TechIn2
1.22K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
በቂና የተመጣጠነ ምግብ ለሁሉም
-----------------------------
የአመጋገብ ባህላችንን መቀየሩ ቀላል ቢሆን ኖሮ በንጥረ ነገሮች የበለፀገ ተመጣጣኝ ምግብ ካለመመገብ ጋራ የተያያዙ ሁሉም ችግሮች ከዘመናት በፊት በተወገዱ ነበር፡፡ ሁሉም የምድራችን ነዋሪም በጤና ሊያቆየው የሚችለውን ምግብ በበቂ ሁኔታ ማግኘት በቻለ ነበር፡፡ 44 የዓለም ሀገራትን ተሳታፊ አድርጎ በአውሮፓውያኑ 1943 በተካሄደው ታሪካዊው የሆት ስፕሪንግ ምግብና ግብርና ኮንፈረንስ ላይ “ደህንነቱ የተጠበቀ በቂና ዘላቂ የምግብ አቅርቦት ለሁሉም” የሚለውን ሀሳብ ወደ ዓለም መድረክ የመጣና እንዲሁም ከሰላሳ ዓመታት በኋላ የተካሄደው የ1974ቱን የሮም የምግብ እና ግብርና ኮንፈረንስ ላይ ሁሉም የሰው ልጅ ከረሀብ ነፃ የመሆን እና ለተሟላ እድገት መረጋገጥ መሰረታዊ በሆኑ ንጥረ ነገሮች የዳበረ ምግብን የማግኘት መብት እንዳለው የተመጠ ቢሆንም ይህ ሁሉ ግን በምኞት ብቻ የቀረ ሆኗል፡፡
እውነታው እኛ የሰው ልጆች ዛሬም መጠነ ሰፊ የአመጋገብ ችግር ውስጥ መሆናችን ነው፡፡ ሁኔታው እጅግ የተወሳሰበ እና ብዙ ነገሮችን የያዘ ቢሆንም ቅሉ እንዲሁ በጠቅላላው ስናየው ግን አሁንም ብዙዎች ይራባሉ፣ በንጥረ ነገሮች የበለፀገ ተመጣጣኝ ምግብን በማግኘት ረገድ በደሃ እና ሀብታም ሀገራት ወይም ክፍለዓተ ዓለማት መካከል ያለው ልዩነት እጅጉን ሰፊ ነው፣ ከምርት እስከ ማከፋፈል ድረስ የሚዘረጋው የምግብ አቅርቦት ስርዓታችንም ቢሆን እኛንም ሆነ ምድራችንን እየጎዳ ይገኛል፡፡ ወደ አንደኛ ዓመቱ የተጠጋው የኮቪድ-19 ወረርሺኝ ደግሞ በምግብ ስርዓታችን ውስጥ ያሉ ችግሮችን ይባስ ያጋለጠ ሆኗል፡፡ የፖለቲካ፣ ምጣኔ-ሐብት እና ባህል ተግዳሮቶችም ዘላቂ በሆነ ሁኔታ ዓለም አቀፋዊውን የዓመጋገብ ልማድ እንዳይለወጥ አድርገዋል፡፡ የቱን እንመገብ በሚለው ላይ ከስምምነት ተደረሰ ብንልም እንኳን ይህን በስፋት መተግበሩ ትልቅ እና በደንብም ያልተጠና ተግዳሮት ነው፡፡
የስነ-ምግብ ተመራማሪዎች አንደሚያሰቀምጡት ከሆነ ለሰው ልጆች አካላዊም ሆነ አዕምሮአዊ ጤና ብሎም ለተፈጥሮ አካባቢ ተስማሚነት ከስጋና ስጋ ተዋፅዖዎች ይልቅ በዋናነት እፅዋትን መሰረት ያደረገ አመጋገብን መከተሉ አስፈላጊ ነው፡፡
ግን ደግሞ ያለ መፍትሄ ፍለጋ ዝም ብለን አልተቀመጥንም፤ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የተለያዩ እርምጃዎች በመወሰድ ላይ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ በግብርና የሚገኘውን ስጋ ለመቀነስ በዓለም ዙርያ ያሉ ተመራማሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ልናገኛቸው የምንችላቸው የፕሮቲን አማራጮችን ወደ መመገቢያ ትሪያችን ለማምጣት እየታተሩ ይገኛሉ፡፡ አሁን ላይ በሚወጡ ትንበያዎች መሰረትም የዛሬ 30 ዓመት በሰው ሰራሽ መንገዶች ከሚከወነው የአሳ እርባታ (Aquaculture) የሚገነው የአሳ ምርት ከተፈጥሮ የውሃ አካላት ተጠምዶ ከሚገኘው የላቀ ምርትን እንደሚያስገኝ ነው፡፡ የግብርና ምርትን የሚያሳድጉ ግን ደግሞ የተፈጥሮ አካባቢንም በዘላቂነት የሚጠብቁ የግብርና ስልቶችን የመጠቀም ልምዳችንም ከጊዜ ወደ ጊዜ በማደግ ላይ ይገኛል፡፡
በአውሮፓውያኑ 2050 በምድራችን ላይ የሚኖረው ሰው ብዛት 10 ቢሊዮን እንደሚደርስ ከትንበያዎች መረዳት እንችላለን፡፡ ይህ አሁን ባለው ህዝብ ላይ ሌላ የቻይናን ህዝብ ሁለት እጥፍ ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑ አዳዲስ ምግብ ፈላጊ ነዋሪዎችን መጨመር ማለት ነውና ለዚህ ሁሉ ህዝብ የተመጣጠነ ምግብንም አቅርቦ የምንኖርባት ምድርንም ከከፋ ጉዳት ጠብቆ መጓዙ ሁሉን አቀፍ የጋራ ስራን ይጠይቃል፡፡ ታድያ ዘላቂ የሆነ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን ለሁላችንም የሚያረጋግጥ መፍትሄ ከአንድ ወገን ብቻ ማግነቱ ለስኬት አይረዳም፡፡ አሁን ያለንበት የኮቪድ-19 ወረርሺኝ የተቀናጀና ሁሉን ያስተባበረ ዓለም አቀፋዊ ምላሽን እንደሚሻው ሁሉ የሰው ልጆችን በንጥረ ነገሮች በበለፀገ ተመጣጣኝ ምግብ መመገቡም እንዲሁ በሳይንስ የታገዘና የተቀናጀ ዘላቂ ዓለም አቀፋዊ ተግባርን ይጠይቃል፡፡
ምንጭ፡ ቴክ ሳይንስ መሔት (ቅፅ 5 ቁ.17) እና Nature
የ3D ማተሚያዎች የሚያስከትሉት የጤና ችግር
**********************
የ3D ማተሚያዎች የሚለቋቸው ቅንጣቶች ወደ ሳንባችን ዘልቀው በመግባት ከፍተኛ የጤና ችግር እንደሚያስከትሉ ተነገረ፡፡ ተመራማሪዎች ይህ ተፈላጊነቱ ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ የመጣው የ3D ህትመት በተጠቃሚዎች እንዲሁም በህጻናት ላይ ሊያመጣ የሚችለውን የጤና እክል ከፍተኛ ሆኖ በመታየቱ ትልቅ ጥያቄ አንስተውበታል፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ በተለይ በቤት ውስጥ፣ በትምህርት ቤቶች፣ በቤተ-መጽሐፍቶች እና በሌሎች ሰዎች በብዛት ጊዜያቸውን በሚያሳልፉባቸው ቦታዎች ተፈላጊነቱ እየጨመረ መጥቷል፡፡
በህትመት ወቅት የሚለቀቁት ብናኞች በጣም ጥቃቅን በመሆናቸው ወደ ሳንባችን ዘልቀው መግባት የሚችሉ ሲሆኑ የአንድን አካባቢ የአየር ጥራት በመቀነስ የህብረተሰብ ጤና ጉዳት ያስከትላሉ፡፡ ለጊዜው የተለያዩ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎችን መጠቀም እንደ መፍትሔ የተወሰደ ቢሆንም ዘለቄታዊ መፍትሔ ሊሆን እንደማይችል ግን ተመራማሪዎቹ ይናገራሉ፡፡
በያዝነው የታህሳስ ወር ቁጥራቸው ብዙ የሆነ የ3D ማተሚያ ብናኞችን መጠን፣ በአየር ላይ ያላቸውን የቆይታ ጊዜ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ጥናቶች በኢንተርኔት በተካሄደው አመታዊው ሊደርሱ የሚችሉ ጉዳቶችን የሚተነትን ጉባኤ (Society for Risk Analysis) ቀርበዋል፡፡
ለ3D ህትመት የሚስፈልጉት መሰረታዊ ግብዓቶች ቴርሞፕላስቲክ፣ ብረት፣ ብረት ነክ ያልሆኑ ነገሮች፣ እንዲሁም ተቀጣጣይ የሆኑና ተቀጣጣይ ያልሆኑ ኬሚካሎች ናቸው፡፡ የህትመት ስራው ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ በሂደቱ የተለያዩ የኬሚካል ተረፈ ምርቶችና ብናኞች ይለቀቃሉ፡፡ በተሰሩ ጥናቶችም እነዚህ ብናኖች በሰዎች የሳንባ ህዋሳት ላይ ጉዳት እንደሚደርሱ ታውቋል፡፡
ይህ የህትመት ሂደት አለማችን በእጅጉ እየተጎሳቆለችበት ያለውን የፕላስቲክ ምርቶች ብክለት ለመቀነስ የሚስችልና ከዋጋ አንጻርም ቀላል በመሆኑ አስፈላጊነቱ የማያጠያይቅ ነው፡፡ ነገር ግን በጊዜ ሂደት በሰዎች ጤና ላይ ጉዳት የሚያደር ከሆነ አፋጣኝ መፍትሔ የሚያሻው ነው ሲሉ በዘርፉ ላይ ጥናት ያካሔዱ ተመራማሪዎች ይመክራሉ፡፡ በዚህም የ3D ህትመት ቴክኖሎጂ እየተስፋፋ የሚሔድ በመሆኑ አምራቾች፣ ተቆጣጣሪዎችና ተጠቃሚዎች ስጋትን በሚቀንስ መልኩ ስራዎችን መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
ምንጭ SciTechDaily
TECHIN seminar
በዚህ ሳምንቱ የቴክኢን ሴሚናር “Understanding and Managing Change” በሚል ርዕስ በአቶ አብዱለጢፍ ሀቢብ ገለፃ አቅራቢነት የሚመራ ውይይት የሚደረግ ይሆናል፡፡
ስፍራው፡ 4 ኪሎ በሚገኘው የዋናው ቢሮዋችን መሰብሰቢያ አዳራሽ
ቀን፡ ነገ ሐሙስ ታህሳስ 07፤ 2013 ዓ.ም
ሰዓት፡ ከጠዋቱ 3፡00-4፡30
In this week’s TECHIN seminar Mr. Abduletif Habib will discuss Understanding and Managing Change.
Location፡ TECHIN meeting hall in our head office (4 kilo)
Date: Thursday, December 17, 2020
Time: 9:00-10:30 AM
This media is not supported in your browser
VIEW IN TELEGRAM
20ዎቹ የምንግዜም ታላላቅ ኢኖቬሽኖች
በሰው ልጆች ረዥም የህይወት ጉዞ ውስጥ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚና እንዲ በቀላሉ የሚገለፅ ጉዳይ አይደለም፡፡ ሰዎች ወደዚች ምድር ከመጡ አንስቶ አካላዊውን ዓለም ለመግራት የሚያስችሉ የተለያዩ ፈጠራዎችንና የኢኖቬሽን ውጤቶች ያለማቋረጥ ሲተገብሩ ቆይተዋል፡፡ እነዚህ መሳሪያዎች አለም አሁን ያላትን መልክ ያጎናፀፏት እና የቀጣዩንም ትውልድ እጣ ፋንታ በበጎም ይሁን በክፉ የመወሰን አቅማቸው በእጅጉ የተጠበቀ ነው፡፡ አለማችን እስካሁን ያየቻቸውን የኢኖቬሽን ውጤቶች ለሰው ልጆች ከሰጡት ግልጋሎት እና በታሪክ ውስጥ ካላቸው ተጽዕኖ አንፃር ተመልክተን ለማስቀመጥ ከሞከርን የሚከተሉት ኢኖቬሽኖች ከምንግዜም ታላላቆቹ መካከል ይገኙበታል፡፡ በዘመን ቅደም ተከተል ፡
1. እሳት (FIRE) - ስለእሳት ስናነሳ ብዙዎች የሚከራከሩበት ጉዳይ ቢኖር እሳት ተፈለሰፈ ከሚባል ይልቅ ተገኝቷል የሚለው ሃሳብ እጅግ ተስማሚ መሆኑን ነው፡፡ ቀደምት የሰው ዘሮች እሳትን እንዴት መፍጠር እና መቆጣጠር እንደሚችሉ ከማወቃቸው በፊት የእሳትን አደጋዎች በየአጋጣሚው ተመልክተው ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን የእሳትን ምንነት ከተረዱና የሚሰጣቸውን ጥቅም ካወቁ በኋላ እሳትን እንደ አንድ ትልቅ መገልገያ መጠቀም ጀምረዋል፡፡ አንዳንድ የአርኪዎሎጂ አጥኝዎች እሳት ጥቅም ላይ የዋለው ከ2 ሚሊዮን አመት በፊት ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ 125 ሺ አመታት እንዳስቆጠረ ይገልፃሉ፡፡ ይህ ክርክር ምንም ተባለ ምንም በሰው ልጆች ታሪክ ታላቅ ግኝት የሆነው እሳት ሰዎች ራሳቸውን ከተለያዩ ነገሮች እንዲከላከሉ እና ማብሰል የሚባለውን ትልቅ ክህሎት እንዲረዱ ያስቻል አስገራሚ ግኝት ነው፡፡
2. ተሽከርካሪ ጎማ (WHEEL) - ይህ ፈጠራ የተገኘው በ3500 ዓመተ ዓለም (B.C) በሜሶፖታሚያ የስልጣኔ ዘመን ነበር፡፡ የሜሶፖታሚያ ህዝቦች ይህንን አስገራሚ ፈጠራ የሸክላ ቁሳቁሶችን ለማበጃጀት ሲጠቀሙበት የቆየ ቢሆንም ከሶስትና አራት መቶ አመታት በኋላ ፈጠራው ለሰረገላ ማሽከርከሪያ ጥቅም ላይ ከዋለ በኋላ የመሳሪያው ተፅዕኖ እጅግ እየናኘ ሄዷል፡፡ ተሽከርካሪ ጎማ ለሰው ልጆች የመጓጓዣ እና የንድግ ስርዓት መፈጠር ትልቅ ሚና ያለው ግኝት ነው፡፡
3. ኦፕቲካል ሌንሶች (OPTICAL LENSES) - የሰዎችን የእይታ አቅም ይበልጥ ለመጨመር እንደ ኦፕቲካል ሌንሶች ያሉ አስገራሚ ግኝቶች እጅግ ወሳኝ ነበሩ፡፡ ረዥም የፈጠራ ሂደት የነበራቸው እነዚህ ግኝቶች በጥንቱ የግብፅ እና የሜሶፖታሚያ የስልጣኔ ዘመን እንደበለፀጉ የሚታመን ሲሆን ከግሪክ የተገኙት የብርሃን ንድፈ ሃሳቦች ደግሞ ለግኝቱ እውን መሆን ትልቅ ሚና ነበራቸው፡፡ ኦፕቲካል ሌንሶች እንደቴሊቭዥን፣ ፎቶግራፍ እና ፊልም ያሉ ትልልቅ የሚዲያ ቴክኖሎጂዎች እንዲፈጠሩ መንገድ የጠረጉም ናቸው፡፡
4. ኮምፓስ (COMPASS) - ይህ እንቅስቃሴን ለመምራት የተዘየደው የቴክኖሎጂ ግኝት የሰው ልጆችን የአሰሳ ጥበብና አቅም ወደ አዲስ ምዕራፍ በመወሰድ ተተኪ የማይገኝለት አስገራሚ ግኝት ነው፡፡ የመጀሪያዎቹ ኮምፓሶች በተፈጥሮ የመግነጢሳዊ ይዘት ባላቸው የማዕድን ቁራጮች ወይም (lodestone) አማካኝነት የተሰሩ ሲሆን፤ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ 300 እና 200 አመተ አለም አካባቢ በቻይና እንደተሰሩም ይነገራል፡፡
5. ወረቀት (PAPER) - በ100 ዓመተ አለም አካባቢ በቻይና የተፈለሰፈው ይህ ግኘት የሰው ልጆችን የፅህፈት እና ሃሳብን የማጋራት ልምድ በእጅጉ የቀየረ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ ከዚህ ጊዜ በፊት በግብፅ እና በሜክሲኮ የስልጣኔ ዘመናት የተፈለሰፉት እንደ ፓፒረስና አሜት ያሉ የመፃፊያ ቁሶች ለወረቅት መፈጠር አስተዋፅዖ ቢኖራቸውም በቻይና የነበረው ግኝት ግን አሁን ላለው የወረቀት ቴክሎጂ ትልቅ መሰረት የጣለ ነው፡፡
6. ባሩድ (GUNPOWDER) - ከተለያዩ የኬሚካል ንጥረ ነገሮች ተቀይጦ የሚሰራው ይህ ተቀጣጣይ ፈንጂ በ9ኛው ክፍለ ዘመን በቻይና እንደተፈለሰፈ የሚነገር ሲሆን ለዘመናዊው የጦር ቴክኖሎጂ መስፋፋትም ፈር ቀዳጅ የሚባል ነው፡፡ ይህ ግኘት በሰው ልጆች የውጊያ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ተፅዕኖ ያሳደረ መሆኑም ይነገርለታል፡፡
7. ማተሚያ (PRINTING PRESS) - እንደአውሮፓውያኑ በ1439 በጀርመናዊው ዮሃንስ ጉተንበርግ የተፈጠረው ይህ መሳሪያ ለሰው ልጆች የአዲስ ህይወት መጀመሪያ ዘመን ተደርጎ በብዙዎች ይወሰዳል፡፡ ይህ አስገራሚ ቴክኖሎጂ በሰዎች እጅ እየተፃፈ የሚሰራጨውን አድካሚ የፅህፈት ስርዓት በሜካናይዝድ ማሽን በመተካት የእውቀት አድማስ በሰዎች ዘንድ በቀላሉ እንዲሰፋፋ እና የሃይማኖት አስተምህሮዎች በአለም ላይ በፍጥነት እንዲናኙ ያስቻለ አስገራሚ ግኘት ነው፡፡
8. ኤሌክትሪክ (ELECTRICITY) - የኤሌክትሪክ ፈጠራ ብዙ ብሩህ አዕምሮዎች ለሺህና ከዚያ በላይ አመታት አስተዋፅዖ ያደረጉበት እፁብ ድንቅ የሆነ የቴክኖሎጂ ግኝት ነው፡፡ በ18ኛው ክፍለ ዘመን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ቤንጃሚን ፍራንክሊን ስለኤሌክትሪክ የነበረውን የአለም መረዳት አንድ እርምጃ ያራመደ የመሪነት አበርክቶት እንደነበረው የሚገለፅ ሲሆን በምርምር ዘርፍ ደረጃ ለመስኩ የሰጠው ሁለንተናዊ ትኩረት የቴክኖሎጂውን እድገት በእጅጉ አፋጥኖታል፡፡ ከዚህ ሂደት በማስከተል በ1879 የቶማስ ኤዲሰን የብርሃን አምፖል መፈጠር የኤሌክትሪክ ቴክኖሎጂ ይበልጥ ወደሰዎች እንዲቀርብ ያስቻለ ክስተት ነው፡፡ ይህ የምንግዜም ታላቅ ፈጠራ የሰው ልጆችን የህይወት መንገድ እስከወዲያኘው የቀየረ ግሩም ቴክኖሎጂ ነው፡፡
9. የእንፋሎት ሞተር (STEAM ENGINE) - በስኮትላንዳዊው የፈጠራ ባለሙያ ጀምስ ዋት ከ1763 እስከ 1775 ተሰራ የሚባለው የእንፋሎት ሞተር ሌላኛው ለሰው ልጆች ትልቅ መሰረት የጣለ አስደናቂ የፈጠራ ውጤት ነው፡፡ ይህ የቴክኖሎጂ ግኝት በጊዜው ለነበሩት ባቡሮች፣ መርከቦች እና በጠቅላለው ለኢንዱስትሪው አብዮት ዋና የሃይል ምንጭ በመሆን ተከትሎ ለመጣው የሰው ልጅ አብርሆት ታላቅ ውለታ ያደረገ አስገራሚ ፈጠራ ነው፡፡
10. የነዳጅ ሞተር (INTERNAL COMBUSTION ENGINE) - በ19ኛው ክፍለዘመን የተዋወቀው ይህ የቴክኖሎጂ ፈጠራ በመጀመሪያ በቤልጄሚያዊው ኢንጅነር ኢትየን ሌኖየር (በ1859) የተፈጠረ ሲሆን ከጥቂት አመታት በኋላ በጀርመናዊው ኒኮላስ ኦቶ ይበልጥ ሊሻሻል ችሏል፡፡ ይህ አስገራሚ ፈጠራ የኬሚካል ኢነርጂን ወደ ሜካኒካል ኢነርጂ በመቀየር ቀድሞ የእንፋሎት ሞተር ሲሰጥ የነበረውን ግልጋሎት በተሻለ ሁኔታ በመተካት ለዘመናዊ መኪናዎችና አውሮፕላኖች ማገልገል የቻለ አስገራሚ ፈጠራ ነው፡፡
ምንጭ፡ Bigthink
ውድ የፔጃችን ተከታዮች 10ን የኢኖቬሽን ውጠቶች በቀጣይ ፅሁፍ የምናቀርብላችሁ ይሆናል፡፡
“ጆሮውን ሰጥቶ ለሚሰማ አለማችን ሁሌም ቢሆን የለዉጥ ያለህ በሚል የማያቋርጥ ጩኸት ውሰጥ እንዳለች ያስተዉላል”
===================
“ለዉጥን መረዳትና ማስተዳደር” በሚል ርዕስ የተዘጋጀው የዚህ ሳምንቱ የቴክኢን ሴሚናር ዛሬ ማለዳ በቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ተካሂዷል፡፡ መድረኩ ላይ በኢንስቲትዩቱ ውስጥ በተመራማሪት በሚያገለግሉት አቶ አብዱለጢፍ ሀቢብ አማካኝነት ስለ ለውጥ ምንነት፣ ባህርያት እና ሌሎችም ዝርዝር ጉዳዮች ገለፃ ቀርቦበታል፡፡
“ጆሮውን ሰጥቶ ለሚሰማ አለማችን ሁሌም ቢሆን የለዉጥ ያለህ በሚል የማያቋርጥ ጩኸት ውሰጥ እንዳለች ያስተዉላል” ያለው አቶ አብዱለጢፍ እኛ የሰው ልጆች ከአደን ሕይወት አንስቶ አሁን እስካለንበት የመረጃ ዘመን ድረስ ታላላቅ ለውጦችን ማስተናገዳችንን ጠቅሷል፡፡ በለውጥ ሂደት ውስጥ ሁለት ተፃራሪ ኃይሎች፤ ማለትም ቆስቋሽ እና መካች ኃይሎች መኖራቸው የተገለፀ ሲሆን በዚህ የለውጥ ሂደት ውስጥም ተቀዳሚው ፈተና የአመለካከት ውስንነት መሆኑ ተቀምጧል፡፡ በተጨማሪም የለውጥ ዋና ምሰሶዎች የሆኑትን ስለ ለውጥ አስፈላጊነት ግንዛቤ መፍጠር፣ በለውጡ ላይ ለመሳተፍ እና ለመደገፍ ያለ ጽኑ ፍላጎት፣ ለውጡ እንዴት እንደሚመጣ ያለ ዕውቀት፣ ለውጡን ለመተግበር /ለማከናወን የሚያስፈልግ ችሎታ/ክሕሎት እና ለውጡን ለማስቀጠል የሚደረገግ ማበረታቻ በአግባቡ ተሟልተው ከተገኙ አንድን ለውጥ ስኬታማ እንደሚያደርገው ተነግሯል፡፡
የለውጥ አመራር ሂደቶችን በተመለከተም ለውጥ ሲሳካ ወይም ተሰናክሎ የሚቀርበት ዋናው ምክንያት የለውጥ አመራሩን ሰብዓዊ ጎን በበቂ ሁኔታ መምራት ባለመቻሉ ነው ሲል አቶ አብዱለጢፍ ተናግሯል፡፡ አከሎም የለውጥ አመራር በዋናነት የለውጥ እንቅፋቶችን ለመምራት፣ የስኬት ዕድሉን ለማስፋት እና የሽግግር ጊዜውን ለማሳጠር እንደሚያስፈል ተናገሮ በአንፃሩ የለውጥ ሰብዓዊ ጎኑን መምራት አለመቻል የአሰራሮች ወደ ኃላ መመለስ፣ የምርታማነት መቀነስ፣ ግልፅ እና ስውር ተቃዉሞዎች እንዲሁም የእኛ እና የእነሱ የሚል ቡድናዊ አመለካከት መፈጠርን ጨምሮ በርካታ ተፅዕኖዎችን እንደሚፈጥር አስቀምጧል፡፡
መድረኩ ሌሎች የኢንስቲትዩቱ ሰራተኞችንም ተሳታፊ ያደረገ እንደመሆኑ የለውጥ አይነቶች፣ ከማህበረሰብ አንፃር ስለሚኖረው ግበረ መልስ እና ሌሎችም ጥያቄዎች ቀርበው በአቶ አብዱለጢፍ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
የቆዳ ጫማ ማቀነባበር እና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍን ለማገዝ የሚረዳ ወርክሾፕ በመካሄድ ላይ ነው
የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት በዛሬው ዕለት ያዘጋጀው የቆዳ ጫማ ማቀነባበር እና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍን ለማገዝ የሚረዳ የባለድርሻ አካላት ውይይት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ወርክሾፕ በመካሄድ ላይ ነው፡፡ ለአንድ ቀን በሚቆው በዚህ የውይይትና የወርክሾፕ መርሃ ግብር ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት የተወጣጡ ባለድርሻ አከላት እና በግሉ ዘርፍ የሚንቀሳቀሱ አነስተኛና መካከለኛ የቆዳ ጫማ አምራች ኢንተርፕራይዞች እንዲሁም ሌሎች የቆዳ ውጤት አምራች ድርጅቶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
በመርሃግብሩ መጀመሪያ ስለኢኒስቲትዩት አጠቃላይ አደረጃጀት እና ተቋማዊ ሃለፊነቶች ገለፃ ያደረጉት የሴክተር ሞደርናይዜሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰልማን መሃመድ ኢኒስቲትዩቱ በተሰጠው ሃለፊነት መሰረት የሀገሪቱን የአሰራር ስርዓት የማዘመን ተልእኮ በማእከላዊነትና ባስተሳሳሪነት በመምራት የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚፋጠንበት እና ለተለያዩ ኢንተርፕራያዞች ድጋፍ የሚደረግበት ሂደት እንዳለ አስረድተዋል፡፡ አቶ ሰልማን አከለውም በዛሬው ዕለት የተዘጋጀው የውይይት እና የወርክሾፕ መርሃ ግብር በዚህ አግባብ መሰረት ከተለያዩ የመንግስትና የግል ተቋማት የተወጣጡ ባለድርሻ አከላት እና በግሉ ዘርፍ የሚንቀሳቀሱ አነስተኛና መካከለኛ የቆዳ ጫማ አምራች ኢንተርፕራይዞች ቀርበው መወያየት እንዲችሉ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲፈጠር ያለመ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የቆዳ ኢንዲስትሪ ልማት ኢንስቲትዩትን ወክለው የተገኙት የተቋሙ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃይለኪሮስ ደበሳይ በቆዳ ጫማ እና በቆዳ ምርቶች ዘርፍ ላይ የሚታየውን ዘርፈብዙ የጥራት ችግሮችን እና ሊወሰዱ በሚገቡ የመፍትሄ ሃሳቦች ላይ ሰፊ ገለፃ አድረገዋል፡፡ አቶ ሃይለኪሮስ በተለይም ሃገሪቱ ከዚህ ዘርፍ ይበለጥ ለመጠቀም የሚያስችላት ተፈጥሮአዊ ሃብት እና ሰፊ የገበያ አማራጭ የያዛች መሆኑን አስረድተው ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን ይበልጥ ተቀራርቦ መሰራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የሴክተር ሞደርናይዜሽን ዳይሬክተር ያዘጋጀው ይህ መርሃ ግብር በባለድረሻ አካለት ዙሪያ በሚደረግ ውይይት የቀጠለ ሲሆን በቀረቡ የቴክኖሎጂ አማራጮች እና የማሽነሪ ግብዓቶች ዙሪያም የወርክሾፕ መርሃ ገብር ይካሄዳል፡፡
የፊታችን ሰኞ 12/04/13 የሚጠበቀው የጁፒተርና የሳተርን ነገር
***********************
በያዝነው ሳምንት ጁፒተርና ሳተርን በደቡብ ምእራብ በኩል ዝቅ ብለው የሚገኙ ሲሆን በወሩ መጀመሪያ አካባቢ በ2.1 ዲግሪ ተራርቀው ነበር ይለናል ከስፔስ ዶት ኮም ያገኘነው መረጃ፡፡ ይሁን እንጂ ወሩ እየገፋ በሔደ ቁጥር በመካከላቸው ያለው ርቀት እየቀነሰ መጥቷል፡፡ ይህ መቀራረባቸው በየእለቱ በ0.1 ዲግሪ እየቀነሰ የፊታችን ሰኞ ግሬት ኮንጃንክሽን ወይም ታላቁ ጥምረት የተሰኘውን ክስተት እናያለን ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡
ይህ ክስተት በስነ ፈለክ ምርምር ከተሰማሩት አልፎ የብዙዎችን ትኩረት የሳበ ሁኗል፡፡ ከስተቱም ፀሐይ ከጠለቀች ከ30 ደቂቃ በኋላ የሚጀምር ሲሆን ጨረቃን፣ ሳተርንንና ጁፒተርን አንድ ላይ ለማየት የተሻለው ሰዓት ከሩብ ጉዳይ ለ1 እስከ አንድ ተኩል በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር እንደሚሆን የመረጃ ምጫችን አስነብቧል፡፡
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲም ክስተቱን ከባላገሩ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር እና ከሌሎች አጋሮች ጋር በመተባበር በቀጥና ለማሳየት ማቀዱን ከተቋሙ የማህበራዊ ድረ-ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ምንጭ Space.com
Capture ts.PNG
571 KB
ቅዳሜን ከቴክ-ሳይንስ ጋር ያሳልፉ
በዚህ ሳምንት የቴክ ሳይንስ ሳምንታዊ የቴሌቪዥን ፕሮግራማችንም አስተማሪ ናቸው ያልናቸውን ልዩ ልዩ ዝግጅቶች አሰናድተን ከናንተው ዘንድ ለማድረስ ነገ 10 ሰዓትን እየጠበቅን ነው፡፡
የግብርና ምርምር ስራዎች አጀማመር በኢትዮጵያ ምን መልክ እንዳለው የሚዳስስ ዝግጅት አብይ ፕሮግራማችን ላይ የምናቀርብላችሁ ሲሆን እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ በርካታ ታዳጊዎችን በሮቦቲክስ ዘርፍ ለማብቃት እየሰራ ያለው ፋሪስ ሮቦቲክ ሴንተርንም እናስተዋውቃችኋለን፡፡
እንደተለመደው ታዳጊ የፈጠራ ባለሙያዎችን ስራ ለእናንተው የምናደርስበት የብላቴናት ዝግጅታችንም የሽንኩርት መፍጫ የሰሩት የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ህፃናትን፤ የቴክኖሎጂ ታሪክም በየቤታችን ጓዳ ስለሚገኙት ፍሪጆች ዳሰሳ የሚያቀርቡላችሁ ይሆናል፡፡ የስኮላርሺፕ ዕድል ጥቆማም ይኖረናል፡፡
ያስታውሱ ዘውትር ቅዳሜ 10 ሰዓት በድጋሚ ደግሞ ማክሰኞ በተመሳሳይ ሰዓት በMOE TV ላይ ያገኙናል፡፡
ያለፉ ፕሮግራሞች ተሟልተው የተቀመጡበት የዩትዩብ ቻናላችንንም ሊንኩን ተጠቅመው ሰብስክራይብ ማድረጉን እንዳይረሱ https://www.youtube.com/channel/UC6jvUOLRSkVEQtc5Annfwvg ፡፡
አካላዊና አእምሯዊ ጤናን የሚያሳድገው ባክቴሪያ
***************************
ተመራማሪዎች አካላዊና አእምሯዊ ጤናን የሚያሳድገውን ባክቴሪያ መለየታቸውን የዘገበው ሜዲካል ኤክስፕረስ ነው፡፡ በአለማችን ከ1980 ጀምሮ ባለው ሁኔታ ከልክ ያለፈ ውፍረት በተቃራኒው ካለው በበለጠ የሰዎችን ህይወት እንደሚቀጥፍ ይነገራል፡፡
ከልክ ያለፈ ውፍረት የአለማችን ትልቅ ችግር የሆነው ይህን ሰበብ አድርገው ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ በሽታዎች በሳይንስ type 2 diabetes የሚባሉት የሰውን ልጅ በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚያጠቁ ነው፡፡ እንዲህ ባሉ በሽታዎች ከአለማችን ህዝብ ቁጥር 6.28 በመቶ ወይም 462 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ተጠቂዎች እንደሆኑ በቅርብ ጊዜ የወጡ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ በአይርላንድ በሚገኝ አንድ የምርምር ተቋም የሚሰሩ ተመራማሪዎች ቢፍዶባክቴሪየም ሎንገም APC1472 የተባለው ባክቴሪያ የሰዎችን የምግብ ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቆጣጠር ተናግረዋል፡፡
ሙሉ ጤና ኖሯቸው ወፍራም በሆኑ ሰዎች ምርምሩ ተሞክሮ ይህ ባክቴሪያ ያላቸውን የስኳር መጠን በመቀነስ የረሀብ ስሜትን የሚቀሰቅሰውን ሆርሞንና ለጭንቀት የሚዳርጉ ሆርሞኖችን እንደሚያስተካክል ተረጋግጧል፡፡ በዚህም ይህ ባክቴሪያ ለበሽታ የሚያጋልጠውን የደማችንን የስኳር መጠን ለመቀነስ ከፍተኛ ሚና እንዳለው የምርምሩ መሪዎች ተናግረዋል፡፡ እደ መረጃ ምንጫችን ከሆነ ይህ ምርምር በዘርፉ የመጀመሪያ ምርምር ሲሆን ከመነሻ ምርምር ተነስቶ የክሊኒካል ሙከራውን አልፎ በሰዎች መረጋገጥ ችሏል፡፡
ለረጅም ጊዜያት ጭንቀትና ከልክ ያለፈ ውፍረት የተያያዙ ነገሮች እንደሆኑ የሚታወቅ መሆኑን የዘገበው የመረጃ ምንጫችን ጭንቀት በጨመረ ቁጥር የምግብ ፍላጎታችንን የሚያንረው ኮሊስትሮል ይጨምራል ሲል አስነብቧል፡፡ በመሆኑም ባክቴሪያው የረሀብ ስሜትን የሚቀሰቅሱና ለጭንቀት መጨመር መንስኤ የሆኑ ሆርሞኖችን በመቆጣጠር ውፍረት ለከፋ የጤና ጉዳት እንዳያጋልጠን ያደርጋል ብለው መናገራቸውን ሜዲካል ኤክስፕረስ ጽፏል፡፡
ምንጭ፡ Medical Xpress
This media is not supported in your browser
VIEW IN TELEGRAM