TechIn2
1.22K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
ቴክ-ሳይንስ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ተሸላሚ ሆነ
====================
በቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ተዘጋጅቶ ለአየር የሚበቃው የቴክ-ሳይንስ የቴሌቪዥን ፕሮግራም የ2020 OFAB Ethiopia chapter annual award ውድድር ላይ የአንደኝነት ደረጃን ይዞ አጠናቋል፡፡ ሽልማቱ የተበረከተው ፕሮግራሙ በቴሌቪዥን ስርጭት ዘርፍ በዓመቱ የግብርና ባዮ ቴክኖሎጂ ላይ በሰራቸው የሳይንስ ጋዜጠኝነት ስራዎች ነው፡፡
ውድድሩ ሲዘጋጅ ይህ ለአራተኛ ጊዜው ሲሆን ከቴሌቪዥን በተጨማሪም በህትመት እና ራድዮን ዘርፎች በየዓመቱ አወዳድሮ ሲሸልም ቆይቷል፡፡ ከዚህ በመቀጠልም ቴክ-ሳይንስን ጨምሮ በኢትዮጵያ ያሸነፉት ሦስት ተወዳዳሪዎች በአፍሪካ ደረጃ በሚደረገው መሰል ውድድር ተሳታፊ የሚሆኑ ይሆናል፡፡
ሽልማቱን ያበረከተው OFAB ወይም በሙሉ መጠሪያው Open Forum on Agricultural Biotechnology in Africa በዓለም አቀፉ የግብርና ከብቶች ጥናት ኢንስቲትዩት (ILRI) አማካኝነት የሚዘጋጅ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በስምንት የአፍሪካ ሀገራት የሚንቀሳቀሰው ፎረሙ በባዮ ቴክኖሎጂ ዙርያ ያሉ ባለ ድርሻ አካላትን በእውቀት እና ልምድ በማስተሳሰር የባዮ ቴክኖሎጂን ትሩፋቶች ለአፍሪካውያን ገበሬ ብሎም ባለሀብቶች ለማቋደስ የሚሰራ ነው፡፡
ቴክ ሳይንስ የቴሌቪዥን ፕሮግራምን ዘውትር ቅዳሜ በ10 ሰዓት በድጋሚ ደግሞ ማክሰኞ በ10 ሰዓት በ MOE TV ያገኙታል
በተጨማሪም የዩትዩብ ቻናላችንን ሰብስክራይብ በማድረግ ያመለጥዎትን ፕሮግራም እና ሌሎች የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ዝግጅቶች ያግኙ>>> https://www.youtube.com/channel/UC6jvUOLRSkVEQtc5Annfwvg
የውሃ መጠን
********
የምድራችን 70 በመቶ የሚሆነው በውሀ የተሸፈነ እንደሆነ ይነገራል፡፡ የውቅያኖሶች አማካኝ ጥልቀት 12ሺ አንድ መቶ ጫማ ይደርሳል፡፡ ለመሆኑ በምድር ምን ያክል መጠን ውሀ አለ? መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ 326,000,000,000,000,000,000 (ሶስት መቶ ሀያ ስድስት ኳንቲሊዮን) ወይም 326 ሚሊዮን ትሪሊዮን ጋሎን ውሀ በምድራችን ላይ ይገኛል፡፡ ይህም በሊትር 1,260,000,000,000,000,000,000 ሊትር (አንድ ሲክስቲሊዮን ሁለት መቶ ስድሳ ኳንቲሊዮን) ይሆናል፡፡ ይህም የውሀ መጠን በመደበኛነት በዑደት የሚኖር ነው፡፡ የውቂያኖስ ውሃ በሙቀት ይተንና ተመልሶ ይዘንባል፡፡
በምድራችን ካለው የውሀ መጠን 98 በመቶ የሚሆነው የሚገኘው በውቂያኖስ ነው፡፡ ይህም በጨዋማነቱ የተነሳ ለመጠጥነት የማይውል ነው፡፡ ቀሪው ከ 3 በመቶ በታች የሚሆነው ውሀ ለመጠጥ መዋል የሚችል ቢሆንም ከዚህ ውስጥ 1.6 በመቶ የሚሆነው ከበረዶ በታች ያለ በመሆኑ መገኘት አይችልም፡፡ እንዲሁም ደግሞ 0.36 በመቶ የሚሆነው ከመሬት በታች የሚገኝ ነው፡፡
0.036 የሚሆነው ውሃ በወንዞችና በሀይቆች ይገኛል፡፡ ምንም እንኳን ይህ በጋሎን በሺዎች የሚቆጠር ትሪሊዮን ቢያክልም ከጠቅላላው አንጻር ዝቅተኛ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ያለው የምድራችን ውሀ በደመና መልክ እየተንቀሳቀሰ ወይም በእጽዋት ውስጥ ይገኛል፡፡ ከዚህም ሌላ አንድ ሰው 65 በመቶ የሚሆነው አካሉ ውሀ መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡
ምንጭ www.hoestuffworks.com
ተጠንቶ የማያልቀው ስነ ከዋክብትና አዲስ መኖሪያ ፍለጋ
***************************************
የዋሽንግተን ስቴት ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች 24 ፕላኔቶችን በፀሐይ ዙሪያ ማግኘታቸው ተሰማ፡፡ The Cosmic Companion የተሰኘ የስነ-ከዋክብት መረጃዎችን የሚያዎጣው ተቋም እንደዘገበው ከምድራችን የተሻለ ምቹነት ያላቸው 24 ፕላኔቶች የራሳቸው ከዋክብትንም የያዙ ናቸው፡፡
ፕላኔቶቹ የሚዞሯቸው አብዛኞቹ ከዋክብት ከፀሐይ በተሻለ መልኩ ለህይዎት ተስማሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ጂኦ ባዮሎጂስት የሆኑት Dirk Schulze-Makuch ተስፋ ሰጪ ሁኔታ በታየባቸው ፕላኔቶች ተጨማሪ ጥናቶችን እናካሂዳለን ብለዋል፡፡
እነዚህ ምቹ መኖሪዎች ከመሬት የተሻለ ሙቀት፣ ርጥበት፣ መጠንና እድሜ ያላቸው እንደሚሆን ተገምቷል፡፡ ተመራማሪዎቹ እንዳሉት በጣም ረጅም እድሜ ያላቸው ፕላኔቶች ለአደገኛ ጨረር ሊያጋልጡ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ለህይዎት አማራጭ ሊሆኑ የሚችሉት ፕላኔቶች ከ5 እስከ 8 ቢሊዮን ዓመት የሚደርስ ዕድሜ ያላቸው ናቸው፡፡
ከእድሜ በተጨማሪ የእነዚህን ፕላኔቶች ለህይዎት ምቹነት ክብደታቸውና መጠናቸው ይወስነዋል፡፡ በተጨማሪም መጠነ-ሙቀት የአዲስ ፕላኔት ፍለጋው አንድ አካል ነው፡፡ በአማካኝ 20 ዲግሪ ሴልሺየስ ያላቸው ፕላኔቶች ከምድራችን የተሻለ ምቹነት ይኖራቸዋል፡፡
ምንጭ፡- The Cosmic Companion
ስለ ዝሆን ምን ያህል ያውቃሉ?
ብዙዎቻችን ከልጅነት ጊዜያችን አንስቶ ስለ ዱር ስናስብ በምዕናባችን ከሚከሰቱት እንስሳት መካከል ዝሆኖች ቀዳሚ ናቸው፡፡ ዝሆኖች በምድራችን ከሚራመዱ እንስሳት ሁሉ በግዝፈታቸው ወደር የሌላቸው እና አፈጣጠራቸው ለየት ያሉ ናቸው፡፡ በረጀክሙ ኩምቢ፣ ግዙፍ ግን ልፍስፍስ ጆሮዎች፣ ወፋፍራም እግር ዝሆኖችን ከሌሎች እንስሳት የሚለዩ አካላዊ ገፅታዎቻቸው ናቸው፡፡
ብዙዎቹ ባለሙያዎች በሁለት አህጉራት የሚኖሩ ሁለት አይነት የዝሆን ዝርያዎች መኖራቸው ላይ ይስማማሉ፤ የአፍሪካ (Loxodonta africana) እና የእሲያ (Elephas maximus) ዝሆን ዝርያዎች፡፡ በእነዚህ ሁለት ዝርያዎች ስር የተለያዩ ቅርንጫረፍ ዝርያዎች አሉ፤ ምንም እንኳን ምን ያህል ናቸው በሚለው ላይ ክርክር ቢኖርም፡፡ የአፍሪካ ዝሆኖች የሳር ምድር (Loxodonta africana) እና የጫካ (Loxodonta cyclotis) ተብለው የተከፈሉ ሁለት የዘር ቅርንጫፍ ሲኖራቸው የእሲያዎቹ በበኩላቸው የህንድ (Elephas maximus indicus)፣ ስሪ ላንካ (Elephas maximus maximus) እና ሱማትራ (Elephas maximus sumatranus) የተሰኙ የዘር ቅርንጫፎች አሏቸው፡፡
የአፍሪካና እሲያ ዝሆኖች ልዩነት
የአፍሪካ ዝሆኖች ከሰሃራ በታች ባለው የአህጉራችን ክፍል በተለያዩ ስፍራዎች ይኖራሉ፡፡ የእሲያ ዝሆኖች በበኩላቸው በኔፓል፣ ህንድ እና ደቡብ ምስራቅ እሲያ ጫካዎች ኑሯቸውን አድርገዋል፡፡ በግዝፈት ያነፃፀርን እንደሆነ የአፍሪካ ዝሆኖች ብልጫውን ይዘው እናገኛቸዋለን፡፡ ቁመታቸው ከ2.5 እስከ 4 ሜትር ሊደርስ ሲችል ክብደታቸውም ከ2,200 ኪ.ግ እስከ 6,350 ኪ.ግ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የእሲያ ዝሆኖች ከ2 እስከ 3 ሜትር ብቻ ሲረዝም ክብደታቸውም ከ2,000 እስከ 5,000 ኪ.ግ ብቻ ነው፡፡
ሁለቱ የዝሆን ዝርያዎች ከግዝፈትም ባሻገር ሌሎች ጥቂት ልዩነቶች አሏቸው፡፡ የአፍሪካ ዝሆኖች ጆሮ ገዘፍ ያለና ቅርፁም የአፍሪካ ካርታን የመሰለ ሲሆን የእሲያዎቹ ዝሆኖች በበኩሉ አነስ ያለና ክብ ቅርፅን የያዘ ነው፡፡ ወንዶቹም ሆነ ሴት የአፍሪካ ዝሆኖች ትላልቅ ጥርስና እቃ ለማንሳት የሚረዳ ሁለት ጣት መሰል ነገር በኩምቢያቸው ጫፍ አላቸው፡፡ የእሲያ ዝሆኖች በኩምቢያቸው ላይ ያለው ጣት አንድ ብቻ ሲሆን ረጃጅም ጥርስ የሚያበቅሉትም ወንዶቹ ብቻ ናቸው፡፡ ሴቶቹ እና አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የእሲያ ዝሆኖች አነስተኛ መጠኑ አነስ ያለ ጥርስን ሲያበቅሉ ጥርሱ ወደ ውጪ ግን የማይታይ ሊሆን ይችላል፡፡
የዝሆን ጥርስ ግዙፍና ረጅም ስር ያላቸው ሲሆን ለዝሆኖቹ መቆፈርያ፣ እቃ ማንሻ፣ ምግብ መሰብሰብያ እና እራሳቸውን መከላከያ ሆኖ ሲያገለግላቸው ኩምቢውንም የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ እኛ የሰው ልጆች ግራኝ ወይም የቀኝ እጅ ተጠቃሚ እንደሆንነው ሁሉ ዝሆኖችም ግራኝ አልያም የቀኝ ቀንዳቸውን ተጠቃሚ ናቸው፡፡ የትኛውን እንደሚጠቀሙ ለማወቅ ቀላሉ መንገድ የደከመውን መለየት ነው፡፡
ሁለቱም የዝሆን ዝርያዎች የተለያዩ የሳር አይነቶችን፣ ፍራፍሬዎችን፣ ቅጠላ ቅጠሎችን፣ የዛፍ ቅርፊት እና ስር የመሳሰሉ የእፅዋት አካላትን ይመገባሉ፡፡ በቀን ውስጥ 16 ሰዓታትንም በመመገብ የሚያጠፉና በዚህም ከ75 እስከ 150 ኪ.ግ የሚሆን ምግብ የሚሰለቅጡ ናቸው፡፡
ማህበራዊ ህይወት
የዝሆኖች ቡድን ዕድሜያቸው በገፋ ሴቶች የሚመራ ነው፡፡ መንጋው በዋናነት በሴት ቤተሰቦችና ህፃናት ዝሆኖች ሲሞላ እንደ ምግብ አቅርቦቱ ከ6 እስከ 20 አባላትን ሊይዝ ይችላል፡፡ ቤተሰቡ ከሚፈለገው በላይ ሲበዛ በቅርብ አካባቢ ወደሚሰፍሩ የተለያዩ ቡድኖች ይከፈላል፡፡ መሪዋ ዝሆን ተግባሯን የምታከናውነው ልምዷን እና የትኛው ስፍራ ጥሩ ምግብ እና መጠለያ እንደያዘ የሚነግራት ትውስታዋን በመጠቀም ነው፡፡ በተጨማሪም ህፃናት ዝሆኖችን ከሌሎቹ ጋራ እንዴት መግባባት አንዳለባቸው የማስተማሩን ድርሻ ይወጣሉ፡፡
ዝሆኖች በከፍተኛ ሁኔታ ማህራዊ ኑሮን ከሚመሩ እንስሳት መካከል ናቸው፡፡ አንድ ዝሆን ከሌላው ጋራ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን የሰው ልጆች መስማት የማንችለውን አነስተኛ ድምፅ በማውጣትም ከሶስት ኪ.ሜ በላይ ርቆ ያለ ዝሆንን መለየት ይችላሉ፡፡ በራሳቸውም ሆነ ሌላ ቡድን ውስጥ ላለ ዝሆንም መልካም ስነ-ምግባር በማሳየትም ይታወቃሉ፡፡ ለምሳሌ ሲገናኙ ኩምቢያቸውን ወደላይ ከፍ በማድረግ አልያም የኩምቢያቸውን ጫፍ ወደ ሌላኛው ዝሆን አፍ በመክተት ሰላምታ ይለዋወጣሉ፡፡ ከዚህ ባለፈም በመንጋቸው ውስጥ ያለ ሌላ የተጎዳ አባል ካለ የሚጠብቁና ስለሌላው የቡድኑ አባል ደህንነት ግድ የሚሰጣቸው ናቸው፡፡
በሌላ መልኩ ዝሆኖች በማሰብ ችሎታቸው የማይታሙ መናቸው ይነገርላቸዋል፡፡ ለዚህ ማሳያ የሆነው ውስብስብ ችግሮችን የመፍታት ብቃት ሲያሳዩ እንዲሁም ለቅሶ ሲደርሱና ሲያፅናኑ መታየታቸው ነው፡፡
ዕድሜ
ዝሆኖች ከተወለዱ ከ8 እስከ 13 ባሉት ዓመታት ውስጥ ለፆታዊ ግንኙነት ይደርሳሉ፡፡ በዚህ ሰዓት ምግባቸውን ፈልገው ማግኘት እና እራሳቸውን መጠበቅ እስከቻሉ ድረስ ወንድ ዝሆኖች መንጋውን ትተው በመውጣት ለብቻቸው አልያም ከሌሎች መሰሎቻቸው ጋራ በአነስተኛ ቡድን ኑሮዋቸውን ይመራሉ፡፡
ሴቶቹ ዝሆኖች በአስራዎቹ አጋማሽ ላይ እስከሚደርሱ ድረስ ልጅ የማይወልዱ ሲሆን ወንዶቹ ግን ዕድሜያቸው ሰላሳዎቹ ውስጥ እስከሚገባ ድረስም ልጅ ላይወልዱ ይችላሉ፡፡ አንድ የዝሆን ልጅ የሚወለደው ከ22 ወራት የእርግዝና ቆይታ በኋላ ነው፡፡ የሚወለዱት ጨቅላ ዝሆኖችም ከ68 እስከ 158 ኪ.ግ ክብደትና 90 ሴ.ሜ አካባቢ ቁመት ይዘው ይህችን ምድር ይቀላቀላሉ፡፡ በተጨማሪም ፀጉር እንዲሁም ረጅም ጭራና አጭር ኩምቢ ያላቸው ናቸው፡፡ ዕድገታቸው ግን እጅግ ፈጣን የሚባል ነው፤ በተወለዱ በአንድ ዓመት ውስጥ በየቀኑ ከ0.9 እስከ 1.3 ኪ.ግ እየጨመሩ ይሄዳሉ፡፡ ሶስት ዓመት ሲሞላቸውም መደበኛ ምግብ መመገብ ይጀምራሉ፡፡
አለም አቀፉ የተፈጥሮ እና የተፈጥሮ ሀብቶች ሕብረት (IUCN) የእሲያ ዝሆኖች የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸው ናቸው ሲል ያስቀምጣቸዋል፡፡ ምንም እንኳን ሙሉ ቁጥራቸው ባይታወቅም እየቀነሱ መሆናቸው ግን ይታመናል፡፡ በአንፃሩ የአፍሪካ ዝሆኖች ቁጥራቸው በመጨመር ላይ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓትም 415,000 የአፍሪካ ዝሆኖች በየዱሩ ይገኛሉ፡፡ በአደጋ ስጋት ረገድ የአፍሪካንም ሆነ የእሲያ የዝሆን ዝርያዎችን የሚያመሳስላቸው የአደን እና የዘር ቅርንጫፎች የመጥፋት ስጋት የተጋረጠባቸው መሆኑ ነው፡፡
ምንጭ፡ Live Science
የምንጊዜውም አጭሩ የጊዜ ርዝማኔ
====================
አንድን ድርጊት አከናውነን ለመፈጸም ርዝማኔው ወይም ቆይታው ይለያይ እንጂ ጊዜ ያስፈልገናል፡፡ ታዲያ አንድን ድርጊት ሰርተን የጨረስንበትን ቆይታ የተለያዩ አሀዶችን በመጠቀም እንለካለን፡፡ ይኸውም በአመታት፣ በወራት፣ በሳምንታት፣ ወይም ደግሞ በቀናት፣ በሰዓታት፣ በደቂቃዎችና በሴኮንዶች ሊሆን ይችላል፡፡
ከጊዜ መለኪያ ምድቦች አንጻር ከሴኮንድ በታች ያሉ ለመደበኛ ጊዜ መለኪያ የማንጠቀማቸው ነገር ግን ለልዩ ልዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ጥቃቅን ምድቦች አሉ፡፡ ለምሳሌ ያክልም ዴሲ ሴኮንድ (የሴኮንድ አንድ አስረኛ)፣ ሴንቲ ሴኮንድ (የሴኮንድ አንድ መቶኛ)፣ ሚሊ ሴኮንድ (የሴኮንድ አንድ ሺኛ)፣ ማይክሮ ሴኮንድ (የሴኮንድ አንድ ሚሊዮንኛ)፣ ናኖ ሴኮንድ (የሴኮንድ አንድ ቢሊዮንኛ)፣ ፒኮ ሴኮንድ (የሴኮንድ አንድ ትሪሊዮንኛ)፣ ፌምቶ ሴኮንድ (የሴኮንድ አንድ ኳድሪሊዮንኛ)፣ አቶ ሴኮንድ (የሴኮንድ አንድ ኳንቲሊዮንኛ)፣ ዜፕቶ ሴኮንድ (የሴኮንድ አንድ ሲክስቲሊዮንኛ)፣ ዮክቶ ሴኮንድ (የሴኮንድ አንድ ሴፕቲሊዮንኛ) እና ፐላንክ (Planck time) የሚታወቁት ናቸው፡፡
ከላይ የተዘረዘሩት ምድቦች በጊዜ ምድብነት ይታወቁ እንጂ በቅርብ በወጣ ዘገባ ተመራማሪዎች የብርሃን ቅንጣቶች የሃይድሮጅን ሞሎኪዩልን ለመቋረጥ የሚወስድባቸውን የጊዜ ርዝማኔ መለካት ችለዋል፡፡ ይህም ልኬት እስካሁን ከተመዘገቡት ርዝማኔዎች የመጨረሻ ትንሹ የጊዜ ርዝማኔ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ የብርሃን ቅንጣቶቹ የሃይድሮጅን ሞሎኪዩልን ለማቋረጥ የወሰደባቸው ጊዜም 247 ዜፕቶ ሴኮንድ (zeptoseconds) ሆኗል፡፡
ከዚህ በፊት በ1999 የኖቤል ሽልማት ማግኘት የቻለ በፌማቶ ሴኮንድ የተለካ የኬሚካል ቦንድ ለመሰራትና ለመከፈል (break and form) የሚወስደው ጊዜ ታውቆ ነበር፡፡
የዚህ ግኝት ተጨማሪ ማብራሪያዎች በጥቅምት 16 የሳይንስ ጆርናል ላይ ታትሟል፡፡
ምንጭ Science alert
መልካም ዜና
=======
ውድ ተከታታዮቻችን “BASIC PRODUCT SKETCHING TECHNIQUE” በሚል ርዕስ በኢንስቲትዩታችን ዩትዩብ ቻናል ላይ ያዘጋጀነውን ተከታታይ ስልጠና እየተከታተላችሁ ነው ?
ስልጠናውን ከተከታተላችሁ በኋላ በሰባተኛው (7ኛ) ክፍል ዲስክርፕሽን ላይ የተቀመጠውን ሊንክ በመጫን የተዘጋጀውን ጥያቄ በወረቀት ላይ (A4 ወይም A3) በመስራት በኢሜይል አድራሻችን (stic.ethiopia@gmail.com) የምታደርሱን ይሆናል፡፡ ታድያ እስካሁን ጥያቄዎቹን ሞልታችሁ ለላካችሁልን ተሳታፊዎች የምስክር ወረቀቱ የተዘጋጀላችሁ ሲሆን በቅርቡም ከእጃችሁ እንደምናደርስ መግለፅ እንወዳለን፡፡
ታድያ አሁንም ጊዜው አላለቀምና ስልጠናውን ከተከታተላችሁ በኋላ በስልጠናው ላይ የተዘጋጀውን ጥያቄ መልስ እስከ ዓርብ ጥቅምት 13 2013 ዓ/ም ድረስ ብቻ በመላክ ሰርተፊኬት ማግኘት የምትችሉ መሆኑን እንገልፃለን፡፡
ያሎት ጊዜ አጭር በመሆኑ ተከታታይ ስልጠናውን በሚገባ ተከታትለው የተዘጋጀውን ጥያቄ ሰርተው ይላኩልን ፡፡
ስለተከታተሉን እናመሰግናለን፡፡
እንጀራን ለ24 ቀናት ሳይሻግት የሚያቆየው ምርምር ማብራርያ ተሰሠጠበት
===================
በቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት የኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ማዕከል ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር እዮቤል ሙሉጌታ በትብብር የተሰራውንና እንጀራ ሳይሻግት እስከ 24 ቀናት ድረስ ማቆየት በሚችለው የምርምር ውጤት ዙርያ ዛሬ ጠዋት በኢንስቲትዩቱ አዳራሽ ተገኝተው ገለፃ አቅርበዋል፡፡
ዶ/ር እዮቤል በገለፃቸው በአሁኑ ወቅት አንጀራ ከሦስት ወይም አራት ቀናት በኋላ እንደሚበላሽና ለዚህም በዋነኝነት ፔኔሲሊየም ጨምሮ ሶስት የፈንገስ አይነቶች ዋነኛ ምክንያት መሆናቸውን ጠቅሰው እንጀራውን ሳይበላሽ ለማቆየት በሚደረገው የማሞቅ እና ሌሎች ተግባራት ወቅት የሚደርሰውን የኃይል ብክነትንና በተለይ ስራውን በዋናነት በሚያከናውኑት እናቶቻችን ላይ የሚያስከትለውን ቀላል የማይባል የስራ ጫና ገልፀዋል፡፡ ሶስት አራተኛው ኢትዮጵያውያን የእንጀራ ተመጋቢ መሆናችንን ያወሱት ዶ/ር እዩቤል የዚህ ምርምር ግኝት ወደ ተግባር መለወጥ በማህበራዊ፣ ምጣኔ ሀብት፣ አካባቢ ጥበቃ፣ ኃይል ቁጠባ ብሎም የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ ትልቅ አውንታዊ ሚናን እንደሚጫወትም አብራርተዋል፡፡
ምርምሩ ሲልቨር እና ዚንክ ኦክሳይድን በናኖ ፓርቲክል ደረጃ በመጠቀም የሚሰራ ሲሆን ውህዱን በእንጀራ ማስቀመጫው ላይ በማኖር ብቻ ነው ለዚህ ያህል ጊዜ እንዲቆይ ማድረግ የተቻለው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በምርምሩ ላይ የተገኙ ዝርዝር የቤተ ሙከራ ውጤቶችን ለታዳሚያኑ አብራርተዋል፡፡
በገለፃው ላይ ተሳታፊ የነበሩት የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪዎችም በቀረበው ምርምር ዙርያ ጥያቄ እና አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ በመድረኩ ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል የፓርቲክል መጠኑ ሁኔታ፣ የጤና ተፅዕኖው፣ በዋጋ ደረጃ ያለው ተደራሽነት፣ ከሌሎች ምርምሮች ጋራ እንዴት በተመጋጋቢነት መሄድ እንደሚችል እና በጥናቱ ላይ በዋለው የጤፍ አይነት ላይ ያውጠነጠኑት ይገኙበታል፡፡
ጥያቄዎቹ ተገቢ መሆናቸውን በምላሻቸው ያነሱት ዶ/ር እዮቤል ምርምሩ በሁለተኛ ዲግሪ ማሟያነት የቀረበና ቀሪ ስራዎች መኖራቸው ከግምት ይገባ ዘንድ አሳስበዋል፡፡ በጥያቄዎቹ ላይም ዝርዝር ምላሽ የሰጡ ሲሆን ከሌሎች የፈጠራ ባለሙያና ምርምሮች ጋራም ወደፊት በጋራ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡ በተጨማሪም ምርምሩ ወደ ህብረተሰቡ ከመድረሱ በፊት በጤና ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ተፅዕንዖ፣ የፓርቲከሎቹ መጠን ሁኔታ እና ሌሎች ጉዳዮችም በቂ ምርምር እንደሚደረግባቸው ዶ/ር እዮቤል አስረድተዋል፡፡
ከዚህ በፊት እንጀራን ሳይሻግት ለ12 ቀናት ያህል ለማቆየት የሚያስችል ምርምር የተሰራ ቢሆንም የእንጀራውን ጣዕም እንዲቀይር የያደረገ ነበር፡፡ በአንፃሩ አዲሱ መርምር የዚህ አይነት ለውጥ የማያስከትል መሆኑን ዶ/ር እዮቤል ገልፀዋል፡፡
ምርምሩ በቀጣይ ለህዝብ ይፋ የሚደረግ ሲሆን እኛም በምርምሩ ዙርያ ዝርዝር ዘገባን ይዘንልዎ የምንመጣ ይሆናል፡፡
የኮቪድ-19 ገጸ-በረከቶች
=============
በኮቪድ 19 ምክንያት የተጣሉ ገደቦችና የኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች መቀዛቀዝ በአለማችን ጉዳት ብቻ ሳይሆን ጥቅምንም ይዘው መጥተዋል፡፡ በተለይ ከአየር ንብረት ብክለት አንጻር የታየው ለውጥ አለማችን ያላትን የኃይል አጠቃቀምና ልቀት ልምድ እንደገና መከለስ እንዳለባት በሰፊው ያመላከተ ነው፡፡ ናሽናል ጆግራፊክ መጽሔት በያዝነው ወር እትሙ ወረርሽኙ ከአየር ንብረት አንጻር ያበረከተውን አስተዋጽኦ በሶስት ከፍሎ አቅርቦታል፡፡ እኛም በዚህ መልክ በአጭሩ አዘጋጅተንላችኋል፡፡
1ኛ. በካርበን ልቀት በአንድ አመት ብቻ ትልቅ የሚባል ቅናሽ ኮቪድ 19 አምጥቷል፡፡ መጽሔቱ ይህን ለካርበን ልቀት መቆም መባቻ ይሆናል የሚል ሀሳብ አስፍሯል፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ የካርቦን ልቀት አስከ 2024 የተጠበቀ ቢሆንም ኮቪድ 19 ሁኔታውን ሳያፋጥነው አልቀረም፡፡ በወረርሽኙ ምክንያት የነበረው የእንቅስቃሴ ገደብና የግዙፋን ፋብሪካዎች ስራ መቀነስ የነበረውን የካርበን ልቀት በሚገርም ሁኔታ ቀንሶታል፡፡ ይህ ግን ለጊዜው መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ የአለም መንግስታት ከዚህ በመነሳት ለካርበን ልቀት መቀነስ ምክንያት የነበሩ ነገሮችን መጣኔ ሐብት እና ማህበራዊ እንቅስቃሴውን በማይጎዳ መልኩ ስራቸውን ከብክለት ነጻ የሚደርጉበትን መንገድ በአፋጣኝ መፈለግ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህም ለተከታታይ አመታት ያክል የካርቦን ጥቅል ልቀቱ ዜሮ እስኪሆን ድረስ መሰራት አለበት፡፡
2ኛ. ኮቪድ 19 የተናጥል እርምጃ የአለም ሙቀትን ለመቀነስ በቂ እንደማይሆን አስተምሯል፡፡ ኮቪድ 19 በኃይል አጠቃቀም ዙሪያ የሚሮረውን ተጽዕኖ በሚያመለክት ትንተናው በአሁኑ ወቅት አማራጭ ኃይል መፈለግ፣ የኃይል አጠቃቀምን ማሻሻልና የትራንስፖርት ኃይል አቅርቦት አማራጭ መጠቀም ተገቢ እንደሆነ አመላክቷል፡፡ በያዝነው አመት የነዳጅ ዘይት ፍላጎት በአየርና ሌሎች ትራንስፖርት እንቅስቃሴ መቆም ምክንያት 60 በመቶ የሚሆነው ፍላጎት ቀንሷል፡፡ ይህም ከካርበን ልቀት መቀነስ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው፡፡ በ2040 የነፋስና የፀሐይ ኃይል አማራጮች ፍላጎት ከአጠቃላይ የድፍድፍ ነዳጅ ፍላጎት 34 በመቶ የሚሆነውን ይሸፍናሉ ተብሎ ተገምቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት እየመጡ ያሉ ቴክኖሎጂዎች እና በትኩረት የሚሰሩ ፖሊሲዎች የአለም አቀፍ የኃይል አማራጭ ሽግግሩን ያፋጥኑታል፡፡ በኮቪድ ምክንያት የታየውን የካርበን ልቀት መቀነስ ካሉን የፖሊሲ ግቦች ጋር ማስተሳሰር የመነሻ ትግባር ሊሆን ይገባል፡፡
3ኛ. የዛሬ የምጣኔ-ሐብት ማገገሚያ እቅዶች የወደፊት የአየር ንብረት ሁኔታን ይወስናሉ፡፡ ከኃይል ጋር የተያያዘ ኢንቨስትመንት በ2020 ያድጋል ተብሎ የታለመ ቢሆንም በኮቪድ ምክንት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ የነዳጅ ዘይት ዋጋ እና የገበያ ተፈላጊነት በዚያው ልክ ወርዷል፡፡ መንግስታት በአሁኑ ወቀት የነበረውን የምጣኔ-ሐብት መቀዛቀዝ ሊያነቃቁ የሚችሉ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ላይ ናቸው፡፡ በመሆኑም አለማችን አሁን ካለው የካርበን ልቀት በላይ ላታስተናግድ ስለምትችል የሚሰሩት የምጣኔ ሐብት ማነቃቂያ ተግባራት ከተፈጥሮ ጋር የተስማሙ ሊሆኑ ይገባቸዋል፡፡
ምንጭ National Geographic
በቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት የተዘጋጀው አዲስ የፖሊሲ ጥናት
=====================
በቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት የፖሊሲ እና ስትራቴጂ ጥናት ዳይሬክቶሬት “Data Privacy Policy for Ethiopia and the need for Compliance with International Standards” በሚል ርዕስ የፖሊሲ ጥናት አውጥቷል፡፡ ጥናቱ በኢትዮጵያ የተደራጀና ሁሉን አለም አቀፍ ስታንዳርዶችን ያሟላ የመረጃ/ጥሬ ሀቅ ጥበቃ ፖሊሲ አልያም ሕግ መኖር አስፈላጊነት ላይ የተለያዩ አመክንዮዎችን በመንተራስ ምክረ ሀሳብ የሚያቀርብ ነው፡፡
ያደጉት ሀገራት የዛሬ 40 እና 50 ዓመታት ገደማ ግለሰባዊ መረጃን የሚጠብቁ ሕጎችን ሲተገብሩ መኖራቸውን ያወሳው ጥናቱ በአንፃሩ ሀገራችን ላይ አሁንም ድረስ ይህን ሁኔታ ባልተደራጁና በቂ ባልሆኑ ሕጎች ለመቆጣጠር እየዳከርን መሆኑን ይጠቁማል፡፡
የፖሊሲ ጥናቱ በኢትዮጵያ የመረጃ ጥበቃ ፖሊሲ አልያም ሕግ መኖር አስፈላጊነት ካደረጉት ምክንያቶች መካከል የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በሌሎች ሀገራት ደረጃ ካለው የፖሊሲ እና ህግጋት ጋራ አለመጣጠም በተለይም ሀገራችንን የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ወይም ኢ-ኮሜርስ ስርዓቱን በሚፈለገው ልክ እንዳታሳድግ እና ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ብሎም ሀገራት ከእኛ ጋራ እንዲሰሩ የማያስችል ሁኔታ እንደሚፈጥር የአውሮፓ ህብረት እና የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ሕግጋትን በተግባራዊ ምሳሌነት አስደግፎ አትቷል፡፡
በሌላ መልኩ ኢትዮጵያ በቅርብ መረጃ እና ግንኙነት ቴክሎጂዎችን (ICT) ጨምሮ ስድስት አባይት ዘርፎች ዋና የትኩረት ማዕከል አድርጎ የያዘ አዲስ የአስር ዓመት የልማት ዕቅድ ማውጣቷ ይታወሳል፡፡ ይህ መሪ ዕቅድ ቴክኖሎጂን ማዕከል ያደረገና ለስኬቱም ያለው ወሳኝነት የማያጠራጥር መሆኑ ዘርፉን የዲጂታል ጥሬ ሀቅን (Data) በሚቆጣጠሩ ሕግጋቶች ለመደገፍ እንደሚገደድ ተነግሯል፡፡ በተጨማሪም ከሚከፍተው አዲስ የዕድል በር እና አሁን ያለንበት የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ሁኔታ ያለ ሕግ እና ፖሊሲ ብዙም የማያራምድ መሆኑ በረቂቁ ላይ ተቀምጧል፡፡
ጥናቱ ግለሰባዊ መረጃን ከሚጠብቁ ፖሊሲ እና ሕግጋት አስፈላጊነት ባሻገርም በሀገራችን በአሁኑ ሰዓት ያለውን የግለሰባዊ መረጃ አጠባበቅ ሁኔታ እንዲሁም የICT ፖሊሲ እና ሌሎች ከጉዳዩ ጋራ ግንኙነት ያላቸው ወሳኝ ሕግጋቶችንም የቃኘ ነው፡፡
ሙሉ ጥናቱን ቀጥሎ የተቀመጠውን pdf ፋይል በመክፈት ያገኙታል፡፡