TechIn2
1.22K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
በክረምት አንጎሉን የሚቀንሰው ልዩ እንስሳ
-----------------------------------
የምድራችን ትናንሾቹ አጥቢ የየብስ ላይ እንስሳት የሆኑት የኤትሩስካን ፍልፈሎች (Suncus etruscus) አውራ ጣትን የሚያክሉ ሚጢጢዬ እንስሳት ናቸው፡፡ ስለዚህም እንስሳቱ አድርቀው የሚያስቀሩት የሰሜናዊው ንፍቀ ክበብ የክረምት ወራትን ያለችግር ለመሻገር የሚያስችላቸውን ጉልበት ለመሰብሰብ ከሰውነት ክብደታቸው ስምንት እጥፍ እና ከዚያ በላይ የሆነ ምግብ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህን ከማድረቅ ይልቅ ግን እንስሳቶቹ በክረምት ወቅቶች ሶማቶሴንሰሪ ኮርቴክስ የተባለው የአንጎላቸውን ክፍል ይዘት በ28 በመቶ በመቀነስ ኃይል እንደሚቆጥቡ አዲስ ጥናት አሳይቷል፡፡
ይህ ፍልፈሎችን ለየት የሚያደርግ ፀጋ ነው፤ ከዚህ ቀደምም ሌላ የፍልፈል ዝርያ በሆኑት ሬድ ሩትድ ፍልፈሎች ላይ የተሰሩ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት እንስሳቱ በተወለዱ በመጀመሪያው በጋ ላይ የሰውነት እድገታቸውን ይጨርሳሉ፡፡ ሆኖም የአውሮፓውያኑ መኸር መግባት ሲጀምር በተቃራኒው መጠናቸው ማሽቆልቆል ይጀምራል፤ የአከርካሪያቸው ርዝመት፣ የራስ ቅል፣ አንጎል፣ አጥንቶች፣ ጉበትና ሌሎች የሰውነት አካላት፣ ጠቅላላው ክብደታቸው ሁሉም መጠናቸው መቀነስ ይጀምራል፡፡ የካቲት አካባቢ ላይ ደግሞ ዳግም እንደቀድሞው አድገው የሰውነት ዕድገት ጣርያቸውን የሚነኩና በፀደይ ወራቱ ለፆታዊ ግንኙነት ዝግጁ የሚሆኑ ይሆናል፡፡ አስከትለው አንዴ ብቻ ዘራቸውን ከተኩ በኋላ ወዲያው ይህችን ዓለም በሞት ይሰናበታሉ፤ ይህች የእነርሱ ምጥን የህይወት ዑደት ናት፡፡
ጥናቱን ለማጥት የተመራማሪዎች ቡድኑ ለአንድ ዓመት በአራቱም ወቅቶች 10 የኤትሩስካን ፍልፈሎቹን ኤም.አር.አይን በመጠቀም ሲከታተላቸው ቆይተዋል፡፡ በውጤቱም ምንም እንኳን እንስሳቱ በየዕለቱ ያለማቋረጥ እንደልብ እንዲመገቡ፣ የስፍራው ሙቀት መጠን ሳይለዋወጥ፣ ብርሃንም ለ12 ሰዓታት እያገኙ የቆዩ ቢሆንም በክረምቱ ወቅት የአንጎላቸው ይዘት መቀነሱን ማስተዋል ችለዋል፡፡ ታድያ ይህ ያልተቋረጠ ለውጥ ከውስጥ ከሚነሱት እንደ ዕድሜ እና የጊዜ ሂደት፤ እንዲሁም የምግብ መኖር አለመኖርን ከመሳሰሉ ውጪያዊ የተፅዕንዖ ምንጭ ሁነቶች የሚነሳ እንደሆነ ተቀምጧል፡፡
የጥናት ቡድኑ ሌሎች ላይ ባደረገው ምልከታም ከእንስሳቱ ዊስከር መልዕክት የሚቀበለውና በአደን ወቅት ጥቅም ላይ የሚውለው ይህ ሶማቶሴንሰሪ ኮርቴክስ የተሰኘ የአንጎል ክፍል መቀነስን አሳይቷል፡፡ አንዱ የሶማቶሴንሰሪ ኮርቴክስ ወለል በክረምቱ ወቅት ስፋቱን በ28 በመቶ መቀነስ ሲችል ከበጋው መግባት ጋራ ተያይዞ ደግሞ ዳግም በ29 በመቶ አድጓል፡፡ የኒሮን መጠኑም ከክረምት ወደ በጋ ሲሸጋገሩ የ42 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
እነዚህ የይዘት ለውጦች በአንጎል እንቅስቃሴው ላይም ለውጦችን አምጥቷል፡፡ የጥናት ቡድኑ ኒሮኖቹን የነቁ፣ የተጨቆኑ እና ምንም ተፅዕንዖ ያልደረሰባቸው ብሎ በሶስት ከፍሎ አስቀምጧቸዋል፡፡ የተጨቆኑት ኒሮኖች በበጋው እና የፀደይ ወቅቶች ከክረምትና መኸር አንጻር ከፍ ያለ እንቅስቃሴን አሳይተዋል፡፡ ይህ ተግባር እንስሳቱ ኃይልን እንዲቆጥቡ የሚያስችላቸው እንደሚሆን የተመራማሪዎቹ እምነት ነው፡፡ በሌላው የአንጎል ክፍል ላይ ግን የመጠን ለውጦች ሳይታዩ ቀርቷል፡፡
ምንጭ፡ The Scientist
አደጋን የመከላከል ከፍተኛ ብቃት ያላቸው የመንገድ ላይ ምልክቶች
**************************
ከራዳር ጋር ተቀናጅተው የመንገድ ላይ መጨናነቅንና የአየር ጠባይን በመተንተን ለአሽከርካሪዎች ተመራጭ የሆነን መንገድና ሰዓት ማመልከት የሚችሉ የትራፊክ ምልክቶች መሰራታቸው ተሰማ፡፡ በአለማችን በተለያዩ በሽታዎች፣ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ምክንያቶች ህይወታቸውን የሚያጡና ለከፍተኛ አካል ጉዳት የሚዳረጉ ሰዎች እየበዙ መጥተዋል፡፡ ከእነዚህ ምክንያቶች ባልተናነሰ የትራፊክ አደጋ ለብዙዎች ህይወት ህልፈትና ምስቅልቅል ከፍተኛ ድርሻ አላቸው፡፡
እነዚህ የመንገድ ዳር ምልክቶች አሽከርካሪውን ለአደጋ ሊያጋልጥ የሚችል ማንኛውንም ችግር ቀድመው በተገጠመላቸው መሳሪያ አማካኝነት ማሳወቅ እንደሚችሉ ተነግሯል፡፡ በፖላንድ የሚገኙ ተመራማሪዎች በተለይ የጉዳት መጠናቸው ከፍተኛ ይሆናል ተብለው በሚገመቱ የፍጥነት መንገዶች ላይ ሊኖር የሚችልን አደጋ መቀነስ የሚያስችሉ በራዳር፣ ምስልና ድምጽ መለያ እንዲሁም የትራፊክ ፍሰት መጠንና እለታዊ የአየር ጠባይን በመረዳትና በመተንተን ለአሽከርካሪዎች በጣም አስፈላጊ መረጃዎችን መስጠት የሚችሉ የመንገድ ላይ ምልክቶችን ሰርተዋል፡፡
አሁን (7-10/12/2020) እየተከናወነ ባለው 179ኛ የAcoustical Society of America አመታዊ ስብሰባ ላይ ለታዳሚዎች የጥናቱ ውጤት ይቀርባል ተብሎ እቅድ ተይዞለታል፡፡ ምርምሩም የፍጥነት መንገዶችን የፍሰት መጠን ለመለካትና በመንገድ ላይ የሚሽከረከሩ መኪኖች የሚፈጥሩትን ድምጽ በመጠቀም ሊኖር የሚችልን የመኪኖች ብዛት ማወቅ እንደሚያስችል ተነግሯል፡፡
በሂደቱም Acoustic vector sensor የተባለ ቴክኖሎጂን የሚጠቀም ሲሆን ለምንም አይነት ኤሌክትሮ መግነጢሳዊ ጣልቃ ገብነት እንደማይጋለጥ ተሰምቷል፡፡ መደበኛ ምልክቶች ላይም ነባራዊ ሁኔታውን መሰረት ያደረገ መላመድ እንዲችሉ ተደርገዋል፡፡ ለምሳሌ ያክል የፍጥነት ወሰን አመልካች ምልክት ካለው የመንገድ መጥበብና መስፋት ጋር የተናበበ የፍጥነት ልክ እንዲያሳይ ያስችላል፡፡
ምንጭ፡ SciTechDaily
አረንጓዴ ሽንት የሸናው ግለሰብ
ሰሞኑን ታሞ ሆስፒታል አልጋ ላይ የተኙ አንድ ግለሰብ ሽንት አረንጓዴ ቀለምን መያዙ አግራሞትን ፈጥሯል፡፡ ሆኖም ድንጋጤን የሚያጭረው ይህ ክስተት ጉዳት አልባና ግለሰቡ የሚደግላቸው ህክምና ውጤት ሆኖ ተገኝቷል፡፡
በ62 ዓመት ዕድሜ ላይ የሚገኙት ግለሰቡ ክሮኒክ ኦብስትራክቲቭ ፓልሞናሪ ዲዚዝ (COPD) የተባለ የሳንባ በሽታ አጋጥሞት መተንፈስ ስለተቸገሩ ነው ወደ ሆስፒታሉ ድንገተኛ ክፍል ውስጥ እንዲገቡ የተደረገው፡፡ ሰውየው ለህይወታቸው ሊያሰጋ በሚችል አኳሀንም በደማቸው ውስጥ ከፍተኛ የካርበን ዳይ ኦክሳይድ ይዘት ተገኝቶባቸዋል፡፡ ይህን ተከትሎም ሆስፒታሉ ውስጥ ወዳለው የከፍተኛ ክትትል ክፍል ውስጥ እንዲገቡ የተደረገ ሲሆን የአተነፋፈስ መርጃ መሳርያ እና ፕሮፎፖል የተባለ የማደንዘዣ መድሀኒት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ከአምስት ቀናት ቆይታ በኋላ በከረጢት ውስጥ ሲሰበሰብ የነበረው የታማሚው ሽንት ወደ አረንጓዴነት ለመቀየር በቅቷል፡፡
አረንጓዴ ሽንት በህክምና የጎንዮሽ ተፅዕንዖ፣ አንዳንድ ኢንፌክሽኖች እና የጉበት ችግርን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል፡፡ በዚህ ግለሰብ ላይ የሆነው ግን በፕሮፎፖል ሳብያ የመጣ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ይህን አይነት ህክምና ለጀነራል አንስቴዢያ ተብሎ ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን አልፎ አልፎም የሰዎችን ሽንት ወደ አረንጓዴነት ሲቀይር ይታያል፡፡ እንዴት ሆነ የሚለው ግን በዘርዝር የሚታወቅ አልሆነም፡፡ ሆኖም አንዳንድ የፕሮፎፖሉ ቁሶች ተሰባብረው ሲወጡና ይህም ከጉበት ይልቅ በኩላሊት አማካኝነት ሲሆን (ለወትሮ የፕሮፎፖል ኬሚካል አፀግብሮት ወይም ሜታቦሊዝም የሚደረገው ጉበት ውስጥ ነው) ሊከሰት እንደሚችል ከ5 ዓታት በፊት ጆርናል ኦፍ ክሊኒካል ኤንድ ዲያግኖስቲክ ሪሰርች ላይ የወጣ ምርምር አመላክቶ ነበር፡፡ ሆኖም ይህ የሽንት ቀለም ለውጥ ጉዳት የሌለው እና የህክምናውን መቋረጥ ተከትሎ የሚያቆም ነው፡፡ እኚህ ታማሚም ፕሮፎፖሉ ሲነሳለት ነገሮች ወደ ቀድሞ ጤናማ ይዞታቸው ተመልሰውለታል፡፡ ኋላም ለሁለት ሳምንታት በሆስፒታሉ ቆይቶ ወደ ማገገሚያ ማዕከል አቅንቷል፡፡
የሰው ልጆች ሽንት ወደ አረንጓዴነት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ቀለሞችንም ይዞ ሊወጣ ይችላል፡፡ ባሳለፍነው የፈረንጆች ዓመት 2019 ላይ የሽንት መሰብሰቢያ ከረጢት ውስጥ የገባ የአንዲት ሴት ሽንት ከረጢቱ ውስጥ በተፈጠረው የኬሚካል አፀግብሮት ሳብያ ወደ ሐምራዊነት ተለውጦ ነበር፡፡
ምንጭ፡ Live Science
የጭንቅላት ትክክለኛ ቦታንና ጊዜን የማስታወስ ብቃት
*************************
በስነ ልቦና የትምህርት ዘርፍ በሰው ልጅ ጭንቅላት ውስጥ የረጅም፣ የመካከለኛና የአጭር ጊዜ የትውስታ ሂደት እንዳለ ይነገራል፡፡ UT Southwestern በሚባል የምርምር ተቋም የሚሰሩ ተመራማሪዎች የሰው ልጅ ጭንቅላት ትውስታዎችን እንዴት ለረጅም ጊዜያት መያዝ እንደሚችል አዲስ ፍንጭ ማግኘታቸው ተሰምቷል፡፡ የምርምሩ ውጤት ከመሰረታዊው የማስታወስ ችሎታ በተጨማሪ በአልዛይመር በሽታና በጭንቅላት ላይ በሚደርስ አደጋ ምክንያት የሚመጣን የትውስታ ማጣት ችግርን ማከም የሚያስችል መፍትሔንም ያካተተ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
ከአስርት አመታት በፊት 'time cells' የተባሉ ህዋሳት በአይጦች ጭንቅላት ውስጥ ተገኝተው ነበር፡፡ እነዚህ ህዋሳትም በየአጋጣሚው የሚከሰቱ ሁኔታዎችን መዝግቦ የማስቀመጥ ልዩ ሚና እንዳላቸው ታውቆ ነበር፡፡ ይህም ጭንቅላት የሚከሰቱ ሁነቶችን በቅደም ተከተላቸው ሰድሮ እንዲያስቀምጥ በማድረግ ነው፡፡ hippocampus በመባል በሚታወቀው የጭንቅላት ክፍል የሚገኙት እነዚህ ህዋሳት ነገሮችን የማደራጀት ተግባር ሲከውኑ ተስተውለዋል ያለው በምርምሩ የተሳተፈው Bradley Lega, M.D ነው፡፡
ከዚህም በመነሳት ተመራማሪዎቹ ተመሳሳይ የጭንቅላት ህዋሳት በሰዎች ውስጥ መኖርና አለመኖራቸውን ማጥናት ጀምረዋል፡፡ በሂደቱም ፈቃደኛ ሆኑ የ epilepsy ህመም ታካሚዎችን የተያዩ ምርምሮች ተሰርተዋል፡፡ ይህ በ27 ፈቃደኞች ላይ የተሰራው ምርምር 'time cells' የተሰኙ የጭንቅላት ህዋሳት በሰዎች የትውስታ ሂደት ውስጥ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ታውቋል፡፡ ይህም ሁነቶች የተከሰቱበትን ትክክለኛ ሰዓት ሰዎች በቀላሉ እንዲያስታውሱ የሚያደርጋቸው እንደሆነ ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
በሌላ ተያያዥነት ባለው ጥናት በሰዎች እና በእንስሳት ጭንቅላት ውስጥ የሚገኙ ነገሮች የተከወኑበትን ትክክለኛ ቦታ ማስታወስ የሚያስችሉ የጭንቅላት ህዋሳት ላይ ምርምር ተደርጓል፡፡ በዚህም ጥናት እንደመጀመሪያው ሁሉ አይጦች ተመሳሳይ ሁኔታ የታየባቸው ሲሆን አይጦች ባላቸው ቦታዎችን የማስታወስ ሂደት ውስጥ እነዚህ የቦታ ህዋሳት ቦታዎች በጭንቅላት ውስጥ በቅደም ተከተል ተደራጅተው እንዲቀመጡ ያደርጋሉ፡፡
በጥናቱም በአይጦች ጭንቅላት ውስጥ የሚስተዋልን የበፊቱንና የቅርብ ጊዜውን የቦታዎች ትውስታ የማፈራረቅ ሂደት ለመመርመር አጥኝዎቹ በአይጦቹ ጭንቅላት ውስጥ ኤሌክትሮዶችን በማስገባት ጥናቶችን አድርገዋል፡፡ በዚህም place cells የሚባሉት ህዋሳት በጭንቅላት ውስጥ የተቀረጹ የቅርብ ጊዜም ሆነ የቆዩ ምስሎችን በቅደም ተከተል እያመላለሱ ሲስተላልፉ ተስተውለዋል፡፡
ከዚህ ግኝት በመነሳት ተመራማሪዎቹ ህዋሳቱ እንዲህ አይነት ተግባራትን እንዲያከናውኑ የሚያግዟቸው ሌሎች የጭንቅላት ክፍሎችን እያጠኑ ሲሆን በዚህ የሚገኘው ውጤትም በአልዛይመርና በአደጋ ምክንያት የሚመጣን የሰዎች ትውስታ ማጣትን ለማከም የሚያስችሉ መሰረታዊ እውቀቶች እንደሚገኙ ተመራማሪዎቹ ተስፋ አድርገዋል፡፡
ምንጭ medicalxpress
የህዋ ሼልን (spacecraft) እንዲሸከም ታስቦ የተሰራው ግዙፉ አውሮፕላን
****************************
በአለማችን ላይ እስከዛሬ ድረስ ከተሰሩ ግዙፍ የአየር ላይ መጓጓዣዎች መካከል Airbus Beluga፣ Boeing Dreamlifter እና Antonov AN-225 ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህም ለተለየ አገልግሎት እና በጣም ግዙፍ የሆኑ በመደበኛ አውሮፕላኖች ሊንቀሳቀሱ የማይችሉ ጭነቶችን ለማንቀሳቀስ ታስበው የተሰሩ ናቸው፡፡ ቁጥራቸው በጣም ጥቂት በመሆኑና የተለየ እይታ ያላቸው በመሆኑ በአየር መንገድ ታሪኮች ውስጥ የታወቁ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ ግን በ1960ዎቹ አሜሪካን በህዋ ላይ ፉክክሩ በረዳው Super Guppy ከተባለው አውሮፕላን ውጭ የማይታሰቡ ናቸው፡፡
NASA ቀላል ክብደት ኖሮት መጠኑ ግን በጣም ከፍተኛ የሆነን ጭነት ማጓጓዝ የሚቻልበትን መንገድ ሲፈልግ ነበር፡፡ በዚህም ተቋሙ እንዲህ አይነት እቃዎችን ከሚያመርትበት ከካሊፎርኒያ እነዚህን እቃዎች ወደ ሚጠቀምበት ፈሎሪዳ ላማንቀሳቀስ የሚያስችል ከፍተኛ ስፋት ያለው አውሮፕላን ሲፈልግ እንደነበር የአቪየሽን ታሪክ ተመራማሪው Graham M ይናገራል፡፡
አሜሪካ የህዋ ፕሮግራሞችን መስራት በጀመረችበት ወቅት የተለያዩ የሮኬት ክፍሎችን ወደ Cape Kennedy በፓናማ ዋሻ ወይም በሜክሲኮ ባህረ ሰላጤ በጀልባዎች ታጓጉዝ ነበር፡፡ በ1962 የተሰራው አውሮፕላን ግን በዘመኑ ካሉት ሁሉ ከፍተኛ መጠን ያለውን ጭነት መጫን የሚያስችል በመሆን በዚህ ረገድ ያለውን ችግር መቅረፍ ችሏል፡፡ ይህም 20 ጫማ የሚደርስ ዲያሚትር የነበረው ሲሆን 18 ቀናት ይወስድ የነበረውን የማጓጓዝ ሂደት ወደ 18 ሰዓታት ዝቅ ማድረግ አስችሏል፡፡
ይህ Pregnant Guppy በመባል የሚታወቀው አውሮፕላን እስካሁን ከተሰሩት ስምንት አውሮፕላኖች ውስጥ የመጀመሪያው ነው፡፡ ከአውሮፕላኖቹ መካከል አንደኛው የ1940 ቴክኖሎጂን የሚጠቀም ቢሆንም NASA አሁንም ለማጓጓዣነት ይጠቀምበታል፡፡
ምንጭ CNN Travel
ለቆዳ ህክምና አዲስ ቴክኖሎጂ
******************
የቆዳችንን አወቃቀር በመመልከት እንደ የቆዳ ካንሰርና ሌሎች የቆዳ በሽታዎችን ማከም የሚያስችል የህክምና መሳሪያ መሰራቱ ተነገረ፡፡ T-ray Imaging የተባለው የህክምና ዘዴ ጨረርን በመጠቀም በቆዳችን ላይ የሚኖርን ማንኛውም አይነት ችግር መለየት የሚያስችል ቴክኖሎጂ እንደሆነ የዘገበው SciTechDaily ነው፡፡
Warwick በተባለ ዩኒቨርሲቲ እና በቻይናው የሆንግኮንግ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ተመራማሪዎች ከተለያዩ አቅጣጫዎች የቴራሄርትዝ ጨረርን በመልቀቅ ውስብስብ የሆነውን የቆዳችንን አወቃቀር በግልጽ በመመሰል (detailed picture) የድርቀት መጠኑንና ሌሎች ችግሮችንን መለየት እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡ ምርምሩ ለህክምናው አለም የእያንዳንዱን ሰው የቆዳ ባህሪ መለየት የሚያስችል አዲስ ግብአት እንዳስገኘም ይታመናል፡፡
ጨረሩ ቆዳችንን ለሌላ ችግር የማያጋልጥና ከቆዳችን ተንጸባርቆ ሲመለስ የቆዳችንን የርጥበት መጠን በመለየት በዚህ ዘርፍ ያለውን ህክምና ቀላልና የተሳካ ያደርገዋል፡፡ ቴክኖሎጂው እስካሁን ካሉት ቴክኖሎጂዎች የሚለየው የቆዳን የድርቀት ልክ (hydration) በትክክል ለክቶ የሚያሳውቅ መሆኑ ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ቴክኖሎጂው ለቆዳ እንክብካቤ የሚያገለግሉ ቅባቶችን እንደየእንዳንዱ ሰው የቆዳ ባህሪ የተስማማ ግብዓት እና ልኬትንም ለመስራት እንደሚያስችል ተጠቁሟል፡፡ የቆዳ ካንሰር ያለባቸውን ሰዎች ቀዶ ህክምና ከመስራት በፊት ይህን የጨረር ምሰላ በማድረግ በሽታው በቆዳ ውስጥ ምንያክል እንደተስፋፋ ማወቅ ይቻላል፡፡
ሙከራውን ለመስራት ተመራማሪዎቹ ፈቃደኞች እጃቸውን በተዘጋጀው የጨረር ፈንጣቂ መሳሪያ ላይ ለ30 ደቂቃዎች ያክል እንዲያስቀምጡ በማድረግ አራት የተለያዩ ልኬቶችን ሰርተዋል፡፡
ምንጭ SciTechDaily
የቀለም አጠቃቀም እና ባህርያት የተዳሰሰበት የዛሬው ቴክኢን ሴሚናር
=========================
በተለያዩ ቀለሞች እርስ በእርሳዊ ጥምረት ላይ ያተኮረው የቴክኢን ሴሚናር ዛሬ በኢንስቲትዩቱ የስብሰባ አዳራሽ ተካሂዷል፡፡ “COLOR THEORY” በሚል ርዕስ የተካሄደው የዛሬው ሴሚናር የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ባልደረባ በሆኑት አቶ ብርሃን ታፈሰ አማካኝነት ገለፃ የቀረበበት ሲሆን ሌሎች የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪዎችንም ተሳታፊ አድርጎ የተዘጋጀ ነበር፡፡
አቶ ብርሃን በገለፃቸው በተለያዩ ቀለማት መካከል ያለውን ግንኙነት እና ይህን ለማመላከት ታስቦ በታላቁ ተመራማሪ አይዛክ ኒውተን እ.አ.አ በ1666 የተፈጠረው የቀለማትን ግንኙነት መመልከቻ ስልትን (Color Wheel) የዳሰሱ ሲሆን የትኛው ቀለም ከየትኛው ቀለም ጋር ተቃርኖ እንዳለውና ይህም ሌሎች ልዩ ቀለማትን እንደሚፈጥር አስቀምጠዋል፡፡ በተጨማሪም የትኛው የቀለም ጎራ ከየትኛው ሁነት ጋራ ቁርኝት እንደሚፈጥር፣ የትኛው ቀለም ከየትኛው ቀለም የእይታ ተስማሚነት እንዳለው እንዲሁም ሌሎች የቀለም አጠቃቀምን የተመለከቱ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ተዳሰውበታል፡፡
ከታዳሚያኑም በተለይ ቀለም ከእይታና ስነ-ልቦናም ባሻገር ጤናን በተመለከተ ሊፈጥር በሚችለው ተፅዕንዖ፣ በተለያየ መልኩ የተቋማትን ገፅታና ማንነት በመገንባት ረገድ የሚጫወተው ሚና እንዲሁም በሀገራዊና ማህበረሰባዊ ማንነት ውስጥ ያለውን ቦታ የሚያትቱ ጥያቄና አስተያየቶች ተነስተዋል፡፡ አቶ ብርሃንም በተነሱት ጥያቄና አስተያየቶቹ ላይ ሙያዊ ማብራርያ ሰጥተውባቸዋል፡፡
ከፍታው በየጊዜው የሚጨምረው ድንቁ ተራራ
***************************
የአለማችን የከፍታ ልክ የሆነው ኤቨረስት ተራራ ታላቅነቱን ለማስጠበቅ ይመስል ዛሬም ከፍታው እየጨመረ እንደሆነ ተነገረ፡፡ ቻይናና ኔፓል ተስማምተው ባወጡት መረጃ መሰረት ከፍታው 8,848.86 ሜትር ወይም 29,031 ጫማ በመድረስ ከኔፓል ልኬት የ86 ሳንቲሜትር ወይም 2.8 ጫማ ጭማሪ ከፍ እንዳለ ታውቋል፡፡ ከቻይና በኩል ደግሞ ይህ ተራራ ከ4 ሜትር በላይ ከፍ ማለቱ ተሰምቷል፡፡ ይህ ልዩነት የመጣውም ቻይናና ኔፓል ተራራውን የሚለኩበት መነሻ የተለያየ በመሆኑ ነው፡፡
በ1859 እንግሊዛውን ቀኝ ገዢ የስነ ምድር አጥኚዎች ተራራው 8840 ሜትር ወይም 29,002 ጫማ ከባህር ጠለል በላይ ከፍ እንደሚል ተናግረው ነበር፡፡ በኋላ ላይ ኢድሙንድ ሂላሪ እና ቴንዚንግ ኖርጋይ የተባሉ ሰዎች ከተራራው ጫፍ ድረስ ግንቦት 1953 መውጣት በመቻላቸው የከፍታ ልኬቱ ተስተካክሎ 8,840 ሜትር ወይም 29,002 ጫማ ከባህር ጠለል በላይ እንደሆነ ታውቋል፡፡
ምንም እንኳን ኔፓል በመንግስት ደረጃ ባትቀበለውም በ1999 የአሜሪካ ብሔራዊ ስነምድር ማህበረሰብ (US National Geographic Society) የኤቨረስት ተራራ ከፍታ was 8,850 ሜትር ወይም 29,035 ጫማ እንደሆነ ደምድሞ ነበር፡፡ ቻይና በሂደት የራሷን ትናት እያደረገች ቆይታ በ2005 ተራራው 8,844.43 ሜትር ወይም 29,015 ጫማ ከፍታ አለው የሚል መረጃ ሰጥታለች፡፡
ከዚያም ኔፓል በኋላ ላይ ቻይና የተካተተችበትን ጥናት በ2015 የነበረው የመሬት መንቀጥቀጥ የተራራውን ከፍታ ቀይሮታል የሚል ሀሳብ በነበረበት ወቅት ሰርታለች፡፡ የመረጃ ስብሰባውን ስራ 300 የሚጠጉ ኔፓላውያን በእግርና በሔሊኮፍተር በመሆን የሰሩ ሲሆን የጥናቱም ውጤት በ2019 በኔፓል አማካኝነት ሊወጣ የነበረ ቢሆንም ፐሬዘዳንት Xi Jinping ኔፓልን በጎበኙበት ወቅት በጥናቱ ላይ ቻይናም እንድትሳተፍበት ተስማምተው በመመለሳቸው ውጤቱ ሳይገለጽ ቀርቷል፡፡ በያዝነው የፈረንጆች አመት የቻይና የተራራ ላይ ተመራማሪዎች በኮቪድ ምክንያት ብቸኛ ተራራ ወጭዎች በመሆናቸው ለስራቸው የተመቻቸላቸው ይመስላል፡፡
ምንጭ sciencealert
እንደ አፍንጫ ሽታን የሚያነፈንፈው ድሮን
**********************
ሲቪል ድሮኖች ካሏቸው ጠቀሜታዎች ውስጥ አንዱ የሰው ልጆች መድረስ በማይችሉባቸው ቦታዎች መድረስ መቻላቸው ነው፤ ለአብነት በደረሰባቸው የተፈጥሮ አደጋ ምክንያት የቀድሞ አቋማቸው ላይ የማይገኙ ህንፃዎች እንዲሁም ሊፈነዱ የሚችሉ ቁሶች ያሉባቸው አደገኛ አከባቢዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ አጥኚዎች ታድያ እነዚህን በመሳሰሉ አደገኛ ሁኔታዎች ውስጥ ያሉ ከአደጋ የተረፉ ሰዎችን እንዲሁም ፈንጂ፣ በተቀደደ ትቦ የሚፈስ ጋዝ እና ሌሎች ችግሮችንም በሚያመነጩት ሽታ ለመለየት የሚችል ድሮን የመስራት ፍላጎትን አድሮባቸው ቆይተዋል፡፡ ሆኖም እስካሁን የተፈጠሩት ሴንሰሮች እነዚህ ሽታዎችን በብቃት እና በሚያስፈልገው ፍጥነትም ለመለየት እየተቸገሩ ነበር፡፡
አሁን ግን በዩኒቨርቲ ኦፍ ዋሽንግተን ምሁራን የሚመራው ምርምር ይህን የሚቀርፍ መስሏል፡፡ ስሜሊኮፍተር የሚል ስያሜን ያገኘው አዲሱ የድሮን ፈጠራ የተገጠመለትን የአፍንጫ አንቴና በመጠቀም ተፈላጊው ሽታ ወዳለበት አቅጣጫ የሚያመራ ነው፡፡ ድሮኑ የተገጠመለት አንቴና በአባቢው ያሉ ኬሚካሎችን ጠረን በመለየት ምግብ እንዲከሁም ሰዎች ወዳሉበት ስፍራ መምራት ይችላል፡፡
ስሜሊኮፍተሩ ሽታን ለማፈላለግ ማንኛውንም እርዳታ ከተመራሪዎቹ መውሰድ አላስፈለገውም፡፡ ይህን ለመከወን ከፍጡራን አፍንጫ የሚመሳሰል ስልትን ይጠቀማል፤ ፍለጋውን ቅድሚያ በተወሰነ ርቀት ወደ ግራ አቅጣጫ በማቅናት የሚጀምር ሲሆን በዚያ የፈለገውን ሽታ ካላገኘ ተመልሶ በተመሳይ ርቀት ወደ ቀኝ ይጓዛል፡፡ በዚህ ሂደት የሚፈልገውን ጠረን ያገኘ እንደሆነ የበረራ አኳሀኑን በመለወጥ ወደ እርሱ ይገሰግሳል፡፡
ስሜሎኮፍተሩ በዙርያው ያሉትን ነገሮች ቅርበት በየ አንድ ሴኮንዱ ለአስር ጊዜ ያህል እንዲለካ በሚያስችሉት አራቱ ሴንሰሮቹን በመጠቀም እራሱን ከመሰናክሎች ይጠብቃል፡፡ አንድ ቁስ በ20 ሴ.ሜ ቀርቦት ሲገኝ የጉዞ አቅጣጫ ማስተካከያ ያደርጋል፡፡
ሌላው ይህ ድሮኑ እንዳለው የተነገረለት ጥቅም ለዚህ እንቅስቃው የጂ.ፒ.ኤስ ቴክኖሎጂን አለመጠየቁ ነው፤ ይልቁንም ልዩ ልዩ በራሪ ነፍሳት አይኖቻቸውን ተጠቅመው ሲያደርጉት እንደሚታየው ሁሉ እርሱም የተገጠመለትን ካሜራ በመጠቀም ዙርያውን ይቆጣጠራል፡፡ ይህ ደግሞ ድሮኑን ትቦ ወይም ጉድጓድን ለመሳሰሉ የምድር በታች እና ውስጥ ለውስጥ ተልዕኮዎች ስል ያደርገዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዋሽንግተን ውስጥ በተደረጉት ሙከራዎች ድሮኑ ከአበባዎች የሚገኙትን የመሳሰሉ ጠረኖችን እንዲለይና ወደ እነርሱም እንዲያቀና ተደርጎ ነበር፡፡ ሆኖም ስራዎች በዚህ አያልቁም፤ ወደፊት በፍርስራሾች ውስጥ የተቀበሩ ሰዎች ትንፋሽ የሚወጣ ካርበን ዳይ ኦክሳይድን በማሽተት እንዲሁም ያልፈነዱ ፈንጂዎችን የሚለቁት የኬሚካል ጠረን በመለየት ህይወት የመታደግ ስራዎችን የመስራት ዓቅም እንደሚኖረው ተመራማሪዎቹ ተስፋ አድርገዋል፡፡
ምንጭ፡ Tech Xplore