መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶክተር) Dr Rodas Tadese
39.7K subscribers
552 photos
42 videos
5 files
993 links
ትክክለኛው ቻናሌ ይሄ ብቻ ነው። በዚ ብቻ ትምህርተ ሃይማኖትንና የኢትዮጵያ ምስጢራትን ሳይንሳዊ ጉዳዮችን በጥልቀት እንዳስሳለን። ሌሎቹ ቻናሎች የእኔ አይደሉም
Download Telegram
የ2018 ዓ.ም. የአጽዋማትና የበዓላት አወጣጥ
👉 በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
(እንደሚታወቀው በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዓመቱ አጽዋማትና በዓላት የሚወጣበት ሲኾን የባሕረ ሐሳብ ሊቅ በቃሉ ማውጣት ካልኾነ በንባብም ቢኾን ወጥቶ መገበሪያው የሚባረክበት ታላቅ ዕለት በመኾኑ በተለይ የባሕረ ሐሳብ መምህር በሌለባቸው እንዲያወጡበት እኔ የተማርኩትን የባሕረ ሐሳብ ዐዋጅ ከዚኽ በመቀጠል ጽፌያለኹ።

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ንዌጥን በረድኤተ እግዚአብሔር ጽሒፈ ቀመረ ባሕረ ሐሳብ ዘድሜጥሮስ ሊቀ ጳጳሳት ዘእስክንድርያ ጸሎቱ ወበረከቱ የሃሉ ምስሌነ ለዓለመ ዓለም አሜን።
👉 ይኽ መጽሐፍ መርሐ ዕውራን፤ ባሕረ ሐሳብ ይባላል፤ መርሐ ዕውራን አለው አላዋቂዎችን መርቶ ወደ ዕውቀት የሚያደርስ ስለኾነ፤ ሐሳብ ቊጥር ነው ብፁዓን እለ ተኃድገ ሎሙ ኀጢአቶሙ ወእለ ኢኃሰበ ሎሙ ኲሎ ጌጋዮሙ እንዲል።
☄️ ባሕረ ሐሳብ አለው ባሕር እስኪለምዱት ድረስ ያስፈራል ይገርማል፤ ከለመዱት በኋላ በልብ ተኝቶ ይውሏል ይኽም መጽሐፍ እስኪለምዱት ድረስ ያስፈራል ይገርማል ከለመዱት በኋላ ብዙ ምስጢር አስታውቆ ደስ ያሰኛልና።
☄️ አንድም ባሕር ከለመዱት በኋላ ከመሠረቱ ወርዶ አሸዋ ይዞ ይወጧል፤ ይኽም መጽሐፍ ከለመዱት በኋላ ብዙ ምስጢር ያስታውቃል ያስመርምራል።
☄️ አንድም የባሕር አዟሪቱ መንገዱ ብዙ ነው የዚኽም መጽሐፍ መንገዱ ስልቱ ብዙ ነውና።
አንድም "ሐሳበ ባሕር" ይላል ባሕር ዘመን ነው "ሠፈራ ለባሕር በመሥፈርት ወደለዋ ለዓለም በመዳልው መኑ ዘአእመረ ስፍሐ ሰማይ ወዕመቀ ቀላይ" እንዲል በባሕር ውስጥ ያለውን እግዚአብሔር እንጂ ሰው እንዳያውቀው በዘመንም ኹሉ የሚደረገውን እግዚአብሔር እንጂ ሰው አያውቀውምና፤ "ኢኮነ ለክሙ ታእምሩ መዋዕለ ወአዝማነ ዘሠርዐ አብ" እንዲል፡፡

👉 ድሜጥሮስ ማለት መጽሔት ማለት ነው፤ አንድም ፀሓይ ማለት ነው ሰውን በትምህርቱ ብሩህ ያደርጋልና የድሜጥሮስ ትውልዱ ነገዱ ከአዝማደ እስክንድርያ ነው ጥንተ ነገሩ እንደምን ነው? ቢሉ ያባቱ ወንድም ያጐቱ ሴት ልጅ ነበረችው አባቷ ሲሞት ልጄን ከልጅኽ አትለይብኝ አደራ ብሎት ሞተ፤ አብረው አደጉ አካለ መጠን አደረሱ ዘመኑ ሐሰተኞች የበዙበት ነበርና ርሱንም ከሌላ ብናጋባው ርሷንም ለሌላ ብንድራት ከሃይማኖት ይወጣሉ ከምግባር ያድጻሉ ሕንጻ ሃይማኖት ከሚፈርስ ሕንጻ ሥጋ ይፍረስ ርስ በርሳቸው እናጋባቸው ብለው መከሩ መክረው አልቀረ ሠርግ አደረጉ፤ ሥርዓተ ከብካቡ ሲፈጸም ሥርዓተ መርዓዊና ሥርዓተ መርዓት ያድርሱ ብለው ከጫጉላው ቤት አግብተዋቸው ኼዱ።

👉 ርሷን አስቀድሞ መንፈስ ቅዱስ አነሣሥቶ ድሜጥሮስ ያንት ወንድምነት ለኔ የኔ እኅትነት ላንተ አልበቃ ብሎ የባዕድ ሥራ እንሥራ አልኽን አለችው፤ እኔስ የናት ያባቴን ፈቃድ ማፍረስ ይኾንብኛል ብዬ ነው እንጂ ፈቃዴም አይደል ፈቃድሽ ካልኾነ አንተወውምን አላት እንተወው አለችው፤ እንኪያስ የተለያየን እንደኾነ አንችን ለሌላ ወንድ እኔንም ለሌላ ሴት ያጋቡናልና መስለን እንኑር አላት እንኑር አለችው፤ በአንድ ቤት በአንድ አልጋ እየተኙ 48 ዘመን ኖሩ፤ ርሱን መልአኩ ቀኝ ክንፉን ርሷን ግራ ክንፉን እያለበሳቸው ያድራል፤ ሲነጋ በመስኮቱ በአምሳለ ርግብ ወጥቶ ሲኼድ ያዩታል ስለምን ቢሉ? በቅተዋልና አንድም በንጽሕናቸው ይትጉበት ብሎ።

👉 በዘመኑ የተሾመው ሊቀ ጳጳስ ሉክዮስ ሉክያኖስ ይባላል አረጀ ደከመ፤ ሕዝቡ ተሰብስበው አባታችን አንተ አረጀኽ ደከምኽ ካንተ ቀጥሎ የሚሾመውን ንገረን አሉት፤ እናንተም ወደ እግዚአብሔር አመልክቱ እኔም ወደ እግዚአብሔር አመለክታለኊ ብሎ ቀን ቀጥሮ ሰደዳቸው ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ መጣ ስሙ ድሜጥሮስ የሚባል ያለጊዜዋ ያፈራች የወይን ዘለላ ይዞ ካንተ ሊባረክ ይመጣል ካንተ ቀጥሎ የሚሾመው ርሱ ነው አለው፤ ሕዝቡም በቀጠራቸው ቀን መጡ አገኛችኹት? አላቸው እኛስ አላገኘንም አሉት እኔ አገኘኹላችኊ አላቸው፤ ስሙ ድሜጥሮስ የሚባል ያለጊዜዋ ያፈራች የወይን ዘለላ ይዞ ሊባረክ ይመጣል ከኔ ቀጥሎ የሚሾመው ርሱ ነው ለጊዜው እንቢ ይላችኋል ግድ ብላችኊ ሹሙት አላቸው፡፡

👉 ይኽም ድሜጥሮስ ተክል አጽድቆ ዕርፍ አርቆ የሚኖር ገበሬ ነበር ይላሉ፤ ከዕለታት በአንድ ቀን ተክል ለመጐብኘት ከተክል ቦታ ገብቶ ሳለ ያለጊዜዋ ያፈራች የወይን ዘለላ አገኘ ይኽንስ ከሊቀ ጳጳሱ ወስዶ ሊባረኩበት ይገባል ብሎ በንጹሕ ዕቃ አድርጎ ይዞ ኺዶ ንገሩልኝ አለ፤ እንዲኽ ያል ይዞ የመጣ ሰው ከደጅ ቁሟል ብለው ነገሩት እንዲኽ ያል ይዞ የመጣውን ከደጅ ያቆሙታልን ያገቡታልን እንጂ ግባ በለው አለው፤ ገብቶ ተባርኳል፤ ከኔ ቀጥሎ የሚሾመው ይኽ ነው ብሏቸው ወዲያው ዐረፈ፤ ቀብረው ሲመለሱ ሕዝቡ ተሾምልን አሉት።

☄️ በማርቆስ ወንበር የሚቀመጥ የተማረ ነው ደግሞም ንጹሕ ድንግል ነው፤ እኔ እንደምታውቁኝ ሕዝባዊ ነኝ ደግሞም ሥጋዊ ነኝ እንደምን አድርጎ ይኾናል አላቸው፤ እኛስ አባታችን ያዘዘንን ትተን ሌላ አንሾምም አሉት፤ ርሱም እንደማይተውት ዐውቆ ሊቀ ጳጳሱ ሲሾም ምን ያደርግላችኊ ነበር አላቸው አንቀጸ አባግዕን አንብቦ ይተረጒምልን ነበር አሉት ወንጌል አምጡልኝ አለ፤ አመጡለት እንኳን ትርጓሜውን ንባቡን አያውቀው የነበረ መንፈስ ቅዱስ ገልጾለት ተርጒሞላቸዋል፤ ይኽም ብቻ አይደለም ብሉይና ሐዲስ ተርጒሟል፡፡

👉 ከዚኽ በኋላ ከደጀ ሰላም ቆሞ አንተ በቅተኻል ተቀበል አንተ አልበቃኽም ቆይ እያለ ከልክሏቸዋል፤ ሕዝቡም ቆንጆ ሚስቱን ከቤቱ አስቀምጦ እኛን ይከለክለናል ብለው አምተውታል፤ መልአኩም "ኢትፍቅድ አድኅኖ ርእስከ ወብእሲትከ አላ አላ አድኅኖ ሕዝብከ" አለው፤ ርሱም ዕንጨት እየያዛችኊ ተሰብሰቡ ብሎ ዐዋጅ ነገረ ምእመናኑም ዕንጨት እየያዙ ተሰበሰቡ ደመራ አሠርቶ በእሳት አቃጥሎ ልብሰ ተክህኖውን ለብሶ ሊቀድስ ገባ ጸሎተ ቅዳሴውን ፈጽሞ ልብሰ ተክህኖውን እንደለበሰ በእሳቱ መኻከል እየተመላለሰ ያጥን ጀመር፤ ሚስቱም ከዚያ ነበረችና "ስፍሒ አጽፈኪ" ልብስሽን ዘርጊ አላት ዘረጋች እሳቱን እየታፈነ ከልብሷ ላይ አደረገላት ልብሷ ሳይቃጠል ቀርቷል ሕዝቡም አባታችን ይኽን ተአምራት ያደረግኸው ስለምን ነው አሉት፤ አምታችኹኝ አላቸው፤ አላበጀንም በድለናል ይቅር በለን አሉት፤ ይፍታሕ ወይኅድግ ያንጽሕ ወይስረይ ብሎ ናዟቸዋል፤ ኑዛዜ ከዚያ ወዲኽ ተጀምሯል፡፡

👉 ድሜጥሮስ በተሸመ በ27 ጌታ ባረገ በ207 ዘመን ይኽን መጽሐፍ ተናግሮታል፤ ስለምን ቢሉ ከሐዋርያት ጀምሮ እስከ ርሱ የነበሩ ምእመናን ዐቢይ ጾምን የጥምቀት ሳኒታ ጀምረው በየካቲት 21 ይፈጽሙ ነበር፤ ሕማማትንም ወአጐንድዮሙ መዋዕለ ይላል በመጋቢት ያደርጉ ነበር እንዲኽ ማድረጋቸው ተጠምቆ ጹሟል ሕማሙም በመጋቢት ነው ሲሉ፤ አጽዋማትን በዓላትን እንዳገኙ ያደርጉ ነበር፤ ርሱ ግን በዘአለበዎ መንፈስ ቅዱስ ይላል ሰኞ የሚኾነውን ከሰኞ ረቡዕ የሚኾነውን ከረቡዕ ኀሙስ የሚኾነውን ከኀሙስ ዐርብ የሚኾነውን ከዐርብ እሑድ የሚኾነውን ከእሑድ እንዳይወጣ ኢየዐርግ ኢይወርድ እየሰጠ ወስኖታል፤ አይወጣም አይናወጥም ቢናወጥስ አጽዋማት በዓላትም እንደቀድሞ በኾኑ ነበር፤ ርሱም በዘአለበዎ መንፈስ ቅዱስ ባልተባለም ነበር፡፡
86👏4👍3🥰2😁1
👉 ድሜጥሮስ ነነዌ፣ ዐቢይ ጾም፣ ጾመ ሐዋርያት ከሰኞ፤ ደብረ ዘይት፣ ሆሣዕና፣ ትንሣኤ፣ ጰራቅሊጦስ ከእሑድ፤ ርክብ፣ ምሕላ ድኅነት ከረቡዕ፤ ዕርገት ከኀሙስ፤ ስቅለት ከዐርብ እንዳይወጣ ግለጽልኝ ብሎ ግብር ገባ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ መጥቶ ከሌቱ በ23 በ23 እስከ 7 ሱባኤ ቈጥረኽ 161 ይኾናል፤ 150ውን ገድፈኽ 11 ይተርፋል፤ አበቅቴ በለው ብሎታል፤ መልአኩም ቅዱስ ሚካኤል ነው፤ ከመዓልቱም እስከ 7ት ሱባኤ ቈጥረኽ 49 ዕለት ይኾናል 30ውን ገድፈኽ 19ኝን መጥቅዕ በለው ብሎታል። የድሜጥስ ጥንተ አበቅቴና መጥቅዕ ይኽ ነው፤ የሌሊቱን አብዝቶ የቀኑን ስለምን አሳነሰው ቢሉ የሌሊት ልቡና ክት የቀን ልቡና ባካና ነውና፤ አንድም ቀን ሲፈርድ ሲተች ጉባኤ ሲያደርግ ይውላልና፤ ሕማማትን ያስቀድማል ትንሣኤን ያስከትላል ሐዘኑ ለደስታው እንዲመች፤ ካላዘኑ ደስታ ካልጾሙ ፋሲካ የለምና፤ የሐዲሱን ያስቀድማል ዘመኑ ነውና የብሉዩን ወደኋላ ያደርጋል፤ አልቦ መጥቅዕ ወአበቅቴ አንድ ወገን ያደርጋል፤ ታሪክ፣ መቅድም፣ አርዕስት እየሰጠ ወስኖታል፤ ታሪኩ ይኽ ነው፤ መቅድሙን ያመጣዋል።

👉 በአብ ስም አምነን አብን ወላዲ ብለን በወልድ ስም አምነን ወልድን ተወላዲ ብለን በመንፈስ ቅዱስ ስም አምነን መንፈስ ቅዱስን ሠራጺ ብለን ምንም ለአጠይቆ አካለት ሦስት ስላልነ በባሕርይ በሕልውና አንድ አምላክ ብለን አምነን ጸሎቱ ልመናው በረከቱ ክብሩ ይደርብንና የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት ድሜጥሮስ የተናገረውን የባሕረ ሐሳብ ቊጥር መጽሐፍን በእግዚአብሔር አጋዥነት እንጀምራለን፡፡

💥 እግዚአብሔር እንደዛሬው ኹሉ አንድነቱ ሦስትነቱን ሳይጠቀልለው ሦስትነቱ አንድነቱን ሳይከፍለው በአንድነት በሦስትነት ሳለ ክብሩ በብቻው እንደቀረ ዐውቆ ዓለምን ልፍጠር ብሎ አሰበ፤ አስቦም አልቀረ ሰውና መላእክትን ስሙን ለመቀደስ ክብሩን ለመውረስ የቀረውን ፍጥረት ግን ለአንክሮ ለተዘክሮ ለምግበ ሥጋ ለምግበ ነፍስ ፈጠረ “ወኲሉ ዘተፈጥረ ለመፍቅደ ነባብያን ቦ እምኔሆሙ ለምህሮ ወቦ እምኔሆሙ ለተገብሮ፤ ወእንዘ ኢየኀድግ ርእሶ ዘእንበለ ሰማዕት፤ ወለእመ ፈቀድከ ታእምር ዘንተ እምአፍአ ብከ ሰማዕት ወመምህር ዘይመርሐከ ኀበ ዝንቱ፤ ወዘኢያስተርኢ እግዚአብሔር እምፍጥረተ ዓለም ይትዐወቅ በፍጥረቱ” እንዲል፤ እግዚአብሔርስ የፈጠረው ፍጥረት እያንዳንዱ ቢቈጠር ፍጡር ተናግሮ ባልፈጸመውም ነበር፤ እየወገን እየወገኑ ግን ብዙውን አንድ ብዙውን አንድ እያሉ ቢቈጥሩ ከእሑድ እስከ ዐርብ የፈጠረው ሥነ ፍጥረት 22 ነው፡፡ እስከዚኽ አርዕስት ነው፤ ይኽንንም በሥነ ፍጥረት ይመለከቷል።

👉 የፀሓይ ጥንታት ሦስት የጨረቃን ዐምስት የሚል ነውና፤ ይኽ ዓለም የተፈጠረበት ዕለተ እሑድ ጥንተ ዕለት፤ አዝርዕት፣ አትክልት፣ ዕፀዋት የተፈጠሩበት ዕለተ ሠሉስ ጥንተ ቀመር፤ ብርሃናት የተፈጠሩበት ዕለተ ረቡዕ ጥንተ ዮን ይባላል፤ “እሑድ ወሠሉስ ወረቡዕ ዘውእቶሙ ሠለስቱ ጥንታት” እንዲል

👉 ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ዘመን ቢቈጠር በፀሓይ 7518 ዘመን፤ በጨረቃ 7748 ዘመን ከ9 ወር ከ12 ዕለት ይኾናል።

ከልደተ ክርስቶስ አስቀድሞ የነበረው በፀሓይ 5500 ዘመን፤ በጨረቃ 5668 ዘመን ከ10 ወር ከ9 ዕለት፤ ይኽ ዓመተ ኩነኔ፣ ዓመተ ፍዳ ይባላል፡፡

👉 ከልደተ ክርስቶስ ወዲኽ ያለው ግን በፀሓይ 2018 ዘመን ነው፤ በጨረቃ 2079 ዘመን ከ11 ወር ከ3 ዕለት ይኽ ዓመተ ሥጋዌ፣ ዓመተ ምሕረት ይባላል፤ መላው ዓመተ ዓለም ነው፤ ዓመተ ዓለም ባለው ዓመተ ምሕረት የሚል ይገኛል፤ ጊዮርጊስ ወልደ አሚድም ዓመተ ዓለምን ዓመተ ምሕረት ብሎ ተርጒሞታል፤ ስለምን ዓመተ ዓለምን ዓመተ ምሕረት አለው ቢሉ? ሰው በዚኽ ዓለም ሳለ ኀጢአት ሠርቶ ንስሓ ቢገባ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረት የሚያገኝበት ስለኾነ ዓመተ ዓለምን ዓመተ ምሕረት ብሎ ተርጒሞታል “በዕለት ኅሪት እሰምዐከ ወበዕለተ መድኀኒት እረድአከ ወናሁ ይእዜ ዕለት ኅሪት ወናሁ ዮም ዕለተ አድኅኖት” እንዲል፡፡

👉 ለዚኹም መሥፈሪያ ሰባት አዕዋዳት አሉት፤ ምንና ምን ቢሉ? ዐውደ ዕለት፣ ዐውደ ወርኅ፣ ዐውደ ዓመት፣ ዐውደ አበቅቴ፣ ዐውደ ፀሓይ፣ ዐውደ ማኅተም፣ ዐውደ ቀመር ናቸው፡፡ ከሊኹም ሦስቱ በዕለት አራቱ በዓመት ይቈጠራሉ፤ በዕለት የሚቈጠሩት ሦስቱ ዐውደ ዕለት፣ ዐውደ ወርኅ፣ ዐውደ ዓመት ናቸው፤ በዓመት የሚቈጠሩ አራቱ ዐውደ አበቅቴ፣ ዐውደ ፀሓይ፣ ዐውደ ማኅተም፣ ዐውደ ቀመር ናቸው፡፡

👉 ዐውደ ዕለት ከእሑድ እስከ ቀዳሚት ያሉ ሰባት ዕለታት ናቸው፤ እሊኽም አውራኅን ለማስገኘት በሰባት በሰባት ሲመላለሱ ይኖራሉ “እስመ ኊልቊ ሰብአቱ በኀበ ዕብራውያን ፍጹም ውእቱ” እንዲል

👉 ዐውደ ወርኅ በፀሐይ ዘወትር ፴ በጨረቃ አንድ ጊዜ 29፤ አንድ ጊዜ ፴ ይኾናል፤ እሊኽም ዓመታትን ለማግኘት በ፴ በ፴ ሲመላለሱ ይኖራሉ፡፡

👉 ዐውደ ዓመት በፀሓይ 365 ዕለት በጨረቃ 354 ዕለት ነው፤ በፀሓይማ ምነው 365 ዕለት ከ15 ኬክሮስ ከ6 ካልኢት፤ በጨረቃ 354 ዕለት ከ22 ኬክሮስ ከ1 ካልዒት ከ37 ሣልሲት ከ52 ራብዒት ከ48 ኀምሲት አይደለውም ቢሉ “ወበውስተ ውሁድኒ ንብል አልቦ ወኢአሐዱ” እንዲል መጽሐፍ ትርፍ ትቶ ጐደሎ መልቶ መቊጠር ልማድ ነውና ፷ ካልመላ ብሎ እንዲኽ አለ እንጂ ቊጥሩስ አለ “እስመ ልማደ መጽሐፍ ይነግር ኊልቈ ምሉዓ ወፍጹመ ወየኀድግ ዘተርፈ ወይዌስክ ዲበ ሕፀፅ ካልዐ” እንዲል፤ ዕለታትን አዕዋድ አላቸው አውራኅን የሚያስገኙ ስለኾነ፤ አውራኅን አዕዋድ አላቸው ዓመታትን የሚያስገኙ ስለኾነ “ወበከመ ይትወለዳ አውራኅ እምዕለታት ወዓመታት እምአውራኅ ከማሁ ይትወለዳ አዕምሮታት እመከራት ወእምግባራት እንዲል፡፡

👉 ዐውደ አበቅቴ 19 ዓመት ነው በዚኽ ፀሓይና ጨረቃ መንገዳቸውን ፈጽመው በተፈጠሩበት ኆኅት ይገናኙበታል፤ ሊቀ ነቢያት ሙሴ፣ መምህራነ ወንጌል ሐዋርያት፣ ሊቀ ጳጳሳት ዲሜጥሮስ ከ፳ው አንድ ቀመር አንድ ተረፈ ቀመር፤ ከ፵ው ኹለት ቀመር ኹለት ተረፈ ቀመር፤ ከ፷ው 3 ቀመር 3ት ተረፈ ቀመር፤ ከ፹ው 4 ቀመር 4ት ተረፈ ቀመር፤ ከ፻ው 5ቀመር 5ት ተረፈ ቀመር እያላችኊ ቊጠሩ ማለታቸው ከዚኽ የተነሣ ነው “ወእምዘተርፈከ እምዐሠርቱ ወተሰዓቱ ተአትት እምኔሁ አሐደ ዓመተ እስመ ለዛቲኒ ዐሠርቱ ወተሰዓቱ ሙሴ ገብራ በጥበበ እግዚአብሔር ዘይገብሩ ባቲ ፍስሐ አይሁድኒ ወክርስቲያንኒ” እንዲል

👉 ዐውደ ፀሓይ 28 ዓመት ነው፤ በዚኽ ዕለትና ወንጌላዊ ይገናኙበታል፤ ዕለቱ ረቡዕ ወንጌላዊዉ ማቴዎስ ነው፤ ረቡዕ ማቴዎስ እንዲል፤ ዕለትን ፀሓይ አለው “ወበትእዛዝከ ይቀውም ዕለት” እንዲል፤ ወንጌላዊዉን ፀሓይ አለው “አንትሙ ውእቱ ብርሃኑ ለዓለም” ካለው አንዱ ርሱ ነውና፤ በሰንጠረዥ ፀ፣ ደ ይላል፤ ዐውደ ፀሓይ ማለት ነው፡፡

👉 ዐውደ ማኅተም 76 ዘመን ነው፤ በዚኽ አበቅቴ ወንጌላዊ ይገናኙበታል፤ አበቅቴው 18 ወንጌላዊዉ ዮሐንስ ነው፤ ማኅተም አለው አበቅቴው ለአበቅቴ ወንጌላዊዉ ለወንጌላዊው ፍጻሜ ነውና፡፡
56👏12
👉 ዐውደ ቀመር 532 ዘመን ነው፤ በዚኽ ዕለት፣ ወንጌላዊ፣ አበቅቴ እሊኽ 3ቱ ይገናኙበታል፤ ዕለቱ ሠሉስ፣ ወንጌላዊዉ ማቴዎስ ነው፤ ሠሉስ ማቴዎስ እንዲል አበቅቴው አልቦ ነው “ጥንቱ ለቀመር ዕለተ ሠሉስ ወንጌላዊ ማቴዎስ ወፍጻሜሁ ዕለተ ሰኑይ ወንጌላዊ ዮሐንስ” እንዲል፤ በዐውደ ፀሓይ ቦታ ዐውደ ማኅተም፤ በዐውደ ማኅተም ቦታ ዐውደ ፀሓይ የሚል ይገኛል፤ ከኹለቱ አንዱ ቢታጣ አንዱ ከቀመር ገብቶ ይቈጠራል፤ ቀመርን ለሦስቱ ስም በሰጡ ጊዜ ዐውደ ቀመር ዐቢይ ቀመር፤ ዐውደ ማኅተም ማዕከላዊ ቀመር፤ ዐውደ አበቅቴ ንዑስ ቀመር ይባላል፤ ዐቢይ ቀመር መደቡ 14 ቊጥሩ 532፣532፤ ማዕከላዊ ቀመር መደቡ 6 ቊጥሩ 76፣76፤ ንዑስ ቀመር መደቡ 3 ቊጥሩ 19፣19 ነው፡፡

👉 ከዚኽም ዓመተ አበቅቴን (ወንበር) ለማግኘት 7518 ዘመን በዐቢይ ቀመር ቢቀምሩ 532፤ 532 የተፈጸመለት 14 ዐቢይ ቀመር፤ 19፤ 19 የተፈጸመለት 3 ንዑስ ቀመር ኾኖ 13 ዓመት ይተርፋል።

👉 መላውንም በማእከላዊ ቀመርም ቢቀምሩ 76፤ 76 የተፈጸመለት 98 ማእከላዊ ቀመር 19፤ 19 የተፈጸመለት 3 ንዑስ ቀመር ኹኖ 13 ዓመት ይተርፋል፡፡

👉 በዐውደ ፀሓይም ቢቀምሩ 28፤ ኻያ ስምንት የተፈጸመለት 266 ዐውደ ፀሓይ፤ 19፤ 19 የተፈጸመለት 3 ንዑስ ቀመር ኹኖ 13 ዓመት ይተርፋል፡፡

👉 መላውንም በንዑስ ቀመር ቢቀምሩ 19፤ 19 የተፈጸመለት 395 ንዑስ ቀመር ኹኖ 13 ዓመት ይተርፋል፡፡

👉 7518ቱን ዘመን በቀመረ ዐረብም ቢቀምሩ 228፤ 228 የተፈጸመለት 32 ቀመረ ዐረብ፤ 19፤ 19 የተፈጸመለት 11 ንዑስ ቀመር ኹኖ 13 ዓመት ይተርፋል።

👉 ስመ አቅማር ብዙ ነው አይቶ መተው ነው፤ አሐደ አዕትት ለዘመን እንዲል ስለተጀመረ ተቈጠረ ስላልተፈጸመ ታተተ ብሎ ከ13ቱ አንዱን ቢያትቱ 12 ይተርፋል፤ 12 ዓመተ አበቅቴ ወጣ ገጠር ወንበር ይላል፡፡

👉 አበቅቴን ለማግኘት ከ12ቱ ዓመተ አበቅቴ 11፤ 11 ዕለት ቢነሡ 132 ይኾናል፤ ከ120ውን 30ውን በ4፤ ፴ ቢገድፉት 1 ይተርፋል፤ 12 አበቅቴ ወጣ በዘመነ ማርቆስ፡፡

👉 መጥቅዕንም ለማግኘት ከ12 ዓመተ አበቅቴ 19 ዕለት ቢነሡ 228 ይኾናል፤ 228ቱን በ7፤ ፴ ቢገድፉት 18 ይቀራል፤ 18 መጥቅዕ ወጣ በዘመነ ማርቆስ፤ 18 መጥቅዕና 12 አበቅቴ ፴ ይኾናሉ እንጂ ከ፴ አይወጡም ከ፴ አይወርዱም፤ “ዓዲ መጥቅዕ ወአበቅቴ ክልኤሆሙ እመ ይበዝኁ ወእመ ይውኅዱ ኢየዐርጉ እም፴ ወኢይወርዱ እም፴ ወባሕቱ ወትረ ይከውኑ ፴” እንዲል።

(ከዚኽ በኋላ አበቅቴ ከመጠነ ሠርቀ መዓልትና ከሚለው ዠምሮ…ኢየዐርግ ኢይወርድ ኹሉ እንደ ታሪኩ አስገባ)

መጥቅዕ 18 መጥቅዕ ቢበዛ በመስከረም ይውላልና መስከረም ኀሙስ ይብታል፤ ኀሙስ እስከ ኀሙስ 8 / 15/ ዓርብ 16/ ቅዳሜ 17/ እሑድ 18 በዓለ መጥቅዕ መስከረም 18 እሑድ።

የእሑድ ተውሳክ 7/ 18 ና 7 = 25 ጥር 25 መባጃ ሐመር
በመስከረም ሳኒታ ጥር ዐርብ ይብታል፡፡ ዐርብ - ዐርብ 8/15/22/ ቅዳሜ 23/ እሑድ 24/ ሰኞ 25 ጥር 25 ነነዌ

የዐቢይ ጾም ተውሳክ 14፤ 14 + 25 = 39 ሠላሳ ቢገድፉ 9 ይተርፋል።
እሑድ እስከ እሑድ 8 ሰኞ 9
የካቲት 9 ዐቢይ ጾም

የደብረ ዘይት ተውሳክ 11፤ 11 እና 25= 36 ሠላሳ ቢገድፉ 6 ይተርፋል መጋቢት ማግሰኞ ይብታል። ማግሰኞ 1/ ረቡዕ 2/ ኃሙስ 3/ ዓርብ 4/ ቅዳሜ 5/ እሑድ 6 መጋቢት 6 ደብረ ዘይት

የሆሣዕና ተውሳክ 2፤ 2 እና 25 = 27፤ ማግሰኞ - ማግሰኞ 8/15/22/ ረቡዕ 23/ ኃሙስ 24/ ዓርብ 25/ ቅዳሜ 26 እሑድ 27 መጋቢት 27 ሆሣዕና።

ከዚኽም በዓለ ፍሥሕን (የአይሁድ ፋሲካን) ይናገሯል፤ ፍሥሕን 4 ነገር ይጠብቃታል፤ ገቦ መጥቅዕ፤ ሰሙነ ሕማማት፤ 190 ዕለት፤ 14 ሌሊት፤ ፍሥሕ የዕለት ተውሳክ አትሻም በደረቅ መጥቅዕ ነው የምትወጣው መጥቅዑ 18 የፍሥሕ ተውሳክ 10= 28፤ መጋቢት 28 ፍሥሕ
በዓሉን አናከብረውም ስለምን እናወጣዋለን ቢሉ ሐዋርያት ፍሥሕን ከትንሣኤ ጋራ አንድ አድርጎ ያዋለ ካህን ቢኾን ከክህነቱ ይሻር፤ ምእመን ቢኾን ከምእመናን ይለይ ብለው አውግዘዋልና ስለዚኽ ለይተን እናወጣዋለን፡፡

የስቅለት ተውሳክ 7፤ 7 እና 25 = 32፤ ሠላሳ ቢገድፉ 2 ይተርፋል። ሚያዝያ ኃሙስ ይብታል። ኀሙስ 1 ዐርብ 2
ሚያዝያ 2 ስቅለት

የትንሣኤ ተውሳክ 9፤ 9 እና 25 =34፤ ሠላሳ ቢገድፉ 4 ይተርፋል። ኀሙስ 1 ዐርብ 2 ቅዳሜ 3 እሑድ 4 ሚያዝያ 4 ትንሣኤ

የርክብ ተውሳክ 3፤ 3 እና 25 = 28፤ ኀሙስ - ኃሙስ 8/15/22/ ረቡዕ 28
ሚያዝያ 28 ረቡዕ

የዕርገት ተውሳክ 18፤ 18 እና 25= 43፤ ሠላሳ ቢገድፉ 13
ግንቦት ቅዳሜ ይብታል። ቅዳሜ - ቅዳሜ 8 እሑድ 9 ሰኞ 10 ማግሰኞ 11 ረቡዕ 12 ኃሙስ 13 ግንቦት 13 ዕርገት

የጰራቅሊጦስ ተውሳክ 28፤ 28 እና 25 = 53፤ ፴ውን ገድፎ 23 ይቀራል፤ ቅዳሜ - ቅዳሜ 8/15/22/ እሑድ 23
ግንቦት 23 ጰራቅሊጦስ

የጾመ ሐዋርያት ተውሳክ 29፤ 29 እና 25= 54፤ ፴ውን ገድፎ 24 ይቀራል፤ ቅዳሜ - ቅዳሜ 8/15/22/ እሑድ 23/ ሰኞ 24 ግንቦት 24 ጾመ ሐዋርያት

የምሕላ ድኅነት ተውሳክ 1፤ 1 እና 25= 26፤ እሑድ 23 ሰኞ 24 ማግሰኞ 25 ረቡዕ 26 ግንቦት 26 ምሕላ ድኅነት።

👉 ዓመተ ወንጌላዊን ከዚኽ ይናገሯል፤ ወለእመ ፈቀድከ ታእምር ዓመተ ወንጌላዊ ትከፍሎ ለዘመን ኀበ አርባዕቱ እድ ለእመ ተርፈ አሐዱ ማቴዎስ ወክልኤቱ ማርቆስ ወሠለስቱ ሉቃስ ወለእመ ዐረየ ክፍል ዮሐንስ እንዲል፤ ዓመተ ወንጌላዊን ለማወቅ ዓመተ ዓለምን ከአራት ከፍሎ አንድ ቢተርፍ ወንጌላዊዉ ማቴዎስ መኾኑ፤ ኹለት ቢተርፍ ማርቆስ፤ ሦስት ቢተርፍ ሉቃስ ቢተካከል ዮሐንስ መኾኑን በዚኽ ይታወቃል፤ 7518 ዘመን ለአራቱ ወንጌላውያን ቢያካፍሉ 1879 ደርሷቸው 2 ይተርፋል። 2 ቢተርፍ ማርቆስ ያለው ይኽ ነው፤ ዛሬ ወንጌላዊዉ ማርቆስ መኾኑ በዚኽ ታውቋል፡፡

👉 ጥንተ ዮንንም ከዚኽ ይናገሯል፤ ወለእመ ፈቀድከ ታእምር ጥንተ ዮን ትከፍሎ ለዘመን ኀበ አርባዕቱ እድ ወትዌስክ ቦቱ መጠነ ራብዒት ወትገድፎ በበሱባኤ ወዘተርፈከ እምሱባኤ ተአትት እምኔሁ አሐደ ዓመተ ወእምዝ ይከውን ጥንተ ዮን እንዲል፤ ጥንተ ዮንንም ለማወቅ ዓመተ ዓለምን ከአራት ከፍሎ 5ኛ መጠነ ራብዒት 6ኛ ጳጉሜንን አክሎ፤ በሱባዔ ገድፎ ከሱባዔ የተረፈውን አንዱን አትቶ 1 ቢተርፍ ጥንተ ዮን ረቡዕ መኾኑን መስከረም ረቡዕ መባቱን፤ 2ት ቢተርፍ ኀሙስ፤ 3 ቢተርፍ ዐርብ፤ 4 ቢተርፍ ቀዳሚት፤ 5 ቢተርፍ እሑድ፤ 6 ቢተርፍ ሰኞ፤ 7 ቢተርፍ ማግሰኞ መኾኑ በዚኽ ይታወቃል፡፡
አከፋፈል እንዳለፈው 7518 ዘመን ለአራቱ ወንጌላውያን ቢያካፍሉ 1879 ደርሷቸው 2 ይተርፋል፤ ይኽን በሱባዔ ይገድፏል፤ ከሺው 300 ነሥቶ 700 ግዱፍ፤ ከ800ው አንዱን መቶ ነሥቶ 700 ግዱፍ፤ 400 ይተርል፤ ከ100ው 2፤ ከ400ው 8፤ ከ8ቱ አንድ፤ ከዚያም 1 እና 79 = 80 ይኾናል፤ ከ80ው 77ቱን በ11 ሱባዔ ቢገድፉ 3 ይተርፋል፡፡
69👍2
ከአንዱ ወንጌላዊ 3 ከ4ቱ ወንጌላውያን 12፤ መጠነ ራብዒት፤ 6ኛ ጳጉሜን 1879 ዕለት ትኾናለች፤ ርሷ በዕለት፤ ወንጌላዊ በዓመት ይተካከላሉና ግድፈት እንዳለፈው፤ መጠነ ራብዒት 3= 15፤ ከዓመተ ወንጌላዊ የተረፈ 2=17፤ ከ17ቱ 14ቱን በ2 ሱባዔ ቢገድፉ 3 ይተርፋል፤ አሐደ አዕትት ለዘመን እንዲል ስለተዠመረ ተቈጠረ ስላልተፈጸመ ታተተ ብሎ ከ3ቱ አንዱን ቢያትቱ 2 ይተርፋል፤ 1 ቢተርፍ ኃሙስ ያለው ይኽ ነው፤ የኃሙስ ጥንተ ዮን 2 ነውና፡፡ ጥንተ ዮንም ማለት ጥንተ ፀሓይ፤ ጥንተ ጨረቃ፤ ጥንተ ከዋክብት ማለት ነው፤ ጥንተ ዮን ብሂል ጥንተ ተፈጥሮቶሙ ለፀሓይ፤ ወወርኅ ወከዋክብት እንዲል፡፡

👉 ዕለተ ቀመርንም ለማወቅ ለጥንተ ዮን ከወጣው አንዱን ሳያትቱ በሱባዔ ገድፎ 1 ቢተርፍ ማግሰኞ መኾኑ፤ 2 ቢተርፍ ረቡዕ፤ 3 ቢተርፍ ኀሙስ፤ 4 ቢተርፍ ዐርብ፤ 5 ቢተርፍ ቀዳሚት፤ 6 ቢተርፍ እሑድ፤ 7 ቢተርፍ ሰኞ መኾኑ በዚኽ ይታወቃል፤ ለጥንተ ዮን የወጣው 3 ነው፤ 3 ቢተርፍ ኃሙስ ያለው ይኽ ነው። ዕለተ ቀመርም ማለት ቀመር የተዠመረበት ዕለት ማለት ነው፤ ቀመር የተዠመረው ማግሰኞ ነውና፡፡

👉 ዕለተ ዮሐንስንም ከዚኽ ይናገሩታል፤ ወለእመ ፈቀድከ ታእምር ዕለተ ዮሐንስ ትከፍሎ ለዘመን ኀበ አርባዕቱ እድ፤ ወትዌስክ ቦቱ መጠነ ራብዒት፤ ወክልዔተ ዕለተ ጠቢባን ወትገድፎ በበሱባዔ ወዘተርፈከ እምሱባዔ ኢተአትት አሐደ ዓመተ፤ ወእምዝ ይከውን ዕለተ ዮሐንስ እንዲል ዕለተ ዮሐንስን ለማወቅ ዓመተ ዓለምን ከአራት ከፍሎ፤ 5ኛ መጠነ ራብዒት፤ 6ኛ ጳጉሜንን አክሎ፤ 7ኛ 2ት ዕለተ ጠቢባንን ጨምሮ በሱባዔ ገድፎ ከሱባዔ የተረፈውን አንዱን ሳያትቱ አንድ ቢተርፍ ዕለተ ዮሐንስ እሑድ መኾኑ፤ 2 ቢተርፍ ሰኞ፤ 3 ቢተርፍ ማግሰኞ፤ 4 ቢተርፍ ረቡዕ፤ 5 ቢተርፍ ኀሙስ፤ 6 ቢተርፍ ዐርብ፤ 7 ቢተርፍ ቀዳሚት መኾኑ በዚኽ ይታወቃል፡፡

👉 ለጥንተ ዮን የወጣ 3 እና 2 ዕለተ ጠቢባን= 5። 5 ቢተርፍ ኃሙስ ያለው ይኽ ነው፤ ዕለተ ዮሐንስም ማለት አሻቅቦ ወደ ላይ እስከ ፍጥረተ ዓለም፤ አቈልቊሎ ወደ ታች እስከ ምጽአተ ክርስቶስ ቢቈጥሩ ለወንጌላዊዉ ዮሐንስ የሚደርሰው ቀን ማለት ነው፤ ወለእመ ፈቀድከ ታእምር ዘኀለፈ ይመርሐከ ዝንቱ እስከ ፍጥረተ ዓለም ወለእመ ፈቀድከ ታእምር ዘይመጽእ ያበጽሐከ ዝንቱ እስከ ምጽአተ ክርስቶስ እንዲል፤ አንድም ሠርቀ ቲቶን ዕለተ ዮሐንስ ይለዋል፤ ቲቶ የተባለው መስከረም ነው፤ የመጥምቁ ዮሐንስ በዓል የሚውልበት ቀን ማለት ነው፤ ርዕሰ ዐውደ ዓመት ዮሐንስ ወላዴ መጥቅዕ ወአበቅቴ እንዲል፡፡

👉 ዕለተ በዓል ዘኀለፈ ዕለተ በዓል ዘይመጽእ የእሑድ አሚሩ ሰንበተ ክርስቲያንን ለማወቅ በዘመኑ የወጣውን ጥንተ ዮን፤ ሠርቀ መዓልት፤ 2 ዕለተ ጠቢባን በየወሩ የሚገኘውን አጽፈ ወርኅ እሊኽን 4ቱን አንድ አድርጎ ቈጥሮ በሱባዔ ገድፎ 1 ቢተርፍ እሑድ አሚሩ፤ 2 ቢተርፍ ሰኞ ሰኑዩ፤ 3 ቢተርፍ ማግሰኞ ሠሉሱ፤ 4 ቢተርፍ ረቡዕ ረቡዑ፤ 5 ቢተርፍ ኀሙስ ኀሙሱ፤ 6 ቢተርፍ ዐርብ ሰዱሱ፤ 7 ቢተርፍ ቀዳሚት ሰቡዑ፤ 8 ቢተርፍ በሱባዔ ገድፎ እሑድ አሚሩ የሚያሰኘው ይኽ ነው፡፡

👉 አጽፈ ወርኅም ማለት የወርኁ ከወርኅ የሚደረብ ማለት ነው፤ ይኽስ ከምን ይገኛል ቢሉ? ወሩን በሱባዔ ቢገድፉ 4 ሱባዔ ኾኖ 2 ይተርፋል፤ የወርኁ 2 የዓመቱ 24፤ እንዲኽ ግን ስለኾነ ለመስከረም አጽፈ ወርኅ የለውም በጥንተ ዮን፤ በሠርቀ መዐልት በኹለት ዕለተ ጠቢባን ይቈጠራል፤ በእሊኽ በ3ቱ ይቈጠራል፤ ጥንተ ዮን 2፤ ሠርቀ መዐልት 1 = 3፤ ኹለት ዕለተ ጠቢባን፤ 5 ይኾናል፤ 5 ቢተርፍ ኃሙስ ያለው ይኽ ነው።

👉 ዕለተ ጠቢባንም ማለት ጠቢባን ሥላሴ ይኽነን ዓለም የፈጠሩበት፤ ጠቢባን መላእክት ሥላሴን የሚያመሰግኑበት ቀን ማለት ነው፤ (ዬ) ጠቢባን ሥላሴ ይኽነን ዓለም ከእሑድ እስከ ዐርብ ፈጥረዋል፤ ጠቢባን መላእክት ሥላሴን ዘወትር ያመሰግናሉ ብሎ የቊጥር መጽሐፍን የተማሩ መምህራን ዕለተ ሰንበትን፤ 6ቱ ዕለታትን፤ ያለፉትን የሚመጡትን በዓላት የሚያውቁባቸው የሚያሳውቁባቸው ማለት ነው፤ ዕለተ ጠቢባንም የተባሉ እሑድና ሰኞ ናቸው፤ ከቀመር ገብተው አልተቈጠሩም፡፡

👉 ዕለተ ምርያ አዕዋዲትንም ለማወቅ የፀሓይ ዐውደ ዓመት 365 ዕለት ከ15 ኬክሮስ ከ6 ካልዒት ነው፤ ይኽነን በሱባዔ ቢገድፉት 52 ሱባዔ ኾኖ 1 ዕለት ከ15 ኬክሮስ ከ6 ካልዒት ይተርፋል፤ ይኽቺውም አንድ ዕለት የተባለችው ዐምስተኛዪቱ ጳጒሜን ናት፤ ዕለተ ምርያ አዕዋዲት ይላታል፤ ዕለተ ምርያ ማለት ዕለተ መድኀኒት ማለት ነው፤ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበትን ቀን የምታሳውቅ ማለት ነው፤ ርሷ በዋለች ልደት ይውላልና፤ አዕዋዲትም አላት ዘመኑን የምታዘዋውር የምታለዋውጥ ማለት ነው፤ እሑድ የዋለውን ሰኞ፤ ሰኞ የዋለውን ማግሰኞ እንዲውል የምታደርግ ርሷ ናትና፡፡

👉 መጠነ ራብዒት 6ኛ ጳጉሜንም ለማወቅ የአንዱ ዓመት ኬክሮስ 15፤ የ2 ዓመቱ 30፤ የ4 ዓመቱ 60 ኬክሮስ ነው፤ 60ው ኬክሮስ 1 ዕለት ይኾናል፤ ይኽቺውም በሉቃስ መጨረሻ ዮሐንስን ተጠግታ የምትውል ስድስተኛዪቱ ጳጉሜን ናት፤ መጠነ ራብዒት፣ ሠግረ ዮሐንስ ይላታል፤ መጠነ ራብዒት አላት ርሷ በዕለት ወንጌላዊ በዓመት ይተካከላሉና፤ ሠግረ ዮሐንስም አላት ዮሐንስ ተራምዶ የሚውልባት ስለኾነ፡፡

👉 ዕሪና መዓልትና ዕሪና ሌሊትንም ለማወቅ የአንዱ ዓመት ካልዒት 6፤ የ5ቱ ዓመት 30፤ የ10ሩ ዓመት 60 ይኾናል፤ 60ው ካልዒት 1 ኬክሮስ ይኾናል፤ የ100ው ዓመት 10 ኬክሮስ፤ የ600 ዓመት 60 ኬክሮስ፤ 60ው ኬክሮስ አንድ ዕለት ይኾናል፤ ይኽቺውም ሰባተኛዪቱ ጳጉሜን ናት፤ ዓለም በተፈጠረ በ600 ዘመን ዕሪና መዓልት ዕሪና ሌሊት ኾኗል፤ ዓለም ከተፈጠረ ዠምሮ እስከ ዛሬ ድረስ 12 ዕሪና መዓልት 12 ዕሪና ሌሊት ኾኖ 13ኛው ከተዠመረ 318 ኾኖ በዘመነ ማርቆስ ይኸውም ሊመላ 282 ይቀራል፡፡

(ከዚኽ በኋላ እንዲኽ ብሎ ባሕረ ሐሳብ አውጪው እንዲኽ ብሎ አሥርቆት ያውጣ፡፡)
በዘንዜከር ሐሳባተ ሕጉ ወትእዛዙ ለእግዚእነ ወአምላክነ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዘ ሀሎነ በዘመነ ቅዱስ ማርቆስ ወንጌላዊ ቡሩክ ያብጽሐነ እስከ ዘመነ ሉቃስ ዜናዊ፤ ወንጌላዊ አለው ማርቆስን ባለዘመን ነውና፤ ዜናዊ አለው ሉቃስን የሚመጣ ነውና ወረኛ ንጉሥ እንዲሉ፡፡

👉 በሰብዐ ወኀምስቱ ምእት ዐሠርቱ ወሰመንቱ ዓመተ ዓለም፡፡ በኀምሳ ወኀምስቱ ምዕት ዓመተ ዓለም፤ በዕሥራ ምዕት ዐሠርቱ ወሰመንቱ ዓመተ ምሕረት፤ ሠረቀ ለነ ወርኀ መስከረም ቡሩክ ያብጽሐነ እስከ ወርኀ ጥቅምት በሰላመ እግዚአብሔር አሜን።

👉 አበቅቴ 12፤ ሠርቀ መዓልት 1፤ ሕጸጽ 1= 14፤ ዐሡሩ ወረቡዑ ሠርቀ ሌሊት፤ ዐሡሩ ወሰሙኑ ሠርቀ ወርኅ፤ አሚሩ ሠርቀ መዓልት፤ ኃሙሱ ሠርቀ ዕለት፤ ዮም በዛቲ ዕለት ዘአቅረብነ ለከ አምኀ ስብሐት ያዐርጉ ለነ መላእክት ተወከፍ ለነ እግዚአ ስብሐት፤ ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡።
ከዚያም ዘመነ ማቴዎስ ዐለፈ ዘመነ ማርቆስ መሾሙን 3 ጊዜ ዐውጆ። ይጠናቀቃል

አዘጋጅ፡- መጋቤ ሐዲስ ዶከተር ሮዳስ ታደሰ
የቴሌግራም ቻናሌ https://t.me/Rodas9
217👍41🥰12👏12
🌓አራቱ ተከታታይ የሰማይ ክስተቶች መንፈሳዊ አምሳል🌒
✍️ በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
🌟 በሉቃስ 21፡25 -28 ላይ ✍️ “በፀሐይና በጨረቃም በከዋክብትም ምልክት ይሆናል ...ይኽም ሊኾን ሲጀምር ቤዛችኹ ቀርቦአልና አሻቅባችኹ ራሳችሁን አንሡ።”
በማለት ጌታችን እንዳስተማረ እነዚኽ ሰማያዊ አካላት በየጊዜው የሚያሳዩት ታላላቅ መንፈሳዊ ምልክት አለና በሰማይ ላይ በተከታታይ ስለታዩት አራት ታላላቅ መንፈሳዊ የጊዜያችን ምልክቶች በስሱ ለማለት ወደድኊ፡፡

💥 በጳጒሜን 2/ 2017 ዓ.ም. “ርኅወተ ሰማይ” (የሰማይ መከፈት) በሚደረግበት በዕለተ እሑድ ምሽት በሑት (ዓሣዎች) (ፓይሲስ) መናዝል ውስጥ የ2017 ዓ.ም. የዓመቱ የመጨረሻዋ የሙሉ ጨረቃ ዕለት ታላቅ የደም ጨረቃ (ሙሉ የጨረቃ ግርዶሽ) ተከናውኖ ኹላችንም በዐይናችን ያየንበት ድንቅ ዕለት ነበረ፡፡

💥 ፀሓይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብትን እግዚአብሔር ከተፈጠረበት ዋና ዓላማ የመዠመሪያው ለምልክት ነውና “በርኅወተ ሰማይ” (በሰማይ መከፈት) ዕለት መከናወኑ ግጥጥሞሽ ሳይኾን ሥርዓት ነው።
☄️ በማጠናቀቂያ የጳጉሜን ወር ዳግመኛም በመናዝል ማጠቃለያ በፓይሲስ (ሑት - ዓሣዎች) ውስጥ የተከናወነ የደም ጨረቃ በፍጻሜው ጊዜ ለዓሣዎች (የሰው) ልጆች ሕይወት የፈሰሰውን የክርስቶስን የመሥዋዕት ደምና በዕለቱ የጨረቃን ደም መምሰል እንድናስታውስ በሚገባ ያደርገናል።

☄️ በዓሉም የቅዱስ ሩፋኤል ከመኾኑ ጋር ተያይዞ "ሩፋ" ማለት "ፈውስ" ኤል "እግዚአብሔር" ነውና አቅንተው ለተማፀኑ ፈውሰ እግዚአብሔር ለተማፀኑ ኹሉ የተሰጠበት ዕለት ነው።

💥 ሑት (ዓሣ - ፓይሲስ) ብዙ ምስጢር በመያዙ በመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ኹሉ ዋና መግባቢያ ነበረ፡፡
🌟 “ዓሣ” ኢክተስ ΙΧΘΥΣ (Ichthys) ሲባል ፍቺውም በምሕጻረ ቃል “ኢየሱስ ክርስቶስ፣ የእግዚአብሔር ልጅ፣ አዳኝ” ማለት ነበረ።

☄️ በተመሳሳይ የውሃ ጠባይዕ በኾነው በዓሣዎቹ መናዝል ቀይ የደም ጨረቃ በዚኽ ዕለት ሲታይ ለመጀመሪያ ጊዜም በግብጽ በዐባይ ውሃ ላይ በሙሴ በትር የተደረገው ተአምር የውሃው ደም መኾንና የዓሣዎቹ መሞት ነበረ። ተመሳሳይ ምልክት በሰማይ በታየ በኹለተኛው ቀን ጳጉሜን 4 የዐባይ ግድብ በመጠናቀቅ የኢትዮጵያ ታላቅ ዑደት ጀምሯል።
💥💥💥
🌒 እሑድ መስከረም 11/ 2018 ዓ.ም. በዐዲሱ ዓመታችን የመዠመሪያዋ ጠፍ ጨረቃ በምትውልበት ዕለት ደግሞ በደቡብ ፓሲፊክ፣ ኒውዝላንድ፣ ምሥራቅና ደቡብ አውስትራሊያ፣ አንታርክቲካ ያሉ ቀለበታማ የፀሓይ ግርዶሽ ይታያል፡፡
🌟 ፀሓይ በዚኽ ግርዶሽ ጊዜ በሰንቡላ (ድንግል - ቪርጎ) መናዝል ውስጥ በመኾን በእሳት ቀለበት 🌚 ተሞሽራ ትታያለች፡፡
☄️ በመንፈሳዊ ትርጓሜ ሰንቡላ (ቪርጎ) በቅድስት ድንግል ማርያም እና በቤተልሔም የምትመሰል ናት፡፡
🌟 በእኛ “ሰንቡላ” በዕብራይስጥ “ቤቱላህ” ትባላላች፤ ፍቺውም “ድንግል” ማለት ነው፡፡ በግሪክም “ሴሬስና ፓርቴኖስ” ስትባል ፍቺውም “ንጽሕት ብላቴና ድንግል” ማለት ነው፡፡
☄️ በዐረቢክም “አዳራህ” ሲሏት ፍቺዋም “ንጽሕት ድንግል” ማለት ነው፡፡ ይኽችን መናዝል አምላክ በሰማይ ማኖሩ የመሲሑን ከድንግል መወለድ የሚያመለክት ሕያው ምልክት ነበረ፡፡
🌟 ፀሓይ በመስከረም 10 በመስከረም 11 ዕለት በዚኽ ግርዶሽ ወቅት በዚኽች ሰንቡላ ውስጥ እንደምታበራ በዮሐንስ ራእ 12፡1 ✍️“ወአስተርአየ ተአምር ዐቢይ በውስተ ሰማይ ብእሲት እንተ ትለብስ ፀሓየ” (“ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ ፀሐይን ተጐናጽፋ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች ያላት በራስዋም ላይ የአሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች።”
— ራእይ 12፥1
ያለውን ምልክቱ ያሳያል፡፡

☄️ መስከረም 10 ሲነሣ ከ33ቱ የእመቤታችን በዓላት አንዱ ነው፤ የቅድስት ድንግል ማርያም ልደትን ጳጒሜን 3 (September 8th) አብዛኞቹ የዓለማት ሀገራትና አብያተ ክርስቲያናት ያስባሉ፡፡ ሌላው መስከረም 10 ሲኾን፤ መጨረሻው ግንቦት 1 ይከበራል፡፡

🌟 በተአምሯ መቅድም ላይ “ቦ እለ ይቤሉ አመ ዐሡሩ ለመስከረም ልደታ ወንሕነሰ ንብል ጥዩቀ በከመ መሀሩነ አበዊነ ሊቃውንት አመ አሚሩ ለግንቦት ልደታ” (መስከረም ዐሥር ቀን ልደቷ ነው የሚሉም አሉ፤ እኛ ግን በተረዳ ነገር አባቶቻችን ሊቃውንት እንዳስተማሩን ልደቷን ግንቦት 1 ቀን ነው እንላለን) ይላል፡፡
💥💥💥
✍️ ሰኞ መስከረም 12/ 2018 ዓ.ም. ፀሐይ ልክ የምድር ወገብ ላይ ኾና በመላው ዓለም “ዕሪና መዓልት ወሌሊት” (ቀኑና ሌሊቱ እኩል የሚኾንበት) ቀን ሲኾን እኩሌ” (Autumn Equinox) ይባላል፡፡ ይህ ዕለት ፀሐይ የሰማያዊውን ሉል ወገብ አቋርጣ ወደ ደቡብ አቅጣጫ የምትሄድበት ጊዜ ሲሆን ፀሐይ ልክ የምድር ወገብ ላይ ሆና ቀንና ሌሊቱ እኩል የሚሆንበት ጊዜ ነው፡፡

✍️ ዲድስቅልያ የወቅቶችን መለወጫ ሲያይ “እስመ ይዔሪ መዓልት ወሌሊት አመ ዕሥራ ወኀሙሱ” (ቀንና ሌሊት በ25 ይተካከላልና) ይላል እንጂ መስከረም 12 – 14 ውስጥ ይመላለሳል፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በግእዝ መዝገበ ቃላት ገጽ 577 ላይ በደቃይቅ ቊጥር አራት ቀን ወደ ታች ወርዶ “አመ ዕሥራ ወአሚሩ” (በ21) ኹኗል፡፡ በኛም ብተት “አመ ዐሡሩ ወሠሉሱ” (በ13ኛው ዕለት) ወይም “ወረቡዑ” (በ14ኛው ዕለት) ኹኗል በማለት የቀመሩን ስልት ጽፈዋል፡፡ ይኽ መተካከል በየ182 ቀን የሚከናወን ሲኾን ይኸውም በግእዝ ፊደላት ቊጥር ስደራ ልክ ነው (26 ፊደላት x 7 = 182)፡፡
💥💥💥
✍️ ሰኞ መስከረም 12 - ረቡዕ 14/ 2018 ዓ.ም ሮሽ ሀሻናህ የቀንደ መለከት በዓል ይኾናል፡፡ “ሮሽ ማለት እራስ “ሀሻናህ” (ዐውደ ዓመት) ማለት ነው፡፡ በዕብራውያን ትውፊትና በቤዛንታይን ባሉት ኹሉ ትውፊት “ልደተ ዓለም” (ዓለም የተፈጠረበት ወር) ተብሎ ይታሰባል፡፡

🌟 እንደ አለቃ ኪዳነ ወልድ ትንታኔ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ቀዳማዊ ወር ኤታኒም ነበር በኋላ ግን ከግብጽ የወጡበት ኔሣን (ሚያዝያ) ስለነበር “ዝንቱ ወርኅ ይኩንክሙ ቀዳማየ አውራኅ” (ይህ ወር የወሮች መጀመሪያ ይሁናችኊ የዓመቱም መጀመሪያ ወር ይሁናችኊ) ተብለው በእነርሱ የጥቅምትን ቅድምና ለሚያዝያ የሚያዝያን 7ተኛነት ለጥቅምት (በእኛ ለመስከረም) እንዲሰጡ ታዘው ነበር ይላሉ (ዘፀ 12፡2)።

☄️ እስራኤላውያን ከግብጽ የወጡበትን ሚያዝያን ዐዲስ ዓመታቸውን እንዲያከብሩ ቢታዘዙም ግን ዓለም የተፈጠረበትን የኤታኒም 7ተኛ ወርን እንዲያከብሩ “አመ ርእሰ ሳብዕ ሠርቀ ወርኅ ግበሩ መጥቅዐ” (በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ዕረፍት በመለከት ድምፅ መታሰቢያ የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችኊ) ተብለው ታዘው ነበርና ቀንደ መለከት እየነፉ ዓለም የተፈጠረበት ወር ያከብሩ ነበር፡፡ (ዘሌዋ 23፡24)፡፡

💥 ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው ላይ
✍️ “ንፍሑ ቀርነ በጽዮን ወስብኩ በደብረ መቅደስየ ዛቲ ዕለት በዓለ እግዚአብሔር እስመ ይቤ ዛቱ በዓለ እግዚአሔር” (በጽዮን ቀንደ መለከትን ንፉ፤ በመቅደሴ ተራራ ስበኩ፤ ይኸቺ ዕለት የእግዚአብሔር በዓል ናት ብሏልና) በማለት የገለጻት ይኽቺ በዓል በብሉይ ይከበሩ ከነበሩት በዓላት አንደኛዋ ስትኾን በዘመነ ሐዲስ ደግሞ ክርስቶስ ለፍርድ ሲመጣ የሚነፋውን ቀንደ መለከት ጠቋሚ ናት፡፡
78👍3👎2🥰1
☄️ ይኸውም 7 ፍጹም ነው = ፍጻሜ ዓለምን
☄️ 7 የዕረፍት ቀን ነው = ዕረፍት መምጣቱን፤
☄️ የቀንደ መለከት መነፋት - በሊቃነ መላእክት የሚነፋውን ቀንደ መለከት ይገልጻል፡-
✍️ “መላእክቱንም ከታላቅ መለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፥ ከሰማያትም ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከአራቱ ነፋሳት ለእርሱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ።”
— ማቴዎስ 24፥31
✍️“አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ፤ ሁላችን አናንቀላፋም ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበተ ዓይን እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ እኛም እንለወጣለን።”
1ኛ ቆሮንቶስ 15፥51-52
✍️ “ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፥ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ”
— 1ኛ ተሰሎንቄ 4፥16
☄️ በመኾኑም በሰማይ መከፈት የተደረገው የጨረቃ ግርዶሽ - የአሮጌ ዑደት መጠናቀቅ
☄️ የቀለበታማ የፀሓይ ግርዶሽ - የዐዲስ ዑደት ዥማሮን
☄️ በሚዛን ወቅት ያለ የቐንና የሌሊት መተካከል - የፍርድ ሚዛንን
☄️ የቀንደ መለከት ድምፅ - ንቃተ ኅሊና በመላው ዓለም መታወጅን ይወክላል
💥 በመጨረሻም የ2018 ዓ.ም. የመጀመሪያዋ የመስከረም ሙሉ ጨረቃ ማግሰኞ መስከረም 28/ 2018 ዓ.ም. ከምሽቱ 12፡26 ላይ ደምቃ በመውጣት እስከ ሌሊቱ 12፡!2 ድረስ ሰማዩን አድምቃው ትውላለችና ለዚያ ዕከት በሰላም ያድርሰን፡፡
ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ መስከረም 10 ተጻፈ።
127👍22👏7👎2🔥2
🌟 መስከረም 12 ኢትዮጵያ የጠበቀችው ድንቅ ዕለት🌟
✍️ በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
💥 መስከረም 12 ለፕላኔታችን መሬት በሙላ ታላቅ ዕለት ናት፤ ይኽነን ጥበብ በዘመን ቀመሯና በፊደሏ የያዘችውና የምትምሰክረው ንግሥተ ጥበብ ኢትዮጵያ ናት፤ በእኛ በኢትዮጵያ አቈጣጠር መስከረም 12 በሌላው ዓለም አቈጣጠር ደግሞ እንደ ኹኔታው መስከረም (September) 21 ወይም 21 አንዳንዴም 22 ይኾናል።
🌟 በዚኽ ቀን ፀሓይ ልክ የምድር ወገብ ላይ ኾና ቀኑና ሌሊቱ በመላው ዓለም እኩል የሚኾንበት ወቅት “ዕሪና መዓልት ወዕሪና ሌሊት ዘመፀው" (የመፀው እኩሌ (Autumnal /fall equinox) ይባላል፡፡
🌟 ይኽ ዕለት ፀሐይ የሰማያዊውን ሉል ወገብ አቋርጣ ወደ ደቡብ አግጣጫ የምትኼድበት ጊዜ ሲኾን በሰሜናዊው ንፍቀ ክበብ መፀው የሚዠምርበት ዕለት ነው፡፡ በዚኽ ጊዜ ፀሓይ ልክ በምሥራቅ ትክክለኛ አቅጣጫ ላይ ወጥታ በምዕራብ ትክክለኛ አግጣጫ ላይ ትጠልቃለች፡፡

🌟 የኢትዮጵያ ዐዲሱ ዓመት መግቢያ “መስከረም” ከኾነባቸው በርካታ ምክንያት ውስጥም አንደኛው በ182 ቀን አንዴ “ዕሪና መዓልት ወዕሪና ሌሊት ዘመፀው” (የመፀው የቀንና የሌሊት መተካከል) (Autumnal /fall equinox) የሚኾንበት ወርም ጭምር በመኾኑ ነው፡፡
🌟 መጽሐፍ ስንክሳርም የዓመቱ መዠመሪያ ስለኾነው የመስከረም ወር እንዲኽ ይተነትነዋል፡-
✍️ “ወርኃ መስከረም ቡሩክ ርእሰ አውራኅ ዓመታት ዘግብጽ ወኢትዮጵያ ሰዓተ መዓልቱ ፲ወ፪ቱ ዕሩይ ምስለ ሌሊቱ ወእምዝ የሐጽጽ”
(የተባረከ የመስከረም ወር የግብጽና የኢትዮጵያ ዓመታት ወሮች ራስ ነው፤ የቀኑ ሰዓትም ከሌሊቱ ሰዓት የተስተካከለ ዐሥራ ኹለት ነው፤ ከዚኽ በኋላ እያነሰ ይኼዳል) በማለት የመፀው እኩሌ የሚደረግበት ወር እንደኾነ አስቀምጧል፡፡

💥 91 ዕለት ከ15 ኬክሮስ የአራቱ ወቅታት የዘመን ቀመር ላለን በዲድስቅልያ 30 ላይ ✍️ “እስመ ይዔሪ መዓልት ወሌሊት አመ ዕሥራ ወኀሙሱ” (መዓልትና ሌሊት በመጋቢት 25 ይተካከላል) ይላል፡፡
🌟 አለቃ ኪዳነ ወልድ በመዝገበ ቃላታቸው ገጽ 577 ላይ ሲያብራሩ በ25 ያለው የድሮውን ነው፤ ዛሬ ግን በደቃይቅ ቊጥር 4 ቀን ወደ ታች ወርዶ “አመ ዕሥራ ወአሚሩ” (በ21) ኹኗል፡፡ በእኛ ብተት ደግሞ “አመ ዐሡሩ ወሠሉሱ ወይም ወረቡዑ” (በ12 ወይም በ13) ይኾናል ብለዋል፡፡
ኹለተኛው በ182 ቀን የሚኾነው የቀንና ሌሊት መተካከል

🌟 በኢትዮጵያ አቈጣጠር መጋቢት 12 በፈረንጆች ደግሞ መጋቢት (ማርች 20 ወይም 21) ላይ የሚውለው እና ፀሓይ ልክ የምድር ወገብ ላይ ኾና ቀንና ሌሊቱ እኩል የሚኾንበት ጊዜ (ወቅት) “ዕሪና መዓልት ወዕሪና ሌሊት ዘጸደይ” (የጸደይ የቀንና ሌሊት መተካከል) (Vernal/spring equinox) ይባላል፡፡

🌟 ይኽ ዕለት ፀሓይ የሰማያዊውን ሉል ወገብ አቋርጣ ወደ ሰሜን አግጣጫ የምትኼድበት ጊዜ ሲኾን ለሰሜናዊው ንፍቀ ክበብ ላሉ ጸደይ የሚዠምሩበት ቀን ነው፡፡ በዚኽ ጊዜ ፀሓይ ልክ በምሥራቅ ትክክለኛ አቅጣጫ ላይ ወጥታ በምዕራብ ትክክለኛ አግጣጫ ላይ ትጠልቃለች፡፡ በየ182 ቀናቱ የሚኾነውን የዕሪና መዓልት ወሌሊት (ኢኪውኖክስ) ሳይንስን በሚገባ በመረዳታቸው ነበር ይኽነን መተካከል የሚደረግበት ሌላኛውን ወር “መጋቢት” ብለው ሠይመውታል፡፡

🌟 መጋቢት የሚለው ቃል “መግቦ መግቦት” ከሚለው የግእዝ ንኡስ አንቀጽ የወጣ ቃል ሲኾን ትርጒሙም የመዓልትና የሌሊት ምግብና እንደ መስከረም ትክክል የሚኾንበት ቀንና ሌሊቱ እኩል የሚመጋገብበት ወርኀ ዕሪና (የመተካከል ወር) ማለት ነው፡፡

💥 በኢትዮጵያ የሥነ ከዋክብት ትምህርት በ12ቱ ወራት የስፍረ ሰዓት የሠንጠረዥ ትምህርት ላይ የመስረምና የመጋቢት ወር ሠንጠረዥ አንድ ሲኾን ቀኑና ሌሊቱ 12 ዐሥራ ኹለት ነው፡፡በምድር ወገብ በየትኛውም ወቅት ቢኾን የሰዓተ መዓልቱ ጊዜ በዚኽ ዕለት 12 ሰዓታት ያኽል ነው፡፡

🌟 ከመጋቢት እኩሌ (March equinox) እስከ መስከረም እኩሌ (September equinox)፤ ፀሓይ በ23.5° ዲግሪ በሰሜን ምሥራቅ በኩል በመውጣት በ23.5° ዲግሪ በሰሜን ምዕራብ በኩል ትጠልቃለች፡፡

🌟 ከመስከረም እኩሌ እስከ መጋቢት እኩሌ፤ ፀሓይ በ23.5° ዲግሪ በደቡብ ምሥራቅ በኩል በመውጣት፤ በ23.5° ዲግሪ በደቡብ ምዕራብ በኩል ትጠልቃለች፡፡

🌟 በመጋቢት እና በመስከረም (ኹለቱ እኩሌዎች) የመዓልቱ ርዝማኔ 12 ሰዓታት ያኽል ነው፡፡ይኽነን ጥበብ በታላቁ የፊደል ቀመራችን ውስጥ በጥበብ ተሠናሥሎ ተዋሕዶና ተጋምዶ የተቀመጠባት ብቸኛዋ የምድራችን ሀገር ንግሥተ ጥበብ ኢትዮጵያ ናት፡፡

💥 ከፊደል [አ] እስከ ፊደል [ፐ] ከላይ ወደ ታች የተደረደሩት 26ት የግእዝ ፊደላት ናቸው፡፡
☄️ወደ ጐን ያሉት [አ] [ቡ] [ጊ] [ዳ] [ሄ] [ው] [ዞ] ደግሞ 7 ናቸው፡፡
☄️ በአጠቃላይ ለማወቅ 26 × 7 =182 ይኾናሉ፡፡
☄️ ይኸውም 365 የዓመት ቀናት ÷ 2 = 182.5 በመምጣት የዓመቱን የግማሽ ዕለት ቀመርን ፊደላቱ ይዘዋል፡፡ በምንኖርባት ምድር ላይ በግእዝ ፊደላችን ቊጥር ልክ በየ182ት ቀናት የሚከሰቱትን፡-
💥 ዕሪና መዓልት ወዕሪና ሌሊት ዘመፀው
💥 ዕሪና መዓልት ወዕሪና ሌሊት ዘጸደይ
ናቸው፡፡

🌟 በዚኽች ቀንና ሌሊቷ እኩል በሚኾንበት ሰኞ መስከረም 12 በ2018 ዓ.ም ሮሽ ሀሻናህ רֹאשׁ הַשָּׁנָה የቀንደ መለከት በዓል ይኾናል፡፡ “ሮሽ ማለት እራስ “ሀሻናህ” (ዐውደ ዓመት) ማለት ነው፡፡

☄️ በዕብራውያን ትውፊትና በቤዛንታይን ባሉት ኹሉ ትውፊት “ልደተ ዓለም” (ዓለም የተፈጠረበት ወር) Έτη Γενέσεως Κόσμου κατά 'Ρωμαίους ተብሎ ይታሰባል፡፡
https://orthochristian.com/97046.html

💥 እንደ አለቃ ኪዳነ ወልድ ትንታኔ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ቀዳማዊ ወር ኤታኒም ነበር በኋላ ግን ከግብጽ የወጡበት ኔሣን (ሚያዝያ) ስለነበር “ዝንቱ ወርኅ ይኩንክሙ ቀዳማየ አውራኅ” (ይህ ወር የወሮች መጀመሪያ ይሁናችኊ የዓመቱም መጀመሪያ ወር ይሁናችኊ) ተብለው በእነርሱ የጥቅምትን ቅድምና ለሚያዝያ የሚያዝያን 7ተኛነት ለጥቅምት (በእኛ ለመስከረም) እንዲሰጡ ታዘው ነበር ይላሉ (ዘፀ 12፡2)።

💥 እስራኤላውያን ከግብጽ የወጡበትን ሚያዝያን ዐዲስ ዓመታቸውን እንዲያከብሩ ቢታዘዙም ግን ዓለም የተፈጠረበትን የኤታኒም 7ተኛ ወርን እንዲያከብሩ፡-
✍️ “አመ ርእሰ ሳብዕ ሠርቀ ወርኅ ግበሩ መጥቅዐ” (በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ዕረፍት በመለከት ድምፅ መታሰቢያ የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችኊ) ተብለው ታዘው ነበርና ቀንደ መለከት እየነፉ ዓለም የተፈጠረበት ወር ያከብሩ ነበር፡፡ (ዘሌዋ 23፡24)፡፡

💥 ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው ላይ
✍️ “ንፍሑ ቀርነ በጽዮን ወስብኩ በደብረ መቅደስየ ዛቲ ዕለት በዓለ እግዚአብሔር እስመ ይቤ ዛቱ በዓለ እግዚአሔር” (በጽዮን ቀንደ መለከትን ንፉ፤ በመቅደሴ ተራራ ስበኩ፤ ይኸቺ ዕለት የእግዚአብሔር በዓል ናት ብሏልና) በማለት የገለጻት ይኽቺ በዓል በብሉይ ይከበሩ ከነበሩት በዓላት አንደኛዋ ስትኾን በዘመነ ሐዲስ ደግሞ ክርስቶስ ለፍርድ ሲመጣ በሊቃነ መላእክት የሚነፋውን የቀንደ መለከት ጠቋሚ ናት፡፡

💥 በተለይ ቢሊየኖች ከተመለከቱት በርኅወት ሰማይ (በሰማይ መከፈት) ከጳጉሜን 2 እሑድ ምሽት በዓሣዎች (ሑት፣ ፓይሲስ) ከተከናወነው የደም ጨረቃ ግርዶሽ ተከናወነ።
93👍9
💥 መስከረም 11/1/2018 (2+0+1+8 = 11) 11/1/11 ቀመር ከተከናወነው ቀለበታማ የፀሓይ ግርዶሽ በሰንቡላ (ቪርጎ) ከታየ በኋላ፤ መላው ዓለም ቀንና ሌሊቱ እኩለ በሚኾንበት መስከረም 12 ዕለት በዋለው በሮሽ ሀሻናህ ዕለት 100 ጥንታዊ የኾኑ ቀንደ መለከት በኢየሩሳሌም ሲነፉ ለመጀመሪያ ጊዜ መላው ዓለም የቀጥታ ሥርጭት እንዲተላለፍ መወሰኑ እንዲኾን መደረጉ እንዲኹ የኾነ አይደለም። በዓለማችን ታላቅ ጉዳይና አንድ ታላቅ የትንቢት ቀጠሮ ጊዜ በጊዜያችን እንደተቃረበ አመላካች ሊኾን ይችላልና በጣም ብዙ ያልተጠበቁ ክንውኖች በዜናም ይኹን በሌላ በሚቀጥሉት ጊዜያቶች ልናይ እንደምንችል በመረዳት ኅሊናችንን ሰብሰብ ማረግ ጥሩ ነው፡፡
✍️ በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ 11/1/2018 ዓ.ም. (2+0+1+8 = 11) 11/1/11 ተጻፈ
118👍29