Sost Kilo
5.09K subscribers
998 photos
45 videos
7 files
107 links
Stories | ሦስት ኪሎ

@leoulz
Download Telegram
Forwarded from Sost Kilo
ᵀʰᵉʳᵉ ʷᵉʳᵉ ᵃˡˡ ᵏⁱⁿᵈˢ ᵒᶠ ˢᵗᵒʳⁱᵉˢ ᵗᵒˡᵈ ᵃᵇᵒᵘᵗ ᵗʰᵉ ʷᵃʳ ᵗʰᵃᵗ ᵐᵃᵈᵉ ⁱᵗ ˢᵒᵘⁿᵈ ᵃˢ ⁱᶠ ⁱᵗ ʷᵃˢ ʰᵃᵖᵖᵉⁿⁱⁿᵍ ⁱⁿ ᵃ ᶠᵃʳᵃʷᵃʸ ᵃⁿᵈ ᵈⁱᶠᶠᵉʳᵉⁿᵗ ˡᵃⁿᵈ° ᴵᵗ ʷᵃˢⁿ'ᵗ ᵘⁿᵗⁱˡ ʳᵉᶠᵘᵍᵉᵉˢ ˢᵗᵃʳᵗᵉᵈ ᵖᵃˢˢⁱⁿᵍ ᵗʰʳᵒᵘᵍʰ ᵒᵘʳ ᵗᵒʷⁿ ••• | 𝙸𝚜𝚑𝚖𝚊𝚎𝚕 𝙱𝚎𝚊𝚑 | 𝙰 𝙻𝚘𝚗𝚐 𝚆𝚊𝚢 𝙶𝚘𝚗𝚎: 𝙼𝚎𝚖𝚘𝚒𝚛.
1
See you in December. Stay safe !
Sostkilo Podcast 📻 | 2021 Wrapped: 3K plays - 100+ subscribers -11 episodes - 14 countries. Merci 🙌 #2021PodcasterWrapped #SpotifyWrapped
ቡዲዝምን በዲንዴን'ግ ተቀበልኩ

ማስታወሻ | July 24 -19

[ ልዑል ፡ ዘወልደ ]

ወደ ነፃይቱ ምድር በመሄጃዬ ቀን የትም ሳሽኳልል ቆየሁና እንደማንኛውም አበሻ በሰዓቴ መዳረሻ መጣደፍ ጀመርኩ ። ቦሌ ስደርስ ፥ መንገደኛው ቼኪ'ን የሚያደርግበት ሰልፍ የኢሮብ ነዋሪዎች አብይን ለመቃወም ከወጡት ቀጫጫ ሰልፍ ይረዝማል ።

እንዳማራጭ ፥ በማሽን ቼኪ'ን ማድረግ ይቻል ስለነበር ይለፈኝ ብዬ ወደ ማሽኑ ሄድኹ ። እንደደረስኩ አንድ ሰውዬ የአያቱን ስም አላልፍልህ ብሎት ሳንቲም እንደዋጠበት ስልክ ሲደበድበው ደረስኩ ። ትካይ ማሽኑን ልገላግል ከመሀል ስገባ ደብዳቢው የኔው ጉድ ነው ።

የለየሁት ከአገጩ ከፍ ብላ በበቀለች ደማቅ ሸንጎበት ነው ። አይ ጌታዬ ፥ ምን ባደርግህ ነው ከቡድሃ ጉተማ በፊት ግራማ ጉተማን ያሳየኸኝ ፥ ሃሃ

ከግርምሽ- አባ ጨብሳ ጋር ትንሽ አወራን ፥ ያው ዶክተሩን ቦጨቅን ብል ይቀላል (መሰለኝ) ። በወቅቱ ወደ ጅጅጋ ይበር ነበር ፤ የበረረበትን ምክኛት በቅጡ ሳልጠይቀው በችኮላ ተለያየን ።

ነገር ሁሉ ሆነና ከምድረ-ታይ በግዜ ገባኹ ። እንደደረስኩ ቀድሞ የገባልኝ የአገሪቷ ጠረንና እንዲህ የማይሉት ወበቅ ነው ። ሽታውን መግለፅ አስቸጋሪ ቢሆንም ለ'ሎንችን መጋረጃ ቅርናት ይቀርባል ።

እንደባላገር መንገደኛ ሰው አጠያይቄ ወደ መሀል አገር ባቡር ተሳፈርኩ ። ባቡሩ ዘመናዊ ባቡር ለመባል እራሱ ብዙ ይዘምናል ። ጋሽ አበራ ሞላ የለገሃር ፉርጎ ላይ ተንጠልጥሎ ሸከተፍ - ሸከተፍ እያለ ስለመዝፈኑ እያሰብኩ ሀሳቤን ሳልጨርስ ደረስኩ ፥ ግነት - ወ - ፍጥነት ሃሃ

ቡክ ያደረግሁት ሆቴል ያለው በስድስተኛው ስቴሽን ላይ እንደመሆኑ ደውል ቆጥሬ አወራረዴ በአምስተኛው ሆነ ። ከሆቴሉ በጠዋት ስለገባሁ ተመልሶ ለመውጣት ገላዬን መታጠብ ጀመርኩ ። ነገሩ የሚጀምረው ከዚህ እጥበት ነው ...

ከፊት ያገኘሁትን ተመትቼ እየታጠብኩ ድንገት ፀጉሬ ውልቅ ውልቅ እያለ ይነቃቀል ገባ ። ተደናግጬ ዉሃውን በመዝጋት ወደ ጎመ'ው መስታወት ሄድኩና አየሁ ። አናቴ ፍንጭት ፈላ የጋጠው አካት መስሏል ።

መስታወቱ ላይ ብዙ ከተከዝኩ በኋላ ሙሉ ዞማዬን በደንበኛው አዳርሼ ላጨሁት ፥ መለጥኩ ። እንዳበቃሁ የሎርድ ኦፍ ዘሪንጉ ጎለም በመተጣቢያ ቤቱ መስታወት አየሁት ፥ እርሱ ይየኝ አይየኝ እርግጠኛ አይደለሁም ።

ወበቅ ቤቴ አልጋ ላይ ያገኘሁትን ቀይ ሽርጥ እንዳሸርጥ አስገድዶኝ ፥ ለብሼ ወደ ሎቢ ቦታው ወረድኩ ። በመውረድ ላይ ሳለሁ ነበር የታጠብኩበትን ፈሳሽ ምንነት አገላብጬ ያየሁት ። ፀጉሬን ስፈትግበት የነበረው ሻምፑ ጭገር ማርገፊያ ክሬም ነበር ..ሃሃ

ከመኝታ ቤቱ ሰገነት ስወርድ ያዩኝ ቢልቦዮች ማስቲካቸውን እየተፉ " ዋይ ዋይ " አሉኝ ። የጉድ አገር ቶሎ አይመሽም ፥ ለመርዶም በረፈደ ሰዓት እንደ ሙሾ አውራጅ ዋይ-ዋይ በማለታቸው ግራ ተጋበሁ ። በዋይታው በርግጌ እንደተገተርኩ አንገታቸውን ሰብረው ደግሞ ሰላም አሉኝ ።

ቆይቶ ሲገባኝ "ዋይ" ታዮች ለታላቅ ሠውና ለመነኩሴ የሚሰጡት የስግደት ሰላምታ መሆኑ ነው ። ከተራ ሰው በአንዴው የቡድሃ ልዑል ከሆኑ በኋላ መፎገር የለም ፥ መደናበሬን ተውኩ ። ከትከሻዬ አንስቶ ያሰመርኩትን ቀይ ሽርጥ እያሰማመርኩ መልሼ እጅ ነሳሁ ። እንደው ግን ፥ ጥቁር ቡዲስት ኖሮ ያውቅ ይሆን ?

ውስጤ በጥያቄ ቢናጥም ፥ የትም ያላገኘሁት ጌትነት ግትነት ግን ተሰምቶኛል ፤ ያልነበረ አይነት ጌትነት ። ደራሲ ስብሓት (ነብስኄር) ለትምህርት ወደ አሜሪካ በሄደ ግዜ የሚቀበለው ሰውዬ በአባቱ ስም " ሚስተር እግዛቤር " ሲለው ፥

- እንዴ ? ለካ እግዚያብሔር ነኝ ! እንዳለው አይነት ጌትነት ሃሃ

------------------------------------
ክፍል - 01 - Land of free.
ማስታወሻ ፥ ወይ ጡቷ | July 26 - 19.

[ ልዑል ዘወልደ ]

በሁለተኛው ቀኔ ገበያ ላረግ ወጣሁ ። በገበያው ከነበሩ አሻንጉሊቶች ቀድሞ ከአይኔ የገባው ጡት የያዘ እጅ ነበር ። ጡት እንዲህ ሸንጉልቶ አደባባይ መውጣቱ ገርሞኝ ቆምኹ።

ነገርዬው ወሲብ መቀስቀሻ ይሁን ጣዖት ግራ ገብቶኝ ብዙ ሳየው ቆየሁና በስተመጨረሻ አባባኝ። መባባቴ ሸንጎሊቱ ትንሽ ቢጠቁር የአኖሌ'ን ሀውልት ቁርጥ በመምሰሉ ነው - Harkaafi Harma Muraa Aanolee ። ሰው ስሜቱን በሚቀሰቅስበት መጫወቻ መባባቴ አናዶኝ ገበያውን ጥዬ ወጣሁ ሃሃ።

በባዶ ሆዴ ባዮኬ ስር ስንሸራሸር መንገድ ዳር ቺክን ሲጠበስ ከሩቅ አየሁ ። ሀላል ምግብ ተብሎ ካልተለጠፈበት ምግብ ቤት በቀር አልበላም ያልኩ ሰው ሆዴ ተላወሰብኝ ። እግዜር በታይ እንደሌለ ወላ ፆሜን ገደፍኩ ። በርግጥ ክንፍ-ክንፉን ብቻ ነው የበላሁት ሃሃ ።

የገረመኝ የምች ከአገር ውጭ አለመኖር ነው ። አገር ቤት ቡና ላይ ጤና አዳም አበዛህ ብሎ የሚያጣፋኝ ከይሲ ባቡር መንገድ ላይ የዶሮ ዳሌ እንደሸንኮራ ስግጥ እንዴት ዝም አለኝ ?

ብቻ ሆዴ ትንሽ ተንፈስ አለች ። ስጠግብ የጠባሹን ሰውዬ መልክ ታየኝ ፥ ሽበታም ሞንጎላይ ነው ። አመሰገንኩ - ካፑን ኽራብ ! ። ያጠለቀው ጋወን ላይ በራሪ ትሁን ቀዛፊ ፥ የሆነች እንስሳ ታትማለች ። ቀና ስል ፥ ከአናቱ በላይ በሜንጦ የተንጠለጠሉ አራት ዳክዬዎች ተዘቅዝቀው አየሁ ፥ ... ፈ ...ጣ ... ሪ ...ዬ ... !

ለምን አስበላኸኝ አልልህም ፤ ምን ይሁን ብለህ ቀና አረከኝ ሃሃ ። የተጣባኝን አጋሰስነት እየረገምኩ ካሁን-አሁን አስታወከኝ ብዬ በጉልበቴ ተደፋሁ ። እንደ ኮብል አንጣፊ አጎንብሼ ብጠብቅ የለም ፤ ብጠብቅ የለም ። ከነባር ምግቦች ጋር ሲብላላ ቆየ መሰለኝ ፥ ጭራሹን አስጋሳኝ ...ኧረ'ረረረ

ሆዴን እንደነገሩ እያሸሁ ካጎነበስኩበት ስነሳ ቁምጣ አድርጋ የምትሸጥ ቢጫ ኮረዳ ታየቺኝ ። የፈጣሪ ስራ በምክንያት ቀና ያረጋል ፥ በምክንያት ያስጎነብሳል ።

ቁምጣ የሚባል ጥብቆ እንደሌለኝ ትዝ ያለኝ ቢጫ ገላዋን እንዳየሁ ነው። ከሱቋ ገብቼ መዟዟር ጀመርኩ ፥ ልጅት ከስልኳ ላይ እንደተደፋች ነው ። ከቶፗ ሊያፈረግጥ የሚታገለው ጡቷ እንደመንግስት ግማሹ ወርዷል ። ጡቷን እያየሁ ብቆይ እንደቅድሙ አሻንጉሊት ልሆን ሆነ ። ድጋሚማ አልባባትም ሃሃ

ወሬ ለመጀመር ያህል ሸምቀቆ ያለው ቁምጣ ስቤ ፥ ሃው ማች ? አልኩ ። እሷ ሰው ጤፏ እቴ ፥ ከስልኳ ቀና ሳትል በእጇ ወደመደብሩ አናት ጠቆመቺኝ ። የመደብሩ አናት ላይ 300 ተሰርዛ #200 ONLY የሚል ካርቶን ተለጥፏል ። እንግሊዘኛ በከንቱ አባክኜ ሳላስወራትማ አሌድም ብዬ ወደ ኪሴ ገባሁ ። ጊቭ ሚ ሃሃ

ቁምጣውን ልታወርድ ስትንጠራራ ያጠለቀችው ቫንስ ሸራ ከአይኔ ገባ ። የእግር ቁጥሯ ርዝመት ከቁመቷ ይስተካከላል ቢባል ማጋነን አይሆንም። የሰው ልጅ ዘሩ እንዲህ በመለያየቱ እየተገረምኩ ከፈልኩ ። ፈገግ ብላ በለዘዘ አፍ ፥

- ታንኪ'ዩዩ ፎ ባይይይንግ ! አለች ።

ከምስጋናዋ ጋር ግን የፈነዳ ፈንጂ ነበር ። ፍንዳታው በእንግሊዘኛ መኮላተፉ አደለም ። ብቻ ... ፈንጂ ለመጀመሪያ ግዜ ከድምፅ ተዳብሎ ከአፍ ሲወጣ አየሁ ። ጎርናና የወንድ ድምፅ ... ታንኪ'ዩዩ ፎ ባይይይንግ ! ቡ... ም !

በእታባ ሞት ፥
ምኔ እንደሮጥኩ ፥ ምኔ ከሆቴሌ እንደገባሁ ፥
ምኔ ክፍሌን እንደቆለፍኩ ፥
ምኔ ድርሳነ ሚካዔል እንዳወጣሁ ፥ ምኔ ... ሃሃሃ

-------------------------------------
Land of the free - ክፍል 2
ዘ ፍ ጥ ረ ት

[ ልዑል ዘወልደ ]

- አባ

የልጁ ድምፅ ነው ። ሁሌም ሲጠራው እንደተለኮሠ ኩራዝ ፊቱ በርቶ ከሌላው ይዳርሳል ። በትከሻው ይዞት የነበረን ፋስ አውርዶ ከቤት ሳይገባ ከበሩ መደብ ተቀመጠ ። ከቤት ተንደርድሮ የወጣው ልጁን እንደታቀፈ አድንኖ መሀል አናቱን ሳመው ።

- አባዬ

- ወዬ ፥ የኔ ልጅ ?

አፍ ከፈታ አመታት ቢሆንም ከርሱ ማውራት አልሰለችህ ብሎታል ። ሆድ ባይኖርና እርሻ ሳይሄድ ከርሱ ሲጫወት ቢውል ፥ እሱን ይመርጣል ። የበኩር ልጅ መርማሪ ነው ይሉትን ሰምቶ የባጥ የለ የቆጡን ሳይታክት ያስረዳል ። ልጁም እንደነገሩ መርማሪ ነው ፥ እስኪደክመው ወይ እስኪረካ መጠየቁን አይተውም ። መሀላቸው ሰው አይገባም ። እታፈራሁ ፥ የባሏን መምጣት እንዳየች የእግር ውሃ ልትጥድለት ወደ ማጀት ገባች ።

ቀጠለ ፤

- እንተ ነክ እንዴ የወለድከኝ አባዬ?

- ሃሃሃ አዎና ! አይ አንተ ሂሂ ፥ እናትህ እታታ'ም ግን አለችበት ።

እታታ እሳቱ ተያይዞላት ፥ አንዴ ከሳቋ አንዴ ከጭሱ ወደውስጥ እየማገች ቀድማ ተንተከተከች ። እርሷ የማያልቁ የልጆቿን ጥያቄ የምትገታበት ግላዊ መላ አላት ። ግራዋ አውልላ በስንት ያስተወችውን ጡቷን መልሳ መወተፍ ። ያኔ ከልቧ ወርዶ ጡቷን መጥባት ይጀምራል። የቸገረ የሆነበት ለአባቱ ነው ። አያጠባው ነገር ደረተ መኻን ነው ። ቀን የበሬው እንዳይበቃው ምሽት-ምሽት በልጁ ጥያቄዎች ይወዘወዛል ።

- እናንተንስ ግን ?

- እኔና እታፈራው ?

- እ ፥ እናንተን ማን ወለዳቹ ነው?

- እኛንም እንዲሁ ፥ እናት አባቶቻችን ናቸዋ ። ባለፈው እስከ ምንጅላት ያስቆጠርኩህን ረሳህ እንዴ ?

- ኧረ አረሳሁም ።

- በል እስኪ ፥

- ደምስ አየለ ፥ አየለ መኩሪያ ፥ መኩሪያ ደረጄ ፥ ደረጄ ቢሰጥ ፥ ቢሰጥ ...

- አዬ የኔ ምላጭ ፥ ና በል ተሳም

- እና እዝጋቤር ሳይሆን አየለ ነው የወለደህ?

- አሃ ሁለቱም ፥ እርሱም እግዚያብሔርም ነው እንጂ ። ሁሉንም እኮ አንድዬ ነው የፈጠረው ።

- ቆይ እሺ እሱንስ ?

- እሱን ምን ?

- እሱንስ ማን ፈጥሮት ነው?

- ማንን ?

- እዝጋቤርን

- እ ?

- እ

- ይኸውልህ አንበሳዬ ፥ እርሱን ደግሞ ...እ....ፈጣሪ በመጀመሪያ ....እ...አለም ሳይፈጠር...እ...ከሁሉ አስቀድሞ...እ...እ...እታ ...እታፈራሁ ነይ ልጅሽን ውሰጅልኝ !
1🔥1
🔥1