TechIn2
1.22K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
እንደ አፍንጫ ሽታን የሚያነፈንፈው ድሮን
**********************
ሲቪል ድሮኖች ካሏቸው ጠቀሜታዎች ውስጥ አንዱ የሰው ልጆች መድረስ በማይችሉባቸው ቦታዎች መድረስ መቻላቸው ነው፤ ለአብነት በደረሰባቸው የተፈጥሮ አደጋ ምክንያት የቀድሞ አቋማቸው ላይ የማይገኙ ህንፃዎች እንዲሁም ሊፈነዱ የሚችሉ ቁሶች ያሉባቸው አደገኛ አከባቢዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ አጥኚዎች ታድያ እነዚህን በመሳሰሉ አደገኛ ሁኔታዎች ውስጥ ያሉ ከአደጋ የተረፉ ሰዎችን እንዲሁም ፈንጂ፣ በተቀደደ ትቦ የሚፈስ ጋዝ እና ሌሎች ችግሮችንም በሚያመነጩት ሽታ ለመለየት የሚችል ድሮን የመስራት ፍላጎትን አድሮባቸው ቆይተዋል፡፡ ሆኖም እስካሁን የተፈጠሩት ሴንሰሮች እነዚህ ሽታዎችን በብቃት እና በሚያስፈልገው ፍጥነትም ለመለየት እየተቸገሩ ነበር፡፡
አሁን ግን በዩኒቨርቲ ኦፍ ዋሽንግተን ምሁራን የሚመራው ምርምር ይህን የሚቀርፍ መስሏል፡፡ ስሜሊኮፍተር የሚል ስያሜን ያገኘው አዲሱ የድሮን ፈጠራ የተገጠመለትን የአፍንጫ አንቴና በመጠቀም ተፈላጊው ሽታ ወዳለበት አቅጣጫ የሚያመራ ነው፡፡ ድሮኑ የተገጠመለት አንቴና በአባቢው ያሉ ኬሚካሎችን ጠረን በመለየት ምግብ እንዲከሁም ሰዎች ወዳሉበት ስፍራ መምራት ይችላል፡፡
ስሜሊኮፍተሩ ሽታን ለማፈላለግ ማንኛውንም እርዳታ ከተመራሪዎቹ መውሰድ አላስፈለገውም፡፡ ይህን ለመከወን ከፍጡራን አፍንጫ የሚመሳሰል ስልትን ይጠቀማል፤ ፍለጋውን ቅድሚያ በተወሰነ ርቀት ወደ ግራ አቅጣጫ በማቅናት የሚጀምር ሲሆን በዚያ የፈለገውን ሽታ ካላገኘ ተመልሶ በተመሳይ ርቀት ወደ ቀኝ ይጓዛል፡፡ በዚህ ሂደት የሚፈልገውን ጠረን ያገኘ እንደሆነ የበረራ አኳሀኑን በመለወጥ ወደ እርሱ ይገሰግሳል፡፡
ስሜሎኮፍተሩ በዙርያው ያሉትን ነገሮች ቅርበት በየ አንድ ሴኮንዱ ለአስር ጊዜ ያህል እንዲለካ በሚያስችሉት አራቱ ሴንሰሮቹን በመጠቀም እራሱን ከመሰናክሎች ይጠብቃል፡፡ አንድ ቁስ በ20 ሴ.ሜ ቀርቦት ሲገኝ የጉዞ አቅጣጫ ማስተካከያ ያደርጋል፡፡
ሌላው ይህ ድሮኑ እንዳለው የተነገረለት ጥቅም ለዚህ እንቅስቃው የጂ.ፒ.ኤስ ቴክኖሎጂን አለመጠየቁ ነው፤ ይልቁንም ልዩ ልዩ በራሪ ነፍሳት አይኖቻቸውን ተጠቅመው ሲያደርጉት እንደሚታየው ሁሉ እርሱም የተገጠመለትን ካሜራ በመጠቀም ዙርያውን ይቆጣጠራል፡፡ ይህ ደግሞ ድሮኑን ትቦ ወይም ጉድጓድን ለመሳሰሉ የምድር በታች እና ውስጥ ለውስጥ ተልዕኮዎች ስል ያደርገዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዋሽንግተን ውስጥ በተደረጉት ሙከራዎች ድሮኑ ከአበባዎች የሚገኙትን የመሳሰሉ ጠረኖችን እንዲለይና ወደ እነርሱም እንዲያቀና ተደርጎ ነበር፡፡ ሆኖም ስራዎች በዚህ አያልቁም፤ ወደፊት በፍርስራሾች ውስጥ የተቀበሩ ሰዎች ትንፋሽ የሚወጣ ካርበን ዳይ ኦክሳይድን በማሽተት እንዲሁም ያልፈነዱ ፈንጂዎችን የሚለቁት የኬሚካል ጠረን በመለየት ህይወት የመታደግ ስራዎችን የመስራት ዓቅም እንደሚኖረው ተመራማሪዎቹ ተስፋ አድርገዋል፡፡
ምንጭ፡ Tech Xplore
ለሀሰተኛ ዜናዎች ቴክኖሎጂ እንደ መፍትሄ
**************************
የሀሰተኛ ዜናዎችን ስርጭት ለመግታት አዲስ ቴክኖሎጂ መሰራቱን Tech Xplore በእለታዊ ዘገባው አስነብቧል፡፡ የRice ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ማህበራዊ ሚዲያ ተቋማት በፕላት ፎርሞቻቸው ሀሰተኛ መረጃዎች እንዳይሰራጩ ለመቆጣጠር የሚያግዛቸው ውጤታማ የሆነ በሰው ሰራሽ አስታውሎት የሚታገዝ ዘዴን መስራታቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡ ይህም የዩኒቨርሲቲው የኮምፒውተር ሳይንቲስት በሆነው Anshumali Shrivastava መሪነት የተዘጋጀ እንደሆነ ታውቋል፡፡ በምርምሩም ለግማሽ ምዕት ዓመታት ያክል ጥቅም ላይ የዋለውን Bloom filters የመፈጸም ብቃት ማሻሻል ችለዋል፡፡
የሙከራ ዳታ ቤዞችን በመጠቀም የተሻሻለው መንገድ ሀሰተኛ ዜናዎችንና የኮምፒውተር ቫይረሶችን ለማጣራት ከበፊቱ በ50 በመቶ ያነሰ የሚሞሪ ፍላጎት እንዳለው ተመራማሪዎቹ ገልጸዋል፡፡ ለምሳሌ ያክልም ከፍተኛ የሆነ የመረጃ ዝውውር ያለበትን ቲውተርን ማሳያ አድርገዋል፡፡ ቲውተር ባወጣው መረጃ መሰረት በአሁኑ ሰዓት በቀን ከ500 ሚሊዮን መልእክቶች በላ ይዘዋወራሉ፡፡ አንድ ሰው አንድ መልእክትን በላከ በአንድ ሴኮንድ ውስጥ መረጃው ይሰራጫል፡፡
የእነዚህን ሁሉ መልእክቶች ትክክለኝነት ለማረጋገጥ ቲውተር ባይገልጸውም Bloom filterን ይጠቀማል ተብሎ እንደሚታሰብ የመረጃ ምንጫችን አስነብቧል፡፡ ይህን ከፍተኛ ቁጥር ያለው መረጃ በዚህ የማጣሪያ ስልት ለመፈተሽ የማይቻል በመሆኑ አንዳንድ ሀሰተኛ መረጃዎች በቀላሉ ሲዘዋወሩ ይታያል፡፡
በተለይ በምርጫ ወቅቶች 10 ሺህ የሚያክሉ መልእክቶች በሴኮንድ ውስጥ ይሰራጫሉ፡፡ ታዲያ በቀደመው መንገድ እያንዳንዱን መልእክት በማንበብ ሀሰት ነው ተብሎ በሚገመተው ላይ ፍለጋ ለማድረግ የማይቻል ነው፡፡ በጥርጣሬ የተያዙ መልእክቶች በበዙ ቁጥር በወረቀት (በማንዋል) የማረጋገጥ ስራውን እጅግ አስቸጋሪና የማይቻል ያደርገዋል፡፡ ስለዚህ በዚህ ረገድ አዲሱ መንገድ የተሻለ የሀሰተኛ መረጃ ቁጥጥር ብቃት እንሚኖረው ታምኖበታል፡፡
ምንጭ Tech Xplore
የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የዲጂታል ክህሎት ሃገራዊ የትግበራ እቅድ
*********************************
የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የዲጂታል ክህሎት ሃገራዊ የትግበራ እቅድ / “Digital Skill Country Action Plan for Higher Education and TVET 2030” የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ግብ ትኩረት ያደረገባቸውን ኢኮኖሚ ደጋፊ ዘርፎችና በብሔራዊ ደረጃ የተያዙ የስራ እድል ፈጠራ፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ማሳደግ እና አካታች ብልጽግና የማረጋገጥ ግቦችን እዉን ለማድረግ የሚያስችሉ በመካከለኛና በከፍተኛ የዲጂታል ክህሎት የሰለጠኑ ምሩቃንን በማውጣት እንዲደግፉ ያስችላል፡፡
እቅዱ ህዳር 30 ቀን 2013 ዓ.ም በአዳማ ከተማ በተካሄደው የከፍተኛ ትምህርት የስትራቴጂክ ዕቅድ ግምገማ መድረክ ላይ የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የስራ ኃላፊዎችና ባለዳርሻ አካላት በተገኙበት ቀርቦ ውይይት ከተካሄደበት በኋላ ወደስራ ገብቷል፡፡ በመድረኩ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ እቅዱ ለሁሉም ሴክተሮችና ለአራተኛዉ የኢንዱስትሪ አቢዮት (4th industrial revolutions) የሚያስፈልጉ በዲጂታል ክህሎት ብቃታቸው የተረጋገጠ ምሩቃንና ዜጎችን ለማፍራት እንዲቻልና የዲጂታል መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋት የትምህርት፣ ምርምርና አስተዳደር ስራዎችን በኢንፎሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ የተደገፉ ለማድረግ እንዲቻል ተደርጎ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።
አክለውም የዲጂታል ክህሎት ሃገራዊ እቅዱ፣ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአስር አመት ስትራቴጂክ እቅድ፣ ከሀገሪቱ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ፣ ከአፍሪካ ህብረት አህጉራዊ የዲጂታል ስትራቴጂ እና ከተባበሩት መንግስታት የዘላቂ ልማት ግቦች ጋር በተጣጣመ መልኩ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሲጸድቅ፣ ሁሉም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ከእቅዱ በመነሳት የራሳቸውን ዘርፍ ማስፈጸሚያ እቅድ እንዲያዘጋጁ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የራሱን ድርሻ በመውሰድ እቅድ ማዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡
የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የዲጂታል ክህሎት ሃገራዊ የትግበራ እቅድ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ላይ የተቀመጡትን ግቦች ለማሳካት የሚተገበር መሆኑን ገልጸው በኢትዮጵያ ያለዉን ዝቅተኛ የዲጂታል ክህሎት ለማሻሻል እንደሚያግዝም አብራርተዋል፡፡ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ተማሪዎችንና መምህራንን ለዚህ ክህሎት ለማዘጋጀት አስፈላጊውን ግብዓት በማሟላት በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል፡፡
እቅዱ በሃገራቸን ትኩረት ተደርጎ እየተሰራባቸው ለሚገኙት አካታች ብልጽግናን የሚያረጋገጡ ግቦችን ለማሳካት የሚያስፈልጉ የሰዉ ሃይል ለማፍራትና የዲጂታል ዕውቀትን ለማሳደግ በሚያስችል መልኩ የተዘጋጀ ሲሆን አምስት የዲጂታል አስቻይ መሪ ግቦችን አካትቷል፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር
ቴክ-ሳይንስ የቴሌቪዥን ፕሮግራም፤ በዚህ ሳምንትም፡-
• በአብይ ፕሮግራም፤ የሚጥል በሽታን (Epilepsy) ፣
• በብላቴናት፤ ድሮን የሰራውን ታዳጊ፣
• በተመራማሪዎች ታሪክ፤ ዶ/ር ሀብቴ ጀቤሳ (ክፍል ፬)፣
• በተቋማት፤ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣
• በቴክኖሎጂ ታሪክ፤ ስለ ቨርቹዋል ሪያሊቲ ዝግጅቶችን አጠናቅረን እየጠበቅናችሁ ነው፡፡
እርሰዎም ነገ ቅዳሜ 10 ሰዓት ላይ የቻናል ምርጫዎን MOE ቴሌቪዥን ላይ በማድረግ ብቻ ይከታተሉን፡፡
በየሳምንቱ ቅዳሜ እንዲሁም በድጋሚ ማክሰኞ 10 ሰዓት በMOE ቴሌቪዥን ከሚቀርበው በተጨማሪ ወደ ዩትዩብ ቻናላችንም ጎራ በማለት አዳዲሶቹን ጨምሮ እስከዛሬ የተሰሩትን ፕሮግራሞች በሙሉ መመልከት ይችላሉ ( https://www.youtube.com/channel/UC6jvUOLRSkVEQtc5Annfwvg )፡፡
ከፍተኛ ውጤት የታየበት የኮቪድ መድሀኒት
************************
Remdesivir የተሰኘው መድሀኒት ኮቪድ 19ኝን ለማከም ከፍተኛ ብቃት እንዳለው የእንግሊዝ ተመራማሪዎች ያወጡት የምርምር ውጤት አመለከተ፡፡ በጥናቱም መድሀኒቱ ለኮቪድ በሽተኞችና መጠነኛ የበሽታ መከላከል ችግር ላለባቸው ሰዎች ተሰጥቶ የበሽታውን ምልክቶችና ቫይረሱን ሙሉ ለሙሉ ማስወገድ እንደሚችል ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ውጤታማ የሆነ መድሀኒት አለመኖሩ የወረርሽኙን የመከላከል ሂደት እጅግ እንዳዘገየው ይታወቃል፡፡
ይህ ተመራማሪዎች ተስፋ የጣሉበት መድሀኒት በዋናነት ሄፓታይተስሲን ለማከም የተዘጋጀ ሲሆን ባሳለፍነው ጥቅምት ወር የአለም ጤና ድርጅት መድሀኒቱ በኮቪድ ምክንያት የሚኖርን የሞት መጠን አይቀንስም ብሎት ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ተመራማሪዎቹ ከቀድሞው የተለየ መንገድን በመከተል መድሀኒቱ ልዩ ክትትል በሚደረግላቸው ታካሞዎች ላይ የሚኖረውን ለውጥ ሲያጠኑ ቆይተዋል፡፡
የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲው ዶክተር James Thaventhiran በመጀመሪያውቸ ዙር የቫይረሱ ስርጭት የነበረው የሞት መጠን መጨመር ብዙ ምክንያቶች የነበሩት በመሆኑ መድሀኒቲ በሞት መጠን መቀነስ ላይ የነበረውን ትክክለኛ ሁኔታ መለየት በጣም አስቸጋሪ ነው ሲሉ ተሰምተዋል፡፡ ተመራማሪዎቹ በአንድ የ31 ዓመት ጎልማሳ ላይ ተከታታይነት ያለው ክሊኒካል ሙከራን ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸው ለታካሚው የተለየዩ የህክምና ድጋፎች ቢደረጉለትም የጤና መሻሻል ብሎም ከበሽታው ነጻ መሆን የቻለው ግን remdesivir የተሰኘውን መድሀኒት መውሰድ ከጀመረ በኋላ ነው፡፡
ታካሚው ይህን መድሀኒት መውሰድ እንደጀመረ ያለው የሰውነት ሙቀት መስተካከል የጀመረ ሲሆን በሰውነቱ ያለው የቫይረስ መጠን በመቀነስ ተጨማሪ ኦክስጅን መውሰድ አቁሟል፡፡ ይህን መድሀኒት መውሰድ በጀመረ በ10ኛው ቀንም ሙሉ ጤነኛ ሆኖ ከሆስፒታል መውጣቱን ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
ምንጭ SciTechDaily
አሜሪካ ፌስቡክን የመገነጣጠል እንቅስቃሴ ጀመረች
*****************************
ባሳለፍነው ሳምነት የአሜሪካኑ የፌደራል ንግድ ኮሚሽን ከጠቅላይነት ወይም የሞኖፖሊ እንቅስቃሴ ጋራ በተያያዘ የፌስቡክ ኮርፖሬሽንን ለመሰነጣጠቅ ያለመ ክስ መስርቷል፡፡ ከከሳሾቹ ዘንድ በፌስቡክ ላይ የቀረበው ማስረጃም ነገሩ እንዲከርበት አድርጎታል፡፡ ይህም በውስጥዊ የኢሜይል ልውውጦች ወቅት የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ ማርክ ዙከንበርግ ብሎም ባልደረባዎቹ ተፎካካሪ የማህበራዊ ሚዲያ ድርጅቶችን በመግዛት እና ሌሎችንም መፈናፈኛ በማሳጣት የማህበራዊ ሚዲያ ገበያውን በጠቅላይነት ለመያዝ ማሴራቸውን ያሳያል፡፡
ፌስቡክ በአውሮፓውያኑ 2012 የምስል መጋርያ የሆነው ኢንስታግራም እንዲሁም ከሁለት ዓመታት በኋላ ዋትሳፕ የተሰኘው የመልዕክት መላላኪያ መተግበሪያዎችን በ715 ሚሊዮን እና 22 ቢሊዮን ዶላር መግዛቱ ይታወሳል፡፡ አሁን ላይ ታድያ ተወዳዳሪዎችን ያለ አግባብ ይገፋሉ ያላቸውን እነዚህን ሁለት ግዢዎች ዳግም ከፌስቡክ እንዲነጠሉ እንደሚፈልግ ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡ ይህ ግን ምናልባትም የፌስቡክን የወደፊት ህልውና ከስሩ የሚንድ ነው፡፡ ምክንያቱም አሁን ላይ ድርጅቱ እያስመዘገበ ካለው የትርፍ ዕድገት ውስጥ አብዛኛው እየመጣ ያለው ከኢንስታግራም በመሆኑና ዋትሳፕም ለተቋሙ ዲጂታል ንግድ ዕቅድ ማዕከል በመሆኑ ነው፡፡
ኮርፖሬሽኑ ዋናው ገፁ በሆነው ፌስቡክ ገፅ ላይ ማስታወቂያዎችን የሚያስቀምጥበት ቦታ እየጠበበው ይገኛል፡፡ ከዚህ በላይ በአንድ ገፅ ላይ ማስታወቂያን ማብዛት ደግሞ ለተጠቃሚዎች ምቾትን የማይሰጥ ስለሆነ ስራውን ወደ ሌሎቹ ገፆቹ ማዘዋወርን ጠይቆታል፡፡ ታድያ ኮርፖሬሽኑ እየተጠናቀቀ ባለው የፈረንጆች ዓመት ደንበኞች የኢንስታግራም ምስል እና ቪዲዮዎችን ብቻ በመጠቀም ግብይት የሚፈፅሙበትን መንገድ መፍጠሩ ይታወሳል፡፡ የተለያዩ ንግድ ተቋማትም ዋትሳፕን በመጠቀም ከደንበኞቸቸው ጋራ እንዲገናኙ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ታድያ ፌስቡክ ድርጅቶች በኢንስታግራም ላይ ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅ የፌስቡክ አካውንት እመንዲኖራቸው ያስገድዳል፡፡ በተጨማሪም በኢንስታግራም የሚፈፀሙ ግዢዎችን ከዋትሳፕ መልዕክት ልውውጦች ጋራ ለማስተሳሰር አቅዷል፡፡ እናም ሁለቱን ማጣት ኮርፖሬሽኑ ወደፊት ኢ-ኮሜርስ ላይ የሚኖረውን ሚና የሚያቀጭጭጨው ይሆናል፡፡
ከትርፍ እድገት አንፃር ያየነውም እንደሆነም በ2019 ኢንስታግራም የ20 ቢሊዮን ደላር ገቢ ለፌስቡክ ኮርፖሬሽን ሲያመነጭ የ29 በመቶ የማስታወቂያ ገቢ ድርሻንም ይዟል፡፡ ቁጥሩ በ2020 ወደ 28.1 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያድግ ይጠበቃል፡፡ ይህ ደግሞ ፌስቡክ ኮርፖሬሽን ከሚያገኘው የማስታወቂያ ገቢ 37 በመቶውን ከኢንስታግራም ብቻ ያገኛል ማለት ነው፡፡ በዚህ ረገድ 2 ቢሊዮን ተጠቃሚዎችን ያፈራው ዋትሳፕን ያየነው እንደሆነ በአሁኑ ሰዓት ምንም አይነት ገንዘብ እያመነጨ ባይሆንም የኢ-ኮሜርስ ክፍያ ስርዓቱን በዚህ መተግበሪያ በኩል ለማድረግ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ዋትሳፕን ወደ ትልቅ የገቢ ምንጭነት ያሳድገዋል፡፡
በተጨማም ኮርፖሬሽኑ ሁለቱን ግዢዎች ሲፈፅም አሁንም ድረስ ግንባር ቀደም ገፁ የሆነው ፌስቡክ አንድ ቀን ተቀባይነቱ እንደሚያሽቆለቁል በመገመት ነው፡፡ እንደ ህንድ እና ብራዚል ያሉ በፍጥነት የሚያድጉ ገበያዎች ላይ ለመስፋፋትም ዋና መሳሪያዎቹ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በህንድ ዋትሳፕ ከፌስቡክ ገፅ በ100 ሚሊዮን የሚልቁ ተጠቃሚዎች አሉት፡፡ በጃፓን ደግሞ ኢንስታግራም ከፌስቡክ አንፃር በ70 በመቶ የተጠቃሚዎች ብልጫን ይዟል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለም ኢንስታግራም በተለይ በወጣት እና ታዳጊዎች ዘንድ ያለው ተወዳጅነት ከፌስቡክ አንፃር በፍጥነት በማደግ ላይ ሲሆን ከመረጃ አሳልፎ መስጠት ውዝግቦች ጋር ተያያዞም ሌሎች ብዙ ሰዎች ፌስቡክ ገፃቸውን በመተው ወደ ኢንስታግራም መሸጋገራቸወን ሲናገሩ ተደምጧል፡፡ ስለዚህም ከላይ የተጠቀሱት ተደማምረው ሁለቱን ማጣት ያለጥርጥር ፌስቡክ ወደፊት የሚኖረውን ዋጋ እንዲያሽቆለቁል ያደርገዋል፡፡
ታድያ ከፌቡክ መነጠሉ ጉዳቱ ለፌስቡክ ብቻ አይደለም፤ በተመሳሳይ ዋትሳፕም ሆነ ኢንስታግራምን ወደ ውድቀት ሊመራቸው ይችላል፡፡ የፌስቡክ ኃላፊዎች ያለ ፌስቡክ እገዛ እነዚህ ሁለት ድርጅቶች አሁን ላሉበት ደረጃ ሊበቁ እንደማይችሉ ይናገራሉ፡፡ እወነትነት ያለው መከራከሪያ ይመስላል፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ዋትሳፕ በእናት ድርጅቱ ገንዘብ እየተመራ ባለፉት ዓመታት ውስጥ ከትርፍ ይልቅ ሲሰራ የቆየው የመልእክት ምስጠራ (encryption)፣ የተጠቃሚዎች ቁጥር እንዲሁም እምነት በማሳደግ ላይ ስለነበር ያለ ፌስቡክ መቀጠሉ ከፍተኛ የገቢ ጫና ውስጥ ይከተዋል፡፡ ኢንስታግራምም ቢሆን ለማስታወቂያ ስርጭት የሚረዱት የተጠቃሚዎቹን መረጃ ለማግኘት እንዲሁም የጥላቻ ንግግር፣ የሽብርተኝነት መረጃዎችን እና ሌሎችም ተገቢነት የሌላቸው ፖስቶችን ለይቶ ለማውጣት ብዙ ቢሊዮን ዶላሮች በፈሰሱበት የፌስቡክ ደህንነት ቴክኖሎጂ ላይ ጥገኛ ነው፡፡
ሆኖም ኮርፖሬሽኑን የመነጣጠሉ ስራ ከባድ እና የመሳካት ዕድሉም አነስተኛ እንደሆነ በተለያዩ ባለሙያዎች ይነገራል፡፡ የሚደረገው የሕግ ጦርነቱ ቀላል የሚሆን አይመስልም፤ የውድድር ሕግ ባለሙያዎች በክሳቸው አሳምነው ለመርታት ከባድ ስራ ይጠብቃቸዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ስራው በኮንግረስ የሚደገፍ መሆን አለበት፡፡ ነግር ግን የተቋማት ያለልክ ሰፍቶ ጠቅላይ መሆንን ስትቃወም ለኖረችው አሜሪካን ይህ አይነት የመገነጣጠል ውሳኔዎች አዲስ አይሆኑም፡፡ ሀገሪቱ ጠቅላይ ሆነው ያገኘቻቸውን ግዙፍ የንግድ የተቋማት ከ19ኛው ክፍለ ዘመን አንስቶ እንደ ዶሮ ስትገነጣጥል ቆይታለች፤ በዚህ ውስጥ ስታንዳርድ ኦይል እና ኤቲ ኤንድ ቲ ተጠቃሽ ዱላው ያረፈባቸው ግዙፍ የንግድ ተቋማት ናቸው፡፡
ታድያ ይህ ክስ በፌስቡክ ብቻ የሚያቆም አይመስልም፡፡ ይልቁንም ሌሎች እንደ አፕል፣ አማዞን እና ጉግል ያሉ ግዙፍ አሜሪካውያን የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችንም የኋላ ኋላ መንካቱ ላይቀር ይችላል፡፡
ምንጭ፡ The Guardian እና Bloomberg
የ2021ዱ ታዳሽ የሀይል አማራጭ (green hydrogen)
***********************
አለማችን በከፍተኛ መጠን እየተጎዳችበት ላለው የአየር ንብረት ለውጥ መሻሻል ሀገራት በተናጥልም ሆነ በጋራ የተለያዩ እርምጃ ሲወስዱ ማየት በጣም አስደሳች ነው፡፡ ለዚህም ብዙ ርቀን ሳንሔድ ሀገራችን ኢትዮጲያ በደን ልማት ዘርፍ እያደረገችው ያለው እንቅስቃሴ በጣም የሚበረታታ ነው፡፡ ሀገራት ከደን ልማት ባሻገር ከተፈጥሮ ጋር ተስማሚ የሆኑ የሀይል አማራጮችን በመጠቀም ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት መቀነስ እንዳለባቸው ብዙዎች ይስማማሉ፡፡
ከተፈጥሮ ጋር ተስማሚ የሆኑ የሀይል አማራጮች ሲታሰቡ እንደ ንፋስና ፀሐይ ያሉ አማራጮች በሰፊው ጥቅም ላይ እየዋሉና ስለ እድገታቸውም ተደጋግሞ እየሰማን እንገኛለን፡፡ ምንም እንኳን በዚህ ረገድ ሰፊ የሆነ የ፣ስፋፋት ስራ በያንዳንዱ ሀገር የሚጠበቅና ከዘርፉ መገኘት የሚችለው የሀይል መጠን ገና ያልተደረሰበት ቢሆንም ሌሎች አማራጮችንም መዳሰስ ተፈጥሮን ለመታደግ ባለ ብዙ አማራጭ ያደርገናል፡፡
በዚህ ጽሁፍ አሜሪካውያን ጆ ባይደንን ከመምረጣቸው ጋር ተያይዞ ስሙ የተነሳውን የ2021 ተስማሚና ታዳሽ የሀይል አማራጭ ልናስቃኛችሁ ወደናል፡፡ መረጃውንም ከ abc news አግኝተነዋል፡፡ የነገሩ ጥንስስ አሜሪካ በጆርጅ ቡሽ ስትመራ በነበረበት ወቅት የተብላላ ሲሆን በወቅቱም ተመራማሪዎቹ "freedom fuel" የሚል ቅጽል ስም ሰጥተውት ነበር፡፡ እንደ ቻይና፣ ጃፓን፣ ሳውዲ አረቢያ፣ ጀርመንና አውስትራሊያ ያሉ ሀገራት በዘርፉ ሰፊ በጀት መድበው እየሰሩበት እንደሆ የዘገበው የመረጃ ምንጫችን የአሜሪካ ተመራጩ ፕሬዘዳንትም ዘርፉ ከተስማሚ የሀይል አማራጭ እቅዳቸው ውስጥ እንደሚካተት ለአሜሪካውያን ቃል ገብተዋልሲል አስነብቧል፡፡
የዘርፉን ባለሙያዎች በምንጭነት የጠቀሰው ABC News የአረንጓዴ ሀይድሮጅን ልማት ገበያ በቀጣዮቹ አስርት አመታት ከፍተኛ እድገት ያስመዘግባል የሚል መረጃ አውጥቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ጥቅም ላይ እየዋለ ያለውን "gray" ሀይድሮጅን ለማምረት fossil fuel መጠቀም የሚያስፈልግ በመሆኑ በሂደቱ ካርቦን ዳይ ኦክሳድ ልቀት አለው፡፡ ከዚህ በተሸለ ሁኔታ በአንጻራዊ ሰማያዊ ሀይድሮጅን ያነሰ የሀይድሮጅን ልቀት እንዳለው በዘርፉ የሚሰሩ ሰውች ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ከብክለት ነጻ የሆነ ሀይድሮጅን ("green" hydrogen) በውሀ ውስጥ ያሉትን የሀይድሮጅንና የኦክስጅን ሞሎኪዩሎች ለመነጣጠል የኤሌክትሪ ሀይልን ስለሚጠቀም ምንም አይነት የካርቦን ልቀት እንደሌለው ይነገራል፡፡
በዚህ መንገድ የሚገኝ ተስማሚ ሀይድሮጅን በሌሎች አማራጮች ሊገኝ የማይችልን ከጠቅላላው ፍላጎት ከ15 እስከ 20 በመቶ የሚሆን የሀይል ፍላጎትን ሊያሟላ እንደሚችል ተገምቷል፡፡ ያለውን የተስማሚ የሀይል አማራጭ ክፍተት ከመሙላት በተጨማሪ በሀይድሮጅን የሚገኘው ሀይል ሌሎች አማራጮች ሊከውኗቸው የማይችሏቸውን ከፍተኛ ፋብሪካዎችን ማንቀሳቅሰ፣ ለረጅም ርቀት ተጓዥ ከባድ ተሸከርካሪዎች፣ ለጭነት መርከቦችና አውሮፕላኖችን ለማንቀሳቀስ የሚያስፈልገውን ሀይል ማሟላት ይችላል፡፡
ለዚህ አይነቱ አማራጭ ተፈላጊነት ሌላው ጉዳይ ለሀይል ማምረት ሂደቱ የሚያስፈልገው መሰረተ ልማት ሙሉ ለሙሉ የተዘጋጀ መሆኑ ነው፡፡ ለቀጣይ 30 አመታት 11 ትሪሊዮን ዶላር ዋጋ የተገመተለት ይህ ፕሮጀክት አለማችን የምትመኘውን ዜሮ የካርቦን ልቀት እቅድ ከማሳካት አንጻር ገንዘቡ እንደማያሳስብ ተነግሯል፡፡
የዘርፉ ሙያተኞች ይህ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በሶስት ምክንያቶች እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡እነዚህም ሀይድሮጅን ለማምረት የሚያስፈልገውን የኤሌክትሪክ ሀይል ለማሟላትና የፀሐይል መሰብሰቢያ ንጣፎችን ለመዘርጋት፣ ሀይድሮጅኑን ለሚያመርቱ ማሽኖች (electrolyzers) እና ሀይድሮጅኑን ለማጓጓዝ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም የሚስፈልገው ግዙፍ ፋብሪካ በ Delta, Utah እየተገነባ ነው፡፡
ምንጭ Abc News
የወታደራዊ አመራሮችን በቀድሞ ታላላቅ ጦርነቶች አንፆ የሚያሰለጥነው አዲስ ቴክኖሎጂ
****************************
አዲስ የተሰራው የጦር ሜዳ ታሪክን ማስተማርያ ስልት በቅርቡ የወደፊት የጦር መሪዎችን ለማሰልጠን ሊውል እንደሚችል ተነገረ፡፡ የፐርጅዩ ዩኒቨርሲቲ አጥኚዎች ቨርቹዋል ሪያሊቲን ተጠቅመው በፈጠሩት የጦር አውድማ መከሰቻ ሲሙሌተር ዲ ዴይ ተብሎ የሚታወቀውንና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የቃልኪዳን ሀገራት የፈረንሳይዋን ኖርማንዲ የባህር ዳርቻ የወረሩበትን ታላቅ የጦር ቀንን ዳግም መፍጠር ችለዋል፡፡ በፊዚክስ ትምህርት ዘርፍ ውስጥ ያለውን ዕውቀት ተጠቅሞ የጦር መርከቡ ከውሃው ጋር ሲቆራኝ ያለውን እውነተኛ የሚመስል ሁነት በቨርቹዋል ቴክኖሎጂ አማካኝነት በመጠቀም ወታደሮችን ለማሰልጠን እንደሚገለገሉበት የሚናገሩት ፕ/ር ሶሪን አዳም ማርቴ የውትድርና መምህራንም ቴክኖሎጂውን የወደፊት የጦር መሪዎችን ስላለፉትን ታሪካዊ ጦርነቶች በማስተማር ለማነፅ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ አስቀምጠዋል፡፡
ስራው ዓለም አቀፋዊ የረጅም ጊዜ ውትድርና፣ ፖለቲካዊ እና ተቋማዊ ውሳኔ አሰጣጥን የሚያንፁ የስትራቴጂ እና ደህንነት እንቅስቃሴዎች አማካኝነት የተረጋጋች እና ደህንነቷ የተጠበቀ ዓለምን ለማምጣት የሚከናወነውን ጥናት የሚደግፍ መሆኑ ተነግሮለታል፡፡ የጥናት ቡድኑ በአላባማ ግዛት ውስጥ ካለው የአሜሪካን አየር ኃይል የአየር ላይ ጦርነት ኮሌጅ ጋራ የሚሰራ ሲሆን የአየር ላይ ጦርነት ኮሌጁ በየዓመቱ ፀደይ ሲደርስ ወደ ኖርማንዲ መጓዝን የካሪኩለሙ አካል አድርጎ ቆይቷል፡፡
የጥናት ቡድኑ በአሜሪካን የእርስ በእርስ ጦርነት አካል የሆነው የጌቲስበርግ ጦርነትን በሲሙሌተሩ ዳግም ለመከሰት እየሰራ ሲሆን ወደፊትም ቴክኖሎጂውን ወደ ንግዱ ዓለም ለመቀላቀል በማሰብ ፎርስስ (FORCES) የተባለ አዲስ ድርጅት አቋቁሟል፡፡ ዋናው ነጥብ አዲስ የውትድርና ታሪክን መማርያ መንገድን መፍጠር እና ማጋራት ብሎም የውትድርና ጥበብ እና ሳይንስን ይበልጥ ማጥናትና መረዳት ላይ ነው ያሉት ደግሞ ሌላኛው የጥናት ቡድኑ አካል ሮበርት ከርቹቤል ናቸው፡፡ አክለውም አዲሱ ስራቸውን በመጠቀም ቀድሞ የተደረጉ ስመጥር ጦርነቶችን ቴክኖሎጂን በመጠቀም ዳግም ወደ አዲሱ የተማሪና ምሁራንን ትውልድ ለመመለስ ጉጉት እንዳደረባቸው ተናግረዋል፡፡
ምንጭ፡ Tech Xplore
This media is not supported in your browser
VIEW IN TELEGRAM
ሰዎች በየአመቱ 30 ጊጋቶን የሚጠጋ ቁስ ነገሮችን ያመርታሉ
***************************
ሰው ሰራሽ የሆኑ ነገሮች ማለት የሸቀጥ ምርቶች፣ መሰረተ-ልማቶች፣ ህንፃዎች እና ሌሎች ቁስ ነገሮች ከምድር አጠቃላይ የባዮማስ መጠን በክብደት እየጨመሩ መምጣታቸውን በኔቸር ጆርናል የወጣ አዲስ ጥናት ጠቁሟል፡፡ ጥናቱ 2020ን እንደ መነሻ አድርጎ ባካሄደው ምርምር ሰዎች የሰሯቸው ቁስ ነገሮች ወይም (anthropogenic mass) በምድር ካሉ ህይወት ያለቸው ነግሮች (total biomass) በክብድት እየላቁ መምጣቸው ተጠቁሟል፡፡
አሁን ላይ የሰው ልጆች በዓመት ወደ 30 ጊጋቶን ወይም 30 ቢሊዮን ቶን የሚጠጋ ቁስ ነገሮችን በብዛት የሚያመርቱ ሲሆን ይህ የምርት መጠንም ባለፉት አስር አመታት ከፍተኛ ጭማሪ እያሰየ መምጣቱ በጥናቱ ተዳሷል፡፡ እንደአውሮፓውያኑ በ1900 ሰዎች የሰሯቸው ቁስ ነገሮች ከአጠቃላይ ባዮማስ አንፃር ሲሰላ 3% የነበረ ቢሆንም ይህ የክብደት መጠን ከ1920ዎቹ አንስቶ ይበልጥ ጭማሪ በማሳየት በተለይም በመጨረሻዎቹ 20 እና 10 አመታት ከኢንዱስትሪ ምርቶች መስፋፋት ጋር ተያይዞ መጠኑ እጅግ እየላቀ መምጣቱን አጥኚዎች ይናገራሉ፡፡
ተመራማሪዎች ይህን የሰው-ሰራሽ ቁስ ነገሮች ክብድት ከባዮማስ አጠቃላይ ክብደት ለማነፃፀርና ለመለካት በኮምፒውተር ሞዴሊንግ የተሰሩ ቀደምት ትንበያዎችን የተጠቀሙ ሲሆን፤ ከዚህ በተጨማሪም የመስክ የዳሰሳ ጥናቶች እና ለማክሮ ኢኮኖሚክ ትንተና የሚውል የስቶክ ፍሎው ሞዴሊንግ (stock-flow modeling) የምርምር ዘዴዎችን በጥናቱ ላይ ለመተግበር ሞክረዋል፡፡
ተመራማሪዎች እንደሚያስረዱት አብዛኞቹ ጥቅም ላይ የዋሉት የምርምር ዘዴዎች ፍፁም ልክ ሊባል የሚችል ቁጠራዊ መረጃ የሚሰጡ ባይሆንም አጠቃላይ የክብደት ንፃሬውን ያልተወሳሰበና የተስተካከለ ለማድረግ በባዮማስ በኩል የውሃ መጠንን በሰው-ሰራሽ በኩል ደግሞ የቁስ ውጋጆችን በትንበያው ላይ አለማካተታቸውን ተናግረዋል፡፡ ተመራማሪዎች እንደሚገልፁት ይህ የምርምር ውጤት የሰው ልጅ በምድር ላይ እያስከተለ ያለውን ከፍተኛ ጫና የሚያሳይ ከመሆኑም ባለፈ በጂዎሎጂካል የጊዜ ምጣኔ አዲስ ዘምን ወደሆነው አንትሮፔሲን (Anthropocene) እየገባን መሆኑን የሚያመለክት ነው ይላሉ፡፡
ምንጭ፡ Scientific American
የ Surface Web እና Deep Web ልዩነት
===================
የሳይበር ደህንነት ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት በጎግልና በሌሎች የመፈለጊያ መሳሪያዎች ሊገኙ የሚችሉ ብዙ ሚሊዮን የበይነ መረብ ገፆች ቢኖሩም ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ገፆች ግን በየትኛውም የመፈለጊያ መሳሪያዎች ሊገኙ የማይችሉ ናቸው፡፡ ይህ ማለት በኢንተርኔት ላይ ማግኘት የማንችላቸው ነገሮች ማግኘት ከምንችላቸው ነገሮች ጋር ሲነፃፀሩ የሰማይ እና የምድር ልዩነት ያላቸው ናቸው ማለት ነው፡፡
ባለሙያዎች የሰርፌስ ዌብ (Surface Web) እና ዲፕ ዌብ (Deep Web) ልዩነት በቀላሉ ለማስቀመጥ የውቂያኖስን ምሳሌ ይጠቀማሉ፡፡ ድር ወይም ዌብ የሚባለውን ነገር እንደውቂያኖስ ቢታሰብ ሰርፌስ ዌብ የምንለው የውቂያኖሱ የላይኛው አካል ወይም መንካት የምንችለው የውሃ ክፍል ሲሆን ዲፕ ዌብ የሚባለው ደግሞ ጥለቁ የውቂያኖስ ክፍል ሆኖ በቀላሉ መንካት የማንችለው የውሃ አካል ነው፡፡
በዚህ መሰረት በአለም አቀፍ ድር (World Wide Web) አጠቃቀም እንደጎግልና ያሆ ያሉ ስታንዳርድ የመፈለጊያ መሳሪያዎችን ተጠቅመን በቀላሉ ልናገኘው የምንችለው የበይነ መረብ አካል ሰርፌስ ዌብ ይባላል፡፡ ይህ የዌብ አይነት ሁሌ የምንጠቀምባቸውን እንደፌስቡክ፣ ጎግል፣ ዊኪፒዲያ እና ሌሎች ድረ-ገፆችን በቀላሉ እንድንጠቀም የሚያስችል እና ምንም አይነት ገደብ የሌለብት የበይነ መረብ አካል ነው፡፡
ዲፕ ዌብ በአለም አቀፍ ድር (World Wide Web) አጠቃቀም እንደጎግልና ያሆ ያሉ ስታንዳርድ የመፈለጊያ መሳሪያዎችን ተጠቅምን በፍፁም ልናገኘው ወይም (access) ልናደርገው የማንችለው የበይነ መረብ አካል ነው፡፡ በዚህ የዌብ አይነት እነደ ኢሜል ኢንቦክስ፣ የኦንላይን ባንኪንግ እና ሌሎችም በይልፍ ቃል የታጠሩ እና የራሳቸው ቀጥተኛ URL ወይም IP አድራሻ (address) ያላቸው ይዘቶች ይገኛሉ፡፡
በዚህ አለም አቀፍ የድር አጠቃቀም ከዲፕ ዌብ በታች ያለውን እና ልዩ መተግበሪያዎች ተጠቅመን ማግኘት የምንችለውን የዌብ አይነት Dark Web እንለዋለን፡፡ ዳርክ ዌብ በውቂያኖሱ ምሳሌ ከጥልቁ የውሃ ክፍል በታች ያለውን ዝቅተኛ ስፋራ ወይም (bottom of the ocean) ሊባል ይቻል፡፡ ይህን የዌብ አይነት access ለማድረግ በተደራቢ አውታረመረቦች ወይም (overlay networks) ማለፈ የሚገባ ሲሆን ይህን ማስጠቀም የሚችሉ ልዩ መተግበሪያዎችም የግድ ያስፈልጋሉ፡፡ የዳርክ ዌብ ገፆች ማንነታቸው ባልታወቀ አካለት የሚዘጋጅ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ድብቅ ፎረሞች፣ ህገ-ወጥ ግብይቶች እና ሌሎች አግባብነት የሌላቸው ነገሮች ይካሄዱበታል ተብሎ ይታሰባል፡፡
ምንጭ፡ Ciso Platform
በቂና የተመጣጠነ ምግብ ለሁሉም
-----------------------------
የአመጋገብ ባህላችንን መቀየሩ ቀላል ቢሆን ኖሮ በንጥረ ነገሮች የበለፀገ ተመጣጣኝ ምግብ ካለመመገብ ጋራ የተያያዙ ሁሉም ችግሮች ከዘመናት በፊት በተወገዱ ነበር፡፡ ሁሉም የምድራችን ነዋሪም በጤና ሊያቆየው የሚችለውን ምግብ በበቂ ሁኔታ ማግኘት በቻለ ነበር፡፡ 44 የዓለም ሀገራትን ተሳታፊ አድርጎ በአውሮፓውያኑ 1943 በተካሄደው ታሪካዊው የሆት ስፕሪንግ ምግብና ግብርና ኮንፈረንስ ላይ “ደህንነቱ የተጠበቀ በቂና ዘላቂ የምግብ አቅርቦት ለሁሉም” የሚለውን ሀሳብ ወደ ዓለም መድረክ የመጣና እንዲሁም ከሰላሳ ዓመታት በኋላ የተካሄደው የ1974ቱን የሮም የምግብ እና ግብርና ኮንፈረንስ ላይ ሁሉም የሰው ልጅ ከረሀብ ነፃ የመሆን እና ለተሟላ እድገት መረጋገጥ መሰረታዊ በሆኑ ንጥረ ነገሮች የዳበረ ምግብን የማግኘት መብት እንዳለው የተመጠ ቢሆንም ይህ ሁሉ ግን በምኞት ብቻ የቀረ ሆኗል፡፡
እውነታው እኛ የሰው ልጆች ዛሬም መጠነ ሰፊ የአመጋገብ ችግር ውስጥ መሆናችን ነው፡፡ ሁኔታው እጅግ የተወሳሰበ እና ብዙ ነገሮችን የያዘ ቢሆንም ቅሉ እንዲሁ በጠቅላላው ስናየው ግን አሁንም ብዙዎች ይራባሉ፣ በንጥረ ነገሮች የበለፀገ ተመጣጣኝ ምግብን በማግኘት ረገድ በደሃ እና ሀብታም ሀገራት ወይም ክፍለዓተ ዓለማት መካከል ያለው ልዩነት እጅጉን ሰፊ ነው፣ ከምርት እስከ ማከፋፈል ድረስ የሚዘረጋው የምግብ አቅርቦት ስርዓታችንም ቢሆን እኛንም ሆነ ምድራችንን እየጎዳ ይገኛል፡፡ ወደ አንደኛ ዓመቱ የተጠጋው የኮቪድ-19 ወረርሺኝ ደግሞ በምግብ ስርዓታችን ውስጥ ያሉ ችግሮችን ይባስ ያጋለጠ ሆኗል፡፡ የፖለቲካ፣ ምጣኔ-ሐብት እና ባህል ተግዳሮቶችም ዘላቂ በሆነ ሁኔታ ዓለም አቀፋዊውን የዓመጋገብ ልማድ እንዳይለወጥ አድርገዋል፡፡ የቱን እንመገብ በሚለው ላይ ከስምምነት ተደረሰ ብንልም እንኳን ይህን በስፋት መተግበሩ ትልቅ እና በደንብም ያልተጠና ተግዳሮት ነው፡፡
የስነ-ምግብ ተመራማሪዎች አንደሚያሰቀምጡት ከሆነ ለሰው ልጆች አካላዊም ሆነ አዕምሮአዊ ጤና ብሎም ለተፈጥሮ አካባቢ ተስማሚነት ከስጋና ስጋ ተዋፅዖዎች ይልቅ በዋናነት እፅዋትን መሰረት ያደረገ አመጋገብን መከተሉ አስፈላጊ ነው፡፡
ግን ደግሞ ያለ መፍትሄ ፍለጋ ዝም ብለን አልተቀመጥንም፤ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የተለያዩ እርምጃዎች በመወሰድ ላይ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ በግብርና የሚገኘውን ስጋ ለመቀነስ በዓለም ዙርያ ያሉ ተመራማሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ልናገኛቸው የምንችላቸው የፕሮቲን አማራጮችን ወደ መመገቢያ ትሪያችን ለማምጣት እየታተሩ ይገኛሉ፡፡ አሁን ላይ በሚወጡ ትንበያዎች መሰረትም የዛሬ 30 ዓመት በሰው ሰራሽ መንገዶች ከሚከወነው የአሳ እርባታ (Aquaculture) የሚገነው የአሳ ምርት ከተፈጥሮ የውሃ አካላት ተጠምዶ ከሚገኘው የላቀ ምርትን እንደሚያስገኝ ነው፡፡ የግብርና ምርትን የሚያሳድጉ ግን ደግሞ የተፈጥሮ አካባቢንም በዘላቂነት የሚጠብቁ የግብርና ስልቶችን የመጠቀም ልምዳችንም ከጊዜ ወደ ጊዜ በማደግ ላይ ይገኛል፡፡
በአውሮፓውያኑ 2050 በምድራችን ላይ የሚኖረው ሰው ብዛት 10 ቢሊዮን እንደሚደርስ ከትንበያዎች መረዳት እንችላለን፡፡ ይህ አሁን ባለው ህዝብ ላይ ሌላ የቻይናን ህዝብ ሁለት እጥፍ ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑ አዳዲስ ምግብ ፈላጊ ነዋሪዎችን መጨመር ማለት ነውና ለዚህ ሁሉ ህዝብ የተመጣጠነ ምግብንም አቅርቦ የምንኖርባት ምድርንም ከከፋ ጉዳት ጠብቆ መጓዙ ሁሉን አቀፍ የጋራ ስራን ይጠይቃል፡፡ ታድያ ዘላቂ የሆነ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን ለሁላችንም የሚያረጋግጥ መፍትሄ ከአንድ ወገን ብቻ ማግነቱ ለስኬት አይረዳም፡፡ አሁን ያለንበት የኮቪድ-19 ወረርሺኝ የተቀናጀና ሁሉን ያስተባበረ ዓለም አቀፋዊ ምላሽን እንደሚሻው ሁሉ የሰው ልጆችን በንጥረ ነገሮች በበለፀገ ተመጣጣኝ ምግብ መመገቡም እንዲሁ በሳይንስ የታገዘና የተቀናጀ ዘላቂ ዓለም አቀፋዊ ተግባርን ይጠይቃል፡፡
ምንጭ፡ ቴክ ሳይንስ መሔት (ቅፅ 5 ቁ.17) እና Nature