TechIn2
1.22K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
This media is not supported in your browser
VIEW IN TELEGRAM
ከምድር የመጥፋት አደጋ የተጋረጠበት የዱር ህይወት 9 አሳዛኝ እውነታዎች
የምድር እጣፈንታ እና የአለማችን የተፈጥሮ ገፅታ ከመቼውም ጊዜ በላይ በከባድ ስጋት ውስጥ እንደሚገኝ የማያጠራጥር ነው፡፡ የምድርን የተፈጥሮ ሚዛኗ ሊያስቱ የሚችሉ አያሌ አደጋዎች በሰው ልጆች የህይወት ዘመን ውስጥ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መፈፀማቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ዓለማችን ከዕለት ወደ ዕለት የሙቀት መጠኗ እየጨመረ፣ አቅፋ የያዘቻቸው የተለያዩ ሰብሎችና እንስሳት የመጥፋት አደጋ እየተጋረጠባቸው ይገኛል፡፡
ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ዘጠኝ እውነታዎች ወይም ምክንያቶች መኖሪያችን ብለን በምንጠራት መሬት እየተከሰቱ ያሉ እና የኛን ፈጣን ምላሽ የሚጠብቁ አሳዛኛ ሁኔታዎች ናቸው፡፡
1 - አሁን ላይ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዝርያዎች የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸዋል
የአለም አቀፉ የብዛ ህይወትና ስነምህዳር አገልግሎት በሳይንስ ፖሊሲ ፕላትፎርም ላይ እንዳስታወቀው በሰው ልጆች ታሪክ እስካሁን ያልታየ የእንስሳትና የእፅዋት ዝርያ የመጥፋት አደጋ ተደቅኗል፡፡ የተቋሙ መረጃ እንደሚያሳየው ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዝርያዎች የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸዋል፡፡
2 - የዱር አንስሳት ብዛት ከ1970 በኋላ በ2/3ኛ ቀንሷል
የዓለም የዱር እንስሳት ፈንድ ሊቪንግ ፕላኔት ኢንዴክስ በተባለው የ2020 አመታዊ ሪፖርቱ እንዳመለከተው እንደአውሮፓውያኑ ከ1970 አንስቶ እስከ 2018 ድረስ የዱር አንስሳ ብዛት መጠን በአማካይ በ68% መቀነስ አሳይቷል፡፡ በዚህ የእንስሳት መጠን ውስጥ ወፎች፣ አጥቢ አሳዎች፣ ተሳቢና አምፊቢያን እንስሳቶች በዋናነት በዝርዝር ውስጥ የሚገኙት ናቸው፡፡
3 - የአሜሪካ ሞቃታማ ንኡስ ክልሎች በውድቀት ላይ መገኘት
የዱር አንስሳት በብዛት ከሚገኝባው አካባቢዎች ቀዳሚ የሆነው ይህ ንኡስ ክልል ከ1970 ጀምሮ 94% የሚሆነው የዱር አንስሳ የጠፋበት አካባቢ ነው፡፡ የዓለም የዱር እንስሳት ፈንድ እንዳመለከተውም የአሜሪካ ሞቃታማ ንኡስ ክልል በየትኛውም የምድር ክፍል ያልተመዘገበ የዱር አንስሳት ጥፋት የታየበት አካባቢ ነው፡፡
4 - ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በተደጋጋሚ የሚሞቱ ዝርያዎች መብዛት
በአሜሪካ በሚገኘው የብራውን ዩኒቨርስቲ በ2014 የተደረገ ጥናት እንደሚያሳው የሰው ልጅ ወደዚች ምድር ከመምጣቱ አስቀድሞ የእንስሳትና የእፅዋት ዝርያ አልፎ አልፎ የመጥፈት እድል ነበረው፡፡ ይሁንና ሰዎች ይህችን ምድር ከተቀላቀሉ በኋላ የተለያዩ ዝርያዎች ከምድር የመጥፋት እድላቸው 1,000 ጊዜ ብልጫ እንዳለው እና ይህም ተደጋግሞ እንደሚፈፀምም ጥናቱ አመላክቷል፡፡
5 - በውሃ ውስጥ የሚኖሩ ዝርያዎች በፍጥነት መቀነስ
የዓለም የዱር እንስሳት ፈንድ ሊቪንግ ፕላኔት ኢንዴክስ በተባለው የ2020 አመታዊ ሪፖርቱ እንዳመለከተው በውሃ ውስጥ የሚኖሩ ዝርያዎች ከሌሎች የዱር አንስሳት በተለየ በፍጥነት በመቀነስ ላይ ይገኛሉ፡፡ በሪፖርቱ እንደተመለከተው ከ1970 አንስቶ እስከ 2018 ድረስ በአማካይ 84 በመቶው በውሃ ውስጥ የሚኖሩ ዝርያዎች በፍጥነት በመቀነስ ላይ ናቸው፡፡
6 - የትሮፒካል ደን በተለያዩ ምክንያቶች መጥፋት
የአለም አቀፉ የብዛ ህይወትና ስነምህዳር አገልግሎት በሳይንስ ፖሊሲ ፕላትፎርም ላይ እንዳስታወቀው አንደአውሮፓውያኑ ከ1980 አንስቶ እስከ 2000 ድረስ ብቻ 100 ሚሊዮን ሄክታር ደን በትሮፒካል የምድር አካባቢ ጠፍቷል፡፡ ይህ የደን ጭፍጨፋ በብዛት የተመዘገበው በላቲን አሜሪካ እና በደቡብ ምስራቅ እስያ ሲሆን በዋናነትም ለከብት እርባታ እና ለግብርና በሚል የተከናወነ ነው፡፡
7 - 40 በመቶው እፅዋት የመጥፋት አደጋ
የአለም የእፅዋትና ፈንገስ ሪፖርት በስሩ በሚገኘው ሮያል ቦታኒክ ጋርደን እንደሚያመለክተው ከአስሩ አፅዋቶች አራቱ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸው ሲሆን ይህም የ39.4% ልኬት ይታይበታል፡፡ በዚህ የመጥፋት አደጋ ውስጥ ከባዱ ስራ እፅዋቶቹ ከመጥፋታቸው በፊት የመለየት ስራ ሲሆን፣ በ2019 ብቻ 1,942 የእፅዋት ዝርያዎች ተለይተው ተመዝግበዋል፡፡
8 - ከግብርና ኢንዱስትሪ ጋር ተያይዞ በአያለው የቀነሱት ነፍሳቶች (insects)
በአለማችን ከግብርና ኢንዱስትሪ መስፋፋት ጋር ተያይዞ በአስር አመት ብቻ ከ40 በመቶ በላይ የነፍሳት ዝርያዎች ከምድር ላይ መጥፋታቸውን በሳይንስ ዳይሬክት ላይ በቅርቡ የወጣ አዲስ ምርምር አስታውቋል፡፡
9 - በራሪ የወፍ ዝርያዎች ብዛታቸው እየቀነሰ መምጣት
የአለም አቀፉ የብዛ ህይወትና ስነምህዳር አገልግሎት በሳይንስ ፖሊሲ ፕላትፎርም ላይ እንዳስታወቀው በአንድ ሃገር ውስጥ መኖሪያቸውን አድርገው የሚራቡ 3.5% የሚሆኑ የወፍ ዝርያዎች ከ2016 ጀምሮ የጠፉ ሲሆን ሌሎች 23 በመቶ የሚሸፍኑ ወፎች ደግሞ በአየር ንብርት ለውጥ ምክንያት ከፍተኛ የመጥፋት አደጋ ያለባቸው ናቸው፡፡
እነዚህ የተፈጥሮ ሃብቶች በዚህ መልኩ አደጋ ውስጥ መገኘታቸው ለኛ ለሰው ልጆች ትልቅ የህልውና ጥያቄ ነው፡፡ የብዛ ህይወት ሃብቶች ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ የተላበሱ በመሆናቸው ማናቸውም በብዛ ህይወት ላይ የሚደርሱ አደጋዎች ለአየር ንብረት መቀያየር ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል፡፡ በመሆኑም አነዚህ አሳዛኝ አውነታዎች አኛኑ ወደማጥፋት ከመሄዳቸው በፊት ተፈጥሮን ከጥፋት መታደግ የዕለት ተዕለት ተግበራችን ሊሆን ይገባል፡፡
ምንጭ፡ World Economic Forum
በጆሯችን አካባቢ የሚፈጠርን ምናባዊ ድምጽ (tinnitus) ለማከም ሰውሰራሽ ክህሎትን መጠቀም
*********************
በጆሯችን የምንሰማውን በገሀዱ አለም የሌለ ምናባዊ ድምጽ ለማስተካከል የጭንቅላት ምስሎችን መጠቀም የሚያስችል ሰውሰራሽ ክህሎት በመጠቀም እንደተቻለ የመረጃ ምንጫችን New scientist ዘገበ፡፡ በአውስትራሊያ ሜልቦርን በሚገኝ አንድ የምርምር ተቋም በአንድ ሰው ጭንቅላት ውስጥ ምናባዊ ድምጽ መኖር አለመኖሩንና ሊያስከትል የሚችለውን የጉዳት መጠን መለካት የሚያስችል የክትትል ሂደት (algorithm) መዘጋጀቱ ተሰምቷል፡፡
ሰውሰራሽ ክህሎቱ በጭንቅላት ውስጥ የሚፈጠርን ድምጽ በ78 በመቶ ትክክለኝነት ከቀላል እስከ ከባድ ደረጃ ያለውን መለካት ያስችላል፡፡ 15 በመቶ የሚሆኑ ጎልማሶች ከባድ በሚባል ምናባዊ ድምጽ የሚጠቁ ሲሆን በአብዛኛው የጀሮ የመስማት አቅምን በመለካትና ታማሚው በሚያቀርበው መረጃ መሰረት ህክምና ይሰጣል፡፡
የምርምር ቡድኑ በመጀመሪያ functional near-infrared spectroscopy, ወይም fNIRS የተሰኘ ሳይንሳዊ መንገድን በከባድ ችግር ላይ ባሉ 25 ሰዎችና ችግሩ በሌለባቸው 21 ሰዎች ተግባራዊ አደረጉ፡፡
ተመራማሪዎች የተለያዩ ልኬቶችን ከሰሩ በኋላ ቀደም ብለው ያዘጋጁትን አሊጎሪዝም ከ fNIRS ጋር የማላመድ ስራ እየሰሩ ነው፡፡ በዚህም በዘርፉ አዲስ ውጤት ይገኛል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡
ለተጨማሪ፡ new scientist
This media is not supported in your browser
VIEW IN TELEGRAM
ለመጀመሪያ ጊዜ በሰው የተሞከረው የሃይፐርሉፕ ቴክኖሎጂ
ሃይፐርሉፕ አዲሱ የትራንስፖርት ቴክኖሎጂ በመሆን አለማችንን የተሻለች ለማድረግ የተወጠነ እጅግ በጣም ፈጣን የትራንስፖርት አማራጭ ነው፡፡ የቴክኖሎጂው አይነት ለረዥም ጊዜ በተለያዩ የምርምር ሂደቶች ያለፈ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ከግልና መንግስታዊ ሙከራዎች ባለፈ ለንግድ የቀረበበት ሁኔታ የለም፡፡
የአሜሪካው ቨርጅን ሃይፐርሉፕ ለመጀመሪያ ጊዜ ቴክኖሎጂውን በሰዎች ላይ የሞከር ድርጅት ሲሆን ምስረታውን ካደረገበት 2014 እንስቶ የተለያዩ ሙከራዎችን በቴክኖሎጂው ዙሪያ ሲያደርግ የቆየ ነው፡፡ ሙከራው ከላስ ቬጋስ ወጣ ባለ የበረሃ ቦታ የተካሄደ ሲሆን ኩባንያው በሰራው 500 ሜትር በሚጠጋ እንደሃዲድ በሚዘረጋ የቫኪዩም ትዩብ እና የመንገደኞች ፖድ አማካኝነት የተከናወነ ነው፡፡ የቫኪዩም ትዩብ አገልግሎት እንደባቡር ሃዲድ እጅግ በፍጥነት የሚጓዘውን የመንገደኞች መያዣ ፖድ የማሳለጥ ስራ ሲሆን ሌሎች የኤሌክትሪክ ማራዘሚያ መሳሪየዎች እና ኤሌክትሮ ማግኔቲክ መወጣጫዎች የቴክኖሎጂው ተጨማሪ አካላት ናቸው ፡፡
በትራንስፖርት ኢንዱስትሪው በጣም ፈጣን ከሚባሉት የኤሌክትሪክ ባቡሮችና በራሪ አውሮፕላኖች በላይ እጅግ ፈጣን ወይም (ultra-fast speeds) የሚባልለት እና ለዘላቂ የአካባቢ ጥበቃ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚኖረው የሃይፐርሉፕ ቴክኖሎጂ ጥንስሱ ከዛሬ 90 አመት በፊት ቢሆንም መንገደኞቹን ይዞ የመጀመሪያው ሙከራውን ያደረገው በፈረንጆቹ 2020 ነው፡፡ ኩባንያው ቴክኖሎጂውን ለመሰራት በሚጀመርብት ግዜ 600 ማይልስ በሰዓት ሊጓዝ የሚችል ሃይፐርሉፕ ለመስራት ያለመ ሲሆን ይህም ከኒው ዮርክ ከተማ እስከ ዋሽንግተን ዲስ ያለውን ርቀት በ30 ደቂቃ የሚያጠናቅቅ ነው፡፡ የቨርጅን ግሩፕ ዋና መሰራች ሪቻርድ ብራንሰን ስለቴክኖሎጂውና ስለተሳካው ሙከራ እንደሚናገሩት በመጪዎቹ ጊዚያት የሰዎችን አጠቃላይ ህይወት መቀየር የሚያስችል ኢኖቬሽን ከመሆኑም በላይ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ትልቅ የመሰርት ድንጋይ የሚያስቀምጥ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ቨርጅን ግሩፕ ቴክኖሎጂውን በመንገደኞች ላይ የሞከረ የመጀመሪው ድርጅት ቢሆንም በሃይፐርሉፕ ዘርፍ ላይ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን የሚያደርጉ የተለያዩ ኩበንያዎች አሉ፡፡ ለአብነት በሎስ አንጀለስ መቀመጫውን ያደረገው ሃይፐርሉፕ የትራንስፖርት ቴክኖሎጂ በተባበሩት የአረብ ኢሜሬትስ፣ በፈረንሳይ እና በጀርመን የተለያዩ የሙከራ ፕሮጀክቶችን በመካሄድ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ እንደአውሮፓውያኑ በ2022 የመጀመሪያውን የንግድ ሃይፐርሉፕ ትራንስፖርት ለማቅረብም በዝግጅት ላይ ነው፡፡
ይህ የትራንስፖርት ቴክኖሎጂ ከደህንነትና ከፍጥነት አንጻር እጅግ የላቀ ቢሆንም ከሚፈልገው የወጪ ምጣኔ አኳያ እና ከሚወስደው የመንገድ መሰረተ ልማት አኳያ በቀላሉ ለመተግበር የሚያስቸግር ቴከኖሎጂ መሆኑን ብዙዎች ይገልፃሉ፡፡ ምንጭ፡ Big Think
ሮቦቶች የወደፊት የህንጻ ምህንድስና ተስፋ
-----------------------------------------
ከዚህ በፊት በተለያዩ የሳይንስ ልቦለድ ፊልሞች ላይ የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዲሰጡ ተደርገው በምናብ የተሳሉና ወደ ምስል የተለወጡ ልዩ ልዩ ፈጠራዎችን ተመልክተናል፡፡ ከእነዚህ መካከል በስታር ዋርስ ፊልም ላይና በሌሎች ሳይንስ ልቦለግ ዘውግ ባላቸው ፊልሞች አንድ ምናባዊ ፈጠራ ራሱን በመቀያየር እንደ ሰው ሲራመድ እንደ መኪና ሲሽከረከር እና ወደ ጦር መሳሪያነት ሲለወጥ ተመልክተናል፡፡
በሳይንስ ልቦለድ ፊልሞች የምንመለከታቸው ልዩ ልዩ ምናባዊ ፈጠራዎች የነገው እውናዊ አለም ፈጠራ መሰረቶች እንደሆኑ ያታመናል፡፡ በዚህ ዘገባችንም ራሳቸውን ወደ ድልድይ፣ ህንጻዎችና መኪናዎች በመለዋወጥ በተግባረ ብዙነት የህንጻ ምህንድስና ተስፋ ይሆናሉ ስለተባሉት ሮቦቶች ከthe next web ያገኘነውን መረጃ ልናካፍላችሁ ወደናል፡፡
በ MIT እና በUS ጦር የሚገኙ ተመራማሪዎች ማንናውንም አይነት ተግባር መፈጸም የሚችሉ መካኒካል የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመስራት ላይ መሆናቸውን የዘገባ ምንጫችን መረጃ ያመለክታል፡፡ እንደ መረጃ ምንጫችን ከሆነ እየተሰራ ያለው ፈጠራ ወደምንፈልገው የህንጻ ቅርጽ ራሱን ማስተካከል የሚችል አገልግሎቱን ሲያጠናቅቅ ደግሞ ወዲያው ራሱን ወደሌላ አገልግሎት ሰጭ ቁስ ምሳሌ ጀልባ፣ ድልድይ ወይም ደግሞ መኪና መለወጥ የሚችልና በቀላሉ ተንቀሳቃሽ እንደሆነ ታውቋል፡፡
የተመራማሪዎቹ ቡድን በአነስተኛ ዋጋ ፈጣንና ተገጣጣሚ እንዲሁም ሰው ሰራሽ ክህሎትን የሚጠቀም የህንጻ ግንባታ ግብአት እንዲኖር እየሰራ ሲሆን በመነሻነት በተጨናነቀ አካባቢ አገልግሎት መስጠት የሚችል ድልድይ ለመስራት አስቦ ነበር ስራውን የጀመረው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ግን ምርምሩ ያሳየው ውጤት ለጦር ሀይሉ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ያለውን የግንባታ ዘርፍ ከፍ ወዳለ ደረጃ ሊያሳድገው ይችላል ተብሎ ታምኖበታል፡፡
ምንጭ The next web
ያለ ዕድሜ ማርጀት በሽታ መድሃኒት ፍቃድ አገኘ
======================
ያለ ዕድሜ ማርጀት በሽታ ወይም ፕሮጄሪያ የተጠቁ ህፃናትን ዕድሜ ማስረዘሙን ተከትሎ ባሳለፍነው አርብ ዞኬንቪ ለተሰኘው መድሃኒት ፍቃድ ተሰጥቶታል፡፡ መድሃኒቶቹን በየቀኑ ሁለት ጊዜ እንዲወስዱ የተደረጉ 62 ህፃናትን ተካፋይ የሆኑባቸው ሁለት ጥናቶች ያሳዩት ውጤት መድሃኒቱን ካልወሰዱ ሌሎች በተመሳሳይ ዕድሜ እና ሁኔታዎች ላይ ከሚገኙ ሌሎች ከዓለም ዙርያ የተውጣጡ 81 ህፃናት ጋራ እንዲነፃጸር ተደርጎ ነበር፡፡ ህፃናቱ ለ11 ዓመታት ያህል ክትትል የተደረገባቸው ሲሆን በመጨረሻ ውጤቱም መድሃኒቱን በተከታታይ የወሰዱት ህፃናት ዕድሜ በሁለት ዓመት ተኩል እንደጨመረ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ይህን ተከትሎ ነው ታድያ የአሜሪካ የምግብ እና መድሃኒት አስተዳደር (FDA) መድሃኒቶቹ ለፕሮጄሪያ እና ተያያዥ የጤና ጉዳዮች ይውል ዘንድ ፈቃድ የሰጠው፡፡
ህክምናው ላይ ሲደረግ የነበረው ጥናት በዋናነት በፕሮጄሪያ ጥናት ፋውንዴሽን ድጋፍ እና መድሃኒት አበልፃጊው ኢገር ባዮፋርማቱቲካልስ አማካኝነት የተከናወነ ነበር፡፡ ህክምናው አስቀድሞ ከደረሳቸው ዕድለኛ የበሽታው ተጠቂዎች መካከል የሆነችው ሜጋን ዋልድሮን ማደግ እና ክብደቷም መጨመር አቁሞ እንዲሁም ፀጉሯ እየረገፈ ነበር፡፡ መድሃኒቱን ከ2 ዓመት ዕድሜዋ አንስቶ መከታተል ስትጀምር ግን ወዲያው ውጤቱ መታየት እንደጀመረ ትናገራለች፡፡ አሁን ላይ በ19 ዓመት ዕድሜዋ ላይ የምትገኘው ሜጋን ቁመቷ 3.6 ሜትር ላይ ሲገኝ በኦክስጅን የበለጸገ ደም የሚያመላልሱት የደም ስሮቿም እየጠነከሩ መጥተዋል፡፡ አሁን ላይ ያ በህይወቷ ጅማሮ ላይ ገጥሟት የነበረው ችግር አልፎ የመሰናዶ ትምህርቷን ለመጨረስ እና የሀገር አቋራጭ ሩጫ ላይ ለመሳተፍ ሁሉ በቅታለች፡፡ መድሃኒቱን ሲወስዱ ከነበሩት ሌሎች የበሽታው ተጠቂዎች መካከል ዕድሜያቸው እስከ 24 ዓመት ድረስ የደረሱም ይገኙበታል፡፡
በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ በብቸኝነት በዘረ መል ለዉጥ ምክንያት ሊመጡ የሚችሉ የጤና እክሎችን በሚመረምረው MRC-ET አድቫንስድ ላብራቶሪ ዳይሬክትር እና ተመራማሪ ዶ/ር ዘዉዱ ተረፈወርቅ ጋራ በነበረን ቆይታ በሽታውን “በዘረመል ለዉጥ (ጄኔቲክ ሚቹዌሽን) ምክንያት ከሚመጡ በሽታዎች” ውስጥ አንዱ እንደሆነ ሲነግሩን ቅድመ እርጅና ወይም ጊዜዉን ያልጠበቀ የእርጅና መከሰት ተብሎ ሊገለጽ የሚችለው በሽታው “ዲ.ኤን.ኤ ወይም ዘረ-መል ላይ በሚከሰት የአጋጣሚ ለዉጥ ምክንያት ሊመጣ የሚችል የጤና ጠንቅ ነዉ” መሆኑን ገልፀውልን ነበር፡፡
ፕሮጄሪያ ያለባቸው ህፃናት ብዙውን ጊዜ በታዳጊነት ዕሜያቸው ጅማሮ ላይ ህይወታቸውን ያጣሉ፡፡ ተላላፊ ያልሆነው በሽታው የዕድገት መገታት፣ የመገጣጠሚያዎች መጠንከር፣ ፀጉር መርገፍ እና ቆዳን የአዛውንትነት ገፅታ መያዝን ያመጣል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በዓለም ዙርያ አራት መቶ የሚሆኑ ሰዎችን ብቻ አጥቅቶ የሚገኘው ፕሮጄሪያ የዚህ ህክምና ሙከራ ከመጀመሩ በፊት የሀኪሞች እርዳታ ምልክቶቹን ለመቀነስ በመጣር ላይ ብቻ የተገደበ ነበረ፡፡
መሰረቱን በሀገረ አሜሪካን ካሊፎርኒያ ግዛት ያደረገው ኢገር የዞኪንቪ መድሃኒትን ዋጋ እስካሁን ይፋ አላደረገም፡፡ ሆኖም በሽታው ተጠቂዎች ቁጥር በጣም አነስተኛ ከመሆኑ ጋራ ተያይዞ ውድ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
ምንጭ፡ Medical Xpress እና ለዶ/ር ዘዉዱ ተረፈወርቅ የተደረገ ቃለ-መጠይቅ
ከ5 ቢሊዮን ኪሎ ሜትር ጉዞ በኋላ የአስትሮይድ ናሙና እየተጠበቀ ነው
*************************************
ከስድስት ዓመት የህዋ ላይ ቆይታ በኋላ የጃፓን የህዋ ምርምር ተቋም ንብረት የሆነችው Hayabusa2 ሳተላይት ወደ መሬት እየተመለሰች እንደሆነ ተሰማ፡፡ ከህዋ ወደ መሬት 5 ቢሊዮን ኪሎሜትሮችን አቋርጣ የፊታችን ታህሳስ ስድስት 2020 በበረሀማው የደቡብ አውስትራሊያ ክፍል በምትገኘው ዉሜራ ከተማ የምትጠበቀው ሳተላይት በትንሹ 100 ሚሊግራም ክብደት ያለው የ asteroid Ryugu ናሙና ይዛ እንደምትመጣ ተነግሯል፡፡
በበረሀማዋ ከተማ ይወድቃል ተብሎ የሚጠበቀው የሳተላይቷ ክፍል በህዋ ምርምር ውስጥ ከፍተኛ ጥቅም ያለው ውጤት ሆኖ እንደሚመዘገብ ይጠብቃል፡፡ ለዚህም አጠቃላ ጉዞው 5.24 ቢሊዮን ኪሎሜትሮችን መሸፈኑ እንደ ማሳያነት ተጠቅሷል፡፡ ይህ Ryugu እየተባለ የሚጠራው አስትሮይድ ከዚህ በፊት 1999 JU3 ይባል የነበረ ሲሆን በፀሐይ ዙሪያ ባለ የመሬት ምህዋር ውስጥ ባለ እንቁላል ቅርጽ (elliptical) ምህዋር ላይ ይገኛል፡፡
የሳተላይቷ ጉዞ ሲታቀድ ወደፊት አስትሮይዱ የት ሊገኝ እንደሚችል በማስላትና የመሬት ስበትን በመጠቀም የሳተላይት የጉዞ መስመርንና ፍጥነትን ልክን ማስተካከል ትልቅ ስራ ነበር፡፡ ከዚያም ከአስትሮይዱ ጋር ናሙና መውሰድ በሚያስችል መልኩ ሁለት ጊዜ በመጋጨት ሳተላይቷ ወደመሬት እንድትመለስ የታሰበ ነበር፡፡ አሁን ሁሉም ነገር በታቀደው መሰረት እየሔደ ያለ ይመስላል፡፡ ለዚህም ነው የናሙና ሰብሳቢ ቡድኑ ቀደም ብሎ በአውስትራሊያዋ ዉማሬ የከተመው፡፡
ከህዋ ወደመሬት የሚደረግ የጭነት ጉዞ እንደ ቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የአስትሮይድ ናሙና ወደመሬት ለማምጣት በተደረገ ሙከራ የተሳካ የሚባለው በ2010 የ JAXAው ወደ Itokawa አስትሮይድ የተደረገው ሲሆን ይህም ሙሉ ለሙሉ ያልተሳካ እና በጣም ጥቂት የሆነ በማይክሮ ግራም የሚለካ ናሙና የተገኘበት ነው፡፡ ለዚህም ምክንያቱ የናሙና መያዣው እቃ በመውደቁ ነበር፡፡ ከዚህ ጋር ሲነጻጸር 100 ሚሊግራም እጅግ ትልቅ ናሙና ነው፡፡
ተመራማሪዎች በሚመጣው ናሙና ሰፊ የሆኑ ምርምሮችን ለመስራት አቅደዋል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ Ryugu የተሰኘው አስትሮይድ በስርዓተ ፀሐይ ውስጥ ያልተበረዙና በመጀመሪያ ተፈጥሯቸው ያሉ ማእድናትን ይዟል ተብሎ ስለሚታሰብ ነው፡፡ አስትሮይዱም ከ4.5 ቢሊዮን ዓመታት በፊት እንደተፈጠረ ይገመታል፡፡
ከአስትሮይዱ በተወሰደ ናሙና ተመራማሪዎች የጥንቱን ስርዓተ ፀሐይ ብሎም የአለታማ ፕላኔቶችን አፈጣጠርና ዝግመተ ለውጥ ለመመርመር አስበዋል፡፡ የምርምር ተቋሙ ከዚህ በኋላ በ2026 በ2031 ወደ ሌሎች አስትሮይዶች ጉዞ ለማድረግ እቅድ እንዳለው አሳውቋል፡፡
ምንጭ Science Alert
ቀኑ የከፋበት በጎ ሰው
-------------------
ለበጎ አድራጎት ስራ ወደ ህንድ ያቀና አንድ ብሪታንያዊ በወባ፣ ዳንጊ ትኩሳት፣ እና ኮቪድ-19 መጠቃቱ አልበቃ ብሎ መርዛማ በሆነ የኮብራ ዕባብ ተነድፎ ከፍተኛ የጤና እክል ውስጥ ይገኛል፡፡ እነዚህ ሁሉ አደገኛ በሽታዎች ያጋጠሙት ኢያን ጆንስ የተባለው ይህ ግለሰብ በምዕራባዊው የህንድ ክፍል በምትገኘው ራጃስታን ግዛት ውስጥ ባለች አንዲት መንደር ውስጥ ነው እጅግ አደገኛ በሚባል እባብ ለመነደፍ የበቃው፡፡ ምንም እንኳን ግለሰቡ ከተነደፈ በኋላም በህይወት መትረፍ ቢችልም አሁን ላይ ግን ማየት እንደተሳነው እና እግሮቹም ፓራላይዝድ መሆናቸው ተዘግቧል፡፡
ከደቡባዊ እንግሊዝ አይል ኦፍ ዌይት ደሴት የመጣው ግለሰቡ ለሁለት ሳምንታት ያህል በከፍተኛ ክትትል ውስጥ የቆየ ሲሆን አሁን ግን በህንድ የኮሮና ቫይረስ ታማሚዎች መብዛትን ተከትሎ ባጋጠመው የአልጋ ማነስ ሳብያ ሆስፒታሉን ሊለቅ ተገዷል፡፡ አያን ጆንስ በሁኔታው ከፍተኛ ፍርሀት ያደረበት ቢሆንም ሀኪሞቹ ሙሉ በሙሉ መዳን እንደሚችል ተስፋ አድርገዋል፡፡ “አባቴ ብርቱ ነው፤ በህንድ ቆይታው ከኮቪድ 19 በፊትም በወባ እና አደገኛ ትኩሳት ተይዞ ነበር” ሲል ልጁ ሰብ ጆንስ እነዚህ የጤና እክሎችን ተከትሎ ከሀገር እንዳይወጣ ያገደው ከፍተኛ የህክምና እዳን በመክፈል ዳግም ወደ እንግሊዝ ለመመለስ በተጀመረው የጎ ፈንድ ሚ እንቅስቃሴ ላይ ተናግሯል፡፡ እነዚህን በሽታዎች እየታገለ ሳለ ለህይወቱ አስጊ በሆነ ሁኔታ በእባብ መነደፉን ሲሰሙ ማመን እንዳቃታቸውም ጨምሮ ተናግሯል፡፡
ቀድሞ የጤና ባለሙያ የነበረው ኢያን ጆንስ በፈራጃስታን ግዛት ውስጥ ያሉ የእደ-ጥበብ ባለሙያዎች የእጅ ስራ ውጤታቸውን ወደ እንግሊዝ እንዲልኩ በማድረግ ከድህነት የማላቀቅ ስራዎችን በሚሰራ የበጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ እየሰራ ይገኛል፡፡ ወረርሺኙ በተከሰተ ጊዜ ተቋሙ በሚሰራበት አካባቢ ያለውን ማህበረሰብ እንዲረዳ ተመርጦ እዚያው በህንድ ውስጥ እንዲቆይ ተደርጓል፡፡
ህንድ በዓለማችን ቀዳሚዋ ሰዎች በአደገኛ እባቦች የሚነደፉባት ሀገር ስትሆን በየአመቱ በአማካኝ 58 ሺህ ዜጎቿ በአደገኛ እባቦች ምክንያት እንደሚሞቱባት የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም ከ9 ሚሊዮን በላይ በኮቪድ-19 የተያዙ ተጠቂዎችን በማስመዝገብ ከአሜሪካ ቀጥላ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ህንድ 134,218 ዜጎቿን በቫይረሱ አጥታለች፡፡
ምንጭ፡ RT
የፊዚክስ ቀዳማዊት እመቤት
*****************
በሳይንስ አለም ውስጥ ጥቂት የማይባሉ ስራቸው ታውቆ እነሱ ግን ያልታወቁና ያልተዘመረላቸው እንዳሉ በዙዎች ይስማማሉ፡፡ ከእነዚህ ካልተዘመረላቸው ከሳይንስ እንቁዎች መካከል በፊዚክስ ዘርፍ ቀዳማዊት እመቤት የሚል ቅጽል ስም የተሰጣት ቺን ሺንግ ዉ አንዷ ናት፡፡ የዚህች ልዩ ሴት ሳይንሳዊ ከፍታ ጉዞ መነሻው ጃንግሱ በተባለችው የቻና የወንዝ ዳር አካባቢ ነው፡፡ በ1936 የዶግትሬት ትምህርቷን ለመማር ወደ አሜሪካ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ መጣች፡፡ ዩኒቨርሲቲ በነበረችበት ወቀት ማንሃታን በመባል ለሚታወቀው ፕሮጀክት በጣም አስፈላጊ የሆነ ሙከራን በጨረር ልቀት (X-ray emissions) እና ዜኖን ጋዝ (xenon gas) ላይ ሰርታለች፡፡
ከጥቂት አመታት በኋላ በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ሳለች በፊዚክስ ዘርፍ አንቱታን ስገኘላትን ስራ ሰርታለች፡፡ ይህች እንቁ እንስት የኤንሪኮ ፈርሚን በእንቅስቃሴ ላይ ያሉ ቅንጣቶች (atoms) እየተረጋጉ በሚሄዱበት ቅጽበት እንዴት ጨረር እንደሚፈነጥቁ የሚገልጸውን የ radioactive beta decay እሳቤ ያረጋገጠችው ሲሆን ቆይታም አሻሽላዋለች፡፡
በ1956 ሌሎች ተመራማሪዎች እንስቷን በተመሳሳይነት ህግ (law of parity) መላምት ላ እንድታግዛቸው ጠይቀዋት ነበር፡፡ ህጉ የነገሮች የመስታዎት ምስል ቀኝና ግራ ከመለዋወጡ ውጭ ተመሳሳ መሆን አለበት የሚል ነው፡፡ ታዲያ ቺን ሺንግ ዉ መላምቱን በሙከራ በማረጋገጧ እገዛ የጠየቀው የምርምር ቡድን በ1957 በፊዚክስ ዘርፍ የኖቤል ሽልማት አግኝቷል፡፡ ይሁን እንጂ ለዚህ ሽልማት ያበቃችውን ቺን ሺንግ ዉን ዘንግቷታል፡፡
በዚህ ጉዳይ የሚገባትን ክብርም ሆነ ምስጋና አለማግኘቷ እንስቷን ወደኋላ አላስቀራትም፡፡ ምርምሮችን አጠናክራ የቀጠለችው ዉ የአሜሪካ የፊዚክስ ማህበረሰብና National Medal of Science recipient ለተባለ ተቋም የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዘዳንት መሆን ችላለች፡፡ በዚህም ምክንያት “First Lady of Physics” የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቷት ስራዋን ለረጅም ጊዜያት አከናውናለች፡፡
ምንጭ Discovery Magazine
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኮምዩኒኬሽን ሳተላይት ግንባታ ላይ እንዲሳተፍ የግል ዘርፉ ታጭቷል
========================
መንግስት ለኢትዮጵያ በታሪኳ የመጀመሪያ የሆነውንና እስከ 350 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚያስወጣ የሚጠበቀውን የኮምዩኒኬሽን ሳተላይት ከግል ዘርፉ ጋራ በትብብር ለመስራት እያጤነ ነው፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋራ ቆይታ አድርገው የነበሩት የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ይልማ መንግስት በመጪዎቹ ሶስት እና አራት ዓመታት ውስጥ የኮምዩኒኬሽን ሳተላይት ለመገንባት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ገልፀዋል፡፡ ለስራው ቅድመ መደላድል የሚፈጥሩ ስራዎች በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን የተናገሩት ዳይሬክተሩ የገንዘብ እጥረት ግን መንግስት የግል ዝርፉን ጨምሮ ወደተለያዩ አማራጮች እንዲያማትር ማስገደዱን አመላክተዋል፡፡ አክለውም የኮምዩኒኬሽን ሳተላይት ማምተቁ እንደ ሀገር ያሉ ክፍተቶችን ለመሸፈን እንደሚያስችልም ተገልፀዋል፡፡
ከዚህ ዕቅድ ባሻገር ኢትዮጵያ በቅርቡ 2ኛ ሳተላይቷን ወደ ህዋ ለማምጠቅ እየሰራች ትገኛለች፡፡ አዲስ የምትመጥቀው ሪሞት ሴንሲንግ ሳተላይት በአየር ሁኔታ እና ፀባይ ጋራ የተያያዙ መረጃዎችን በማቅረብ የሀገራችንን ግብርና፣ ደን ልማት እና ተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ እንደምታግዝ ይጠበቃል፡፡ ከሳምንታት በፊትም የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ይሽሩን አለማየሁ በቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት በመገኘት ስለ ሳተላይት እና የኢትዮጵያ ሳተላይት ፕሮግራም ዙርያ ባቀረቡት ገለፃ ታህሳስ 11 እንደምትመጥቅ በምትጠበቀው በዚህች አዲስ ሳተላይት ዙርያ ማብራራታቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በዚህ ማብራርያ ላይም አዲሷ ሳተላይት ከአንድ ዓመት የበለጠ የአገልግሎት ዘመን ይኖራታል ተብሎ እንደሚጠበቅ የተጠቀሰ ሲሆን በ512 ኪ.ሜ ከፍታ ላይ በመሽከርከር መረጃ የምታቀብል መሆኗ በዶ/ር ይሽሩን መነገሩ ታወሳል፡፡ ET-SMART-RSS የሚል ስያሜን ያገኘችው ሳተላይቷ መጠኗ አንድ ዓመት ቀድማት ወደ ህዋ ከተጓዘችው ETRSS-1 አንፃር አነስ ያለች ስትሆን በቻይናዋ ሃይናን ግዛት ውስጥ ካለው ዌንቻንግ የማምጠቂያ ማዕከል የምትመጥቅ መሆኑ በመድረኩ ተገልፆ ነበር፡፡
ኢትዮጵያ የኮምዩኒኬሽን ሳተላይት የሌላት በመሆኑ የተለያዩ ተቋማቶቿ ከውጭ ሀገራት ድርጅቶች ዘንድ የእነዚህን ሳተላይቶች ግልጋቶት እተከራዩ እንደሚጠቀሙ ይታወቃል፡፡ ኢትዮ-ቴሌኮም እንኳን ብቻውን በዓመት እስከ 12 ሚሊዮን ዶላር ድረስ ለኮምዩኒኬሽን ሳተላይት ኪራይ እንደሚያወጣ ሲዘገብ የሚዲያ አካላት፣ መከላከያ እና ሌሎች የግል እና መንግስታዊ ተቋማትም በየፊናቸው እነዚህን ሳተላይቶች ለመከራት ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ላይ ናቸው፡፡
በፋይናንስ ረገድ እንደሚሆን ከተቀመጠው ድርሻ ባሻገር የግል ዘርፉ ኢትዮጵያ ለማምጠቅ ባሰበቻት በዚህች የኮምዩኒኬሽን ሳተላይት ላይ ምን ምን አስተዋፅዖ እንደሚኖረው በዝርዝር አልተቀመጠም፡፡
ምንጭ፡ The Reporter
የበረሃ አንበጣን በምስራቅ አፍሪካ አስከወዲያኛው ለመከላከል የሚያግዘው አዲሱ ሞዴል
-----------------------------------------------
ብዙዎቹ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በተለይም ኢትዮጵያ፣ ኬኒያ እና ደቡብ ሱዳን በ70 አመት ውስጥ እጅግ ከባድ የተባለለትን የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝ በመፋለም ለይ ይገኛሉ፡፡ ይህ መንጋ በአካባቢው ላይ በሚያደረገው እንቅስቃሴ በዙ ሄክታር የሚሸፍኑ የእርሻ ሰብሎችን በአንዴ ድምጥማጡን በማጥፋት የምግብ ዋስትና ፈተናን እየደቀነ ያለ እና በሃገር ኢኮኖሚ ላይም ከባድ ጥፋት እያስከተለ የሚገኝ ነው፡፡ የአለም ባንክ በቅርቡ ይፋ ባደረገው መረጃ በእነዚህ አካባቢዎች የተከሰተው የበረሃ አንበጣ እስከ 2020 መጠናቀቂያ 8.5 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ጥፈት ሊያስከትል እንደሚችል ግምቱን አስቀምጧል፡፡
እነዚህ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት መንጋው በተስፋፋባቸው አካባቢዎች የኬሚካል እርጭት በማድረግ እና ሌሎች የመከላከያ መንገዶችን በመጠቀም ወረርሽኙን ለማስወገድ ጥረት እያደረጉ ቢሆንም የመንጋው ደረጃ በከፍተኛ የመራባት አቅም ላይ የሚገኝ በመሆኑ ከእርምጃው በላይ እየደረሰ ያለው ውድመት እጅግ ከባድ ሊሆን ችሏል፡፡ በዚህ ዘርፍ ላይ ለረዥም ጊዚያት ምርምር ሲያደርጉ የቆዩ ተመራማሪዎች የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የበረሃ አንበጣ ጉዳትን ከመነሻው ለመሳጠር አንዲችሉ የማሽን ለርኒንግ አልጎሪዝም የተከተለ አዲስ ሞዴል ይፋ አድርገዋል፡፡
በአለም አቀፍ የነፍሳት ፊዚዮሎጂ እና ኢኮሎጂ ማዕከል (ICIPE) የሚሰሩ ተመራማሪዎች ከሰሞኑ ይፋ እንዳደረጉት የበረሃ አንበጣ የመራቢያ ቦታዎችን በትክክል በመለየት ወረርሽኙ የሚያስከትውን ከፍተኛ አደጋ ከወዲሁ ማስቀርት እንደሚቻል በጥናታቸው ይገልፃሉ፡፡ ተመራማሪዎቹ እንደሚያስረዱት በምስራቅ አፍሪካ አከባቢ ያለው የመረጃ አያያዝ እጅግ ደካማ በመሆኑ የበረሃ አንበጣ መራቢያ ቦታዎችን በትክክል ለማወቅ እጅግ አስቸጋሪ ቢያደርገውም በተገበሩት የማሽን ለርኒንግ አልጎሪዝም አማካኝነት እምቅ አቅም ያላቸው የመራቢያ ቦታዎችን ለመገመት የሚያስችል ሞዴል አበልፅገዋል፡፡
ተመራማሪዎች የተገበሩት ይህ አዲስ ሞዴል በአለም አቀፍ ደረጃ ከዚህ በፊት በተመዘገቡ 9,134 በሚጠጉ የአንበጣው መራቢያ ቦታዎች በመተንተን የተከናወነ ሲሆን እምቅ አቅም ያላቸው የመራቢያ ቦታዎችን በትክክል ለመተንበይ የሚያስችልም የማሽን ለርኒንግ አልጎሪዝም በምርምሩ ላይ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ ይህ አልጎሪዝም በምስራቅ አፍሪካ ሊኖር የሚችለውን የአንበጣ መራቢያ ቦታ በትክክል ለመገመት የሚችለው የባዮ-ክላይሜቲክ ማለትም (የሙቀት እና የዝናብ መጠን) ተፅዕኖችን በመተንተን ሲሆን ከዛ በተጨማሪም የedaphic ወይም የአሸዋ እና እርጥበት ይዘቶች የሚያስከትሉትን ትፅእኖም በጋራ ይመለከታል፡፡ እነዚህ የአየር ንብረት ተፅእኖዎች እና የአፈሩ ባህሪዎች የበረሃ አንበጣው ለሚጥለው አንቁላልቅና ከዚህ ሂደት በኋላ ለሚኖረው የእንቁላል መፈልፈል ትልቅ ሚና እንደሚኖራቸው ተመራማሪዎች ያስረዳሉ፡፡

ከዚህ በፊት የተመዘገቡት አብዛኛቹ የመራቢያ ቦታዎች እንደሚያሳዩት ብዙዎች የመራቢያ አከባቢዎች ከ40 እስከ 80 ሚሊዮን የበረሃ አንበጣዎችን በአንድ ስኬር ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ ይዘው ሊቀመጡ ይችላሉ፡፡ ታዲያ እነዚህ ቦታዎች ከፍተኛ የበረሃ አንበጣ መፈልፈያ አካባቢዎች በመሆናቸው የክትትል አቅምን በማሳደግ በአጭር ጊዜ፣ በትንሽ ወጪ እና አከባቢን በማይጎዳ መልኩ የበረሃ አንበጣውን እስከወዲያኘው ማስወገድ የሚቻልበት መንገድ ነው፡፡
ተመራመሪዎች የተገበሩት አዲሱ ሞዴል የማሽን ለርኒንግ አልጎሪዝምን በመተግብር እምቅ አቅም ያላቸው የመራቢያ ቦታዎችን የሚለይ እና እሱንም በካርታ መልክ የሚያስቀምጥ በመሆኑ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የሚከሰተውን የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝ በቀላሉ ለመከላከል እና ውድመቱ ከፍተኛ ደረጃ ሳይደረስ ከመነሻው ለማቆም በእጅጉ የሚያግዝ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በነበሩ ሙከራዎች እና የትብብር ስራዎች የበረሃ አንበጣ ወደ ምስራቅ አፍሪካ በሚገባባቸው አካባቢዎች እና በሚፈለፈልባቸው ቦታዎች የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራዎች የሚከናወኑ ቢሆንም የመራቢያ ቦታዎችን በትክክል ተገንዝቦ መፍትሄ የሚጠቁም ባለመኖሩ፤ የማዕከሉ የምርምር ውጤት ከዚህ ቀደም ከነበሩት በተሻለ ሁኔታ ጉዳቱን ለመቀነስ ትልቅ እገዛ ያደርጋል፡፡
ይህ ምርምር በሞዴሉ አማካኝነት የለያቸው የምስራቅ አፍሪካ የበረሃ አንበጣ መራቢያ ቦታዎች ኬኒያ ኡጋንዳ እና ደቡብ ሱዳን ቢሆኑም በውስጣቸው የሚገኙ አያሌ የሰፈር ቦታዎች በካርታው ተገልፀው የሚገኙ ናቸው፡፡ እንደካርታው ማብራሪያ ከሆነ የኬኒያ እና የሱዳን ሰፊ ቦታዎች ዋና የመራቢያ አካባቢዎች ተደርገው የተቀመጡ ሲሆን ከዛ ባለፈም የኡጋንዳ ሰሜን ምስራቅ አካባቢዎች እና የደቡብ ሱዳን ሰሜናዊ ክልሎች የበረሃ አንበጣው ዋና የመራቢያ ቦታዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ተጠቁሟል፡፡
በናይሮቢ መቀመጫውን ያደረገው ይህ የምርምር ማዕከል በምክረ ሃሳብ ደረጃ በሚያስቀመጣቸው ቀጣይ እርምጃዎች መሰረት እና ከማዕከሉ ጋር በሚኖር ግንኙነት ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ የሚገኘውን የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝ እስከወዲያኘው ለመከላከል በንቃት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ እና የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትም በዚህ የአሰራር ሞዴል በመታቀፍ በትብብር እንዲሱሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ምንጭ፡ International Centre of Insect Physiology and Ecology (icipe) እና theconversation