TechIn2
1.22K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
ሲ.አይ.ኤ ስለ ዩፎዎች ያሉትን መረጃዎች ይፋ አደረገ
======================
የሜሪካኑ የስለላ ተቋም ሲ.አይ.ኤ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ሲሰበስብ የቆየውን ያልታወቁ በራሪ አካላት ወይም ዩፎዎችን የሚመለከቱ መረጃዎችን ይፋ አድርጓል፡፡ ይፋ ከተደረጉት ሰፊ መረጃዎች መካከል ከ2,700 በላይ ገፅ ያላቸው ከዩፎ ጋራ የተገናኙነ ሰነዶች ይገኙበታል፡፡ መረጃዎቹ ይፋ የሆኑት መሰል ሰነዶችን በሚሰበስበው ዘ ብላክ ቫውት የተሰኘው ጆን ግሪንዋልድ ጁኒየር ያቋቋመው ድረ-ገፅ አማካኝነት ሲሆን እርስዎም መረጃዎቹን ከስር በተቀመጠው ሊንክ አማካኝነት ማግኘት ይችላሉ፡፡
ለረጅም ጊዜያት ሲቀርቡለት በነበሩት ጥያቄዎች መሰረት ሲ.አይ.ኤ ዘ ዩፎ ኮሌክሽን የተሰኘ ሲዲ ላይ ቀድሞ በሚስጥር ተይዘው የነበሩ መረጃዎቹን አንድ ላይ በሲዲ አማካኝነት ሰብስቦ አስቀምጦ ነበር፡፡ ጆን ሲዲውን ከተቋሙ የገዛው ሲሆን አሁን ላይ መረጃዎቹን ድረ-ገፁ ላይ ጭኖ በመጨረሱ ማንኛውም ሰው ድረ-ገፁን በመጎብኘት መረጃዎቹን በፒዲኤፍ መልኩ ማግኘት ይችላል፡፡ ይፋ ከሆኑት መረጃዎች መካከል በአወውያኑ 1976 እኩለ ሌሊት ላይ በአንድ የሩሲያ ከተማ ውስጥ የደረሰ ምስጢራዊ ፍንዳታን እና በሌላ ጊዜ በአዘርባጃን መዲና ባኩ ሰማይ ላይ የታየ ልዩ በራሪ ነገርን የተመለከቱት ይገኙበታል፡፡
ታድያ ዩፎን የተመለከቱ መረጃዎች ይፋ ሲሆኑ ይህ የመጀመሪያው አይደለም፤ ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ላይም የአሜሪካን ባህር ኃይል በሦስት የተለያዩ ወቅቶች ቀርፆ ያስቀመጣቸውን ምንነታቸው ያልታወቁ ነገሮች በከፍተኛ ፍጥነት ሲበሩ የሚያሳዩ ምስሎችን ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ በቀጣይም ከጥቂት ወራት በኋላ የአሜሪካን መከላከያ እና የስላላ ተቋማት ኃላፊዎች ስለ ዩፎዎች ሚያውቁትን እያንደንዱን ነገር በኮንግረስ ፊት ቀርበው እንደሚናገሩ የሚጠበቅ ሲሆን ባለፈው ወርም መሰል ጉዳዮችን ለሚከታተለው የኮንግረሱ ኮሚቴ ዩፎዎቹን የሚመለከት ሪፖርት በ180 ቀናት ውስጥ እንዲቀርብለት ኮንግረስ ጠይቆ ነበር፡፡
ሲ.አይ.ኤ በዩፎዎች ዙርያ አሉኝ የሚላቸውን መረጃዎች በሙሉ ይፋ አድርጊያለው ቢልም የቀሩ ድብቅ መረጃዎች ስላለመኖራቸው ማረጋገጥ አይቻል ይሆናል የሚለው ጆን ተጨማሪ መረጃዎች ካሉም ለማግኘት እንደሚጥር ድረ ገፁ ላይ ባሰፈረው ፅሁፉ ገልጿል፡፡ አሁን ላይ ድረ-ገፁ ከ2.2 ሚሊዮን በላይ ገፅ ያላቸው ዩፎን የሚመለከት ሰነድ መያዙ ሚነገርለት ሲሆን እነዚህም ጆን የ15 ዓመት ታዳጊ ከነበረበት ከ1996 (እ.አ.አ) አንስቶ ባቀረባቸው ከአስር ሺህ በላይ ጥያቄዎች አማካኝነት ማከማቸት የቻላቸው ናቸው፡፡
የድረ ገፁ ሊንክ https://www.theblackvault.com/documentarchive/ufos-the-central-intelligence-agency-cia-collection/?fbclid=IwAR2_Caclhnjgn6QnHYFKwE7UP7PWF18jAURcpmxQbQLpK1ysAIpZVZyTjgE
የማሽተትን ስሜት ለኮምፒውተሮች
******************
ተመራማሪዎች ለኮምፒውተሮች የማሽተትን ብቃት እንዲኖራቸው የሚያደርግ የባዮሀይብሪድ ኦልፋክቶሪ ሴንሰር መስራታቸው ተሰማ፡፡ ከስሜት ህዋሳት መካከል የማሽተት ስሜት ለብዙ ህይወት ላላቸው ነገሮች ተፈጥሯዊ ስጦታ ነው፡፡ በሳይንስ ምርምር ውስጥ ከስሜት ህዋሳት ጋር የተያያዘ ከፍኛ ምርምር ተደርጓል፡፡ የኤልክትሮኒክ ቁሶች ድምጽን፣ እይታንና አካዊ ንክኪን (መስማት፣ ማየት፣ መንካት) በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ መፈጽም ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ ማሽተት አንዱ ተፈጥሯዊ ስሜት ቢሆንም ለሳይንሱ አለም ግን እጅግ አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል፡፡
ውጤት ካላገኙ እረፍት የማያቁት የዘርፉ ተመራማሪዎች የስነ-ህይወትና የኢንጅነሪንግ ክህሎቶችን በማቀናጀት ለኤሌክትኒክስ ቁሶች የማሽተት ብቃትን የሚያላብስ ባዮሀይብሪድ ግኝትን አስተዋውቀዋል፡፡ ይህ ግኝትም ሽታንና የጋዝ ውቅርን መለየት እንደሚያስችል ተነግሮለታል፡፡
ልዩ ልዩ ሽታዎችና በአየር ውስጥ የሚርመሰመሱ የተለያዩ ኬሚካሎች ስለ ከባቢ አየር ሁኔታ በጣም ጠቃሚ መረጃዎችን የያዙ ናቸው፡፡ ይሁን እንጄ ብቁ የሆነ ሴንስ ማድረጊያ መሳሪያ ባለመኖሩ ምክንያት ለከባቢ አየር ጥናት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን ማሰባሰብ አልተቻለም፡፡ በቶኪዮ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ሾጂ ታኩቺ ስነ-ህይወታዊ ፍጥረታት ሽታን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጠቀሙ ገልጸው አሁን ላይ የሚገኙትን ስነ-ህየህወታዊ ሴንሰሮች ከሰው ሰራሽ ፈጠራዎች ጋር በማጣመር ከፍተኛ የማሽተት ብቃት ያላቸው ቁሶችን ለመስራት ጥረት እንዳደረጉ ተናግረዋል፡፡
ምንጭ SciTechDaily
እቁብን ዲጂታል የሚያደርገው አዲስ መተግበሪያ
===================
እኛ ኢትዮጵያውያን አሉን ብለን ከምንኮራባቸው ባህላዊ የፋይናንስ ስርዓቶቻችን መመካከል አቁብ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል፡፡ አሁን ደግሞ ይህ ባሀላዊ የቁጠባ ስርዓታችንን ዲጂታል በሆነ መልኩ እንዲከወን የሚያደርግ መተግበሪያ ይዞ መምጣቱንና በቅርቡም ለአገልግሎት እንደሚያበቃው መተግበሪያውን የሰራው የእቁብ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂስ ይናገራል፡፡ መተግበሪው የቁጠባ ስርዓቱን ከኤሌክትሮኒክስ ክፍያ የሚያቀናጅ እንደሆነም ተነግሮለታል፡፡ ድርጅቱ መተግበሪያው ይፋ በሚያደርግባቸው ሦስት ወራት ውስጥ ብቻ ከ30 ሺህ በላይ ተጠቃሚዎችን የማፍራት ዕቅድን ይዟል፡፡
መተግበሪያው በበይነ መረብ አማካኝነት ሲሰራ እቁብተኞቹ ክፍያዎችን ከመከታተልም ባሻገር መረጃ እንዲለዋወጡ የሚያስችላቸው ይሆናል፡፡ እቁባቸውን በጊዜው ይጥሉ ዘንድ ማስታወሻ የሚልክላቸው መተግበሪያው በጊዜ የሚጥሉትንም ኋላ ላይ ማበረታቻ የሚሰጥ ይሆናል፡፡ በተጨማሪም ማን እቁቡን እንደጣለና እንዳልጣለ፣ ማን አርፍዶ ገንዘቡን እንደላከ እንደሆ መረጃ እንዲሰጥና በአካባቢያቸው ያሉ ሌሎች እቁቦችንም መፈለግ እንዲችሉ ሆኖ የተሰራ ነው፡፡ ሆኖም መተግበሪያ ተጠቃሚዎቹ ሌሎች እቁቦችን በሚቃኙበት ሰዓት እቁቡ የስንት ብር እንደሆነ ከማስመልከትና ለመቀላቀል ጥያቄ እንዲያቀርቡ ከማመቻቸት በቀር ሌሎች የእቁብ ቡድኑን መረጃዎች በሚስጥር ይጠብቃል፡፡
በመተግበሪያው እቁቦቹ ልክ እንደ ባህላዊ ስርዓቱ ሁሉ ከእቁብተኞች የሚላከውን ገንዘብ የሚቆጣጠር የየራሳቸው ሰብሳቢ ሲኖራቸው የእቁብ አወጣጡም እንዲሁ በእጣ የሚወሰን ይሆናል፡፡ ለአስተማማኝነቱ ሲባል መተግበሪያውን ለመጠቀምና እቁብተኛ ለመሆን ስም፣ አድራሻ እና የመታወቂያ ካርድ ማቅረብ ግን እንደ ግዴታ ተቀምጧል፡፡
መተግበሪያው ባህላዊው የቁጠባ ስርዓታችንን ማህበረሰባዊነቱን በጠበቀ መልኩ ወደ ዘመናዊ አሰራር እንደሚቀይረው የድርጅቱ ኃላፊዎች ይጠቁማሉ፡፡ አሁን ላይ መተግበሪያውን ከባንክ አገልግሎት ጋራ ለማስተሳሰር እና የገንዘብ ልውውጡንም ቀላል ለማድረግ ያስችል ዘንድ ከተለያዩ የባንክ ዘርፉ ባለድርሻዎች ጋራ እየተነጋገሩ መሆኑን የምትናገረው የእቁብ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂስ መስራች እና ቺፍ ቴክኖሎጂካል ኦፊሰሯ ዮሓና ኤርሚያስ ይህም በኢትዮጵያ ለሚካሄደው የፋይናንስ ቴክኖሎጂ እና ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ትልቅ አስተዋፅዖን እንደሚያበረክት ገልፃለች፡፡
ድርጅቱ መተግበሪያውን የሚጠቀሙ እቁብተኞችን ታላሚ አድርገው ከሚሰሩ ማስታወቂያዎች ይሆናል ገቢውን የሚያገኘው፡፡
ምንጭ፡ Addis Fortune እና The Reporter
ዊንዶውስ 10X ወንጀልን ለመከላከል የሚያግዝ የፀረ-ሌብነት ጥበቃ ሊታከልበት ነው
=======================
ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ማይክሮሶፍት የተሰረቁ ኮምፒውተሮች እንደገና ተስተካክለው ወይም (resetting) ተደርገው ጥቅም ላይ እንዳይውሉ የሚያስችል አዲስ የፀረ-ሌብነት ጥበቃ (anti-theft protection) በዊንዶውስ 10X ላይ እያዘጋጀ መሆኑ ተነግሯል፡፡ ይህ ዊንዶውስ የተጫነባቸው ኮምፒውተሮች የፀረ-ሌብነት ጥበቃ ሞድ ከተጨመረላቸው በኋላ የግድ በተሰጣቸው የማይክሮሶፍት አካውንት የይለፍ ቃል የሚገለገሉ ሲሆን ይህን ኮምፒውተር ዳግም ለማስጀመር የሚፈልግ ሰውም ይህን የይለፍ ቃል የግድ ማስገባት ይኖርበታል፡፡
ይህ ደግሞ ማንኛውም የተሰረቀ ኮምፒውተር እንደገና ተስተካክሎ ወይም (reset) ተደርጎ ጥቅም ላይ እንዳይውል በማድረግ የሌብነት ወንጀልን ለመቀነስ ሊያግዝ ይችላል፡፡ በዚህ ዊንዶውስ የሚገለጉ ሰዎች ንብረታቸው ቢሰረቅ እንኳን በአዲሱ ጥበቃ አማካኝነት ኮምፒውተራቸውን በማንኛውም ቦታ ሆነው መቆለፍ የሚያስችላቸው ሲሆን፤ ጎግል ባቀረበው ‘Find my device’ በተባለው የመፈለጊያ አማራጭ ደግሞ የኮምፒውተሩን መገኛ ሊረዱ ይችላሉ፡፡
የማይክሮሶፍት ባለሙያዎች እንደጠቀሱት አዲሱ የፀረ-ሌብነት ጥበቃ አሁን ላይ ሊሰራበት የታሰበው የዊንዶውስ አይነት መደበኛው ዊንዶውስ 10 ሳይሆን በሱ ቨርዥን በቀረበው ዊንዶውስ 10X ላይ የሚሰራ ሲሆን ወደፊት በሌሎች የዊንዶውስ አይነቶች ላይ የመተግበር እቅድ እንዳለም አስረድተዋል፡፡
ዊንዶውስ 10X አሁን ላይ ባለሁለት ስክሪን ባላቸው የኮምፒውተር አይነቶች ላይ እየተሞከረ ያለ ቢሆንም ወደፊት በሌሎች መደበኛ የላፕቶፕ አይነቶች እና የኮምፒውተር ዝርያዎች ላይ የመጠቀም እድል ሊኖር ይችላል፡፡
ምንጭ፡ Tech Radar
ቴክ-ሳይንስ መፅሔቶችን ለናንተው
================
ቀድሞ በየ ሦስት ወሩ ትወጣ የነበረው የቴክ ሳይንስ መፅሔት ካለፈው ዓመት አንስቶ እንደ አዲስ ከተዋቀረች በኋላ የወጡት ቅፅ 18 እና 19ኝን መፅሔቶችን እንካችሁ ብለናችኋል፡፡
በተለያዩ ዓምዶች ተዘጋጅተው የቀረቡት መፅሔቶቹ የተለያዩ ኢትዮጵያውያን ፈጠራ ሰዎችን፣ የሀገራችን የተፈጥሮ ሐብት፣ የፖሊሲ ሁኔታዎች እንዲሁም ልዩ ልዩ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ውጤቶችን የሚዳስሱ ፅሑፎችን ያካተቱ ናቸው፡፡
በመፅሔቶቹ ከተካተቱት ውስጥ በቅፅ 18፤ በፕላስቲክ አጠቃቀማችን ላይ ከኢንዶኔዢያ የምንማረው ጉዳይ፣ ፕሮፌሰር ተከተል፣ አስደናቂው የሶፍ ኡመር ዋሻ፣ የቴሌፎን ቴክኖሎጂ ታሪካዊ ዳራ፣ የማይቻል ሚመስለውን ሰርቶ ያሳየን የፈጠራ ሰው፣ ግብርና ተኮር ሚቲዎሮሎጂና ኢትዮጵያ እና አነስተኛ ሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል በኢትዮጵያ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በቅፅ 19 ላይም ባዮስፌር ሪዘርቭ በአለም ያለው አንድምታ፣ ፕሮፌሰር ኢሳያስ፣ ቢግ ዳታ እና የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ፣ ያልታወቁ በራሪ አካላት (ዩፎ)፣ የፈጣሪዎች ስነ-ልቦና፣ አፍሪካና ቴክኖሎጂ፣ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ስርዓት፣ እንዲሁም ከወዳዳቁ ፕላሰቲኮች የጫማ ቀለም የሰራው ኢትዮጵያዊ እና ሌሎች ጉዳዮችን ይዘንልዎ ቀርበናል፡፡
በተጨማሪም በቀድሞ መልክ ከተዘጋጁት መፅሔቶች የመጨረሻው የሆነውን ቅፅ 17ን መመልከት ይችላሉ፡፡
ታድያ እርስዎም መፅሔቱን በተቀመጠው ሊንክ አማካኝነት ወደ ድረ-ገፃችን በማምራት ማውረድ ይችላሉ፡፡
ቴክ-ሳይንስ ቅፅ 17፤ http://techin.gov.et/post/632/
ቴክ-ሳይንስ ቅፅ 18፤ http://techin.gov.et/post/633/
ቴክ-ሳይንስ ቅፅ 19፤ http://techin.gov.et/post/634/
መልካም ንባብ !!!
TechIn2 pinned a photo
ቴክ-ሳይንስ ሳምንታዊ የቴሌቪዥን ፕሮግራም፤ በዛሬው መሰናዶም
===================
ስለ ፓርኪንሰን የተዘጋጀውን በአብይ ፕሮግራም (ክፍል ሁለት)፤
ኮምፓስን በቴክኖሎጂ ታሪክ፤
አካባቢ እና ደን ምርምር ኢንስቲትዩትን በተቋማት፤
ፕ/ር ዘመደ አስፋውን በተመራማሪዎች ታሪክ (ክፍል አራት)፤
እንዲሁም የቧንቧ ውሃ ሲመጣ የማሳወቂያ መልዕክት የሚሰጥ ፈጠራ ያበረከተልን ታዳጊን በብላቴናት ዝግጅቶቻችን ይዘንላችሁ እንቀርባለን፡፡
እነዚህን ለእርስዎም ሆነ ልጆችዎ የሚጠቅሙ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ተኮር ዝግጅቶች ከስኮላርሺፕ ጥቆማ ጋር በማዳበል ዛሬ ቅዳሜ በ10 ሰዓት በMOE ቲቪ ይዘንልዎ እንመጣለን፡፡ በተጨማሪም እዚሁ ጣብያ ላይ ማክሰኞ 10 ሰዓት ስለሚደገም ያመለጥዎትን መከታተል ይችላሉ፡፡
የዩትዩብ ቻናላችንንም (https://www.youtube.com/channel/UC6jvUOLRSkVEQtc5Annfwvg) ሰብስክራይብ በማድረግ ከዓመታት በፊት ከተላለፈው የመጀመሪየው ክፍል አንስቶ ያሉትን ሁሉንም የቴክ ሳይንስ ፕሮግራሞች አንድ በአንድ መመልከትና ዕውቀትን መገብየት ይችላሉ፡፡
TechIn2 pinned a photo
ስለ ሰው ሰራሽ እግሮች አዲስ ነገር
*******************
የሰው ልጅ ባልተጠበቀ አጋጣሚም ይሁን በልዩ ልዩ አደጋዎች ምክንያት የተለያዩ የአካል ጉዳቶች ሊደርስበት ይችላል፡፡ ታዲያ እነዚህ የአካል ጉዳቶች አንዳንዶቹ እንደ ተፈጥሯዊው ባይሆንም ሰው ሰራሽ ምትኮች ይሰራላቸዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የተሻለ አገልግሎት የሚሰጠውና ጥሩ ተደራሽነት ያለው ሰው ሰራሽ እግር ነው፡፡ እዚህ ላይ ይህ ሰው ሰራሽ እግር ከሚሰጠው ጥቅም በተቃራኒው የሚነሱበት የተለያዩ ችግሮች መኖራቸውን ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ ከችግሮቹ መካከል እግሩ ከብረትና ከተለያዩ ቁሶች የተሰራ በመሆኑ በቀላሉ የማይታዘዝና ከአእምሮ ሀሳብና የእንቅስቃሴ ፍላጎት ጋር የማይገናኝ በመሆኑ ለመንቀሳቀስ እጅግ አስቸጋሪ መሆኑ ነው፡፡
ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለሰው ልጆች ከሚሰጧቸው ጥቅሞች መካከል እንደዚህ ለአጠቃቀም ምቹ ያልሆኑ መገልገያዎችን ሰዎች በቀላሉ መጠቀም እንዲችሉ የሚያግዙ የተለያዩ ምርምሮችን መስራት ነው፡፡ ዘመናዊው ሳይንስ ከእግር ማጣት ጋር በተያያዘ ለችግሩ ተጠቂዎች በልዩ ልዩ ጊዜያ የተለያዩ መፍትሔዎችን ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡
በዙሪክ በሚገኘው የሲዊዝ የፌዴራል ቴክኖሎጂ ምርምር ተቋም የሚሰሩ ተመራማሪዎች ሰው ሰራሽ እግሮችን ከጉዳተኛው ስርዓተ ነርቭ ጋር ማገናኘት እግሮቹን ቀላልና ታዛዥ እንደሚያደርጋቸው ማረጋገጥ ችለዋል፡፡ እዚህ ላይ ያለው መሰረታዊው ነገር እጅግ አስደናቂ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ምንም ከባድና አስቸጋሪ ቢሆኑም ሰው ሰራሽ እግሮች የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡
ለመቆምና ለመንቀሳቀስ የሚያስችሉት ሰው ሰራሽ እግሮች ከስርዓተ ተውነት ጋር የተቆራኙበት ምንም አይነት መንገድ ስለሌላቸው እንደ ተፈጥሯዊው እግር ግብረ-መልስ አይሰጡም፡፡ ከላይ በተጠቀሰው የምርምር ተቋም የተሰራው ግኝት ይህን ችግር መቅረፍ የሚያችል እንደሆነ ተነግሮለታል፡፡ ተመራማሪዎች ሰው ሰራሽ እግሮችን ከስርዓተ ነርቭ ጋር በማገናኘት ተፈጥሯዊ እግር የሚሰማውን ስሜት እንዲሰማቸው ማድረግ የሚያስችል መንገድ ነው ያገኙት፡፡ የህንንም የተወሰኑ የተጠቃሚውን ነርቭ ሴሎች ሰው ሰራሽ እግሩ ካሉት ሴንሰሮች ጋር በማገናኘት እንደሆነ ታውቋል፡፡
በሙከራ ወቅት ተመራማሪዎቹ የምርምሩ ተሳታፊ በሆኑ ሰዎች ላ የተለያዩ ሙከራዎችን አድገዋል፡፡ ከዚህም መካከል ኒውሮ ፊድባኩን በማብራትና በማጥፋት በተሰራ ሙከራ የሰው ሰራሽ እግሩ ክብደት ኒውሮ ፊድባኩ ሲበራ በ23 በመቶ መቀነስ ችሏል፡፡
ምንጭ Technology.Org
የፊት መልክን በማየት ብቻ የፖለቲካ አስተሳሰብን የሚለየው አዲሱ ቴክኖሎጂ
=========================
በስታንፎርድ ኒቨርሲቲ የሚገኝ አንድ የአጥኚዎች ቡድን የሰውን የፊት ገፅታ የሚያሳይ አንድ ምስልን በመመልከት ብቻ የዛን ሰው የፖለቲካ አሰላለፍ በ70 በመቶ ስኬት ማወቅ የሚችል የሰው ሰራሽ አስተውሎት ስርዓትን መስራት ችለዋል፡፡
ብዙውን ጊዜ በተለይም በምርጫ ሰሞን ሰዎች ፖለቲካዊ አመለካከታቸውን የሚያንፀባርቁ ከኔቴራ ወይም ኮፍያ መልበሳቸው የተለመደ ቢሆንም ለራሳቸው እንኳን በማይታወቃቸው ሁናቴ በፊት ገፅታቸው አማካኝነት የፖለቲካ ዕይታቸውን እንደሚገልፁ የጥናት ቡድኑ በሳይንቲፊክ ሪፖርትስ ጆርናል ላይ በሰጠው ማብራርያ ይገልፃል፡፡
አዲሱ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ስርዓት ልክ እንደሌሎች መሰሎቹ ሁሉ የሰው ልጆች ብዙም የማያስተውሏቸውን አዳዲስ መረጃዎች እንዲሰበስብ ተደርጎ የተሰራ ነው፡፡ አጥኚዎቹ ታድያ ውሃ አጣጭን ከሚያገናኙ ድረ-ገፆች የፕሮፋይል ምስልን እና ፖለቲካዊ አመለካከታቸውን የሚጠቁም መረጃ ወስደው ስርዓቱን በማለማመድ የሰዎች የፖለቲካ አመለካከት ከፊት ገፅታቸው አኳሀን እና የጭንቅላት አቀማመጣቸው ጋር ያለውን ግንኙነት እንዲረዳ ለማድረግ ጥረዋል፡፡ ወደ ኋላ ስርዓቱን ምስሎችን በመስጠት ብቻ ሰዎቹ ወግ አጥባቂ አልያም ሊበራል መሆኑን መጠቆም ይችል እንደሆን ሲሞክሩትም ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑትን በትክክል መገመት መቻሉን ተረድተዋል፡፡
አጥኚዎቹ ስርዓታቸው በምን ምለኩ የፊት ገፅታ አኳሀንን በመጠቀም የፖለቲካ እምነትን መለየት እንደቻለ እርግጥ የሆነ ምላሽ ማግኘት ባይችሉም እንደ ጭንቅላት አቀማመጥ/አዟዟር እና ስሜት አገላለፅ ያሉ የተወሰኑ ነገሮችን ግን ለማወቅ ችለዋል፡፡ ለምሳሌ ቀጥታ ወደ ካሜራው ፊታቸውን ያዞሩ ሰዎች በይበልጥ ሊበራል የመሆን እድላቸው የላቀ መሆኑን ተረድተዋል፡፡ በሌላ መልኩ የተቃውሞ አይነት መልክ የሚያሳዩት ደግሞ ወደ ወግ አጥባቂነት ያደሉ ሆነው አግኝተዋቸዋል፡፡
አጥኚዎቹ ከግለሰብ መብት ጋራ በተያያዘ ለጥናቱ የተጠቀሙባቸውን ምስሎች ለማጋራት ባለመቻላቸው ሳብያ ሌሎች እነርሱ ባሳዩት ልክ ውጤታማ የመገመት ተግባርን ማከናወኑ አዳጋች እንደሚሆንባቸው ተናግረዋል፡፡
ምንጭ፡ Tech Xplore
ልዩ የዚንክ ባትሪ በአዲስ ቀመር
*****************************
የባትሪ ፍላጎትን ለማሟላት የተዘጋጀ በዘርፉ ተመራማሪዎች የተበረከተ የዚንክ አየር ባትሪ የወደፊቱ ተመራጭ ባትሪ እንደሚሆን ተነገረ፡፡ አለማቀፍ የሆነ የምርምር ጥምረት ከፍተኛ ብቃት ያለው፣ ለአካባቢ ተስማሚ የሆነ፣ ምቹና በተመጣጣኝ ዋጋ ሊቀርብ የሚችል የወደፊቱ ተመራጭ ባትሪን በዚንክ አየር መስራታቸው ታውቋል፡፡
እስከ ዛሬ ድረስ ያለው የዚንክ አየር ባትሪ ከፍኛ ኬሚካዊ አለመረጋጋት የሚታይበትና የተለያዩ ችግሮች የሚታዩበት የነበረ ነው፡፡ አዲሱ የሀይል ማከማቻ ባትሪ ግን ከአልካላይን የጸዳ በመሆኑ ከዚህ በፊት የነበሩትን ችግሮች በሙሉ የቀረፈ ነው፡፡
ተመራማሪዎቹ የምርምር ውጤታቸውን ባሳወቁበት ወቅት ግኝቱ ከአልካላይን የጸዳ ኤሌክትሮላይት የበፊቱን ዚንክ ፐርኦክሳይድ ወደ ዚንክ አየር ባትሪ መለወጥ ያስቻለ ነው ብለዋል፡፡ የዚንክ አኖድ በከፍተኛ ኬሚካዊ መረጋጋትና ኤሌክትሮ ኬሚካል ሪቨርሴብሊቲ በጥሩ ሁኔታ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል፡፡ አንዴ የተሞሉ የዚንክ አየር ባትሪዎች ለ320 ዙሮች እና ለ1600 ሰዓታት ያክል ግልጋሎት ሊሰጡ ይችላሉ፡፡
ይህ ቴክኖሎጂም ከበፊቱ የተሻለ ለአካባቢ ተስማሚ እንዲሁም ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸው የሀይል ማከማቻ ባትሪዎች እንዲኖሩ ያስችላል ሲሉ ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል፡፡ ምርምሩም በሙንስተር ዩኒቨርሲቲ ተጨማሪ ጥናቶች እየተካሄዱበት ሲሆን በሻንጋዩ ፉዳን የኒቨርሲቲ፣ የውሃን ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲና የአሜሪካ ጦር የምርምር ቤተ-ሙከራ ትብብር የተሰራ ነው፡፡
ምንጭ SciTechDaily
ዘርፎ መደራደርን የለመዱት አስገራሚ ጦጣዎች
================
በኢንዶኔዢያው ኡሉዋቱ የሂንዱ ቤተ እምነት የሚገኙ ማፊያ ጦጣዎች ሌብነት ምትክ የለሽ ስራቸው ሆኖላቸዋል፡፡ በጥንታዊው ቤተ-መቅደስ ዙርያ ኑሮዋቸውን ያደረጉት ጦጣዎቹ ያልጠረጠረ ወይም ሚነገረውን ያልሰማ ሀገር ጎብኚ ሲያገኙ በመዝረፍ እና እቃውን በማስያዣነት አስቀምጠው ምግብን በመጠየቅ ዕውቅናን አትርፈዋል፡፡ በቅርብ የተሰራ ጥናት ደግሞ እነዚህ ጦጣዎች በአስገራሚ ሆኔታ ሀገር ጎብኚዎቹ ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጧቸው እቃዎችን በመለየት ከዝርፊያቸው የሚያገኙትን ትርፍ ለማሳደግ እንደሚሰሩ አመላክቷል፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው ሰዎች ያን ያህል ዋጋ ማይሰጧቸው እንደ ፀጉር ማስያዣና የካሜራ ማስቀመጫ ቦርሳ ያሉትን በመተው መሰረቃቸው ሊያሳብዱ የሚደርሱትን እንደ ዋሌት፣ ሞባይል ስልክ፣ በሀኪም የታዘዙ መነፅሮችን ይዘው ይፈተለካሉ፡፡
የጥኛት ቡድኑ ለዘጠኝ ወራት ያህል የጦጣና ሀገር ጎብኚዎቹን ግንኙነት በምስል ቀርፆ ሲመለከት ከቆዩ በኋላ ነው ጦጣዎቹ የሰረቁት እቃ ዋጋው ከፍ ባለ ቁጥር የሚጠይቁት ምግብ ብዛትንም እንደሚያሳድጉ ማረጋገጥ የቻለው፡፡ ቡድኑ መመልከት እንደቻለው ጦጣዎቹ የሰረቁትን እቃ አስመልክቶ ከቤተ-እምነቱ ሰራተኞች እና ሀገር ጎብኚዎቹ ጋር ሚያደርጉት ድርድር እስከ ግማሽ ሰዓት ሊወስድ ይችላል፡፡ በቆይታቸው ከተመለከቱት ውስጥ አድን እቃ ለማስመለስ የወሰደው ረጅሙ ጊዜ 25 ደቂቃ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 17 ደቂቃው በድርድር የጠፋ ነው፡፡ ሆኖም የሰረቁት ዕቃ ዋጋው አነስተኛ ከሆነ አነስተኛ ምግብን ተቀብለው ድርድሩን በስኬት ለመዝጋት ፍቃደኛ ናቸው፡፡ አዲሱን ጥናት ከሌሎች መሰል ባህርይን ካመላከቱ ጥናቶች ለየት የሚያደርገው ጦጣዎቹ ነገሮች ተመጥነው በሚገኙበት በቤተ-ሙከራ ውስጥ የሚኖሩ ሳይሆን እንደ ፍቃዳቸው የሚንቀሳቀሱ ራስ ገዝ ዱር አዳሪዎች መሆናቸው ነው፡፡
እንደ ጥናቱ ከሆነ ጦጣዎቹ ይህን መሰል ባህርይን የሚያዳብሩት 4 ዓመት ዕድሜ ላይ እስከሚደርሱ ባለው የታዳጊነት ዘመናቸው ውስጥ ነው፡፡ መስረቅ እና የሰረቁትን ለድርድር ማቅረባቸው ደግሞ የብልህነት ባህላቸው መገለጫ መሆኑን የሚናገሩት የጥናቱ መሪና በካናዳው የሌዝብሪጅ ዩኒቨርሲቱ የስነ-ልቦና ረዳት ፕሮፌሰር የሆነው ዦን-ባፕቲስ ሌካ ባህርዩን ላፉት ሦስት አስርት ዓመታት በባህላቸው ውስጥ ሲማሩትና ከትውልድ ትውልድ ሲያስተላልፉት የቆየ መሆኑን ገልጿል፡፡
በኡሉዋቱ ሀገር ጎብኚዎች በቤተ-እምነቱ ዙርያ ካሉት ቀማኛ ጦጣዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት መልካም ለማድረግ የሚሰሩ ሰዎች ያሉ ቢሆንም ሌሎች ቦታዎች ግን ለዚህ ባለመታደላቸው በጦጣዎች እና የሰው ልጆች መካከል ያለው ፍቅር አልባ ግንኙነት እየተካረረ ሄዷል፡፡ ለምሳሌ በህንድ የሚገኙ ራስ ገዝ ጦጣዎች የገበሬዎችን ማሳ በመብላት፣ መንደርና ከተሞችን በመውረር ባስ ሲልም የኮሮና ቫይረስ ተመርማሪዎችን የደም ናሙና የያዙ የጤና ባለሙያዎችን በቡድን ማጥቃት ውስጥ ተሰማርተዋል፡፡ በሌሎች የዓለማችን ስፍራዎችም የኮቪድ-19 ወረርሺኝ ተከትሎ የሚበሉትን በማጣታቸው ሳብያ ከሰው ልጆች ጋር ተጠጋግተው የሚኖሩ ጦጣዎችን ጠብ አጫሪና ከቀን ወደቀንም አብሮ ለመኖር አስቸጋሪ ሆነዋል፡፡
ምንጭ፡ The Guardian