መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶክተር) Dr Rodas Tadese
39.7K subscribers
552 photos
42 videos
5 files
993 links
ትክክለኛው ቻናሌ ይሄ ብቻ ነው። በዚ ብቻ ትምህርተ ሃይማኖትንና የኢትዮጵያ ምስጢራትን ሳይንሳዊ ጉዳዮችን በጥልቀት እንዳስሳለን። ሌሎቹ ቻናሎች የእኔ አይደሉም
Download Telegram
💥 ጳጉሜን 2 የደም ጨረቃ በኢትዮጵያ ሊታይ ነው
✍️ ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ (መነበብ የሚገባው ወቅታዊ)
💥 ታላቅ ክብር ባላት በ13ኛ ወራችን በጳጒሜን 2/ 2017 ዓ.ም. እሑድ ማታ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በሙሉ በዐይናቸው ሙሉ የጨረቃ ግርዶሽ ወይም ታላቅ የደም ጨረቃን ያያሉ፡፡

💥 ከ6 ዓመታት በፊት በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ እና በዶክተር ጌትነት ፈለቀ በተዘጋጀው አንድሮሜዳ መጽሐፍ ገጽ 193 ላይ የሠኔ 14/ 2012 ዓ.ም. ላይ በኢትዮጵያ በላስታ ላሊበላ ስለሚከሰተው ቀለበታማ የፀሓይ ግርዶሽ እና ጳጉሜን 2/ 2017 ዓ.ም. በኢትዮጵያ በሙሉ ስለሚታየው የሙሉ ጨረቃ ግርዶሽ (የጨረቃ ደም መስሎ መታየት) ላይ አስቀድሞ እንደተገለጸ ይታወቃል፡፡

💥 በዓመት ውስጥ 13 ሙሉ ጨረቃዎች ይታያሉ፡፡ ሌሎቹ ሀገራት 13ኛ ወራቸውን በማጥፋታቸው በ12 ወራት ውስጥ 13ኛ ሙሉ ጨረቃ ይከሰትባቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ግን ትክክለኛዋን የጳጉሜን 13ኛ ወራትን በመያዙ 13 የዓመቱ ሙሉ ጨረቃዎችን በአንድ ዓመት ውስጥ እናያለን፡፡

💥 ታላቅ የዘመን ቀመርን፣ አስደናቂ ፊደላትን፣ የራሳችን ዜማ፣ ድንቆች ባህሎችን፣ ድንቅ መልክአ ምድርን አስተባብራ የያዘችውን ታላቋን ኢትዮጵያ ለመውረርና በራሳቸው ማንነት ለመቀየር ሮማውያን አህጉር አቋርጠው ቢመጡም በብዙ መሥዋዕትነት በ1888 ዓ.ም. በዐድዋ ላይ አባቶቻችን እናቶቻችን ዋጋ ከፍለው ድል በመንሣት ሙሉ ክብራችንን አስጠብቀውልን ታሪክን በወርቅ ቀለም ጽፈው ለመላው ጥቁር ሕዝቦች አብሪ ብርሃን ኾነው የዘመን ቀመራችን ወደ ሮማ ሳያፈልሱ በክብር ዐልፈዋል፡፡

💥 አኹንም በዚኽች ድንቅ የጳጒሜን ወር አፍሪካውያን፣ አውስትራሊያ፣ በእስያ ያሉ የጨረቃ ግርዶሽን በማየት ምሽታቸውን ያሳልፋሉ፡፡

💥 በመኾንም ውድ ኢትጵያውያን ጳጉሜን 2 ምሽታችኹን ከጨረቃ ግርዶሽ ጋር በማድረግ በሕይወታችኍ የማትረሱትን የደም ጨረቃን በዐይናችኍ በማየት ድንቅ ምሽት እንድታደርጉ መልእክቴን በማስተላለፍ በተለይ ደመና በአካባቢያችኍ ከሌለ በግልጽ የሚታይ ሲኾን በዚኽ 13ኛ የሙሉ ጨረቃ ዕለት የሚከሰተውን የሰማይ መርሐ ግብር ለመከታተል እንድትችሉ ሰዓቱን ከዚኽ በታች አስቀምጬላችኋለኊ፡፡

👉 ከምሽቱ 12፡21 (6:21 PM) - ደማቋ ሙሉዋ ጨረቃ በምሥራቅ አድማስ መውጣት ትጀምራለች፡፡

👉 ከምሽቱ 12፡28 (6፡28 PM) መሬት ጨረቃን መከለል ስትዠምር ድብዝዙ ግርዶሽ መታየት ይጀምራል፡፡

👉 ከምሽቱ 1፡27 (7:27 PM) ከፊል ግርዶሹ ይጀምራል፡፡

👉 ከምሽቱ 2፡30 ላይ (8፡30 PM) ተጠባቂው ሙሉው የጨረቃ ግርዶሽ ዠምሮ ጨረቃ ደም የምትመስልበት ሰዓት ይኾናል፡፡

👉 ከምሽቱ 3፡11 (9:11 PM) ላይ ጨረቃ በጥላው ማእከል የምትኾንበት ደም መምሰሏ የሚጨምርበት ሰዓት ይኾናል፡፡

👉 ከምሽቱ 3፡52 (9:52 PM) ሙሉ የጨረቃ ግርዶሽ (ደም መምሰሏ) ማብቂያ ይኾናል፡፡

👉 በመጨረሻዋ 13 ወራችን በርኅወተ ሰማይ በጳጉሜን 2 የዚኽ የሙሉ ጨረቃ ግርዶሽ መታየቱ እና የጨረቃ ደም መምሰል ያለው ሳይንሳዊ፣ ኢትጵያዊ ዕውቀት፣ ሃይማኖታዊ፣ ምልክትና መጻኢ ጉዳይ ዙሪያ በዶክተር ሮዳስ ታደሰ እና በዶክተር ጌትነት ፈለቀ፣ በመምህር መስፍን ሰሎሞን የቀረበውን ሰፊና ጥልቅ ትንተና ለማየትና ለማድመጥ በዚኽ ሊንክ ከፍተው ይመልከቱ፡፡

https://youtu.be/OoiU6WHxsWM?si=nIaFrhIfSIcfc6H9

👉 በመኾኑም ይኽነን ቪዲዮና ጽሑፍ ለኹሉም ሼር በማድረግ በዕለቱ ያለውን ክስተት በመላ ኢትዮጵያ ስለሚታይ ኹሉም ኢትዮጵያውን ከቤታቸው ወጥተው በሰዓቱ ክስተቱን እንዲመለከቱና ጨረቃ ደም መስላ ስትታይ እንዳይደናገጡ መልእክቴን አስተላልፋለኍ፡፡

💥 እኔ ከሥራ ባልደረቦቼ እና ከጓደኞቼ ጋር የማይረሳ በዕለቱ ታላቅ የምሽት መርሐ ግብር የምናደርግ ሲኾን እናንተም ከቤተሰቦቻችኊ፣ ከጓደኞቻችኍ ጋር ክስተቱን በማየት እንድታሳልፉ ምክሬን በማቅረብ የደም ጨረቃን (ሙሉ የጨረቃ ግርዶሽን) በዐይን ማየት ምንም የሚያስከትለው የጤንነት ችግር ስለሌለው ምንም አሳሳቢ ነገር ስለሌለ በተጠቀሰው ሰዓት ባላችኹበት አካባቢ ደመና ከሌለ በሚገባ ማየት ትችላላችኍ፡፡

💥 በዕለቱም ካላችኹበት ቦታ የማስታወሻ ፎቶዎችን በመነሣት በሶሻል ሚዲያዎች እንድታጋሩን በማሳሰብ መጪው 2018 ዓ.ም. ለኹላችኹም የበረከት፣ የምሕረት፣ የከፍታ እንዲኾንላችኍ ከአኹኑ እመኛለኍ፡፡

መጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ

(ነሐሴ 24/ 2017 ዓ.ም.)
212👍50👎4🔥1
🌝 የፀሐይና የጨረቃ መጨለም በኢትዮጵያ ሰነዶች🌚
🌓 የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች ሊቃውንት ስለ ግርዶሽ በመርሐ ዕውር፣ በአቡሻህር ይልቁኑ በትርጓሜ ሚጠተ ብርሃናት ዘሔኖክ ጋር ከመራቀቅ ባለፈ
በኢትዮጵያ የተከሠቱ ግርዶሾችን የመመዝገብ ልምድ ነበራቸው።
🌒 ለምሳሌ ያህል ስመ መንግሥታቸው መሲሕ ሰገድ በተባሉት በዐጼ በካፋ ዘመነ መንግሥት ስለተደረገው ግርዶሽ በታሪከ ነገሥት የብራናው ጽሑፍ ላይ፡-
🌛 “ወበስድስቱ ዓመተ መንግሥቱ አመ ሰብዑ ለመስከረም በዕለተ ሰኑይ በጊዜ ሠለስቱ ሰዓት ፀልመ ፀሓይ ወተርእዩ ከዋክብት ወተሐውኩ ኲሉ ሰብእ ወተማሕለሉ ወኮነት ከመ ቀዳሚሃ ብርህት”
(ዐጼ በካፋ በነገሠ በስድስተኛው ዓመት በመስከረም ሰባት በዕለተ ሰኞ ሦስት ሰዓት ላይ ፀሓይ ጨለመች ከዋክብት ታዩ ሰው ሁሉ ታወከ፤ ለመኑ፤ ፀሓይም እንደ ቀደመው በራች) በማለት የፀሓይ ግርዶች በተገለጠ ጊዜ በተከሰተው ክስተት የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደደነገጠ ጭምር አስፍረዋል፡፡

🌒 ከደርቡሽ ጋር በተደረገው ፍልሚያ በዐጼ ዮሐንስ ዕረፍት ጊዜ ግርዶሽ እንደነበረ ታሪከ ነገሥት ሲያስረዳ፡-
☄️ “አመ አሚሩ ለመጋቢት በዕለተ ቀዳሚት ሰንበት አሜሃ ኮነ ድልቅልቅ ሌሊተ ኮነ ቀትር ወጸልመ ፀሓይ ወኲሉ ዓለም ሠለስተ መዓልተ ወንጉሥ ዮሐንስ አዕረፈ ውስተ ሐይመቱ”
(መጋቢት 1 በቀዳሚት ሰንበት ዕለት ያን ጊዜ ንውጽውጽታ ሆነ በቀትር ጊዜ ፀሓይ በመላው ዓለም ጨልሞ እንደ ሌሊት ሆነ፤ ንጉሥ ዮሐንስም በድንኳኑ ውስጥ ዐረፈ) ይላል፡፡

🌞 ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በባሕረ ሐሳብ መጽሐፋቸው ላይ በኢትዮጵያ በየዘመናቱ የተደረጉ ታሪኮችን ታሪከ ነገሥትንና በኢትዮጵያ ያሉ የነገሥታት ዜና መዋዕሎችን አመሳክረው በዳሰሰቡት ክፍል ላይ በኢትዮጵያ የተደረጉትን የፀሓይና የጨረቃ ግርዶሾችና የሥነ ፈለክ ክስተቶችን በእኛ በኢትዮጵያ አቈጣጠር እንዲህ አስፍረውታል፡-

🌖 ➢ በዐጼ ገላውዴዎስ (አጽናፍ ሰገድ ዘመነ መንግሥት) በ1545 ዓ.ም. ፀሓይ ጨለመች፡፡

🌑 ➢ በጻድቁ ዮሐንስ (አእላፍ ሰገድ) ዘመነ መንግሥት በ1661 ዓ.ም. ኅዳር 5 (ጥቅምት 28 የሚልም አለ) በ9 ሰዓት ላይ ፀሓይ ጨለመች፤ በዚህ ምክንያት ንጉሡ በዕለቱ ሞት ተፈርዶባቸው የነበሩት ወንጀሎቹ እንዳይነኩ አዘዘ፡፡፡ ➢ በጻድቁ ዮሐንስ (አእላፍ ሰገድ) ዘመነ መንግሥት በድጋሚ በ1672 መጋቢት 24 ፀሓይ ጨለመች፡፡

🌑☄️ ➢ በዐጼ ኢያሱ አድያም ሰገድ ዘመነ መንግሥት በ1682 ዓ.ም. ኅዳር 1 ጅራታማ ኮከብ ታየ፡፡

🌟 ➢ በዐጼ በካፋ (ዳግማዊ እስክንድር) ዘመነ መንግሥት ጊዜ በ1720 ዓ.ም. ፀሓይ ጨለመ፡፡

🌒☄️ በዐጼ ኢያሱ (ብርሃን ሰገድ) ዘመነ መንግሥት በ1735 ዓ.ም. ጅራታማ ኮከብ ታየ፡፡

⛅️ ➢ በዘመነ መሳፍንት ጊዜ በ1792 ዓ.ም. ተክለ ጊዮርጊስ ለስድስተኛ ጊዜ ከዙፋኑ ላይ በወጣበት ዓመት በ1792 ዓ.ም. በሚያዝያ ወር ጨረቃ ጨለመች፡፡

💥 ➢ በዐጼ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ጊዜ በ1902 ዓ.ም. በሚያዝያ ወር ለጥቂት ቀናት ጅራታም ኮከብ ታየ በማለት አስቀምጠውታል፡፡

🌞 በዘመናችን ደግሞ የሠኔ 14/ 2012 ዓ.ም. የቀለበታማ የፀሐይ ግርዶሽ እንደተመዘገበ፤ የጳጉሜ 2/ 2017 ዓ.ም የሙሉ ጨረቃ መጨለም (የደም ጨለማ) በክብር ይመዘገባል።

☄️ ስለ ጳጉሜን 2 ምሽት የጨረቃ ግርዶሽ ለመረዳት በዚህ YouTube ሊንክ ይመልከቱ https://youtu.be/OoiU6WHxsWM?si=-5ZvCjFBptZTSKiP
አንድሮሜዳን ያንብቡ።
🌒 መጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
161👍28👏11
የ13 ወራትና የ13 ሙሉ ጨረቃዎች ጸጋ ባለቤቶች
☄️ በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
💥 ቀመር 13 መቼም አስገራሚ ናት፤ ብዙዎች ስለዚኽ ቊጥር ሲሰሙ ይሸበራሉ፡፡ በተለይ በምዕራቡ ዓለም ቊጥር 13 በእጅጉ ይፈራል፡፡ triskaidekaphobia (ትሪስ ካይ ዴካ ፎቢያ) ይባላል፡፡ ከተመዘገቡት የፍርሃት ዓይነቶች አንዱ ይኽ ነው፡፡
☄️ በግሪክ ቋንቋ τρεισκαίδεκα “ትሪስ” ማለት “3” “ካይ” ማለት “እና” “ዴካ” (ዐሥር) “ፎቢያ” (ፍርሃት) በአጠቃላይ የ13 ቊጥር ፍርሃት ማለት ነው፡፡
በተለይ ዐርብ እና 13 ሲገጥሙ ፍርሃቱ የሚጨምር ሲኾን የፍርሃቱ መጠሪያውም paraskevidekatriaphobia ይባላል፡፡
☄️ በምዕራቡ ዓለማት ያሉት ሀገራት እጅግ ብዙዎቹ 13ኛ ፎቅ የላቸውም፡፡ በሊፍት ሲወጣ 13ኛ ቊጥርን በመዝለል 14 ቊጥር ሲል ማየት የተለመደ ነው፡፡
☄️ ሪልስቴቶች 13ኛ ፎቅ ገዢ ስለሌላቸው 12 ኤ፤ 12 ኤም … እያሉ መሸጥ የተለመደ ነው፡፡

💥 ታላላቆች አየር መንገዶች ለምሳሌ እንደ ዩናይትድ፣ አላስካ፣ ራያኔር፣ ሉፍታንዛ፣ ፓሲፊክ፣ ሲንጋፓር ያሉ 13ኛ መቀመጫ በመዝለል 12 ብለው 14 እንደሚሉ በነዚኽ አየር መንገዶች የሚበሩ መንገደኞች ኹሉ ያውቁታል፡፡

💥 13 ቊጥር ግን ማያውያንን ጨምሮ በጥንት ሥልጡን ሕዝቦች ግን ተወዳጅ ቀመር ናት፡፡ ለምሳሌ በእስራኤል ቀመረ ፊደለ ዕብራይስጥ ፍቅር ማለት “አሀባህ” (אהבה) ሲባል በ22ቱ አሌፋት ሲቀመር (1 + 5 + 2 + 5 = 13) ይሰጣል፡፡ ☄️ በእኛም በግእዝ አልፍ ቤት ቀመረ ግእዝ “ጥበብ፣ ኤል” ይኽንኑ ቀመር ይሰጣሉ፡፡

🌓 ሴቶች በዓመት ውስጥ የሚያዩት የወርኅ አበባ የጨረቃን ዑደት ማእከል ያደረገ በመኾኑ 13 ነው - 28 ቀናት (365/28 = 13) ነው።
☄️ በግእዝ ወር የሚለው ቃል “ወርኅ” (ጨረቃ) ከሚለው ቃል የመጣ ነው፡፡ በእንግሊዝኛም menstruation መባሉ በላቲኒ ሜኔ - ሙን “ጨረቃ” ማለት ነውና ይኽነን ዑደት ማእከል ያደረገ ነው፡፡

☄️ በአፍሮ አይገባ መስቀል ላይ እንደምናየው ከጐን 6 ከጐን 6 ከላይ 1 በድምሩ 13 በማሳየት 12ቱ ሐዋርያትን ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በመወከል፤ 13ቱን ሕማማተ መስቀል በማሳየት አስደናቂ ምሳሌን ያስነብባል፡፡

☄️ የ2017 ዓ.ም. ደግሞ በእጅጉ ልዩ የሚያደርገው ከታላቅነቷ የተነሣ ብዙ ፈተና የተነሣባት 13ኛዋ ወር ጳጒሜን 13ኛው ሙሉ ጨረቃ በዚኽች በ13ኛ ወር ላይ ማረፉ ነው፡፡
🌓 ይኸውም የ2017 ዓ.ም. 13ቱ ሙሉ ጨረቃዎች እነሆ፡-
1ኛ) መስከረም 8 🌞
2ኛ) ጥቅምት 7 🌚
3ኛ) ኅዳር 7 🌞
4ኛ) ታኅሣሥ 6 🌚
5ኛ) ጥር 5 🌞
6ኛ) የካቲት 5 🌚
7ኛ) መጋቢት 5 🌞
8ኛ ሚያዝያ 5 🌑
9ኛ) ግንቦት 4 🌞
10ኛ) ሠኔ 4 🌑
11ኛ) ሐምሌ 3 🌞
12ኛ) ነሐሴ 3 🌑
13ኛ) ጳጉሜን 2 🌓☄️☄️☄️☄️

☄️ በመፈጸም የጨረቃ መጨለም (ግርዶሽ) በምልአተ ወርኅ (በሙሉ ጨረቃ) ጊዜ ብቻ ነውና የሚኾነው ጳጕሜን 2 ተጠባቂዋ የሙሉ ጨለማ ግርዶሽን ቢሊየኖች ያዩታል፡፡ ከምሽቱ 2፡30 ጀምሮ (82 ደቂቃዎች (1 ሰዓት ከ22 ደቂቃዎች) ሙሉ ግርዶሽ የደም ጨረቃ በርኅወተ ሰማይ ምሽት እንደነቅባታለን፡፡

☄️ በነገው የጳጉሜን 2 ምሽት ሰብሰብ ብላችኊ ይኽነን የተፈጥሮ ክስተት በማድነቅ ፎቶዎች እያነሣችኊ ለዐዲሱ ዓመት በጎ እየተመኛችኊ እንድትደሰቱበት መልእክቴን በመግለጽ የተባረከ ምሽት ለኹላችኹም እመኛለኍ፡፡

☄️ 13 ወር የፀሓይ ጸጋ ተብላ ብትደነቀው ውቧ ሀገራችንም በዚኽ ዓመት 13ኛ ሙሉ ጨረቃ በ13ኛዋ የጳጒሜን ወር ላይ በመግጠም 13 ወር የጨረቃ ጸጋ እንድንላት አስችሎናል፡፡
ጳጒሜን 2 የዓመቷን ሙሉ ጨረቃ ከግርሽዋ ጋር ካየን በኋላ የ2018 ዓ.ም. የዐዲሱ ዓመት ሙሉ የመስከረም ሙሉ ጨረቃ ማግሰኞ መስከረም 27 ደምቃ በምሥራቅ አድማስ ትወጣለችና ለዐዲሱ ዓመት የመስከረም 27 ሙሉ ጨረቃ በሰላም ደምቀን ያገናኘን፡፡
🌓 የነገው ሰዓት ለማወቅ
🌓 ከምሽቱ 12:21 ላይ 13ኛዋ ሙሉ ጨረቃ በምሥራቅ አድማስ ደምቃ ትወጣለች
👉 ከምሽቱ 12፡28 (6፡28 PM) መሬት ጨረቃን መከለል ስትጀምር ድብዝዙ ግርዶሽ መታየት ይጀምራል፡፡
👉 ከምሽቱ 1፡27 (7:27 PM) ከፊል ግርዶሹ ይጀምራል፡፡
👉 ከምሽቱ 2፡30 ላይ (8፡30 PM) ተጠባቂው ሙሉው የጨረቃ ግርዶሽ ጀምሮ ጨረቃ ደም የምትመስልበት ሰዓት ይኾናል፡፡
👉 ከምሽቱ 3፡11 (9:11 PM) ላይ ጨረቃ በጥላው ማእከል የምትኾንበት ደም መምሰሏ የሚጨምርበት ሰዓት ይኾናል፡፡
👉 ከምሽቱ 3፡52 (9:52 PM) ሙሉ የጨረቃ ግርዶሽ (ደም መምሰሏ) ማብቂያ ይኾናል፡፡

💥 አልፋ እግዚአብሔር ሆይ ቀጣዩ ዘመናችን ኹሉ አንተን በመውደድ፤ ሰውን ኹሉ በእውነት በመውደድ፤ ከአንተ የሚገኘው ሰላም በረከት ጸጋ ኹሉ በቅናት ሳይኾን በቅንነት ነውና ሥጋዊ ቅናትን ከልባችን አስወግደኽ፤ በጠብ ሳይኾን በአንተ ጥበብ፤ በምስጋና በምድራዊ ሰማያዊ በረከቶችኽ እየተደሰትን እንድንጓዝ ፈቃድኽ ይኹንልን። መልካም የጳጉሜን ወር።
መጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
497👍77👏38🔥15😁6👎4
☄️ ሀገራቸውን ላከበሩ ምስጋና ለጉጉል አድናቂዎች ተግሣጽ🌓
✍️ ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
🌓 ጳጉሜን 2/ 2017 ዓ.ም. ላይ የተከሰተውን የሙሉ ጨረቃ ግርዶሽ በጣም በታላቅ መደነቅ ኹላችንም ተመልክተናል፡፡ በግርዶሹ ዙሪያ ሳይንሳዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ትውፊታዊ፣ ምልክታዊ ፍቺውን፤ ቀድመው የረቀቁ የኢትዮጵያ ሊቃውንት የተራቀቁበትን፣ ዛሬ ዓለም ከደረሰበት ጋር እያመሰጠርን በተለያዩ ሚዲያዎች ስናስተላልፍ ቆይተናል፡፡

🌓 ግርዶሹ ከተናወነ በኋላ ሀገራቸውን የሀገራቸውን ዕውቀት ያከበሩ ኹሉ ደስታቸውን ሲገልጹ እንደ ጎርጎርዮሳዊ አቆጣጠር መስከረም 4/ 1998 ዓ.ም. የተመሠረተውን 27 ዓመት ላስቆጠረውን ለጉጉል እና ሐምሌ 29/ 1958 ዓ.ም. ላይ ከተመሠረተ ገና 67 ዓመት ብቻ ላስቆጠረው ለናሳ ጠበቃ ኾነው ሲሟገቱ ሲታዩ የ4000 ዓመት የከዋክብት ዕውቀት ያላት የሀገራቸውን ዕውቀትና ጥበብ ምን ያኽል አለማወቃቸው በእጅጉ አስገራሚ ነው፡፡

🌓 እኔም የብዙ ሺ ዘመን ሥልጣኔ የብዙ ሺዎች የብራና መጻሕፍት ባለቤት የራሷ ፊደል፣ የራሷ የዘመን ቀመር፣ የራሷ ዜማ ለሺዎች ዓመታት ጠብቃ የዘመንን ዑደት ስትሰፍር ስትቆጥር የነበረችውን ታላቋን ኢትዮጵያ ከ67 ዓመት ተቋም ጋር ጥቂቶች እያነጻጸሩ የሀገራቸውን ዕውቀት ሲያብጠለጥሉ ባይ ራስን ያለማወቅና ያለማክበር ውጤት ምን ያህል ጨለማ እንደኾነ ስለተሰማኝ ትንሽ ልጽፍ ወደድኹ፡፡

🌓 ለማንኛውም ጥቂት ስለ ኢትዮጵያ የሥነ ፈለክ ዕውቀት
በዓለም ታሪክ የዛሬ 4000 ዘመን ከአክናሁስ ሳባ እና ከነክህቲ ካልንሶ በመቀጠል ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ1890-1871 ለ19 ዓመት ኢትዮጵያን በመራችው በንግሥት ካሲዮፕያ ጊዜ ሕብራተ ከዋክብት (Constellations) በማወቅና በመሰየም በቀደምትነት ያላችና ዛሬም በ88ቱ ሕብራተ ከዋክብት ካርታ ላይ እንደ ሀገር በብቸችኝነት የተጻፈች ኢትዮጵያ ብቻ መኾኗን ዕወቁ፤ ዐውቃችኹም አክብሯት።

☄️ ከጉጉል ውጪ ስለ ሀገራችሁ ዕውቀት የሌላችኹ ደግሞ የዛሬ 27 ዓመት የተመሠረተውን ጉጉል ተጠቅማችኹ እንድታዩ እነሆ ሊንኩ
https://starchild.gsfc.nasa.gov/docs/StarChild/questions/88constellations.html
ከፈለጋችሁ ጉጉል አድርጉ፡፡

🌓 ቀደምት አባቶቻችን ለሺዎች ዓመታት ተፈጥሮን በመመርመር በፀሓይ፣ በጨረቃ፣ በከዋክብት፣ በፈለከ ፈለካት፣ በአየረ አየራት፣ በመባርቅት፣ በነጐድጓድ፣ በ12ቱ ነፋሳት ላይ በመራቀቅ ብራና ፍቀው፣ ቀለም በጥብጠው፣ ብርዕ ቀርጸው እጅግ ድንቅ የኾኑ ዓለም የሚደመምባቸው መጻሕፍትን የጻፉ ድንቆች ናቸው፡፡

🌓 ካላቸው ታላቅ ዕውቀት የተነሣ በዘረፋ በስርቆት እየወጡ በዶክትሬት ደረጃ የሚጠኑ በሺዎች የሚቆጠሩ የውጪ ሀገራት ቤተ መጻሕፍትን ያጣበቡ የግእዝ መጻሕፍት ምስክር ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ እናታችን ዓለም የበተነውን ጳጉሜንን የጠበቀች፣ ዲዮናስዮስ በስሌት ስሕተት የጨመረውን 7 ዓመት የጠበቀች፤ ፓፕ ጎርጎርጎስ 1582 ዓ.ም. የጨመረውን 11 ዕለት ሳትጨምር ጠብቃ የያዘች፣ እስከ ሳድሲት ድረስ ተራቅቃ የዘመን ቀመሯን ለሺዎች ዘመናት አስከብራ የኖረች ስንዱ እመቤት ናት፡፡

🌓 ዓለም ለብዙ ሺሕ ዘመን አጥቶት ዕንቆቅልሽ የኾነውን የሔኖክን መጽሐፍ ጠብቃ ይዛ ዓለም ድጋሚ እንዲያገኘው ያደረገች ብቸኛ ሀገር ናት፡፡ ለማንኛውም ስለ ግርዶሽ ዕውቀት ኢትዮጵያውያኑ ተራቅቀው በመርሐ ዕውር (ባሕረ ሐሳብ)፣ አቡሻህር ላይ የሚውቁት ዕውቀት ሲኾን በመጽሐፈ ሔኖክ ላይ በእጅጉ በመራቀቅ ያያቸውን ብርሃናት እያራቀቁ በተረጎሙበት “ትርጓሜ ሚጠተ ብርሃናት ዘሔኖክ” ላይ ለሺዎች ዓመታት ሲራቀቁበት ሲያመሰጥሩት ሲመዘግቡት ኖረዋል፤ እንጂ 67 ዓመት ያስቆጠረ ተቋም መረጃቸው አላደረጉም፡፡

🌓 ናሳ እንኳን የኒውተን የስበት ሕግና የኬፕለር ኦሪቢታል ሜካኒክስን ከመጨመር ባለፈ የጥንቱን ዕውቀት ተጠቅሞ ግርዶሽን ያሰላል እንጂ የጥንቱን ዕውቀት ገሸሽ አያደርግም፡፡ ይኸውም የኢትዮጵያ ሊቃውንት በዐውደ ፀሓይ 365 ዕለት ከ15 ኬክሮስ ከ6 ካልዒትና በዐውደ ወርኅ (ጨረቃ) 354 ዕለት ከ22 ኤክሮስ፣ ከ1 ካልዒት፣ ከ37 ሣልሲት፣ ከ52 ራብዒት ያለውን 11 ዕለትና ፀሓይና ጨረቃ መንገዳቸውን ፈጽፈው በተፈጠሩበት ኆኅት እንደሚገኛኙ ስለ ግርዶሽ የኢትዮጵያ ሊቃውንት የሚያመሰጥሩትን ስለተጀመረ ተቆጠረ ስላልተፈጸመ ታተተ የሚሉት የ19 ዓመት ዑደትን 1 በመቀነስ የኢትዮጵያ ሊቃውንት 19 – 1 = 18 ዓመት ከ11 ቀናት ዑደትን ጭምር በመጠቀም በብዙ ሒሳቦች ስለ ግርዶሽ ሲያሰሉ ይኽም የሳሮስ ዑደት (Saros Cycle) በመባል ይታወቃል፡፡

🌓 ይኽነን የዐውደ አበቅቴ ዑደት በመጠቀም ለማስላት ከፈለጋችኹ ለምሳሌ ጳጉሜን 2/ 2017 ዓ.ም. ሙሉ የጨረቃ ግርዶሽ አይተናል፡፡ መስከረም 6/ 2036 ዓ.ም. የኀሙሱን የ128ኛ ዑደትን ማወቅ ይቻላል፡፡

☄️ ይኽ ዑደት ከ1,200 - 1,500 ዓመታት ሲገሠግሥ በውስጡ በአማካይ ከ70–80 ግርዶሾችን ያካተተ ነው፡፡ ለማንኛውም ሀገራችኹን የማታከብሩ ዓለም ኢትዮጵያን በዚህ ዕውቀቷ እንዴት እንዳከበራት ለማወቅ ጥንታዊውን ዕውቀታችንን ዓለም ከደረሰበት የሥነ ፈለክ ዕውቀት ጋር እያዋሐደ የሚተነትነውን አንድሮሜዳ ቊጥር 1 እና ቊጥር 2 አንብቡ፡፡

🌓 መጪው 2018 ዓ.ም. ጳጉሜን 2 ቀና ብለን ሰማይን እየተመለከትን እንደጀመርነው ከመሬት ወደ ሰማይ ከፍ ብለን ዓለም የሚመረምራቸው የሺዎች ዓመታት የኢትዮጵያ መጻሕፍት እኛው እየመረመርን፣ ዓለም አኹን የደረሰበትን የሳይንስ ዕውቀት ጋር እያዋሐድን ታላላቅ ሥራዎችን ለእናታችን ኢትዮጵያ በመሥራት እንድናሳልፍ ምኞቴ ነው፡፡

በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
259👏27👍14🥰3😁1