መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶክተር) Dr Rodas Tadese
39.8K subscribers
567 photos
42 videos
5 files
1.03K links
ትክክለኛው ቻናሌ ይሄ ብቻ ነው። በዚ ብቻ ትምህርተ ሃይማኖትንና የኢትዮጵያ ምስጢራትን ሳይንሳዊ ጉዳዮችን በጥልቀት እንዳስሳለን። ሌሎቹ ቻናሎች የእኔ አይደሉም
Download Telegram
[ደብረ ታቦር]
ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
❖ ይኽ በዓል ከጌታችን 9ኙ ዐበይት በዓላት አንደኛው ሲኾን በዓሉ በየዓመቱ ነሐሴ 13 ላይ በታላቅ ድምቀት ይከበራል፡፡ ታሪኩ በ3ቱ ወንጌላት ላይ የተጻፈ ሲኾን ጌታችን አምላችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሌሎቹን ሐዋርያትን ከእግረ ደብር (ከተራራው ሥር) ትቶ የምስጢር ደቀ መዛሙርት የሚባሉት፣ በእምነት በተስፋ በፍቅር የሚመሰሉት፤ ዳግመኛ በነገደ ሴም በነገደ ካም በነገደ ያፌት የተመሰሉት ሦስቱን (ጴጥሮን፣ ያዕቆብን፣ ዮሐንስን) ይዟቸው ወደ ታቦር ተራራ ወጣ።

💥 የሞተውን ሙሴን ከ1644 ዓመታት በኋላ አምጥቶ፤ የተሰወረውን ኤልያስንም ከብሔረ ሕያዋን አምጥቶ የሕያዋን አምላክና የሙታን አሥነሺያቸው ርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ መኾኑን የገለጸበት ታላቅ ምስጢር የተከናወነበት ነው፡፡ (ማቴ 17፡1-9)።

❖ ጌታ 8ቱን ሐዋርያት ይዟቸው ያልወጣበት በይሁዳ ምክንያት ነው ምክያቱም ከምስጢረ መንግሥቱ ቢለየኝ ከሞቱ ገባኹበት ባለ ነበርና ነው፤ ነገር ግን በተራራው ላይ ለ3ቱ የተገለጸው ምስጢር ከተራራው ሥር ላሉት ከይሁዳ በስተቀር ተገልጾላቸዋል፤ ለእኛም እንደ ሐዋርያት ምስጢሩን ጥበቡን ይግለጽልን፡፡

❖ ብዙ ተራሮች ሳሉ የታቦር ተራራን የመረጠበት
1)አስቀድሞ የጌትነት ክብሩ በዚያ ተራራ ላይ እንደሚገልጽ ነቢዩ ዳዊት በመዝ 88፡12 ላይ፦ “ታቦር ወአርሞንኤም በስመ ዚኣከ ይትፌሥሑ” (ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ይደሰታሉ) በማለት ጌታ በዚያ ተራራ ላይ ብርሃኑን ሲገልጽ የብርሃኑ ነጸብራቅ እስከ አርሞንኤም ተራራ ድረስ እንደሚታይ የተናገረውን ትንቢት ለመፈጸም ነው፡፡

❖ ሌላው ታቦር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ 12 ጊዜያት ሲጠቀስ በተለይ በመሳ 4 እና 5 ላይ እንደተጻፈው አስቀድሞ በብሉይ ኪዳን የእስራኤል ጠላት የነበረው ሲሳራን መስፍኑ ባርቅ በተራራው ላይ ድል ነሥቶበት ነቢይቱ ዲቦራም በተራራው ላይ በደስታ አመስግናበታለች ዘምራበታለች። በተመሳሳይ መልኩ የእስራኤል ዘነፍስ የክርስቲያኖችን ጠላት የኾነውን ዲያብሎስን የኹላችን ፈጣሪ ንጉሠ ነገሥት ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራው ላይ አምላክነቱን ገልጦ ድል ስለነሣው ነቢያት ሐዋርያት ምእመናን የሚያመሰግኑት ስለኾነ ለምሳሌነቱ ተስማሚነት ያለውን የታቦርን ተራራን መርጦታል፡፡

በሲና ተራራ የአባቱን ክብር እንዳየን የርሱን ክብር ደግሞ በብሩህ ደመና በታቦር ገልጦታል።

❖ ለምን ሙሴንና ኤልያስን ከነቢያት መኻከል መረጠ? ቢሉ፦
ሀ) በማቴ 16፡13 ላይ ሐዋርያትን ስለማንነቱ እንደጠያቃቸው እንደመለሱለት ኹሉ በእውነት ጌታችን የሙሴና የኤልያስ በአጠቃላይ የነቢያት ፈጣሪ የእግዚአብሔር ልጅ መኾኑን ሲገልጽላቸው ነው።

ለ) በዘፀ 33፡17-23 ላይ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ካለው ጥልቅ ግንኙነት የተነሣ “እባክኽ ክብርኽን አሳየኝ” ብሎ ልመናን አቀረበ፤ እግዚአብሔርም "ወአነብረከ ውስተ ስቊረተ ኰኲሕ ወእከድን እዴየ በላዕሌከ እስከ አኃልፍ" (በሰንጣቃው ዐለት አኖርሃለኍ፤ እስካልፍ ድረስ እጄን በላይኽ እጋርዳለኍ፤ ካለፍኍ በኋላ እጄን አንሥቼልኽ ጀርባዬን ታያለኽ፤ ፊቴ ግን አይታይም) ብሎታል (ዘፀ ፴፫፥፲፯-፳፫)፡፡

❖ ይኸውም ጀርባ በስተኋላ እንደሚገኝ ኹሉ በኋላ ዘመን አካላዊ ቃል ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ በታቦር ተራራ ላይ እንደሚገለጽለት ሲያመለክተው ነው።

❖ ሊቁ ቅዱስ ያዕቆብም ስለ ታቦር በሚተነትነው መጽሐፉ ሙሴ በቃዴስ ባለው በመሪባ ውሃ ከእስራኤል ጋር በበደለው በደል ምክንያት ምድረ ርስት ኢየሩሳሌም እንዳይገባ አይቷት ብቻ በናባው ተራራ ላይ እንዲያርፍ ኾኗል (ዘፀ ፴፪፥፶፪፤ ዘፀ ፴፬፥፩-፰)፡፡

❖ ይኽ ለሙሴ አሳዛኝ ቢኾንም በኋላ ዘመን አካላዊ ቃል ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ሙሴ በፊት በሩቁ ያያት ግን ያልገባባት በምድረ ርስት በኢየሩሳሌም ያለች ታቦር ተራራ ላይ አምጥቶት በዘመነ ብሉይ በአካለ ሥጋ ያልገባባትን ርስት እንዲገባባት አድርጎታል፤ ይኸውም አዳምና ልጆቹ በአካለ ሥጋ ያጡትን ርስታቸው ገነትን በአካለ ነፍሳቸው ዳግመኛ ሊያገባቸው እንደመጣ የሚያመለክት መኾኑን በስፋት አስተምሯል፡፡

❖ ጌታችን በብሉይ ኪዳን ከነበሩት ከነቢያት ሙሴንና ኤልያስን በሐዲስ ኪዳን ከነበሩት ከሐዋርያት ሦስቱን በታቦር ተራራ ላይ ማውጣቱ፦

1) የታቦር ተራራ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ በመኾኗ ሲኾን በቤተ ክርስቲያናችን ብሉይ ኪዳንና ሐዲስ ኪዳን እንደሚነገሩ ለማመልከት

2) በተራራ በተመሰለች በጉባኤ ቤት ብሉይና ሐዲስ እንደሚነገሩ ለመግለጽ፡፡

3) ሌላው የታቦር ተራራ የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ስትኾን ይኸውም ጌታ ነቢያትንና ሐዋርያትን በተራራዋ ላይ መሰብሰቡ መንግሥተ ሰማያትን ነቢያትም ሐዋርያትም እንደሚወርሷን ለማመልከት

4) ሙሴ ያገባ ሲኾን ኤልያስ ድንግል ነውና መንግሥተ ሰማያትን ደናግልም ያገቡም እንደሚወርሷት ለማጠየቅ ነው፡፡

5) እንደ ያዕቆብ ዘሥሩግ ትርጓሜ ሙሴ ኦሪት ዘፍጥረትን ሲጽፍ፦ “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” (ዘፍ 1፡1) እንዳለ፤ ዮሐንስም “በመጀመሪያ ቃል ነበር” (ዮሐ 1፡1) ብሎ እንደ ሙሴ አምላክነቱን የሚመሰክር ነውና ሙሴ አስቀድሞ የጻፈልኝ፤ አኹንም ዮሐንስ አምላክነቴን የሚጽፍልኝ እኔ ነኝ ሲል ነው፡፡

6) ሙሴና ኤልያስ ይመሳሰላሉ፤ ይኸውም በሲና ተራራ 40 ቀንና ሌሊት እንደጾመ ኤልያስም በደብረ ኮሬብ 40 ቀንና ሌሊት የጾመ ነውና፨

7) ሙሴ ንጉሡ ፈርዖንን የገሠፀ እንደነበር ኤልያስም ንጉሡ አክዐብን የገሠፀ ነውና፨

8) ሙሴ ከንጉሡ ፈርዖን ፊት ሸሽቶ እንደሄደ ኤልያስም ከንግሥቲቱ ኤልዛቤል ፊት ሸሽቶ ሄዶ ነበር።

9) ዳግመኛም ሰማይኑን ዝናብ እንዳያዘንም በተሰጠው ሥልጣን ባሰረውና ከ3 ዓመት ከ6ወር ቆይታ በኋላ እንዲዘንብ በፈታው ኤልያስን እንዳመጣ ኹሉ የማሰር የመፍታት ሥልጣን ሥልጣነ ተሰጥቶት “እኔም እልሃለኹ፥ አንተ ጴጥሮስ ነኽ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥኻለኹ፤ በምድር የምታስረው ኹሉ በሰማያት የታሰረ ይኾናል፥ በምድርም የምትፈታው ኹሉ በሰማያት የተፈታ ይኾናል” (ማቴ 16፡18-19) ላለው ለጴጥሮስን ታላቅ ሰማያዊ ሥልጣን መስጠቱን ለማመልከት አምጥቷቸዋል፡፡

❖ በቤተ ክርስቲያንና በሀገራችን ያለው መንፈሳዊ አከባበር ደማቅ ነው፤ ይኽ በዓል በቤተ ክርስቲያን በማሕሌት በቅዳሴ በትምህርት የሚከበር በዓል ሲኾን በሀገርኛ የቡሄ በዓል ይባላል፤ ቡሔ ማለት ሊቁ ደስታ ተክለ ወልድ በመዝገበ ቃላት ላይ ሲገልጹት ቧ ብሎ በደብረ ታቦር የተገለጠው የጌታችንን የፊቱን ብርሃን ጸዳል የልብሱን እንደ በረዶ ነጭ መኾን ያስረዳል ስለዚኽ የብርሃን፣ ብርሃናዊ ማለት ነው፡፡

❖ በዚህ በዓል በታቦር የታየው የብርሃኑ ምሳሌ የሚሆን ችቦ ይበራል፤ ሌላው በዚኽ በዓል ሰሞን በገጠር ከተራራ ላይ እረኞች ሕጻናት ዥራፍ እየገመዱ ማስጮኻቸው ጌታ በተራራ ላይ ብርሃኑን በገለጸ ጊዜ አብ በደመና ኾኖ “እርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” ባለ ጊዜ ሐዋርያት በድምፁ ደንግጸው መውደቃቸውን ለማመለክት ነው፡፡
80👍4🔥3👎1
💥 ጌታችን ጌትነቱን ገልጦበታል። የአብ ድምፅ ተሰምቶበታልና ታቦር ተራራ ቅዱስ ነው። ቅዱስ ጴጥሮስም በመልእክቱ "ከገናናው ክብር፦ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይኽ ነው የሚል ያ ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ምስጋናን ተቀብሎአልና፤ እኛም በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይኽን ድምፅ ከሰማይ ሲወርድ ሰማን።" በማለት ገልጦታል (2ኛ ጴጥ 1:17-18)

❖ ሌላው ሙሉሙሉ ዳቦ መጋገሩ በትውፊት እንደምንረዳው ጌታ ብርሃኑን ሲገልጽ ብርሃኑ እስከ አርሞንኤም ተራራ ድረስ ያበራ ስለነበር እረኞች ሌሊቱ ኹሉ ቀን መስሏቸው እዛው ስለዋሉ ቤተሰቦቻቸው “ኅብስት” ይዘውላቸው ኼደዋልና የዚያ ምሳሌ እንደኾነ በአበው ትውፊት ይነገራል፡፡

💥[በደብረ ታቦር ላይ ብርሃኑን የገለጠው አምላካችን ክርስቶስ ምስጋና ይግባው]፡፡
[መልካም በዓል]
መጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ (በድጋሚ የተለጠፈ)
113👍12
🌍👑 የእመቤታችንን ዕርገት በብሔራዊ በዓልነት የሚያከብሩ የዓለማችን ሀገራት
✍️ ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
🌸 የቅድስት ድንግል ማርያም ዕረፍት፣ ትንሣኤና ዕርገት የአንድ ሀገር፣ የአንድ ቋንቋ ወይም የአንድ ባህል በዓል ብቻ አይደለም።

💥 "እነሆም ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ኹሉ ብፅዕት ይሉኛል" (ሉቃ 1፥48) ያለቸው ትውልደ ሴም፣ ትውልደ ካም፣ ትውልደ ያፌት በመላ የሚያመሰግናት የሕዝቦች ኹሉ እናት በመኾኗ
የዕርገቷ ክብረ በዓል ከአህጉር ወደ አህጉር፣ ከሕዝብ ወደ ሕዝብ፣ ከቋንቋ ወደ ቋንቋ ተሻግሮ የሚከበር ዓለም ዐቀፍ መንፈሳዊ በዓል ነው።

🌍 ከኹሉም የሚያስደንቀው ግን በብዙ ሀገራት ይህ በዓል በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብቻ የሚከበር መንፈሳዊ በዓል ሳይሆን፣ Assumption of Mary — የድንግል ማርያም ዕርገት በመባል መንግሥታዊ ዕውቅና ያለው የሕዝብ ዕረፍት ቀን መሆኑ ነው።

🌍 የእመቤታችንን ዕርገት በሕጋዊ የሕዝብ ዕረፍት የሚያከብሩ ሀገራት

🇦🇩 አንዶራ
የእመቤታችን ዕርገት በAugust 15 ሀገር አቀፍ የሕዝብ ዕረፍት ሆኖ ይከበራል።

🇦🇹 ኦስትሪያ
Assumption Day በሚል ስም August 15 በሕጋዊ የዕረፍት ቀንነት ይከበራል።

🇧🇪 ቤልጂየም
የድንግል ማርያም ዕርገት በሀገር አቀፍ ደረጃ የሕዝብ ዕረፍት ነው።

🇭🇷 ክሮኤሺያ
የእመቤታችን ዕርገት በሀገሪቱ ታላቅ የክርስቲያን በዓልና የሕዝብ ዕረፍት ነው።

🇨🇾 ቆጵሮስ
በኦርቶዶክሳዊ ትውፊት የእመቤታችን ዕረፍት በከፍተኛ ክብር ይከበራል፤ August 15 የሕዝብ ዕረፍት ነው።

🇫🇷 ፈረንሳይ
Assomption (ዕርገታ ለማርያም) በሚል ስም August 15 በመላ ሀገሪቱ የሕዝብ ዕረፍት ነው።

🇬🇷 ግሪክ ☦️
የእመቤታችን ዕረፍት ከታላላቅ መንፈሳዊ በዓላት አንዱ ነው። በብዙ ደሴቶችና ከተሞች ሕዝቡ በሥርዓተ አምልኮ፣ በሰልፍ፣ በዝማሬና በታላቅ ሕዝባዊ ጉባኤ ያከብረዋል።

🇮🇹 ጣሊያን
August 15 Ferragosto በሚለው የታወቀ ስም ይከበራል፤ የእመቤታችን ዕርገት የዕለቱ ዋና ሃይማኖታዊ በዓል ነው።

🇱🇹 ሊቱዌኒያ
የእመቤታችን ዕርገት August 15 የሕዝብ ዕረፍት ሆኖ ይከበራል።

🇱🇺 ሉክሰምበርግ
Assumption Day በሚል ስም የሀገር አቀፍ ዕረፍት ቀን ነው።

🇲🇹 ማልታ
የእመቤታችን ዕርገት እጅግ ታላቅ ሃይማኖታዊና ሕዝባዊ በዓል ሲሆን August 15 ሕጋዊ የዕረፍት ቀን ነው።

🇲🇨 ሞናኮ
Assumption of Mary በሚል ስም በሀገር አቀፍ ደረጃ ይከበራል።

🇵🇱 ፖላንድ
የድንግል ማርያም ዕርገት August 15 ታላቅ የሃይማኖት በዓልና የሕዝብ ዕረፍት ነው።

🇵🇹 ፖርቱጋል
የእመቤታችን ዕርገት በመላ ሀገሪቱ የሕዝብ ዕረፍት ሆኖ ይከበራል።

🇷🇴 ሮማኒያ ☦️
Adormirea Maicii Domnului “የእግዚአብሔር እናት ዕረፍት” በሚል ስም ይከበራል፤ ይህም ሕጋዊ የሕዝብ ዕረፍት ነው።

🇸🇲 ሳን ማሪኖ
የእመቤታችን ዕርገት August 15 ሀገር አቀፍ የሕዝብ ዕረፍት ነው።

🇸🇮 ስሎቬኒያ
Assumption of Mary (ዕርገታ ለማርያም) በሚል ስም በሀገር አቀፍ ደረጃ ይከበራል።

🇪🇸 ስፔን
August 15 የእመቤታችን ዕርገት በብዙ ከተሞች በሃይማኖታዊ ሰልፍና በታላቅ ክብር ይከበራል፤ ሀገር አቀፍ የሕዝብ ዕረፍትም ነው።

🇻🇦 ቫቲካን
የድንግል ማርያም ዕርገት ከታላላቅ የድንግል ማርያም በዓላት አንዱ ሆኖ በታላቅ ሥርዓት ይከበራል።

🇱🇧 ሊባኖስ
ብዙ ሃይማኖቶች የሚኖሩባት ሀገር ቢሆንም፣ የድንግል ማርያም ዕርገት ሕጋዊ የሕዝብ ዕረፍት ነው። ይህም የእመቤታችን ክብር ከአንድ ሃይማኖታዊ ማኅበረሰብ በላይ የማኅበራዊ ስፋት እንዳለው ያሳያል።

🇨🇱 ቺሊ
በላቲን አሜሪካ የእመቤታችንን ዕርገት August 15 በሕጋዊ የሕዝብ ዕረፍት ደረጃ ከሚያከብሩ ሀገራት አንዷ ናት።

🌍 በአፍሪካ የሚያከብሩ ሀገራት

🇧🇯 ቤኒን
የእመቤታችን ዕርገት August 15 ሕጋዊ የሕዝብ ዕረፍት ነው።

🇧🇫 ቡርኪና ፋሶ
የዕርገት በዓል በመንግሥት ዕውቅና ያለው የሕዝብ ዕረፍት ነው።

🇧🇮 ቡሩንዲ
August 15 የእመቤታችን ዕርገት በሕጋዊ የዕረፍት ቀንነት ይከበራል።

🇨🇲 ካሜሩን
Assumption Day በሚል ስም ሀገር አቀፍ የሕዝብ ዕረፍት ነው።

🇨🇫 ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ
የእመቤታችን ዕርገት በሀገሪቱ ሕጋዊ የሕዝብ ዕረፍት ነው።

🇨🇮 ኮትዲቯር
August 15 የእመቤታችን ዕርገት በሕዝባዊ ዕረፍት ደረጃ ይከበራል።

🇬🇦 ጋቦን
የዕርገት በዓል መንግሥታዊ ዕውቅና ያለው የሕዝብ ዕረፍት ነው።

🇬🇳 ጊኒ
August 15 የእመቤታችን ዕርገት ሕጋዊ የዕረፍት ቀን ነው።

🇲🇬 ማዳጋስካር
የድንግል ማርያም ዕርገት በሀገር አቀፍ ደረጃ ይከበራል።

🇲🇺 ሞሪሸስ
የእመቤታችን ዕርገት በሕጋዊ የሕዝብ ዕረፍት ደረጃ ይከበራል።

🇷🇼 ሩዋንዳ
August 15 የእመቤታችን ዕርገት ሕጋዊ የሕዝብ ዕረፍት ነው።

🇸🇳 ሴኔጋል
ብዙዎቹ ሕዝቦቿ ሙስሊም ቢሆኑም የእመቤታችን ዕርገት የሕዝብ ዕረፍት ቀን ሆኖ ይከበራል።

🇸🇨 ሲሸልስ
የእመቤታችን ዕርገት August 15 ሕጋዊ የሕዝብ ዕረፍት ነው።

🇹🇬 ቶጎ
Assumption Day በሚል ስም ሀገር አቀፍ የሕዝብ ዕረፍት ሆኖ ይከበራል።

እነዚህ ሀገራት በቋንቋ፣ በባህል፣ በአህጉር፣ በታሪክና በማኅበራዊ አወቃቀር የተለያዩ ቢሆኑም፣ በአንድ ዕለት የአምላክን እናት ዕርገት ክብር በማሰብ ይገናኛሉ።

🌹 በአውሮፓ ትከበራለች፤
🌍 በአፍሪካ ትከበራለች፤
🌎 በላቲን አሜሪካ ትከበራለች፤
🌏 በመካከለኛው ምሥራቅም ትከበራለች።

👑🌹 የንጉሡ የክርስቶስ እናት በዕርገቷ በሰማይ ባሉ መላእክት እንደተመሰገነች ስሟም በምድር ላይ በብዙ ሕዝቦች ይመሰገናል።

🌸 ኢትዮጵያ ሀገራችንም የእመቤታችንን ክብር በጥልቅ መንፈሳዊ ትውፊት ከጠበቁ ጥንታዊ ክርስቲያናዊ ሀገራት አንዷ ናት።
☦️ ጾመ ፍልሰታ ከነሐሴ 1 እስከ 16 ድረስ በጾም፣ በጸሎት፣ በቅዳሴ፣ በሰዓታት፣ በስብሐተ ነግህ፣ በውዳሴና ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ በማሕሌት፣ በምስጋና ይከበራል።

💥 እመቤታችን ለኢትዮጵያውያን በበዓል ቀን ብቻ የምትታሰብ እናት አይደለችም። ስሟ በየዕለቱ በቅዳሴ፣ በውዳሴ፣ በማሕሌት፣ በሰዓታት፣ ይዘከራል።

💐 ይኹን እንጂ የፍልሰታ በዓል በኢትዮጵያ የፌዴራል ሕጋዊ የሕዝብ ዕረፍት አይደለም። ይህም ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነጻጸር ለ60 ሚሊየን አማኞቿ በእጅጉ ያሳዝናል።

🌸 ቅዱስ ሲኖዶስም ይኽ በበዙ ሀገራት በብሔራዊ በዓልነት የሚከበረውን የእመቤታችንን ዕርገት ከሚመለከታቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመመካከር የቅድስት ድንግል ማርያም በዓለ ዕርገቷን በብሔራዊ በዓል ደረጃ እንድናከብር እንዲያደርግ በታላቅ አክብሮት እጠይቃለሁ።

💐 በአስተያየት መስጫው ላይ እናንተም ጥያቄያችሁን አቅርቡ።

https://t.me/+xN518gdGKvswNzE0

💥 መጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
(ነሐሴ 15/ 2018 ዓ.ም.)
161👍25
🌕🌑 በዓመቱ የ2018 ዓ.ም. የመጨረሻዋ ሙሉ ጨረቃ የሚታይ ከፊል የጨረቃ ግርዶሽ በኢትዮጵያ
ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
🔭 ሳይንሳዊ፣ 📖 መጽሐፍ ቅዱሳዊና 🇪🇹 የኢትዮጵያ ሥነ ፈለክ እይታዬ

💥 ባለፈው ዓመት 2017 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የዓመቱ መጨረሻ የመጨረሻዋ ሙሉ ጨረቃ ጳጉሜን 2 ከምሽቱ 2 ሰዓት ሙሉ የጨረታ ግርዶሽ በአድናቆት አይተናል።

🌓 በዚህም 2018 ዓ.ም በድጋሚ የነሐሴ 22 ማለዳ (ሊነጋጋ) በ2018 ዓ.ም. የመጨረሻዋ ሙሉ ጨረቃ ዕለት ከፊል የጨረቃ ግርዶሽ (Partial Lunar Eclipse) ይታያል።

በተለይ ይህ ግርዶሽ የሚያስደንቀው በከፍተኛው ደረጃ ጨረቃዋ ሙሉ በሙሉ ሳትጋረድ እስከ 96% ገደማ የሚሆነው ክፍሏ በምድር ዋና ጥላ ውስጥ መግባቱ ነው።
🌓 ለአንባብያን በተራ ቁጥር ጥቂት ለመጻፍ ያህል:-

🌍 1. የጨረቃ ግርዶሽ ምንድን ነው?

☀️ ፀሐይ 🌍 ምድር 🌕 ጨረቃ

በአንድሮሜዳ መጽሐፍ ላይ በስፋት እንደተጻፈው የጨረቃ ግርዶሽ የሚፈጠረው ምድር በፀሐይና በጨረቃ መካከል ስትገባ ነው።

ፀሐይ ብርሃኗን ወደ ጨረቃ ትልካለች፤ ነገር ግን ምድር በመካከል ስትገባ የምድር ጥላዋ በጨረቃ ላይ ያርፋል።

🌑 የምድር ጥላ ኹለት ዋና ክፍሎች አሉት፦

🔸 Penumbral Shadow ደብዛዛው የውጭ ጥላ
🔸 Umbral Shadow ጥቁሩና ዋናው ጥላ

ጨረቃ ከፊል ክፍሏን ወደ Umbra ስታስገባ Partial Lunar Eclipse ከፊል የጨረቃ ግርዶሽ ይባላል።

ስለዚኽ በስፋት ለማወቅ የኢትዮጵያ የከዋክብት ሊቃውንት የተራቀቁበትን "ትርጓሜ ሚጠተ ብርሃናት ዘሔኖክ" መጽሐፍ አንብቡ።

🇪🇹 2. የዚህ ግርዶሽ መጀመሪያውን ከኢትዮጵያም ማየት ይቻላል።

🌘 ዛሬ ሊነጋጋ በኢትዮጵያ ሰዓት ሌሊት 10:23 ወይም በፈረንጆች 4:23 አካባቢ Penumbral ግርዶሽ ይጀምራል።

🌑 ሊነጋጋ 11:33 ወይም (5:3 አካባቢ የሚታየው ከፊል ግርዶሽ ይጀምራል።

🌅 12:17 ጠዋት (6:17) ጠዋት አካባቢ ጨረቃ በአዲስ አበባ ትጠልቃለች።

ስለዚህ በኢትዮጵያ የምናየው የግርዶሹን መጀመሪያ ክፍል ብቻ ነው፤ የግርዶሹ ዓለም ዐቀፍ ከፍተኛ ደረጃ ሲደርስ ጨረቃዋ በአዲስ አበባ ከአድማስ በታች ትሆናለች።

👁️ የሚመከረው የመመልከቻ አቅጣጫ፦ ምዕራብ ደቡብ ምዕራብ

⛰️ ሕንፃና ተራራ ያልጋረደው የምዕራብ አድማስ ያለው ከፍ ያለ ቦታ የተሻለ ነው።

🌑 ይህ ግርዶሽ ሙሉ የጨረቃ ግርዶሽ (Total Lunar Eclipse) አይደለም።

ነገር ግን ጨረቃዋ በጣም ጥልቅ ምድር ጥላ ስለምትገባ፣ በከፍተኛው ደረጃ 96% ገደማ የሚሆነው የጨረቃ ዲስክ በምድር ዋና ጥላ ውስጥ ይሆናል።

🌕➡️🌖➡️🌗➡️🌘

በመሆኑም በዓይን ሲታይ ወደ ሙሉ ግርዶሽ በጣም የቀረበ ይመስላል።

🔴 4. “የደም ጨረቃ” ለምን ትባላለች?

በጨረቃ ግርዶሽ ጊዜ ጨረቃ አንዳንድ ጊዜ ቀይ፣ መዳብማ ወይም ብርቱካናማ መልክ ልትይዝ ትችላለች።

ይህ የሚፈጠረው ብርሃን በምድር ከባቢ አየር ሲያልፍ ነው።

🌍 የምድር ከባቢ አየር አጭር ሞገድ ያለውን ሰማያዊ ብርሃን በብዛት ይበትናል፤ ቀይና ብርቱካናማ ብርሃን ግን ወደ ምድር ጥላ ውስጥ ተጣምሞ ሊደርስ ይችላል።

ይህ በሳይንስ Rayleigh scattering ከሚባለው የብርሃን መበተን ጋር የተያያዘ ነው።

🌅 ፀሐይ ስትጠልቅ ሰማዩ ቀይ የሚመስለውና በጨረቃ ግርዶሽ ጨረቃ ቀይ የምትመስለው ተዛማጅ የብርሃን ሂደት ነው።

📖 5. ጨረቃ፣ ፀሐይና ከዋክብት በመጽሐፍ ቅዱስ

መጽሐፍ ቅዱስ ፀሐይን፣ ጨረቃንና ከዋክብትን በተደጋጋሚ ይጠቅሳል።

«“እግዚአብሔርም ሁለት ታላላቅ ብርሃናትን አደረገ፤ ታላቁን ብርሃን ቀንን እንዲገዛ፥ ታናሹንም ብርሃን ሌሊትን እንዲገዛ።”
✠ ዘፍጥረት 1፥16»

እንዲሁም፦

«“ለምልክቶችና ለዘመናት፥ ለዕለታትና ለዓመታትም ይሁኑ።”
✠ ዘፍጥረት 1፥14»

ይህ ክፍል የሰማይ ብርሃናት ቀን፣ ዘመንና ዓመትን ለመለየት እንደሚያገለግሉ ያሳያል።

🌕 6. “ጨረቃ ወደ ደም እንደምትለወጥ”

በነቢዩ ኢዩኤል፦

«“ፀሐይ ወደ ጨለማ፥ ጨረቃም ወደ ደም ትለወጣለች፥ ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ።”
✠ ኢዩኤል 2፥31»

ይህንኑ ቃል ቅዱስ ጴጥሮስ በሐዋርያት ሥራ ይጠቅሳል፦

«“ፀሐይ ወደ ጨለማ፥ ጨረቃም ወደ ደም ትለወጣለች።”
✠ ሐዋርያት ሥራ 2፥20»

⚠️ ነገር ግን አንባብያን በእዚህ ላይ ጥንቃቄ ያስፈልጋል።

እያንዳንዱን የጨረቃ ግርዶሽ “ይህ የኢዩኤል ትንቢት ፍጻሜ ነው” ብሎ መወሰን አይገባም።

መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ምስሎች በትንቢታዊና በፍጻሜያዊ ዐውድ ይጠቀምባቸዋል፤ የጨረቃ ግርዶሽ ደግሞ በሥነ ፈለክ ሕግ ሊሰላና አስቀድሞ ሊታወቅ የሚችል የተፈጥሮ ክስተት ነው።

7. ሰማያት የፈጣሪን ሥራ ይናገራሉና ግርዶሽን መመልከት ፍርሃት ብቻ የሚፈጥር ነገር መሆን የለበትም። የፍጥረትን ሥርዓትና ድንቅነት ለማሰብም ዕድል ነው።

«“ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፤ ጠፈርም የእጆቹን ሥራ ያወራል።”
✠ መዝሙር 19፥1»

☀️ ፀሐይ
🌍 ምድር
🌕 ጨረቃ

በተወሰነ ሥርዓት መጓዛቸው የሰማይ አካላት እንቅስቃሴ በሕግና በሥርዓት መሆኑን ያሳያል።

🇪🇹 8. ጨረቃና የኢትዮጵያ የዘመን የሥነ ፈለክ እውቀት

ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ከፀሐይ፣ ከጨረቃ፣ ከከዋክብትና ከዘመን አቆጣጠር ጋር የተያያዘ ረጅም ታሪክና ዕውቀትና ሀብት አላት። ከ88ቱ ሕብራተ ከዋክብት ውስጥ እንደ ሀገር ለ3 ጊዜያት የተጠቀሰችው ኢትዮጵያ ብቻ ናትተ

በቤተ ክርስቲያንም የበዓላት አቆጣጠር፣ በፀሐይም በጨረቃም ይለካሉና የባሕረ ሐሳብ ስሌት ትልቅ ቦታ አለው።

ስለዚህ የሰማይ አካላትን መመልከት ለአባቶቻችን የማይታወቅ ነገር አልነበረም፤ ዘመንን ለመለየት፣ ወራትን ለማስላትና የበዓላትን ጊዜ ለመወሰን የሥነ ፈለክ ምልከታና ስሌት ከዘመን አቆጣጠር ጋር ተያይዞ ኖሯል። እጅግ የብዙ ብዙ የአስትሮኖሚ መጻሕፍት ጽፈውልናል። በመኾኑም ትውልዱ ይህንን ሀብቱን በሚገባ መጠበቅ ይገባዋል።

🌓 ሳይንስ በዘመናችን በብዙ የተራቀቁ መሣሪያዎች ታግዞ የሚነግረንን ግርዶሽ ቀደምቶቹ ኢትዮጵያውያን ተራቀውበት መርምረውት ጽፈውበት ኖረዋል።

👁️ 9. ግርዶሹን እንዴት እንመልከት? ለሚለው
🌑 ከፊል የጨረቃ ግርዶሽ በዓይን ማየት ደህንነቱ የተጠበቀ ነው።

☀️ የፀሐይ ግርዶሽ እንደሚያስፈልገው ልዩ eclipse glasses አያስፈልግም።

🔭 Binoculars ወይም Telescope ካለ የምድር ጥላ በጨረቃዋ ላይ ሲገባ በተሻለ ሁኔታ ለመመልከት ይረዳል።

📷 ፎቶ ለማንሳትም ከ11:30 ጠዋት በኋላ ጨረቃዋ ወደ ምዕራብ አድማስ በጣም ዝቅ ስለምትል ከፍ ያለና አድማሱ ክፍት የሆነ ቦታ ይመረጥ።

🌕🌑 10. በጨረቃ ግርዶሽ ጊዜ የምናየው በጨረቃ ላይ የወደቀውን የምድራችንን ጥላ ነው።

🌍➡️🌑

ስለዚህ ነሐሴ 22 ሊነጋጋ ሲል ማለዳ ወደ ጨረቃ ስንመለከት፣ በሌላ የሰማይ አካል ላይ የራሳችንን ዓለም ጥላ እያየን ነው።

በመጨረሻም 🌕 ነሐሴ 22 ቀን 2018 ዓ.ም.
🌑 August 28, 2026
🇪🇹 ኢትዮጵያ — አዲስ አበባ
ማለዳ ደመና ከሌለ ወደ ምዕራብ ሰማይ ተመልከቱ።

የምድር ጥላ በጨረቃ ላይ ሲገባ፣ የሰማይ አካላትን ሥርዓት ያስረዳናል፤ እምነት ደግሞ ፍጥረትን በድንቅነትና በምስጋና እንድናይ ይጋብዘናል።

«“ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፤ ጠፈርም የእጆቹን ሥራ ያወራል።”
✠ መዝሙር 19፥1»
79👍13👏6🔥2
🌌🌕🌍☀️🌑🌌
🌸ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
49👍9
ያስገረመኝ ግርዶሹ በሑት Pisces = 12ኛው የዞዲያክ ምልክት ነው፤ ግርዶሹም በኢትዮጵያ የተከሰተው በ12ኛው ወር — ነሐሴ ውስጥ ነው። ውሃ፣ ስሜት፣ ሕልም፣ ውስጣዊ እውቀት (intuition)፣ ርኅራኄ፣ መንፈሳዊነት፣ መልቀቅና የአንድ ዑደት ፍጻሜ ጋር ይያያዛል። ስለዚኽ በተለያየ ቦታ ከውሃ መድረቅ ወይም ከውሃ መጥለቅለቅ ጋርም ሊያያዝ ይችላል።
115👏18👍15