንቁላልን ይሰጡ ዘንድ ሴት ሆነው እንዲወጡ ይፈለጋል፡፡ ሆኖም ግማሾቹ እንቁላሎች ወንድ ሆነው በመፈልፈላቸውና እነርሱን አደል በየዓመቱ ከ7 ቢሊዮን በላይ ወንድ ጫጩቶች እንቁላል ለማግኘት ሲባል በቄራ ይሰዋሉ፡፡ ከሱስ ቴክኖሎጂስ በተጨማሪ ሌላ ጀማሪ የቴክኖሎጂ ኩባንያም በተለየ አኳሀን ገና እንቁላሎቹ ወደ ማስፈልፈያ ማሽኑ ከመግባታቸው አስቀድሞ ፆታቸውን በመለየት እና እንዳይገቡ በማድረግ ላይ አተኩሮ እየሰራ ነው፡፡ ለዚህም የእንቁላሉን ፈሳሽ በናሙናነት ወስዶ የመመረምርና ሌሎች ስልቶችን የሚጠቀም ይሆናል፡፡
ምንጭ፡ The Guardian
ታዳሽ ኃይል እና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ
-------------------------------
ኢትዮጵያ የሃይድሮ ሀይልን ጨምሮ የነፋስ፣ ጂኦተርማል፣ ሶላር ባዮማስን እና ሌሎች በርካታ የታዳሽ ሀይል ሀብቶች ያሏት ሃገር ናት፡፡ አነዚህ ብዛት ያላቸው የታዳሽ ሃይል ሀብቶች ሀገሪቱ ከ 60,000 ሜጋዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም እንዲኖራት የሚስችሉ ቢሆንም አሁን ላይ ጥቅም ላይ የዋሉት የታዳሽ ሃይል ሀብቶች በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ አብዛኛው የሀገሪቱ ህዝብ በገጠራማ አካባቢ ከመኖሩ ጋር ተያይዞ ዘመናዊ የሃይል አማራጮችን የማግኘት እድሉ እጅግ የጠበበ ሲሆን፤ ከእነዚህ የሃይል ምንጮች በላይ በኤሌክትሩክ ሃይል የማይመደቡ እንደ ባዮማስ ያሉ የሃይል አማራጮች ይበልጥ ጥቅም ላይ እየዋሉ የሚገኙ ናቸው፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያ የተትረፈረፈ የታዳሽ ኃይል ሀብቶች ባለቤት ብትሆንም በአፍሪካ በነፍስ ወከፍ ደረጃ ዝቅተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ከሚጠቀሙ ሀገራት አንዷ ነች፡፡ በአሁኑ ሰዓት የሀገሪቱ ሀይል የማምረት አቅም 4,200 ሜጋዋት የደረሰ ሲሆን ከዚህም ውስጥ ከ12 በላይ የሀይል ማመንጫ ጣቢያዎች የሚካተቱበት የሃይድሮ ሀይል 94 በመቶውን የሀገሪቱን የሃይል አቅርቦት ይሸፍናል፡፡ በቅርቡ የተሰሩ የኢትዮጵያ የሀይል ፍላጎት ዳሰሳ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት የአገሪቱ የሀይል ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ሲሆን በአገሪቱ ያሉ ሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች ማለትም የኢንዱስትሪ፣ የግብርና፣ የንግድ እና የመሳሰሉት ዘርፎች የሀይል ፍላጎታቸው ይበልጥ እየጨመረ መምጣቱ በግልጽ የሚታይ ነው፡፡
ሃገሪቱ አሁን በያዘችው የሀይል አቅርቦት እንቅስቃሴ እንደአውሮፓውያኑ በ2025 ለሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች የኤሌክትሪክ ሃይልን ለማዳረስ ወጥና እየሰራች ቢሆንም በዘርፉ ከሚያግጡ መሰናክሎች አንጻር እቅዱ በተባለለት ግዜ ማሳካት እንዲቻል የሁሉም ባለድርሻ አካለት ሁለንተናዊ ተሳትፎ እጅጉን ወሳኝ ነው፡፡ በዚህ የሃገሪቱ የሀይል አቅርቦት እንቅስቃሴ ውስጥ በእቅድ ደረጃ የተያዘው 35 በመቶ የሚሆነው የኤሌክትሪክ ሃይል ከማእከላዊ ስርጭት ውጭ በሆነ የ (off-grid) አማራጮችን ለማልማት የታሰበ ሲሆን፤ ቀሪውን ደግሞ በመደበኛው የመንግስት የሃይል ስርጭት ውስጥ የተካተተ ነው፡፡
ታዲያ በዚህ የሀይል አቅርቦት እንቅስቃሴ ውስጥ ቢያንስ ከ35 በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ ከታዳሽ ሃይል ከሚገኙ ዘመናዊ የሃይል አማራጮች ኤሌክትሪክን እንዲያገኝ የታቀደ ሲሆን በዚህ ማዕቀፍ ውስጥም 8,370 የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ያላቸው የታዳሽ ኃይል ፕሮጀክቶች በስራ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህ ሂደት ሀገራችን አትዮጵያን በአሁኑ ወቅት ለአለማችን ስጋት የሆነውን የአካባቢ ብክለትን ከግምት ውስጥ በማስገባት አረንጓዴ አብዮትን በማራመድ ላይ ከሚገኙ ጥቂት ሀገሮች መካከል አንዷ የሚያደርጋት ከመሆኑም ባለፈ እዚህም እዚያም የተጀመሩት የአማራጭ ሀይል ምንጮች፣ የሀገሪቱ አረንጓዴ ፖሊሲ እና በፕሮጀክቶች ላይ ለአካባቢ ጥበቃ እየተሰጠ ያለው ትኩረት ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ መጎልበት ተጨማሪ ማሳያ ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡
በጠቅላላው በዚህ ዘርፍ እየታየ ያለው እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ መሆኑ እንዳለ ሆኖ የአለም የእድገት ሩጫ ተወዳዳሪ በበዛበት በዚህ ወቅት ያለውን አማራጭ ሁሉ በመጠቀም ትንፋሽ መሰብሰብ አስፈላጊነቱ አጠያያቂ አይሆንም፡፡ እንደዚህ ያለው የሀይል ፍላጎት ወደ ተደራጀና ዘመናዊ የሀይል አቅርቦት የተሸጋገረ ማህበረሰብ፣ መሰረተ-ልማት በአጠቃላይ ስርአት ይፈልጋል፡፡ ይህም የሚረጋገጠው ከፍተኛ ሀይል ማመንጨት ሲቻል ብቻ ሳይሆን የመነጨውም ሀይል የሚሰራጭበት ስርዓት የዳበረ ሲሆን፣ የተለያዩ የሀይል አማራጮችን በአንድ ጊዜ ማቅረብ ሲቻል፣ የአገሪቱ ዋና ዕቅድ ፕሮጀክቶች ውጤታማና እርስ በርሳቸው የተሰናሰሉ ሲሆኑ እንዲሁም የግል ኢንቨስትመንቱን የሚያበረታታ አካባቢ መፍጠር ሲቻልም ጭምር ነው፡፡
ምንጭ፡ Ethiopian Herald እና IEA