TechIn2
1.22K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት ከቱሪዝም ኢትዮጵያ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ።

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት በቱሪዝም ዘርፉ ላይ የራሱን ሚና ለመወጣት ብሎም ዘርፉን ለማመንደግ የሚደረግ ሀገራዊ ጥረትን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ የሚያስችለውን ስምምነት ከቱሪዝም ኢትዮጵያ ጋር ተፈራርሟል።

የስምምነት ሰነዱን በቱሪዝም ኢትዮጵያ በኩል ወይዘሪት ሌንሳ መኮንን የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስኪያጅ የፈረሙ ሲሆን በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት በኩል ደግሞ የኢኒስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳንዶካን ደበበ ፈርመዋል።

ይህ በቱሪዝም ኢትዮጵያና በቴክኖሊጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት መካከል የተደረሰው መግባቢያ ብዙ የጋራ የሆኑ አንኳር ስራዎች የተካተቱበት ሲሆን በመጀመሪያ ምእራፍ ላይም የቱሪዝም ሳተላይት አካውንትን ለማስተዋወቅና በኢትዮጵያ ደረጃም በራስ አቅም አዳብሮና ኣልምቶ ስራላይ ለማዋል የሚደረግ ጥረትን ለመደገፍ የተደረሰ ስምምነት ነው።

የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት በአለም አቀፍ ደረጃ የሚገኙ የቱሪዝም እንቅስቃሴዎችና መዳረሻዎችን ጨምሮ ሌሎችም ቱሪዝም ነክ መረጃዎች የተካተቱበት ስርአት ሲሆን ኢትዮጵያም ይህን ስርአት መተግበሯ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ፋይዳ እንደሚኖረው በፊርማ ስነስረአቱ ላይ ተገልጿል።
በቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን አስተዳደር እንዲሁም በኢትዮጵያ ኢነርጂ ዘርፍ ላይ ያተኮረ ሴሚናር ተካሄደ።

በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት በቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን አስተዳደር እንዲሁም በኢትዮጵያ ኢነርጂ ዘርፍ ላይ ያተኮረ የአንድ ቀን ሴሚናር ተከናውኗል፡፡ ኢኒስቲትዩቱ ያዘጋጀው ይህ ሴሚናር ላይ በደቡብ አፍሪካው ሽዋኔ ዩኒቨርሲቴ ኦፍ ቴክኖሎጂ ውስጥ በተመራማሪነት እያገለገሉ የሚገኙት ፕሮፌሰር ማሞ ሙጬ እንዲሁም መቀመጫውን በሃገረ አሜሪካን ካሊፎርኒያ ውስጥ ያደረገው የኤ ኤስ ሲ ኢንጂነሪንግ መስራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ኢንጂነር በሃይሉ አሰፋ ለተሳታፊዎች ገለጻዎች አድርገዋል፡፡

ዝግጅቱን በመክፈቻ ንግግር ያስጀመሩት የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ተሾመ ሳህለማርያም በዓለም ሃገራት መካከል ያለው የሃብት ክፍፍል ምጣኔ በቴክኖሎጂ ባለቤትነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ታድያ ይህን ልዩነት ማጥበብና የሃገራትን እድገት ማረጋገጥ የሚቻለውም ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽንን እንደ ዋና መሳሪያ በመገልገል እንደሆነና፤ ኢኒስቲትዩቱም በዚህ ረገድ የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ አክለው አስታውቀዋል፡፡

በሴሚናሩ የጠዋት ክፍለ ጊዜ ፕሮፌሰር ማሞ ሙጬ Economic Development and Innovation፣ Components Making System of Innovation እና ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተው አብራርተዋል፡፡ ቀጣዩን ክፍለ ጊዜም ኢንጂነር በሃይሉ አሰፋ በኢትዮጵያ የኢነርጂ ዘርፍ በተለይም ተቋማቸው ኤ ኤስ ሲ ኢንጂነሪንግ በሃገራችን እያከናወነ ያለውን የፀሃይ እና ነፋስ ሃይል ማመንጫ መሰረተ ልማቶች ዝርጋታ ተግዳሮቶችና ተስፋዎች ላይ ለታዳሚዎቹ ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡
ስለ ፎሊክ አሲድ ምን ያህል ያውቃሉ ?
****************************
ሴቶች ከእርግዝና በፊትና በእርግዝና ወቅት የሚያደርጉት ጥንቃቄ ለራሳቸውም ሆነ ለሚወለደው ልጅ ጤንነት የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ በተለይም በእርግዝና ወራት የሚያደርጓቸው ነገሮች ለልጁ ጤንነት ወሳኝ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ከእነዚህ ነገሮች ውስጥ አንዱ ደግሞ ፎሊክ አሲድን በእንክብል መውሰድ ነው፡፡
ፎሊክ አሲድ ለጽንስ ዕድገት እጅግ አስፈላጊ የሆነና ከእርግዝና በፊት ለመጀመሪያዎቹ 12 ሳምንታት የሚወሰድ ንጥረ ነገር ነው፡፡ እንደሚታወቀው ሁሉም ሴቶች ለማርገዝ ሲያስቡና በእርግዝና ወቅት ፎሊክ አሲድን መውሰድ እንዲሚገባቸው ይታመናል፤ ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፎሊክ አሲድን መውሰድ ለሁሉም ሴቶች ጠቃሚ ይሆናል የሚለው ሀሳብ እንደማይሰራ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡ አንዳንድ ሴቶች ሰውነታቸው ውስጥ ያለው ጂን ለፎሊክ አሲድ ተስማሚ ላይሆን ስለሚችል ከፎሊክ አሲድ የተሻለ አማራጭ በመጠቀም ከፎሊክ አሲድ የሚገኘውን ጥቅም ማግኘት ይችላሉ፡፡
ፎሊክ አሲድና ፎሌት የሚሉት ቃላት ተቀራራቢ ትርጉም ያላቸው ሲሆኑ ሁለቱም የሚገልጹት ቫይታሚን ቢ9ን ነው፡፡ ፎሌት የተፈጥሮ ቫይታሚን ቢ9 ሲሆን እንደ ብሮኮሊ (አበባ ጎመን) እና ስፒናች ዓይነት ያሉ አረንጓዴ አትክልት ውስጥና ደረቅ ባቄላ መሳይ የቅባት እህል ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ ፎሊክ አሲድ ግን በፋብሪካ ሂደት ውስጥ አልፈው በሚታሸጉ ምግቦች ውስጥ ሰው ሰራሽ ሆኖ የሚገኝ ቫይታሚን ቢ9 ነው፡፡
ከፍተኛ የፎሌት መጠን ያላቸውን ምግቦች ዘወትር በመመገብ በቀን 200 ማይክሮ ግራም ፎሌት ማግኘት ይቻላል፡፡ ሆኖም ግን ለአንዳንድ ሰዎች ከዚህ የበለጠ የፎሌት መጠን አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፡፡ ፎሌት ወይም ፎሊክ አሲድ ጤናማ ለሆነ የጽንስ ዕድገት አስፈላጊ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ለዚህም ነው ነፍሰጡር የሆኑ ሴቶች ከመደበኛው መጠን ዕጥፍ /400 ማይክሮ ግራም ፎሊክ አሲድ/ፎሌት መውሰድ እንዳለባቸው የሚነገረው፡፡ ይህን በማድረግም በጽንስ ወቅት ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን በማስወገድ ጤናማ የሆነ ልጅ መውለድ ይቻላል፡፡ ሆኖም ግን ይህን ያህል ፎሌት አሲድ በተፈጥሮ ምግብ ውስጥ ማግኘት ከባድ በመሆኑ በተጨማሪነት በሕክምና የሚመረተውን እንዲወስዱ ይደረጋል፡፡
ምንጭ፡ medical news today
የኢንተርኔት አጠቃቀሞን/ቢዝነሶን ከደህንነት ስጋት ውጪ ማድረግ ይፈልጋሉ
*****************************************
*****************
እንግዲያውስ እንዚህን 5 ነጥቦች በሚገባ ይመልከቷቸው
በየትኛውም ሁኔታ ስራዎ ከኢንተርኔት ጋር ተያያዥነት ካለው እንደ ድረገፅ፣ የማህበራዊ ሚዲያ አካውንት እንዲሁም እንደ የኢሜል አድራሻ ያሉ የዲጂታል ሃብቶች ለስራዎ የጀርባ አጥንት መሆናቸው አይቀሬ ነው፡፡ በመሆኑም እነዚህን የዲጂታል መሳሪያዎች በሚጠቀሙበት ወቅት መረጃዎ ከርሶዎ አልፎ ወደ ሌላ ሶስተኛ ወገን ወይም ሌሎች የመረጃ መንታፊዎች ጋር እንዳይደርስ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል፡፡
አንደሚታወቀው ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ በኢንተርኔት አጠቃቀም ዙሪያ ያሉ የደህንነት ስጋቶች ከመቼውም በላይ እየጨመሩ መምጣታቸው ብዙዎችን የሚያስማማ ሃቅ ነው፡፡ በየቀኑ ከፍተኛ ጥፋት የሚያደርሱ እና በተለያዩ የሳይበር ወንጀሎች የሚሳተፉ አካለት እጅግ በረቀቁ ስልቶችና በአዳዲስ ቴክኒኮች በመታገዝ ትልቅ የሚባሉ ኮርፖሬተሮችን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት ተቋማት ድረገፆችን በመበርበርና ጥቃት በማድረስ ላይ ይገኛሉ፡፡ ታዲያ በዚህ ሁኔታ እንዚህ ትልልቅ የቢዝነስ ተቋማት ከመሰል የሳይበር ጥቃት የማያመልጡና እንደዚህ አይነት ስጋት የተጋረጠባቸው ከሆነ በመካከለኛ እና በትንንሽ የኦንላይን ቢዝነስ የተሰማሩ አካለት እጅጉን የሰፋ የደህንነት ስጋት እንደሚኖርባቸው የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ በመሆኑም ከኢንተርኔት ጋር ተያያዥነት ያለው ቢዝነስ የሚያካሂዱ ሰዎች እንዚህን አምስት ነጥቦች በሚገባ ቢያያዋቸው ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
1. አውቶማቲክ ማሻሻያዎች (Automated Updates)
አብዛኛውን ጊዜ የኦላይን ቢዝነስ የሚያካሂዱ ሰዎች የሚዘነጉት ጉዳይ ቢኖር ሲስተምን ያለማሻሻል ወይም system updates ያለማድረግ ጉዳይ ነው፡፡ ይህም በቀላሉ ሃከሮች ሲስተሙን እንዲያውቁትና የሚፈልጉትን ጥቃትም በቀላሉ እንዲፈፅሙ ያግዛቸዋል፡፡ በመሆኑም ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸውን እያንዳንዳቸውን ሴስተሞች ማለትም ኦፕሬቴንግ ሲስተምን (operating systems) ጨምሮ ሌሎች የአፕሊኬሽን ሴስተሞችን እና የድረገፅ ፕለጊኖችን (website plugins) በሚገባ እንዲሻሻሉ ማድረግ ያለባቸውን ሳንካ (bugs) እንዲያስወግዱና የዲጂታል ሃብቱም በሚገባ እንዲጠበቅ ይረዳል፡፡
2. ባለብዙ-ንብርብር ደህንነት (Multi-Layer Security)
የድረገፅ መቆጣጠሪያ ፓኔልን ለማግኘት መሞከር እና በቁጥጥር ውስጥ እንዲሆን ማድረግ ብዞዎቹ የሳይበር ጥቃት አድራሾች የሚተገብሩትና የሚጠቀሙበት መንገድ ነው፡፡ ስለሆነም የኦላይን ቢዝነስ የሚያካሂዱ ሰዎች በድረገፃቸው ላይ የሚያደርጉት ቁጥጥር እንድ ጊዜ ከእጃቸው ወቶ በሃከሮች ቁጥጥር ውስጥ ከገባ መልሶ ለማግኘት እጅግ አዳጋች በመሆኑ አጠቃላይ ቢዝነሳቸው ለአደጋ ይጋለጣል፡፡ ስለዚህም ከምንም በላይ የድረገፅ አጠቃቀም ቁጥጥርን ወይም (access control)ን ማጥበቅ እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ታዲያ ባለብዙ-ንብርብር ደህንነት ማከል እና የሚጠቀሙትን የይለፍ ቃል አይነት በማርዘምና እጅግ በተወሳሰቡ የቁጥርና የፊደላት ጥርቅም በማስገባት ለግምት እንዲከብድ ማድረግ፤ የደህንነት ስጋቱን በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሰዋል፡፡
3. የአንቲቫይረስ ፕሮግራሞች (Antivirus Programs)
ዘላቂነት ባለው ሁኔታ ኮምፒውተሮን ከተለያዩ አጥፊ መተግበሪያዎች (malwares) እና አላስፈላጊ የሆኑ መልእክቶችን ለብዙዎች የማላክ ሁኔታ (spam) በመጠበቅ የኦንላይን ቢዝነሶ ከየትኛውም የሳይበር ጥቃት ራሱን እንዲከላከል ማድረግ የአንቲቫይረስ ፕሮግራሞች ከሚሰጧቸው ጥቅሞች ውስጥ ቀዳሚው ነው፡፡ በመሆኑም እነዚህን ፕሮግራሞች በሚጠቀሙበት ወቅት ከፍተኛ ትኩረት ለሚያስፈልጋቸው ብሮውዘሮች (browsers) እና መተግበሪዎች ቅድሚያ በመስጠት ኮምፒውተሮን ከማንኛውም ቫይረስ እንዲጠብቁ ያስፈልጋል፡፡
4. የኔትዎርክ ጥበቃ
አብዛኛውን ጊዜ የኢንተርኔት ግንኙነትን በጋራ ኔትወርክ ሲጠቀሙ የሚያስተዳድሩት መረጃ ኔትወርኩን በሚጋራ ሌላ ተጠቃሚ ሊገኝና ሊደረስበት ይችላል፡፡ በተለይም በግንኙነቱ ወቅት የጠነከረ የኢንክሪፕሽን ቴክኒክ የማይኖር ከሆነ መረጃው በማንኛውም ሁኔታ ለጥቃት የመጋለጥ እድሉ ሰፊ ነው፡፡ በዚህ ረገድ እንደ ፋየርዎል (Firewall) ያሉ የኔትዎርክ ደህንነት መጠበቂያ መሳሪያዎችን በመጠቀም በኔትዎርክ ትራፊኩ ላይ የሚገቡና የሚወጡ አካለትን መቆጣጠር ይቻላል፡፡ በመሆኑም በኮንትሮል ፓኔል (Control Panel) ላይ የፋየርዎል ገፅታን በማከል የኔትዎርክ ጥበቃን ማጎልበት ያስፈልጋል፡፡
5. አጠራጣሪና የማይታወቁ ኢሜሎችን አለመክፈት
ብዙዎቹ የሳይበር ጥቃት ወንጀሎች የሚፈፀሙት የማይታወቁ ኢሜሎች በተጠቃሚዎች ሲከፈት እና መልስ (reply) ሲላክባቸው ነው፡፡ ብዙዎቹ የኢሜል ዓባሪዎች (attachments) የተለያየ ይዘት ያላቸው ቫይረሶች እና Trojan horses ይሰራጭባቸዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ታዲያ እንደዚህ አይነት ኢሜሎችበአላስፈላጊ ማህደሮች (junk folders) ውስጥ የሚከማቹ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ግን በኢሜል ኢንቦክስ (inbox) ውስጥ ሊታዩ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም ማናቸውንም አጠራጣሪ እና ማን እንደላካቸው የማይታወቁ ኢሜሎችን በቀጥታ ከመክፈት መቆጠብ ከመሰል አደጋ ራስን ያድናል፡፡
ምንጭ፡ HACK READ
ዓለምን ለማጥፋት ያልማሉ? ቁልፉ ይኸውልዎ
ለዘመናት ጨካኝ የሳይንስ ተመራማሪዎች ዓለምን ለማጥፋት የሚያስችላቸውን መንገድ ለመያዝና ተጠቅሞ በማስፈራራት ንዋይ፣ ጉልበት፣ ዕውቅና እና ክብር ማግኘትን ሲያልሙ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም ይህን ማድረግ ቀላል ተግባር አይደለም፡፡ አደገኛ የኒውክለር መሳሪያዎችን፣ ሰዎችን ሁሉ ማጥፋት የሚችል በሽታ በማሰራጨት አሊያም ከባቢ አየርን በማጥፋት ህይወት ያለውን ፍጡር ሁሉ መኖሪያ በማሳጣት ምድርን ህይወት አልባ ስፍራ ማድረግ ይቻል የሆናል፡፡ ግን ይህ ሁሉ ሆኖም ቢሆን ከስራችን ያለው ድንጋይ ህይወት አልባ ሆኖ በዛቢያው እና ፀሐይ ዙሪያ ከመሽከርከር በቀር ምንም የከፋ ጉዳት አያጋጥመውም፡፡ ታድያ እርስዎም ምድርን እስከነ ጭራሿ ለማጥፋት ከሚያልሙት አንዱ ከሆኑ ተከታዮቹን ሂደቶች መጓዝ የግድ ይልዎታል፡-
፩ኛ. ሂሳቡን በትክክል ያስሉት
ፕላኔታችን ተያይዛ ያለችው በራሷ ስበት አማካኝነት ነው፡፡ ልክ ከድንጋይ እንደተሰራ ሽንኩርት ናት፡፡ በጥልቁ የውስጣዊ ስፍራዋ የሚገኘው ኮር የተባለው አካል በላዩ ላይ ተደርቦበት የሚገኘውን ንጣፍ አጣብቆ ይይዛል፡፡ ከዚያም የሁለቱ ድምር የስበት ኃይል ተከታዩን ድርብ ንጣፍ አጣብቆ ይይዘዋል፡፡ ይሄም ተከታዩን፤ በተመሳሳይ መንገድ እያጣበቀ በመጨረሻም እኛን እና ለኑሮ የሚያስፈልጉንን ግብዓቶች ሁሉ ስቦ አስቀምጧል፡፡ ስለዚህ ምድርን ማጥፋት ከፈለጉ ይህችን የቅልጥ እና ደረቅ ድንጋይ ንብርብር የሆነች ሽንኩርት አንድ በአንድ ንጣፍ በንጣፍ መገነጣጠል እና ወደ ጠፈር እንዲቀኑ ማድረግ ይጠበቅብዎታል፡፡ ታድያ ይህ ሲሆን ወደ ጠፈር የላኩት ድንጋይ በምድር የስበት ኃይል ተጎትቶ ዳግም እንዳይመጣ ማድረጎን እንዳይረሱ፡፡ በሌላ ቋንቋ ሁሉም ቁሶች ከምድራዊ የስበት ቀንበር ነፃ ማውጣት አለብዎ፤ ግን ቀላል አይሆንልዎትም፡፡
በተለምዶአዊው መንገድ ይህን ለማድረግ ግዙፍ ሮኬቶችን ተጠቅመው የምድርን አለት አንድ በአንድ ቶን በቶን ከምድራችን ምህዋር እስኪርቁ መሸኘት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ሂደት ከምድር ላይ አንድ ኪ.ግ ድንጋይ ባጎደሉ ቁጥር የስበት ኃይሏን በአንድ ኪ.ግ ይቀንሱባታል፡፡ ስለዚህም ቀጣዩን ድንጋይ ለማሸሽ ቀላል እየሆነልዎ ይመጣል፡፡
ይህን ሂደት ተከትሎ ምድርን ለመገነጣጠል የሚያስፈልገው ኃይል እኩሌታ ታድያ ምድርን አጣብቆ ለመያዝ ከሚያስፈልገው ኃይል መብለጥ አለበት፡፡ ታድያ ምድርን ለመገነጣጠል ካሰቡ በትንሹ 10^32 ጁልስ (Joules) የሚሆን ኃይል ያስፈልግዎታል፡፡
፪ኛ. ኃይል ማሰባሰብ
ከላይ የተቀመጠው ኃይል እጅግ ብዙ ነው፡፡ ለንፅፅር እንኳን ብናይ የማገዶ እንጨት፣ ሞተር እና ኤሌክትሪክን ጨምሮ የሰው ልጅ በ2013 የተጠቀመው እያንዳንዱ ኃይል ቢደመር መጠኑ 10^20 ጁልስ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን የሰው ልጅ እየተጠቀመ ያለውን ኃይል አንድም ሳያስቀሩ እንኳን ምድርን ለመገነጣጠል ተግባር ለማዋል ከከጀሉ አስፈላጊውን ኃይል አሰባስቦ ለመጨረስ አንድ ትሪሊዮን አመታትን መጠበቅ ይኖርብዎታል፡፡ ሆኖም ይህን ማድረግ ስለማይቻልዎ (የእርስዎ ዕድሜ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የኃይል ምንጮቻችን መሰረት የሆነችው ፀሐይ እንኳን ከዚህ በኋላ የቀራት ዕድሜ አምስት ቢሊዮን አመታት ብቻ ስለሆነም ጭምር እንጂ) ከሌላ ዕቅድ እናስተዋውቅዎ፡፡
ፀሐይ የምታመነጨውን ኃይል ቢጠቀሙስ? አዎ ፀሐይ በየአንዳንዱ ሴኮንድ ውስጥ 4 ሚሊዮን ቶን የሚሆን ሃይድሮጅንን ስትጠቀም፤ በውጤቱም ወደ ሂሊየም በመቀየር ወይም ፊዩዝ በማድረግ እጅግ ከፍተኛ ኃይልን በጨረር መልክ ትለቃለች፡፡ ፀሐይ ከምታመነጨው ይህ ሁሉ ኃይል ውስጥ ቅንጣት ያህሉ ብቻ ምድር ላይ ሲደርስ ሌላው በህዋ ላይ ባክኖ ይቀራል፡፡ ምድርን ከሚነካው የፀሐይ ኃይል መጠቀም አንደኛው የኃይል ማሰባሰቢያ መንገድ ነው፡፡ ይህን አልጌዎች ከቢሊዮን ዓመታት በፊት አንስቶ እያደረጉት ያሉት ተግባር ሲሆን እኛም ቢሆን ምሳና እራታችንን የምናገኘው ከዚህ ሂደት ተነስቶ የምግብ ሰንሰለቶችን (Food Chain) በማለፍ የሚቀርብልንን ምግብ ነው፡፡
፫ኛ. የጊዜ ጉዳይ
እንደተገለፀው ምድር ላይ የሚያርፈውን የፀሐይ ኃይል ምድርን በፀሐይ ኃይል ማመንጫዎች (Solar Panels) ሸፍነዋት ሙሉ በሙሉ መጠቀም ከቻሉ ምድርን ለመበተን የሚያስችልዎትን ኃይል በ18 ሚሊዮን ዓመታት ውስጥ ማግኘት ይችላሉ፡፡ ይህ ትሪሊዮን ዓመታትን ከሚፈልገው የቀድሞው ዕቅድ አንፃር እጅግ የተሻለ ቢሆንም 18 ሚሊዮን ዓመታትን እንደማይኖሩ ግን መገመት ይቻላል፡፡ ከዚህ በተለየ ግን ፀሐይ የምታመነጨውን ኃይል አንድም ሳያባክኑ መጠቀሚያ ዘዴ ካበጁ የተሻለ ውጤት ያገኛሉ፡፡ ፀሐይ ከምታመነጨው ኃይል ውስጥ አንድ ቢሊየንኛው ብቻ ነው ምድርን የሚነካት፤ መላው የፀሐይን ኃይል መጠቀም ከቻሉ ግን ምድርን እንዲበታትኗት የሚያስችሎትን ኃይል በአንድ ሳምንት ውስጥ ብቻ ማግኘት ይችላሉ፡፡
ምንጭ፡ Space.Com
የዝሆኔ በሽታን በሚከላከሉ ምርቶች ላይ የዘጠና ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ሊደረግ ነው
**********************************************መቀመጫውን አሜሪካን ያደረገው ፈርትል ክርኤቲቭ ላብስ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ከሼዲ ግሮቭ ግሩፕ አማካሪ ተቋም ጋር በሚሰሯቸው የዝሆኔ በሽታን (Mycetoma) ተከላካይ ጓንት እና ጫማዎች ዙሪያ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት ውስጥ ውይይት አድርገዋል፡፡ በውይይቱም የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌታሁን መኩሪያ እንዲሁም የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳንዱካን ደበበን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት ተወካዮች የተሳተፉበት ሲሆን የፈርትል ክርኤቲቭ ላብስ እና ሼዲ ግሮቭ ገሩፕ ሃላፊ የሆኑት ዶ/ር ሙሉጌታ አለምሰገድ እና ዶ/ር ደረጄ ተሰማ ተገኝተውበታል፡፡ ተቋሙ በኢትዮጵያ ለማምረት ስላቀዳቸው የዝሆኔ በሽታን መከላከያዎች በዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር ሙሉጌታ አለምሰገድ አማካኝነት ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን ስለ ተቋማቸው ምንነት፣ ስለሚያከናውኗቸው ተግባራት እንዲሁም ለኢትዮጵያ ሊያመጡ ባቀዷቸው ትሩፋቶች ዙሪያ ለታዳሚዎቹ ገለፃ አቅርበዋል፡፡
ፕሮጀክቱ እነዚህን የመከላከያ ጓንት እና ጫማዎችን የዝሆኔ በሽታ በብዛት በሚታይባቸው አራት ዋና ዋና የዓለማችን ክፍሎች የሚያሰራጭ ሲሆን ኢትዮጵያም ከሌሎች የአፍሪካ ቀንድ ሃገራት ጋር በጋራ በመሆን ዞን አንድ ውስጥ ተካታለች፡፡ ታድያ የመከላከያዎቹ ቅድመ ምርት ስራዎቹ በሃገረ አሜሪካን የሚሰሩ ሲሆን የማምረት እና ማሰራጨት ተግባራቱ ግን እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ይከወናሉ፡፡ በዚህም ሳቢያ የዘጠና ሚሊዮን ዶላር መዋዕለ ንዋይ ፈሰስ ኢትዮጵያ ውስጥ ለማድረግ ታቅዷል፡፡ ይህም 1,600 የፋብሪካ ውስጥ እና 2,400 ከምርት ሽያጭ ጋር ለተገናኙ የስራ ዕድሎች መፈጠር ምክንያት እንደሚሆን ታምኖበታል፡፡ ምርቱን ተግባራዊ ለማድረግ ከተለያዩ የሃገሪቱ የምርምር እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በጋራ እንደሚሰሩ ዶ/ር ዮናታን በውይይቱ የገለፁ ሲሆን ከመንግስት አፋጣኝ የኢንቨስትመንት ፍቃድን ከማግኘት አንስቶ የተለያዩ ድጋፎች ይደረግላቸው ዘንድ ጥያቄን አቅርበዋል፡፡
ፈርትል ክርኤቲቭ ላብስ መቀመጫውን ሚሺጋን አሜሪካን ውስጥ በማድረግ የተመሰረተና እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ካሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በጋራ የሚሰራ ኩባንያ ሲሆን በምርምር እና ስርፀት ላይ ትኩረቱን በማድረግ ይንቀሳቀሳል፡፡ ሳና ብሎ የሰየማቸው የዝሆኔ በሽታን መከላከያ ጫማና ጓንቶቹም በአይነታቸው የመጀመሪያ ናቸው፡፡ እነዚህ ምርቶች ፀረ-ባክቴሪያ እና ውሃን የማያሳልፉ ከመሆናቸውም ባሻገር ምቹና ሌሎች ገፅታዎችንም አቅፈው የያዙ ናቸው፡፡ የምርት ሂደታቸውም በዋነኝነት በ3ዲ ማተሚያ ማሽኖች ላይ የተመሰረተ ነው፡፡
ከባድ አጫሾች ዓይናቸው ሊጠፋ ይችላል
***************************************
ምንም እንኳን ማጨስ በጤናችን ላይ የሚያስከትለውን ትልቅ አደጋ የሚያመላክቱ የተለያዩ ሳይንሳዊ እውነታዎችና ማረጋገጫዎች መውጣታቸውን የቀጠሉ ቢሆንም አሁንም ሰዎች ጆሮ ዳባ በሚመስል መልኩ ማጨሳቸውን ቀጥለዋል፡፡

እስካሁን ድረስ እንኳን በተረጋገጡ ጥናቶች መሰረት ማጨስ ከሚያመጣብን ከፍተኛ የጤና ጉዳት መካከል አስም፣ የሳምባ በሽታ፣ ስትሮክ እና ካንሰር በቀዳሚነት የሚጠቀሱ በሽታዎች ናቸው፡፡ ከዚህ ባለፈ ከልብ ችግር ጋር በተገናኘ በየቀኑ አንድ ሲጋራ የሚያጨስ ሰው ለልብ በሸታ የመጋለጥ እድሉ በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ታዲያ ሰሞኑን በወጣ አንድ ጥናት በከባድ ሁኔታ ሲጋራ ማጨስ ከላይ ከተጠቀሱት በሽታዎች ባሻገር ለእውርነት እንደሚዳርግ ተገልጿል፡፡ በአሜሪካ ሩትጀርስ ዩኒቨርስቲ በተከናወነው በዚህ ጥናት ተመራማሪዎች እንደገለፁት ከሆነ በቀን ውስጥ ከ20 በላይ ሲጋራዎችን የሚጨስ ሰው የዓይን መታወር ሊደርስበት እንደሚችል ገልፀዋል፡፡

ጥናቱ ላይ ከ25 እስከ 45 የሚገመቱ 71 ሰዎች በጠቅላለው የተሳፉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥም ትንሽ ቁጥር ያለቸው አልፎ አልፎ የሚያጨሱና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ደግሞ ከ20 በላይ ሲጋራዎችን በየቀኑ የሚያጨሱ እና ከሱሳቸው ማየል የተነሳ አንድም ጊዜ ለማቆም የልሞከሩ ናቸው፡፡ በዚህም መሰረት ተመራማሪዎቹ የተሳተፊዎቹን የቀለም ልየታና የዕይታ ንፅፅር ለመረዳት እንዲያስችላቸው 19-ኢንች ከሚሆን የካቶድ ሬይ መቆጣጠሪያ 59 ኢንች ርቀው አንዲቀመጡ ካደረጉ በኋላ ስቲሙሊው (stimuli) እንዲገለፅና ሁለቱም ዓይኖቻቸው እንዲመረመሩ ተደርጓል፡፡

በወጤቱም መሰረት አጥኘዎቹ እንደገለፁት በአጫሾቹ የቀለም ልየታ ላይ ሰፊ ለውጥ ማየታቸውን ተናግረዋል፡፡ በተለይም የጥናቱ ዋና መሪ ስቴቨን ሲልቨርስቲን እንደሚናገሩት በሲጋራ ውስጥ ለፍጆታ የሚውሉት የኒዩሮቶክሲክ ኬሚካሎች የአዕምሮን የዕይታ ማመዛዘኛ ሂደት በማሰተጓጎል ወይም እንቅስቃሴውን በመቀነስ አጠቃላይ የእይታ አቅምን አንደሚያዳክም ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ተመራማሪው እንደሚገልፁት ከባድ አጫሾች የዕይታ ንፅፅር አቅማቸው ሳይቀር አልፎ አልፎ ከሚያጨሱት ተሳታፊዎች አንፃር በእጅጉ እንደሚቀንስ ተናግረዋል፡፡

ምንጭ፡ Tech Explorist