TechIn2
1.22K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
“ጆሮውን ሰጥቶ ለሚሰማ አለማችን ሁሌም ቢሆን የለዉጥ ያለህ በሚል የማያቋርጥ ጩኸት ውሰጥ እንዳለች ያስተዉላል”
===================
“ለዉጥን መረዳትና ማስተዳደር” በሚል ርዕስ የተዘጋጀው የዚህ ሳምንቱ የቴክኢን ሴሚናር ዛሬ ማለዳ በቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ተካሂዷል፡፡ መድረኩ ላይ በኢንስቲትዩቱ ውስጥ በተመራማሪት በሚያገለግሉት አቶ አብዱለጢፍ ሀቢብ አማካኝነት ስለ ለውጥ ምንነት፣ ባህርያት እና ሌሎችም ዝርዝር ጉዳዮች ገለፃ ቀርቦበታል፡፡
“ጆሮውን ሰጥቶ ለሚሰማ አለማችን ሁሌም ቢሆን የለዉጥ ያለህ በሚል የማያቋርጥ ጩኸት ውሰጥ እንዳለች ያስተዉላል” ያለው አቶ አብዱለጢፍ እኛ የሰው ልጆች ከአደን ሕይወት አንስቶ አሁን እስካለንበት የመረጃ ዘመን ድረስ ታላላቅ ለውጦችን ማስተናገዳችንን ጠቅሷል፡፡ በለውጥ ሂደት ውስጥ ሁለት ተፃራሪ ኃይሎች፤ ማለትም ቆስቋሽ እና መካች ኃይሎች መኖራቸው የተገለፀ ሲሆን በዚህ የለውጥ ሂደት ውስጥም ተቀዳሚው ፈተና የአመለካከት ውስንነት መሆኑ ተቀምጧል፡፡ በተጨማሪም የለውጥ ዋና ምሰሶዎች የሆኑትን ስለ ለውጥ አስፈላጊነት ግንዛቤ መፍጠር፣ በለውጡ ላይ ለመሳተፍ እና ለመደገፍ ያለ ጽኑ ፍላጎት፣ ለውጡ እንዴት እንደሚመጣ ያለ ዕውቀት፣ ለውጡን ለመተግበር /ለማከናወን የሚያስፈልግ ችሎታ/ክሕሎት እና ለውጡን ለማስቀጠል የሚደረገግ ማበረታቻ በአግባቡ ተሟልተው ከተገኙ አንድን ለውጥ ስኬታማ እንደሚያደርገው ተነግሯል፡፡
የለውጥ አመራር ሂደቶችን በተመለከተም ለውጥ ሲሳካ ወይም ተሰናክሎ የሚቀርበት ዋናው ምክንያት የለውጥ አመራሩን ሰብዓዊ ጎን በበቂ ሁኔታ መምራት ባለመቻሉ ነው ሲል አቶ አብዱለጢፍ ተናግሯል፡፡ አከሎም የለውጥ አመራር በዋናነት የለውጥ እንቅፋቶችን ለመምራት፣ የስኬት ዕድሉን ለማስፋት እና የሽግግር ጊዜውን ለማሳጠር እንደሚያስፈል ተናገሮ በአንፃሩ የለውጥ ሰብዓዊ ጎኑን መምራት አለመቻል የአሰራሮች ወደ ኃላ መመለስ፣ የምርታማነት መቀነስ፣ ግልፅ እና ስውር ተቃዉሞዎች እንዲሁም የእኛ እና የእነሱ የሚል ቡድናዊ አመለካከት መፈጠርን ጨምሮ በርካታ ተፅዕኖዎችን እንደሚፈጥር አስቀምጧል፡፡
መድረኩ ሌሎች የኢንስቲትዩቱ ሰራተኞችንም ተሳታፊ ያደረገ እንደመሆኑ የለውጥ አይነቶች፣ ከማህበረሰብ አንፃር ስለሚኖረው ግበረ መልስ እና ሌሎችም ጥያቄዎች ቀርበው በአቶ አብዱለጢፍ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
የቆዳ ጫማ ማቀነባበር እና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍን ለማገዝ የሚረዳ ወርክሾፕ በመካሄድ ላይ ነው
የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት በዛሬው ዕለት ያዘጋጀው የቆዳ ጫማ ማቀነባበር እና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍን ለማገዝ የሚረዳ የባለድርሻ አካላት ውይይት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ወርክሾፕ በመካሄድ ላይ ነው፡፡ ለአንድ ቀን በሚቆው በዚህ የውይይትና የወርክሾፕ መርሃ ግብር ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት የተወጣጡ ባለድርሻ አከላት እና በግሉ ዘርፍ የሚንቀሳቀሱ አነስተኛና መካከለኛ የቆዳ ጫማ አምራች ኢንተርፕራይዞች እንዲሁም ሌሎች የቆዳ ውጤት አምራች ድርጅቶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
በመርሃግብሩ መጀመሪያ ስለኢኒስቲትዩት አጠቃላይ አደረጃጀት እና ተቋማዊ ሃለፊነቶች ገለፃ ያደረጉት የሴክተር ሞደርናይዜሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰልማን መሃመድ ኢኒስቲትዩቱ በተሰጠው ሃለፊነት መሰረት የሀገሪቱን የአሰራር ስርዓት የማዘመን ተልእኮ በማእከላዊነትና ባስተሳሳሪነት በመምራት የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚፋጠንበት እና ለተለያዩ ኢንተርፕራያዞች ድጋፍ የሚደረግበት ሂደት እንዳለ አስረድተዋል፡፡ አቶ ሰልማን አከለውም በዛሬው ዕለት የተዘጋጀው የውይይት እና የወርክሾፕ መርሃ ግብር በዚህ አግባብ መሰረት ከተለያዩ የመንግስትና የግል ተቋማት የተወጣጡ ባለድርሻ አከላት እና በግሉ ዘርፍ የሚንቀሳቀሱ አነስተኛና መካከለኛ የቆዳ ጫማ አምራች ኢንተርፕራይዞች ቀርበው መወያየት እንዲችሉ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲፈጠር ያለመ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የቆዳ ኢንዲስትሪ ልማት ኢንስቲትዩትን ወክለው የተገኙት የተቋሙ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃይለኪሮስ ደበሳይ በቆዳ ጫማ እና በቆዳ ምርቶች ዘርፍ ላይ የሚታየውን ዘርፈብዙ የጥራት ችግሮችን እና ሊወሰዱ በሚገቡ የመፍትሄ ሃሳቦች ላይ ሰፊ ገለፃ አድረገዋል፡፡ አቶ ሃይለኪሮስ በተለይም ሃገሪቱ ከዚህ ዘርፍ ይበለጥ ለመጠቀም የሚያስችላት ተፈጥሮአዊ ሃብት እና ሰፊ የገበያ አማራጭ የያዛች መሆኑን አስረድተው ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን ይበልጥ ተቀራርቦ መሰራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የሴክተር ሞደርናይዜሽን ዳይሬክተር ያዘጋጀው ይህ መርሃ ግብር በባለድረሻ አካለት ዙሪያ በሚደረግ ውይይት የቀጠለ ሲሆን በቀረቡ የቴክኖሎጂ አማራጮች እና የማሽነሪ ግብዓቶች ዙሪያም የወርክሾፕ መርሃ ገብር ይካሄዳል፡፡
የፊታችን ሰኞ 12/04/13 የሚጠበቀው የጁፒተርና የሳተርን ነገር
***********************
በያዝነው ሳምንት ጁፒተርና ሳተርን በደቡብ ምእራብ በኩል ዝቅ ብለው የሚገኙ ሲሆን በወሩ መጀመሪያ አካባቢ በ2.1 ዲግሪ ተራርቀው ነበር ይለናል ከስፔስ ዶት ኮም ያገኘነው መረጃ፡፡ ይሁን እንጂ ወሩ እየገፋ በሔደ ቁጥር በመካከላቸው ያለው ርቀት እየቀነሰ መጥቷል፡፡ ይህ መቀራረባቸው በየእለቱ በ0.1 ዲግሪ እየቀነሰ የፊታችን ሰኞ ግሬት ኮንጃንክሽን ወይም ታላቁ ጥምረት የተሰኘውን ክስተት እናያለን ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡
ይህ ክስተት በስነ ፈለክ ምርምር ከተሰማሩት አልፎ የብዙዎችን ትኩረት የሳበ ሁኗል፡፡ ከስተቱም ፀሐይ ከጠለቀች ከ30 ደቂቃ በኋላ የሚጀምር ሲሆን ጨረቃን፣ ሳተርንንና ጁፒተርን አንድ ላይ ለማየት የተሻለው ሰዓት ከሩብ ጉዳይ ለ1 እስከ አንድ ተኩል በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር እንደሚሆን የመረጃ ምጫችን አስነብቧል፡፡
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲም ክስተቱን ከባላገሩ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር እና ከሌሎች አጋሮች ጋር በመተባበር በቀጥና ለማሳየት ማቀዱን ከተቋሙ የማህበራዊ ድረ-ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ምንጭ Space.com
Capture ts.PNG
571 KB
ቅዳሜን ከቴክ-ሳይንስ ጋር ያሳልፉ
በዚህ ሳምንት የቴክ ሳይንስ ሳምንታዊ የቴሌቪዥን ፕሮግራማችንም አስተማሪ ናቸው ያልናቸውን ልዩ ልዩ ዝግጅቶች አሰናድተን ከናንተው ዘንድ ለማድረስ ነገ 10 ሰዓትን እየጠበቅን ነው፡፡
የግብርና ምርምር ስራዎች አጀማመር በኢትዮጵያ ምን መልክ እንዳለው የሚዳስስ ዝግጅት አብይ ፕሮግራማችን ላይ የምናቀርብላችሁ ሲሆን እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ በርካታ ታዳጊዎችን በሮቦቲክስ ዘርፍ ለማብቃት እየሰራ ያለው ፋሪስ ሮቦቲክ ሴንተርንም እናስተዋውቃችኋለን፡፡
እንደተለመደው ታዳጊ የፈጠራ ባለሙያዎችን ስራ ለእናንተው የምናደርስበት የብላቴናት ዝግጅታችንም የሽንኩርት መፍጫ የሰሩት የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ህፃናትን፤ የቴክኖሎጂ ታሪክም በየቤታችን ጓዳ ስለሚገኙት ፍሪጆች ዳሰሳ የሚያቀርቡላችሁ ይሆናል፡፡ የስኮላርሺፕ ዕድል ጥቆማም ይኖረናል፡፡
ያስታውሱ ዘውትር ቅዳሜ 10 ሰዓት በድጋሚ ደግሞ ማክሰኞ በተመሳሳይ ሰዓት በMOE TV ላይ ያገኙናል፡፡
ያለፉ ፕሮግራሞች ተሟልተው የተቀመጡበት የዩትዩብ ቻናላችንንም ሊንኩን ተጠቅመው ሰብስክራይብ ማድረጉን እንዳይረሱ https://www.youtube.com/channel/UC6jvUOLRSkVEQtc5Annfwvg ፡፡
አካላዊና አእምሯዊ ጤናን የሚያሳድገው ባክቴሪያ
***************************
ተመራማሪዎች አካላዊና አእምሯዊ ጤናን የሚያሳድገውን ባክቴሪያ መለየታቸውን የዘገበው ሜዲካል ኤክስፕረስ ነው፡፡ በአለማችን ከ1980 ጀምሮ ባለው ሁኔታ ከልክ ያለፈ ውፍረት በተቃራኒው ካለው በበለጠ የሰዎችን ህይወት እንደሚቀጥፍ ይነገራል፡፡
ከልክ ያለፈ ውፍረት የአለማችን ትልቅ ችግር የሆነው ይህን ሰበብ አድርገው ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ በሽታዎች በሳይንስ type 2 diabetes የሚባሉት የሰውን ልጅ በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚያጠቁ ነው፡፡ እንዲህ ባሉ በሽታዎች ከአለማችን ህዝብ ቁጥር 6.28 በመቶ ወይም 462 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ተጠቂዎች እንደሆኑ በቅርብ ጊዜ የወጡ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ በአይርላንድ በሚገኝ አንድ የምርምር ተቋም የሚሰሩ ተመራማሪዎች ቢፍዶባክቴሪየም ሎንገም APC1472 የተባለው ባክቴሪያ የሰዎችን የምግብ ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቆጣጠር ተናግረዋል፡፡
ሙሉ ጤና ኖሯቸው ወፍራም በሆኑ ሰዎች ምርምሩ ተሞክሮ ይህ ባክቴሪያ ያላቸውን የስኳር መጠን በመቀነስ የረሀብ ስሜትን የሚቀሰቅሰውን ሆርሞንና ለጭንቀት የሚዳርጉ ሆርሞኖችን እንደሚያስተካክል ተረጋግጧል፡፡ በዚህም ይህ ባክቴሪያ ለበሽታ የሚያጋልጠውን የደማችንን የስኳር መጠን ለመቀነስ ከፍተኛ ሚና እንዳለው የምርምሩ መሪዎች ተናግረዋል፡፡ እደ መረጃ ምንጫችን ከሆነ ይህ ምርምር በዘርፉ የመጀመሪያ ምርምር ሲሆን ከመነሻ ምርምር ተነስቶ የክሊኒካል ሙከራውን አልፎ በሰዎች መረጋገጥ ችሏል፡፡
ለረጅም ጊዜያት ጭንቀትና ከልክ ያለፈ ውፍረት የተያያዙ ነገሮች እንደሆኑ የሚታወቅ መሆኑን የዘገበው የመረጃ ምንጫችን ጭንቀት በጨመረ ቁጥር የምግብ ፍላጎታችንን የሚያንረው ኮሊስትሮል ይጨምራል ሲል አስነብቧል፡፡ በመሆኑም ባክቴሪያው የረሀብ ስሜትን የሚቀሰቅሱና ለጭንቀት መጨመር መንስኤ የሆኑ ሆርሞኖችን በመቆጣጠር ውፍረት ለከፋ የጤና ጉዳት እንዳያጋልጠን ያደርጋል ብለው መናገራቸውን ሜዲካል ኤክስፕረስ ጽፏል፡፡
ምንጭ፡ Medical Xpress
This media is not supported in your browser
VIEW IN TELEGRAM
20ዎቹ የምንግዜም ታላላቅ ኢኖቬሽኖች
…….የቀጠለ
11. ስልክ (TELEPHONE) - የስኮትላንድ ተወላጁ አሌግዛንደር ግርሃም ቤል በሰው ልጆች የመገናኛ ጥበብ ውስጥ ትልቅ አብዮት የፈጠረውን የስልክ ቴክኖሎጂ በራሱ ስም ያስመዘገበ ታላቅ የፈጠራ ባለሙያ ቢሆንም ከሱ ቀደምና እሱ በነበረበት ዘመንም ብዙ የፈጠራ ባለሙያዎች ለቴክኖለጂው ማበብ የራሳቸውን አሻራ ጥለዋል፡፡ አሌግዛንደር ግርሃም ቤል አንደአውሮፓውያኑ በ1876 በኤሌክተሪክ ስልክ የመጀመሪያውን ፓትንት ካገኘ በኋላ የሰው ልጆች እርስ በእርስ የመገናኘት ልምድ እስወዲያኛው ተቀይሯል፡፡
12. ክትባት (VACCINATION) - የክትባት ግኘት ለአንዳንዶች አከራካሪ ፈጠራ ቢሆንም ብዙዎች እንደሚገልፁት ከሆነ ግን በአለም ላይ የተከሰቱ በሽታዎችን በማጥፋት እና የሰው ልጆችን በመታደግ በኩል እስካሁን ከታዩ አስደናቂ ግኝቶች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው፡፡ በአለማችን ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰራው ክትባት እንደአውሮፓውያኑ በ1796 ለፈንጣጣ (smallpox) በሽታ የተሰራው ክትባት ሲሆን ኤድዋርድ ጄነር በተባለ ተመራማሪ የተገኘ ነው፡፡ ከዚህ ክትባት በኋላ በ1885 በፈረንዊው ኬሚስትና ባዮለጂስት ሊዩስ ፓስተር የተሰራው የሬቢስ (rabies) ቫይረስ ክትባት ደግሞ ለዘመናዊው የመድሃኒት ቴክኖሎጂ ትልቅ በር የከፈተ ነበር፡፡
13. መኪና (CARS) - ተሽከርካሪ መኪናዎች የሰዎችን የጉዞ ስርዓት እና ተያይዞ የመጣውን የከተሞች ባህሪ እስከወዲያኛው የቀየረ ግሩም የቴክኖሎጂ ፈጠራ ነው፡፡ ተሽከርካሪ መኪናዎች በዘመናዊው ቅርፃቸው በአለም ላይ ብቅ ማለት የጀመሩት በ19ነኛው ክፍለ ዘመን የመጨረሻ አመታት ላይ ሲሆን በዋናነት በጀርመናዊው ካርል ቤንዝ እና ባልደረቦቹ የተከናወኑ ናቸው፡፡ ካርል ቤንዝ እንደአውሮፓውያን አቆጣጠር በ1885 የመጀመሪያዋን ሞተር ብስክሌት ተግባራዊ ካደረገ በኋላ የመኪና ቴክኖሎጂ በአለም ላይ እየናኘ ሄዷል፡፡
14. አውሮፕላን (AIRPLANE) - በ1903 በአሜሪካውያን ወንድማማቾች ለውጤት የበቃው ይህ አስገራሚ ቴክኖሎጂ የሰው ልጆችን የረዥም ርቀት ጉዞ ፈጣን አማራጭ በመስጠት የትራንስፖረት ኢንዱስትሪን እስከወዲያኛው የቀየረ ነው፡፡ የአውሮፕላን ቴክኖሎጂ የአለም ሰዎችን ይበልጥ እንዲቀራረቡ በማድረግ የባህል፣ የምጣኔ ሃብት እና የእውቀት ልውውጦችን ይበልጥ ያዳበረ ቢሆንም በቴክኖሎጂው የማብሰሪያ ጊዚያት በአለም ላይ ለተከሰተው አለምአቀፍ ጦርነት ሌላ አባባሽ ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
15. ፔኒሲሊን (PENICILLIN) - እንደአውሮፓውያኑ በ1928 በስኮትላንዳዊው ሳይንቲስት አሌክዛንደር ፍሌሚንግ የተቀመረው ይህ ግኘት የፋርማሲዩቲካል ዘርፉን አንድ እርምጃ በማራመድ የመጀመሪያውን አንቲባዮቲክ መድሃኒት ለአለም ያስተዋወቀ ነው፡፡ ፔኒሲሊን እጅግ ብዛት ያላቸው ተላላፊ ባክቴሪያዎችን በመከላከል ለረዥም ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለ አንቲባዮቲክ ሲሆን ለዘመናዊው የመድሃኒት ቴክኖሎጂም ፈር ቀዳጅ የሚባል ነው፡፡
16. ሮኬቶች (ROCKETS) - ቀደምት የሚባለው የሮኬት ቴክኖሎጂ ሙከራ በቻይና የስልጣኔ ዘመናት እንደነበር የሚያወሱ የታሪክ ማዛግብቶች ቢኖሩም አሁን ላይ የሚታወቀው ዘመናዊ የሮኬት ቴክኖሎጂ ግን በ20ኛው ክፍለ ዘመን የተዋወቀ ነው፡፡ ይህ ግኝት በሰው ልጆች የህዋ ምርምር እና የጠፈር አሰሳ ላይ ትልቅ አበርክቶት የነበረው ፈጠራ ሲሆን በወታደራዊው ዘርፍም የማይናቅ አስተዋፅኦ ያለው ነው፡፡
17. የኒውክለር ማብሊያ (NUCLEAR FISSION) - አተሞችን ይበልጥ ጥቃቅን ወደሆኑ ቅንጣቶች መከፋፈል እና በዚህም ከፍተኛ መጠን ያለው ኢነርጂ የመፍጠር ሂደት የኒውክለር ኃይል ማመንጫዎች እና አቶሚክ ቦምቦች እንዲፈጠሩ አስችሏል፡፡ ይህ አስገራሚ ግኘት በ20ኛው ክፍለ ዘመን በዚህ ዘርፍ ዙሪያ ሲሰሩ በነበሩ ስመጥር የፊዝክስ ሊቃውንት የተከናወነ ቢሆንም የኒውክለር ማብሊያውን በዋናነት በመስራት ረገድ ጀርመናውያኑ ኦቶ ሃን እና ፍሪትዝ ስታስመን አንዲሁም የኦስትሪያ ተወላጅ የሆኑት ሊዝ ማይትነር እና ኦቶ ፍሪሲች በቀዳሚነት ይጠቃሳሉ፡፡
18. ሴሚኮንዳክተሮች (SEMICONDUCTOR) - የአሜሪካ ወይም የአለም የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ማዕከል ከሆነችወ ሲልከን ቫሊ ቅጽል ስም ጀርባ የሚገኘው የሴሚኮንዳክተር ግኘት ብዙ ነገሩ ከሲልከን የተሰራ ሲሆን የአፈጣጠር ሁኔታውም በኤሌክትሪክ ዘመን እና እየመጣ በሚገኘው ዲጂታል ዘመን መካከል ላይ ነበር፡፡ የመጀመሪያው የሴሚኮንዳክተር ቁስን የያዘ መሳሪያ እንደአውሮፓውያኑ በ1947 የተዋወቀ ሲሆን በአሜሪካውያኑ ጆን ባርደን እና ዋልተር ብራታን የተሰራ ነው፡፡
19. የግል ኮምፒውተሮች (PERSONAL COMPUTER) - አንደአውሮፓውያኑ በ1970ዎቹ የተፈጠሩት የግል ኮምፒውተሮች የሰው ልጀችን ሁለንተናዊ አቅም በማሳደግ በኩል ተወዳዳሪ አልነበራቸውም፡፡ በ1974 በማይክሮ ኢኒስትሩመንቴሽን እና ቴሌሜትሪ ሲስተም (MITS) የመጀመሪያ የሚባለው የግል ኮምፒውተር ከተዋወቀ በኋላ ቀጥለው የመጡት እንደ አፕል፣ ማይክሮሶፍት እና አይ ቢ ኤም ያሉ ግዙፍ ኩባንያዎች ዘርፉን እስከወዲያኛው አራቀውታል፡፡
20. በይነ መረብ (INTERNET) - አሁን አሁን የሰው ልጅ እስትንፋስ እስከመሆን የደረሰው ይህ አስገራሚ ግኘት ከ1960ዎቹ ጀምሮ ሙከራዎች ሲደረጉበት የቆየ ቢሆንም አሁን በምናውቀም መልኩ ለሰው ልጆች መድረስ የጀመረው ከ1990ዎቹ ጀምሮ ነው፡፡ በጊዜው አንግሊዛዊው ቲም በርነር-ሊ የመጀመሪያውን የበይነ መረብ መግባቢያ የአለም አቀፍ ድር (WWW) ከቀመረ በኋላ አጠቃላይ የአለም መልክ ሊቀየር ችሏል፡፡ ከዚህ ጊዜ አንስቶ ንግዳችን፣ ፖለቲካችን፣ መዘናኛችን የፈለጋችሁን ስም ስጡት ብቻ ሁለ ነገራችን በኢንተርኔት እና በኢንተርኔት ሁኗል፡፡
ምንጭ፡ Bigthink
ውድ የፔጃችን ተከታዮች የቀደመውን ክፍል ወደኋላ ተመልሰው ማየት ይችላሉ
የማያ ህዝቦች የቀን አቆጣጠር
************
የማያ ህዝቦች ሜሶአሜሪካዊ ህንዳውያን ሲሆኑ ግዛታቸውም በተከታታይ ደቡዳዊ ሜክሲኮ፣ ጓቲማላ እና ሰሜናዊ ብራዚል ነው፡፡ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መግቢያ አካባቢ 30 የሚደርሱ የእነዚህ ህዝቦች ቋንቋዎች ከ5 ሚሊዮን በሚበልጡ ሰዎች ይነገሩ ነበር፡፡ ከእነዚህ መካከልም አብዛኛዎቹ በተጨማሪነት የስፓኒሽ ቋንቋ ተናጋሪዎች ናቸው፡፡
እነዚህ ህዝቦች ስፔን ሜክሲኮንና ማእከላዊ አሜሪካን ከመውረሯ በፊት የምእራብ ንፍቀ ክበብ ታላቅ ስልጣኔ ባለቤቶች እንደነበሩ ይነገራል፡፡ ከስልጣኔያቸው መገለጫዎች መካከል እንደ ግብርና፣ የድንጋይ ህንጻዎች፣ የፒራሚድ ቤተ መንግስቶች፣ የወርቅና የብር ስራ እንዲሁም ስዕላዊ ጽሁፎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
የማያ ህዝቦች ከሚታወቁባቸው የስልጣኔ መገለጫዎች አንዱ የዘመን አቆጣጠራቸው ነው፡፡ የቀን አቆጣጠራቸውም 260 የራሳቸው ስም ያላቸው ተከታታይ ቀናትና 365 ቀናት ያሉት አመትን ያካተተ ነው፡፡ የረጅም ጊዜ ዑደት ያለው የ18 ሺ 980 ቀናት ወይም የ52 አመታት አቆጣጠር ሲኖራቸው ይህንንም የዙር ቀን ቆጠራ ወይም ካላንደር ራውንድ ብለው ይጠሩታል፡፡
የ260ው ቀናት የመጀመሪያ ስም በጊዜ ሂደት እንደጠፋ የሚታመን ሲሆን በብዛት ትዞለኪን(Tzolkin) የሚል ስያሜ እንደነበረው ነገራል፡፡ ትርጓሜውም የቁጥር ቀን፣ ተከታታይ የቀን ቆጠራ የሚል ነው፡፡ ትዞልኪን በሚባለው አቆጣጠር ሁለት ንዑሳን ዑደቶች ያሉ ሲሆን የመጀመሪያው ከ1 እስከ 13 የሚደርስ የቀናት ዙር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የ20 የየራሳቸው ስም ያላቸው ቀናት ክትትል ነው፡፡
በማያ ህዝቦች የቀን አቆጣጠር ውስጥ የሚገኙት የአንድ አመት 365 ቀናት 20 ቀናት ባላቸው በ18 ወራት እና አንድ ባለ አምስት ቀናት ስም አልባ ወር የተከፋፈሉ ናቸው፡፡ እነዚህ ስም አልባ አምስት ቀናት በማህበረሰቡ ዘንድ የእድለቢስነት ምልክት ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡ እንደ ታሪክ ተመራማሪዎች እይታ የማያ ህዝቦች ረጅሙ የዘመን አቆጣጠር መነሻው ነሐሴ 11፣ በ3111 ከልደተ ክርስቶስ በፊት እንደሆነ ይታመናል፡፡ ይህም ቀን የረጅሙ የቀን ቆጠራ የመጀመሪያ ቀን ነው፡፡ ይህ ቀን ለባለ 5125 አመታቱ ታላቁ ዑደት መነሻም እንደሆነ ይነገራል፡፡
የታላቁ ዑደት መጨረሻ ታህሳስ 21 2012 በፈረንጆች አቆጣጠር ይሆናል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ከዛሬው የጁፒተር፣ ሳተርንና ፕሉቶ መቀራረብ ጋር ተያይዞ እለቱ ዛሬ ሊሆን እንደሚችልና አቆጣጠሩም ከኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ጋር የተስማማ እንደሆነ አንዳንድ የኢትዮጵያ ስነ ፈለክ ተመራማሪዎች (ሮዳስ ታደሰ (ዶ/ር) ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
ምንጭ፡ Britannica
ወደር የለሽ ፎቶግራፎችን የምታነሳው ሳተላይት
******************
ባለው እጅግ ከፍተኛ ጥራት የተነሳ በምድራችን ያሉ አብዛኛውን ነገሮች በጥራት መመለክከት የምትችለው ሳተላይት አሁን ላይ ለሲቪሎችም አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡ በቅርቡ ለህዝብ ይፋ ካደረጋቸው ባለ ከፍተኛ ጥራት ምስሎች መካከልም ከሳምንታት በፊት በአክሱም ኤርፖርት ላይ የደረሰውን ጉዳት የሚያሳው ይህ ምስል ይገኝበታል፡፡
ካፔላ-2 የሚል ስያሜ ያላትና ሳን ፍራንሲስኮ ውስጥ በሚገኘው ካፔላ ስፔስ በተሰኘ ተቋም የተሰራችው ሳተላይቷ ሲንተቲክ አፓቸር ራዳር (SAR) የተባለውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ለውትድርና፣ አካባቢ ጥበቃ፣ ኃይል እና የሕግ ማስከበር አገልግሎቶች የሚውሉ ጥንቅቅ ያሉ ምስሎችን ታቀርባለች፡፡ አሁን ላይ ማንኛውም ሰው በይነ-መረብን በመጠቀም ተመዝግቦ በሳተላይቷ አማካኝነት ከየትኛውም የምድራችን ክፍል የተወሰደ ጥርት ያለ ምስልን ማግኘት ይችላል፡፡ ቅድሚያ ግን ተመዝጋቢው ከአሜሪካን የዓለም አቀፍ የጦር መሳርያ ዝውውር ተቆጣጣሪዎች ፍቃድ ማግኘት ይኖርበታል፡፡
50 ሴ.ሜ በ50ሴ.ሜ የሆነ ስፍራን ምስል መውሰድ የምትችለው ካፔላ ይህ ቴክኖሎጂያዊ አቅሟ ከማንኛውም ሳተላይት በላቀ የጠራ ምስል መስጠት የምትችል እንድትሆን አድርጓታል፡፡ ካፔላን ከሌሎች ይህን ቴክኖሎጂም ሆነ ተለምዶአዊውን የኦፕቲካል ፎቶግራፊክ ፕሮሰሲንግ ስልት ከሚጠቀሙ ተፎካካሪዎቿ የሚለያት ሌላው ብቃቷ ደግሞ በማንኛውም የአየር ፀባይ ውስጥ እንዲሁም በቀንም ሆነ በማታ ፎቶግራፎችን ማንሳት መቻሏ ነው፡፡ በዚህ አማካኝነትም ሳተላይቷ ሰደድ እሳቶችን፣ የነዳጅ ማውጣት እንቅስቃሴዎችን፣ በአየር ንብረት ለውጥ የተጎዱ አካባቢዎችን እንዲሁም ሕገ-ወጥ አደንን የመቆጣጠር ኃይል አላት፡፡
በቀን ውስጥ በእያንዳንዱ ሰዓት ምድራችን ግማሽ ክፍሏ ፀሐያማ የተቀረው ደግሞ በምሽት ሲዋጥ በአማካኝ ግማሹ የመሬት ክፍል በደመና ውስጥ ነው የሚለው ቀድሞ በናሳ በሲስተም መሃንዲስነት ያገለገለው የአሁኑ የካፔላ ስፔስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፓያም ባናዛዲ ይህ በአማካኝ 75 በመቶ የሚሆነው የምድራችንን ክፍል ጨለማ ወይም ደመናማ የያደርገዋል ሲል ይነገራል፡፡ የሰብአዊ ስራዎችን እንደ አንድ ተግባር በመጥቀስ ካፔላ-2 ምድራችንን በየትኛውም የአየር ፀባይ እና ብርሃን ሁኔታዎች ውስጥ ሳለች እንኳን አስተማማኝ መረጃ መስጠት እንደምትችል አክሎ ተናግሯል፡፡
ፓያም ይህን ሳተላይት እውን እንዲያደርግ መነሻ የሆነለት ከ6 ዓመታት በፈት በረራ ላይ እያለ ድንገት የተሰወረው የማሌዢያ አየር መንገዱ በረራ ቁጥር 370 አውሮፕላንን ለማግኘት የተደረጉ ስኬት አልባ አሰሳዎችን በመመልከትና ነገሮችን በተሻለ ለመከታተል ብሎም የምንኖርባት ምድርንም የበለጠ ለመረዳት የሚያስችል ነገር ይኖር ዘንድ ባደረበት ፍላጎት ነው፡፡ አሁን ላይ ተቋሙ በህዋ አንድ ሳተላይት ያለችው ሲሆን በቅርቡም በስፔስ ኤክስ አማካኝነት ሌላ ለመጨመር አቅዷል፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ይህ የሳተላይቷ ብቃት እርሷን አስመልክቶ እጅግ ኃይለኛ ከመሆኗ የተነሳ ወደ ህንፃዎች ውስጥ ሁሉ ለማየት ትችላለች የሚል አሉባልታን አስነስቶባት ነበር፤ ፓያምም አርብ ላይ ነገሩን በቲዊተር ገፁ ላይ እንዲያስተባብል ተገዷል፡፡
ምንጭ፡ Tech Xplore