TechIn2
1.22K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
20ዎቹ የምንግዜም ታላላቅ ኢኖቬሽኖች
…….የቀጠለ
11. ስልክ (TELEPHONE) - የስኮትላንድ ተወላጁ አሌግዛንደር ግርሃም ቤል በሰው ልጆች የመገናኛ ጥበብ ውስጥ ትልቅ አብዮት የፈጠረውን የስልክ ቴክኖሎጂ በራሱ ስም ያስመዘገበ ታላቅ የፈጠራ ባለሙያ ቢሆንም ከሱ ቀደምና እሱ በነበረበት ዘመንም ብዙ የፈጠራ ባለሙያዎች ለቴክኖለጂው ማበብ የራሳቸውን አሻራ ጥለዋል፡፡ አሌግዛንደር ግርሃም ቤል አንደአውሮፓውያኑ በ1876 በኤሌክተሪክ ስልክ የመጀመሪያውን ፓትንት ካገኘ በኋላ የሰው ልጆች እርስ በእርስ የመገናኘት ልምድ እስወዲያኛው ተቀይሯል፡፡
12. ክትባት (VACCINATION) - የክትባት ግኘት ለአንዳንዶች አከራካሪ ፈጠራ ቢሆንም ብዙዎች እንደሚገልፁት ከሆነ ግን በአለም ላይ የተከሰቱ በሽታዎችን በማጥፋት እና የሰው ልጆችን በመታደግ በኩል እስካሁን ከታዩ አስደናቂ ግኝቶች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው፡፡ በአለማችን ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰራው ክትባት እንደአውሮፓውያኑ በ1796 ለፈንጣጣ (smallpox) በሽታ የተሰራው ክትባት ሲሆን ኤድዋርድ ጄነር በተባለ ተመራማሪ የተገኘ ነው፡፡ ከዚህ ክትባት በኋላ በ1885 በፈረንዊው ኬሚስትና ባዮለጂስት ሊዩስ ፓስተር የተሰራው የሬቢስ (rabies) ቫይረስ ክትባት ደግሞ ለዘመናዊው የመድሃኒት ቴክኖሎጂ ትልቅ በር የከፈተ ነበር፡፡
13. መኪና (CARS) - ተሽከርካሪ መኪናዎች የሰዎችን የጉዞ ስርዓት እና ተያይዞ የመጣውን የከተሞች ባህሪ እስከወዲያኛው የቀየረ ግሩም የቴክኖሎጂ ፈጠራ ነው፡፡ ተሽከርካሪ መኪናዎች በዘመናዊው ቅርፃቸው በአለም ላይ ብቅ ማለት የጀመሩት በ19ነኛው ክፍለ ዘመን የመጨረሻ አመታት ላይ ሲሆን በዋናነት በጀርመናዊው ካርል ቤንዝ እና ባልደረቦቹ የተከናወኑ ናቸው፡፡ ካርል ቤንዝ እንደአውሮፓውያን አቆጣጠር በ1885 የመጀመሪያዋን ሞተር ብስክሌት ተግባራዊ ካደረገ በኋላ የመኪና ቴክኖሎጂ በአለም ላይ እየናኘ ሄዷል፡፡
14. አውሮፕላን (AIRPLANE) - በ1903 በአሜሪካውያን ወንድማማቾች ለውጤት የበቃው ይህ አስገራሚ ቴክኖሎጂ የሰው ልጆችን የረዥም ርቀት ጉዞ ፈጣን አማራጭ በመስጠት የትራንስፖረት ኢንዱስትሪን እስከወዲያኛው የቀየረ ነው፡፡ የአውሮፕላን ቴክኖሎጂ የአለም ሰዎችን ይበልጥ እንዲቀራረቡ በማድረግ የባህል፣ የምጣኔ ሃብት እና የእውቀት ልውውጦችን ይበልጥ ያዳበረ ቢሆንም በቴክኖሎጂው የማብሰሪያ ጊዚያት በአለም ላይ ለተከሰተው አለምአቀፍ ጦርነት ሌላ አባባሽ ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
15. ፔኒሲሊን (PENICILLIN) - እንደአውሮፓውያኑ በ1928 በስኮትላንዳዊው ሳይንቲስት አሌክዛንደር ፍሌሚንግ የተቀመረው ይህ ግኘት የፋርማሲዩቲካል ዘርፉን አንድ እርምጃ በማራመድ የመጀመሪያውን አንቲባዮቲክ መድሃኒት ለአለም ያስተዋወቀ ነው፡፡ ፔኒሲሊን እጅግ ብዛት ያላቸው ተላላፊ ባክቴሪያዎችን በመከላከል ለረዥም ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለ አንቲባዮቲክ ሲሆን ለዘመናዊው የመድሃኒት ቴክኖሎጂም ፈር ቀዳጅ የሚባል ነው፡፡
16. ሮኬቶች (ROCKETS) - ቀደምት የሚባለው የሮኬት ቴክኖሎጂ ሙከራ በቻይና የስልጣኔ ዘመናት እንደነበር የሚያወሱ የታሪክ ማዛግብቶች ቢኖሩም አሁን ላይ የሚታወቀው ዘመናዊ የሮኬት ቴክኖሎጂ ግን በ20ኛው ክፍለ ዘመን የተዋወቀ ነው፡፡ ይህ ግኝት በሰው ልጆች የህዋ ምርምር እና የጠፈር አሰሳ ላይ ትልቅ አበርክቶት የነበረው ፈጠራ ሲሆን በወታደራዊው ዘርፍም የማይናቅ አስተዋፅኦ ያለው ነው፡፡
17. የኒውክለር ማብሊያ (NUCLEAR FISSION) - አተሞችን ይበልጥ ጥቃቅን ወደሆኑ ቅንጣቶች መከፋፈል እና በዚህም ከፍተኛ መጠን ያለው ኢነርጂ የመፍጠር ሂደት የኒውክለር ኃይል ማመንጫዎች እና አቶሚክ ቦምቦች እንዲፈጠሩ አስችሏል፡፡ ይህ አስገራሚ ግኘት በ20ኛው ክፍለ ዘመን በዚህ ዘርፍ ዙሪያ ሲሰሩ በነበሩ ስመጥር የፊዝክስ ሊቃውንት የተከናወነ ቢሆንም የኒውክለር ማብሊያውን በዋናነት በመስራት ረገድ ጀርመናውያኑ ኦቶ ሃን እና ፍሪትዝ ስታስመን አንዲሁም የኦስትሪያ ተወላጅ የሆኑት ሊዝ ማይትነር እና ኦቶ ፍሪሲች በቀዳሚነት ይጠቃሳሉ፡፡
18. ሴሚኮንዳክተሮች (SEMICONDUCTOR) - የአሜሪካ ወይም የአለም የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ማዕከል ከሆነችወ ሲልከን ቫሊ ቅጽል ስም ጀርባ የሚገኘው የሴሚኮንዳክተር ግኘት ብዙ ነገሩ ከሲልከን የተሰራ ሲሆን የአፈጣጠር ሁኔታውም በኤሌክትሪክ ዘመን እና እየመጣ በሚገኘው ዲጂታል ዘመን መካከል ላይ ነበር፡፡ የመጀመሪያው የሴሚኮንዳክተር ቁስን የያዘ መሳሪያ እንደአውሮፓውያኑ በ1947 የተዋወቀ ሲሆን በአሜሪካውያኑ ጆን ባርደን እና ዋልተር ብራታን የተሰራ ነው፡፡
19. የግል ኮምፒውተሮች (PERSONAL COMPUTER) - አንደአውሮፓውያኑ በ1970ዎቹ የተፈጠሩት የግል ኮምፒውተሮች የሰው ልጀችን ሁለንተናዊ አቅም በማሳደግ በኩል ተወዳዳሪ አልነበራቸውም፡፡ በ1974 በማይክሮ ኢኒስትሩመንቴሽን እና ቴሌሜትሪ ሲስተም (MITS) የመጀመሪያ የሚባለው የግል ኮምፒውተር ከተዋወቀ በኋላ ቀጥለው የመጡት እንደ አፕል፣ ማይክሮሶፍት እና አይ ቢ ኤም ያሉ ግዙፍ ኩባንያዎች ዘርፉን እስከወዲያኛው አራቀውታል፡፡
20. በይነ መረብ (INTERNET) - አሁን አሁን የሰው ልጅ እስትንፋስ እስከመሆን የደረሰው ይህ አስገራሚ ግኘት ከ1960ዎቹ ጀምሮ ሙከራዎች ሲደረጉበት የቆየ ቢሆንም አሁን በምናውቀም መልኩ ለሰው ልጆች መድረስ የጀመረው ከ1990ዎቹ ጀምሮ ነው፡፡ በጊዜው አንግሊዛዊው ቲም በርነር-ሊ የመጀመሪያውን የበይነ መረብ መግባቢያ የአለም አቀፍ ድር (WWW) ከቀመረ በኋላ አጠቃላይ የአለም መልክ ሊቀየር ችሏል፡፡ ከዚህ ጊዜ አንስቶ ንግዳችን፣ ፖለቲካችን፣ መዘናኛችን የፈለጋችሁን ስም ስጡት ብቻ ሁለ ነገራችን በኢንተርኔት እና በኢንተርኔት ሁኗል፡፡
ምንጭ፡ Bigthink
ውድ የፔጃችን ተከታዮች የቀደመውን ክፍል ወደኋላ ተመልሰው ማየት ይችላሉ
የማያ ህዝቦች የቀን አቆጣጠር
************
የማያ ህዝቦች ሜሶአሜሪካዊ ህንዳውያን ሲሆኑ ግዛታቸውም በተከታታይ ደቡዳዊ ሜክሲኮ፣ ጓቲማላ እና ሰሜናዊ ብራዚል ነው፡፡ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መግቢያ አካባቢ 30 የሚደርሱ የእነዚህ ህዝቦች ቋንቋዎች ከ5 ሚሊዮን በሚበልጡ ሰዎች ይነገሩ ነበር፡፡ ከእነዚህ መካከልም አብዛኛዎቹ በተጨማሪነት የስፓኒሽ ቋንቋ ተናጋሪዎች ናቸው፡፡
እነዚህ ህዝቦች ስፔን ሜክሲኮንና ማእከላዊ አሜሪካን ከመውረሯ በፊት የምእራብ ንፍቀ ክበብ ታላቅ ስልጣኔ ባለቤቶች እንደነበሩ ይነገራል፡፡ ከስልጣኔያቸው መገለጫዎች መካከል እንደ ግብርና፣ የድንጋይ ህንጻዎች፣ የፒራሚድ ቤተ መንግስቶች፣ የወርቅና የብር ስራ እንዲሁም ስዕላዊ ጽሁፎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
የማያ ህዝቦች ከሚታወቁባቸው የስልጣኔ መገለጫዎች አንዱ የዘመን አቆጣጠራቸው ነው፡፡ የቀን አቆጣጠራቸውም 260 የራሳቸው ስም ያላቸው ተከታታይ ቀናትና 365 ቀናት ያሉት አመትን ያካተተ ነው፡፡ የረጅም ጊዜ ዑደት ያለው የ18 ሺ 980 ቀናት ወይም የ52 አመታት አቆጣጠር ሲኖራቸው ይህንንም የዙር ቀን ቆጠራ ወይም ካላንደር ራውንድ ብለው ይጠሩታል፡፡
የ260ው ቀናት የመጀመሪያ ስም በጊዜ ሂደት እንደጠፋ የሚታመን ሲሆን በብዛት ትዞለኪን(Tzolkin) የሚል ስያሜ እንደነበረው ነገራል፡፡ ትርጓሜውም የቁጥር ቀን፣ ተከታታይ የቀን ቆጠራ የሚል ነው፡፡ ትዞልኪን በሚባለው አቆጣጠር ሁለት ንዑሳን ዑደቶች ያሉ ሲሆን የመጀመሪያው ከ1 እስከ 13 የሚደርስ የቀናት ዙር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የ20 የየራሳቸው ስም ያላቸው ቀናት ክትትል ነው፡፡
በማያ ህዝቦች የቀን አቆጣጠር ውስጥ የሚገኙት የአንድ አመት 365 ቀናት 20 ቀናት ባላቸው በ18 ወራት እና አንድ ባለ አምስት ቀናት ስም አልባ ወር የተከፋፈሉ ናቸው፡፡ እነዚህ ስም አልባ አምስት ቀናት በማህበረሰቡ ዘንድ የእድለቢስነት ምልክት ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡ እንደ ታሪክ ተመራማሪዎች እይታ የማያ ህዝቦች ረጅሙ የዘመን አቆጣጠር መነሻው ነሐሴ 11፣ በ3111 ከልደተ ክርስቶስ በፊት እንደሆነ ይታመናል፡፡ ይህም ቀን የረጅሙ የቀን ቆጠራ የመጀመሪያ ቀን ነው፡፡ ይህ ቀን ለባለ 5125 አመታቱ ታላቁ ዑደት መነሻም እንደሆነ ይነገራል፡፡
የታላቁ ዑደት መጨረሻ ታህሳስ 21 2012 በፈረንጆች አቆጣጠር ይሆናል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ከዛሬው የጁፒተር፣ ሳተርንና ፕሉቶ መቀራረብ ጋር ተያይዞ እለቱ ዛሬ ሊሆን እንደሚችልና አቆጣጠሩም ከኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ጋር የተስማማ እንደሆነ አንዳንድ የኢትዮጵያ ስነ ፈለክ ተመራማሪዎች (ሮዳስ ታደሰ (ዶ/ር) ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
ምንጭ፡ Britannica
ወደር የለሽ ፎቶግራፎችን የምታነሳው ሳተላይት
******************
ባለው እጅግ ከፍተኛ ጥራት የተነሳ በምድራችን ያሉ አብዛኛውን ነገሮች በጥራት መመለክከት የምትችለው ሳተላይት አሁን ላይ ለሲቪሎችም አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡ በቅርቡ ለህዝብ ይፋ ካደረጋቸው ባለ ከፍተኛ ጥራት ምስሎች መካከልም ከሳምንታት በፊት በአክሱም ኤርፖርት ላይ የደረሰውን ጉዳት የሚያሳው ይህ ምስል ይገኝበታል፡፡
ካፔላ-2 የሚል ስያሜ ያላትና ሳን ፍራንሲስኮ ውስጥ በሚገኘው ካፔላ ስፔስ በተሰኘ ተቋም የተሰራችው ሳተላይቷ ሲንተቲክ አፓቸር ራዳር (SAR) የተባለውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ለውትድርና፣ አካባቢ ጥበቃ፣ ኃይል እና የሕግ ማስከበር አገልግሎቶች የሚውሉ ጥንቅቅ ያሉ ምስሎችን ታቀርባለች፡፡ አሁን ላይ ማንኛውም ሰው በይነ-መረብን በመጠቀም ተመዝግቦ በሳተላይቷ አማካኝነት ከየትኛውም የምድራችን ክፍል የተወሰደ ጥርት ያለ ምስልን ማግኘት ይችላል፡፡ ቅድሚያ ግን ተመዝጋቢው ከአሜሪካን የዓለም አቀፍ የጦር መሳርያ ዝውውር ተቆጣጣሪዎች ፍቃድ ማግኘት ይኖርበታል፡፡
50 ሴ.ሜ በ50ሴ.ሜ የሆነ ስፍራን ምስል መውሰድ የምትችለው ካፔላ ይህ ቴክኖሎጂያዊ አቅሟ ከማንኛውም ሳተላይት በላቀ የጠራ ምስል መስጠት የምትችል እንድትሆን አድርጓታል፡፡ ካፔላን ከሌሎች ይህን ቴክኖሎጂም ሆነ ተለምዶአዊውን የኦፕቲካል ፎቶግራፊክ ፕሮሰሲንግ ስልት ከሚጠቀሙ ተፎካካሪዎቿ የሚለያት ሌላው ብቃቷ ደግሞ በማንኛውም የአየር ፀባይ ውስጥ እንዲሁም በቀንም ሆነ በማታ ፎቶግራፎችን ማንሳት መቻሏ ነው፡፡ በዚህ አማካኝነትም ሳተላይቷ ሰደድ እሳቶችን፣ የነዳጅ ማውጣት እንቅስቃሴዎችን፣ በአየር ንብረት ለውጥ የተጎዱ አካባቢዎችን እንዲሁም ሕገ-ወጥ አደንን የመቆጣጠር ኃይል አላት፡፡
በቀን ውስጥ በእያንዳንዱ ሰዓት ምድራችን ግማሽ ክፍሏ ፀሐያማ የተቀረው ደግሞ በምሽት ሲዋጥ በአማካኝ ግማሹ የመሬት ክፍል በደመና ውስጥ ነው የሚለው ቀድሞ በናሳ በሲስተም መሃንዲስነት ያገለገለው የአሁኑ የካፔላ ስፔስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፓያም ባናዛዲ ይህ በአማካኝ 75 በመቶ የሚሆነው የምድራችንን ክፍል ጨለማ ወይም ደመናማ የያደርገዋል ሲል ይነገራል፡፡ የሰብአዊ ስራዎችን እንደ አንድ ተግባር በመጥቀስ ካፔላ-2 ምድራችንን በየትኛውም የአየር ፀባይ እና ብርሃን ሁኔታዎች ውስጥ ሳለች እንኳን አስተማማኝ መረጃ መስጠት እንደምትችል አክሎ ተናግሯል፡፡
ፓያም ይህን ሳተላይት እውን እንዲያደርግ መነሻ የሆነለት ከ6 ዓመታት በፈት በረራ ላይ እያለ ድንገት የተሰወረው የማሌዢያ አየር መንገዱ በረራ ቁጥር 370 አውሮፕላንን ለማግኘት የተደረጉ ስኬት አልባ አሰሳዎችን በመመልከትና ነገሮችን በተሻለ ለመከታተል ብሎም የምንኖርባት ምድርንም የበለጠ ለመረዳት የሚያስችል ነገር ይኖር ዘንድ ባደረበት ፍላጎት ነው፡፡ አሁን ላይ ተቋሙ በህዋ አንድ ሳተላይት ያለችው ሲሆን በቅርቡም በስፔስ ኤክስ አማካኝነት ሌላ ለመጨመር አቅዷል፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ይህ የሳተላይቷ ብቃት እርሷን አስመልክቶ እጅግ ኃይለኛ ከመሆኗ የተነሳ ወደ ህንፃዎች ውስጥ ሁሉ ለማየት ትችላለች የሚል አሉባልታን አስነስቶባት ነበር፤ ፓያምም አርብ ላይ ነገሩን በቲዊተር ገፁ ላይ እንዲያስተባብል ተገዷል፡፡
ምንጭ፡ Tech Xplore
ይፋ የሆነው የመሬት መንቀጥቀጥ ያለበት የውቂያኖስ ክፍል
***************************
ከዚህ በፊት ያልተለየ የውቂያኖስ ውስጥ መሬት መንቀጥቀጥ አዲስ በተሰራ ሞዴል ሊታወቅ ተችሏል፡፡ የጹኩባ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች የ2020ውን የካረቢያን የመሬት መንቀጥቀጥ ሞዴል የሲስሞ ሜትር መረጃን በመጠቀም ሰርተዋል፡፡
እስከዛሬ ድረስ ውቅያኖሳዊ የመሬት መንቀጥቀጥ እንዳለ ቢታወቅም ቀላልና ለተለያዩ ጥናቶች ግብዓት የሚውሉ እንደነበር ነው የሚታመነው፡፡ በዚህ የሞዴል ስራ ግን ተመራማሪዎቹ በጠም አስቸጋሪ የሆነና ከፍተኛ ፍጥነት ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ ሊከሰት እንደሚችል የሚያመላክት ሞዴል መስራታቸው ተሰምቷል፡፡
በጥር 28፣ 2020 የፈረንጆች አመት 7.7 የለካ የውቅያኖስ ውስጥ የመሬት መንቀጥቀጥ በጀማይካና በኩባ መካከል መከሰቱ ይታወቃል፡፡ ተመራማሪዎቹ አዲስ በተከተሉት መንገድ ከግምት ይልቅ ከጊዜና ከቦታ አንጻር የተለያዩ ምዘናዎችን አድርገዋል፡፡
ይህም ከ52 የመሬት መንቀጥቀጥ ልኬት ጣቢያዎች ያለውን መረጃ በመጠቀም ሊከሰት የሚችልን የመሬት መንቀጥቀጥ ዝርዝር መረጃ ማወቅ እንደሚያስችል ተነግሯል፡፡
ምንጭ PHYS.ORG
በአዲስ መልክ ተሻሽሎ የቀረበው የመኪና ሞተር
*****************************
የቴክኖሎጂ እድገት ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት በአሁኑ ወቅት ብዙ አይነት የቴክኖሎጂ አማራጮችን ማየት የተለመደ ነው፡፡ በገበያ ከቀረቡት የቴክኖሎጂ አማራጮች መካከል አንደኛውን መርጦ ለመሸመት ሁሉም ሰው የየራሱ መመዘኛ መስፈርት ይኖረዋል፡፡ በዘመናዊው አለም አብዛኞችን የሚያስማማው ግን ጊዜን፣ ገንዘብንና ጉልበትን መቆጠብ የሚስችል እንዲሆም ለአጠቃቀም ምቹ የሆነና ከተፈጥሮ ጋር የተስማማ መሆኑ ነው፡፡ የብዙዎች የቴክኖሎጂ ውጤቶች አምራች ተቋማት ድካማቸውም ይህን የሰዎችን ፍላጎት በማሟላት ተፈላጊነታቸውን ማሳደግ ነው፡፡
በአዳዲስ ቴክኖሎጂ ውድድር ውስጥ ካሉ አምራቾች መካከል የመኪና መለዋወጫ አምራች ድርጅቶች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የመኪና መሰረታዊ ክፍሎች የሚባሉት ጎማ፣ ሞተርና ሌሎች መለዋወጫዎች የአንድን መኪና ዘመናዊነትና ተፈላጊነት ሊያሳድጉት ይችላሉ፡፡
በተለይ በአሁኑ ወቅት አለማችን የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በምታደርገው ጥረት በካይ ያልሆኑ መኪኖች ለገበያ ማቅረብ እጅግ ትርፋማ የገበያ አማራጭ መሆኑ የማይካድ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል በኦካ ሪጅ ብሔራዊ ቤተ-ሙከራ የሚሰሩ ተመራማሪዎች ከዘመናዊ መኪኖች ጋር የተስማማ የመኪና ሞተርን በማምረት ለአለም ገበያ ለማቅረብ እየሰሩ ያሉት፡፡
ይህ ኒውትሮኒክ የመኪና ሞተር በተለይ ከፍተኛ ሙቀት ባለባቸው አካባቢዎች ሙቀትን በመቋቋም ብቁ አገልግሎግት መስጠት የሚችል ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የመኪና ሞተሩ ሀይል ቆጣቢ ሲሆን ብክለትን በመቀነስ ረገድ የተዋጣለት እንደሆነ የምርምር ተቋሙ ዳይሬክተር ሮበርት ዋግነር ተናግሯል፡፡
ምንጭ SciTechDaily
እርግዝናና የኮቪድ 19 ክትባት
***************
ምንም እንኳን የሚያጠቡና ነብሰጡር ሴቶች በክትባቱ ሙከራ ጊዜ ባይሳተፉም የመረጃ ምንጫችን ላይቭ ሳይንስ ከሙያተኞች አገኘሁት ያለው መረጃ መድሀኒቱ በሚያጠቡ እናቶችና በነብሰጡሮች ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል ሲል ዘግቧል፡፡ በጉዳዩ ላይ መረጃ የሰጡትን ዶክተር ስቴፋኔ ጋው ጠቅሶ የዘገበው የመረጃ ምንጫችን በጉዳዩ ያለው ትልቁ ጉዳት ሳይንሳዊ የሆነ መረጃ አለመኖሩ ነው ሲል አስነብቧል፡፡ ለዚህም እስካሁን እውቅና በተሰጣቸው ሁለቱ የፊዘርና የሞደርና መድሀኒቶች በሰውነት ውስጥ የሚሰባበርና የሚሰራጭ ኢንፌክሽን የማያስከትል mRNA የተሰኘ ሞሎኪዩል የያዙ መሆናቸውን ዶክተሯ ተናግረዋል፡፡
በጥቅሉ ሲታይ ለነብሰጡሮች የሚሰጡ መድሀኒቶች በሙከራ ወቅት መደበኛ የሆነ ክሊኒካዊ ሙካራ በነብሰጡሮች የማይደረግባቸው መሆኑን በ2014 የወጣ የአለም ጤና ድጅት መረጃ ያመለክታል፡፡ ይሁን እንጂ መረጃዎች ቀጥታ ባልሆነ መንገድ በእንስሳትና በሌሎች ምልከታዎች ተሰብስበው የትርፍና ኪሳራ ስሌት እንደሚሰራ ይነገራል፡፡
ተመራማሪዎች እደሚሉት ከሆነ እርግዝና በኮቪድ 19 ምክንያት በጽኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ የመቆየት እድልን ከፍ ያደርጋል፡፡ በዚህም የሚያጠቡ እናቶችና ነብሰጡሮች መድሀኒቱን ከመውሰዳቸው በፊት ከጤና ግልጋሎት ሰጭዎች ጋር በእርግዝና ወይም በማጥባት ወቅት መድሀኒቱን መውሰድ ባለው ጥቅምና ጉዳት ዙሪያ መነጋገር እንዳለባቸውና መድሀኒቱን በመውሰድና ተጨማሪ መረጃ እስከሚገኝ በመጠበቅ ዙሪያ መወሰን ይኖርባቸዋል ተብሏል፡፡ ዶክተሯ አክለውም የተጋላጭነት መጠናቸው ከፍ ያሉ ሰዎች ከመጠበቅ ይልቅ ፈጥነው መድሀኒቱን ቢወስዱ እንደሚሻል ተናግረዋል፡፡
የበሽታ መቆጣጠርና መከላከል ማእከል (CDC) መድሀኒቱን የወሰዱ የሚያጠቡና ነብሰጡር ሴቶችን ለይቶ ክትትል እያደረገ መሆኑን የዘገበው የመረጃ ምንጫችን በቀጣዩ ወር በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ መረጃ እንደሚኖር አመልክቷል፡፡ መረጃውንም የበሽታ መቆጣጠርና መከላከል ማእከል (CDC) እና የምግብና መድሀኒት አስተዳደር (FDA) አሁን ላይ ያሉ የመረጃ መሰብሰቢያ መንገዶችን በመጠቀም እንደሚሰበስቡ ተነግሯል፡፡
ባጠቃላይ ለላይቭ ሳይንስ መረጃ የሰጡት ዶክተር በአብዛኛው ጥቅም ላይ የዋሉ ክትባቶች በእርግዝና ላይ የከፋ ጉዳት የማያደርሱ መሆናቸውን ቢናገሩም ስሞልፎክስ፣ MMR የተሰኙ ደካማ የሆኑ ቫይረሶችን የተሸከሙ ክትባቶች ለነብሰጡሮችና ለአጥቢዎች የማይሰጡ መሆናቸው መዘንጋት እንደሌለበት አሳስበዋል፡፡
እንደ ምክረ ሀሳብ ዶክተሯ አጥቢና ነብሰጡር እናቶች ሌሎች ሰዎች ከሚወስዱት መጠን ያነሰ ክትባት ቢወስዱ የተሻለ መሆኑን ሲገልጹ አስተማማኝ የሚሆነው ግን ተገቢ የሆነ ክሊኒካዊ ሙከራ መደረጉ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ምንጭ Live science
ስንጥቃቸውን በራሳቸው ማደስ የሚችሉ የስማርት ስልክ ስክሪን ሽፋኖች
************************************
በአሁኑ ወቅት የስማርት ስልክ ተጠቃሚዎች ከሚቸገሩባቸው ነገሮች መካከል ስልካቸው በወደቀ ቁጥር የስክሪኑ ሽፋን መስታወት በቀላሉ መሰነጣጠቁ ነው፡፡ አለፍ ሲልም ከአነስተኛ እስከ ከፍ ያለ ዋጋ የሚጠይቅ የጥገና ወጭ ሊያስከትል ይችላል፡፡ ምስጋና ይግባቸውና የዘርፉ ተመራማሪዎች ጊዜቸውን ራሳቸውን የሚያድሱ የስማርት ስልክ ስክሪን ሽፋኖችን ለመስራት እያዋሉ እንደሆነና ጥቅም ላይ ለማዋልም እንደተቃረቡ ተናግረዋል፡፡
በኮሪያ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የምርምር ተቋም የሚገኝ አንድ የምርምር ቡድን የራሱን ስንጥቅና ሌላ አካላዊ ጉዳት መጠገን የሚችል ምስጢራዊ የሆነ ዘይትን በግብዓትነት በውስጡ የያዘ የኤሌክትሮኒክስ ቁስ ማበልጸጉን የዘገበው ሳይንስ አለርት ነው፡፡
ይህ ልዩ ዘይት ፍላክስ ከሚባል ቃጫ መሰል ተክል ዘሮች የሚዘጋጅ ሲሆን ተመራማሪዎች ለስራቸው አመቺ የሚሆን ቀለም አልባ ግብዓትን ለማግኘት የሚያስችል የማላመድ ስራን ሰርተውበታል፡፡ ይህ ዘይት ጉዳት የደረሰበትን የስክሪኑን ሽፋን ክፍል ሰርስሮ በመግባት ስንጥቁን ወይም ስብራቱን ማስተካከል እንዲችል የታለመ ነው፡፡ ይህ ጥናት ሙሉ ለሙሉ ሲሳካ ስብራታቸውን የሚጠግኑ የስልክ ስክሪን ሽፋኖች ኖሩንና በየጊዜው የተሰነጣጠቀ ስልክ ከመያዝ ይገላግሉናል ሲል የመረጃ ምንጫችን አስነብቧል፡፡
የዚህ ቴክኖሎጂ ጥቅም የተሰበረ የስልክ ስክሪን ሽፋንን ከመጠገን ባለፈ ሌሎች ቀለም አልባ ፖሊማይድ (CPI) የሚጠቀሙ እንደ የጸሐይ ሀይል መሰብሰቢያ ንጣፎችና ሌሎች የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በቀላሉ መጠገን እንደሚያስችል ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
ምንጭ Sciencealart
ከ21 ሺህ ብር በላይ የሚያወጣው አዲሱ የአፕል ኤርፖድ
============================
ስመ ጥሩ የቴክኖሎጂ ኩባንያ አፕል እስከ 21,740 ብር ወይም 549 ዶላር ድረስ (በአሜሪካን የሚሸጡበት ብቻ) ዋጋ የተመነላቸው የድምፅ ማዳመጫ ኤርፖዶቹን በቅርቡ ይፋ አድርጓል፡፡ ኤርፖዱ ከብረት እና አልሙኒየም የተሰራ ሲሆን እንደየ ደረጃው ከ130 እስከ 385 ግራም ክብደት አለው፡፡ ዋናው ክብደት ጆሮ ላይ በሚለጠፉት የኤርፖዱ ክፍሎች (Ear Cups) ላይ በመሆኑም ጭንቅላት በሚነቃነቅበት ወቅት ብዙም ቦታቸውን ሳይለለቁ እንዲቆዩ ያደርጋቸዋል፡፡
ኤርፖዶቹ ከውጭ ድምፅ እንዳይገባ የማድረጊያ ቴከኖሎጂ (Noise-Cancelling) የተገጠመላቸው ሲሆኑ በአንድ ቻርጅ ብቻ እስከ 20 ሰዓት ያክል አገልግሎት እየሰጡ መቆየት እንደሚችሉ አፕል ተናግሯል፡፡ ኤርፖዶቹ የአፕል ኤች1 ቺፕ የተገጠመለት በመሆኑም ብሉቱዝ 5.0 ያላቸውና የተለያዩ የኦዲዮ አይነቶችንም ማጫወት የሚችሉ አድርጓቸዋል፡፡ በተጨማሪም የድምፅ ተዕዛዝ መቀበል እንዲሁም አጭር የፅሁፍ መልዕክቶችን እንደገቡ ማንበብ የሚችል ነው፡፡ ኤርፖዱ ከአፕል ውጪም ከሌሎች ምርቶች ጋራ መገናኘት የሚችል ቢሆንም አንዳንድ ገፅታዎቹ ግን ከአፕል ምርቶች ጋር ሲሆኑ ብቻ ይሆናል የሚሰሩት፡፡
ኤርፖዶቹ ያላቸው ድምፅ እንዳይገባ የማድረጊያ ቴክኖሎጂ ማይክሮፎኖችን በመጠቀም ያልተፈለጉ ድምፆች ሁሉ ከጆሮ እንዳይደርሱ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ እንበልና ኤርፖዱን ያደረገ አንድ ሰው በመንገድ ላይ ሲራመድ በዙርያው ያሉ የመንገድ ዳር እና ሌሎች ረባሽ ድምፆች ምንም እንዳልተፈጠሩ ሁሉ ሳይሰማቸው ሙዚቃውን ማጣጣም ይችላል ማለት ነው፡፡ ሆኖም ይህ ሰው በዙርያው የመኪና እና ሌሎች ድምፆችን እየሰማ እራሱን ጠብቆ ለመጓዝ ካሻው ትራንስፓረንት ሞድ ላይ በማድረግ ኤርፖዱን ያላደረገ እስኪመስለው ድረስ የውጭ ድምፅ እንዲገባ ማድረግ ያስችለዋል፡፡
የባትሪያቸውን ቆይታ ያየን እንደሆን ድምፅ እንዳይገባ ማድረጊያው በርቶ እስከ 20 ሰዓት ድረስ አገልግሎት መሰጠት የሚችሉ ሲሆን ይህ ጠፍቶ ግን ከዚያ ለበለጠ ጊዜም ግልጋሎት መስጠት የሚችል ነው፡፡ ይህ ከቦስ ኤርፖዶች ጋራ ተመሳሳይ ቢሆንም ከB&W አቻዎቹ አንፃር ግን በ10 ሰዓት ያነሰ ያደርጋቸዋል፡፡ የ5 ዋት እና ከዚያ በላይ የሆነ የዩኤስቢ ቻርጀር በመጠቀምም ኤርፖዱን ሙሉ ለሙሉ ቻርጅ ለማድረግ ሁለት ሰዓታት መጠበቅ ግድ የሚል ቢሆንም ለ5 ደቂቃ ብቻ ቻርጅ አድርጎ ለ90 ደቂቃ ሙዚቃ ማጫወት የሚያስችለውን ኃይል ማግኘት ይችላል፡፡
ኤርፖዶቹ ባላቸው የድምፅ ጥራት፣ ቴክኖሎጂ እና ቅንጦት ብዙ ሰዎችን መሳብ የቻሉ ቢሆንም ዋጋቸው ግን እጅጉን አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ ከአንዳንድ የቅርብ ተፎካካሪ የሆኑ ተመሳሳይ ምርቶች አንፃር እንኳን 200 ዶላር እና ከዚያ የዋጋ ልዩነት አላቸው፡፡ በተጨማሪም ከአሜሪካ ውጪ ሲሸጡ ዋጋቸው ከዚህም በላይ እየጨመረ ይሄዳል፡፡
ምንጭ፡ The Guardian
ከሌላው ዓለም ፍጡራን የተላከ ሊሆን ይችላል የተባለለት አዲስ የራዲዮ ሞገድ
=========================
የሌላ ዓለም ፍጡራንን ፍለጋ ውስጥ በቀዳሚነት በሚቀመጠው ፕሮጀክት ስር የሚሰሩት ተመራማሪዎች ለፀሐይ በቅርብ ርቀት ከምትገኘውና ከምድር የ4.2 ብርሃን ዓመት ርቀት ካላት ፕሮክሲማ ሴንታዎሪ ኮከብ አቅጣጫ የመጡ የሚመስሉ አጠራጣሪ የሬዲዮ ሞገዶችን እየመረመሩ ናቸው፡፡ የሬዲዮ ሞገዶቹ አውስትራሊያ ውስጥ ባለው የፓርከስ ቴሌስኮፕ አማካኝነት ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ሚያዝያ እና ግንቦት ወራት ላይ ነው የተገኙት፡፡ ሲግናሉ ከተላከበት ጊዜ አንስቶ በተመራማሪዎቹ ትንተና እየተደረገበት ሲሆን ዝርዝሩ እስካሁን ለህዝብ ይፋ አልተደረገም፡፡
ተመራማሪዎቹ ምዕራብ ቨርጂኒያ ውስጥ ባለው ቴሌስኮፕ አማካኝነት መሰል የራዲዮ ዌቮችን መስማታቸው የተለመደ ነው፡፡ ሆኖም እነዚህ ሞገዶች የሰው ልጆች ተፅዕንዖን ተከትለው የተገኙ ሲሆን ይህን ግን ለየት የሚያደርገው 980 ሜጋ ኸርዝ በሆነው የሬዲዮ ሞገዱ ባንዶች ውስጥ ሰው ሰራሽ የሆኑ ሳተላይትም ሆነ ቁስ ሲግናል አልተገኘበትም፡፡
ሲግናሉ በአውሮፓውያኑ 1977 ከተገኘውና “ዋው ሲግናል” ተብሎ ከሚታወቀው በኋላ በሌላው ዓለም ፍጡራን ፍለጋ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠው ሲግናል እንደሆነም በባለሙያዎች ዘንድ ተነግሮለታል፡፡ ሲግናሉን የመተንተኑን ስራ ስትመራ የቆየችው ሶፊያ ሼክ በፕሮጀክታቸው ውስጥ እስከዛሬ ከተሰሙት ሁሉ አጓጊው ሲግናል መሆኑን ትናገራለች፡፡ ሲግናሉንም ብሬክስሩ ሊስን ካንዲዴት 1 (BLC1) ብለውታል፡፡
በሌላው ዓለም ፍጡራን ፍለጋ ውስጥ ከሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች መካከል አንዱ ከእነዚህ ፍጡራን ጋራ የመገናኛው/መግባብያው መንገድ አለመታወቁ ነው፡፡ በተጨማሪም በዩኒቨርስ ውስጥ የሚፈጠሩ የሬዲዮ ሞገዶች ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉት ተፈጥሮአዊ መነሻዎችም ቢሆን ሙሉ በሙሉ አይታወቁም፡፡ ስለዚህም ብዙውን እንደዚህ አይነት ሲግናሎች ሲገኙ ቴክኖሎጂ አፈራሽ እንደሆኑ ግምት የሚወሰድና ከተፈጥሮአዊ ምንጭ መሆናቸውን የሚያስረዳ ማብራርያንም በቀላሉ የማይገኝባቸው ሲሆን ነገሩን ወደ ሌላኛው ዓለም ፍጡራን መውሰዱ ግን ትኩረት ሳቢ ነው፡፡ ስለ ሲግናሉ የሚገልፅ መረጃ ለህዝብ ይፋ ያልተደረገ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ወደፊት ይፋ ቢሆን እንኳን ልክ እንደ ዋው ሲግናል ሁሉ በማስረጃ የዋጀ ድምዳሜ ላይ የሚደረስበት አይመስልም፡፡
ከማንኛውም ኮከብ በላይ ለምድር በምትቀርበው ፕሮክሲማ ሴንታዎሪ ውስጥ ቢያንስ ሁለት የሚዞሯት ፕላኔቶች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ አንደኛው በጋዝ የተሞላ ሲሆን ሌላኛው ግን ባለው ለውሃ ፍሰት የተስማማ ሙቀት ሳብያ ሰውን ሊያኖሩ ይችላሉ ተብለው ግምት ከሚወሰድባቸው ፕላኔቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ይህች ፕላኔት ከምድር በ17 በመቶ የግዝፈት ብልጫ ያላት ድንጋያማ ስፍራ ናት፡፡ ፕሮክሲማ ቢ በሚል ስያሜ የምትታወቀው ፕላኔቷ በየ 11 ቀናቱ ኮከቧን የምትዞር ናት፡፡ ሆኖም ለሰው ልጆች ኑሮ አደገኛ ልትሆንም እንደምትችል ይነገራል፡፡ ከሦስት ዓመታት በፊት የናሳ ተመራማሪዎች የኮምፒውተር ሞዴልን ተጠቅመው ፕላኔቷ በቀላሉ ለከባድ ጨረር እና ድንገተኛ የኮከብ ብርሃን ነበልባል የተጋለጠች ልትሆን እንደምትችል አሳይተዋል፡፡
ምንጭ፡ The Guardian እና Live Science
ናኖ ቴክኖሎጂ ለዘመናዊ ግብርና
የግብርና ቴክኖሎጂ መሠረታዊ መለኪያው የምርት መጠንን መጨመር፣ የጥራት ደረጃ ማሻሻል፣ የሥራ ቅልጥፍና መፍጠርና ማቀነባበርን ያካትታል፡፡ እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ መጨረሻ አካባቢ በኢንዱስትሪ የበለፀጉ ሀገራት የናኖ ቴክኖሎጂን የሚደግፉ ተቋማትን በመመስረት ምርምር በሰፊው ከማካሄድ ባለፈ ወደ ምርት ተግባር መግባታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከቅርብ ዓመታት በኋላ ታዳጊ ሀገራትም ናኖ ቴክኖሎጂን በኢንዱስትሪዎቻቸው ውስጥ እየተጠቀሙባቸው ይገኛል፡፡
ናኖ ቴክኖሎጂ የምርት ጥራትና ብዛት ማሳደግ የሚያስችል በመሆኑ በግብርና ምርት ላይ መጠቀም የሚፈለገዉን ለዉጥ ለማምጣት ያግዛል፡፡ ከዚህም በተጓዳኝ ናኖ ቴክኖሎጂ በግብርና ኬሚካል ቅመም በመጠቀም የአፈር፣ የውሃና የአየር ብክለትን በመቀነስ ግብርናው የበለጠ አስተማማኝ እንዲሆን ያደርጋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በድረ-ገጹ ባወጣው የግብርና ፖሊሲ መግለጫ በ2050 የዓለም ህዝብ ብዛት 9 ቢሊዮን እንደሚደርስና እየጨመረ ያለውን የህዝብ ቁጥር ለመመገብ ግብርናውን ማዘመን የግድ እንደሚል አስቀምጧል፡፡ ለዚህ ደግሞ ናኖ ቴክኖሎጂ መፍትሄ ያመጣል ተብሎ ከፍተኛ ተስፋ ተጥሎበታ፡፡ ናኖ ቴክኖሎጂ የምርትን ጥራትና ብዛት ከመጨመር ባሻገር ለዘላቂ የውሃ አጠቃቀም፣ ለንፁህ ዘር አቅርቦት፣ ተባይ እና በሽታን ለመለየት፣ አልሚ የምግብ አቅርቦትን ለመጨመር ፋይዳው የጎላ ነው፡፡ የእፅዋት ጥበቃና ተፈጥሮ ሃብት ከብክለት ነፃ ለማድረግ ወይም ለመቀነስ የሚረዳ መድሃኒት ማቅረብ ትኩረት ሊደረግበት የሚገባ ነው፡፡
ናኖ ቴክኖሎጂ በተፈጥሮ ላይ የጎንዮሽ ጉዳት ሳይደርስ ሚዛኑን ጠብቆ አረንጓዴና የተመቻቸ ስነ-ምህዳራዊ አካባቢን በመፍጠር የግብርና ምርትን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ ይሁን እንጅ በበለፀጉትና በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት የናኖ ቅንጣቶች በረዥም ጊዜ አደጋ ያስከትላሉ ብሎ በመጠራጠር ለመቀበል መቸገር እንደሚስተዋል መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ማንኛውም የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች እንደሚሰጡት ትሩፋት ሁሉ መጠነኛ ጉዳት ሊኖራቸው ስለሚችል የአጠቃቀም ሁኔታን ይበልጥ በማሻሻል እና ተሞክሮዎችን በመቀመር የቴክኖሎጂውን ፍሬ በበልሃት መጠቀም ግድ ይላል፡፡ የናኖ ቴክኖሎጂ ወጭ ቆጣ፤ ምርታማነትን ይበልጥ የሚያሳድግ እና ወቅቱን የዋጀ ቴክኖሎጂ መሆኑን ለማህበረሰቡ ግንዛቤ መፍጠር በአጠቃቀም ሂደቱ ላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው፡፡
ምንጭ፡ Frontiersin