TechIn2
1.22K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
ክፍት የስራ ቦታ ማስታወቂያ
============
የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ከዚህ በታች ለተገለፁት የስራ መደቦች ስራ ፈላጊዎችን አወዳድሮ በቋሚነት መቅጠር ይፈልጋል፡፡
የምዝገባ ቦታ፡- አራት ኪሎ ከፓርላማ ፊትለፊት ከሚገኘው የትራፊክ መብራት ወረድ ብሎ፣ አልያም በ http://recruit.techin.gov.et/ በመግባትና ቅድሚያ ሬጂስተር በማድረግ መመዝገብ ትችላላችሁ፡፡
የመመዝገቢያ ቀን፡- ማስታወቂያው ከወጣበት ቀን ጀምሮ እስከ ጥር 28 2013 ድረስ ባሉት ተከታታይ የስራ ቀናት ውስጥ
በምዝገባ ወቅት መቅረብ የሚገባቸው ማስረጃዎች፡- ለሁሉም የስራ መደቦች የትምህርትና አግባብ ያለው የስራ ልምድ ማስረጃዎች ዋናውና የማይመለስ ፎቶ ኮፒ
መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የተሰጡ የስራ ልምዶች ተቀባይነት የሚኖራው ተገቢውን የመንግስት ግብር መከፈሉን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች ሲቀርቡ ብቻ ነው፡፡
ሴት አመልካቾች ይበረታታሉ፡፡
ለበለጠ መረጃ በ0118547758 ይጠቀሙ
የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት
10 ሳይንስና ታሪክ ነክ የአለማችን አስደናቂ እውነታዎች
====================
1. ረዘም ያለ የምግብ አብሳዮች ወይም ሼፎች ኮፍያ በጎኑ በኩል 100 እጥፋቶች ያሉት ሲሆን ይህም እንቁላልን ማዘጋጀት የሚቻልባቸውን 100 መንገዶች ያመለክታል፡፡
2. ከአለማችን ቢራ አምራቾች መካከል የሆነው ጊነስ በእንግሊዝ ብቻ 93,000 ሊትር ቢራ ባለ ረጃጅም ጺም ሰዎች በሚጠጡበት ጊዜ ወደ ጺማቸው ገብቶ እንደሚባክን ግምቱን አስቀምጧል፡፡
3. የእንግሊዟ ንግስት ኤልሳቤት ሁለተኛ የተዋጣላት መካኒክ ነበረች
4. በሲውዲን ሃገር የሚገኙ ደም ለጋሾች የለገሱት ደም ጥቅም ላይ በሚውልበት ጊዜ የምስጋና መልእክት ይደርሳቸዋል፡፡
5. የአለማችን እውቁ ጠፈርተኛ ኒል አርምስትሮንግ የስራ ማመልከቻ ያስገባው ለማመልከት ከተሰጠው ቀን አንድ ሳምንት ዘግይቶ ነበር፡፡
6. ውሻዎች እስከ 250 ቃላትንና ምልክቶችን የመረዳት ብቃት አላቸው፡፡ የውሾች አማካኝ የአእምሮ አቅም ከሁለት ዓመት ህጻን ልጅ ጋር ይወዳደራል፡፡
7. የሳሙና አረፋ የመታጠቢያ ውሃ ለረጅም ጊዜ ሳይቀዘቅዝ እንዲቆይ ማድረግ ያስችላል
8. ረጅም እግር ባላቸው ፍላሚንጎ በሚባሉ የወፍ ዝርያዎች እግር መካከል ያለው እጥፋት ጉልበት ሳይሆን እንደ አልቦ አይነት ጌጥ ነው
9. በ1967 በናይጀሪያ የርስበርስ ጦርነት ወቅት በተዋጊዎቹ መካከል ለሁለት ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት ተደርጎ ነበር፡፡ ለዚህም ምክንያቱ እውቁ የእግር ኳስ ኮከብ የሚያደርገውን ጨዋታ ለመመልከት ነበር፡፡
10. የጎግል መስራች በ1999 ድርጅቱን ከ1ሚሊዮን ዶላር በታች በሆነ ዋጋ ለመሸጥ ተስማምቶ የነበረ ቢሆንም ገዥ የሆነው ድርጅት አያዋጣኝም ብሎ ትቶታል፡፡
ምንጭ Mental floss
አዲሱ ቲክቶክ?
=======
ከቲክ ቶክ ጋራ በቀጥታ እንዲሚፎካከር የሚጠበቀው አዲሱ የጎግል የቪዲዮ መጋሪያ ድረ ገፅ “ዩትዩብ ሾርትስ” ህንድ ውስጥ እያደረገ ባለው ሙከራ በየዕለቱ 3.5 ቢሊዮን ተመልካቾችን እያስተናገደ መሆኑን አስታወቀ፡፡ የዩትዩብ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሱዛን በያዝነው የፈረንጆች ዓመት ምርቱን ወደተለያዩ ገበያዎች ለማዳረስ እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡
በጉግል ባለቤትነት ስር ያለው ዩትዩብ አዲሱን የአጫጭር ምስሎች መጋሪያ ገፁን ይፋ ያደረገው ከወራት በፊት መስከረም ላይ ነበር፤ በ15 ሴኮንዶች ውስጥ እራስን የመግለጫ መንገድ ነው በሚል፡፡ ገፁ ከዩትዩብ ጋራ በቀጥታ እንዲተሳሰር የተደረገም ሲሆን አሁን ግን የሙከራ አገልግሎቱን እየሰጠ ያለው ህንድ ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ዩትዩብ ሾርትስ ጉግልን በዓለም ዙርያ አንድ ቢሊዮን ያህል ተጠቃሚዎችን ካፈራው ቲክ ቶክ ጋራ ተፎካካሪ ለማድረግ ተወጥኖ የተዘጋጀ ነው፡፡
ነገር ግን ከቲክ ቶክ ጋራ የሚፎካከር አማራጭ ይዞ የመጣው ጎግል ብቻ አይደለም፤ ባሳለፍነው ነሀሴ በፌስቡክ ባለቤትነት የሚተዳደረው ኢንስታግራምም ሪልስ የተባለውን የአጭር ቪዲዮ ምስል መመልከቻ ገፅ ይፋ አድርጓል፡፡ ስናፕ ቻትም በበኩሉ ስፖትላይት የተሰኘውን ምርቱን ይፋ አድርጓል፡፡
በቻይናው የቴክኖሎጂ ኩባንያ ባይትዳንስ ስር የሚገኘው ቲክቶክ ከነዚህ አዳዲስ ፉክክሮች በተጨማሪ በተወሰኑ መንግስታት አለመወደድንም አፍርቷል፡፡ ህንድ መተግበሪያውን ከሰኔ አንስቶ ያገደቺው ሲሆን ይህ በቲክቶክ እና ሌሎች የቻይና መተግበሪያዎች ላይ የተላለፈው እገዳዋ ዘላቂ እንደሚሆን አስታውቃለች፡፡ የቀድሞው የአሜሪካን ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕም ለቻይና የስለላ ስራን ይሰራል ሲሉ የከሰሱት ሲሆን ለማገድ ዝተው ነበር፡፡
ምንጭ፡ Tech Xplore
የአለማችን የመጀመሪያው የቤት ውስጥ ባለ 5G አንቴና
**************************
በኮሪያ የሚገኙ ተመራማሪዎች የበይነ መረብ ተጠቃሚዎች የአምስተኛ ትውልድ ኔትወርክን በቤት ውስጥ መጠቀም የሚያስችላቸውን ስልት ማበልጸጋቸው ተሰማ፡፡ ይህ ቴክኖሎጂም የአምስተኛ ትውልድ የበይነ መረብ አገልግሎትን መዳረሻ ለማስፋት የሚደረገውን ስራ እጅግ እንደሚያግዘው ተነግሮለታል፡፡
በኮሪያ የሚገኘው የኤሌክትሮኒክስ እና የቴሌኮሚኒኬሽን ምርምር ተቋም ይህን በአለማችን የመጀመሪያ የሆነውን ግኝት በስኬት መስራቱን ሲያስተዋውቅ ከዋና ማሰራጫ 28GHz የ5G ሲግናልን ወደ ተለያዩ ህንጻዎች ማስተላለፍ የሚያስችል የአንቴና ስርዓት መሆኑን ገልጧል፡፡
በዓለማችን ውስጥ አገልግሎት ከሚሰጠው የሞባይል ዳታ ውስጥ 80 በመቶ የሚሆነው ጥቅም ላይ የሚውለው በቤት ውስጥ እንደሆነ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ አዲሱ ቴክኖሎጂ 20Gbps በሚደርስ ፍጥነት እንደ አየር መንገድ፣ የባቡር ጣቢያዎችና ትልልቅ የንግድ ማእከላት የአምስተኛ ትውልድ በይነ መረብ አገልግሎትን መጠቀም ያስችላል፡፡
ቴክኖሎጂው በተጨማሪም የ5G ገመድ አልባ ሲግናሎችን ወደ ኦፕቲካል ሲግናሎች መለወጥ የሚያስችል ሲሆን ያለምንም መቆራረጥ እስከ 5 ኪሎሜትሮች ድረስ ማስተላለፍ ያስችላል፡፡
በህንጻዎች ጣሪያ ላይ የሚገጠመው መሳሪያው በአካባቢው ካለ የ5G ሲግናልን በመውሰድ በገመድ ወደሚተላለፍ ሲግናል በመቀየር በተገጠሙለት ብዙ አንቴናዎች አማካኝነት ሲግናሉን ወደ ህንፃው የተለያዩ ክፍሎች ያሰራጫል፡፡
ምንጭ Tech Xplore
የኢላማ ለውጥ ያደረጉት ሀከሮች
==============
ባሳለፍነው የፈረንጆች ዓመት 2020 ሀከሮችና የሳይበር ላይ ቀበኞች የግለሰቦችን መረጃ ከመስረቅ ይልቅ ትኩረታቸውን ከፍ ያለ ትርፍ በሚያስገኙ ተቋማት ላይ ማድረጋቸውን ከአይደንቲቲ ተፍት ሪሶርስ ሴንተር (ITRC) የወጣ ሪፖርት አመላከተ፡፡ የሳይበር ጥቃት የደረሰባቸው ግለሰቦች ላይ ትኩረቱን አድርጎ ሚንቀሳቀሰው ድርጅቱ እንዳስታወቀው በአሜሪካን የመረጃ ስርቆት በ13 በመቶ ሲቀንስ በግለሰብ ደረጃ የሚደርሰው የሳይበር ጥቃት ግን ከቀደመው ዓመት አንፃር በ66 በመቶ ወርዷል፡፡
በኮምፒውተር ስርዓቶች ላይ ጥቃት ሰንዝሮ በማበላሸትና ወደነበረበት ለመመለስ ክፍያ መጠየቅ ከፍ ያለ ትርፍን በማስገኘታቸው ተመራጭ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ ድርጅቱ እንዳስታወቀው እነዚህ ጥቃቶች በደቂቃዎች ውስጥ ብቻ የሚያስገኙት ገቢ ለወራት ያህል በመቶዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦችን በማጥቃት ከሚገኘው ጋር ተነፃፃሪ ነው፡፡ የሳይበር ደህንነት ተቋም እንደሆነው ኮቭዌር መረጃ ከሆነ በ2020 ከነዚህ ጥቃቶች የሚገኘው ገንዘብ በ2018 ከነበረበት 10 ሺህ ዶላር በሁለት ዓመት ውስጥ ብቻ ከ20 እጥፍ በላይ አድጎ 233 ሺህ ዶላር ደርሷል፡፡ ይህ ግን ግለሰቦች የሳይበር ጥቃትን ችላ ማለት አለባቸው ማለት እንዳልሆነ ባለሙያዎች ያሳስባሉ፤ አሁንም በብዙ መቶ ሚሊዮንች የሚቆጠሩ ግለሰቦች የጥቃት ሰለባ እየሆኑ ነውና፡፡
አሁን ላይ እየተስተዋለ ያለው የጥቃት ስልት በሦስተኛ አካል በኩል የሚከናወነው ነው፡፡ ለምሳሌ አነስተኛ ተቋማት ለራሳቸው የዘረጉት የሳይበር ደህንነት ቁጥጥር የላላ ቢሆንም አብረውት ከሚሰሩትና ዋናው የጥቃት ዕቅድ ከሆነው ተቋም ጋራ ትስስር ያላቸው በመሆኑ የሳይበር ቀበኞቹ በእነርሱ በኩል ትልቁን አሣ ማጥመድ ይችላሉ፡፡ በተጨማሪም የኮቪድ-19 ወረርሺኝን ተከትሎ ብዙ ሰዎች ከቤት ሆነው ስራ መስራታቸው ተቋማቸው ለእነዚህ ወንጀለኞች ተጋላጭ እንዲሆን እስችሎታል፡፡
ምንጭ፡ Tech Xplore
ስልጠና፣ ምርምርና ቢዝነስ የሃገራችንንና የህዝቦቿን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል
***********************
የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት በአምስቱ ሴንተሮች የሚገኙ ተመራማሪዎችንና ፈጻሚዎችን የሚያስተዋውቅና በ2012ዓ.ም ተቋሙ ሲያከናውናቸው በነበሩ ተግባራት ለመጣው ውጤት የተሻለ አፈጻጸም ለነበራቸው የተቋሙ ሰራተኞችና ፈጻሚዎች በትላንትናው ዕለት የእውቅና አሰጣጥ መርሃ ግብር አከናውኗል፡፡ በእንጦጦ ፓርክ በተዘጋጀው በዚህ መርሃ ግብር የተቋሙ ቤተሰቦች የተሳተፉበት የጠዋትና የከሰዓት ዝግጅቶች ተካሂደዋል፡፡ የጥዋቱ መርሃ ግብር አራት ኪሎ ከሚገኘው የተቋሙ ዋና መስሪያ ቤት ወደ አዲሱ የእንጦጦ ፓርክ በተደረገ ጉዞ ተጀምሯል፡፡ በፓርኩ ውስጥ እሴት በተጨመረበትና በተፈጥሮ በተዋበው ጫካ ውስጥ የእግር ጉዞ የተካሄደ ሲሆን የጥዋቱ መርሃ ግብርም አዝናኝ በነበረው የፈረስ ግልቢያ ውድድር ተጠናቋል፡፡
የከሰዓት በኋላው ዝግጅት ከምሳ ግብዣ በኋላ የቀጠለ ሲሆን የዚህን ዝግጅት መክፈቻ የቷቋሙ ዋና ዳሬክተር አቶ ሙሉቀን ቀሬ በንግግር አቅርበዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ ንግግራቸውን ላለፉት ጊዜያት እንደ አለም እና እንደ ሀገር በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ማለፋችንን አስታውሰው የጀመሩ ሲሆን በተደራረበ ችግር ውስጥም ቢሆን የቴክኢን ቤተሰቦች ችግር ፈቺ የሆኑ የተለያዩ ስራዎች መስራታቸውን አስገንዝበዋል፡፡ አቶ ሙሉቀን አክለውም ‹‹ቴክኢን ሰው ነው፤ ሰው ያስባል፣ ያቅዳል እንዲሁም ይፈጽማል፡፡ ስለዚህ በተቋሙ ውስጥ ያሉ ተመራማሪዎችና ሁሉም ሰራተኞች ያላቸውን የማሰብ፣ የመፍጠርና የመፈጸም አቅም በብቃት መጠቀም አስፈላጊ ነው›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ ያለባትን የፈጠራ፣ የጥናትና ምርምር እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግር ክፍተት ለመሙላት ታስቦ በተደራጀ ተቋም ውስጥ የምንሰራ ሙያተኞች የሀገራችንንና የህዝቦቿን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት ችግር ፈቺ ስልጠና፣ ምርምርና ቢዝነስ ተኮር ተግባራትን በመስራት የበኩላችንን ሀላፊነት ልንወጣ ይገባል ሲሉ አቶ ሙሉቀን ተናግረዋል፡፡
በንግግራቸው ማብቂያ ላይም አቶ ሙሉቀን ፕሮግራሙ የተዘጋጀው አምስቱን የተቋሙን ሴንተሮች ማቀላቀል፣ ባለፉት ጊዜያት የተሰሩ ስራዎች በተቋሙ ሰራተኞች የተከናወኑ በመሆናቸው ለስኬቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላላቸው ተመራማሪዎችና ፈጻሚዎችን ለማበረታታትና በስድስት ወር ውስጥ በአስደናቂ ጥራትና ፍጥነት ከተሰራው ፓርክ ልምድ መውሰድ የሚሉ ሶስት አላማዎችን ያነገበ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በመቀጠልም የተቋሙ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ተሾመ ከጥቂት ዓመታት በፊት ተቋሙ በሰው ሃይልና በመፈጸም አቅም የነበረበትን ሁኔታ አስታውሰው ዛሬ ላይ ከ340 በላይ ሰራተኞችን ሲይዝና በአምስት ሴንተሮች ሲደራጅ ተጨማሪ ሀላፊነቶችንም በመጨመር ነው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ተቋማችን የተለያዩ ኢንዱስትሪዎችና ተቋማት የተሸለ የአሰራር ስርዓት እንዲኖራቸው የሚጠበቅብንን ሀላፊነት መወጣት አለብን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ከተቋሙ ሃላፊዎች በተጨማሪም ተጋባዥ እንግዳ የነበረው አዲስ ቡርሃን (ሙሃመድ አሊ ቡርሃን) ለተቋሙ ሰራተኞች በጣም ጠቃሚ የሆነ በማሰብና በአእምሮ ብቃት ላይ ያተኮረ ንግግርን አቅርቧል፡፡ ከቀረበው ንግግርም በመነሳት ታዳሚዎች የተለያዩ ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲሆን አዲስም ምላሾችን ሰጥቷል፡፡
በመጨረሻም በ2012 በተቋሙ ውስጥ የተሻለ አፈጻጸም የነበራቸው ተመራማሪዎችና ሌሎች ፈጻሚዎች የተዘጋጀላቸውን የምስክር ወረቀት እና የማበረታቻ ሽልማት ከተቋሙ ዋና ዳይሬክተር እጅ ተቀብለዋል፡፡ ዝግጅቱም አቶ ሙሉቀን ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር ተጠናቋል፡፡
በነገው የቴክ-ሳይንስ መሰናዶዋችን
================
በአብይ ፕሮግራም፤ ወደ ደሴ አቅንተን ስመ ጥሩን ወ/ሮ ስህን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ
በተመራማሪዎች ታሪክ፤ ዶ/ር ተስፋዬ ሽምብር
በብላቴናት፤ የህክምና ቁሳቁሶችን ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ የሚረዳ ሮቦት የሰራው ታዳጊ
በተቋማት፤ የጎግል ዳታ ሴንተር የደንበኞቹን መረጃ እንዴት እንደሚጠብቅ
በቴክኖሎጂ ታሪክ፤ የልብስ ስፌት ማሽን
ከነዚህ አባይት ዝግጅቶቻችን ባሻገር የስኮላርሺፕ መረጃንም ጨምረን ነገ በ10 ሰዓት እና ዕለተ ማክሰኞ በተመሳሳይ ሰዓት በMOE TV እንጠብቃችኋለን፡፡
የዩትዩብ ቻናላችንንም (https://www.youtube.com/channel/UC6jvUOLRSkVEQtc5Annfwvg) ሰብስክራይብ ማድረጉን እንዳይረሱ፤ ከዓመታት በፊት ከተላለፈው የመጀመሪየው ክፍል አንስቶ ያሉትን ሁሉንም የቴክ-ሳይንስ ፕሮግራሞች አንድ በአንድ መመልከትና ለእርስዎም ሆነ ቤተሰብዎ ዕውቀትን መገብየት ይችሉበታልና፡፡