TechIn2
1.22K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
የመጀመሪያው ሳይንቲስት
************************
ሳይንቲስት የሚለው ቃል በእንግሊዝኛ ቋንቋ መዝገበ ቃላት የተካተተው በ1834 ነው፡፡ ይኸውም የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ፈላስፋና የታሪክ ምሁር William Whewell ቃሉን አንድን የተፈጥሮን ባህሪና ውቅር በምልከታና በሙከራ የሚያጠናን አካል ለመግለጽ ከተጠቀመበት ወዲህ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የተለያዩ ክርክሮች ሊነሱ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ እንደ ቻርለስ ዳርዊንና ሚካኤል ፋራዳይ ያሉትን በዊሊያም ዌልስ ዘመን የነበሩትን ልዩ የሳይንስ ሰዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ምንም እንኳን ሳይንቲስት የሚለው ቃል ከ1830 በፊት ባይኖርም የቃሉን መገለጫዎች ግን የሚተገብሩ ሰዎች መኖራቸውን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡
የመጀመሪውን ሳይንቲስት ለማወቅ ወደኋላ እጅግ ርቀን መጓዝ ይኖርብናል፡፡ ይህም ሲባል ወደ ጥንታዊው የግሪክ ስልጣኔ መጀመሪያ ወደ 624 እስከ 545 ከልደተ ክርስቶስ በፊት የማልተሱ ታለስ ዘመን ማለት ነው፡፡ ምንም እንኳን የተመዘገቡ በቂ መረጃዎች ባኖሩም ታለስ በሳይንስና በሒሳብ ዘርፍ ብዙ ግኝቶችን እንዳገኘ ይታመናል፡፡
ሌላም የጥንት ግሪካዊን በዚህ ዙሪያ ማሳታወስ ተገቢ ነው፡፡ በዚህም የጆሜትሪ አባት እየተባለ የሚታወቀውን Euclid እንዲሁም Ptolemy (በጥሊሞስ) የሚባለውን በተሳሳተ አረዳድ መሬት የስርአተ አለም ማእከላዊናት ያለውን የስነፈለክ ሰው መጥቀስ ይቻላል፡፡ ምንም እንኳን እነዚህ ሰዎች ባለምጡቅ እሳቤ ቢሆኑም ሀሳባቸውን ግን ለማረጋገጥ የሄዱበት መንገድ የለም፡፡
አንዳንድ ተመራማሪዎች የዘመናዊ ሳንስ መሰረት ከአውሮፓውን ስልጣኔ በፊት በመካከለኛው ምስራቅ ይሰሩ የነበሩ አረብ ፈላስፎችና የሒሳብ ሊቆች እንደነበሩ ያምናሉ፡፡ በዚህም እንደ al-Khwarizmi, Ibn Sina, al-Biruni and Ibn al-Haytham ያሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ብዙ የዚህ ዘርፍ ተመራማሪዎች በአሁኗ ኢራቅ ከ965 እስከ 1039 የነበረው Ibn al-Haytham የመጀመሪያው ሳይንቲስት እንደሆ ይስማማሉ፡፡ ይህም ሰው ፒነሆል ካሜራን የፈለሰፈ፣ የጽብረቃን ህግ ያጠና እንዲሁም የተለያዩ እንደ ቀስተ ደመና እና ግርዶሽ ያሉ ተፈጥሯዊ ጉዳዮች ላይ ምርምር ያደረገ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ከነ መላጥዮስና በጥሊሞስ የተለየ አካሔድ የተከተለ መሆንና አለመሆኑን ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡
እንደ ጸሀፊው ብሬን ሴልጅ አንድ ዘመናዊ ሳይንቲስት የሙከራን ጥቅም በደንብ የለየ፣ ሒሳብን እንደ መሰረታዊ መሳሪያ የሚጠቀምና መረጃን በፍትሀዊ መንገድ የሚጠቀም መሆን አለበት፡፡ በሌላ አገላለጽ ሳይንቲስት ለመባል በሳይንሳዊ ስራው ላይ ምንም አይነት ሐይማኖታዊ እሳቤን የማይከተል መሆን አለበት፡፡ በዚህ ረገድ በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩት እነ ክርስቲያን ሁይገንስ፣ ሮበርት ሁክ እና አይዛክ ኒውተን አብዛኛውን የሳይንቲስትን መገለጫ የሚያሟሉ ሆነው ይገኛሉ፡፡ ነገርግን ሙሉ የሳይንቲስት ባህሪያትን የሚያሟላ ለማግኘት የግድ ወደ 16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ መምጣት ይኖርብናል፡፡
በዚህ ረገድ ቀድሞ የሚነሳው ጋሊሊዮ ጋሊሊ ሲሆን ጆን ግሪቢን የተባለ ጸሀፊ በ2002 በወጣ "The Scientists" በተባለ መጽሀፉ ምንም እንኩዋን የሚገባውን ያክል እውቅናና ክብር ባይሰጠውም የመጀመሪያው ሳይንቲስት ዊሊያም ጊልበርት እንደሆነ ተናግሯል፡፡ በ1544 ተወልዶ በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ከ1558 እስከ 1569 ትምህርቱን ተከታትሏል፡፡ የመጀመሪያው ሳይንቲስት ያሰኘውም ስራዊ በማግኔት ተፈጥሮ ላይ የሰራው ስራ ነው፡፡ በእንግሊዝም ወሳኝ የሚባል የፊዚካል ሳይንስ መጽሀፍ "On the Magnet, Magnetic Bodies, and the Great Magnet of the Earth" በሚል ርእስ ታትሟል፡፡ ጊልበርት በመጽሀፉ መግቢያ ላይ ከሀሳብ በተጨማሪ የሳይንሳዊ ሙከራን አስፈላጊነት አብራርቶ ጽፏል፡፡
ጋሊሊዮ ጋሊሊም በዊሊያም ጊልበርት አስተሳሰብ ተጽእኖ ስር በመሆኑ የተለያዩ ሙከራዎችን እንዳደረገ ይታመናል፡፡
ምንጭ www.howstuffworks.com
የጆሮ ኩክ ስለ ጭንቀታችን ይናራል
አዲስ የጆሮ ኩክን መሰብሰብያና መተንተኛ መንገድ የጭንቀት ሆርሞን የሆነውን ኮርቲሶል በመመርመር በድባቴ እና ፍርሀት ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን የአዕምሮ ጤና ለመከታተል አዋጪው መንገድ ሊሆን እንደሚችል አዲስ ጥናት ጠቆመ፡፡ ኮርቲሶል አንድ ሰው በሚጨነቅበት ጊዜ የሚጨምር እና በተቀራኒው ጭንቀት ሲቀንስ የእርሱም መጠን የሚቀንስ ወሳኝ የሆርሞን አይነት ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ኮርቲሶል በድባቴ እና ፍርሀት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ላይ በተደጋጋሚ ከፍ የሚል ሲሆን በበሽታ መከላከል ስርዓታችን፣ ደም ግፊት እና ሌሎች የሰውነት ስራዎች ላይም አሉታዊ ውጤት ሊኖረው ይችላል፡፡
ከፍርሀት እና ድባቴ ባሻገርም ከተለመደው ውጪ የሆነ የኮርቲሶል መጠን ከሌሎች የጤና ችግሮች ጋራም ትስስር አለው፡፡ ከነዚህ መካከል ከመጠን ባለፈ የኮርቲሶል ምርት ምክንያት የሚከሰተው ካሺንግ እና በኮርቲሶል ምርት ከሚገባው በላይ ማነስ ምክንያት የሚከሰተው አዲሰን በሽታዎች ይጠቀሳሉ፡፡ በካሺንግ በሽታ የተጠቁ ሰዎች ከተለመደው የተለየ የስብ ክምችት የሚገኝባቸው ሲሆን በሽታን የመከላከል ስርዓታቸውም አቅሙ የወረደ እና አጥንታቸውም የሳሳ (brittle bone) ነው፡፡ በሌላ መልኩ በአዲሰን በሽታ የተጠቁት ደግሞ አደገኛ ሊባል በሚችል መጠን የደም ግፊታቸው የወረደ ነው፡፡
የኮርቲሶል መጠንን ለመለካት የተለያዩ መንገዶችን መጠቀም ይቻላል፤ የምራቅ፣ ደም እንዲሁም ፀጉር ናሙናዎች፡፡ ሆኖም ከደም እና ምራቅ ውስጥ የሚወሰደው ናሙና በአንድ የተወሰነ ጊዜ ውስጥ ብቻ ያለውን የኮርቲሶል መጠን የሚለካ ነው፤ ኮርቲሶል ደግሞ በቀን ውስጥ በተለያዩ ሁኔታዎች ከፍና ዝቅ ሊል ይችላል፡፡ ከፀጉር ላይ የሚወሰደውውም ከቀናት ይልቅ በወራት ውስጥ የታየውን የኮርቲሶል መጠን የሚያሳዩና ለመተንተንም ውድ ናቸው፡፡
በአንፃሩ የጆሮ ኩክ የተረጋጋና የባክቴሪያ ብክለትንም መቋቋም የሚችል በመሆኑ በቀላሉ ወደ ቤተ-ሙከራ በመውሰድ ትንተናን መስራት ያስችላል፡፡ በተጨማሪም ከሳምንት በላይ ላለ ጊዜ ያለውን የኮርቲሶል መጠን መዝግቦም ማስቀመጥ ይችላል፡፡ ሆኖም ቀድሞ ይህን የጆሮ ኩክ ለማውጣት ጥቅም ላይ ይውል የነበረው መንገድ የህክምና መርፌን ወደ ጆሮ በመክተት እና ወደ ውስጥ ከተከተተው ውሃ ጋራ አንድ ላይ አድርጎ መጦ በማውጣት ነበር፡፡ ይህም የተወሰነም ቢሆን ህመም ያለውና በራሱም ጭንቀትን የሚፈጥር ነበር፡፡ ይህን መንገድ በመቀየር ተመራማሪዎች ከኩክ ማውጫ ያልበለጠ ስሜት የሚፈጥር መጥረጊያ ወይም ስዋብ መስራት ችለዋል፡፡ በተጨማሪም ስዋቡ በመያዣው በኩል ጋሻ መሰል ነገር ያለው በመሆኑ ሰዎች ወደ ጆሮዋቸው ከሚፈለገው በላይ በጥልቀት ከተውት ታምቡራቸውን እንዳይጎዱ ይጠብቃቸዋል፡፡ ጫፉ ላይ ያለው ስፖንጅ ደግሞ ኮኩን ለመሰብሰብ ይችላል፡፡
አጥኒዎች ባከናወኑት አነስተኛ ጥናት በሁለት የተለያዩ ጊዜያት ከ37 ተሳታፊዎች ላይ የደም፣ ፀጉር እና የጆሮ ኩክ ናሙናዎችን ወስደው ነበር፡፡ በየእያንዳንዱ የስብሰባ ወቅት በአንዱ ጆሮ ያለውን ኩክ የህክም መርፌን በሌላው በኩል ያለውን ደግሞ ስዋቡን በመጠቀም ሰብስበዋል፡፡ በመቀጠልም በሁለቱ መካከል ያለውን የኮርቲሶል ልኬት መጠን አነፃፅረዋል፡፡
በውጤቱም ኮርቲሶል ከፀጉር ይልቅ በጆሮ ኩክ ውስጥ ይበልጥ እንደሚገኝና ለትንተናም ቀላል እንደሚሆን ማረጋገጥ ችለዋል፡፡ በስዋብ አማካኝነት የሚገኘውን ኮርቲሶልን መተንተንም ከህክምና መርፌው አንፃር ፈጣን እና አዋጭ እንደሆነ አረጋግጠዋል፡፡ በመጨረሻም የጆሮ ኩክ እንደ አልኮል ባሉ ነገሮች ሳብያ ተለዋዋጭነት ካላቸው ከሌሎቹ መንገዶች አንፃር በውስጡ በያዘው የኮርቲሶል መጠን የማይለዋወጥ እና የተረጋጋ ሆኖ አግኝተውታል፡፡ ተሳታፊዎቹም ከህክምና መርፌው ስዋቡ ምቾት እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል፡፡
ምንጭ፡ Live Science
የሳል ድምፅን በመስማት ብቻ ኮቪድ-19ን መለየት ተቻለ
==========================
ከወራት በፊት፤ ኮቪድን እንደአሁን ብዙም ሳናውቀው እና ሳንደፋፈረው ድንገት ሳል ያሳለን አልያም ሌላ ሰው ሲያስል የሰማን እንደሆን ኮቪድ-19 ነው? ወይስ አይደለም? የሚለው የጭንቀት ጥርጣሬ በብዙዎቻችን ዘንድ ነበር፡፡ ታድያ በአሜሪካኑ የማሳቹሴት ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ የሚገኙ የሳይንስ ተመራማሪዎች የዚህን ሳል ድምፅ በመስማት ብቻ ምንጩ ኮቪድ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ጥያቄ የሚመልስ አዲስ አልጎሪዝምን ሰርተዋል፡፡ ተመራማሪዎቹ በአሁኑ ሰዓት ይህን በሰው ሰራሽ አስተውሎት አማካኝነት የሚሰራ ምርምር ሙከራ እያደረጉበት ሲሆን በአሜሪካን የምግብ እና መድሃኒት አስተዳደር (FDA) ፍቃድ የማግኘት ሂደቱንም አስጀምረውታል፡፡
አልጎሪዝሙ ከዚህ ቀደም በተሰራው የሳንባ ምች፣ አስም እና አልዛይመርን እንዲለይ ተደርጎ በተሰራ ሞዴል ላይ መሰረቱን በማድረግ ነው፡፡ እኛ ሰው አቀላጥፎ መናገር ሲጀምር ብቻ የምንረዳቸውን ነገሮች ሰው ሰራሽ አስተውሎት ግን በሳል ብቻ ይረዳቸዋል ሲሉ የምርምር ቡድኑ አካል ብራያን ሰቢራና በዚህ ላይ በመመስረት ብቻ የሰውን ፆታ፣ አፍ መፍቻ ቋንቋ ወይም ስሜት መረዳት መቻሉን በምሳሌነት በመጥቀስ ያስረዳሉ፡፡
በመጀመሪያ ተመራማሪዎቹ የተለያዩ በጎ ፈቃደኛ ተሳታፊዎች የእጅ ስልክ እና ኮምፒውተራቸውን በመጠቀም የቀዱትን የሳል ድምፅ የሚልኩበት ድረ-ገፅ ፈጠሩ፤ በተጨማሪም የበሽታው ምልክት እያሳዩ እንደሆን መረጃ የሚወስድ መጠይቅ ለተሳታፊዎቹ አቅርበዋል፡፡ በድረ-ገፁ አማካኝነት ከ70 ሺህ በላይ ሰዎች በግድ የተሳሉ ሳሎችን ድምፅ መብሰብ ችለዋል፡፡ ከነዚህ ሰዎች ውስጥ 2,660ቱ የበሽታው ምልክት የሚታይባቸው እንዲሁም የማይታይ የኮቪድ-19 ራማሚዎች ናቸው፡፡ በመቀጠልም 4,256 ናሙናዎችን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ስርዓቱን ለማሰልጠን የተጠቀሙበት ሲሆን 1,064 ናሙናዎችን ደግሞ በጤነኛና በኮቪድ-19 በተጠቁ ሰዎች መካከል ያለውን ልዩነት ማሳየት ይችል እንደሆን ሞክረውበታል፡፡
በውጤቱ ስርዓቱ ከኮቪድ ጋራ ትሰስር ባላቸው አራት የሳል መሰረታዊ ገፅታዎች፤ ማለትም የጡንቻ መኮሰስ፣ የድምፅ አውታሮች መጠንከር፣ እንደ መሰላቸት እና እርግጠኛ አለመሆን ያሉ ስሜቶችን እንዲሁም የአተነፋፈስ እና ሳንባ ብቃት ላይ በመመስረት ልዩነቶችን ማስተዋል ችሏል፡፡ በዚህም መሰረት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ሞዴሉ 98.5 በመቶ የሚሆኑትን የኮቪድ-19 ተጠቂዎች በስኬት ማወቅ ሲችል ካልተያዙት ውስጥ ደግሞ 94.2 በመቶውን መለየት ችሏል፡፡ ስርአቱ ምንም አይነት የበሽታው ምልክት ከማይታይባቸው ውስጥ ደግሞ ኮቪድ-19 ያለባቸውን ሰዎች መቶ በመቶ መለየት ሲችል ከሌለባቸው ውስጥ ደግሞ 83.2 በመቶውን ለይቶ አውጥቷቸዋል፡፡
ይህ በተራማሪዎቹ ዘንድ እንደስኬት የሚታይ አስደሳች ውጤት ቢሆንም በተለያዩ የዕድሜና ዘር ቡድኖች ላይ ውጤታማ እንዲሆን ተጨማሪ ጥናት መደረግ እንዳለበት ከባለሙያዎች የተሰጠ አስተያየት ይጠቁማል፡፡
በአሁኑ ሰዓት የኮቪድ-19 ተጠቂዎችን በድምፅ የመለየቱን ስራ እየሞከረ ያለው ይህ ጥናት ብቻ አይደለም፤ ሌላ በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ እየተሰራ ያለ ጥናትም በተመሳሳይ መንገድ የቫይረሱ ተጠቂዎችን የሚለይ ስራን በመስራት ላይ ነው፡፡
ምንጭ፡ Live Science
ኮቪድን ተከትሎ በሳንባ ነቀርሳ የሚሞተው ሰው ብዛት በ400 ሺህ ሊጨምር ይችላል
ኮቪድ 19 በጤና ስርአቶቻችን ላይ በሚያደርሰው ጫና ሳብያ በሳንባ ነቀርሳ ወይም ቲቢ የሚሞተው ህዝብ ቁጥር በመቶ ሺዎች ሊያሻቅብ እንደሚችል የተለያዩ ተመራማሪዎች ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል፡፡ በብዙ ሀገራት ዶክተር እና ሌሎች የጤና ባለሙያዎች ሳንባ ነቀርሳ ላይ ይሰጡ የነበረው ህክምና አገልግሎት ወደ ኮቪድ-19 ተሻግሮ ይገኛል፡፡ ለዚህ ይውሉ የነበሩት በጀት እና የህክምና ቁሳቁሶችም እንዲሁ አዲሱን ወረርሺኝ ተከትለው የአገልግሎት ለውጥ ማድረጋቸውን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡ በዚህም ሳብያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የሳንባ ነቀርሳ ህክምና ክትትሎች እንደቀድሞው እንዳይደረጉ ስለተስተጓጎሉ በዚህ ዓመት ብቻ በበሽታው ሚሞተው ሰው ብዛት ቀድሞ በነበረበት ላይ ከ200 እስከ 400ሺህ የሟቾች ቁጥር ጭማሬ እንደሚያሳይ ተገልጿል፤ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታትም ይህ ችግር እንደሚቀጥል ታምኗል፡፡
የሳንባ ነቀርሳ ኤድስ እና ወባን ጭምር በመብለጥ ከማንኛውም በሽታ በላይ የሰው ልጆችን ህይወት በየዓመቱ የሚያረግፍ ነው፡፡ ተላላፊ በሽታው ማይክሮባክቴሪየም ቲዩበርክሎሲስ በተሰኘ ባክቴሪያ አማካኝነት ይከሰታል፡፡ ብዙውን ጊዜ ይህ ባክቴሪያ ሳንባን የሚያጠቃ ቢሆንም ከደም ዝውውር አንስቶ እስከ አንጎል ድረስ ያሉትን ማንኛውንም አካላት ሊጎዳ ይችላል፡፡
የሳንባ ነቀርሳ ለሺዎች ዓመታት ከሰው ልጆች ጋራ ኖሯል፡፡ በቅርብ ዘመናትም በዓለም ዙርያ በየዓመቱ 10 ሚሊዮን ሰዎችን ሲያጠቃ 1.5 ሚሊዮን የሚሆኑትንም ለህልፈት በመዳረግ ላይ ነው፡፡ ከሳንባ ነቀርሳ ለመዳን መድሃኒቱን ለስድስት ወር መውሰድ ያስፈልገዋል፡፡ ታድያ ከ5 ዓመታት በፊት አንስቶ የተደረጉ በሽታውን የመቆጣጠር እርምጃዎች በመጀመርያ ስኬታማ እየሆኑና የሟቾች ቁጥርም እያሽቆለቆለ የነበረ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የሞት ማሽቆልቆሉ መቀዛቀዝ ገጥሞታል፡፡ ለዚህ አንዱ ምክንያት ፀረ-ተህዋሲያንን መቋቋም የሚችል ሳንባ ነቀርሳ በተለይ በቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት አባል ሀገራት ውስጥ መስፋፋት ነው፡፡ የኮቪድ-19 መነሳት ደግሞ ነገሮችን ይባስ ወደ አስከፊ ደረጃ አሸጋግሯቸዋል፡፡ አዲሱን ወረርሺኝ ተከትሎ የጤና ባለሙያዎች እና የህክምና ቁሳቁሶች ላይ ለውጥ ከመምጣቱም ባሻገር አንዳንድ ሀገራት ለሳንባ ነቀርሳ ታማሚዎች የሚደረግ የህክምና ክትትልን እስከማቋረጥም ደርሰዋል፡፡
አዲሱን ወረርሺኝ ተከትለው በህክምና ስርዓቱ ላይ ለውጥ ከተደረገባቸው ውስጥ አንዱ የሳንባ ነቀርሳ ባለባቸው ሰዎች ውስጥ ያለውን ማይክሮባክቴሪየም ቲዩበርክሎሲስን በብቃት ሲለይ የቆየው GeneXpert የተባለ የመመርመሪያ መሳርያ ነው፡፡ መሳርያው ኮቪድ-19ኝንም በመመርመር ረገድ ያሳየው ውጤታማነት የአገልግሎት ለውጥ አድርጎ ከሳንባ ነቀርሳ ይልቅ አዲሱ ወረርሺኝን ለመመርመር እንዲውል ሆኗል፡፡
እንደ አለም ጤና ድርጅት ትንበያ ከሆነ የሳንባ ነቀርሳ እስከ አውሮፓውያኑ 2025 ድረስ ባሉት ዓመታት ውስጥ አዲስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በየዓመቱ በ1 ሚሊዮን የሚያድግ ሲሆን በገፍ የሚጨምረው የዚህ የአዳዲስ ተጠቂዎች ቁጥርን ተከትሎ የሚመጣው የስራ ፈቶች ብዛት ብዙ ቤተሰቦችን ለአስከፊ የኑሮ ምስቅልቅል ሊዳርግ ይችላል፡፡
ምንጭ፡ The Guardian
ከናይለን ጨርቅ የተሰሩ ልብሶች የወደፊት የሀይል ምንጮች
**********************************************************
ተመራማሪዎች ከናይለን ልብስ የኤሌክትሪክ ሀይል ማግኘት የሚቻልበትን መንገድ ማግኘታቸውን ቴክኖሎጂ ዶት ኦርግ ባዝ ዩኒቨርሲቲን ጠቅሶ ዘገበ፡፡ ዘገባው እንዳመለከተው ከናይለን የተሰራው ልብስ የሰውነታችንን እንቅስቃሴ በመጠቀም የኤሌክትሪክ ሀይል በማመንጨት የውጫዊ ሀይል ሳይጠቀም የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን ሀይል መሙላት ያስችላል፡፡
ጥናቱ የባንዝ ዩኒቨርሲቲ፣ እና በጀርመን የፖሊመር ምርምር ተቋም እና የፖርቹጋል ኮይምብራ ዩኒቨርሲቲ ጥምረት የተሰራ ነው፡፡ በዚህም Piezoelectricity የሚባል የሜካኒካል ሀይልን ወደ ኤሌክትሪክ ሀይል የመቀየር ሂደት ጥቅም ላይ እንደሚውል ምርምሩን የመራው ፕሮፌሰር ከማል አሳዲ ተናግሯል፡፡ በዚህ መልክ የተመረተው ሀይል በካፓሲተር ተጠራቅሞ እንደ ስልክ ያሉ ሀይል ፈላጊ እቃዎችን ቻርጅ ማድረግ ያስችላል፡፡
እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጻ piezoelectric ልብሶች ለምሳሌ ቲ ሸርቶች በትንሽ የእጅ እንቅስቃሴ ብቻ ሀይል ማመንጨት ይቻላል፡፡ በዚህ ረገድ ያለው ፍላጎት እየጨመረ ቢመጣም የልብስ አምራች ፋብሪካዎች ጋጠማቸው የዚህ አይነቱን ልብስ ለማምረት የሚያስችል ጥሬ እቃ እጥረት ፍላጎቱን ለማሟላት እንቅፋት መሆኑን ፕሮፌሰሩ አክሎ ገልጧል፡፡
ተመራማሪዎች የናይለንን ኤሌክተሪክ አመንጭነትን ከ1980ዎቹ ጀምሮ እንዳወቁት ይነገራል፡፡ ዘወትር ለቲ ሸርቶችና ለስቶኪንጎች የምንጠቀምባቸውን ሰው ሰራሽ ክሮች ኤሌክትሪክ እንዲያመነጩ ማድረግ በጣም አስቸጋሪ ስራ እንደሆነ ፕሮፌሰር ከማል አሳዲ ይናገራል፡፡
የ Piezoelectric ባህሪ ያላቸውን ሰው ሰራሽ ክሮች ማምረት ከተቻለ በቅርብ አመታት ውስጥ ትንንሽ ሀይል የሚጠይቁ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን ቻርጅ ማድረግ የሚያስችል ሀይል በልብሶቻችን እና በሰውነታችን እንቅስቃሴ በመታገዝ ማግኘት እንደምንችል ፕሮፌሰር ከማል አሳዲ ተስፋቸውን ተናግረዋል ሲል የዘገበው ቴክኖሎጂ ዶት ኦርግ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የቴሌኮምዩኒኬሽን ልማት ጉባኤ ልታስተናግድ ነው
በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደውን የዓለም የቴሌኮምዩኒኬሽን ልማት ጉባኤ (WTDC) 2021ድን ለማስተናገድ የሚያስችላትን ስምምነት ተፈራርማለች፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ በሚደረገው በዚህ ጉባኤ ላይ ከዓለም ዙርያ የተውጣጡ 2500 ታላላቅ የዘርፉ ተዋንያን የሚሳተፉበት ሲሆን በየ አራት ዓመት አንዴም የሚከናወን ነው፡፡ ከዓለም ዙርያ የተውጣጡ 240 ያህል ግለሰቦች ተሳታፊ በሆኑበት በዚህ የፊርማና ውይይት ስነ-ስርዓት ላይ ኢትዮጵያን በመወከል የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ዶ/ር አህመዲን መሐመድ የስምምነት ፊርማቸውን ሲያኖሩ በተባበሩት መንግስታት የዓለም አቀፍ ቴሌኮምዩኒኬሽን ህብረትን ወክለው ደግሞ ዋና ፀሀፊው አቶ ሆውሊን ዣው ፈርመዋል፡፡
እንደዚህ አይነቱን ጉባኤ ለማዘጋጀት የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት ሀገር መሆኗ ለኢትዮጵያ ክብር እንደሆነ ያወሱት ዶ/ር አህመዲን ጉባኤውን የማዘጋጀቱ ውሳኔም ኢትዮጵያም ሆነ አፍሪካ ዲጂታል ልማትን ለዘላቂ ልማታቸው መስፈንጠርያ አድርገው በቀዳሚነት ለመውሰዳቸው ማሳያ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ዶ/ር አህመዲን ሀገራች ለምታከናውነው የዲጂታል ምጣኔ-ሐብት ግንባታ ቁልፍ ተዋፅዖ እንደሚኖረው የሚጠበቀውን ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂንም ለተሳታፊዎቹ አብራርተዋል፡፡
አቶ ሆውሊን ዦው በበኩላቸው በአህጉሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚከናወነው በዚህ ጉባኤ ላይ ወሳኝ የተለያዩ ጉዳዮች እንደሚዳሰሱበት በመጥቀስ ወጣቶች የኮንፈረን ዋና ትኩረት መሆናቸውን አውስተዋል፡፡
ስድስት ዋና ዋና አብይ ጉዳዮችን (ትብብር፣ ተካታችነትን፣ የፋይናንስ ድጋፍ፣ አመራር፣ ኢኖቬሽን እና ወጣቶች) ማዕከል አድርጎ የሚዘጋጀው የ2021 የዓለም የቴሌኮምኒኬሽን ልማት ጉባኤ በዘርፉ ዙርያ የተለያዩ ምክረ ሀሳቦችን የሚያቀርብ እና በዘርፉ የሚሰሩ ስራዎች ከዘላቂ የልማት ግቦች ጋራ ተዋደው መሄዳቸውንም የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ጉባኤው በቀጣዩ ዓመት 2014 ላይ ከጥቅምት 30 እስከ ህዳር 10 ድረስ ባሉት 11 ቀናት ውስጥ የሚደረግ ሲሆን ከዚያ በማስቀደም ግን መዳረሻ የሚሆኑ ሌሎች ተያያዥ ጉባኤዎች በዓመቱ ውስጥ የሚደረጉ ይሆናል፡፡
ኮንፈረንሱ በኢትዮጵያ እንዲዘጋጅ ትልቅ ጥረት መደረጉን የገለፁት ዶ/ር አህመዲን ሀገራችን የቀረፀችው ሀገር በቀል የልማት እቅድ እና እተከናወኑ ያሉት የተለያዩ ዘርፎችን የሚሸፍኑ የዲጂታላይዜሽን ስራዎች ኢትዮጵያ በውድድሩ ላይ ተመራጭ ሆና ጉባኤውን እንድታስተናግድ እንዳስቻሏት አስረድተዋል፡፡ ለኮንፈረንሱ ዝግጅት ይረዳ ዘንድ ይመለከታቸዋል የተባሉ ባለ ድርሻ ተቋማትን ያካተተና የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሚመራው ሀገር አቀፍ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን በውስጡም 10 ንዑስ ኮሚቴዎችን አዋቅሮ እንቅስቃሴውን እንደጀመረ ሚኒስትር ደኤታው ገልፀዋል፡፡
ኮንፈረንሱ በኢትዮጵያ ከመዘጋጀቱም ባሻገር አፍሪካን የሚመስል እንደሚሆን በመግለፅ እንደ አለባበስ እና አመጋገብ ያሉት የተለያዩ አፍሪካ ባህል መገለጫዎች እንዲወከሉበት እንደሚሰራና እስካሁንም ይህን የሚያሳኩ ስራዎችን ከአፍሪካ ሀገራት ጋራ በመሆን መሰራት መጀመሩን አክለው ተናግረዋል፡፡
ከ20 አመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የአልዛይምር መድሃኒት ፍቃድ ሊያገኝ ነው
በፋርማሲዩቲካል ዘርፍ ትልቅ ዝናን ካተረፉ የመድሃኒት አምራቾች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ባዮጂን (Biogen) ከጃፓን አቻው ኢዛይ (Eisai) ጋር በመተባበር ያበለፀገው የአልዛይምር መድሃኒት ከሁለት አስርት አመታት በኋላ አገልግሎት ላይ ለመዋል የሚያስችለውን ፈቃድ ሊያገኝ እንደሚችል ሲ ኤን ኤን በዘገባው አስታውቋል፡፡
የማዕከላዊ እና የከባቢያዊ የነርቭ ሥርዓት መድኃኒቶች አማካሪ ኮሚቴ አርብ እለት በነበረው ስብሰባ አዲሱ የአልዛይምር መድሃኒት ፍቃድ የሚገኝበት ሁኔታ እንዲመቻች ለአሜሪካ የምግብና የመድሃኒት አስተዳደር ምክረ ሃሳብ ማቅረቡን እና በዚህ ውሳኔ መሰረትም ከረዥም ጊዜያት በኋላ በሽታውን የሚከላከል መድሃኒት ጥቅም ላይ የመዋል እድል እንዳለው የአማካሪ ኮሚቴው አባል ፕሮፌሰር ሩዶልፍ ታንዚ ተናግረዋል፡፡ እንደሳቸው ገለፃ የአማካሪ ቡድኑ ፍቃድ የማግኘት ውሳኔው ላይ ትልቅ ተፅዕኖ እንደሚኖረው በማንሳት የምግብና የመድሃኒት አስተዳደር (FDA) ምክረ ሃሳቡን ከግምት ውስጥ እንደሚያስገባ ያላቸውን እምነት ይገልፃሉ፡፡
Aducanumab የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ የአልዛይምር ማከሚያ መድሃኒት እስካሁን ባለፈበት የኪሊኒካል ሙከራ ብዙ ታማሚዎች ላይ መልካም ተስፋ እንዳሳየ የሚናገሩት የአልዛይምር መቆጣጠሪያ ክሊኒክ ዋና ዳይሬክትር ዶ/ር ሪቻርድ ኣይዛክሰን መድሃኒቱ በአግባቡ ከመስራቱ ውጭ ግን የደህንነቱ ጉዳይ፣ ከወጪ ምጣኔው አንፃር እንዲሁም ከሌሎች ህጋዊ እሳቤዎች አኳያ ጥብቅ ምርመራ እንደሚደረግበት አንስተዋል፡፡ መድሃኒቱ ለረዥም ጊዜያት በተለያዩ ሂደቶች ሙከራ ሲደረግበት የቆየ ቢሆንም ከሃምሌ 2020 እነስቶ ውጤታማነቱ እየተረጋገጠ በምጣቱ ፍቃድ የሚያገኝብት ሁኔታ እንዲመቻች መደረጉንም የመድሃኒት አምራቹ ባዮጂን አስታውቋል፡፡
እንደአውሮፓውያኑ ከ2004 አንስቶ በሽታውን የሚከላከል ኖቬል መድሃኒት ፍቃድ አለማግኘቱን የሚያወሳው ዘገባው፤ አዲሱ መድሃኒት ግን አሁን ባለው ሁኔታ ፍቃድ የሚያገኝ ከሆነ በአልዛይምር በሽታ ምክንያት በአንጎል ውስጥ የሚፈጠረውን amyloid beta ለማስወገድ እና በሽታ የመከላክለ አቅምን ለማጎልብት በእጅጉ አንደሚረዳ ገልጿል፡፡ CNN
መግነጢሳዊ ክልልን ለማጥፋት ባለ 178 ዓመት እድሜ ጠገብ እሳቤ
*****************************************
መግነጢሳዊ ክልልን (magnetic field) ማጥፋት እንደ ኳንተም ቴክኖሎጂ፣ ባዮሜዲሲንና ስነ-አእምሮ ላሉ ዘርፎች እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ሁለት የሰሴክስ ዩኒቭርሲቲ የፊዚክስ ምሁራንን ያካተተው የተመራማሪዎች ቡድን ከርቀት በመሆን መግነጢሳዊ ክልልን በትክክል ማጥፋት የሚችሉበትን መንገድ ማግኘታቸውን SciTechDaily የተሰኘ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ የመረጃ ተቋም በድረ-ገጹአስነብቧል፡፡ በዚህም እነዚህ ተመራማሪዎች በዘርፉ ረብ ያለው ነገር በመስራት የመጀመሪያ እንደሆኑ የወጣው መረጃ ያሳያል፡፡
ስራው በተለያዩ መስኮች ጥቅም ይሰጣል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ ለምሳሌ ያክል እንደ አልዛይመርና ፓርኪንሰን ያሉ የስነ-አእምሮ ጤና ችግር ያለባቸው ህመምተኞች ለወደፊት አስተማማኝ ህክምና ሊያገኙ ይችላሉ የሚል ተስፋ ተጥሏል፡፡ ለህክምና ስራ አዋኪ የሆነው መግነጢሳዊ ክልልን ለማስወገድ መላ ከተገኘ ሀኮሞች በበሽተኞች ጭንቅላት ውስጥ እየተከናወነ ያለውን ትክክለኛ ነገር አጥርተው መመልከት ይችላሉ ሲል መረጃው አክሎ አስነብቧል፡፡
“Earnshaw’s Theorem” በመባል የሚታወቀው እሳቤ በ1842 የመግነጢሳዊ ክልልን መወሰን ወይም መከለለል እንደማይቻል አሳውቆ ነበር፡፡ የምርምር ቡድኑም ይህን እሳቤ ፈጠራ በታከለበት ስልት እሳቤውን ይቻላል ወደሚል መለወጥ ችሏል፡፡ ይህንንም በጣም በትንቃቄ የተደረደሩ የኤሌክትሪክ ሽቦወች ያሉበት መሳሪያ በመስራት እንዳሳኩት መረጃው ጠቁሟል፡፡
ግኝቱ ለቴክኖሎጂው አለም እድገት ካለው አስተዋጽኦ በይበልጥ በስነ- አእምሮ ህክምና ላይ ያለው አስተዋጽኦ በጣም ከፍተኛ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡
ምንጭ፡ SciTech Daily
እናት ወይስ አባት? ማንን መስለን እንወለዳለን?
-------------------------------------
“አንተ እኮ ቁርጥ እናትህን ትመስላለህ”፤ “የአባትሽን መልክ ይዘሽ ነው የተወለድሽው”፤ “አፍንጫሽ የእናትሽን ይመስላል”፤ “እዩት እስቲ በአባቱ ቤተሰቦች ነው የወጣው”… እነዚህ አስተያየቶች በተለይ በልጅነት ጊዜያቶቻችን ደጋግመን መስማታችን በብዙዎቻችን ዘንድ የተለመደ ነው፡፡ ግን ማንን መስለን እንወዳለን? በዚህ ጉዳይ ላይ ሳይንስ ተከታዩን ማብራሪያ ይሰጠናል፡፡
የዚህ ጥያቄ መልስ በዋናነት ከእናት ወይ አባት የወሰድነው በራሂ (ጂን) ይበዛል? ወይስ የማን ጂን ተፅዕኖው የጎላ ነው? በሚለው ጥያቄ ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡ ታድያ የሳይንስ ጠበብት ሁለቱ ወላጆቻችን የሚያበረክቱት ድርሻ እኩል እኩል እንደማይሆን ያምናሉ፡፡ ለምሳሌ በራሂዎች 23 X ወይም የY ቅርፅ ባላቸው ክሮሞሶሞች ውስጥ ባሉት የዲ.ኤን.ኤ ስንስሎች ላይ ይቀመጣሉ፡፡ እነዚህ ኦቶሶሞች (ፆታዊ ያልሆኑ ክሮሞሶሞች) በህዋሶቻችን ኒውክሊየሶች ውስጥ ያሉ ሲሆን የያዙት DNAም ከሁለቱም ወላጆቻችን በእኩል መጠን የተወሰደ ነው፡፡ ሆኖም ሕዋሶቻችን ማይቶኮንድሪያ ውስጥ የተደበቀ ሌላ ክሮሞሶም ይዘዋል፡፡ ማይቶኮንድሪያ የሕዋሶች የኃይል ምንጭ ሲሆን በእንቅስቃሴ እና እርጅና ላይም ትልቅ ተፅዕንዖ አለው፡፡ ታድያ ማይቶኮንድሪያ የራሱ የሆነ የDNA አኳሀን ሲኖረው ከእናታችን ብቻ የምንወርሰው ነው፡፡ ይህ ታድያ ከአባት ይልቅ እናታችንን ለመምሰላችን ማሳያ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል፡፡
አንዳንድ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ከሆነ የማይቶኮንድሪያ DNAያችን (በዚህ ምክንያትም እናታችን) በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ችሎታችን ላይ የጎላውን ሚና ይጫወታል፡፡ የእስራኤል እና ስፔን ተመራማሪዎች በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ወቅት ከሚኖረን የኦክስጅን አጠቃቀም ልኬት ጋራ በሚያያዘው የማይቶኮንድሪያ ሕዋስ ላይ ያተኮረ ጥናት ሰርተው ነበር፡፡ ከ15 ዓመታት በፊት ተሰርቶ ይፋ ሆኖ የነበረው ይህ ጥናታቸው እንደሚያሳየው ከሆነ ከዝቅተኛ የአካላዊ እንቅስቃሴ ብቃት ጋራ የተያያዙ በራሒዎች ከሌላው ህዝብ በተለየ በብስክሌት ግልቢያ ተወዳዳሪዎች እና ሯጮች ላይ አነስ ብለው መገኘታቸውን ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ሌሎች የተለያዩ ጥናቶችም እነዚህ እና ሌሎች በራሒዎችን በማውረስ ረገድ እናቶቻችን የሚወስዱትን ላቅ ያለ ሚና አሳይተዋል፡፡ ጥናቶቹ ከአባቶች ይልቅ እናቶች ያላቸው አካላዊ ብቃት ብቻውን የልጆችን የወደፊት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ችሎታ ሊተነብይ እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡
ሆኖም ግን ከየትኛው ወላጅ የሚመጣው በራሂ ይበዛል? ከሚለው ይልቅ የትኛው ከፍ ያለ ተፅዕንዖን ያሳድራል? የሚለው ጥያቄ ጎልቶ ሊነሳ ይችል ይሆናል፡፡ እዚህ ላይ ልብ ማለት ያለብን በፊት አልያም ሌላ ውጫዊ ገፅታችን ላይ የሚታየው ልዩነት በበራሂዎች መሰረታዊ መነሻነት የሚመነጭ ሳይሆን በDNA ጫፍ ላይ ተቀምጠው ባሉት የኬሚካል መቀያየሪያዎች (switches) አማካኝነት ለሰውነታችን በሚተላለፈው ንባብ እና ይህን ተከትሎ በሚመጣው የየትኛው ፕሮቲን አይነት ይመረት እና የተኛው ይተው ትርጓሜ ነው፡፡ ኢምፕሪንቲንግ ተብሎ በሚጠራ ሁነት አማካኝነት እነዚህ መቀያየሪያዎች አንዳንድ ከአንደኛው ወላጅ ብቻ የመጡ በራሂዎችን ሙሉ ለሙሉ ፊት ሊነሱ ይችላሉ፡፡ ይህ ሁኔታ በትውልዶች ውስጥ ሊቀጥል ይችላል፡፡ ለምሳሌ አንድ በራሂ በአባት በኩል ኢምፕሪንት ከሆነ ምንጊዜም የሚሰራው ከእናት በኩል ሲመጣ ብቻ ነው፡፡ ምንም እንኳን በዚህ ላይ ልዩነቶች ቢኖሩም ብዙዎቹ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ከሆነ የሰው ልጆች ከ100 እስከ 200 የሚደርሱ ኢምፐሪንት የተደረጉ በራሂዎችን በሰውነታችን እንይዛለን፡፡
ኢምፕሪንቲንግን ተከትሎ በሚመጣው ወደ አንደኛው ወይም ሌላኛው ወላጅ የሚደረግ ማዘንበል መኖሩ ላይ ግን ሁሉን አቀፍ ስምምነት የለም፡፡ “ማስረጃዎች እንደሚጠቁሙን ከሆነ ከእናት እና አባት የሚወረሱት ኢምፕሪንት የሆኑ በራሂዎች ሰውነት ውስጥ በእኩል መጠን ይገኛሉ” ሲሉ የጀነቲክ ባለሙያው አንድሪው ዋርድ ያስረዳሉ፡፡ ታድያ ኢንፕሪንት በሆኑ በራሒዎች አማካኝነት በሚመጡ አካላዊ መገለጫዎች ላይ ወደ አንዱ ወላጅ ልናደላ እንደምንችልም አክለው ይገልፃሉ፡፡ በሌላ አነጋገር ኢምፕሪንቲንግ እንደ ሰውነት መጠን፣ እንቅልፍ እና ማስታወስ ባሉ ልዩ ገፅታዎቻችንም ላይ ተፅዕንዖ ሊኖረው ይችላል ማለት ነው፡፡ ሆኖም ኢምፕሪንቲንግ የሚደረግባቸው በራሂዎች በአንፃሩ አነስተኛ በመሆናቸው እና እነርሱም ቢሆን ከሁለቱም ወላጆቻችን በተመጣጣኝ መጠን የሚወሰዱ በመሆናቸው ሳብያ ከእናት አልያም አባት በጣም የተለየ መመሳሰል እንዳይኖር የማድረግ እድል አለው፡፡
ሆኖም አይጦች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት የሚያመላክተው ግን ምናልባትም ወደ አባቶቻችን የቀረብን መሆናችንን የሚያሳይ አድሎ ሊኖር መቻሉን ነው፡፡ እ.አ.አ በ2015 ኔቸር ጀነቲክስ ጆርናል ላይ ታትሞ የወጣው ጥናቱ እንደሚያሳየው ከሆነ በእናት በኩል ያሉት ኢንፕሪንት የሆኑ በራሒዎች ከአባት በኩል ከሚመጡት አንፃር ተቀባይነት የማጣት እድላቸው (በተቃራኒው የአባቶች ተቀባይንነት የማግኘታቸው እድል) በ1.5 እጥፍ የላቀ ነው፡፡ ቀድሞ በ2008 (እ.አ.አ) የወጣ ሌላ ጥናትም ተመሳሳይ ውጤት አሳይቶ ነበር፡፡ በአንጎል ውስጥ ያሉት ኢምፕሪንት ከሆኑ በራሂዎች ውስጥ ከአባት የመጡ ሲሆኑ ይበልጥ ንቁ ናቸው፤ በእንግዴ ልጅ ላይ ደግሞ በተቃራኒው ይሆናል፡፡ ሆኖም ይህ አለመመጣጠን ለሰው ልጆችም ይስራ አይስራ የሚያሳይ መረጃ እስካሁን አልተገኘም፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን በተለይ በበራሂ ላይ ከአንደኛው ወላጃችን የወሰድነው ኢምፕሪንት የሆነ በራሂ ቢበልጥ እንኳን ከሌላኛው ወላጅ በበለጠ ወደ እርሱ/እርሷ እንቀርባለን ማለት አይደለም፡፡ ምናልባትም በእኛ ውስጥ ንቁ ሆኖ ያለው አንድ የበራሂ አይነት እናትም ይሁን አባት ባወረሰን ወላጅ ላይ ንቁ ሆኖ ላይገኝ ይችላልና፡፡
ምንጭ፡ Live Science