TechIn2
1.22K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
መሬት ስበት ህግ በቅንጣቶች (atoms)
**********************************
በፊዚክስ ታሪክ ውስጥ ከሚነገሩ የምርምር ስራዎች የጣሊያናዊው ጋሊሊዮ ጋሊሊ የመሬት ስበት ሙከራ አንዱ ነው፡፡ እነደሚታወቀው ጋሊሊዮ ከተወሰነ ከፍታ ላይ የተለያየ ክብደት ያላቸውን ነገሮች ወደታች እኩል በመልቀቅ ሁለቱም በእኩል ሰዓት መሬት ላይ በመድረሳቸው የመሬት ስበት ሀይል ተመሳሳይ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ተመራማሪዎች ይህ የጋሊሊዮ የምርምር ውጤት የሆነው የመሬት ስበት ህግ በቅንጣቶች (atoms) መስራትና አለመስራቱን ለማረጋገጥ የተለያዩ ሙከራዎችን ሲደርጉ ቆይተዋል፡፡
አዲስ በተሰራው ጥናት በጣም አስቸጋሪ የሆነው ቅንጣቶችን ከእኩል ከፍታ ወደ መሬት የመልቀቅ ሙከራ ከጋሊሊዮ ሙከራ ጋር ተመሳሳይ ውጤት አሳይቷል፡፡ የተለያዩ ቅንጣቶች በመሬት ስበት ምክንያት ከላይ ወደ ታች በተመሳሳይ ፍጥነት (acceleration) ተንቀሳቅሰዋል፡፡
ተመራማሪዎች የሩቢዲየም (rubidium) ቅንጣትን ሁለት የተለያዩ ክፍሎች (isotopes) አወዳድረዋል፡፡ እነዚህ ክፍሎች በማዕከላዊ ክፍላቸው (nuclei) የተለያየ የኒውትሮን ቁጥር ያላቸው ናቸው፡፡ ሙከራውን 8.6 ሜትር ከፍታ ካለው ቱቦ ውስጥ የተሰራ ሲሆን ሁለቱ ክፍሎች (isotopes) ከመነሻቸው እስከ መድረሻቸው ተመሳሳይ እንቅስቃሴ አሳይተዋል፡፡
ይህ ግንኝት ከአልበርት አንስታይን general relativity እሳቤ ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ በስበት ህግ የአንድ ነገር የእንቅስቃሴ ፍጥነት በነገሩ መጠነቁስ ወይም ውቅር (composition) አይወሰንም፡፡
ምንጭ Sciences News Magazine
ለውድ ተከታታይ ቤተሰቦቻችን በሙሉ፤ እንኳን 1 ሺህ 495ኛው የነብዩ ሙሐመድ መውሊድ በዓል አደረሳችሁ፡፡
መልካም በዓል ይሆንላችሁ ዘንድ ምኞታችን ነው!!!
ሰዎች የኮሮናቫይረስን ቢያንስ ለ5 ወራት የመቋቋም አቅም ይኖራቸዋል፡ ጥናት
የሰው ልጆች በሽታ የመከላከል ስርዓት ማንኛውም የውጭ ጠላት (ቫይረስ) ወደሰውነት ሲገባ በሽታውን ሊቋቋምና ሊከላከል የሚችል አንቲቦዲ ማዘጋጀት ይጀምራል፡፡ በዚህ የዝግጅት ሂደት ሰውነታችን በሽታ አምጪ ተህዋሲው አደጋ የሚያመጣ መሆኑን ለይቶ የመከላከያ ውህዶችን እስከሚያመርት ድረስ ብዙ ደረጃዎችን የሚያልፍ ቢሆንም ፕሮቲኑ አንዴ ተመርቶ ስራውን ከጀመረ በኋላ ለረዥም ጊዚያት ተህዋሲውን የመለየት አቅሙ ከፍተኛ አንደሚሆን ባለሙያውች ይናገራሉ፡፡
ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ይህ የኢሚዩኒቲ ጉዳይ ለብዙ ጊዚያት ክርክሮች ሲያስነሳ እና የተለያዩ ግኝቶች ሲንፀባረቁበት መቆየቱ የሚታወቅ ሲሆን ከሰሞኑም በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረቱን ያደረገ አንድ ጥናት አዲስ ውጤት ማግኘቱን ይፋ አድርጓል፡፡ በማውንት ሳናይ የኣይካን ሜዲሰን ትምህርት ቤት ይፋ የተደረገው ይህ አዲስ ጥናት 90 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ከኮሮናቫይረስ ካገገሙ በኋላ በሽታ የመከላከል ስርዓታቸው፤ ቫይረሱን ለይቶ አንቲቦዲ የማምረት አቅሙ እና ቆይታው ከአምስት ወራት እንደሚሻገር ያሳየ ነው፡፡
የጥናት ቡድኑ በምርምሩ ሂደት ላይ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ከ30,000 ሰዎች በላይ ማሳተፍ የቻለ ሲሆን የተሰታፊዎቹን የአንቲቦዲ ምላሽም በሚገባ ለማየት ሞክሯል፡፡ አጥኝዎቹ በዚህ ምርምር ላይ የተሳታፊዎቹን የአንቲቦዲ ምላሽ በዝቅተኛ፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ መመዘኛዎች ከፋፍለው ያስቀመጡ ሲሆን፤ በግኝታቸው መሰረትም 90 በመቶ የሚሆኑት የጥናቱ ተሳታፊዎች በመካከለኛ እና ከፍተኛ የአንቲቦዲ ምላሽ ውስጥ መገኘታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ የጥናት ቡድኑ ከተሳታፊዎቹ መካከል 121 ታካሚዎችን መርጠው በቅርበት ለመከታተል እንደሞከሩትም የተሳታፊዎች የአንቲቦዲ ምላሽ ከሶስትና ከአምስት ወራት በኋላም ተመሳሳይ የመለየት እና የመከላከል እቅም እንደነበረው ለማረጋገጥ ችለዋል፡፡
በኣይካን የሜዲሰን ትምህርት ቤት የቫክሲኖሎጂ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ፍሎሪያን ክራመር እንደሚያስረዱት ከዚህ በፊት የተሰሩ ጥናቶች የአንቲቦዲ ምላሽ ለአጭር ጊዜያት የሚቆይ መሆኑን የጠቆሙ ቢሆንም በኛ ጥናት መሰረት ግን በቫይረሱ ክፉኛ ያልተጎዱ እና ቀላል ምልክት የታየባቸው ከ90% በላይ ሰዎች ቫይረሱን ለአምስት ወራት የመለየትና የመከላለከል አቅም እንዳላቸው ተረድናል ብለዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ በቫይረሱ ዳግመኛ የመያዝ ሁኔታ (reinfection) አስመልከተው እንደሚናገሩት ይህ ግኘት በቫይረሱ ዳግመኛ የመያዝ ሁኔታን ሙሉ ለሙሉ ከስጋት ውጭ ያደርገዋል ባንልም የክስተቱ መጠን ግን እጅግ ያነሰ መሆኑ ያመላከታል ብለዋል፡፡ ምንጭ፡ CNN
ይህንን ያውቁት ይሆን
******************
ነገሮችን በምልክት መግለጽ የሰው ልጅ ቋንቋን መጠቀም ለመጀመሩ እንደ መነሻ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ምንም እንኳን ቋንቋ በአሁኑ ወቅት ሙሉ የሚባል የእድገት ደረጃ ላይ ቢደርስም ዛሬም ድረስ በምልክት የምንገልጻቸው ልዩ ልዩ ስሜቶች አሉን፡፡ ለምሳሌ የረሀብና ድካም ስሜቶችን በማፏሸግ (ቅጽበታዊ የሆነ አፍ መክፈት) እንገልጻለን፡፡ ለመሆኑ አንድ ሰው አንድን ነገር ለማስታወስ ሲጥር ራሱን ለምን ይዳብሳል?
አንዳንድ ሰዎች አንድን ነገር ለማስታወስ ስንጥር ራስን የመዳበስ ድርጊት ከጥንት ጀምሮ የመጣ ልማድ ነው ብለው ያስባሉ፡፡ ይህም ተፈጥሯዊ የሆነ ከቀወድመ አያቶቻችን የወረስነው ስሜትን የመግለጫ መንገድ ነው ይላሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በጭንቀት ውስጥ ስንሆን አእምሯችን እንደ ግንባርን ማሸት፣ ከንፈርን መንከስ፣ የእጅ ማላብ የመሳሰሉ ቅጽበታዊ ክስተቶች እንዲኖሩ ያደርጋል፡፡ ራስን ማሸትም (ማከክ) የዚሁ የአእምሯችን ቅጽበታዊ የመጨነቅ ውጤት ነው የሚል መረጃ በ2009 በPsychology Today የወጣ ጆ ናቫሮ የተባለ የ FBI አባል የጻፈው ጽሁፍ ያመለክታል ፡፡
የቅርብ ጊዜ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ደግሞ ይህ አይነት የእጅ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ፍርሀትና ጭንቀት ጊዜ እንደሚፈጠር ያመለክታሉ፡፡ ለምሳሌ በ2017 በተሰራ አንድ ጥናት በአስጨናቂ ነገር ፊትለፊት ያለ አንድ ሰው ራሱን በመዳበስ መፍራቱንና ምንም አማራጭ እንደሌለው በአእምሮው ቅጽበታዊ መልስ ይሰጥበታል፡፡ ይህን በምሳሌ ለማሳየት አንድ ዝንጀሮ በጉልበት ከሚያሸንፈው እና እጅግ ከሚፈራው ሌላ ትልቅ ዝንጀሮ ፊት ሲቀርብ ራሱን የሚያሽ ከሆነ አሸናፊው ዝንጀሮ ይራራለታል፤ ጉዳትም አያደርስበትም ማለት ነው፡፡
ምንጭ www.howstuffworks.com
አስደናቂው የሸንኮራ አገዳ… የቀጠለ
****************************
በክፍል አንድ ጽሁፋችን የሸንኮራ አገዳ ጭማቂ ለጤና ያለውን ከፍተኛ ጥቅም በጥቂቱ ለማብራራት ሞክረናል፡፡ በክፍል ሁለት ጽሁፋችን የሸንኮራ አገዳ ጭማቂ ያለውን ከሐይል አማራጭ ጋር የተያያዘ ጥቅምን እናስነብባችኋለን፡፡ ከዚህ አንጻር የመጀመሪያ አድርገን ልናቀርብላችሁ የወደድነው ስለ ኢታኖል ነው፡፡
ይህ በብዛት ከስኳር ፋብሪካዎች ተረፈምርት ሆኖ የምናገኘው አማራጭ የሀይል ምንጭ ሆኖ የሚገለግል ምርት ነው፡፡ በተለይ በብራዚል በብዛት ለመኪኖች አገልግሎት ላይ ይውላል፡፡ ምናልባትም ከገበታ ስኳር በበለጠ የመጀመሪያ ምርት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ እንደሚታወቀው ስኳር በሸንኮራ አገዳ ወይም በስኳር ድንች ዋና ግብአትነት የሚዘጋጅ በየእለቱ ከሚያስፈልጉን ምርቶች መካከል አንዱ ነው፡፡
ከሸንኮራ አገዳ የሚገኘው የኢታኖል ምርት ከበቆሎ፣ ከስኳር ድንች እና ከፓልም ዘይት ከሚገኘው ይልቅ በምርት ጊዜ አነስተኛ ሀይል ይጠቀማል፡፡ እንዲሁም ከመደበኛው ጋዝ በ90% ያነሰ የካርቦንዳይ ኦክሳይድ ልቀት አለው፡፡
በብራዚል በየአመቱ 75 ቶን የሚሆን ሸንኮራ አገዳ በሔክታር ይመረታል፡፡ አንድ ሔክታር ሸንኮራ አገዳ 4000 ሊትር ኢታኖል በየአመቱ ይመረታል፡፡
ሌላው በሸንኮራ አገዳ ምርት ልናገኝ የምንችለው ጥቅም የኤሌክትሪክ ሐይል ነው፡፡ ይህም የሚሆነው ሸንኮራ አገዳው በሚቃጠልበት ጊዜ የሚገኝ ትነት (steam) ወደ ኤልክትሪክ ሐይልነት የሚቀየር ነው፡፡ አሁን ባለ ሂደትም ከአንድ ቶን ሸንኮራ አገዳ 100 kWh ኤሌክትሪክ ይመረታል፡፡ በዚህም በአመት በአለማችን ከሚመረተው ከ1 ቢሊዮን ቶን በላ ሸንኮራ አገዳ እስከ 100,000 GWh የኤሌክትሪክ ሐይል ሊመረት ይችላል፡፡
ምንጭ www.livestrong.com እና www.organicfacts
በአንድ ቀን ብቻ ለግማሽ ህዝቧ የኮቪድ ምርመራ ያደረገቸው ሃገር
በምስራቅ አውሮፓ የምትገኘው ስሎቫኪያ ከአጠቃላይ ህዝቧ ግማሽ የሚያህለውን የኮሮናቫይረስ ምርመራ በማድረግ አዲስ ሪከርድ አስመዝግባለች፡፡ 5.5 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ያላት ይህች አውሮፓዊት አገር ቅዳሜ ዕለት ባደረገችው ሀገርአቀፍ የኮሮናቫይረስ የምርመራ ዘመቻ 2.58 ሚሊዮን የሚጠጋ ሰዎችን በአንድ ቀን መመርመር ችላለች፡፡
የሃገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር ጃራሶልቭ ናድ አንደገለፁት በዕለቱ በተደረገው ሃገርአቀፍ የኮቪድ ምርመራ ከ10 አመት በታች ካሉ ህፃናት ውጭ ሁሉም የሃገሪቱ ዜጋ በምርመራው እንደተሳተፈ ተናግረዋል፡፡ ሚኒስትሩ እንዳስረዱት አጠቃላይ ምርመራ ከተደረገላቸው የሃገሪቱ ዜጎች መካከል 25,850 ወይም 1% የሚሆኑት ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን፤ በሃገሪቱ የጤና አሰራር መሰረትም የለይቶ ማቆያ ሂደት እንደሚጀምሩ ተናግረዋል፡፡
በዚህ ሃገርአቀፍ የምርመራ ሂደት ከ40,000 በላይ የጤና ባለሙያዎች ሲሳተፉ ሌሎች ድጋፍ የሚሰጡ ፖሊሶች፣ ወታደሮች እና የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰጪዎችም 5,000 በሚጠጋው የመመርመሪያ ጣቢያ ዜጎችን ሲያስተናግዱ እንደነበር ተገልጿል፡፡ የምርመራ ሂደቱ በፍቃደኝነት እና ከክፍያ ነፃ በሆነ መልኩ የተከናወነ ቢሆንም ምርመራውን ላላደረጉ ሰዎች በቤት የመቀመጥ እገዳ እንደሚጣልባቸው የሃገሪቱ መንግስት አስታውቆ ነበር፡፡
ስሎቫኪያ ያደረገቸው የአንድ ቀን የዜጎች ምርመራ ከላብራቶሪ ውጭ የሚከናወን የሞሎኪውላር PCR ወይም በአፍንጫ በኩል የሚደረግ የስዋብ (swab) ምርመራ ሲሆን፤ አንዳንድ የዘርፉ ባለሙያዎች ግን ይህ የምርመራ ሂደት ትክክለኛ ውጤት እንደማያሳይ ሲገልፁ ተስተውሏል፡፡
The Guardian
መረጃን ከብርሀን በተሸለ ፍጥነት ማስተላለፍ ይቻል ይሆን?
*********************************************************
ከአንስታይን Special Relativity እሳቤዎች አንዱ ብርሃን በወና ውስጥ ካለው ፍጥነት ሊፈጥን የሚችል ምንም ነገር የለም የሚል ነው፡፡ በዚህም እሳቤ መሰረት የብርሀን ፍጥነት አጠቃላይ የፍጥነት ልክ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ በሳይንስ ጠንካራና አይነኬ የሚባል ህግ ማስቀመጥ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ይህ የሚሆን ከሆነ ምርምር የሚለው ሀሳብ ትርጉም ሊያጣ ይችላል፡፡ ዝርዝሩን ለማንበብ ሊንኩን ይጫኑ
ብርሃን በወና ውስጥ በአማካኝ 299,792 ኪሎ ሜትሮች ያክል በሴኮንድ ይጓዛል፡፡ በ2011 Oscillation የሚባል ፕሮጀክት የሚሰሩ የፊዚክስ ተመራማሪዎች neutrinos የተባሉ ከፊል ቅንጣቶችን (subatomic particles) ከሲውዘርላንዱ የአውሮፓ የኑክሌር ምርምር ተቋም ወደ ጣልያኑ ግራን ሳሶ ብሔራዊ ቤተ ሙከራ ከብርሃን በ60 ናኖ ሴኮንዶች ቀድሞ መላክ ችለዋል፡፡ ይህ እንዴት ሊከሰት እንደቻለ ምርምር ሲያደርጉ የነበሩ ተመራማሪዎች ከገመድ ጋር የተያያዘ ችግር ወይም ስህተት በመኖሩ ምክንያት እንጂ የአንስታይንን ህግ ሊያሻሽል የሚችል ግኝት እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የአለማችን መረጃ የሚተላለፈው በኮፐር ገመድ ወይም በፋይበር ኦፕቲክ ገመድ ነው፡፡ ከነዚህም የተሸለ ፍጥነት ያለው ሁለተኛው ነው፡፡ በብርሀን ጉዞ ውስጥ ወና የሚለው ሃሳብ መሰረታዊ ሀሳብ ነው፡፡ ብርሃን በወና ውስጥ ሲጓዝና በገመድ ውስጥ ሲጓዝ ፍጥነቱ ተመሳሳይ አይደለም፡፡ ብርሀን በምንም ነገር ውስጥ ቢጓዝ በወና ውስጥ እንደሚያደርገው ጉዞ ፈጣን ሊሆን አይችልም፡፡
የብርሀን ሁለት አይነት ተፈጥሮ በተለያዩ ነገሮች ውስጥ ሲጓዝ ፍጥነቱ እንዲለያይ አድርገውታል፡፡ እነዚህም የሞገድና የቅንጣቶች ባህሪ ናቸው፡፡ ብርሃን photons የሚባሉ ቅንጣቶች ስሪት በመሆኑ በገመድ ውስጥ በቀጥታ መጓዝ አይችልም፡፡ photons ከገመዱ ሞሎኪዩሎች ጋር ሲጋጩ አቅጣጫቸውን ይቀያይራሉ፡፡
Fiber optic የሚባለው የገመድ አይነት ከኮፐር ገመድ በጣም የተሻለ ፍጥነት ሲኖረው ከኤሌክትሮ መግነጢሳዊ ጣልቃ ገብነት የጸዳ ነው፡፡ ፋይበር በሴኮንድ በመቶወች የሚቆጠር ጌጋ መረጃን እንዳንዴም በቴራባይት የሚለካ መረጃን ማስተላለፍ ይችላል፡፡ የቤት ውስጥ የኢንተርኔት አገልግሎቶች ይህ የላቀ ፍጥነት የላቸውም፡፡
በ National Institute of Standards and Technology (NIST) የሚሰሩ ተመራማሪዎች ኳንተም መጠን ያለው መረጃን ከብርሀን በተሻለ ፍጥነት ለማስተላለፍ እየሰሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በሙከራቸውም ከ50 እስከ 90 ናኖ ሴኮንድ ከብርሃን የተሸለ ፍጥነት መመዝገብ ችለዋል፡፡ ይህ ምንም እንኳን በወና ውስጥ ቢሆንም ትርጉም ያለው መረጃ ግን አይደለም፡፡ በዚህ ዘርፍ ያለው ሌላው የምርምር መንገድ quantum teleportation ይባላል፡፡
ከላይ ለተነሳንበት ጥያቄ አሁናዊ መልስ ትርጉም ያለው መረጃ ከብርሀን በተሻለ ፍጥነት ሊጓዝ አይችልም ነው፡፡ አንድ ትርጉም ያለው መረጃ ከብርሃን በተሻለ ፍጥነት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማስተላለፍ ከተቻለ ለወደፊቱ የመረጃ አለም ትልቅ ለውጥ ማምጣቱ የማይቀር ነው፡፡ ይህም ከፍተኛ ጥራት ያለው የቴሌቪዥን ፕሮግራም ለመከታተልና ልዩ ልዩ ድረ- ገጾችን በፍጥነት ለመክፈት ያስችላል፡፡
ምንጭ፡ www.howstuffworks.com
የጭንቀት በሽታ መገኛው ይታወቅ ይሆን
ከእውቀት አንጻር ሲታይ, ጭንቀት በጣም አስፈላጊ የአዕምሮ ሁኔታ ነው፤ ነገር ግን ከቁጥጥር ውጪ ሲሆን የድባቴ (ድብርት) ስሜት ውስጥ በማስገባት የመገለል ስሜትን ይፈጥራል፡፡ አሁን ላይ ያሉት ፀረ-ጭንቀት መድሃኒቶች ደግሞ አንዳንድ አሉታዊ የጎንዮሽ ጉዳቶች ይመጣሉ፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ ተመራማሪዎች አንድ መላ ያገኙ ይመስላል፡፡ በማክስ ፕላን ኢንስትቲዩት የህክምና ሙከራ ተመራማሪዎች ይህን የጭንቀት በሽታ ለመከላከል ዋናው እና ቁልፍ የሆነውን በአንገጎላችን ውስጥ የሚገኘውን ፕሮቲን ለይተው አግኝተውታል፡፡
አንጎላችን እጅግ ውስብስብ አካል ሲሆን ጭንቀትን የሚፈጥረው ችግር በርግጠኝነት የትኛው የአንጎላችን ክፍል እንደሆነ ማወቅ አይቻልም፡፡ ነገርግን አሚግዳላ (amygdala) ችግሩ የሚከሰትበት የአንጎላችን ክፍል እንደሆነ ይታመናል፡፡ አሚግዳላ በአንጎላችን ውስጥ የሚገኝ ክፍል ሲሆን እንደ ጭንቀት እና ፍርሀት ያሉትን ስሜቶች የሚሰተናገዱበት የአዕምሮ ክፍል ነው፡፡ ከልክ ያለፈ የአሚግዳላ እንቅስቃሴ የጭንቀት መዛባትን (anxiety disorder) ያመጣል፡፡
አሁን ላይ ያሉት የጭንቀት መድሀነኒቶች በተለይም ደግሞ ቤንዞዲያስፒን በዋናነት አሚግዳላ ኢላማ አድርጎ የሚሰራ መድሀኒት ሲሆን ተግባሩም በአሚግዳላ አካባቢ ያሉ የነርቭ እንቅስቃሴዎችን በመቀነስ በጭንቀት ወይም በፍርሀት ውስጥ ያለን ሰው እንዲረጋጋ ያደርጋል፡፡ ይሁንና እንደዚህ ያሉ መድሀኒቶች በሚወሰዱበት ጊዜ ሌላ የጎንዮሽ ጉዳት እንደ ከፍተኛ የሆነ እንቅልፍ እና የትኩረት ማጣት ያስከትላሉ፡፡
በሆኑም እንዚህን የጎንዮሽ ችግር ለመቅረፍ እና ውጤታማ የሆነ የጭንቀት መደሀኒት ለመስራት የማክስ ፕላን ኢንስትቲዩት ተመራማሪዎች IgSF9b የተባለ በአንጎላችን ውስጥ የሚገኝ ፕሮቲን አግኝተዋል፡፡ የዚህ ፕሮቲን ተግባር በአጋጅ ሲናፕሲስ መካከል የሚገኘውን ክፈተት መሙላት ሲሆን ከዚህ ባለፈም ለአእምሮ ስጋት የሆኑ ተግባራትን በማገድ የጭንቀት መዛባትን መከላከል የሚያስችል ፕሮቲን ነው፡፡ ይህን የምርምር ውጤት በቤተ ሙከራ አይጥ ላይ በመሞከር ውጤታማነቱን ማረጋገጥ መቻሉን የሚያስረዱት ተመራማሪዎች የፕትሮቲን ተለይቶ መታወቁ የጭንቀት መዛባትን ለመቅረፍ በእጅጉ እንደሚረዳ ይናገራሉ፡፡
ምንጭ፡ Medicalxpress
TechIn2 pinned a file
በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዙሪያ ያለው የማህበረሰባችን ግንዛቤ/Perception/፤ በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት በቅርቡ ይፋ የተደረገ ሀገራዊ የዳሰሳ ጥናት
====================
ለአንድ ሀገር እድገት የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን አስተዋፆ ጉዳይ አጠያያቂ አይሆን ዘንድ ማህበረሰቡ በጉዳዩ ላይ ያለው ግንዛቤ (perception) እጅግ ወሳኝ ይሆናል፡፡ መንግስትን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት በዘርፉ ሚናቸውን በሚገባ እንዲወጡም ከፖሊሲ ቀረፃ ጀምሮ ማህበረሰቡ ያለበትን የግንዛቤ ደረጃ ማወቅና መገንዘብ ተገቢና ቀዳሚው ተግባር ሊሆን ይገባዋል፡፡
ምናልባትም ማህበረሰባችን ለሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ያለው ምልከታ እምብዛም ነው ብለው ያስቡ ይሆን?
የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስትቲዩት (TechIn) አስር-ሺህ (10,000) ከሚጠጉ የማህበረሰባችን ክፍሎች በጉዳዩ ላይ መረጃዎችን በሳይንሳዊ መንገድ በመሰብሰብ ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገራዊ የዳሰሳ ጥናት በማድረግ በቅርቡ ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል፡፡ ጥናቱ በአጠቃላይ ማህበረሰባችን በሳይንስ፣ ቴክኖሎጅና ኢኖቬሽን ጉዳዮች ዙሪያ ያለውን የግንዛቤ (awareness)፣ የእውቀት (knowledge)፣ የፍላጎት (interest) እና አመለካከት (attitude) ደረጃ ያሳየ ሲሆን በተጨማሪም የመረጃ ምንጮቻቸውን ይዳስሳል፡፡
ሪፖርቱ እንሚያሳየው ማህበረሰባችን ለሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ያለው ፍላጎት እና አመለካከት ከእውቀት እና ግንዛቤ አኳያ ሲታይ የተሻለና ጥሩ ደረጃ ላይ እንደሆነ ያመለክታል፡፡
በሌላ በኩል (ከጥናቱ እንደሚጠበቀው) ከገጠር ይልቅ የከተማው፤ ከሴቶች ይልቅ የወንዶች እንዲሁም በተሻለ የትምህርት ደረጃ ላይ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች በአንፃራዊነት በአማካይ የተሻሉ መሆናቸውን በሪፖርቱ ተዳሷል፡፡
በአጠቃላይ በጥናቱ ሰፊ ጉዳዮች ላይ ዳሰሳ የተካሄደ ሲሆን ከአስገራሚ ግኝቶችም መካከል አንዱ የግብርና ጉዳዮችን በተመለከተ የታየ ግኝት ነው ይህም ከነዚህም ውስጥ የትምህርት ደረጃ ሲጨምር ለዘርፋ (ማለትም ለግብርናው ዘርፍ) የሚኖር ፍላጎት (interest) በመጠኑም ቢሆን እንደሚቀንስ የሚያሳይ እንደሆነ ያመላክታል፡፡ ይህም ግብርናችንን በተማረ የሰው ኃይል ለመምራት፣ ለማሳለጥና ለማዘመን ለሚደረገው ከፍተኛ ጥረት ትልቅ ማነቆ መሆኑን በማመላከት ጥናቱ የመፍትሄ ሃሳብ ጠቆም ያደርጋል፡፡
ሌሎች በርካታ የጥናቱን ዉጤቶች ከላይ በተቀመጠው PDF ፋይል አማካኝነት ከሪፖርቱ ትመለከቱ ዘንድ እንጋብዛለን፡፡
የሰውነት በሽታ መከላከል ብቃት እና የአፍ እጥበት
***********************************************
በአሁኑ ወቅት ንጽህና የአለማችን ትልቁ መርህ እየሆነ ይገኛል፡፡ ይህም በእያንዳንዱ ቅጽበት ለንጽህናችን ጥንቃቄ ማድረግ እንዲኖርብን ያደርገናል፡፡ ንጽህናን መጠበቅ የባክቴሪንና የቫይረስን መስፋፋት ለማስቆምና ጤናችንን ለመጠበቅ እጅግ ትልቅ ጥቅም አለው፡፡ ለዚህም ማሳያ እንዲሆን እጅን መታጠብ ከብዙ ተላላፊ በሽታዎች የሚጠብቅ መሆኑን ማስታወስ ይቻላል፡፡
ንጽህናን መጠበቅ ያለው ጥቅም ምንም ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነገር አይደለም፡፡ በአንጻሩ ግን በተለይ የአፍ ጤናን ለመጠበቅ ብለን ጥርሳችንን ከሚገባው በላይ የምንታጠብ ከሆነ በሽታ የመከላከል አቅማችንን ልንጎዳው እንችላለን ብለው የሚያስቡ ተመራማሪዎችን ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ እንደነዚህ ተመራማሪዎቹ ከሆነ ከዚህም ከዚያም የሚገኙ ጥቂት ጀርሞች የሰውነታችን በሽታ ተከላካይ ክፍል እንዳይዘናጋና በተጠንቀቅ እንዲቆም ያደርጉታል፡፡
የሰው ልጅ በሽታ የመከላከል ብቃት የጦር ሜዳ ልምድ ለውን ወታደርን ይመስላል፡፡ ይህ ልምድ ያለው ወታደር ልምድ ከሌለው ወታደር ይልቅ እንዴት መከላከል እና እንዴት ማጥቃት እንዳለበት የተሸለ ያውቃል፡፡ በመሆኑም የተሻለ ጠላትን የመቋቋም ብቃት አለው፡፡ ይህ ሲባል ግን የአፍ ንጽህና በጠበቅን እናቁም ማለት እንዳልሆነ መረዳት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ጉዳዩ ከመጠን በላይ ስለሆነ እጥበት ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እንደ አለርጂ እና ከሰውነት የበሽታ መከላከል አቅም ጋር የተያያዙ በሽታዎች በተለይ በምእራቡ አለም እየተስፋፉ ነው፡፡ በ2016 በተሰራ ጥናት በአሜሪካ ከሚገኙ ህጻናት 40 በመቶ የሚሆኑት ከሰውነት የበሽታ መከላከል ብቃት ማነስ ጋር በተያያዘ ወደ ህክምና ተቋማት ያመራሉ፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያትነት የተነሳው ከልክ በላይ የሆነ የንጽህና አጠባበቅ ባህል ነው፡፡
በሰውነታችን ውስጥ ሊኖሩ የሚገባቸው ጠቃሚ ትላትሎች (worms) ደቂቅ ዘአካላት (microbes) ሙሉ በሙሉ ከሰውነታችን የሚጠፉ ከሆነ የሰውነታችን በሽታ ተከላካይ ክፍል ስራ ፈት ይሆናል፡፡ ይህ በሂደት የበሽታ መከላከል አቅምን ያደክምና በአጋጣሚ በሚመጡ አነስተኛ ህመሞች ሳይቀር በቀላሉ እንድንጠቃ ያደርገናል፡፡ ከኮቪድ 19 ጋር ያለው የመጠቃት መጠንም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ ይህ ሲባል ግን መቆሸሽ በየትኛውም መንገድ መፍትሔ ሊሆን እንደማይችል ሊሰመርበት ይገባል፡፡
ምንጭ፡ www.howstuffworks.com እና www.theconversation.com
፲ የኦንላይን የደህንነት ምክሮች ከጎግል
--------------------------------------------
ባለፉት ወራቶች የሳይበር ደህንነት ማስገንዘቢያ መርሃ ግብሮች ሲካሄዱ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ በተለይም የጥቅምት ወር ይህን የግንዛቤ ስራ ለማካሄድ በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ ስትውል ተመልክተናል፡፡ ይህን በማከናወን ሂደት ግዙፉ የጎግል ኩባንያ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ድርጅት ሲሆን በአሰራር ፕሮቶኮሉም የበይነ-መረብ ተጠቃሚዎች ደህንነታቸው በተጠበቀ መልኩ ስራቸውን እንዲያከናውኑ ትልቅ እገዛ ያደርጋል፡፡ እነዚህ የምትመለከቷቸው የጎግል የደህንነት ማሻሻያ አማራጮች በኢንተርኔት ላይ የሚኖረንን እያንዳንዷን እንቅስቃሴ ከማስጠበቅ አልፎ ለስራችን መሳካትም ትልቅ ሚና ሊኖራቸው ስለሚችል በሚገባ ማየቱ ጠቃሚ ነው፡፡
፩. በአይነታቸው የተለዩ እና ለመገመት አስቸጋሪ የሆኑ የይለፍ ቃሎችን ለመፍጠር የጎግልን የይለፍ ቃል አስተዳደር (password manager) መጠቀም የመጀመሪያው የጥንቃቄ መንገድ ነው፡፡
፪. በዴስክቶፕ እና በሞባይል የኦፕሬቲንግ ስርዓቶች የሚጫኑ የድር ማሰሻ (web browser) መተግበሪያዎች ምንግዜም የመጨረሻው ማዘመኛ (up-to-date) የተደረገላቸው መሆን አለባቸው፡፡ ይህ ደግሞ የምንጠቀማቸውን የኦንላይን ቴክኖሎጂዎች ከደህንነት ስጋት ውጭ ያደርጋቸዋል፡፡
፫. ስልካችን ጠፍቶ ቢገኝና በፍፁም የማናገኝበት ሁኔታ ቢፈጠር በጎግል አካውንታችን አማካኝነት ( myaccount.google.com.) በመግባት ከየኛውም ቦታ ሆነን ስልካችንን መቆለፍ እና ሚገኝበትን አካባቢ መረዳት እንችላለን፡፡
፬. የበይነ መረብ አገልግሎት ስንጠቀም የግል መረጃዎቻችንን የሚያጠምዱ የተለያዩ ድረ ገፆች ሊያጋጥሙን ይችላሉ፡፡ እነዚህ የመረጃ አጥማጆች በተከታታይ የሚቀርቡልንን ጥያቂዎች በንቃት መከታተል አንደኛው የመጠበቂያ መንገድ ሲሆን፤ ከዚያ በለፈም በመተግበሪያችን (browser) ላይ ሊጫኑ ወይም (extended) ሊደረጉ የሚችሉ መሳሪያዎችን በማከል ችግሩን ማስቀረት አንችላለን፡፡ በዚህ አንፃር የጎግል ሳይቶች ያልሆኑ (non-Google site) አድረሻዎች ላይ የይለፍ ቃል ስናስገባ ማስጠንቀቂያ የሚልክልን እንደ (Password Alert extension) ያለ መሳሪያ በመተግበሪያችን ላይ መቀላቀል እንችላለን፡፡
፭. አንዳንድ ጊዜ የመረጃ መንታፊዎች ወይም ሃካሮች የኛኑ የመጠቀሚያ ስም (username) እና የይለፍ ቃል በአካውንታችን ላይ በማስገባት አጠቃላይ መረጃችንን ሊሰርቁና ሊያጠቁን ይችላሉ፡፡ ይህ ሊሆን የሚችልበት ምክንያት የተለያየ ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ ግን የጠነከረ የይለፍ ቃል ሳይኖር ሲቀርና የተለያዩ ማዘመኛዎች ሳናደርግ ስንቀር ነው፡፡ አነዚህ የአጠቃቀም ክፍቶች ብዙዎቻችን ላይ የሚስተዋሉ ቢሆንም ካዛ ባለፈ በስራቸው ላይ ከፍተኛ ስጋት ያለባቸው ሰዎች ግን በጎግል አካውንት ላይ (security.google.com) በመግባት የሁለተኛ ደረጃ ማረጋገጫ (2-Step Verification) በማስቻል እያንዷንዷን እንቅስቃሴያቸውን መመልከት ይኖርባቸዋል፡፡
፮. አሁን አሁን ከየትኛውም የማህበረሰብ ክፍል በላይ የፖለቲካ መሪዎች እና የማህበረሰብ አክቲቪስቶች ለሳይበር ጥቃት እጀግ ተጋላጭ እየሆኑ መምጣቸው የሚታወቅ ነው፡፡ ታዲያ አንደዚህ አይነት ግለሰቦችና ሌሎች ከፍተኛ የሳይበር ስጋት ያለባቸው አካላት ጎግል የሚያቀርበውን የላቀ የጥበቃ መርሃ-ግብር (Advanced Protection Program) መጠቀም ይችላሉ፡፡ ይህ ፕሮግራም መረጃ አጥማጆችን በሚገባ ለመከላከል የሚጠቅም ሲሆን በታመኑ መተግበሪያዎች ላይ የኔትወርክ አጠቃቀችንን ለመገደብ እና አካውንታችንን አጭበርብረው ለሚጠቀሙ ሃከሮችም ጥሩ መፍትሄ ነው፡፡
፯. አብዛኛውን ጊዜ በስልካችን የምናወርዳቸው ምንጫቸው ያልታመነ መተግበሪያዎች ለየትኛውም የሳይበር ጥቃት በቀላሉ ሊያጋልጡን ይችላሉ፡፡ ከጎግል ፕለይ ያወረድናቸው መተገበሪያዎች እንኳን አልፎ አልፎ መሰል ስጋት ስለሚኖርባቸው የጎግል ፕለይ ጥበቃ ላይ (Google Play Protect) የደህነት ፍተሻ መድረግ እጅግ ተመራጭ ይሆናል፡፡
፷. በጎግል የበይነ መረብ አጠቃቀማችን ላይ እያንዷንዷን እንቅስቃሴያችንን በየጊዜው ለመፈተሸና ለመከታተል የጎግልን (Security Checkup) በቀላሉ መጠቀም እንችላለን፡፡ ይህ ሲስተም የጎግል አካውንታችንን ደህንነት ለመተንተን እና ያጋጠሙ ችግሮችንም በቀላሉ ለመፍታት የሚያገለግለን ነው፡፡
፱. ምንግዜም ቢሆን የህዝብ ወይም ነፃ የዋይፋይ ኔትወርኮችን ስንጠቀም በምላሹ ሊኖር ስለሚችለው የደህንነት ስጋት መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ የዋይፋይ ኔትወርኩ የይለፍ ቃል የታከለበት ቢሆንም እንኳን መረጃዎቻችንን አሳልፎ እንዳይሰጥ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
፲. ከእነዚህ ጥንቃቄዎች በተጨማሪ በጎግል አካውንታችን ላይ የደህንነት ቁልፍ (security key) በማዋቀር አጠቃላይ የበይነ መረብ አንቅስቀሴያችንን ማስጠበቅ እንችላለን፡፡
ምንጭ፡ Gadgets Africa