TechIn2
1.22K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
፲ የኦንላይን የደህንነት ምክሮች ከጎግል
--------------------------------------------
ባለፉት ወራቶች የሳይበር ደህንነት ማስገንዘቢያ መርሃ ግብሮች ሲካሄዱ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ በተለይም የጥቅምት ወር ይህን የግንዛቤ ስራ ለማካሄድ በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ ስትውል ተመልክተናል፡፡ ይህን በማከናወን ሂደት ግዙፉ የጎግል ኩባንያ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ድርጅት ሲሆን በአሰራር ፕሮቶኮሉም የበይነ-መረብ ተጠቃሚዎች ደህንነታቸው በተጠበቀ መልኩ ስራቸውን እንዲያከናውኑ ትልቅ እገዛ ያደርጋል፡፡ እነዚህ የምትመለከቷቸው የጎግል የደህንነት ማሻሻያ አማራጮች በኢንተርኔት ላይ የሚኖረንን እያንዳንዷን እንቅስቃሴ ከማስጠበቅ አልፎ ለስራችን መሳካትም ትልቅ ሚና ሊኖራቸው ስለሚችል በሚገባ ማየቱ ጠቃሚ ነው፡፡
፩. በአይነታቸው የተለዩ እና ለመገመት አስቸጋሪ የሆኑ የይለፍ ቃሎችን ለመፍጠር የጎግልን የይለፍ ቃል አስተዳደር (password manager) መጠቀም የመጀመሪያው የጥንቃቄ መንገድ ነው፡፡
፪. በዴስክቶፕ እና በሞባይል የኦፕሬቲንግ ስርዓቶች የሚጫኑ የድር ማሰሻ (web browser) መተግበሪያዎች ምንግዜም የመጨረሻው ማዘመኛ (up-to-date) የተደረገላቸው መሆን አለባቸው፡፡ ይህ ደግሞ የምንጠቀማቸውን የኦንላይን ቴክኖሎጂዎች ከደህንነት ስጋት ውጭ ያደርጋቸዋል፡፡
፫. ስልካችን ጠፍቶ ቢገኝና በፍፁም የማናገኝበት ሁኔታ ቢፈጠር በጎግል አካውንታችን አማካኝነት ( myaccount.google.com.) በመግባት ከየኛውም ቦታ ሆነን ስልካችንን መቆለፍ እና ሚገኝበትን አካባቢ መረዳት እንችላለን፡፡
፬. የበይነ መረብ አገልግሎት ስንጠቀም የግል መረጃዎቻችንን የሚያጠምዱ የተለያዩ ድረ ገፆች ሊያጋጥሙን ይችላሉ፡፡ እነዚህ የመረጃ አጥማጆች በተከታታይ የሚቀርቡልንን ጥያቂዎች በንቃት መከታተል አንደኛው የመጠበቂያ መንገድ ሲሆን፤ ከዚያ በለፈም በመተግበሪያችን (browser) ላይ ሊጫኑ ወይም (extended) ሊደረጉ የሚችሉ መሳሪያዎችን በማከል ችግሩን ማስቀረት አንችላለን፡፡ በዚህ አንፃር የጎግል ሳይቶች ያልሆኑ (non-Google site) አድረሻዎች ላይ የይለፍ ቃል ስናስገባ ማስጠንቀቂያ የሚልክልን እንደ (Password Alert extension) ያለ መሳሪያ በመተግበሪያችን ላይ መቀላቀል እንችላለን፡፡
፭. አንዳንድ ጊዜ የመረጃ መንታፊዎች ወይም ሃካሮች የኛኑ የመጠቀሚያ ስም (username) እና የይለፍ ቃል በአካውንታችን ላይ በማስገባት አጠቃላይ መረጃችንን ሊሰርቁና ሊያጠቁን ይችላሉ፡፡ ይህ ሊሆን የሚችልበት ምክንያት የተለያየ ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ ግን የጠነከረ የይለፍ ቃል ሳይኖር ሲቀርና የተለያዩ ማዘመኛዎች ሳናደርግ ስንቀር ነው፡፡ አነዚህ የአጠቃቀም ክፍቶች ብዙዎቻችን ላይ የሚስተዋሉ ቢሆንም ካዛ ባለፈ በስራቸው ላይ ከፍተኛ ስጋት ያለባቸው ሰዎች ግን በጎግል አካውንት ላይ (security.google.com) በመግባት የሁለተኛ ደረጃ ማረጋገጫ (2-Step Verification) በማስቻል እያንዷንዷን እንቅስቃሴያቸውን መመልከት ይኖርባቸዋል፡፡
፮. አሁን አሁን ከየትኛውም የማህበረሰብ ክፍል በላይ የፖለቲካ መሪዎች እና የማህበረሰብ አክቲቪስቶች ለሳይበር ጥቃት እጀግ ተጋላጭ እየሆኑ መምጣቸው የሚታወቅ ነው፡፡ ታዲያ አንደዚህ አይነት ግለሰቦችና ሌሎች ከፍተኛ የሳይበር ስጋት ያለባቸው አካላት ጎግል የሚያቀርበውን የላቀ የጥበቃ መርሃ-ግብር (Advanced Protection Program) መጠቀም ይችላሉ፡፡ ይህ ፕሮግራም መረጃ አጥማጆችን በሚገባ ለመከላከል የሚጠቅም ሲሆን በታመኑ መተግበሪያዎች ላይ የኔትወርክ አጠቃቀችንን ለመገደብ እና አካውንታችንን አጭበርብረው ለሚጠቀሙ ሃከሮችም ጥሩ መፍትሄ ነው፡፡
፯. አብዛኛውን ጊዜ በስልካችን የምናወርዳቸው ምንጫቸው ያልታመነ መተግበሪያዎች ለየትኛውም የሳይበር ጥቃት በቀላሉ ሊያጋልጡን ይችላሉ፡፡ ከጎግል ፕለይ ያወረድናቸው መተገበሪያዎች እንኳን አልፎ አልፎ መሰል ስጋት ስለሚኖርባቸው የጎግል ፕለይ ጥበቃ ላይ (Google Play Protect) የደህነት ፍተሻ መድረግ እጅግ ተመራጭ ይሆናል፡፡
፷. በጎግል የበይነ መረብ አጠቃቀማችን ላይ እያንዷንዷን እንቅስቃሴያችንን በየጊዜው ለመፈተሸና ለመከታተል የጎግልን (Security Checkup) በቀላሉ መጠቀም እንችላለን፡፡ ይህ ሲስተም የጎግል አካውንታችንን ደህንነት ለመተንተን እና ያጋጠሙ ችግሮችንም በቀላሉ ለመፍታት የሚያገለግለን ነው፡፡
፱. ምንግዜም ቢሆን የህዝብ ወይም ነፃ የዋይፋይ ኔትወርኮችን ስንጠቀም በምላሹ ሊኖር ስለሚችለው የደህንነት ስጋት መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ የዋይፋይ ኔትወርኩ የይለፍ ቃል የታከለበት ቢሆንም እንኳን መረጃዎቻችንን አሳልፎ እንዳይሰጥ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
፲. ከእነዚህ ጥንቃቄዎች በተጨማሪ በጎግል አካውንታችን ላይ የደህንነት ቁልፍ (security key) በማዋቀር አጠቃላይ የበይነ መረብ አንቅስቀሴያችንን ማስጠበቅ እንችላለን፡፡
ምንጭ፡ Gadgets Africa
የፕሮጀክት ማኔጅመንት ስልጠና በመካሄድ ላይ ነው
-----------------------------------
በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት የተዘጋጀው በፕሮጀክት ማኔጅመንት ላይ ያተኮረ መርሃ ገብር በመካሄድ ላይ ነው፡፡ በኢኒስቲትዩቱ በቅርብ ጊዜ በተቋቋመው የፕሮጀክት ማኔጅመንት ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀው ይህ ስልጠና ከተለያዩ ዳይሬክቶሬቶች ለተወጣጡ የፕሮጀክት ማናጀሮች መሰረታዊ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ሂደቶችን የሚያስቃኝ ነው፡፡
በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ ሃሳባቸውን ያካፈሉት የኢኒስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን ቀሬ በቅሩቡ የተቋቋመው የፕሮጀክት ማኔጅመንት ዳይሬክትር ተቋሙ የሚያከናውናቸውን የፕሮጀክት ስራዎች በማዕከላዊነት ለማስተዳደር እና በቀጣይም ትልልቅ ሃሳቦችን ከመነሻው አንስቶ አስከመጠናቀቂያው ጊዜ ድርስ በስኬት ለማጠናቅ ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀን በሚቆየው በዚህ የስልጠና መረሃ ግብር የፕሮጀክት አፈፃፀም ሂደት ላይ ያሉ ክፍተቶች፣ ከፕሮጀክት መነሻ ሃሳብ እስከ ማጠናቀቅ ብሎም የፕሮጀክቱን ዓላማ ከማሳካት አኳያ ያሉ ሂደቶችን፣ በቀጣይ መሻሻል ስለሚገባቸው ጉዳዮች፣ ከመምራት እስከ መፈፀም ድረስ መከተል ስለሚገባን የስነምግባርበ ሂደቶች እና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን አድርጎ እንደሚቆይ ይጠበቃል፡፡
ለሁለተኛ ዙር የሚካሄደው ይህ ስልጠና የኢኒስቲትዩትን የፕሮጀክት የአሰራር ሂደት አለም አቀፍ ስታንዳርድ በተላበሰ መልኩ ለማስኬድ እና የፕሮጀክት እቅዶችን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ለመምራትና ለማስፈፀም አላማ አድርጎ የሚካሄድ ነው፡፡
በቀን የሚያስፈልገን የኦክስጅን መጠን
********************************
አንድ ጎልማሳ በአማካኝ በደቂቃ ከ7 እስከ 8 ሊትር የሚሆን አየር ወደውስጥ ስቦ ያስወጣል፡፡ በሌላ መ ልኩ 388 ኪዩቢክ ጫማ እንደማለት ነው፡፡ ይህም አንድ ሰው በቀን የሚጠቀመውን አየር ወደ 11 ሺህ ሊትር ያደርሰዋል፡፡ መጠቀም የሚለው ቃል ኦክስጅን ወደ ውስጥ መማግንና የተቃጠለውን አየር ማስወጣትን የሚገልጽ ነው፡፡
ወደ ሰውነታችን ከምናስገባው አየር ውስጥ 20 በመቶ የሚሆነው ኦክስጅን ሲሆን በእምጋት ከምናስወጣው አየር ውስጥ ኦክስጅን 15 በመቶ የሚሆነውን ይሸፍናል፡፡ ስለዚህ በየአንዳንዱ ትንፋሽ 5 በመቶ የሚሆን ኦክስጅን ለአጠቃላይ ስርዓተ-ሰውነት አገልግሎት ይውላል ማለት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት አንድ ሰው ከወጭ ቀሪ 550 ሊትር ንጹህ ኦክስጅን ይጠቀማል ማለት ነው፡፡
ነገር ግን አንድ ሰው አዘውትሮ የሰውነት እንቅስቃሴ የሚሰራ ከሆነ ከዚህ የበለጠ የኦክስጅን መጠን ይጠቀማል፡፡ በሳንባችን ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን አየር ይዘቱ በሚታወቅ ፕላስቲክ ወደውጭ በመተንፈስ መጠኑን መለካት እንችላለን፡፡
ምንጭ፡ www.howstuffworks.com
ኢትዮጵያ በ15 ዓመታት ውስጥ 10 ሳተላይቶችን ለማምጠቅ አቅዳለች
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ይሽሩን አለማየሁ ዛሬ በቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት በመገኘት ስለ ሳተላይት እና የኢትዮጵያ ሳተላይት ፕሮግራም ዙርያ ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡ የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪዎችን ተሳታፊ በሆኑበት በዚህ ዝግጅት ዶ/ር ይሽሩን በሳተላይቶች ታሪክ፣ አይነት እንዲሁም በግብርና፣ ጤና፣ መጓጓዣ፣ የህዝብ አሰፋፈር….ረገድ ሳተላይቶች ሊያቀርቡ ስለሚችሉት ጥልቅ ግልጋሎት ለታዳምያኑ አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በህዋ ምርምር ረገድ እስካሁን የተራመደቻቸውን እርምጃዎች እንዲሁም አሁን ያሉ እቅድ እና እንቅስቃሴዎችን ዳይሬክተሩ የዳሰሱ ሲሆን ከነዚህ መካከል የሆነውን በ15 ዓመታት ውስጥ 10 ሳተላይቶችን የማምጠቅ ዕቅድንም አውስተዋል፡፡ የዚህ ግዙፍ እቅድ አካል የሆኑት ከ3-4 ባሉት ዓመታት ውስጥ የኮምዩኒኬሽን እና የምድር ምልከታ ሳተላይቶችን እንዲሁም በ 10 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የአየር ትንበያ ሳተላይት የማምጠቅ እቅዶችንም ማብራርያ ቀርቦባቸዋል፡፡
ሌላው በመድረኩ ማብራርያ ያገኘው ኢትዮጵያ በያዝነው ዓመት ታህሳስ 11 ዕለተ እሁድ እንደምታመጥቀው የሚጠበቀው አዲስ ሳተላይት ጉዳይ ነው፡፡ ከአንድ ዓመት የበለጠ የአገልግሎት ዘመን እንደሚኖራት የሚጠበቀው አዲሷ ሳተላይት ከምድር በ512 ኪ.ሜ ከፍታ ላይ በመሽከርከር መረጃ የምታቀብል ይሆናል፡፡ ሳተላይቷ ET-SMART-RSS የሚል ስያሜን ያገኘች ሲሆን መጠኗ አንድ አመት ቀድማት ወደ ህዋ ከተጓዘችው ETRSS-1 አንፃር አነስ ያለች (8.9 ኪ.ግ የምትመዝን) ስትሆን በቻይናዋ ሃይናን ግዛት ውስጥ ካለው ዌንቻንግ የማምጠቂያ ማዕከል የምትመጥቅ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ቀድሞ የመጠቀችው ሳተላይት ባስገኘቸችው ምጣኔ ሐብታዊና ሌሎች ጥቅሞች ብሎም በሀገሪቱ የተከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎችን በመተንበይ ረገድ ስለነበረባት ክፍተት ጥያቄ የተነሳ ሲሆን ዳይሬክተሩም የተለያዩ የሀገራችን ተቋማት ቀድሞ ከሌላ ያገኟቸው የነበሩትን መረጃ አሁን በሳተላይቷ አማካኝነት ማግኘት መጀመራቸውን በማውሳት ጭምር ምላሽ ሰጥተውበታል፡፡ በህዋ ምርምር ዙርያ ታዳጊዎችን በማውጣት ረገድ ኢንስቲትዩቱ እየሰራቸው ስላሉት ስራዎችም ተጠይቀው ኢንስቲትዩታቸው በበቂ ደረጃ ታዳጊዎችን በዘርፉ የማብቃት ስራዎችን እየሰራ እንዳልሆነ አምነው ወደፊት ግን በትምህርት ካሪኩለሙ ውስጥ እስከማካተት የሚደርስ ታዳጊዎችን የማብቃት ስራ ለመስራት እንደታሰበ ዶ/ር ይሽሩን ተናግረዋል፡፡
በሽታው የጋራችን፤ ክትባቱ የግላችን?
=======================
የሐብታም ሀገራት መንግስታት 8.8 ቢሊዮን ፍሬ ክትባት ለመግዛት የሚያስችላቸውን ስምምነት እያከናወኑ ሲሆን ይህም ደሀ ሀገራት ክትባቶቹን ቢያንስ እስከ አውሮፓውያኑ 2024 ድረስ እንዳያገኙ የሚያደርግ መሆኑ ተነግሯል፡፡
እስካሁን በሙከራ እና ሌሎች ሂደቶች ውስጥ እያለፉ ካሉት 320 በላይ ክትባቶች ውስጥ አንዳቸውም ጥቅም ላይ እንዲውሉ ፍቃድ ያልተሰጣቸው ቢሆንም እስካሁን ድረስ የሐብታም ሀገራት መንግስታት 3.73 ቢሊዮን ፍሬዎችን ለመግዛት የሚያስችል ስምምነት ከመድሃኒት አምራች ኩባንያዎች ጋራ ገብተዋል፤ 5 ቢሊዮን ፍሬ ለመግዛት የሚያስችሉት ስምምነቶችም በቅርብ የሚደረሱ ይሆናሉ፡፡
የመድሃኒት አምራቾች በአሁኑ ሰዓት ያላቸው አቅም እነዚህ እጩ ክትባቶችን በማምረት ብቻ የተወሰነ ነው፤ ይህ ማለት ክትባቶችን ወደተቀረው የዓለማችን ህዝብ በማድረስ ከወረርሺኙ ለመታደግ ሦስት አልያም አራት ዓመታት ሚያስፈልጉ ይሆናል፡፡ በነዚህ ወቅቶች የደሃ ሀገራት ዜጎች በክትባት አማካኝነት ከወረርሺኙ ከመጠበቃቸው አስቀድሞ ሐብታም ሀገራት ጠቅላላው ህዝባቸውን በተደጋጋሚ ክትባት ለማስከተብ የሚችሉ ይሆናል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ኮቫክስ (Covax) በተባለው እቅዱ አማካኝነት ፈራሚ ሀገራት ስኬታማ የሆኑትን ክትባቶች በእኩል መጠን እንዲካፈሉ ለማድረግ እየሰራ ነው፡፡ በዚህም ክትባቶቹን በመጀመሪያ ለጤና እና የደህንነት ባለሙያዎች፤ በመቀጠልም ቢያንስ 20 በመቶ ለሚደርሰው የሀገራቱ ህዝብ ለማድረስ ለማድረስ አስቧል፡፡ ታድያ ሐብታም ሀገራቱ ለዚህ እቅድ ድጋፍ ሲያደርጉ ቢቆዩም አሁን ግን ከመድሃኒት አምራቾቹ ጋራ ከጥታ ስምምነት ውስጥ ገብተዋል፡፡ ይህም በኮቫክስ አማካኝነት በእኩሌታ ይከፋፈል የነበረውን ክትባት ለራሳቸው ብቻ ያስቀረ ነው፡፡
ኢትዮጵያን ለምሳሌ ብናነሳ በኮቫክ አማካኝነት 20 በመቶ የሚሆነው ህዝቧ ክትባቱን ያገኝ የነበረ ቢሆንም ምንም አይነት የጎንዮሽ ስመምነት ውስጥ ሰባለመግባቷ ምክንያት እንደ እንግሊዝ ያሉት ሀገራት ህዝባቸውን ሙሉ ለሙሉ ከበሽታው ሲጠበቁ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ግን ለዓመታት ክትባቱን ሳያገኝ ይቀራል፡፡
ሌላኛው በክትባት ዙርያ ያለ ችግር በቅዝቃዜ ስፍራ መቀመጥ ላለባቸው ክትባቶችን እንዲሁም በከፍተኛ ሙቀት መቀመጥ የሚገባቸው ቁሳቁሶችን ለማስቀመጫ የሚሆን በቂ መሰረተ ልማረትና አቅም ማጣት ነው፡፡ ጆንሰን እና ጆንሰን ድርጅት በቅድሚያ የሚያመርታቸው በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆተሩ በመጠነኛ የማቀዝቀዣ ቅዝቃዜ ውስጥ ያለምንም ችግር ለብዙ ወራት መቀመጥ የሚችሉ እጩ ክትባቶች ይህን የማቀዝቀዣ ችግር ሊያቃልሉ የሚችሉ ናቸው፤ ሆኖም እነዚህ ክትባቶችንም አሜሪካን፣ ካናዳ፣ እንግሊዝ እና የአውሮፓ ሕብረት አስቀድመው በገፍ ገዝተዋቸዋል፡፡
ኮቫክስ እስካሁን ድረስ 250 ሚሊዮን ህዝብን መከተብ የሚችል ክትባት መግዛቱ ታውቋል፡፡ ይህ ግን ቀድሞ ሊሸፍነው አስቦት ከነበረው 1.14 ቢሊዮን ህዝብ አንፃር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ቸርነት ካሳዩት ጥቂት ሐብታም ሀገራት መካከል የሆነችው አውስትራሊያ ለ25 ሚሊዮን ህዝቧ ለመግዛት ከተስማማችው 80 ሚሊዮን ክትባቶች ውስጥ ለደሀ ሀገራትም ለማካፈል ፍቃደኝነቷን ገልፃለች፤ ምንም እንኳን የምታካፍለው በህዝብ ብዛት ሚጢጢ ለሚባሉት እንደ ቫኑአቱ እና ፊጂ ላሉ ጎረቤት ሀገራት ቢሆንም፡፡
ከዚህ ቀደም ከጤና ባለሙያዎች ሰፈር ሀገራት ግብዓቶቻቸውን ለራሳቸው በመሰብሰብ እና ወደውጭ የሚላኩት ላይም ከፍተኛ ቁጥጥር በማድረግ የሚከናወን የክትባት ብሔረተኝነትን የኮቪድ-19 ወረርሺኝን ይበልጥ ላልተፈለገ ጊዜ በዓለም ላይ እንዲቆይ ያደርግ ይሆናል የሚል ስጋታቸውን ሲያነሱ ነበር፡፡
ምንጭ፡ The Guardian
ከአንድ ምዕተ ዓመት በኋላ ዳግም የተገኘው እስስት
================================
ቮልትዝኮው (Furcifer voeltzkowi) የተባለው የእስስት ዝርያ ከአንድ መቶ አመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ታይቷል፡፡ የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች ከ4 ቀናት በፊት ነበር የቮልትዝኮው እስስትን ዳግም መገኘት ይፋ ያደረጉት፡፡ በማዳጋስካር ብቻ የሚገኘው ይህ እንስሳ በሳይንሱ ዓለም ለመጨረሻ ጊዜ የታየው እ.አ.አ በ1913 ነበር፤ ሴት የቮልትዝኮው እስስቶችን ደግሞ የትኛውም የሳይንስ ሰው በአይኑ አይቷቸው አያውቅም ነበር፡፡ ታድያ ሴቶቹ እጅግ ያማሩ የቀለማት ህብርንም ማሳየት የሚችሉ ሆነው ተገኝተዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ተቋም የጠፉ ፍጥረታትን በሚፈልግበትና ግኝቶችን በመጠቀም በመጥፋት አደጋ ላይ ካሉት እንስሳትም ባለፈ በዙርያቸው ባለው ስነ-ምህዳር ላይ የሚደረግ ጥበቃን ማበረታታት አላማ ባደረገው ፕሮግራሙ ነው ይህን የቮልትዝኮው እስስት ያገኘው፡፡
የቮልትዝኮው እስስቶች ለአንድ ምዕተ ዓመት ያልታዩ ብቻም ሳይሆን ብዙም ስለ እነርሱ የማይታወቅ የእስስት ዝርያዎችም ናቸው፡፡ ስለ ህይወት ዘይቤያቸው ያለው መረጃ እስከዛሬም አነስተኛ ሲሆን በዘር የሚቀርቧቸው ዝርያዎቻቸው ግን ቶሎ አድገው ቶሎ ሚሞቱ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ሌላኛው የማዳጋስካር ብርቅዬ እስስት ሌበርድ (Furcifer labordi) በህዳር ወር ከእንቁላሉ ተፈልፍሎ ወዲያው በማደግ ምትክ እንቁላሎችን የሚጥል ሲሆን መጋቢት ላይም የሚሞት ይሆናል፡፡ አጥኚዎቹ የቮልትዝኮው እስስቶች እንደ ሌበርድ ከሚሊየን ከሆኑ በመጠን አነስተኛ ብቻም ሳይሆን እንደ ለግማሽ ዓመት ብቻ የሚታዩ እንደሆኑ ያውቁ ነበር፡፡
አሳሽ ቡድኑ አሰሳውን የጀመረው ከ2 ዓመታት በፊት ነበር፤ በአሰሳቸው ጅማሬ ግን ብዙም ዕድል አልቀናቸውም ነበር፡፡ የቮልትዝኮው እስስቶችን የማግኘት ትልማቸውም የመከነ መስሎ ነበር፡፡ ሆኖም አሰሳው ሊያልቅ ቀናት ብቻ ሲቀሩት የአስጎብኙነት ስራ የሚሰራው አንጄላክ ራሳፊሚናንሳ የተባለ ማዳጋስካራዊ ከቮልትዝኮው እስስቶች መካከል አንዷን መመልከት ቻለ፡፡ የኋላ ኋላ የአሰሳ ቡድኑ ሦስት ወንድ እና 15 ሴት የቮልትዝኮው እስስቶችን ማግኘት ችሏል፡፡
ሴት የቮልትዝኮው እስስቶች ከወንዶቹ አንፃር አነስተኛ መጠን ያላቸው ሲሆን ርዝማኔያቸውም 15 ሴ.ሜ ነው፡፡ ወንዶቹ በበኩላቸው እስከ 16.4 ሴ.ሜ ሲረዝሙ ብዙውን ጊዜ ፈካ ያለ አረንጓዴ ቀለም ያላቸውና ጭንቅ ወይም ንዴት ወስጥ ሲገቡ ደግሞ ጠቆር ያለ አረንጓዴ ቀለም ያላቸው ጭረቶችን በሰውነታቸው ላይ ያወጣሉ፡፡
ዘና በሚሉበት ሰዓት ሴቶቹ የቮልትዝኮው እስስቶች አረንጓዴ ቀለም ጠቆር ባለ አረንጓዴ ጭረት እና ቀይ ነጥብ በጎናቸው ያሳያሉ፡፡ ጭንቀት ውስጥ ሲገቡ ደግሞ ይህ ጠቆር ያለ አረንጓዴ ጭረት ወደ ጥቁር ቀለም ሲቀየር በጎናቸው በኩልም ሀምራዊ ቀለም ያለው የሰፋ ረጅም ቀለም ያሳያሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ከእነዚህ እና ፈካ ያለ ብርቱካናማ ቀለም ከሚለብሰው ጉሮሮዋቸው በቀር ያለው ሴት የቮልትዝኮው እስስቶች አካል ደግሞ በነጭ ቀለም ይወረሳል፡፡
አሳሾቹ የቮልትዝኮው እስስቶችን ያገኟቸው በካትሰፒ ከተማ አንድ አነስተኛ ሆቴል ውስጥ የሚገኝ ዛፍን ሲወጡ ነው፡፡ የሆቴሉ ባለቤት እንደተናገረው ከሆነ የቮልትዝኮው እስስቶቹ ከጥር አስከ መጋቢት ድረስ ባሉት የከፍተኛ እርጥበት ወቅቶች በአካባቢው በዛ ብለው ይገኛሉ፡፡
አጥኚዎቹ የቮልትዝኮው እስስቶችን በማግኘታቸው ደስ ቢሰኙም ፈርሲፈር ሞኖሰሪስ የተሰኙትን ሌላ የእስስት ዝርያዎችን ማግኘት ሳይቻላቸው ቀርተዋል፡፡ ይህ ዝርያ አንድ ጊዜ ብቻ በአውሮፓውያኑ 1905 ላይ የታየ ሲሆን ከዚያ በኋላ አስካሁንም ድረስ ከሳይንሱ ዓለም ተሰውሮ ይገኛል፡፡
ምንጭ፡ Live Science
በቴክኖሎጂ ዙሪያ የታሰበው አዲሱ የአውሮፓ ህብረት ህግ
*****************************************
የአውሮፓውያን ኮሙሽን የቀረበውን ረቂቅ ህግ ታላላቅ የቴክኖሎጂ ድርጅቶችና ባለሙያዎች የቴክኖሎጂውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ሊጎዳው ይችላል ማለታቸውን CNBC Technology በዘገባው አስነብቧል፡፡ የፊታችን ታህሳስ ይቀርባል የተባለው የዲጂታል አገልግሎት ክዋኔ እንደ ጎግልና ፌስቡክ ባሉ ፕላትፎርሞች የይዘት አስተዳደር ላይ በ2000 ዓመታት ውስጥ ያልታየ ለውጥ ያመጣል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ ህብረቱ የቴክኖሎጂው አለም መሪዎች በፕላትፎርሞቻቸው ይዘት ላይ ከፊት ይልቅ የጸና ሀላፊነት እንዲኖርባቸውና ሌሎች ተወዳዳሪዎች ፍትሀዊ የመወዳደር እድል አግኝተው በገበያ እንዲቆዩ ፍላጎት አለው፡፡
ይወጣሉ ተብለው እየተጠበቁ ያሉት ህጎች በቴክኖሎጂው አጠቃላይ የገበያ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ለውጥ የሚያመጡ እንደሆነ ለCNBC ሀሳቧን ያካፈለችው Thomas Vinje ተናግራለች፡፡ አዳዲሶቹ ህጎች ትልልቅ ፕላትፎርም ያላቸው የዲጂታል አገልግሎቶች በቴክኖሎጂው አለም ባላቸው እንቅስቃሴ ዙሪያ ግልጽነት እንዲኖራቸው ለማድረግ የታሰቡ ናቸው ስትል አክላለች፡፡
የቴክኖሎጂ ተቋማት በሚያሳልፏቸው የተለያዩ ውሳኔዎች ህብረቱ ተሳታፊ እንዲሆንና ተቋማቱ ለጥቅም እንዲውል ባሰቡት እንዲሆም ግልጽ ባወጡትና በደበቁት መረጃ ዙሪያ ተጽእኖ እንዲያሳድር ታስቧል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የማስታወቂያ ወጭዎችን ማን እንደሚሸፍን ማወቅ የሚያስችሉ ህጎችም አብረው ተካትተዋል፡፡ ይህ ለአመታት ያክል በምስጢር ሲንቀሳቀሱ ለነበሩ ተቋማት አስቸጋሪ ህግ መሆኑ የማይቀር ነው፡፡
ባለፉት ቅርብ አመታት የአውሮፓ ህብረት እንደ አማዞን፣ ፌስቡክ፣አፕልና ጎግል ያሉ ካምፓኒዎች የገበያ ውድድርን የተመለከተ ከፍተኛ ጥናት አካሂዶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የጥናቱን ግኝት መሰረት ያደረገ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ አልተቻለም ነበር፡፡ እዚህ ላይ ትልቁ ችግር ህብረቱ የዲጂታል ገበያው ፍትሀዊና ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማድረግ ህጋዊ መብት ያለው መሆኑን አለማረጋገጡ ነው፡፡
ለምሳሌ ጎግል በ2017 የመገበያያ ፕላትፎርሙን ለማስተዋወቅ ከ2.8 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሲያወጣ አብዛኛው ማስፈንጠሪያ ወደራሱ ብቻ የሚያስገባ እንደነበር በጥናት ተረጋግጧል፡፡
የሚወጣው ህግ እንደ አማዞን፣ ፌስቡክ፣አፕልና ጎግል ያሉ ካምፓኒዎችን እንቅስቃሴ መቆጣጠር የሚያስችል እንደሚሆንና ፍትሀዊ የገበያ ውድድር ሊያመጣ እንደሚችል ሀሳባቸውን ለ CNBC Technology የሰጡ የህብረቱ ባለሙያዎች አስረድተዋል፡፡
ምንጭ፡ CNBC Technology
የመጀመሪያው ሳይንቲስት
************************
ሳይንቲስት የሚለው ቃል በእንግሊዝኛ ቋንቋ መዝገበ ቃላት የተካተተው በ1834 ነው፡፡ ይኸውም የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ፈላስፋና የታሪክ ምሁር William Whewell ቃሉን አንድን የተፈጥሮን ባህሪና ውቅር በምልከታና በሙከራ የሚያጠናን አካል ለመግለጽ ከተጠቀመበት ወዲህ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የተለያዩ ክርክሮች ሊነሱ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ እንደ ቻርለስ ዳርዊንና ሚካኤል ፋራዳይ ያሉትን በዊሊያም ዌልስ ዘመን የነበሩትን ልዩ የሳይንስ ሰዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ምንም እንኳን ሳይንቲስት የሚለው ቃል ከ1830 በፊት ባይኖርም የቃሉን መገለጫዎች ግን የሚተገብሩ ሰዎች መኖራቸውን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡
የመጀመሪውን ሳይንቲስት ለማወቅ ወደኋላ እጅግ ርቀን መጓዝ ይኖርብናል፡፡ ይህም ሲባል ወደ ጥንታዊው የግሪክ ስልጣኔ መጀመሪያ ወደ 624 እስከ 545 ከልደተ ክርስቶስ በፊት የማልተሱ ታለስ ዘመን ማለት ነው፡፡ ምንም እንኳን የተመዘገቡ በቂ መረጃዎች ባኖሩም ታለስ በሳይንስና በሒሳብ ዘርፍ ብዙ ግኝቶችን እንዳገኘ ይታመናል፡፡
ሌላም የጥንት ግሪካዊን በዚህ ዙሪያ ማሳታወስ ተገቢ ነው፡፡ በዚህም የጆሜትሪ አባት እየተባለ የሚታወቀውን Euclid እንዲሁም Ptolemy (በጥሊሞስ) የሚባለውን በተሳሳተ አረዳድ መሬት የስርአተ አለም ማእከላዊናት ያለውን የስነፈለክ ሰው መጥቀስ ይቻላል፡፡ ምንም እንኳን እነዚህ ሰዎች ባለምጡቅ እሳቤ ቢሆኑም ሀሳባቸውን ግን ለማረጋገጥ የሄዱበት መንገድ የለም፡፡
አንዳንድ ተመራማሪዎች የዘመናዊ ሳንስ መሰረት ከአውሮፓውን ስልጣኔ በፊት በመካከለኛው ምስራቅ ይሰሩ የነበሩ አረብ ፈላስፎችና የሒሳብ ሊቆች እንደነበሩ ያምናሉ፡፡ በዚህም እንደ al-Khwarizmi, Ibn Sina, al-Biruni and Ibn al-Haytham ያሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ብዙ የዚህ ዘርፍ ተመራማሪዎች በአሁኗ ኢራቅ ከ965 እስከ 1039 የነበረው Ibn al-Haytham የመጀመሪያው ሳይንቲስት እንደሆ ይስማማሉ፡፡ ይህም ሰው ፒነሆል ካሜራን የፈለሰፈ፣ የጽብረቃን ህግ ያጠና እንዲሁም የተለያዩ እንደ ቀስተ ደመና እና ግርዶሽ ያሉ ተፈጥሯዊ ጉዳዮች ላይ ምርምር ያደረገ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ከነ መላጥዮስና በጥሊሞስ የተለየ አካሔድ የተከተለ መሆንና አለመሆኑን ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡
እንደ ጸሀፊው ብሬን ሴልጅ አንድ ዘመናዊ ሳይንቲስት የሙከራን ጥቅም በደንብ የለየ፣ ሒሳብን እንደ መሰረታዊ መሳሪያ የሚጠቀምና መረጃን በፍትሀዊ መንገድ የሚጠቀም መሆን አለበት፡፡ በሌላ አገላለጽ ሳይንቲስት ለመባል በሳይንሳዊ ስራው ላይ ምንም አይነት ሐይማኖታዊ እሳቤን የማይከተል መሆን አለበት፡፡ በዚህ ረገድ በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩት እነ ክርስቲያን ሁይገንስ፣ ሮበርት ሁክ እና አይዛክ ኒውተን አብዛኛውን የሳይንቲስትን መገለጫ የሚያሟሉ ሆነው ይገኛሉ፡፡ ነገርግን ሙሉ የሳይንቲስት ባህሪያትን የሚያሟላ ለማግኘት የግድ ወደ 16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ መምጣት ይኖርብናል፡፡
በዚህ ረገድ ቀድሞ የሚነሳው ጋሊሊዮ ጋሊሊ ሲሆን ጆን ግሪቢን የተባለ ጸሀፊ በ2002 በወጣ "The Scientists" በተባለ መጽሀፉ ምንም እንኩዋን የሚገባውን ያክል እውቅናና ክብር ባይሰጠውም የመጀመሪያው ሳይንቲስት ዊሊያም ጊልበርት እንደሆነ ተናግሯል፡፡ በ1544 ተወልዶ በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ከ1558 እስከ 1569 ትምህርቱን ተከታትሏል፡፡ የመጀመሪያው ሳይንቲስት ያሰኘውም ስራዊ በማግኔት ተፈጥሮ ላይ የሰራው ስራ ነው፡፡ በእንግሊዝም ወሳኝ የሚባል የፊዚካል ሳይንስ መጽሀፍ "On the Magnet, Magnetic Bodies, and the Great Magnet of the Earth" በሚል ርእስ ታትሟል፡፡ ጊልበርት በመጽሀፉ መግቢያ ላይ ከሀሳብ በተጨማሪ የሳይንሳዊ ሙከራን አስፈላጊነት አብራርቶ ጽፏል፡፡
ጋሊሊዮ ጋሊሊም በዊሊያም ጊልበርት አስተሳሰብ ተጽእኖ ስር በመሆኑ የተለያዩ ሙከራዎችን እንዳደረገ ይታመናል፡፡
ምንጭ www.howstuffworks.com
የጆሮ ኩክ ስለ ጭንቀታችን ይናራል
አዲስ የጆሮ ኩክን መሰብሰብያና መተንተኛ መንገድ የጭንቀት ሆርሞን የሆነውን ኮርቲሶል በመመርመር በድባቴ እና ፍርሀት ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን የአዕምሮ ጤና ለመከታተል አዋጪው መንገድ ሊሆን እንደሚችል አዲስ ጥናት ጠቆመ፡፡ ኮርቲሶል አንድ ሰው በሚጨነቅበት ጊዜ የሚጨምር እና በተቀራኒው ጭንቀት ሲቀንስ የእርሱም መጠን የሚቀንስ ወሳኝ የሆርሞን አይነት ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ኮርቲሶል በድባቴ እና ፍርሀት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ላይ በተደጋጋሚ ከፍ የሚል ሲሆን በበሽታ መከላከል ስርዓታችን፣ ደም ግፊት እና ሌሎች የሰውነት ስራዎች ላይም አሉታዊ ውጤት ሊኖረው ይችላል፡፡
ከፍርሀት እና ድባቴ ባሻገርም ከተለመደው ውጪ የሆነ የኮርቲሶል መጠን ከሌሎች የጤና ችግሮች ጋራም ትስስር አለው፡፡ ከነዚህ መካከል ከመጠን ባለፈ የኮርቲሶል ምርት ምክንያት የሚከሰተው ካሺንግ እና በኮርቲሶል ምርት ከሚገባው በላይ ማነስ ምክንያት የሚከሰተው አዲሰን በሽታዎች ይጠቀሳሉ፡፡ በካሺንግ በሽታ የተጠቁ ሰዎች ከተለመደው የተለየ የስብ ክምችት የሚገኝባቸው ሲሆን በሽታን የመከላከል ስርዓታቸውም አቅሙ የወረደ እና አጥንታቸውም የሳሳ (brittle bone) ነው፡፡ በሌላ መልኩ በአዲሰን በሽታ የተጠቁት ደግሞ አደገኛ ሊባል በሚችል መጠን የደም ግፊታቸው የወረደ ነው፡፡
የኮርቲሶል መጠንን ለመለካት የተለያዩ መንገዶችን መጠቀም ይቻላል፤ የምራቅ፣ ደም እንዲሁም ፀጉር ናሙናዎች፡፡ ሆኖም ከደም እና ምራቅ ውስጥ የሚወሰደው ናሙና በአንድ የተወሰነ ጊዜ ውስጥ ብቻ ያለውን የኮርቲሶል መጠን የሚለካ ነው፤ ኮርቲሶል ደግሞ በቀን ውስጥ በተለያዩ ሁኔታዎች ከፍና ዝቅ ሊል ይችላል፡፡ ከፀጉር ላይ የሚወሰደውውም ከቀናት ይልቅ በወራት ውስጥ የታየውን የኮርቲሶል መጠን የሚያሳዩና ለመተንተንም ውድ ናቸው፡፡
በአንፃሩ የጆሮ ኩክ የተረጋጋና የባክቴሪያ ብክለትንም መቋቋም የሚችል በመሆኑ በቀላሉ ወደ ቤተ-ሙከራ በመውሰድ ትንተናን መስራት ያስችላል፡፡ በተጨማሪም ከሳምንት በላይ ላለ ጊዜ ያለውን የኮርቲሶል መጠን መዝግቦም ማስቀመጥ ይችላል፡፡ ሆኖም ቀድሞ ይህን የጆሮ ኩክ ለማውጣት ጥቅም ላይ ይውል የነበረው መንገድ የህክምና መርፌን ወደ ጆሮ በመክተት እና ወደ ውስጥ ከተከተተው ውሃ ጋራ አንድ ላይ አድርጎ መጦ በማውጣት ነበር፡፡ ይህም የተወሰነም ቢሆን ህመም ያለውና በራሱም ጭንቀትን የሚፈጥር ነበር፡፡ ይህን መንገድ በመቀየር ተመራማሪዎች ከኩክ ማውጫ ያልበለጠ ስሜት የሚፈጥር መጥረጊያ ወይም ስዋብ መስራት ችለዋል፡፡ በተጨማሪም ስዋቡ በመያዣው በኩል ጋሻ መሰል ነገር ያለው በመሆኑ ሰዎች ወደ ጆሮዋቸው ከሚፈለገው በላይ በጥልቀት ከተውት ታምቡራቸውን እንዳይጎዱ ይጠብቃቸዋል፡፡ ጫፉ ላይ ያለው ስፖንጅ ደግሞ ኮኩን ለመሰብሰብ ይችላል፡፡
አጥኒዎች ባከናወኑት አነስተኛ ጥናት በሁለት የተለያዩ ጊዜያት ከ37 ተሳታፊዎች ላይ የደም፣ ፀጉር እና የጆሮ ኩክ ናሙናዎችን ወስደው ነበር፡፡ በየእያንዳንዱ የስብሰባ ወቅት በአንዱ ጆሮ ያለውን ኩክ የህክም መርፌን በሌላው በኩል ያለውን ደግሞ ስዋቡን በመጠቀም ሰብስበዋል፡፡ በመቀጠልም በሁለቱ መካከል ያለውን የኮርቲሶል ልኬት መጠን አነፃፅረዋል፡፡
በውጤቱም ኮርቲሶል ከፀጉር ይልቅ በጆሮ ኩክ ውስጥ ይበልጥ እንደሚገኝና ለትንተናም ቀላል እንደሚሆን ማረጋገጥ ችለዋል፡፡ በስዋብ አማካኝነት የሚገኘውን ኮርቲሶልን መተንተንም ከህክምና መርፌው አንፃር ፈጣን እና አዋጭ እንደሆነ አረጋግጠዋል፡፡ በመጨረሻም የጆሮ ኩክ እንደ አልኮል ባሉ ነገሮች ሳብያ ተለዋዋጭነት ካላቸው ከሌሎቹ መንገዶች አንፃር በውስጡ በያዘው የኮርቲሶል መጠን የማይለዋወጥ እና የተረጋጋ ሆኖ አግኝተውታል፡፡ ተሳታፊዎቹም ከህክምና መርፌው ስዋቡ ምቾት እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል፡፡
ምንጭ፡ Live Science
የሳል ድምፅን በመስማት ብቻ ኮቪድ-19ን መለየት ተቻለ
==========================
ከወራት በፊት፤ ኮቪድን እንደአሁን ብዙም ሳናውቀው እና ሳንደፋፈረው ድንገት ሳል ያሳለን አልያም ሌላ ሰው ሲያስል የሰማን እንደሆን ኮቪድ-19 ነው? ወይስ አይደለም? የሚለው የጭንቀት ጥርጣሬ በብዙዎቻችን ዘንድ ነበር፡፡ ታድያ በአሜሪካኑ የማሳቹሴት ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ የሚገኙ የሳይንስ ተመራማሪዎች የዚህን ሳል ድምፅ በመስማት ብቻ ምንጩ ኮቪድ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ጥያቄ የሚመልስ አዲስ አልጎሪዝምን ሰርተዋል፡፡ ተመራማሪዎቹ በአሁኑ ሰዓት ይህን በሰው ሰራሽ አስተውሎት አማካኝነት የሚሰራ ምርምር ሙከራ እያደረጉበት ሲሆን በአሜሪካን የምግብ እና መድሃኒት አስተዳደር (FDA) ፍቃድ የማግኘት ሂደቱንም አስጀምረውታል፡፡
አልጎሪዝሙ ከዚህ ቀደም በተሰራው የሳንባ ምች፣ አስም እና አልዛይመርን እንዲለይ ተደርጎ በተሰራ ሞዴል ላይ መሰረቱን በማድረግ ነው፡፡ እኛ ሰው አቀላጥፎ መናገር ሲጀምር ብቻ የምንረዳቸውን ነገሮች ሰው ሰራሽ አስተውሎት ግን በሳል ብቻ ይረዳቸዋል ሲሉ የምርምር ቡድኑ አካል ብራያን ሰቢራና በዚህ ላይ በመመስረት ብቻ የሰውን ፆታ፣ አፍ መፍቻ ቋንቋ ወይም ስሜት መረዳት መቻሉን በምሳሌነት በመጥቀስ ያስረዳሉ፡፡
በመጀመሪያ ተመራማሪዎቹ የተለያዩ በጎ ፈቃደኛ ተሳታፊዎች የእጅ ስልክ እና ኮምፒውተራቸውን በመጠቀም የቀዱትን የሳል ድምፅ የሚልኩበት ድረ-ገፅ ፈጠሩ፤ በተጨማሪም የበሽታው ምልክት እያሳዩ እንደሆን መረጃ የሚወስድ መጠይቅ ለተሳታፊዎቹ አቅርበዋል፡፡ በድረ-ገፁ አማካኝነት ከ70 ሺህ በላይ ሰዎች በግድ የተሳሉ ሳሎችን ድምፅ መብሰብ ችለዋል፡፡ ከነዚህ ሰዎች ውስጥ 2,660ቱ የበሽታው ምልክት የሚታይባቸው እንዲሁም የማይታይ የኮቪድ-19 ራማሚዎች ናቸው፡፡ በመቀጠልም 4,256 ናሙናዎችን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ስርዓቱን ለማሰልጠን የተጠቀሙበት ሲሆን 1,064 ናሙናዎችን ደግሞ በጤነኛና በኮቪድ-19 በተጠቁ ሰዎች መካከል ያለውን ልዩነት ማሳየት ይችል እንደሆን ሞክረውበታል፡፡
በውጤቱ ስርዓቱ ከኮቪድ ጋራ ትሰስር ባላቸው አራት የሳል መሰረታዊ ገፅታዎች፤ ማለትም የጡንቻ መኮሰስ፣ የድምፅ አውታሮች መጠንከር፣ እንደ መሰላቸት እና እርግጠኛ አለመሆን ያሉ ስሜቶችን እንዲሁም የአተነፋፈስ እና ሳንባ ብቃት ላይ በመመስረት ልዩነቶችን ማስተዋል ችሏል፡፡ በዚህም መሰረት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ሞዴሉ 98.5 በመቶ የሚሆኑትን የኮቪድ-19 ተጠቂዎች በስኬት ማወቅ ሲችል ካልተያዙት ውስጥ ደግሞ 94.2 በመቶውን መለየት ችሏል፡፡ ስርአቱ ምንም አይነት የበሽታው ምልክት ከማይታይባቸው ውስጥ ደግሞ ኮቪድ-19 ያለባቸውን ሰዎች መቶ በመቶ መለየት ሲችል ከሌለባቸው ውስጥ ደግሞ 83.2 በመቶውን ለይቶ አውጥቷቸዋል፡፡
ይህ በተራማሪዎቹ ዘንድ እንደስኬት የሚታይ አስደሳች ውጤት ቢሆንም በተለያዩ የዕድሜና ዘር ቡድኖች ላይ ውጤታማ እንዲሆን ተጨማሪ ጥናት መደረግ እንዳለበት ከባለሙያዎች የተሰጠ አስተያየት ይጠቁማል፡፡
በአሁኑ ሰዓት የኮቪድ-19 ተጠቂዎችን በድምፅ የመለየቱን ስራ እየሞከረ ያለው ይህ ጥናት ብቻ አይደለም፤ ሌላ በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ እየተሰራ ያለ ጥናትም በተመሳሳይ መንገድ የቫይረሱ ተጠቂዎችን የሚለይ ስራን በመስራት ላይ ነው፡፡
ምንጭ፡ Live Science